ምክንያተ ጽሕፈት
በዕለተ ሰንበት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን አንድ ቅን ካህን ከቅዳሴና ትምህርት በኋላ መልእክት ለማስተላለፍ ተነሱ። ካህኑ በሚያገለግሉበት ደብር ያለውን የገንዘብ እጥረት በሚመለከት ከተናገሩ በኋላ ሰበካ ጉባኤውንና የደብሩን ካህናት ለማሳሰብ እንዲህ አሉ “ሁሉም ደብር ገቢውን የሚያሳድገው ምዕመናን በቅዳሴ ጊዜ ስማቸው እንዲጠራ የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ነው።” የእኒህ ካህን ንግግር በዘመናችን ጸሎትን እንደሸቀጥ የማየት አስተሳሰብና ተግባር የወለደው ነው። በተለይም ነውር በሚንቆለጳጰስባቸው፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ከምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ስም ለሚገነቧቸው ገቢ ማስገኛ ፎቆችም ሆነ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኖች በሚጨነቁባቸው ቦታዎች የተጀመረና በብዛት እየተዛመተ የመጣ ወፍ ዘራሽ ልማድ ነው።
ከዚህም ጋር በሚመሳሰል መልኩ “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በማለት ከምዕመናን ገንዘብ ለመቀበል ጸሎትን መደለያ የሚያደርጉ አካላት ብዙዎች ናቸው። ይህ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምን ሲሞናዊ ልማድ በቅዱሳት መጻሕፍት የተወገዘ ነው። ይሁንና በጥቅም ሰንሰለት የተያዙ ወይም “ስንት ችግር እያለ ስለዚህ ለምን እንጨነቃለን?” በሚል ስንኩል አመክንዮ ይህን ክፉ ልማድ የሚያበረታቱ፣ በተዛባ አስተምህሮ የሚደግፉ፣ እንዲሁም በዝምታ የሚያልፉ ካህናትና መምህራን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በቅዳሴ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎችን “ስም ለማስጠራት” ስለሚከፈል ክፍያ፣ “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁንና መባችሁን ስጡን” ስለሚሉት ሰዎችና ከእነዚህ አዳዲስ ልማዶች የተነሳ ጸሎትን ለውዳሴ ከንቱ ማስገዛት የሚፈጥረውን የአስተምህሮ መፋለስና የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ድቀት እንዳስሳለን። ምዕመናንም እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ብቻ እንዲከተሉ ለማስገንዘብ እንሞክራለን።
ጸሎት የጽድቅ መሰላል ናት!
ጸሎት የእምነት መገለጫ፣ የልጅነት ማረጋገጫ፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝባትና ጸጋ እግዚአብሔር የሚገኝባት የጽድቅ መሰላል ናት። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ስለ ጸሎት ሲያስተምር “በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በአደባባይ ማዕዘን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና፣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ 6:5) በማለት የተናገረው ጸሎት ለታይታ መደረግ እንደሌለበት ያስረዳናል። ከቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጻሕፍት አንዱ ፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጸሎትን የሚጀምረው የጸሎትን መንፈሳዊ ትርጉም በግልፅ በማስቀመጥ ነው። “ጸሎትሰ ይእቲ ተናግሮተ ሰብእ ኀበ እግዚአብሔር ልዑል።/ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት።” (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14)
ጸሎት በግልም በማኅበርም (በኅብረትም) ሊፈጸም ይችላል። ከግል ጸሎት ይልቅ የማኅበር ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው። በኃጢአት የተመሰለ ቅጽረ ኢያሪኮን (የኢያሪኮን ግንብ) ያፈረሰው በእምነት የቀረበ የማኅበር ጸሎት ነው (መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 6)፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የከበረችበትን የበዓለ ጰራቅሊጦስ በረከት የተቀበሉት በኅብረት ጸሎታቸው ዝግጁ ሆነው በመጠበቃቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:14 እና 2:1-4)። ከማኅበር ጸሎቶች ሁሉ የከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምዕመናን የሚታደልበት ጸሎተ ቅዳሴ መሆኑን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያስረዳናል። ጸሎተ ቅዳሴ ዋነኛ ዓላማው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በስሙ ላመኑ ካህናትና ምዕመናን ለማደል ነው። ጸሎተ ቅዳሴ የማይነካው ጸሎት የለም ማለት ይቀላል። በጸሎተ ቅዳሴ ከሚጸለዩ ጸሎቶች አንዱ “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መብአ/ መባ ስለሚያስገቡ ሰዎች የሚጸለይ ጸሎት” ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ “መባ” የሚለው ቃል በልዩ ልዩ መልክ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምዕመናን የሚሰጧቸውን ንዋየ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ቁሳቁሶች ያጠቃልላል።
