ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፬): በወር አበባ ጊዜና ከወሊድ በኋላ

women in church_2መግቢያ

“ሴቶች በቤተክርስቲያን” በሚለው ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሌላው የሚያወያየው ነጥብ ሴቶች በወር አበባ (ደመ ጽጌ፣ ልማደ አንስት) ወቅትና ድኅረ ወሊድ (ሕፃን ልጅ እስኪጠመቅ ድረስ) ወደ ቤተክርስቲያን መግባት የለባቸውም የሚለው የሠለስቱ ምዕት ትዕዛዝ (ፍት ነገ አንቀፅ 6) እና ይህን እንደመነሻ በመጠቀም በልማድ የዳበሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች ጉዳይ ነው። የፍትሐ ነገሥቱን ክልከላ ዓላማ በሚገባ ያልተረዱ አንዳንድ ወገኖች የወር አበባን በዘሌ 12:1-8 ካለው መርገም/ርኩሰት ጋር ያያይዙታል። በዚህም የተነሳ በወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶችን በተለየና ከርኩሰት ጋር በማያያዝ የሚመለከቱ አሉ። በሌላም በኩል ይህ ሥርዓት “ሴቶችን አግላይ ነውና መሻሻል ይገባዋል” ብለው የሚከራከሩም አሉ። የወር አበባን ከእርግማን ጋር በማነፃፀር ሴቶችን ወደ ቤተክርስቲያን ከመሄድ፣ ጸሎት ከመፀለይ፣ መስቀል ከመሳለምና መሰል መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከለክሉ እንዳሉ ሁሉ የፍትሐ ነገሥቱን ክልከላ መሠረታዊ ምክንያት ባለመረዳት “ሴቶች በወር አበባ ወቅት ቤተክርስቲያን ቢገቡ ምንም ችግር የለውም” የሚሉም ይሰማሉ። በዚህች ጦማር ሴቶች በወር አበባና በድኅረ ወሊድ ወቅት ቤተክርስቲያን ስለመግባት ያለውን ሥርዓትና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳለን።

የወር አበባ ወቅት

የወር አበባ ሴቶች ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ተፈጥሯዊ የመውለድ ፀጋ የሚያሳይ ምልክት ነው። የወር አበባን በማየት የመጀመሪያዋ ሴት የሁላችን እናት ሔዋን ናት። የወር አበባ በሔዋን ዘመን ባለመታዘዝ (የመጀመሪያ በደል) ምክንያት የመጣ የእርግማን ምልክት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ይሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በአዳም፣ በሔዋንና በልጅ ልጆቻቸው (የሰው ዘር) በሙሉ ተወግዷል። የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን በቀዳማዊ አዳም አለመታዘዝ ምክንያት የመጣ ኃጢአትና ርግማን በዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም መታዘዝ ርቆልናል፣ ቀርቶልናል። ምክንያተ ሞት በሆነች በቀዳማዊት ሔዋን አለመታዘዝ የመጣ ርግማን ምክንያተ ሕይወት በሆነች በዳግሚት ሔዋን በድንግል ማርያም መታዘዝና ትህትና ቀርቶልናል። መቅድመ ተአምረ ማርያም “የሔዋን ጽኑ (የሚጎዳ) ማሰሪያዋ በአንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ” እንዲል። በዚህ መልኩ በዘመነ ሐዲስ የርግማን ማሳያነታቸው ቀርቶ የእግዚአብሔር ተቆጥሮ የማያልቅ የጸጋ ስጦታ መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በሴቶች ያለ ወርኃዊ ልማድ ነው። ምንም እንኳ የወር አበባ የመውለድ ጸጋ እንጂ የርግማን ምልክት ባይሆንም ከሚያስከትላቸው አካላዊና ስነልቦናዊ መገለጫዎች የተነሳ ሴቶች በወር አበባ ወቅት የክርስቶስ ሥጋና ደም ተፈትቶ ለምዕመናን ወደሚሰጥበት የቤተክርስቲያን ክፍል (ቅድስት ወይም ቅኔ ማኅሌት) እንዳይገቡ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ይደነግጋል።

ይህን ሴቶች በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ የሚከለክለውን የቤተክርስቲያን ሥርዓት ከሁለት የተሳሳቱ ሀሳቦች ጋር የሚያገናኙ ወገኖች አሉ። አንደኛው ስሁት ሀሳብ የወር አበባን እንደ መርገም ከመቁጠር የመነጨ ነው። ይህም የሰው ልጅን ፍፁም ድኅነት በሚገባ ካለመረዳትና የወር አበባን ምንነት ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመጣ ስህተት ነው። የወር አበባ ተፈጥሮአዊ አጀማመር ከሔዋን አለመታዘዝ ጋር መገናኘቱ በዘመነ ሐዲስ በክርስቶስ ቤዛነት የተዋጁ ሴቶች ካላቸው ተፈጥሯዊ ዑደት ጋር መምታታት የለበትም። ዛሬም በርግማን ሥር እንዳለን አድርጎ ማሰብና ማስተማር የክርስቶስን ቤዛነት ማቃለል፣ የሰውነትን ክብር ማዋረድ ነው። ከሰናዖር ሰዎች አመፅ የተነሳ በመደበላለቅ (ርግማን) ብዙ ቋንቋዎች ቢፈጠሩም በዘመነ ሐዲስ ግን እነዚያ ቋንቋዎች (ልሳናት) የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ማሳያ እንደሆኑት ሁሉ ከርግማን ጋር የተያያዘ መነሻ ታሪክ ያለው የሴቶች የወር አበባም በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ የመርገም ምልክት አይደለም። የምንናገረው ቋንቋ የርግማን ምልክት አለመሆኑን እንደምናምን፣ እንምንረዳ ሁሉ የወር አበባንም “የርግማን ምልክት” አድርጎ የሚያይ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም።

ከላይ እንደተገለጠው በወር አበባ ወቅት ተለይተው ወደታወቁ የሕንፃ ቤተክርስቲያን ክፍሎች መግባትና ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ መቀበል የሚከለከለው በርግማን ምክንያት ሳይሆን የወር አበባ ፈሳሽ በሚፈጥረው ወይም ይፈጥረዋል ተብሎ በሚገመተው አካላዊና ስነልቦናዊ ጫና ምክንያት ነው። እንደመነሻ የሚያገለግለውም  በዘሌዋውያን 15:19 “ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው”  የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ  ንባብ ነው። ነገር ግን ከርግማንና ከቁራኝነት ጋር የተያያዙ የዘመነ ብሉይ ንባባት ከዘመነ ሐዲስ የክርስቶስ ቤዛነት ጋር ተስማምተው መነበብና መተርጎም እንዳለባቸው የታወቀ ነው። በክርስቶስ ድኅነት የተፈጸመለት ሰው (ሴትም ወንድም) በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ርኩሰት ካልሆነ በቀር በተፈጥሮው መርገም የለበትም። የወር አበባ የሚባለው በማኅፀን ውስጥ ፅንስን ለመንከባከብ የተዘጋጀ መደላድል ፅንስ ሳይመጣ ሲቀር ለሌላ ዑደት ቦታውን የሚለቅበት ሂደት እንጂ ከመርገም ጋር የሚያያዝ አይደለም። ሁላችንም በማኅፀን ሳለን እንክብካቤ ያገኘነው በዚህ መልኩ መሆኑን ማስተዋልም ያስፈልጋል። በአጭር ቋንቋ ልማደ አንስት ከርኩሰት ወይም ከመርገም ጋር አይገናኝም። ሴቶችም በዚህ ወቅት “ርኩስ ነኝ” የሚል ስሜት ሊሰማቸው ከቶ አይገባም።

ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ሴቶች በደመ ፅጌ ወቅት ወደ ቤተክርስቲያን ቢገቡ ቤተክርስቲያኑን ያረክሱታል ከሚል የአይሁድ ሥርዓት የተወሰደ ነው። በመጀመሪያው እንዳየነው የወር አበባ መርገም/ርኩሰት ስላልሆነ ማንንም አያረክስም። በሌላ በኩልም በሰዎች ምክንያት የምትረክስ ቤተክርስቲያን የለችንም። ሰዎች ሥርዓቷን ቢጥሱ እንኳን ራሳቸው በኃጢአታቸው ይረክሳሉ እንጂ ቤተክርስቲያንን አያረክሷትም። ስለዚህ የዚህ ስህተት ሌላው መሠረቱ ቤተክርስቲያን የማትረክስ መሆኗን ካለማስተዋልም ጭምር የመጣ ነው። ሴቶችም በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን ብሄድ፣ መስቀል ብሳላም፣ የጸሎት መጻሕፍትን ብነካ ‘ላረክስ እችላለሁ’ የሚል ስጋት ሊገባቸው ከቶ አይገባም።

ታዲያ “ሴቶች በወር አበባ ወቅት ለምን ወደ ቤተክርስቲያን አይገቡም?” ቢሉ የዚህ ምክንያት ከቤተክርስቲያን ምስጢራት አንዱ ከሆነው ከቅዱስ ቁርባን ክብር ጋር የተያያዘ ነው። ሰው ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄደው ለማስቀደስና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለመቀበል ነው። ከቅዱስ ቁርባኑ የሚቀበል ሰው ደግሞ መንፈሳዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ከአካላዊ ዝግጅት መካከልም ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ (ህልመ ሌሊት፣ ደመ ፅጌ፣ የቁስል ፈሳሽ፣ የአፍንጫ ፈሳሽና የመሳሰሉት) ሊኖረው አይገባም የሚለው አንዱ ነው። ይህም የሚሆነው ለቅዱስ ቁርባን ከሚሰጠው ልዩ ክብር የተነሳ ነው። በዚህም መሠረት ሴቶች በወር አበባ ወቅት፣ ወንዶችም ህልመ ሌሊት ከመታቸው፣ ባለትዳሮችም ለሦስት ቀናት ራሳቸውን ከሩካቤ ካልከለከሉ ከቅዱስ ቁርባኑ አይቀበሉም (ዘሌ 7:19-21)። በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 6 “ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ወገን አንዱስ እንኳ አደፋፍሮ ከግዳጅዋ (ከደሟ) ያልነጻችውን ሴት ቤተክርስቲያን ያስገባ በደሟም ወራት ሥጋውንና ደሙን ያቀበላት ቢኖር ከሹመቱ ይሻር፡፡ ምንም ከነገሥታት ሴቶች ወገን ብትሆን፡፡” በማለት ሥርዓቱ ተቀምጧል። ከዚህ ውጭ ግን ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሳተፉ የሚከለክላቸው ነገር የለም።

ድኅረ ወሊድ ያለው ወቅት

እናቶች ድኅረ ወሊድ ወቅት ለተወሰኑ ሳምንታት ከማኅፀናቸው ደም/ፈሳሽ እንደሚፈሳቸው ይታወቃል። ይህም ድኅረ ወሊድ እስከ አራት ሳምንት ድረስ ሊቆይ ይችላል። በተጨማሪም እናቶች በዚህ ወቅት በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ከደረሰባቸው አካላዊ ድካም እንዲያርፉ፣ ጨቅላ ሕፃኑ(ኗ)ንም ጡት እንዲያጠቡና እንዲከባከቡ ሲባል ከመደበኛ ሥራም ጭምር ያርፋሉ። በመንፈሳዊውም አገልግሎት እንዲሁ ጾምና ስግደት አይጠበቅባቸውም። ጸሎትም ቢሆን የቻሉትን ያህል ብቻ እንዲጸልዩ ይመከራሉ። ከዚህ ባሻገር ስለየወር አበባ በተገለፀው ምክንያትም አካላዊ ዝግጅት ስለሚያስፈልጋቸው በዚህ ወቅት ቅዱስ ቁርባንን አይቀበሉም። ሕፃኑ(ኗ) 40/80 ቀን ሲሆነው/ናት ወደ ቤተክርስቲያን ወስደው ያስጠምቃሉ፣ ያስባርካሉ።

ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ጸሎት የሚደረግላቸውና ጠበል የሚረጩትም ሕፃን እና እናትን ለመባረክ ነው እንጂ መርገም ስላለባቸው ለማንፃት አይደለም። በዚህም ቀን እግዚአብሔር ልጅን ስለሰጣቸው የሚያመሰግኑበትና የተሰጣቸውም ልጅ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለድበት የደስታ ቀን ነው። የባለትዳሮች የፍቅርና የአንድነታቸው ፍሬ እንዲሁም የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን ልጅ በመውለድ በሴቶች ላይ የሚመጣ መርገም/ርኩሰት አለ ብሎ ማሰብ ምንኛ አለመታደል ነው?!። በተጨማሪም በብዙ ድካም የወለደችን እናት ከድካሟ እንኳን ሳታገግም ደስታዋን በመካፈልና በማበርታት ፈንታ የረከሰች አድርጎ መቁጠር፣ አለመቅረብ፣ ዕቃ እንኳን ብትነካ ይረክሳል ብሎ ማሰብ ኃጢአትም በደልም ነው። የሕይወትን ምንጭ (እናትን) በዚህ መልኩ ማቃለል ከቃለ ሕይወት (ከፍርድ ቀን ሽልማት) የሚከለክል በደል ነው ማለት ይቀላል።

ደም ይፈሳት የነበረች ሴት

አንዳንዶች “አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት ክርስቶስን ነክታ ከዳነች (ማቴ  9:20-22) ለምንድን ነው ሴቶች በወር አበባ  ወቅት የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የማይቀበሉት?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህንን ለመረዳት ሁለት ነጥቦችን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንደኛው ይህች ሴት ያለማቋረጥ ደም ይፈሳት የነበረው በተፈጥሮ ልማድ ሳይሆን በበሽታ ምክንያት ነበር። ወደ ክርስቶስም የመጣችው ከዚህ በሽታዋ ለመፈወስ ነበር። ሁለተኛው በፍጹም እምነት የነካችውም የልብሱን ጫፍ ብቻ ነበር። እነዚህ ሁለት ነጥቦች የዚህችን ሴት መዳን ከሴቶች የወር አበባ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ጋር በፍፁም የማይነፃፀር ያደርጉታል።

በሌላ በኩል ጥንት በነበረው ሥርዓት (ንፅሕና መጠበቂያ ግብዓቶች ባልነበሩበት ዘመን) ሴቶች በወር አበባ ወቅት ቤተክርስቲያን አይግቡ መባሉ እና አሁን ሁሉ ነገር በሰለጠነበትና ዘመናዊ የንፅሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ባሉበት ዘመንም እንዴት ተመሳሳይ ሥርዓት ሊኖር ይችላል? ብለው የሚጠይቁ ወገኖችም አሉ። እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገው ሥርዓቱ የተሠራው የቅዱስ ቁርባንን ክብር፣ የቤተክርስቲያንን ክብር፣ እንዲሁም “ከሰውነት የሚፈስ ፈሳሽን” ምክንያት በማድረግ እንጂ የንፅሕና መጠበቂያ ግብዓት አለመኖርን መነሻ በማድረግ አይደለም። ሴቶችም በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተክርስቲያን የማይገቡት ቤተክርስቲያንን እና ቅዱስ ቁርባንን ከማክበር አንጻር መሆኑን በሕሊናቸው ሊያኖሩት ይገባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤተክርስቲያን ውስጥም ሆነ በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ የሚደረግ ጸሎትና የሚቀርብ ምስጋና ወደ እግዚአብሔር ከመድረስ አንጻር ልዩነት የለውም። ይልቁንም በትህትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግና ህሊናን ሰብስቦ መጸለይና ማመስገን ላይ ነው ዋናው ቁም ነገሩ ያለው።

ይህ ሥርዓት ሴቶችን አግላይ ነውን?

ሴቶች በአማካይ ከ12-15 ዓመታቸው ጀምሮ እስከ 45-49 ዓመታቸው ድረስ በአጠቃላይ ለ34 ዓመታት ያህል በአማካይ በየ28 ቀኑ የወር አበባ ያያሉ። በዕድሜያቸውም በአማካይ ለ444 ጊዜ (ነፍሰ ጡር ካልሆኑ) ያያሉ። እያንዳንዱም ዑደት ከ3-7 ቀናት ሊቆይ ይችላል። የወር አበባቸው ከመጣ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ቤተክርስቲያን አይገቡም። በዚህ ቀመር እያንዳንዷ ሴት ከ4 ሳምንት አንድ ሳምንት በተፈጥሮ ምክንያት ቤተክርስቲያን አትገባም ማለት ነው። በአጠቃላይም ከዕድሜዋ ለ3,105 ቀናት (8 ዓመት ከ6 ወር) በወር አበባዋ ምክንያት ቤተክርስቲያን እንዳትገባ ትሆናለች ማለት ነው። ከዚያም ባሻገር ከወሊድ በኋላ ባለው ወቅት ከላይ በተገለፀው መልኩ በቤተክርስቲያን የውስጥ አገልግሎቶች የተገደበ ሱታፌ ይኖራቸዋል።

ታዲያ “ይህ ሥርዓት ሴቶችን አግላይ አይደለምን?” የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ሥርዓቱ የተሠራው ሴቶችን በተፈጥሮ በሚያዩት የወር አበባ ወይም የድኅረ ወሊድ ፈሳሽ ምክንያት ለማግለል ሳይሆን ለቅዱስ ቁርባን የሚሰጠውን ክብር ለመግለፅ የተሠራ ሥርዓት ነው። ሴቶችም በወር አበባቸው ምክንያት ምንም አይነት መገለል ሊደርስባቸው እንደማይገባ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ያስረዳል። ይሁን እንጂ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የሆኑ ካህናትን ጨምሮ ቀላል የማይባል ቁጥር ባላቸው ምዕመናን ዘንድ ከላይ የተጠቀሱት የወር አበባንና ድኅረ ወሊድ ፈሳሽን ከርግማን ጋር የማምታታት ክፉ ልማድ አለ። ይህ ልማድ በሥርዓት ከተደነገገው የአገልግሎት ገደብ ጋር በመደበላለቁ ሴቶችን የሚያገል አስተሳሰብ ሥር እንዲሰድ ምክንያት ሆኗል። ስለሆነም ቤተክርስቲያን የወር አበባና የድኅረ ወሊድ ወቅትን በተመለከተ በሚገባው ልክ ልታስተምር ይገባል።

ሴቶችን በተፈጥሮ በሚያዩት የወር አበባ ምክንያት የሚያገላቸው ካለ ክርስትናንም ይሁን የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ያልተረዳ ነው። ይልቁንም ሁላችንም “ትምክህተ ዘመድነ/የባሕርያችን መመኪያ” የምንላት፣ አምላክን በድንግልና ከልማደ አንስት ልዩ በሆነ ሁኔታ በመውለዷ በሔዋን ምክንያት የመጣ የሴቶችን መናቅ ያስቀረች የድንግል ማርያምን  የነገረ ድኅነት ሱታፌ ባለማወቅ የሚያቃልል ነው። ሴቶችን ከተፈጥሮ ጸጋ የተነሳ ማቃለልና እንደርኩስ ማየት እግዚአብሔር ከክብር ሁሉ የበለጠውን ክብር ለሰው ልጆች በድንግል ማርያም በኩል የገለጠበትን መቅደስ ማቃለል ነውና። ይህንንም በተአምረ ማርያም ከተመዘገበው ዮሐንስ የተባለ ካህንና አንዲት በወር አበባ ምክንያት እንደርኩስ ተቆጥራ የአምላክን ሰው መሆን በሚያናንቁ ንስጥሮሳውያን እርቃኗን በተተፋባት ሴት ታሪክ መረዳት እንችላለን። ዮሐንስ የተባለ ካህን በሚተፉባት ሰዎች ፊት የተዋረደ እርቃኗን ስሞ “እኔስ እግዚአብሔር ከሴት እንደተወለደ አምናለሁ” በማለት እምነቱን መሰከረ። የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር የማይረዱ መናፍቃን ግን የዚህን ፃድቅ ታሪክ በማይረባ መልኩ እየተረጎሙ ስተው ያስቱበታል። በእውነት ደም እየፈሰሰው፣ ምራቅ እየተተፋበት ያለን የሴት አካል ከሥጋዊ ፍትወት ጋር አነፃፅረው የሚያምታቱ መናፍቃን ምን ያህል የጎሰቆለ አዕምሮ እንዳላቸው እንረዳለን። እነርሱ የቅዱሳት መጻሕፍት ጠላቶች መሆናቸው የተገለጠ ነውና። ካህኑ ዮሐንስ ግን ሰው የሚፀየፈውን ደም ይፈሳት የነበረችውን የዚህችን ሴት እርቃን  መሳሙ በወር አበባ ላይ ሴቶችን ከባሕርያቸው የተነሳ ርግማን ያለባቸው አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ መሆኑን ያስረዳናል። ስለሆነም በወር አበባም ሆነ ድኅረ ወሊድ በሚመጣ የተፈጥሮ ፈሳሽ የተነሳ ሴቶችን ማቃለልም ሆነ ማግለል የእግዚአብሔርን ስጦታ ማቃለል መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል። ሴቶችም በወር አበባ ወቅት ከቅዱስ ቁርባኑ ስለተከለከሉ የመገለል ስሜት ሊሰማቸው አይገባም። ይልቁንም ይህን ጊዜ የሚጸልዩበት፣ በቂ ዕረፍት የሚያደርጉበትና ራሳቸውን የሚንከባከቡበት ሊያደርጉት ይገባል።

ቤተክርስቲያን የገነት ምሳሌ ናት። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱን ሔዋን ከአዳም ጋር በገነት ለሰባት ዓመታት ስትኖር የወር አበባ አታይም ነበር። ስለዚህም ቤተክርስቲያን የገነት አማናዊ ምሳሌ መሆኗን ለማሳየት ሴቶች በወር አበባ ወቅት፣ ወንዶችም ህልመ ሌሊት ከመታቸው ወደ ቤተክርስቲያን አይገቡም። ነገር ግን አገልግሎቱን የሚከታተሉበት ሥፍራ በሚገባ ሊዘጋላቸው ይገባል። ለምሳሌ እንደየቦታው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሚወሰን ቢሆንም ቅዳሴውን ከውጭ ሆነው ቀጥታ እያዳመጡና እያዩ የሚከታተሉበት ስክሪን፣ የተሟላ ወንበር፣ የጸሎት መጻሕፍትና በአጠቃላይ ውስጥ ያለው አገልግሎት (ከቅዱስ ቁርባኑ በቀር) ባሉበት እንዲደርሳቸው ጥረት ሊደረግ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ እህቶችና እናቶች የሚያስቀድሱበት ቦታ መለየቱን መነሻ በማድረግ እዚያ ሆነው የሚያስቀድሱት ላይ ሌላ መገለል እንዳይደርስ ምዕመናንን ስለየወር አበባ ምንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ማስተማር ይገባል። ይህንን ሳያደርጉ “መግባት የለባቸውም” ማለት ብቻውን ሴቶች ከቤተክርስቲያን ከአገልግሎት እንዲርቁ ሊያደርጋቸው ይችላል። እኛም የቤተክርስቲያን አባቶች እና መምህራን ለዚህ ጉዳይ በቂ ትኩረት ሰጥተው እንዲያስተምሩ በልጅነት መብታችን እንጠይቃለን።

3 thoughts on “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፬): በወር አበባ ጊዜና ከወሊድ በኋላ

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡ፀጋውን ያብዛልን፡፡እኔ ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ፡
    1:-መቅደስ ውስጥ አይግቡ እንጂ ከመቅደስ ምን ያህል መራቅ አለባቸው? ወንድም ህልመ ሌሊት ካየ እንደዛው?
    2:-አንዳንድ ሴቶች ላይ ደመ ፅጌ ካዩ በአራተኛ ቀን ሙሉበሙሉ ሊቆም ይችላል፡፡እና አምስተኛውን ቀን ታጥበው በስድስተኛው ቀን መግባት አይችሉም ወይ?
    3:-በደመ ጽጌ ወቅትና ህልመ ሌሊት በገጠመ ጊዜ መቅደስ ባይገባም የቅዳሴ ጠበል መቅመስ ይከለክላል?እዚሁ ላይ በአጭሩ ቢመለስልኝ ደስ ይለኛል፡፡የብዙም ሰው ጥያቄ ስለሆነ ነው፡፡

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s