ንግሥ እና ንግድ: የተቀደሰውን የማርከስ ክፉ ልማድ

nigs and nigd
መግቢያ

በዓለ ንግሥ ማለት ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔር ያከበራቸው፣ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታቸውና ምግባራቸውን መርምራ በጸሎታቸው ምዕመናን እንዲጠቀሙ፣ ከሕይወት ልምዳቸው መንፈሳዊነትን እንዲማሩ ብላ በቀኖና የወሰነቻቸው ቅዱሳን ሰዎች፣ መላእክት እንዲሁም የሁሉም አስገኝ አምላካችን እግዚአብሔር ሰማያዊ ክብር (ንግሥና) የሚታሰብበት የከበረ በዓል ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማይ የተገኘ መንፈሳዊ ሥርዓትም በዓለ ንግሥ በዕለቱ በሚከበረው ቅዱስ የተሰየመ ታቦት በካህናትና ምዕመናን ታጅቦ መንፈሳዊ ደስታን በማድረግ የሰማዩን ክብር በምድር የምንገልጥበት ልዩ መንፈሳዊ እሴት ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን መንፈሳዊ በዓል ለንግድና ለልዩ ልዩ ሸቀጥ ማራገፊያ፣ ለገቢ ማስገኛ እንዲሁም መንፈሳዊነት ለተለያቸው ልዩ ልዩ ግብሮች መፈፀሚያ የማድረግ ልማድ እየተንሰራፋ ይገኛል። በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ንግሥ ለማብዛት መንፈሳዊነቱን በለቀቀ አሠራር ታቦታትን መደረብ፣ የቤተክርስቲያኑን ስም ለንግድ በሚመች መልኩ የሁለትና ሦስት ቅዱሳንን ስም ጨምሮ መቀየር፣ የንግሥ በዓሉንም እንደ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ቀን በመቁጠር የተቀደሰውን ንግሥ የማርከስ የተቀናጀ አሠራር እየታየ ነው።

የቤተክርስቲያን የንግሥ በዓላት የእግዚአብሔር የክብሩ መግለጫ የሆነው ታቦተ ህግ ከመንበሩ ተነስቶ ሕዝቡን የሚባርክበት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ቃለ ወንጌልን በልዩ ሁኔታ የሚማሩበት፣ ሊቃውንቱ በማኅሌት፣ ሰንበት ተማሪዎችም በመዝሙር ሁሉም እንደየጸጋው እግዚአብሔርን የሚያመልክበትና የሚያመሰግንበት ቅዱሳንንም የሚያከብርበት ዕለት ነው። የንግሥ በዓል አጠቃላይ ዓላማም ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት በልዪ ሁኔታ እንዲከናወን ማስቻል ነው። በዘመናችን ግን ከዚህ በተቃራኒው የንግሥ በዓላትን ለገንዘብ ማስገኛነት የማዋል ነገር በስፋት ይታያል። ብዙ ምዕመናንም በዚህ የተቀናጀ የልመናና የንግድ እንቅስቃሴ እየተማረሩ ይገኛሉ። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የዚህን ችግር ዓይነትና ስፋት፣ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች፣ የሚያደርሳቸውን መንፈሳዊ ጉዳቶችና ይረዳሉ ያልናቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች ተዳስሰዋል።

ምስል ከሳች አውድ

በአንዱ ከተማ በአንዱ የንግሥ ቀን በጠዋት ተነስተው ንግሥ ለማንገሥ ወደ ቤተክርስቲያን ሲቃረቡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ለኑሯቸው ሲሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የሚሸጡ ወገኖችን ያያሉ። በዚያውም በመስመር ተቀምጠው የምግብና የገንዘብ ምፅዋት የሚለምኑ ነዳያንን ያገኛሉ። እነዚህ ሁለቱም ወገኖች በድህነትና በኑሮ መጎሳቆል የተጎዱ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያየ አካላዊና አዕምሮአዊ ችግር ምክንያት ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ቤተክርስቲያንን የተጠጉና የሁላችንንም እርዳታ የሚሹ ናቸው። እነዚህን መርዳት ሰማያዊ መዝገብን ማከማቸት መሆኑ እሙን ነው። ጌታችን እንዳስተማረን ምፅዋት በሰው እጅ የማይፈርስ፣ የማይወሰድ ሰማያዊ መዝገብ የምናከማችበት ክርስቲያናዊ ምግባር ነው። በንግሥ በዓላትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት የተቸገሩትን ሁሉ በአቅማችን መርዳት መንፈሳዊ ዋጋው ታላቅ ነው። መሠረታዊው ጥያቄ ግን “የምንረዳቸው በመንገድ ዳር ጥቂት ገንዘብ በየጊዜው በመጣል ነው ወይስ ከዚህ የተሻለ የሠለጠነ አሠራርን በመዘርጋት ነው?” የሚለው ነው።

እነዚህን ወገኖች ተዘክረው/አልፈው ወደ ቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ሲዘልቁ ደግሞ ብዙ ምዕመናን ቆመው ከመቅደስ የሚፈሰውን ዜማ ሲያዳምጡ ያገኛሉ። በእነዚህ ምዕመናን መካከል እየተሯሯጡ የተለያዩ መጻሕፍትን፣ የቶምቦላ/የዕጣ ትኬት፣ የመዝሙርና የስብከት ቪ/ሲዲዎችን፣ የአንገት መስቀል፣ የአንገት ማዕተብ፣ ጧፍና ሌሎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመሸጥ የሚፋጠኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ልብስ የለበሱ ወጣቶችን ያያሉ። አንዳንድ በሰው መካከል እየተሽሎከሎኩ የሰው ንብረት ወስደው የሚሠወሩም በዚህ አይጠፉም።

ወደ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሲገቡ ግን ሊቃውንቱና ካህናቱ ሌሊቱን በማኅሌት ሲያመሰግኑ አድረው፣ ጠዋት ላይ ኪዳን አድርሰው፣ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት ልዩ የሆነውን ያሬዳዊ ዝማሬ ሲያንቆረቁሩት ያገኛሉ። እርሰዎም ከዚህ ልዪ በረከትን ተሳትፈው፣ ቅዳሴውን ያስቀድሳሉ። ቅዳሴው እንዳለቀ የንግሱን መርኃግብር የሚመራ አንድ ሰው ወደ አውደምሕረቱ ብቅ ይልና የቀሩትን መርኃግብሮች ያስተዋውቃል። ትምህርተ ወንጌል፣ መዝሙር በግልና በማኅበር፣ የሰበካ ጉባዔና የልማት ኮሚቴ ሪፖርት ወዘተ… ይልና ለገቢ ማስገኛነትና ለሽያጭ የተዘጋጁ የተለያዪ ዓይነት ቁሳቁሶችንም ያስተዋውቃል።

ከዚያም ታቦተ ሕጉ በዝማሬና በእልልታ ታጅቦ ከመንበሩ ተነስቶ ሕዝቡን እየባረከ ወደ ውጭ በመውጣት ዑደት አድርጎ በፊት ለፊት ባለው አውደ ምሕረት ይቆማል። ካህናት እና/ወይም የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ወረብ ያቀርባሉ። ከዚህ በኋላ የዕለቱን በዓል የሚመለከት ትምህርት ተሰጥቶ የመርኃግብሩ ፍፃሜ ቢሆን የሁሉም ደስታ ነበር። ነገር ግን የሚቀጥለው መርኃግብር ነው ምዕመኑን እጅግ የሚያሳዝነው። የተለያዩ የሽያጭ ማስታወቂያዎች፣ ስዕለት ያስገቡ ሰዎች ስም እየተጠራ እልልታና ጭብጨባ፣ የዕጣ/ቶምቦላ ማስታወቂያ፣ ለተለያዪ ጉዳዪች ርዳታ አድርጉ የሚል ጉትጎታ፣ ከዚያም እጅግ የተንዛዛና የቤተክርስቲይንን መንፈሳዊነት ሳይቀር የሚፈታተን ጨረታ፣ ግዙልኝ ግዙልኝ የሚሉ ዘፋኝ መሳይ የግል ዘማርያን የሚያቀርቡት “መዝሙር”፣ የተለያዩ ኮሚቴዎች ሪፓርት ወዘተ… ሰውን አማርሮት “መቼ ይሆን የሚጨርሱት? መቼም ታቦት ሳይገባ መሄድ ይከብዳል!” እያለ ፀሐይ እየበላው የኋላ ኋላ የንግሥ በዓሉ ፍፃሜ ይሆናል።

ንግሥና ንግድ: የችግሩ ዓይነትና ስፋት

በቤተክርስቲያን የሚታየው የንግሥና የንግድ ቁርኝት በሁለት ደረጃዎች ተከፍሎ ሊታይ ይችላል። የመጀመሪያው ገንዘብ ማግኘትን ዓላማ ያደረገ ንግሥን የማብዛት ዝንባሌ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያሉትን የንግሥ በዓላት ለንግድ ዓላማ የማዋል እንቅስቃሴ ነው። የመጀመሪያው  መንገድ ሕዝብ በጣም ይወዳቸዋል በሚባሉት ቅዱሳን ስም ‘ደባል ታቦት’ በማስመጣት በዓመት ውስጥ የሚከበሩትን የበዓላት ቁጥር መጨመር ነው። ለቅዱሳን ያለን ክብር የሚታወቀው አጥቢያ ቤተክርስቲያኑ በመታሰቢያነት ከተሰጠው ወይም ከተሰጣት ቅዱስ ሌላ ታቦት በመደረብ አይደለም። ይህን በታቦት የመነገድ ክፉ ልማድ አባቶቻችን አላወረሱንም። ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ ከሆዳቸውና ከገንዘብ በቀር ምንም የማይታያቸው ሰዎች ባለፉት ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት እያባዙት የመጡት አሠራር ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ይህ ነውር ሁሉም ነገር መነገጃ በሆነባቸው ከተሞችና የዲያስፖራ አብያተክርስቲያናት ብቻ የሚገን መሆኑ ነው።

በብዙዎች ዘንድ ንግሥ ለማብዛት የሚደረገው እሽቅድምድም መንፈሳዊ እንዳልሆነ ይታወቃል። በተለይም መሠረታዊ ስህተት የሚሆነው ዓላማው የቅዱሳንን ክብር ለመዘከር መሆኑ ቀርቶ ‘የትኛው ቅዱስ የተሻለ ገቢ ያስገኝልናል?’ የሚለውን ስሁት አስተሳሰብ መነሻ ሲያደርግ ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ አጥቢያዎች በዓመት ዋናውን የጥምቀት በዓል ጨምሮ በሁለት አኃዝ የሚቆጠሩ የንግሥ በዓላትን እስከማክበር ደርሰዋል። አንድም ቋሚ ቄስ የሌላቸው አጥቢያዎችን ጨምሮ በክፉ የእሽቅድምድም መንፈስ የከበሩ ታቦታትን መነገጃ የማድረግ ግልፅ የወጣ ነውረኝነት ተንሰራፍቷል። ሁለትና ሦስት ቄስ ያላቸው ደግሞ እንደተራ ሸቀጥ ለቁጥር የሚታክቱ ንግሦችን ሲያከብሩ “ልደቴ በየወሩ ይከበርልኝ” የሚል ቂላቂል ልጅን ይመስላሉ። ለምሳሌ በአንድ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት የውጭ ሀገር ከተማ እስከ አምስት የሚደርሱ ታቦታትን በመደረብ በዓመት እስከ አስር የሚደርሱ “ንግሦችን” ማድረግ ቀስ በቀስ እየተለመደ ነው። ይህ አካሄድ በተለይ ብዙ መቧደኖች ባሉበት የዝርወት ዓለም ምዕመናን ወደ ሌላ አጥቢያ እንዳይሄዱ ለመከልከል በሚመስል መልኩ “እኛም ጋር ታቦቱ አለ፣ ወደ ሌላ አጥቢያ አትሂዱ” የምትል ምክንያትን ለመፍጠር ሲደረግ አስተውለናል።

በሁለተኛ ደረጃ ያለው ደግሞ ባሉት በንግሥ በዓላት ላይ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ነው። ይህም ቃለ ወንጌልን ለመማርና ምስጋናን ለማቅረብ በንግሥ ዕለት የሚመጣውን ምዕመን እያማረረ ያለና አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው ችግር ነው። በንግሥ በዓላት ላይ አሰልቺ የሆነ ጨረታ፣ ቶሎ ተሸጦ የማያልቅ ቶምቦላ፣ ዪኒፎርም በለበሱ ወጣቶች የሚዞሩ ነገር ግን በይድረስ ይድረስ የታተሙና የረባ ይዘት የሌላቸው መጽሔቶች እና ቪ/ሲዲዎች የንግሥ ላይ ንግድ መገለጫዎች ናቸው። በመድረክ ላይም ታቦት አቁሞ እነዚህን ቁሳቁሶች ማሻሻጥ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት የጣሰ ከመሆኑም ባሻገር ቤተክርስቲያንን ለትችትና ለነቀፋ የሚዳርግ ነው።

ንግሥና ንግድ: መንስኤ ምክንያቶች

በንግሥ በዓላት ላይ የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ለመብዛቱ እንደምክንያት የሚነሳው የቤተክርስቲያን ገቢ ማነስ እና የተለያዩ ‘የልማት’ ሥራዎችን ወጪ ለመሸፈን የሚል ነው። የቤተክርስቲያን አገልግሎትም ሆነ የልማት ሥራዎች ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው። ነገር ግን ይህ ገንዘብ መገኘት ያለበት ምዕመናን በግልፅ በፈቃዳቸው ለቤተክርስቲያን ብለው በሚሰጡት አሥራት፣ በኩራት፣ መባዕ/ምጽዋት ነው እንጂ በንግሥ በዓላት ላይ ምዕመናንን በሚያማርር የንግድ እንቅስቃሴ መሆን የለበትም። የሰው ልጅም ጽድቅን የሚያገኘው በነፃ ፈቃዱ ካለው ከፍሎ በመስጠት ነው እንጂ በመግዛት (ሰጥቶ በመቀበል) አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያንም ሰዎችን ለዚህ ክብር እንዲበቁ መስጠትን ልታስተምር ይገባል እንጂ በምዕመናን ላይ እንዲነገድባቸው መፍቀድ የለባትም፡፡

ሌላው ለዚህ ዓይነት ንግድ የሚጠቀሰው ምክንያት “ለሕንፃ ግንባታና ለሌሎች የልማት ሥራዎች ገንዘብ ያስፈልገናል” የሚል ነው። የቤተክርስቲያን የልማት ሥራ የሚደገፍ ቢሆንም እርሱን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገቢ ለማሰባሰብ ሲባል ግን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እየተጣሰና ሕንፃ ሥላሴ የተባሉ ምዕመናን በአሰልቺ ልመናና ንግድ ከቤተክርስቲያን እንዲርቁ እየተደረገ መሆን የለበትም። የቤተክርስቲያን ዋና ጌጦች ምእመናን እንጂ የሚፈርሱት ሕንፃዎች አይደሉም። በተጨማሪም የምዕመናኑን ቁጥርና የአጥቢያውን የገቢ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ በብዙ ብድር የሚገዙ መሬቶች፣ የሚታቀዱ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች የቤተክርስቲያንን አውደምሕረት እስከ ቀጣዩ ትውልድ ድረስ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ እያደረጉት ስለሆነ ገቢን ያገናዘበ የልማት ሥራ እንዲታቀድ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል።

