About Astemhro Ze Tewahdo

ይህ የጡመራ መድረክ (አስተምህሮ) የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡

ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን

መግቢያ

በዚህ ዘመን በአብዛኞቻችን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሚስተዋል ጉልህ ችግር አለ። ይህም በክርስትናችን እንድንኖር የሚጠበቅብን ሕይወትና በተጨባጭ የምንኖረው ሕይወት መራራቅ (አልፎ አልፎም መቃረን) ነው። እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል እናውቀዋለን፣ ግን አንኖረውም። እንናገረዋለን፣ ግን አንፈፅመውም። እግዚአብሔርን እናምናለን፣ በእርሱም እንታመናለን ብለን እናስባለን። ነገር ግን ማመናችንና መታመናችን በተግባር ሲፈተን ይወድቃል። ይህንን ችግራችንን ብናውቀውም ለመፍታት ግን ቁርጠኝነት ይጎድለናል። በደካማነት፣ በዘመናዊነት፣ በድህነትና በመሳሰሉት ላይ ለማሳበብም ምክንያትን እንፈጥራለን። የዚህን ሁሉ ችግር ሥረ-መሠረት ለሚመረምር ሰው ግን የችግሩ እውነተኛ መንስኤ ሆኖ የሚያገኘው ግን ዘመናዊ የጣዖት አምልኮን (Modern Idolatry) ነው።

በእርግጥ በዚህ በሰለጠነ ዘመን “ጣዖት ይመለካል” ቢባል ማን ያምናል?! ነገር ግን በዚሁ የመረጃ ዘመን ጣዖት እንደ አምላክ እየተመለከ ማየት እጅግ ያሳቃቅል። ከዚህ የበለጠ ኅሊናን የሚያቆስለው እና ልብን የሚሰብረው ነፍስንም የሐዘን ካባ የሚያለብሰው ግን ዘመናዊው ጣዖት የሚመለከው የእግዚአብሔር ስም እየተጠራ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እየተጠቀሱ፣ በእግዚአብሔርና በቅዱሳን ስምም እየተዘመረ መሆኑ ነው። የበለጠ የሚገርመውም ብዙዎች “ዘመናዊ ጣዖታትን” የሚያመልኩት እግዚአብሔርን እያገለገሉ ያሉ በሚመስላቸው ሁኔታ ውስጥ ነው። ጣዖታቱን ሲያነግሡም ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ ያደረጉት ይመስላቸዋል። ጣዖት አምላኪዎቹም “ጣዖትን አታምልኩ” ብለው የሚገስጿቸውን “ፀረ-ክርስትና” ብለው ሲያሳድዱ ጽድቅን ያደረጉ ይመስላቸዋል።

ስለእነዚህ ዘመናዊ ጣዖታትና ጣዖት አምላኪዎች ስንናገር በተለምዶ “ባዕድ አምልኮ” ተብሎ ስለሚታወቀው ግዑዝ የሆኑ ነገሮችን (ከወርቅ የተሠሩ ጣዖታትን/idols) የማምለክና ለእነርሱም የመስገድ ልማድን ወይም ርኩሳን መናፍስትን ማምለክን እያልን አይደለም። እነዚያ የባዕድ (የጣዖት) አምልኮዎች ብዙ የተባለላቸውና ግንዛቤም የተፈጠረባቸው ስለሆኑ የዚህች የአስተምህሮ ጦማር ትኩረት አይደሉም። በሌላ በኩልም የዚህች ጽሑፍ ትኩረት ‘ማክበር’ እና ‘ማምለክን’ ባለመለየት የምናከብራቸውን ቅዱሳንን ‘ታመልካላችሁ’ የሚሉትን ከእውቀትና እምነት የተፋቱ ደፋሮች የሚመለከት አይደለም። በዚህች ጽሑፍ የምንመለከታቸው “ዘመናዊ ጣዖታት” በዓይነታቸውም ይሁን በባሕርያቸው ለየት ያሉ ናቸው። እስኪ ወደ እነርሱ ከመግባታችን በፊት የማምለክን ወይም የአምልኮን ምንነት በተመለከተ ጥቂት ነጥቦች እናንሳ።

ማምለክ: ማምለክ ማለት አንድን አካል የሁሉ የበላይ፣ የሁሉ ገዥ፣ ንጉሥ፣ ጌታ፣ አድራጊ ፈጣሪ አድርጎ ማመን፣ ለእርሱ መገዛት፣ መንበርከክ እና ለእርሱ መታመንን፣ በእርሱ መመካት፣ እርሱንም መስበክ፣ ማንገሥና ተስፋ ማድረግን ያጠቃልላል። ማምለክ ስንል የመኖርና ያለመኖር፣ የመቻልና ያለመቻል ውሳኔን ለምናመልከው አካል መስጠት ማለታችን ነው። እንዲሁም የምንኖርለት ዓለማ ከማምለክ ጋር በእጅጉ ማቆራኘትን ያካትታል። ከክፉ የሚጠብቀን፣ ወደ መልካም ነገር የሚያደርሰን፣ መውጣት መግባታችንን የሚቆጣጠረን፣ ያገኘነውን የሚባርክልን የምናመልከው አካል ብቻ መሆኑን በፅኑ መቀበልንና ይህንንም ማክበርን ይመለከታል።

አምልኮ: ከላይ የተጠቀሱትን በግልም ይሁን በጋራ፣ በንግግርም ይሁን በተግባር፣ በቤትም ይሁን በቤተ-እምነት የመፈጸም ሂደትና ሥርዓት (process and procedures) ደግሞ አምልኮ ይባላል። አምልኮ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ሲሆን ለሌሎች ሲሰጥ “የጣዖት አምልኮ” ይሆናል። በተለይም አንድን ነገር ከሁሉም አብልጦ መውደድ፣ ኅሊናን ለእርሱ ማስገዛት፣ ሙሉ ትኩረትን በእርሱ ላይ ማድረግ የጣዖት አምልኮ ነው። እግዚአብሔር ዐሠርቱ ትዕዛዛትን ሲሰጥ በመጀመሪያ ያስቀመጠው “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” የሚል ነው። ከዚህ ትዕዛዝ የሚወጣ አምልኮ በተለምዶ “ጣዖት” በመባል የሚታወቀው በሰው የተሠራ ግዑዝ ነገርንና ርኩሳን መናፍስትን ማምለክ ተደርጎ ይወሰዳል። በዘመናችን ግን ለማይሰሙ፣ ለማይናገሩ ጣዖታትና ለርኩሳን መናፍስት መገዛት ቢቀንስም በምትኩ ግን ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ ተንሠራፍቶ ይታያል። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ዋና ዋና የሚባሉትን የዘመናዊ ጣዖት አምልኮ መገለጫዎች እንዳስሳለን።

ዘመናዊ ጣዖት 1: የዕውቅና እና ዝነኝነት አምልኮ

በቀደመው ዘመን የነበሩት መምህራን ክርስቲያኖች ሁሉ በተለይም አገልጋዮች “ውዳሴ ከንቱን” መጠየፍ እንደሚገባቸው በሰፊው አስተምረዋል፣ በሚነበብ፣ በሚተረጎም ሕይወታቸውም ኖረው አብነት ሆነውናል። የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ብሎ ያስተማረውን በርካታ ቅዱሳን በሕይወታቸው ፈጽመውታል። (ፊል 2:3-4) በዘመናችን ያሉት አንዳንድ ‘አገልጋዮች’ ግን ውዳሴ ከንቱን በታቀደ መልኩ ገንዘብ በማድረግና ተንከባክቦ በማሳደግ ወደ አምልኮነት እንዲደርስ አድርገውታል። አንዳንድ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኃንም ዓላማዬን ያስፈጽምልኛል ብለው ያሰቡትን ‘አገልጋይ’ በማድነቅ፣ በማስተዋወቅና፣ ስለእርሱም በተቀናጀ መልኩ የታወቀ ውሸትን ጨማምሮ በመስበክ እንዲነግሥና “እንዲመለክ” ከማድረግ አንጻር የበኩላቸውን አድርገዋል። የዋሃን ምዕመናንም ይህንን የጥፋት መንገድ ባለማስተዋል ይሳተፉበታል። ይህ ክፉ ልማድም ብዙ ታዋቂና ዝነኞች አማልክትን ፈጥሯል። የታዋቂና የዝነኞች ጣዖታት አምልኮ በሚከተሉት መንገዶች ይፈጸማል።

በስም: የስምን አሸንክታብ የሚያግተለትሉትን፣ የራሳቸውን ስም ሲጽፉ/ሲናገሩ በመንፈሳዊ የመዓርግ ስም ላይ ዓለማዊ የመዓርግ ስሞችን የሚደርቡትን ተመልከቱ። የአስተሳሰብ እድገት ባለባቸው ቦታዎች በእምነታቸውም በእውቀታቸውም በምግባራቸውም ተመዝነው የሚቀሉ ሰዎች በደጋፊ ብዛት “መልአከ ምናምን፣ ሊቀ ምናምን፣ በኩረ ምናምን” ይባላሉ። እንደምንም ብለው ዩኒቨርስቲ ውስጥ አንድ ኮርስ የሚያስተምሩ ሰዎች ለማጭበርበር “ፕሮፌሰር” የሚል የሌለ መዓርግ ይጨመርላቸዋል። አንድ ገጽ ጽሁፍ እንኳ ያለድካም (effortlessly) በእንግሊዝኛ መጻፍ ዳገት የሚሆንባቸው ሰዎች (አጭበርባሪ ጳጳሳትን ጨምሮ) ለስም አምልኮ ስለሚፈልጉት፣ አስተዳደራዊ ስልጣንን ለመያዝም ስለሚጠቅማቸው “ዶክተር” ይባላሉ። በዚህ ሁሉ ዝክንትል ስም ላይ ዲያቆን፣ መምህር፣ ቄስ፣ አባ፣ ጳጳስ የሚለውን ጨምረው ስማቸውን በማስረዘም ስማቸውን ያስመልካሉ። የሚከተላቸውም ከስብከታቸው ይልቅ ስማቸው ላይ ሲያተኩር ይስተዋላል። እስኪ እነዚህን ግለሰቦች “በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት አንዱ ስም ብቻ ለምን አይበቃችሁም?” ብላችሁ ጠይቁ። ተከታዮቻቸውንም “ለምን በዚህ ሁሉ የስም ዝርዝር ትጠሯቸዋላችሁ፣ አንዱ አይበቃችሁም ወይ?” ብላችሁ ጠይቁ። “ጌቶቻችንን አትንኩብን” ወይም “ስለሚበልጧችሁ ቀንታችሁባቸው ነው” ትባላላችሁ። ይህ ምን እንደሚያሳይ መናገር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው። ግለሰቦች ራሳቸውን አንግሠው፣ ተከታዩም እንደ አማልክት እያመለካቸው ስለመሆኑ ድርጊታቸው ያረጋግጣል። እስኪ እናስተውል! የዓለም ብርሃን የሆነ ቅዱስ ጳውሎስ “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ (1ኛ ቆሮ 15:8-9)” ካለ አንድ አገልጋይ እንዴት በስም ማግተልተል ለታዋቂነትና ዝነኝነት ሲባክን ይኖራል? የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን ስም ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን የእግዚአብሔርን የተቀደሰ ስም እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

በአካል: እነዚህ አማልክት እንደ ጣዖታት በአልባሳት እየተሸለሙ ከአገልግሎታቸው ይልቅ አለባበሳቸው ላይ የሚያተኩሩ፣ ተከታዮቻቸውንም በአለባበስ ለመማረክ የሚደክሙ ደካሞች ናቸው። ስለ እግዚአብሔር በሚሰብክ ጽሑፍ/መጽሐፍ ጋር (ፊት ለፊት) ግዙፍ የሆነ ‘የአገልጋዩን’ ፎቶ መለጠፍ፣ ከቅዱሳት መካናት (እስራኤል ያሉትን ጨምሮ) በፎቶ ለማሳየት በሚመስል እሳቤ ነገር ግን በአሥር እጥፍ የሚገዝፍ የሰባኪውን ፎቶ ከፊት ለፊት መለጠፍ፣ የስብከትና የመዝሙር ማስታወቂያዎች ‘የአገልጋዩን’ ተክለ ሰውነትና አለባበስ አጉልተው የሚያስተዋውቁ መሆናቸው፣ የስብከትና የመዝሙር ውጤቶችም እንዲሁ የግለሰቦችን ፎቶና ቪዲዮ ማስተዋወቂያ መሆናቸው የአምልኮው ማሳያ ናቸው። ይባስ ብሎም ፎቶዎቹን የሚለጥፈውም ራሱ ‘አገልጋዩ’ መሆኑ፣ ይህንንም የሚወድ (like የሚያደርግ)፣ የሚያደንቅና የሚያጋራ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ተከታይ መኖሩ የዘመናዊ ጣዖታት አምልኮ አይነተኛ ማሳያ ነው።

ይህንን የበለጠ ለመረዳት እስኪ ታዋቂና ዝነኞቹን “ጽሑፎቻችሁ፣ ስብከቶቻችሁና መዝሙሮቻችሁ የእናንተን ፎቶ አስቀርታችሁ የቅዱሳንን ስዕል ብቻ ለምን አይዙም?” ብላችሁ ጠይቁ። “የቪዲዮ ስብከቶችና መዝሙራት የአገልጋዮችን ተክለ ሰውነት ከማጉላት ይልቅ ስለምን ስለሚሰበከው ወይም ስለሚዘመረው መልእክት የሚያሳዩ ስዕሎችና ቪዲዮዎች ብዙውን ጊዜ አይወስዱም?” ብላችሁ ጠይቁ። “የጉባዔ ማስታወቂያዎች የተጋባዦችን ፎቶ ትተው አገልግሎት መኖሩን፣ የሚኖረውን አገልግሎት ዝርዝር ብቻ ቢናገሩ አይበቃም ወይ?” ብላችሁ ጠይቁ። የምታገኙት መልስ “ሰው አይወድልንም ወይም አይመጣልንም” የሚል ነው። ታዲያ ሰው የሚመጣው ‘የአገልጋዩን’ ፎቶ አይቶ ከሆነ (አገልግሎቱን ብሎ ካልሆነ) ችግሩ የዘመናዊ ጣዖታት አምልኮ መሆኑ ግልጽ ይሆናል። ምዕመኑን ለግለሰባዊ ወይም በሃይማኖት ስም ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ሸቀጥ ለሚሸቅጡ አስመሳይ ማኅበራት አምልኮ የሚያመቻቹት ሰዎች ለክፋታቸው ያበላሹትን ምዕመን ተጠያቂ አድርገው ያቀርባሉ። በድጋሜ እናስተውል! ቅዱስ ጳውሎስ “ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ (ኤፌ 3:8-9)።” ካለ ከሁሉ በልጦ ለመታየት መትጋትን ምን አመጣው? ለምንስ ይጠቅማል? የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን አካል ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን የእግዚአብሔርን የማይመረመር አካል እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

በግብር: በየማኅበራዊ ሚዲያው ባላቸው ተከታይና በጉባዔ በሚመጣላቸው ምዕመን ብዛት በመመካት በምዕመናን ላይ ራሳቸውን ንጉሥ አድርገው የሾሙ፣ ምዕመናን ወደ ጉባዔ የሚመጡት እነርሱን ለማንገሥ እንዲሆን ያደረጉ፣ እነርሱ ከሌሉ ጉባዔ እንዲቀዘቅዝ ያደረጉ፣ በጎዳና ላይ እየተንጎማለሉና ከድሆች ጋር ፎቶ እየተነሱ ለድሆች መመጽወትን ሳይቀር መነገጃ ያደረጉ፣ የራሳቸው የሠርግ ድግሥ እንደ ንግሥ እንዲከበር የሚያደርጉ ሁሉ ዘመናዊ ጣዖታት ናቸው። እነዚህ አማልክት ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠትና ለማምለክ የመጣውን ምዕመን በጉባዔም በማኅበራዊ ሚዲያም የእነርሱ ተከታይ አድርገዋል። ብዙ ምዕመንም በጠዋት ተነስቶ ከመጸለይ ይልቅ “ታዋቂው ምን አለ/ፃፈ?” ብሎ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲሰፍር ያደረጉ፣ ካህናት ጭምር “ስማችንን ያጠፋሉ” በሚል ስጋት ከእግዚአብሔር በላይ እንዲፈሯቸው ያደረጉ ጣዖታት ካልተባሉ ሌላ ምን ሊባሉ ይችላሉ? በመንፈሳዊ ጉባዔያትም ምዕመን እነርሱን ብሎ የሚመጣ፣ እነርሱ ሲሄዱ አብሮ የሚሄድ ከሆነ እውነተኛ አምልኮ ከወዴት አለ? እነርሱ ሲመጡ ብቻ ገንዘብ የሚሰጥ ምዕመን ለማን እንደሚሰጥ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ራሳቸውን ሁሉን አዋቂ አድርገው የሚያቀርቡበትን፣ መሰሎቻቸው ሌሎች “መሰል አማልክትን” ሲያዳንቁ የሚውሉበትን፣ ይቃወመኛል የሚሉትን አካል ሲሳደቡና ሲያወግዙ የሚውሉበትን ንግግር (“ስብከት”) እንደ እግዚአብሔር ትዕዛዝ የሚቀበል፣ የሚፈፅም፣ የሚያደንቅ፣ ሰው መኖሩ እነዚህ ዘመናዊ ጣዖታት የመሆናቸው ግልፅ ማሳያ ነው። ይህ ተከታይም እነዚህን አማልክት “መስተካከል ይገባቸዋል!” የሚለው ወገኑን በድንጋይ ሊወግር መነሳቱ ለአማልክቱ ያለውን የአምልኮ ፍቅር ያሳያል።

አሁንም እናስተውል! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ (1ኛ ጢሞ 1:15-16)” ብሎ ያስተማረውን እያወቅን እንዴት በእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ታዋቂነትንና ዝነኝነትን እናነግሳለን?

ይህንን በመሰለ የውዳሴ ከንቱ ሽንገላ የተገኘ ዝናና እውቅና መጨረሻው ምን እንደሆነም በሚገባ ይታወቃል። አንዳንዱ በመንፈሳዊ አገልጋይነት ስም ያገኘውን እውቅና የፍቅረ ንዋይ ጥሙን ለማርካት ሲጠቀምበት ሌላው ደግሞ ለፖለቲካ ግብ/ስልጣን ማሳኪያ መሣሪያ ያደርገዋል። በመንፈሳዊ አገልግሎት የተገኘ እውቅና ቢያንስ ለተመሳሳይ አገልግሎት ቢውል ባላስነቀፈን ነበር። ከዚህ አንጻር አስተምህሮ ዘተዋሕዶ እውነተኞቹ መንፈሳዊ አገልጋዮች ክብር እንደሚገባቸው ታምናለች። በዚህች ጦማር የተነሳውም በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም ታዋቂነትንና ዝናን እያመለኩ የሚነግዱትን የሚመለከት ነው። አካሄዳቸውንም የምንነቅፍበት ብቸኛ ምክንያት ምዕመናን በአምልኮተ እግዚአብሔር ብቻ እንዲጸኑ ያለን ጽኑ ፍላጎት ብቻ ነው። የሚሸቅጡትን ሸቀጥ መግዛትና አለመግዛት የእያንዳንዱ ምዕመን ውሳኔ መሆኑ የታወቀ ነውና።

ዘመናዊ ጣዖት 2: የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አምልኮ

የክርስትና አስተምህሮ መሠረቱ ነገረ-መለኮት (Theology) ነው። የክርስትና አስተምህሮ በማንኛውም ምድራዊ ርዕዮተ ዓለም (Ideology) ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚህ አንጻር የክርስትናን አስተምህሮ በምድራዊ ርዕዮተ ዓለም ላይ ለመመሥረት መሞከር የጣዖት አምልኮ ነው። ከሰው ሕይወት አስበልጠው፣ ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ አስቀድመው የሚሰብኩት፣ ሰው እንዲሞትለት የሚፈልጉት ማንኛውም ርዕዮተ ዓለም ዘመናዊ ጣዖት ነው። የዚህ ዓይነቱን ርዕዮተ ዓለም መስበክ እንደ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲቆጠር የጣዖት አምልኮ መሆኑ አያሻማም። የእንደዚህ ዓይነቱ ጣዖት አምልኮ (ርዕዮተ ዓለምን) በእምነት አደባባይ በመስበክ፣ እርሱን በሚመለከት በመዘመርና እርሱን የሚገልፅን ምልክት በመጠቀም ይከናወናል። የተወሰኑትን መገለጫዎች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

በስብከት: በሃይማኖት ስም የተወሰኑ የርዕዮተ ዓለም መሪዎችን እንደ ፍጹማን፣ አንድን ርዕዮተ ዓለም እንደ ጽድቅ መንገድ፣ ለአንድ ርዕዮተ ዓለም መሞትን እንደ ሰማዕትነት አድርጎ የሚሰብክ አገልግሎት የጣዖት አምልኮን የሚሰብክ ነው። አንድ ርዕዮተ ዓለም ፍጹም የሆነ፣ የማይተች፣ በውጤቱ የማይለካ፣ መለኮታዊ ኃይል ያለው፣ ተቀዳሚም ተከታይም የሌለው ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማሰብ የርዕዮተ ዓለም አምልኮ ቁራኝነት መገለጫ ነው። ፖለቲካዊ ርዕዮትን መንፈሳዊ ነገር በሚሰበክበት መድረክ ማቅረብ ደግሞ ልዩ አምልኮ መሆኑን ያረጋግጠዋል። አንድን ርዕዮተ ዓለም የማይቀበሉትን እንደ ከሃዲ መቁጠር፣ የርዕዮተ ዓለምን የበላይነት ለማረጋገጥ ሲባልም ሌላ አማራጭ ርዕዮተ ዓለም ያላቸውን ለማጥፋት የሚረዳ ስብከትን መስበክ ለጣዖት አምልኮው መታመንን ያሳያል። በተቃራኒው ደግሞ ይህንን ርዕዮተ ዓለም የሚያራምድ እስከሆነ ድረስ የሌላ ሃይማኖት ተከታይም (ወይም መሪም) ቢሆን እንደ ቤተኛ አድርጎ በመቁጠር የቤተ ክርስቲያንን ስም በያዙ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ይህንን አመለካከት እንዲሰብኩ ማድረግ የመጨረሻ ግቡ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው።

በመዝሙር: መንፈሳዊ መዝሙራት ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብባቸው፣ ስለቅዱሳን ክብር የሚነገርባቸውና በአማላጅነታቸውም ተማጽኖ የሚቀርብባቸው፣ እምነትን፣ ተስፋንና ፍቅርን የሚሰብኩ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል። ‘ስንቶቹ መዝሙራት ይህንን ያሟላሉ?’ የሚለውን ለአንባብያን እንተወውና እኛ ያስተዋልነውን በአጭሩ እናቅርብ። ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የወጡና በብዛት የሚዘመሩ አንዳንድ የአማርኛ መዝሙራት መንፈሳዊነታቸው መንምኖ ርዕዮተ ዓለማዊ መልእክታቸው ገንግኖ ይታያል። ይህ መልእክታቸውም አንድን ርዕዮተ ዓለም ብቻ የሚሰብክ መሆኑ ደግሞ ዝማሬውን ወዳልተፈለገ የጣዖት አምልኮ እየወሰደው ይገኛል። ይህንን ለመረዳት እንዲያግዝ ለምሳሌነት የሚሆኑትን ከመጥቀስ ይልቅ አንባብያን “ስለሀገር ወይም የሀገር ስም በመጥቀስ” የተዘመሩ መዝሙራትን በመመርመር የመልእክታቸውን ይዘት እንዲያጤኑ እንጠይቃለን። አስተምህሮ ስለሀገር ሰላም የሚሰብኩትን መዝሙራት አትነቅፍም። የምትነቅፈው በሀገርና በሃይማኖት ስም አንድን ርዕዮተ ዓለም በምዕመናን ላይ ለመጫን የሚጥሩትን፣ በርዕዮተ ዓለም ብቻ የሚለየውን ክርስቲያን ወገናቸውን “ጠላቴ ሆይ” በማለት ጥላቻን የሚዘሩትን፣ ምዕመናንን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ “አምልኮተ ርዕዮተ ዓለም” የሚወስዱትን፣ አንድን ርዕዮተ ዓለም የሚያራምደውን ብቻ የሀገርና የሃይማኖት ብቸኛ ጠበቃ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩትንና ሀገርንና ሃይማኖትን እያምታቱ ምዕመናን አንድን ርዕዮተ ዓለም እንዲያመልኩ የሚያደርጉትን ነው። እነዚህ ሊታረሙና መንፈሳዊ ነገር ላይ ብቻ ሊያተኩሩ ይገባል።

በምልክት: በደጋጎቹ ቅዱሳን ዘመን አንድ ሕንፃ “ቤተ ክርስቲያን” መሆኑ የሚታወቀው በላዩ ላይ ወይም በፊት ለፊቱ ባለው የመስቀል ምልክት ነበር። የንግሥ በዓላት ልዩ መገለጫም ከሩቅ የሚታየውና ለታቦታቱ ክብር ሲባል የሚዘረጋው የወርቅ ጥላ፣ ድባብና ካህናቱ የሚይዙት መስቀል፣ የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ማክበሪያ፣ የእመቤታችን ምሳሌ መሶበ ወርቅና የመሳሰሉት ነበሩ። የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያንም የሚለዩት እንደ መላእክት በሚያስመስላቸው ነጫጭ አልባሳት ነበር። ዛሬ ላይ ግን በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በንግሥ በዓላት ላይ፣ በመዘምራን አልባሳት ላይ የሚታዩት ቀለማት አንድን ርዕዮተ ዓለም የሚያሳዩ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህም የተነሳ ይህንን ርዕዮተ ዓለም የማይደግፉ አካላት የዚህ ምልክት በቤተ ክርስቲያን አሰልቺ በሆነ ትኩረት (pointless and boring obsession) መዘውተር ሲመለከቱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ እንዲመስላቸውና ጭራሹን ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ ያደርጋል። እንግዲህ እናስተውል ክርስቶስ በደሙ የሰበሰበውን ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን የሚያስቀር ምልክት ለቤተ ክርስቲያን ምን ይጠቅማታል? የሰውን ልጅ ሕይወት ከማዳን በላይ መንፈሳዊ አገልግሎትስ አለን? ለዚህ ነው ከሰው ልጅ መዳን ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ርዕዮተ ዓለምም ሆነ እርሱን የሚገልፅ ምልክት ጣዖት አምልኮ ነው የምንለው።

እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ርዕዮተ ዓለም ማራመድ መብቱ እንደሆነ እናምናለን። በሃይማኖት ስም ግን ምዕመናን የተወሰነ ርዕዮተ ዓለም እንዲያመልኩ ማድረግ ኢ-መንፈሳዊነት ነው እንላለን። ይህንን የምንለው ርዕዮተ ዓለም ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ እንዳልሆነ ካለን ግንዛቤና ቤተ ክርስቲያንም የመንፈሳዊነት ዐውድ ብቻ ሆና ለማየት ካለን ልባዊ ፍላጎት የተነሳ ነው። ስለሆነም የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

ዘመናዊ ጣዖት 3: ስልጣንንና ኃይልን ማምለክ

መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኞች ባለስልጣናትን (በቀድሞ አጠራር ነገሥታትን) ማክበር እንደሚገባ ያስተምረናል። ከእውነት አፈንግጠው የተገኙትን መገሰፅ ደግሞ ከመንፈሳውያን አባቶች እንደሚጠበቅ መጥምቁ ዮሐንስ ሄሮድስን በመገሰፅ አብነት ሆኖ አልፏል። በዘመናችን የምናስተውለው ግን ከዚህ ተቃራኒ መሆኑ የታወቀ ነው። ባለስልጣናት መልካም ሲያደርጉ ማመስገን፣ መጥፎ ሲያደርጉ ደግሞ መምከርና መገሰፅ የሚጠበቅባቸው የሃይማኖት መሪዎች ባለስልጣናትን ፍፁም (የማይሳሳቱ)፣ መለኮታዊ ስልጣን ያላቸው፣ የማይተቹ፣ በሥራቸው የማይመዘኑ አድርገው ማቅረብ የተለመደ ሆኖል።

በቀደመው ዘመን መለካዊነት (የንጉሥ ፈቃድ ፈፃሚነት) ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ችግር ነበር። ዛሬ ግን ይህ አድጎ ወደ ንጉሥ አምላኪነት ተሸጋግሯል። ይህንን ለማሳየት አንድን ባለሥልጣን/ንጉሥ (ዛሬ በሕይወት የሌለ ሁሉ ሊሆን ይችላል) ሥራውን እንኳን በአግባቡ ሳያዩ “ከእግዚአብሔር የተላከ” ብለው የሚሰይሙ ንጉሥ አምላኪ የሃይማኖት መሪዎችን ማየት በቂ ነው። የሃይማኖት መሪዎቹ እንዲህ ካሉት ምዕመናኑ ምን ሊሉት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። በእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች “ሙሴ” የተባለው ባለሥልጣን ሌላ ጊዜ እስራኤልን ከባርነት የሚያወጣ ሳይሆን በእስራኤል ላይ መከራን ያደረሰ የፈርኦንን ሥራ ሲሠራ ሲያዩ ግን ያፍራሉ። ኃላፊነታቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት መስበክ ሆኖ ሳለ ፈርኦንን በሙሴ ስም ስለሰበኩ ፍርዳቸውን በጊዜው ይቀበላሉ።

በሌላ በኩል በሌላው ዓለም ሰላማዊ ሰዎችን የሚያቃጥለውን ጦርነት ያወጀን መሪ ለሕዝቦች የሚቆም “ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ መርቆርዮስ” አድርጎ ማቅረብ መሠረታዊውን የሃይማኖት መርህ ካለማወቅ ይመነጫል። ይህንንም ከቆስጠንጢኖስ ጋር እያወዳደሩ ግፍንና ኢ-ሰብአዊነትን የጽድቅ ሥራ አድርጎ ማቅረብ የንጉሥ አምላኪነት ካልተባለ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን የሰው ልጅ የሚጨፈጭፉትን መሪዎች “ጻድቅ፣ መልአክ” አድርጎ የሚሰብክ የሃይማኖት መሪስ ከወዴት ይገኛል?! እኛ ግን እንላለን – ኃጢአትንና ግፍን እንደ ጽድቅ ሥራ እየቆጠሩ፣ ግፈኞችን እንደ መላዕክት እያወደሱ እንኳን ጽድቅ ምድራዊ ሞራልም ሊኖር አይችልም።

የቀድሞ ነገሥታን (ሐሳውያን ገና ይመጣል የሚሉትን ንጉሥ) “መልአክ” አስመስሎ ክርስቶስ በሚሰበክበት የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት መስበክም አይገባም። ሰው መልአክ አይደለም፣ ሰይጣንም አይደለም። ሰው ያው ሰው ነው። ንጉሥም ሰው ነው፣ መልካምን ይሰራል፣ ይበድላልም። ከሥልጣንም ይወርዳል (ለዘላለም ንጉሥ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው)፣ እንደ ሰውም ይሞታል፣ ይቀበራል፣ለሠራው መልካም ሥራ ይመሰገናል፤ ላጠፋውም በሕግ እና/ወይም በታሪክ ፊት ይቀርባል። በፍርድ ቀንም የሥራውን ዋጋ ይቀበላል። ስልጣንም መልካም የሠራበት ይጠቀምበታል፣ ክፉ የሠራበትም ይጎዳበታል። እርሱም ያልፋል። ስልጣንን እና ባለሥልጣንን እንደ ፈጣሪ የሚያመልኩም ያልፋሉ፣ ፍርዳቸውንም ከእውነተኛው አምላክ ዘንድ ያገኛሉ። ባለስልጣን ሲቀየር እነርሱም ስልታቸውን እየቀያየሩ ባለስልጣንን የሚያመልኩም በጣዖት አምላኪነታቸው ቅጣታቸውን ይቀበላሉ።

በተጨማሪም “የመኖርና ያለመኖር ዕጣችን የሚወሰነው በአንድ ‘ወታደራዊ ኃይል’ ነው፣ ተስፋችንም አለኝታችንም እርሱ ነው፣ እርሱንም ለመተቸት አንችልም” ብለው የሚሰብኩ ካህናት ራሳቸው ወታደራዊ ኃይልን ማምለካቸው ሳያንስ የዋሁን ምዕመንም በኃይል አምልኮ ያስታሉ። በዚህም ሳይበቃ ይህንን ምድራዊ ኃይል ‘እንደ እግዚአብሔር ቢያስቀይሙትም በክፉ ቀን የማይጨክን የሕዝብ ታዳጊ ነው” በማለት አፋቸውን ሞልተው ሲናገሩ ትንሽ እንኳን አይሰቀጥጣቸውም። ‘ኃይል የእግዚአብሔር ነው’ ብለው የሚያስተምሩ ‘ሰባክያን’ ሳይቀር ቅዱሳት ስዕላትን የያዙ ታጣቂዎችን በፎቶ እያሳዩ የኃይል አምልኮን እውነተኛና እግዚአብሔር የፈቀደው አስመስለው ያቀርባሉ። እነርሱ ‘ጠላቴ’ የሚሉትን የገዛ ወገናቸውን የሚጎዳላቸውንና የሚያጠፋላቸውን ሁሉ (እምነቱና አመለካከቱ ምንም ቢሆን) እንደ አማልክት ያመልኩታል። እጅግ የሚያሳዝነው እንቆምላታለን የሚሏት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይቀር የመከራ ዶፍ የሚያወርደውን ‘ጠላቴ’ የሚሉትን እስከተዋጋላቸው ድረስ ያመልኩታል። ምክንያቱም ስልጣንና ኃይልን ያመልካሉ። እኛም የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን ስልጣንና ኃይል ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን የእግዚአብሔርን ኃይልና ስልጣን እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

ዘመናዊ ጣዖት 4: ገንዘብን/ሀብትን ማምለክ

ሌላውና በሰፊው የሚታየው የጣዖት አምልኮ የገንዘብ አምልኮ (ለገንዘብና በገንዘብ መገዛት፣ በገንዘብ ሁሉን ነገር ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ) ነው። ቅዱስ መጽሐፍ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” ቢልም በዘመናችን ግን ገንዘብን መውደድ አልበቃ ብሎ ገንዘብን ማምለክ ተንሠራፍቷል። ይህም በግለሰብም በተቋምም ደረጃ የሚታይ ነው። በግለሰብ ደረጃ ገንዘብን(ሀብትን) የሚያመልከውን ቤት ይቁጠረው። በተቋም ደረጃ ግን ገንዘብ ለመንፈሳዊ አገልግሎት አስፈላጊ ቢሆንም አገልግሎት ለገንዘብ ሲሆን ግን ጣዖት አምልኮ ነው። “ብዙ ገንዘብ የሚያስገባልን አገልጋይ እንጋብዝ”፣ “ገቢ ማስገኛ ጉባኤ እናዘጋጅ”፣ የገቢ ማስገኛ እጣ/ቶምቦላ እናዘጋጅ፣ የገቢ ማስገኛ እራት/ምሳ እናዘጋጅ፣” እያንዳንዱ ምዕመን ይህን ያህል ገንዘብ ቢያዋጣ በማለት የምዕመናንን ቁጥር ለገቢ ስሌት መጠቀም” የሚሉትና ሌሎች የዚህ መገለጫዎችን ተመልከቱ። ይህ አሠራርም የብዙ እምነት ተቋማት “core business”/መገለጫ እየሆነ መጥቷል።

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የከበረ መንፈሳዊ አገልግሎት ያላቸውን ታቦታት ለገንዘብ ማግኛ ሲባል በየቦታው እየደረቡና እየሰለሱ ትርጉም የሚያሳጡት፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ስያሜ ለገንዘብ ማስገኛነት ሲባል ስም እየቀጣጠሉ መቀለጃ የሚያደርጉት፣ የንግሥ በዓላትን እንደ ገቢ ማስገኛ የታይታ መድረክ ለማድረግ ሲባል የሚሸቅጡት፣ በዚህም የተነሳ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሰረት በሚቀርብ አመክንዮ የማይደገፍ (scripturally and traditionally indefensible) የሚያደርጉት ነውረኞች ገንዘብን እንደሚያመልኩ ለመናገር የተለየ ምርምር አያስፈልግም። የከበረውን ሁሉ ለነውራቸው ሲባል የሚያቀሉ ክብረ ቢስ ጣዖት አምላኪዎች ናቸው።

ብዙ የዘመናችን አገልጋዮችም አገልግሎትን እንደ ሸቀጥ የዋጋ ተመን አውጥተው “ይህን ያህል ካልከፈላችሁኝ አላገለግልም” የሚሉት አካሄድ የአገልግሎትን ዓላማ የሳቱ ናቸው። በእግዚአብሔር ቤት “ሙስናን” የሚፈጽሙም ተገዥነታቸው ለገንዘብ ነው። ከሳምንት ሳምንት፣ ከወር ወር፣ ከዓመት ዓመት በቤተ ክርስትያን ዐውደ ምሕረት ስለገንዘብ በመናገር የቤተ ክርስቲያንን ዓላማ “ቢዝነስ” ያስመሰሉም ዋና ትኩረታቸው ገንዘብ እንጂ አገልግሎት አይደለም። ለእነዚህ ሰዎች ክርስቲያን ማለት የተመደበበትን ገንዘብ የሚከፍል ብቻ ነው፣ የማይከፍል ደግሞ እንደ ነዳይ ወይም ንዑሰ ክርስቲያን ይቆጠራል። በዚህ ረገድ ምዕመናን የገንዘብ ምንጮች ብቻ ተደርገው መቆጠራቸው ያሳዝናል። ምዕመናንም በመሰላቸት እስኪ አንድ ቀን እንኳን “ገንዘብ አምጡ” ባለማለት አሳርፉን እስኪሉ ድረስ የሚያማርሩ ለገንዘብ ተገዢዎች ናቸው።

ከዚህ ውጭ ከግልፅ የገንዘብ መውደድ ጋር የሚገናኘው “Prosperity theology” ነው። ይህ አስተምህሮ ገንዘብን ከፈጣሪ የሚሰጥ ስጦታ አድርጎ የሚወስድ ሲሆን በገንዘብ መባረክም የእምነት መገለጫ ተደርጎ ይቀርባል። በዚህም የተነሳ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ልዩ ግብና የደስታ ምንጭም ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህም ሰዎች “ገንዘብ ማግኘትን” አንድ የሃይማኖት እሴት አድርገው እንዲወስዱት ሆነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ሁሉን ነገር በገንዘብ ማድረግ የሚችሉ የሚመስላቸው ወይም ገንዘብ ስለሌላቸው ብቻ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችሉ የሚሰማቸው ሰዎች በገንዘብ ላይ ያላቸውን አመለካከት መለስ ብለው ሊያዩት ይገባል። የሁሉ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ገንዘብ አይደለምና። እኛም የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን የእግዚአብሔርን ስም እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

ዘመናዊ ጣዖት 5: ራስን ማምለክ

አምላክ ለመሆን መመኘት አስቀድሞም አዳምና ሔዋን ከገነት ያስባረረ ምክንያት ነበር (ዘፍ 3)። ይህ ምኞት ግን በዚያ ብቻ አላበቃም። በተለያዩ ዘመናት ራሳቸውን አምላክ አድርገው ሌሎችም እንዲያመልኳቸው የሚያስገድዱ ምድራውያን ኃያላን ነበሩ። ዛሬ ዛሬ ግን ብዙ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት (የጸሎት ሕይወት) እየላላ ሲመጣ ሳያስተውለው ራሱን አምላኪ ይሆናል። በተለይም ዕውቀትን፣ ውበትንና የሙያ ደረጃን (career) ማምለክ በዚህ ይካተታሉ። የእነዚህ አምልኮም በሀሳብ፣ በንግግር፣ በተግባርም ሊፈፀም ይችላል። ሰዎች ራሳቸውን ማምለካቸው ከሚታወቅባቸው መገለጫዎች የሚከተሉት ይገኙበታል።

ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ፡ በጥቂት ዕውቀት ራስን ሁሉን አዋቂና ለሁሉ ነገር ተጠያቂ አድርጎ ማሰብ ራስን ማምለክ ነው። የሁሉ ነገር አዋቂ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። በተከታይ ብዛት በመመካት ራስን ሁሉን ማድረግ የሚችል አድርጎ መቁጠርም እንዲሁ ራስን ማምለክ ነው። የዚህ አይነቱ ራስን ማምለክ (ትዕቢት) ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌላውን መናቅና ማሳነስም ያካትታል። በተለይም ብዙ ተምረውና አውቀው በትህትና የተነሳ ራሳቸውን እንደ አላዋቂ የሚቆጥሩ ታላላቅ ሊቃውንት ባሉባት ቤተ ክርስቲያን የረባ ትምህርት እንኳን ሳይማሩ ራሳቸውን “ሊቅ” አድርገው የሚቆጥሩ “ራስ አምላኪዎችን” ማየት በእጅጉ ያሳዝናል። በውበት ወይም በስኬት መመካትም ከዚህ ይመደባል። በሥራ/ሙያና በትምህርት ደረጃ የተነሳ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግም እንዲሁ።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል (ማቴ 23:12)” እንዳለው ራስን ከፍ ማድረግ ለውርደት ይዳርጋል። ሳጥናኤል ከክብሩ የተዋረደው ራሱን አምላክ አድርጎ በመቁጠር ነበር። ዛሬም ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ዕድል ፈንታቸው ይኸው ነው። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሁታን ግን ጥበብን፣ ክብርንና ሞገስን ይሰጣል።

