ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ አትሆንም፡፡ ከአንድም አታንስም፡፡ አይጨመርባትም፡ አይቀንስባትምም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ …”በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” አለ እንጂ “ቤተክርስቲያኖቼን” አላለም፡፡ ማቴ 16፡18 በአንድ መሠረት ላይ አንዱ መሥራች የመሠረታት ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በእርሷ ያለውን አንድነትም ያመለክታል፡፡ በቤተክርስቲያን ሦስት አይነት አንድነት አለ፡፡ የመጀመሪያው በምድር ላይ የምንኖር ክርስቲያኖች (እርስ በእርሳችን) ያለን አንድነት ነው፡፡ ሁለተኛው በአካለ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ያለን አንድነት ነው፡፡ ሦስተኛው አንድነት ሁላችንም (በአካለ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን) ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት ነው፡፡ ይህ አንድነት ነው እንግዲህ ቤተክርስቲያንን አንዲት ያደረጋት፡፡

እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ እንዳለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የበቀሉ ቅርንጫፎች ናቸውና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አለምንም . . . አንተ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” ዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 20 – 23፡፡ ከሚለው የጌታ አነጋገር የምንረዳው ይህን አንድነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ፥ ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት” ኤፌሶን 4 ፥ 4 – 5። በማለት ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ እንዲት መሆንዋን አስገንዝቡዋል፡፡ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በእብነ በረድ ትሠራ በጭቃ፤ በሀገር ቤት ትመስረት በውጭ ሀገር እምነትዋ ሥርዓትዋ አንድ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በዋናነት የሚመለከተው ከአንዱ ክርስቶስ ጋር ያለንን ውህደት ነው እንጂ አስተዳደራዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድነታችን የአንዱ ግንድ የክርስቶስ ቅርንጫፎች መሆናችንና በአንዱ በክርስቶስ ሥጋና ደም የምንድን መሆናችን ነው፡፡ ዮሐ 15፡1-10 በዚህ በአንዱ መሠረትነት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s