ስለ አስተምህሮ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

ከሁሉ አስቀድመን ምስጋና የባሕርይው ለሆነው አምላካችን ምስጋናን እናቀርባለን፡፡ በሥራችንም ሁሉ ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ እንዲሆንልንም ዘወትር በፊቱ እንቆማለን፡፡

አስተምህሮ ዘተዋሕዶ የጡመራ መድረክ ዛሬ ህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ተመሠረተች፡፡ የጡመራ መድረኳ ስያሜ ‘አስተምህሮ’ እንደመሆኑ በዚህ የመጀመሪያው ጡመራችን አስተምህሮ የሚለውን ቃል ትርጉም በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ አስተምህሮ የሚለው ቃል ሁለት ዓይነት ትርጉም አለው፡፡

አስተምህሮ: አስተምህሮ ማለት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ማለት ሲሆን ይህም የትምህርቱን ይዘት፣ የይዘቱንም ምንጭ፣ የትምህርቱን አሰጣጥ ስልት፣ የመምህራኑና የተማሪዎቹን መስተጋብር ወዘተ… ያጠቃልላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከሚገለፅባቸው መንገዶች መካከልም የአውደ ምሕረት ስበከት (ለምዕመናን የሚሰበከው)፣ የወንበር ትምህርት (በአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው) ፣ ልዩ ስልጠናና (በኮርስ መልክ የሚሰጠው ትምህርት) በመገናኛ ብዙሀን (በጋዜጣ በመጽሔት በድረ ገፅ) የሚሰጡት ትምህርቶች ይገኙበታል፡፡

አስተምሕሮ: መሐረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤  አስተምሕሮ ማለት ይቅርታ መጠየቅ /ምልጃ/ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመንም ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡

አስተምህሮ ዘተዋሕዶ የጡመራ መድረክ በርቱዓ ሃይማኖት (በቀናች ሃይማኖት)፣ በሕጹጸ አእምሮ (በጎዶሎ ዕውቀት)፣ በንዑሰ ምግባር (በታናሽ ምግባር) የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ትምህርቶች የምንማርባትና የተማርነውንም ለሌሎች የምናጋራባትም አዲስ የጡመራ መድረክ (ብሎግ) ናት፡፡

አስተምህሮም በይዘቷ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ በማተኮር ለአንባቢያን ይበጃሉ ይጠቅማሉ ያልናቸውን ትምህርቶችን የምናጋራባት መድረክ ናት፡፡ በዘመነ አስተምህሮ ስለተመሠረተችም ስያሜዋን “አስተምህሮ” ብለናታል፡፡ ለሁላችንም መንፈሳዊ ሕይወታችን የተቃና ይሆንልን ዘንድ በጸሎታችሁ እንድታስቡንና በሚቀርቡት ጽሑፎች ላይ ገንቢ አስተያየታችሁንም በማጋራቱ በኩል እንዳትለዩንም በትህትና እንጠይቃለን፡፡

ማሳሰቢያ: በአስተምህሮ በሚቀርቡት ትምህርታዊ ጽሑፎች ላይ የአዘጋጆችን ስም የማንጠቅስበት ብቸኛ ምክንያት አንባቢያን የጽሑፎቹ ይዘት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ከመፈለጋችን የተነሳ ነው። ይህንንም የምናደርገው የቀደሙትን አባቶችን አስተምህሮ መሠረት አድርገን መሆኑን እንገልጻለን። ሆኖም በአስተምህሮ ጽሑፎች ላይ ጥያቄ ወይም አስተያየት ካለዎት አግኙን/contact ላይ በተቀመጡት አማራጮች ቢልኩልን ለአስተምህሮ አዘጋጆች በቀጥታ ይደርሳል፣ አስተያየትዎን በአክብሮት እንቀበላለን፣ ለጥያቄዎም ምላሽ እንሰጣለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር