እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሰሎሞን ቤተመቅደስ ትመሰላለች (1ኛ ነገ 9፡1)፡፡
‹‹ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው፡- በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። …እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። መልሰውም፡- ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።›› 1ኛ ነገ 9፡1-8
ከደብተራ ኦሪት ቀጥሎ እግዚአብሔር አምላክ እንደልቤ ብሎ ያከበረው ቅዱስ ዳዊት በዘመኑ ለአምላኩ ቤተ መቅደስ ሊሠራ ቢፈልግም ቤተመቅደስ የሆነ የኦርዮን ሠውነት አፍርሰሃልና አትሠራም ነገር ግን ልጅህ ይሠራዋል ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ንጉሥ ሠሎሞንም ቃል እንደተገባለት ውብና ያመረ በወርቅ የተለበጠ ቤተ መቅደስ ሠርቷል፡፡ ይህችም ቤተ መቅደስ ለአማናዊቷ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ›› እንዳለ በዚያች ቤተመቅድስ እግዚአብሔርና ሰው ተገናኝተዋልና የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በዚህች ቤተመቅደስም ክርስቶስ ተገኝቶ ባርኮ ከወንበዴዎች አፅድቶ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ያለው የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ስለሆነች ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ለእርሱ ስንታዘዝ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን ትዕዛዙን የማንጠብቅና በእርሱም ላይ የምናምጽ ከሆነ ‹‹እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ›› እንዳለ እድል ፈንታችን የዘላለም ሕይወት አይሆንም፡፡ የማንታዘዝ ከሆነ ‹‹ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ›› እንዳለ በምድር ያለችው ቤተክርስቲያን ለፈተና ትዳረጋለች፡፡ ከእርሱ ፈቀቅ የምንል ከሆነ ‹‹እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ።›› እንዳለ በእኛም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ስንኖር እግዚአብሔርን ፈርተን እርስ በእርስም በፍቅር እየኖርን ሊሆን ይገባል፡፡ በጥልና በክርክር ወይም በዘረኝነትና በመከፋፈል የምንኖር ከሆነ ግን የዚህ ትንቢት መፈፀሚያ መሆናችን አይቀርም፡፡