“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ(ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጿማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሲሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር በዮሴፍ ቤት፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ዐሥራ አራት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ እንደሌሎቻችን ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ነሐሴ ፲፮ በልጇ ስልጣን ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ነገረ ፍልሰቷን እንዳስሳለን፡፡
“እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” (አይሁድ)
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድ “እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ከእነርሱም መካከል ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የአልጋውን አጎበር ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡
“ተንሥአት እሙታን፡ ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል/ እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሳች/” (ቅዱስ ኤፍሬም)
ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም በልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፣ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው ቀን ሙስና መቃብርን (የመቃብርን ሥልጣን) አጥፍቶ ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ (ከመ ትንሳኤ ወልዳ ) በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡
“አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!” (ድንግል ማርያም)
ይህ ቃል እመቤታችን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተናገረችው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት “አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡
“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” (ቅዱስ ቶማስ)
ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ ሲሰማ ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታችን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ሰበንም ሊቁ በመልክዓ ማርያም ድርሰቱ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡” እንዳለው ቅዱሳን ሐዋርያት ሞገሳቸውን እመቤታችንን ለመቅበር የገነዙበት ነበር፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምርሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፤ቅዱሳን ሐዋርያት ለበረከት ተካፍለውታልና፡፡
“ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” (ቅዱሳን ሐዋርያት)
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችንን ዕርገት ባየ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ይሰጣቸው (ዕርገቷን ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል፡፡
ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይሁን፡፡ (ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)
የእመቤታችንን የትንሣኤና የዕርገት ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡ በእመቤታችን የትንሣኤ በዓል ላይ “ተንሥአት እሙታን ማርያም ድንግል! ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል” ማለትም “ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ተነሣች! ይህውም ልዑል አምላክ ልጇ እንደተነሳው ትንሳኤ ነው!” የሚለውን የምስራች ቃል ምእመናን ይለዋወጣሉ። ይህ የደስታ መንፈስና ስርአት እንደልጇ ዘመነ ትንሳኤ እስከ ነሓሤ 21 ቀን ድረስ ይቀጥላል። የመልክአ ማርያም ደራሲም ‹‹ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ (እመቤቴ ማርያም ሆይ በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል)›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡
በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ ይነበባል (ሰዓሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት)፡፡
በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽህና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሰረት ነውና፡፡
በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም ሱባዔ ይገባሉ፡፡
በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በቤተክርስቲያናችን በፆመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከታወቁ የሕግ ምንጮች ከቅዱሳን አባቶቻችን በተማረችው መሰረት “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡
እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ ተስፋ እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ ጽንዕት በድንግልና፣ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፣ አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ መልክአ ማርያም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