በመንፈሳዊ አገልግሎት ካባ ግለሰባዊ ታዋቂነትና ዝነኝነት ሲገነባ

ምክንያተ ጽሕፈት

ዝነኝነት (celebrity) እና ታዋቂነት (popularity/fame) በዓለም ያሉ በተለይም የጥበብ ባለሙያዎች የሚተጉለት፣ ኮትኩተው የሚያሳድጉት፣ አሳድገው የሚንከባከቡት፣ ተንከባክበውም ፍሬውን የሚያፍሱበት እሴት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ የዝነኝነትና የታዋቂነት ስነ-ልቡና ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችም እየተዛመተ ይገኛል። በተለይም በሰባክያንና በግል ዘማርያን ዘንድ ይህንን ስነ-ልቡና የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች በየአውደምህረቱና በየማኅበራዊ ሚዲያው ይስተዋላሉ። አንዳንድ አገልጋዮች ታዋቂነትን የሚፈልጉት ለተሻለ አገልግሎት ሳይሆን በተለይም የተሻለ ገንዘብ ለማፍራት፣ ቅንጡ እንክብካቤ ለማግኘት፣ በፓለቲካ ሲሳተፉ ደጋፊን ለማብዛትና ሌሎችንም አላፊ ነገሮችን ዒላማ በማድረግ ነው። ለዚህም ቤተክርስቲያንን ከሕዝብ የመተዋወቂያ መድረክ እያደረጓት ይገኛሉ። ታዋቂ ነን ብለው የሚያስቡትም ራሳቸውን “ጥቃቅን አማልክት” አድርገው ሌላው እንዲያመልካቸው ይጠብቃሉ። ገንቢ አስተያየት የሚሰጣቸውም “የፈጣሪን ስም እንደተሳደበ” ተቆጥሮ በደጋፊዎቻቸው የስድብና የግልምጫ ናዳ ይወርድበታል። ይህም ልማድ እውነተኛውን መንፈሳዊ አገልግሎት በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል። በዚህች የሁለተኛ ዓመታችን የመጨረሻዋ በሆነችው የአስተምህሮ ጦማር የዝነኝነትንና የታዋቂነትን ምንነትና በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ተዳስሷል።

ታዋቂነትና ዝነኝነት

“ታዋቂነት” የአንድን ሰው በብዙ ሰዎች ዘንድ መታወቅን ያመለክታል። ሰዎችም በብዙ ምክንያት (በመልካምም በመጥፎም ነገር) ታዋቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ዝነኝነት ደግሞ በብዙ ሰዎች ዘንድ ዝናን፣ መሞገስንና መወደስን ያመለክታል። የሰው ልጅ በሚሠራው ሥራ በሰዎች ዘንድ ሊታወቅ፣ ሊወደድና ሊደነቅ ወይም ሊጠላ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ለመወደድና ለመደነቅ መስራት የተጠላ ቢሆንም በዓለማውያን ዘንድ ግን ይህ ታላቅ ዋጋ ይሰጠዋል። ምክንያቱም ይህ ታዋቂነትና ዝነኝነት በተመልካች ላይ ተፅእኖን ስለሚፈጥር በተለይ በማስታወቂያ ሥራ ወደ ገንዘብ ሊቀየር የሚችል ሀብት ስለሆነ ነው። ከሥራቸው ፀባይም የተነሳ ሳይፈልጉት ታዋቂ የሚሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል የሚዲያ ባለሙያዎችን፣ የፊልም ተዋንያንን እና የእግር ኳስ ተጫዋቾችን መጥቀስ እንችላለን። እነዚህ በሥራቸው ቢታወቁም መታወቃቸው በሥራቸው እንዲተጉ የበለጠ ብርታትን ይሰጣቸዋል ተብሎ ይታሰባል።

በዓለማዊው ሕይወት ታዋቂነት/ዝነኝነት የራሱ የሆኑ መልካምና መጥፎ ጎኖች አሉት። ታዋቂ የሆኑ ሰዎች በሄዱበት በሰዎች ዘንድ ልዩ ከበሬታን ያገኛሉ። ብዙ ሰው ያውቃቸዋል፣ ያደንቃቸዋል፣ ያወድሳቸዋል። ታዋቂ መሆንም ብዙውን ጊዜ ብዙ ሀብት የማግኛ ዕድሎችን ሊከፍት ይችላል። ከዚህም የተነሳ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ሀብታም ይሆናሉ። በአንጻሩ ታዋቂ ሰዎች ማንኛውም ሰው የሚያደርገውን ነገር የማድረግ ነፃነት የላቸውም። የፈለጉትን የመናገር/የመጻፍ፣ የፈለጉትን የመልበስ፣ የፈለጉት ቦታ በፈለጉት ጊዜ የመሄድ ነፃነታቸው የተገደበ ነው። የጥፋተኛች ወጥመድ ዒላማ የመሆን ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው። ብዙ የይምሰል ጓደኞችም ስለሚኖራቸው የልብና የአፍ ጓደኞቻቸውን ለመለየት ይቸገራሉ። በሚያደርጉት ጥቃቅን ጥፋት ሁሉ ሰው በሩቅ ሆኖ ይፈርድባቸዋል።  በአጠቃላይም ግላዊ ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ሰውን ለማስደሰት (አድናቆትን ለማትረፍ ወይም ላለማጣት) ብለው ይኖራሉ። እውነትን ለመናገር እንኳን ብዙ ይፈተናሉ። ስማችን በመጥፎ  እንዳይነሳ ብለውም ብዙ ይጨነቃሉ። በዚህም የተነሳ በአእምሮ ሕመም የሚጠቁ ታዋቂ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።

ታዋቂነትን ለማትረፍ የሚደረግ ፉክክር

በሰዎች መታወቅ በራሱ ኃጢአት አይደለም። በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም እውቅናን መፈለግ፣ እውቅና ለማግኘት መሮጥና እውቅናን ማምለክ (personality cult) ግን ትልቅ ኃጢአት ነው። በዘመናችን በሰፊው እንደምናየው “ታዋቂ” ወይም “ዝነኛ” ሰባኪ ወይም ዘማሪ ለመሆን የሚደረግ ሩጫ በዝቷል። ይህም የውድድር መንፈስን ስለፈጠረ አስበውበትና አቅደው፣ የሰው ኃይል አሰማርተው ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ፣ አገልግሎቱን ያስተዋወቁ መስለው ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ ሰባክያንና የግል ዘማርያን በዝተዋል። “ድንቅ ስብከት” እያሉ፣ “ምርጥ ሰባኪ” እየተባሉ፣ የቀሚስ ቀለም እየቀያየሩ፣ የስብከት ርዕሶችን በሳቢና ማራኪ ቃላት እያስዋቡ ራሳቸውን የሚሸጡ ተበራክተዋል። ከስብከታቸው ተወዶልናል ብለው የሚያስቡትን፣ ከምስላቸው (ፎቶአቸው) ሳቢውን በመለጠፍ በሰዎች ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚደክሙ ሰባክያን ተፈጥረዋል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በፕሮቴስታንት ፓስተሮች ላይ ብቻ ይታይ የነበረው ይህ ካፒታሊዝም የወለደው የመታየት ጥማት አሁን በኦርቶዶክሳዊ አገልግሎቶች ላይም ጎልቶ የሚታይ ነውር ነው። የሰባክያንን ፖስተሮችና የስብከት ቪዲዮ ያየ ሰው ይህንን እውነት ማረጋገጥ ይችላል። ከልባቸው ንፅሕና ይልቅ ለልብሳቸው ቀለም የሚጨነቁ፣ መንፈሳዊውን ትምህርት ከማሳወቅ ይልቅ ማወቃቸውን ለማሳወቅ የሚደክሙ፣ ከምስጢር ይልቅ ለቃላት ውበት ትኩረት የሚሰጡ የውዳሴ ከንቱ አገልጋዮችን መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በመዝሙር ዘርፍም እንዲሁ ከዘፈን የተሸቀጡ መዝሙሮችን ለማስተዋወቅ የሚደረገው ሩጫ፣ የፈጣሪን ሥራና የቅዱሳንን ክብር እየተናገሩ ከመዘመር ይልቅ “እኔ እኔ፣ የኔ የኔ” በምትል ራስ ወዳድ ቃል መዝሙር በማሰራጨት ሰበብ የራሳቸውን ዝና እና ታዋቂነትን የሚፈልጉ የግል ዘማርያን ተፈጥረዋል። ይህንን ለመረዳት የመዝሙር ፖስተሮችን ማየት በቂ ነው። ፖስተሮቹ ትኩረታቸው የዘማሪው አለባበስና ተክለ ሰውነት ላይ እንጂ የመዝሙሩ ይዘት ላይ ስላልሆነ ዘፋኞችንና ዘፈናቸውን ከሚያስተዋውቁ ፖስተሮች ብዙም አይለዩም። ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖችም ታዋቂ ሰባኪ/ዘማሪ ሲመጣ የሚመጡት ሲሄድ አብረው የሚሄዱት በዚሁ ምክንያት ነው። ሰባኪውና ዘማሪውም ይህንን ልማድ ከመገሰፅ ይልቅ የታዋቂነትና የዝነኝነት መለኪያ አድርጎ የማየት መንገድ ሰፍቷል። አንዳንዶቹም ያላቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮችና የሸጧቸውን መዝሙርና ስብከቶች ብዛት እየጠቀሱ “እኔኮ ቀላል ሰው አይደለሁም” የሚል ንግድ ውስጥ ያለሀፍረት ገብተዋል።

ለሰባኪ ወይም ዘማሪ በአገልግሎቱ ምክንያት መታወቅ አንድ ነገር ነው። ለመታወቅ/ለመታየት ብሎ መስበክ፣ መዘመር፣ በየማኅበራዊ ድረ ገፅ ራስን ማስተዋወቅ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። ልዩ ልዩ ክስተቶችን እንደ ልዩ አጋጣሚ በመውሰድ ራሳቸውን የሚሸጡም እንዲሁ በዝተዋል። የሆን ሀገራዊ ችግር ሲደርስ የስብከት ርዕስ፣ አዲስ ነጠላ መዝሙር፣ የግጥም መነባንባቸውን ይዘው ብቅ የሚሉ በዝተዋል። “ተዓምር” ተከሰተ ከተባለ “ተዓምሩን እናብራራለን” የሚል ማስታወቂያ በመልቀቅ ምልክት ፍለጋ የሚባክነውን ትውልድ ለመሳብ የሚሞክሩም አሉ። በተለይም ጉዳት የደረሰባቸው ምዕመናንን እና አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠቀሚያነት የሚያውሉ ይታያሉ። በሰው ሀዘን ላይ ለመነገድ ከመሞከር በላይ ምን በደል አለ? የአገልግሎት ዓላማ መታወቅና ዝነኛ መሆንን ያነገበ ሲሆን የክርስትናን መስመር የሳተ ይሆናል የምንለው ለዚህ ነው። በተለይም ታዋቂ ሆኖ ለመቆየት የሚደረገው ሩጫ ሲታይ አንዳንድ ጊዜ የፋሽን ውድድር ይመስላል።

ራስን ከማሳወቅ ይልቅ መንፈሳዊ ምግባራትን በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ወይም በመንፈሳውያን የክርስቲያኖች አንድነቶች (ለምሳሌ ገዳማት፣ ማኅበራት፣ ሰንበት ት/ቤቶች) በኩል መፈፀምና ከግለሰቦች ይልቅ እነዚህን ኅብረቶች የትኩረት ማዕከል (centers of attention) ማድረግ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮና ከቀደሙ ቅዱሳን ሕይወት ጋር የተስማማ ነው። ይህንንም ለማስረዳት ከቀደሙ መልካም አገልግሎቶች ሁለት ማሳያዎችን በማንሳት በዘመናችን ካሉ “የታዋቂነት ሽሚያ” ካደከማቸው አገልግሎቶች ጋር በማነፃፀር እናቅርብ።

አስረጂ እውነታዎች
ማሳያ አንድ: ጠበልና አጥማቂዎች በቤተክርስቲያን

በተባረከ ውሀ (ጠበል) በደዌ ሥጋና በደዌ ነፍስ የተያዙትን መፈወስ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከምትታወቅባቸው መንፈሳውያን አገልግሎቶች አንዱ ነው። በቀደሙት ዘመናት ጠበሉ የሚታወቀው በአጥቢያው ታቦት ስም ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በአገልግሎት ካባ ታዋቂነትና ዝነኝነትን በመገንባት የሚታወቁ ሰዎች ራሳቸውን “አጥማቂ”፣ “ፈዋሽ” በማለት እየጠሩ በጠበል ቦታዎች የሚደረጉ አገልግሎቶችን በመጥለፍ የግለሰብ ዝና ማዳበሪያ እያደረጓቸው ነው። ማንም በእነርሱ “ተጠምቆ” ቢፈወስ የተፈወሰበት ጠበል መታሰቢያ የሆነውን የክፍሉን ታቦት (ቅዱስ) ስም አያነሳም። “ፈውሱ” “ከአጥማቂው ጸጋ” ጋር የተገናኘ ተደርጎ ለታዋቂነት ግብዓት ስለሚውል አጥማቂውን በልዩ ልዩ መልክ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እየከፈሉ እንደ ዘፋኝና አርቲስት በየከተማውና በውጭ ሀገራት ባሉ የተሻለ ገንዘብ በሚገኝባቸው ቦታዎች መዘዋወር የተለመደ ሆኗል።

ይህን ጦማር የምታነቡ ሁላችሁ በዓይነ ህሊና ሁለትና ሦስት ዐስርት ዓመታትን ወደኋላ ተመለሱና “በጠበል ቦታዎቻችን ስለ ጠበሉና ታቦቱ ይነገር ነበር ወይስ ስለ አጥማቂዎቹ?” ብላችሁ ጠይቁ። መልሳችሁ የመጀመሪያው እንደሚሆን መገመት አይከብድም። አሁንስ? አሁንማ “ጸጋ ያላቸው አጥማቂ አስመጥተናል” የሚሉ የድለላ ንግግሮች በበርካታ ኦርቶዶክሳዊ አጥቢያዎች እየተለመዱ የመጡ ፕሮቴስታንታዊ አረሞች በርክተዋል። በአገልግሎት ካባ ታዋቂነትና ዝነኝነትን መገንባት ካፒታሊዝም የወለደው፣ የታዋቂነት ባህል (celebrity culture) ያገነነው ክፉ ልማድ ነው።

ማሳያ ሁለት: የኅብረት ወይስ የተናጠል አገልግሎት?

በቤተክርስቲያናችን አብዛኛው አገልግሎት በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ በኅብረት የሚፈፀም ነው። ከጸሎተ ቅዳሴ ጀምሮ ያሉ አገልግሎቶች ሁሉም እንደ አቅሙ የሚሳተፍባቸው እንጂ አንድን ግለሰብ ወይም የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ማዕከል ያደረጉ አይደሉም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለህዝብ ተደራሽ በሆነ አሰራር የሚፈፀሙ የመዝሙርና የትምህርት አገልግሎቶችም የዚህ የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ልማድ (church tradition) ነፀብራቅ መሆን አለባቸው። ይሁንና ከተወሰኑ የአገልግሎት ማኅበራት አጥጋቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ውጭ በዘመናችን ገኖ የሚታየው የግለሰብ ሰባክያንና ዘማርያን ስብእና ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ነው። በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚደረጉ ሰርክ ጉባኤያት እንኳ በደላላ አሠራር የሰባኪውን ታዋቂነት ለመገንባት ሲባል “የእገሌ ጉባኤ” እያሉ የመጥራት ክፉ ልማድ የዚህ ማሳያ ነው። በመዝሙርም በኩል መዘምራን በኅብረት ከመዘመር ይልቅ ድምፁ ያምራል ወይም ለንግድ የሚመች ቀሚስ ይለብሳል ተብሎ በሚታወቅ ሰው ስም “የእገሌ መዝሙር ይቀርባል” ማለት እየተለመደ ነው። ይህን መሰል ልማድ በተንሰራፋባቸው ቦታዎች አገልጋይ ሊሆኑ የሚገባቸው ሰዎች (መምህራንና ዘማርያን) ራሳቸው አገልግሎት (የትኩረት አቅጣጫ) ሲሆኑ ይስተዋላል።

በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ በሀገራችን ኢትዮጵያ የነበሩ ኦርቶዶክሳዊ አገልግሎቶችን አሁን ካሉት አገልግሎቶች ጋር ብናነፃፅረው በአገልግሎት ካባ የግለሰቦችን ዝናና ታዋቂነት የመገንባት ክፉ ልማድ ያደረሰብንን መንፈሳዊ ኪሳራ ለመረዳት ይጠቅማል። በቀደመው አገልግሎት የካሴት መዝሙሮች በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራን በኅብረት ይቀርቡ ነበር። ምዕመናንም መዝሙሩ ላይ እንጂ መዘምራኑ ላይ ትኩረት አያደርጉም ነበር። ከእነዚያ መዘምራን አንዳንዶቹ በጊዜ ሂደት ከመንፈሳዊ መስመር ቢወጡ በምዕመናን ህይወት ላይ ብዙም ተፅዕኖ አይኖረውም ነበር። ቀስ በቀስ ግን ይህ የአገልግሎት መስመር ተቀየረ። መዝሙርና ስብከትም አገልግሎት ሳይሆን “ሙያ” (profession) መሆን ጀመረ። የምዕመናንም ትኩረት ትምህርቱ ወይም መዝሙሩ ላይ ሳይሆን መምህሩ ወይም ዘማሪው ላይ ሆነ። ይህም በምዕመናን ስህተት ብቻ የመጣ ሳይሆን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሚከተሉት የማስተዋወቅ መንገድ (publicity approach) የተነሳ ነው። ውጤቱ ምን ሆነ? ታዋቂ የተባለው ሰባኪ ወይም ዘማሪ መናፍቅ ሲሆን መናፍቅ የሚሆኑ፣ በሌሎችም መንገዶች ተከትለው ገደል የሚገቡ ምዕመናን በዙ።

በቀደሙት ዘመናት በርካታ ካህናትና ምዕመናን በሰንበት ት/ቤትና በመሰል የአገልግሎት ማኅበራት ዘመን የማይሽራቸው አገልግሎቶችን ፈፅመዋል። በአገልግሎቱም የሰንበት ት/ቤቱ ወይም የአገልግሎት ማኅበሩ እንጂ የግለሰብ አገልጋዮቹ ስም የሚገንንበት አሠራር በብዛት አልነበረም። የዚህም ምክንያቱ “የከንቱ ውዳሴ” ምንጭ ነው የሚል ፍፁም መንፈሳዊ እይታ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እነዚህ የኅብረት አገልግሎቶች እየቀነሱ ነው። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ጥሩ ስፍራ የነበራቸው፣ በተነፃፃሪነትም አንጋፋ ሊባሉ የሚችሉ ሰንበት ት/ቤቶችና የአገልግሎት ማኅበራት ተቋማዊ አቅም እየተዳከመ ወይም በተወሰኑ እውቅና ፈላጊ ግለሰቦች ተጠልፎ እየወደቀ ይታያል። የኅብረት አገልግሎትን ለግለሰባዊ ታዋቂነት የማዋል አሠራር በየቦታው በግልፅ ይታያል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በዚህ መልኩ የተገኘ ታዋቂነትን ለፖለቲካዊ ትርፍ የማዋል እሽቅድምድም ነው።

ታዋቂነትና መንፈሳዊ ሕይወት

ዝነኝነትንና ታዋቂነትን በጽኑ መፈለግ በክርስትና አስተምህሮ ሲመዘን ራስን ከማምለክ ተለይቶ አይታይም። ሰውን በማድነቅ ሱስ መለከፍም እንዲሁ ሰውን በየጥቂቱ ማምለክ ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት ክርስቶስን የመስበክ አገልግሎት ነው። ሰዎች አምላካቸውን እንዲያውቁ፣ እርሱን እንዲያመልኩና ትዕዛዛቱን ጠብቀው እንዲኖሩ ማገዝ ነው። ነገር ግን ሰባኪ ራሱን የሚሰብክ ከሆነ፣ ዘማሪም ስለራሱ የሚዘምርና ራሱን የሚያስተዋዉቅ ከሆነ መንፈሳዊነቱ ምኑ ላይ ነው? ከምንም በላይ የከበረውን የስብከትና የመዝሙር አገልግሎት ራስን ለማስተዋወቅ መጠቀም መንፈሳዊነቱ ምኑ ላይ ነው? አገልጋይ ዓላማው በእግዚአብሔር መታወቅ ሳይሆን በሰዎች ለመታወቅ ከሆነ መንፈሳዊነቱ ምኑ ላይ ነው? አገልጋይ በአገልግሎቱ ሰዎች የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እንዲያደንቁ ማድርግ ሲገባው ራሱ አድናቆትን ለማግኘት የሚሮጥ ከሆነ መንፈሳዊነቱ ምን ላይ ነው? በሰዎች መታወቅንና መደነቅን የሚሻ ሰባኪ/ዘማሪ ለሌሎችስ እንዴት አብነት ሊሆን ይችላል? በዚህም የተነሳ ለእውቅና እና ለዝና የሚሮጡ ወይም ታዋቂ ስለተባሉ ብቻ ተጠርተው የሚመጡ አገልጋዮች መንፈሳዊነት የጎደላቸው መሆናቸውን በብዙ አጋጣሚዎች ተመልክተናል።

ታዲያ ምን ይደረግ?

ለሌላው “ከከንቱ ውዳሴ እንራቅ” እያሉ ራሳቸው ከንቱ ውዳሴን የሚናፍቁና ታላቅ ስጦታ አድርገው የሚቆጥሩ አገልጋዮች ከንቱ ናቸው። “መብራታችሁ በሰው ፊት የበራ ይሁን” የተባለውም ለእነዚህ ዓይነት ለመታወቅ ለሚሮጡ የስም አገልጋዮች አይደለም። በክርስትና የሚያስፈልገው በሰዎች ዝነኛ ወይም ታዋቂ መሆን ሳይሆን ለሰዎች አርአያ/ምሳሌ መሆን ነውና። ሰባኪም ይሁን ዘማሪ ወይም ሌላ አገልጋይ ሊተጋ የሚገባው ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያውቁ ነው እንጂ እርሱ/ሷ በሰዎች ለመታወቅ መሆን የለበትም። መንፈሳዊ አገልግሎቱም ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያውቁ፣ ሥራውንም እንዲያደንቁ እንጂ ሰባኪውን/ስብከቱን ዘማሪውን/መዝሙሩን እንዲያደንቁ አይደለም። ምዕመናንንም ትኩረታቸውን ነገ የሚያልፈውን ሰውና ሥራው ላይ ከማድረግ ይልቅ የዘላለም ሕይወትን ከሚያስገኘው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ሊሆን ይገባል። ሰውን በማድነቅና ታዋቂ/ዝነኛ በማድረግ የሚገኝ መንፈሳዊ ክብር የለምና።

በመንፈሳዊ አገልግሎት ካባ ግለሰባዊ ዝናንና ታዋቂነትን መገንባት በተለመደበት በዚህ ዘመን ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ የሚያስብ ሰው “ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጣል?” ሳይሆን “ማን ያስተምራል?”፣ “ምን ይዘመራል?” ሳይሆን “ማን ይዘምራል?” ብሎ ነው የሚጠይቀው። በጠበሉም በኩል “ለመዳን ወደ ጠበል ልሂድ!” ሳይሆን የሚለው “የትኛው አጥማቂ ጋር ብሄድ እድን ይሆን?” ብሎ ያስባል። ይህ ውሎ ካደረ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ “ማነው የሚቀድሰው?” የሰበካ ጉባዔ አባል ለመሆን “ማነው አስተዳዳሪው?” ንስሐ ለመግባት “የትኛው ካህን ጋር ብናዘዝ ነው ኃጢአቴ የሚሠረይልኝ?” ለመቁረብም፣ ለተክሊልም ወዘተ አገልጋይ መምረጥ ሊከተል ይችላል። ስለዚህ አገልግሎቱን ወደ ጎን ትቶ አገልጋዩን የመከተል አዝማሚያ የሚያመጣው ችግር ከግምት ውስጥ ገብቶ ትምህርትና እርምት ሊሰጥበት ይገባል።

ብዙ ተአምራትን ይሰሩ የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት “እኛም እንደ እናንተው ሰው ነን” (ሐዋ 14:15) በማለት ነበር የሚያደርጉትን ተአምራት አይተው “አማልክት ናችሁ” ላሏቸው ሰዎች የተናገሩት። ሰው ላገለገለው አገልግሎት ምስጋናን ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው መጠበቅ የለበትምና። ከሰው ምስጋናን የሚጠብቅ ሰውን እንጂ እግዚአብሔርን አያገለግልም። ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንዳስተማረን ከሰው ምስጋናን እና አድናቆትን የሚቀበል ሰማያዊ ዋጋን አያገኝም። (ማቴ 6:1-18) አገልግሎቱም ለምድራዊ ታይታ ሆኖ ይቀራል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት (1ኛ ቆሮ 10:31)” እንዳለ መንፈሳዊ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ክብር እንጂ ለአገልጋዮች ክብር፣ ዝና፣ እውቅና መዋል የለበትም። እኛም የራሳችንን እውቀት ሳይሆን የእግዚአብሔርን እውነት እንድናሳውቅ፣ ለራሳችን ዝናና እውቅና ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር አገልግለን የመንግስቱ ወራሾች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት ከእኛ ጋር ይሁን። አሜን!

 

 

1 thought on “በመንፈሳዊ አገልግሎት ካባ ግለሰባዊ ታዋቂነትና ዝነኝነት ሲገነባ

  1. Pingback: ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s