ኪዳነ ምህረት: የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር!

ኪዳን ምንድን ነው?

እግዚአብሔር አምላክ ዓለሙን ከፈጠረ ጀምሮ ፍጥረታቱን ሁሉ በቸርነቱ በርኅራሄው ይጠብቃል፤ ይመግባል፡፡  የሰው ልጆች ህግን በመተላለፍ፣ ኃጢአትን ሰርተው እግዚአብሔርን ባሳዘኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዝለው ከእርሱ ከልዑል እግዚአብሔር በረከት ጥበቃ እንዳይርቁ ስለባለሟሎቹ ቅዱሳኑ ብሎ በቃል ኪዳኑ ይጠብቃል:: እግዚአብሔር ከከባለሟሎቹ ጋር የሚያደርገው ቃል ኪዳን የቸርነቱን ብዛት ከሚገልጥባቸው መንገዶች አንዱ የሆነ ፍኖተ እግዚአብሔር ነው:: ‘ኪዳን’ በግእዙ ‘ተካየደ’ ትርጉሙም ተማማለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ ማለት ሲሆን እግዚአብሔር አምላክም ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ጋር የገባው ውል ‘ቃል ኪዳን’ ይባላል:: ቃል ኪዳን ማለትም ‘ውል፣ ስምምነት’ ማለት ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን በምህረቱ የሚጠብቅበትን ‘ቃል ኪዳን’ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር እንማራለን:: በተለይም ከቃል ኪዳን ሁሉ የከበረች ስለሆነች በየዓመቱ በየካቲት ፲፮ ስለምናስባት ከ፴፫ቱ የእመቤታችን በዓላት ከሆኑት አንዷ ስለሆነች የእመቤታችን የቃል ኪዳን ዕለትን በተመለከተ እንዳስሳለን::

ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር አምላክ ከመረጣቸው ከወዳጆቹና ከባለሟሎቹ ከቅዱሳኑ ጋር በየዘመናቱ የፈጸማቸው ኪዳናት እንደነበሩ ያስተምሩናል:: በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት መዝሙር “ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ:- ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” (መዝ.፹፱፡፫) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላክ በበደላችን ምክንያት እንዳንጠፋ የሚጠብቀን በዚሁ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው። ለምሳሌ ምድርንና ሥጋ ለባሹን በንፍር ውኃ ዳግመኛ ላያጠፋ ለአባታችን ለኖኅ ቃል ኪዳን ገብቶለታል (ዘፍ.፱፡፩-፲):: ለቀደሙት አባቶችም ለእነ አብርሃም ለቅዱስ ዳዊት ቃል ኪዳን ገብቷል፤ መሃላንም አድርጓል: (ዘፍ.፳፪፡፲፰ ዘፍ.፳፮፡፬ መዝ.፹፱፡፫):: ይህም ቃል ኪዳን እንደ ተርታ ውል ያለ ሳይሆን የፀና የምህረት ቃል ኪዳን ነው:: በብሉይ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት በዓመተ ፍዳ የተፈጸሙ ስለሆኑ የመከራውን ጊዜ ያወሳሉ:: በሐዲስ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት ደግሞ ዘመነ ምህረትን የሚያውጁና ጸጋቸውም የበዛ አማናዊ ኪዳናት ናቸው። በአንጻሩ ከቅዱሳኑ ጋር ያደረገው ኪዳን በአምላክ ሰው መሆን ፍጻሜን አግኝቷል::

የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን ለቅዱሳኑ ከሃይማኖታቸው ጽናት ከፍጹምነታቸውና ከሥራቸው ትሩፋት የተነሳ በቅድስና ክብር አክብሮ ለገድላቸው እንዲሁም በተጋድሎ ላሳለፉበት ቦታ ለረገጡት አፈር ሁሉ በረከታቸው ተርፎ ዛሬ እኛ ምእመናን በየመካናቱ እምነቱን በመተሻሸት በመጠጣት ከቅዱሳኑ በረከት እንሳተፋለንል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ምህረት የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ለሚወዱትም ትእዛዙን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን እንደሚያደርግ በመጽሐፍ እንደተጻፈ ከቅዱሳኑ ጋር ውልን የሚያደርገው እኛን የሰው ልጆችን በቅዱሳኑ በጎ ሥራ ለመጥቀም ፈልጎ ነው (ዘጸ ፳:፪-፮):: “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል” ዘዳ ፯:፲፪::

ኪዳነ ምህረት

ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጹም ከከበሩ የእመቤታችን በዓላት አንዱ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የማይጠፋ የዘላለም ኪዳን የሰጠበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ታላቁ የነገረ ማርያም መጽሐፍ እንደሚያስረዳን ጌታችን ካረገ በኋላ እመቤታችን ጌታ ወደ ተቀበረበት ጎልጎታ እየሄደች ትጸልይ ነበር:: ከዕለታት ባንዳቸው በየካቲት ፲፮ ዕለት ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ልጄ ወዳጄ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ ጌታችንም ምን እንዲያደርግላት ሲጠይቃት በስሟ ለሚማጸኑ መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ ለችግረኛ ለሚራሩ በስሟ ቤተ ክርስቲያን ለሚያንጹ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን ለሚሰጡ ምሕረትን እንዲያደርግላቸው ጠየቀችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ በየካቲት ፲፮ እለት ቃል ኪዳን ገብቶላታል:: ይህንን ቃል ኪዳን በነሐሴ ፲፮ ቀን ድግሞታል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም በየዓመቱ የካቲት ፲፮ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምህረት ውል ሰምምነት የተቀበለችበት ቀን በታላቅ መንፈሳዊ በረከት ታከብራለች፡፡ ይህ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የኪዳነ ምህረት በዓል ቀድሞ ለነበሩ ኪዳናት ኪዳነ አዳም ኪዳነ ኖህ ኪዳነ አብርሃም ኪዳነ ዳዊት መደምደሚያ ነው፡፡ ለዚህም የማያልፍ የምህረት ቃል ኪዳንን ስለገባላት ኪዳነ ምሕረት የምሕረት የይቅርታ መሐላ ውል ስምምነት እየታሰበ በመዝሙር፣ በማኅሌትና በቅዳሴ ይከበራል፡፡ ምዕመናንም በዚሁ ዕለት በረከትን ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ይቀበላሉ፡፡

ኪዳነ_ምህረት

በየካቲት ፲፮ ዕለት በስንክሳር እንደተጻፈ “መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድሆችና ለችግረኞች ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላላች:: በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የምህረት ቃል ኪዳን ውስጥ “ስምሽን የጠራ” ሲል በጸሎቱ በእርሷ የተደረገለትን የአምላክ ቸርነት እያሰበ ዘወትርና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በእምነት ጸንቶ በጎ ምግባርን እየፈጸመ ስሟን የሚጠራ ይድናል ማለቱ ነው፡፡ ቅዱሳን የሰው ልጆችን ልመና እንዲያቀርቡ መላእክቱም የቅዱሳኑን ጸሎት በማዕጠንታቸው እንዲያሳርጉ (ራእ ፰:፫-፬) ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነቢዩ ኤልሳዕም የነቢዩ ኤልያስን ስም እየጠራ በመጸለዩ በረከትን አግኝቷል፡፡ የነቢያት ትንቢታቸው፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ የመላእክት እህታቸው፣ የሐዋርያት ሞገሳቸው የሆነችው የድንግል ማርያምን ስም አምኖ ለሚጠራት ከዚህ በላይ ድንቅ ያደርጋል፡፡ እርሷ ለዓለማት ፈጣሪ እናቱ ናትና፡፡

ዝክርሽንም ያዘከረ” ሲል በእርሷ የተደረገለትን ድኅነት እያሰበ፣ በስሟ ለተቸገረ የሚመጸውት የዘላለም ሕይወትን ያገኛል ሲል ነው፡፡ እርሷን እናት ብሎ ያመነና የጠራት ልጅዋንም ወልድ ዋሕድ ብሎ ያምናል ይጠራልና ይህ ቃል ፍጹም እውነት ነው፡፡ “የአምላክ እናት” ብሎ ዝክሯን የሚያዘክር ልጅዋን “አምላክ” ብሎ አምኗልና “ዝክርሽን ያዘከረ ይድናል” የሚለው ቃል ጽኑዕ ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት መባዕን በስሟ የሚሰጡትም እንዲሁ ነው፡፡ ስም መጥራት የማመን የመታመን መገለጫ ነው፡፡ ዝክርን ማዘከርም በእምነት የሚደረግ የትሩፋት ሥራ ነው፡፡ በቅዱሳን ስም የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ማሳነጽ ደግሞ ከሁሉ የከበረ የጽድቅ ሥራ ነው፡፡

በስምሽ ቤተክርስቲያን ያሠራ” የሚለው ሀረግ የምዕመናንን ኅብረት በእምነት ያጸና፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትበትን ቤተ እግዚአብሔር ያሳነጸ፣ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆነውን የሰውን ልጅ የተዋሕዶን ትምህርት አስተምሮ ያሳመነና ያጠመቀ ድኅነትን ያገኛል ማለቱ ሲሆን ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት የተቀመጠ እውነተኛው የጽድቅ ሥራን የሚገልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ምልዕተ ፀጋ ብሎ ያመሰገናት ድንግል የአምላክ እናት እንዲሁም መልዕልተ ፍጡራን በመሆኗ በቅዱሳት መጻሕፍትም ‘ለእስራኤል የማልሁላቸው መሐላ የገባሁላቸው ቃል ኪዳንም ይህቺ ናት" (ኢሳ.፶፱፡፳-፳፩) እንዲሁም በቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው”; (መዝ.፹፮:፫) እንዳለ የእመቤታችን ቃል ኪዳን ከሁሉ ኪዳናት ልዩ ነው:: መልዕልተ ፍጡራን የሆነች እመቤታችን ከተመረጡትም ሁሉ በላይ የተመረጠች ናት:: በዚህም ፍጥረታት ሁሉ ተስፋ የሚያደርጓት ምክንያተ ድኅነት አማናዊት የድኅነተ ዓለም ተስፋ ናትና ከሁሉ ኪዳን በተለየ ‘ኪዳነ ምህረት’ ተብላ ትጠራበታለች::

ይህ ቃል ኪዳን የሚያገለግለው ለማን ነው?

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የምህረት ቃል ኪዳን የሚያገለግለው በሃይማኖታቸው ጸንተው በመልካም በቅድስና ሥራ በመትጋት ለሚደከሙ ለኃጥአን ነው:: አባታችን ቅዱስ ሕርያቆስም ይህንን በቅዳሴ ማርያም “አዘክሪ ድንግል ለኃጥአን ወአኮ ለጻድቃን:- ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥአን አሳስቢ” በማለት ይገልጸዋል:: አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌው “ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ:- የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር” በማለት የእመቤታችንን ቃል ኪዳን አማናዊነት ይገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የእመቤታችን የምህረት ቃል ኪዳን አለና በእርሱ ድኅነትን እናገኛለን በማለት በጎ ምግባርን፣ ትሩፋትን ከመሥራት ቸል ማለት አይገባም፡፡ እርሷ የሚላችሁን አድርጉ እንዳለች ልጅዋ የሚለንን ለማድረግና ባልቻልነው ነገር ደግሞ የእርሷን አማላጅነት እንጠይቃለን፡፡

የእመቤታችን የቃል ኪዳን ምልጃ: ታሪክ ዘስምዖን 

አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ለንጹሃን ሳይሆን በኃጢአት ላሉ ለደካሞች የእመቤታችን ቃል ኪዳን መድሃኒት ምህረት ነው ብሎ እንደገለጸው በተአምረ ማርያም ከተመዘገቡትና የእመቤታችንን አማላጅነት ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ በዚህች እለት በየካቲት ፲፮ የሚነገረው የስምዖን (የበላዔ ሰብእ) ታሪክ ነው:: በላዔ ሰብእ አስቀድሞ ቅምር በምትባል ሀገር በአብርሃማዊ ኑሮ የሚኖር ደግ ሰው ነበር:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ቆሮ ፲፩፥፲፬ ላይ “ሰይጣን ራሱን የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ይለውጣል” በማለት እንደገለጸው በበላዔ ሰብእ የቀናው ዲያብሎስም በቅድስት ሥላሴ አምሳል ሦስት ሰዎችን ተመስሎ እንግዳ ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በላዔ ሰብእም እግዚአብሔርን ያስተናገድኩ መስሎት በደስታ ያማረ ምንጣፍ ጎዝጉዞ ወገቡን ታጥቆ የሰባውን ፍሪዳ በመሰዋት አስተናገደው:: በሥላሴ ተመስሎ በቤቱ የተገኘው ዲያብሎስ ግን አዳምንና ሔዋንን በክፋት ስራው እንዳሳተ ስምዖንንም “ልጅህን ሠውተህ እራት አዘጋጅልን” ብሎ ጠየቀው፡፡ ስምዖንም የእንግዶቹን ፈቃዳቸውን ሁሉ ሊፈጽም ቃል ገብቶ ነበርና መሃላውን እያሰበ ልጁን አቅርቦ ሰዋው:: እንደትእዛዛቸው ከቀረበው መስዋዕት አስቀድሞም ቀመሰ:: ከዚህ በኋላ ዲያብሎስም ተሰወረው፡፡

በላዔ ሰብእ የልጁን ሥጋ በመብላቱ ጠባዩ ተለውጦ ከዚያ በኋላ ቤተ ሰቦቹን ጨምሮ ሰባ ስምንት ሰዎችን በልቷል:: በላዔ ሰብእ የሚለው ስያሜውም ከዚሁ ታሪክ እንደምንረዳው ሰውን የሚበላ በሚል ነው:: በዚህም ሕይወት ሲዘዋወር ሳለ ሁለንተናው በቁስል የታመመ ሰው ተመለከተ:: ይህም ሰው በላዔ ሰብእን ‘አምላክን ስለ ወለደች ድንግል ማርያም ብለህ ውሃ አጠጣኝ” ሲለው በላዔ ሰብእም ልቡ ራርቶ ወደ ልቡናው ተመልሶ ለድሀው ያለውን ውኃ ሰጠው፡፡ ይህም በላዔ ሰብእ በመልካም ሥራ ደካማ ሲሆን ነገር ግን የሃይማኖት ልብ እንዳለው የሚያሳይ ነው:: በላዔ ሰብእ ከሞተ በኋላ ነፍሱ በፈጣሪ ፊት ለፍርድ ስትቆም ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት ይህቺን ነፍስ እያስፈራሩ ወደ ሲዖል ወሰዷት:: እመቤታችን ግን ልጄ ወዳጄ ማርልኝ ስትል ለመነችው፡፡ በመልክአ ኪዳነ ምህረት ድርሰት “እንበለ ምግባር ባሕቱ እመ ኢይጸድቅ አነ ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ:- ያለ በጎ ሥራ የምንጸድቅ መንግስተ ሰማያትን የምንወርስ ካልሆነ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ቃል ኪዳንሽ በከንቱ ነበርን?” ተብሎ እንደተጻፈ ሰባ ስምንት ነፍሳትን የበላው በላዔ ሰብእ የእመቤታችን ቃል ኪዳኗ በሚታሰብበት እለት ለድሃው ውኃን ስላጠጣ ነፍሱ በእመቤታችን ቃል ኪዳን አማላጅነት ዳነች::

እግዚአብሔር አምላክ እንኳንስ ለድኅነተ ዓለም ለመረጣት መዓዛ ንጽሕናዋን ቅድስናዋን ለወደደላት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ይቅርና እግዚአብሔርን ከማያውቁ ከአሕዛብ ወገን ከሆነች ከነናውት ሴት ስለ ልጇ ብትለምን ምሕረት የባህሪው ነውና  በልመኛዋ ልጇን ምሮላታል:: ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁላችን አማላጅ እናት ትሆን ዘንድ በቀራዮ ተሰጥታናለችና ለልጆችዋ ምህረትን የምትለምን አዛኝት እናት ነት (ዮሐ ፲፱:፳፮ – ፳፯):: ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ላይ “ወዮ ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው የቀድሞ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ፤ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል ሆይ፤ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት እመቤታችን ለፍጥረት ሁሉ አማላጅ መሠረተ ድኂን መሆኗን መስክሯል::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጥነሽ የምትደርሽ

ጌታችን በወንጌል እንደተናገረው “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ፃድቅንም በፃድቅ ስም የሚቀበል የፃድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም” (ማቴ.፲፡፵፩-፵፪) የበላዔ ሰብእ ሕይወትም እግዚአብሔር አምላክ የምህረት አምላክ እንደሆነ በምክንያት በመረጣቸው ላይ አድሮ ለእኛ ለልጆቹ የሚሰጠው ምሕረቱ መገለጫ ነው::

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ጸሎት “አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወዓጸባ፣ ለዓይን እምቀራንባ:- ማርያም ሆይ በችግርና በመከራ ጊዜ ከዓይን ጥቅሻ ይልቅ ለእርዳታ ፈጥነሽ የምትደርሽ” በማለት ለሚጠሯት ፈጥና የምትደርስ እናት መሆኗን ተናግሯል፡፡ አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል:: አንተ ‘መታሰቢያሽን ያደረገ ስምሽንም የጠራ የዘላለም ድኅነትን ይድናል’ ብለሃታልና” ብሎ እንደገለጸው ዛሬም ስሟን ጠርተው ለማይጠግቡ ሲያወድሷት ለማይሰለቹ ዝክሯን በማዘከር መታሰቢያዋን በማድረግ ዘወትር ተአምሯን በመስማት በማሰማት ለሚተጉ መቅደሷን ለሚሰሩ ፈጥና የምትደርስ አፍጣኒተ ረድኤት ናት።

በአጠቃላይ በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው የኪዳነ ምህረት በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጅዋ ከወዳጅዋ የምህረት ቃል ኪዳንን የተቀበለችበት ነው፡፡ በዚህ ቃል ኪዳንም የምንጠቀመው እኛው ነንና ስለ ቅዱሳኑ ብሎ የሚምር አምላክ ስለ ምህረት ቃል ኪዳኗ ሲል እንዲምረን በቅዳሴ ዘወትር ስሟን እያነሳን “ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን” እያልን እንለምናታለን:: ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ስድሳ አራት ጊዜ “ቅድስት ሆይ ለምኝልን” እያለ፣ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሀን አሥራ ሦስት ጊዜ “ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን” እያለ እንዳመሰገናት እኛም በአባቶቻችን ፈንታ የተወለድን ልጆችዋ ዛሬም እስከ ዘላለሙ ቅድት ሆይ ለምኝልን ብለን እንማጸናታለን፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ እመቤታችን በአማላጅነቷ በረድኤቷ አትለየን፤ በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

4 thoughts on “ኪዳነ ምህረት: የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር!

  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! ለበለጠ አገልግሎት ያትጋልን! ረጅም የአገልግሎት ዕድሜ ይስጥልን! በፀጋው ያክብርልን አሜን!!!

    Liked by 1 person

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s