መግቢያ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የክርስቲያኖችን አንድነት በሦስት “ፆታ ምዕመናን” ይከፍላቸዋል። እነርሱም ወንዶች፣ ሴቶችና ካህናት ናቸው። እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተናገረን በመንፈሳዊ ህይወት የሁሉም ፆታ ምዕመናን ዓላማ መስዋዕትነትና ከራስ በላይ ለሌሎች መኖር ነው። ወንዶች የቤተሰብ ራስ (ተጠሪ) መባላቸው እንደ ክርስቶስ ራሳቸውን ስለቤተሰባቸው ቤዛ እስከማድረግ የሚገለጥ ነው። ሴቶች የሕይወት ምንጭ (እናት) በመሆናቸው በብዙ መከራ እየተፈተኑ የቤተክርስቲያንን ሕይወት ያስቀጥላሉ። ካህናትም ክህነታቸው “እናንተም እንዲሁ አድርጉ” ብሎ አብነት እንደሆናቸው ጌታ ዝቅ ብለው ምዕመናንን እንዲያገለግሉ ነው።
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉም ምዕመን እንደየድርሻው ይሳተፋል። ይሁንና በታሪክ ሂደት ከሦስቱ ፆታ ምዕመናን መካከል ሴቶች በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ መንፈሳዊ ሱታፌአቸውን በሚያቀጭጩ ችግሮች ተይዘዋል። ስለሆነም “ሴቶች በቤተክርስቲያን” በሚል መሪ ርዕስ ሥር በተከታታይ በምናወጣቸው የአስተምህሮ ጦማሮች በመንፈሳዊ ከቅዱሳት መጻሕፍት ሳይሆን ከሌሎች ልማዶች የፈለቁ ሴቶች በቤተክርስቲያን ያላቸውንና ሊኖራቸው የሚገባውን ሱታፌ የሚያደበዝዙ ልማዶችና ዘልማዳዊ ትንተናወችን በቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን ትውፊት ሚዛንነት እንዳስሳለን። ለዚህም እንዲረዳን በቅድሚያ የሴትቶች (የእናትነት) አገልግሎት በቅድስት ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ክብር በአጭሩ እናቀርባለን።
የሴትነት (የእናትነት) አገልግሎት ክብር
የሴቶች መንፈሳዊ አገልግሎት በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ታላቅ ቦታ ይሰጠዋል። ይህም ከሚገለጥባቸው ነገሮች አንዱ የፈጠረንን አምላክ “ቅድስት ሥላሴ” ብለን በእናት አንቀፅ መጥራታችን ነው። ይህም ከእናት በሥጋ እንደተወለድን ከሥላሴም በጥምቀት መወለዳችንን ለማጠየቅና ሥላሴም እናትም አባትም እንደሆኑን ለመመስከር ነው። በተጨማሪም የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም “እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” ብለን የምናከብራትና የምልጃዋን በረከት የምንማፀነው ለእናትነቷ ካለን ታላቅ አክብሮት የተነሳ ነው። እርስዋ “ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል (መዝ 86:5)” ተብሎ በትንቢት የተነገረላት፣ “እነኋት እናትህ (ዮሐ 19:38)” ብሎ በአካል የሰጠን እናታችን ናት። የእርስዋን እናትነት መሠረት በማድረግ ቤተክርስቲያን የእናትነትን አገልግሎት አመስጥራ ታስተምርበታለች።
እንዲሁም ዕለት ዕለት ቅዱስ ቃሉን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምትመግበንን አማናዊት ቤተክርስቲያን “እናት ቤተክርስቲያን” እንላታለን። ሥጋዊት እናት ከምድራዊ አባት ዘርን ተቀብላ ልጆችን በምጥ፣ በህማም እንደምትወልድ ሁሉ መንፈሳዊት እናት ቅድስት ቤተክርስቲያንም መንፈሳዊ ዘርን (ቅዱስ ቃሉን፣ ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን) ከሰማያዊ አባት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብላ ምዕመናንን በመከራ በሚገለጥ ሰማዕትነት አልፋ ምዕመናንን ወልዳ ታሳድጋለች። ይህም የቤተክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት ለሴቶች የእናትነት ድርሻ ምን ያህል ታላቅ ቦታን እንደሚሰጥ ሌላው ማሳያ ነው።
የሴቶች አገልግሎት በብሉይ ኪዳን
እናት ቤተክርስቲያን ጠብቃ ባቆየችልን የክርስትና ታሪክና አስተምህሮ ቅዱሳንን ከመውለድና በመንፈሳዊ ጥበብ ከማሳደግ ባሻገር ታላላቅና ድንቅ ተጋድሎን የፈጸሙ፣ በሕይወታቸው አርአያና ምሳሌ ሆነው ያስተማሩ ብዙ ቅዱሳት አንስት አሉ። የእናትነት አገልግሎት የጀመረው የሰው ሁሉ እናት በሆነችው በመጀመሪያዋ ሴት በሔዋን ነው (ዘፍ 3:20)። የአብርሃም ባለቤት የተቀደሰች እናታችን ሣራ ደግሞ የእስራኤል ዘሥጋ እናት ተብላ ትታወቃለች (ዘፍ 17:16)። ያዕቆብ በረከትን እንዲያገኝ ያደረገችው ርብቃና የዮሴፍ እናት ራሄል እንዲሁ እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ተብሎ ሲጠራ (ቤተሰቡን እንደሚጠራ ልብ ይሏል) አብረው የሚነሱ የመጀመሪያዎቹ ቅዱሳት አንስት ናቸው። ታላቁን የእስራኤል መሪ ሙሴን በፈርኦን ቤት በጥበብ ያሳደገችው የሙሴ እናት (ዮካቤድ) ሴቶች መሪዎችን ቀርፀው በማሳደግ ረገድ ያላቸውን እጅግ ታላቅ ሚና ያሳየች ታላቅ እናት ናት (ዘፀ 1:28)።
ሕዝበ እስራኤል ባህረ ኤርትራን ከተሻገሩ በኋላ ከበሮን ይዛ ምስጋናውን ስትመራ የነበረችው የሙሴ እህት ማርያምም ሴቶች በዝማሬ እና በምስጋና ዘርፍ ለሚያበረክቱት ድርሻ አብነት ሆናለች (ዘጸ 15:20)። የእስራኤልን ሰላዮች ተቀብላ ያተረፈቻቸው በኢያሪኮ ትኖር የነበረችውና በኋላም በዳዊትና በክርስቶስ የዘር ሀረግ ለመቆጠር የበቃችው ረዓብ ሌላዋ ታላቅ ሴት ነበረች። እግዚአብሔር በገለጠላት ጥበብ የጠላትን መሪ ድል ያደረገችው ዮዲት (መጽሐፈ ዮዲት 1)፣ በድንቅ እምነቷ እግዚአብሔር ከሐሰት ፍርድ ያዳናት ሶስና (መጽሐፈ ሶስና 1) ሴቶች በእምነትም ሆነ በጦርነት የመጣውን ፈተና ድል ማድረግ እንደሚችሉ ልዩ ማሳያዎቻችን ናቸው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ተአምራት ሲያስተምር “ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ (ማቴ 12:42)” በማለት የተናገረላት ንግሥተ ዓዜብ በመንግሥት አመራርና በመንፈሳዊውም ጥበብ ምንኛ ታላቅ እንደነበረች ከታሪክ ድርሳናት መማር ይቻላል። አስቴር ለእስራኤል ድኅነት ምክንያት የሆነች ታላቅ ሴት እንደነበረች መጽሐፍ ይናገራል (አስቴር 4:14)። አቢጊያ ከባልዋ ከናባል ይልቅ ባለታላቅ አእምሮ ስለነበረች ከዳዊት ጦር የታዘዘውን የሞት ቅጣት በጥበብ መመለስ ችላለች (1ኛ ሳሙ 25:3)።
ጌታችንን በመቅደስ ያመሰገነችው (በሉቃ 2:36-38) ነቢይት ሐና ሴቶች ነቢያት ሆነው (በፆም በጸሎት ተወስነው መጻዕያትን እየተናገሩ፣ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ እየመሰከሩ) ሲያገለግሉ እንደነበር ጥሩ ማሳያ ናት። በተጨማሪም ሂልዳ እና ኖአዲያ እንዲሁ ነቢያት ነበሩ (2ኛ ነገ 22:14 ነህምያ 6:14)። እንዲሁም በነቢዪ ኢሳይያስ የተነገረላቸው ሴት ነቢያት ነበሩ (ኢሳ 8:3)። በእስራኤል የፍርድ ወንበር ተቀምጣ ትፈርድ የነበረችው ዲቦራም (መሳፍ 4:4-5) ሴቶች በኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ለሕዝብና ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራን መሥራት እንደሚችሉ ጥሩ ምሳሌ ናት። የእምነቷ ጽናት በልዩ ሁኔታ የተመሰከረላትና ከክርስቶስ የትውልድ ሀረግ የተቆጠረችው ሞአባዊቷ ሩት እንዲሁ ልዩ ምሳሌያችን ሆና ትኖራለች። የታላቁ ነቢይ የሳሙኤል እናት ሐና እና የጠቢቡ ሰሎሞን እናት ቤርሳቤህ በታላቅ የእናትነት ሥራቸው ሲታወሱ የሚኖሩ እናቶች ናቸው። እነዚህን እናቶች ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ ሌሎችም ዘርዝረን የማንጨርሰውን ድንቅ የእናትነት አገልግሎትን ያስተማሩ ታላላቅ እናቶች በብሉይ ኪዳን ነበሩ።
የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሥጋዌ
ከሁሉም በላይ ወልደ እግዚአብሔርን ያስገኘችልን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች ሁሉ የተለየች ናት (ሉቃ 1:26-30)። በሔዋን አለመታዘዝ የተዋረደው ሴትነት በእመቤታችን ትህትና እና መታዘዝ ፍፁም ከብሯልና። ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥላ ድንግል ማርያምን ያመሰገነችውና መጥምቁ ዮሐንስን በበረሀ ያሳደገችው ቅድስት ኤልሳቤጥም በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የነበረች ታላቅ ቅድስት እናት ነበረች (ሉቃ 1:39-44)። ከጌታችን እና ከእናቱ ጋር አብራ ግብፅ ድረስ የተሰደደችው ሰሎሜም የክርስትና ታሪክ ሲያስታውሳት ይኖራል። ለሰማርያ ሐዋርያ የሆነችው ሳምራዊቷ ሴትም (ቅድስት ፎቲና) ቀጥላ ተጠቃሽ ናት (ዮሐ 4:4-26)። ጌታችን በዚህ ምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜም ከ12ቱ ደቀመዛሙርትና ከ72 አርድዕት ጋር 36 ቅዱሳት አንስትን ለአገልግሎት መምረጡ በክርስትና አገልግሎት ሴቶች ታላቅ ቦታ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።
ጌታችን በሚያስተምርበት ወቅትም ተቀምጣ ቃሉን ትማር የነበረችውና “ማርያምስ የማይቀሟትን መልካሙን መረጠች” ተብሎ የተነገረላት፣ በመስተንግዶ ትደክም የነበረችውና ኋላም ወንድሟ አልዓዛር እንደሚነሳ ታላቅ እምነቷን የገለጸችው እህቷ ማርታ የእህቶች እምነትና አገልግሎት ድንቅ ምሳሌዎች ናቸው (ዮሐ 10:38):። ያላትን አንዲት ዲናር ሰጥታ ጌታችን እምነቷን ያደነቀላት ሴት፣ የልብሱን ጫፍ ብነካ እድናላሁ ብላ በማመን ልብሱን ነክታ የዳነችው ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት (ዮስቃና)፣ በብዙ ገንዘብ ሽቱን ገዝታ በራሱ ላይ ያፈሰሰችውና እግሩን በእንባዋ እያጠበች በፀጉሯ ያበሰችውና ያም ታሪኳ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነገርላት ማርያም በእንተ ዕፍረት፣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ በጎልጎታ መከራን ሲቀበል አይሁድን ሳትፈራ ላቡን እንዲጠርግበት መጎናጸፊያዋን የሰጠችው ቅድስት ቬሮኒካ፣ የጌታችንን ትንሣኤ ከሁሉ በፈት አይታ ለደቀመዛሙርቱ ያበሰረችው ማርያም መግደላዊት (ማቴ 28:1) ሴቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት እጅግ ታላቅ ድርሻ እንዳላቸው ድንቅ ማሳያዎቻችን ናቸው።
የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሐዋርያት
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ 16:1-7) የጻፈላቸው ፌቤንና፣ ጵርስቅላና አቂላ ሌሎችም ቅዱሳት ሴቶች እንዲሁ የጎላ መንፈሳዊ አገልግሎትን ፈፅመዋል። ይህንንም ሲናገር “በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት። በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ” በማለት ገልጿቸዋል።
ወንጌላዊው ዮሐንስም (2ኛ ዮሐ 1:1) “በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።” በማለት ያገለግሉ ከነበሩ ቅዱሳት ሴቶች መካከል ለነበረችው ሮምናን “እመቤቴ” ይላት ነበር።
ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር የነበረችውና (ሐዋ 16:13-15) “በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።” ተብሎ የተነገረላት ልዲያም ለቤተሰቦቿ ሐዋርያ ሆና አስተምራለች።
እንዲሁም በሐዲስ ኪዳን የፊሊጶስ አራቱ ደናግል ሴት ልጆቹ ነቢያት እንደነበሩ መገለጹ ሴቶች በሐዲስ ኪዳን የነበራቸውን እና ያላቸውን ድርሻ ያጠናክረዋል (ሐዋ 21:9)። በትንቢትም “እግዚአብሔር ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ (ሐዋ 2:17)” ተብሎ የተነገረው ሴቶች ትንቢትን ከመናገር (ቃለ እግዚአብሔርን ከመመስከር) አንጻር ከወንዶች ተመሳሳይ ድርሻ እንዳላቸው ያሳያል። በዚህ ረገድ በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያ ክርስቲያኖችም በጸሎት ሲተጉ ያለ ልዩነት እንደነበር ወንጌላዊው ሉቃስ ሲጽፍ “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር (ሐዋ 1:14)” ብሏል።
የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሰማዕታትና ሊቃውንት
በእምነት ጸንታ የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበለችው በዚህም ስትዘከር የምትኖረው ቅድስት አርሴማ (ስንክሳር መስከረም 29)፣ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከ50 ቅዱሳት አንስት ጋር በንጉሥ ዑልያኖስ ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ሶፊያ፣ በንጉሥ ዴሲየስ ዘመን ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት አንስጣስያ፣ ገድላቸው ሲዘከር የሚኖረው ቅድስት ባርባራ፣ ቅድስት ዮልያና እና ቅድስት ዮስቲና፣ በጽኑ ተጋድሎ ክብርን ያገኘች ቅድስት ዕንባ መሪና (ስንክሳር ነሐሴ 25)፣ ገዳማዊ ሕይወትን ለእናቶች ያስተማረች ሰማዕቷ ዴምያና፣ ከልጇ ጋር ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት እየሉጣና (ስንከሳር ሐምሌ 19) ሌሎችም ሰማዕታት ታሪካቸውን በደም የጻፉ ቅዱሳት አንስት ናቸው።
ለ25 ዓመታት በገዳም የተጋደለችው ቅድስት ማርታ ተሐራሚት (ስንክሳር ሰኔ 3)፣ በዘመነ ሰማዕታት ልጇን በደም ያጠመቀችው ቅድስት ሣራ፣ የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከ300 ዓመታት በላይ ከተቀበረበት እንዲወጣ ያደረገችው ንግሥት ኢሌኒ የክርስትና ታሪክ ፈርጦች ናቸው። የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን በሚባለው በ4ኛው መቶ ከፍለ ዘመን የነበሩት የቅዱስ አውግስቲን እናት ቅድስት ሞኒካ፣ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እህት ቅድስት ማክሪና እና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ረዳት የነበረችው ቅድስት ኦሊምፒያ የቤተክርስቲያን ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታላላቅ ቅዱሳንን ያስገኙልን እንደ ቅድስት እግዚእ ኃረያና ቅድስት አቅሌስያ ያሉትም ቅዱሳት እናቶች ሲታሰቡ ይኖራሉ። እነዚህን ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ ሌሎችም ስማቸውን ዘርዝረን የማንጨርሰው ቅዱሳት አንስት ያደራጉት ተጋድሎና ያገኙት ክብር በስንክሳርና በተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍት ይገኛል።
የሴቶች አገልግሎት በቅርብ ዘመን
ዲያብሎስን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ምህረትን የጠየቀችለት ጻድቋ ክርስቶስ ሠምራ (ስንክሳር ነሐሴ 24)፣ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት በመዐርግ የተስተካከለችውና ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱን ያነፀችው ቅድስት መስቀል ክብራ (ስንክሳር ሐምሌ 28)፣በቅድስናና በንጽሕና ኖራ ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) (ስንክሳር የካቲት 29)፣ ካቶሊካውያን ቅኝ ገዥዎች በሀገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንን አስገድደው እምነት በማስለወጥ ላይ በነበሩበት ዘመን በቅድስናና በጥብዓት ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ (ስንክሳር ህዳር 17) በሀገራችን ኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ቅዱሳት አንስት ናቸው። በአንድነት ቆመው የህንድን ቤተክርስቲያን ከተሃድሶ ጥፋት የታደጓት የህንድ እናቶች ተጋድሎም የቅርብ ትዝታችን ነው።
