ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት?

ዕቅበተ እምነት

መግቢያ

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በየዘመናቱ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ባሕታዊያን፣ ሰባክያን፣ አጥማቂዎች፣ ጠንቋዮች/ቃልቻዎች፣ ባለመድኃኒቶች፣ ነገሥታት ወዘተ ተነስተዋል። በሐሰት ትምህርታቸውም ብዙዎችን አስተው፣ ተከታዮችንም አፍርተው ገማልያል እንዳለው ከእግዚአብሔር ስላልሆኑ ጊዜያቸው ሲደርስ ጠፍተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን እስከ ጌታ ምጽአት ድረስ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ሐሰተኞቹ ዛሬም መልካቸውንና ስልታቸውን እየቀያየሩ ምዕመናንን እየተፈታተኑና እያሳቱ  ይገኛሉ።  የተነገረው ትንቢት ስለሚፈጸም ወደፊትም እንዲሁ በክርስቶስ ስም፣ በቅዱሳን ስም እንደሚነሱ እሙን ነው፡፡ ስለዚህ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ፣ እኔ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እኔ አርሴማ ነኝ፣ እኔ ኤልያስ ነኝ፣ እኔ ዮሐንስ መጥምቅ ነኝ’ ቢሉ ወይም ‘እገሌ የሚባል ቅዱስ፣ ነቢይ ወይም ሐዋርያ ተነስቷል ወይም ክርስቶስ ተናገረኝ፣ ድንግል ማርያም ተናገረችኝ’ ቢሉ ትንቢቱ እየተፈጸመ መሆኑን ማስተዋል ይገባናል እንጂ ሊገርመን አይገባም፡፡

በአንጻሩ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ራሳቸውን የሚጠብቁበት፣ ቤተ ክርስቲያንም ምዕመናንን የምትጠብቅበትና የሐሰተኞችን ቅሰጣ የምትከላከልበት የራሷ የሆነ የዕቅበተ እምነት (እምነት የሚጠበቅበት) አስተምህሮ አላት፡፡ ነገር ግን በዘመናችን በግልና በማኅበር የሚካሄዱ የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴዎች ከሐሰተኞች አስተምህሮ ይልቅ ግለሰቦቹን ዒላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ እውነተኛው የዕቅበተ እምነት አስተምህሮ ወደ ጎን እየተተወ ስሜታዊነትና ዓለማዊው የመጠቃቃት ስነ-ልቦና የተጫነው አካሄድ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ስለዚህ አንባቢያን ይህን ጠንቅቀው እንዲያዉቁና ራሳቸዉንም ከመምህራነ ሐሰት እንዲጠብቁ፣ ዘመኑን በዋጀ ሐዋርያዊ የዕቅበተ እምነት አገልግሎትም ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ የበኩላችንን ለማበርከት በማሰብ የዚህችን ጦማር ትኩረት ዕቅበተ እምነት ላይ አድርገነዋል፡፡

የሐሰተኞች ዓላማ

የዚህች ጦማር ትኩረት የሌሎች እምነት ተከታዮች (የሃይማኖት ድርጅቶች) ሳይሆኑ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ሐሰትን የሚያስተምሩ፣ የሐሰት ድርጊቶችን የሚፈጽሙና ምዕመናንን የሚያታልሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ሐሰተኞች በይዘት የተለያዩ የሚመስሉ ነገር ግን የተሳሰሩ ዓላማዎች አሏቸው። ብዙዎቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥና ውጭ ሆነው ምንፍቅናን የሚያስተምሩና እምነትን በመሸርሸር ምዕመናንን ከእናት ቤተ ክርስቲያን የሚለዩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ስም በምዕመናን ላይ የሚነግዱና ለራሳቸው ሀብትን የሚሰበስቡ ናቸው። እነዚህ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ምንም ከማድረግ የማይመለሱና እምነት የለሾች ናቸው። ከእነዚህም መካከል ርኩሳን መናፍስትን የሚስቡና በዚህም ፈውስን እንሰጣለን፣ “ዕጣ ፈንታችሁን” እንተነብያለን በማለት ምዕመናንን እያጭበረበሩ ገንዘብ የሚሰበስቡ ይገኙበታል። ከእነዚህ ለየት ያሉት ደግሞ የስነ–ምግባር ችግር ያለባቸው፣ ሙስናን፣ ዝሙትን፣ ቅጥፈትን እና የመሳሰሉትን በመፈጸም የታወቁና በንስሐም ከመመለስ ይልቅ በዚያው ምግባራቸው በመቀጠል ሥጋዊ ኑሮአቸውን የሚያመቻቹ ናቸው። እነዚህም የሐሰት አገልጋዮች (የሚናገሩትን የማይሠሩ) ስለሆኑ ከዚህ ይመደባሉ፡፡

በአጠቃላይ ሁሉም ሐሰተኞች ከእውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይልቅ ሐሰትን የሚዘሩ፣ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ፣ ምዕመናንን ለመጥቀም ሳይሆን በምዕመናን ላይ የሚነግዱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አልፎ አልፎ አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሆነዉ በከንቱ ፍልስፍናና በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ሐሰተኛ ትምህርትን የሚያስተምሩ አሉ። የእነዚህ ችግር በስልትና በስሌት ሐሰትን ከሚያስተምሩና በሐሰት ከሚነግዱት ተለይቶ መታየት ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ ወገኖችም ሕሊናቸውን ርኩስ መንፈስ ተቆጣጥሮት (ወይም የአእምሮ ህመምተኛ ሆነው) የሚናገሯቸውን ነገሮች እንደ ሐሰት ትምህርት የመቁጠሩ ነገርም ወደ መፍትሄ የሚያደርስ መንገድ አይደለም፡፡ አንድ ሰው የሚናገረውን ነገር እውነት ነው ወይም ሐሰት ነው ብሎ አስተያየት ከመስጠት በፊት ግለሰቡ አእምሮው ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ዕቅበተ እምነት

ዕቅበተ እምነት ስንል እያንዳንዱ ክርስቲያን እምነቱ፣ ሥርዓቱና ትውፊቱ ምን እንደሆነ በሚገባ ተረድቶ ራሱንና ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰተኛኞች ቅሰጣ የሚጠብቅበት ሂደት ነው፡፡ ስለ እምነታችን ነቢያት የተናገሩትን፣ ጌታ ያስተማረዉን፣ ሐዋርያት የሰበኩትን ሊቃዉንት የጻፉትን ጠንቅቆ ማወቅና መጠበቅ በቅድሚያ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ኃላፊነት (individual responsibility) ነው፡፡ ይህም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን (1ኛ ጴጥ 3:15)” ያለውን ቃል መፈጸም ነው። ከፍ ሲልም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ኃላፊነት ነው፡፡ ለምሳሌም አርዮስ መናፍቅ በተነሳ ጊዜ በቅድሚያ የተቃወሙት የሚያስተምራቸው ምእመናን እንደነበሩ መጻሕፍትና የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያስረዱናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ዕቅበተ እምነት ከእያንዳንዱ ክርስቲያን ጀምሮ የምንተጋለት አገልግሎት መሆኑን ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሐሰተኞች እንድንጠበቅ የምታስተምረው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ወንጌል፣ ሐዋርያት በሰበኩት ስብከት፣ ሊቃውንትም በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ሐሰተኞችን አሳፍረው ቤተ ክርስቲያንን ባጸኑበት መንገድ የሚፈጸም ነው። የጌታችን ትምህርት “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠበቁ (ማቴ 7:15)፣ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ( ማቴ 24:4)፣ በበረሃ ነው ቢሏችሁ አትውጡ፣ በእልፍኝ ነው ቢሏችሁ አትመኑ (ማቴ 24:30)፣ እውነተኛውን ቃል አስተውሉ፣ እስከመጨረሻው ጽኑ” የሚሉት ትምህርቶች መጠበቅን፣ መጠንቀቅን፣ መጽናትን መሠረት ያደረጉና ለክርስቲያኖች ሁሉ የተነገሩ ናቸው። ለእኛም ሕይወት እነዚህ መርሆቻችን ናቸው።

ክርስትናን እስከ ዓለም ዳርቻ ያስተማሩት ሐዋርያትም ከሐሰተኞች መጠበቅ እንዳለብን ያስተማሩት በዚሁ መንገድ የተቃኘ ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ (1ኛ ዮሐ 4:1)” በማለት መመርመር እንደሚገባን አስተምሯል።  ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና (2ኛ ጢሞ 3:2)” በማለት ጸንቶ መኖርን ነው ያስተማረው። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ስለ ሐሰተኞች ሲናገር “እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህንን (የሐሰተኞችን ቃሉን ማጣመም) አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ (2ኛ ጴጥ 3:17)” በማለት በሐሰተኞች የስህተት ትምህርት እንዳንወድቅ ጽፎልናል። በሐዋርያት እግር የተተኩት ሊቃውንትም ሐሰተኞችን በግል በማስተማር፣ መልእክት በመላክ፣ ጉባዔ ሠርተው ተከራክረው በመርታት ነው እውነተኛይቱ የተዋሕዶ እምነትን ያቆዩልን። ለዚህም በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ የተሰነዱት የቀደምት አባቶች መልእክታት ምስክሮች ናቸው።

ከጥንት ጀምሮ ያለው ምዕመናንን ከሐሰተኞች የመጠበቅ አገልግሎት በአራት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሐሰተኛ ሲነሳ በመጀመሪያ ደረጃ የሐሰት ትምህርቱ (ተግባሩ) ምን እንደሆነና እና ይህንን የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ ግለሰቦች (ቡድኖች) እነማን እንደሆኑ በሚገባ መለየት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃም የሐሰት ትምህርቱ (ተግባሩ) ለምን ሐሰት እንደሆነና በተነሳው ጉዳይ ላይ እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ምን እንደሆነ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማረጋገጥ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሐሰት ትምህርቱ ምን ያህል ተጽእኖ እንዳሳደረ በሚገባ መመርመር፣ የሐሰተኞቹን መነሻቸውን፣ የማጥመጃ ስልታቸውን፣ የመጨረሻ ግባቸውንና ያላቸውን ደጋፊ/ተከታይ በሚገባ ማወቅና ግለሰቦቹ የሐሰት ትምህርት (ተግባር) እንዲያቆሙ (የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት እንዳይጠቀሙ) ማድረግ ነው፡፡

በአራተኛ ደረጃም የሐሰት ትምህርቱን (ተግባሩን) መግለጥ፣ እውነተኛው ትምህርት (ተግባር) ምን እንደሆነ በሚገባ ማሳወቅ ሐሳውያኑና ተከታዮቻቸው ስህተታቸውን ተረድተው ከስህተታቸው እንዲመለሱ ጠንክሮ መሥራትና ካልተመለሱም አውግዞ ከክርስቲያኖች ህብረት መለየት የዕቅበተ እምነት ሥራ ነው፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ሳይቀር ይደረግ የነበረ የዕቅበተ እምነት ተግባር ነው፡፡ ዛሬም እንደ ጥንቱ በእንያንዳንዱ ደረጃ ሐሳውያኑና ተከታዮቻቸው ስህተታቸውን ተረድተው እንዲመለሱ የቤተ ክርስቲያን መምህራንና የሚቀርቧቸው ወዳጆቻቸው የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎ የማይመለሱ ከሆነና በሐሰት መንገዳቸው ለመቀጠል ከወሰኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ሐሰተኞቹን ጠርቶ በማነጋገር በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበትና ምዕመናንም ይህንን አውቀው እነዚህን የሐሰት መምህራንና ትምህርታቸውን እንዳይቀበሉ ማሳወቅ ቀጣዩ እርምጃ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ፍላጎት እነዚህ ሰዎች መለየታቸው ሳይሆን ከስህተታቸው መመለሳቸው ስለሆነ በማንናውም ጊዜ ስህተታቸውን ትተውና እውነተኛውን አስተምህሮ ተቀብለው ቢመለሱ እጇን ዘርግታ ትቀበላቸዋለች፡፡

የዘመናችን ዕቅበተ እምነት

ምንም እንኳን ትክክለኛው የዕቅበተ እምነት ተግባር ከላይ በተብራራው መንገድ የሚፈጽሙ አባቶችና ምዕመናን ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሐሰተኞችን የመከላከሉ አካሄድ በክርስትና አስተምህሮ መነጽርነት ሲታይ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ ሐሰተኞችን የመከላከሉ ሂደት የተጠናከረ ተቋማዊ ቁመና የሌለው፣ የሐሳውያኑ እንቅስቃሴ ሥር ከሰደደ በኋላ የሚጀመር፣ በአብዛኛው ማስወገዝን/መለየትን ግብ ያደረገ፣ ተነሳሽነት ባላቸው ግለሰቦች ወይም ማኅበራት እንቅስቃሴ ብቻ የሚመራና ከሐሰተኛ አስተምህሮው ይልቅ የሐሳቡ አቀንቃኝ ግለሰቦችን ብቻ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የተጠናከረ ተቋማዊ ቁመና የለውም።

ሐሰተኞችን የመከላከሉ ሂደት በአብዛኛው የራሳቸው ተነሳሽነት ባላቸው ግለሰቦች ወይም ማኅበራት እንቅስቃሴ ብቻ የሚመራ መሆኑ ግልጽ ነው:: የምናየውም ሐሰተኞችን የመከላከል አካሄድ (ትክክለኛውን የዕቅበተ እምነት ስራ የሚሰሩትን ሳይጨምር) መክሰስን፣ ማሳሰርን፣ ማሳደድን/ማባረርን፣ ማስወገዝን ትኩረት ያደረገ ይመስላል፡፡ በብዙ ቦታዎች የሚታየው አካሄድም የሐሰተኞችን ትምህርት በግልጽ ከመቃወም ይልቅ በስውር መረጃ መሰብሰብ፣ እንደሰላይ መከታተል፣ መረጃ ማጠናቀርና በሚዲያ ማሠራጨት፣ መስደብ፣ ማስፈራራት፣ አልፎ አልፎም አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ ከሀገር ማሳደድ፣ ማስወገዝ፣ ማሳገድ ወዘተ ናቸው፡፡

ይህ ያልተቀናጀና ያልተጠናከረ አካሄድ ሐሳውያኑ የልብ ልብ እንዲሰማቸውና በማን አለብኝነት እንዲፏልሉ አድርጓቸዋል፡፡ ለተከታዮቻቸውም ‘እገሌ የተባለው ግለሰብ ወይም ማኅበር የሚያሳድደኝ የራሱ የዕውቀት ጎዶሎነት ስላለበት፣ በአገልግሎቴ (በዝናዬ) ስለሚቀናብኝ፣ የራሱ ጥቅም ስለተነካበት፣ የዚህ ወገን/ዘር ስለሆንኩ ወይም እኔን በመቃወም ታዋቂነትን ለማግኘት ነው እንጂ የሃይማኖት ችግር ኖሮብኝ አይደለም’ በማለት በድፍረት ይናገራሉ። በተጨማሪም የተቀናጀና ተቋማዊ ይዘት ያለው አሠራር ባለመኖሩ ምዕመናን አቤት የሚሉበት የዕቅበተ እምነት አካል በአጥቢያና በሀገረ ስብከት ደረጃ የለም። የሐሰተኞችን ትምህርትም የሚቃወምና ሐሰተኞቹን ፊት ለፊት የሚናገራቸው ካለም በሕይወቱ ላይ አደጋ የሚያደርስ ወይም የሚያስፈራራ የጥቅም ሰንሰለት ስለሚኖራቸው አስቸጋሪ ይሆንበታል፣ አንዳንዴም የሚደግፈውም ላያገኝ ይችላል፡፡ በብዙ ድካምና ዋጋ የሐሰተኞችን ማስመሰል የሚከታተሉ ትጉሀንም በዚህ ያልተቀናጀ አሰራር ከአቅማቸው በላይ ያለ ብልሃት ሮጠው ይደክማሉ።

‘እሳት የማጥፋት’ ዘመቻ ነው።

የዘመናችን ዕቅበተ እምነት አካሄድ በጥቅሉ ሲታይ የሐሳውያኑ እንቅስቃሴ ሥር ከሰደደ በኋላ የሚጀመርና ‘እሳት የመከላከል’ ሳይሆን ‘እሳት የማጥፋት’ አካሄድ ይመስላል፡፡ አንድ ሐሰተኛ ሰባኪ ሲነሳ ሳይታወቅና ብዙዎችን ውስጥ ለውስጥ ሲመለምል ቆይቶ ብዙ ተከታይ ካፈራ በኋላ ነው ‘ዘመቻ’ የሚከፈትበት፡፡ ሐሰተኛ አጥማቂ/ፈዋሽም እንዲሁ በብዙዎች ከታወቀ፣ ገበያው ከደራና በሀብት ከፈረጠመ በኋላ ነው ትኩረት ውስጥ የሚገባው፡፡ ጠንቋይም ይሁን አስማተኛም ይሁን ሌላ በሐሰት የሚነግድ፣ እንዲሁም አማሳኝ ብዙ ጉዳት ሳያደርስና እውቅናና ዝናን ሳያተርፍ ገና በእንጭጩ የመከላከሉ ነገር እምብዛም ጎልቶ አይታይም፡፡ ይህም ቸልተኝነት ሐሰተኞቹ ብዙ ነፍሳትን እንዲያስቱና ብዙ ገንዘብ እንዲመዘብሩ አድርጓቸዋል። በተጨማሪም ይህ የቸልተኝነት አካሄድ በመጨረሻ ለሌላ አገልግሎት ሊውል የሚችለውን ጊዜና ሀብትን የየሚያባክን አካሄድ ነው። ምክንያቱም ሥር ከሰደዱ፣ ብዙ ሰው ከያዙና የገንዘብ አቅማቸውን ካፈረጠሙ በኋላ እነርሱን መዋጋት ዓመታትን የሚፈጅ፣ ብዙ ክትትልም የሚሻና መስዋእትነትም የሚጠይቅ ነውና፡፡

ግለሰቦችን ትኩረት ያደረገ ነው።

ሐሳውያንን የመከላከሉ ሂደት ብዙውን ጊዜ ከአስተምህሯቸው ይልቅ ግለሰቦቹንና የንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ ያተኮረ ነው። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚታየው አካሄድ የእነርሱን የሐሰት ትምህርት ለይቶ እውነተኛውን አስተምህሮ ከማሳወቅና ምዕመናንን ከመጠበቅ ይልቅ የግለሰቦቹን አጠቃላይ ማንነትን አደባባይ የሚያወጣ፣ ሰብእናቸውንና ሐሰተኛ ትምህርታቸውን ሳይለይ ጨፍልቆ የሚያጎድፍ፣ እንዲታረሙና እንዲመለሱ ሳይሆን እስከመጨረሻው ደብዛቸው እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው፡፡ እውነተኛውን ትምህርት እያስተማሩ ምዕመናንን ከመጠበቅ ይልቅ ከሐሰተኞች ጋር ፍልሚያ ውስጥ በመግባት የስድብ፣ የመበሻሸቅ፣ የፉከራ፣ የማስፈራራት፣ የዛቻ ወዘተ ተግባራት ክርስቲያናዊ ጠባይ የሌላቸውና ለሌላው አርአያ የማይሆኑ ናቸው። ለሚያደርጋቸውም የማያንጹ፣ ለሚመለከታቸውም የጦርነት እንጂ የሐዋርያዊነት ተግባር የማይመስሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ይህ አይነቱ መንፈሳዊ ይዘት የሌለው እንቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያንን መምህራን ጭምር በሕግ ፊት ሲያስቀርብ አስተውለናል።

ምዕመናንን ማስተማርና መጠበቅ እንጂ ሐስተኞችን ማጥቃትና ማሳደድ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ አይደለም። የመጠቃቃት አካሄድም ቤተ ክርስቲያንን ከመንፈሳዊ አውድ ይልቅ የፉክክርና የፍልሚያ መድረክ ያደርጋታል። “ልክ እናስገባቸዋለን” እያሉ መፎከርም ቢሆን ስሜታዊነት እንጂ መንፈሳዊነት አይደለም። ሐሰተኛ ትምህርታቸው (ድርጊታቸው) በግልጽ ተተንትኖ ባልቀረበበት ሁኔታ ሐሳውያኑ ‘የምታሳድዱን ተከታይ ስላገኘን፣ እውቅና ስላተረፍን፣ ሀብት ስላፈራን ቀንታችሁ ነው’ እያሉ የሚያቀርቡትን ማስመሰያም ለማስተባበል ያስቸግራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥቂት የማይባሉ ኦርቶዶክሳውያን በሐሰተኞቹ መጎዳት፣ መታሰር፣ መወገዝና መለየት፣ መሰደድና መጥፋት ደስታቸውን ሲገልጹ ማየት ሌላው አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው። በእውነት ለሚጠፋው ሕዝብ አዝነን እነርሱም እንዲመለሱ ፈልገን ብንሠራ እንዲህ አይነት በጥፋት የመደሰትን ልማድ አናይም ነበር። ክርስቲያን መደሰት የሚገባው በሐሳውያኑ መመለስ እንጂ መጎዳት ወይም መለየት መሆን የለበትም።

ግለሰቦችን ትኩረት ያደረገ የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴ መሠረታዊ ለውጥ ስለማያመጣ አንዱ ሐሳዊ ሲረታ ሌላው በቦታው እንዲተካ የሚያደርግ (ክፍት ቦታ የሚፈጥር) አካሄድ ነው። ምክንያቱም የሐሰቱን ትምህርት ሳይሆን ግለሰቡን ከቦታው ዞር የሚያደርግ ነውና። ‘ተነጂ እስካለ ነጂ አይታጣም’ እንደሚባለው ምዕመናንን በሚገባ እስካልተማሩ ድረስ አንዱ ሐሰተኛ ቢሄድ ሌላ መጥቶ ያሳስታቸዋል። በሌላም በኩል አስተምህሮ ላይ ሳይሆን ግለሰብ ላይ ያተኮረ አካሄድ በጠንካራ አቋማቸው የሚታወቁና በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ስህተቶችን የማይታገሱ ክርስቲያኖች በምንደኞቹ “ቆርጦ ቀጥል” ስም እየተሰጣቸው እንዲሳደዱ አድርጓል። ምንደኞችን እንደየዓመላቸው መያዝ የቻሉ ሐሰተኞች ደግሞ በተድላና በደስታ እየኖሩ ምንፍቅናቸውን ሲያስፋፉ አንዳች እንኳ የሚናገራቸው የለም።

ሐሰተኞቹን የሚያስተዋውቅ ነው።

በዘመናችን ሐሰተኞችን ለማጋለጥ የሚደረገው በአግባቡ ያልታቀደ የሚዲያ ዘመቻ ሐሰተኞን በነፃ ለሕዝብ የሚያስተዋውቅ እንደሆነ እየታየ ነው። የእነርሱን የተንኮል መንገድም ብዙ ጊዜ ወስዶ (ለዛውም በቂ ትምህርትና ምላሽ ሳይሰጥበት) በየዐውደ ምሕረቱ እየደጋገሙ መለፈፉ ምዕመናን ግራ እንዲጋቡ ያደርጋል፣ ውድ የሆነውን የወንጌል መማርያ ጊዜም ያባክናል። የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዲሰበክበት እንጂ ስለሐሰተኞች ከበቂ በላይ እንዲሰበክበት መፈቀድ የለበትም። የሐሰተኞችን ትምህርት በቂ ምላሽ ሳይሰጡ በየማኅበራዊ ሚዲያው ማሰራጨትም ከእነርሱ ጋር እንደመተባበር ነው። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ነገ ሌሎች በእነርሱ መንገድ እንዲሄዱ ጤናማ ዕውቀት ሊሰጥ እንደሚችልም መጤን ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሌላ በስውርም ሆነ በግልጽ የእነርሱን መንገድ ከሚከተል/ከሚደግፍ አካልም ድጋፍ እንዲያገኙ ጉልበት ሊሆናቸው ይችላል፡፡ አንዳንዴም ዘመቻ የተከፈተባቸው በሐሰት ትምህርታቸው ሳይሆን በማንነታችን (በዘራችን) ነው ብለው ለማወናበድ በር ይከፍትላቸዋል። ከዚህ አንጻር ስህተቱ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆናል።

ለእውቅናና ገንዘብ ማግኛነት እየዋለ ነው።

ይህ ያልተቀናጀና ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴ ለአንዳንድ ሰባክያን እውቅናና ገንዘብ ማግኛነት እየዋለ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለታዋቂ ሐሳውያን መስበክና መጻፍ ተገቢ ቢሆንም ዓላማው ምዕመናንን ለመጠበቅ እንጂ ‘ማወቅን ለማሳወቅ’ ወይም እንደ ስቴዲየም አስጨፋሪ ጡሩምባ እየነፉ ታዋቂነትና ዝናን ለማትረፍ ወይም የተሻለ ቢዝነስ ለመሥራት መሆን የለበትም። ዕቅበተ እምነት በይድረስ በይድረስ ለተዘጋጁና ግለሰቦችን ትኩረት ላደረጉ መጻሕፍት፣ ሲዲ፣ ቪሲዲ፣ ስብከት ማሻሻጫ መሆኑ ሲታይ ሐሰተኞችን የምንከላከልበትን አካሄድ መልሰን መቃኘት እንዳለብን ያመለክተናል። ይህ አካሄድ መንፈሳዊነቱ የደበዘዘ፣ ቢዝነስነቱ (ንግድነቱ) የጎላ፣ ስሜታዊነት የሚያይልበት፣ እውነተኛውን ትምህርት በተገቢው መንገድ የሚያስረዳ ሳይሆን ለተጠየቃዊ አካሄድ የማይመች የሰነፎች መንገድ የሚሆንበት ጊዜ ቀላል አይደለም። የመናፍቃን መነሳት እውነተኛ መምህራንን ማንቃት ሲኖርበት ሁሉንም አጋጣሚ መነገጃ ለሚያደርጉ ሰዎች ቢዝነስ ማስተዋወቂያ ሲሆን ታዝበናል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ መምህራን የትምህርታቸውንና የመጻሕፍቶቻቸውን ርዕስ ሳይቀር ‘እገሌ ለተባለ ሐሳዊ መልስ’ ብለው  በታዋቂ ሐሰተኞች ስም በመሰየም የሐሰተኞችንና የራሳቸውን ስም አብረው ሲያስተዋውቁ ይታያሉ። ይህንን ስንል ግን ያለው አካሄድ እንዲሻሻል ካለን ፍላጎት እንጂ በመልካም መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚተጉትን ለመንቀፍ አይደለም።

ለማጥቂያነት እየዋለ ነው

አንድን ሰው “መናፍቅ” ብሎ ለመለየት መመዘኛ መሆን ያለበት መንፈሳዊ አስተምህሮ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው። ይሁንና በታሪክ ትንታኔ የማይስማማቸውን፣ በፖለቲካዊ አቋም የሚቃረናቸውን፣ በልዩ ልዩ ምድራዊ የልዩነት ምክንያቶች “የእኔ” ከሚሉት ቡድን የተለዩ ሰዎችን ለማጥቃት፣ የማያምኑትን ክህደት እንደሚያምኑ፣ የማያስተምሩትን ምንፍቅና እንደሚያስተምሩ እየተደረጉ በሐሰት ምስክር ተገፍተው ከቤተ ክርስቲያን በተቃርኖ እንዲቆሙ የሚደረጉ ሰዎችም አሉ። በአንፃሩ ደግሞ መንፈሳዊ አስተምህሮው የለየለት መናፍቅ ሆኖ በዘር ቆጠራ፣ በፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ መመሳሰል የተነሳ ቢቻል የሚሸለም ባይቻል ነገሩ “በደምሳሳው” የሚታለፍለት አለ። ከዚህ በላይ እግዚአብሔር የሚጠላው ግፍ የለም። ለቤተ ክርስቲያን ክብር የሚደረግ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት የሚወዱትን ለማቅረብ፣ የሚጠሉትን ለማጥቃት መዋል የለበትም።

የሚያንጽና የሚያጸናው አካሄድ

ከሁሉም አስቀድሞና ከሁሉም በላይ የምናምነው አምላክ ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰተኞች እንዲጠብቅልን አጽራረ ቤተክርስቲያንን እንዲያስታግስልን በጉባዔም በግልም ሁል ጊዜ በጸሎት መጠየቅ ይገባናል። ነቢየ ልኡል ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል (መዝ 126፦2)።” እንዳለ እግዚአብሔርን በጸሎት ልንጠይቅ ይገባል።

ምዕመናንን በሚገባ ማሳወቅ

የሐሰተኞችን አስተምህሮ ለመከላከልና ምዕመናንን ለመጠበቅ ቀደምት አባቶቻችን ሲያደርጉት እንደነበረው ምዕመናንን በሚገባ ማስተማርና በመንፈሳዊ ዕውቀትና ክህሎት ማብቃት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ምዕመናንም በሐሰተኞች ምክንያት የሚሳሳቱት በቂ ትምህርት ባለማግኘታቸው የተነሳ ስለሆነ በዋናነት ሊተኮርበት የሚገባው አገልግሎት ይህ ነው፡፡ መጽሐፍም ከሐሰተኞች ተጠበቁ የሚለው መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አውቀን ከሐሰት ትምህርት እንጠበቅ ዘንድ ነውና ዋናው ማስተማር ነው፡፡ በጎችን በዱር በትኖ ተኩላን በተኩላ ላይ የሚፈርድ እረኛ ትርፉ ምንድን ነው። የአገልጋዮችም ድርሻ ተኩላዎችን አድኖ ማጥፋት ሳይሆን በጎችን መጠበቅ ነው።

ምዕመናን በሐሰተኞች እንዳይወሰዱ ማስተማር ያስፈልጋል ሲባል የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ መሠረታዊ የእምነት ትምህርት ማስተማር ማለት ነው እንጂ “እገሌ የሚባል ሐሳዊ እንዲህ ይላል” እያሉ ማስተማር አይደለም፡፡ በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነት ሥርዓትና ትውፊት በደንብ ሳያስተምሩ የመናፍቃንን አካሄድ መተንተን ምዕመናንን አያንጽም። በባዶ ፉከራም ማጥላላቱ እንዲሁ እርባና የሌለው ጩኸት ነው። የሐሰተኞች ትምህርት ለማስረዳት ያህል ይጠቀስ ካለሆነ በቀር የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ትምህርት ቦታ ወስዶ መሠጠት የለበትም፡፡ መጻሕፍትም ሲዘጋጁ እንዲሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል እንጂ “እገሌ ለሚባል ሐሳዊ መልስ” ተብለው ሐሰተኞችን ዒላማ አድርገው መዘጋጀታቸው ገንቢ አይደለም፡፡

የሐሰት አስተምህሮን ከጅምሩ መከላከል

በሚገባ የተማረ ምዕመን ቤተ ክርስቲያንን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡ ሐሰተኛ ትምህርትም ሲኖር ገና ከጅምሩ ቶሎ መከላከል እንዲቻል ይረዳል፡፡ ሐሳዊያንም ሥር ሳይሰዱ፣ ብዙ ሰው በሐሰተኛ ትምህርታቸው ሳይበክሉ ለመከላከል ይረዳል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያን ሐሰተኞች ገና ተከታይ ሳያፈሩ መለየትና ማረም ትችላለች፡፡ ጉዳትም ሳያደርሱ በቀላሉ መከላከል፣ ወደ ቀናው መንገድ መመለስም ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር የተሻለው አካሄድ በየአጥቢያው ምዕመናንን በሚገባ አስተምህሮ ከካህናትና ከሰባክያነ ወንጌል ጋር በመሆን የሐሰተኞች እንቅስቃሴ ገና አዝማሚያው ሲታይ ለምዕመናኑ መረጃን በማድረስ ሁሉም ራሱን እንዲጠብቅና ለሌላውም እንዲያሳውቅ በማስታወስ ሐሰተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርገውን አካልም በተለያየ መንገድ በመቅረብ ማስተማር፣ መምከርና መመለስ የሚያስችል አሠራር መፍጠር ያስችላል፡፡

መዋቅራዊ አሠራርን ማጠናከር

ሐሳውያኑ ምንጊዜም ስልማይጠፉ ችግሩን ራሱ ተከታትሎ መፍትሔ የሚሰጥ እና የዕቅበተ እምነት አገልግሎቱን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር ጠንካራ የቤተክርስቲያን መዋቅራዊ አካል እና አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባለመኖሩ ምክንያት የሐሰተኞችን እንቅስቃሴን ለመመከት በሚል ሌላ የገንዘብ ማግኛ መንገድ እንዲከፈት እየሆነ ነው፡፡ ሐሰተኞቹ ምዕመናንን በአንድ በኩል ሲመዘብሩ አንዳንድ የእኛው አገልጋዮች ደግሞ በዚህ በኩል እገሌ ስለሚባለው ሐሳዊ ትምህርት እንሰጣለን እያሉ በምዕመናን ላይ ሲነግዱ ከሐሳውያኑ ጋር ተማክረው የሚያደርጉት ሁሉ ያስመስላል፡፡ ይህ ችግር የሚፈታው ጠንካራ መዋቅራዊ አሠራር ሲኖርና ምዕመናንና ካህናት አካሄዳቸውን መንፈሳዊ በማድረግ ብቻ ነው፡፡

ለሐሰተኞቹ በር የከፈቱ ክፉ ልማዶችን ማስወገድ

ሐሰተኞቹ በብዛት የሚከተሏቸው ማሳሳቻዎች በምንደኛ አገልጋዮች መስመራቸውን በሳቱ አንዳንድ መደበኛ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ለገንዘብ ማግኛነትና ለከንቱ ውዳሴ መሰብሰቢያነት የሚውሉ አሠራሮችን ነው። የተሳሳተ አካሄድን በመጠኑ የተለማመደ ምዕመን ለሐሰተኞቹ  የተጋነነ ቅሰጣ የተመቸ እርሻ መሆኑ አይቀርም። ከእነዚህ ክፉ ልማዶች ውስጥ የእውነትም የሐሰትም ተዓምራትን ለገቢ ማስገኛነት መጠቀም፣ ለጸሎት ገንዘብ መቀበል፣ በራዕይና ሱባኤ ሰበብ ምዕመናንን ለፕሮቴስታንታዊ የውሸት መገለጥ ማመቻቸት፣ ቁሳዊ ልማትንና ገንዘብ ማስገኘትን የመንፈሳዊ አገልግሎት ግብ አድርጎ ማየት፣ ታቦታትን በማቃለል በአንድ ቦታ ድርብርብ ንግሥ ማድረግ፣ ካህናትና መምህራን የሕዝብ አገልጋዮች መሆናቸው ቀርቶ እንደ ዓለማዊ ዝነኞች አለባበስና ፎቶ አነሳስ እያሳመሩ በውሸት አንቱታ ነግሠው ሥራ ሳይሠሩ የምዕመናንን ገንዘብ የሚበሉባቸው አሠራሮች ተጠቃሽ ናቸው። በመንፈሳዊ ቦታ ያገኙትን እውቅና ለገንዘብ ማግኛነትና ለሚወዱት ፖለቲካዊ አሰላለፍ በማዋል ምዕመናንን በየጎሬያቸው ማስከተል ከመለመዱ የተነሳ ባለፉት ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት ከግላዊ ከንቱ ውዳሴ እንዲርቅ ይደክሙ የነበሩ ግለሰቦችና ማኅበራትም በጎርፉ ተወስደው ፕሮቴስታንታዊ ልማዱን በመከተል የራሳቸውን “ለፎቶ የሚመቹ፣ ሰው ሊከተላቸው የሚችል፣ ታይታ የሚወዱ” ሰዎች ወደማከማቸት ሲያዘነብሉ እያየን ነው። ይህን የሚያደርጉትም ለሃይማኖታዊ አቋም ሳይሆን በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምልከታ ተጠልፈው መሆኑን የሚያሳዩ ጠቋሚዎች ብዙ ናቸው።

እነዚህ ክፉ ልማዶች ለሐሰተኞች መፈልፈል የተመቸ ሜዳ ይፈጥራሉ። ብዙዎቹ ሐሰተኞች በምንደኞች የተከፈተውን የስህተት መንገድ በማስፋት ያለሀፍረት ለጸሎት ገንዘብ ይጠይቃሉ፣ ስለራሳቸው ክብር አብዝተው ያወራሉ፣ ያስወራሉ። ምዕመናን እንደ አቅማቸው ጥረው ወደ ጽድቅ ጎዳና ከመመለስ ይልቅ በተዓምራት ተስፋ እንዲያደርጉ አስረው ያስቀምጧቸዋል። ከላይ በተገለፁት የተሳሳተ የአገልግሎት አቅጣጫዎች የተማረኩ ምዕመናንም ከመንፈሳዊ ሚዛን ይልቅ አለባበስ፣ ስምና ተዓምራት የሚመስጣቸው ሆነዋል። በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከመንፈሳዊ አስተምህሮ ይልቅ መስማት የሚፈልጉት ፖለቲካዊ ትንታኔና ተአምራታዊ መፍትሔ ነው። ሐሰተኛ መምህራንም ይህን በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ተለይቶ በሚታወቅ ዓለማዊ እውቀት (Standardized secular knowledge) የማይመራ ግልብ ማኅበራዊ መሠረት (social base) በሚገባ ይጠቀሙበታል። ስለሆነም ከእምነትና ዕውቀት ይልቅ በስሜትና በእልህ የሚመሩ “ምዕመናንን” ለማብዛት እንዲሁም ለገንዘብ፣ ለዝና እና ለፖለቲካዊ ዓላማ ሲባል በመልካሙ እርሻ ላይ የሚዘሩ አረሞችን በእምነትና በዕውቀት ተመርተን በማስወገድ የሐሰተኞችን የመባዛት አቅም መቀነስ ይገባናል።

መልእክተ አስተምህሮ

በአጠቃላይ ሐሰተኞችን የምንከላከልበት መንገድ የሚያንጽና የሚያጸና ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይም ከቤተክርስቲያን አስተምህሮና ከዓለማዊ ሕግ ጋር አብሮ የሚሄድና የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የዋጀ አሠራርን ይጠይቃል፡፡ ሐሰተኞቹን በሰውነታቸው ማጥቃት ላይ ሳይሆን ማስተማር ላይ በማተኮር፣  ሐሰተኞችን ከማሳደድ ይልቅ ምዕመናንን በሚገባ መጠበቅ ላይ መትጋቱ ይበጃል፡፡ ሐሰተኞችን የመከላከሉ እንቅስቃሴም ከግለሰቦቹ ይልቅ የሐሰት ትምህርታቸው/ተግባራቸው ላይ የበለጠ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ ምዕመናንን መጠበቅ የሚቻለው የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን እውነትነት፣ የሐሰተኞችን ቅሰጣ ስህተትነትን በሚገባ ለይቶ በማሳየት መሆን ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል ወንጀል የፈጸሙ ሐሳውያን በሕግ መጠየቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሐሳውያንን በግለሰብ ደረጃ ከመስደብ፣ ከመክሰስ፣ ከማስፈራራትና ከማሳደድ ይልቅ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድና ግላዊ ስብእናቸውን ባከበረ መልኩ ትምህርት መስጠት ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ግለሰቦቹና ግብረ አበሮቻቸው ሐሰትን በማስተማርና ምዕመናንን በማሳሳት ቤተ ክርስቲያንን ቢጎዱም እነርሱ ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከር ራስን በኃጢአትና በወንጀል ውስጥ መክተት፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንንም የበለጠ መጉዳት ነው፡፡ በመጨረሻም ምዕመናንን ከሐሳውያን ለመከላከል የሚተጉ አገልጋዮች ለዝናና ለመታወቅ ሳይሆን ምዕመናንን ከሐሰት ትምህርት መጠበቅን ብቻ ዓላማ አድርገው እንዲያገለግሉ በታናሽ ወንድምነት እንመክራለን፡፡

1 thought on “ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s