መንፈሳዊ አገልግሎትና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም

social mediaመግቢያ

ማኅበራዊ ሚዲያ በልዩ ልዩ ሁኔታ በዘመናችን ታላቅ ተፅዕኖ የመፍጠሪያ መንገድ እየሆነ መጥቷል። የሀገራት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሂደቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ ስር ሲወድቁ እናስተውላለን። ይህ ተፅዕኖ በመንፈሳዊ ሥፍራዎችና አገልግሎቶችም ላይ ይስተዋላል። በተለይም ነገሮችን በመመርመር  አግባብ ባለው ሁኔታ ከመጠቀም ይልቅ በጥራዝ ነጠቅ እይታና በተዛነፈ አስተሳሰብ ማኅበራዊ ሚዲያን በአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ በግብታዊነት መጠቀም ያልታሰቡ ጉዳቶችን ሲያመጣ ማስተዋል እንችላለን።

አንዳንድ አጥቢያዎች ሁሉንም የቤተክርስቲያን አገልግሎት በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ቀጥታ ያስተላልፋሉ። ቅዳሴም፣ ትምህርትም፣ መዝሙርም፣ ማስታወቂያም፣ ምንም ሳይቀር ሁሉም በማኅበራዊ ሚዲያ ይተላለፋል። በንግሥ በዓላትና በአንዳንድ ጉባዔያትም ቪዲዮ የሚቀርፀው ሰው ብዛት ከሚቀረፀው የሚበልጥ ይመስላል ። ሁሉም በየፊናው ያስተላልፋል፣ ያጋራል። የቤተክርስቲያን ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ ማስተላለፍ መልካም ቢሆንም በሥርዓት መመራት ግን ያስፈልገዋል። ቀጥታ የሚተላለፍ፣ ተቀርፆና አርትዖት ተሠርቶበት የሚሰራጭ፣ መተላለፍ የማያስፈልገው አገልግሎት ይኖራል። አንድን አገልግሎት ወደ ሚዲያ ከማምጣት በፊትም መቅደም ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በዚህች አጭር ጦማር እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳለን።

የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ አስፈላጊነት 

ማኅበራዊ ሚዲያ ለመንፈሳዊ ትምህርት አንዱ ጠቃሚ መድረክ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። አጠያያቂው የአጠቃቀሙ ስልትና ሂደት ነው። ተቋማዊ ህልውና ባላት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ስም የተከፈቱና የሚከፈቱ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች የቤተክርስቲያን ሥርዓት፣ ትውፊትና አስተምህሮ የሚተላለፍባቸው ሊሆኑ ይገባል። የቤተክርስቲያንን ስም በያዘ ገፅ ላይ የሚለጠፉ መረጃዎችም እንዲሁ የግለሰብን ሳይሆን የቤተክርስቲያንን ነገር የሚያሳዩ መሆን ይኖርባቸዋል። ወገንተኝነታቸውም በመንፈሳዊ አስተምህሮ ሚዛን እንጂ በግለሰቦችና በቡድኖች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የለበትም። ለዚህም ቢያንስ በአጥቢያ ደረጃ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔው የተስማማበት ማኅበራዊ ድረ-ገፅ አጠቃቀምን የሚመለከት መመሪያ ያስፈልጋል። በዚህ መመሪያም አጠቃቀሙን ሥርዓት ማስያዝ ይቻላል። መመሪያ በሌለበት ሁኔታ የአጠቃቀሙን ሁኔታ በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ የማይቻል ነው። ይሁንና የሚወጡት መመሪያዎች ይዘትና አፈፃፀም በጥንቃቄ ሊቀመርና መንፈሳዊ ዓላማን በዘላቂነት ለማስፈፀም በሚረዳ መልኩ ያለ አድልዎ ሊተገበር ይገባል።

የትኛው አገልግሎት ይተላለፍ/ይለጠፍ?

የማኅበራዊ ድረ-ገፅ አጠቃቀምን በሚመለከት መሠረታዊው ጉዳይ “ምን ይተላለፍ? ምንስ አይተላለፍ?” የሚለው ነው። ቅዳሴ ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ? መዝሙር ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ? ስብከት ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ? የምዕመናን ፎቶ ይለጠፍ ወይስ አይለጠፍ? የሕፃናት መርኃግብር ይተላለፍ ወይስ ይቅር? ምዕመናንና ካህናት ምግብ ሲመገቡ ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ? ምዕመናን ለቤተክርስቲያን ገንዘብ ለመስጠት ቃል ሲገቡ ይተላለፍ ወይስ ተቀርፆ ይቀመጥ? ሕፃናት ሲጠመቁ ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ? ምዕመናን ንስሐ ሲገቡ፣ ሲቆርቡ፣ ምፅዋት ሲሰጡ…ወዘተ ይተላለፍ ወይስ አይተላለፍ (ፎቷቸው ይለጠፍ ወይስ አይለጠፍ) የሚሉ ጉዳዮችን በዝርዝር አይቶ ቢተላለፉ ምዕመናንን የሚያንፁትን፣ ህገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቁትን ለይቶ ሥርዓት ባለው መንገድ የሚተላለፉበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። በአጠቃላይ እይታ ግን ቤተክርስቲያን ለሰው ልጅ የምታስተምረው ትምህርት በማኅበራዊ ሚዲያ ቢቀርብና ለማኅበራዊ ሚዲያ ግብዓት ብቻ ሲባል የተለየ ነገር ባይደረግ መልካም ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፎቶና የቪዲዮ ልክፍት (obsession) የያዛቸው ሰዎች “እስኪ ለፌስቡክ የሚሆን ፎቶ አንሱኝ” እንደሚሉት አገልግሎቱን ሁሉ ለማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ የመቃኘት የታይታ ልማድ እየነገሰ ነው። በተለይም ስብከትና መዝሙርን እንደ መተዳደሪያ የያዙ፣ አገልግሎቱንም መነገጃ ያደረጉ ሰዎች በዚህ የታወቁ ናቸው። ይህ ክፉ ልማድ ከመንሰራፋቱ የተነሳ ብዙዎች የዋሀንም መነገጃውን ልማድ ሥርዓት እያስመሰሉት ይገኛል።

የማስተላለፍ/መለጠፍ ጥቅም

አንድን መርኃግብር ወይም ክስተት የቤተክርስቲያንን ስም በያዘ ማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ለማስተላለፍ/ለመለጠፍ ከመወሰናችን በፈት ማስተላለፍ ወይም መለጠፍ የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድን ነው? ለመድረስ የታለመለት አድማጭ እና/ወይም ተመልካች ማነው? እንዴትስ ነው የሚያንጸው? የሚሉና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል። ትምህርትን በሚገባ አቀናብሮ ማስተላለፍ ያንፃል። እንደወረደ ቀጥታ ማስተላለፍ ደግሞ እንደሰባኪው ሁኔታ እየታየ ቢሆን መልካም ነው። ብዙ ዳህፀ ልሳን ወይም ግድፈት የሚፈጽም ሰባኪ የሚናገረውን ሁሉ ማስተላለፍ ለስህተቱ ዕውቅና ከመስጠት አይተናነስም። በመዝሙሩም ቢሆን ዘፈን የሚመስሉና በጭፈራ የታጀቡትን ማስተላለፍ እንዲሁ ነው። መጥፎ ልማድን የሚያስተምሩትን እየተው የሚጠቅሙትን እየለዩ ማስተላለፍ ይበጃል። የሚተላለፈውን ምስል፣ ድምፅና መልእክት ለመልካም ነገር የሚጠቀም ሰው እንዳለ ሁሉ ያንኑ የሚዲያ ውጤት መንፈሳዊ ላልሆነ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልም ማስተዋልም ያስፈልጋል።