የቤተክርስቲያንን የከበሩ በዓላት መነገጃ ማድረግ “ከገንዘብ ችግርና ምዕመናን አስራታቸውን በተገቢው ሁኔታ ባለማውጣታቸው” ብቻ የተፈጠረ አስመስለው የሚናገሩ ብዙዎች አሉ። ይህ አስተሳሰብ የችግሩን ሥር የሚደብቅ ቅርንጫፍ ለቀማ ነው። መሠረታዊው ችግር መንፈሳዊውን አውደምህረት ለሥጋዊ ጥቅም የማዋል ስግብግብነት ነው። ለዚህ ማሳያዎችን እናቅርብ። በሀገራችን ታላላቅ ከተሞች በበርካታ ሚሊዮኖች ገቢ የሚያስገኙ አጥቢያዎች ከልመና ወጥተዋል? አልወጡም። እንዲያውም መሠረታዊ ተልእኳቸውን ረስተው በፎቅና በቁሳቁስ የጭቅጭቅ አውዶች እየሆኑ ነው። አንድ አጥቢያ በመቶ ሚሊዮኖች ወርኃዊ ገቢ ሲያገኝ ለ”አገልጋዮቹ” መኪና ሲሸልም፣ የቤት እቃ ሲያሟላ፣ ደመወዝ ሲጨምር እንጂ ለተቸገሩት የገጠርና የጠረፍ አብያተ ክርስቲያናት ሲረዳ ማየት ብርቅ ነው። በውጭ ሀገራት ያሉ አጥቢያዎችም በዘረኝነት፣ በፖለቲካ ቡድንተኝነት፣ በግለሰቦች ጥቅምና ልታይ ልታይ ባይነት ስለሚከፋፈሉ በልዩ ልዩ ምክንያት የተቸገሩትንና  የተዘጉትን የሀገራችን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሊረዱ ይቅርና ራሳቸው ለ30 እና 40 ዓመታት የማይከፈል እዳ ውስጥ በፈቃዳቸው የሚዘፈቁ ናቸው። ገንዘብ ሲያገኙም በመጠናከር ፈንታ ይከፋፈላሉ። አንድና ሁለት ጠንካራ አጥቢያዎችን ከመፍጠር ይልቅ አምስትና ስድስት ደካማ አጥቢያዎችን ያበዛሉ። ይህንንም እንደስኬት ያዩታል። እዚህ ግባ በማይባል ርቀት፣ በኢኮኖሚ በጎሰቆለ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ትከሻ አምስትና ስድስት አጥቢያዎች በአጠቃላይ ከሰላሳ ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ የሚያስወጡ መሬቶችና ህንፃዎችን ሲይዙ እናያለን። ይህም በቋንቋው ላላስተማሩት ቀጣይ ትውልድ የሚጣል “የመከፋፈል እዳ” ውጤቱ ያስጨንቃል።

ንግሥና ንግድ: የችግሩ ጉዳቶች

በንግሥ በዓላት ላይ የንግድ ሥራን ማከናወን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ትልቅ የአስተምህሮ፣ የሥርዓትና የትውፊት ጉዳትን ያስከትላል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የንግድ ሥራ በቤተክርስቲያኒቱ ያለውን መንፈሳዊውን የንግሥ ዓላማ በማስረሳት ንግሥ በመጣ ቁጥር በቤተክርስቲያን አገልጋዮች ዘንድ “ምን ብንሸጥ ያዋጣል?” ወደሚል የንግድ አስተሳሰብ እንድናመራ የሚያደርግ አደገኛ አዝማሚያን ይፈጥራል፡፡ ለንግሥ የሚመጣው ምዕመንም የንግሡን ዓላማ ቸል በማለት ትኩረቱን ወደሚሸጡት ቁሳቁሶች እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል። በዚህም የተነሳ የንግዱ እንቅስቃሴ እየሰፋ ሄዶ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” ያለውን አምላካዊ ቃልን ወደመተላለፍ ያደርሳል። በተግባርም የሚታየው ይሄው ነው።

በሁለተኛ ደረጃም መጥፎ የንግድ ልምድን በማስፋፋት የንግሥ “ውጤታማነት” የሚለካበት በተካሄደው ንግድ ትርፍ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህም የንግሥን መንፈሳዊ ዓላማ በማስረሳት የአገልጋዮች ትኩረትን ወደ ገንዘብ ስሌት ላይ እንዲሆን ያደርጋል። ሰው ምን ይማር ሳይሆን ምን ይግዛ? ምን እሽጥለት? ስንት አገኘን? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ይገፋፋል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በንግሥ በዓላት ላይ የሚመጣውን ሕዝብ እንደ ምዕመን ሳይሆን እንደ “ደንበኛ/customer” እንዲቆጠሩ በማድረግ በረከት ሊያገኝ የመጣውን ሕዝብ ‹‹መነገጃ›› ያደርጋል፡፡ በዚህ አስልቺ ንግድም ሰው እየተማረረ ከቤተክርስቲያን እንዲርቅ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥርዓትና በደንብ የማይመራ ንግድ ዋና የሙስና ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ቤተክርስቲያንን የግጭትና የንትርክ መድረክ ያደርጋታል፡፡

በአራተኛ ደረጃ ንግስ በዓላት ላይ ትኩረቱ ሁሉ ወደ ንግድ፣ ምግብና ጨዋታ እየተቀየረ መምጣቱ ለመጭው ትውልድ የሚያስተላልፈው መልእክት አስደንጋጭ ነው። በተለይም የንግድ ንግሶች በሚበዙባቸው የውጭ ሀገር አጥቢያዎች የሚያድጉ ሕፃናትና ወጣቶች ቤተክርስቲያንን በሌላ መንገድ ስለማያውቋት የከበሩ የቤተክርስቲያን በዓላት የገቢ ማስገኛ መንገዶች (fund raising accessories) አድርገው የማሰብ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ንግሶቹ ከመደጋገማቸው የተነሳ የሚዘመሩት መዝሙራት፣ የሚሰጡ ትምህርቶች ወቅቱና በዓሉን የሚመለከቱ ሳይሆኑ “ለንግሥ የተዘጋጁ፣ የተለመዱ” አሠራሮች ሲሆኑ ታዝበናል። አንድ ሰው የተለያዩ ንግሦችን የተቀረፀ ቪዲዮ ቢመለከት የትኛው ቪዲዮ የየትኛው በዓል መሆኑን ለመገንዘብ እንኳ ይቸግረዋል። ዓላማቸው በነጋዴዎች ተደበላልቋልና።

ከሁሉም የሚበልጠው ችግር ግን መሰረታዊ የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮዎችን የሚቀስጥና በሂደት የሚያጠፋ መሆኑ ነው። በሐዲስ ኪዳን የታቦት አገልግሎት የጌታችንን የከበረ ሥጋና ደም መሰዊያ መሆኑ ይታወቃል። የአጥቢያ አብያተክርስቲያናት አሰያየምም ለአንድ ወይም በአንድ ላይ ሰማዕትነትን ለተቀበሉ ቅዱሳን የሚሰጥ እንጂ በንግድ አስተሳሰብ የሚመራ አይደለም። ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ለአንድ ምዕመን አንድ ስመ ጥምቀት እንጂ ሁለት ወይም ሦስት ስመ ጥምቀት እንደማትሰጠው ሁሉ ለአንድ አጥቢያም ከሥርዓቱ ባፈነገጠ መንገድ ለንግድ ሲባል በሁለት ወይም በሦስት ቅዱሳን ስም አትጠራም። ለንግድና ገቢ ሲሉ ታቦታትን የሚደራርቡ፣ የአብያተ ክርስቲያናትን ስያሜ የሚቀጣጥሉ ሰዎች የሚታያቸው ጊዜያዊ ገቢና ሆይ ሆይታ መሆኑ ለማንም የታወቀ ነው። ይህ ክፉ ልማድ ግን መሠረታዊ አስተምህሮዎቻችንን የሚቃረን በልማድ አረም እንዲዋጡ የሚያደርግ በሂደትም እንደተርታ ነገር እንዲናቁ የሚያደርግ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ሊቃናተ አይሁድ በዘመነ ብሉይ ከጌታ የተቀበሉትን ክህነትና አገልግሎት ለንግድና ለግላዊ ክብር በማዋላቸው ክህነታቸውም አገልግሎታቸውም የተናቀ ሆኖ ነበር። እኛም ከመምሸቱ በፊት ራሳችንን መመርመር ይገባናል። ለቤተክርስቲያን የቅን አገልግሎት መክሊትን የሰጠ ጌታ ሊቆጣጠረን እንደሚመጣ መዘንጋት የለብንም።

ንግሥና ንግድ: የመፍትሔ ሀሳቦች

በዘመናችን ያለውን የንግሥና የንግድ ቁርኝት ችግር ለመፍታትና በቤተክርስቲያን ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ በሁለት ደረጃ የሚከናወን እርምጃ ከምዕመናን (በተለይም ከወጣቶች) ይጠበቃል፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ መፍትሔ ለንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት ተደርገው የሚነሱትን ‹‹የገንዘብ ችግር›› መንስኤዎች ማምከን ነው፡፡ ሁሉተኛው ደግሞ በሃይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ላይ መንፈሳዊ ነገር ብቻ እንዲከናወን ያለመታከት መሥራት ነው፡፡ ለሕዝበ ክርስቲያኑም ይህንን በሚገባ በማስረዳት ወደ ንግሥ በዓላት የሚመጣው ምዕመን መንፈሳዊ ነገሩ ላይ ብቻ እንዲያተኩርና የንግድ እንቅስቃሴውን ወደ ጎን እንዲተወው ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ የሚሆን ከሆነ ‹‹የንግድ አቅርቦት ያለደንበኛ ፍላጎት ስለማይቆም›› ይህ ያሰለቸን የንግሥ ላይ ንግድ እየከሰመ ይሄዳል፡፡ይህንንም ለማሳካት በተለይ ወጣት ምዕመናን የሚከተሉትን መንገዶች ሊከተሉ ይችላሉ፡፡

የቤተክርስቲያን አሥራት በወቅቱ መክፈል

የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በቤተክርስቲያን ያለው እንቅስቃሴ ሥርዓትን ይዞ እንዲሄድ መጠየቅ ይገባል፡፡ አሥራትን በሚገባ ሳይከፍሉ መጠየቅ ሌላ አመክንዮ እንዳያመጣ ይህንን አስቀድሞ ማወቅና ሌሎችም አሥራታቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ ማበርታት ያስፈልጋል፡፡ ምዕመናን አስራታቸውን እንዲከፍሉ የሚያስተምሩ ሰዎች እጥረት የለም። ብዙ ትምህርት ተሰጥቷል። ወደፊትም ይሰጣል፣ መሰጠትም አለበት። ይሁንና ሰው ከሚሰማው ይልቅ በሚያየው ይማራልና የሚያስተምሩ ካህናትና መምህራን ለአደባባይ ፍጆታ ሳይሆን በጽድቅ በሚደረግ አገልግሎት አስራታቸውን መክፈል፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን ከመነገድ መቆጠብ አለባቸው። አጥቢያ አብያተክርስቲያናትም ምዕመናንን “የገንዘብ ደሀ ብትሆኑ እንኳ ካላችሁ ላይ አስራት ብታወጡ ያላችሁ ይባረክላችኋል” የሚለውን የማይታበል አምላካዊ ትዕዛዝ እንደሚያስተምሩ ሁሉ እነርሱም ለሌሎች የተቸገሩ አጥቢያዎች፣ ምዕመናን ወይም ገዳማት በግልፅ አሰራር አስራታቸውን ሊያወጡ ይገባል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ የሚፈታ ችግር የለም። በመሠረቱ ብዙ ምዕመናን አሥራታቸውን እንዳይከፍሉ ያደረጉ ገፊ ምክንያቶችም በሂደት እየታዩ እንዲፈቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የሚታቀዱ ሥራዎች ገቢን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ማድረግ

በቤተክርስቲያን የሚታቀዱ የግንባታም ሆነ ሌሎች ሥራዎች የቤተክርስቲያንን ገቢና የምዕመናንን ድርሻ ከግንዛቤ ያስገቡ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ እጅግ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ሕንፃዎች ሲሠሩ ዘመናትን/ትውልድን ከማሳለፍ ይልቅ ለአገልግሎቱ የሚመጥን ሕንፃ ሠርቶ ሌላው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በአንጻሩ ለስብከተ ወንጌል፣ ለሕፃናትና ለወጣቶች ትምህርት ትኩረት እንዲሰጥ መትጋት ይገባል፡፡

ሌሎች ገቢ ማስገኛ የልማት ሥራዎችን መሥራት

የቤተክርስቲያንን ገቢ በገንዘብ ለመደጎም ለሕዝብ የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ገቢ እንድታገኝ ማድረግ አንድ አማራጭ ነው፡፡ በተለይ ለቤተክርስቲያንም ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶችን (ለምሳሌ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ እጣን፣ የካህናት ልብስ ወዘተ) በማቅረብ በዚያውም የቤተክርስቲያንን ገቢ መደጎም ይቻላል፡፡

የንግሥን ዓላማ ለምዕመናን በሚገባ ማሳወቅ

በመሠረታዊነት በንግሥ በዓላት ላይ የሚመጣው ምዕመን የንግሥን ዓላማ የተረዳ ሆኖ በዚያ ሊካሄድ የሚችለውን ንግድም ሆነ ሌላ መንፈሳዊ ያልሆነ ተግባር ተባባሪ እንዳይሆን ማድረግ ዋናው መፍትሔ ነው፡፡ “እኛ ቤተክርስቲያን የምትጠብቅብንን አድርገናል፤ በሌላ ንግድ አታስቸግሩን!” ማለት የሚችል ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የንግዱ እንቅስቃሴም ገዢ ከሌለው በራሱ ይከስማል፡፡

ማጠቃለያ

በዓለ ንግሥ እግዚአብሔር የከበረ ሥራ የሠራባቸው ዕለታት እንዲሁም በምግባርና በሃይማኖት ያስደሰቱት ቅዱሳን ከምድርና ከሰማይ ንጉሥ ከእግዚአብሔር በጸጋ የተቀበሉት ክብር (ንግሥና) የሚታሰብበት የምስጋና እና የመንፈሳዊ አምልኮ በዓል ነው። በዕለቱም እንደቤተክርስቲያን ሥርዓት ታቦቱ በስሙ የተሰየመለት (የተሰየመላት) ቅዱስ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይታሰባል፣ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ ይመሰገናል፣ የከበረ ታቦቱም በካህናትና ምዕመናን ታጅቦ ሰማያዊ ክብሩን በሚያጠይቅ ዑደት መንፈሳዊ በረከትን እንቀበላለን። ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህን የከበረ በዓል ለንግድና ለገቢ ማስገኛነት የማዋል መንፈሳዊ መሠረት የሌለው ነውረኛ ልማድ እየተስፋፋ መጥቷል። የንግሥ በዓላቱን መነገጃ ከማድረግ የበለጠ የሚከፋው አሠራር ደግሞ ሁሉን ነገር መነገጃ በሚያደርግ አሠራር “ንግሦችን ለማብዛት ታቦታትን መደራረብ እንዲሁም የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መታሰቢያ ስም በተለያዩ ጊዜያት የሚከበሩ በዓላት ባላቸው ቅዱሳን ስም °እገሌ ወእገሌ° በማለት የመሰየም” የተቀደሰውን የማርከስ ክፉ ልምምድ ነው።  በብዙዎች ዘንድ ይህ መጤ ልማድ “ምን እናድርግ ምዕመናን አስራት ስለማያወጡ አማራጭ አጥተን ነው” በሚል አመክንዮ የሚታጀብ ቢሆንም መንፈሳዊነቱን ከመሳቱ ባሻገር አሳማኝ አመክንዮ አይደለም። ንግድና ማጭበርበር አልጠግብ ባይነትን እንጂ መንፈሳዊ ፍሬን አያስገኙምና።

ስለሆነም የከበሩ በዓሎቻችንንና እሴቶቻችንን ለጥቅም ሲሉ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያጠፉትን ልናውቅባቸው ራሳችንንም የመፍትሔው እንጅ የችግሩ አካል ባለማድረግ ልንጸና ይገባል። በታቦታት መነገድ ጌታን እንደሸጠ ይሁዳ የሚያዋርድ ርኩሰት እንጂ በምንም መንገድ ሊቃና ወይም ሊስተባበል የማይችል ነውር ነው። ስለሆነም በአንድ አጥቢያ ለንግድ ብለው ንግሥን ሳያበዙ ይልቁንም ያላቸውን ሁሉ እየሰጡ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን በትውልድ መካከል ያቆዩልንን ቀደምቶቻችንን ልንመስል ይገባል እንጂ በማባበያ ቃላት መነገጃ ልናደርጋቸው አይገባም። የባሕርይ ክብሩን (ንግሥናውን) ላከበራቸው ቅዱሳን ያለመሰሰት የሰጠ አምላካችን እግዚአብሔር የከበሩ ንግሦቻችንን መነገጃ ካደረገ ክፉ ልምምድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቅልን፣ የጠመመውንም እንዲያቀናልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።

1 thought on “ንግሥ እና ንግድ: የተቀደሰውን የማርከስ ክፉ ልማድ

  1. Pingback: ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት? – አስተምህሮ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s