ራስን ብቻ መውደድ፡ ራስን ማምለክ ከሚገለጥባቸው መንገዶች መካከል ሁለተኛው ለሁሉ ነገር እኔ፣ ሁሉም ነገር የእኔ፣ ሁሉም ነገር ለእኔ፣ ሁሉም ነገር በእኔ ማለት ነው። ጌታችን “እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አሳብህ በፍጹም ነፍስህ ውደድ” ያለውን ወደጎን ትቶ ራስን ብቻ መውደድ ጣዖት አምልኮ ነው። እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ትዕዛዝ ረስቶ ራስን ብቻ መውደድ ጣዖት አምልኮ ነው። ወገን እየተቸገረ እኔ ይድላኝ፣ ወገንህ እያዘነ እኔ ልደሰት ማለት ራስ አምላክነት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በዘመኑ እንዲህ ያሉትን “ሆዳቸው አምላካቸው (ፊልጵ 3:19)” ሲል ገልጿቸዋል። እነዚህ ከሆዳቸው (ከራሳቸው ፍላጎት) ሌላ አይታያቸውም። የሚኖሩለት ዓላማም ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ብቻ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ስለዚህ ነው ‘ሆዳቸው አምላካቸው’ የተባሉት።

በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ‘ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ (ሮሜ 16:18-19)” በማለት እውነተኛውን ትምህርት የሚቃወሙትንና መለያየትን የሚሰብኩትን “ለገዛ ሆዳቸው የሚገዙ” እንደሆኑ አስተምሯል። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው።

ነውርን እንደ ክብር መቁጠር: ሌላኛው ሰው ራሱን ማምለክ የሚገለጥበት ነውርን እንደ ክብር መቁጠር ነው። መዋሸትንና ማታለልን እንደ ስልት(strategy)፣ ኃጢአትን እንደ ጽድቅ፣ መጉዳትን እንደ መጥቀም፣ መግደልን እንደ ማዳን፣ ማስራብን እንደ ማብላት፣ ማሰቃየትን እንደ መንከባከብ የክብር ምንጭ አድርጎ መቁጠር ነውርን ማምለክ ነው። “አትግደል” የተባለውን አምላካዊ ትዕዛዝ እያወቁ ጦርነት የሚሰብኩ፣ በሰው ልጅ ሞት የሚሳለቁ፣ መግደልን እንደ ጀግነት የሚቆጥሩ፣ ይህንንም እንደ መልካም ሥራ በቪዲዮ ቀርፀው የሚያሰራጩ ነውር አምላኪዎች ናቸው። መሥረቅን እንደሥራ ቆጥረው፣ የራሳቸው ያልሆነን ሀብት ልክ እንደራሳቸው አድርገው እያሰቡ የሚመጻደቁም ከእነዚህ ወገን ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዮስ መልእክቱ “ክብራቸው በነውራቸው (ፊልጵ 3:19)” በማለት የገለፃቸው እነዚህን ነውረኞችና ነውር አምላኪዎችን ነው።

በሌላም በኩል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም (ሮሜ 1:28-32)” በማለት ያስተማረው እነዚህን ይመለከታል።

ራሳቸውን የሚያመልኩና ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ እርስ በእርስ ይመሰጋገናሉ። ጌታችን ስለ እነዚህ ሲናገር “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? (ዮሐ 5:44)” ብሏል። አንዱ ሌላውን በሠራው ነውር ሲያመሰግነው ይውላል። በዚህም በጽድቅ ሥራ ከእግዚአብሔር ከሚገኘው ክብር ይልቅ ከሰው የሚገኝ ምስጋናን ፈልገዋልና ራሳቸውን የሚያመልኩ ናቸው። እግዚእብሔርን የሚያመልክ ሰው እንኳን ለነውር ሥራ ለጽድቅ ሥራም ቢሆን ምስጋናን ከሰው አይጠብቅምና። ስለሆነም ራሳቸውን የሚያመልኩትን የሚያስመልኩትን ነውረኞች የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” ልንላቸው ይገባል።

ዘመናዊ ጣዖት 6: የሀገር/የብሔር አምልኮ

ሀገርንና ወገንን መውደድ ተፈጥሮአዊና ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ነው። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ፈጠረ። የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ ሲመጡ ደግሞ ቦታን በማካለል ሀገራትን ፈጠሩ፣ ተመሳሳይ ባሕል ያላቸው በአንድነት በመሆንም ‘ብሔር’ ተባሉ። ሁሉም ሀገር፣ ሁሉም ብሔር እግዚአብሔር ከፈጠረው የተገኘ ነው። በምድር ላይ ከሚኖር አንድ ክርስቲያን የሚጠበቀው ሁለቱንም መውደድ ነው። እውነተኛ ክርስቲያን የሰውን ልጅ ሁሉ ስለሚወድ ሀገሩንም ብሔሩንም ይወዳል። እዚህ ላይ ሀገር ስንል በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ፣ ብሔርም ስንል በእያንዳንዱ ብሔር ስም የሚጠራውን ሕዝብ ማለታችን ነው። በመንፈሳዊ አተያይ ሁለቱም ሕዝብ ናቸውና። ፖለቲካዊ ድንበር በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የለውምና። በሌላው ገጽታ ሰው ሀገሩን ይውደድ ሲባል የሌላውን ሀገር አይውደድ ማለት አይደለም፣ ብሔሩን (ወገኑን) ይውደድ ማለትም ሌላውን ብሔር አይውደድ ማለት አይደለም። በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢፅ ሕግ ይመራ ማለት እንጂ።

በዘመናችን ግን ሀገርን ወይም ብሔርን የማምለክ ዝንባሌ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ዘንድ ይስተዋላል። ይህም ለእግዚአብሔር ካላቸው ፍቅር ይልቅ ለሀገር ወይም ለብሔር ያላቸው ፍቅር ሲበልጥ፣ ለሰው ልጅ ካላቸው ፍቅር ይልቅ ለሀገር ወይም ለብሔር ርዕዮት ያላቸው ፍቅር ሲበልጥ፣ ለመንፈሳዊ ሕግ ከመታመን ይልቅ ለወገንተኝነት መታመን ሲበልጥ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊ ላልሆነ ዓላማ ሲውል የጣዖት አምልኮ ይሆናል። የሀገር አምልኮን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶችን ማቅረብ ቢቻልም ለዚህች ጦማር ግን ጥቂቶችን እንጥቀስ።

በስብከት፣ በመዝሙራትና በየሚዲያው በመንፈሳዊነት ስም የሚነሳው “የሀገር ትንሣኤ” አንዱ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ በሚሰበክባት፣ ትንሣኤ ሙታንም ተስፋ በሚደረግባት ኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገር ትንሣኤ (ለዚያውም የሚናፈቅ ታሪክ መኖሩ እንኳን ሳይረጋገጥ) መስበክ የጣዖት አምልኮ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያዊትና ሰማያዊት የሆነችዋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን “ሀገር ናት” (የሀገር ትርጉም አሻሚ ነው) ብሎ ማሰብና መግለጽ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሀገር አምልኮ ከመቅናት የሚመነጭ ነው። ክርስቶስን የዓለም ብርሃን ብላ በምትሰብክ ቤተ ክርስቲያን (እርሱ ‘የዓለም ብርሃን ነኝ’ እንዳለው)፣ ቅዱሳን ሐዋርያትንም የዓለም ብርሃን ብላ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን (‘እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ’ ያለውን መሠረት አድርጋ) በዚህ ፈንታ አንድን ሀገር “የዓለም ብርሃን” (ለዚያውም በክፋት፣ በሰው ሰራሽ ረሃብና በጦርነት የሚታወቅን ሀገር) ብሎ ‘ማስተማርም’ ከዚሁ የሀገር አምልኮ ይመደባል።

በተመሳሳይ መልኩ የብሔር አክራሪነት የተጫናቸው ግለሰቦች እንደሚያደርጉት ብሔርን ከሁሉም በላይ፣ ከሁሉም በፊት አድርጎ ማሰብ የጣዖት አምልኮ ነው። የሁሉም የበላይ፣ የሁሉም መጀመሪያና የሁሉም መጨረሻ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። በተለይም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ እኔን ምሰሉ” ብሎ ባስተማረው መሠረት ክርስቶስን መምሰል ያለባት ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር “የእኔን ብሔር መምሰል አለባት” ማለት የጣዖት አምልኮ ነው። በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የታነፀች ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋ የየማኅበረሰቡን ባሕል የዋጀ መሆን ቢገባውም ሁለመናዋ በተወሰነ ባሕል ብቻ መታጠር የለበትም። ይልቁንም ሰማያዊነትን፣ መንፈሳዊነትና ዓለም አቀፋዊነትን የሚያንፀባቅ መሆን ይኖርበታል እንጂ። ስለሆነም የመስፍነ እስራኤል ኢያሱን ቃል በመዋስ “ተስፋ የምታደርጉትን ሀገር ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን ሀገረ እግዚአብሔርን ተስፋ እናደርጋለን” ልንላቸው ይገባል።

ዘመናዊ ጣዖት 7: ሰይጣንን ማምለክ

እግዚአብሔር ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በመጀመሪያ አምላክ ነኝ ብሎ የተዋረደው፣ ኋላም የሰውን ልጅ አምላክነትን እንዲመኝ አድርጎ ከገነት ያስወጣው፣ ሐሰት ከራሱ አፍልቆ የሚናገር የሐሰት አባቷ፣ ክፋትን ሲፈጥር የሚውል የክፋት ደራሲ ሰይጣን/ዲያብሎስ ነው። ጌታችን እንደተናገረው የዲያብሎስን ሥራ መሥራት (እርሱን በግብር መከተል፣ አብነት ማድረግ) የዲያብሎስ ልጅነት/አምላኪነት ነው። በአንደበት “እክህደከ ሰይጣን” እያሉ በተግባር ግን የሰይጣንን ሥራ መሥራት ዘመናዊ የጣዖት አምልኮ ነው። በአንዳንድ ምዕራባውያን ፈላስፋዎች የሚቀነቀነውን ዲያብሎስን “የመጀመሪያው የነፃነት ታጋይ” የሚለውን አስተሳሰብ መግዛትም እንዲሁ።

ጌታችን በትምህርቱ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፣ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፣ እውነትም በእርሱ ዘንድ ስለሌለ አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።(ዮሐ 8:44)” ሲል ያስተማረው በግልፅ ዲያብሎስን የሚያመልኩትን ይመለከታል። ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልዕክቱ “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” (1ኛ ዮሐ 3:8-10) ሲል የገለፃቸው እነዚህን ነው። ቅዱስ ጳውሎስም ኤልማስ የተባለውን ጠንቋይ “የዲያብሎስ ልጅ” (ሐዋ 13:10) ሲል የገለፀው ይህን አምልኮ ያሳያል።

በወንጌል “ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፥ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።” ተብሎ እንደተጻፈ ጌታን ሳይቀር በአምልኮ የፈተነ ዲያቢሎስ ዛሬም የሚመለክብትን የተለያየ ስልት እየቀየሰ ራሱን ያስመልካል። በራዕይም “ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል፧ እያሉ ሰገዱለት።…ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል። …ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።” (ራዕ 13:4-12) ተብሎ እንደተጻፈው በመጨረሻው ዘመን ዲያብሎስን ማምለክ ይበዛል። ስለዚህ ዲያብሎስን በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም መካድ ይኖርብናል።

ማጠቃለያ

ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮዋ፣ በአምልኮቷ፣ በምዕመናንና አገልጋዮቿ ሕይወት ትመዘናለች። እነዚህን የተቀደሱ አገልግሎቶቿን ከቅዱሳት መጻሕፍት መመዘኛዎች የሚለይ፣ ከመንፈሳዊ ተልዕኮዋ የሚያስወጣ ልዪ ልዪ ልማድ በሂደት ገንግኖ የዘመናዊ ጣዖት አምልኮ መገለጫዎችን እየያዘ መምጣቱን በዚህች ጦማር አሳይተናል። እነዚህን የዘመናዊ አምልኮተ ጣዖት ቅሪቶች መለየትና በጥንቃቄ ማስወገድ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከሚገደው ሁሉ ይጠበቃል። ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው “ካህናት ሆይ ብሩሃን የእግዚአብሔር ዓይኖች እናንተ ናችሁ። እርስ በርሳችሁ አንዱ ካንዱ ጋር ተመለካከቱ፣ ከወገናችሁ ውስጥ በፈሊጥ መርምሩ” በማለት ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎች ተቀላቅለው ቤተ ክርስቲያንን እንዳያውኩ መመርመር እንደሚገባ የነገረንን መተግበር ይገባል። እንዲሁም “የቤተ ክርስቲያን መብራት አገልጋዮቹዋም የምትሆኑ ዲያቆናት ሆይ ተኩላ ከበግ ጋራ፣ ጭላት ከርግብ ጋራ፣ ክርዳድ ከስንዴ ጋራ እንዳይኖር ከውስጥዋ ንቀሉ። እናንተስ የውስጡን ያይደለ የአፍኣውን መርምሩ፣ የውስጡን ግን እግዚአብሔር ያውቃል፣ በራሱ መብራትም ይመረምራል።” እንደተባለ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በጉልህ የሚታዩትን የዘመናዊ ጣዖት አምልኮ ምልክቶች በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መብራትነት ልንመረምራቸው፣ ልንነቅላቸው ይገባል። መስፍነ እስራኤል ኢያሱ በቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያሱ 24:15) እንዳለ እኛም የምናመልከውን ዛሬ እንምርጥ። እግዚአብሔርንና ጣዖትን አብሮ እያመልኩ ክርስትና የለም። ታዋቂነትና ዝና፣ ፖለቲካዊ አመለካከት፣ ስልጣንና ኃይል፣ ገንዘብና ሀብት፣ ራሳችንም እናልፋለን። የማያልፈው እግዚአብሔር ብቻ ነው። መጽሐፍ “ለእግዚአብሔር ስገድ፣ እርሱንም ብቻ አምልክ” እንዳለው በማስመሰል ተቀላቅለው መንፈሳዊ አምልኮአችንን የሚያቆሽሹትን ዘመናዊ ጣዖታትን ተጠይፈን ዘላለማዊውን አምላክ ብቻ አምልከን የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ እንድንተጋ የአባቶቻችን፣ የእናቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን።