መግቢያ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሴቶች ያላቸው የቅድስና ሱታፌ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ከሚሉት ጦማሮቻችን በመጀመሪያው በስፋት ተዳስሷል። ይሁንና በዘመናችን ባለ ኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከመዘመር፣ ከማስቀደስ፣ ከፅዳት፣ ከመሰናዶና ከማስተናገድ ያለፈ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈፅሙ አይታይም። አልፎ አልፎም የሰበካ ጉባዔ አባል ይሆናሉ። ይህ እውነታ ሲታይ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ቤተክርስቲያን የሚያዘወትሩና ከምስጢራትም የሚሳተፉ ከመሆናቸው አንፃር ያላቸውን የአገልግሎት ሱታፌ አነስተኛ ያደርገዋል። በተለይም በማስተማር ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ ጎልቶ የሚታይ አይደለም። ለዚህም ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው “ሴቶች ማስተማር የለባቸውም” የሚለው አስተሳሰብ ነው። ይህም መነሻ የሚያደርገው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም” (1ኛ ጢሞ 2፡11-12) በማለት የተናገረው ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ ወንጌልን ማስተማርና ሌሎች ሴቶች ሊያበረክቷቸው የሚችሉትን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ እንዳስሳለን።
ማስተማር ምን ምን ያካትታል?
አስቀድመን የጠቀስነውን “ሴት ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ እንድትሰለጥን አልፈቅድም” የሚለውን ቃል ከማየታችን በፊት “ማስተማር” ማለት ምን ምን እንደሚያጠቃልል እንይ። በዘመናችን ማስተማርን በተመለከተ እጅግ የተዛባ፣ ንግድ የወለደው አስተሳሰብ አለ። ለብዙዎች ማስተማር ማለት ቀሚስ ለብሶ እና/ወይም መስቀል አንጠልጥሎ/ይዞ አውደ ምህረት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ማብራራት፣ ቀልድና ተረት መናገር ወይም ታሪክ መተረክ ብቻ ይመስላቸዋል። ይሁንና ዋናው ማስተማር ክርስትናን በሕይወት እየኖሩ ለሌሎች ምሳሌና አርአያ መሆን ነው። ይህ ደግሞ ወንድ ወይም ሴት ሳይል ከሁሉም ክርስቲያን የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው። ሐዋርያውም “ሴት ልታስተምር … አልፈቅድም” ያለው ይህንን እንዳልሆነ ግልፅ ነው።
ስለዚህ ሴቶች በሕይወታቸው መልካም አርአያ በመሆን ብዙዎችን ማስተማር እንደሚችሉና በዚህም ረገድ ብዙ እንደሚጠበቅባቸው ማስተዋል ይገባል። ከዚያም ባሻገር “ማስተማር” በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሚፈስ ጎርፍ (unidirectional) አስተማሪው ጮሆ እየተናገረ፣ ተማሪዎች በፀጥታ እያዳመጡ የሚታዩበት ሥርዓት ብቻ አይደለም። ይህን መሰሉ የማስተማር ስልት በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎችን ለማስተማር የሚጠቅም ቢሆንም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና ትውፊት ዋነኛው የማስተማሪያ መንገድ አልነበረም። ይህን የማይረዱ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን ወንጌልን የማስፋፋት ተግባር በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩ የሰንበት ት/ቤትና መንፈሳዊ ኮሌጅ አሠራሮች ጋር አዳብለው በማየት የተሳሳተ ምስል ይፈጥራሉ። አብነት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በበርካታ ማኅበራዊና መንፈሳዊ አውዶች ትምህርተ ወንጌል የሚሰጠው በእርጋታ በሚደረግ አሳታፊ ምልልስ እንጅ አንዱን ተናጋሪ ብቻ፣ ሌሎችን አድማጭ ብቻ በሚያደርግ አሰራር አይደለም።
ክርስትናን መማርም ይሁን ማስተማር ብዙውን ጊዜ ኢ-መደበኛ (informal teaching) ነው። ብዙ ለውጥ የሚያመጣውም የዚህ አይነቱ የማስተማሪያ ዘዴ ነው። ይህም በቤተሰብ፣ በጓደኝነት፣ በሥራ ባልደረባነት፣ በማኅበራዊ ትሥሥር (social networks) በንግግር፣ በፅሑፍ በድራማና በመሳሰሉት ሰዎችን በግልና በቡድን የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ማስተማር ነው። ሐዋርያው “አልፈቅድም” ያለው ይህንን ይጨምራል ብሎ መከራከር የክርስትናን አስተምህሮ መፃረር ይሆናል። ታላላቅ ነቢያት፣ መሪዎች፣ ጠቢባን፣ ሊቃውንት እንዲሁም ቅዱሳን ክርስትናን እና ጥበብን ከእናቶቻቸው እንደተማሩ በክፍል ፩ በሰፊው አይተናል። ይህም የእናቶችን የማስተማር ድርሻ ግልፅ ያደርግልናል።
ወንጌል ማስተማር በመደበኛ ትምህርት ቤት (በአብነት ትምህርት ቤት፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች፣ በተከታታይ ስልጠና) የተደራጀ ትምህርት መስጠትንም ያካትታል። በእነዚህም ትምህርት ቤቶች ያለው የሴቶች ሚና ጥቂትም ቢሆኑ በአብነት ትምህርት ቤትና በመንፈሳዊ ኮሌጆች በማስተማርና ምርምር በመሥራት ፍሬ ያፈሩ ሴቶች እንዳሉ ግልፅ ነው። በተለይም በአብነት ትምህርት ቤት ቅኔ በማስተማር የተመሠከረላቸውን ቅዱሳት አንስት በክፍል ፩ በሰፊው አሳይተናል። ይህም የሚያሳየን ሴቶች መንፈሳዊውን ትምህርት በሚገባ ተምረው በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች ከማስተማር የሚከለክላቸው ነገር እንደሌለ ነው። ነገር ግን ከልጅነታቸው ጀምሮ ይህንን አውቀው እንዲያድጉና በማኅበረሰቡም ዘንድ ሴቶች በመደበኛው ትምህርት ማስተማር እንደሚገባቸው ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
የምንፈጥረው ግንዛቤ ግን በዓለም እንዳለው ቅኝት ከፆታ መበላለጥና እኩልነት አንፃር የሚቃኝ ሳይሆን የመንግስቱን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ በሚል ትሁት እይታ ብቻ ሊሆን ይገባዋል። ማስተማር ማለት እንደ ጧፍ ለሌሎች እያበሩ መንደድ እንጅ በሌሎች ላይ የመሰልጠን (ራስን የመጫን) አጋንንታዊ ልማድ አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 12 ሐዋርያትንና 72 አርድእትን ለወንጌል መልእክተኝነት እንደጠራው ሁሉ 36 ቅዱሳን አንስትንም እንደሚገባቸው መጠን የክርስቶስን ወንጌል በሰማዕትነት ጭምር እንዲመሰክሩ የጠራቸው መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህም ለሁሉም ሴቶች እንደ ሰማዕትነት አቅማቸው የተሰጠ እንጂ የቄስ ወይም የመርጌታ ልጆች ለሆኑ ሴቶች ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ የዝምድና ማወራረጃ አይደለም። በእነ እሙሃይ ገላነሽ ቅኔ የሚኮራ ሰው የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርትና የቤተክርስቲያንን ትውፊት በአግባቡ ተረድቶ የተመዘነ እይታ ሊኖረው ይገባል እንጂ ክህነትን በማይጠይቁ አገልግሎቶች ሁሉ “ለሴት አይፈቀድም!” በማለት ባህላዊና ማኅበራዊ ጫናዎችን ፍፁም መንፈሳዊ አስመስሎ ማቅረብ የተሳሳተ ነው፣ ለቤተክርስቲያንም አይጠቅማትም።
አራተኛውና በተለምዶ “ማስተማር” ተብሎ የሚታወቀው “የአውደምህረት ስብከት” ነው። ይህም በተለይ ከቅዳሴ መካከል/በኋላ የሚሰጠው ስብከት ነው። ይህም በካህናት የሚከናወን ስለሆነ ሐዋርያው በወቅቱ “ሴት ልታስተምር አልፈቅድም” ብሎ በኤፌሶን ለነበረው ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቴዎስ የፃፈው ይህንን እንደነበር ብዙዎች ይስማሙበታል። ነገር ግን በአውደምህረትም ቢሆን ከተለመደው ስብከት ውጭ በስነ-ጽሑፍ፣ በመዝሙር፣ በድራማና በመሳሰሉት ሴቶች ብዙ እያስተማሩ እንዳሉ ይታወቃል። በተጨማሪም ሴቶች ብቻ በሚገኙበት ጉባዔ (ለምሳሌ በሴቶች ገዳም፣ በሴቶች ፅዋ፣ በሴት ተማሪዎች መኖሪያ ወዘተ) ሴቶች በአውድምሕረትም ጭምር ሲያስተምሩ ኖረዋል፣ ሊያስተምሩም ይገባል። ይህ አገልግሎታቸውም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ሴቶች በስብከተ ወንጌል
“ሴት ልታስተምር አልፈቅድም” ያለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሌላው መልእክቱ “እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ” (ቲቶ 2፡3) በማለት ሴቶች (በተለይም አረጋውያን ሴቶች) ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል። ጌታችንን በሰማርያ ያገኘችው ሳምራዊቷ ሴትም ስለጌታችን ለሰማርያ ሰዎች ሰብካለች (ዮሐ 4:1:)። መግደላዊት ማርያምም ከሁሉ በፊት ትንሣኤውን አይታ ለደቀመዛሙርቱ አብስራለች። የመድህን መምጣት ለሰማርያ ሰዎች ማብሰርና የክርስቶስን ትንሣኤ ለደቀመዛሙርቱ ማብሰር ስብከት ካልተባለ ሌላ ምን ሊባል ነው? በሐዋርያት ዘመን የነበሩ እነ ፌቨንም ወንጌልን በማስተማር ይራዱ እንደነበር በሐዋርያት ሥራ ተፅፏል (ሮሜ 16:1)። ነቢይት ሐናም እንደ ስምዖን አረጋዊ እውነተኛ የክርስቶስ ምስክር ሆና አምላክነቱን መመስከሯን ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል (ሉቃ 2:36~40)። እነዚህን ለምሳሌ አነሳን እንጂ በቤተክርስቲያን ታሪክ ወንጌልን በማስተማር ብዙ ድርሻ ያበረከቱ ቆጥረን የማንጨርሳቸው ብዙ ቅዱሳት አንስት አሉ።
“ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ”
አንዳንድ ወገኖች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ “ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና። ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ (1ኛ ቆሮ 14:34-35)” በማለት የተናገረውን በመጥቀስ ሴቶች ማስተማር የለባቸውም ብለው ይከራከራሉ። መልእክቱን ለሚያስተውል ግን ይህ ትዕዛዝ በማኅበር ሊኖር ስለሚገባው ሥርዓት እንጂ ስለማስተማር አይደለም። ሁሉም በሥርዓት እንዲሆን፣ ሁከት እንዳይነግሥና መደማመጥ እንዲኖር ያስተማረው ነው። ይህንንም ሲል በጉባዔ የታደሙ እርስ በእርሳቸው አይነጋገሩ፣ ትምህርቱን ጸጥ ብለው ያዳምጡ የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ስለሆነ አስቀድሞ በቁጥር 33 ላይ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ብሏል። ስለዚህ የዚህ መልእክት ጭብጥ ማስተማርን የሚመለከት አይደለም።
ሴት እንድታስተምር አይፈቀድምን?
ከሴቶች የማስተማር ሚና አንጻር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል መመርመር ያስፈልጋል። ለጢሞቴዎስ “ሴት ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሠለጥን አልፈቅድም” ያለው በወቅቱ በኤፌሶን የነበረውን ልዩ ሁኔታ የሚመለከት ቢሆንም በዋናነት ከክህነት ጋር ተያይዞ መታየት ይኖርበታል። ሐዋርያው “ልታስተምር አልፈቅድም” እንጂ “ልታስተምር አይገባም” አለማለቱ መልእክቱ ያተኮረው በወቅቱ በኤፌሶን የነበረው ልዩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ያሳያል። “ልትሠለጥን” የሚለውም በዚሁ አግባብ ሊታይ ይገባዋል። ምክንያቱም ‘መሠልጠን’ መበላለጥን የሚያሳይ ስለሆነ ይህ መልእክት በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል።
የተወደደች የቅኔ መምህር የእማሆይ ገላነሽ ሐዲስ የልጅነት ታሪክና ክስተት የቅዱስ ጳውሎስን ክልከላ ሀሳብ መነሻ ለማሳየት ሊጠቅመን ይችላል። እማሆይ ገላነሽ በልጅነታቸው ወራት የቅኔ መምህር ከሆኑት ከአባታቸው ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ቅኔን በሚገባ ተምረዋል። ከዕለታት በአንዱ በከበረ የደብረታቦር በዓል ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ በዓሉን የተመለከተ ቅኔ ማቅረብ ጀመሩ። “በታቦርሂ አመቀነፀ መለኮትከ ፈረስ•••” (መለኮትን በጉልበተኛ ፈረስ መስለው በታቦር ተራራ መለኮት በዘለለ ጊዜ•••) ብለው የጀመሩትን ሳይጨርሱ በቅኔ ቤት እንዳለው ልማድ በምቅዋመ አንስት (በሴቶች መቆሚያ) የነበረችው የያኔዋ ሕፃን እማሆይ ገላነሽ ሳትጠበቅ ተነስታ “ኢክሀሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” (ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት፣ ሊቋቋሙት አልቻሉም) በማለት ቅኔውን በእውቀት ነጠቀቻቸው። ይህን በእውቀት የተሞላ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የፈለቀ ቅኔ ነጠቃ ሌላ የቅኔ መምህር ወይም ተማሪ ቢፈፅመው ኖሮ “ይበል ነው” ተብሎ ይደነቅለታል፣ ካልሆነም ቅኔውን የተነጠቀው ሊቅ የጀመረውን ቅኔ በተለየ መልኩ መጽሐፋዊ ምስጢሩን ጠብቆ ይፈፅመዋል እንጂ ነጣቂው ላይ አላግባብ ማሸማቀቅ አይፈፀምበትም። በልጃቸው ቅኔውን የተነጠቁት አባት ግን እንደ ልማዱ በጀመሩት ቅኔ ከመመለስ ይልቅ “ወእንዘ ትትናገሪ ዘንተ በአድንኖ ክሳድ ወርእስ በከመ አነ ስማዕኩኪ ኢይስማዕኪ ጳውሎስ።” (እዩኝ በማለት (በትዕቢት) እንዲህ ስትናገሪ እኔ እንደሰማሁሽ ጳውሎስ እንዳይሰማሽ) በማለት ተናገሯት። የቄሰ ገበዙ መልስ ሥጋዊ እልህ የወለደው ማሸማቀቂያ ይሁን የገላነሽ አነጋገር ትዕቢታዊ ሆኖ የተገባ ተግሳፅ የሚያስረዳ አውድ (context) እንደነበረ ማወቅ ያስፈልጋል። የቅዱስ ጳውሎስ ክልከላ የሚመለከተው እዩኝ፣ እዩኝ በማለት ማስተማርን ራስን በሌሎች ላይ ከመሾም (ከመሰልጠን) አንፃር የሚያዩትን እንጂ በትህትና የሚናገሩትን አይመለከትም። ከዘመናት በኋላ እማሆይ ገላነሽ ትልቅ ሰው ሆነው የአባታቸውን ወንበር በመምህርነት መተካታቸው ምን ያስተምረን ይሆን?
ብዙ ሊቃውንት ይህንን “ሴት ልታስተምር አልፈቅድም” የሚለውን የሐዋርያውን መልእክት ሲያብራሩ በሦስት ነገሮች ላይ ያተኩራሉ። የመጀመሪያው ትህትናን የሚመለከት ነው። ይህም ሴት “እኔ ከሌላው እልቃለሁና ላስተምር” አትበል ማለቱ ነው። ይህም በወቅቱ እንዲህ የሚያደርጉ ሴቶች ስለነበሩ ትህትናን እና እኩልነትን ለማስተማር ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በቤተክርስቲያን (በማኅበር) ያለውን እኩልነትን የሚያረጋግጠው የፆታ ቅደም ተከተል (ካህናት፣ ወንዶች፣ ሴቶች) በማስተማርም ጭምር የሚገለጥ መሆኑን ለማሳየት ነው። ወንድ ከካህን ቀድሞ ላስተምር አይበል፣ ሴትም ከወንድ በፊት ላስተምር አትበል ሲል ነው። ሦስተኛው ደግሞ መልእክቱ የተጻፈው በኤፌሶን ለነበረው ለጢሞቴዎስ እንደመሆኑ በማኅበር ማስተማር ያለባቸው ካህናት መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው። ምክንያቱም ካህናት የክርስቶስ እንደራሴ ናቸውና። ይህም የአገልግሎት ጸጋን፣ ኃላፊነትና ድርሻን የሚያንጸባርቅ ነው።
በዘመናዊው ትምህርት ሴቶች ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ በማስተማር ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ። በመንፈሳዊው ዘርፍም እንዲሁ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል። የሴቶችን ዕውቀትና ልዩ የማስተማር ጸጋ ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት አለመጠቀም ዕድልን ማባከን እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በተለይም በቂ መምህራን በሌሉበት አካባቢ ይህን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል። ይሁንና በእውቀትና በመንፈሳዊነት ሳይሆን በባህላዊ ፍርደ ገምድል አድልዎ ሴቶች ሕፃናትን እንኳ እንዳያስተምሩ የሚከለክል ስሁት ምልከታ በብዛት ይስተዋላል። በዚህም የተነሳ የሚያስተምሩትን የሚያውቁ እናቶችና እህቶች እየተገፉ የሚናገሩትን የማያውቁ ሰዎች “ወንዶች ስለሆኑ ብቻ” የማስተማር ድርሻ የሚሰጥባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው። ይህ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከቤተክርስቲያን ትውፊት የተፋታ አስተሳሰብና አሠራር በአግባቡ ተመርምሮ ሊስተካከል ይገባል። በሌሎች ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ልጆችን እና ወጣቶችን የሚያስተምሩት እናቶችና እህቶች መሆናቸው ከእነርሱም ብዙ መማር እንዳለብን ያመላክታል።
ወንጌልን መስበክና ክርስትናን ማስተማር የሁሉም ኃላፊነት ነው። የትምህርትና የስብከት መንገዱ ቢለያይም ወንድም ሴትም፣ ካህንም ምዕመንም፣ አረጋዊም ወጣትም፣ መነኩሴም ሕጋዊም ሁሉም የየራሱ ድርሻና ጸጋ አለው። ከቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና ከቤተክርስቲያን ትውፊት እንደምንረዳው ሴቶች ትምህርተ ወንጌልንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለሌሎች በማስተማርና በመመስከር የራሳቸው ድርሻ አላቸው። ስለሆነም ይህንን ሚና በሚገባ ተረድተን፣ ከሴቶች የማስተማር ሚና ወሰን ጋር ተያይዘው የሚነሱ መንፈሳዊ አመክንዮዎችን በአግባቡ ተረድተን፣ መንፈሳዊ መሰረት ከሌለው ጥቅል ፍረጃ ርቀን፣ በመንፈሳዊ ጉባኤዎቻችን ሴቶች ከምግብ አብሳይነት የዘለለ የማስተማር ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባናል። ይህም የሁሉም የቤተክርስቲያን አካላት ድርሻ መሆን አለበት እንጂ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በስብከተ ወንጌል የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ሚና ባለማወቅ ማሳነስና ማንኳሰስ አይገባም። ከወሰናቸው ሳይተላለፉ በትዕቢት ሳይሆን በትህትና የእግዚአብሔርን ቃል በንግግርም በሕይወትም ያስተማሩን የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በጥበብና ማስተዋል ተመርተን አገልግሎታችንን ለመፈፀም ይርዳን። አሜን።