ቅዱስ መስቀል: እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!

መግቢያ

የተመረጠ ምስጋና መፍሰሻ የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት በምታቀርበው ምስጋና ከሥሉስ ቅዱስ (በፍጹም አንድነትና በልዩ ሦስትነት ከሚመሰገን እግዚአብሔር) ቀጥሎ ለሁለት ፍጥረታት በልዩ አንክሮ የጸጋ ምስጋናን ታቀርባለች። እነዚህም ሥጋን የተዋሐደ የመለኮት ክብር መገለጫ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ ምክንያትና ምልክት የሆኑት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ መስቀል ናቸው። ለእያንዳንዱ የሚገባውን ምስጋና ቆጥረው ለይተው ያስተማሩን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ስለ ቅዱስ መስቀልም “ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ/ ኃይላችን፣ መመኪያችን (መጠጊያችን)፣ የመድኃኒት መገኛ ለሆነ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምስጋና ይገባል።” የሚለውን ምስጋና አስተምረውናል። በዚህች ጦማር ቅዱስ መስቀልን የምናከብርበትንና የምናመሰግንበትን ምክንያት እናብራራለን፣ ተያይዘው የሚነሱ የመናፍቃን ማምታቻዎችን እንሞግታለን፣  በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበረውን የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መሠረት እንዳስሳለን፣ የመስቀል በዓል ለምን የአዲስ ዘመን ምልክት ተደርጎ እንደሚከበርም እናብራራለን።

ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ!

ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት መጻሕፍት አንዱ የሆነው “መስተብቁዕ ዘመስቀል” እመቤታችን ድንግል ማርያምና ቅዱስ መስቀል በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ያላቸውን ሱታፌ አድንቆ፣ የጸጋ ምስጋናቸውን አመክንዮ ሲያስረዳ “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ/ለእነዚህ ሁለት ፍጥረታት (ለእመቤታችን ማርያምና ለቅዱስ መስቀል)  የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል፣ በክብር ተካክለዋልና (ተመሳስለዋልና) ይላል።” ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ ተረድቶ ለተመስጦ፣ ለጸሎት ከመጠቀም ይልቅ ትርጓሜን የፊደል ጨዋታ የሚያስመስሉ ሰዎች ይህን ምስጋና ባለማወቅ ይተቹታል። ሰይጣን ለአዳም የተሰጠ ትዕዛዝን አዛኝ መስሎ በማጣጣል ወደሞት እንደመራው እነዚህም ሰዎች መግቢያ ቀዳዳ በመሰላቸው መንገድ ሁሉ እየገቡ ርትዕት አስተምህሯችንን፣ የቀናች የቅዱሳን አባቶቻችንን ሃይማኖት በአላዋቂነት በመተቸት የሚደነግጡላቸውን የዋሀን ምዕመናንና ያወቁ የመሰላቸው ፊደላውያን ካህናትና መምህራንን ያስታሉ።

ይሁንና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የሥላሴን ክብር ለፍጡራን አትሰጥም። የእመቤታችንና የቅዱስ መስቀልም ክብር ተለይቶ የታወቀ ነው። “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን” የሚለው የመስተብቁዕ ክፍልም ማን ፍጡር፣ ማን ፈጣሪ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፣ የሚያከራክርም አይደለም። ስህተት ፈላጊዎቹ ግን በግልፅ ከሚታወቅ አስተምህሮ ይልቅ እንደ ሰይጣን “የተደበቀ  ዓላማ” ያለው የሚመስላቸውን “እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ” የሚለውን በመጥቀስ የጸጋ ግምጃ ቤት የሆነች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ይተቻሉ። ይህም በሕግ ቋንቋ እግረ መንገድ የተጠቀሰን አገላለፅ (obiter) እንደዋና ሀሳብ ወስዶ፣ ያንንም አጣሞ የሚተረጉም አላዋቂ ነገረፈጅ መሆናቸውን ያሳያል። ፍጡራን የፈጣሪን ምስጋና በጸጋ ወሰዱ ማለት “ፈጣሪ ሆኑ” ማለት ነው ብሎ ማሰብ እንዴት ያለ አላዋቂነት ነው?!

በቀላል ምሣሌ ለማስረዳት ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ልዩ ምስጋና “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር” የሚለው መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል። (ኢሳ. 6:3፣ ራዕይ 4:8) በጥሬ ንባብ ካየነው መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር በቀር ቅዱስ የለም ይለናል። (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2:2) በአንፃሩ ደግሞ ቅዱሳን ሰዎችን፣ መላእክትን፣ ከተሞችና ተራሮችን ሳይቀር “ቅዱስ” ብሎ ይጠራቸዋል? (1ኛ ጴጥ. 1:16፣ 2ኛ ጴጥ. 1:18፣ ኢሳ. 62:1-3፣ ራዕይ 21:2) ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪን ምስጋና ለፍጡራን ሰጠ ያስብላል? አያስብልም። ይቅርና የእግዚአብሔርና የፍጡራን ቅድስና፣ በፍጡራን መካከል ያለ የቅድስና ደረጃ እንኳ በቃላት ቅፅል ብቻ የሚለይ፣ የሚታወቅ አይደለም።

እግዚአብሔርን ቅዱስ ስንል የቅድስና ምንጭ፣ በባሕርይው ምንም ምን ሕፀፅ የሌለበት መሆኑን እንናገራለን። እመቤታችንን ቅድስት ስንል ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ መለየቷን/መጠበቋን እንናገራለን። ቅዱስ መስቀልን ስናስብ የመዳናችን ዓርማና ምልክት መሆኑን እንመሰክራለን። ለሁሉም “ቅዱስ” የሚለውን መግለጫ መጠቀማችን ለፊደላውያን አንድ ቢመስላቸውም በመንፈስ ለሚኖሩ፣ በአግባቡ ለሚረዱ ግን ትርጉሙ የተገለጠ ነው። መስተብቁዕ ዘመስቀል ከላይ በተገለፀው ዐውድ እመቤታችንና መስቀልን “በክብር የተካከሉ” ማለቱም የመለኮት ዙፋን በመሆን የተካከለ (የተመሳሰለ) ግብር አምላካዊ ስለተገለጠባቸው እንጂ የፍጡራን ምስጋና ከፈጣሪም ሆነ እያንዳንዳቸው በንፅፅር የሚምታቱ፣ የሚደበላለቁ ናቸው ማለት አይደለም።

"ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ/ እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!" 

የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ሊቁ አባታችን ቅዱስ ኤራቅሊስ እመቤታችንና ቅዱስ መስቀል ዕሩያን (የተካከሉ) የሆኑበትን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ በአንክሮ በገለጠበት የሃይማኖተ አበው ንባብ ያመሰጠረው ምሥጢር፣ የመሰከረው ሃይማኖት የእኛም ሃይማኖት ነው። “ኦ ከርሥ ዘተጽሕፈ ውስቴታ መጽሐፈ ግእዛን እምግብርናት ለኩሉ ሰብእ!/ለሰው ሁሉ ከመገዛት የነፃነት መጽሐፍ የተጻፈበት ማሕፀን ወዮ እንደምን ያለች ናት?” ብሎ  ማሕፀነ ድንግል ማርያምን እንዳመሰገነ “ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ/ እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!” በማለት ደግሞ የቅዱስ መስቀልን ክብር፣ የእመቤታችንን ልዕልና አስተምሮናል። (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ ምዕራፍ 48:15-17)

የቅዱስ መስቀል የክብሩ መሰረት እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለገለበት መቅደስ መሆኑ ነው። ካህን (አገልጋይ) መባል ለፍጡር የሚስማማ ነው። የሰማይና የምድር ጌታ እግዚአብሔር ካህን (አገልጋይ) መሆኑ (መባሉ) ግን ይደንቃል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ በአገልጋይ ሥርዓት ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን (ዐወቃችሁን)?” በማለት በዮሐ. 13:12 የተናገረው ቅዱስ ቃል በዕለተ ዓርብ የፈጸመውን ዘላለማዊ አገልግሎት በአንክሮ ለመረዳት ይጠቅመናል። መምህረ ትህትና፣ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልዪ ሊቀ ካህናት ብላ የምታመሰግነው አገልጋይነቱ ከኅሊናት ኹሉ በላይ ስለሆነ ነው።

በቸርነቱ ልዩ ሊቀ ካህናት ሆኖ ራሱን የተወደደ መሥዋእት አድርጎ ያቀረበ፣ መሥዋእቱን እንደ እግዚአብሔርነቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተቀበለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለገለበት የቀራንዮ መቅደስ እንደምን የከበረ ነው?! ፍጡራን የሆኑ የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ዘላለማዊ ሕይወት የማያስገኝ፣ የሚያልፍ መሥዋእት ያቀረቡባቸው መቅደሶች ክቡራን ከተባሉ ራሱ እግዚአብሔር ያገለገለበት፣ የከበረ ሥጋውን፣ የተቀደሰ ደሙን መሥዋእት አድርጎ እስከ ዓለም ፍፃሜ ለሚመጡ ካህናትና ምእመናን ባርኮ የሰጠበት፣ መዳናችን የተፈጸመበት ቅዱስ መስቀል ክብሩ፣ ገናናነቱ እንዴት ሊገለፅ ይችላል? ስለሆነም ዘወትር በመልክአ ኢየሱስ ጸሎታችን “ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናቲነ አስተጋብአነ ኀበ ትረፍቅ መካነ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንህነ።” እያልን በፈቃዱ አገልጋይ ለተባለ ጌታ በፈቃዳችን እንገዛለታለን፣ ያገለገለበትን መቅደስ: ቅዱስ መስቀሉንም በልዩ ክብር እናከብረዋለን።

ሰይጣን ባጣመመው የመናፍቅነት ልቦና ይህን የምታነብ ዓይን ሆይ አንድ ጥያቄ እንጠይቅህ: “ከሙሴና ከሙሴ ፈጣሪ ከክርስቶስ ማን ይልቃል? ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የተነጋገረባት ድንኳን ከተገለጸው ረድኤተ እግዚአብሔር የተነሳ ንዑድ ክቡር ተብላ ጫማውን ያላወለቀ የማይገባባት ከሆነች ራሱ እግዚአብሔር ያገለገለባት፣ መቅደስ (ቅዱስ መስቀልማ) ክብሯ ምን ያህል ይሆን? ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙባት በሙሴ እጅ የተሰጠችውን ታቦት ክብሯን ንቀው ያቃለሉት ዳታንና አቤሮን ምድር ተከፍታ ከዋጠቻቸው ራሱ እግዚአብሔር ያገለገለበትን (ሥጋውን ደሙን ያዘጋጀበትን) ቅዱስ መስቀል ክብር በሰይጣን ማታለል የሚያቃልል ሰውማ በቸርነቱ አገልጋይ በተባለ ጌታ ፊት ምን ያህል ጎስቋላ ይሆን?!” ስለዚህ ኅሊናችንን በክህደት አናጎስቁል። ይልቁንስ እንደ ቅዱስ ኤራቅሊስ ያሉ የከበሩ ምስክሮች ካሉልን እኛም እንደ አባቶቻችን “በክብር የተካከሉ” እመቤታችን ድንግል ማርያምንና ቅዱስ መስቀልን በጸጋ ምስጋና እናመሰግናቸዋለን፣ እናከብራቸዋለን እንጂ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ሰይጣን፣ ያልተባለውን እንደተባለ አስመስለው ከቀናች አስተምህሮ ሊያወጡን የሚደክሙትን ፊደላውያን አንከተላቸውም።

የሞት ምልክት የነበረ መስቀል የሕይወት መገኛ ሆነ!

የመስቀል በዓል የሚከበረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት የከበረ የእንጨት መስቀል በአይሁድ ክፋት ከተቀበረበት የቆሻሻ ክምር በቅዱሳን ጸሎት፣ በምዕመናን ጥረት፣ በእግዚአብሔር ተዓምር የተገኘበትን ዕለት ለማሰብ፣ ከበዓሉም በረከትን ለመሳተፍ ነው፡፡ ጌታችን እኛን ለማዳን ሰው ሆኖ፣ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለመስጠት በአይሁድ ዘንድ የተረገመ ተብሎ ይታወቅ በነበረው የመስቀል ስቅላት ሞትን በፈቃዱ ተቀብሎ የሞት ምልክት የነበረ መስቀልን የሕይወት መገኛ ወደመሆን ለውጦታል፡፡

ቅዱስ መስቀል ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ የተዓምራት ምንጭ ሆኖ የሚዳስሱት ከልዩ ልዩ ደዌያት ይድኑ ነበር፡፡ ይህም የአይሁድን የሐሰት ወሬ የገለጠ ነበር፡፡ አይሁድ በሐሰት ወሬ ጌታችን ከሞት ተለይቶ መነሳቱን ይክዱ ነበርና፡፡ ይልቁንም ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሰረቁት እንጂ አልተነሳም ይሉ ነበር፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ደግሞ በእውነት ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን፣ ከትንሣኤም በኋላ በልዩ ልዩ መንገድ የተገለጠላቸውን የጌታችንን ትንሣኤ አጽንተው ይመሰክሩ ነበር፡፡ ከቅዱስ መስቀሉ የተነሳ የሚደረገው ተዓምር የአይሁድን ሐሰት፣ የቅዱሳን ሐዋርያትን እውነት ስለገለጠ ብዙዎች በክርስቶስ አምነው ይጠመቁ ነበር፡፡ አይሁድም በዚህ ተበሳጭተው በኢየሩሳሌም ከተማ ባለ ቆሻሻ መጣያ ቅዱስ መስቀሉን ቀብረው በዘመናት ሂደት የቆሻሻ ተራራ ፈጠሩበት፡፡

የአይሁድ ተንኮል የክርስትናን መስፋፋት አላስቀረውም!

ምንም እንኳ የአይሁድ ተንኮል የሐዋርያትን አገልግሎት፣ የክርስትናን መስፋፋት ባያስቀረውም የድኅነታችን ዓርማ፣ የሕይወት ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም መገኛ ቅዱስ መስቀል መጣልና መጥፋት በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች “የቤትህ ቅንዓት በላኝ” (መዝ. 68፡9፣ ዮሐ. 2፡17) እያሉ እንዲቆጩ ያደርጋቸው ነበር፡፡ ይሁንና በዘመኑ ኃያላን የነበሩት የሮማ ነገሥታት ጣዖት አምላኪዎች ስለነበሩ ክርስቲያኖችን በማሳደድና በመግደል፣ የክርስትና ቅርሶችንም በማጥፋት የሚታወቁ ስለነበሩ የመስቀሉን ነገር ማንሳት ከባድ ነበር፡፡ ከዘመናት በኋላ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሰራበት፣ ተዓምራቱን የሚገልጥበት ጊዜ መጣ፡፡ “የቤትህ ቅንዓት በላኝ” እያሉ ስለክርስቶስ መስቀል መጥፋት ይጨነቁ ከነበሩ ጽኑዓን ክርስቲያኖች አንዷ ቅድስት እሌኒ ነበረች፡፡ እርሷም የክርስቶስን መስቀል መሳለም፣ ከተቀበረበት ፈልጎ ማውጣት ተምኔቷ ነበር፡፡ በ326 ዓ.ም. ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ስለነገሠ ጽኑ ክርስቲያን የሆነች እናቱ ቅድስት እሌኒ መስቀሉን መፈለግ ጀመረች፡፡ ፍለጋዋ ግን አስቸጋሪ ነበር፡፡

ከ70 ዓ.ም. ጀምሮ ኢየሩሳሌም በወራሪዎች ፈራርሳ፣ ህዝቡም ተበትኖ ስለነበር ታሪኩን የሚያውቅ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ የቤተክርስቲያንን ታሪክ ያለምስክር የማይተው ጌታ ግን ቅድስት እሌኒን ኪራኮስ ከሚባል አረጋዊ ጋር አገናኛት፡፡ ኪራኮስም ለንግሥት እሌኒ “ከእነዚያ ሦስት የቆሻሻ ተራሮች በአንዱ መስቀሉ ተቀብሯል፡፡” አላት፡፡ አይሁድ ግራ ለማጋባት ሦስት የቆሻሻ ተራሮችን ከ300 ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ፈጥረው ነበርና ለንግሥት እሌኒ ትክክለኛውን ተራራ መርጦ ለመቆፈር በጥበበ እግዚአብሔር የእንጨት ደመራን ደምራ በመለኮስ እጣን ጨመረችበት፡፡ የደመራው እሳትና ጭስ የቅዱሳን ጸሎት ከሚያርግበት እጣን (ራዕይ. 5፡8) ጋር ተቀላቅሎ መስቀሉ የተተከለበትን ተራራ ጠቆመ፡፡ እንጨቶችና ቅጠሎች በአንድነት ነድደው የእንጨቶች ሁሉ ንጉሥ የሆነ ቅዱስ መስቀል የተቀበረበትን አሳዩ፡፡ እመቤታችን ግዕዛን ካላቸው ፍጡራን (ሰዎችና መላእክት) ሁሉ የበላይ እንደሆነች ቅዱስ መስቀልም ግዕዛን ከሌላቸው ፍጡራን (እንስሳትና ዕጽዋት) የበላይ መሆኑ ተገለጠ፡፡

ቅድስት እሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ከተቀበረበት ያወጣችው መጋቢት 10 ቀን ነው::

ያን ተራራ ከመስከረም 17 እስከ መጋቢት 10 ድረስ ከስድስት ወራት በላይ ቆፍረው ሦስት መስቀሎችን አገኙ፡፡ ከእነርሱ አንዱ ጌታችን የተሰቀለበት ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በግራና በቀኙ የተሰቀሉት ሽፍቶች መስቀል ነበር፡፡ የቅድስት እሌኒ መንግስታዊ ባለጸግነትና ጥበብ ተራራ መቆፈር እንጂ እውነተኛ የክርስቶስ መስቀልን ከሚመሳሰሉት የሽፍቶች መስቀል መለየት አያስችልም፡፡ ቅድስት እሌኒም ቀድማ እንዳደረገችው በጥበቧና በጥረቷ ብቻ ሳትመካ በፈቃደ እግዚአብሔር እውነተኛው መስቀል እንዲገለጥላት ከካህናትና ምዕመናን ጋር ጸሎት አቀረበች፡፡

የተዓምራት ባለቤት እግዚአብሔርም ከቅዱስ መስቀሉ ልዩ ልዩ ተዓምራትን ገለጠ፡፡ የጌታ መስቀል በተዓምራቱ ከሽፍቶቹ መስቀሎች ተለይቶ ታወቀ፡፡ ቅድስት እሌኒም የጌታን መስቀል አገኘች፤ ተምኔቷ ተፈጸመ፡፡ ከዘመናት በኋላም በየሀገራቱ ያሉ ክርስቲያን ነገሥታት መስቀሉን ለበረከት ተካፈሉት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም በደጉ ክርስቲያናዊ ንጉሥ በአጼ ዳዊት ዘመን የጌታችንን ግማደ መስቀል (የቀኙን ክፍል) በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በደጋግ ምዕመናንና ነገሥታት እምነትና ትጋት አገኘች፡፡ ዛሬ በግሸን ደብረ ከርቤ የሚገኝ ይህ መስቀል ከብሉይ ኪዳን ስጦታችን ከታቦተ ጽዮን ቀጥሎ ከጌታ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተቀበለችው የእምነት ስጦታ ነው፡፡

ቅድስት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ያደረገችው ፍለጋ የክርስትና ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን የተባላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አስተውሉ ቅድስት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ያደረገችው ፍለጋ፣ ጥረትና የእግዚአብሔር ረዳትነት ለእያንዳንዳችን የክርስትና ሕይወት ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የክርስትና ዓላማ ሰማያዊ መንግስትን መውረስ ነው፡፡ ያለ እምነት (በክርስቶስ አምላክነት ሳያምኑ) ሰማያዊ መንግስትን ማግኘት አይቻልም፡፡ (ሮሜ. 3፡25) ያለ እምነት በሥራ በመመካት የሚገኝ ጽድቅ የለም፡፡ (ሮሜ. 9፡31) ይሁንና በዘመናችን ስንፍናቸውን በጥቅስ ለመሸፈን የሚፈልጉ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በተራ ጥራዝ ነጠቅ የመረጣ ንባብ ለሚረዱና ለሚተረጉሙ ሰዎች (picky readers) እንደሚመስላቸው እምነት ያለሥራ ለድኅነት የሚያበቃ አይደለም፡፡ ሰዎችን ከአጋንንት የሚለያቸው እምነት ሳይሆን በእምነት ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ በጎ ምግባር ነው፡፡

እምነቱን በምግባር የማይገልጽ ሰውም በእግዚአብሔር መንግስት ድርሻ የለውም፤ ከአጋንንት ጋር ይቆጠራል እንጂ፡፡ (ያዕቆብ 2፡17-26፣ ሐዋ. 14፡22) በምግባራችን ደካሞች ብንሆን እንኳ ሰው በምግባሩ ብቻ እንደማይድን አውቀን የእግዚአብሔርን ረዳትነት ተስፋ እያደረግን የአቅማችንን ልንፈጽም ይገባል እንጂ በውድድር መሀል ህጉን እንደሚቀይር አጭበርባሪ “ለመዳን ስራ አያስፈልግም” ለሚል ፍጹም ሰይጣናዊ ማመቻመች ተላልፈን መሰጠት የለብንም፡፡ ይህንንም ዛሬ የተቀደሰ ታሪኳን ከምናነሳላት ከቅድስት እሌኒ መማር እንችላለን፡፡ ጽኑዕ ክርስቲያን የሆነች እምነትን ከምግባር በተዋሕዶ ያስተሳሰረች ቅድስት እሌኒ በሥራዋ ብቻ መስቀሉን ፈልጋ አላገኘችውም፤ ፍለጋዋ በእምነት የተመሠረተ ነበር፡፡ እንዲሁም በእምነት ተመክታ እንደሰነፎች “ጌታ ተራራውን እንዲቆፍርላት” በመመኘት አላቆመችም፡፡ የራሷን ድርሻ ስለተወጣች ከአቅሟ በላይ የሆነውን በእምነት የፈለገችው ጌታ ገለጠላት፡፡ እኛም ከአስመሳዮች ማታለል ተጠብቀን እምነታችንን በሥራ ልንተረጉም እንደሚገባ ትምህርት ስለሆነችን ታሪኳን እንዘክራለን፣ በጸሎታችን እናስባታለን፣ በጸሎቷ እንማጸናለን፡፡ ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ካለው የጸሎት ኃይል ይልቅ ከሥጋ ሞት በኋላ የሚኖረው ጸሎት የበለጠ ነውና፡፡

ቀደምት ሊቃውንት በዓለ መስቀሉ መስከረም 17 ቀን እንዲሆን ወስነዋል!

ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅድስት እሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ከተቀበረበት ያወጣችው መጋቢት 10 ቀን ነው፡፡ ይሁንና ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በዓሉ መስቀሉ ከተቀበረበት ከወጣበት ቀን ይልቅ ደመራው በተለኮሰበት፣ ቁፋሮው በተጀመረበት፣ በቅዱስ መስቀል ስም የታነጸ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በከበረበት መስከረም 17 ቀን እንዲሆን ወስነዋል፡፡ ለዚህ ከሚቀርቡ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መጋቢት 10 የፆም ወቅት ስለሆነ በመስቀሉ መገኘት እንደተደሰቱ እንደ ንግስት እሌኒና በዘመኗ የነበሩ ምዕመናን በዓሉን በደስታ፣ በመብል በመጠጥ ለማክበር ስለማይመች ነው፡፡ ይህም ለቅዱስ መስቀል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በአርባ ፆም የሚከበሩ የንግሥ በዓላትም የሚሰጥ አመክንዮ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መስከረም ለኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ ወር ስለሆነ ቅዱስ መስቀልም በብዙ መልክ የአዲስ ዘመን ምልክት ስለሆነ የአዲስ ዘመንን ምልክት በአዲስ ዘመን መጀመሪያ ለማክበር ነው፡፡

ቅዱስ መስቀል የአዲስ ዘመን ብስራት መሆኑን ማሳያዎች 

ቅዱስ መስቀል በዓለመ መላእክት ዲያብሎስ (ሳጥናኤል) በቅዱሳን መላእክት ላይ የነበረው ኃይል በኋላ ዘመን በሚገለጥ የመስቀል ኃይል የተሸነፈበት፣ በዓለመ መላእክት ለነበረች ቤተ ክርስቲያን አዲስ ዘመን የተበሰረበት ምልክት ነው፡፡ (ራዕይ 12፡11) በዘመነ ብሉይ መስቀል የመርገም ምልክት ነበር፡፡ በዘመነ ሐዲስ ግን ቅዱስ መስቀል ከኦሪት መርገም የተላቀቅንበት የሐዲስ ኪዳን (የአዲስ ዘመን) የምንመካበት ምልክት ነው፡፡ (ገላትያ 3፡13፣ ገላትያ 6፡14፣ 1ኛ ቆሮ. 1፡18)

“መስቀል” ማለት መከራ ማለት ነው፡፡ መስቀል ስንልም ጌታ የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀል ብቻ ሳይሆን እኛን ለማዳን ከጽንሰት እስከ ሞት የተቀበለውን መከራ ሁሉ ማለታችን ነው፡፡ መስቀል የሚለው በዋናነት የክርስቶስን የመስቀል ላይ መከራ ለመግለጽ የሚውለውም የመከራው ከባዱ ክፍልና፣ ፍጻሜ ስለሆነ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ቅዱሳን ስለሃይማኖታቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ቃል እጅግ ብዙ መከራዎችን (መስቀል) ተቀብለዋል፡፡ ይሁንና ድኅነት በራስ ጥረት ሳይሆን በእምነት የሚገኝ የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና ከክርስቶስ ቤዛነት (መከራ መስቀል) በፊት የነበረ መከራቸው ድኅነትን አላስገኘላቸውም፡፡ እንዲያውም መልካም ስራቸው “እንደ መርገም ጨርቅ” ሆነ ተብሏል፡፡ (ኢሳይያስ 64፡6)

ከጌታችን መከራ መስቀል በኋላ ግን ስለ ሃይማኖት (እምነት) መከራ መቀበል እንደ ዘመነ ብሉይ ዋጋ የሌለው ሳይሆን በእምነት ተደግፈን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት መሰላል እንጂ ዋጋ የሌለው አይደለም፡፡ (ሐዋ. 14፡22፣ ማቴ. 5፡1-ፍጻሜ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡” (ማቴ. 10፡38) ያለው ይህንኑ ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል እንደ መርገም ጨርቅ ይቆጠር የነበረ ምግባር ኃይል ያገኘበት የአዲስ ዘመን ብስራት ነው፡፡ (ፊልጵ. 2፡12)

መስከረም የአዲስ ዘመን መገለጫ መሆኑ አከባበሩም ከደመራና ከመስቀል ጋር የተያያዘ መሆኑ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ መሠረት ባለው መንፈሳዊ አስተምህሮ የማይመሩ፣ ይልቁንም የታሪክ አጋጣሚዎችንና ማኅበራዊ ተቃርኖዎችን በመጠቀም ለዘመናት በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ጸንቶ ይኖር የነበረውን (በተለይም በደቡቡ የኢትዮጵያችን ክፍል የሚገኙ ምዕመናንን) በለብ ለብ ይዘት አልባ ጩኸት (contentless noise) በክርስትና ስም ወደ ተሳሳተ አስተምህሮ የወሰዱ ቡድኖች ለዘመናት የሰሩት ታሪክን የማጥፋት ተንኮል ቢያደበዝዘውም ያላጠፋው የታሪካችን አካል ነው፡፡ እኛም ኦርቶዶክሳውያን እንደ ቅድስት እሌኒ የተቀበረውን የምናወጣበት፣ የተንኮልን ተራራ በጥበበ እግዚአብሔር የምንንድበት ጥበብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህን ወቅት መሻገር የምንችለው እንደ አባቶቻችን መንፈሳዊውን ነበር በማስቀደም ቤተ ክርስቲያንን የየትኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ማራገቢያ ከማድረግ ስንጠበቅ ነው፡፡

የመስቀሉ ቃል ለእኛ የእግዚአብሔር ኃይል ነው!

ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፡፡ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው (1ኛ ቆሮ 1፡18)፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ‹‹የመስቀሉ ቃል›› የሚለውን በሦስት ይተረጉሙታል፡፡ የመጀመሪያው በመስቀል ላይ የተሰቀለው ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሁለተኛው ጌታችን በመስቀል ላይ የተናገረው ቃል ነው፡፡ እነዚህም ሰባቱ አጽርሀ መስቀል ናቸው፡፡ በሦስተኛም የመስቀሉ ቃል የሚለው ነገረ መስቀሉን (መከራውንና ምልክትነቱን) ነው፡፡

ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድ ክርስቶስን አንገላተው የሰቀሉት ምዕመናን እንዳይከተሉት፣ እንዳያምኑበት አስበው ነበር። ኃይል ያሳጡት መስሏቸው ነበር። አይሁድ የድካም ምልክት የመሰላቸው የጌታችን ትሁት ስብእና (በአትኅቶ ርእስ የተፈፀመ የማዳን ሥራ) ለእኛ በስሙ ለምናምን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ስለሆነም “የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን”፣ እንመካበታለንም። “ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ስንፍና (ሞኝነት) ነው። ለእኛ ለዳንነው ግን…ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል ነው።” (1ኛ ቆሮ. 1:23-25) ስለሆነም “ልዑል ክንዱን ሰደደልን”፣ እግዚአብሔር የኃይሉን መገለጫ ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮ አዳነን በማለት ዘወትር በሰኞ ውዳሴ ማርያም እናመሰግነዋለን።

በሁለተኛ ደረጃ የመስቀሉ ቃል ተብለው የሚተረጎሙት ጌታችን በዕፀ መስቀል ላይ፣ ዘላለማዊ አገልግሎትን ባገለገለበት መቅደስ ላይ ሆኖ የተናገራቸው ሰባቱ አጽርሃ መስቀል (የመስቀል ላይ ንግግሮች) ናቸው። ፈያታዊ ዘየማንን (በጌታችን ቀኝ የተሰቀለውን ሽፍታ) ያዳኑ፣ ዲያብሎስን በእሳት ዛንጅር ያሰሩ፣ የአዳምንና የልጆቹን የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የሰቆቃ ለቅሶ ያስቀሩ፣ እመቤታችንን በዮሐንስ በኩል ለቤተ ክርስቲያን በእናትነት የሰጡ፣ የሰው ልጆችን የጽድቅ ጥማት ያረኩ፣ ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ የነበሩ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚኖሩ ምዕመናንን በደልና ኃጢአት ያስተሠረዩ፣ የድኅነት ተስፋቸውን “ተፈፀመ” ብለው ያወጁ እነዚህ አምላካዊ የመስቀል ላይ ቃላት ጌታችንን ለሰቀሉ አይሁድ፣ ነገረ ስቅለቱን እንደ ተራ ታሪክ ለሚያስቡ ሰዎች የድካምና የሞኝነት ንግግሮች ቢመስሉ እንኳ ለእኛ በመስቀሉ ለዳንን፣ ለምንድን ምዕመናን ግን የእግዚአብሔር ኀይል መገለጫዎች ናቸው። “የእግዚአብሔር ስንፍና ከሰው ይልቅ ይጠበባልና፣ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።” (1ኛ ቆሮ. 1:25)

በሦስተኛ ደረጃ የእግዚአብሔር ኀይል የተባለው እግዚአብሔር ራሱ ያገለገለበት መቅደስ፣ ቅዱስ መስቀል ነው። ቅዱስ መስቀል የክርስቶስ የሚያድን መከራ፣ የሚፈውስ ቁስል ወካይና ክርስቲያኖች ቀስት ከተባለ የዲያብሎስ ፍላጻ ራሳችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ሀገራችንን የምንጠብቅበት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምልክት ነው። ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ እንዳለ “ወወሃብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ፣ ከመ ያምስጡ እም ገፀ ቅስት ወይድኃኑ ፍቁራኒከ/ ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፣ ወዳጆችህ እንዲድኑ።” (መዝ. 59:4)  በዓለመ መላእክት ለዲያብሎስና ሰራዊቱ፣ በዘመነ ሐዋርያት ለሲሞን መሠርይና መሰሎቹ፣ በዘመነ ሊቃውንት ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ወደረኞች፣ በእኛ ዘመንም ላሉ የመስቀሉ ጠላቶች የመስቀል ምልክት ኃያልነት አልገባቸውም፣ አይገባቸውም።

ስለሆነም አካላዊም አስተሳሰባዊም ቆሻሻ እየከመሩ መስቀሉን ሊያጠፉ፣ ትእምርትነቱን በአልባሌ ነገር ሊተኩ ሞክረዋል፣ እየሞከሩም ነው። ለእኛ ለዳንን፣ ለምንድን ግን መስቀል የድኅነታችን ዓርማ፣ የቤተ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ አሸናፊ የመሆን ምልክት ነው። ስለሆነም ሊቃውንት አባቶቻችን እንዳስተማሩን “ተሲነነ ዘወንጌል ቃለ ኅቡረ ተመርጉዘነ መስቀለ/የወንጌልን ቃል ተጫምተን መስቀልን በኅብረት (በአንድነት) እንመረኮዛለን።” ብለን እንዘምራለን፣ በሕይወታችን ኹሉ በቅዱስ መስቀል ምልክት የጠላቶቻችንን ቀስት እንመክታለን፣ እንደ ቅዱሳን መላእክትም የዲያብሎስን ሠራዊት እናሸንፍበታለን።

ይህንንም ዘወትር በጸሎታችን እንዲህ እያልን እንመሰክራለን:- “መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ፣ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ፣ ወእለአመነ በኃይለ መስቀሉ ድኅነ/መስቀል ኃይላችን ነው፣ መስቀል መጽኛችን (መጽናኛችን) ነው፣ መስቀል ቤዛችን (ቤዛነት የተፈጸመበት መቅደሳችን) ነው፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው። አይሁድ ይክዱታል፣ እኛ ግን እናምነዋለን (መቅደስነቱን፣ መድኃኒትነቱን እንመሰክራለን)፣ ያመነውም እኛ በመስቀሉ እንድናለን፣ ድነናልም።” (ጸሎት ዘዘወትር/የዘወትር ጸሎት)

ማጠቃለያ: መስቀሉን በመስቀል

በመስቀል በዓል ገኖና ከብሮ መነገር፣ መታየት፣ መብራራት፣ መሰበክ ያለበት ሕይወት የሆነን የክርስቶስ መስቀል (መከራ)፣ ድል ያደረግንበት፣ የምናደርግበት የቅዱስ መስቀል ክብር፣ አይሁድ በተንኮል የቀበሩት የጌታ መስቀል መገኘት፣ የመስቀሉን መንፈሳዊ ትርጉምና ታሪካዊነትም በመጠቀምም የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት ማጽናት ብቻ መሆን አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት “መስቀልን ባለማክበር ፖለቲከኞችን ማበሳጨት” በሚል ተንኮለኛ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በመናጆ አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን በዓል በሞኞች ልጆቿ ሲያስተጓጉሉ ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለተቃውሞ ፖለቲካ ማድመቂያ ሲባል በተንኮለኞች ምክር፣ በአላዋቂና ቂላቂል ሰዎች አስተባባሪነት መስቀልን በአደባባይ ያለማክበር ውሳኔ ማስታወስ ይቻላል።

ያ እንደ ቀልድ የተጀመረ ሃይማኖትና ፖለቲካን በወገንተኝነት የመቀላቀል ክፉ ልማድ የተመኘነው ይመስል አሁንም “መስቀልን አታከብሩም!” በሚሉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ፉከራና የሞኞች ምዕመናን “መስቀልን ባለማክበር የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ” የሚያመጣውን መዘዝ እያየነው ነው።  ስለሆነም “በመስቀል በዓል ላይ ፖለቲካዊ ዓላማን በማራመድ” የሚገለጸው የመለካውያን አስተሳሰብ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም ስላልሆነ የክርስቲያናዊ አንድነት መገለጫ የሆነ መንፈሳዊ በዓላችንን፣ እግዚአብሔር ያገለገለበትን የቅዱስ መስቀልን ክብር መንፈሳዊም ዓለማዊም ዕውቀትና ብልሃት በሌላቸው ሰዎች አስተሳሰብ እየተመራን ዕንቁአችንን በእሪያዎች ፊት መጣል አይገባንም እንላለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን መመዘን በሚገባት መንፈሳዊ ሚዛን ሳይሆን ጥራዝ ነጠቆች በጫኑባት ልዩ ልዩ ርዕዮተ ዓለማዊ መነጽሮች መሆን የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ስስ ጉዳዮችን እየመረጡ ቤተክርስቲያንን ከምዕመናን፣ ምዕመናንን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል ሲጠቀሙበት የየግልና ቡድን አስተሳሰባችንን ወደጎን በመተው ቅዱሳን ሐዋርያት የሰበሰቧትን፣ በየዘመኑ የተነሱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል መብራቶች ያጸኗትን የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አንድነት በስሜት ሳይሆን በጥበብ ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉ እናት መሆኗ የሚገለጠው በምድራዊ ምልክት ሳይሆን “የአዲስ ዘመን ብስራት” በሆነ በቅዱስ መስቀልና በመስቀሉ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ማዳን በመግለጥ ነውና፡፡

አይሁድ እግዚአብሔር ያገለገለበትን መቅደስ (ቅዱስ መስቀልን) በመናቅና በማቃለል የቆሻሻ ክምር ቢደፍኑበትም የእነርሱ ክፉ ሥራ፣ የመስቀሉ ክብር እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ የቀደመ ባሏ አናንቆ በጣላት፣ እግዚአብሔር ግን “የመቅደሱ ሠራተኛ” አድርጎ ባከበራት በእሌኒ ንግሥት ጥረት ድጋሚ ተገልጧል። ዛሬም ተረፈ አይሁድ የመስቀሉን ክብር መከፋፈልና ጥላቻን በሚወልድ ነገር ግን በሽንገላ ንግግር “ስለ ፍቅር” አብዝቶ በሚያወራ የጥላቻ ፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ ክምር፣ በዘፈን በዳንኪራና በትርኢት ቁልል፣ ባሕሉን ሃይማኖት ሃይማኖቱን ባሕል በሚያስመስል ማምታታት ሊቀብሩት ሲሞክሩ እናያቸዋለን። እኛ ግን እግዚአብሔር ያገለገለበትን መቅደስ የምድራዊ ልዩነት፣ ወይም መንፈሳዊነት የተለየው ዓለማዊ አንድነት ማሳያ አድርገው ከሚስሉ ተረፈ አይሁድ ተለይተን እንደ አባቶቻችን መስቀሉን በመስቀል ሥፍራ እናቆማለን። እንደ ንግሥት እሌኒ በመስቀሉ ላይ የተደረቱ፣ የቆሸሹ መጋረጃዎችን በቀናች ኦርቶዶክሳዊት አስተምህሮ ብርሃንነት ለይተን እናሳያለን። በሊቁ አባታችን ቅዱስ ኤራቅሊስ አገላለፅ እግዚአብሔር ያገለገለበት መቅደስ፣ የቅዱስ መስቀሉ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን እንላለን፡፡ አሜን ለዘለዓለም።

ስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራት: ትኩረት የሚሹ ዐበይት ጉዳዮች

መግቢያ

አምላካችን እግዚአብሔር ሰማይና ምድር የማይወስኑት ምሉእ በኵለሄ (በዓለም ሁሉ የመላ) አምላክ ነው። በዓለም ሁሉ የመላ አምላካችን ራሱን በተለየ ሁኔታ በረድኤት ይገልፃል። እግዚአብሔር ራሱን በረድኤት ከሚገልፅባቸው ቦታዎች ቀዳሚዎቹ ስሙ የሚቀደስባቸው፣ አምላክነቱ የሚመሰከርባቸው ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። በየዘመናቱ የነበሩ ቅዱሳን በታላቅ መንፈሳዊ ትጋት የተቀደሱ መቅደሶችን አንጸው ለሰማያዊው እግዚአብሔር የተቀደሰ ምድራዊ ማደሪያን አዘጋጅተዋል። በቅን ልቦና፣ በመንፈሳዊ ሀሳብ ያዘጋጁለትን መቅደስም የቅድስና ምንጭ ቅዱስ እግዚአብሔር ባርኮላቸዋል፣ የበረከት የጸጋ መገኛም አድርጎላቸዋል።

አስቀድሞ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበትን ደብተራ ድንኳን በእግዚአብሔር ትዕዛዝ በመሥራት የመጀመሪያው ነው። ሕዝበ እስራኤል በደብተራ ድንኳን ለ900 ዘመናት ያህል ሲገለገሉ ቆይተው ጠቢቡ ሰሎሞን የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሠራ ሆኗል። ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር “ዓይኖቼና ልቤ በዚህ ይሆናሉ” ብሎ ቃል ኪዳን የገባበት ነበር። ይህም ቤተ መቅደስ በ500 ዓ.ዓ አካባቢ የፋርስ ንጉሥ በነበረው በናቡከደነፆር ቢፈርስም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በዘሩባቤል እንደገና ተሠርቶ ነበር። ይህን ቤተ መቅደስ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሆሳዕና ገብቶ ቤቴ ብሎታል፣ አጽድቶታል። በተነገረው ትንቢት መሠረትም በ70ዓ.ም በጥጦስ የሚመራ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋት ቤተ መቅደሱንም አፍርሶታል።

በሐዲስ ኪዳን የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚተጉት በቤት ውስጥ ነበር። ለምሳሌም የማርቆስ እናት የማርያምን ቤት መጥቀስ ይቻላል። በዘመነ ሰማዕታትም የዓላውያን ነገሥታት ግፍና መከራ በክርስቲያኖች ላይ ከብዶ ስለነበር ክርስቲያኖች ጸሎት የሚያደርጉት፣ መሥዋዕትንም የሚያቀርቡት በግበበ ምድር (ካታኮምብ) ውስጥ ነበር። ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በይፋ መሠራት የተጀመረው ክርስትና ከመሳደድ ወጥቶ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በታወጀበት በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ነው። ከዚያን ዘመን ጀምሮ በተለያየ ቦታ፣ መጠን፣ ቅርፅና ዲዛይን፣ በተለያዩ ዘመናት ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ታንጸዋል። በተለያዩ ዘመናት በእነዚህ ሕንፃዎች ላይ ጥቃት ቢደርስባቸውም ብዙዎቹ ከእኛ ዘመን ደርሰዋል።  ከቅርብ ዘመን ወዲህ ግን ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሂደት ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። በዚህች ጽሑፍም ቢሻሻሉ የምንላቸውን አስተሳሰቦችና አሠራሮች እንዳስሳለን።

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን

‘ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው ቃል አንዱ ዘይቤያዊ ትርጉሙ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር ቤት፣ የክርስቲያኖች የጸሎት ቤት፣ የክርስቲያኖች መኖሪያ ማለት ነው፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም መሠረትነት የምትተከል፣ በብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሜሮን የከበረች፣ ሥላሴ በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑባት፣ የክርስቶስ ሥጋዌ የሚነገርባት፣ በቀራንዮ የፈሰሰ የጌታችን ፈዋሽ ደም ዕለት ዕለት ከመንጠብም በላይ እንደአዲስ የሚቀዳባት፣ የከበረ ሥጋው የሚፈተትባትና ለምዕመናን የሚታደልባት ቅድስት መካን “ቤተ ክርስቲያን” ተብላ እንደምትጠራ ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ያስተምሩናል።

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ. 121: 1) ብሎ እንደዘመረው፣ ቅዱስ ሉቃስም “በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ” (ሐዋ. 11፡21) እንዳለው የቤተ ክርስቲያን አንደኛው ዘይቤአዊ ትርጕም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም “የእግዚአብሔር ቤት” (ዘፍ. 28: 17)፣ “በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ” (መዝ 5: 7)፣ “የአባቴ ቤት” (ሉቃ 2፡49)፣ “የእግዚአብሔር ቤት” (ዕብ 10፡21) የሚሉት ንባባት ይህን የሚያስረዱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ “ብዘገይ ግን፣ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው” (1ኛ ጢሞ. 3፡15) በማለት የገለጠው በዋናነት የእግዚአብሔር ቤት (ሕንፃ) ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡

ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን

በሰኔ 20 ስንክሳር እንደተገለጠው ቅዱሳን ሐዋርያት በፊልጵስዮስ በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ “በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ” ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ24፤ ወርዱን በ12 ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ይህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ19ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ4ኛው ዓመት ሰኔ 20 ቀን ሲሆን፣ በ21ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት (የክብሩ መገለጫ)፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ሆኖ ቀድሶ ካቆረባቸው በኋላ “እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ /ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ/” ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ከወንጌላዊው ከቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ለአምልኮ ይሰበሰቡ የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት (ሐዋ. 12:12) በፊልጵስዮስ በተሠራች በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያንም መንፈሳዊ ጉባኤያቸውን፣ አምልኮአቸውን ይፈጽሙ ነበር።

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት የአብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች ቤተ ክርስቲያን፣ ደብር ወይም ገዳም ተብለው ይጠራሉ። ደብር ማለት ‘ተራራ’ ማለት ሲሆን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል። ተራራ ከምድር ከፍ ብሎ ዙሪያ ገባውን ለመቃኘት እንደሚያስችል ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ከዓለም ተለይታ፣ ከፍ ብላ፣ ጽድቅን ከኃጢአት ለመለየት የምታስችል መሆኗን ያመለክታል። በተራራ ሰዎች ከጎርፍ፣ ከመከራ እንደሚጠለሉ በቤተ ክርስቲያንም ምዕመናን ከመከራ ሥጋ፣ ከመከራ ነፍስ ይጠለሉባታልና። ገዳም ደግሞ አገልግሎቱ በገዳማውያን ሥርዓት መሠረት ስለሚከናውን ይህንን ስያሜ ይዟል።

የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊታዊ የሥነ ሕንፃ ጥበብ ዓይነቶች አምስት ናቸው። እነርሱም ክብ ፤ መስቀል ቅርፅ ፤ ዋሻ ፤ ፍልፍል እና ሰቀልማ ናቸው። ክብ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት በብዛት በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን ባለሦስት ዙሪያ ክፍል ዙሪያ ክብ አሠራር ሆነው ውስጣቸው በሦስት ግድግዳ የተከፈለ (ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ) ሲሆን ስያሜው የተወረሰው ከግብሩ፣ ከሚሠጠው አገልግሎት ነው፡፡ መስቀል ቅርጽ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በብዛት በከተማ አካባቢ ይገኛሉ። ይህ አሠራር የምኩራብ ዓይነት ሲሆን የተወረሠው ከአይሁድ ምኩራብና በዘመነ ክርስትናም የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ በኢየሩሳሌም ካሠራችው ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ዋሻ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በብዛት በተራራማ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን በመጋረጃ የተከፈሉ ናቸው። ይህ አሠራር ራሱን ችሎ በዘመነ ሐዲስ መናንያን የሚገለገሉበት ቤተ ክርስትያን ነው፡፡ ሰማዕታት ከዓላውያን ነገሥታት ሸሽተው በዋሻ ሲሸሸጉ የጀመሩት የቤተ መቅደስ አሠራር ነው፡፡ በሩ አንድ ሲሆን በውስጥ ያሉትን ክፍሎች በአብዛኛውን ጊዜ በመጋረጃ የተከፈሉ ናቸው፡፡ ፍልፍል አብያተክርስቲያናት ደግሞ ከአንድ ቋጥኝ ተፈልፍለው የተዘጋጁ ናቸው። የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ሰቀልማ የሚባለው አሠራር ደግሞ ብዙውን ጉዜ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሆኖ ሞላላ የሆነና ከፍ ብሎ የሚታነጽ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሕንፃ ሃሳቡ የተወሰደው ጠቢቡ ሰሎሞን ካሠራው ቤተ መቅደስ ነው::

ትኩረት የሚሹ ዐበይት ጉዳዮች
ሕንፃ ሥላሴን ማነጽ ይቅደም!

የክርስትና ሃይማኖት ወሳኙ ግብ ሕንፃ ሥላሴ የተባለ የሰውን ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት በወንጌል መሠረትነት ላይ መገንባትና ለእግዚአብሔር መንግስት ማብቃት ነው። ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አገልግሎትም ይህ ነው። ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን መገንባት የዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት አንድ አካል እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም መመዘን ካለበት መመዘን ያለበት የምሥጢራት ተሳታፊ የሆኑ ምዕመናንን በማፍራት መሆን ይኖርበታል እንጂ ሕንፃ በማነጽ ብቻ መሆን የለበትም።

መንፈሳዊ ሕይወቱ የታነጸ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን በራሱ ተነሳሽነት ያንፃል፣ በረከትም ያገኝበታል። ነገር ግን ሕንፃ ሥላሴ የተባለ ሰውን በመንፈሳዊ ሕይወት በሚገባ ሳንገነባ ታላላቅ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናትን ለመገንባት መሞከር ውጤታማነቱ አጠያያቂ ነው። ለሕንፃ ሥራውም ቢሆን መንፈሳዊ ሕይወቱ ያልታነፀን ሰው ለሕንፃ ግንባታ በየጊዜው ገንዘብ ማዋጣት ‘ዕዳ’ ይሆንበታል። የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴዎችን ሥራ ከባድ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

ከዚህም ባሻገር ዛሬ ሕንፃ ሥላሴን እየገነባን ካልሄድን የሚሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማን ይሆናል? በተለይም በዝርወት ዓለም የሚሠሩት ሕንፃዎችን ተረክቦ የሚገለገልባቸው የወደፊት ትውልድ የመኖሩ ነገር አሳሳቢ ነው። ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ የምዕራባውያን ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰው የምዕመናን ማነስና ሕንፃዎቹ ለሌላ አገልግሎት መዋል በእኛም አብያተ ክርስቲያናት ላይ ሊደርስ ይችላል። ዛሬ ዛሬ ብዙዎች ይህን ስጋት ይጋራሉ። ይኹንና ተተኪ ሕፃናትና ወጣቶችን ጨምሮ በእምነትና ምግባር የጎለመሰ ምዕመን ለማፍራት የሚደረገው እንቅስቃሴ ትኩረት አይሰጠውም። በብዙ ቦታዎች የመምህራንና የካህናት ትኩረት የሚገነቡ ሕንፃዎች መሆናቸውን ታዝበናል። በመንፈሳዊ እይታ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት ላልታነፀ ምዕመን በድንጋይ ላይ ድንጋይ ደርቦ ሕንፃ መሥራት ትርጉም የለውም። ሕንፃ ለሰው እንጂ ሰው ለሕንፃ አልተፈጠረምና።

የሕንፃ ሥራው የምዕመናንን ብዛትና አቅም ያገናዘበ ይሁን!

ለእግዚአብሔር ከሁሉ የሚበልጠውን ማድረግ የበለጠ ዋጋ ያስገኛል። ይሁንና በየአካባቢው የሚሠሩ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የምዕመኑን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ከአቅም በላይ በሆነ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ለመገንባት ከምንደክም ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ በቂ የሚሆን ሕንፃን በጥራት ገንብተን የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል አገልግሎት የበለጠ ተደራሽ ማድረግ የተሻለ ይሆናል። በአንድ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘመናችንን ሙሉ ብዙ ገንዘብ ከምናወጣ ለአገልግሎቱ የሚበቃ ሕንፃ በአጭር ጊዜ ሠርተን ቀሪውን ጊዜ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማጠናከር ብናውለው ቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን ኅብረት) ትሰፋለች።

እያንዳንዱ ምዕመን በቅርብ ርቀት ላይ ሄዶ የሚገለገልበት ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገዋል። በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት በቀጣይነት ለማከናወን ደግሞ የምዕመናን ብዛትም ወሳኝ ነው። በቅርብ ርቀት ላይ ቤተ ክርስቲያን ባለበትና መንፈሳዊ አገልግሎቱ ተደራሽ በሆነበት ሁኔታም ሌላ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከመገንባት በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በታላላቅ የሀገራችን ከተሞች አብያተ ክርስቲያናት በቅርብ ርቀት የታነጹት የምዕመናንን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ ስለተሠሩ ነው። በዝርወት ዓለም ጥቂት ምዕመናንን ይዘው በአንድ አካባቢ (በቅርብ ርቀት) ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከመገንባት ተግባብቶ አብሮ መ(ማ)ገልገል የተሻለ ይሆን ነበር።

በተግባር የሚታየው ግን እድሜ ልካቸውን “አስተዳዳሪ” እየተባሉ በምዕመናን ሕይወት ላይ ሥጋዊ የበላይነትን በሚፈልጉ ካህናትና ከዓለም በቃረሙት የልዩነት ኮተት “የራሳቸው ቤተ ክርስቲያን” በሚፈልጉ ምዕመናን የተነሳ የሚፈጠር ማለቂያ የሌለው መከፋፈል ነው። በውጭ ሀገራት የሚገኘው ምዕመን በሀገር ቤት ያሉትን ለችግር የተጋለጡ ምእመናንና አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ ከመርዳት ይልቅ በቅርብ ርቀት የሚተከሉ የተከፋፈሉ አጥቢያዎችን ለ40 እና 50 ዓመታት የሚቆይ እዳ ሲከፍል እንዲኖር ማድረግ ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም።

ጥቂት ምዕመናንን ይዞ የመከፋፈሉ አካሄድ ሕንፃ በመገንባትም ይሁን አገልግሎቱን ከማስቀጠል አንጻር ያለው ጥቂት ምዕመን ላይ ጫና እንደሚፈጥር ያየ ያውቀዋል። በአንዳንድ ቦታዎችም ለሕንፃ ቤተክርስቲያን ማሠሪያነት የሚውል ገንዘብ የሚሰጥ ምዕመን ቁጥር ከማነሱ የተነሳ እያንዳንዱ የአጥቢያው አባል የተወሰነ መጠን ገንዘብ እንዲከፍል ሲጠየቅ ይስተዋላል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ለሕንፃው ሥራ ከሚያስፈልገው አንጻር ጥቂት መስሎ ቢታይም ወይም አንደንዶች በቀላሉ ሊከፍሉት የሚችሉ ቢሆንም የአካሄዱ አስገዳጅነት ግን ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮ ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡ ጥቂት ለማይባሉ ምዕመናንም ከባድ ጫናን የሚፈጥርና ያልጸኑትን ከቤተ ክርስቲያን ሊያርቅ የሚችል አካሄድ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የተዘጉትን፣ የተቸገሩትን፣ እየፈረሱ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትንም እናስብ!

በገጠርና በጠረፋማ አካባቢዎች ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ዝናብ እያፈሰሰባቸው፣ ንዋየ ቅድሳቱ ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው፣ ምዕመናኑ የሚናዝዛቸውና ቀድሶ የሚያቆርባቸው ካህን አጥተው እያለቀሱ በታላላቅ ከተሞች ያሉትን በወርቅና በዕንቁ ማስጌጥ ለቤተ ክርስቲያን መስፋት ምን ያህል ይጠቅማል? ቢያንስ በጥቂቱም ቢሆን ያለ ከባድ ችግር አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው። እነዚያ አብያተ ክርስቲያናት ካህን አጥተው እየተዘጉ፣ ዕጣንና ጧፍ አጥተው ቅዳሴ እየታጎለ፣ አልባሳት አጥተው ካህናት ሲቸገሩ ዝም ብሎ ትኩረትን መንፈግ ከአብያተ ክርስቲያናት አይጠበቅም። ‘ቤተ ክርስቲያን አንዲት’ ናት ስንልም በአንድ ሀሳብና በአንድ ልብ ሆኖ መደጋገፍን ያካትታል።

ይልቁንም ከዕድሜ ብዛትና ከዕድሳት እጦት የተነሳ እየፈረሱ ያሉት ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የበለጠ ትኩረትን ይሻሉ፡፡ እነዚህ ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ቅርስም መዝገብም ናቸው፡፡ ይህንንም ስንል በከተማ ያሉት ታላላቅ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያናትን መሠራት የለባቸውም ማለታችን ሳይሆን በገጠር ላሉት ማሰብንም ገንዘብ ያድርጉት ማለታችን ነው። ምዕመናንን ስለ አሥራት የሚያስተምሩ ለራሳቸው ግን ከገቢያቸው አሥራት የማያወጡ፣ ገቢ ባገኙ ቁጥርም እንደ ስስታም ነጋዴ ሌሎችን እየበደሉ ተጨማሪ ገቢ በመፈለግ የሚደክሙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምን ያደርጉልናል?!

በተጨማሪም ከቅርብ ዘመናት ወዲህም ጥቂት በማይባሉ አካባቢዎች በጽንፈኞች አማካኝነት በክርስቲያኖች ላይ ብዙ ግፍና መከራ እየደረሰ፣ ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ፣ ከፍተኛ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው፣ ንብረታቸው እየተቃጠለና እየተዘረፈ፣ አገልግሎት የሚያገኙባቸው አብያተ ክርስቲያናት እንደ ጧፍ በእሳት እየነደዱ ባሉበት ሁኔታ ከምንም በፊትና በላይ ለዚህ ቅድሚያ ለሰጠው ይገባል። በዚህም አስቸኳይ ድጋፍ ምዕመናንም አብያተ ክርስቲያናትም ዛሬም እንደ ጥንቱ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።

የሕንፃ ግንባታ ለልመናና ለሙስና አይዋል!

ምዕመናን ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ በሚያደርጉት አስተዋፅኦ ዋጋ ያገኙበታል። ሱታፌአቸውም እንዲጠናከር ማበርታት ይገባል። ነገር ግን ከቅርብ ዘመን ወዲህ የሕንፃ ሥራ እንደ አንድ የመለመኛ መንገድ እየተወሰደ መጥቷል። በየጉባኤው፣ በየበዓላቱ፣ በየሆቴሉ፣ በየመንገዱ ለሕንፃ ማሠሪያ እየተባለ ሲለመን ማየት የተለመደ ነው። ብዙ የንግድ ሥራዎችም ወደ ቤተ ክርስቲያን የገቡት “ሕንፃ ማሠሪያ” በሚል ምክንያት ነው። ይህ ዓይነቱ አሠራር ግን ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ችግሮች እያጋለጣት ይገኛል። በአንዳንድ ቦታዎች ሕንፃውን ሊያስጨርስ የሚችል ገንዘብ ከተገኘ በኋላም ለመለመኛነት ሲባል የሕንፃውን ሥራ የማጓተት ዝንባሌን አስተውለናል። በሌሎች ስፍራዎች ደግሞ ለሕንፃ ሥራ በሚል ከምእመናን የሚሰበሰበው ገንዘብ ለሙስና እየተጋለጠ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህንን ችግር ከመሠረቱ የሚቀርፍ አሠራርን መዘርጋት ወሳኝ ነው። ለሕንፃ ሥራው ድጋፍ የሚያደርጉ ምዕመናን ድጋፋቸውን በቀጥታ የሕንፃውን ሥራ ገንዘብ ለሚያስተዳድረው አካል የሚያደርሱበትንና የተፈለገው ሥራ ላይ የሚውልበትን አሠራር መዘርጋት ይገባል።

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የክርክር ምክንያት አይሁን!

ሁላችን የምናውቀው ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤትና ምዕመናን ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙባት የጸሎት ቤት መሆኗን ነው። ሕንፃውን “ቤተ ክርስቲያን” የሚያደርገው በውጭ የሚታየው ውበት ሳይሆን በውስጡ የሚገኘው ሕይወት ነው። ያማሩና ለዓይን የሚማርኩ ሕንፃዎችን ሠርተን ውስጣቸው ጥልና ክርክር ከነገሠ ከቶ ምን እናተርፋለን? የራሳቸው ሕንፃ ሳይኖራቸው ወይም በመቃኞ ሲገለገሉ የነበሩ ምዕመናን ሕንፃ ከገነቡ በኋላ የቀደመ ፍቅራቸው ከቀዘቀዘ ትርፉ ምንድን ነው?  በተለይም በውጭው (በዝርወት) ዓለም ባለው የብሔርና የፖለቲካ አሰላለፍ ምክንያት የሚፈጠረው ክፍፍል፣ ንትርክና የፍርድ ቤት ክርክር የሚጀምረው ሕንፃ ከተሠራ በኋላ መሆኑና ማዕከልም የሚያደርገው “ሕንፃው የማን ይሁን?” የሚለው ሆኖ መመልከት ያሳፍራል፣ ያሳቅቃልም።

ትልቁ ጉዳይም የፍቅር መጥፋቱ ሳይሆን የሕንፃው ‘ባለቤትነት’ ሲሆን እያስተዋልን ነው። በልዩነትና በክፍፍል ምክንያት የምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት በእጅጉ መጎዳት ተረስቶ ትኩረቱ ሁሉ ሕንፃ ላይ እየሆነ ነው። በየቦታው የሚከሰቱትን ችግሮች ላስተዋለ ሰው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የክርክር ማዕከል መሆኑ ያሳዝነዋል። የጸሎት፣ የምስጋናና የሰላም ማዕከል መሆን ያለበት ሕንፃ ‘የባለቤትነት’ ክርክር ሲነሳበት ማየት ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ላይ ብዙ መሥራት እንዳለብን ያመለክታል። መንፈሳዊ ሕይወትን በሚገባ ያለማነጽ አንዱ ውጤትም ይኸው ነው።

ታላላቅ የኢትዮጵያ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናትን "ካቴድራል" ብሎ መሰየም አይገባም!

ከላይ እንደተገለፀው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት “ቤተ ክርስቲያን፣ ደብር ወይም ገዳም” ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተለቅ ብሎ የሚታየውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ‘ካቴድራል’ እያሉ የመጥራት ልማድ መጥቷል። ካቴድራል የሚለውን የላቲን ስያሜ በሀገራችን መጠቀም የተጀመረው በ1924 ዓ.ም ነው። ይህም “ትልቅና በሦስት መንበር የሚቀደስበትንና ብዙ ምዕመናንን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ ነው” የሚሉ አሉ። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ አስቀድሞ የበቀለ ፈረንጅ አምላኪነት የወለደውን አረም በአመክንዮ ለማቃናት የሚቀርብ መጠገኛ እንጂ ከቀደምት አባቶቻችን የተቀበልነው አይደለም።

አብያተ ክርስቲያናትን ካቴድራል በሚል ቅጽል መጥራት ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የፈረንጅ ንጉሣውያን ቤተሰቦችን በብዙ መልኩ ለመኮረጅ ከነበረው ልማድ ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር አይስማማም። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን “ካቴድራል” የሚለው ስያሜ የመጣበት የታሪክ አጋጣሚ “በኦርጋን መዘመር፣ ያለ ቅዱስ ቁርባን ተክሊል መፈጸም፣ የመናፍቃንን አስተምህሮ የስልጣኔ ማሳያ አድርጎ ማየት” እና የመሳሰሉት የተስተዋለበት ጊዜ ነበር። እነዚህ ከትውፊታችንና ከታሪካችን የሚቃረኑ ልማዶች ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ በአመክንዮ ተሞግተው እንዲቀሩ ቢደረግም ለኢትዮጵያዊ አብያተ ክርስቲያናት “የፈረንጅ የዳቦ ስም” የመስጠቱ ልማድ ግን እየጨመረ ሄዷል።

ቀደምት አባቶቻችን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንፁ “ካቴድራል” የላቲን ቅፅል መስጠት አላስፈለጋቸውም። ከ1920ዎቹ በኋላ፣ በተለይም ባለፉት አምስትና ስድስት ዐስርት ዓመታት ግን ፈረንጅ አምላኪነት በመስፋፋቱ የሚያምር (ተለቅ ያለ) ዛፍ እንኳ ሲገኝ “የፈረንጅ” እያሉ የመጥራት ልማድ አለ። በአብያተ ክርስቲያናት ስያሜ የሚንፀባረቀውም ይህ የቅኝ ተገዥነት አስተሳሰብ ይመስላል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በየቦታው የምንሰማው “ይህን ቤተ ክርስቲያን አፍርሰን ትልቅ ካቴድራል እንገነባለን” የሚለው አላዋቂ ተናጋሪዎች የሚያደርጉት ንግግር ነው። ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቸርች፣ ደብር የሚለውን ማውንቴን፣ ገዳም የሚለውን ሞናስትሪ እያልን የራሳችንን ጥለን በተውሶ (ያውም አባቶቻችን ካቆዩልን ትውፊት በዘመንም በአመክንዮም በተለየ) ስያሜ መጥራት አሳፋሪ መሆኑን እንደምናውቀው ሁሉ በታሪክ አጋጣሚ የመጣን የፈረንጅ ስያሜ የታላቅነትና የክብር ማሳያ እያስመሰልን ራሳችንንም ታሪካችንንም ማዋረድ አይገባንም፡፡

በኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንቶች ዘንድ በአማርኛ እየተነጋገሩ ቤተ ክርስቲያን ከማለት ‘ቸርች’፣ ጉባኤ ከማለት ‘ኮንፈራንስ’፣ ንስሃ አባት ከማለት ‘ፓስተር’፣ የእግዚአብሔር ሰው ከማለት ‘ማን ኦፍ ጋድ’ ሲሉ የቃላት ምርጫው ጉዳይ አስተሳሰባቸውን በኢትዮጵያዊ ርዕዮት ያለመቃኘት ችግር እንደሆነ መረዳት ይቻላል፤ ከታሪካዊ ሂደታቸው አንፃር አያስገርምም። በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ግን እንዲህ ዓይነት መርህ አልባ “ፈረንጅ አምላኪነት” ሲታይ ይገርማል፣ ያሳዝናል፡፡ ስለሆነም የሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት አሰያየማችን ትውፊታችንና ታሪካችንን የተከተለ መሆን አለበት እንላለን።

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ አሠራር ሕግን፣ ሥርዓትንና ትውፊትን የተከተለ ይሁን!

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይኑ ከውጫዊ ውበት ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ትውፊት መገላጫነት ትኩረት የሚሰጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አሠራሩም ቢሆን በእያንዳንዱ ሂደት በሥራው የሚሳተፉት ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚሆን ትምህርትን እየቀሰሙ የሚሄዱበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይም የክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር የሚገለጥበት ታላቅ አገልግሎት ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉንም በመተሳሰብ በጸሎት ማከናወን ይጠበቃል፡፡ ሕግን በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ስም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ሲታሰብ አካሄዱ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ሕጋዊ አሠራርንና የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የተከተለ ሊሆን ይገባዋል።

በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ፣ ሕጋዊ ፈቃድና የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያለው ባለሙያ የሠራው የሕንፃ ዲዛይን፣ ሥርዓቱን ተከትሎ የወጣ የግንባታ ፈቃድ፣ ሕጋዊ ፈቃድ ያለውና ሙያው የተመሰከረለት የሕንፃ ተቋራጭ፣ በግልፅና ሕጋዊ መንገድ የሚገኝ ሕንፃ ማሠሪያ ገንዘብ፣ ግልፅና ኦዲት የሚደረግ የግዢና የፋይናንስ አሠራር እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በተጨማሪም የሚሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም መጠኑ፣ ቅርፁ፣ የበሮቹና የመስኮቶቹ አቀማመጥ፣ የጉላቶቹ መስቀል መሆን፣ የስዕላቱ አሳሳልና አቀማመጥ፣ የውጭና የውስጥ ቀለሙ ወዘተ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለና ለሁሉም አስተማሪ ሊሆን ይገባዋል። በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው የክርስቶስ መስቀል ከሁሉም በላይ ቀድሞ ሊታይ የሚገባ የቤተ ክርስቲያን መለያ ምልክት ስለሆነ በበሮችዋ፣ በግድግዳዋና በጉላልትዋ ጎልቶ ሊሳል/ሊሠራ ይገባዋል።

በአጠቃላይ የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት፣ ስሙ የሚቀደስበትና ምዕመናን ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመውን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት በጠበቀና የሚሠራበትን ሀገር ሕግ ባከበረ መልኩ ሊታነጽ ይገባል። የሕዝበ ክርስቲያኑም ትኩረት ከሚታየው የሕንፃ ውበት ይልቅ በውስጡ የሚገኘው ሕይወት ላይ፣ ከአካላዊ ግዝፈቱ ይልቅ በውስጡ የሚከናወነው ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ሊሆን ይገባል። ዋናው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ግን ሕንፃ ሥላሴ የተባሉ የምዕመናንን ሕይወት ማነጽ፣ የክርስቲያኖች ኅብረት/ጉባኤ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ማስፋትና ማጽናት ናቸው። እነዚህን የሚሸረሽሩ ከሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራርም ይሁን አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ልማዶች ተለይተው ሊታረሙ ይገባል እንላለን።

ምክሐ ዘመድነ: በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ!

117114150_10217970288956643_3853398957298516931_o

ቅዱሳን ሊቃውንት በድርሰቶቻቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተለያዩ አገላለፆች ጠርተዋታል። እነዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው ዓለምን የማዳን ጉዞ ውስጥ እመቤታችን ያላትን ድርሻ፣ እንዲሁም በቃል ኪዳኗ፣ በአማላጅነቷ ለሚታመኑ የክርስቶስ ወገኖች የነፍስና የሥጋ መጠጊያ (ጸወነ ሥጋ ወነፍስ) መሆኗን የሚያመለክቱ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ) የሚለው አንዱ ነው። በዚህች አጭር ጦማር ቅዱሳን አበው እመቤታችንን ለምን “ምክሐ  ዘመድነ – የባሕርያችን መመኪያ” ብለው እንደ ሰየሟት እንመለከታለን፡፡

“የባሕርያችን መመኪያ” ብለው ያመሰገኗት ቅዱሳን

እመቤታችንን በልዩ ልዩ አገላለፅ “ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ)” ብለው ያመሰገኗት ቅዱሳን ሊቃውንት ብዙ ናቸው። በዚህች ጦማር ለአቀራረብ ይመች ዘንድ እነዚህን ሊቃውንት በሁለት ወገን ከፍለን ከምስጋናቸው እንማራለን። በመጀመሪያ በቅዳሴና በጸሎት መጻሕፍት የተቀመጡትን የሊቃውንት ቃል እናስቀድማለን። ከእነዚህ  በመቀጠልም ሃይማኖተ አበው ተብሎ ከሚታወቀው የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ አቋም ከሚያስረዳ መጽሐፍ ለማሳያ እንጠቅሳለን።

ትምክሕተ ዘመድነ: ቃለ ሊቃውንት ቅዱሳን

በሊቃውንት ዘንድ ቃላት ተመጥነው፣ ተለክተው ይነገራሉ እንጂ ያለቦታቸው አይነገሩም። በተለይም በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የሚናገሩ ቅዱሳን ሊቃውንት ቃላቸው፣ አገላለፃቸው የሚያነበውን ሰው ልቡና ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ የማድረግ ኃይል አለው። እመቤታችንን “ትምክሕተ ዘመድነ/ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ)” ብለው ካመሰገኗት ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግን፣ የውዳሴ ማርያምን ደራሲ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን፣ እንዲሁም ከቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድን፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫንና አባ ጽጌ ድንግልን ለአብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡

ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ

የሥሩግ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ያዕቆብ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በደረሰው አኮቴተ ቁርባን (የቁርባን ምስጋና) ቅዳሴው የኃዳፌ ነፍስ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ በፊቱ ለፍርድ ስንቆም ይራራልን ዘንድ በተማጸነበት አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡ “አሜሃ ከመ ትምሐረነ ወትሣለነ… ተማኅፀነ በማርያም እምከ እንተ ይእቲ እግዝእትነ ወትምክህተ ዘመድነ/በዚያን ጊዜ ትምረን ይቅርም ትለን ዘንድ…በእናትህ በማርያም ተማጽነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት/” (የያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ)፡፡ ይህንን አብነት በማድረግ ዛሬም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው “የባሕርያችን መመኪያ” እያለች ታመሰግናለች።

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም በውዳሴ ማርያም የሰንበተ ክርስቲያን ጸሎቱ “አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ። ወሰአሊት ሕይወተ ለነፍሳቲነ /በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ። ለሰውነታችንም ሕይወትን የምትለምኝ ነሽ/” በማለት አመስግኗታል። በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ድርሰቱም “አክሊለ ምክሕነ፣ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ፣ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል እንተ ወለደት ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ ዘኮነ ሰብአ በእንተ መድኃኒትነ/የመመኪያችን ዘውድ፣ የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችንም መሠረት እኛን ለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን” በማለት እመቤታችን የሰው ባሕርይ የከበረባት የማየ ሕይወት ምንጭ መሆኗን ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ “ትምክህተ ኩልነ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ዘበእንቲአሃ ተስዕረ ዘቀዳሚ መርገም እንተ ኅደረት ዲበ ዘመድነ በዕልወት ዘገብረት ብዕሲት በልዐት እምዕፅ/ሔዋን እንጨት ብልህ ባደረገችው ዓመፅ በባሕርያችን ያደረ እርግማን በእርስዋ የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የሁላችን መመኪያ ናት/” በማለት መመኪያነቷን መስክሯል። በዓርብ ውዳሴ ማርያም ላይም “ቡርክት አንቲ ማርያም ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ። ኦ ድንግል ወላዲተ አምላክ ምክሖን ለደናግል/ የደናግል መመኪያቸው አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው።/” በማለትም አወድሷታል። እንዲሁም በቀዳሚት ሰንበት ውዳሴው “ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናንነትሽን እናመሰግናለን እናደንቃለን። እንደ መልአኩ ገብርኤልም ምስጋና እናቀርብልሻለን የባሕርያችን መዳን በማህጸንሽ ፍሬ ተገኝቷልና፡፡ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔርም አቀረበን፡፡” በማለት አመስግኗታል፡፡ እኛም አባታችን ቅዱስ ኤፍሬምን አብነት አድርገን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ‘የባሕርያችን መመኪያ’ እንላታለን።

ቅዱስ ያሬድ

በምስጋና ቅዱሳን መላእክትን የመሰለ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ እመቤታችንን ሲያመሰግን “አንቲ በአማን ዘኮንኪ ምክሐ ለዘመደ ክርስቲያን/ለክርስቲያን ወገኖች በእውነት መመኪያ የሆንሽ አንቺ ነሽ/” ብሏታል። በተጨማሪም “ማርያም ድንግል ምክሖን ለደናግል፣ ይእቲኬ ቤተ ምስአል፣ ለኩሉ ፍጥረት ትተነብል/ድንግል ማርያም የደናግል መመኪያ፣ የጸሎት ቤት ናት፣ ለፍጥረታት ሁሉ የምትለምን አማላጅ ናት/” በማለት አመስግኗታል፡፡ ይህም መመኪያነቷ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለሚያምኑ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ መሆኑን ያስረዳናል። ምክንያቱም የአምላክ ልጅ ከእርስዋ ሰው በመሆኑ በእርስዋ ከምድር ወደ አርያም የቀረብን ሆነናልና በእውነት መመኪያችን ናት። በጸሎቷ ለምናምን ሁሉ ምሕረትን የምታሰጥ ናትና ድንግል ማርያም ለክርስቲያን ወገኖች ሁሉ መመኪያችን ናት።

አባ ጽጌ ድንግል

የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል (ብርሃን) ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርያችን መመኪያ መሆኗን ሲናገር “እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ/ የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የባሕርያችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለቅድስት ማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግንሻለን” ብሏል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት አርጋኖን በተባለው መጽሐፉ በብዙ ስፍራ “የደናግል መመኪያ የቅዱሳንም የመመረጣቸው አክሊል፣ ያልበደሉት የድንግልናቸው መመኪያ፣ ያላደፉትም የንጽሕናቸው አክሊል፣ ሥጋ የለበሰ ሁሉ መመኪያ፣ ነፍስ የተዋሐዳቸው ፍጥረት ሁሉ አክሊል፣ የነዳያን ሀብት የንጹሐን መመኪያ፣ ለባሕርያችንም መመኪያ ሆንሽ፣ የዓለም ሁሉ መድኃኒት በአንቺ ተደረገ” እያለ አመስግኗታል፡፡

ምክሐ ዘመድነ: ሃይማኖተ አበው ቀደምት

እመቤታችን ድንግል ማርያምን ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ) ብሎ ማመስገን ቃለ ሊቃውንት ከመሆኑም በላይ የነገረ ድኅነትን ምስጢር የሚያስረዳ የቀደሙ አባቶቻችን ርትዕት ሃይማኖት መገለጫ መሆኑን በሃይማኖተ አበው ክታባቸው የተደጎሰላቸው ቅዱሳን አባቶች ትምህርት ያስረዳናል። ለማሳያ እንዲሆነን ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ

ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ያለ ደም ሰማዕት የሆነ) የአርማንያ ኤጲስ ቆጶሳት አለቃ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጌታ ከእመቤታችን በመወለዱ ሰዎች መለኮትን ለማየት መብቃታቸውን አንስቶ ባመሰገነበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል። “ኮነ በአርያም ሰብእ እስከ ኮኑ ሰብአ ድልዋነ ይርአይዎ ለመለኮት እስመ ሶበ ርኢነ ዘመደ ሥጋነ ንሴብሖ ለመለኮተ ወልድ በኂሩቱ ለአብ/ሰዎች መለኮትን ያዩት ዘንድ የበቁ እስኪሆኑ ድረስ በሰው ባሕርይ ተገለጠ፣ በሥጋ ዘመዳችን ሆኖ ባየነው ጊዜ በአብ ቸርነት የወልድን ጌትነት እናመሰግነዋለንና።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ 15:11)

ቅዱስ አትናቴዎስ

ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ሥጋን ነፍስን ነስቶ መወለዱን ክደው “ቃል ሥጋ ለመሆን ተለወጠ” በሚል ክህደት የጠፉ መናፍቃንን በገሰጸበት ድርሳኑ ጌታ ከእመቤታችን የእኛን ባሕርይ መንሳቱ የድኅነታችን መሠረት መሆኑን ገልፆ አስተምሯቸዋል። ጌታ በተዋሕዶ ባሕርያችንን ባሕርይው ከማድረጉ በላይ ለሰው ልጅ የተሰጠ ክብርና መመኪያ የለምና። “ለብው ኦ አብዳን ሰሚዐክሙ ቃለ መጻሕፍት ወእመኑ እስመ ሥጋሁ ለእግዚእነ እማርያም እምቅድስት ድንግል ውእቱ ወአኮ እም ካልእ/እናንት አላዋቆች የመጻሕፍትን ቃል ሰምታችሁ ዕወቁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነ ከሌላ እንዳይደለ እመኑ።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 30:9)። “ደካማ ባሕርያችንን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ስለመጣ” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ባስልዮስ 33:35) ከባሕርያችን መመኪያ ከእመቤታችን ሥጋን ነፍስን ነስቶ ተገለጠ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ፍጡር ለሆነ ለሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር መዛመድን (በተዋሕዶ መክበርን) የመሰለ ምን ሞገስ አለ? ይህን ክብር ያገኘነው ተስፋ ቅዱሳን አበው በተፈፀመባት በባሕርያችን መመኪያ በድንግል ማርያም ነው። የተወደደ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለ: “ለቡ ዘተብህለ ወኢተኀሊ ከመ ንስቲት ክብር ይእቲ ዘነሥአ እግዚአብሔር እምኔነ እስመ ኢወሀበ ዘንተ ለመላእክት ወኢህላዌ መላእክት እንተ ተወክፈቶ አላ ህላዌ ዚአነ። …ለዝንቱ ሶበ እዜከሮ ብዙኃ ጊዜያተ አነክር እምኔሁ ወእዴመም ወእኔጽር ብዙኃ ክብራተ ዘአልቦቱ ወሰን ዘረክበ እጓለ እመሕያው ወፍቅረ ዐቢየ ዘኢይትነገር ዘረከበ ህላዌነ ዘእምእግዚአብሔር/ የተነገረውን አስተውል እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና፣ የመላእክት ባሕርይም አልተዋሐደችውምና፣ የተዋሐደችው የኛ ባሕርይ ናት እንጂ።…ይህን መላልሼ ባሰብኩት ጊዜ  ሰው ያገኘውን ልክ መጠን የሌለውን ፍጹም ክብር ከእግዚአብሔር የተደረገውን ባሕርያችን ያገኘውን ታላቅ ፍቅር አይቼ ከዚህ የተነሣ አደንቃለሁ።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62:4-7)

እስራኤል ዘሥጋ ሙሴ ስለ እነርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ደጋግሞ በመነጋገሩ የሚመኩበት ከሆነ እኛማ በዘመነ ሐዲስ የምንገኝ፣ በሐዲስ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጆች የመባልን ጸጋ ያስገኘችልንን የባሕርያችን መመኪያ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የቱን ያህል ማክበር ይገባን ይሆን?! የዘመነ ብሉይ ቅዱሳት አንስት (ሴቶች) እንደ ሐና እመ ሳሙኤል ምድራውያን ካህናትን ስለወለዱ እስራኤል ያከበሯቸው ከሆነ እኛማ መፈታትን ያገኘንበት ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ያዛመደችንን ድንግል ማርያምን ምን ብለን ብናመሰግናት ይበቃን ይሆን?! በሥጋ ማርያም በመገለጡ፣ ፍጹም እግዚአብሔር፣ ፍጹም ሰው (አብሲዳማኮስ፣ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ) በመሆኑ ማለፍ መለወጥ የሌለበት የዘለዓለም ሊቀ ካህናት ሆኗልና።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ አለ: “ወአኮ ይኩነነ እኅወ ባሕቲቶ አላ ተሣሃለነ ፈድፋደ ወፈቀደ ዓዲ ይኩነነ ሊቀ ካህናት ለኀበ አብ ከመ ይስረይ ኃጢአተነ፣ ወበእንተ ዝንቱ ወሰከ በዲበ ነገሩ ወይቤ ከመ ይኩኖሙ መሐሬ በኵሉ ምእመን ሊቀ ካህናት ለመንገለ እግዚአብሔር ከመ ይስረይ ኃጢአተ ሕዝብ።/ሰው የሆነም ዘመድ ሊሆነን ብቻ አይደለም፣ ፈጽሞ ይቅር አለን። ኃጢአታችንን ለማስተስረይ ከአብ ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናትም ይሆነን ዘንድ ወደደ እንጂ። ስለዚህም ሰዎችን ሊመስላቸው ይገባል ባለው ነገሩ ላይ ጨምሮ በሁሉ አዛኝ የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ አስታራቂ ይሆናቸው ዘንድ ነው።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62:13)

ቅዱስ ኤራቅሊስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከባሕርያችን መመኪያ ከድንግል ማርያም ሥጋና ነፍስን ስለነሳ አማኑኤል (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ተባለ። ፍጹም ሰው በመሆኑም የወደቀ ባሕርያችንን ወደቀደመ ክብሩ መለሰልን። ይህን አምላካዊ ምስጢር ለማድነቅ ቃላት ያጠረው ቅዱስ ኤራቅሊስ እንዲህ አለ: “ኦ ከርሥ ዘተጽሕፈ በውስቴታ መጽሐፈ ግዕዛን እምግብርናት ለኩሉ ሰብእ!?…ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ/ ለሰው ሁሉ ከመገዛት የነፃነት መጽሐፍ የተጻፈባት ማኅፀን ወዮ እንደምን ያለች ናት!?…እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48:15-17) ስለሆነም ዕለት ዕለት በጸሎተ ቅዳሴ በካህኑ መሪነት “የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ” እያልን እናመሰግናታለን።

የባሕርያችን መመኪያ ሲባል ምን ማለት ነው?

ባሕርይ የምንነት መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ከአራት ባሕርያተ ሥጋና ከሦስት ባሕርያተ ነፍስ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” እንዲል፡፡ (ዘፍ. 1፡26) ሰው በሥጋ ባሕርይ ውኀነትን፣ እሳትነትን፣ ነፋስነትንና መሬትነትን ሲይዝ በነፍስ ባሕርይ ደግሞ ልባዊነትን (ማስተዋልን)፣ ነባቢነትንና (መናገርን) ሕያውነትን (ለዘላለም መኖርን) ይዟል፡፡ የእነዚህ ባሕርያት ፍጹም ተዋሕዶ ሰብአዊ ባሕርይ ይባላል፡፡ ይህ የሰውነት ባሕርይ በውጫዊ ነገር መለዋወጥ በኑሮ ጉስቁልና ወይም ምቾት አይቀየርም።

ሰው በባሕርይው ባለ ነፃ ፈቃድ ተመሥርቶ ጽድቅንም ኃጢአትንም ማድረግ ይችላል። በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን ምክንያት የመጣው ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፍም ይህን እውነታ በግልጥ ያስረዳናል። አዳምና ሔዋንም በነፃ ፈቃዳቸው ተመርተው በፈጸሙት መተላለፍ የሰው ባሕርይ (ሰውነት) ከነበረበት የቅድስናና የንጽሕና አኗኗር ተለይቶ ነበር፡፡ ባሕርይው ጎስቁሎ፣ ልጅነቱን አጥቶ ነፃነቱንና ሕያውነቱን አጥቶ በሞት መዳፍ ተይዞ ነበር። ይህ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ኀጢአትና ውጤቱ ከእነርሱ በባሕርይ ለሚወለድ ሁሉ ተላለፈ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “…ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ…ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና” እንዳለ፡፡ ሮሜ. 5፡ 12-14። ይህ የአዳምና የሔዋን በደልም ጥነተ አብሶ ይባላል። ከእነርሱ የሚወለዱ ሁሉ በጥንተ አብሶ የሚያዙ ሆኑ።

እግዚአብሔር ከዚህ ያድናቸው ዘንድ አዳምና ልጆቹ በዘመናት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ ኖሩ። እግዚአብሔርም ቃል ገባላቸው። ቃል ኪዳኑ እስኪፈፀም ድረስም ላደፈው ባሕርይና ለጎሰቆለው ሕይወት መታደስ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛቸውን ድልድይ ሲጠባበቁ ኖሩ። ይህች ድልድይ ወይም መሰላል የኾነችም እመቤታችን ድንግል ማርያም ነች፡፡ ለዚያም ነው ‘የባሕርያችን መመኪያ’ የምንላት። እርስዋ በቅድስና ተጠብቃ በውስጥ በአፍኣ በነፍስ በሥጋ በንጽሕና ተሸልማ የሰውን ባሕርይ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከባሕርያችን የተገኘች ምክንያተ ድኅነት ናትና፡፡

ይህ የእመቤታችን ድልድይነት ከዘመነ ብሉይ እስከ ዘመነ ሐዲስ በብዙ ሕብረ አምሳል የተገለጠ፣ ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቆጠረለት ነው፡፡ አባታችን ያዕቆብ ሰው ከእግዚአብሔር በተለየበት፣ እግዚአብሔርም ከሰው በረድኤት በራቀበት ዘመን መጭውን የድኅነት ብሥራት በሕልም አየ። በሕልሙ የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ እግዚአብሔር በላዩ ቆሞበት መላእክት በመሰላሉ ሲውጡ ሲወርዱ አየ። “ሕልምንም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፣ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፣ እነሆም የእግዚአብሔር መላዕክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር” እንዲል (ዘፍ. 28፡12-13)፡፡ ይህች አባታችን ያዕቆብ በሕልሙ ያያት መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ነበረች፡፡ ይህም ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በማኅፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሮ ከእመቤታችን በቤተልሔም በተወለደ ዕለት መላዕክት ከእረኞች ጋር በአንድነት ባመሰገኑበት ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ (ሉቃስ 2፡ 8-14)።

የብህንሳው ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ወዮ ይህ ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው የቀደሙ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ፣ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል ሆይ፣ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ፡፡ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት አመስግኗታል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 30)። ስለዚህም እመቤታችንን የባሕርያችን መመኪያ እንላታለን፡፡

እመቤታችንን የባሕርያችን መመኪያ ያስባሏት ዋና ዋና ነጥቦች

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ስለሆነ ሙሉ ምስጋናዋን አንሥተን መፈጸም አይቻለንም፡፡ ነገር ግን የባሕርያችን መመኪያ ከሚያስብሏት መጽሐፋዊ ምክንያቶች የተወሰኑትን እናያለን፡፡

አምላክ የሰውን ባሕርይ በእርሷ ስለተዋሐደ

እግዚአብሔር የወሰነው ዘመን ደርሶ የገባውን የምሕረት ቃል ኪዳን ሊፈጽም በወደደበት ወቅት ማደርያው ትሆነው ዘንድ የመረጣት ድንግል ማርያም ነች፡፡ እርሷም ዓለም ሳይፈጠር ለዓለም ድኅነት ምክንያት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር የቀደሳት በውስጥ በአፍኣ፣ በነፍስ በሥጋ ፍጽምት ቅድስት ሆና የተገኘች ናት። ይህችውም ከአዳም ዘር የተወለደች እግዚአብሔር ለድኅነተ ዓለም ያዘጋጃት ሰዋሰወ ብርሃን (የብርሃን መሠላል) ናት። እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን የሰውን ባሕርይ እንጅ የመላእክትን ባሕርይ አልፈለገምና፡፡ ለዚያም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመዳናችን ራስና ፈጻሚ ስለሆነው ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረበት አንቀጽ “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጅ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ያለው፡፡ (ዕብራ. 2፡16)

ስለዚህ የባሕርይ አምላክ የሰውን ባሕርይ ተዋሕዶ ከነፍስዋ ነፍስ፣ ከሥጋዋም ሥጋ ነስቶ ተወለደ። በተዋሐደው የሰው ባሕርይም እንደ ሕፃን አደገ። ወደ ግብፅ ተሰደደ። በዮርዳኖስ ተጠመቀ። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በምድር ላይ ተመላልሶ ወንጌልን አስተማረ። በተዋሐደው ሥጋ መከራን ተቀበለ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ። በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ። በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ከእንዲህ እናስተውል በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ወልድ ዋሕድ እየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው በተዋሕዶ የከበረው ከእርሷ ተወልዶ ነው። በእትሷ የተፈፀመው የተዋሕዶ ምሥጢር ሰው (የሰው ባሕርይ) አምላክ አምላክም (መለኮት) በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ነውና በእውነት የባሕርያችን መመኪያ ናት።

በባሕርያችን ያደረ እርግማን በእርሷ ስለራቀልን

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” (የሐሙስ ውዳሴ ማርያም) በማለት የእመቤታችንን ምክንያተ ድኅነትነት አስረድቷል፡፡ የውዳሴ ማርያም መተርጉማንም ሲያስተምሩ እናታችን ሔዋን የሞት ምክንያት ስለ ተባለች ወቀሳ፣ ከሰሳ ይበዛባት ነበር፡፡ በሔዋን አንፃርም ሴቶች ሁሉ የስሕተት ምክንያት እንደ ሆኑ አድርገው የሚያስቡ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ወንዶችም ይህን እየጠቀሱ በሴቶች ላይ ይመኩባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ድኅነት በእመቤታችን በኩል ሆኗልና የወንዶች ትምክህት ቀርቷል፡፡ እመቤታችንም ቅዱስ ገብርኤል የድኅነት ምክንያት መሆኗን ባበሰራት ሰዓት የሔዋንን ጸሎትና ልመና በማስታወስ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች….የባርያይቱን መዋረድ ተመልክቷልና” (ሉቃ. 1፡47-48) በማለት የሔዋን ምክንያተ ሞት መሆን በእርሷ ምክንያተ ድኂን መሆን መታደሱን ተናግራለች፡፡

በንጽሐ ባሕርይዋ የሰውን ንጽሐ ባሕርይ ስለምታሳይ

የሰው ልጅ ሕግን ተላልፎ በመበደሉ (ጥንተ አብሶ) እግዚአብሔር ተለየው፣ ከእግዚአብሔርም ተለየ፡፡ በራሱ ትሩፋትም ወደ እግዚአብሔር መመለስና መዳን አልተቻለውም። ስለዚህ ድካሙን ያግዝለትና ድኅነቱን ይፈጽምለት ዘንድ ጌታ ለአዳም ቃል ኪዳን ገባለት። ቃል ኪዳኑም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ ሞቼ አድንሃለሁ የሚል ነበር። ለዚህ ቃል ኪዳን ፍጻሜም ምክንያት ትሆን ዘንድ እመቤታችንን በንጽሕና ፈጥሮ፣ ከጥንተ አብሶ ጠበቃት። በዘመነ ብሉይ የነበሩ ሁሉ በዚህ በደል የተያዙ ነበሩና (ሮሜ. 5፡12-14)። ሁሉም ከኃጢአት በታች እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፣ ጽድቃችንም እንደ መርገም ጨርቅ ነው” ብሏል፡፡ (ኢሳ. 64፡ 6)

ነቢዩ ኢሳይያስ ከላይ የተጠቀሰውን የተናገረው ከሕግ በታች ይኖርበት ከነበረው ዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ ለመሸጋገር የጌታን መወለድ (አስተርዕዮ) በተማጸነበት የትንቢቱ ክፍል ነው፡፡ ምዕራፉን ሲጀምርም “ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ!” (ኢሳ. 64፡1) ብሏል፡፡ ይህን የተናገረ ኢሳይያስ በዘመነ ብሉይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ለይቶ እመቤታችን ድንግል ማርያም በጥበበ እግዚአብሔር ከመጀመሪያው በደል (ጥንተ አብሶ) ተጠብቃ መቀመጧን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ ነበር፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር” (ኢሳ. 1፡9) ብሏል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በመዝሙሩ “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም” (መኃልይ. 4፡7) በማለት በምሳሌ የእመቤታችንን ፍጹም ንጽሕና ተናግሯል፡፡ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች ጠፍተን፣ በኃጢአት ተይዘን እንዳንኖር የድኅነት ምክንያት የሆነች፣ ንጹሕ ዘር የተባለች፣ የባሕርያችን መመኪያ የሆነች እመቤታችንን ከአዳም ጀምሮ እስከ ኢያቄም አብራክ ያስቀረልን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ይህን የእመቤታችንን ፍጹም ንጽሕና ባሰብን ጊዜ እርሷ እንደ እኛ ከሰው ባሕርይ ተፈጥራ ንጽሐ ሥጋና ንጽሐ ልቦናን አስተባብራ የያዘች በመሆኗ ከአዳም ልጆች ከአንስተ ዓለም እርሷን መርጦ የሰጠንን አምላክ እናመሰግናለን። እርሷንም በቅድስናዋ መዓዛ ከርኵሰታችን ሽታ ታነጻን ዘንድ እንለምናታለን። እርሷን ምሳሌ አድርገን ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ቅዱስ ማደርያው ይኾን ዘንድ በንጽሕና እንጠብቀዋለን። እርስዋ የንጽሕናና የቅድስና አብነት ሆናልናለችና፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም በቀዳሚት ሰንበት ምስጋናው “ከዳዊት ዘር የተገኘሽ ባሕርይ /ዘር/ አንቺ ነሽ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና” በማለት ያወደሳት፡፡

በትንሣኤዋ ለሰው ልጆች የክብር ትንሣኤ ማሳያ ስለሆነች

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ባስረዳበት መልእክቱ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1ኛ ቆሮ. 15፡20) ብሏል፡፡ የጌታ ትንሣኤ ሞት የተሸነፈበት ትንሣኤ ስለሆነ የሰው ልጆች በሙሉ በዳግም ምጽአት እርሱን አብነት አድርገን የማይፈርስ የማይበሰብስ አካል ይዘን እንነሣለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን የትንሣኤያችን በኩር የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ሲነገራቸው “እርሱ በገዛ ሥልጣኑ ስለ ተነሣ እኛ ግን እንዴት እንነሣለን?” በማለት ታላቁ የእምነታችን መሠረት የሆነውን ትንሣኤ ሙታንን የሚጠራጠሩ በየዘመናቱ አሉ። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ለእነዚህ ወገኖች በእውነት ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አንድ ማሳያ ነው።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው፣ ሁሉም ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት እንደሚስማሙበት፣ በሊቃውንት አበው እንደተጻፈው እመቤታችን ድንግል ማርያም በሥጋ ባረፈች ጊዜ ጌታ ሥጋዋን ለመፍረስ ለመበስበስ አልተወውም፡፡ ይልቁንም የከበረ ሥጋዋን ለማቃጠል ከተሰበሰቡ ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድ በጥበብ አስጥሎ ቅዱሳን ሐዋርያት ከቀበሯት በኋላ ጌታ የከበረ ሥጋዋን በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው እንጅ፡፡ የእውነተኛው ዕፀ ሕይወት (የሕይወት ፍሬ) መገኛ የሆነች የባሕርያችን መመኪያ የድንግል ማርያም የከበረ ሥጋ በሕይወት ዛፍ ስር ተቀመጠ፡፡ ትንሣኤና ዕርገቷንም በሱባኤ ይማጸኑ ለነበሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት በልዩ ልዩ ተአምራት ገለጠላቸው፡፡ ድንግል ማርያም በተፈጥሮ እንደ እኛው ምድራዊት ስትሆን በልጅዋ ሥልጣን ሞትን ድል አድርጋ በመነሣት ወደ ሰማይ ዐረገች። ስለሆነም ትንሣኤዋ ለምድራውያን ሰዎች የማይቀር ትንሣኤ ማሳያ ሆነልን፡፡

የሰው ባሕርይ በሔዋን የሞት ምክንያትነት ሞት፣ ጉስቁልና እና መፍረስ መበስበስ አግኝቶት ነበር። አማኑኤል የተባለ የተወደደ ልጇን በወለደችልን በድንግል ማርያም የሕይወት ምክንያትነት ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ። ሔዋን ለሞት፣ ድንግል ማርያም መፍረስ መበስበስ ለሌለበት ሕይወት ከሰው ልጆች ሁሉ የመጀመሪያ ሆኑ። ሔዋን በበደሏ፣ በትዕቢት ባለመታዘዟ ለሰይጣን መገዛትን ወደ ሰው ባሕርይ ለማምጣት የመጀመሪያዋ እንደነበረች ንጽሕት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ባስደሰተ ቅድስናዋ፣ በፍጹም ትህትና በመታዘዟ በልጇ ሥልጣን ሞትን፣ መፍረስ መበስበስን አሸንፈው ለዘለዓለም በሕይወት ሊኖሩ የክብር ትንሣኤን ከሚነሱ ሁሉ ቀድማ በመነሣቷ የባሕርያችን መመኪያ መሆኗ ታወቀ።

የባሕርያችን መመኪያ ስለሆነች በጸሎታችን እንማጸንባታለን

እስራኤል ዘሥጋ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ሲፈልጉ የሚመኩባቸውን ቅዱሳን አበው የአብርሃምን፣ የይስሐቅን፣ እስራኤል የተባለ የያዕቆብን ስም ይጠሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይራራላቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አግዚአብሔር በእስራኤላውያን ተቆጥቶ ሊያጠፋቸው ባለ ጊዜ ለሕዝበ እስራኤል ምሕረትን የለመነው የእነዚህን ቅዱሳን አበው ስም በአማላጅነት ጠርቶ ነበር፡፡ “ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አለም፡፡…ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፣ ይኽችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፣ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባርያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ”። ዘጸ. 32፡11-13።

የዘመነ ብሉይ ምዕመናን በታላላቅ አርዕስተ አበው ቅዱሳን በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ ቃል ኪዳን ተመክተው እግዚአብሔርን ይለምኑት እንደነበር እኛም የባሕርያችን መመኪያ በሆነች በድንግል ማርያም ጸሎትና ቃል ኪዳን እንታመናለን። በምርኮ የነበሩ አይሁድ በምድራዊ ንጉሥ ቤተ መንግስት ባለሟልነት ባላት በወገናቸው በደካማዋ በአስቴር ተመክተው ከሞት ፍርድ ካመለጡ (መጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 4-ምዕራፍ 8) እኛማ አምላክን በወለደች፣ በንጽሕና በቅድስና ባጌጠች፣ የሰማያዊ ንጉሥ የክርስቶስ ምድራዊት ቤተ መቅደስ በሆነች በባሕርያችን መመኪያ በእመቤታችን ድንግል ማርያም የመመካታችን ዋጋ ምን ይሆን!? ስለሆነም እስራኤል ዘነፍስ የምንባል የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ከቅዱሳን ሁሉ በምትበልጥ፣ የባሕርያችን መመኪያ በሆነች በድንግል ማርያም ስም ልጇ ወዳጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እንማጸነዋለን፡፡ ዘወትርም በቅዳሴና በጸሎት “በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ/ ክርስቶስ ሆይ ስለ እናትህ ስለ ማርያም ብለህ ይቅር በለን” እያልን እንለምነዋለን፡፡ እርሱም ይታረቀናል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትን ባለማወቅ ትስታላችሁ!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥራዝ ነጠቅ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ተነሥተው ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያንን ሲገስፅ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቅ ትስታላችሁ” (ማቴ 22:29) ብሏቸው ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍትና ቅዱሳን ሊቃውንት በአንድነት ተስማምተው ድንግል ማርያምን “ወላዲተ አምላክ ማእምንት/የታመነች አምላክን የወለደች”፣ “ምክሐ ዘመድነ/የባሕርያችን መመኪያ” በማለት ያመሰግኗታል። የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ለሚረዳ ሰው እነዚህ ምስጋናዎች ጌታ እኛን ያዳነበትን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዱ መሆናቸውን ይገነዘባል።

ስለ ድንግል ማርያም ክብር፣ አማላጅነት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ንጹሕ ሐዋርያዊ ወንጌልም ከውድቀት የተነሣ የሰው ባሕርይን የሚመለከት፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ለሰው ልጅ የሰጠው መጠንና መመርመር የማይቻል ጸጋ ማሳያ መሆኑን ይረዳል። ይሁንና የነገረ ድኅነትን ትምህርት ባለማወቅ የሚቆነጻጽሉ፣ የድንግል ማርያምን ክብር የማይረዱ ሰዎች ምክንያተ ድኂን (የድኅነት ምክንያት) መሆኗን መረዳት ሲከብዳቸው እናስተውላለን። ባለማወቅና በድፍረት ተሞልተውም የባሕርያችን መመኪያ የእመቤታችንን የድኅነት ምክንያትነት ያቃልላሉ። በአንፃሩ ደግሞ የሔዋንን የሞት ምክንያትነት ግን መረዳት አይከብዳቸውም። ቅዱሳት መጻሕፍትን ባለማወቅ ስተዋል፣ ይስታሉ።

ከቅዱሳን ሐዋርያት ርትዕት ሃይማኖትን የተቀበለች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ግን የእመቤታችንን የድኅነት ምክንያት መሆን ዘወትር ታስባለች፣ በጸሎቷም ታሳስባለች። በሔዋን አለመታዘዝ፣ ሕግን መተላለፍ ሞት ወደ ዓለም እንደመጣ በእመቤታችን መታዘዝ፣ ሕግን መፈጸም ሕይወት ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቷልና እመቤታችንን “የባሕርያችን መመኪያ” ብለን እናመሰግናታለን።

ከጥሩ ምንጭ ቀድቶ ቃለ እግዚአብሔርን መረዳት የከበዳቸው ወገኖቻችን “የባሕርያችን መመኪያ” የሚለውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትኩረት (theme) መረዳት ቢችሉ ወደ ርትዕት ሃይማኖት በተመለሱ ነበር። ይሁንና አንዳንዶቹ ባለማወቅና በትዕቢት በማያውቁት ጉዳይ ራሳቸውን “መምህራን” እያሉ ጠማማ ትምህርትን ያስተምራሉ። ይህን የሚያደርጉት ጥሩ ምንጭ በሌለበት የሚኖሩት ብቻ አይደሉም። የሕይወት ውኃ ምንጭ በሚፈልቅባቸው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች ራሳቸውን ሾመው፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት በሚያናንቅ፣ የምዕራባውያንና ሌሎች ምስራቃውያን ሴሚናሪዎችን ልማድ በመከተል ጌታ በወንጌል (ማቴ 23) የገሰፃቸውን ፈሪሳውያንን በሚያስንቅ ግብዝነት፣ በተገዛ ቀሚስና ሀብል፣ ማዕረግ አልባ በሆኑ በሐሰትና በማጭበርበር በተሰበሰቡ የማዕረግ ስሞች ተከልለው ኦርቶዶክሳዊውን ዐውደ ምሕረት ከአባቶቻችን ከተረከብነው ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት፣ ትውፊትና ላህይ ለይተው ርካሽ የጭብጨባና የእንቶ ፈንቶ ዐውድ የሚያደርጉትንም ይመለከታል።

እነዚህ ከምንጩ የተለዩ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ምልክት ተደርገው “ዕንቁ፣ ብርቅዬ” መባላቸው በእውነተኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ በአላዋቂ ልብስ ሰፊ እንደተደረተ መጋረጃ ይመስላሉ። ቤተ ክርስቲያን ልትመዘንበት በሚገባው በእውነተኛ አስተምህሮዋ ሳይሆን በምንፍቅና ወይም ለመወደድና ለንግድ ተብለው በሚቀርቡ ሰዎች የለብ ለብ (simplistic) አስተምህሮ እንድትታይ ያደርጋሉና። በዚህም ምክንያት ብዙዎች የቤተ ክርስቲያንን ዕንቍ ትምህርት ሳያገኙ ይቀራሉ። ስለሆነም ቀላል የማይባል ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን ጥልቅ አስተምህሮ ባለማወቅ እየተለየ፣ ልቡናውን ከፍ ከፍ አድርጎ ስለ “ባሕርያችን መመኪያ” ከማሰላሰል ይልቅ ዲያብሎስ ትንንሾችን ለመጣል ባጠመደው እንቅፋት እየተጠለፈ ስለ ምልጃ፣ ስለ ትንሣኤና ዕርገት “ሀ” ብሎ የሚነታረክ ሆኗል። ለዚህ መሰል ትውልድ የአባታችን ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ተግሳፅ የሚጠቅም ይመስለናል።

ተግሳፅ ዘአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሳይረዱ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ምንታዌ (ከተዋሕዶ በኋላ የሥጋና የመለኮት ባሕርይ ሳይነጣጠሉ፣ ሳይከፋፈሉ) ባሕርያችንን ባሕርይው ማደረጉን በመካዳቸው፣ እመቤታችን ድንግል ማርያምም የባሕርያችን መመኪያ መሆኗን በማቃላላቸው ንስጥሮሳውያንን በገሰፀበት የመጽሐፈ ምሥጢር ንባብ ያስተማረው ትምህርት በዘመናችን ላሉ የድንግል ማርያምን ክብር ባለማወቅ ለሚያሳንሱ ሰዎች የሚስማማ ነው።

አባ ጊዮርጊስ እንዲህ አለ: “በተከማቸ መጽሐፍ ውስጥ የተሸሸገ ዕንቍን ልቡ የታወረ አያየውም። በነቢያትና በሐዋርያት አፍ የመለኮት ድምፅ ይጮሀል ኅሊናው በደነቈረ ሰው ጆሮ ግን አይገባም። የብረት መዝጊያ ቢበረታም በብረት ሰሪው እጅ ይከፈታል፣ የናስም መቀርቀሪያዎች በማንጠሪያ እሳት ይቀልጣሉ፣ የዝንጉዎችን ልብ ግን በጥበብ ቃልም ቢሆን፣ በመጻሕፍትም ቃል ቢሆን ሊከፍተው የሚችል የለም። መጻሕፍትን ማንበብ በሰነፍ አፍ ውስጥ እንደ ነፋስ መንቀሳቀስ ነው፣ ስላነበባት ይመካል፣ በውስጧ ያለውን ግን አያውቅም። የተዘጋን የንጉሥ ቤት ሳጥኖችን የሚያድን ወደ ውስጧ ግን ያልገባን ሰው ይመስላል። ስለነገሥታት ገንዘብ ለሚጠይቀው ሰው ምን ይመልስለታል?።” (መጽሐፈ ምሥጢር የጌና ምንባብ ቁጥር 33)

እንግዲህ እኛስ ምን እንላለን? የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር መረዳት አቅቷቸው በስህተት ጎዳና በድፍረት የሚራመዱትን አላዋቂዎች ምን እንላቸዋለን? ተማሪዎች ነን ቢሉ የቅዱሳት መጻሕፍትን በር ከፍተው እንዲገቡ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እንዲመራቸው፣ ማስተዋልን እንዲያድላቸው እንለምንላቸዋለን። የሚያሳዝነው አላዋቂነታቸው በግልጽ እየታየ ራሳቸውን “መምህራን” የሚሉት ይበዛሉ። እነዚህን ለመገሰፅ አሁንም ከአባታችን ጊዮርጊስ ዘጋሰሥጫ ቃል ተውሰን እንወቅሳቸዋለን፣ እንዲመለሱ እናሳስባቸዋለን።

“መጻሕፍትን ከማወቅ የተራቆቱ ሲሆኑ መምህራን የሚባሉ በከበረ ደንጊያ ካጌጡ በወርቅም ቅጠል ከተለበጡ፣ ቀለም በተነከሩ ልብሶች ከተሸፈኑ፣ በሐር ምንጣፍም ላይ ከተቀመጡ ውስጣቸው ግን ከተቆረጡ እንጨቶች፣ ከረከሱም የእንስሳ አጥንቶች ከተሠሩ ዕጣንና ሽቱ ከሚያጥኑአቸው፣ ነገር ግን የዕጣኑ መዓዛ በአፍንጫቸው ከማይገባ፣ ከመሥዋዕታቸው ስብ ከማይበሉ፣ ከወይን ጭማቂአቸውም ከማይጠጡ፣ የሚያምንባቸውን ከማይረዱት፣ በሚገፉአቸውም ላይ ክፉ ከማያደርጉ፣ በከንቱም አማልክት ከሚባሉ የአሕዛብ ነገሥታት ጣዖታት ከአዛጦን ሰዎች ዳጎንና አጵሎን ያልተሻሉ ናቸው። እነርሱ የእግዚአብሔርን ቃል የተጠሙ ሲሆኑ በከንቱ መምህራን የሚባሉ እኒህም እንዲሁ ናቸው፣ ወደነርሱ የመጣውን እንግዲህ እንዴት ያረኩታል? ቢያጠጡትም የደፈረሰውን ውኃ ከነቢያትና ከሐዋርያትም ምንጭ ያልተቀዳውን የተበላሸ ውኃ ያጠጡታል።” (መጽሐፈ ምሥጢር የጌና ምንባብ ቁጥር 34-35)

እንግዲህ እኛም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንመርምር። ከእውነተኛ መምህራን ተምረን የባሕርያችንን መመኪያ እንወቅ እንጂ በሐሰተኛ መምህራን ማደናገሪያ ተታለን ከርትዕት ሃይማኖት የተለየን አንሁን። የንጽሕና አብነት የምትሆን፣ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች፣ የባሕርያችን መመኪያ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አብነት አድርገን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ለጽድቅ ሥራ የተጋን እንሁን፡፡

ኦ ማርያም አንቲ ውእቱ ወላዲተ አምላክ በአማን ወምክሐ ዘመድነ ለኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን፣ አዕርጊ ጸሎተነ ቅድመ ገጸ ፍቁር ወልድኪ፣ ለዓለመ ዓለም አሜን።

እመቤታችን ማርያም ሆይ አንቺ በእውነት የአምላክ እናት፣ የባሕርያችን መመኪያ ነሽና ጸሎታችንን በተወደደ ልጅሽ ፊት አሳርጊልን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር።

ፍልሰታ ለማርያም፡ ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት!

“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ(ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጿማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሲሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር በዮሴፍ ቤት፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ዐሥራ አራት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ እንደሌሎቻችን ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ነሐሴ ፲፮ በልጇ ስልጣን ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ነገረ ፍልሰቷን እንዳስሳለን፡፡

“እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” (አይሁድ)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድ “እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ከእነርሱም መካከል ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የአልጋውን አጎበር ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡

Filseta2

“ተንሥአት እሙታን፡ ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል/ እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሳች/” (ቅዱስ ኤፍሬም)

ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም በልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፣ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ሙስና መቃብርን (የመቃብርን ሥልጣን) አጥፍቶ ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ (ከመ ትንሳኤ ወልዳ ) በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡

“አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!” (ድንግል ማርያም)

ይህ ቃል እመቤታችን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተናገረችው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት “አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡

“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” (ቅዱስ ቶማስ)

ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ ሲሰማ ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታችን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ሰበንም ሊቁ በመልክዓ ማርያም ድርሰቱ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡” እንዳለው ቅዱሳን ሐዋርያት ሞገሳቸውን እመቤታችንን ለመቅበር የገነዙበት ነበር፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምርሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፤ቅዱሳን ሐዋርያት ለበረከት ተካፍለውታልና፡፡

“ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” (ቅዱሳን ሐዋርያት)

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችንን ዕርገት ባየ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ይሰጣቸው (ዕርገቷን ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል፡፡

ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይሁን፡፡ (ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)

የእመቤታችንን የትንሣኤና የዕርገት ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡ በእመቤታችን የትንሣኤ በዓል ላይ ተንሥአት እሙታን ማርያም ድንግል! ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል” ማለትም “ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ተነሣች! ይህውም ልዑል አምላክ ልጇ እንደተነሳው ትንሳኤ ነው!” የሚለውን የምስራች ቃል ምእመናን ይለዋወጣሉ። ይህ የደስታ መንፈስና ስርአት እንደልጇ ዘመነ ትንሳኤ እስከ ነሓሤ 21 ቀን ድረስ ይቀጥላል። የመልክአ ማርያም ደራሲም ‹‹ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ (እመቤቴ ማርያም ሆይ በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል)›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

በጾመ ፍልሰታ  የእመቤታችን ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ ይነበባል (ሰዓሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት)፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽህና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሰረት ነውና፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም ሱባዔ ይገባሉ፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቤተክርስቲያናችን በፆመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከታወቁ የሕግ ምንጮች ከቅዱሳን አባቶቻችን በተማረችው መሰረት “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡

እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ ተስፋ እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ ጽንዕት በድንግልና፣ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፣ አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ መልክአ ማርያም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ

 

 

መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ: ጸሎት በገንዘብ አይሸጥም!

ምክንያተ ጽሕፈት

በዕለተ ሰንበት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን አንድ ቅን ካህን ከቅዳሴና ትምህርት በኋላ መልእክት ለማስተላለፍ ተነሱ። ካህኑ በሚያገለግሉበት ደብር ያለውን የገንዘብ እጥረት በሚመለከት ከተናገሩ በኋላ ሰበካ ጉባኤውንና የደብሩን ካህናት ለማሳሰብ እንዲህ አሉ “ሁሉም ደብር ገቢውን የሚያሳድገው ምዕመናን በቅዳሴ ጊዜ ስማቸው እንዲጠራ የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ነው።” የእኒህ ካህን ንግግር በዘመናችን ጸሎትን እንደሸቀጥ የማየት አስተሳሰብና ተግባር የወለደው ነው። በተለይም ነውር በሚንቆለጳጰስባቸው፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ከምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ስም ለሚገነቧቸው ገቢ ማስገኛ ፎቆችም ሆነ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኖች በሚጨነቁባቸው ቦታዎች የተጀመረና በብዛት እየተዛመተ የመጣ ወፍ ዘራሽ ልማድ ነው።

ከዚህም ጋር በሚመሳሰል መልኩ  “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በማለት ከምዕመናን ገንዘብ ለመቀበል ጸሎትን መደለያ የሚያደርጉ አካላት ብዙዎች ናቸው። ይህ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምን ሲሞናዊ ልማድ በቅዱሳት መጻሕፍት የተወገዘ ነው። ይሁንና በጥቅም ሰንሰለት የተያዙ ወይም “ስንት ችግር እያለ ስለዚህ ለምን እንጨነቃለን?” በሚል ስንኩል አመክንዮ ይህን ክፉ ልማድ የሚያበረታቱ፣ በተዛባ አስተምህሮ የሚደግፉ፣ እንዲሁም በዝምታ የሚያልፉ ካህናትና መምህራን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በቅዳሴ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎችን “ስም ለማስጠራት” ስለሚከፈል ክፍያ፣ “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁንና መባችሁን ስጡን” ስለሚሉት ሰዎችና ከእነዚህ አዳዲስ ልማዶች የተነሳ ጸሎትን ለውዳሴ ከንቱ ማስገዛት የሚፈጥረውን የአስተምህሮ መፋለስና የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ድቀት እንዳስሳለን። ምዕመናንም እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ብቻ እንዲከተሉ ለማስገንዘብ እንሞክራለን።

ጸሎት የጽድቅ መሰላል ናት!

ጸሎት የእምነት መገለጫ፣ የልጅነት ማረጋገጫ፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝባትና ጸጋ እግዚአብሔር የሚገኝባት የጽድቅ መሰላል ናት። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ስለ ጸሎት ሲያስተምር “በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በአደባባይ ማዕዘን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና፣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ 6:5) በማለት የተናገረው ጸሎት ለታይታ መደረግ እንደሌለበት ያስረዳናል። ከቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጻሕፍት አንዱ ፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጸሎትን የሚጀምረው የጸሎትን መንፈሳዊ ትርጉም በግልፅ በማስቀመጥ ነው። “ጸሎትሰ ይእቲ ተናግሮተ ሰብእ ኀበ እግዚአብሔር ልዑል።/ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት።” (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14)

ጸሎት በግልም በማኅበርም (በኅብረትም) ሊፈጸም ይችላል። ከግል ጸሎት ይልቅ የማኅበር ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው። በኃጢአት የተመሰለ ቅጽረ ኢያሪኮን (የኢያሪኮን ግንብ) ያፈረሰው በእምነት የቀረበ የማኅበር ጸሎት ነው (መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 6)፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የከበረችበትን የበዓለ ጰራቅሊጦስ በረከት የተቀበሉት በኅብረት ጸሎታቸው ዝግጁ ሆነው በመጠበቃቸው ነበር።  (የሐዋርያት ሥራ 1:14 እና 2:1-4)። ከማኅበር ጸሎቶች ሁሉ የከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምዕመናን የሚታደልበት ጸሎተ ቅዳሴ መሆኑን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያስረዳናል። ጸሎተ ቅዳሴ ዋነኛ ዓላማው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በስሙ ላመኑ ካህናትና ምዕመናን ለማደል ነው። ጸሎተ ቅዳሴ የማይነካው  ጸሎት የለም ማለት ይቀላል። በጸሎተ ቅዳሴ ከሚጸለዩ ጸሎቶች አንዱ “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መብአ/ መባ ስለሚያስገቡ ሰዎች የሚጸለይ ጸሎት” ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ  “መባ” የሚለው ቃል በልዩ ልዩ መልክ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምዕመናን የሚሰጧቸውን ንዋየ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ቁሳቁሶች ያጠቃልላል።

ትክክለኛ የመባ ጸሎት

በጸሎተ ቅዳሴ ንፍቁ ዲያቆን “ጸልዩ በእንተ እለ ያበውኡ መባአ” (መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ) በማለት ካህናትና ምዕመናን በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ መባ ስለሚሰጡ ሰዎች እግዚአብሔር መባቸውን ይቀበል ዘንድ እንዲጸልዩ ያሳስባል። ካህናትና ምዕመናንም በአንድነት “ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ” (የወንድሞችን መባ ተቀበል፣ የእህቶቻችንንም መባ ተቀበል፣ የእኛንም መባችንንና ቁርባናችንን ተቀበል) ብለው በዜማ ይጸልያሉ። በዚህም ጊዜ መባ ስለሚያገቡ ሁሉ በኅብረት፣ በአንድነት ይጸለይላቸዋል። በየስማቸው ለይቶ የሚያውቃቸው እግዚአብሔርም የጸሎቱን ፍሬ ያደርግላቸዋል። ለማንም በስም ተለይቶ የሚጸለይ ጸሎት አይደለም።

እንደ ንፍቁ ዲያቆን፣ ንፍቁ ካህንም በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ጸሎተ ቡራኬን በሚጸልዩበት ጊዜ “አምላካችን ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ዋጋቸውን ይከፍላቸው ዘንድ እጣንና ቍርባን ወይንና ሜሮን ዘይትም መጋረጃም የንባብ መጻሕፍቶችን የቤተ መቅደስንም ንዋያት በመስጠት የሚያገለግሉትንም ባርክ።” ይላሉ። በተጨማሪም ካህናት በሐዋርያት የመባ ጸሎት “ሁሉን የሚይዝ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን። ከሁሉ በላይ በምትሆን በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን መባ ስለሚያገቡ፣ መስዋዕቱን፣ ቀዳምያቱን፣ ከአሥር አንዱን የመታሰቢያ ምስጋና ብዙውንና ጥቂቱን የተሰወረውንና የተገለጠውን ይሰጡ ዘንድ ሲወዱ የሚሰጡት ከሌላቸው ላይ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ መንግስተ ሰማያትን ይሰጥ ዘንድ ለሁሉ በረከትን የሚያድልበት ስልጣን ገንዘቡ የሚሆን አምላካችን እግዚአብሔር።” በማለት ይጸልያሉ። በተመሳሳይ መልኩ በቅዳሴ ባስልዮስ ካህኑ “አቤቱ ይህን ቍርባን (መባ) ያመጡልህን ስለነርሱ ያቀረቡላቸውንም አስብ…ከነርሱ ዘንድ ላቀረቡትም ሁሉ በሰማይ ያለ ዋጋቸውን ስጣቸው ያንድ ልጅህ ትእዛዝ ይህ ነውና፣ ከጥንት ጀምሮ ያገለገሉህ ቅዱሳንህን እናስብ ዘንድ።” (ቅዳሴ ባስልዮስ ቁጥር 68-70)

በእነዚህና በመሳሰሉት የጸሎተ ቅዳሴ ክፍሎች መባ ስለሚያገቡ ሁሉ ይጸለያል እንጅ በስም ተለይቶ እንዲጸለይ የሚያዝ ሥርዓት የለም።  ለቤተ ክርስቲያን መባ ማቅረብ ሁሉም ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመጣ ምዕመን የሚያደርገው (ሊያደርገው የሚገባ) ምግባር፣ ትሩፋት እንጂ “ስማቸው እንዲጠራ ለሚፈልጉ ሰዎች” ብቻ የሚተው አይደለም። መባ ማቅረብን “ስምን ለማስጠራት የሚከፈል ስጦታ” አስመስሎ የሚያቀርብ አሰራር ጌታችን በወንጌል “እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” (ማቴ 6:2) በማለት ያወገዘውን ግብር መድገም ይሆንብናል።

የማይገባ የመባ ጸሎት

የጸሎት ዓላማ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኘት እንጂ እወደድ ባይ “ስማቸው በሰዎች ፊት እንዲጠራላቸው” የሚፈልጉ ሰዎችን ፈቃድ መፈፀም አይደለም። “እንደ ግብዞች ለሰው ይታዩ ዘንድ” (ማቴ 6:5) የሚደረግ ጸሎትም ሆነ መባ የተወገዘ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸሎተ ቅዳሴና መሰል የማኅበር ጸሎቶች “ስማችሁ በጸሎት እንዲጠራ ይህንና ያንን ክፈሉ” የሚሉና ለዚያም ገንዘብ የሚተምኑ ካህናት እየታዩ ነው። ይህ ለጸሎት ገንዘብ የመተመን ክፉ ልማድ በሌሎች የእምነት ድርጅቶች የተለመደና ምንደኞች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እያስገቡት ያለ ዘመን አመጣሽ እንክርዳድ ነው።

ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይታ መታሰቢያ የምታደርግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩትን ነው። ንፍቁ ካህን በጸሎተ ቅዳሴ ጸሎተ ቡራኬን ሲጸልይ “አምላካችን ሆይ በቀናች ሃይማኖት ሆነው ያንቀላፉትንና ያረፉትን ያባቶቻችንንና የወንድሞቻችንን የእኅቶቻችንንም ነፍስ አሳርፍ።” ይላል። መጽሐፈ ቅዳሴም “እዚህ ላይ የሞቱትን ስም ያንሳ” ይላል። በሞተ ሥጋ የተለዩንን ወገኖቻችንን መታሰቢያ (ተዝካር) ስናደርግላቸው ካህኑ ስማቸውን ያነሳል። ስማቸው የሚነሳውም በሞተ ሥጋ ቢለዩም በክርስትና ኅብረት አንድ ላይ መሆናችንን ለማሳየት “መዋዕያነ ዓለም አንትሙ፣ ሰዓሉ ቅድመ ፈጣሪ/ዓለምን ያሸነፋችሁ (ከዚህ በኋላ ለዘለዓለም በሕይወት የምትኖሩ፣ ሞት የማያገኛችሁ) እናንተ ስለ እኛ ጸልዩ” እያልን በጸሎታቸው እንማጸናለን። በሕይወተ ሥጋ ላሉ ሰዎች ግን ስለ መባቸው በጸሎተ ቅዳሴ የኅብረት ጸሎት ይደረግላቸዋል እንጂ “ስማቸውን አንሱ” የሚል ሥርዓት የለንም።

መባ የሚያገቡትን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይቶ መጥራት በቆየው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያልነበረ የቅርብ ጊዜ ልማድ መሆኑን ከልምድም ከመጽሐፈ ቅዳሴ ንባብም መረዳት እንችላለን። ይህ ከሆነ ገንዘብ እየተመኑ “በጸሎት ስምን ማስጠራት” ምን አመክንዮአዊ መሰረት አለው? ይህን ልማድ የሚያስፋፉ ሰዎች ሊያነሷቸው ከሚችሉ መከራከሪያዎች አንዱ “መባ ስለሚያገቡ ሰዎች መጸለይ የሚገባ ከሆነ ስማቸው መጠራቱ ምን ችግር አለው?” የሚለው ነው። “የሚጠራውም ዓለማዊ ስማቸው ሳይሆን ስመ ክርስትናቸው ስለሆነ ለውዳሴ ከንቱ አያጋልጥም” ሊባል ይችላል። እውነትም ስመ ክርስትና ውዳሴ ከንቱን ይቀንሳል። ይሁንና በአንዳንድ ቦታዎች “እነ እገሌኮ ማሰቀደሻ እየከፈሉ ስማቸውን ያስጠራሉ” የሚል ሽንገላን የሚጠቀሙ አሉ። በግልፅም በስውርም መባ ስለሚያገቡት ሁሉ  በአንድነት የሚጸለየውን ጸሎት አቃለው በልዩ ክፍያ ስም ለመጥራትም ለማስጠራትም የሚባክኑ ሰዎች “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መባአ/መባ ስለሚያገቡ ሰዎች የሚጸለየውን ጸሎት” ባለማወቅ ያቃልሉታል። እምነት እንደሌለው ሰው ሆነው ለራሳቸው ማጽናኛ በመፈለግ ከምዕመናን አንድነት ሳይታወቃቸው ይለያሉ።

ቤተ ክርስቲያንን መነገጃ አድርገው የሚያስቡ፣ አገልግሎቷም ግንብ መገንባትና የምንደኛ ካህናትንና ምዕመናንን የማይጠግብ ኪስ መሙላት የሚመስላቸው ሰዎች ከገንዘብ ስብሰባ ጋር የተገናኘ ማምታቻቸውን የሚሞግት ማንኛውንም አስተያየት መስማት እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። ስለሆነም ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑበትን “ወፍ ዘራሽ ልማድ” ለመከላከል (ትክክል ለማስመሰል) የማይሄዱበት ርቀት የለም። ለዚያ ሲሉ ቅዱስ ወንጌልን ያጣምማሉ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በልካቸው ይሰፋሉ፣ ውዳሴ ከንቱን ለገቢ ማስገኛ በሚል ያስፋፋሉ። ለማሳመኛ የሚነሱት ነጥቦች ግን ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ጋር በግልፅ ይጋጫሉ፣ አመክንዮአዊ መሠረታቸውም በጣም የደከመ ነው። ከሚቀርቡት ማሳመኛዎች የሚበዙት በራሳቸው አዲሱን ክፉ ልማድ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ለማደናገር በማሰብ ከሌሎች የተለየ አፈፃፀም ካላቸው የመባም ሆነ በችግር ላይ ላሉ ምዕመናን ከሚደረግ ጸሎት ጋር ያምታቱታል። ለዚህም ማሳያ እንዲሆነን የሚከተሉትን የሚገቡ ጸሎቶች ከገንዘብ መሰብሰቢያው ጸሎትን ሸቀጥ የማድረግ ልማድ ለይተን ለማሳየት እንሞክራለን።

መባ ለሚያገቡ ሰዎች መባውን በሚቀበለው ካህን የሚደረግላቸው ጸሎት

ለቤተ ክርስቲያን መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። መባ በመስጠታችንም ውዳሴና ሙገሳ መጠበቅ የለብንም። ምዕመናን ለቤተ እግዚአብሔር የሚሆነውን ልዩ ልዩ መባ በስውርም በግልፅም መስጠታቸው የሚገባ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የቆየ ክርስቲያናዊ ትውፊት መባ የሚሰጥ ሰው ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ መባውን በሚቀበለው ካህን ፊት በትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ እግዚአብሔር መባውን እንዲቀበልለት ይጸለይለታል። ያለ ከንቱ ውዳሴ በቅንነት የሚቀርብ መባ ኃጢአትን የሚያስተሰርይ፣ ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ጸጋ ከምታቀርበው ሰማያዊ አምሃ ከቅዱስ ቁርባን ጋር ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ ስለሆነ መባውን የሚሰጠው ምዕመን በካህኑ ጸሎት ተማጽኖ “አቡነ ዘበሰማያት” ይቀበላል/ይጸልያል። ይህ ጸሎት ምንም ከንቱ ውዳሴ የለበትም። የሚጸለየውም በግል ካህኑና መባ አቅራቢው ባሉበት እንጂ በአዋጅ፣ በጭብጨባ አይደለም። ስለሆነም ገንዘብ ተምነው “ስም ለማስጠራት” ከሚያደርጉት ክፉ ልማድ ጋር መምታታት የለበትም።

በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክህነትና የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት ከድለላና ምዕመናንን በማጭበርበር ገንዘብ ከመሰብሰብ “ችሎታ” ጋር የተምታታባቸው ብዙዎች ናቸው። “ጨረታ እናጫርታለን፣ በማነቃቃት ምዕመናን ገንዘብ እንዲሰጡ እናደርጋለን፣ ምርቃት እንመርቃለን” እያሉ በየዐውደ ምሕረቱ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ለተለያዩ በጎም ሆነ በግልፅ የማይታወቁ ዓላማዎች ገንዘብ መሰብሰብ የተለመደ ነው። ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በልግስና ቢሰጡ መልካም ነው። ይህንንም የሚያስተባብሩ ግልፅ አሰራርና ተጠያቂነት ያላቸው ካህናትም ሆኑ ምዕመናን መኖራቸው መደበኛ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያን አካላት ማገዝ እንደሚችሉ ይታወቃል። ይሁንና ምዕመናን ልዩ ልዩ መባ የሚሰጡት አምነውበት፣ ለጽድቅ በሚበጅ ግልፅ አሰራር እንጂ ኮሚሽን በሚቆረጥለት፣ የግለሰቦች “ገንዘብ የመሰብሰብ ጸጋ” እየተባለ ደርዝ የሌለው ከንቱ ውዳሴ በሚዘንብበት፣ “ምርቃት” በገንዘብ የሚሸጥ በሚመስልበት የአጭበርባሪዎች መንገድ አይደለም። መባ ስለሚያገቡ ሰዎች በካህን የሚደረግ ጸሎት ኢያቄምና ሐና የተወደደች ልጃቸውን ድንግል ማርያምን እንደ ስዕለታቸው ለቤተ መቅደስ በሰጡበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ያደረገውን ዓይነት ከንቱ ውዳሴ የሌለበት ጸሎት እንጂ “ለማነቃቃትና” ለማጭበርበር የሚግተለተል የአስመሳዮች የሽንገላ ምርቃት መሆን የለበትም። ስለሆነም ምዕመናን መባቸውን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ለማግኘት በቅንነት ሊሰጡ ይገባል እንጂ “ታዋቂ፣ ብዙ ተከታይ ያላቸው” በሚባሉ የዐውደ ምሕረት ደላሎችን ፊት የሽንገላ ውዳሴና ምርቃትን ሊናፍቁ አይገባም።

በልዩ ልዩ ችግር ላሉ ምዕመናን የሚደረግ ጸሎት

ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን እናት ናት። እናት ለልጆችዋ እንደምትጨነቅ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ ላሉ ልጆቿ ትጸልያለች። እናት ልጆቿን በእናትነት በሰጠቻቸው በቁልምጫ ስማቸው እንደምትጠራቸው ቤተ ክርስቲያንም በጸሎት የምታስባቸውን ልጆቿን በስመ ጥምቀታቸው (በክርስትና ስማቸው) እየጠራች በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ትጸልይላቸዋለች። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ሃይማኖቱ በታሠረ ጊዜ እንደጸለየችለት (ሐዋ 12:5)፣ ጸሎቷም ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ የቅዱስ ጴጥሮስን የእሥር ሰንሰለት የሚፈታ መልአክ እንደተላከለት ዛሬም በቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል፣ የተቸገሩትን ይረዳል።  ነገር ግን የተቀደሰውን ጸሎት እንደ ሸቀጥ በገንዘብ መተመንና “በችግራችሁ ጊዜ ስማችሁን እየጠራን እንድንፀልይላችሁ ይህንና ያን ክፈሉ” እያሉ ማምታታት የቤተ ክርስቲያንን ቅን አገልግሎት ጥላሸት የሚቀባ ነውር እንጂ ሌላ ስም የለውም። ለተቸገረው ያለ ዋጋ የምትጸልይ እንጂ ጸሎትን መደራደሪያ የምታደርግ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን አልተቀበልንም።

በ2002 ዓ.ም. በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በወቅቱ አዲስ ከተቋቋመች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር ሲወያዩ የተናገሩት አባታዊ መልዕክት ከእውነተኛ አባቶቻችን የተቀበልናትን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የምታጸና ናት። ይቅርና በውጭ ሀገር በሀገር ቤትም ቢሆን አዲስ ደብር መትከል ከባድ የገንዘብ ወጭ እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ሰይጣንም በገንዘብ እጥረት እያሳበበ አብያተ ክርስቲያናትን ከሚያስተምሩት ወንጌል እንደሚለያቸው ከልምዳችን ተረድተናል። ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው አዲስ ደብር ለመትከል የሚፋጠኑ አገልጋዮችም ወደ አባታችን ቀርበው ለክርስትናና ለፍትሃት ምን ያክል ማስከፈል እንዳለባቸው ለማማከር ጠየቋቸው። አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሲመልሱ እንዲህ አሏቸው “አይ ልጆቼ! አሁን በዚህ ቦታ ክርስትና ከሚነሳና ፍትሃት ከሚያስደርስ ምዕመን ገንዘብን መሰብሰብ ትፈልጋላችሁ? ብንችልስ እኛ እየከፈልን የጠፋው ሁሉ እንዲመለስ፣ በሥጋ የተወለደው ሁሉ ድጋሚ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያለ ዋጋ እንዲወለድ፣ የሞቱት ምዕመናን ሁሉ በጸሎተ ፍትሃት እንዲታሰቡ ማድረግ አለብን።” አሏቸው። ይህም አባታዊ ትዕዛዝ ብዙዎችን አሳምኖ አቡነ ጴጥሮስ ይህን ትምህርት ባስተማሩበት ቦታ ገንዘብ ተምኖ “ይህን ካልከፈላችሁ ክርስትና ማስነሳት፣ ፍትሃት ማስፈታት አትችሉም” የሚል ሲሞናዊ እንዳይኖር፣ ቢኖርም እንዳያድግ አደረገ። ይህን መሰል መልካም ዘር በተዘራባት እርሻ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ጸሎትን በገንዘብ ተምኖ “የሚሸጥ”፣ ምዕመናንንም ሳይረዱት ከጽድቅ ጎዳና አውጥቶ በውዳሴ ከንቱ ጠልፎ የሚጥል እንክርዳድ ከየት መጣ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደተናገረው “ጠላት ሰው ይህን አደረገ”። (ማቴ. 13:28)

በረከት በማስመሰል አይገኝም!

“የክርስትና ስማችሁ በቅዳሴ እንዲጠራ መባ ስጡ” የሚሉት ሰዎች በምዕመናን ደካማ ጎን በመግባት የመባ ጸሎትንም ሲያሻሽሉ ታዝበናል። ከዚህም የተነሳ በአንዳንድ አጥቢያዎች “ስም ለማስጠራት የሚከፈለውን ዓመታዊ ወጭ” ከፍለው ስማቸውን በምድር እያስጠሩ ከሰማይ መዝገብ የሚያስፍቁ የዋሀን ይታያሉ። አንዳንዶቹም ከፍለው ያገኙት “ስምን የማስጠራት መብት” ምድራዊ ገንዘባቸውን የሚጠብቁበት መድኅን ይመስላቸዋል።  ከላይ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ የመባ ጸሎት መባ ያቀረበውን ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አንድነት የሚደምር እንጂ ምድራዊ በረከትን የሚለምን አይደለም። ይሁንና የጸሎትን ይዘት ለጥቅማቸው የሚቀይሩ ሰዎች በፈጠሩት ልማድ ስማቸውን ለሚጠሩላቸው ባለጸጎች የሚፀልዩት መጤ ጸሎት “ቤታቸውን በበረከት ሙላላቸው፣ ባለጸግነታቸውን ጠብቅ” የሚል ይዘት ያለው ነው። እግዚአብሔር ቸር መጋቢ ነው። ለደሃውም ለባለጸጋውም ያለመከልከል የሚሰጥ የማያልቅበት ሰጭ ነው። መባ ለሚሰጡም  በረከትን እንደሚሰጥ የታመነ ነው። ነገር ግን በማስመሰል ጸሎት ከንቱ ውዳሴ የሚፈልጉ ባለጸጎችን እንጂ እግዚአብሔርን ማታለል አይቻልም። በረከት በማስመሰል አይገኝምና።

መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም!

መባ ስለሰጡት ቤተ ክርስቲያን እንደምትጸልይ፣ ጸሎቱም ውዳሴ ከንቱን ከሚያመጣ ልማድ የተለየ መሆኑን አይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ “አባቶች በጸሎት እንዲያስቧችሁ ስመ ክርስትናችሁን አምጡ” የሚል ልማድ እየተስፋፋ ነው። ከላይ እንደተገለጠው ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት የከበረ ስጦታ የላትም። መባ ስለሚያገቡት ሁሉ የምታደርገው ጸሎትም በረከትን ያሰጣል። ምዕመናንንም የምታውቃቸው በስመ ጥምቀታቸው ስለሆነ መባ ስለሚያገቡት ለመጸለይ ስመ ክርስትናቸውን መያዝ ክርስቲያናዊ ትውፊት ነው። ይሁንና በጸሎት የሚነግዱ “አገልጋዮች” በማስመሰል የሚሄዱበት አካሄድ ምዕመናን እንዲጸለይላቸው መባ እንዲሰጡ በመገፋፋት የበረከትን በር ይዘጋል። በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ፣ በቤተ ክርስቲያንም ትውፊት መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ ጸሎት እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም። እንዲጸለይልኝ ብሎ መባ መስጠት “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ለመግዛት” በማሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።” ብሎ የረገመውን ሲሞን የተባለውን ጠንቋይ መምሰል ነው። (ሐዋ. 8:8-25)

ምዕመናን መባ በመስጠታችን የምንጠቀመው በእግዚአብሔር ፊት የቀና ልብ ይዘን ስንቀርብ እንጂ በስሌት አስተሳሰብ ጸሎትን በመባ ለመግዛት በሚያስብ ሲሞናዊ አካሄድ መሆን የለበትም። እንዲጸለይላችሁ “ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በሚል ማነቃቂያ ገንዘብ ከሚሰበስቡ ሰዎች እንኳ ምን ያህሉ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ ቃል የገቡትን ጸሎት እንደሚያደርጉ እግዚአብሔር ይወቅ! ይበልጥ የሚያሳዝነው በጎ ያደረጉ መስሏቸው ይህንን ልማድ ያስፋፉ ሰዎች ምዕመናንን እንደሚሸለቱ በጎች ለሚቀራመቱ ሀሰተኛ ካህናትና መምህራን አጋልጠው መስጠታቸው ነው። ዛሬ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑ፣ የማይራሩ ሰዎች ራሳቸውን “ሰባኬ ወንጌል፣ ባህታዊ፣ አጥማቂ፣ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጅ” እያሉ የሚጠሩና የሚያስጠሩ በየቦታው በምዕመናን ላይ የሚያደርሱትን በደል ማየት ያሳምማል። በሐሰተኞች ወይም አርቀው በማያዩ ቅን አገልጋዮች ጉትጎታ እንዲጸለይለት መባ መስጠትን የተለማመደ ምዕመን የጨካኞች መረብ ውስጥ መውደቁ የሚደነቅ አይደለም።

ማጠቃለያ

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። በቅንነት የምናቀርበውን መባችንን በምድር ካህናት፣ በሰማይ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይቀበሉናል። ቤተ ክርስቲያንም መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ትጸልያለች። ይሁንና መባ መስጠት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚደምረን፣ ከሚያርገው መሥዋዕተ እግዚአብሔር የሚያሳትፈን የትህትና አገልግሎት እንጂ በዘመናችን እየተለመደ እንደመጣው ክፉ ልማድ “በቅዳሴ ጊዜ ስማችንን ለማስጠራት” ወይም “አባቶች እንዲጸልዩልን” የምንሰጠው ቀብድ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መጻሕፍት ከምዕመናን መካከል በስም ተለይተው የሚጸለይላቸው በዕለቱ መታሰቢያ የሚደረግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩት ናቸው። ይህም የሚደረገው በሞተ ሥጋ ቢለዩንም በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ምዕመናን አንድነት ከሆነች ኦርቶዶክሳዊት ማኅበር እንዳልተለዩ ለማሳየት ነው። ከዚያ ባሻገር የተለየ ችግር የደረሰባቸውን ምዕመናን በክርስቲያናዊ ልማድ በጸሎት ስማቸውን እያነሱ ማሳሰብ ይገባል እንጂ ገንዘብ ተምኖ “ስማችሁ እንዲጠራ መባ ስጡ” ማለት የለየለት ክህደት ነው። ስለሆነም መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ በመስጠት ጸሎትን በገንዘብ በሚተምን ሲሞናዊ ክፋት መተባበር የለብንም። ጸሎት በገንዘብ አይሸጥምና።

ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ። አሜን።

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።

 

 

 

ራሳችንን አናታልል: ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም!

መግቢያ

በዚህ ዘመን ከገጠሙን የክርስትና ሕይወት ፈተናዎች መካከል ዋነኛው በኅሊና የሚታሰበው፣ በልብ የሚመላለሰው፣ በአንደበት የሚነገረውና በእጅ የሚተገበረው ከክርስትና አስተምህሮ ጋር እየተራራቀ መሄዱ ነው። የክርስትናን አስተምህሮ በተደጋጋሚ ሰምተነዋል፣ እንደየ አቅማችንም በተገለጠልን መጠን አውቀነዋል። ነገር ግን ኅሊናችን መልካም ነገርን ብቻ ማሰብ ሲኖርበት የጥላቻ አስተሳሰብ ሲንሸራሸርበት ይውላል። ልባችን ትህትናንና ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ሲገባው ትዕቢትና ንቀት ሲነግስበት ይታያል። አንደበታችን እውነትና ሕይወት የሆነውን የወንጌል ቃል ተናግሮ የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት ማነጽ ሲገባው በስድብ፣ በውሸትና በሽንገላ ያለዚያም እውነትን ከመናገር በመቆጠብ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሲገዘግዘው ይስተዋላል። ሰውን ለመርዳት መዘርጋት የነበረባቸው ብዙ እጆችም ሰውን ለመጉዳት ሲዘረጉ ማየት ልብን ይሰብራል።

እነዚህ መሰል ግብዝነቶች በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ለማያባራ ችግር ካጋለጡት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፣ ከዚህም የከፋ መከራ እንዳይመጣ የሚከለክል ማኅበረሰባዊ ቁመናችን በእጅጉ እየተዳከመ ነው። ምንም እንኳ ለዚህ መሰሉ ችግር የመንግስትና የሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች ተጠያቂነት ጉልህ ቢሆንም ችግሩም ሆነ መፍትሔው ከፖለቲካዊ ኃይሎች አቅምና ቁጥጥር ውጭ መሆኑ ግልፅ ነው። ወደ መፍትሄ የሚደረግ ጉዞ ከአስመሳይነት የተላቀቀ፣ ለእውነት የሚቆምና ራስን በማታለል በእውነት ላይ የማይሸቅጥ ማኅበረሰባዊ ስነ-ልቦና ይፈልጋል። እንደ ክርስቲያን ከበጎ ነገር ጋር ብቻ መተባበር፣ ክፉውንም ያለግብዝነት መቃወም ይኖርብናል። ስለሆነም በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ እነዚህን በክርስትና ሕይወታችን ላይ የተደቀኑ አሁናዊ ፈተናዎች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንዳስሳለን። ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለክቡራን ሊቃውንት ጦማር ኃይልን የሰጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን።

ጥላቻን ከኅሊናችን እናስወግድ!

ከኅሊና የሚመነጭ ሀሳብ የማንኛውም ድርጊት መነሻ ነው። ሀሳብ የፍቅርም የጥላቻም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮ ለጥላቻ አስተሳሰብ አንዳች ቦታ አይሰጥም። የክርስትና አስተምህሮ መጀመሪያውም ማሠሪያውም ፍቅር ነው። የእግዚአብሔር ልጅ (እግዚአብሔር) ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው ስለ ሰው ልጅ ፍቅርና ለሰው ልጅ ፍቅርን ለማስተማር ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‘ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና’ ያለው ለዚህ ነው (1ኛ ዮሐ 4:7-21)። ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‘ከትዕዛዛት ሁሉ የትኞቹ ይበልጣሉ?’ ተብሎ ሲጠየቅ ፍቅረ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን መውደድ) እና ፍቅረ ቢፅ (ባልንጀራን መውደድ) እንደሆኑ በግልፅ ተናግሯል (ማቴ 22:37)። ሕግንና ነቢያትን የሚገልፃቸው ቃልም ‘ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን እናንተም አድርጉላቸው’ የሚለው ቃል መሆኑን አስተምሮናል (ማቴ 7:12)። ከሁሉም የሚበልጠው ፍቅሩ ግን “ነፍሱን ለወዳጁ የሚሰጥ ቢኖርም ለጠላት የሚሞት ከቶ አይገኝም” እንዳለው ራሱን ስለእኛ በመስቀል ላይ ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ነው።

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚያጠነጥነው ፍቅርን በኅሊናችን እንድናኖርና ጥላቻን ከኅሊናችን እንድናርቅ በማስገንዘብ ላይ ነው። ወንድምን/እህትን በምንም ምክንያት መጥላት ተቀባይነት እንደሌለው ለማረጋገጥ ነው “እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ትባሉ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ” (ማቴ 5:44) የተባልነው። ታዲያ እኛ እንኳን ጠላቶቻችንን ይቅርና ወዳጆቻችንስ በአግባቡ እንወዳለንን? አስተሳሰቡን፣ አመለካከቱንና ስነ-ምግባሩን እንኳን ጠንቅቀን የማናውቀውን ሰው በሚጠራበት ስም፣ በሚናገረው ቋንቋ፣ በተወለደበት አካባቢ፣ በሚደግፈው የፖለቲካ ቡድን ብቻ ተነስተን የምንጠላና የምናሳድድ የለንምን? የሞተውን ወንድማችንን እንኳ ከእኛ የተለየ ሀሳብ ስላለው ብቻ በጥላቻ ተሞልተን ድጋሚ መግደል ባንችል “አስከሬኑን ወይም ሀውልቱን እንዲህና እንዲያ እናድርግ” እያልን የጥላቻን ጥግ የምናንፀባርቅ የለንምን? በሃይማኖትም በባሕልም ለማይመስሉን የሌሎች ሀገራት ዜጎች ጠብ-እርግፍ እያልን የምንሰጠውን ክብር ለገዛ ወንድማችን የምንነሳ ‘የስም ክርስቲያኖች’ አይደለንምን? ይህንን ሳናደርግ ‘ክርስትና ፍቅር ነው’ እያልን በየአደባባዩ ስንለፍፍ ብንውል ከእንግዲህ ማን ይሰማናል? እኛ ከሀሳባችን የተለዩት ላይ የምናደርገውን ክፋት ሌሎች በእኛ ላይ ሲያደርጉት “የእውነት አምላክ ሆይ ፍረድ!” ብንል በፍርዱ ሐሰት የሌለበት ጌታ በሚዲያና በምድራዊ ማዕረግ ወይም በመንፈሳዊ ስልጣን ተከልለን እንደምናነሆልለው ጭፍን ተከታይ የሚታለል ይመስለናልን? ይልቁንስ በመጀመሪያ ጥላቻን ከኅሊናችን እናስወግድ! ኅሊናችንንም ለፍቅር እናስገዛ!

በሰዎች መካከል ጥላቻ እንዲነግሥ ዲያብሎስ የሚያማክራት በሚመስል መልኩ በመጥፎ ሀሳብ ስትብሰለሰል የምትውልና የምታድር ኅሊናን ይዘን ክርስቲያን ነን ማለት ራስን ማታለል ነው። ይልቁንስ ‘ምን ብናደርግ ነው በወንድሞች መካከል ያለው ፍቅር ወደላቀ ደረጃ የሚደርሰው?’ የሚለውን መልካም ሀሳብ የምታስብ ኅሊና ልትኖረን ይገባናል። ሌሎች ወገኖቻችን ሲሳካላቸው የምትከፋ፣ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ የምትደሰት ኅሊና ካለችን ራሳችንን እንመርምር። ራሷን እየጎዳችም ቢሆን ሌላውን ወገን መቀመቅ ለመክተት የምትውተረተር ነፍስ ምንኛ የቆሸሸች ናት?! በዚህች ፈንታ ሰዎች ሲሳካላቸው አብራ የምትደሰት፣ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ ስሜታቸውን በመረዳት በቀጣይ እንዲሳካላቸው የሚረዳ ሀሳብን የምታመነጭ ኅሊናን እንያዝ። ‘የሌሎች ኅሊና የሚያስበው ሁሉ ተንኮል ነው!’ ብላ የምትፈርጅ ኅሊና አትኑረን። ይልቁንስ የሌሎች አስተሳሰብ ከቅንነት የመነጨ ነው፣ ክፋት ቢገኝበት እንኳን ካለማወቅ የመጣ ነው ብላ የምትገነዘብና ለማስረዳት የምትጥር ኅሊና ትኑርልን። ኅሊናችንን የመልካም ሀሳብ መፍለቂያና ማብለያ እንጂ የተንኮልና የክፋት ማምረቻና ማከፋፈያ ከመሆን ይጠብቅልን!

ትዕቢትና ንቀት ከልባችን ይወገድ!

የሰውን ልጅ ሁሉ በእኩልነት ማየትና ራስን በትሁት ልብ ዝቅ ማድረግ የክርስትና መሠረታዊ መርሆዎች ናቸው። ሁሉም የሰው ልጅ በሥላሴ አምሳል የተፈጠረ ነው። በሰዎች መካከል በአፈጣጠር መበላለጥ የለም። ከዚህ አንጻር መሠረታዊው የክርስትና መርህ የሰዎችን እኩልነት ማመን ነው። ‘የእኛ ወገን ከሌላው ይበልጣል’ ብለን የምናስብ ከሆነና ለሰውነት ደረጃ የምንሰጥ ከሆነ እንኳን የክርስትናን አስተምህሮ የዓለምን ሕግ አላወቅንም። የሰው ልጅ የትም ቢወለድ፣ የትኛውንም ቋንቋ ቢናገር፣ የፈለገውን ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አቋም ቢይዝ፣ በጫካም ይሁን በተንጣለለ ፎቅ ቢኖር፣ ወርቅ ቢለብስ ወይም ራቁቱን ቢሄድ፣ ድንጋይ ወይም ዛፍ ቢያመልክ፣ በዶማ ቢቆፍር ወይም በትራክተር ቢያርስ፣ የሀገር መሪ ወይም የከብቶች እረኛ ቢሆን፣ ቢማር ወይም ጭራሽ ባይማር በሰውነቱ እኩል ነው። ሁሉም በሥላሴ አምሳል የተፈጠረ፣ በዚህች ዓለም ሲመጣ ራቁቱን የተወለደ፣ ሲሞትም ሥጋው ወደ አፈር የሚመለስ፣ በመጨረሻው ዘመንም በእግዚአብሔር ፊት እንደ ሥራው ሊሰጠው ለፍርድ የሚቀርብ ፍጡር ነው። በምድር ላይ ስንኖር በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕድሜ፣ በዕውቀት፣ በአመለካከት፣ በሃይማኖት፣ በጉልበት፣ በሥልጣን፣ በሥልጣኔ፣ በሀብት፣ በመኖሪያ ቦታ ብንለያይም ሁላችንም እኩል ሰዎች ነን።

ትዕቢት ራስን የበላይ አድርጎ የመመልከትና ሌሎችን ዝቅ አድርጎ የማየት ልክፍት ናት። ከትዕቢት ሁሉ አስቀያሚዋ “ጊዜ ሰጠን” ብለን የሀሳብ ተቀናቃኞቻችንን በሀሰት እያሸማቀቅን “እነርሱ ካልጠፉ ሰላም አይኖረንም” የምትል የሀሳብ ልምሾ ያጠቃቸው ደካሞች ሾተል ናት። እርሷም የውድቀት ሁሉ የመጀመሪያ እርምጃ ናት። ሳጥናኤል ከክብሩ ለመውረድና ለመዋረድ ሲጀምር በትዕቢት ነበር (ኢሳ  14:12)። በትዕቢት የጀመረውን የውርደት ጉዞ በውድቀት ፈፅሞታል። የፈርዖን ከልክ ያለፈ ትዕቢትም በኤርትራ ባሕር ከመስጠም ውጭ ያተረፈለት አንዳች ነገር አልነበረም። የጎልያድ ትዕቢትም እንዲሁ በአንዲት ጠጠር ፍጻሜውን አግኝቷል። በተለይም በጎ አሳቢ መስላ በሌሎች ላይ መዓትን የምትጠራ አንደበት ሰውን እንጂ እግዚአብሔርን ማታለል አትችልም። ለእያንዳንዷ የግፍ ንግግራችንና ተግባራችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንከፍልባታለን። በዚህ ምክንያት ነው ትዕቢት የውድቀት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው የምንለው። ትዕቢት የምንይዘው እሴት ሳይሆን ታግለን የምናሸንፈው ፈተና መሆኑን ሲያስተምረን ነው ጌታችንም በገዳመ ቆሮንቶስ ድል ካደረጋቸው ሦስት ፈተናዎች አንዱ ያደረገው። (ማቴ 4:1)

በጥበብ የተመላች ትህትና ግን የብልህነት ውጤትና የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት የመጀመሪያ ምዕራፍ ናት። ስለዚህ ነው ጌታችን እርሱ ከሁሉ በላይና የሁሉ ፈጣሪ ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ በፍጹም ትህትና በበረት የተወለደው (ሉቃ 2:10)፣ የሰማያውያን ሠራዊት ጌታ ሲሆን በሄሮድስ ሠራዊት ወደ ግብፅ የተሰደደው (ማቴ 2:13)፣ በተናቀችው ናዝሬት ያደገው (ዮሐ 1:47)፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ ያጠበው (ዮሐ 13:1)፣ ፈጣሪ ሲሆን በፍጡር እጅ የተጠመቀው (ማቴ 3:15)። ፈራጅ ሲሆን በጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቀረበው። መላእክቱን ልኮ ሰዎችን ከመከራ የሚያድን ሆኖ ሳለ እርሱ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ መከራን የተቀበለው። ትህትናን በቃልና በተግባር ለማስተማር መጥቷልና “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደግ ይዋረዳል፣ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ከፍ ይላል” (ሉቃ 14:11) በማለት ያስተማረውም ለዚሁ ነው። ይህች ትህትና ራስን ዝቅ በማድረግ ከሁሉም ጋር በጥበብ የምታኖር ምሥጢር ናት።  ይህች ትህትና በጥበብ ላይ የተመሠረተችና የትዕቢተኞችን የሞኝነት ትምክህት የምትንድ እንጂ በድክመትና በድንዙዝ አስተሳሰብ የበታችነትን ተቀብላ ለትዕቢተኞች ክፉ ሀሳብ ተገዢ ልትሆን አይገባም።

በልባችን ‘እኔ ታላቅ ነኝ፣ እኔ ኃያል ነኝ፣ እኔ አዋቂ ነኝ፣ እኔ ብልህ ነኝ፣ እኔ ባለሥልጣን ነኝ፣ እኔ ውብ ነኝ፣ እኔ ባለሀብት ነኝ፣ እኔ መንፈሳዊ ነኝ፣ እኔ ስልጡን ነኝ ወዘተ’ በማለት ራሳችንን ከሌላው ሰው ከፍ ባለች ማዕረግ ላይ ማስቀመጥ የውድቀታችን መጀመሪያ መሆኗን እናስተውል። ይልቁንስ እኛ ከሌላው መካከል እንደ አንዱ መሆናችንን እንቀበል። እኛ የተለየን መሆናችንን ለማሳየትና አድናቆትን ለማትረፍ አንድከም።  ይልቁንም እኛ አንድ የተለየ ነገር ቢኖረን እንኳን ሌላው ቢያንስ እንደ እኛ የራሱ የተለየ ነገር እንዳለው እናስተውል። ሌሎች በከፍታ አስቀምጠውን ወደላይ አሻቅበው እንዲያዩን፣ እኛም በከፍታ ተቀምጠን ሁሉንም ቁልቁል ለማየት አንመኝ። ይህ ሳጥናኤል ከመጨረሻው የፍጡራን ልዕልና ወደ መጨረሻው የፍጡራን ውርደት የወደቀበት ነውና። ይልቁንም ለሌሎች ከልባችን ክብርን በመስጠት ዝቅ ብለን በትህትና እናገልግላቸው። ያን ጊዜ ከፍ ከፍ እንላለን።

የስድብ ቃል ከአንደበታችን ይራቅ!

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው አንደበት እሳት ነው (ያዕ 3:1)። እሳት በአግባቡ ካልተያዘ ሀገርን ያቃጥላል፣ ዓለምንም ወደ አመድነት ሊቀይራት ይችላል። እሳት በአግባቡ ስንጠቀምበት ደግሞ ምግብ ያበስልልናል፣ ለሰውነታችን ሙቀትን በመስጠት ብርድን ያስወግድልናል፣ ነበልባሉም በጨለማ ብርሃን ይሆንልናል። አንደበትም እንዲሁ ነው። የምንናገረውን ካልመረጥን ንግግራችን ጥፋትን ያስከትላል። መርጠንና መጥነን ስንናገር ሰውን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እንገነባለን። ስለዚህ አንደበታችን ለእኛ የሚጠቅመንን ብቻ ሳይሆን ለሚሰማን ሰው የሚጠቅመውን ነገር ጭምር ልትናገር ይገባታል።

የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ከሚያክል ጌታ ገነትን ከምታክል ቦታ ተለይቶ ወደ ምድረ ፋይድ የተጣለው ዲያብሎስ ካደረባት እባብ አንደበት የወጣውን ቃል ሰምቶ ነው እንጂ ዲያብሎስ እጁን ይዞ ዕፀ በለስን አላስቆረጠውም፣ ቆርጦም አላጎረሰውም። በእባብ አንደበት “ዕፀ በለስን ብትበሉ ሞትን አትሞቱም፣ ይልቁንም አምላክ ትሆናላችሁ” (ዘፍ 3:4) ብሎ ምክር በመስጠት ብቻ አሳሳተው እንጂ። ዛሬም ብዙዎችን በወንድም እህቶቻቸው ላይ በጭካኔ የሚያነሳሳቸው፣  ከእውነተኛ የሃይማኖት መንገድ የሚያስወጣቸው፣ ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን የሚያሠራቸው ከአንደበት የሚወጣው ክፉ ቃል ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን “ከአፍ የሚወጣው እንጂ ወደ አፍ የሚገባው ሰውን አያረክሰውም (ማቴ 15:1)” በማለት ያስተማረው። ከአንደበት የሚወጣው ክፉ ንግግር ተናጋሪውንም ሰሚውንም የማርከስ አቅም አለው። ከዚህ በተቃራኒውም የሰው ልጅ የወንጌልን ቃል የተቀበለውና የሚቀበለው ከአንደበት በሚወጣው ቃል (ስብከት) ነው። ጌታችን በምድር ላይ ሐዋርያትን የጠራቸው፣ ያስተማራቸውም በአንደበቱ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ክርስትናን ወደ ዓለም ያዳረሱት በአንደበታቸው በመስበክ ነው። በየዘመናቱ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ለጽድቅ የበቁት የእግዚአብሔርን ወንጌል በጆሮአቸው ሰምተው፣ በልባቸው አምነው፣ በአንደበታቸው መስክረው ነው። ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙባት ጸሎትም የምትደረገው (እግዚአብሔር የልብን ቢያውቅም) በአንደበት በመናገር ነው።

ከአንደበታችን ምስጋናና መልካም ነገር እንጂ የስድብ ቃል ሊወጣ አይገባም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብ በስድብ ፈንታ አትመልሱ፣ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፣ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና” (1ኛ ጴጥ 4:9) እንዳለው አንደበታችን እውነተኛ እምነትን፣ ፍቅርና ተስፋን የምትሰብክ ልትሆን ይገባል። ወንድሙን የሚሳደብ በሰማይም በምድርም ፍርድ እንደሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል (ማቴ 5:22)። በዘመናችን ግን ከወንድሞቻችንም አልፎ አባቶቻችን በአደባባይ በዱርየ ቋንቋ ሲሰደቡ እያየን ነው። የሚያሳዝነው በፖለቲካ አቋም የሚመስሏቸውን በሃይማኖት ግን ምንፍቅናቸው የታወቀውን ‘አገልጋዮች’ እያሞገሱ፣ በሃይማኖት አቋም የማይለዩትን በፖለቲካ አስተሳሰብ የተለዩትን አባቶች እጅግ በወረደ ጸያፍ ቋንቋና በውሸት ስማቸውን የሚያጠፉ፣ ራሳቸውን ግን “ታላላቅ” እንደሆኑ የሚቆጥሩ መንፈሳውያን አገልጋዮች ለምዳቸውን እየገፈፉ ያለሀፍረት መገለጣቸው ነው። ይህም የክርስትና ሕይወታችን ምን ያህል እየተጎዳ እንደመጣ ያመለክታል። በዓለማዊ አስተሳሰብ እንኳን ቢሆን አንደበታችን ሰላምን፣ እኩልነትን፣ ፍትሕን፣ ዕድገት፣ ብልጽግናን የምትሰብክ መሆን ይጠበቅባታል። ሲቻል በግልፅ ሳይቻል በአሽሙር የሰውን ልጅ በጅምላም ይሁን በተናጥል በተወሰነ ሳጥን ውስጥ እያስገባች የምትፈርጅ አንደበትን እናርቅ። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ:- በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ” (1ኛ ዮሐ 3:18) ብሎ እንዳስተማረው የሽንገላ ፍቅርን ከልባችን እና ከአንደበታችን እናስወግድ። እኔ የምናገረው ብቻ እውነት፣ እኔ የምናገረው ብቻ አዋጭ፣ ሌሎች የሚናገሩት አፍራሽ ነው ብላ የምትናገር አንደበትም ትታረም።

በፍጹም ትዕቢት ‘አንተ የተመረጥክ ዘር ነህ፣ ከሌላው ጋር ለመሥራት አትውረድ’ እያለች በሰዎች መካከል የሰውነት ደረጃን የምትሰብክ አንደበት አታስፈልገንም። ይልቁንስ ሁላችንም ወንድማማቾች/እህትማማቾች ነን፣ አብረን እንኑር እያለች ፍቅርን የምትሰብክ አንደበት ትለምልምን። ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ፣ ወንድም ከወንድሙ እንዲጣላ በሐሰት የምትሠራ አንደበት አትኑረን። ይልቁንስ ወንድማማቾች እንዲተባበሩ ፍቅርን የምትሰብክ አንደበት ትኑረን እንጂ። በኢንተርኔት መስኮት ብቅ ብላ ‘እገሌ የሚባል ወገን በድሎሃል፣ ገድሎሃል፣ ሰብሮሃል፣ አሁንም ተገዢ ሊያደርግህ ነውና ተባብረህ ስበረው፣ በለው፣ ግደለው’ እያለች በሰዎች መካከል መገዳደልን የምትሰብክ አንደበት አትኑር። መቶ አመታትን ወደኋላ ተጉዛ በእውነትም ሆነ በሐሰት የተደረተ የታሪክ ምራጭን ለማጋጨት የምትጠቀም አንደበት አትኑረን። እንዲሁም “ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አንይ” በሚል ምክንያታዊ ትንታኔ ታጅባ የሌሎችን የታሪክ ምልከታ የምትወቅስ ለራሷ ሲሆን ግን ምዕተ ዓመታትን ወይም አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዛ የሚጠቅማት የመሰላትን የእውነትም ሆነ የፈጠራ ታሪክ ለመሰብሰብ የምትሮጥ አንደበት አትኑር።

በምድራዊ አመለካከትም ቢሆን የአንዱን አመለካከት ርኩስ የሌላውን ቅዱስ፣ የአንዱን የሰይጣን የሌላውን የመልአክ፣ ያንዱ እንጦሮጦስ መግባት ያለበት የሌላው ወደ ቤተ መንግስት መግባት ያለበት አድርጋ ለምትናገር አንደበት ማስተዋልን ይስጥልን። የተለየ ሀሳብ የሚያነሳን ወገን ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ሀገር፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ኦርቶዶክስ፣ ፀረ-ሙስሊም፣ ፀረ-ሕዝብ ወዘተ እያለች በመፈረጅ ምክንያታዊ ተዋስኦን ለምትዘጋ አንደበት ማስተዋልን ይስጥልን። ይልቁንም የሁሉንም አመለካከት በማክበር ኑ እንመካከር፣ እንነጋገር፣ ሀሳቦችን እንሞግት፣ ለሁላችንም የሚበጀውን እንያዝ የምትል አንደበት ትስፋፋ! ‘እነርሱ ይጥፉ እኛ እንስፋ’ የምትል ፀረ-ሰው አንደበት አታስፈልገንም። ይልቁንስ ‘እኛ እና እነርሱ’ ሳይሆን ሁሉም እንዲሰፋ የምትሰብክ አንደበት ትብዛ።

አንዱ ወገን ሲበድል ምንም እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ፣ አንዳንዴም አሞግሳ፣ ሌላው ሲበድል ግን ሀገር ይያዝልኝ ብላ እሪሪሪ የምትል አንደበት ፍትሐዊነት የጎደላት ስለሆነች ትታረም። አንዱ ወገን ላይ መከራ ሲደርስበት በግልፅ በመናገር፣ በደስታ በመጨፈር ወይም በልቧ ‘እሰይ፣ እንኳን፣ ይበለው፣ የእጁ ነው’ እያለች ሌላው ወገን በተራው ተመሳሳይ መከራ ሲደርስበት ደግሞ ዋይ ዋይ በማለት አጥፊዎችንም ንፁሐንንም ይጥፉ የምትል አንደበት በክርስትና መዶሻ ተስተካክላ ሁሉንም በእኩልነት ትመልከት። አንዱ ወንድም ወይም እህት በአንዲት ሀሳብ ብቻ ስለተለየ እንመካከር፣ እነጋገር፣ እንወያይና የተሻለውን እንያዝ ከማለት ይልቅ “ይታሰር፣ ይገረፍ፣ ይሰቀል!” እያለች ያለ ፍትሕ በሰው ላይ የምትፈርድ አንደበት በክርስትና አስተምህሮ ትታረቅ! ያለ አንዳች ገደብ ሌላውን ወገን በመናቅና በመሳደብ ለምዕመናንና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻን የምታተርፍ፣ በቀለኛውም ወገን በአስመሳይ አንደበተኞች ጥፋት ተነስቶ በንፁሐን ምዕመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ምክንያት የምትሆን አንደበት ከዚህ ድርጊቷ ትታቀብ።

እጆቻችን ለመጉዳት ሳይሆን ለመርዳት ይዘርጉ!

እጆቻችን እርዳታን የሚሻ ሰውን ለመርዳት ሊዘረጉ ይገባል። የሰውን ንብረት ለመውሰድ ሳይሆን የእኛን ለተቸገረ ሰው ለመስጠት ሊዘረጉ ይገባል። ያለውን በመስጠት እንጂ የሌላውን በመውሰድ የተጠቀመ የለምና። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም በሰው ላይ ለማትረፍ፣ ገንኖ ለመታየት፣ ሳይሆን የሰውን ሕይወት ለማትረፍ ሊተጉ ይገባል። ከእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የጠፉትንም ቢሆን የፍቅርን እጅ በመዘርጋት መፈለግ ይገባል እንጂ የጠብና የክርክርን ሰይፍ በመምዘዝ በማሳደድ መመለስ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ክርስቶስ የጠፋውን አዳም በፍቅር እንደፈለገው ማስተዋል ይገባናል። በቤተ ክርስቲያን ያሉትን ለማስወጣት ሳይሆን የወጡትን ለመመለስ እጃችን ይዘርጋ። ያን ጊዜ ክርስቶስ ይሰማናል።

ሰዎች ብዙ ደክመው ያፈሩትን ንብረት ለማጥፋት የምትዘረጋ እጅ አትኑር። ይልቁንስ ሰዎች ደክመው ያፈሩትን የምትጠብቅና በዚያም ላይ ሠርታ የምትጨምር እጅ ትዘርጋ። የሰው አካል ላይ ጉዳትን ለማድረስ የምትዘረጋ ክፉ እጅ አትኑር። ይልቁንስ እንደ ደጉ ሳምራዊ የተጎዳውን ለማከም መልካም እጆች ሁሉ ይዘርጉ እንጂ። ሰዎች ተወልደው ካደጉበት፣ ለወግ ለማዕረግ ከበቁበት፣ ወልደው ከከበዱበት ቤታቸውና ሠፈራቸው ለማፈናቀል የምትዘረጋ እጅ አትኑር። ይልቁንስ ማደሪያ ማረፊያ ለሌላቸው ወገኖች መኖሪያን ለመሥራት እጆች ሁሉ ይዘርጉ እንጂ። የመገፋትን፣ የመበዝበዝንና የመፈናቀልን ክፉነት ለመረዳት በየግላችን እስኪደርስ አንጠብቅ። የራሳችን በምንለው ወገን ላይ የደረሰው ወይም የሚደርሰው መሰል በደል እንደሚያመን “የእኛ” የምንለው ወገን በሌሎች ላይ መሰል በደል ሲያደርስ ብንችል እናስቁመው፣ ቢያንስ ግን አንተባበረው፣ ለጥቅማችን አንሸፋፍነው። ለተበደሉት ካልቆምንላቸው፣ በተለይም በጉዳታቸው ከተባበርን፣ ከተሳለቅን እንዴት በመከራችን ወቅት አምላካችንን “አቤቱ የደረሰብንን እይ!” ማለት እንችላለን?!

የጦር መሣሪያን በወገን ላይ ለማንሳት የምትጣደፍ እጅ አትበርታ። በተለይም ገዳይነትን “ባሕል” አድርጋ የምታንቆለጳጵስ አላዋቂነት ከእኛ የተለየች ትሁን።  ይልቁንስ ለልማት ሥራ የሚውሉ የተለያዩ መሣሪያዎችን የምታነሳ እጅ ትበርታ። ለእግዚአብሔር ምስጋናን ለማቅረብ የዜማ መሣርያን የምታነሳ እጅም ትጠንክር። ጸሎትና ልመናን ለማቅረብ ወደ እግዚአብሔር የምትዘረጋ እጅም መሻቷን ታግኝ። ከዚህም በላይ ሰውን ለመባረክ፣ አጋንንትን ለማንበርከክ የክርስቶስን መስቀል የምታነሳ የካህናት እጅ ትጽና። በደለኞችን ለማበረታታት፣ ንፁሐንን በሐሰት ለመርገም የከበረውን የክርስቶስ መስቀል በሽንገላ የሚያነሱ ፍኖተ በለዓምን የተከተሉ ነቢያተ ሐሰት (የሀሰት ካህናት) እጆች ከአህዮቻቸው ይማሩ። የካህናት እጆች በረከትን ለማውረስ እንጂ ከጥላቻ ፖለቲከኞች ጎን ተሰልፈው “የግፋ በለው” መፈክር አንጋቢዎች መሆን የለባቸውም። እጆች ለሰው ልጅ የተሰጡት የሚጠቅምና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራን ለማከናወን ነውና።

የሰውን ልጅ እርስ በእርስ እንዲጋጭ ወይም ሰውን ወደ ኃጢአት የሚመራን ጽሑፍ የሚጽፉ እጆች ይህንን ትተው ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም፣ ሰውን ከሰው የሚያቀራርብ፣ ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ጽሑፍን ለመጻፍ ይትጉ። የተዛባ ትርክትን እየጻፉ ለትውልድ ጥላቻን ከማትረፍ እውነተኛውን ታሪክ ጽፈው የሰውን አዕምሮ ለማነጽ ይትጉ። አንዱን ወገን የሚያንቋሽሽና የሚያሳንስ፣ ሌላውን ብቻ የሚያኩራራና የሚኮፍስ ጽሑፍን የሚጽፉ እጆች ክብር ለሚገባው ክብርን ሰጥተው ፍቅርን ለማፅናት ይጽፉ ዘንድ እንጸልይ። ለትውልድ የሚተርፍ ዕውቀትንና ጥበብን በጽሑፍና በስዕል ማስቀረት የሚችሉ እጆች ከዚህ በተቃራኒ ለድንቁርናና ለተንኮል የሚዳርግን ጽሑፍ እየጻፉ ለትውልድ የሚተርፍ ጠባሳን እንዳያስተላልፉ እንጸልይ። መጸለይም ብቻ ያይደለ የበኩላችንን ድርሻም እናበርክት።

ማጠቃለያ

ጥላቻን በኅሊናችን ይዘን፣ ትዕቢትና ንቀትን በልባችን አኑረን፣ አንደበታችን ስድብን እያፈለቀና እጆቻችን ሰውን ለመጉዳት ያለመከልከል እየተዘረጉ ፍቅር በእኛ ዘንድ አለ ብንል ራሳችንን እናታልላለን፣ እግዚአብሔርም ያዝንብናል። በመርህ ሳይሆን በወገንተኝነት እየመረጥን የምናሞግስና፣ እየመረጥን የምናወግዝ ከሆንንም ፍትሐዊነት በእኛ ዘንድ የለችም። እውነትን እየሸሸግንና በሐሰት መነገድን እንደ ስልት እየቆጠርን ራሳችንን የእውነት ጠበቃ አድርገን ብናቀርብ ድንጋዮች ሳይቀሩ ይታዘቡናል። መስደብንና ማሸማቀቅን አፋችን ገንዘብ ካደረገው በምን አንደበታችን ጸሎትን እናቀርባለን? መጽሐፍ “ከእንግዲህ ወዴት እንደወደቅህ አስብ፣ ፈጥነህም ንስሐ ግባ፣ ያለዚያ እመጣብሃለሁ (ራዕይ 2:16)” እንዳለ በደላችንንና ኃጢአታችንን አምነን ንስሐ እንግባ። በፍትሕና በእውነት ሳይሆን በወገንተኝነት ተይዘን “አገልጋዮች” እየተባባልን “ጠላት” ያልነውን ወገን ለማጥፋት በአንደበት ስንዘላብድ፣ በተግባር እኩይ አስተሳሰብን ስናራምድ እየዋልን ስለ ፍቅር ብንደሰኩር ሰው የፍቅር ትርጉም እንዲጠፋበት እናደርግ እንደሆን እንጂ ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ ጸሎት የለንም። ስለሆነም ፍቅራችን ያለ ግብዝነት ይሁን፣ ክፉውን እንጸየፍ፣ ከበጎ ጋር እንተባበር (ሮሜ 12:9)። ፍቅርን ገንዘብ ሳናደርግ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ብንል ራሳችንን እናስታለን። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅምና።

ኢታርዕየነ እግዚኦ ሙስናሃ ለቤተ ክርስቲያን!

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።

በሥራ መትጋት: ሊሠራ የማይወድ አይብላ!

መጽሐፍ ቅዱስ ገና ሲጀምር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ (ዘፍ 1:1)” በማለት የእግዚአብሔርን ሥራ ይናገራል። በዕቅዱ መሠረት ለስድስት ቀናት ከፈጠረ በኋላ  “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ (ዘፍ 2:2)” እንደተባለ ሥራውን ሲፈጽም ዐርፏል። ጌታችንም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ (ዮሐ 5:16)” ብሎ እንዳስተማረን እግዚአብሔር ድንቅ ነገርን ሲሠራ ይኖራል። በሥራ አንቀፅ የጀመረው መጽሐፍ ቅዱስ “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ (ራዕ 22:12)” በማለት በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር ለሁሉም እንደ ሥራው ሊሰጠው እንደሚመጣ አበክሮ በመግለጽ መልእክቱን ያጠቃላል። ይሁንና በአንዳንድ ኦርቶዶክሳዊያን ዘንድ ለሥራ ያለው አመላካከት ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጋር የማይስማማና ወገኖቻችንንም ለድህነት የሚዳርግ ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ ሥራን የሚመለከተውን አስተምህሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ እንዳስሳለን፡፡

ሰው የተፈጠረው ለሥራ ነው!

የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ ዋነኛው ሥራን ለመሥራት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረ በኋላ “እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው (ዘፍ 1:28)” ብሎ እንዳዘዘው የሰው ልጅ ለሥራ ነው የተፈጠረው። በዓለም የተፈጠረውን ሁሉ መግዛት (ማስተዳደር)  ለሰው ልጅ የተሰጠው የሥራ ድርሻ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከፈጠረው በኋላ ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔደን ገነት ያኖረውም (ዘፍ 2:15) ለሥራ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። የሰው ልጅ ዕፀ በለስን በልቶ ከተሳሳተ በኋላ ግን ሥራ እንዲከብድበት ሆኗል። “አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህእሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና (ዘፍ 3:17-19)” እንደተባለ በሥራ ደክሞ የላቡን ዋጋ እንዲበላ ተፈርዶበታል። በክርስቶስ ቤዛነት ወደ ቀደመው ክብሩ ቢመለስም በምድር ላይ እስካለ ድረስ ግን እየሠራ ይኖራል።

ሥራ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው!

ሥራን መሥራት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ትዕዛዛት መካከል አንዱ ነው። “ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ (ዘፍ 20:9 34:21)” እንዳለው የሰው ልጅ ስድስቱን ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን ሰንበትን ሊያከብር ይገባል። “ሰንበትን አክብር” የሚለውም ሰው በሰንበት ቀን በተለየ ሁኔታ ምስጋናን እንዲያቀርብና ትሩፋትን እንዲሰራባት እንጂ ተቀምጦ ወይም ተኝቶ እንዲውል አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። የበዓል ቀናትም እንዲሁ መንፈሳዊ ሥራ የሚከናወንባቸው ናቸው፡፡ የበዓል ቀናት ማኅሌት፣ ኪዳን፣ ቅዳሴና የመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከናወኑባቸው፣ እኛም ምስጋናን የምናቀርብበት፣ ወገኖቻችንን የምንጎበኝባቸው (የምናስብባቸው) እንጂ ሳንሠራ የምንውልባቸው የዕረፍት ቀናት አይደሉም፡፡

ይህንን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በማክበር በገዳም ያሉ አባቶችና እናቶች ከጸሎት ሰዓት በስተቀር ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ ተጠምደው ያሳልፋሉ፡፡ ይህም ትጋታቸው ገዳማቸውን ከመጥቀሙ ባሻገር የመንፈሳዊ ትጋታቸው አንዱ አካል መሆኑን የቅዱሳን ገድላትና በዘመናችን የምናውቃቸው ደገኛ ገዳማውያን ተጋድሎ ይመሰክራሉ፡፡ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ያሉ ካህናትም እንዲሁ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ከሚፈጽሙበት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜ የግብርና ሥራቸውን በመሥራት ይተጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ትጋት አንዳንድ በከተማዎች ለሚኖሩ ካህናትና አገልጋዮችም ትምህርት ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ልበ አምላክ የተባለ ንጉስ ዳዊት “የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይሆንልሃል (መዝ 128:2)” እንዳለው ሁሉም መልካም እንዲሆንልን በሥራ ልንተጋ ይገባናል፡፡ በከተማና በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች መንፈሳዊ አገልግሎት ቁሳዊ ከሆነባቸው፣ አብያተ ክርስቲያናትም የግለሰቦችና የቡድኖች መነታረኪያ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ከስራ ይልቅ በአሉባልታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ምንደኛ ሰዎች አገልግሎትን እንደ ተራ ስራ መያዛቸውና በጥቅም መነፅር መመልከታቸው መሆኑን መታዘብ ይቻላል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን:- ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና:- ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና (ተሰሎ 3:10)” በማለት ሥራን የማይወዱትንና በማያገባቸው ነገር የሚገቡትን ገስጿቸዋል፡፡ ‘ሊሠራ የማይወድ አይብላ’ የሚል ታላቅ ትዕዛዝንም አስተላልፎ ነበር፡፡ ሰው የተፈጠረው ለመሥራት ነውና ሊሠራ የማይወድ ሰው አይብላ አለ፡፡ ሰው ሠርቶ የላቡን ዋጋ እንዲበላ ተፈርዶበታልና ሊሠራ የማይወድ አይብላ ማለቱም ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው የሰጣቸው ትዕዛዝ ‘የማይሠራ አይብላ’ ሳይሆን ‘ሊሠራ የማይወድ አይብላ’ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች መሥራት እየፈለጉ ነገር ግን መሥራት የማይችሉባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች አሉና ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች መሥራት እየወደዱ/እየፈለጉ መሥራት ባለመቻላቸው ልንረዳቸው ይገባል እንጂ አይሠሩም ተብለው ሊገለሉ አይገባም፡፡

ለመልካም ሥራ እንትጋ!

ሥራን ለመሥራት የተፈጠረው የሰው ልጅ ሥራውን ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በሥራ መትጋት እንዳለባቸው ሲያስተምር “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት (ገላ 6:9)” በማለት ነበር ያሳሰባቸው፡፡ በሮሜ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖችም በጻፈው መልእክቱ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ (ሮሜ 12:11)” በማለት በሥራ እንዳይለግሙ ጽፎላቸዋል፡፡ በሥራ መለገም፣ በሥራም የተነሳ ማንጎራጎር የሚያስነቅፍ ተግባር ነውና ስለዚህም ለፊልጵስዮስ ሰዎች ሲጽፍ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ (ፊልጵ 2:14)” በማለት አስተምሯቸዋል፡፡

ይኸው የተወደደና ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን የሚባለው ሐዋርያ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስም በምድር ላይ ያለውን አገልግሎትና ሥራ በትግል መስሎ ሲያስተምረው “ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል (2 ጢሞ 2:6-7)” በማለት የሰው ልጅ በተሰማራበት ዘርፍ ጸንቶ መታገል (መሥራት) እንዳለበት በአጽንኦት መክሮታል፡፡ ራሱም በሰው ላይ ላለመክበድ እየሠራና እየደከመ ይኖር እንደነበር ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን (1 ቆሮ 4:12-13)” በማለት ምሳሌ ሆኗቸዋል፡፡ ይህ አምደ ቤተ ክርስቲያን የተባለ ሐዋርያ ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ድንኳን ይሰፋ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ (ሐዋ 18፡1-4)፡፡

ስለዚህም ሲናገር “እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ” (ሐዋ 20፡33-35) ብሏል፡፡ ሌሎችንም ማስቸገር እንደሌለበት ሲናገር “ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም” ( 2ኛ ተሰሎ 3፡8) በማለት አስገንዝቦናል፡፡ ለፊልጵስዮስ ቤተ ክርስቲያንም ያለ አንዳች ክፍያ እንዳገለገላቸው ሲናገር  “የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ” (ፊልጵ 4፡14-16) ብሏል፡፡ ይህም ለዘመናችን አገልጋዮች ሁሉ አርአያ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ የተባለ ሐዋርያ ከሰፊው ስብከቱ በተጨማሪ ድንኳን ይሰፋ ከነበር የዘመናችን አገልጋዮችማ እንደምን ሥራቸውን በመደበኛነት አይሠሩ?!

በተለይም በዝርወት ዓለምና በታላላቅ ከተሞች ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ካህናትና ሌሎችም አገልጋዮች (አረጋውያኑን ሳይጨምር) ለሥራ የሚሆን በቂ ጊዜና ጥሩ የሥራ ዕድልም ስላላቸው ሠርተውበት ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን በብዙ መጥቀም ይችላሉ። እንደሚታወቀው በአብዛኞቹ የውጭው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት አብዛኛው (አንዳንዴም ሙሉው) መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወነው በሰንበተ ክርስቲያን (እሁድ) ነው። ምንም እንኳን ከቤተ መቅደስ ውጭ የሚሰጡ ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ቢኖሩም እነዚህ አገልጋዮች ቢያንስ በከፊል (part-time) መሥራት ይችላሉ። ብዙዎቹም የመሥራት ፍላጎቱ ያላቸውና ቤተ ክርስቲያንንም ያለ ክፍያ ማገልገል የሚፈልጉ እንደሆኑ እንረዳለን። ምዕመናንንም ይህንን የማበረታታት፣ የሥራ ዕድሎችንም የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸው። ሥራ የማይሰራ አእምሮ የተንኮል፣ የክፋትና የአሉባልታ ተጠቂ ስለሚሆን ከአገልጋዮቹ ግላዊ ሕይወት አልፎ ቤተ ክርስቲያንንም እንደሚያውክ በየቦታው የምናየው እውነታ ነው።

በሌላ በኩል በ(ለ)ሥራ መትጋት ማለት ሥራ ቦታ በተመደበው ሰዓት መግባት፣ በተመደበው ሰዓት መውጣት ወይም ለተወሰነው ሰዓት ሥራ ላይ መቆየት ማለት ብቻ አይደለም። ለሥራ መትጋት ማለት ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ መሠራት ያለበትን ሥራ በጊዜው ማከናወን ነው። ለሥራ መትጋትም የሚባለው አለቃን ለማስደሰት የሚደረግ ሳይሆን ለኅሊናና ለእግዚአብሔር ብሎ የሚገባውን በጥራት ማከናወን ነው። ለሥራ መትጋት የሚባለውም የሚከፈለንን ያህል ብቻ መሥራት አይደለም፣ ሊሠራ የሚገባውን ያህል መሥራት እንጂ። ለሥራ የሚተጋ ክርስቲያን ስለ ሠራ ይከፈለዋል እንጂ የሚከፈለውን ያህል ብቻ አይሠራም። ገንዘብ ለሥራ ከሚያተጉን ብዙ ምክንያቶች አንዱ ምክንያት እንጂ ብቸኛው ምክንያት አይደለም። ለገንዘብ ብቻ ብለን በሥራችን የምንተጋ ከሆነ ጉልበታችንን እየሸጥን እንጂ ለሥራ እየተጋን አይደለም፣ ገንዘብ ብቻውን የመንፈስም ሆነ የኅሊና ዕረፍትን አይሰጥምና። ይልቅስ የምንሠራው ሥራ ለማኅበረሰቡ ሕይወት ያለውን ጠቀሜታ እያየን ልንተጋ ይገባናል።

ታካችነትን እናስወግድ!

በሥራ ታካች መሆን በምድር ድህነትን ሲያስከትል በሰማይ ደግሞ ድኅነትን ያሳጣል፡፡ ታካችነት በሥጋም በነፍስም እንደሚጎዳ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ ስለሥራ በልዩ ሁኔታ የተሰጠውን ሀብተ ጥበብ ተጠቅሞ የጻፈው ጠቢቡ ሰሎሞን ታካችነትን እናስወግድ ዘንድ በብዙ ምሳሌ አስተምሮናል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ ታካቾችንና ታካችነትን ሲገስፅ “አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂት ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል (ምሳሌ 6:7-11)” እያለ ታካችነት ለድህነትና ለረሃብ እንደሚያጋልጥ በግልፅ ነግሮናል፡፡ ይኸው ጠቢብ ስለታካች እጅ ሲናገርም “የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች (ምሳሌ 12:24)” ይልና  “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል (ምሳሌ 10:4-5)” በማለት የታካችነትን አስከፊነት አጉልቶ ያስረዳል፡፡

ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጥበብ ድንቅ ምሳሌዎችን እየመሰለ ነገረ ሃይማኖትን ያስተማረው ይህ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለታካችነትና አስከፊነቱ ብዙ ተናግሯል፡፡ በተለይም ሥራን የማይወዱና በምኞት ብቻ የሚፈልጉትን የሚያገኙ ሰለሚመስላቸው ሰነፎች ሲናገር “ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና (ምሳሌ 21:25)” በማለት ታካችን ክፉ ምኞቱ እንደምትገድለው በመጽሐፈ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች (ምሳሌ 13:4)” በማለት ጠንክሮ መሥራትን ወደጎን በመተው ምኞታቸውን በአቋራጭ ለማግኘት የሚያስቡ ይህ ምኞታቸው እንደሚያጠፋቸው በማያወላዳ መልኩ አስረድቶናል፡፡በሌላም አገላለጽ ሥራን ለመሥራት የሚሰንፍ ሰውን ሲገስፅ “በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው (ምሳሌ 18:9-10)” በማለት ታካችነት ከሀብት አጥፊነት ተርታ እንደሚቆጠር በግልጽ አስተምሯል፡፡ ይህንንም ያለው ታካችነት በሥራ ለወደፊት ሊገኝ የሚችል ሀብትን ማምከን ስለሆነ ነው፡፡ አጥፊነት ደግሞ አሁን ያለውን ሀብት ማጥፋት ስለሆነ ሁለቱን ወንድማማች አድርጎ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡

ክርስቲያን በሥራ መትጋትን በምንም ሊተካው አይችልም፡፡ ምድራዊ ሀብትም ይሁን ሰማያዊ ጽድቅ በመትጋት እንጂ በመታከትና በመተኛት አይገኝም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፤ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ (ምሳሌ 14:23-24)” በማለት ልምላሜ (ትርፍ) በድካም (በመሥራት) እንጂ በከንፈር (በማውራት) እንደማይገኝ አስገንዝቦናል፡፡ በተጨማሪም “ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል። የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም (ምሳሌ 28: 19-20)” ብሎ መትጋትን ገንዘብ እንድናደርግ አስተምሮናል፡፡ እንቅልፍን መውደድም እንዲሁ ለድህነት እንደሚዳርግ ሲናገር “ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ (ምሳሌ 20:13)” ብሏል፡፡

በሥራችን እግዚአብሔርን እናስቀድም!

ሥራም ሆነ ለሥራ የሚያስፈልጉን ዕውቀትና ክህሎት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። የሰው ልጅ የሚሠራውን ሥራ በዕውቀቱና በጉልበቱ የሚያከናውነው ቢሆንም ዕውቀትን እና ጤነትን የሠጠውን እግዚአብሔርን በሥራው ሁሉ ሊያስቀድም ይገባል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት (ቊላ 3:17)” ብሏል። በተጨማሪም ክርስቲያን ሥራን ሲሠራ በትጋትና ያለ አንዳች ልግመት መሆን እንዳለበት ሲያስተምር “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት (ቆላ 3:23)” በማለት አስተምሯል። ጠቢቡ ሰሎሞንም ሥራችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ማከናወን እንዳለብን ሲነግረን “ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች (ምሳሌ 16:3)” ብሏል።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሌለበት የሰዎች ድካም ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሠራተኞች ድካምም ከንቱ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዚህ “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ (መዝ 127:1-2)” በማለት በሥራችን ሁሉ እግዚአብሔርን እንድናስቀድም በመዝሙሩ አስተምሮናል፡፡   ይህንንም ዘወትር በጸሎታችን እግዚአብሔርን “የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና (መዝ 90:17)” እያልን ልንለምንና ሥራችንም ሲከናወንልን ምስጋናን ልናቀርብ ይገባናል፡፡

ክርስትናን በሥራ እንመስክር!

ለሥራ ስንተጋ በሥራ ቦታ ሊኖረን የሚገባው መንፈሳዊነት (ክርስትና) በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሲሆን ይታያል። አንዳንዶችም ክርስትናን በሥራና በእውነት ከመግለፅ ይልቅ የማስመሰል ሕይወት ውስጥ በመግባት ራሳቸውንም ሌሎችንም ይጎዳሉ። ሃይማኖታዊ ግብ በሌላቸው ተቋማት ውስጥ ማንኛውም ዓይነት እምነት ያለው (እምነት የሌለውም ጭምር) በሙያው ሊሠራ ይችላል፡፡ እነዚህ ተቋማትም የሚመሩት በየራሳቸው የሥራ ቦታ መመሪያ ነው፡፡ በቅጥርም ሂደት ሰውን በእምነቱ ምክንያት ማግለልና አድልኦ መፈጸም እንደሌለባቸው ይታመናል፡፡ በሥራ ቦታም የየራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት ይኖራቸዋል፡፡ በመሠረታዊነት እነዚህ ተቋማት የእምነት መገለጫ (እምነትን መግለጫ) ቦታዎች ስላልሆኑ ሁሉም ሠራተኛ አለባበሱም ሆነ አነጋገሩ የየተቋማቱን ሥርዓትና መመሪያ ያከበረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እውነተኛ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ እምነቱን የሚገልጸው በመልካም ስነ-ምግባሩ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማትም በሥራ በመትጋት፣ የተቋሙን መመሪያ በማክበር፣ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር፣ ተቋሙ የቆመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚችለውን ሁሉ በማድረግና ለሌሎችም መልካም አርአያ በመሆን ነው ክርስትናውን የሚገልጠው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ያለው እንዲሁ ነው፡፡ ክርስትናችን የሚገለጠው በአስተሳሰባችን፣ በአነጋገራችንና በምግባራችን መልካምነት ሊሆን ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንዳንዶች ዘንድ ነጠላ ለብሶ ወደ መሥሪያ ቤት ወይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግባት መከልከሉ ትልቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ሲሆን አስተውለናል፡፡ መሥሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሴኩዩላር እስከሆኑ ድረስ የራሳቸው የአለባበስ ደንብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህም ለማንኛውም ወገን የማያዳላ፣ ማንንም የማያገልል ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን ወደጎን ትተን እኛ እምነታችንን የሚገልጽ ነገር እንልበስ የምንል ከሆነ መመሪያውን እንተላለፋለን፡፡ ይሁንና ብዙ ተቋማት አካታች ስለሆኑ እንደሁኔታው ለሠራተኞቻቸው የሚጸልዩበት ቦታና ሰዓት ሁሉ እስከመፍቀድ ሲደርሱ አስተውለናል፡፡ በተቋም ውስጥ ነጠላ መልበስ የሚከለከል ከሆነ አለመልበስ ይመረጣል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በሌሎች ተቋማት ውስጥ ነጠላ ልበሱ የሚል ትዕዛዝ የላትም፡፡ ሌሎች እምነትን የሚገልጡ ነገሮችንም ሴኪዩላር በሆኑ ተቋማት ውስጥ አጉልቶ ማሳየት እንዲሁ ተቋማቱን የሃይማኖታዊ ምልክቶች መፎካከሪያ ዐውድ በማድረግ ከቆሙለት ዓላማ ያዘናጋቸዋል፡፡ ይህንን በማድረግ ከምናተርፈው ይልቅ የምናጠፋው ይበልጣልና ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም፡፡ የሌላ እምነት ተከታዮች ይህንን ሲያደርጉ ብናይ ህግን እንጂ ህግ ተላላፊዎችን መከተል የለብንም፡፡

የማዕተብ ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ማዕተብ የሥላሴ ልጅነትን ስናገኝ የተሰጠን የክርስትናችን ምልክት ነው። በአንገታችን የምናስረው ስለሆነ ብዙውን ጊዜ በግልፅ ከሩቅ የሚታይ ምልክት አይደለም። ዓላማውም የእምነት (የጥምቀት) ምልክት እንጂ ለጌጥ፣ ለታይታ ወይም ለፉክክር የሚደረግ አይደለም። በሴኪዩላር ተቋማትም ቢሆን ከአብዛኛው የአለባበስ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው። ይልቁንም የተለያዩ ጌጣጌጦችን በአንገት ላይ ማሰር የተለመደ ነገር በሆነበት ዘመን በመመሪያውም ሆነ በአመራሩ ‘ማዕተብ አትሠሩ’ የሚል ተቋም ካለ ልንሞግተው ይገባል። በተጨማሪም የሌሎች እምነት ተከታዮች የሚመሯቸው ሴኪዩላር ተቋማት በእምነት ምክንያት በግልፅ አድሎና ማግለል የሚፈፀምበት ሁኔታ ሲያጋጥም ችግሩ በህግ አግባብ እንዲታይ ማድረግ ይኖርብናል። በራሳችን የክህሎትና የአፈፃጸም ማነስ ወይም በተቋማቱ ሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት ሳንቀጠር ስንቀር ወይም ተቋማቱን ስንለቅ ‘ማዕተብ በማድረጌ ነው’ ወይም ‘ኦርቶዶክስ ስለሆንኩ ነው’ ማለት ግን በምድራዊም በሰማያዊም ህግ ያስጠይቃል።

ማጠቃለያ

ሥራን በመሥራት የምናገኛቸው ብዙ ትሩፋቶች አሉ፡፡ ተግተን ስንሠራ ለራሳችን ሕይወት የሚያስፈልገንን ማሟላት እንችላለን፣ ለሌሎችም አንከብድባቸውም፡፡ በመሥራታችን ለማኅበረሰባችንና ለሀገራችን ዕድገትና ልማት የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን፡፡ ጠንክረን ስንሠራ አዕምሮአችን በሙሉ አቅሙ ሥራ ላይ ስከሚያተኩር ኃጢአትን ከምትወልድና ለሞት ከምታደርስ ክፉ ሀሳብ እንርቃለን፣ ኃጢአትንም አንሠራም፡፡ በሥራ ስንተጋ ከሥራችን በምናገኘው ገንዘብ፣ እውቀትና ልምድ ሌሎች ወገኖቻችንን መርዳት እንችላለን፣ ለእነርሱና ለቀጣዩ ትውልድም መልካም አርአያና ምሳሌ መሆን እንችላለን፡፡ በርትተን ስንሠራ ለቤተ ክርስቲያንም በገንዘብ፣ በዕውቀት/በልምድ፣ በምሳሌነት አለኝታ እንሆናታለን፡፡ የቀደሙት ቅዱሳንም ለመንፈሳዊውም ለምድራዊውም ሥራ በመትጋታቸው ነው ለሁላችንም አብነት ሆነው ያለፉት፡፡ በሥራ ከመትጋት ውጭ ለሰው ልጅ ሌላ የሚበጀው ነገር እንደሌለም ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

ስለዚህም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና አገልጋዮች የሚያምኑት እውነተኛ እምነት በሥራ የሚገለጥ መሆኑን በማስተዋል ለሥራ መትጋትን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታየውም “በአቋራጭ የመክበርን” አስተሳሰብ ከልባቸውና ከህሊናቸው ማራቅ አለባቸው። እውነተኛ እምነት ጭብጥ በሌለው ልፍለፋና በየቀኑ በሚቀያየር የፋሽን ልብስ፣ በሰው ዘንድ ልታይ ልታይ በማለት ሳይሆን በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ሀሳብና በፍጹም ልብ ውስጥ ተዋሕዶ በመንፈሳዊና በምድራዊ ሥራ የሚገለጥ ስለሆነ ለሥራ መትጋትን ሁሉም ገንዘብ ሊያደርገው ይገባል እንላለን፡፡

 

ክርስቲያናዊ አንድነትና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት

ምክንያተ ጽሕፈት

በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የውጭ ሀገር ከተሞች አብያተ ክርስቲያናት ከመንፈሳዊ ዐውድነት ባላነሰ (በአንዳንዶችም ዘንድ በበለጠ) መልኩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዐውድ እየሆኑ ሲሄዱ መታዘብ ችለናል። ከዚህም የተነሳ ፖለቲካዊ የአመለካከት ልዩነቶች መንፈሳዊውን አንድነት በእጅጉ ጎድተውታል። ይህ በአመዛኙ በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች ጎልቶ የሚታይ ችግር በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ካለው የፖለቲካ አሰላለፍ የተነሳ ያለ ከልካይ በሀገር ቤት ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶችም ላይ በብዛት መታየት ጀምሯል። በሩቅ እየታየ ይወገዝ የነበረው፣ በተደራጀ መንግስታዊ ጉልበትና የመንፈሳውያን አገልጋዮች ቅን ተጋድሎ ተገድቦ የቆየው መንፈሳዊውን ዐውድ የፖለቲካ ነጥብ ማወራረጃ የማድረግ ክፉ ልማድ በሙሉ ኃይሉ ቤተ ክርስቲያናችንን እየፈተናት እንዳለ እንረዳለን። ይሁንና የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ተረድቶ በቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በውጤት ተኮር አስተዋይነት (pragmatic perspective) ተገቢ መፍትሄ የሚያመላክት የቤተ ክርስቲያን አካል አይስተዋልም። የዚህ ችግር አንዱ መነሻ ክርስቲያናዊ አንድነትን በፖለቲካዊ የአመለካከት ልዩነት የሚገድብ አርቆ የማያይ ምልከታ መስፈኑ ነው።

በምድራችን ላይ ብዙ አይነት የፖለቲካ አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል። እያንዳንዱ ግለሰብም ይሻላል ብሎ የሚወስደውና የራሱ የሆነ ፓለቲካዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል። ተመሳሳይ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችም ይህንን አመለካከታቸውን ለማራመድ በፖለቲካ ፓርቲነት ሊደራጁ ይችላሉ። ይህም በፖለቲካው ዘርፍ የራሱ የሆነ ሕጋዊ አሠራር አለው። በአንፃሩ ቤተ ክርስቲያን በምድራዊ የፖለቲካ ርዕዮት የማትገደብ ሁሉም ከጥፋት ውኃ የሚድንባት መርከብ እንጂ የፖለቲካዊ ርዕዮት መታገያ ዐውድ አይደለችም። ይሁንና በቤተ ክርስቲያን የተለያየ ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው እና/ወይም በተለያዩ ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉና ለሕዝብና ለሀገር ይበጃል ብለው የሚያምኑበትን ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን የሚያራምዱ ሰዎች መኖራቸው የልዩነትና የክፍፍል ምንጭ ሲሆን ይታያል። በተለይም በዝርወት ዓለም (ዲያስፖራ) በአጥቢያ ደረጃ ሳይቀር የመንግስት (ወይም የተወሰነ ፖለቲካዊ ቡድን) ደጋፊና ተቃዋሚ ተብሎ መቧደን የተለመደ ሆኗል። የዚህም መነሻ የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችን በሚገባ ካለመረዳት ወይም የቤተ ክርስቲያንን መድረክ ለፖለቲካዊ ዓላማ ለመጠቀም ከማሰብ የሚመነጭ ነው። በዚህም የተነሳ የፖለቲካ አመላካከት ልዩነቶች ክርስቲያናዊ አንድነታችንን እየተፈታተኑት ይገኛሉ። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የዚህን ችግር መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳስሳለን፣ የመፍትሔ ሀሳቦችንም እንጠቁማለን።

ፖለቲካ ምንድን ነው? 

ከሁሉ አስቀድመን ፖለቲካ (ፖለቲከኛ መሆን) ሰው ሀገሩን እና ሕዝብን የሚያገለግልበት አንድ የሙያ/የሥራ ዘርፍ/ክህሎት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል እንላለን። ይህም ሲባል ልክ እንደ ሕክምና፣ ምህንድስና ወይም የመምህርነት ሙያ ፍላጎትን፣ የትምህርት ዝግጅትንና ልምድን የሚጠይቅ ነው ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያንም አስተምህሮ የፖለቲካው ዘርፍ እንደ አንድ የሙያ/የሥራ ዘርፍ/ክህሎት ሊታይ ይገባል እንጂ የተለየ የጽድቅም ሆነ የኩነኔ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አያስፈልገውም። ይህ ማኅበረሰቡ ውስጥም ሊሠርፅ የሚገባው አመለካከት ነው። ክርስቲያንም ፖለቲከኛ መሆንን በዚሁ አግባብ ሊመለከተው ይገባል። ፖለቲከኛ መሆንም የግለሰብ የሙያ ዘርፍ (career) እንጂ የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ ሊወሰድ አይገባውም። አንዳንድ አገልጋዮችም በፖለቲካ መሳተፋቸውና ለሥልጣን መብቃታቸው የተለየ የብቃት መለኪያ ወይም የመንፈሳዊ ልህቀት ከፍታ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፣ አለመሳተፋቸውም የተለጠጠ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም። የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ይህ አይደለምና። ነገር ግን ጥንት የነበረው የቤተ ክህነትና የቤተ መንግስት ቁርኝት የፈጠረው ዳራ (legacy)፣ እንዲሁም በሀገራችን ሰፍኖ የሚታየው የጥቅመኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ይህን አስተሳሰብ ሲፈታተነው ይታያል።

ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ምዕመን በእኩልነትና በነፃነት የሚገለገልበትንና የሚያገለግልበትን መንፈሳዊ ዐውድ መፍጠሩ ላይ ነው። ሌላው ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ የፖለቲካ (የመንግስት አስተዳደር) እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ግንኙነት ነው። በተለይም በሴኩላሪዝም አስተሳሰብ የመንግስት አስተዳደርና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በሕግ የተደነገገ ቢሆንም ሁለቱ ተቋማት በትብብር/ተናበው የሚሠሩባቸው ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። አንዳንድ መንግስት የሚሠራቸው ሥራዎችም በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያን የምትሠራቸው ሥራዎችም እንዲሁ። በዚህም የተነሳ ነው የፖለቲካና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አንድ መወያያ ርዕስ ሆኖ የሚመጣው። ይህ በግልፅና በሥርዓት የሚመራበትን ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀቱ በመንግስት በኩል የግለሰቦች፣ የፖለቲካዊ አመለካከት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ሲቀየሩ ችግር እንዳይፈጠር ይረዳል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት  

በአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ውዝግብ የሚያስነሳው የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ መታወቅ ያለበት ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አይኖራትም፣ ሊኖራትም አይገባም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም በተለይም ካህናት በአገልግሎታቸው ይህንን የፖለቲካ ገለልተኝነት (neutrality) ሊያንጸባርቁ ይገባል፡፡ አገልግሎታቸው የተለያየ ዓይነት ፖለቲካዊ አመላከከት ላላቸው ምዕመናን ነውና፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የየራሱ ፖለቲካዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህም ክርስትና የማይገድበው መብቱ ነው፡፡ ክርስቲያንም ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ወንጌልን ለመማር፣ ለመጸለይ፣ ለማስቀደስ፣ ለመባረክ ነው። እነዚህም ከፖለቲካዊ አመለካከት ጋር የማይጋጩ፣ የምድርን ሳይሆን የሰማይን መንግስት የሚሰብኩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን (ካህናትን ጨምሮ) በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት አንዱን የፖለቲካ አመለካከት ጽድቅ፤ ሌላውን ኩነኔ፤ አንዱን የፖለቲካ መሪ መልአክ፤ ሌላውን መሪ ሰይጣን አድርገው የሚያቀርቡ ከሆነ ድርጊቱ መንፈሳዊ ዓላማውን ከመሳቱም ባሻገር ምዕመናንን የሚከፋፍልና ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ይሆናል፡፡

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መንፈሳዊ አንጂ ፖለቲካዊ ስላልሆነ ከማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ጋር የማይጋጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዱን ፖለቲካዊ አመለካከት (ቡድን) ደግፋ ሌላውን አትኮንንም፡፡ ክርስቲያኖች ግን የየራሳቸው ፖለቲካዊ አመለካከት ሊኖራቸውና ይህንንም አመለካከታቸውን (ከቤተ ክርስቲያን ውጭና የቤተ ክርስቲያንን ስም ሳይጠቀሙ) ከማራመድ የሚከለክላቸው ነገር የለም፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው በቤተ ክርስቲያን የተለየ ክብር ሊሰጣቸው ወይም የተለየ መገለል ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ ፖለቲከኛም የቤተ ክርስቲያን አባል ስለሆነ የተለየ ነገር ለቤተ ክርስቲያን እንዲያደርግ ሊጠበቅበት አይገባም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በእምነት ስም ፖለቲካን ማራመድም ሆነ በፖለቲካ ስም እምነትን ለማራመድ መሞከር ቤተ ክርስቲያንን ሲጎዳት እንጂ ሲጠቅማት አላየንም።

ቤተ ክርስቲያንና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት

የክርስትና አስተምህሮ ለብዙ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶች መሠረት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። በዘመናችን ያለውም የክርስትና አስተምህሮም በዚህ ዘመን ያሉትና ወደፊት የሚኖሩትን ፖለቲካዊ አመለካከቶች በእውነት፣ በእኩልነትና በፍትህ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል። በተጨማሪም በሕዝብ ዘንድ ሊኖር ስለሚገባው የመልካም አስተዳደር ሥርዓትም መሪዎችን የሚያስገኘውን የሕዝብ አመለካከትና ባህል በመቅረፅ ዘንድ ታላቅ ድርሻ አለው። በተቃራኒም የመልካም አስተዳደር እጦት መገለጫዎች የሆኑት ሙስናና የሰብአዊ መብት ረገጣዎች የክርስትና አስተምህሮ ሥር ያለመስደድ ምልክቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮ ፖለቲካዊ አመለካከቶችን የማቃናት ሚና ይኖረዋል ሲባል ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በሌለበት ዐውድ ልዕልና ያለውን ሀሳብ ከመቅረፅና የማኅበረሰቡ እሴት ከማድረግ ረገድ መሆኑን ማስተዋል ይገባል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍለው አገልጋዮች (በተለይም ካህናትና ሰባክያን) የፖለቲካ አመለካከታቸውን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ወይም በቤተ ክርስቲያን ስም ማንጸባረቅ ሲጀምሩ ነው፡፡ በተለይም የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ በሚል ጎራ አንዳንድ አገልጋዮች የፖለቲካ መሪዎችን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሲያወድሱ ወይም ሲኮንኑ ቤተ ክርስቲያንን እየከፋፈሉ እንደሆነ አይረዱትም፡፡ አንዳንዶችም መንግስትን ሲያሞግሱ፣ ሌሎችም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አጀንዳ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትና በቤተ ክርስቲያን ስም ሲያራምዱ ያን ጊዜ በምዕመናን መካከል መለያየት ይፈጠራል፣ የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያንም በምድራዊ ልዩነት ትከፋፈላለች፡፡ ነገር ግን አገልጋዮች ወገንተኝነታቸውን ለክርስቶስ ብቻ አድርገው ቢያገለግሉ መከፋፈል አይኖርም፡፡ መከፋፈል የሚመጣው ቤተ ክርስቲያንን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል ሲታሰብ/ሲጀመር ነው፡፡

እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ውስጡን አንድ አይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችን በቁልፍ ቦታዎች በማስቀመጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሽጎ በሃይማኖት ስም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት በመጠቀም ፖለቲካዊ አመለካከትን ለማስፋፋት መሞከር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ምዕመናን ተስፋ በመቁረጥ ቤተ ክርስቲያንን በጥቅሉ እንዲጠሏትና በብዛት እየለቀቁ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ አቤት የሚባልበት አካል ራሱ የችግሩ ምንጭ ከሆነ ደግሞ ለእግዚአብሔር ካልሆነ ለማን አቤት ይባላል?! እነዚህ አካላት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ምልክቶች ሳይቀር የቤተ ክርስቲያን በማስመሰል ምዕመናንን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ሲመለምሉ ማየት ያሳፍራል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን የንትርክ መድረክ ያደርጋታል፡፡ ሁላችንም ቤተ ክርስቲያንን ለተቋቋመችበት ዓላማ ብቻ ብንጠቀምና የማኅበራዊ ማንነታችንን ጓዝ ማስፋፊያ ባናደርጋት ክርስቲያናዊ አንድነታችን ይጠናከራል፡፡

ሃይማኖትንና ፖለቲካን መቀላቀል
ማሳያ ምሳሌ

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆነና “የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት” የተባለ ፖለቲካዊ ተቋምን የሚመራ ታዋቂ ሰው በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ይዘዋወር ነበር። ይህ ሰው የያዘው ዓላማ በፖለቲካዊ መነፅር ሊወደስም ሆነ ሊነቀፍ ይችላል። መንግስታዊ ስልጣንን ራሳቸውን “ባላባት” ብለው ለሚጠሩ ሰዎች ብቻ በዘር የማስተላለፍ ርዕዮት ደጋፊዎች ያሉትን ያህል በጥብቅ የሚኮንኑትም አሉ። ይሁንና ይህን አስተሳሰብ ለማስረፅ የሚንቀሳቀስ ተቋምና ግለሰብ እንደ ምዕመን ሳይሆን እንደ ልዩ መልእክተኛና ባለስልጣን በውጭ ሀገራት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ሲጎበኝ ካህናትና ምዕመናንም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሲያጎበድዱለት አስተውለናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ  ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ፓለቲካና ሃይማኖትን የመቀላቀልን ችግር ያሳያል ብለን እናስባለን። “ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ለዚህ ግለሰብና ለሚወክለው ፖለቲካዊ ርዕዮት ያጎበደዱ ካህናትና ምዕመናን ለሌሎች መሰል ፖለቲከኞች፣ ለልጅ ልጆቻቸውና ለሚወክሉት ፖለቲካዊ ርዕዮት በተመሳሳይ መልኩ ያጎበድዳሉ?” መልሱ “አዎ” በሚሆንባቸው ቦታዎች ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሸቀጥ ማራገፊያ ትሆናለች። መልሱ “አይደለም” በሚሆንባቸው ቦታዎች (በእኛ ግምት በአብዛኞቹ ቦታዎች) ደግሞ ከሚጎበደድለት ፖለቲካ የተለየ ርዕዮት ያላቸው ሰዎች “አሃ ይሄ ቦታ የእነ እገሌ ነው” ብለው እንዲገፉ ያደርጋቸዋል። ከመንፈሳዊ አስተሳሰብ ይልቅ ያልቦካ የፖለቲካ ሊጥ ይዘው ምዕመናንን ከቤተ ክርስቲያን የሚያርቁ ሞኞች በበዙበት ዘመን ይህ ሃይማኖትና ፖለቲካን የመቀላቀል አይሁዳዊ ልማድ የሚያመጣው መዘዝ ብዙ ነው።

ፖለቲካና ሃይማኖትን መለየት የሚጀመረው በመጀመሪያ በአእምሮ ውስጥ (ይህ ሀሳብ ሃይማኖታዊ ነው፣ ያ ደግሞ ፖለቲካ ነው ብሎ በማስተዋል) ሊሆን ይገባል። ቀጥሎም ሃይማኖትና ፖለቲካ መለየት ያለባቸው በንግግር (በጽሑፍ) ነው። ይህም ሁለቱን ለይቶ በመናገር ወይም በመጻፍ ነው። ሦስተኛም ሃይማኖትና ፖለቲካ የሚለዩት በተሳትፎ ነው። ይህም አቻችሎ በመሳተፍ ሊሆን ይችላል። ሌላውና ዋናው መለያቸው የዓላማ፣ አስተምህሮ፣ የሥርዓትና ተቋማዊ አወቃቀራቸው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን እና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ዙሪያ የሚስተዋለው ችግር በክርስትና ልብስ/ሽፋን ወይም ስም የተወሰነ ፖለቲካዊ አመለካከትን ለማራመድ መሞከር ነው። ይህም በተለይ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን የሚያንጸባርቁ ወይም ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የቆሙ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህን እና ሰባኪ ወይም የማኅበረሰብ አንቂ (activist) የሆኑ ሰዎች ሲያደርጉት የሚታይ ነው። እነዚህ ግለሰቦች በግልፅ የሚታወቁት በቤተ ክርስቲያን ሰውነታቸው (ማዕረጋቸው) ወይም የመንፈሳውያን ማኅበራት አባልነታቸው ቢሆንም በስብከታቸውና በጽሑፎቻቸው ግን በሃይማኖት የተጠቀለለ ፖለቲካዊ አመለካከትን ወይም ለሌላው ወገን ያላቸውን የጥላቻና የንቀት ጥግ ሲያራምዱ ይስተዋላሉ። ይህ ዓይነቱ ጎራውን ያልለየ በእምነት ስምና ሽፋን የሚደረግና የትም የማያደርስ ሩጫ ክፋትንና ልዩነትን ከማስፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።

በአንድ ወቅት በቤተ ክርስቲያን በሰባኪነታቸው የሚታወቁ ግለሰቦች በፖለቲካ መሳተፍ ሲጀምሩ ስብከቱንና ፖለቲካዊ ሥራቸውን ለይተው ለማራመድ ሲቸገሩ እናያለን። ፖለቲካው ስብከት፣ ስብከቱም ፖለቲካ ይሆንባቸዋል። ፖለቲካ ሃይማኖትን የማይለይ (ሁሉንም ሃይማኖት በእኩልነት ማየትን የሚጠይቅ)፣ ስብከት ደግሞ ፖለቲካዊ አመለካከትን የማይለይ (ሁሉንም ፖለቲካዊ አመለካከቶች በእኩልነት የሚያይ) መሆኑን ይዘነጉታል። እንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች አንዱን አጥብቀው ቢይዙና ሌላውን ለሌላው ቢተዉ ሕዝብን ከማወዛገብ፣ ቤተ ክርስቲያንንም ከማስወቀስ ይድናሉ። በመንፈሳዊ አገልግሎት ያገኙትን ተሰሚነት ለፖለቲካ ዓላማ የተጠቀሙ ተብለው ከመወቀስም ይድናሉ። ምናልባት በሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ያሉ ግለሰቦች ሁለቱን እያጣቀሱ መሄዳቸው እንደ መከራከሪያ የሚቀርብ ከሆነ ‘ሁለት ስህተት አንድ እውነት አይሆንም’ እንላለን። ምዕመናንንም ቢሆኑ ፖለቲከኛንና መንፈሳዊ አገልጋይን ለይተው ሁሉንም በሚገባው ሚዛን ሊመዝኑ ይገባል እንጂ አንድን ግለሰብ ‘ጥሩ ሰባኪ’ ስለነበር/ስለሆነ ጥሩ ፖለቲከኛም ይሆናል ከሚል ድምዳሜ ራሳቸውን ማራቅ ይገባቸዋል።

የመፍትሔ ሀሳቦች
ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባርን ማስተማር

በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነቶች ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠረውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን በሚገባ ማስተማር ሊቀድም ይገባዋል። ይህም ሰው የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችን እንዲያውቅና የሰዎችን የተለያየ አስተሳሰብና አመለካከትም እንዲያከብር ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ መሆኑን በሚገባ በማሳወቅ ሰዎች በፍላጎታቸውና በክህሎታቸው በድብቅ (በሃይማኖት ስም) ሳይሆን በግልፅ በአደባባይ፣ በፍርሃትና በመሸማቀቅ ሳይሆን በልበ ሙሉነት፣ በሃይማኖት ተከልለው ሳይሆን ራሳቸውን ሆነውና ራሳቸውን ችለው እንዲያራምዱ ማኅበረሰቡ ሊያበረታታቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ለእምነቱም ለፖለቲካውም ይበጃል።

ግለሰብንና ተቋምን መለየት

ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንፃርም የግለሰብና የተቋምን (የቤተ ክርስቲያንን) አቋም ለይቶ የሚያይ አገልጋይና ምዕመን መፍጠር ያስፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የሚቆሙ አገልጋዮች የራሳቸውን አመለካከት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሊሰብኩ ይገባል። የራሳቸውን አመለካከትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚቀላቅሉ ከሆነ ምዕመናንን ይጎዳሉ። የግለሰቦች ፖለቲካዊ አመለካከት የየራሳቸው እንጂ የቤተ ክርስቲያን አይደለምና። ምዕመናንም ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት በክርስትናቸው እንጂ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የሰባኪን ፖለቲካዊ ትንታኔ ሊሰማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ ምዕመን የለም፣ ካለም የክርስትናን አስተምህሮ ያልተረዳ ነው። ቤተ ክርስቲያንም የክርስቲያኖች አንድነት/ኅብረት እንጂ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ኅብረት አይደለችም።

የአገልግሎት መመሪያመተግበር

ከመንፈሳዊ አገልግሎት አንፃርም የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ (code of conduct) ማዘጋጀትና ትግበራውንም ማጠናከር ይገባል። ይህም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መንፈሳዊ አገልግሎትን እና የራሳቸውን ፖለቲካዊ አመለካከት ለይተው በመንፈሳዊው ዐውድ መንፈሳዊ መልእክትን ብቻ እንዲያስተላልፉ ይረዳል። ከሥርዓት ሲወጡም እንዲታረሙ ያደርጋል። በተለይ ካህናት ሁሉንም ያለ ልዩነት በእኩልነት እንዲያገለግሉ ያደርጋል። ከዚህ ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እንደሌላት ማረጋገጥና በቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ አዝማሚያ ሲታይ ቶሎ መከላከልና የእርምት እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል። ይህም በምዕመናን መካከል በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተነሳ መከፋፈል እንዳይፈጠር ይረዳል። ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሳይቀር የራሳቸውን ፖለቲካዊ አመለካከት ሲስብኩ ዝም ማለት ግን መንፈሳዊውን ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊ ረብ ለሌለው አላፊና ጠፊ የሰዎች ፍልስፍና ማስፋፊያነት መፍቀድ ነው።

ትርክትንና አስተምህሮን መለየት

በስተመጨረሻም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሱ የሐሰት ትርክቶችም ሆኑ የቀድሞ መሪዎችና የግለሰቦች ድርጊቶች (ያራምዱት የነበረው የፖለቲካዊ አመራር ዘዴዎች) ቤተ ክርስቲያንን እንደማይወክሉ በግልፅ ማሳወቅ ይገባል። የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮንና የተለያዩ ግለሰቦችና ጸሐፍያን በተለያዩ ዘመናት የጻፏቸውን መጻሕፍትና የተናገሯቸውን ንግግሮች ለይቶ ማየት ይገባል። በዚህም የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር እየሰጠን ሁሉንም በአግባቡና በተሠራለት ሥርዓት መሠረት እየፈጸምን በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተነሳ ክርስቲያናዊ አንድነታችን ሳይፈተን ጸንተን ልንቆም ይገባል።

ማጠቃለያ

የክርስትና አስተምህሮና የፖለቲካ አመለካከት ፍጭትና ግጭት ከጥንት ጀምሮ የነበረና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አንዱ አካል ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እንኳን ብንመለከት ንጉሥ ሄሮድስ ጌታችንን ማሳደዱ፣ ሌላው ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ማስገደሉ፣ አይሁድ ጌታችንን ከቄሳር ጋር ለማጋጨት ያደረጓቸው ሙከራዎች፣ በመጨረሻም ጌታችን በጲላጦስ ፊት መቅረቡንና ለመስቀል ተላልፎ መሰጠቱ ልዩ መገለጫዎች ናቸው። ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ሰማዕታትና ሊቃውንትም በየዘመኑ በነበሩት ነገሥታት መከራን መቀበላቸው የዚሁ አካል ነው። እነርሱ የተፈተኑት ለእውነተኛይቱ እምነት ብቻ ሲሉ መሆኑ ግን ሊሠመርበት ይገባል። ይህ በክርስትና ላይ የሚደርሰው እንዲህ ዓይነት ፈተናም መልኩንና ይዘቱን እየቀያየረ የሚቀጥል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በዘመናችን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችና ፖለቲካዊ ድርጅቶች አሉ። የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ይበጀናል ያሉትን ፖለቲካዊ አመለካከት ሊደግፉ፣ አይበጀንም ያሉት ላይም አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። ፖለቲካም አንድ የሙያ ዘርፍ እስከሆነ ድረስ በግልም በቡድን ተሳትፈውበት ለሀገርና ለሕዝብ የራሳቸውን ድርሻ ማበርከት ይችላሉ፣ ይገባቸዋልም። ይሁንና ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም የሁሉም ስለሆነች ለፖለቲካዊ አመለካከትም ይሁን ድርጅት ወገንተኝነት የላትም። የክርስትና አስተምህሮም ሁሉንም ፖለቲካዊ አመለካከቶች በአንድ መነጽር የሚመለከት እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን የሚሰብክ ነው። የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት አንድነት ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ክርስቲያኖች ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙበት ሰገነት ነው። በቅዱሳን ጸሎት የከበረው ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊው ጸሎትና ትምህርት ብቻ ሊከናወንበት ይገባል። ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በተገቢ ቦታቸው ሊፈጸሙ ይገባል። ነገሮችን ያለ ዐውዳቸው በመጥቀስ፣ በማጣቀስና በማምታታት በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች መካከል ያለ የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ሊፈትነው አይገባም፣ ለዚህም ሁሉም በእውቀት፣ በማስተዋልና ለሌላው በማሰብ የተመላ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል እንላለን።

 

በየቋንቋው ማ(መ)ገልገል: ሐዋርያዊነትን ከብሔርተኝነት እንለይ!

ምክንያተ ጽሕፈት

በዓለማችን ላይ ብዙ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ቅዱስ ወንጌል ለሁሉም ይዳረስ ዘንድ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ሐዋርያትን አሰረ ፍኖት በመከተል ሰዎች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች ሁሉ ስታስተምር ኖራለች፣ አሁንም እያስተማረች ትገኛለች። ይህም በሐዋርያት ዘመን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው ልሳናት (ቋንቋዎች) የተፈጸመ ሲሆን በዘመናችን ደግሞ የየቋንቋውን ተናጋሪ ካህናትና አገልጋዮችን በማፍራት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችም ተጨማሪ ቋንቋን ተምረው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሊፈጸም ይችላል። ይሁንና በተለያየ ቋንቋ የማስተማር ነገር በሰፊው ሊሠራበት የሚገባ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ወገኖች ይህ አካሄድ “ብሔርተኝነትን በማስፋት ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፍላል” የሚል ስጋት አላቸው።

በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቋንቋ አገልግሎት መስጠቷ “የሌላ ብሔርን ባሕል በማስፋፋት የባሕል ወረራ እያደረሰችብን ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ። ለእነዚህ የተቃረኑ አመለካከቶች ምንጭ ከሆኑት ነገሮች ዋነኞቹ ብሔርና ብሔርተኝነት በሚባሉት አስተሳሰቦች ላይ ያለ አለመግባባትና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለፖለቲካዊ ዓላማ ለማስገዛት የሚደረግ እሽቅድምድም ናቸው ብለን እናምናለን። ስለሆነም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የየብሔሩን (የየሀገሩን) ቋንቋ በጸጋ የገለጠበትን በዓለ ጰራቅሊጦስን በምናከብርበት ሳምንት፣ በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ በየብሔሩ ቋንቋ ማስተማር/ማገልገልና ብሔርተኝነት ያላቸውን ልዩነት እንዳስሳለን።

‘ብሔር’ ምንድን ነው?

‘ብሔር’ የሚለው ቃል ‘ዓለም’ የሚለውን ትርጉም ሊይዝ ይችላል። ይህም እግዚአ-ብሔር የሚለው ቃል ‘የዓለም ጌታ’ ተብሎ በመተርጎሙ ይታወቃል። ‘ብሔረ ሕያዋን’ እና ‘ብሔረ ብፁዓን’ በመባል የሚታወቁት የስውራን ቅዱሳን መኖሪያ የሆኑት የዓለመ መሬት ክፍሎች ስያሜም ይህንኑ የሚያስረዳ ነው። ብሔር ‘ሀገር’ ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል። ‘አይቴ ብሔራ ለጥበብ’ የሚለውን ‘የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው?’ እንዲል። እንዲሁም የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባሕል፣ የሕዝብ አሰፋፈርና ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶች ያለው ወገን/ማኅበረሰብ ‘ብሔር (Ethnic group)’ ይባላል። ከኖኅ ልጆች ጀምሮ፣ በባቢሎን ቋንቋ መደበላለቁን ይዞ፣ አሥራ ሁለቱን ነገደ እሥራኤል ጨምሮ፣ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ብዙ ልሳናትን መግለጡን ስንገነዘብ የብሔር ምንነትና ልዩነት መኖሩን ማንም ሊክደው የማይችልና በምድር ላይ የሚታይ ሐቅ መሆኑን እንረዳለን።

ብሔር የሚለው ቃል ለአንዳንዱ ሀገር ማለት ሲሆን፣ ለሌላው በቋንቋና በባሕል የተሳሰረ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሀገራት ውስጥ የሚኖር (የግድ ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ ድንበር ሊኖረው ይገባል የማይባል) የኅብረተሰብ ክፍል ማለት ነው። ብሔር ከሀገር ጋር የሚመሳሰልባቸው ሀገራት ያሉትን ያህል በሀገራት ውስጥ የየራሳቸው (ተወራራሽ) ባሕል፣ ቋንቋና ልዩ ልዩ ማኅበረሰባዊ አንድነቶች ያሏቸው ሕዝቦች በብዙ ሀገራት አሉ። “ብሔር የፖለቲካ ድንበርን መወሰን አለበት ወይስ የለበትም?” በሚለው ሀሳብ ላይ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት እንዳለ ይታወቃል። ይሁንና በቋንቋና በባሕል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየሀገራቱ አሉ። እነዚህ ብሔሮችም የሚያመሳስሏቸው መገለጫዎች እንዳሏቸው ሁሉ፣ የሚለያዩአቸው መገለጫዎችም አሉ።

ከዚህም የተነሳ ለየራሳቸው መጠሪያና መገለጫ ያላቸው፣ በዘመናት ሂደት የዳበረ ተመሳሳይ ቋንቋና ባሕል የሚያንፀባርቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ብሔር” ሊባሉ ይችላሉ፣ በተግባርም ይባላሉ። ብሔር የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ “ብሔር” የሚለውን ቃል “ብሔረሰብ” ከሚለው ተመሳሳይ ቃል ጋር በተለዋጭነት እንጠቀማለን። አንድ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን እየተማረ እንደሚያድገው ሁሉ በማኅበረሰቡ ውስጥም ቋንቋን ባሕልንና የተለያዩ የማኅበረሰቡ መገለጫ የሚሆኑ እሴቶችን እየተማረ ያድጋል፡፡ በዚህም ሰው ካደገበት ማኅበረሰብ ወይም ከትውልድ ሐረጉ የተነሳ የራሱ ‘ብሔር (ባሕልና ቋንቋ) ይኖረዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ብዙ የብሔር ስም ተጠቅሷል። ክርስቲያንም እንዲሁ የማኅበረሰቡ አካል ስለሆነ የራሱ ‘ብሔር’ ይኖረዋል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት!

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ይህም ማለት “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ ታንጻችኋል (ኤፌ 2:20)” እንደተባለ የሐዋርያትን አስተምህሮና ትውፊት የምትከተል፣ ሐዋርያት ባስተማሩበት መንገድ በተለያየ ቋንቋ ወንጌልን የምትሰብክ፣ ከሐዋርያት ቀጥታ የመጣ የሢመት ሐረግ ያላት ናት ማለት ነው፡፡ አገልጋዮችም እንዲሁ አገልግሎትን የሚፈጽሙት የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለው ስለሆነ አገልግሎታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ይባላል፡፡ ሐዋርያዊነት የምንለውም ለዚህ ዓላማ መታመንንና መቆምን ነው፡፡ የሐዋርያነት ዋናው ተግባርም ለሁሉም ሰው በሚናገረው ቋንቋ የክርስቶስ ወንጌልን መስበክ ነው፡፡

በማኅበራዊና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን በየብሔረሰቡ ቋንቋ ማስተማር እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው የሚተከሉ አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተቋማት የየአካባቢውን ማኅበረሰብ ቋንቋ የሚጠቀሙና የየማኅበረሰቡን የአኗኗር ባህል የዋጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን ወንጌል በሕዝቡ ቋንቋ ይሰበክ ማለት ነው እንጂ በቋንቋ በመ(ማ)ግልገል ሽፋን ከወንጌል ይልቅ ብሔርተኝነት ይሰበክ ማለት አይደለም፡፡ የተለያየ የብሔረሰብ ስብጥር ባለባቸው አካባቢዎችም አብዛኛው ማኅበረሰብ በሚረዳው ቋንቋ እያገለገሉ ቋንቋውን ለማይናገሩ ሰዎች ደግሞ የተለየ መርኃግብር ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቋንቋ ብቻ አገልግሎት ትስጥ የሚል በሀሳብም ሆነ በተግባር የሚገለጥ አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በእጅጉ የሚገድብ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህን አስተሳሰብ መያዛቸውን ሳያውቁ፣ ሌሎች ደግሞ በፖለቲካዊ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን በየቋንቋው የማስተማር ተልዕኮ ይቃወማሉ ወይም ለሚፈልጉት ፖለቲካዊ ዓላማ ግብዓት በሚሆን መልኩ “ከአንድ ቦታ እየተቆረሰ የሚሰጥ ምጽዋት” ያስመስሉታል።

ቤተ ክርስቲያን በየማኅበረሰቡ ቋንቋ ልታስተምር ይገባል ሲባል በመዋቅር፣ በመመሪያ እና በዕቅድ በተደገፈና ወጥነት ባለው መልኩ እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንደምናየው የተወሰኑ ሰባክያን በሚዲያ ብቅ እያሉ በተለያየ ቋንቋ ስለሰበኩ ብቻ ወይም የተወሰኑ መምህራን አንዳንድ መጻሕፍትን በተለያየ ቋንቋ ስላሳተሙ ብቻ ቤተ ክርስቲያን በተሟላ ተቋማዊ አቅም ምዕመናንን በየቋንቋቸው እያስተማረች ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ዓለማዊ መንግሥታት እንኳን ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና በየቋንቋዉ አገልግሎት እንዲያገኝ ባደረጉበት በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በቋንቋቸው ለማገልገል ሳትችል ስትቀር ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ የሆነው የተለያየውን ቋንቋ የሚናገር አገልጋይ ጠፍቶ ሳይሆን በአስተዳደር ብልሽትና በዘረኝነት መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ገና ብዙ መሥራት እንደሚቀረን ያመለክታል፡፡ ከዚህም አልፎ በአንድ ቋንቋ መገልገልን (ማገልገልን) የመንፈሳዊ አንድነት ማሳያ በማስመሰል ምድራዊ ፍላጎታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሯሯጡትን ማየትም ያሳፍራል።  

የቋንቋ መለያየት ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍላት አድርጎ ማሰብም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይልቁንስ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍላት አንድ ቋንቋ ብቻ ለመጠቀም መሞከር ነው፡፡ አንድ ዓይነት ምድራዊ አስተሳሰብና ቋንቋ በቤተ ክርስቲያንን የበላይ ለመሆን ሲሞክር፣ ሌላው ደግሞ ‘በሥርዓት እንመራ’ በማለቱ ሲገለል ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆኗ ይዘነጋና መከፋፈል ይፈጠራል፡፡ በተለይም የብሔር ብዙኅነት ባለበት ሀገር ሁሉም በቋንቋው መገልገል ይፈልጋል፣ ይገባዋልም፡፡ ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እየፈለጉ ይህንን የማይፈጽም አስተዳደር ሲኖር ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ባይተዋርነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፣ ያልጸኑትም እየተው ይሄዳሉ፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ ለእነርሱ ተደራሽ አይደለምና፡፡

በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ቋንቋ በላይ ለመንፈሳዊ አገልግሎት መጠቀም የሚያመጣው ችግር የለም፡፡ በተለያዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተለያየ ቋንቋ ማገልገልም እንዲሁ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ተደራሽነት ያሰፋዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አይከፋፍልም፡፡ ለምሳሌ በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ አጥቢያ በሁለት መቅደስ በተለያየ ቋንቋ ይቀደሳል፡፡ በሁለት አጥቢያም በአንድ ጊዜ በተለያየ ቋንቋ ይቀደሳል፡፡ ምዕመናንም የተሻለ በሚሰሙት ቋንቋ የሚቀደሰው ጋር ሄደው ያስቀድሳሉ፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሰንበት ትምህርት ቤትም እንዲሁ ነው። ይህ ቤተ ክርስቲያኗን አጠናክራት እንጂ አልከፋፈላትም፡፡ በሌሎችም አኃት አብያተ ክርስቲያናት ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሐዋርያዊነት በእኛም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሊለመድ ይገባዋል፡፡

ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ርዕዮት ነው!

‘ብሔርተኝነት (nationalism)’ በቀጥታ ትርጉሙ ለአንድ ሀገር/ብሔር መብት መከበር መታገል፣ ለብሔር/ለዜጎች እኩልነትንና ራስን በራስ ለማስተዳደር ይችሉ ዘንድ (የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆኑ) የብሔረሰቡን አባላት በማደራጀት አብሮ መሥራት ነው። በዚህ ትርጉሙም ለብሔረሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልፅግና መቆምን ያመለክታል። ብሔርተኝነት በተለይም አንድ ሀገር/ብሔር ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲጋረጡበት ተደራጅቶ ችግሮችን የሚፈታበትና በቀጣይም ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥበት ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም (Political ideology) ነው። በጥቅሉ ብሔርተኝነት ለአንድ ብሔር/ሀገር በታማኝነት መቆምን ያመለክታል፣ አጠቃላይ ዓላማውም ምድራዊ ነው።

ከፖለቲካ ሳይንስ አንጻር ሁለት አይነት ብሔርተኝነት አለ ማለት ይቻላል። እነዚህም ሀገርን፣ ዜግነትን ወይም ሕገ መንግስትን መሠረት ያደረገ “ሀገራዊ ብሔርተኝነት” (Civic nationalism) እና ቋንቋን፣ ባሕልን እና የሕዝብ አሠፋፈርን መሠረት ያደረገ “ብሔር-ተኮር ብሔርተኝነት” (Ethnic nationalism) ናቸው። ምንም እንኳ “ከዶሮና ከእንቁላል ማን ይቀድማል?” እንደሚለው ውል አልባ አመለካከት ለመበየን የሚያስቸግር ቢሆንም በግርድፉ ስንመለከተው የመጀመሪያው ሀገርን የሚያስቀድም ሲሆን ሁለተኛው ብሔርን የሚያስቀድም ነው ሊባል ይችላል። የብሔርተኝነትንም ሆነ ሌላ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ጥቅሙንና ጉዳቱን አመዛዝኖና ተንትኖ ለመከተል ወይም ላለመከተል መወሰን የፖለቲካ መሪዎችና የሚመሩት ማኅበረሰብ ድርሻ ነው፡፡

በመሠረታዊ አስተሳሰቡ ብሔርተኝነት ከብዙ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች አንዱ ነው። በቅርብ ጊዜ የጽሁፍ ታሪክ ምንጭነት ከተመለከትነው ብሔርተኝነት እንደ ፖለቲካዊ ርዕዮት የተጀመረው በአውሮፓ ሲሆን ኋላ ወደ አፍሪካና ኤስያ ሀገራት ተሰራጭቷል። ማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የራሱ በጎና ደካማ ጎኖች እንዳለው ሁሉ ብሔርተኝነትም የራሱ የሆኑ በጎና ደካማ ጎኖች አሉት። በተለይም በአንድ ብሔርና በሌላው መካከል ለባህል፣ ለስልጣን ወይም ለሀብት ፉክክር ባለበት ሀገር የአንዱ ብሔር መጠናከር በሌላው ዘንድ በመልካም ላይታይ ይችላል። በተጨማሪም አንዱ የራሱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ሌላውን ሊጎዳ ይችላል። በዚህም የተነሳ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ክርስትና ምድራዊ ‘ብሔር’ የለውም፣ ራሱን የቻለ ምድራዊ ‘ብሔርም’ አይደለም። ቤተ ክርስቲያንም ለሁሉም ብሔረሰብ በእኩልነት መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጥ መንፈሳዊት ተቋም ናት፡፡ ከዚህም የተነሳ የክርስትና አስተምህሮ ሁለቱንም የብሔርተኝነትን ርዕዮቶች እንደ ማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሊመለከታቸው ይገባል። የክርስትና አስተምህሮ መሠረታዊ ዓላማው መንፈሳዊ/ሰማያዊ ስለሆነ አንዱን ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የሚደግፍበት ሌላውን ደግሞ የሚቃወምበት አግባብ የለም። ይህ የመንግስት አስተዳደር እና የሚመሩት ሕዝብ ምርጫ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት አይደለምና። ይሁንና በማንኛውም ርዕዮተ ዓለም ተፈጥሮአዊ ጠባይም ይሁን በአፈፃፀም ችግር ምክንያት በሰው ልጆች ላይ በደል ሲደርስ ቤተ ክርስቲያን በደልን በቸልታ ማለፍ የለባትም። የዚህም ዋና ዓላማው የመንግሥትን ሥርዓት (ርዕዮተ ዓለም) ለማስቀየር ሳይሆን በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ችግር እንዲቆምና የተበደለው እንዲካስ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

‘ኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት’

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ፈተና እንደ ምክንያት በመጠቀም “ኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት” የሚል ሀሳብን ሲያነሱ አስተውለናል። በመሠረታዊ ባሕርይው ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ርዕዮት እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ደግሞ ሰማያዊት ስለሆነች ምድራዊ የሆነው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሊደረትባት አይገባም። በአጭር አገላለጽ ፖለቲካዊ ርዕዮት ለክርስትና አይስማማም። የብሔርተኝነት ግብ የአንድ ‘ብሔርን’ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በማረጋገጥ ራሱን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በግልጽ በብሔር የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ ነው። ከዚህ አንፃር የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለማንቀሳቀስ ማሰብም በሃይማኖት ካባ ፖለቲካን ማራመድ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት ዋናው መነሻ ሀሳቡ የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከብር ከሆነ የሀገሪቷን ሕግ በመጠቀም ማስከበር ይገባል። ይህ የማያሰራ ከሆነ በጠራ አስተሳሰብ በግልም ይሁን በቡድን ለሁሉም ሰው ፍትህን ሊሰጥ የሚችል ፖለቲካዊ ፕሮግራም ያለው ፓርቲን በመፍጠር፣ በመደገፍ፣ ገብቶ በመሳተፍ መምረጥና/መመረጥ ይገባል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ተጠግቶ ፖለቲካዊ ርዕዮትን መጎተት ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳታል፣ አንዳችም አይጠቅማትም። ስንዱ እመቤት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንስ ምን ጎድሎባት ነው የብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ፍልስፍናን የምትዋሰው? በምድራዊ የብሔርተኝነት ቁርቁስ በጥላቻ ተሞልተው፣ ብሔር ተኮር ፖለቲካዊ ቅስቀሳና ቀረርቶ በማቅረብ የሚታወቁ ሰዎች ሳይቀሩ እንደ “ባጣ ቆየኝ” ስሌት ቤተ ክርስቲያን የእነርሱን “ገዥ ያጣ ፖለቲካዊ ሸቀጥ” እንድትሸከም የሚፈልጉት አዝነውላት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ተጠግተው “ጠላት” ያሉትን ለመውጋት ነው። ይህ ደግሞ ሌላ በደል ነው።

ሐዋርያዊነት በብሔር አይወሰንም!

