ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፪): የፆታ እኩልነት

women in church_2

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ የተጠመቀ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ባገኘው የሥላሴ ልጅነት ያለምንም ልዩነት አንድ ነው። ይሁንና በአንዳንድ ወገኖች በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የተፈጥሮ ልዩነት መነሻ በማድረግና በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ አንዳንድ ታሪኮችንና ትምህርቶችን የተለያየ ትርጓሜ በመስጠት ወንዶችን ከሴቶች አስበልጦ የመመልከት (ሴቶችን ከወንዶች አሳንሶ የማየት) ነገር ይስተዋላል። በዚህም የተነሳ  በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የፆታ እኩልነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የእኛ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የሴቶችን ድርሻ በጉልህ ቢገልጽም አሁንም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ ከመታየቱም በላይ በዚህ ዘመንም ሴቶችን አግላይ የሆኑ አገልግሎቶችና በሴቶችም ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሉ። ሴቶች በቤተክርስቲያን በሚለው ዋና ርዕሰ ጦማር የመጀመሪያ ክፍል በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተክርስቲያን የኋላ ዘመን ታሪክ የቅዱሳት አንስት(ሴቶች)ን አገልግሎት በመጠኑ አሳይተናል። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር “ሴቶች በቤተክርስቲያን” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ሥር ሁለተኛ የሆነውን የፆታ እኩልነትን (Gender Equality) የሚመለከቱ ሀሳቦችን እንዳስሳለን።

ሔዋን ከአዳም መፈጠሯ ከአዳም አያሳንሳትም!

እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን፣ እንደምሳሌያችን እንፍጠር” ካለ በኋላ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። አስቀድሞ አዳምን ከመሬት አበጀው። የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበትና ሕያዊት ነፍስ ያለው ሆነ። ለአዳምም እንደርሱ ያለ ረዳት ስላልተገኘለት እግዚአብሔር ከአዳም ጎን አንዲት አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት። ይህችም ሴት የሁሉ እናት የሆነችው ሔዋን ናት። አንዳንድ ወገኖች ሔዋን ከአዳም ተገኝታለችና “ወንድ ከሴት ይበልጣል፣ ሴትም ከወንድ ታንሳለች” ሲሉ ይከራከራሉ። የመጽሐፉን ቃል በሚገባ ላስተዋለው ግን ወንድ ከሴት ይበልጣል፣ ሴትም ከወንድ ታንሳለች የሚል መልእክት የለውም። በመጀመሪያ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው (ዘፍ 1:28)” የሚለው ሁለቱንም በምሳሌውና በመልኩ እኩል አድርጎ መፍጠሩን ያሳያል። የሰጣቸው በረከትና ስልጣንም እንዲሁ አንድ ዓይነት ነው። ለአዳም ትልቅ ስልጣን፣ ለሔዋን ትንሽ ስልጣን ወይም ለአዳም ትልቅ በረከት ለሔዋን ትንሽ በረከትን አልሰጠም። ሁለቱንም ባረካቸው፣ በምድር ላይ ይበዙ ዘንድ፣ በምድርም ያሉትንም ሁሉ ይገዙ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው እንጂ።

አዳም ከእርሱ የተፈጠረችውን ሔዋን “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ያለው፣ እንዲሁም “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ (ዘፍ 2:23-24 ማቴ 19:4-6)” የተባለው አዳምና ሔዋን አንድ እና እኩል መሆናቸውን ያረጋግጣል። አንድ አካል የሆኑ አዳምና ሔዋን እኩል እንጂ የሚበላለጡ አይደሉም። ሌላው ማስተዋል ያለብን ግን አዳም ከመሬት፣ ሔዋንም ከአዳም ቢገኙም ከእነርሱ በኋላ ያሉ ሴቶችም ወንዶችም በእኩልነት ከእናትና ከአባት የተወለዱ መሆናቸውን ነው። ይህም ከእናትና ከአባት ነፍስና ሥጋ ነስተው መወለዳቸው እኩልነታቸውን ያረጋግጣል።

አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ ከሔዋን አያስበልጠውም!

ሔዋን ከአዳም ጎን መፈጠሯ የታወቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። ይህን መነሻ በማድረግ ማኅበራዊ ብዥታ በፈጠረው አስተሳሰብ በመገፋት ያልተፃፈ እያነበቡ አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ ከሔዋን እንደሚያስበልጠው የሚናገሩ አሉ። ይሁንና በአፈጣጠራቸው አዳምን ከመሬት፣ ሔዋንንም ከአዳም አጥንት የሠራቸው እግዚአብሔር ነው። በዚህም ሁለቱም የእጆቹ ሥራዎች ናቸው። አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ መቀዳደምን እንጂ መበላለጥን አያመለክትም። “አዳም ቀድሞ ስለተፈጠረ ከሔዋን ይበልጣል” የምንል ከሆነ እንስሳት ከሰው ቀድመው ተፈጥረዋልና “ይበልጣሉ” ወደሚል ስህተት ይመራናል። የሔዋን ከአዳም አጥንት መሠራትም እንዲሁ መገኛዋን ያመለክታል እንጂ ማነስዋን አያሳይም። ይልቁንስ የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ከፍ ብሎ ከራሱ ወይም ዝቅ ብሎ ከባቱ ሳይሆን ከመካከል ጎኑ መገኘቷ ከእርሱ የማታንስ ወይም የማትበልጥ መሆኗን ያመለክታል። ለዚህም ነው እግዚአብሔር “እንደ እርሱ ያለ ረዳት እንፍጠርለት” ያለው። “እንደ እርሱ ያለ” ሲል ከእርሱ እኩል የሆነ ነገር ግን የሚረዳው አጋር እንፍጠርለት ማለቱን ልብ ይሏል።

ሔዋን ቀድማ መሳሳቷ ከአዳም አያሳንሳትም!

“ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ” ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ወገኖች ሌላ የሚያነሱት ምክንያት “ሔዋን ቀድማ ተሳስታለች፣ አዳምንም አሳስታለች፣ ስለዚህ ከአዳም ታንሳለች” የሚል ነው። ሔዋን በእባብ፣ አዳምም በሔዋን ምክንያት ሕግ ማፍረሳቸው መበላለጥን አያሳይም። ሁለቱም ተሳስተው ሕግን አፍርሰዋልና። ይልቁንም አባታችን አዳም ቀድማ የተሳሳተችውን ሔዋንን ከመርዳት ይልቅ ራሱም ተሳሳተ። የተሳሳተችውን ሔዋንን ወደ ንስሐ ከመምራት ይልቅ በነፃ ፈቃዱ እርስዋን ለመከተል ወሰነ። ስለዚህ ነው ለአዳም መሳሳት ሔዋን ምክንያት ናት እንጂ ተጠያቂ አይደለችም የምንለው። ይልቁንም ሁለቱም መሳሳታቸውና ሕግን ማፍረሳቸው፣ ሁሉቱም በሕግ መቀጣታቸው እኩልነታቸውን ያሳያል። ምክንያቱ ቢለያይም፣ በመሳሳት ቢቀዳደሙም፣ የቅጣታቸው ይዘት በጥቂቱ ቢለያይም በሰው ደረጃ ግን የሚያበላልጣቸው አልነበረም። የመጀመሪያዋ ሴት (ሔዋን) ቀድማ ተሳስታለችና ሁሉም ሴቶች እንደ እርስዋ ናቸው ብሎ ማጠቃለልም አይቻልም።

ይልቁንም የዓለማትን ፈጣሪ በመውለዷ ለሰው ልጆች ሁሉ የድኅነት ምክንያት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጡራን ሁሉ የሚበልጥ ክብር አላት። በዚህም “ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች” ትባላለች። ክብሯም በቃላት የማይገለፅና ዕፁብ ድንቅ ተብሎ የሚታለፍ ነው። ስለዚህም ቅድስት ድንግል ማርያም አይደለም የአዳም ልጆች ከሆኑት ከወንዶች ይቅርና ከሱራፌልና ከኪሩቤልም ትበልጣላች። ይህ ማለት ግን ሴቶች ከወንዶች ይበልጣሉ ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ሔዋን ቀድማ ስለተሳሳተች ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ አይባልም።

“ባልሽ ገዥሽ ይሆናል” የሚለው እኩልነትን ይፃረራልን?

ታዲያ “ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል (ዘፍ 3:16)” ለምን ተባለ? እንል ይሆናል። ይህም ቢሆን ሕግን ከመተላለፋቸው አንጻር የተነገረ ነው እንጂ እግዚአብሔር እኩል ሰው አድርጎ የፈጠራቸውን አዳምን እና ሔዋንን ለማበላለጥ የተናገረው አይደለም። ሔዋንን “ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል” ያላት አንዳንዶች እንደሚሉት ጾታዊ ፍላጎትን (ፈቃድን) የሚያመለክትም አይደለም። ይልቁንም የእባብን ምክር ሰምታ በራስዋ ፈቃድ ብቻ ሕግን አፍርሳ ነበርና ከዚህ በኋላ ከባልዋ ጋር በትዳር ስትኖር በአንድነት መወሰን እንደሚገባት የሚገልፅ ነው። ለአዳምም “እርሱም ገዥሽ ይሆናል” የተባለው የአንቺን ምክር ብቻ ሰምቶ አትብላ የተባለውን እንደበላው ሳይሆን ከዚህ በኋላ ሀሳብሽን ምክርሽን የሚሞግትና ያለ እርሱ ተሳትፎ በትዳር ውስጥ ብቻሽን አትወስኝም ሲል ነው። “ይገዛሻል” የተባለውም በፍቅር በትዳር አንዱ ለአንዱ እንደሚገዛው ‘በፍቅሩ ይገዛሻል’ የሚል እንጂ እንደ ምድር ነገሥታት ምርኮ በባርነት መግዛትን አያመለክትም።

እግዚአብሔር ፍትሐዊ አምላክ ስለሆነ ሁሉቱም እኩል ሕግን አፍርሰው የበደሉትን አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ (አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች) አያደርግምና። እዚህ ላይ ማስተዋል የሚሻው ሌላው ነገር ለይቶ “ባልሽ” አለ እንጂ “ወንድ” አላለም። እንዲህም ማለቱ በትዳር ውስጥ ያለውን ለይቶ ለማሳየት ነው። አንድም “ፈቃድሽ” የተባለው ሔዋን አምላክ ለመሆን የፈለገችውና ሕግን ለመተላለፍ ያበቃት መሻት/ፍላጎት ነው። ይህም ፈቃድ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆኑ ተፈጽሟል። ይህም እግዚአብሔር “እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” በማለቱ ይታወቃል (ዘፍ 3:21)። ያ አምላክ የመሆን ፈቃድ በእርሱ ተፈጸመ። “እርሱም ገዥሽ ይሆናል” የተባለውም በመስቀል ተሰቅሎ በፍቅሩና በደሙ የገዛን መሆኑን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ይህ ቃል ለጊዜው ለአዳምና ለሔዋን ይነገር እንጂ ፍጻሜው በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ በደሙ የተገዛን መሆናችንን የሚያሳይ ነው።

“የሴት ራስ ወንድ ነው” የሚለውስ እንዴት ይገለጻል?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ራስም ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (1ኛ ቆሮ 11:3) ያለውም ቢሆን መበላለጥን አያሳይም። ይልቁንም አዳም መገኛው ከእግዚአብሔር፣ የሔዋን መገኛዋ ከአዳም፣ የወልድም መገኛው (የተወለደው) ከአብ መሆኑን ያረጋግጣል እንጂ። “የሴት ራስ ወንድ ነው” የሚለውን ይዘን ‘ወንድ ከሴት ይበልጣል’ የምንል ከሆነ “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” የሚለውንም ወስደን ‘አብ ከወልድ ይበልጣል’ ልንል ነው? ይህ ደግሞ ወደ አርዮስ ክህደት ያስገባናል። ስለዚህ የሴት ራስ ወንድ ነው የሚለው ሔዋን ከአዳም አጥንት መገኘቷን የሚያሳይ ነው እንጂ ወንድ የሴት የበላይ (አለቃ) ነው ማለት አይደለም። በሌላም ትርጓሜ የሴት ራስ ወንድ ነው የሚለው የቤተሰቡ ተጠሪ እርሱ ነው ለማለት ነው። እግዚአብሔር አዳም ወይም አብርሃም ወይም ይስሐቅ ወይም ያዕቆብ ብሎ ሲጠራ መላውን ቤተሰብ መጥራቱ እንጂ አንድን ወንድ ብቻ መጥራቱ አይደለም። ይህም ድርሻን እንጂ የበላይነትን የሚያሳይ አይደለም።

“ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” የሚለውስ?

ይህን ቃል በመያዝ “የወንዶች የበላይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተነግሯል” የሚሉ ወገኖች አሉ። ቃሉን ላስተዋለው ግን ይህ ስለትዳር ጉዳይ እንጂ ስለፆታዊ መበላለጥ የተነገረ አይደለም። ሐዋርያው ያለው “ሴቶች ሆይ ለወንዶች ተገዙ” ሳይሆን ለይቶ “ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ነው (ኤፌ 5:22-24)። ይህም እንደቀደመው “ገዥሽ ይሆናል” ብሎ እንደተነገረው ነው። በትዳር ያሉ ጥንዶች አንድ እንጂ ሁለት ስላልሆኑ አንዳቸው ለሌላው በፍቅር ሕግ መገዛት እንደሚገባቸውና ትዳራቸውን በግል ፈቃድ ሳይሆን በጋራ እየተመካከሩ መምራት እንደሚገባቸው ለማስረዳት የተነገረ ነው። ለዚህም ነው በዚሁ ክፍል “ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ስለእርሷም ራሱንም አሳልፎ እንደሰጠ ሚስቶቻችሁን ውደዱ” የተባለው። በዚህ መልእክት ሐዋርያው በትዳር ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት አስተማረ እንጂ የወንድ የበላይነትን አላስተማረም።

ወንዶችና ሴቶች መለየታቸው

በቤተክርስቲያን ወንዶች በግራ ሴቶች በቀኝ በኩል ሆነው ያስቀድሳሉ። በሌሎች መርኅግብሮችም እንዲሁ ተለይተው ይቀመጣሉ። ቅዱስ ቁርባንንም ሲቀበሉ እንዲሁ በቅደም ተከተል ነው። ይህ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው። ሥርዓቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው። ኖኅና ቤተሰቡ በመርከብ ሲገቡ ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ ነበሩ። ይህንንም መነሻ በማድረግ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ወንዶች ከወንዶች ጋር ሴቶችም ከሴቶች ጋር እንዲቆሙ፣ በቅዳሴም ጊዜ ሰላምታ እንዲሰጣጡ በማዘዝ ይህም በቤተክርስቲያን በተመስጦ ለመጸለይ እንደሚረዳ አስተምሯል። ይህም ለሁሉም ተገቢውን ቦታ የመስጠት እንጂ የሚያበላልጥ ሥርዓት አይደለም። የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትም እንዲሁ ምስጢራትን በተገቢው መንገድ ያላንዳች ልዩነት ለመፈጸም የተሠራ ነው። መቀዳደሙም መበላለጥን አያሳይም። እንደዚያ ቢሆን የሚበላውን እና የሚጠጣውን ያስገኘችልን ድንግል ማርያም ስለሆነች ከምስጢረ ቁርባን አንጻር ሴቶች ይበልጣሉ በተባለ ነበር።

የሴቶችና የወንዶች ተፈጥሮአዊ ልዩነት

ወንዶችና ሴቶች ተፈጥሮአዊ ልዪነት (biological difference) እንዳላቸው ሁሉም የሚገነዘበው እውነታ ነው። ይህም በዋናነት ትውልድን ከማስቀጠል አንጻር ዘርን ለመተካት ካላቸው ድርሻ ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ወንዶችና ሴቶች ነገሮችን የሚመለከቱበት መንገድ፣ የሚረዱበት ሁኔታ፣ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ፣ ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጡበት አካሄድ ይለያያል። ይህም ጠንካራ ጎኖቻቸውን እንዲያስተባብሩ፣ በደካማ ጎኖቻቸው ደግሞ እንዲረዳዱ ያግዛል። ከፆታ ጋር የተያያዘ ተፈጥሮአዊ ልዩነት የመከባበር እንጂ የመበላለጥ ምንጭ ሊሆን አይችልም። ከአባታችን ከአዳም በቀር ሁሉም ሰው በእኩልነት ከሴት (ከእናት) የተወለደ ነው። የሰው ዘርም የሚቀጥለው በዚሁ መልክ ነው። በተፈጥሮ ልዩነት ቢሆንማ ይልቁንም ዘጠኝ ወር በማህፀን የሚንከባከቡት፣ ቀጥሎም ጡት እያጠቡ የሚያሳድጉት፣ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወትም ጉልህ ድርሻ ያላቸው እናቶች በበለጡ ነበር።

መደምደሚያ

በአጠቃላይ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚመሰክሩት እውነትና የቀደሙት ቅዱሳን ያስተማሩት በሴቶችና ወንዶች መካከል መበላለጥን ሳይሆን አንድነትንና ፍቅርን ነው። ሴቶችና ወንዶች የተለያየ ድርሻ (different roles) ቢኖራቸውም እኩል መብት (equal rights) አላቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለገላቲያ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ሴት የለም፣ ወንድ የለም፣ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ነው” በማለት እኩልነትን አስተምሯል (ገላ 3:28)። የክርስትናችን መርህም ይህ ነው። ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የተወለደ ሁሉ በክርስቶስ አንድ ነው። የተሰጠው ጸጋ ሊለያይ ይችላል። ጽድቅም በእምነት፣ በምግባርና በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ በፆታ ወይም በሥጋዊ ክህሎት የሚገኝ አይደለም። በመንፈሳዊ ሕይወትም ሰው ሁሉ በአንድ መንፈስ ሆኖ የሚያገለግለው አንድ እግዚአብሔርን ነው። በሥጋዊ ተፈጥሮ ወንድና ሴት የሚለያዩባቸው ነገሮች እንዳሉ ግልፅ ነው። ይህ የሆነው ዘርን በመተካት ሂደት የየራሳቸው ተመጋጋቢ ድርሻ ያላቸው ስለሆነ ነው። የግል ክህሎት ግን ሁሉም ሰው ያሉትን ዕድሎች ተጠቅሞ የሚያዳብረው እንጂ በተፈጥሮ ለወንድና ለሴት ተብሎ የተከፈለ አይደለም።

በመጽሐፍ ያሉትን ጥቅሶች ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ሴቶችን የበታች አድርጎ መመልከትም ሆነ እንደዚህ ማስተማር ሁለት መሠረታዊ ስህተቶችን መፈጸም ነው። የመጀመሪያው የመጽሐፍን ቃል ባልተገባ መንገድ መተርጎም፣ ሁለተኛው ደግሞ በተሳሳተ ትርጉም በደልን ለማድበስበስ መሞከር። ይህ በተለይም “ወንዶች ብቻ በሚያዙበት” ነገር ግን ሴቶች በብዛት በየጉባዔው በሚሳተፉበት በእኛው ቤተክርስቲያን ሲሆን ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። ከዚህ አንጻር ቤተክርስቲያን በፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚታዩ ሥር የሰደዱ ስሁት አመለካከቶችን በማፅዳትና ሴቶችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ባከበረ መልኩ ቁልፍ በሆኑ የቤተክርስቲያን አገልግሎቶችና ውሳኔዎች በበቂ ሁኔታ ከማሳተፍ አንጻር ብዙ ይጠበቅባታል። እኩልነትንም ለማረጋገጥ ከቃልና ከመመሪያ በተጨማሪ በተግባር ሊገለጥ ይገባዋል እንጂ ቁጭ ብሎ መማርም ታላቅ አገልግሎት ነው በሚል መሸንገያ ሊታለፍ አይገባውም። በባህል ተፅእኖ ምክንያትም የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጓሜ እያጣመሙ ሴቶችን አሳንሶ የማየትን ልማድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍ በመስጠት (ወይም በዝምታ በማለፍ) የቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚያዳክሙትን ሰዎችም በትምህርት፣ በምክርና በተግሳጽ ማስተካከል ይገባል እንላለን።

1 thought on “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፪): የፆታ እኩልነት

  1. Pingback: ሴቶች በቤተክርስቲያን (ክፍል ፫): አለባበስ – አስተምህሮ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s