ይሁንታን አለመጠየቅ

ሌላው ጉዳይ በምስል ወይም በምስል ወድምፅ በሚተላለፈው መርኃግብር ላይ የተሳተፉ ሰዎች (በተለይም ሕፃናትና ሕሙማን) ፎቶ ለመነሳት፣ ቪዲዮ ለመቀረፅ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ለማስተላለፍ/ለመለጠፍ ምንም ባልተጠየቁበትና ይሁንታ ባልሰጡበት ሁኔታ መቅረፅም ይሁን በማኅበራዊ ድረ-ገፅ የማስተላለፍ ነገር ነው። ይህ ተግባር ሞራላዊም ይሁን ሕጋዊ መሠረት የለውም። ዛሬ ላይ ምናልባትም አንዳንዶች በቤተክርስቲያኑ ሚዲያ ላይ መታየታቸው ሊያስደስታቸው ይችል ይሆናል። ነገር ግን ልጆች ሲያድጉ፣ ብዙ ነገሮችን ማገናዘብ ሲጀምሩና ሲጠይቁ፣ ወይም በተላለፉ ነገሮች ላይ ክርክር ሲነሳ ይሁንታ ያልተገኘበት ቀረፃም ይሁን ማስተላለፍ ሕጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በዚህን ወቅት ይሁንታን አለማግኘት በራሱ ህገወጥ ሊሆን ይችላል። ይህ ህገወጥነት ደግሞ በቤተክርስቲያን ስም የተፈፀመ ሆኖ ሲገኝ ታላቅ ውርደት ይሆናል።

በተለይም ከፕሮቴስታንታዊ የታይታ ልማድ በተኮረጀ መንገድ የምዕመናንን፣ በተለይም በልዩ ልዩ የመንፈስ ጭንቀት፣ ስጋዊ በሽታና የአጋንንት እስራት የተያዙ ምዕመናንን ኑዛዜ ሳይቀር በካሴት የሚሸጡ፣ በዩቲዩብና በመሳሰሉት መንገዶች መነገጃ ማድረግን እንደ በጎ አገልግሎት የሚደጋግሙ “አጥማቂዎች”፣ “ሰባክያንና” መሰሎቻቸው ጉዳይ የበርካቶችን የግላዊነት መብት በግልፅ የሚቃረን ነው።  ተቸግሮ ለፈውስ የመጣን ምዕመን ያለፈቃዱ እየቀረፁ መነገጃ ማድረግ መንፈሳዊ መሰረት የለውም፣ በምድራዊ ህግም ያስጠይቃል። በዚህ መልኩ የሚሰሩት “አጥማቂዎች” በፕሮቴስታንቶች ዘንድ እንዳሉት መሰሎቻቸው ሁሉ በማስመሰልና በአጋንንታዊ አሠራር ምዕመናንን የሚያደናግሩ ናቸው። ይሁንና ፈውሱ እውነተኛ ቢሆን እንኳ የምዕመናንን የተቀረፀ ቪዲዮ (በተለይም ኑዛዜና ጫጫታ ያለበትን) ያለፈቃዳቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለንግድና ለእውቅና ማግኛ መጠቀም ነውርም፣ ወንጀልም፣ ኀጢአትም ነው።

የማስታወቂያ ጋጋታ

እያንዳንዱን መንፈሳዊ መርኃግብር በፖስተር ላይ እየሠሩ በየቀኑ መለጠፍ የተለመደና ብዙዎችን እያሰለቸ የመጣ ጉዳይ ሆኗል። ቅዳሴ፣ ኪዳን፣ ማኅሌት፣ ጸሎት፣ መዝሙር፣ ስብከት፣ ፅዋ፣ መኪና ማቆሚያ ወዘተ ሁሉ በየቀኑ ማስታወቂያ ተሠርቶላቸውስ እንዴት ይቻላል? የዘወትር/ሳምንታዊ መርኃግብር ለሆኑትስ ሰው አስታውሶ እንዲመጣ ለማድረግ የግድ ፖስተር መለጠፍ ያስፈልጋል? ከዚህም አልፎ እጅግ በተጋነነና የዘፈን ወይም የፊልም ማስታወቂያ በሚመስል መልኩ መምህራንና ዘማርያንን ማስተዋወቅና ገፅታ ግንባታ ማድረግ የቤተክርስቲያን ድርሻ ነውን? የግለሰቦችን ፎቶ ሳይደነቅሩ፣ “ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ” ሳይሉ፣ በባንዲራ ቀለማት ሳያዥጎረጉሩ መንፈሳዊ መልእክትን ብቻ ማስተላለፍስ አይቻልምን? ይህ የፖስተር ፉክክር የሚታይበት አካሄድ ወዴት እንደሚወስደን ቆም ብለን ልናስብ ይገባል።

የ”በተገኙበት” ድራማ

ከማስታወቂያ ጋር ተያይዞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ጉዳይ መንፈሳዊ በዓላትን ለማስተዋወቅ ታዋቂ የሚባሉ አርቲስቶችን፣ ዘማርያን ወይም ዘፋኞችን፣ አትሌቶችን፣ ሰባክያንን፣ ጳጳሳትን ወይም ካህናትን ስም በመጥቀስና ፎቶ በመለጠፍ “በተገኙበት ይከበራል” የሚል አስቂኝ ድራማ ነው። የዚህ ዓይነት ማስታወቂያ ዓላማው ምንድን ነው? በዓላት ካህናትና ምዕመናን ሳይገኙ እንደማይከበሩ እየታወቀ አለባበስና አዘፋፈን ያሳመሩትን ቀሚስ ቀያያሪ የአውደ ምህረት አርቲስቶች ወይም ድራማ በመስራት ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦችን ስም ለመንፈሳዊ በዓል ማድመቂያነት መጥራት በበዓሉ የሚከበረውን ፃድቅና፣ በዓሉን የሚያከብረውን ጌታ መናቅ አይሆንም ወይ? በአንዳንድ ቦታ ታላላቅ ጳጳሳት እያሉ እንኳ “በተገኙበት” “የሚባልላቸው” ካሴት በመሸጥ የሚታወቁት ደላሎች ወይም አርቲስቶች ናቸው። በዚህ መልኩ ማስታወቂያ ሲሰራላቸው የማይቃወሙ፣ በተለይም እንዲሰራላቸው የሚፈልጉ ሰዎች በበዓሉ ከሚከብረው ጻድቅ፣ ከሚመሰገነው ስመ እግዚአብሔር በላይ “ጣዖት” ሆነው መታየት የሚፈልጉ መሆናቸውን መረዳት አይከብድም። ጣዖትን መጣል እንጂ ማድነቅ አያስፈልግም።

ቡድኖችና ቡድንተኝነታቸው

በቤተክርስቲያን አገልግሎት ብዙ ዓይነት መተግበሪያዎችን (apps)/የሚጠቀሙ የሚዲያ ቡድኖችን (online groups) ማየት የተለመደ ነገር ነው። ለምሳሌ ቫይበር፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም ወዘተ ቡድኖች አሉ። እነዚህም የካህናት፣ የሰንበት ተማሪዎች፣ የማኅበራት ወዘተ ቡድኖች እየተባሉ በየስማቸው group የሚከፍቱ ናቸው። ቡድን ሀሳብ ለመለዋወጥ መልካም ነው። በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ግን መንፈሳዊነት ይጎድለውና ተራ ወሬ የሚወራበትና ቡድንተኝነት ተኮትኩቶ የሚያድግበት መድረክ ይሆናል። በተለይም ለየት ያለ ሀሳብ የሚያነሱ ሰዎችን የማያስተናግድ ወይም የሚያጠቃ ቡድን ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ባይኖር ይመረጣል። መንፈሳዊነት የራቀውና ሰዎች እርስ በእርስ የሚመሰጋገኑበት ወይም የሚነታረኩበትና ሰውን የሚያሙበት መድረክም እንዲሁ ለክርስቲያናዊ ሕይወት ብዙም አስተዋጽኦ አይኖረውም።

ግለሰቦችና አቋማቸው

በመደበኛውና በማኅበራዊ  ሚዲያ ስለቤተክርስቲያን ጉዳዮች የራሳቸውን ምልከታ የሚጽፉ ግለሰቦች የሚያንጸባርቁት አቋም የግላቸው እንጂ የቤተክርስቲያን ወይም በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ተቋማት አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንድ ግለሰብ ካህን፣ ሰባኪ/መምህር፣ የሰበካ ጉባዔ አባል ወይም ጥሩ ምዕመን ስለተባለ ብቻ የሚጽፈው ሁሉ ቤተክርስቲያንን ይወክላል ማለት አይቻልም። ይህ በተለይም አንድ ጊዜ የቤተክርስቲያን ጠበቃ፣ ሌላ ጊዜ የሆነ ብሔር ወይም ሌላ ፖለቲካዊ ቡድን መብት ተሟጋች የሚሆኑትን አገልጋዮች ይመለከታል። በስብከታቸው የምናውቃቸው ግለሰቦች ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ያለችሎታቸው በመደዴ እይታ ሲንቦጫረቁ ስናይ ይህ የግል ምርጫቸውና ውሳኔያቸው ተደርጎ መታየት ይኖርበታል እንጂ የቤተክርስቲያን አቋም ወይም የአብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ አመለካከት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። እነርሱም ቢሆኑ በቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው የተነሳ ያገኙትን ተቀባይነት/ዕውቅና ለሌላ ዓላማ ማዋል አይገባቸውም። የሚያሳዝነው እውነታ ግን ቀላል ቁጥር የሌላቸው “አገልጋዮች” አገልግሎታቸውን ለፖለቲካዊ ዓላማቸው መደላድል አድርገው ሲጠቀሙና ፖለቲካዊ ዲስኩራቸውን ከቃለ እግዚአብሔር ጋር ሲያምታቱ ነው። መንፈሳዊ ትምህርታቸውን የሚወደው ምዕመን ፓለቲካቸውንም እንዲወድ መጠበቅም አይገባም፣ ሁለቱ የተለያዩ ናቸውና።

የሚዲያ ፉክክር

አንዳንድ በቤተክርስቲያን ስም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መርኃግብሮች ትኩረት የሚያደርጉት የምዕመኑን ብዛት፣ የዝግጅቱን ድምቀት፣ የሰባኪውን ተክለ ሰውነት ወይም እንቅስቃሴ፣ የዘማርያኑን አለባበስና የአንዳንድ ግለሰቦችን ድምፅና ውበት ማሳየት ላይ ነው። ይህም የማስተላለፉን ዓላማ መንፈሳዊ አስተምህሮን ከማሳየት ይልቅ “የእኛ ከእነርሱ ይበልጣል” በሚል የፉክክር መንፈስ የሚመራ ያስመስለዋል። እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድም ምናልባት ሰውን ወደ ዝግጅቱ ይስብ ይሆናል እንጅ መንፈሳዊ ሕይወትን አያንጽም። የቤተክርስቲያን ዓላማ ደግሞ ቲፎዞ ማብዛት ሳይሆን ክርስቲያኖችን በክርስትና ማጽናት ነው። የቤተክርስቲያን ዓላማ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ወይም የእነርሱን ፍላጎት ማስተዋወቅ ሳይሆን የሰው ልጆች የወንጌልን ቃል እንዲያውቁ፣ እንዲያምኑና እንዲኖሩት ማስቻል ነው። በቤተክርስቲያን ስም በማኅበራዊው ድረ-ገፅ የሚተላለፈው መልዕክትም ይህንን የሚገልጽ ሊሆን ይገባል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ

ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ለምን፣ መቼና ለምን ያህል ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያን ለማየት ሳይወስኑ ለረጅም ሰዓት ስልክ/ኮምፒዮተር ላይ ሆኖ ማኅበራዊ ሚዲያን መመልከት የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ተጠቂነትን ያመለክታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የሚጠቅመውን፣ የማይጠቅመውንና የሚጎዳውን ሳይለዩ በአጠቃላይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቀውን መረጃ ለመመልከት መሞከር ለመንፈሳዊ ሕይወትም፣ ለሥጋዊ ኑሮም ይሁን ለጤንነት ከፍተኛ ጉዳት አለው፡፡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ሊውል የሚችለውን ዕንቁ ጊዜ በከንቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጥፋትና ለመንፈሳዊ ሕይወት ጎጂ የሆኑ ጽሑፎችን (ለምሳሌ ስድብ)፣ የሰዎች መራቆትን የሚያሳዩ ፎቶዎችን፣ ከዝሙት ጋር የተያያዙ ፊልሞችን በማኅበራዊ ሚዲያ ማየት መንፈሳዊ ሕይወትን በእጅጉ ይጎዳል፡፡

አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች፣ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን አስክሬን፣ ሰዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ወዘተ ማየት ደግሞ የአእምሮን ጤንነት ያውካል፡፡ ለብዙ ጊዜ ተቀምጦ የስልክ/ኮምፒዩተር ሰሌዳ (screen) ማየትም እንዲሁ የዓይንን ጤንነት ከመጉዳቱም በላይ ለጤንነት ጠንቅ ለሆነው የውፍረት በሽታ (obesity) ይዳርጋል፡፡ ከኢኮኖሚም አንጻር ሲታይ ሰው ሊሠራበትና ገንዘብ ሊያገኝበት የሚችለውን ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማሳለፉ ለድህነት ይዳርገዋል፡፡ በተለይም በሥራ ቦታ/ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያን መከታተል ውጤታማነትን ቀንሶ ከሥራ እስከመባረርም ሊያደርስ ይችላል፡፡ ከዚህም አልፎ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ማኅበራዊ ሚዲያ መከታተል ቤተሰብን በማግለል የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስ ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው በተለይም ክርስቲያን ማኅበራዊ ሚዲያን ለምን አገልግሎት እንደሚጠቀም፣ ከማኅበራዊ ሚዲያ ምን መረጃ እንደሚፈልግ/እንደሚያስተላልፍ፣ መቼ መቼ እንደሚያይና፣ በየጊዜው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚጠቀም ካልወሰነ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ሱስ የተጠቁ ሰዎችም ልዩ የምክር አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

ማኅበራዊ ሚዲያ ዓለማችንን በአዎንታዊም በአሉታዊም መልኩ እየቀየረ ነው። በቤተክርስቲያናችን የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችም ሆነ ምዕመናንና ምዕመናት በግላቸው ባላቸው ማኅበራዊ ሱታፌ የማኅበራዊ ሚዲያ ሚና እየጨመረ ነው። መንፈሳዊ አስተምህሮን ለማስፋፋት፣ የቤተክርስቲያን ትምህርት ተደራሽነት በመጨመርና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ሚዲያ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይሁንና ከአጥቢያ ጀምሮ ባሉ የቤተክርስቲያን ተቋማትም ሆነ በምዕመናን ግላዊ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እጅግ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። “መታየትን” ግብ ያደረገው የማኅበራዊ ሚዲያ ፍልስፍና “ራስን መግዛትን፣ ከከንቱ ውዳሴ መራቅን” የሚጠይቀውን የክርስትና አስተምህሮ በተግባር እየተፈታተነው ነው። ይህም በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ጀምሮ ባሉ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አካላት በተከፈቱ “የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆች” (accounts) ላይ ይታያል። የትኛው አገልግሎት በምን መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ መተላለፍ እንዳለበት ትልም የሚያሳይ አስተሳሰብና አሠራር ባለመዳበሩ አገልግሎቶቻችን መንፈሳዊነት እየተለያቸው፣ በምድር ሕግ እንኳ የሚያስነቅፉ እየሆኑ ነው። ስለሆነም ማኅበራዊ ሚዲያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በግብታዊነት ከመጠቀም ይልቅ አሠራራችንን መመርመር ይገባል እንላለን። ዘመን ያመጣልንን ቴክኖሎጂ ለአገልግሎት መጠቀም ያለብን ቢሆንም ሕገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንደየዘመኑ ነፋስ መቀየር እንደማይገባን የታወቀ ነውና።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s