በቅርብ ዘመን በቅኔው ዘርፍም ድንቅ ታሪክን ያስመዘገበችው እሙሐይ ሐይመት፣ እሙሐይ ገላነሽ፣ ቀጥሎም የመጡት ሴት የቅኔ መምህራን እሙሐይ ኅርይትና እሙሐይ ወለተ ሕይወት ያሳዩት አርአያነት ሴቶች ከባድ በሚባለው የቅኔ ዘርፍ ሳይቀር በማስተማር ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ማረጋገጫዎቻችን ናቸው። ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለቤተክርስቲያን ያበረከቱት እቴጌ ኢሌኒም እንዲሁ የቤተክርስቲያን ባለውለታ ናቸው። በዘመናችንም ያሉት መምህርት ጥዕምተ ዜማ፣ መምህርት ሶስና በላይ፣ መምህርት ሕይወት ፀሐይ ሴቶች በመንፈሳዊው ዕውቀትና በማስተማሩም ሥራ ታላቅ ድርሻ ማበርከት እንደሚችሉ አርአያዎች ናቸው።
መልእክተ አስተምህሮ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሴቶች ገዳማት ለሴቶች ገዳማዊ ሕይወትና የመንፈሳዊ ትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል። እነዚህ ገዳማት ለሴት ሊቃውንትና ቅዱሳት ሴቶች መፍለቂያ ናቸው። በዘመናችንም ይህንን አገልግሎት የሚሰጡና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የሴቶች ገዳማት ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። በአንጻሩም ሴቶች በዘመናዊው የቤተክርስቲያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ተምረው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ሊበረታቱ ይገባል።
በተጨማሪም ሴቶች ከእልልታ ባለፈ በመዝሙርና እና በዜማ መሣሪያዎች (ለምሳሌ በገና በመደርደር) ዘርፍ የሚያበረክቱት አገልግሎት በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እየታገዘ ሊጎለብት ይገባዋል። የቤተክርስቲያን አልባሳትንና የተለያዩ ንዋየ ቅድሳትን በእጃቸው ሠርተው በማዘጋጀት፣ ቅፅረ ቤተክርስቲያንን በማፅዳት፣ መገበሪያውን መርጠው በማዘጋጀት፣ የአብነት ተማሪዎችን እና ካህናቱን በመመገብ፣ በእንግዶች መስተንግዶ፣ በአስተዳደር ሥራዎችና በመሳሰሉት ዘርፎችም ሴቶች የሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች ታላቅ ዋጋ እንዳላቸውና ሰማያዊ ክብርን እንደሚያሰጧቸውም ማስተዋል ያስፈልጋል። በበጎ አድራጎት ዘርፍም ገዳማትን፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመርዳት ሴቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ታላቅ ነው። ይህም ሊበረታታ ይገባዋል።
ሴቶች (እናቶች) የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጀምሮ እስካላንበት ዘመን ድረስ ተነግሮ የማያልቅ ድንቅና ታላላቅ መንፈሳዊ አገልግሎትን ሲፈጽሙ ኖረዋል። በዚህም ለራሳቸው የጽድቅ አክሊልን አግኝተዋል፣ ለትውልድም አርአያ የሚሆን የተጋድሎ ታሪክን አቆይተዋል። በዚህ ዘመንም በዓለምና በገዳም ሃይማኖትን በመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ወሳኝ የሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ስለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን የታሪክ መዛግብት ያሰፈሩትን የእናትነት አገልግሎት በዘመናችን ላለው ትውልድ በበቂ ሁኔታ ማስተማርና ጽፎም ማሰራጨት ያስፈልጋል። በዘመናችን ላሉት ሴቶች እህቶቻችን አብነት ይሆን ዘንድ የቤተክርስቲያን አውደምሕረትም አሁን ከሚደረገው በበለጠ የእነዚህ ቅዱሳት አንስት ተጋድሎ የሚሰበክበት፣ ስለእነርሱም የሚዘመርበት፣ ገድላቸው የሚነበበት ሊሆን ይገባል እንላለን። የእነዚህ ደጋግ ቅዱሳን እናቶች በረከታቸው ይደርብን። አሜን!
Pingback: ሴቶች በቤተክርስቲያን (ክፍል ፫): አለባበስ – አስተምህሮ
Pingback: ሴቶች በቤተክርስቲያን (ክፍል ፭): የማስተማር ሚናቸው እንዴት ይታያል? – አስተምህሮ
good
LikeLike