ትክክለኛ የመባ ጸሎት
በጸሎተ ቅዳሴ ንፍቁ ዲያቆን “ጸልዩ በእንተ እለ ያበውኡ መባአ” (መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ) በማለት ካህናትና ምዕመናን በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ መባ ስለሚሰጡ ሰዎች እግዚአብሔር መባቸውን ይቀበል ዘንድ እንዲጸልዩ ያሳስባል። ካህናትና ምዕመናንም በአንድነት “ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ” (የወንድሞችን መባ ተቀበል፣ የእህቶቻችንንም መባ ተቀበል፣ የእኛንም መባችንንና ቁርባናችንን ተቀበል) ብለው በዜማ ይጸልያሉ። በዚህም ጊዜ መባ ስለሚያገቡ ሁሉ በኅብረት፣ በአንድነት ይጸለይላቸዋል። በየስማቸው ለይቶ የሚያውቃቸው እግዚአብሔርም የጸሎቱን ፍሬ ያደርግላቸዋል። ለማንም በስም ተለይቶ የሚጸለይ ጸሎት አይደለም።
እንደ ንፍቁ ዲያቆን፣ ንፍቁ ካህንም በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ጸሎተ ቡራኬን በሚጸልዩበት ጊዜ “አምላካችን ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ዋጋቸውን ይከፍላቸው ዘንድ እጣንና ቍርባን ወይንና ሜሮን ዘይትም መጋረጃም የንባብ መጻሕፍቶችን የቤተ መቅደስንም ንዋያት በመስጠት የሚያገለግሉትንም ባርክ።” ይላሉ። በተጨማሪም ካህናት በሐዋርያት የመባ ጸሎት “ሁሉን የሚይዝ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን። ከሁሉ በላይ በምትሆን በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን መባ ስለሚያገቡ፣ መስዋዕቱን፣ ቀዳምያቱን፣ ከአሥር አንዱን የመታሰቢያ ምስጋና ብዙውንና ጥቂቱን የተሰወረውንና የተገለጠውን ይሰጡ ዘንድ ሲወዱ የሚሰጡት ከሌላቸው ላይ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ መንግስተ ሰማያትን ይሰጥ ዘንድ ለሁሉ በረከትን የሚያድልበት ስልጣን ገንዘቡ የሚሆን አምላካችን እግዚአብሔር።” በማለት ይጸልያሉ። በተመሳሳይ መልኩ በቅዳሴ ባስልዮስ ካህኑ “አቤቱ ይህን ቍርባን (መባ) ያመጡልህን ስለነርሱ ያቀረቡላቸውንም አስብ…ከነርሱ ዘንድ ላቀረቡትም ሁሉ በሰማይ ያለ ዋጋቸውን ስጣቸው ያንድ ልጅህ ትእዛዝ ይህ ነውና፣ ከጥንት ጀምሮ ያገለገሉህ ቅዱሳንህን እናስብ ዘንድ።” (ቅዳሴ ባስልዮስ ቁጥር 68-70)
በእነዚህና በመሳሰሉት የጸሎተ ቅዳሴ ክፍሎች መባ ስለሚያገቡ ሁሉ ይጸለያል እንጅ በስም ተለይቶ እንዲጸለይ የሚያዝ ሥርዓት የለም። ለቤተ ክርስቲያን መባ ማቅረብ ሁሉም ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመጣ ምዕመን የሚያደርገው (ሊያደርገው የሚገባ) ምግባር፣ ትሩፋት እንጂ “ስማቸው እንዲጠራ ለሚፈልጉ ሰዎች” ብቻ የሚተው አይደለም። መባ ማቅረብን “ስምን ለማስጠራት የሚከፈል ስጦታ” አስመስሎ የሚያቀርብ አሰራር ጌታችን በወንጌል “እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” (ማቴ 6:2) በማለት ያወገዘውን ግብር መድገም ይሆንብናል።
የማይገባ የመባ ጸሎት
የጸሎት ዓላማ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኘት እንጂ እወደድ ባይ “ስማቸው በሰዎች ፊት እንዲጠራላቸው” የሚፈልጉ ሰዎችን ፈቃድ መፈፀም አይደለም። “እንደ ግብዞች ለሰው ይታዩ ዘንድ” (ማቴ 6:5) የሚደረግ ጸሎትም ሆነ መባ የተወገዘ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸሎተ ቅዳሴና መሰል የማኅበር ጸሎቶች “ስማችሁ በጸሎት እንዲጠራ ይህንና ያንን ክፈሉ” የሚሉና ለዚያም ገንዘብ የሚተምኑ ካህናት እየታዩ ነው። ይህ ለጸሎት ገንዘብ የመተመን ክፉ ልማድ በሌሎች የእምነት ድርጅቶች የተለመደና ምንደኞች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እያስገቡት ያለ ዘመን አመጣሽ እንክርዳድ ነው።
ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይታ መታሰቢያ የምታደርግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩትን ነው። ንፍቁ ካህን በጸሎተ ቅዳሴ ጸሎተ ቡራኬን ሲጸልይ “አምላካችን ሆይ በቀናች ሃይማኖት ሆነው ያንቀላፉትንና ያረፉትን ያባቶቻችንንና የወንድሞቻችንን የእኅቶቻችንንም ነፍስ አሳርፍ።” ይላል። መጽሐፈ ቅዳሴም “እዚህ ላይ የሞቱትን ስም ያንሳ” ይላል። በሞተ ሥጋ የተለዩንን ወገኖቻችንን መታሰቢያ (ተዝካር) ስናደርግላቸው ካህኑ ስማቸውን ያነሳል። ስማቸው የሚነሳውም በሞተ ሥጋ ