የሰው ልጅ ሕግን ተላልፎ ጸጋውን ከተገፈፈ በኋላ ሰውነቱን መሸፈን አስፈልጎታል። ይህም በመጀመሪያ በቅጠል፣ ከዚያም ከቆዳ በተሠሩ ‘አልባሳት’ እና ቀጥሎም የሰው ልጅ የስልጣኔ ውጤት በሆኑት ከጨርቅ የተሠሩ አልባሳትን በመጠቀም ሲፈጸም ኖሯል። ልብስ የመልበስ ዋናው ዓላማ ሰውነትን መሸፈንና ከብርድና ከሐሩር መከላከል ቢሆንም በዘመናት ብዛት አለባበስ የባህልና የማንነት ነፀብራቅ እንዲሁም የውበት መገለጫ ሆኗል። በክርስትና ሃይማኖትም አለባበስ (በተለይም የሴቶች አለባበስ) አንዱ የሚያወያይ ጉዳይ ነው። የሴቶችን አለባበስ በተመለከተ ማስተማርም ይሁን መመካከር የሚገባቸው በዋናነት ሴቶች ራሳቸው መሆናቸውን እንገነዘባለን። ይህን ታሳቢ በማድረግ በዚህች ጦማር የሴቶች አለባበስን የሚመለከቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎችንና ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን እንመለከታለን።
የጸሎት ጊዜ (የቤተክርስቲያን) አለባበስ
በቤተክርስቲያን ያለው የሁሉም ሰው አለባበስ ሥርዓት ያለውና በተለይም ለጸሎት የሚገባ መሆን እንዳለበት ቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን ትውፊት ያስረዳሉ። ይህም ወንዶችም ሴቶችም ነጭ ነጠላ ለብሰውና መላእክትን መስለው (ነጭ የነፃነትና የጽድቅ ምሳሌ ነውና)፣ ሴቶች ፀጉራቸውን ሸፍነው፣ ወንዶች ራሳቸውን ሳይሸፍኑ መጸለይ እንደሚገባቸው የተነገረው ነው። ሐዋርያው ይህን አብራርቶ ሲገልፅ “ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና። ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን። ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።… በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን? ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታልና።” በማለት አስተምሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ለጸሎት (በቤተክርስቲያን ለማስተማር ለመማር፣ ለመዘመር፣ ቅዳሴ ለማስቀደስ ፣ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል) ወቅት የተነገረ መሆኑን ማስተዋል ይገባል (1ኛ ቆሮ 11:4-15)።
በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ቆጥራ፣ ለይታ ከምትቀበላቸው ከ81ዱ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ በሆነው የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጽሐፍ ‘ነገር ግን ላመኑ ሴቶች ራሳቸውን በንጽሕና ሊከናነቡ ይገባል፡፡ የፊታቸውን ውበት በማሳመርና ቀለም በመቀባት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በፈጠረው መልክ ውስጥ ጥቅም በሌለው ኩል መኳልና ማጌጥም አይደለም፡፡ እንደዚህ ያለውን ሁሉ አይሥሩ፡፡ ነገር ግን እነርሱ ተከናንበው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይሂዱ። (ዲድስቅልያ አንቀጽ 3)” በማለት ተገልጿል። ቅዱሳት መጻሕፍት “ራስን ዝቅ ስለማድረግ” የሚያስተምሩት ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም፣ ይልቁንም ከፍ ባለ አገልግሎት ለተሰማሩት ሁሉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል እንጂ የመጻሕፍትን ንባብ ያለአውድ እየጠቀሱ ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነትን ለማንበር መጠቀም አይገባም።
ሴቶች በሚገባ ልብስ ሰውነታቸውን ይሸልሙ!
ሴቶች በሚገባው መንገድ እንዲሸለሙ፣ እንዲዋቡና እንዲያጌጡ መጽሐፍ ያስተምረናል። ከዚህ አኳያ የወንድም ይሁን የሴት ክርስቲያን አለባበስ ሌሎችን በዝሙት ምኞት እንዳይፈትን መደበኛ ልብስ፣ የራሳቸውን ኢኮኖሚም እንዳይፈታተን በአቅማቸው ያለውን ልብስ ቢለብሱ መልካም ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በሚመለከት “እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። (1ኛ ጢሞ 2፡9-10) በማለት አስተምሯል።
ቅዱስ ጴጥሮስም “እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና” በማለት ስለአለባበስ አስተምሯል፡፡ 1ኛ ጴጥ 3፡2-5
የሴትና የወንድ ልብስ የተለያየ ነው!
በሴቶች አለባበስ ዙሪያ ከሚነሱ ነገሮች አንዱ ሱሪ የመልበስ ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ስለ ወንዶች አለባበስ ባይነሳም የሴቶች አለባበስ ግን ታላቅ ርዕስ ነው የሚሆነውን ከዚህ የተነሳ ነው። አንዳንዶችም “ለምን የሴቶች አለባበስ ላይ ብቻ ታተኩራላችሁ? የወንዶች አለባበስስ ቅጥ እያጣ መጥቶ የለም ወይ?” ሲባሉ “የሴቶች አለባበስ ወንዶችን በዝሙት ስለሚፈትን ነው” ይላሉ። ምክንያቱ ይህ ከሆነ “ወንዶች በአለባበስ የማይፈተን ልብ እንዲኖራቸው፣ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ለምን አታስተምሩም?” ሲባሉ መልስ የላቸውም። ችግሩ የዝሙት ፈተና ከሆነ የሚመለከተው ሁለቱንም እንጂ ሴቶችን ብቻ አይደለም። የዝሙት ሀሳብም ከሰው ልብና ሕሊና የሚመነጭ እንጂ አንድ አይነት አለባበስ ሲያዩ የሚከሰት ሌላ አይነት አለባበስ ሲያዩ የሚከስም ፍላጎት አይደለም። ከሌላም አንጻር ሲታይ ሴቶች የሚለብሱት የሚገባውን፣ ለሥራ የሚመቻቸውን፣ የሚወዱትንና የሚያምርባቸውን ልብስ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ሴቶች የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ብለው ይለብሳሉ ማለት በጣም የተሳሳተ ጥቅል ፍረጃ (hasty generalisation) ነው። የዚህ ሁሉ ስሁት አስተሳሰብ መሠረታዊው መነሻ ግን ለሴቶች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ነው።
በተለይም “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፣ ወንድ የሴት ልብስ አይልበስ” (ዘዳ 22:5) የሚለውን በመጥቀስ “ሴት ሱሪ መልበስ የለባትም” ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ቁጥር ጥቂት አይደለም። ይህ የመጽሐፍ ቃል ግን ለሚያስተውለው ሰው የሚያመለክተው የወንድና የሴት ልብስ የተለያየ መሆን እንዳለበትና ለአንዱ የተዘጋጀውን ወይም አንዱ የሚለብሰውን ልብስ ሌላው እንዳይለብስ ነው። ይህም የፆታ ልዩነት በአለባበስም ጭምር የሚገለጥ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ ባለፈ ግን “የወንድ ልብስ ይህ ነው፣ የሴት ልብስ ያ ነው” በሚል አስተሳሰብ ሊወሰን አይገባውም። የወንድና የሴት ልብስም እንደየባህሉ፣ የአየር ፀባይ፣ የሙያ ዘርፍና ሥልጣኔ ደረጃ የሚለያይ ስለሆነ ከዚህ ልብስ ውጭ ወይም ይህንን ልብስ ብቻ ልበሱ ማለት አስቸጋሪ ነው። በተለይም ወንዶችን ትቶ ሴቶችን ብቻ የማይለወጥ አለባበስ እንዲኖራቸው የሚጎተጉት እይታ ምንጩ ከመንፈሳዊነት ይልቅ በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሴቶችን አሳንሶ የማየትና የፆታ እኩልነትን ያለመቀበል ዝንባሌ የወለደው ይመስላል።
ክርስትና ክርስቶስን መልበስ ነው!
ጠቢቡ ሰሎሞንም “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት (ምሳ 11፡22)” በማለት ሴት ውብ ብቻ ሳይሆን በልቧም ጥበበኛም መሆን እንደሚገባት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ስለልባም ሴት ሲናገር “ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች (ምሳ 31፡25)” በማለት ገልጿታል፡፡ ይህም ሴቶች ከውጭ ውበት ጋር ውስጣዊ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ እንዳላባቸው ያስተምረናል። ከዚህም አንጻር በክርስትና ሕይወት ዋናው ጉዳይ ክርስቶስን መልበስ ነው እንጂ የሚያረጅ ልብስን መልበስ አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልፅ “ክርስቶስን ልበሱት” (ሮሜ 13:14) ነው ያለው። ስለዚህ ክርስትናችን በልብስ ጉዳይ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የሕይወታችን መሠረት የሆነው ክርስቶስን የመልበስ ጉዳይ ላይ ሊያተኩር ይገባል። ክርስቶስን መልበስ በምን ይገለፃል? በማኅበረሰባችን ዘንድ ያለው የሴቶችን አለባበስ ብቻ ነጥሎ የሚያጠቃ መንፈሳዊ መሠረት የሌለው ፍረጃ የአስተሳሰብ ምንጮቹ ምንድን ናቸው? የሚከተሉትን ማሳያዎች ተጠቅመን እነዚህን ሀሳቦች እንመርምር።
ማሳያ 1: ቀሚስ ዋነኛ የአገልግሎት መመዘኛ?
መንፈሳዊ አገልግሎት ራስን ከማሳየት እግዚአብሔርን ወደማሳየት ለማደግ የሚደረግ ጉዞ ነው ልንለው እንችላለን። ስለሆነም ለአገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጡ መንፈሳውያን አገልጋዮች በኑሮአቸው ሁሉ የግል ፍላጎታቸውን በመጫን፣ ራስን መግዛትን በሚያሳይ አለባበስ መታየታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ለመንፈሳዊ ዓላማ ሥጋዊ ውበትና ምቾትን መተው ዋጋ ያለው ሰማዕትነት ነው። ይሁንና በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ቀሚስ መልበስን ብቸኛ (ዋነኛ) የመንፈሳዊነት ማሳያ እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት የመመረጥ የይለፍ ኮድ (pass code) ሲሆን ይታያል። ቀሚስ መልበስ በሰንበት ት/ቤቶች፣ በግቢ ጉባኤያትና መሰል የአገልግሎት ማኅበራት ሴቶችን ወደአገልግሎት ለማቅረብ በታዋቂም በውስጠ ታዋቂም እይታ እንደ ዋነኛ መመዘኛ የሚቀርብባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው። በብዙዎች ዘንድ ሊታወቁ የሚችሉ ውሳጣዊ የመንፈሳዊነት ማሳያዎችን እንደአቅም ከመመርመር ይልቅ በቀሚስ መልበስ ላይ የተንጠለጠለ የአገልግሎት ምርጫ ይደረጋል።
ስለሆነም ከላይ በተጠቀሱት መስኮች ሴቶችን ወክለው በአገልግሎት ኃላፊነት የሚቀመጡት እህቶቻችን በቁጥር በጣም አነስተኛ ይሆናሉ። በአንፃሩ ሌሎች በልዩ ልዩ ማሳያ እውነትም ክርስቶስን የለበሰ ማንነት ያላቸው እህቶቻችን ከሚወዱት፣ ከሚፈልጉት አገልግሎት በቀሚስ ምክንያትነት በአፍአ ይቀራሉ። ለወንዶች ሲሆን እምብዛም የማይተኮርበት አለባበስ በቤተክርስቲያን አገልግሎት በቂ ሱታፌ እንዳይኖራቸው ባህልና ልማድ የከለከላቸውን ሴቶች የበለጠ ያርቃል። በተለይም ለራሳቸው ከቤተክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት በሚጣላ ሁኔታ ቀሳውስቱ እንደመነኮሳት፣ እንደ ጳጳሳት፣ መምህራኑና ዘማርያኑም እንደቤተክርስቲያን ውርስ ሳይሆን እንደ ምዕራባውያን ሴሚናሪ ሰዎች በማስመሰል በዓለማዊ አሸንክታብ የተሞሉ የማስመሰል ቀሚሶችን የሚለብሱ የዘመናችን ተርእዮ (ታይታ) ወዳጅ ካህናትና መምህራን ይህን መሰሉን ያልተመጠነ ትችት በሴቶች አገልጋዮች ላይ ማቅረባቸው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ መሰረትም የለውም።
ማሳያ 2: ቀሚስ ሲወልቅ አብሮ የሚወልቅ መንፈሳዊነት
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የሚገለፀውbምክንያት ቀሚስ ብቻ መልበስን ሲተው በሚገርም ሁኔታ በርካታ የመንፈሳዊነት መገለጫዎችንም አብረው ያወልቋቸዋል። ይህም ቢቻል በፈሪሐ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን በመፍራት) ባይቻል ደግሞ በአክብሮተ ሰብዕ (ሰዎችን በማክበር) የሚፈፀሙ መንፈሳዊ ፍሬዎችን ከአለባበስ ለውጥ ጋር በመተው “ከታሰረበት እንደተፈታ” የመሆን ውጤት ሲያመጣ ታዝበናል። ለሴቶች ቀሚስ መልበስ ብቻውን የጥሩ ክርስቲያንነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ቀሚስ አለመልበስም ብቻውን የኃጢአተኝነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ነጭ ነጠላን መልበስም እንዲሁ ነው። ሥርዓት ያለው አለባበስ አስፈላጊ ቢሆንም ብቸኛ የጥሩ ክርስቲያንነት መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። መንፈሳዊ ሕይወት በልብስ ብቻ ሳይሆን በልብ፣ በሀሳብ፣ በንግግርና በተግባር የሚገለጥ ነውና። ይሁንና በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው “አለባበስ ከመንፈሳዊነት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም” ወደሚል የተሳሳተ ፅንፍ መሄድ አይገባም። የዚህ ጦማር ዓላማም ሴቶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ የአለባበስ እሳቤዎች ከመንፈሳዊ ይልቅ የተዛባ ማኅበራዊ እይታን እንደሚያሳዩ መተንተን እንጂ “ችግር የለውም፣ ያለ ገደብ ያሰኛችሁን ሁሉ ልበሱ” ለማለት አይደለም።
መልእክተ አስተምህሮ
በአለባበስ ጉዳይ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና የሚደረጉ ክርክሮች ሴቶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩት በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሴቶች ባለው የተዛባ አመለካከት የተነሳ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን የምንለው የአለባበስ ችግሮች የሚታዩት በሁለቱም ፆታዎች ስለሆነ ነው። ከአለባበስ አንጻር የቤተክርስቲያን አስተምህሮ የሚመለከተው በቤተክርስቲያን (በጸሎት ጊዜ) ያለውን አለባበስ ነው። ይህም በዋናነት በጸሎት ጊዜ ሴቶች ጸጉራቸውን ይሸፍኑ፣ ወንዶች ጸጉራቸውን አያሳድጉ (አይሸፍኑ) የሚል ነው። ቤተክርስቲያን እንደተቋምም ቢሆን የራሷን የአለባበስ ሥርዓት ማስቀመጧ የተገባ ነው። እንኳን በሰማያዊ ንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት ለሚደረግ አምልኮና አገልግሎት ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ተቋማትም የራሳቸው የአለባበስ መመሪያ (dressing code) አላቸውና። በምድራዊ መሥሪያ ቤት እንኳን የአለባበስ መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ ሰማያዊት በሆነችው ቤተክርስቲያን እንዴት አብዝቶ አይከበር?! የቤተክርስቲያን የአለባበስ ስርዓት እንዳለ ሆኖ ከቤተክርስቲያን (ከጸሎት ውጭ) ያለው አለባበስ ግን የየማኅበረሰቡን የአለባበስ ባህል (norm) ያማከለ ሊሆን ይገባዋል። ክርስቲያን በሥራ ቦታም የየመስሪያ ቤቱ መመሪያ በሚያዘው ወይም የሥራው ፀባይ (dressing code) መከተል አስገዳጅ ሊሆን ይችላል።
የሴቶችን አለባበስ ስናነሳ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ስለሴቶች አለባበስ ጥናት በማድረግ፣ በማስተማር፣ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ሴቶች መሪ ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸው ነው። ለዚህም ሴቶችን በዕውቀትና በክህሎት ማብቃትና የውሳኔ ሰጭነት ኃላፊነት መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ (የቤተክርስቲያን ሥርዓት የተጠበቀ ሆኖ) ‘እኛ እናውቅላችኋለን፣ እኛ የምንላችሁን ብቻ አድርጉ’ አይነት አካሄድ የትም አያደርስም፣ ይልቁንም ቤተክርስቲያንን በሂደት ያደክማታል እንጂ አይጠቅማትም። በአጠቃላይ ሲታይ ግን የክርስቲያን በተለይም የሴቶችን አለባበስን በሚመለከት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በአራት መልእክቶች ላይ ያተኩራል።
መልእክት 1: የማይፈትን አለባበስ
የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እያንዳንዱ ክርስቲያን (ወንድም ሴትም) የራሱን እና የሌላውን ሰው ክርስቲያናዊ ሕይወት የማይጎዳ አለባበስን እንዲያዘወትር ይመክራል። ክርስቲያን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ሕይወት ያስባልና አለባበሱ ሌላውን የሚፈትን ከሆነ የሚወደው አለባበስ እንኳን ቢሆን በማይፈትን መልኩ ሊያደርገው ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ከእንግዲህ ሥጋ አልበላም” ባለው መሠረት አለባበሳችንም ሌላውን የሚያሰናክል ከሆነ “የራሱ ጉዳይ” ማለት ሳይሆን ለሌላውም ሊያስብ ይገባዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተለይ በአለባበስ ሰውን መፈተን እንደሚያስጠይቅ አስተምሯል። ነገር ግን ሰውን የሚፈትን ወይም ከቤተክርስቲያን ሥርዓት የወጣ አለባበስ ለብሰው ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡ ምዕመናንን በፍቅር ቀርቦ ማስተማር ይገባል እንጂ በመፍረድ፣ በማንጓጠጥ፣ በመሳደብ፣ በመተቸት፣ በማጥላላት፣ በማግለል፣ በሐሜት ወይም ሌሎች ኢ-ክርስቲያናዊ የሆኑ ጸባያትን በማሳየት ከቤተክርስቲያን ማራቅ አይገባም።
መልእክት 2: በአቅም መልበስ
የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ክርስቲያኖች ከኢኮኖሚ አቅማቸው በላይ ውድ የሆኑ ልብሶችን መልበስ ጉዳት እንዳለው ያስተምራል። ከአቅም በላይ ውድ የሆኑ ልብሶችን መልበስ የኢኮኖሚ አቅምን አቃውሶ ለድህነት ከመዳረጉም በላይ ለጥፋት በሚታትሩ ሰዎች ትኩረት ውስጥ መግባትን እና በክርስትና ሕይወትም መፈተንን ያመጣልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ” ብሎ ያስተማረው በአለባበስም ጭምር መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይልቁንም ክርስቲያን ለራሱ በመጠን እየለበሰ የታረዙትን ሊያለብስ ይገባዋል እንጂ ለራሱ ብቻ ውድ ልብስን መልበስ ላይ ሊያተኩር አይገባውም።
መልእክት 3: ባህልን መዋጀት
ክርስትናን በተወሰነ ባህላዊ ማንነት አጥረው “ክርስትና የራሱ ባህል ስላለው ክርስቲያን ባህልን መዋጀት አያስፈልገውም” በሚል እሳቤ የሚያምኑ ወገኖች ቢኖሩም ከተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ግን ክርስቲያን ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ያለውን የአለባበስ ባህል ከክርስትናቸው ጋር አጣጥመው ሊዋጁ ይገባል እንላለን። ክርስቲያን በሕይወቱ ክርስቶስን መምሰል እንዳለበት ግልጽ ነው። ከክርስትናው ጋር በሚጣጣም (በማይጋጭ) መልኩ የአካባቢውንም ባህል መዋጀትም መልካም ነው። ይህም ቅዱሳን ሐዋርያት ጭምር የሚያስተምሩትን ሕዝብ አለባበስ ለብሰው በማስተማራቸው ተገልጧል። ክርስቲያንም በአካባቢው ባህል መሠረት መልበሱ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ፈተና ላይ ከመጣል ያድነዋል። በማኅበረሰቡም “አፈንጋጭ” ተብሎ ከመገለልም ይተርፋል። በሌላ በኩል በክርስቲያናዊ አለባበስ ስም የአንድን ማኅበረሰብ የአለባበስ ባህል በሌላው ላይ መጫን አይገባም። ይህንን ማድረግ የአንድን ማኅበረሰብ ባህል ካለማክበሩም ባሻገር ቤተክርስቲያንን በዚያ ማኅበረሰብ ዘንድ ባዕድ እንድትሆን ያደርጋታል። ሁሉም በራሱ መንገድ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ መልክ እንዲያንፀባርቅ ማድረግ እንጂ “ቀድሞ የተንፀባረቀውን ብቻ እንከተል” ማለት አይገባም።
መልእክት 4: የቤተክርስቲያንን ሥርዓት መጠበቅ
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና ካህናት የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚያንጸባርቅ አለባበስ ሊኖራቸው እንደሚገባ እሙን ነው። ይህ በተለይም በቤተክርስቲያን እና መንፈሳዊ አገልግሎቶች በሚፈጸሙባቸው መርኃግብሮች ሊተገበሩ ይገባል። የቤተክርስቲያን መምህራንም ይህንን በሰፊው ማስተማር ይገባቸዋል። እናቶች ለሴት ልጆቻቸው፣ እህቶችም ለሌሎች በዕድሜ ታናናሽ ለሚሆኗቸው እህቶቻቸው በመንፈሳዊ አገልግሎት የቤተክርስቲያንን የአለባበስ ሥርዓት ማስተዋወቅና ማስተማር ይገባቸዋል። ነገር ግን ሁሉም አስተምህሮ በመጻሕፍትና በትውፊት ባለው ላይ ሊመሠረት ይገባዋል እንጂ በተወሰነ ማኅበረሰብ ባህል ወይም በተወሰኑ ግለሰቦች የወግ አጥባቂነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ይህን መሰሉ አካሄድ ቤተክርስቲያንን የአልባሳት ፉክክር መድረክ ከማድረግ አያልፍም።
ስለዚህም ሁሉም ክርስቲያን በጸሎት ወቅት (በቤተክርስቲያን) የክርስቶስን ትንሣኤ ምስክርነት የሚገልጸውን ነጭ ልብስ መልበስ ይገባዋል። ከሥርዓት የወጣ አለባበስ በቤተክርስቲያን ሲታይም ስለ መልካም አለባበስ ቀስ በቀስ በማስተማር እንጂ ሰውን በማንጓጠጥ፣ ማሸማቀቅና በማግለል በሰው ላይ በደል መፈጸም አይገባም። ማሸማቀቅና ማግለል ሰውን ከቤተክርስቲያን ያርቀዋል እንጂ አያቀርበውም። ሰውን በመፍራት ብቻ የምንከተለው አለባበስም ዘለቄታ የለውም። ሰው ተምሮ፣ እውቆ፣ ተረድቶና አምኖበት አለባበሱን እንዲያስተካክል ዕድል ሊሰጠው ይገባል። በመጨረሻም የክርስትናችን ዋናው ትኩረት በውጭ በሚታየው አለባበስ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ሊሆን ይገባል እንላለን። በልጅነት ጥምቀታችን የለበስነው ክርስቶስ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጸንተን መንግስቱን ለመውረስ ያብቃን። አሜን!
የተሀድሶ ጽሁፍ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ መቼ ነው የምትወርዱት??? ቤተክርስቲያን እናንተ እንደጻፋችሁት አታስተምርም። የሴት ቀሚስ ከሆነ ቀሚስ መልበስ እንጅ ለጸሎት ግዜ እንጅ ከዚያ ውጭ ችግር የለውም አይነት ቅመም ያለው ጽሁፍ ከላይ እስከ ታች የማይረባ ጽሁፍ ነው።
LikeLike