በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
ከሁሉ አስቀድመን ምስጋና የባሕርይው ለሆነው አምላካችን ምስጋናን እናቀርባለን፡፡ በሥራችንም ሁሉ ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ እንዲሆንልንም ዘወትር በፊቱ እንቆማለን፡፡
አስተምህሮ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጡመራ መድረክ ዛሬ ህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ተመሠረተች፡፡ የጡመራ መድረኳ ስያሜ ‘አስተምህሮ’ እንደመሆኑ በዚህ የመጀመሪያው ጡመራችን አስተምህሮ የሚለውን ቃል ትርጉም በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ አስተምህሮ የሚለው ቃል ሁለት ዓይነት ትርጉም አለው፡፡
አስተምህሮ፤ አስተምህሮ ማለት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ማለት ሲሆን ይህም የትምህርቱን ይዘት፣ የይዘቱንም ምንጭ፣ የትምህርቱን አሰጣጥ ስልት፣ የመምህራኑና የተማሪዎቹን መስተጋብር ወዘተ… ያጠቃልላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከሚገለፅባቸው መንገዶች መካከልም የአደባባይ ስበከት (ለምዕመናን የሚሰበከው)፣ የወንበር ትምህርት (በአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው) ፣ ልዩ ስልጠናና (በኮርስ መልክ የሚሰጠው ትምህርት) በመገናኛ ብዙሀን (በጋዜጣ በመጽሔት በድረ ገፅ) የሚሰጡት ትምህርቶች ይገኙበታል፡፡
አስተምሕሮ፤ መሐረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤ አስተምሕሮ ማለት ይቅርታ መጠየቅ /ምልጃ/ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመንም ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡
አስተምህሮ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጡመራ መድረክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት የሚቀርብባትና ወቅታዊ የቤተክርስቲያን መረጃዎችንም ለአንባቢያን የሚሰራጩባት አዲስ ብሎግ ናት፡፡
አስተምህሮም በይዘቷ በመጀመሪያው ላይ በማተኮር ለአንባቢያን ይበጃሉ ይጠቅማሉ ያልናቸውን ትምህርቶችንና ወቅታዊ መረጃዎችን የምናደርስባት አዲስ የጡመራ መድረክ ናት፡፡ በዘመነ አስተምህሮ ስለተመሠረተችም ስያሜዋን “አስተምህሮ” ብለናታል፡፡ ለሁላችንም መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንልን በጸሎታችሁ እንድታስቡንና ገንቢ አስተያየታችሁንም በማጋራቱ በኩል እንዳትለዩንም በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር