ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ በእውነት ላይ ብዙ ጠላቶች ተነስተዋል። አስቀድሞ በዓለመ መላእክት በእውነት ላይ የተነሳው ጠላት ሳጥናኤል ነበር። ይህ ጠላት በራሱ ክህደት ምክንያት ከወደቀ በኋላ ለሰው ልጅ ውድቀትም ምክንያት ሆኗል። የሰው ልጅም በምድር ላይ ሲኖር ከእግዚአብሔር እውነት እንዲለይ የእውነት ጠላቶችን ሲያሰማራ ኖሯል። እነዚህም የእውነት ጠላቶች አስቀድሞ ከእግዚአብሔር የተላኩ ነቢያትን ይገድሉ ነበር። ኋላም የነቢያትን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ሰቅለው ገደሉ። የእርሱን ወንጌል ባስተማሩት ሐዋርያትና ክርስቲያኖች ላይም ሥጋዊ መከራን ሲያጸኑ፣ ትምህርታቸውንም ሲበርዙ ኖረዋል። ከጥንት እስከዛሬም የእውነት ጠላቶች ሆነው እውነትን ለማጥፋት ሲደክሙ ኖረዋል።
በዘመናችንም እነዚህ የእውነት ጠላቶች የሰው ልጅ በምድር ላይ በሰላም እንዳይኖር፣ የእውነትን መንገድ ተከትሎም ወደ ጽድቅ እንዳይደርስ የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ብቻ ሳይሆን የእርሱ ባለሟልም በመምሰል ጭምር እንቅፋት እየሆኑት ይገኛሉ። ራሳቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የማይገቡ፣ ሌላውንም የማያስገቡ፣ በአገልጋይነት ስም የመንግሥተ ሰማያትን በር የሚዘጉ እነዚህን የእውነት ጠላቶች ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱ ደቀ መዛሙርት ግብራቸውን በሚገልጹ ልዩ ልዩ መጠሪያዎች ጠርተዋቸዋል። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ምዕመናን የእውነት ጠላቶችን ከፍሬአቸው እንዲያውቋቸው የግብር መጠሪያዎቻቸውን እንዳስሳለን።
የእፉኝት ልጆች (Brood of Vipers)
የእውነት ጠላቶች እውነተኞችን የሚያሳድዱና የሚገድሉ የእፉኝት ልጆች ናቸው። እፉኝት ስትፀነስ አባቷን፣ ስትወለድ እናቷን፣ ስትነድፍ በመርዝዋ ሰውን የምትገድል ክፉ የምድር አውሬ ናት። የእውነት ጠላቶችም አስቀድሞ ነቢያትን ኋላም ሐዋርያትን የገደሉ ክፉዎች ናቸው። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ስለ እነዚህ ሲናገር “አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ፤ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ። ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው።” (መዝ 140:3) እንዳለው እነዚህ የእውነት ጠላቶች ከአንደበታቸው የሚወጣው የእፉኝት መርዝ ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ስለ እነዚህ የእውነት ጠላቶች ሲናገር “በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል፤ የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፤ መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም።” (ኢሳ 59:4-8) በማለት ግብራቸውን ገልፆታል።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።” (ማቴ 3:7) ብሏቸዋል።
ጌታችንም በትምህርቱ ስለ እነዚህ የእውነት ጠላቶች ሲናገር “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል። ” (ማቴ 12:34) በማለት በልባቸው የሞላውን የሚያውቅ አምላክ ማነታቸውን ነግሮናል።
እንዲሁም በተግሳጽ ትምህርቱ “እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።” (ማቴ 23:33) በማለት ስለእውነት ጠላቶች ተናግሯል።
እነዚህ የእውነት ጠላቶች እውነተኛ አገልጋዮችን ለመግደል የሚነድፉ እፉኝቶች ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በመላጥያ ደሴት ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ።” እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም። (ሐዋ 28:3) ዛሬም የምንታመንበት ጠባቂያችን እግዚአብሔር እውነተኛ አገልጋዮችን በእፉኝት ከተመሰሉ የእውነት ጠላቶች መርዝ ይጠብቃቸዋል።
እንዲሁም በመጽሐፍ “ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።” (ሮሜ 3:10-18) ተብሎ ስለ እነዚህ የእውነት ጠላቶችን ምንነት በጥልቀት ተጽፏል።
የዲያብሎስ ልጆች (Children of the devil)
የእውነት ጠላቶች ዲያብሎስ የዘራቸው የእርሱንም ሥራ የሚሠሩ የዲያብሎስ ልጆች ናቸው። መጽሐፍ በግልጥ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች የተገለጡ መሆናቸውን ያስረዳል። ጽድቅን የሚያደርጉና ወንድማቸውን የሚወዱ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ጽድቅን የማያደርጉና ወንድማቸውን የማይወዱ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደሉም። (1ኛ ዮሐ 3:10) እነዚህ የእውነት ጠላቶችና የዲያብሎስ ልጆች ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ዘመን ጠንቋዩ ኤልማስ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃውሟቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ እየተመለከተው “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን አለው።” (ሐዋ 13:10)። እነዚህም የእውነት ጠላቶች ግብራቸው እንደ ኤልማስ ነው።
ጌታችንም “መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” (ማቴ 13:38-42) እንዳለ በእንክርዳድ የተመሰሉ ዲያብሎስ የዘራቸው የዲያብሎስ ልጆች መጨረሻቸው እቶን እሳት ነው።
እነዚህ የእውነት ጠላቶች ፍላጎታቸው የአባታቸው የዲያብሎስን ምኞት መፈጸም እንደሆነ ጌታችን በግልጽ ነግሮናል። ይህንንም ለጻፎችና ፈሪሳውያን “…እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፣ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።” (ዮሐ 8:44) በማለት የእውነት ጠላቶች ዓላማ የአባታቸው የዲያብሎስን ምኞት መፈጸም እንደሆነ ነግሮናል። የዲያብሎስ ምኞት ደግሞ የታወቀ ነው።
አንገተ ደንዳኖች (Stiff-necked)
የእውነት ጠላቶች እውነትን ሳይሰሙ የሚቃወሙ አንገተ ደንዳኖች ናቸው። ቀዳሜ ሰማእት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለእውነት ጠላቶች ሲናገር: “እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።” (ሐዋ 7:51) በማለት እውነትን ለመስማት እንኳን የማይፈቅዱ አንገተ ደንዳና መሆናቸውን ተናግሯል።
አስቀድሞ እግዚአብሔር እስራኤል ዘሥጋ በሙሴ መሪነት በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ባሕር ከፍሎ፣ ጠላትን ገድሎ፣ ደመና እየጋረደ፣ መና እየመገበ ከግብፅ ባርነት ያወጣቸውን አምላክ ረስተው ከወርቅ ለተሠራው የጥጃ ምስል ሲሰግዱ በተመለከተ ጊዜ ሙሴን “እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። እንዳጠፋቸው ተወኝ፣ አንተን በሌላ ሕዝብ ላይ እሾምሀለሁ” ብሎት ነበር። (ዘጸ 32:9 33:3 33:5 34:9 ዘዳ 9:6 9:13) የዘመናችን የእውነት ጠላቶችም እንዲሁ ናቸው። የተደረገላቸውን ሁሉ ረስተው በእውነት ላይ በክፋት የሚነሱ፣ ለክፋታቸውም ለከት የሌላቸው ናቸው።
ልባቸው የታወረ መሪዎች (Blind guides)
የእውነት ጠላቶች ሰውን ወደ ሞት የሚመሩ ልባቸው የታወረ መሪዎች ናቸው። ጻፎችና ፈሪሳውያን ማንም በቤተ መቅደስ/በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ (በመባው) የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ይሉ ነበር። ጌታችን እነዚህ ዕውሮች መሪዎች “እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ (መባው) ነውን? ወይስ ወርቁን (መባውን) የቀደሰው ቤተ መቅደስ/መሠዊያው?” ሲል ጠይቋቸዋል። (ማቴ 23:16-19) እነዚህ የሥጋ ዓይናቸው ያይ፣ የሥጋ ጆሮአቸውም ይሰማ ነበር። የታወረውና የደነቆረው ልባቸው ነው። ከመቅደሱ ይልቅ ወርቁ ይበልጣል ማለታቸው ምን ያህል ልባቸው እንደታወረ ያሳያል። ከአገልግሎቱ ይልቅ የግል ጥቅማቸው ላይ አተኩረው የእግዚአብሔርን ሕዝብ በተሳሳተ መንገድ እየመሩ ነበር።
በዘመናችን ያሉ የእውነት ጠላቶችም እንዲሁ ናቸው። ጉዳያቸው መንፈሳዊ አገልግሎትና የምዕመናን ሕይወት ሳይሆን የራሳቸው ስምና ዝና/ታዋቂነት፣ የሚያገኙት ገንዘብ፣ የሚዘረጉት ትስስር (network) ነው። ስለዚህም ነው ትኩረታቸው ወንጌል ሳይሆን ገንዘብ፣ ግላዊ ክብርና የመሳሰለው ጊዜያዊ ጥቅም የሆነው። እነርሱ ይህንን ልብ ይዘው ለጥቃቅን ነገሮች ስለሚያስቡ ጌታችን “እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።” (ማቴ 23:24) በማለት ገስጿቸዋል።
የተለሰኑ መቃብሮች (Whitewashed tombs)
የእውነት ጠላቶች በውጭ የሚያምሩ በውስጥ ግን በሞትና ርኩሰት የተሞሉ የተለሰኑ መቃብሮች ናቸው። ጌታችን የእውነት ጠላቶችን “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።” (ማቴ 23:27-28) በማለት በተለሰኑ መቃብሮች መስሏቸዋል።
በተጨማሪም “ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ።… እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ። ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል።” (ሉቃ 11:44-49) በማለት ግብራቸውን ገልጦባቸዋል።
እንዲሁም “የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።” (ማቴ 23:29-31) በማለት የእውነት ጠላቶችን ትክክለኛ ማንነት ተናግሯል።
በዘመናችንም ለታይታ በሚጎተቱ ሕገ ወጥ ባለቀለም ቀሚሶችና ሀብሎች፣ ግብዝነትን በተሞሉ መዓርግ አልባ የመዓርግ ስሞች፣ ለይስሙላ በሚነገሩ የሽንገላ ንግግሮች ውጫቸውን አሳምረው በውስጣቸው ግን ፍጹም የእውነት ጠላቶች፣ ማስመሰልን እንደ ማሳያ ሊገልጹ የሚችሉ ሆነው ራሳቸውንም ምዕመናንንም ያሰናክላሉ።
ግብዞች (Hypocrites)
ግብዞች ያልሆኑትን በመምሰል የሚቀስጡ ናቸው። ለታይታ የሚጦሙ፣ ለታይታ የሚጸልዩ፣ ለታይታ የሚመጸውቱ (ማቴ 6:2፣5፣16)፣ በዓይናቸው ምሰሶ እያለ ከሰው ዓይን ትንኝን ለመጥራት የሚጥሩ (ማቴ 7:5)፣ እያዩ የማይመለከቱ እየሰሙ የማያስተውሉ (ማቴ 15:7)፣ የሰማዩን ፊት እንጂ የዘመኑን ምልክት የማይለዩ (ማቴ 16:3)፣ ዘወትር ሰውን በክፋት ለማጥመድ የሚደክሙ (ማቴ 22:18) ናቸው። ግብዞች የእውነት ጠላቶች ናቸው ስንል ክርስትናን በድራማ መልክ ቢተውኑትም የእውነት ስለማይኖሩት ግብራቸው የክፋት ብቻ ነው ማለታችን ነው። በሰው ፊት ጥሩ መምህር በልባቸው ግን የክፋት ሁሉ ማጠራቀሚያ ናቸው።
እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ የእውነት ጠላት ስለሆኑ ግብዞች ሲናገር “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።” (ማር 7:6) በማለት የግብዞች አምልኮ ከንቱ፣ ትምህርታቸውም የሰው ሥርዓት መሆኑን ተናግሯል። ወግና ባሕልን በመጠረቅ ለመልካም ሥራ እንቅፋት የሆኑትን የእውነት ጠላቶች ጌታችን ሲገስጻቸው “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? (ሉቃ 13:15)” በማለት በሰንበት መልካም ማድረግ እንደሚገባም አስተምሯል።
እነዚህን ግብዞች ጌታችን በተግሳጹ ሰባት ጊዜ “እናንተ ግብዞች:-ወዮላችሁ” በማለት በግብር ስማቸው በመጥራት ገስጿቸዋል። እነዚህ ግብዞች መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት የሚዘጉ፥ እነርሱ የማይገቡ የሚገቡትንም እንዳይገቡ መሰናክል የሚሆኑ ናቸው። (ማቴ 23:13) ግብዞች የተለያየ ምክንያት እየፈጠሩ የድሆችን ገንዘብ የሚበዘብዙ፥ ስለዚህ የባሰ ፍርድን የሚቀበሉ ናቸው። (ማቴ 23:14) ሀሳባቸውን የማይቀበለውን ለማሳመን በባሕርና በደረቅ የሚዞሩ፥ ባመነላቸውም ጊዜ ከእነርሱ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ የሚያደርጉ ናቸው። (ማቴ 23:15) ግብዞች ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ትተው በጥቃቅን ነገር ላይ በማተኮር የእግዚአብሔርን ሕዝብ በከንቱ የሚያደክሙ ናቸው። (ማቴ 23:23) በአጠቃላይ በውስጣቸው ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የሚያማምሩ፣ ረጃጅምና ደማቅ ቀሚስ በመልበስ፣ ቆብም በመድፋት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሚነግዱ ናቸው። (ማቴ 23:25)
ምንደኞች (Hirelings)
ምንደኞች ለጥቅማቸው እንጂ ለበጎች የማይገዳቸው ቅጥረኞች ናቸው። ጌታችንም በወንጌሉ “እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። (ዮሐ10:12)” በማለት የምንደኞችን እውነተኛ ማንነት አስረድቶናል። ምንደኞች እረኞች አይደሉም፣ የበጎች ባለቤቶችም አይደሉም። ምንደኞች ስለራሳቸው እንጂ ስለባጎቹ አይጨነቁም። ምንደኞች በጎቹን የሚፈልጓቸው ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለበጎች አስበው አይደለም። እነዚህ ራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያመልኩ ምንደኞች በእውነተኛ አገልጋዮች ስም ስለሚመጡና ለበጎች የሚያስቡ መስለው በጎቹን የሚስቡ ስለሆኑ የእውነት ጠላቶች ናቸው። እንዲህ አይነት ምንደኞች ለራሳቸው ጽድቅን የምይሠሩ ሌላው እንዲሠራ የማይፈቅዱ ይልቁንም የበጎችን ሕይወት አስይዘው ለጥቅማቸው ከተኩላ ጋር የሚደራደሩ የእውነት ጠላቶች ናቸው። ምንደኞች ምዕመናንን የሚፈልጓቸው ለገንዘብ ምንጭነት፣ ለእውቅናና ለሥልጣን፣ ለፖለቲካ ቁማር እና ለመደበቂያነት ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ስለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት አይገዳቸውም።
ማጠቃለያ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። (2ኛ ጢሞ 3:1-5)” እንዳለው በመጨረሻው ዘመን ይህ ሊሆን የግድ ነውና እኛም ከእውነት ጠላቶች ልንርቅ ከእውነት ጋርም ልንቆም ይገባል።
እነዚህ የእውነት ጠላቶች መጨረሻቸው ጥፋት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስተምር “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵ 3:18-19)” ብሏልና።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
LikeLike