የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን አለባበስ፡ ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ!

መግቢያ

የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ያልሆኑትን መስሎ ለመታየት የማስመሰል ጥረት ያደርጉ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችን በገሰጸበት መልእክቱ “ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ” (1ኛ ቆሮ. 14፡40) ብሏል፡፡ አስተምህሮዋን በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ያጸናች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም መንፈሳዊ አገልግሎቷ በሥርዓት የሚመራ፣ ከግለሰባዊ ከንቱ ውዳሴ ይልቅ ህገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚጎላባት በመሆኗ በእግዚአብሔር ቸርነት ሺህ ዘመናትን ለመሻገር ችላለች፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ማለት የተጻፈ ወይም በመንፈሳዊ ዓላማ በልማድ የዳበረ መንፈሳዊ አምልኮና አስተምህሮን የምንመራበት መክብብ ነው፡፡ ለሚሰራ ሥራ (ለሚፈጸም አገልግሎት) ተብሎ ሥርዓት ይተከላል እንጂ ሥርዓት በራሱ የሚቆም አይደለም፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ከፍ ያለ መንፈሳዊ ዓላማን የምንፈጽምበት መንገድ ነውና፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የቤተክርስቲያን ሥርዓት ከፍ ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎቻችንና መንፈሳዊ እሴቶቻችንን ሊያጸና እንጂ ሊገዳደር አይገባውም፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የተዳሰሰው የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን (መዘምራን) አለባበስም ፍጹም መንፈሳዊነትን የተላበሰና ከግለሰቦች ስጋዊ ፍላጎት አንጻር ያልተቃኘ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሺህ ዘመናት የአምልኮተ እግዚአብሔር ኀልወቷ ጠብቃ ካቆየቻቸው መንፈሳዊ ትውፊቶች መካከል መነኮሳት፣ ካህናት፣ መዘምራንና ምዕመናን በአገልግሎት ወቅት የሚለብሷቸው አልባሳት ይጠቀሳሉ፡፡ ካህናትም ሆኑ ምዕመናን የትንሣኤው ምስክሮች እንደሆኑ ቅዱሳን መላእክት ነጭ ነጠላ በመስቀል ቅርጽ አመሳቅለው ለብሰው ሞትን ያሸነፈ የክርስቶስን ትንሣኤ ይመሰክራሉ፡፡ ካህናት በጸሎተ ቅዳሴ ለአምልኮ የተለየ አለባበስ ይለብሳሉ፡፡ የመነኮሳት ከካህናት፣ የካህናት ከዲያቆናት አለባበሳቸው የተለየ ነው፡፡ የአልባሳቱ መንፈሳዊ ዓላማም ለተለየ መንፈሳዊ አገልግሎት መቆምን የሚያሳይ እንጂ ለውበት ወይም ለታይታ የሚደረግ አይደሉም፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገልግሎት ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት አለባበስን ያልሆኑትን መስሎ ለመታየት (ለማስመሰል) እንዲሁም ግለሰባዊ ስብዕናን ከፍ በማድረግ በሰዎች ዘንድ መንፈሳዊ ለዛ የሌለው መወደድን ለማግኘት ሲውል ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ ቄሶች መነኮሳትን ለመምሰል የመነኮሳትን ዓይነት አለባበስ ሲለብሱ ሰባክያንና መዘምራንም ከመደበኛ ልብሰ ተክህኖ ውጭ ትውፊታዊ መሰረት የሌለው ቀሚስ በማድረግ፣ ሀብልና መስቀልን  ለታይታ በማንጠልጠል ሲደክሙ ይስተዋላሉ፡፡ ከዚያም ባሻገር ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ዘፋኞችና ሌሎችም ምዕመናን በዚህ መሰል የአለባበስ ፉክክር ውስጥ እየገቡ የቤተክርስቲያንን አልባሳት ልማድና ትውፊት ለየራሳቸው እውቅናና ዝና ሲጠቀሙበት እያስተዋልን ነው፡፡ በባቢሎን ምርኮ ዘመን የቤተመቅደስ ንዋያትን ያለአግባብ የሚጠቀሙትን የቀጣ እግዚአብሔር ዛሬም እንዳለ፣ ስለ ቤቱ፣ ስለ ሥርዓቱም እንደሚገደው ማወቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ ሰርጎ ገብ ልማዶች በተለያዩ ምክንያቶች ትክክል መስለው እንዲቀርቡ፣ ከአለባበሶቹ ጀርባ ያለው ስር የሰደደ የከንቱ ውዳሴ ፍላጎትም በትክክለኛ እይታ ታይቶ ችግሮች እንዳይቀረፉ የተለያዩ ምክንያቶች የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ስለዚህ ጉዳይ በአደባባይ የሚሞግቱ ጽሁፎችም ሆነ የኦዲዮ ቪዥዋል ምንጮች አለመኖር (ማነስ) ነው፡፡ አንዳንዶች “ቤተክርስቲያን ስንት አሳሳቢ ጉዳይ እያለባት በዚህ ጉዳይ ጊዜ ማባከን ወቅታዊ ላይሆን ይችላል” የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ እውነትም የአለባበስ ጉዳይ ከላይ ሲታይ አሳሳቢ ያልሆነ ቀላል ጉዳይ ይመስላል፡፡ በአጽንኦት ለተመለከተው ግን የብዙ ዘመናውያን ችግሮች ማሳያ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ካህን ወይም መምህር የተሻለ ተቀባይነት የሚያገኘው አለባበሱ ደማቅና ለፖስተር ማስታወቂያ የተመቸ ነው ተብሎ ሲታሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡ በዚህም የተነሳ የአገልግሎቱ ትኩረት ከይዘት ወደ ቅርጽ እየተለወጠ መሄዱንና አስመሳይነትን በቋሚነት የሚያነብር ድባብ እየተፈጠረ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚያም ባሻገር የአለባበስ ሥርዓት አልበኝነት ከተባባሰ  (ከ1990ዎቹ ፣ በተለይም ከ2000 ዓ.ም) በኋላ የችግሩን ምንጭ ከነባራዊው የቤተክርስቲያን ልማድ ጋር ከማገናዘብ ይልቅ ተበራክቶ ለሚያዩት ልማድ (ሁነት) የአስተምህሮ ድጋፍ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ከሁነት በኋላ የሚሰጡ በልክ የተሰፉ ማሳመኛዎች (ex post facto justifications) በመጽሐፍ መልክ የሚጽፉ ሰዎች ስላሉ፤ እንደዚሁም እነዚህ መጤ ልማዶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመስፋፋታቸው የተነሳ ብዙዎች መጤውን ልማድ የማይከተሉ የነበሩ አገልጋዮችም እየተጠለፉ ሲወድቁ እያስተዋልን ነው፡፡ በብዙ መመዘኛዎች ቤተክርስቲያንን በቅንነትና፣ በእምነት፣ በእውቀትና በመሥዋዕትነት የሚያገለግሉ በርካታ ካህናት፣ ሰባክያንና ዘማርያን በዚህ ልማድ መወሰዳቸው ለሌሎችም የስህተት ማስተባበያ አመክንዮ ሆኖ ሲቀርብ መስማት ያልተለመደ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች ጉዳዩን በራሱ ከመመርመር ይልቅ “እገሌና እገሌ እንኳ እንደዚያ ይለብሱ የለም እንዴ?” በሚል ያልበሰለ አተያይ ግራ ሲጋቡ እናስተውላለን፡፡ በጊዜ ሂደትም አረሙ ሰብል፣ ሰብሉ አረም መስሎ ማደናገሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ለመነሻ ይሆን ዘንድ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የካህናትን፣ የሰባክያነ ወንጌልንና የመዘምራንን አለባበስና ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችን እንዳስሳለን የመፍትሄ ሀሳብም እንጠቁማለን፡፡ ሌሎቻችሁም በጉዳዩ ላይ ብትጽፉ ወደተሻለ  ተጠየቃዊ ተግባቦት መድረስ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

capes_all4

የካህናት አለባበስ በአገልግሎት ጊዜያት 

ልብሰ ተክህኖ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡

ልብሰ ተክህኖ (የክህነት ልብስ) የሚባለው ካህናት ለቤተመቅደስ አገልግሎት ሲፋጠኑ የሚለብሱት ለአገልግሎት የተለየ ልብስ ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲህ በማለት ትዕዛዝን ሰጥቶታል፡፡  “የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት፡፡ አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር፡፡ እነርሱም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለአሮን ቤተመቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ፤ የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዓ፣ ልብሰ መትከፍ፣ ቀሚስም፣ ዥንጉርጉር እጀ ጠባብ፣ መጠምጠሚያ፣ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፣ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ፡፡ ወርቅ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ፣ ቀይ ግምጃ፣ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ” (ኦሪት ዘጸአት 28፡2-5)፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ኦርቶዶካሳዊት ቤተክርስቲያን ልብሰ ተክህኖን ለቅዳሴ ጸሎትና ለሌሎች አምልኮተ እግዚአብሔር ለሚፈጸምባቸው አገልግሎቶች ትጠቀምበታለች፡፡ ለጽድቅ አገልግሎት የተመረጡ ካህናትም የአገልግሎታቸውን ክብር ለማሳየት የተለየ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ሥርዓተ አምልኮን ይፈጽማሉ፡፡

በዚህም መሠረት በጸሎተ ቅዳሴ የሚሳተፉ አምስቱም ልዑካን በችግር ምክንያት ካልሆነ በቀር ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ  (ብፁዓን ጳጳሳቱ የጳጳስ፣ ቀሳውስቱ የካህን፣ ዲያቆናቱም የዲያቆን) ማድረግ እንዳለባቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያስረዳል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያለ ምንም አሳማኝ የጤና ምክንያት የራሳቸውን ልብስ አሰፍተው የሚቀድሱ ሰዎች ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህም ልማድ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሰ ከመሆኑም በላይ እየዋለ እያደረ ሲሄድ ሰዎች በራሳቸው ልብስ (ያለ ልብሰ ተክህኖ) የመቅደሱን አገልግሎት እንፈጽም ወደ ማለት ሊመራ ይችላል፡፡ ስለዚህም ካህናትና ምዕመናን እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት በጊዜ እንዲታረም የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ምክር ለሚሰሙት መምከር ይገባል፡፡ ምክር ለማይሰሙትና ለተራ ውዳሴ ከንቱ ለሚያደርጉት ደግሞ የሚሳሱለትን ክብር ሆን ብሎ በመንፈግ ለጥቅማቸው መቅጣት ይሻላል፡፡

ልብሰ ተክህኖን ለታይታ ማድረግ ኃጢአት ነው፡፡

የልብሰ ተክህኖ ዓላማ ለተለየ አገልግሎት መቆምን በማሳየት ልዩ ለሆነ አምልኮ ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አለባበስን መጠቀም ነው፡፡ የልብሰ ተክህኖ ዓላማ ማማር፣ መድመቅ ወይም ጎልቶ መታየት አይደለም፡፡ ይሁንና የእግዚአብሔርን ቤት ለማገልገል ምልክት እንዲሆናቸው የተሰጣቸውን ልብሰ ተክህኖ ለግል ታይታና ክብር የሚጠቀሙ አስመሳይ አገልጋዮች በየዘመናቱ ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ የአይሁድ አለቆችን ከነቀፈባቸው ምክንያቶች አንዱ የታይታና የማስመሰል አለባበሳቸው ነው፡፡ “የሚሠሩትን ሥራቸውን ሁሉ ለሰው ሊታዩ ይሠሩታልና፤ አሸንክታባቸውን ይዘረጋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ፡፡ በማዕድ ጊዜ በክብር ስፍራ በምኩራብም በፊተኛው ወንበር መቀመጥን ይወድዳሉ፡፡” (ማቴ. 23፡5-6)እንዲል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ጌታ የአይሁድ አለቆችን የወቀሳቸው ልብሰ ተክህኖ በመልበሳቸው ሳይሆን ለታይታ በማድረጋቸው ነው፡፡ ዛሬም ልብሰ ተክህኖን ለታይታና ለማስመሰል እንዲሁም ፎቶ በመነሳት በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚለጥፉና ምድራዊ ታዋቂነትንና ዝናን የሚናፍቁ ‘ካህናት’ ለእነዚያ የአይሁድ ካህናት የተነገረው አምላካዊ ተግሳጽ ይመለከታቸዋል፡፡ 

በአለባበስ መነኩሴ መምሰል የሚፈልጉ ቀሳውስት

በቤተክርስቲያን ሥርዓት መነኮሳት ራሳቸውን ለመንፈሳዊ ሕይወት ለይተው፣ ከጋብቻና ሌሎች ምድራዊ ደስታዎች ርቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡ መነኮሰ ማለት ሞተ ማለት ስለሆነ መነኮሳት ለተግባረ ሥጋ የሞቱ መሆናቸውን ለማሳየት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በለበሳትና በመከራው ወቅት ገራፊዎቹ እጣ በተጣጣሉባት ሥርወጥ ቀሚስ አምሳል ቀሚስን ይለብሳሉ፤ አይሁድ በጌታችን ዘላለማዊ ንግስና በመዘበት በራሱ ላይ ባቀዳጁት አክሊለ ሶክ (የእሾህ አክሊል) አምሳል በራሳቸው ላይ አክሊልን (ቆብን) ያደርጋሉ፡፡  መነኩሴ ካህን ሆነም አልሆነም ቀሚስና ቆብ ማድረግ የቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ልማድ መሰረት ቀሳውስት እንዲሁም ሌሎች መነኮሳት ያልሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ህጋውያን (በጋብቻ ተወስነው መኖርን የመረጡ) ናቸውና እንደ መነኮሳት ለዓለም ሥራ የሞቱ ናቸው አይባልም፡፡ አለባበሳቸውም እንዲሁ ከመነኮሳት የተለየ ነው፡፡ መደበኛ ልብሰ ተክህኖ ከሚለበስባቸው ከቅዳሴና መሰል የአምልኮ ጊዜያት ውጭ ቀሳውስትና ሌሎች መነኮሳት ያልሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደማንኛውም ምዕመን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶችን የጠበቀ አለባበስ፣ እንዲሁም እንደየክብራቸው እንደየማዕረጋቸው በቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የተለመደውን (ከመነኮሳት ጋር የማይምታታ) አለባበስ እንዲለብሱ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ይፈቅዳል፡፡ እንደ ሕጋዊው ሙሴ በቤተ እግዚአብሔር የተሾሙ የክርስቶስ መልእክተኞች ናቸውና ከሙሴ በተወረሰ ሥርዓት በራሳቸው ላይ ጥምጣም ይጠመጥማሉ፡፡

በኦሪት ዘፀአት 34፡29-35 ታሪኩ እንደተፃፈው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ሁለቱን ጽላቶች ተቀብሎ ከተራራው ሲወርድ ፊቱ በብርሃን ተመልቶ ያንጸባርቅ ስለነበር እሥራኤል ዘሥጋ ቀርበው ሊያነጋግሩት አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሮ በወጣ ጊዜ ፊቱን በጨርቅ ይሸፍንላቸው ነበር፡፡ አባቶቻችን ቀሳውስትና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ጌታችን እንደተናገረ “ሙሴና ነቢያትን (የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር)” ለምዕመናን እንዲያስተምሩ የተሾሙ ናቸውና ከሙሴ በተወረሰ መንፈሳዊ ትውፊት በራሳቸው ላይ ነጭ ጥምጣምን ይጠመጥማሉ፡፡ (ማቴ. 23፡2፣ ሉቃስ 16፡29) ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ (በተለይም ከሀገር ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያክርስቲያናት) እየተዘወተረ የመጣው ልማድ ህጋውያን ካህናት (ቀሳውስት) እንደ ሥርዓቱ የካህናትን አክሊል አድርገው ከመቀደስ ይልቅ የመነኮሳትን አስኬማ የሚመስል ቆብ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ከጸሎተ ቅዳሴ ባሻገርም በሌሎች “በህዝብ የመታያ” ተብለው በሚታሰቡ ጊዜያት ቀሳውስት (ቄሶች) ከመነኩሴ ጋር የሚመሳሰል አልባሳትን ማዘውተር በአንዳንድ የከተማ አካባቢዎችና በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች እየተለመደ መጥቷል፡፡ መነኩሴ ሳይሆኑ መነኩሴ መምሰል ምን ያደርጋል? በቀደመው ልማድ ቀሳውስት ከመደበኛ ልብስ በላይ ነጠላ እና (ወይም) ጥምጣም ያደርጋሉ እንጂ እንደ መነኩሴ ቀሚስና አስኬማ ማድረግ የቀሳውስት መለያ አይደለም፡፡ የዚህ መሰረቱ የማይታወቅ አዲስ ልማድ መነሻ ምንድን ነው? የሚለውን በተመለከተ ልዩ ልዩ መላምት መስጠት ይቻላል፡፡ መንፈሳዊ አመክንዮ ግን የለውም፡፡ የቀሳውስት ቆብ የማጥለቅ ልማድ እንደ አሁኑ በአንዳንድ ቦታዎች የተለመደ ከመምሰሉ በፊት በልዩ ልዩ ቀልድ መሰል ማባበያ የተጀመረ ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ “የፀሐይ መከላከያ ቆብ” የሚለው መሰረተ ቢስ አመክንዮ ሲሆን ሌላው “የክብር ቆብ” የሚባለው ወለፈንድ አገላለጽ ነው፡፡ ይሁንና በሰው ዘንድ ያልተገባ ክብርን ለማግኘትና ያልሆኑትን ለመምሰል የሚደረግ አስመሳይነት የክብር ሳይሆን የክብረ ቢስነት ማሳያ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ መጤ ልማድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምን ያህልስ አሳማኝ ናቸው? እስኪ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን ምክንያቶች እንመልከት፡፡ 

ከነጠላና ጥምጣም ይልቅ ቀሚስና ቆብ ለሥራና ኑሮ ስለሚቀል ነው?

አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ከተሞችና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ቀሳውስት ለጀመሩት ይህን መሰል ልማድ እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ነጠላና ጥምጣም ማድረግ ለሥራና ኑሮ ስለሚከብድ ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ እውነት ነው ነጠላና ጥምጣም አድርጎ መደበኛ ሥራን ማከናወን ሊከብድ ይችላል፡፡ ይሁንና ነጠላና ጥምጣም ማድረግ ቀሚስና ቆብ ከማድረግ ይቀላል እንጂ አይከብድም፡፡ ቀሳውስት ሕጋውያን እንደመሆናቸው ኑሮን ለማሸነፍ ላይ ታች ማለታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ በሁሉም ጊዜ ነጠላና ጥምጣም ማድረግ አለባቸው የሚል ሥርዓትም ልማድም የለም፡፡ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ያሉ ደገኛ ካህናት በዋናነት እንደሌላው ገበሬ እያረሱ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ይታወቃል፡፡ በዚህም ጊዜ እንደ ካህን መስቀላቸውን ይዘው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ደግሞ ለሥራቸው በሚገባ አለባበስ ተግባራቸውን እንደሚፈጽሙ ይታወቃል፡፡ በከተማም ቢሆን ከተወሰኑ በመጤው ልማድ ከተሸነፉ ቦታዎች ውጭ ካህናት የመነኩሴ የሚመስል ቆብ አያደርጉም፡፡ ቀሚስና ቆብ ማድረግ ጥምጣም ከማድረግ ይልቅ “ለሥራ የሚያመች” ነው ሊባል አይችልም፡፡ስለዚህ በማይመስል አመክንዮ ተደግፎ አዲስ ሥርዓት ማንበር አያስፈልግም፤ ምክንያታዊም መንፈሳዊም አይደለምና፡፡

ቀሳውስት ከሌላው ተለይተው ለመታወቅ እንደ መነኩሴ መልበስ አለባቸው?

በአንዳንዶች ዘንድ መነኩሴ የሚያስመስለው አለባበስ ከሚመረጥባቸው ምክንያቶች አንዱ “ነጠላ መልበስማ ማንም ሊለብስ ይችላል፣ ስለዚህ ካህናት ተለይተው እንዲታወቁ ቀሚስና ቆብ ያስፈልጋል” የሚለው መከራከሪያ ነው፡፡ ቀሳውስት ለምዕመናን መንፈሳዊ ሀኪሞቻቸው ናቸውና በየሄዱበት ሁሉ ምዕመናን ለይተው ቢያውቋቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ለሚቻላቸው ቀሳውስት ሁሉ በተቻለ መጠን የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ልማድ በጠበቀ መልኩ ቢታወቁ መንፈሳዊ ክብሩም ጥቅሙም ከቀሳውስቱ ይልቅ ለምዕመናን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሆነ ካህን በቡራኬው፣ በጸሎቱ፣ በምክሩ፣ በማጽናናቱ፣ በመናዘዙና በመሳሰለው አገልግሎቱ ይረዳናልና፡፡ ይሁንና ተለይቶ ለመታወቅ ሲባል ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና ልማድ ያፈነገጠ አለባበስ መልበስ ግን አሳማኝ አመክንዮ ሊቀርብለት አይችልም፡፡ ቀሳውስት በማትመረመር ክህነታቸው፣ በልዩ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው፣ ለምዕመናን በሚሰጡት ትምህርትና ልዩ ልዩ የኖላዊነት (ጠባቂነት) ሚና በልዑል እግዚአብሔርና በገዛ ደሙ በዋጃት በቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ ከዚህ የተለየ የውዳሴ ከንቱ ፍለጋ መታወቂያ መፈለግ መንፈሳዊ ጤንነትን አያሳይም፡፡ ቀሳውስት ልብሰ ተክህኖ ከሚደረግባቸው የአምልኮተ እግዚአብሔር ጊዜያት ውጭ ቀሚስም ሆነ ቆብ ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት፣ ልማድ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሌሎች የተኮረጀ የአለባበስ ሥርዓትን ማዘወተር ቤተክርስቲያኒቱን የራስዋ የሆነ የአለባበስ ሥርዓት የሌላት ያስመስላታል፡፡

ታዲያ ከበስተጀርባው ያለው አመክንዮ ምንድን ነው?

የካህናት የአገልግሎት ሥልጣን ቀሚስን በማስረዘም፣ ደማቅ ቀለም ያለው ልብስ በመልበስ፣ ጎላ ያለ ፎቶ ተነስቶ በየማኅበራዊ ሚዲያው በመለጠፍ አይገለጥም፡፡ ይህ መስሎ የመታየት አባዜ ርካሽ ተወዳጅነትን ከመሻት፣ ምድራዊ ታዋቂነትን ከመናፈቅ፣ የከንቱ ውዳሴ እስረኛ ከመሆን የሚመነጭ አላፊ የአለባበስ ፉክክር ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያት መልካም ካህን መስሎ በመታየት የየዋሀን ምዕመናንን ገንዘብ ዘርፎ በአቋራጭ ለመክበር መቋመጥ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን ለተወሰኑ ጊዜያት በልብስ ውስጥ በተደበቀ ምንፍቅና ወይም ሌብነት የቆዩ ብዙ የሥም “ካህናት” ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁሉንም ትተውት ፍጹም ዓለማዊ መሆናቸው ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዕውቀት ሳይበስሉ፣ በእውነተኛው እምነት ሳይጠነክሩ፣ ራሳቸውን በጾምና በጸሎት ሳይገዙ፣ የሚያማምሩ አልባሳትን ብቻ የሚገዙ፣ ሕይወታቸውን ሳይቀይሩ ልብሳቸውን በየዕለቱ የሚቀያይሩ ለራሳቸው ፍላጎት እንጂ ለቤተክርስቲያን ሥርዓት ያልቆሙ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አይነት አለባበስ እውነተኞቹ አገልጋዮችም እንዳይጠለፉ እንዲህ አይነቱን ልማድ በቤተክርስቲያን ሥርዓት ማረም ያስፈልጋል፡፡ ምዕመናንም ከእነዚህ የአለባበስን ፋሽን ተከታይ ከሚመስሉ ሐሰተኛ ሰዎች ራሳቸውንና ገንዘባቸውን ሊጠብቁ ያስፈልጋል፡፡ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ልንደግፍ እንጂ የግለሰቦችን ቤትና ኑሮ ልናቋቁም አልተጠራንምና፡፡

እነዚህ ሰዎች የሚመርጧቸው ቀለማት በዓለም እንዳሉ ዘፋኞች ጎልቶ ለመታየት እጅግ የደመቁ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ የባሰባቸው ደግሞ ነጭ ቀሚስ በቀይ ቆብ ዓይነት አለባበስ እየለበሱ ደርዝ የሌለው የመታየት ፍላጎታቸውን ግልጽ ያደርጉታል፡፡ዓላማቸውም መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማውያን ዘናጮች እንደሚያደርጉት ከሌላው አለባበሳቸው ጋር የሚናበብና ለዓይን የሚማርክ (“ማች” የሚያደርግ) የሚሆንባቸውን ጊዜያትም ታዝበናል፡፡ እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል የሚቀልዱ ነውረኞች ስለሆኑ ዓላማቸው እየታወቀ “ለምን እንዲህ አደረጋችሁ?” ሲባሉ የማይገናኘውን የከበሩ ቅዱሳንን ህይወት ለማደናገሪያነት ያቀርቡታል፡፡ በዚህ መልኩ የራስን ጥፋት ለመሸፈን በአስመሳይነት ከሚጠቅሷቸው ታሪኮች አንዱ በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ታሪኩ የሚነገርለት የደገኛው ጻድቅ አባት የቅዱስ ባስልዮስ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ጻድቅና ተጋዳይ አባት ቅንዋት ታጥቆ፣ ማቅ ለብሶ በትህርምት እየኖረ ለወንጌል ክብር ሲል ያማረ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ወንጌልን ሲያስተምር ክብርና ልዕልናውን ሰምቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ እርሱ የመጣው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በልቡ አዝኖበት ነበር፡፡ የወንጌል መምህር ልታይ ልታይ ማለት የለበትምና፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ባስልዮስ ያማረ ልብስ መልበሱ ስለ ክብረ ወንጌል ነበር እንጂ እርሱስ በውስጡ ቅንዋትን የታጠቀ ተሐራሚ ነበር፡፡ በአለባበሱም ለማስመሰል የማይገባውን የለበሰ አልነበረም፡፡ የዘመናችን አስመሳዮች የራሳቸውን የመታየት በሽታ ለመሸፈን ቅዱስ ባስልዮስን ሲጠቅሱ አለማፈራቸው ይገርማል፡፡

ሰባክያን አለባበስ

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማት በአንዱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የአጭር ሣምንታት ሥልጠና ከሚወስዱ ሰልጣኞቹ አንዱ የጠየቀው ጥያቄ በዘመናችን በሰባኬ ወንጌልነት ሰበብ ከንቱ ውዳሴ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን አስተሳሰብ ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰልጣኙ ከመምህራኑ ለአንዱ እንዲህ በማለት ጠየቀ “እንግዲህ ሰልጥነን ከወጣን የሰባኪ ቀሚስ ለብሰን፣ መስቀል አንጠልጥለን እንዳናስተምር የሚከለክለን ማን ነው?” የዚህ ሰልጣኝ ጭንቀት የተማረውን የእግዚአብሔር ቃል ወንጌልን ለተጠሙ ምዕመናን እና አህዛብ ማድረስ ሳይሆን ከእርሱ የቀደሙ ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ሲያደርጉት እንዳየው ማንነቱን በቀሚስ ሸፍኖ የበላይ መስሎ የመዘባነን ፍላጎት እንደነበረው ነው፡፡ ከሚያስተምሩት ወንጌል ይልቅ ስለሚለብሱት ሥርዓትን ያልተከተለ የማስመሰል ቀሚስ የሚጨነቁ ሰዎች እውነተኛ ምዕመናንን “ስለምትለብሱት አትጨነቁ” እያሉ ለማስተማር አለመሳቀቃቸው ይገርማል፡፡ ለማሳያነት የተጠቀምንበት ሰልጣኝ በከንቱ ደከመ እንጂ ቀሚስ ለመልበስና መስቀል ለማንጠልጠል እምነትም፣ ትምህርትም፣ እውቀትም፣ ሹመትም ሲያስፈልግ አይታይም፡፡ ከዚያ ይልቅ ድፍረትና ማን አለብኝነትን የተላበሱት ከራሳቸው ራስ ወዳድ ዓላማ በላይ ማሰብ የማይችሉት የአስተሳሰብ ድሆች ለዚህ ነገር የፈጠኑ ናቸው፡፡ እምነትም፣ ትምህርትም፣ እውቀትም የሌላቸው ብዙዎች የዋሐን ምዕመናንን ለማጭበርበር ቀሚስ መልበስንና መስቀል ማንጠልጠልን እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነውና፡፡   

ካህናት (ቀሳውስት) በቅዳሴና መሰል አገልግሎቶች ከሚለበሱ መደበኛ የካህናት ልብሶች (ልብሰ ተክህኖ) በቀር ቀሚስም ሆነ ቆብ ማድረግ ዘመናዊ ታይታን የመፈለግ አስመሳይነት የወለደው፣ መንፈሳዊ የት መጣ የሌለው ልማድ መሆኑን አይተናል፡፡ ካህን (ቄስ) ሳይሆኑ (ዲያቆን ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ) በልዩ ልዩ ቦታዎች ቀሚስ መልበስ ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል “ዘመናዊ” ሰባክያንና ዘማርያን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አንድ ሰባኪ ለመስበክ የግድ መነኩሴ የሚያስመስል ቀሚስ፣ እንደ እውነተኞቹ መነኮሳት ለቅንዋት (ራስን ለመጎሰም ከልብስ በታች የሚታጠቁት ሰንሰለት) ሳይሆን ለሰው እይታ የሚንጠለጠል በመስቀል ቅርጽ የተሰራ ሀብልና ጌጥ ማንጠልጠል የቤተክርስቲያን መለያ እስኪመስል ድረስ አደባባዮቻችንን በጊዜ ሂደት መሙላት ከጀመረ ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት እያለፈው ነው፡፡ ይህም ከቤተክርስቲያናችን ትውፊትና ልማድ ያፈነገጠ፣ በጊዜ ሂደት ግን መንፈሳዊ ለማስመሰል እየተሞከረ ያለ ልማድ ነው፡፡ የተለያዩ አካላት ለዚህ ልማዳቸው የማይናበቡ ልዩ ልዩ አመክንዮዎችን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህን ማሳመኛ ተብለው የሚቀርቡ ሀሳቦች እንመልከታቸው፡-

ከመንፈሳዊ ተቋማት የተመረቁ ሰባክያን አለባበስ

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በሺህ ዘመናት ኀልወቷ አስተምህሮዋን አጽንታ የቆየችው ልዩ በሆነ ሀገርኛ አደረጃጀትና አመራር የሚሰሩ በርካታ የአብነት ትምህርት ቤቶች በየገዳማቱና አድባራቱ ሊቃውንትን በመጠቀም ተተኪ ደቀመዛሙርትን በማፍራታቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ሀገር በቀል የትምህርት ዘርፍ እስካሁን ድረስ ለቤተክርስቲያን መከታ የሆኑ አያሌ ሊቃውንትን እያፈራ ይገኛል፡፡ ይሁንና ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትና ከማኅበረሰባችን አኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲሁም ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ ሀገርኛ ቅርጽ ካለው የአብነት ትምህርት ቤት በተጨማሪ የዘመናዊ ትምህርትን ቅርጽና አካሄድ የተከተሉ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት አስፈላጊነታቸው እየጨመረ መጣ፡፡ ይሁንና የቤተክርስቲያን አስተዳደር ለዚህ ሽግግር ተገቢውን ተቋማዊ ዝግጅት ያደረገ አይመስልም፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ መንፈሳዊ ትምህርት (ቲዮሎጂ) የሚያስተምሩት በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት ሲመሰረቱ አንግበው ከተነሱለት ዓላማ ዋነኛው የውጭ ሀገራት ቋንቋ በማጥናት የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ለሌሎች ዓለማት (በተለይም ለአፍሪካና ካሪቢያን ወገኖቻችን) መድረስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ የተቀደሰ ዓላማ ቢያዝም ተቋማቱ ሀገራዊ መልካቸውን ከዓለም አቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤ ጋር አዛምደው መያዝ የቻሉ አይመስልም፡፡ በመደበኛ የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ካለው ጋር ከሚመሳሰል ስር የሰደደ የትምህርት ጥራት ችግር ባሻገር መንፈሳዊ አስተምህሮን እንደ ሥጋዊ ጥበብ ለእውቅናና ክብር ፍለጋ የሚፈልጉት እየበዙ ሲመጡ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ከሚሆኑን ጉዳዮች አንዱ የቤተክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት የሌለው የምሩቃኑ ወይም የተማሪዎቹ አለባበስ ነው፡፡

አንድ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋም ምሩቅ ቀሚስና ካልለበሰ፣ ሀብልና መስቀል ካላንጠለጠለ የተማረ የማይመስለው ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ እነዚህ የትምህርት ተቋማት ከጣልያን ወረራ በኋላ የተከፈቱ በዋናነትም ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተስፋፉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ደግሞ ሀገራዊ እሴቶችን “የፈረንጅ” በሚመስሉ ልማዶች መተካትን እንደ እውቀት የሚቆጥር ኮራጅ ትውልድና ሀገራዊ መዋቅር ተፈጥሯል፡፡ የመንፈሳዊ ኮሌጆቹ ደቀመዛሙርትም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተለመዱትን አለባበሶች መኮረጅን የሥልጣኔ መገለጫ አድርገው ያሰቧቸው ይመስላል፡፡ በመሰረቱ መንፈሳዊ ኮሌጆቹ ደቀመዛሙርቶቻቸው የተለየ አለባበስ እንዲለብሱ ማድረጋቸው  በራሱ ችግር የለውም፡፡ ይሁንና ዓላማውና አጠቃቀሙ ታውቆ በመንፈሳዊ እይታ ሊጠቀሙበት ሲገባ ፋሽን ማሳመሪያ፣ ገበያ መሰብሰቢያ መሆኑ ነው መሰረታዊ ችግሩ፡፡ ይህ አለባበስ የመታየት ልማድ የወለደው እንጂ በተቋማቱ ከመማር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ከመማሪያ ግብዓቶች እጥረት የተነሳ ካልሆነ በቀር በመንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ወንዶችም ሴቶችም እኩል የመማር መብት እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው እህቶቻችን በተቋማቱ እየተመረቁ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተቋማቱ የሚመረቁ ሴቶች እንደ ወንዶቹ “የሰባኪ ቀሚስ”፣ ሀብልና መስቀል ይዘው በአገልግሎት ቦታዎች ቢገኙ ግብረ መልሱ ምን ይሆናል? መገመት አይከብድም፡፡ አያችሁ? ቀሚስ፣ ሀብልና መስቀል እወደድ ባይ ልማድ የፈጠረው የታይታ ልማድ እንጂ ከመንፈሳዊ ተቋም ምሩቅነት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡

የሌሎች ሰባክያነ ወንጌል አለባበስ

ቀሚስ መልበስን ልማድ ያደረጉ በዘመናዊ መልክ የተደራጁ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት በቤተክርስቲያናችን ያላቸው ታሪክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ በብዛት መስፋፋት የጀመሩበት ጊዜም ካለፉት 20 እና 30 ዓመታት አይዘልም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌል በዋናነት በአብነት ትምህርት ቤት መምህራን፣ በደቀመዛሙርቶቻቸው፣ በእውነተኞች ባህታውያን፣ በደጋግ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ከእነዚህ በተማሩ ቀናኢ ምዕመናን ሲሰጥ የኖረ ነው፡፡ በእነዚህ የሺህ ዘመናት ቆይታዎች ሰባክያነ ወንጌል ከነጠላና (ወይም) ጥምጣም (የሚገባቸው) ከመደበኛ ልብሰ ተክህኖ ውጭ የሚለብሱት ቀሚስ፣ የሚያንጠለጥሉት ሀብልና መስቀል አልነበረም፡፡ ለታይታ የሚደረግ፣ ምንዳ የሚጠየቅበት ስብከተ ወንጌል ለቤተክርስቲያን ባዕድ የነበረ መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስላል፡፡ የታይታ ልማዱ መስፋፋት ከከተሞችና በውጭ ሀገራት በሚገኙ አጥቢያዎች ገዝፎ መታየቱ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ በእነዚህ ቦታዎች መንፈሳዊ አገልግሎትን በገንዘብ መተመንና ለገንዘብ ሲሉ ማገልገል እየተለመደ መጥቷልና፡፡ ይህም የታይታ ልማዱ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለግላዊ የገንዘብና የክብር ጥቅም ማስገኛነት ለመዋል ዋና መሳሪያ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

ስለሆነም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንደተባለ በአብነት ትምህርት እውቀታቸው የተመሰከረላቸው፣ አልያም ቢያንስ የተመሰከረላቸውን ሊቃውንት አሰረ ፍኖት እንደ አቅማቸው የሚከተሉ ሰባክያነ ወንጌል እንደየማዕረጋቸው ከነጠላቸው በላይ ጥምጣምና ካባ ያደርጋሉ፡፡ መነኮሳት የምንኩስና ልብሳቸውን፣ ባህታውያን ለታይታ ሳይሆን ለጽድቅ የሚያደርጉትን አለባበስ ለብሰው ያስተምራሉ፡፡ሌሎች ቀሚስ፣ ሀብልና መስቀል የሚያዘወትሩት ደግሞ በመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት ያልተማሩ ነገር ግን በራሳቸው እይታም ሆነ በእውነት ምስክርነት “በተቋማቱ ከተማሩት አናንስም” ብለው የሚያስቡ ሰዎች መሆናቸውን ከልምድ መረዳት እንችላለን፡፡ አንዳንዶችም የምስክር ወረቀት (ሰርትፊኬት) ስልጠና መውሰድ “ቀሚስ ለመልበስ ፈቃድ እንደሚያሰጥ” የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡ እውነታው ግን በቅዳሴና መሰል የአምልኮ አገልግሎቶች ከሚለበሱ መደበኛ የካህናት ልብሶች (ልብሰ ተክህኖ) ውጭ የሚለበሰው ቀሚስ፣ የሚንጠለጠለው ሀብልና መስቀል የቤተክርስቲያንን ትውፊት ያልተከተለ ለተርዕዮ የሚደረግ ልማድ መሆኑ ነው፡፡

“የግል” ዘማሪያን አለባበስ

የዘማርያኑ ጉዳይ ከላይ ስለ ሰባክያኑ ከተነገረው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መዝሙርና መዘምራን ምንጊዜም የቤተክርስቲያን አካላት ናቸው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መዝሙር በዋናነት እንደቅዱሳን መላእክት በኅብረት የሚዜም ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ መዘምራን በአገልግሎት ወቅት የሚለብሱት ልብስ ነጠላን በመስቀል ቅርጽ መልበስና እንደየማዕረጋቸው የተማሩት ጥምጣምን መጠምጠም እና/ወይም ካባ መደረብ ናቸው፡፡ ካላፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በካሴትና በሲዲ መዝሙራትን በማተም፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት በግለሰብ ዘማርያን መዝሙር ማቅረብ እየተስፋፋ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህ የዘማርያን አገልግሎት በቅንነት ከተያዘ ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ይሁንና  መንፈሳዊ መዝሙርን በካሴት ወይም በሲዲ በማሳተም ለሽያጭ ማቅረብ “ቀሚስ የመልበስ ያልተጻፈ ፈቃድ” ማግኛ የሚመስላቸው ሰዎች በዝተዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ዘማርያን በቪዲዮ የተቀረጹ መዝሙሮችን ሲያሳዩ ወይም በአውደ ምህረት ሲዘምሩ እንደ ቀደመው ልማድ፣ ታይታ ባለመፈለግ የምዕመናንን ልብስ (ነጠላ) በመልበስ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት (ባለፉት 20 ዓመታት) መዝሙር የገንዘብና እውቅና ምንጭ መሆን ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ዘማርያኑም እንደ ዘፋኞች የታዋቂነት ስሜት (sense of celebrity status) እያጠቃቸው ስለመጣ “ከሰው ለመለየት” በሚል ፈሊጥ ቀሚስ መልበስ፣ ሀብልና መስቀል ማንጠልጠል ፋሽን እየሆነ መጣ፡፡ የማይገባውን ቀሚስ መልበስ ክብር ነው ከተባለ መዝሙርን መሸጥ እንደ አርቲስት ሊያስደንቅ ቢችልም ሳይሸጥ ከሚዘምረው የበለጠ ክብር የሚያሰጥ አለመሆኑ ግን ግልጽ ነው፡፡ በመስጠት እንጂ በመሸጥ መንፈሳዊ ክብር አይገኝምና፡፡ ስለሆነም መዝሙር ማሳተም ከዚህ መሰል አለባበስ ጋር ምንም የሚያገናኘው አመክንዮ የለም፡፡ ለምሳሌ የምናከብራቸው፣ የምንወዳቸው መንፈሳውያን ሴት ዘማርያን “ተመሳሳይ ቀሚስ” ሳይለብሱ፣ ሀብልና መስቀል ሳያንጠለጥሉ ማገልገል ከቻሉ ወንዶቹ ለታይታ የሚለብሱት ለምንድን ነው?

ታይታ የሚወዱት ቀሚስ ለባሽ ሰባክያንና መዘምራን ካላቸው አሳዛኝና አስቂኝ ልማድ ውስጥ ጎልቶ ለመታየት ሲሉ የሚመርጧቸው የልብስ ቀለማት ናቸው፡፡ ይህም ፉክክራቸው ከዘፋኞች ጋር መሆኑን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ሰባክያንና መዘምራን ከቀሚስ ቀለም መብዛት የተነሳ ትዝብትንና መጥፎ ስምን ያተርፋሉ፡፡ በየቀለማቱ ቀሚስ እያሰፉ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቀለም ያለው ሲለብሱ የተለያየ ተቀጥላ ስም እየወጣላቸው መዘባበቻ ይሆናሉ፡፡ ለእነርሱ የተለያየ ስም የሚሰጡም ይሰናከሉባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ቀይ ቀሚስ ሲለብሱ “ቀለሙ”፣ ደማቅ ቀሚስ ሲለብሱ “ደመቀ”፣ የሚያበራ ሲለብሱ “አበራ”፣ የጎላ ቀለም ያለው ሲለብሱ “ቦጋለ”…ወዘተ እየተባሉ ራሳቸውን ትዝብት ላይ ይጥላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ራስ ተሰናክሎ ሰውንም ማስናከል ያመጣው ሥርዓትን ያልተከተለ አለባበስ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አለባበስ

በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ከተማ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ለማክበር ከኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የተጋበዙ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ከፕሮቴስታንቶች የተጋበዙ የኪነት ቡድን (Choir) አባላት የየራሳቸውን መዝሙር በሚያቀርቡበት ሰዓት የለበሱት አለባበስ ይገርም ነበር፡፡ ከሰንበት ት/ቤት የተጋበዙት መዘምራን ኢትዮጵያዊ ውርስ የሌለውን ዩኒፎርም ሲለብሱ ከፕሮቴስታንቶች የተጋበዙት ደግሞ በአንጻሩ የኢትዮጵያውን መገለጫ የሆነውን ነጭ ልብስ ለብሰው ታድመው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከአጨፋፈራቸው ሥርዓት አልባነት እንዲሁም ሴቶቹ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትዕዛዝ ጸጉራቸውን ባለመሸፈናቸው የተነሳ ፕሮቴስታንቶቹ መንፈሳዊ ላህይ ባይኖራቸውም  ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የተሻለ ነበር፡፡ ይህን የሚታዘብ ሰው በዚያ ሰዓት እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችላል “ኦርቶዶክሳውያኑ ሌሎችን መምሰል የሚያስከብር መስሏቸው የሌሎችን ሲናፍቁ አባቶቻቸው ለዘመናት የጠበቁትን መንፈሳዊ መገለጫ ሌሎቹ ለማላገጫነት ይጠቀሙበታል፡፡”

ሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናትና ወጣቶች ትምህርተ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እየተማሩ የሚያድጉበት በቤተክርስቲያን ትልቅ ድርሻ ያለው የአገልግሎት ክፍል ነው፡፡ ሰንበት ተማሪዎች ለቤተክርስቲያን ከሚያበረክቱት አገልግሎት አንዱ መዝሙራትን በጋራ አጥንተው መዘመር ነው፡፡ ብዙዎቹም ለዚህ አገልግሎት የሚጠቀሙበት አልባሳት (uniform) አሏቸው፡፡ በዘመናችን እንደምናየው ከተለያየ ቀለምና በተለያየ ቅርፅ (አንዳንዶቹም የዲያቆናትን አልባሳት ለማስመሰል በሚመስል መልኩ) የሚሰሩ ቀሚስ፣ በራስ የሚደፋ ቆብ፣ በትከሻ ወርዶ በወገብ የሚታሠር ተንጠልጣይ ያለቸው ተጨማሪ ጌጦች ያሉበት የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ዋና የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን መገለጫ ሆኗል፡፡ በአደባባይ በዓላትም ከምስጋና መዝሙሩ ይልቅ የአልባሳቱ ቀለምና ጌጥጌጥ ላይ ያለው ፉክክር እየጎላ የመጣባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ የፖለቲካ ፍክክሩም እየጦዘ ሲመጣ የሰንበት ተማሪዎች ዩኒፎረም በሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ማሸብረቅ ጀምረዋል፡፡ የሰንበት ት/ቤት መዋቅር በቤተክርስቲያናችን እንዲመሰረት በቃለ አዋዲ የደነገጉልን አባቶቻችን ሰንበት ተማሪዎች ስለሚለብሱት ልብስ ሲደነግጉ “ዩኒፎርም” የሚለውን አገላለጽ መጠቀማቸው ልማዱ ከማን የመጣ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ ይህ እውነት ቢሆንም ይህ ልማድ ከሌሎች መምጣቱ በራሱ ልማዱን ስሁት ሊያደርገው አይችልም፡፡ እንዲያውም መነኩሴ መምሰል ከሚፈልጉ ቀሳውስትና ያለ ምንም መሰረት ቀሚስና መስቀል ከሚያደርጉ ዘመናውያን ሰባክያንና ዘማርያን ይልቅ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን አለባበስ ግለሰባዊነት የማይታይበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዘመናችን የምናየው የሰንበት ተማሪዎች ዩኒፎርም ቀድሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ያልነበረ፣ ከካቶሊካውያን የተወረሰ፣ ዘመን አመጣሽ ልማድ ከመሆኑ በላይ ከእርሱ ጋር ተያይዞ የመጣው የቀለማትና የመታየት ውድድር ግን ቤተክርስቲያኒቱን አይጠቅማትም፡፡ ይልቁንም ከሃይማኖታዊ አውድነት ይልቅ ወደ ምድራዊ ጥበብ (Art) መገለጫነት ሊለውጣት ይችላል፡፡ በአንዳንድ በዓላት ላይ ከመንፈሳዊ መዝሙርና ልባዊ አምልኮ ይልቅ እንደ ፖሊስ ማርሽ ቡድን ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ሥጋዊነቱ የሚጎላ ትርኢት ማሳየትን ቁም ነገር አድርገው የሚወስዱ አገልጋዮችም የዚህ ክፉ ልማድ ነጸብራቆች ናቸው፡፡ አገልግሎቱንም የልብ ሳይሆን የልብስ ያደርገዋል፡፡ ሕጻናትና ወጣቶቹም ከአስተምህሮውና ከሥርዓቱ ይልቅ ትኩረታቸው አልባሳቱ ላይ እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥንት የነበረው የመዘምራን አለባበስ ነጭ ሲሆን አንዳንዴ የቤተክርስቲያኒቱ ዓርማ የሆነው መስቀል ወይም የሰማዕታት ምልክት የሆነው ቀይ ምልክት ይደረግበታል፡፡ ይህም ከሥርዓቱና ከትውፊቱ ጋር አብሮ ከመሄዱም ባሻገር የሰው ልጆች እንደመላእክት ሆነው የሚያመሰግኑ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን አይነት አለባበስ ሲለብሱ የሚታዩት ዘማርያን ካህናትና የአንዳንድ ማኅበራት (ለምሳሌ የማኅበረ ቅዱሳን) ዘማርያን ናቸው፡፡ በተረፈ የተለያየ አሸንክታብ ቀለም የበዛባቸው ዩኒፎርሞች ግን እንኳን ከሰማያውያን ጋር አንድ ሊያደርጉን ይቅርና እርስ በእርሳችንም እያለያዩን ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በአለባበስ ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔው ምንድን ነው?

በአለባበስ ሰንበት ተማሪው ዲያቆን መምሰል፤ ዲያቆኑ፣ ሰባኪው፣ ዘማሪው ቄስ መምሰል፤ ቄሱ መነኩሴ መምሰል፤ መነኩሴው ጳጳስ መምሰል፤ ጳጳሱ ፓትርያርክ መምሰል ሥር የሰደደ የማስመሰል ችግር ማሳያ ነው፡፡ የአለባበስ ጉዳይ ትዕምርታዊ ነውና ያልሆኑትን መስለው መታየት የሚፈልጉት ሰዎችም የሚያሳዩት በውስጣቸው ያለውን ደካማ መንፈሳዊ ስብዕና ነው፡፡ ስለሆነም መፍትሄው በዋናነት ወደ ከንቱ ውዳሴ ከሚገፋና ለተርዕዮ ብቻ ከሚያፋጥን ፍጹም ዓለማዊ እይታ ራስን መከልከል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንኩስናን የምድራዊ ክብርና ዝና ምንጭ፣ በቤተክርስቲያን የገንዘብ አስተዳደር ላይ ለማዘዝ የሚያበቃ የምድራዊ ባለስልጣንነት መነሻ አድርጎ የሚያስብ ዘመን አመጣሽ በሽታ የችግሩ ማዕከል ስለሆነ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በቀለምና በጌጣጌጥ አሸንክታብ የታጀበ አለባበስ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ካለመከተሉም ባሻገር የአገልጋዮችንና የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያደበዝዝና ዓለማዊነትን እያጎላ መጥቶ በመጨረሻም ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ቢመራ መልካም ነው እንላለን፡፡

ቤተክርስቲያናችን በሥርዓትና በትውፊት የዳበረ የአገልግሎት አለባበስ አላት፡፡ የቤተክርስቲያን መለያ የሆኑ የመነኮሳትን ቀሚስና አስኬማ መናፍቃን ለማጭበርበር ሲያደርጉት ብዙዎቻችን ስህተት መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የሚገደን ሌሎች ሲጥሱት ብቻ ነው? የራሳችን ልማድና ሥርዓት በራሳችን አገልጋዮች እወደድ ባይነት ሲቃለልና ባዕድ ልማድ ሲቀላቀልበት የማይገደን ከሆነ ወገንተኝነታችን ለእውነትና ለቤተክርስቲያን አይደለም ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የካህናቱ፣ የዘማርያኑና የምዕመናኑ ቅድሚያ ትኩረት አገልግሎቱ ላይ ሆኖ ይህ አገልግሎትም ሲፈጸም የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ የዋጀና ሥርዓቷን የጠበቀ እንዲሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ለሥራና ለኑሮ የማይመቹ አለባበሶች ካሉም ሥርዓቱን ጠብቆ ማሻሻል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ጥምጣም መጠምጠም ለሁሉም ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ጥምጣም መጠምጠም ከባድ ሆኖባቸው በዚያ ምክንያት ወደ ቀሚስና ቆብ ለሚሄዱ ሰዎች መፍትሄ አለ፡፡ በተለያየ ምክንያት ከብዷቸው ከችግር የተነሳ ሌሎችን ለመምሰል ቀሚስና ቆብ ለሚያደርጉትም በአንዳንድ የውጭ ሀገራት አጥቢያዎች እንደሚታየው ተዘጋጅተው የሚሸጡ ጥምጣሞችን መጠቀም አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ ሥርዓቱን ካላከበርነው “ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ…” እንደሚባለው ይሆናል፡፡ 

ከቅዳሴ ውጭ ባሉ አገልግሎቶች ከመነኮሳት ውጭ ያሉ ሌሎች አገልጋዮች አለባበስን በተመለከተ ግልጽ የሆነ የሚነበብ ሥርዓት አለመኖሩ በብዙዎች ዘንድ ለሥርዓት አልበኝነቱና ግራ ለመጋባቱ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁንና በዓለማዊ የሕግ መርህም ሆነ በቤተክርስቲያን ልማድ ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ ሁሉ አስገዳጅ ሕግና ሥርዓት ማውጣት የሚደገፍ አካሄድ አይደለም፡፡ ለመንፈሳዊት ቤተክርስቲያን የአገልጋዮች ግላዊ አለባበስና ደካሞቹ የሚሳሱለት “ግርማ ሞገስ” ዋና ጉዳይዋ አይደለምና የግድ ግልጽ ሥርዓት ያስፈልጋል ማለት አሳማኝ ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ይልቅ ነገሮችን ለህሊና ፍርድ እየተው በቅንነት መንፈሳዊ ግዴታን መወጣት የተሻለ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ግልጽ ሕግና ሥርዓት ያልተደነገገባቸው ጉዳዮች በልማድና በአመክንዮ አይዳኙም ማለት አይደለም፡፡ አባታችን አቤል ግልጽ የመሥዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ባልነበረበት ዘመን በንጹህ ህሊና ተመርቶ ያቀረበው መሥዋዕት የተወደደ እንደሆነ ሁሉ ወንድሙ ቃየል ግን “በግልጽ አልታዘዝኩም” የሚል በሚመስል እሳቤ ህሊናውን ተቃርኖ ያቀረበው የሰነፍ መሥዋዕት የመንፈሳዊ ሞቱ ዋዜማ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህን ሕገ መጽሐፍ የሚረዱ፣ የሚያስረዱ፣ የሚተነትኑ መምህራን እንዴት ይህን ማስተዋል ተሳናቸው? ምናልባት በራስ ላይ መፍረድ ከፍርዶች ሁሉ ከባዱ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ለከንቱ ውዳሴ መታየትን የሚጠየፉ፣ ከስጋዊ ውበት ይልቅ መንፈሳዊ ዓላማን ያስቀደሙ የደጋግ አባቶቻችን አምላክ በዘመናችን ላሉ ካህናት፣ ሰባክያንና መዘምራን ማስተዋልን ያድልልን፡፡ አሜን፡፡

6 thoughts on “የካህናት፣ የሰባክያንና የዘማርያን አለባበስ፡ ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ!

  1. Pingback: ሰባኪ ማስመጣት: የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞና ዓለማዊ ጓዙ – አስተምህሮ

  2. Pingback: ሴቶች በቤተክርስቲያን (ክፍል ፫): አለባበስ – አስተምህሮ

  3. Pingback: ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት? – አስተምህሮ

  4. Pingback: መዓርግ አልባ የመዓርግ ስሞች በቤተ ክርስቲያን | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ

  5. Pingback: ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s