በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ያሉ ምዕመናን የተለያየ የትውልድ ሀረግ (ቦታ) ያላቸው፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የ(ሚ)ኖሩ፣ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው፣ በተለያዩ የሕይወት መስተጋብሮች ያለፉና በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በሀብት መጠን፣ በአመለካከት፣ በልምድ ወዘተ የሚለያዩ ናቸው። ነገር ግን ሁሉም በእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት የሚያምኑ፣ በክርስቶስ ሰው መሆን የተዋጁ፣ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ፣ የአንዱን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ፣ በመጨረሻው ትንሣኤ ሙታንም ተስፋ መንግስተ ሰማያትን የሚጠባበቁ ናቸው። በዘመናችን ማኅበራዊ ብዙኅነት በአንዳንዶች ዘንድ ክርስትናዊ አንድነትን እንደሚከፋፍል ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በሌላም በኩል ማኅበራዊ ብዙኅነትን አገናዝቦ ማገልገልን ከዘረኝነት ጋር የማምታት ሁኔታ ይታያል፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበራዊ ብዙኅነትን ባለመገንዘብና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች መከፋፈል የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎትና የክርስትና ሕይወታችንን በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ክርስቲያናዊ አንድነትን (Christian Unity)፣ ማኅበራዊ ብዙኅነትን (Social diversity) እና ዘረኝነትን (Racism) በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽርነት እንዳስሳለን።
ክርስቲያናዊ አንድነት ምንድን ነው?
ክርስቲያናዊ አንድነት ከአስተዳደራዊ (የቤተክርስቲያን አስተዳደር) አንድነት፣ ከፖለቲካዊ አንድነትና የሀገር (ሀገራዊ) አንድነት የተለየ ነው። እዚህ ላይ ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይገባል። 1) ክርስቲያናዊ አንድነት ምንድን ነው? 2) ክርስቲያናዊ አንድነት በምን ይገለጣል? 3) ቤተ ክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት ስንልስ ምን ማለታችን ነው? ክርስቲያናዊ አንድነት በእምነት አንድነትና በአስተምህሮ ስምምነት የሚገለጥ በመሆኑ በትውልድ ሀረግ፣ በቋንቋ ልዩነት፣ በፖለቲካዊ ርዕዮት መለያየት፣ በፖለቲካዊ የሀገራት ድንበር መለያየት የማይገደብ ነው። ‘ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት’ ስንል በአንድ በክርስቶስ መሠረትነት ላይ የታነጸች፣ በእርሱ የተዋጀች፣ በእርሱ የምታምን፣ እርሱንም የምታመልክ፣ እርሱንም የምትሰብክ መንፈሳዊ ተቋም ናት ማለታችን ነው (ማቴ 16:18-19 ኤፌ 4:1-4)።
የቤተክርስቲያን አንድነት የሚገለጠው በአምስቱ አዕማደ ምሥጢራትና በሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ነው። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው አንድነትን ያመለክታል። ይህም ሲባል በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን እና በሰማይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን አንድ ናቸው ማለት ነው። በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ያለን ክርስቲያኖችም ‘አንድ ነን’ ስንል ይህንን ማለታችን ነው እንጂ አስተዳደራዊ አንድነት፣ ወይም የቋንቋ አንድነት ማለታችን አይደለም። ክርስቲያኖች ‘አንድ ነን’ ስንል ‘በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር የተወለድን ነን’ ማለታችን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሲናገር “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” ብሏል (1ኛ ጴጥ 1:23)
ማኅበራዊ ብዙኅነት (Social diversity)
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኩላዊት (የሁሉም፣ ዓለም አቀፋዊት) ከመሆኗ የተነሳ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችም ማኅበራዊ ብዙኅነት (Social diversity) እንዳላቸው ግልፅ ነው። ይህም የቋንቋ፣ የባህል (አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አኗኗር ወዘተ) ፣ የሙያ፣ የብሔር፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የዘር የትውልድ ሀረግ፣ የትውልድ ሥፍራ እና የመሳሰሉትን ብዙኅነት ያጠቃላል። ይህም ብዙኅነት የየማኅበረሰቡ ማኅበራዊ ማንነት መገለጫ ከመሆኑ የተነሳ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚጠብቀውና የሚያሳድገው እሴት ነው። ሰው የነፍስና የሥጋ ውሕደት እንደሆነ ሁሉ ማንነቱም የመንፈሳዊና የማኅበራዊ ማንነቶቹ ውሕደት ነው። ይህም ከክርስትና አስተምህሮ ጋር ተጣጥሞ መሄድ የሚችል፣ ይልቁንም ክርስትናን ለማስተማር ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር እንጂ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ቤተክርስቲያንን የሚጎዳው ከክርስትና ጋር የማይጋጨውን ጤናማ የሆኑትን ማኅበራዊ ልዩነቶች በልዩ ልዩ ተጽዕኖ በመጨፍለቅ ቤተክርስቲያንን “የአንድ ወጥ ምድራዊ ማንነት” መገለጫ ለማድረግ መሞከር ነው።
የትውልድ ሀረግና ዘር (Ancestry and Race)
የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የኢየሱስ ክርስቶስን የትውልድ ሀረግ በማቅረብ ይጀምራል (ማቴ 1፡1-16)። የቅዱሳንም የትውልድ ሀረግና ወገን በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሥፍራ ተዘግቧል። ይህም ክርስቲያናዊ አንድነት የትውልድ ሀረግ ልዩነቶችን አገናዝቦ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ አስቀድሞም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ ክርስትናን ከመቀላቀሉ በፊት የራሳቸው ማኅበራዊ ማንነት (Social identity) ካላቸው ከእናትና ከአባቱ በአንድ ቦታ በሥጋ ይወለዳል፡፡ የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳምና ሔዋን ቢሆኑም ሰው የእናትና የአባቱ የትውልድ ሀረግና ዘር አለው፡፡ ሁሉም ሰው የየራሱ የትውልድ ቦታም ይኖረዋል፡፡ የትውልድ ሀረግ፣ ዘር እና የትውልድ ቦታ የሌለው ሰው የለም፡፡ ክርስትና ከማይጠፋ ዘር መወለድ ቢሆንም በአካለ ሥጋ ለሚኖር ሰው ከትውልድ ሀረግና ዘር ጋር አብሮ የሚታይ እንጂ ዘርን የሚተካ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ ሰውም ክርስቲያን ለመሆን የትውልድ ሀረጉን እና የትውልድ ስፍራውን መርሳት አይጠበቅበትም፡፡
ግለሰቦች የተለያየ ዘር አላቸው፣ ክርስትና ግን የክርስቶስ ወገን መሆን ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል፣ ክርስቲያኖችም ብልቶች ናቸው፡፡ስለዚህም በቤተ ክርስቲያን ያለ ሰውም በዘሩ ወይም በትውልድ ሥፍራው ሳይለ(ያ)ይ በአንድነት አምልኮውን መፈጸም ይኖርበታል፡፡ ችግር የሚፈጠረው አንዱ ተነስቶ ‘የኔ ዘር ከሌላው ይበልጣል (ልዩ ክብር ይገባዋል)፣ የሌላውም ዘር ከእኔ ዘር ያንሳል (ያነሰ ክብር ይገባዋል)’ ማለት ሲጀምር ነው፡፡ ሌላው የችግር ምንጭ በአንዳንድ የፖለቲካ ዝንባሌ ባላቸው ግለሰቦች ዘንድ የሚታየው የቤተ ክርስቲያንን መድረክ ዘርን ለመስበክ ማዋል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መድረክ ወንጌልን ብቻ ለመስበክ ቢውልና የማንኛውንም ዘር የማያስበልጥ ወይም የማያሳንስ መልእክት የሚተላለፍበት ቢሆን የዘር ጉዳይ የልዩነት ምክንያት ባልሆነም ነበር፡፡
ዘረኝነት (Racism)
የሰው ልጅ የተገኘበት (ምንጩ አዳም የሆነ) የትውልድ ሀረግና ዘር ቢኖረውም ማንኛውም የሰው ልጅ በዘሩ ምክንያት ከሌላው ሰው አያንስም፣ አይበልጥምም፡፡ መንፈሳዊና ዓለማዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሁሉ ሰውን በዘሩ ምክንያት ሳያገሉ ለሁሉም በእኩልነት አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአጭር አገላለፅ የሰው የትውልድ ሀረጉና ዘሩ የማኅበራዊ ማንነቱ መገለጫ እንጂ የበላይነት ወይም የበታችነት መስፈርት ሊሆን አይችልም፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉም የሰው ልጅ ከአንድ ንፁህ ዘር ከአዳምና ከሔዋን መገኘታቸውን ያስረዳሉ። የሰው ልጆች የትውልድ ማንነት በመንፈሳዊ አንድነት ላይ የማንንም የበላይነት ወይም የበታችነት አያሳይም። የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በላከው ጦማር በክርስቶስ በማመን በሚገኝ የጥምቀት አንድነት ይህን መሰል ክፍፍል ማድረግ እንደማይገባ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል: “በዚህም አይሁዳዊ ወይም አረማዊ የለም፣ ገዢ ወይም ተገዥ የለም፣ ወንድ ወይም ሴት የለም፣ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁና።” (ገላትያ 3:28) በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ መሆን ከአዳም የተነሳ ሁሉም የሰው ልጆች ካላቸው የተፈጥሮ አንድነት የሚመነጭ መሆኑን ይኸው ቅዱስ ሐዋርያ በሮሜ መልእክቱ ምዕራፍ 5 ቁጥር 12-21 ያስገነዝበናል። ዘረኝነት የሚባለው ይህን የተፈጥሮና የእምነት አንድነት በማንኛውም ምድራዊ ልዩነት የተነሳ በማቃለል በሰው ልጆች መካከል በቅናትና ፉክክር መንፈስ የሚጎለብት የመጠፋፋትና ያንንም መንገድ የሚያጸና ስንኩል አመክንዮ ነው። አንዳንድ ሰዎች “ዘረኝነት” የሚለው ብያኔ በተወሰኑ የትውልድ ሐረግ ልዩነቶች ለሚፈጠር አስተሳሰብና ተግባር ብቻ ሊውል ይገባል ይላሉ። ለዚህም የሚያቀርቡት ማሳመኛ “የተለያዩ ዘሮች የሚባሉት ነጭ፣ ጥቁርና ቢጫ የሚባሉ ሕዝቦች ብቻ ናቸው።” የሚል ነው። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ በቅዱሳት መጻሕፍት የተቀመጠውን የሰው ልጆች የተፈጥሮ አንድነት የሚሸረሽርና አሳማኝ ያልሆነ ነው። ዘረኝነት የሚባለው በማንኛውም የትውልድ ሐረግ፣ የቀለም፣ የቋንቋ ወይም ሌላ ልዩነት የተነሳ የሚፈጸም መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።
ዘረኝነትን በምታወግዝ ቤተክርስቲያን በአንዳንድ ግለሰቦች አለማወቅና ግብዝነት ምክንያት አንዱ ወገን የቅዱሳን/የጻድቃን ዘር እየተደረገ ሌላው ደግሞ የአሕዛብ/የአረማዊያን ዘር ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ቅድስና በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእምነትና በምግባር እንጂ በዘር የሚታደል አይደለምና (ዮሐ 8:39)፡፡ በሌላም በኩል አንዱን የሊቃውንት ዘር (ወላጆቹ የተማሩ ናቸው የሚለውን አገላለጽ አይመለከትም)፣ ሌላውን ደግሞ የጨዋ (ያልተማረ፣ ወይም ትምህርት የማይዘልቀው) ዘር አድርጎ የሚወስድ ዕውቀት ከጥረትና ጸጋ እግዚአብሔር ይልቅ በሥጋዊ ትውልድ የሚገኝ አስመስሎ የሚተርክ ስሁት እይታም ሊታረም ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም መንፈሳዊ ዕውቀትና ክህሎት በእግዚአብሔር ጸጋና በትምህርት እንጂ በዘር የሚወረስ አይደለምና፡፡ አንዱ ወገን በተፈጥሮ ባለሀብት ሆኖ የተወለደ ሌላው ደግሞ እርሱን ለማገልገል የተፈጠረ ደሀ አድርጎ ማሰብም ኋላ ቀር አስተሳብና ኢ-ክርስቲያናዊ ነው፡፡ አንዱ ዘር ሞት እንኳን የማይበግረው ጀግና (ለእምነቱ ሟች) ሌላውን በተቃራኒው አድርጎ ማሰብም እንዲሁ ዘረኝነት ነው። በአጠቃላይ የሰው ዘር ሁሉ እኩል ስለሆነ ሰው በዘሩ ብቻ አንዱ ምርጥ/የተሻለ ሌላው ምርጥ ያልሆነ ተደርጎ ሊወስድ አይገባም፡፡
የአንዱን ዘር ቋንቋ የመላእክት ቋንቋ አስመስለው እየወሰዱ ሌላውን ቋንቋ ደግሞ ለወንጌል (ለእግዚአብሔር ቃል) የማይስማማ አድርጎ የመረዳትም ምንጩ ዘረኝነትና አለማወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጊት መንፈስ ቅዱስ ብዙ ልሳናትን ለሐዋርያት የገለጠበትን ዓላማ መቃወም ነውና፡፡ በተጨማሪም የአንዱ ዘር ለክህነት አገልግሎት የተመረጠ ሌላው ዘር ደግሞ ለምዕመንነት ብቻ የሚያበቃ አድርጎ ማሰብም እንዲሁ ዘረኝነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት በሐዲስ ኪዳን አይሠራምና፡፡ ልቦናውን ለመለወጥ ክፍት አድርጎ ለሚሰማ ሁሉ እነዚህ ችግሮች ጥቂት በማይባሉ ቦታዎች ይታያሉ። የሚያሳዝነው ግን ሰምቶ ከመለወጥ ይልቅ በጓሮ የተሰበሰበ የቆሻሻ ክምርን ላለማጽዳት ሳሎንን በማሳመርና እንግዶችን “እዩልኝ!” በማለት መቀየር የሚቻል የሚመስለው ሰው ብዙ መሆኑ ነው። ለቤተክርስቲያን የሚጠቅማት የአስተዳደር መዋቅሯን በማጠናከር ለየማኅበራዊ ፍላጎታቸው ሲሉ ክርስቲያናዊ አንድነትን በድቡሽት መሰረት ላይ የሚጥሉ አሰራሮችና አስተሳሰቦችን ነቅሶ በመለየት ማረም ነው።
በሌላ በኩል ዘረኝነት ያልሆኑ ነገር ግን ባለማወቅ ‘ዘረኝነት’ ተብለው የሚወሰዱ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሰው ከሁሉ አስቀድሞ ቅርርብ (Intimacy) ያለው ከቤተሰቡ አባላት (እናት አባት፣ ወንድም እህት) ጋር ነው፡፡ ቀጥሎም ከጎረቤትና ከዘመድ አዝማድ ጋር ነው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ከአካባቢው ወይም አንድ ቋንቋና አንድ ዓይነት ባሕል ከሚጋራቸው ሰዎች ጋር ነው፡፡ ሰው ‘የኔ’ የሚለውን ማኅበረሰብ የመውደድ፣ የማስቀደም፣ ድጋፍ የመስጠት ጠባይም አለው፡፡ የዚህ ዓይነትን የሰዎችን ቅርርብና መደጋገፍ ‘ዘረኝነት’ ብሎ መፈርጅ ታላቅ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የማኅበራዊ ትስስር ውጤት እንጂ ሌላውን ለማግለል ተብሎ የሚደረግ አይደለምና፡፡
የዘረኝነት ፍረጃና አስከፊ ገፅታው
የአንዱን ወገን ብቻ ነጥሎ ዘረኛ አድርጎ በጥቅሉ መፈረጅም እንዲሁ በራሱ ዘረኝነት ነው፡፡ ዘረኝነት ዘር የለውምና፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ የሆነ ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ፣ ከእነርሱ የተለየ አስተሳሰብን የሚያራምድ ሰው ሁሉ በጅምላ ‘ዘረኛ’ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ይህ ፍረጃ እጅግ አደገኛና አሳፋሪ ነው፡፡ ይህ ዘረኝነትን እንጸየፋለን በሚሉት ወገኖች ዘንድ ሲንፀባረቅ ማየት የተለመደ ነው። በተለይም በክርስትና አስተምህሮ ግለሰቦች ወይም ተቋማት ዘረኝነትን ሲያራምዱ ቢገኙ እንኳን በፍቅር ምክር፣ ትምህርትና ተግሳፅ ሊሰጣቸው ይገባል እንጂ ‘ዘረኛ’ ተብለው ተፈርጀው ሌላ መገለል ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ መጽሐፍም ‘እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ’ የሚለው ለእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ነውና፡፡ ምክንያቱም ዘረኝነትን በሌላ ዘረኝነት መከላከል አይቻልምና፡፡
አንዳንድ ጊዜም ሰዎች ድክመታቸውን ለመሸፈን ወይም ሌላውን ወገን ለማራቅ ሲፈልጉ ‘ዘረኛ’ ብለው ይፈርጃሉ፡፡ ለምሳሌ በችሎታቸው ተወዳድረው ማሸነፍ/ማለፍ ሳይችሉ ሲቀሩ፣ ወይም ሌላው ወገን በሚያደርገው የእርስ በእርስ መደጋገፍ ምክንያት ተሽሎ ሲገኝ ‘ዘረኛ’ የሚል ቅጽል ሊለጠፍበት ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ በዘረኝነት ካባ ድክመትን ለመሸፈን መሞከር ውድቀትን ከማፋጠን ባለፈ ብዙም አያራምድም፡፡ ይልቁንም የሚበጀው ከሌላው በመማርና ጥንካሬን በማጎልበት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ የማይወዱትን ወይም ይፎካከረኛል ብለው የሚያስቡትን ሰውም ‘ዘረኛ’ እያሉ ለማሸማቀቅና ለማጠልሸት መሞከርም እንዲሁ የክሽፈት መገለጫ ነው።
ወገንተኛ የሆነ ግለሰብ የቤተ ክርስቲያንን ማዕረግ ይዞ በሌላው ወገን ላይ ግልፅ የሆነ የዘረኝነት ተግባር ሲፈፅም እሹሩሩ እያሉና እንደ ጀግና ወይም የመብት ተሟጋች እያወደሱ (እያበረታቱ) ለተመሳሳይ ድርጊት ሌላውን ወገን ነጥሎ ‘ዘረኛ’ ብሎ መፈረጅም ዓይን ያወጣ ዘረኝነት ነው። ከዚህ አንጻር የዘረኝነት ዝንባሌ ያለው እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ስም ወይም ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ተብሎ ቢፈፀም እንኳን ድርጊቱን አስቀድማ ማውገዝና ማስቆም እንዲሁም የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚገባት ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው በእምነት ጽናትና በመስዋዕትነት ስለሆነ በሌላ ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ ማሰብ ኃጢአት ነው፣ ከተፈጸመ ደግሞ በደልም ወንጀልም ነው።
ዘረኝነትና ጉዳቱ
ዘረኝነት በማኅበራዊም ሆነ በመንፈሳዊ መስፈርት የሰው ልጅ ሕይወትን የምትጎዳ ካንሰር ተደርጋ ልትታይ ይገባል፡፡ ዘረኝነት የሚጎዳው ሁሉንም አካል ነው፡፡ በዘረኝነት ድርጊት የዘረኝነት ድርጊት የተፈጸመበት ሰው/ቡድን፣ የዘረኝነት ድርጊት የፈጸመው አካልና የዘረኝነት ድርጊት ሰለባ የሆነው አገልግሎት እንዲሁም የድርጊቱ ተሳታፊ አካላት በሙሉ ተጎጂ ይሆናሉ፡፡ ከዘረኝነት ድርጊት የሚጠቀም አንዳች አካል የለም፡፡ ድርጊት ፈጻሚው አካል ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ኢ-ሰብአዊና ኢ-ሞራላዊ በሆነው የዘረኝነት ጥቃት በመጉዳቱ የራሱን ክብር አጥቶ ለቅጣት ይዳረጋል፡፡ የራሱን ወገንም ያዋርዳል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመበት አካልም እንዲሁ ኢ-ሰብአዊና ኢ-ሞራላዊ በሆነ መንገድ በደልና ወንጀል ስለተፈጸመበት ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ይደርስበታል፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንድ አካል በዘሩ ምክንያት ጥቃት ሲፈጸምበት አንድምታው ለእርሱ ወገኖች ሁሉ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የዘረኝነት ሰለባ በሆነው አገልግሎትም ውስጥ የሚሳተፉ ሌሎች አገልጋዮችም አመኔታ ያጣሉ፡፡ ይህም እያደገ ከሄደ በዘር መካከል ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን የዘረኝነትን ተግባር በሚፈጽሙ ጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ሌላውን ወገን አክብሮና አብሮ የሚኖረው የዋህ ማኅበረሰብ ላይ የአፀፋ ጉዳት ማድረስ ሌላ የዘረኝነት አጸያፊና ኢ-ሰብአዊ ተግባር ነው። ግለሰቦች በጥፋታቸው በግል ሊጠየቁና ሊታረሙ ይገባል እንጂ ሌላው ባጠፋው የዋሁ ማኅበረሰብ መወቀስም ይሁን መጠቃት የለበትም።
በመንፈሳዊ እይታም የዘረኝነት ድርጊት በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታላቅ ኃጢአትና በደል ነው፡፡ እግዚአብሔር እኩል አድርጎና አክብሮ የፈጠረውን ሰው በዘሩ ምክንያት ልዩነት ፈጥሮ ማበላለጥ ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ መጽሐፍ “በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል” (ማቴ 6፡22-23) የሚለው ይህንን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ አንዱን ወገን መናቅ፣ አሳንሶ ማየት፣ ማግለል፣ መስደብና የመሳሰሉት እስከ ገሃነም እሳት ፍርድ ድረስ የሚያደርስ ቅጣትን ያመጣል፡፡ በተለይ የዘረኝነት ድርጊት በቤተ ክርስቲያን (በቤተ ክርስቲያን ስም) ከተፈጸመ ተጠቂው አካልና የእርሱም ወገን ለቤተ ክርስቲያን ያለው ፍቅር ሊቀንስ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ጥሎ ሊወጣ ይችላል፡፡ ፈጥነው ንስሐ ካልገቡና የበደሉትን ካልካሱ የዘረኝነትን ድርጊት የሚፈጽሙ በእነዚህም ነፍስ ይጠየቃሉ፡፡
ዘር ክርስትናን አይከፋፍለውም!