የክርስቶስ አካል የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ብሔር የላትም። እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ጌታ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ዓለም ዓቀፋዊትና የሁሉም ናት። በአገልግሎት ውስንነት ምክንያት በሁሉም ብሔረሰብ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ባትስፋፋ እንኳን ቤተ ክርስቲያን የብሔር ወሰን የላትም፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብም ሆነ በታሪክ ትንታኔ ልዩነት አትገደብም፡፡ ዶግማዋ፣ ሥርዓቷና አስተምህሮዋ መልክአ ምድራዊም ሆነ ማኅበራዊ ድንበር የለውም። ይህን መንፈሳዊ የአስተሳሰብ ልዕልና የሚያጠፉና ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፉትን አሰራሮችና ልማዶችን ለይቶ አውቆ ማረም ያስፈልጋል። ከእነዚህም ውስጥ በተወሰነ ቋንቋ ብቻ መጠቀም፣ ካህናትን ከተወሰኑ ብሔሮች ብቻ በብዛት ማፍራት፣ የተወሰኑ ብሔሮችን ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መገለጫዎች ብቻ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማዘውተርና የቤተ ክርስቲያን እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን የተወሰነ ብሔር/ወገን የሆነች ሊያስመስሏት ይችላሉ።

ከውጭም ቢሆን አንዳንድ አካላት በሚያራምዱት ጽንፍ የረገጠ የብሔርተኝነት ፖለቲካ የቀድሞ ነገሥታት ወይም የቀድሞ ሥርዓቶች የፈጸሙትን ስህተት ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን “የዚህ ወገን መገልገያ መሣርያ ናት” ብለው የፖለቲካ ነጥብ ሊያስቆጥሩ ይሞክራሉ። ይህ ፍጹም ስህተትና መታረም የሚያስፈልገው ነው። በተመሳሳይም ቀድሞ የነበሩት ክርስቲያን ነገሥታት የሠሩትን መልካም ነገር ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አድርጎ ማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን የነገሥታቱ ብቻ፣ ነገሥታቱም የቤተ ክርስቲያን ብቻ የነበሩ ያስመስልና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ወገን ብቻ የነበረች ያስመስላታል። መታወቅ ያለበት እውነት ምንም እንኳን በጥንት ዘመን ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የተቆራኙ የነበሩ ቢሆንም የነገሥታቱ አገዛዝና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ግን በመሰረተ ሀሳብ የተለያየ የነበረ መሆኑ ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ነገሥታቱ ለሠሩት መልካም ነገር ሁሉ የምትወደስበት፣ ለበደሉት በደል የምትወቀስበት ሁኔታ መጤን ይኖርበታል። 

የሐዋርያዊነት ዓላማ ተስፋ መንግስተ ሰማያት ናት!

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት” (ፊልጵ 3:20) እንዳለው የእኛ ክርስቲያኖች ሀገራችን በሰማይ ነው። “ሀገራችን በሰማይ ነው” ማለት ከቁሳዊ እይታ፣ ከምድራዊ ደስታ በላይ የምንታመንለት እምነት፣ ከምንም በላይ ተስፋ የምናደርጋት መንግስተ ሰማያት አለችን ማለት እንጂ በምድር ኑሯችን ማኅበረሰባዊ ልዩነቶች የሉንም ማለት አይደለም። በተጨማሪም የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና (ገላ 3:28)” ሲል ለገላቲያ ክርስቲያኖች የጻፈው በተለያዩ ማኅበራዊ ልዩነቶች የተነሳ እንዳይከፋፈሉ ነበር። ይህ ቃል ዛሬም ሕያው ነው።  ይህች ምድር በእንግድነት የምንቆይባት፣ ነገር ግን ለማያልፈው ሕይወታችን ቁም ነገር ሠርተን የምናልፍባት ሥፍራ ናት። ሀገራችን በሰማይ፣ አምላካችንም እግዚአብሔር፣ አንድነታችንም ከቅዱሳን ጋር ነው (ፊልጵ 3:20)።

በምድር ላይ ስንኖር ከማንኛውም ብሔር ጋር ብንመደብ፣ የትኛውንም ቋንቋ ብንናገር የመጨረሻው ዓላማችን በእምነታችን ጸንተን መንግስተ ሰማያትን መውረስ ነው። መጽሐፍ በግልፅ ከሁሉም ነገድ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት እንደሚችል ይነግረናል። ይህም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ (ራእይ 7:9-10) “ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ፡- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው፡ አሉ” በማለት ገልጾታል። በምድር ላይ ስንኖርም “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ (ሮሜ 12:18)” እንደተባልን በሥላሴ አምሳል ከተፈጠረ ሰው ጋር ሁሉ በሰላም ልንኖር ይገባናል። የቋንቋና የባህል ልዩነትም ክርስትናችንን ሳይከፋፍለው ሁሉም በቋንቋው እየተማረና እየተገለገለ ለመንግስተ እግዚአብሔር ልንበቃ ያስፈልጋል።

ገንዘብና ክርስትና: አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን!

መግቢያ

በሥላሴ አምሳል ተፈጥሮና በሥላሴ ስም ተጠምቆ ክርስቲያን የሆነ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር በመሠረታዊነት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገዋል። እንደየዘመኑም ስልጣኔ የውኃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የመጓጓዣ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ያስፈልጉታል። የእነዚህንም ወጪ ለመሸፈን ሥራን ይሠራል። ከሥራውም ሊጠቀምበት የሚችለውን ሀብት/ገንዘብ ያገኛል። ካገኘውም የእግዚአብሔርን ድርሻ (አሥራቱን በኩራቱን መባውን) ከሰጠ በኋላ ለቤተሰቡ ወጪ ይጠቀምበታል፣ ልጆችን እያስተማረ ያሳድግበታል፣ ኢንቨስት ያደርገዋል፣ ለወደፊት ያስቀምጠዋል፣ ወይም የተቸገሩትንም ይረዳበታል። ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገነ መሥራቱንም ጤናና አቅም እስካለው ድረስ ይቀጥላል።

ይሁንና በዘመናችን በክርስቲያኖች የግል ሕይወት ከገንዘብ ማግኛ መንገዶች፣ ከገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። ችግሮቹም በብዛት ስለገንዘብ ካለው የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ከግለሰቦች ገንዘብ ወዳድነትና ከገንዘብ አጠቃቀም ችግሮች የሚመነጩ ናቸው። በዚህ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚሰሙ ስብከቶችም በብዛት ችግሩን የሚኮንኑና ግለሰቦችን የሚፈርጁ እንጂ መፍትሔን የሚያመላክቱ አይመስልም። ምዕመናንም ገንዘብ እንዲሰጡ እንጂ ገንዘባቸውን እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው በቂ ትምህርት እየተሰጠ አይደለም። ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በክርስትና ሕይወት ያለውን ገንዘብን የሚመለከተውን አስተምህሮ፣ ተያያዥ ችግሮችን እና የመፍትሔ ሀሳቦችን እንዳስሳለን።

ገንዘብና ክርስትና 

ገንዘብ የሰው ልጆች የሚገበያዩበት መሣሪያ (tool) እና የሀብት መጠን መለኪያ ነው። ገንዘብ የማግኛ ዋናው መንገድም ሥራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ (2ኛ ተሰሎ 3:10)” በማለት ክርስቲያን ሠርቶ ሀብት/ገንዘብ ማፍራት እንዳለበት በዚህም ለሥጋዊውና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ሊጠቀምበት (ሊገዛበት) እንደሚገባ በማያሻማ ሁኔታ ይገልፃል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በተግሳጹ (የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተግሳጽ አንቀጽ 20) ስለገንዘብ በሰፊው አስተምሯል። በተለይም ገንዘብን መውደድ፣ ለገንዘብ መገዛትንና በገንዘብ (ገንዘብን ለማግኘት) የማይገባ ነገር ማድረግን መንፈሳዊ ሕይወትን እንደሚጎዱ በጥልቀት አስተምሯል። እኛም እነዚህን በዝርዝር ቀጥሎ እናያቸዋለን።

ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው።

ገንዘብን መውደድን በሚመለከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው (1ኛ ጢሞ 6:10)” በማለት ገልፆታል። ይህ ሲባል ግን የክፋት ሁሉ ሥር የተባለው ገንዘብ ራሱ ሳይሆን ገንዘብን መውደድ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ምክንያቱም ገንዘብ በራሱ የክፋትም ሆነ የጽድቅ ሥር ሊሆን አይችልም። ክፋትም ይሁን ትሩፋት የሚሆነው የሰው ልጅ የገንዘብ አጠቃቀም ነው። ሐዋርያው “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁ ይብቃችሁ (ዕብ 13:5)” በማለት ያስተማረው ይህንን ያጠናክረዋል። ሰው ገንዘብን ከወደደ ልቡን በገንዘብ ላይ ያደርግና “በፍፁም ልብህ፣ በፍፁም ነፍስህ፣ በፍፁም አሳብህ አምላክህን ወደድ” እና “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” (ማቴ 22:37) የሚሉትን ሕግጋት ይዘነጋል። ገንዘብን ያለመውደድ ሲባልም ገንዘብን መጥላት ይገባል ማለት አይደለም። ሁሉንም አመዛዝኖ ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን በማስቀደም መጽናት ይገባል ማለት ነው እንጂ።

ጠቢቡ ሰሎሞን “ገንዘብን የሚወድ ገንዘብ አይጠግብም (መክ 5:10)” እንዳለው የማይጠገብ ነገር መጨረሻ የለውምና የክፋት ሥር መባሉም ለዚህ ነው። ከሐዋርያት አንዱ የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ አምላኩን የሸጠው ለገንዘብ ባለው ልዩ ፍቅር ነበር። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው ዮሴፍን ለግብፅ ነጋዴዎች የሸጡትም እንዲሁ ለገንዘብ ነበር። ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ገንዘብን የሚወዱ ይሆናሉ (2ኛ ጢሞ 3:2)” እንዳለው ዛሬም ገንዘብን መውደድ እውነተኛዋን እምነት እስከ መካድ የሚያደርሳቸው፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲነግዱ የሚያደርጋቸው ብዙዎች መኖራቸውን እንገነዘባለን። በአንጻሩ የአባቶቼን ርስት በገንዘብ አልሸጥም ብሎ ሰማዕትነትን እንደተቀበለው ናቡቴ የቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገው በገንዘብ በኩል የሚመጣን የሰይጣን ፈተና ተቋቁመው በኑሮአቸው ሁሉ የእውነት ምስክሮች የሆኑና የሚሆኑ ቅዱሳን ምዕመናን የእምነት ጽናት ተምሳሌት ናቸው።

ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ “ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም (ማቴ 6:24)” ያለውም ሰው መገዛት ያለበት ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለማስተማርና ሰው በገንዘብ ሊገዛበት እንጂ ለገንዘብ ሊገዛለት እንደማይገባ ለማስገንዘብ ነው። ስለዚህም የሰው ልጅ ሁሉን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር እንጂ ሠርቶ ለሚያገኘው ገንዘብ ሊገዛ አይገባውም። ለገንዘብ መገዛት ማለት ገንዘብ ማግኘትን ብቻ ግብ አድርጎ መኖር፣ ከእምነት ይልቅ ገንዘብን መውደድ፣ ከባልንጀራ ይልቅ ገንዘብን መውደድ፣ ገንዘብን ማምለክ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ፍቅር ይለያል። ጌታችን “አትችሉም” ያለው አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት (ሁለት አምላክ ማምለክ) የማይቻለው ስለሆነ ነው። ነገር ግን ‘ለገንዘብ አትገዙ’ ማለት ‘ለገንዘብ አትሥሩ፣ ስለገንዘብ አታስቡ’ ማለት አይደለም፣ ገንዘብን አታምልኩት፣ ለገንዘብ ብላችሁ ከቅን ህሊናችሁ፣ ከጸናች ሃይማኖታችሁ አትለዩ ማለት ነው እንጂ። ለገንዘብ መገዛትም ‘ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ (ዘፀ 20:1)’ ያለውን ትዕዛዝ መሻር ስለሆነ ከአምልኮተ ጣኦት ይመደባል።

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለም።

በክርስትና አስተምህሮ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚወገዘው ተግባር ሳይሠሩ ገንዘብ ማግኘት ወይም ገንዘብ ለማግኘት መሞከር ነው። በስርቆት፣ በሙስና፣ በማታለልና ይህንን በመሳሰሉት መንገዶች የራስ ያልሆነን ገንዘብ ማግኘት ወንጀልም ኃጢአትም ነው። ክርስቲያን ገንዘብ ማግኘት ያለበት በመሥራት ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ያስተምረናል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከእርሱ ዘንድ መጥተው “እኛ ደግሞ ምን እናድርግ” ያሉትን ጭፍሮች ሲገስፅ “ደሞዛችሁ ይብቃችሁ (ሉቃ  3:14)” ማለቱ ሰው ሠርቶ የሚያገኘው ሊበቃው እንደሚገባ ያስተምረናል። ያልተለፋበት ገንዘብም እንደ ጉም የሚተን ብኩን መሆኑን ብዙዎች የሚመሰክሩት ነው። ሁሉም በልክ መሆን እንዳለበትና የሰው ልጅም ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ጌታችን ሲያስተምርም (ሉቃ 12:15) “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል። 

ገንዘብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናል።

የሰው ልጅ ሠርቶ  በላቡ ያገኘውን ገንዘብ ለሥጋዊና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል እንጂ ኃጢአትን ለመሥራት ወይም ሌላውን ወንድሙን/እህቱን ለመጉዳት ማዋል የለበትም። ይልቁንም የራሱን ኑሮ ለመምራት፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት ሊያውለው ይገባል። ይህንንም ሲያደርግ ብልና ዝገት በማያገኙት በሰማይ መዝገብን ያከማቻል። ጌታችን “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና (ማቴ 6:21)” በማለት ያስተማረው ገንዘቡን (ያለ ከንቱ ውዳሴ) የሚመጸውት ልቡም በሰማያት (መዝገቡ ባለበት) ይሆናል ማለቱ ነው። “ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል (ምሳ 37:16)” የተባለውም ለዚህ ነው። ክርስቲያን ገንዘቡን ለእውነትና በእውነት ብቻ መጠቀም አለበት። ሐናንያና ሰጲራ የሚባሉ ባልና ሚስት ገንዘባቸውን ለሐዋርያት ኅብረት ለመስጠት ወስነው ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን በማታለላቸው ተቀጥተዋል (ሐዋ 5:1-10)። በሌላም በኩል ባልተገባ መንገድ (በጥንቁልና) ባገኘው ገንዘብ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመግዛት የተመኘው ሲሞንም እንዲሁ ከገንዘቡ ጋር ጠፍቷል (ሐዋ 8:20)።

ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ አታድንም! 

የገንዘብ ባለጠጋ ሆኖ የተወለደ የለም። ሀብትም የመንፈሳዊ ጸጋ መለኪያ አይደለም። ማንኛውም የሰው ልጅ ጠንክሮ ከሠራም ባለጠጋ መሆን ይችላል። ነገር ግን ባለጠግነትን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። አንዳንድ ባለጠጎች ብዙ (ጊዜ) ገንዘብ በመስጠት ጽድቅ የሚገኝ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ባለጠጋ በምድር ‘ተድላን’ ስላገኘ ወደ መንግስት ሰማያት የማይገባ ይመስላቸዋል። ባለጠግነትን ብቻ የመጨረሻ ግብ አድርጎ አግባብ ባልሆነ መንገድ ለመክበር መሞከርም ለክርስትና ሕይወት ታላቅ ፈተና መሆኑ እርግጥ ነው።  ጠቢቡ ሰሎሞን “ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና (ምሳ 23:4-5)” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ጌታችንም በትምህርቱ “ለባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው፣ ባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል (ማቴ 19:23)” ብሎ ያስተማረው ባለጠግነት የክርስትና ሕይወት ፈተና መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።

ጌታችን ይህንን የተናገረው  ከአምላኩ ይልቅ ገንዘቡን ይወድ ስለነበረው አይሁዳዊ ነበር። ይህንንም ሲል ሰው ከአምላኩ ይልቅ ሀብቱን ከወደደ ወይም በሀብት ብዛት ጽድቅን ለማግኘት ካሰበ መንግስተ ሰማያት መግባት ከባድ ነው ለማለት እንጂ በእውነት ሠርቶ ሀብታም የሆነ፣ እውነተኛ እምነት ያለውና መልካም ምግባር ያለው ባለጠጋ መንግስተ ሰማያት አይገባም ማለቱ አይደለም። በተጨማሪም በዘርና በዘሪው ምሳሌ ሲያስተምርም “በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል (ማር 4:19)” በማለት የተረጎመላቸው ባለጠግነት የክርስትና ሕይወት ዕድገት ማነቆ መሆኑን ሲያስገነዝበን ነው።

ሐዋርያው ያዕቆብ ስለባለጠጎች በተናገረበት መልእክቱ “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል (ያዕ 5:1-6)” በማለት ባለጠግነትን መውደድ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል አስተምሯል። በተመሳሳይም ጠቢቡ ሰሎሞን “በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል፣ በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች” ብሎ ስለባለጠግነት በጥበብ አስተምሮናል። በተጨማሪም “በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና” በማለትም ስለ ገንዘብ አጠቃቀም ተናግሯል (ምሳ 11:28 13:11 17:16)።

ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ አታድንም። ጠቢቡ ሰሎሞን ስለዚህ ሲናገር “በቍጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች (ምሳ 11:4)” ብሏል። የሰው ልጅም በገንዝቡ ከመመካት ወጥቶ ገንዘብ ማግኘት እንዲችል ጤናና ጉልበት፣ እውቀትን ጥበብን የሰጠውን እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ይገባዋል። ስለዚህ ነው እግዚአብሔር ለባለሟሉ ለሙሴ “ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ (ዘዳ 8:18)” በማለት የተናገረው። ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ እንደማያድን፣ ይልቁንም የተሰጠንን ባለ ጠግነት ለተቸገሩት ካላካፈልን መጨረሻችን የዘላለም ሞት መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ካስተማረን የነዌ ታሪክ መማር እንችላለን። 

ለድሃው ደሃ ስለሆነ ብቻ አይራራለትም!

የገንዘብ ደሀ ሆኖ እንዲኖር ተፈርዶበት የተወለደ ሰው የለም። ነገር ግን ሰው ያለውን ዕውቀትና ጉልበት ተጠቅሞ ተግቶ ካልሠራ ወይም ያገኘውን ሀብት ባአግባቡ ካልያዘ ደሃ መሆኑ አይቀርም። በተፈጥሮአዊና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ደሃ የሚሆኑ ሰዎችም አሉ። ሰው በዚህ ምድር በድህነት ስለኖረ ብቻ በሰማይ ጽድቅን አያገኝም፣ አይኮነንምም። “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” የሚለውም ከምድራዊ ድህነት ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም። በሀብታሙ ሰው በነዌ ደጅ የነበረው ደሃው አልዓዛር ጽድቅን ያገኘው ደሃ ስለነበር ብቻ አልነበረም። ነዌም የተኮነነው ሀብታም ስለነበረ አይደለም። አልዓዛር በእምነቱ፣ በንጽሕናው ጽድቅን አገኘ። ነዌም በትዕቢቱና በስግብግብነቱ ተኮነነ (ሉቃ 16:19)። ስለዚህ ነው ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው “እግዚአብሔር ለሁሉም እንደየሥራው ይሰጠዋል፣ ለድሃው ደሃ ስለሆነ አይራራለትም፣ ለባለጠጋውም ባለጠጋ ስለሆነ አይፈርድበትም” የሚለው። በእርግጥ ገንዘብ የሌለው ደሃ ብዙውን ጊዜ በረሃብና በመቸገር ሲኖር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የሚሠሯቸውን ሌሎች ኃጢአቶችን ላይሠራ ይችላል። በሌላም በኩል ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የሚሠጡትን ያህል መስጠት አይችልም። ነገር ግን ሁሉም ሰው ኃጢአትን ይሠራል፣ በአቅሙም ሌላውን ወንድሙን መርዳት ይችላል። ስለዚህ ምድራዊ ድህነትም ይሁን ሀብት የጽድቅ መስፈርቶች አይደሉም።

የገንዘብ አጠቃቀም ጥበብ

ብዙ ሰው አተኩሮ የሚተጋው ገንዘብ ለማግኘት ነው። ስለገንዘብ አጠቃቀም ግን ብዙም ትከረት አይሰጥም። በዘመናችን ያሉ ሰባክያነ ወንጌልም የሚያተኩሩት ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እንዲሰጡ መወትውቱ ላይ ነው እንጂ ምዕመናን በገንዘባቸው እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አይደለም። ዋናው መሠረታዊው ጥያቄና ክርስቲያናዊው አስተምህሮ ሊያተኩርበት የሚገባው ግን “በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያለው የገንዘብ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት?” የሚለው ነው። የክርስቲያን ቤተሰብ የገንዘብ አጠቃቀም በዕቅድ የሚመራና ቅድሚያ መሰጠት ላለባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለገንዘብ አጠቃቀም በብዙ ምሳሌዎች ያስተምራል። ጠቢቡ ሰሎሞን (ምሳሌ 6:6-8) “አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች” በማለት የገንዘብ አጠቃቀምን (በተለይም መቆጠብን) ከገብረ ጉንዳን መማር እንዳለብን ይነግረናል። እንዲሁም (ምሳ 21:20) “የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል። አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል” በማለት ጠቢብ የከበረ መዝገብ እንዳለው ያስረዳል። ክርስቲያንም በገንዘብ አጠቃቀም ችግር ምክንያት ወደ ብድር መግባት እንደሌለበት ሲናገር (ምሳሌ 22:7) “ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” ብሏል። በአጠቃላይ የገንዘብ አጠቃቀም የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ሊያተኩር ይገባል። 

ከሰጠኸኝ ሁሉ ከአሥር አንዱን እሰጥሃለሁ

ክርስቲያን ሠርቶ ከሚያገኘው አሥራት (10% ወይም ከአሥር አንድ) ለእግዚአብሔር ይሰጥ ዘንድ ይገባዋል (ዘፍ 28:22)። መቼም የጸጋ ሁሉ ምንጭ የሆነ አምላክ የእኛን ምድራዊ ገንዘብ እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና በቸርነቱ የሰጠንን፣ የባረከልንን ገንዘብ በተራቡ፣ በተጠሙ፣ በታመሙ፣ በተቸገሩ፣ በተሰደዱ፣ በማጣት በተጨነቁ ሰዎች አድሮ ይቀበለናል። ለእነዚህ ሰዎች በልግስና የምንሰጠው ምጽዋትም ለባለጸጋው አምላካችን እንደምንሰጠው እንደሚቆጠር ጌታችን በወንጌል ተናግሯል። በምድር ያለች ቤተ ክርስቲያንን የጽድቅ አገልግሎት ስንደግፍ ለቤተ ክርስቲያን አምላክ እንደሰጠነው ይቆጠራል። ይህም ቤተ ክርስቲያን ለምትፈጽመው መንፈሳዊ (የወንጌል) አገልግሎት እንዲውል ነው።  ይህ ማለት ግን የተቀረውን 90%  የእኛ ስለሆነ “እንደፈለግን እንጠቀምበት” ማለት አይደለም። ሁሉም ገንዘብ የእግዚአብሔር ስለሆነ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ሕይወታችን እናውለው ማለት ነው እንጂ።

ከዚህ ውጭ በሃይማኖት ስም ለሚያታልሉና የራሳቸውን ጥቅም ለሚያሳድዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ምዕመናን ሠርተው ያፈሩትን ገንዘባቸውን መስጠት የለባቸውም። ምዕመናንም አሥራታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሚሠጡት ተምረው፣ ተረድተውና አምነውበት በራሳቸው ፈቃድ እንጂ ተወትውተው (ተገደው) መሆን የለበትም። ከአሥራት ጋር በተያያዘ ሌላው ጉዳይ ምእመናን በየአጥቢያው ቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ ያላቸው አመኔታ (trust) መቀነስ ነው። የሚሠጡት አሥራት ለተፈለገው የወንጌል አገልግሎት እንደሚውል ማረጋገጫ ይፈልጋሉ። ይህንንም በግልጽና በዘመናዊ አሠራር ማረጋገጥ ይገባል እንጂ “የምዕመናን ድርሻ መስጠት ብቻ ነው፣ ሌላው አይመለከታችሁም” በማለት ኋላቀርና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር የማይሄድ ምላሽን መስጠት አይገባም። ምዕመናንን አስራት እንዲያወጡ የምትጠይቅ እያንዳንዷ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለተቸገሩት ገዳማትና አድባራት በልግስና ልትሰጥ ይገባል እንጂ በግለሰቦች የምናወግዘው ስግብግብነት በተቋም ደረጃ እንዲደገም መፍቀድ የለብንም። በግልፅ በሚታወቅ አሰራር እያንዳንዱ አጥቢያ ከሙዳየ ምጽዋቱ ለድሆች መመጽወት፣ ከመብዓው ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ማካፈል እንዳለበት መዘንጋት የለበትም። ይሁንና በዘመናችን ያሉ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ለምዕመናን ግላዊ ሕይወት አርአያ የሚሆን አሰራር ስለማይከተሉ ሁላችንም በየአቅማችን ይህን መሰል የአስተሳሰብ ልዕልና ቃለ እግዚአብሔርን መነገጃ በሚያደርጉ ብልጣ ብልጥ አገልጋዮች እንዳይደፈን ልንጥር ይገባናል።

ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ስጡ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ (ሮሜ 13:7)” እንዳለው ክርስቲያን ሠርቶ ከሚያገኘው ገንዘብ ለመንግስት የሚገባውን ክፍያ (ግብር ወይም ቀረጥ) በወቅቱና በአግባቡ መክፈል ይጠበቅበታል። ይህ መንግስት ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ወጪ ለመሸፈን የሚውል ነውና። የመንግስትን ግብር ወይም ቀረጥ ማስቀረት ወይም ላለመክፈል ህጋዊ ያልሆነ አሠራርን መከተል (ለምሳሌ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ በርካታ የሀገራችን ሰዎች እንደተለመደው ለማጭበርበር በማሰብ የእጅ በእጅ ካሽ ክፍያን መጠቀም) ኃጢአትም ወንጀልም ነው። ከመንግስት ለሚገኘው አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ አለመክፈል ከሌብነት ተለይቶ አይታይም። ይህም “አትስረቅ” ያለውን ትዕዛዝ መተላለፍ ነው። ስለዚህ ክርስቲያን የመንግሥትን ድርሻ ሳንቲም ሳያስቀር መስጠት ይኖርበታል። የመንግስትን ድርሻ በሚገባ ሳይከፍሉ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ገንዘብ መስጠትም ከተጠያቂነት አያድንም። ለሁሉም የሚገባውን እንደሚገባው መስጠት ያስፈልጋል እንጂ።

ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝመሩ ለጢሞቴዎስ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል” (1ኛ ጢሞ 6:7-8) እንዳለው ሰው በምድር ላይ ሲኖር ለኑሮ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ለማሟላት ገንዘብን ይጠቀማል። ለዚህም “በመጠን ኑሩ” (1ኛ ጴጥ 5:8) እንደተባለው ሁሉንም በልክና በእቅድ መምራት ያስፈልጋል። የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሚያስፈልጉበት መጠንና ጊዜ ገዝቶ ሳያባክኑ በአግባቡ መጠቀም ከክርስቲያን ይጠበቃል። በማኅበራዊ ጉዳዮችም የሚደረገው ተሳትፎ እንዲሁ በአግባቡና በዕቅድ ሊሆን ይገባዋል። ይህም እንደየቤተሰቡ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ቤተሰቡ ከትምህርት ይሁን ከልምድ በሚያገኘው ክህሎት ላይ ተመስርቶ በማቀድ፣ በመተግበርና በመመዘን ሊመራው ይገባል። ጌታችንም በወንጌሉ (ሉቃስ 14:28) “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ገንዘቡን የማይቈጥር ማን ነው?” በማለት ሰው የሚያቅደውንና ለሚያደርገውን ነገር ሁሉ ባለው ገንዘብ ልክ መሆን እንዳለበት አስተምሯል። 

መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና (ዕብ 13:16) እንዳለው ሰው ያለውን ሊያካፍል ይገባዋል። ክርስቲያን ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ የራሱ የሆኑት ቤተሰቦቹን ሊደግፍ ይገባዋል (1ኛ ጢሞ 5:8)። ከላይ እንደተገለፀው ሌሎችም የተቸገሩና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን አቅሙ በፈቀደለት መጠን ሊደግፋቸው ይገባል። በዚህም በምድር የወገኖቹን ችግር ለመፍታት የራሱን ድርሻ ያበረክታል። በሰማይም ለዘላለም ሕይወት የሚሆነውን መዝገብ ያከማቻል። እነዚህን ወገኖች መደገፍ እየቻሉ አለመደገፍ ከኃጢአት እንደሚቆጠርም ማስተዋል ያስፈልጋል (ያዕ 4:17)። ይህ የትሩፋት ሥራዎች ተብለው የሚታወቁትን መፈጸም ስለሆነ ልዩ ትኩረት ሊደረግበትም ይገባል። ለቤተ ክርስቲያን አሥራት ሰጥቻለሁና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አልደግፍም ማለትም አይቻልም። በተጨማሪም ይህ አገልግሎት ውዳሴ ከንቱን እንዳያመጣ ሰማያዊ ዋጋን ብቻ ዓላማ አድርጎ መፈጸም ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ 9:7) “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ያለውም ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። የተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራት የሚሰሩትን በጎ አገልግሎት ተጠያቂነት ያለበት አሰራርን በመከተል በገንዘብ መደገፍም በዚህ ሥር የሚታይ ነው።

በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው።

ክርስቲያን ለነገ ሕይወቱ ተስፋ የሚያደርገው እግዚአብሔርን ነው። ነገር ግን የራሱም ድርሻ ስላለው “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም እንዲህ እናደርጋለን በሉ (ያዕ 4:17)” እንደተባለው ለወደፊት እና ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ (Saving)፣ እንዲሁም ባለው ገንዘብ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት (investment) ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር ሠርቶ ለራስም ተጨማሪ ገንዘብን ማግኘት ይችላል። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። ‘ለማግኘትም ለማጣትም ጊዜ አለው’ እንደተባለ ይህንን ማድረግ ይገባል። ለነገ ብሎ ገንዘብ ማጠራቀም የእምነት ማነስ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይልቁንም ነገም እኖራለሁ ብሎ በእግዚአብሔር የመታመን እንጂ። ጠቢቡ ሰሎሞን (ምሳ 13:22) “ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች” ያለውም ቁጠባ ለመጪው ትውልድ ድረስ እንደሚጠቅም ያስረዳናል። በተጨማሪም (ምሳ 10:4-5) “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉህ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል” በማለት ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም ገንዘብን የመቆጠብ ጥበብን አስተምሯል።

በአጠቃላይ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብና ጉልበት ተጠቅሞ በመሥራት ገንዘብ ማግኘት (ሀብት ማፍራት) ይገባዋል። ያፈራውንም ሀብት መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወቱን ለሚጠቅም ዓላማ ሊያውለው ይገባል። ይህንንም ሲያደርግ እግዚአብሔርን በመፍራትና የሰውንም ልጅ በማክበር ሊሆን ይገባዋል። ከዚህ ውጭ ባልተገባ መንገድ ገንዘብን ለማግኘት መሞከር፣ በተገባ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ላልተገባ ዓላማ ማዋል፣ ገንዘብን መውደድ፣ ለገንዘብ መገዛትና የመሳሰሉት መንፈሳዊምና ሥጋዊ ሕይወትን የሚጎዱ ናቸው። በተጨማሪም ክርስቲያን ገንዘብን ለማግኘት ተግቶ ከመሥራት ጎን ለጎን ባገኘው ገንዘብም ቁም ነገር ሠርቶበት ለማለፍ መትጋት ይኖርበታል እንላለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር