ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ የክርስቲያኖች አንድነት ነው፡፡
እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡፡
“ቤተ-“ ማለት ወገን ህብረት የሚለውን ትርጉምም ይይዛል፡፡ ለምሳሌ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ ፣ቤተ አሮን ሲል የእስራኤል ወገን ፣የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን እንደሚል ማለት ነውና፡፡ ማቴ 16÷18 18 ÷17 የሐዋ. 18 ÷22 20÷28 መዝ. 117፡3 በዘህም መሠረት ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ (የምእመናን አንድነት ጉባኤ) የሚጠራበት ስም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህም ስብስቡን ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመካከላችን ያለውን ፍቅር ትስስር ህብረት አንድነት ነው የሚመለከተው፡፡ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ራስነት አንድ አካል የሆኑ የምእመናን አንድነት ናት፡፡
“እርሱም የአካለ ማሇት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው . . .” ቆሊ. 1፡18፣24 “በየአብያተ ክርስቲያናትና ይህንንም ነገር በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤” ይላል። የሐዋ 5፥11።በዚህ ምዕራፍና ቁጥር ላይ “አብያተ ክርስቲያናት” የተባሉት ማኅበረ ምዕመናን ናቸው። በሌላም ስፍራ፦ “በይሁዳ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።” የሚል አለ። የሐዋ 9፡31 በቅዳሴም ላይ “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት (አንዲት ቅድስት የሐዋርያት ጉባዔ ስለሆነች ቤተክርስቲያን ሰላም ጸልዩ)” የሚለው የሚያመለክተው ይህንን የክርስቲያኖችን ህብረት ነው፡፡