ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ፡ የአዲስ ዘመን ምልክት

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓል የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በዓል ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቅዱስ ዮሐንስ የአሮጌ (ብሉይ) ዘመን ማብቃት ብስራት፣ የአዲስ ዘመን መምጣት ማሳያ ሆኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለሚታወቅ ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መካከል ከነበሩት ቅዱሳን አበው አንዱ የሆነ፣ ከነቢያት እነ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ከመላእክት ቅዱስ ገብርኤልና ከካህናት አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት ነቢይና ሐዋርያ ነው፡፡ ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፣ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፣ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወቱን፣ ትምህርቱን፣ አገልግሎቱንና ሰማዕትነቱን እንዳስሳለን፡፡

ትንቢቱና ብሥራቱ፡ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።

ካህኑ ዘካርያስ እና ከካህኑ ከአሮን ወገን የሆነች ኤልሳቤጥ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም /ሉቃ.፩፥፭-፯/፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ብሎ አበሠረው (ሉቃ.፩፥፰-፲፯)፡፡

ካህኑ ዘካርያስም “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” አለው፡፡ መልአኩም “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም፤” አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር (ሉቃ.፩፥፲፰-፳፩)፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በዚህም በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ ከመልአኩም ቃል ተነሳ ካህኑ ዘካርያስ ልጁ ቅዱስ ዮሐንስ እስኪወለድ ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ” ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች (ሉቃ.፩፥፳፪-፳፭)፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ጌታችንን በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት “ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?” ባለችው ጊዜ እግዚአብሔር ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለው ለማስረዳት መካኗ ቅድስት ኤልሳቤጥ በስተእርጅና መውለዷን ጠቅሶላታል፡፡

ጽንሰቱና ልደቱ፡ አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው:: አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ተብሎ እንደተነገረው የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ በማለት ፊት አውራሪ ሆኖ የሚላከውን ቅዱስ ዮሐንስን የፀነሰችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልትጠይቃት ወደ እርሷ በሔደች ጊዜ እጅግ የሚያስገርም ሁኔታ ተፈጠረ። ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ ኾኖ ለቅድስት ድንግል ማርያም እና በማኅፀኗ ላለው ለዓለም መድኃኒት ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰግዷል (ሉቃ. ፩፥፳፮-፵፩) ። ቅድስት ኤልሳቤጥም ድምጿን ከፍ አድርጋ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል? እነሆ የሰላምታሽን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሏልና፡፡ ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸምላት ያመነች ብፅዕት ናት፤” በማለት እመቤታችንን አመስግናታለች (ሉቃ.፩፥፵፪-፵፭)፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ። ዘመዶቹ የሕፃኑን ስም በአባቱ መጠሪያ “ዘካርያስ” ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን “ዮሐንስ ይባል” አለች፡፡ የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ “ዮሐንስ” ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታና በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ “… አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኃጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤” ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይነትና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት እንደሚያበሥር አስቀድሞ ትንቢት ተናገረ (ሉቃ.፩፥፶፯-፸፱)፡፡

ስደቱና ገዳማዊ ሕይወቱ፡ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ የመድኀኒታችን የክርስቶስን መወለድ ከሰብአ ሰገል ሲሰማ መንግሥቴን ይወስድብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ጌታችንን ያገኘ መስሎት የቤተልሔም ሕፃናትን መግደል ጀመረ (ማቴ.፪፥፩-፲፮)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሄሮድስ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: “ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ ‘ዮሐንስ’ የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል” አሉ:: እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን ገድለውታል:: የሄሮድስ ጭፍሮችም ዮሐንስን ፈልገው ባጡት ጊዜ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ ውስጥ በሰይፍ ገደሉት፤ ካህናቱም በንጹሕ ልብስ ገንዘው በአባቱ በበራክዩ መቃብር ቀበሩት፡፡ ደሙም እስከ ፸ ዓመት ድረስ ሲፈላ ኖረ። ጌታችንም የዘካርያስ ደም እንደሚፋረዳቸው ሲያስረዳ “ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል” በማለት ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ገሥጿቸዋል (ሉቃ.፲፩፥፶፩)፡፡

በዚህ ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጇን ከሞት ለማዳን ስትል ሕፃኑ ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ተሰደደች። በበረሃም ድንጋይ ቤት ኾኖላቸው፣ እግዚአብሔርም ከብርድ፣ ከፀሐይና ከአራዊቱ አፍ እየጠበቃቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ወደ በረሃ ሲገቡ ቅዱስ ዮሐንስ የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሕፃን ነበር፡፡ አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: “ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ” (ሉቃ.፩፥፹)፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ ወደ በረሃ በገባች በአምስተኛ ዓመቷ፤ ቅዱስ ዮሐንስም ሰባት ዓመት ሲሞላው ሕፃኑን በበረሃ ትታ ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈች፡፡ በገድሉ እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያምና ሰሎሜ እንዲሁም ቅዱሳን መላእክት፣ካህኑ ዘካርያስና ሰምዖን በአካለ ነፍስ ተገኝቶ ገንዘው ቀብረዋታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም እግዚአብሔር ከአራዊት አፍ እየጠበቀው፤ ሲርበው ሰማያዊ ኅብስትን እየመገበው ሲጠማውም ውኃ እያፈለቀ እያጠጣው፤ አናብስቱና አናምርቱ እንደ ወንድምና እኅት ኾነውለት በበረሃ መኖር ጀመረ፡፡ በበረሃ ሲኖርም የግመል ጠጉር ይለብስ፣ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣ (በአቴና ቀምሲስ፣ በኢትዮጵያ ሰበቦት /የጋጃ ማር/) የሚባል /የበረሃ ቅጠል/ እና መዓረ ጸደንያ /ጣዝማ ማር/ ይመገብ ነበር (ኢሳ.፵፥፫-፭)። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ በረሀ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ፡፡ ለሃያ ሦስት ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም፡፡ ይህችን አመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

ኤልያስ ፀጉራም እንደ ኾነ ኹሉ ዮሐንስም ልብሱ የግመል ፀጉር መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን (ፈቃደ ሥጋን የተዉ)፣ ዝጉሐውያን (የሥጋን ስሜት የዘጉ)፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ኤልያስ አክአብና ኤልዛቤልን፣ ዮሐንስ ደግሞ ሄሮድስና ሄሮድያዳን መገሠፃቸው፤ ኤልያስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ቀድሞ እንደሚመጣ ኹሉ ዮሐንስም ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት (በአካለ በሥጋ መገለጥ) ቀድሞ ማስተማሩ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ኤልያስ ብሎታል። “እነርሱም ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ.፲፩፥፪-፲፱)። ቅዱስ ዮሐንስ በብሕትውና በበረሃ/በገዳም የኖረ፣ የብሉይና የሐዲስ መሸጋገሪያ፣ የመጨረሻው ነቢይና የመጀመሪያው ሐዋርያ ነው፡፡

ስብከቱና ጥምቀቱ፡ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!

ሠላሳ ዓመት ሲሞላውም በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል “… የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፡፡ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ኹሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፤ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ ኹሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤” ተብሎ እንደ ተነገረ ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!” እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ኹሉ ወጣ (ሉቃ.፫፥፫-፮)። ዮሐንስ ወንጌላዊም ይህንን “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።” በማለት ገልጾታል፡፡

በዚያም ወቅት የይሁዳ አገር ሰዎች ኹሉ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። እርሱም፡- “… እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤” ይላቸው ነበር፡፡ “ምን እናድርግ?” ብለው ሲጠይቁት “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ” ይላቸው ነበር። ቀራጮችን፡- “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ” ጭፍሮችንም፡- “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ” እያለና ሌላም ብዙ ምክር እየመከረ ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር /ሉቃ.፫፥፯-፲፬/፡፡

በተጨማሪም “በዚያን ጊዜ በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምና በዮርዳኖስ አውራጃ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፡ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ሁሉም በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፮ ከሰዱቃውያንና ከፈሪሳውያን ወገን መጥተው ሲጠመቁ አይቶ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ ትሸሹ ዘንድ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህስ ለንስሐ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ፡፡ አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ …ምሳር በዛፎች ግንድ ላይ ሊቆርጥ ተዘጋጅቷልና መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፱ ጥምቀቱንም በተመለከተ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከእኔ አስቀድሞ የነበረ ነው ከእኔ ይበልጣል፤ እርሱ በእሳት ያጠምቃችኋል፤ የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም (ማቴ. ፫ ፥ ፲፩) እያለ ያስተምር ነበር፡፡ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣውና ከእኔ ይልቅ የሚበረታው እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ሥንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል” በማለት የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ እና አምላክነት ነግሯቸዋል (ማቴ.፫፥፩-፲፪፤ ሐዋ.፲፫፥፳፬-፳፰)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ታላቅ ምስክርነትን የሰጠ ሐዋርያ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከፈሪሳውያን ወገን የኾኑ ካህናትና ሌዋውያን ‹‹ስለ ራስህ ምን ትላለህ?›› ብለው በጠየቁት ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንዳልኾነና “የጌታን መንገድ አቅኑ” ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ቃለ ዐዋዲ (ዐዋጅ ነጋሪ) መኾኑን ተናግሯል (ሉቃ. ፫፥፲፭-፲፰፤ ዮሐ.፩፥፲፱-፳፫)። ቅድስት ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?” (ሉቃ.፩፥፵፫) ስትል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መኾኗን እንደ መሰከረችው ኹሉ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ እርሱ በሔደ ጊዜ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ባሪያ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ እንዴት ጌታ ወደ ባሪያው ይመጣል?” በማለት የጌታችንን አምላክነት በትሕትና ተናግሯል (ማቴ.፫፥፲፬)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን “… ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተንስ በማን ስም ላጥምቅህ?” ሲለው “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሥልጣንህ ዘለዓለማዊ የኾነ የዓለሙ ካህን፤ የዓለምን ኃጢአት የምታስወግደው የእግዚአብሔር በግ፤ ብርሃንን የምትገልጽ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለን?” እያልህ አጥምቀኝ ብሎት እንደታዘዘው አድርጎ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን አጥምቆታል፡፡ ቅዱስ ጌታችንን ባጠመቀው ጊዜ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚለውን የእግዚአብሔር አብ ቃል መስማቱንና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱን በመመስከር ምሥጢረ ሥላሴን አስተምሯል (ማቴ.፲፯፥፭፤ ዮሐ.፩፥፴፬)፡፡

ሰማዕትነቱና ዕረፍቱ፡ በሕፃንነቱ ያለፈችውን የሰማዕትነት ጽዋ በሠላሳ ዓመቱ ተቀበላት፡፡

በመጨረሻም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ” እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡ የሰማዕትነቱ ዜናም እንዲህ ነበር፡፡

“የሄሮድያዳ ልጅ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ ‹እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡” እንዲህም እያለ ‘የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?’ እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ልመና ከአፏ በሰማ ጊዜ ‹የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ› ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ ለሰው ይምሰል አዘነ፣ ተከዘ፡፡ ኃዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት አይደለም፣ ዮሐንስን ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ ከዳ እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንም በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡ ‹የለመንሽውን ሁሉ እሰጥሻለሁ› ብሎ ስለማለ ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡ መስከረም ፪ ቀን ሰማዕትነት የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የሄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስን አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ አስቀድሞ በሕፃንነቱ ስለጌታ ከተሰየፉት ሕፃናት መካከል በስደት ምክንያት ባይኖርም ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን እውነትን መስክሮ የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀበለ፡፡  በመሐላ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፤ አለልክ መብላና መጠጣት ካለበት ቦታ እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት ይገኝበታል፡፡ ስካር ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኝበት ቦታ የእግዚአብሔር መቅሰፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል ይፈጸምበታልና፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ያስገደለው ዘፈን፣ ስካርና የዘማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት:: ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች:: የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት) ዕለት ነው፡፡ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ስሞቹና ትርጉማቸው፡ ፍስሐ ወሐሴት፣ ጸያሔ ፍኖት፣ ቃለ ዓዋዲ… ይባላል፡፡

ዮሐንስ ማለት “እግዚአብሔር ጸጋ ነው” ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ.፩፥፲፬)፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ፣ በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣ በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ፣ እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ፣ የጌታችንን መንገድ የጠረገ፣ ጌታውን ያጠመቀና፣ ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው:: ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ጻድቅ፣  ካሕን፣ ባሕታዊ/ገዳማዊ፣  መጥምቀ መለኮት፣ ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)፣ ድንግል፣ ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)፣ ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)፣ መምሕር ወመገሥጽ፣ ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ) ብላ ታከብረዋለች::

ስለዮሐንስ የተሰጠ ምስክርነት፡ እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ በነብዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም፤ በምድረ በዳ የሚያስተምር የአዋጅ ነጋሪ ቃል ኢሳ. ፲፩ ፥ ፩ ተብሎ የተነገረለት ነው፡፡ ጌታችንም፡- “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል። (እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ) ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ተናግሯል (ማቴ.፲፩፥፱-፲፩)።

ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ስለ ዮሐንስ ሲናገር “ወዝንቱ ውእቱ ማኅቶት ዘየኃቱ ወያበርህ – እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ” ነው ያለው (ዮሐ ፭፡፴፭)፡፡ ዮሐንስን የሚነድና የሚያበራ ፋና (መብራት) ብሎ ገለጸው፡፡ ይህን ለጨለማው ዓለም ታላቅ ብርሀን ነበረ፡፡ እርሱ ሰማዕትነትን እየተቀበለ (እየነደደ) ለሌላው አበራ፡፡ ፀሐይ  በወጣ ጊዜ የፋናን ብርሀን የሚሻው እንደሌለ ጌታም ባስተማረ ጊዜ የዮሐንስን ትምህርት የሚሻው የለምና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት በፀሐይ መስሎ ተናገረ፡፡ በሌላም መልኩ ፋና ለመጣለት ነው የሚያበራው፡፡ ፀሐይ ግን ለሁሉም ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ዮሐንስ ያስተማረው ለመጣለት ሕዝብ ነው፡፡ ጌታ ያስተማረው ለሁሉም ነውና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት ደግሞ በፀሐይ መስሎ አስተማረ፡፡

የመልክአ ዮሐንስ መጥምቅ ፀሐፊም  ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ “ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ /ዮሐንስ ሆይ ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ሆነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም/” ሲል መስክሮለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና ሰማዕትነቱ በገድሉ በሰፊው ተጽፏል፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ክብሩን ለማስታወስ ያህል በጥቂቱ አቀረብን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ትጠብቀን፡፡አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ)፣ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

3 thoughts on “ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ፡ የአዲስ ዘመን ምልክት

  1. ከሁሉም አስቀድሜ በእግዚአብሔር ፍጹም ሠላምታ ሠላም እላለሁ ! ገድለ ዮሐንስ መስከረም 2 ቀን ሲነበብ ሰምቼ መጽሐፉን ለመግዛት ፈልጌ አጣሁት ። ገድለ ዮሐንስ የሚል 2 አይነት መጽሐፍ ነው ያለው ባለቃል ኪዳኑ እና ቃል ኪዳን የሌለው ። እኔ የፈለግሁት ባለቃል ኪዳኑ ነው እባካችሁ ስለ መጥምቀ ዮሐንስ ብላችሁ ማህበረ ቅዱሳን አሳትሞ በገበያ ላይ ቢያውለው ጥሩ ስለሆነ ከዛው ውስት የምትሰሩ ተወያዩበት። ከገበያ ላይ ካገኛችሁት እባካችሁ ግዙልኝ ወረታውን እከፍላለሁ። 09 35 85 78 47

    Like

Leave a comment