መግቢያ
ባለፈው ኅዳር ወር 2012 ዓ.ም. (በፈረንጆቹ አቆጣጠር November 2019) በይፋ የታወቀው COVID-19 የተባለ ወረርሽኝ በበርካታ ሀገራት ብዙዎችን ለሕማምና ሞት ከመዳረጉ ባሻገር በመላው ዓለም ከፍተኛ ጭንቀትና አለመረጋጋትን ፈጥሯል። የዘርፉ ምሁራን ከሚገልጹት የበሽታ አምጭው ተሕዋስ ባሕርይ የተነሣ የበሽታውን መስፋፋት ለመከላከልና ለመገደብ በልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል ሰዎች በአንድ ቦታ በርከት ብሎ መሰባሰብን፣ መጨባበጥና መሳሳምን የመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ መንገዶችን እና መሰል አካላዊ ንክኪ የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን እንደየሁኔታው ማስቀረት፣ መገደብ ወይም በልዩ ጥንቃቄ መፈጸምን ያጠቃልላል። ክርስቲያኖችና በምድር ያለች ቤተ ክርስቲያን በዓለም የምንኖር በመሆኑ እነዚህ አዳዲስ መመሪያዎች ይለመከቱናል። በሽታውም ሆነ በሽታውን ለመከላከል የሚወሰዱት መመሪያዎች በቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎትና በምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ቀጥተኛ ተፅዕኖ አላቸው። አንዳንዶች በሽታውን ለመከላከል በባለሙያ ምክር የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን “የእምነት መጉደል ማሳያ” በማስመሰል የሚጠነቀቁትን ሲነቅፉ ይስተዋላል። በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ከልክ በላይ በመጨነቅ ራሳቸውንና ሌሎችን ይጎዳሉ። እምነት እንደሌላቸው አሕዛብ የእግዚአብሔርን መግቦት፣ ጥበቃና የማይመረመር ቅዱስ ፈቃዱን ዘንግተው በማይገባ ጭንቀት ራሳቸውን ይጎዳሉ። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትና ለጥንቃቄ የሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ መንፈሳዊ ጉዳዮችን እንዳስሳለን።
ወረርሽኝ በቅዱሳት መጻሕፍት እይታ
አምላካችን እግዚአብሔር የዓለማችን አስገኝ፣ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ ነው። ፍጥረታቱን ሁሉ በማይመረመር ጥበቡ ይጠብቃቸዋል፣ ይጠብቀናል። ፍጥረቱን የሚጠብቅ አምላካችን በየዘመናቱ ልዩ ልዩ ሥጋዊ መቅሰፍቶችን አስነስቷል። በቅዱሳት መጻሕፍት ከተመዘገቡት መቅሰፍቶች በመጠኑ ብንመለከት እግዚአብሔር መቅሰፍትን (በሽታን) ለማስተማር፣ ለመገሰጽ፣ ለማስጠንቀቅ እንደሚገልጥ መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ፈርኦንና ሠራዊቱ ሕዝበ እግዚአብሔርን በማስጨነቃቸው ሞተ በኩርን ጨምሮ በዐሥር የተለያዩ መቅሰፍቶች ተመተዋል። (ኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ 7 እስከ 10) በስሙ የሚታመኑትን እስራኤል ዘሥጋን ለመርዳት መቅሰፍትን ያወረደ ጌታ የተዋጋላቸው ምእመኖቹ ጥበቃውንና መግቦቱን ረስተው ባጉረመረሙና ከእምነት ባፈነገጡ ጊዜ በደላቸውን ለማሳሰብ በተናዳፊ እባቦች ቀጥቷቸው ነበር። በንስሐ በተመለሱ ጊዜም የሚድኑበትን የእምነት መንገድ ሰጥቷቸዋል። (ዘኁልቍ 21:4-9) በሌላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ በዘመነ ብሉይ ታቦተ ጽዮንን (የእግዚአብሔርን ማደሪያ) እንዲያገለግሉ የተሾሙት አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ ካህናት በፈጸሙት በደል የተነሣ ሕዝበ እስራኤል የእግዚአብሔር ጸጋ ተለይቷቸው ታቦተ ጽዮንም ተማርካባቸው ነበር። ፍልስጤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት እንደተራ የምርኮ ዕቃ በጣዖት ቤታቸው ባስገቧት ጊዜ ግን እግዚአብሔር ተቆጣ፣ በዕባጭና በመቅሰፍትም መታቸው። መቅሰፍቱ የወረደባቸው የአዛጦን ሰዎችም በምን ምክንያት እንደተቀጡ ዐውቀው “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አትቀመጥ አሉ።” (1ኛ ሳሙ. 5:6-7)። እነዚህን መሰል መቅሰፍቶች በሥጋዊ ጥበብ የምናመልጣቸው አይደሉም። ዓላማቸውም ለሁሉም የተገለጠ ነው። እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ ያስተምራልና።
በሽታ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተላከ መቅሰፍት ነውን?
እግዚአብሔር በመቅሰፍትና በበሽታ የበደሉትን እንደሚቀጣ፣ እምነት የጎደላቸውን እንደሚገስጽ ከላይ ከተጠቀሱት ታሪኮችና ሌሎች በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተክርስቲያን ታሪክ ከተመዘገቡ ታሪኮች እንማራለን። ይሁንና በሰዎች ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ሁሉ “ከእግዚአብሔር የተላኩ መቅሰፍቶች” ናቸው ማለት አይደለም። የሥጋ ሞት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የማይቀር ዕጣ ነው። ይሁንና ሞት ወደእኛ ይመጣል እንጂ እኛ በፈቃዳችን ወደ ሞት አንሄድም፣ ብንሄድም (ራሳችንን ብንገድል) ኃጢአት እንጂ ጽድቅ ሆኖ አይቆጠርልንም። በፈቃዱ ወደ ሞት ሄዶ የሞትን ኃይል ካጠፋልን፣ ከትንሣኤያችን በኩር ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም ማን ሞትን ሊስበው አይቻለውም/አይገባም። የሕያዋን ሁሉ እናት እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ በገድል በትሩፋት የከበሩ ቅዱሳን ጻድቃንና እስከ ሞት ድረስ በስሙ ታምነው የሞቱ ሰማዕታት ሞትን ቢንቁትም ሕይወታቸውን በፈቃዳቸው አልፈጸሙም፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ። ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በሽታ በመጣ ጊዜ እንደ አቅማችን ለመዳን መሞከር ይገባናል እንጂ “ከእግዚአብሔር የመጣ መቅሰፍት ነው” ብለን ወደ ሞት መሄድ እንደሌለብን ነው። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ እንደ ሰው ኑሮን ለማሸነፍ፣ ምድራዊ ሀልወታችንን ለማስጠበቅ በሽታን ከመከላከልና ለመዳን ከመሞከር ሊገድበን አይገባም። በሽታ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተላከ መቅሰፍት አይደለምና።
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ለዘለዓለም ሊኖር አልተፈጠረም። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን የምድር ኑሮ ለሰው ልጆች “የእንግድነት ዘመን” ነው። ለዚያ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ “በእንግድነታችሁ (በሕይወታችሁ) ዘመን በፍርሃት ኑሩ” ያለን (1ኛ ጴጥ. 1:17)። የሰው ልጅ በምድር የሚኖረውን የእንግድነት ዘመን በሞት ይፈጽማል። ሞት ሁሉ መቅሰፍት አይደለም። ይልቁንስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሚፈጽሙ ሰዎች ሞት ወደ ዘላለም ሕይወት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። መቅሰፍት ሞትን ሊያመጣ ቢችልም በሽታ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር የተላከ መቅሰፍት አይደለም። በተሰጠን አዕምሮ በመጠንቀቅ፣ በመታከም ማለፍ የምንችለውን በሽታ ሁሉ ለፈተና ከመቀመጡ በፊት “መውደቄ አይቀርም” ብሎ መዘጋጀትን እንደሚተው ሰነፍ ተማሪ የድርሻችንን ሳንወጣ ሞትን መጋበዝ አይገባንም።
የክርስቲያኖች ድርሻ ሕይወታችንን በፈቃደ እግዚአብሔር በሕግጋተ ቤተ ክርስቲያን መምራት እንጂ የትኛው በሽታ ከእግዚአብሔር የተላከ መቅሰፍት ነው፣ የትኛውስ መቅሰፍት አይደለም በሚል ምርምር ራስንም ሌላውንም ማስጨነቅ አይደለም። በሰው ልጆች ታሪክ ብዙ በሽታዎች መጥተዋል። ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንማረው የእግዚአብሔርን መቅሰፍት የሰው ጥበብ አያስቀረውም። እግዚአብሔር መቅሰፍትን ሲያመጣም በወዳጆቹ አድሮ ይናገራል ወይም ልንስተው በማንችለው መልኩ ያሳውቀናል። ለመዓት የወረደ መቅሰፍት ቢኖር እንኳ እንደ ሰብአ ነነዌ በጾምና በጸሎት እንጂ በጭንቀትና በመታወክ አንሻገረውም።
እምነትና ጥንቃቄ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚመጣውን በሽታ የሚያድን ወይም የሚከላከል መድኃኒት እስካሁን ድረስ አልተገኘም። በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች ትኩረት በሽታው እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ነው። እነዚህም አካላዊ ንክኪን መቀነስ፣ ጥግግት ባለበት መንገድ በኅብረት አለመሰብሰብና የመሳሰሉትን ይጨምራሉ። በየሀገሩ ያሉ መንግሥታትም አስገዳጅነት ያላቸው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅና መመሪያዎችን እያወጡ መተግበር መጀመራቸው ይታወቃል። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ጥንቃቄዎች “የእምነት ጉድለት” አድርገው ሲመለከቷቸው እናስተውላለን።
እምነት ማለት የማናየውን በተስፋ የምንቀበልበት እንጂ ውጤቱን የምናየውን ነገር በጥራዝ ነጠቅ አተያይ ተመርተን ራሳችንን የምናሳውርበት መሸፈኛ አይደለም። እምነት አለኝ ብሎ ከፎቅ ወደ መሬት ዘልየ ልውረድ የሚል ሰው የለም፣ ቢኖርም የእምነትን ምንነት የማይረዳ ነው። እምነት አለኝ ብሎ በኤች አይ ቪ የተያዘ ሰውን ደም ጠብቶ ከሰውነቱ ጋር የሚያዋሕድ የለም፣ ቢኖርም የእምነትንም የሕይወትንም ትርጉም የማይረዳ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ሊፈትነው የመጣ ሰይጣን የእምነትን ነገር በዚህ መልኩ ለጥጦ “አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ከዚህ መር ብለህ ወደ ታች ውረድ፣ ይጠብቁህ ዘንድ ስለ አንተ መላእክቱን ያዝዝልሃል፣ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና።” ባለው ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ “አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል።” (ማቴ. 4:6-7) በማለት ያስተማረን ትምህርት የእምነትና የጥንቃቄን ነገር በሚገባ ሊያስረዳን ይችላል። እምነት ከጥንቃቄ ጋር መምታታት የለበትም። እምነት አለኝ ብሎ ራስን ወደ ታወቀ አደጋ መክተት አይገባም። በተለይም ከተላላፊ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚገባውን ጥንቃቄ ካላደረግን ከራሳችን አልፎ ሌሎችንም ለአደጋ እናጋልጣለን። እምነታችን በሞት ጥላ ውስጥ እንኳ ብንሆን ወደ ፀጥታ ወደብ የምንሻገርበት መርከብ እንጂ በግብዝነትና አለማወቅ ወጀብና ማዕበልን ሳንገደድ የምንጋፈጥነት የጀብደኝነት መሸፈኛ አይደለም፣ መሆንም የለበትም።
ጥንቃቄ እምነትን አይተካም
ጥንቃቄ የሚገባ ቢሆንም እምነትን የሚተካ አለመሆኑን ግን ማስተዋል ያስፈልጋል። የእኛ የእምነትና የዕውቀት ድካም የበረታ ስለሆነ እንደ አዲስ እምነትና ጥንቃቄን ለማስታረቅ መድከማችን የሚያሳዝን ቢሆንም ብዙዎች በዚህ ጉዳይ ሲነታረኩ እንሰማለን። ስለእምነት ጥራዝ ነጠቅ እይታ ያላቸው ሰዎች እምነትን ከሥራ ለይተው ጥንቃቄን ሲያወግዙ፣ እምነትን የሚያቃልሉ ግብዞችም በጥንቃቄ ብቻ ተመክተው ከእምነት የተለየ ሥራን የዕውቀት መገለጫ አድርገው ሲያቀርቡት እናያቸዋለን። እኛ ግን እምነት ያለ ሥራ የሞተ እንደሆነ፣ ሥራም ያለ እምነት ከጽድቅ መንገድ እንደሚያወጣን ልናስተውል ይገባል። (ያዕቆብ 2:14-26) ስለሆነም እምነትን ከጥንቃቄ፣ ጥንቃቄን ከእምነት ጋር ያለመቀላቀል፣ በተዓቅቦ አዋሕደን በመያዝ በየዘመናቱ የሚመጡብንን ምድራዊ ፈተናዎች ልናልፍ ይገባናል።
በዕለት ተዕለት ኑሯችን እንደምናደርገው እንደ አቅማችን እየተጠነቀቅን ባለማወቅ የምናደርገውን የጥንቃቄ ጉድለት ጨምሮ ከእኛ ችሎታ በላይ የሆነውን ሁሉ እስከዛሬ ለጠበቀን፣ ወደፊትም ለሚጠብቀን ቸር ጠባቂ ልዑል እግዚአብሔር በእምነት ልንተውለት ይገባል። ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ እንዳስተማረን “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ቤትን የሚሠሩ በከንቱ ይደክማሉ። እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ የሚጠብቁ በከንቱ ይተጋሉ።” (መዝ 126:1) ለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ በጥብርያዶስ ባሕር ያደረጉት ሊያስተምረን ይገባል። ቅዱሳን ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት እየዋሉ፣ ባደረበት እያደሩ፣ የቃሉን ትምህርት የእጆቹን ተዓምራት እያዩ አብረውት ኖረዋል። ሁሉን ከሚሰጥ ጌታ ጋር መኖራቸው ግን በተዓምራት እየጠገቡ እንዲኖሩ አላደረጋቸውም። ከጌታችን ሳይለዩ እንኳ በረሃብ የተቸገሩበት ጊዜ ነበር። (ማቴ 12:1) ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ በተለያቸው ጊዜም የሚበሉትን ፈልገው ዓሣ ለማጥመድ ወደሚያውቁት፣ ወደ ለመዱት የጥብርያዶስ ባሕር ወረዱ። ዓሣ ለማጥመድም በብርቱ ደከሙ። ይሁንና ምንም ዓሣ ማግኘት አልቻሉም ነበር። ምናልባት መመካታቸው በራሳቸው ዓሣ የማጥመድ ጥበብ ብቻ ሆኖ ከትንሣኤው በኋላ የተለያቸው ጌታ የማይረዳቸው መስሏቸው ይሆን? ድካምን የሚረዳ፣ እምነትን የሚባርክ ጌታ ግን በባሕሩ ዳር ተገለጠላቸውና ዓሣ ለማግኘት መረባቸውን “በታንኳይቱ በስተቀኝ በኩል ጣሉ፣ ታገኛላችሁም።” አላቸው። (ዮሐ 21:1~8) ሌሊቱን ሙሉ ደክመው ዓሣ ለማግኘት ያልተሳካላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ለሸክም የከበደ ብዙ ዓሣ አገኙ። ይህንን ያገኙት በሌሊቱ ድካማቸው በታንኳይቱ በስተቀኝ በኩል መረቡን ስላልጣሉ አልነበረም። በተደጋጋሚ ጥለው አልተሳካላቸውም ነበር። ጥረታቸውን ሳያቋርጡ ቀኝ የተባለ የጌታችንን ቃሉን በማመናቸው የጎደለው ሞላላቸው፣ የራቀው ቀረበላቸው።
አባታችን ኖኅ በዘመኑ ከመጣበት የጥፋት ውኃ እግዚአብሔርን በማመን መርከብን ሠርቶ ዳነ፣ ዓለምንም አዳነ። (ዘፍ 7:1-24) የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በዘመኑ የመጣውን ረሃብ እግዚአብሔርን አምኖ እህል በማከማቸት የግብፅን ሕዝብና ወገኖቹ እስራኤልን አዳነ። (ዘፍ 41:46-57) የተወደደ ሐዋርያ እንድርያስ ጌታችንን ይከተሉ የነበሩ ምእመናን የሚበሉት ባጡ ጊዜ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእምነት አቀረበ፣ በአቅማችን የምናቀርበውን የሚባርክ ጌታም አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን በተዓምራት አበርክቶ ከአምስት ገበያ ሕዝብ በላይ ተመግበውት 12 መሶብ ተርፎ ተነሳ። (ማቴ 14:13-21) በየዘመናቱ ያለፉ ቅዱሳን ምእመናንም ከጥረታቸው ሳያጎሉ፣ እምነታቸውን ጠብቀው የመጣባቸውን ችግርና ፈተና አለፉ። እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነንና እምነትና ጥንቃቄን ያለመቀላቀል በተዓቅቦ ጠብቀን በዘመናችን የሚገጥሙንን ችግሮችና ፈተናዎች እንደ ባለ አእምሮ ማለፍ ይገባናል እንጂ በመጠጥ ብዛት ቀኝና ግራ እግሩን እያማታ እንደሚወድቅ ደካማ ሰው ሕይወታችንን የምንመራባቸውን ሁለት እግሮቻችንን (እምነትና ሥራን) እያምታታን፣ እየቀላቀልን መደነቃቀፍ የለብንም።
በስብከት ስም የሚቀርብ አለማወቅ፣ ማምታታትና ግብዝነት ይቁም!
በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የመጣው በሽታ በሌሎች ሀገራት ላይ በርትቶ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመግባቱ አስቀድሞ አንዳንድ ሰባክያንና መምህራን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች በሽታውን በማስመልከት የሚናገሩት ንግግር በመንፈስ ያለመብሰላቸውን ከጥበብ ተለይተው በአለማወቅ መኖራቸውን በይፋ የገለጠ ነበር። በተለይም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ወይም በቤተ ክርስቲያንን በሚወክል አኳኋን የሚሰጡ ትምህርቶች ከባድ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል።
አንዳንድ ሰባክያን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የኮሮና ቫይረስን መነሻ ምክንያትና መከላከያ መንገድ “እግዚአብሔር የነገራቸው” አስመስለው ሲያቀርቡ ታዝበናል። “በሽታው የመጣው በመጽሐፍ ቅዱስ የማይበሉ የተባሉ እንስሳት ስለተበሉ ነው።” ብለው በፍጹም እርግጠኝነት የሚናገሩ ነበሩ። ሌሎችም በየዓለሙ ያለውን ኀጢአት እየዘረዘሩ በጉዳዩ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር የተማከሩ በሚያስመስል ድምፀት “ይህ በሽታ የመጣው በዚህና በዚያ ምክንያት ነው” እያሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ። እንኳን እኛ በነቀፋ የተሞላ አገልግሎት የምንሰጥ ደካሞች የከበሩ ቅዱሳን እንኳ በየዘመናቸው መሰል ችግር ሲገጥማቸው “እግዚአብሔር የተቆጣን ለዚህ ወይም ለዚያ ይሆንን?” ብለው ራሳቸውም ሕዝቡም አነዋወራቸውን በቅዱሳት መጻሕፍት መሪነት እንዲያደርጉ ይመክራሉ እንጅ በግልጽ ጌታ ሳይልካቸው በግብዝነት ራሳቸውን የእግዚአብሔር ምስጢረኛ አስመስለው በማቅረብ በምእመናን ላይ ለመሠልጠን አይሽቀዳደሙም ነበር።
ወቅታዊውን በሽታ በተመለከተ በዐውደ ምሕረት ስሁት ንግግር ከሚያዘወትሩት መካከል ብዙዎቹ የመረጃ ምንጫቸው እጅግ ተራ ሊባሉ የሚችሉ የመንደር ወሬዎች ወይም ዊኪፒዲያን የመሳሰሉ ድረ ገጾች ናቸው። በምድራዊ መመዘኛ እንኳ የሚናቁ ምንጮችን “የእግዚአብሔር ቃል” አስመስሎ የማቅረብ ክፉ ልማድ በሂደት ምእመናን “በሌላውም ጉዳይ የሚያስተምሩት እንዲሁ በልብ ወደድ የፈጠሩትን ነው” ብለው ወዳልታሰበ የክህደት ጎዳና እንዲሄዱ ይገፋቸዋል። ስለሆነም “ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን።” (ቈላስይስ 4:6) የተባሉ መምህራነ ወንጌል የግምት ንግግርና ምንጭ የሌለው ዕውቀትን በስብከት ስም እየጋቱ ቤተ ክርስቲያንን እንዳያሰድቡ ሊጠነቀቁ ይገባል። ሌሎች መምህራንና ምእመናንም በመዘላመድ የሚናገሩትን ሰዎች እብደት ሊለዩ ይገባል እንጂ ለአሰሱም ለገሰሱም “ያስተማረን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ” እያሉ የመንፈስ ቅዱስን ስም ማቃለል የለባቸውም።
በታመሙት ላይ የመፍረድና የማግለል ግብዝነት
ቅዱሳት መጻሕፍት ለታመሙና ለተቸገሩ እንድናዝን፣ በአቅማችንም እንድናግዛቸው እንጂ ባለማወቅና በግብዝነት ተሸብበን እነርሱ መታመማቸውን የኀጢአት፣ እኛ አለመታመማችንን የጽድቅ ማሳያ አድርገን እንድንመፃደቅ አላስተማሩንም። ይሁንና አሁን ባለንበት የወረርሽኝ ወቅት ጅማሮ ላይ በብዙ ሀገራት ያሉ ሰዎች የቻይናውያንን መከራ አይቶ ከማዘንና ስለ እነርሱ የምሕረት ባለቤት የሆነ እግዚአብሔርን ከመለመን ይልቅ ኀጢአትን እያወዳደሩ የመመፃደቅ ሁኔታ በብዛት አስተውለናል። ይህ መመፃደቅ ግን ተመፃዳቂዎቹን እንደጎዳቸው አሁን ያለንበት ወቅት በግልጽ አስረድቶናል። በሀገራችን ኢትዮጵያም “እኛ መንፈሳውያን ስለሆንን ይህ ለኀጢአተኞች የተላከ መቅሰፍት አይመታንም” የሚል መንፈሳዊም ዓለማዊም አመክንዮ የሌለው ግብዝነት አስተውለናል። ብንችል የተጎዳውን ሰው እንደ ደጉ ሳምራዊ ልናክመው ይገባል። (ሉቃስ 10:30-37) ቢያንስ ግን የራሳችንን ኀጢአት ረስተን የታመሙትን በማይገናኝ አመክንዮ መዝለፍና ማግለል አይገባም። ሌሎች በበደልና በኀጢአታቸው መከራ እንደደረሰባቸው በእርግጠኝነት ብናውቅ እንኳ እግዚአብሔር በምሕረቱ ኀጢአታችንን ታግሦ እንደማረን አውቀን በንስሓ መመለስ እንጂ በሌሎች መፍረድ የክርስቲያን ግብር አይደለም።
ይህ ግብራችን በሉቃስ ወንጌል 13:1-5 ታሪካቸው የተመዘገበው ሰዎች ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው በበደላቸው ምክንያት ጲላጦስ ስለቀላቀለው ሰዎች እንዲሁም በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ ስለገደላቸው ሰዎች ለማውራት የመጡትን ሰዎች ያስመስለናል። ሌሎች ሲቀጡ አይተው ንስሓ ከመግባት ይልቅ ለወሬና በንፅፅራዊ እይታ ራሳቸውን ጻድቅ ለማስመሰል የመጡትን ሰዎች ጌታችን የገሰጸበት ቅዱስ ቃል ለእኛም የተገባ ነው። “ይህች መከራ ስለአገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኀጢአተኞች የሆኑ ይመስላችኋልን? አይደለም። እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።”
ቤተ ክርስቲያንና የባሕል መድኃኒት
በሀገራችን ኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ዘመናዊና ባሕላዊ ሕክምናዎች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው። በየሰፈሩ ያለውን ሳንቆጥር የመንግስሥትን ስልጣን በመጠቀም በባሕልና በሃይማኖት ስም ረብ የለሽ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚሽቀዳደሙትንም ታዝበናል። የባሕል ሕክምና ዓዋቂ ነን የሚሉ ብዙዎችም “ደንበኛ ለመሰብሰብ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም” የሚል በሚመስል እሳቤ ብዙዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንሰማቸዋለን። በእነዚህ ውይይቶች መሀል ቤተ ክርስቲያንና በሁኔታው ላይ ያላት አስተምህሮ ጉዳይ ለድጋፍና ለተቃውሞ በሚመች መልኩ እየተለካ ሲቀርብ ታዝበናል።
ቤተ ክርስቲያን ስለ ሥጋዊ ፈውስ ያላት አስተምህሮ ምንድን ነው?
የቤተክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ለዘላለም ሕይወት ማብቃት ነው። የአስተምህሮዋም ትኩረት የነፍስን ቁስል መፈወስ ነው። ይሁንና ነፍስ ያለ ሥጋ ስለማትቆም ምእመናን በምድራዊ ሕይወታቸው ከቤተክርስቲያን በተዓምራትና በእምነት የሥጋ ፈውስን እናገኛለን። ጸበሏን ጠጥተን፣ እምነቷን ተቀብተን፣ ሕንፃዋን ተሻሽተን፣ በጸሎተ ቀንዲል በቅብዓ ቅዱስ ብዙዎቻችን ፈውሰ ሥጋን ያለ ዋጋ እንዲሁ በጸጋ እንቀበላለን። የቤተክርስቲያን ፈውስ የሚባለው በጸሎትና በእምነት የሚገኝ እንጂ በሌላ የሥጋ ጥበብ የሚመጣ አይደለም። መንፈሳዊ ፈውስና ተአምራት ሰዎችን በእምነት ለማጽናት ለምልክት የሚደረግ፣ እንደ እምነትም የሚፈጸም ስጦታ እንጂ እንደ ምድራዊ ሆስፒታል በመደበኛነት ለሁሉም የሚሰጥ አይደለም። በመሆኑም መንፈሳውያን የሆኑ ሰዎች በእምነት የሚደረግላቸው ፈውስ እንዳለ ሆኖ ለሚገጥማቸው ሥጋዊ ደዌና በሽታ በባሕላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለባቸው።
ለመሆኑ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ ደረጃ ከባሕልና ከዘመናዊ ሕክምና የምትመርጠው አለ?
ባሕላዊም ሆነ ዘመናዊ የሚባሉት ሕክምናዎች ምድራዊ ጥበቦች ናቸው። እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲፈጥረን አካል ብቻ ሳይሆን ነፍስና አእምሮንም ሰጥቶናል። የሰው ልጅ በየዘመኑ በደረሰበት ዕውቀት እየተመላለሰ ለራሱና ለሌሎች ፍጥረታት የአቅሙን ጥበቃ ማድረጉ ከፈጣሪ የተቀበለው የጸጋ ገዥነት ስልጣን ማሳያ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። በተለምዶ “ባሕላዊ” የሚባሉት ሕክምናዎች አሰራራቸው “ዘመናዊ” ከሚባሉት ቢለይም በመሰረታዊነት በየዘመኑ የሚዳብሩ “ዘመናዊ እውቀቶች” መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ዕውቀት ያው ዕውቀት ነው። ሊመዘን የሚገባውም በውጤቱና በምክንያታዊነቱ ነው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በዘመናት ቆይታ “የዕውቀት ሁሉ ማኅደር” ሆና የኢትዮጵያውያንንም ሆነ ሌሎች ጠቢባን ድርሳናት ሰንዳ ከትውልድ ትውልድ አስተላልፋለች። ይህን አበርክቶዋን በዘመናችን ካሉ የመረጃ ቋቶች ጋር ልናነፃፅረው እንችላለን። አንድ ዘመናዊ ቤተ ጽሑፍ (ቤተ መጻሕፍት) ልዩ ልዩ እምነትና ኀልዮት ባላቸው ሰዎች ጽሑፎችና መዛግብት ሊሞላ ይችላል። የቤተ መጻሕፍቱ ሚና ዕውቀት የተባለውን ሁሉ ለሚመረምር አዕምሮ ቅርብ ማድረግ እንጂ በቤተ መጻሕፍቱ ያሉትን ጽሑፎች ሁሉ የቤተ መጻሕፍቱ ባለቤት ይቀበላቸዋል ማለት አይደለም። ቅድስት ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ ቀደምት አባቶችና እናቶች) በቤተ ክርስቲያን መዝገብነት ያቆዩልን ጽሑፎችና መዛግብትም እንዲሁ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን መዝገብነት ለመንፈሳዊም ሆነ ለሥጋዊ ፈውስ የሚሆኑ ደጋግ መጻሕፍት እንደቆዩልን ሁሉ የሟርትና የጥንቆላ ጽሑፎችም ዘመንን ተሻግረው ደርሰውናል። አንድ መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያን መዝገብነት ስለተገኘ ወይም በግዕዝ ስለተጻፈ ብቻ ለይዘቱ ቤተ ክርስቲያንን መንቀፍም ሆነ ማመስገን የሀገራችንን ታሪክና የቤተ ክርስቲያንን ሚና ካለማወቅ የሚመጣ ነው። ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ሚና ጽሑፎችና መዛግብቱን ለትውልድ ማስተላለፍ እንጂ የአስተምህሮ ውሳኔ አይደለም።
በሚገባ ጥበብ የተሞሉ ቀደምቶቻችን በየዘመናቸው ለነበሩ በሽታዎች “ሳር ምሰው፣ ቅጠል በጥሰው” ለመድኀኒትነት የለዩአቸውን ዕፅዋትና ሌሎች ቁሳቁስ ተጠቅሞ ፈውሰ ሥጋን መስጠት ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር አይጋጭም። በአንፃሩ ኮከብ በመቁጠር፣ መዳፍ በማንበብ፣ ልዩ ልዩ ሰይጣናዊ ድግምትና መጠበብን የሚያስተምሩ መጻሕፍት በቤተ ክርስቲያን (ምእመናንና ሊቃውንት) ጠባቂነት ከዘመናችን ቢደርሱም ሰይጣናዊ ሐሳባቸውና ትምህርታቸው በቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው። ይሁንና የጥንቁልና ገበያ ማድራት የሚፈልጉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን የስሕተት መሸፈኛ በማድረግ የጥንቆላ “ዕውቀታቸውን” ለማሻሻጥ ሲሞክሩ እናስተውላለን። “የእግርን መዳፍ በማየት ከበሽታችሁ እንፈውሳችኋለን” እና የመሳሰሉትን የሚሉ አጭበርባሪ ጠንቋዮችም በዘመነ ኮሮና ቫይረስ ቀን ወጥቶላቸው “በሚኒስትር ማዕረግ” በየሚዲያው እየቀረቡ ሕዝባችንን እንደ ጠፍ ከብት ሲነዱት፣ ለአስመሳይ ፖለቲከኞች መገበሪያ ሲያደርጉት ታዝበናል። እነዚህ ሰዎች ለንግዳቸው እስከጠቀመ ድረስ የእግዚአብሔርን ቃል ማጣመማቸው የሚደንቅ አይደለም። “ዘመናዊ” የሚባለው ሕክምና በሕግ ከተቀመጠለት ገደብ እንዳያልፍ ቁጥጥር እንደሚደረገው ሁሉ “ባሕላዊ” የሚባለውም በውጤትና በምክንያታዊነት እየተገመገመ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል እንጂ አስመሳዮች ለንግዳቸው ሲሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስላስጠጉት “የመንፈሳዊነት ካባ” ደርቦ ከተጠያቂነት ማምለጥ የለበትም። ካህናትና ምእመናንም ይህን ተረድተን ራሳችንን ከአጭበርባሪዎች መጠበቅ ይገባናል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የጤና ባለሙያዎች በሰጡት ምክር የተነሣ የሰዎችን አካላዊ መቀራረብ ለመቀነስ በመንግሥታት ውሳኔ በየሀገራቱ ማኅበራዊ ግንኙነቶች በልዩ ልዩ ደረጃ ተገድበዋል። በብዙ ቦታዎች እነዚህ አስገዳጅ መመሪያዎች በአምልኮ ሥፍራዎችም ተፈጻሚነት አላቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ መዋቅር የመጨረሻ ሥልጣን ባለቤት የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስም በዚህ ወቅት የቤተክርስቲያን አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት የሚገልጽ መንፈሳዊ መመሪያና ምክር አስተላልፏል። ይህም መመሪያ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ካሉባቸው ሀገራት አስገዳጅ መመሪያዎች ጋር እየተናበበ የሚፈጸም ነው። ይህን በመሰለ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ማንም ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሊወጣ አይገባም። ምንም እንኳ አፈጻጸሙን በተመለከተ እንደቦታውና ሁኔታው ሊለያይ ቢችልም በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ “ከእምነት ማነስ የተነሳ የተወሰደ የጥንቃቄ እርምጃ” አስመስለው የሚናገሩ “መምህራንና ምእመናንን” ማየት ያሳቅቃል። ይልቁንስ እንደታዘዝነው በልጅነት መንፈስ “ቤተ ክርስቲያን ሆይ ደጆችሽ አይዘጉብን” ብለን ልንጸልይና በንስሓ ከበረታ ኀጢአታችን ልንመለስ ይገባል።
ጠበል፣ ጸሎትና ማዕጠንት
ወረርሽኝና ጭንቀት በበዛበት በዚህ ወቅት ብዙዎች ከወትሮው በበለጠ የካህናትን ጸሎትና ማጽናኛ)ይፈልጋሉ። ስለሆነም ካህናት በየንስሓ ልጆቻቸው ቤት እየተገኙ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ለበሽታ በማያጋልጥ መልኩ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ያለ ዋጋ ቢፈጽሙ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌአዊ ትምህርት ከተጠቀሰው በሽተኛውን አይቶ ሳይረዳው ካለፈው ካህን ተለይተው “ደግ ሳምራዊ” የተባለ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን በግብር ይመስሉታል። (ሉቃስ 10:30-37) ይህም አዲስና ልዩ አገልግሎት አይደለም። የክህነት አገልግሎት በዘመናችን እየበዛ እንደመጣው “በሰጥቶ መቀበል” መርህ ለንግድ የሚደረግ ባልነበረበት ዘመን ሁሉ ካህናት በምእመናን ቤት በመገኘት ጸሎት ጸልየው፣ የታመመውን ጎብኝተው፣ የደከመውን አጽናንተው፣ የተጣላውን አስታርቀው መሄድ በቅርብ ጊዜ የሀገራችን ታሪክ የተለመደ ንጹሕ አገልግሎት ነው። ስለሆነም ካህናት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለቅን አገልግሎት በመፋጠን ምዕመናንም ለካህናት በመታዘዝና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንደ ምቹ ጊዜ ልንጠቀምበት ይገባል።
የጠበል፣ የጸሎትና የማዕጠንት አገልግሎታችንም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን የተከተለ መሆን አለበት። ይሁንና ዘመኑ ከፍቶ ሁሉም በየመንደሩ የራሱን ሥርዓት እየሠራ መንፈሳዊ አገልግሎቶቻችን በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሳይሆን ራሳቸውን በሾሙ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይክና ሼር ባሰከራቸው፣ በስሜት በሚመሩ፣ በሞቀበት ሁሉ ካልዘፈንን በሚሉ አጉራ ዘለሎች የሚመራ ምእመን እየበዛ ነው። እነዚህ ሰዎች ዋና ዓላማቸው “መታየትና መግነን” ስለሆነ ጸሎቱና ማዕጠንቱም በዚያው ቅኝት እንዲደረግ በልዩ ልዩ መንገድ ያበረታታሉ። በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በማዕጠንት ጸሎት የሚደረግባቸው ቦታዎችና ሁኔታዎች የታወቁ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ግን ቅዱስ ሲኖዶስ “ጸሎተ ዕጣን በቤተ መቅደስ በካህናት እንዲፈጸም” የሰጠው ትእዛዝ ለታይታ ጩኸታቸው ስላልተመቻቸው ሥርዓቱና ትዕዛዙን ትተው በራሳቸው መንገድ ሲሄዱ እናያቸዋለን።
የከበረ የዕጣን መሥዋዕት እንደ አልባሌ ጢስ በሰፈር ጎረምሳ ጩኸትና በመኪና ታጅቦ በብዛት ስለተነነ “የተሻለ የድኅነት አገልግሎት” እንደፈጸሙ አድርገው ያወራሉ። ለተርእዮ የተሰለፉ ሰዎችም ስማቸውና አለባበሳቸውን አሳምረው “አሜሪካን ባረክናት፣ አውሮፓን ቀደስናት፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት መሆኗን ዓወጅን” እና የመሳሰሉትን የፈሪሳዊ ጸሎት ማሳረጊያ የሚመስሉ መፈክሮችን እያሰሙ ሰውን ከእምነትና ከሥርዓት እንዲያፈነግጥ ያደርጉታል። በቤተ መቅደስ የሚሰዋ የዕጣን መሥዋዕት ሙሴ በአላማ ላይ እንደሰቀለው የናስ እባብ (ዘኁልቍ 21:4-9) ላመኑትና የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ለሚሰሙት ሁሉ መድኀኒት እንደሚሆን ማስተዋል አቅቷቸው የእምነትን ሥራ በእጃቸው ለመጨበጥ፣ በአፍንጫቸው ለማሽተት ሲሽቀዳደሙ የከበረውን መሥዋዕት ለአሕዛብ መቀለጃ እንዲሆን አደረጉት። የማያምኑትም ባለማወቅ ክፉ እየተናገሩ በራሳቸው ላይ በደልን እንዲጨምሩ ሆነ። ጌታችን በወንጌል “በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሷችሁ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፣ ዕንቍአችሁንም በዕሪያዎች ፊት አታኑሩ።” (ማቴ. 7:6) ያለውን ትእዛዝ ለታይታ የግብዝነት አገልግሎት ስንል ልንዘነጋው አይገባም። ጠበል፣ ጸሎትና ማዕጠንት በመንፈሳዊነት የሚቀርቡ አገልግሎቶች እንጂ “እነርሱኮ ጸሎተኞች ናቸው” ለመባል የሚቀርቡና “እዪልን!” የምንልባቸው አይደሉም።
አምላካችን ያድነናል፣ ባያድነን እንኳ ለጥቅማችን ነው!
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ በሽታና ችግርን ከልክ በላይ አግንና አትመለከትም። ሞት እንኳ ቢመጣ ለጥቅማችን እንደምንሞት እናምናለን። በወረርሽኝ ምክንያት በየቦታው የምናየው አለመተዛዘንና ከልክ ያለፈ ጭንቀት በክርስቲያኖች ላይ ሲታይ ምን ያህል ከቃለ እግዚአብሔር የራቀ ሕይወት እንደምንመራ አጋልጦናል። በእውነቱ የእኛ ሕይወት “እግዚአብሔርን አያውቁም፣ ቤተ ክርስቲያንን አይሰሙም” ከምንላቸው ሰዎች ካልተለየ ክርስትናችን የት ላይ ነው?! በመጠንቀቅ ብዛት ብቻ የምንድን፣ ጠባቂ መጋቢ የሌለን አድረገን ራሳችንን ልንቆጥር አይገባም። የምናመልከው አምላካችን ከታሰበም ከተወረወረም ሰይፍ የሚያድን ነው። በምድር የምናየው መከራም ወደ ንስሓ የሚመራን እንጂ ተስፋ እንደሌላቸው የሚያሳዝነን መሆን የለበትም። ሠለስቱ ደቂቅ የሚነድድ እሳት በፊታቸው እያለ አምልኮታቸውን፣ መታመናቸውን “እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፣ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ።” (ዳን. 3:17-18) እንግዲህ ምን እንላለን? እነዚህ ሦስት ሕፃናት በሚነድድ እሳት ፊት እምነታቸውን እንዲህ ከገለጡ እኛማ ከእሳት ጋር በማይነፃፀር መልኩ የመግደል አቅሙ እጅግ ደካማ የሆነ ቫይረስ ፈርተን እንዴት እንጨነቃለን? ይህችን ለወሬ የማትበቃ የጭንቀት ፈተና በእምነት ካላለፍንስ የበለጠ ፈተና ቢገጥመን ምን ልንሆን ነው? ስለሆነም ወደ ልቦናችን እንመለስ። “የምናመልከው አምላካችን ያድነናል፣ ባያድነን እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት አይቀይረውም።” እንበል።
አሁን ያለንበት ወቅት ብዙ ሰዎች በጉያቸው ተሸክመውት በኑሮአቸው የረሱትን የሥጋ ሞት እንዲያስታውሱ እያደረጋቸው ነው። በእውነት ከሞት በኋላ ባለ ሕይወት ተስፋ የሌላት ሰውነት ምንኛ ጎስቋላ ናት!? እስኪ በሐሳባችን የአንድ ክርስቲያን ሰውነትን ከኢአማኒ ሰውነት ጋር እናነፃፅረው። ከሞት በኋላ ተስፋ ሕይወት የሌለው ሰው በሞት ጣር ቢያዝ እንኳ ከቁሳቁስ የዘለለ ተስፋ የለውም። ዘመኑን ሙሉ በእቅድ ሲመራ የኖረ ባለ አእምሮ “ከሞት በኋላስ ምን ይገጥመኝ ይሆን?” ብሎ እንዳይጠይቅና ከእምነት በቀር ዋጋ የማያስከፍለውን እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን የመዳን መዐድ እንዳይካፈል አዚም ያደረገበት ማን ነው?! ለተቆጠረ ምድራዊ ኑሮው ከነገ አልፎ ለከነገ ወዲያ በማሰብ የሚጨነቅ ጥበበኛ ለማይቆጠሩ ዘመናት ከሞት በኋላ ሕይወትን የሚያገኝበትን እምነትና ምግባር እንዳያስተውል የከለከለው ማን ነው?! እኛ ዐይኖቻችንን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ ጽድቅን ከማየት፣ ጆሮዎቻችንን ቅዱስ ቃሉን ከመስማት፣ ህዋሳቶቻችንን ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወት የተገባን በሚያደርግ በጎ ምግባር ከማስጌጥ ብንከለክልም እግዚአብሔር ግን በበጎውም በክፉውም ታሪካችን ውስጥ በእምነት የሚፈልጉት ሁሉ እርሱን ወደ ማግኘት የሚመራቸውን ጎዳና ያመለክተናል። ዛሬስ ሰምተነው ይሆን?
የእግዚአብሔርን ድምፅ ማን ይሰማል?
“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ። በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን።” (ዕብ. 1:1-2) በተለይም የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ቁጥር እጅግ የከፋ መቅሰፍትና መከራ እንደሚመጣ ጌታችን አስተምሮናል። (ማቴ. 24:1-12) ለዚህም መፍትሔው እስከ መጨረሻው በእውነተኛ እምነትና በደገኛ ምግባር ጸንቶ መኖር እንጂ በዓለም ወሬና መከራ በመደናገጥ የነፍሳችንን ቤዛ ረስተን በሚፈርስ በሚበሰብስ የሰው ጥበብ ብቻ አለመደገፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን “እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፣ ሰው ግን አያስተውለውም።” (ኢዮብ 33:14) ስለሆነም የአንዱ ሞት ለሌላው ትምህርት ሆኖት ከሚያልፈው የማያልፈውን፣ ከጊዜአዊው ዘላለማዊውን መርጠን፣ ከአጉል ጭንቀትና ፍርሃት ተለይተን፣ ለራሳችንም ለሌሎችም እየተጠነቀቅን ይህንን ክፉ ዘመን እንድናልፈው የምሕረት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን። የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳኑ ሁሉ ቃል ኪዳን፣ የቅዱስ መስቀሉ ኃይል ካለውም ከሚመጣውም፣ ከምናውቀውም ከማናውቀውም መከራና ችግር እንዲጠብቀን፣ ለምእመናን የተዘጉ የአብያተ ክርስቲያናትን ደጆች እንዲከፍትልን፣ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ፈቃድ ይሁንልን። አሜን።