በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መንፈሳዊ አገልጋዮች ልዩ ልዩ የመዓርግ ስሞች ይሰጧቸዋል። ሊቀ ካህናት፣ መምህራን፣ ነቢያት፣ ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት የሚሉትን እንደ ምሣሌ መውሰድ እንችላለን። እነዚህ መዓርጋት የየራሳቸው አመክንዮ አላቸው። ነገር ግን አገልግሎትን መጠቀሚያ በሚያደርጉ ምንደኞች ዘንድ እነዚህና ሌሎች መዓርጋት ከመንፈሳዊ ዓላማ በፍፁም ባፈነገጠ መልኩ ምዕመናንን ለመበዝበዝ፣ ሥጋዊ ተቀባይነትን ለማግኘትና ለመሳሰለው ሥጋዊ ዓላማ ሲውል ማየት የተለመደ ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ከመዓርግ ስም አሰጣጥና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊትና በዘመናችን ካሉ ቅሰጣዎች አንፃር እንዳስሳለን፣ በተጠየቃዊ አቀራረብም ተገቢ ነው የምንለውን የመፍትሔ ሀሳብ እናቀርባለን።
የጌታችን ትምህርት ስለ መዓርጋት አጠቃቀም
በዘመናችን የምናየው በመዓርግ ስም የመሸቀጥ ልማድ በዘመነ ብሉይ በነበሩ ጻፎች፣ ፈሪሳውያንና ሌሎች የአይሁድ ሊቃናት ዘንድ የተለመደና በጌታችን ትምህርት የተወገዘ ነበር። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ “ፈሪሳውያን በገበያም ሰላምታና፡— መምህር ሆይ፡ መምህር ሆይ፡ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። እናንተ ግን፡— መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፡— አባት፡ ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፡— ሊቃውንት፡ ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።”(ማቴ 23:7-11) በማለት አስተምሯል።
ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ይህንን ያላቸው መዓርጋት ጭራሽ አያስፈልጉም ለማለት አይደለም። ደቀ መዛሙርቱን “መምህራን” አድርጎ የሾማቸው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እናትና አባታችሁን አክብሩ” ብሎ ሕግን የሰራ ጌታ “በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ” ሲል የተናገረበትን ምክንያት መመርመርና በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል እንጂ በጥራዝ ነጠቅ ንባብ መቆነፃፀል አይገባም። የጌታችን ትምህርት ዓላማ በየዘመናቱ የሚመጡ የቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ መምህራንና ምዕመናን ስምና ግብር ለየቅል የሆነባቸውን ፈሪሳውያንን እንዳይመስሉ (ፈሪሳውያን ከተግባር ይልቅ እይታን የሚወዱ እና ከፍብለው መታየትን የሚመርጡ እንጂ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር የያዙ ስላልነበሩ) ለማስጠንቀቅ የተነገረ ነው።
የቤተ ክርስቲያንን መዓርግ ለሥጋዊ ክብር የሚጠቀሙትን ሁሉ “በገበያ ሰላምታ መምህር ሆይ! መምህር ሆይ!” መባል በመውደዳቸው ፈሪሳውያንን የወቀሰ የጌታ ቃል ይወቅሳቸዋል። የቤተ ክርስቲያን “መምህር” መሆናቸውን ዝቅ ብሎ ለማገልገል ሳይሆን “በምዕመናን ላይ ለመንገሥ” የሚጠቀሙበትን ምንደኞች “ሁላችሁ ወንድማማቾች ናችሁ”፣ የበላይና የበታች የለም የሚለው የጌታ ቃል ይገስፃቸዋል። በምዕመናን ላይ በእረኝነት፣ በጠባቂነት የተሾሙ አባቶች አባትነታቸው እንደ ጌታችን፣ እንደ ሐዋርያት ዝቅ ብሎ እግር ለማጠብ (ለማገልገል) መሆኑን ረስተው አባትነትን የክብር፣ የገንዘብና የፖለቲካዊ ተደማጭነት ማግኛ መሰላል ሲያደርጉት “አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ።” የሚለው አምላካዊ ትዕዛዝ ይወቅሳቸዋል። ምዕመናንን ለማስተማር፣ የመናፍቃንን ክህደት በመለየት እውነተኛውን የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ለማፅናት “ሊቃውንት” የተባሉ የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት በክብር ከተጠሩበት አገልግሎት ይልቅ ለራሳቸው ምድራዊ ታዋቂነት ወይም ለሌሎች አካላት “ድለላ መሰል” ሥራ ለመሥራት ክብራቸውን በነውር ቢለውጡ “ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ንባብ ከክብር ይለያቸዋል።
የመዓርግ ስሞች በቤተ ክርስቲያን ትውፊት
በዘመነ ብሉይ እንደነበረው በዘመናችንም ብዙ ለእውነት የሚተጉ መምህራንና ካህናት ቢኖሩም ሳይገባቸው የቤተ ክርስቲያንን የመዓርግ ስም ይዘው ቤተ ክርስቲያን ከምትጠብቅባቸው በተቃራኒ የሚያደርጉ ወይም የቤተ ክርስቲያንን መዓርግ ለሥጋዊ ዓላማ የሚጠቀሙ አሉ። የመዓርግ ስሞች የሚሰጡት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ነው። ይህም የአገልጋዩን የአገልግሎት ድርሻ ለመግለጽ ነው። በአብዛኛው የመዓርግ ስም የሚሰጡትም ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ስሞች የደብር አለቆችን፣ መምህራን ሌሎች ሊቃውንትን የመዓርግ ስሞች ያሳያሉ።
የደብር አስተዳዳሪዎች (አለቆች) የመዓርግ ስም ከሚያገለግሉበት ደብር ስም ጋር ተያይዞ መልአከ ሰላም፣ መልአከ ብርሃን፣ መልአከ አሚን፣ መልአከ ምህረት፣ መልአከ ገነት፣ መልአከ ፀሐይ፣ መልአከ ኃይል፣ መልአከ ጽዮን… ወዘተ ይባላል። “መልአክ” ማለትም “አለቃ” ማለት ነው። የገዳም አስተዳዳሪዎችም አበምኔት (ጸባቴ -ለደብረ ሊባኖስ፣ ንቡረ ዕድ -የአክሱምና የአዲስ ዓለም አለቃ ) ይባላሉ። እንዲሁም ሊቀ ሥልጣናት (የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ አለቃ)፣ ሊቀ ሊቃውንት (የበዓታ ገዳም አለቃ)፣ ሊቀ ካህናት (የካህናት ሹም) ይባሉ ነበር።
የደብር የክህነት አገልግሎት የመዓርግ ስሞች ደግሞ መምሬ (የምዕመናን መሪ፣ አስተማሪ፣ የንስሐ አባት)፣ ቀሲስ/ቄስ (አገልጋይ)፣ ቄሰ ገበዝ (የቤተ ክርስቲያን ነዋየ ቅድሳት ጠባቂ)፣ ሊቀ ዲያቆናት (የዲያቆናት አለቃ)፣ ዲያቆን (ለተልዕኮ የሚፋጠን የቄስ ረዳት፣ የምዕመናን አገልጋይ) ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለሚያገለግሉ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የአማርኛ መዝሙር (የካሴት) ዘማርያን እና ምዕመናን ጭምር የመዓርግ ስም እየተሰጠ ይገኛል።
የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን የመዓርግ ስሞች ደግሞ መጋቤ ምሥጢር (የቅኔ መምህር)፣ መጋቤ መዝሙር (የዝማሬ መዋስዕት፣ የአቋቋም መምህር)፣ መጋቤ ብሉይ (የብሉይ ኪዳን መምህር)፣ መጋቤ ሐዲስ (የሐዲስ ኪዳን መምህር)፣ መጋቤ መምህራን (የሊቃውንት መጻሕፍት መምህር)፣ መጋቤ ምክር (የመጽሐፈ መነኮሳት መምህር)፣ መጋቤ ስብሐት (የምዕራፍና ጾመ ድጓ መምህር)፣ መጋቤ ላዕካን (የፊደል ንባብ መምህር) … ወዘተ ይባላሉ። “መጋቢ” ማለት መምህር ወይም አስተማሪ ማለት ነው።
የሊቅነት፣ የመዘምርነት የመዓርግ ስሞች ደግሞ ሊቁ (የአራቱ ጉባዔያት ሊቅ)፣ ሊቀ ማእምራን (አጠቃላይ ዕውቀት ያለው)፣ ሊቀ ጉባዔ (የሐዲስና የብሉይ መምህራን አለቃ)፣ ሊቀ ጠበብት (የጠቢባን የበላይ)፣ ሊቀ መዘምር (የመዘምራኑ አለቃ)፣ ርዕሰ ደብር (የደብሩ ጸዋትወ ዜማ ሊቅ)፣ መሪ ጌታ (የአቋቋም፣ የጸዋትወ ዜማ ይትበሐልን ጠብቆ የማኅሌትን ሥርዓት የሚመራ)፣ ቀኝ ጌታ (በቀኝ በኩል የሚቆም የጸዋትወ ዜማ ሊቅ)፣ ግራ ጌታ (በግራ በኩል የሚቆም የጸዋትወ ዜማ ሊቅ) ….ወዘተ ናቸው።
የመነኮሳት ገዳማውያን የመዓርግ ስሞች ደግሞ ቆሞስ (ምንኩስና ሰጭ፣ ታቦት ባራኪ)፣ አበምኔት (የገዳም አስተዳዳሪ)፣ እመምኔት (የመነኮሳይት አስተዳዳሪ)፣ አኀው (ወንድሞች መነኮሳት)፣ አኀት (እኅቶች መነኮሳይት)፣ ሊቀ ምርፋቅ (ስለገዳሙ ጉዳይ የሚሰበስብ አለቃ)፣ ሊቀ ረድ (በገዳም መነኮሳትን የሚረዱ መነኮሳት ሹም)፣ ሊቀ መጣኒ (መጋቢ፣ የመጋቢዎች አለቃ) ናቸው።
ከመዓርግ ስሞች ጋር የተያያዙ ችግሮች
የመዓርግ ስም ለሚገባው አገልጋይ ሲሰጥ የተገባ ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ጸጋ ያለዋጋ የሚያገለግሉ፣ ዕድሜአቸውን ለአገልግሎት የሰጡ ካህናትና መምህራን ከገንዘብና የቁሳቁስ ጥቅም ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎታቸው ያላትን ፍቅርና አክብሮት በምትገልጥበት መጠሪያ ሲጠሩ የማይደሰት ይኖራል ብለን አናስብም። ይሁንና ስምና ግብር የማይገጥመበት መዓርግ የጥቅማ ጥቅም ማስከበሪያ፣ ሰዎችን ማታለያ የሚሆንበት ክፉ ልማድ እየተንሰራፋ መምጣቱ የአደባባይ ነውር ሆኗል። ከዚህ አንጻር ከመዓርግ ስሞች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በሦስት ደረጃዎች ከፍሎ ማየት ይቻላል።
የመጀመሪያው ችግር ከስሙ አሰጣጥ ሂደት ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም የመዓርግ ስም ሲሰጥ ብዙም ከትምህርት ዝግጅትና ከአገልግሎት ድርሻቸው ጋር አብሮ የማይሄድ ወይም የማይገናኝ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም መንፈሳዊነት ለጎደለው ዓላማ በጠያቂው ፍላጎት መሰጠቱ ነው። አስተዳደራዊ ተፅዕኖ ላላቸው (አምባገነንና ነገር አመላላሽ በሆኑት ይብሳል) ዲያቆናት ለካህናት የተለመደውን “መልአከ ሰላም፣ መጋቤ ሃይማኖት…” የሚል መዓርግ ሲሰጥ ጤናማ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። አልፎ አልፎም ለአንዳንድ ክህነታቸውና እምነታቸው ጭምር አጠያያቂ ለሆነ “መምህራን” “አጥማቂያን”፣ ምንኩስናቸውን ትተው ጋብቻ ለመሠረቱ፣ በድጋሜ ጋብቻ ምክንያት ክህነታቸውን ለተው እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች አርዓያነት ለሌላቸው ሰዎች ሲሰጥ ይስተዋላል። በአንዳንድ ቦታዎችም የመዓርግ ስሞችን በየጊዜው የመቀያየር ሁኔታ ይታያል። ምንም የአገልግሎት ድርሻና አጥቢያ ወይም የክህነት ሥልጣን ለውጥ በሌለበት የመዓርግ ስም መለወጥ ለአገልጋዮችና ለምዕመናን ግርታን ይፈጥራል። የቀደሙት አባቶች ከትህትናቸው የተነሳ የመዓርግ ስም ለመቀበል እንኳን ብዙ ተለምነው ነበር። አሁን ግን ከዚህ በተቃራኒው እየሆነ ነው ያለው።
ሁለተኛው ችግር ከስሙ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ችግር ነው። የመዓርግ ስሞች ለአገልግሎት እንዲውሉ ታስቦ የሚሰጡ ቢሆኑም የውዳሴ ከንቱ ተደርገው መወሰዳቸውና ከአገልግሎት ይልቅ “መጠሪያ” ብቻ መሆናቸው ነው። በተለይም በዚህ ዲጂታል ዘመን የመዓርግ ስሞች ራስን ማስተዋወቂያ ዋና መሣሪያ ሆነው ይገኛሉ። የቀደሙት አባቶች ከትህትናቸው የተነሳ የመዓርግ ስማቸውን ይደብቁ ነበር። ዛሬ ግን የመዓርግ ስም መድረክ ማድመቂያ፣ ለፖለቲካና ለሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝነት ካባ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፅ ማስተዋወቂያና የረባ ይዘት የሌላቸውና በፍጥነት ለሚፈለፈሉ መጻሕፍት ማሻሻጫ ሆኖ ማየት ያሳዝናል።
ሦስተኛው ደግሞ ለመዓርግ ስሞች ካለ የተሳሳተ አመለካከት የሚመነጭ ነው። የዚህም ምክንያት በምዕመናን ዘንድ በመዓርግ ስሞች ላይ ካለው አነስተኛና የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የመዓርግ ስሞች የአገልጋዩን ሁለንተናዊ የበላይነት (ልዕልና) ለማሳየት የሚሰጡ አይደሉም። እንዲሁም የአገልጋዩን ቅድስና ማሳያም አይደሉም። በተጨማሪም “የሁሉን አዋቂነት” ማረጋገጫም አይደሉም። የመዓርግ ስሞች የአንድ አገልጋይን የመንፈሳዊ አገልግሎት ድርሻ ብቻ የሚገልጹ ናቸው። እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመረዳት የሚከተሉትን ማሳያዎች እንደምሳሌ አቅርበናል።
ማሳያ 1: “ለየት ያለ” የመዓርግ ስም መፈለግ
የመዓርግ ስም ከበዛ በኋላ፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ምዕመንም ስሞቹን በተላመደ ጊዜ በስም የሚነግዱት ሰዎች “ለየት ያለ” ስያሜን ሲፈልጉ ይስተዋላል። ብዙዎቹም “ስም የሚሰጣቸው” በቲፎዞዎቻቸው አቅራቢነት፣ አንዳንዴም “ይሄ ይሻለኛል፣ ይሄ ይቅርብኝ” ብለው በመደራደር ነው። እነዚህ ሰዎች ከሌሎች የተለየ ስም በመያዛቸው “የገበያ ዋጋቸውን” መጨመር የሚፈልጉ ነጋድያን ናቸው። የቀደመው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚያስረዳን የተለየ የመዓርግ መጠሪያ ለተወሰኑ አገልጋዮች በልዩ ሁኔታ የሚሰጥ፣ አጠቃቀሙም ለመንፈሳዊ ዓላማ መሆኑን እንረዳለን። ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሁሉም ካህናት፣ ሰባክያን ወይም ዘማርያን “የመዓርግ ስም ያስፈልጋቸዋል” የሚል ያልተፃፈ ልማድ ይስተዋላል። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በምንደኞች የተነሳ መስመሩን ሲስት ከሚታወቅባቸው መንገዶች አንዱ በሥርዓት መጻሕፍትም ሆነ በደገኛ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ማብራራት የማይቻል ይሆናል።
በአንድ ወቅት አስተምህሮ ስለ አለባበስ ባወጣችው ጦማር ሰባክያንና ዘማርያን “የአገልግሎት” እያሉ የሚጎትቱትን ዘባተሎ ቀሚስና ሀብል ስትሞግት “ወንዶች ዘማርያን ካሴት በማውጣት ወይም በዐውደ ምሕረት በመዘመር ወይም እንዲሁ በፈቃዳቸው ቀሚስና ሀብል የሚጎትቱ ከሆነ በተመሳሳይ አገልግሎት ያሉ ሴት አገልጋዮች ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተኮረጀውን ቀሚስና ሀብል ቢለብሱ የሚኖረው ምላሽ ምን ይሆን?” ብላ ጠይቃ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ ለወንዶች ዘማርያን በየመንገዱ የሚታደለው መዓርግ አልባ የመዓርግ ስም ለሴቶቹ የሚከለከልበት አመክንዮ ምንድን ነው ብለን እንጠይቃለን። የዚህ አመክንዮአዊ ሙግት ዓላማ ሴቶች አገልጋዮችም ስማቸውና የሚገባ ቀሚሳቸውን ትተው የሽንገላ መዓርግና የማስመሰል “ቀሚስ ወይም ስካርፍ” እንዲያገለድሙ አይደለም። ይልቁንስ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የግለሰባዊ ተክለ ስብዕና መገንቢያ፣ ደምቆ መታያ ለሚያደርጉ ሁሉ “የምናደርገው ትክክል ነውን?” ብለው ራሳቸውን እንዲመረምሩ ለመርዳት (Aha moment ለመፍጠር) ነው።
ማሳያ 2: “በእደ ገብሩ ካህን” መባልን እንደንቀት መቁጠር
በቤተ ክርስቲያናችን ሥር እየሰደደ የመጣውን የመዓርግ “አምልኮ” ከሚያሳዩን ተደጋጋሚ ኩነቶች አንዱ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያልተፃፈ ሕግ ሆኖ የሚታይ ልማድ ነው። በጸሎተ ቅዳሴ ፍጻሜ ሠራዒው ዲያቆን “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ በእደ ገብሩ ካህን ከመ ይባርክሙ/ በባርያው (በአገልጋዩ) ካህን እጅ ይባርካችሁ ዘንድ ራሳችሁን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ (ዘንበል) አድርጉ።” ይላል። የመዓርግ አምልኮ በገነነባቸው ቦታዎች “ካህን” የሚለው መጠሪያ ዝቅ ያለና የሚያሳንስ ስለሚመስላቸው ገባሬ ሰናዩ ካህን መነኩሴ ከሆነ “በእደ ገብሩ መነኮስ”፣ ቆሞስ ከሆነ “በእደ ገብሩ ቆሞስ”፣ ጳጳስ ከሆነ “በእደ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ”፣ ፓትርያሪክ ከሆነ “በእደ ቅዱስ ፓትርያሪክ” እያሉ ማዜም እየተለመደ ነው። ያገቡ ቀሳውስት ሆነው “በልዩ ሁኔታ መጠራት” የሚፈልጉት ደግሞ “በእደ ገብሩ መምህር” ያስብላሉ። ብዙዎችም “ካህን” ሲባሉ “ክብር የተወሰደባቸው” ይመስላቸዋል፣ የባሰባቸውም “ስህተት ነው!” ብለው ያርማሉ ወይም ያሳርማሉ።
ይህ ልማድ በቀደመው የቤተ ክርስቲያን ልማድ ያልነበረ የክህነትን መሠረትም የሚፃረር ፈሪሳዊ ልማድ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ሊቅ ሊቀ ካህናት” ብለው የሚጠሩ መነኮሳት፣ ቆሞሳትና ጳጳሳት “ካህን” መባል ካሳፈራቸው ክህነታቸው እንደ ዋኖቻችን ምዕመናንን ለማገልገል ሳይሆን በምዕመናን ለመገልገል ያስመስልባቸዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ጳጳሳትና ፓትርያሪኮች “ገብረ እግዚአብሔር” መባል የለባቸውም የሚል በሚመስል አስተሳሰብ “በእደ ገብሩ ካህን” ከሚለው ውስጥ “ገብር” እና “ካህን” የሚሉትን ትተው “በእደ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ” ወይም “በእደ ቅዱስ ፓትርያርክ” በማለት መሠረታዊውን አስተምህሮ “ለመዓርግ አምልኮ” ይሰውታል። ቀዳስያን መሥዋእታቸው የሚያርገው በክህነታቸው፣ በአገልጋይነታቸው እንጂ በመዓርግ ስማቸው ወይም በስልጣን ደረጃቸው አይደለምና። ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ አገልግሎቱ ለማን ነው?!
ማሳያ 3: መዓርግ መደርደር እንደ ሱስ
በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምህረት ለማስተማር ወይም መልእክት ለማስተላለፍ የሚቆሙ አገልጋዮች በጉባዔው ያሉትን የመዓርግ ስም ያላቸውን መዓርግ አልባ ውዳሴ ፈላጊዎች ሁሉ በተደጋጋሚ መጥራት (overuse) እየተለመደ መጥቷል። በመዓርግ ስማቸውም ላይ (አንዳንድ የሕዝብ እንደራሴዎች በልማድ እንደሚቀጽሉት ያለ) “ክቡር” የሚል ሌላ ቅጥያ መጨመርም እንዲሁ ተለምዷል። በአጠቃላይ “ብጹዓን አባቶች፣ አበው ካህናት፣ አኀው ዲያቆናት እንዲሁም ምዕመናን” ብለው የሚጠሩም በይፋ የማይገለጥ ተግሳፅ ሲደርስባቸው አስተውለናል። “ክርስቲያን፣ ምዕመን” መባልማ ባልተፃፈ ሕግ እንደ ትልቅ “ስድብ” ይቆጠራል። ይህ ሁሉ የማስመሰል ጋጋታ የሥጋ እንጂ የመንፈስ ፍሬ አይደለም። ይልቁንስ ራስን የማግነን አምልኮ ጣዖት ነው።
የአንዳንዶችም የዘመናዊ ትምህርት/የሙያ መዓርግና የመንፈሳዊ መዓርግ በአንድነት (ለምሳሌ ቀሲስ ዶ/ር፣ ዲያቆን ዶ/ር፣ ቀሲስ ኢንጂነር ….ወዘተ) በቤተ ክርስቲያን ሲጠራ ይታያል። አንድ በሙያው ዶክተር የሆነ ቄስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለቡራኬ ሲነሳ ቅስናውን እንጂ ዶክተርነቱን መግለፅ ምንም ተገቢነት (relevance) የለውም። ይሁንና ዓለማዊ መዓርጋትን ከዓለማውያን መድረኮች ባልተናነሰ አሰልቺ በሆነ መልኩ አብዝቶ የመጠቀም (boring overuse) ልማድ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች ይስተዋላል። ዶክተር፣ ኢንጅነር፣ መምህር፣ አርክቴክት፣ አካውንታንት፣ ኢኮኖሚስት፣ ረዳት ፕሮፌሰር፣ አርቲስት፣ አክቲቪስትና የመሳሰሉትን ዓለማዊ መዓርጋት ከቤተ ክርስቲያን መዓርጋት ጋር በመቀላቀልም ሆነ እንዲሁ በዐውደ ምሕረት መጠቀም የደረስንበትን የሞራል ዝቅታና መንፈሳዊ ክስረት የሚያሳዩ ናቸው።
እነዚህ ቢያንስ የዘመናዊውንና የቤተ ክርስቲያንን የመዓርግ ስሞች በየቦታቸው ቢጠቀሙ የተሻለ ይሆናል። በተጨማሪም ይህ የመዓርግ ስም ሱስ አንዳንድ አገልጋዮች በመዓርግ ስማቸው ብቻ “መልአከ እገሌ” እየተባሉ እስኪጠሩ አድርሷቸዋል። በሌላ በኩል ሃይማኖታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ በመገናኛ ብዙኃን ወጥተው የግላቸውን አመለካከት የሚያንጸባርቁና ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚያቀርቡ ሳይቀር በቤተክርስቲያን የመዓርግ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ ይታያል። የጀርመን ናዚዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የፈፀሟቸውን ዓለም የተጸየፈው ጭፍጨፋ እንደ መልካም ተሞክሮ የሚጠቅስ ሰው በአደባባይ ሀሳቡን ሲናገር ለማሳረጊያ “ግሩም ነው አባታችን መልአከ ምናምን” ይባልለታል። የመልአከ ምናምን መጠሪያና ክፋትን እየተነተኑ “ይፍቱኝ ይባርኩኝ” መባባል ዓላማው የቤተ ክርስቲያንን መዓርግ ለማኅበራዊ ተቀባይነት የማስገበር የተጠና (calculated) አሰራር ነው። ይህም የተሰጣቸውን የመዓርግ ስም ለሌላ ዓላማ መጠቀም (misuse) ነው። ይህ አካሄድ ሄዶ ሄዶ አገልጋዮችን ክብር የሚያሳጣና ምዕመናን የሚጥሉባቸውን አመኔታ (trust) የሚሸረሽር ይሆናል።
ማሳያ 4: ራስን በመዓርግ የመደለል ክፉ ልማድ
እውነተኛ አገልጋዮች የመዓርግ ስም የሚያገኙት የትምህርት ማረጋገጫቸው፣ የአገልግሎት ዝግጅታቸውና መንፈሳዊ ሕይወታቸው ታይቶ ነው። የመዓርግ ስም የሚሰጣቸውም በአገልግሎታቸው ከበፊቱ ይልቅ የበለጠ እንዲተጉ ለማድረግ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን የአብነት ትምህርት በሚገባ ሳይማሩ በመድረክ ላይ ባላቸው ታይታ ብቻ የመዓርግ ስም የሚያገኙ ግን “ብማርስ ከዚህ የተሻለ ምን አገኛለሁ?” ወደሚል ራስን የማታለል አዝማሚያ ይወሰዳሉ። ራሳቸውንም ብዙ ምስጢር ጠንቅቀው ከተማሩት ያስተካክላሉ። ተሳስታችኋል ሲባሉ እንኳን መታረም ውርደት ስለሚመስላቸው ልባቸውን እልከኛ ያደርጋሉ። በስነ-ምግባርም እንዲሁ ያስቸግራሉ። ከእነዚህም የተነሳ እውነተኛው አገልግሎት ይሰደባል።
ይህን ራስን በመዓርግ የመደለል ክፉ ልማድ ለማስረዳት የሚከተለውን እውነተኛ ታሪክ እንደ ማሳያ እንውሰድ። በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን መካከል አስተዳደራዊ አለመግባባት ይከሰታል። ይህን ችግር ለመፍታትም የሚመለከተው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሚራዷቸው አገልጋዮች አለመግባባት ወዳለባት አጥቢያ ይሄዳሉ። በነበረው ውይይት የደብሩ አስተዳዳሪ አስተሳሰብና የሊቀ ጳጳሱ ልዑካን ሀሳብ መጣጣም አልቻለም። በዚህ ሰዓት ሊቀ ጳጳሱ የተናገሩት ንግግር ማኅበረሰባችን ምን ያክል “የመዓርግ እስረኛ” መሆኑን የታዘብንበት ነበር። ሊቀ ጳጳሱ የካህኑን ክህነት “ማገዳቸውን” ለማሳወቅ እንዲህ አሉ “እስከ አስር ቆጥረን እስክንጨርስ ካልተስማማህ ከዛሬ ጀምሮ ‘አቶ’ ብየሃለሁ።” ክህነትን ‘አቶ’ ከመባልና ካለመባል ወይም ከስም በፊት የመዓርግ ዘባተሎ ከመዘርዘር ጋር የሚያገናኝ አስተሳሰብና አሰራር ራስን በመዓርግ የመደለል ክፉ ልማድ ማሳያና መገለጫ ሆኗል።
የመፍትሔ ሀሳቦች
መፍትሔ 1: የመዓርግ ስም ለሚገባው ብቻ ይሰጥ
ከሚስተዋሉት ችግሮች አንጻር የመዓርግ ስም አሰጣጥ ሂደትን በመፈተሽ ለሚገባው ብቻ ይሰጥ ዘንድ እናሳስባለን። የመዓርግ ስሞች ሲሰጡም አብረው የሚሰጡ መመሪያዎች (Terms and conditions) በግልጽ ሊታወቁ ይገባል። ከመዓርግ አልባ የመዓርግ ስሞች ጋር የተያያዘው ችግር ከቤተ ክርስቲያን ባሻገር በሀገራችን ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚታየው “የክብር ዶክትሬትን ለፖለቲካዊ ዓላማ፣ ለብሔርና መሰል ማኅበረሰባዊ ወገንተኝነት ማሳያ” የመጠቀም ልማድ ነፀብራቅ ነው። “በክብር ዶክትሬት” ስም የሚደረገውን አሳፋሪ እሽቅድምድም በቤተ ክርስቲያን ካለው “የመዓርግ ሽሚያ” ጋር በንፅፅር ካየነው የቤተ ክርስቲያኑ ቢከፋ እንጂ አይሻልም።
“የክብር ዶክትሬት” የሚሰጠው በታወቁ ዩኒቨርስቲዎች እንደሆነ ይታወቃል። የቤተ ክርስቲያን መዓርግ ግን አሁን ባለው ልማድ ምንም ተጠያቂነት በሌለው መልኩ በየአጥቢያው አስተዳዳሪዎች ጭምር ሲታደል እናስተውላለን። አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ከነችግሩም ቢሆን ተለይቶ የታወቀ “የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መመሪያ” አላቸው። በቤተ ክርስቲያን ግን የቀደመው ትውፊት በልማድ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። እርሱን የሚተካ ወይም የሚያፀና የታወቀ ሕግና ሥርዓትም የለም ማለት ይቻላል። የሥርዓት ቤት መሆን የነበረባት ቤተ ክርስቲያን ነገሮች በልብ ወደድ የሚደረጉባት ሆናለች። ስለሆነም የመዓርግ ስም ማን ይሰጣል? ለማን ይሰጣል? መመዘኛዎቹ ምን መሆን አለባቸው? አጠቃቀሙስ ምን መምሰል አለበት? የሚሉት ጉዳዮች ቢቻል በታወቀ ሥርዓት መመራት አለባቸው። ቢያንስ ግን ካህናትና ምዕመናንን ባሳተፈ መንገድ እንጂ የምንደኛ አለቆችና ጥቅመኛ ምዕመናን መነገጃ እንዳይሆን በአጥቢያ ደረጃም ቢሆን እየተመረመሩ ማለፍ አለባቸው እንላለን።
መፍትሔ 2: የመዓርግ ስም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ይዋል
የመዓርግ ስሞች ለተለየላቸው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ለማመልከት ብቻ እንዲውሉና ከተፈቀደው ውጭ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ በማታዝዛቸው ሥራዎች እንዳይውሉ ማድረግ ይገባል። አንድ ሰው “መጋቤ ሐዲስ” መባሉ ብቁ የማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ አያደርገውም። ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር ባልተገናኙ ጉዳዮች የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሱታፌ ማድረጋቸው የተገባ ነው፣ የሚያስነቅፍ ግብር እስካልተቀላቀለበት ድረስ። ይሁንና በእነዚህ መሰል ተሳትፎዎች የቤተ ክርስቲያንን መዓርግ መጠቀም “የራሳቸውን ሀሳብ በቤተ ክርስቲያን ልብስ ጠቅልለው እንደማቅረብ” ይቆጠራል። በግል ስማችሁ መጠራትን እንደ ስድብ የምትቆጥሩ ሁሉ “መምህር፣ ሊቅ፣ አባት ተብላችሁ አትጠሩ” ያለውን የጌታ ቃል አስቡ። ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻችሁን የመዓርግ ሰም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ አውሉት። ለሌላው የራሱ ሰዎች አሉት። እናንተም በከበረ አዕምሯችሁ ተሳተፉ። ነገር ግን ራሳችሁን ችላችሁ ቁሙ እንጂ ደካማ አስተሳሰብን በቤተ ክርስቲያን ስም አሽጋችሁ በማቅረብ በእናንተ ድክመት ቤተ ክርስቲያንን አታሰድቧት።
መፍትሔ 3: የመዓርግ ስምን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ይታረሙ
መዓርጋትን ከልክ ባለፈ ሁኔታ መጠቀም መዓርጋቱን መቀለጃ በማድረግ በተገቢው መልኩ መዓርጉን ለተቀበሉትና ለሚጠቀሙበትም ሊቃውንት አሳፋሪ ይሆናል። የቤተ ክርስቲያንን መሰረታዊ አስተምህሮ የማያውቅን ሰው “መጋቤ ብሉይ፣ መጋቤ ሐዲስ፣ ሊቀ ማእምራን ወዘተ” ብሎ መሰየምም ሆነ መጥራት በሚገባ መልኩ ለተሰየሙትና ለሚጠሩበት ሊቃውንት ስድብ ይመስላል። የመዓርግ ስም የሚሰጡ አባቶች በሀገረ ስብከታቸው ያሉትን አገልጋዮች በመከታተል የመዓርግ ስም ያለአግባብ የሚፈልጉ/የሚጠቀሙ ወይም የመዓርግ ስም ይዘው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሳይፈጽሙ ሲገኙ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል እንላለን። መዓርግ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ያለ አግባብ ሲጠቀሙበት የሚወሰድ መሆን አለበት። ለመዓርግ አሰጣጥ ሥርዓት እንዳለው (ሊኖረው እንደሚገባ) ሁሉ አጠቃቀሙም በሥርዓት መመራት አለበት።
መፍትሔ 4: በመዓርግ ስም ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ እናሳድግ
አስተሳሰቡ ያደገ፣ መጠየቅና መመለስ የሚችል ምዕመንና ካህን ያላት ቤተ ክርስቲያን ነፋስም ቢነፍስ፣ ዝናምም ቢዘንም ትጸናለች እንጂ አትናወጥም። በአንፃሩ ምዕመናንን እንደ ተከታይ እንጂ አዕምሮ እንዳለው ፍጥረት፣ መሪውንም መምሪያውንም መመርመር እንደሚችሉ የማይገነዘብ፣ አሠራሩንም አካሄዱንም በዚህ መልኩ የማይቃኝ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቤተ ክርስቲያንን በድቡሽት ላይ የሚተክል ሰነፍ ግንበኛን ይመስላል። ለጊዜው በድቡሽት ላይ የተመሠረተው ቤት ትልቅ መስሎ ሊታይ ቢችልም የመናፍቅነት ነፋስ፣ በዝናም የሚመሰል የምድር ኃያላን ፈተና በመጣ ጊዜ አወዳደቁ አያምርም። ስለሆነም በሌሎች የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ላይ እንደምናደርገው (ልናደርገው እንደሚገባው) ሁሉ የመዓርግ ስም ምንነት እና ለአገልግሎት ያለውን አጠቃቀም በሚመለከት የአገልጋዮችና የምዕመናንን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል እንላለን። ይህን ካደረግን የመዓርግ ስሞች እውነትም ባለ መዓርግ ይሆናሉ። በአንፃሩ ደግሞ በተለመደው ልማድ በመዓርጋት መነገድ ከቀጠልን በመዓርግ አልባ መዓርጋት ቤተ ክርስቲያንን እናሰድባለን።
አምላከ ሊቃውንት የቤተ ክርስቲያንን መዓርጋት ለሚገባቸው ብቻ በታወቀ ተገማች ሥርዓት ተጠቅመን ቤተ ክርሰቲያን በመዓርግ አልባ መዓርጋት እንዳይቀለድባት ማድረግ የምንችልበትን ጥበብ፣ ማስተዋልና መንፈሳዊነት ያድለን። አሜን።