ክርስቲያናዊ አንድነት በዘር ሊፈተን አይገባም፡፡ ሰው ከማንም ዘር ይወለድ ሙሉ ሰው ነው፡፡ ክርስትናም ሲነሳ (ሲጠመቅ) ሙሉ ክርስቲያን ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ዘር ሳትለይ መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጥ ተቋም ናት፡፡ በዚህም ገለልተኝነቷ (neutrality) ቤተ ክርስቲያን የዘር እኩልነትን (Race equality) ታከብራለች። እንኳንስ ቤተ ክርስቲያን ይቅርና ምድራዊ ተቋማትም በአገልግሎታቸው የዘር ልዪነት አያደርጉም፡፡ ዘር ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍለው በአስተዳደራዊና በአገልግሎት ድክመት ነው፡፡ የአንዱ ዘር ለማየል (የበላይነትን ለማሳየት) ሲሞክር ወይም ቤተ ክርስቲያንን የራሱ ብቻ መገልገያ ለማድረግ ሲሞክርና ሌላውን ወገን ሲበድል፤ ሌላውም ወገን በእልህ ሲነሳ ልዩነት ይፈጠራል፡፡ ይህም እያደገ ይሄድና እኛም የራሳችን አጥቢያ ይኑረን ወደሚል ክፍፍል ያመራል፡፡ እንዲህ እያለ ልዩነቱ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ መጀመሪያውኑ በየደረጃው የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የሚመሩ ሁሉ ሥርዓትን ጠብቀው መንፈሳዊ ነገር ላይ አተኩረው ቢሠሩ እንደዚህ ዓይነት ክፍፍል የመፍጠር ዕድል አያገኝም፣ ቢፈጠርም አድጎ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊም ሆነ አስተዳደራዊ ህልውና አይገዳደርም።
ማጠቃለያ
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት (የጸሎት ቤት) ናት፡፡ በውስጧም መንፈሳዊ ነገር ብቻ ሊፈጸም ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያሉ ምዕመናንም ማኅበራዊ ብዙኅነት ቢኖራቸውም በክርስቶስ (በክርስትና) አንድ ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያንም የሰው እምነቱ እንጂ ማኅበራዊ ማንነቱ ሊጠየቅ አይገባም፡፡ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የአገልግሎት ዐውድም ሰዎች ሊመዘኑ የሚገባቸው በክርስትና እምነትና ምግባራቸው እንጂ በትውልድ ማንነታቸው ወይም ተያያዥ ጉዳዮች መሆን የለበትም። ይሁንና በአንዳንድ በተግባር ስሁታን በሆኑ አገልጋዮች የተነሳ በዓለም የምናየው ዘረኝነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግዘፍ ነስቶ በተደጋጋሚ እያየነው ነው። ይህ ችግር በማስመሰልና በውሸት ብዛት ሊሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ቆይቷል። መፍትሔውም የችግሩን ምንጭ ተረድቶ ማስተካከል እንጂ በይስሙላ ማምታቻ ቀለም ቀባብቶ ማለፍ አይደለም። አንድ ሰው ከየትኛውም ወገን ቢወለድ በቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ማንነቱ ብቻ በእኩልነት እና በነፃነት ሊያገለግልና ሊገለገል ይገባዋል፡፡ የጎላ ማኅበራዊ ልዩነት መኖርም ሆነ አለመኖር ከክርስቲያናዊ አንድነት ጋር መምታታት የለበትም። ይህን መሰል መምታታት የሚፈልጉት በስውርም ሆነ ግልፅ ዘረኝነት መንፈሳዊውን ቦታ “የመደበቂያ ዋሻ” ለማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖቻቸው ናቸው። ከእነዚህ ለመጠበቅ ሕዝበ ክርስቲያኑ ማኅበራዊ ብዙኅነትን አገናዝቦ ክርስቲያናዊ አንድነቱን ማጠናከር ላይ እንዲያተኩር ማስተማር ይገባል እንላለን፡፡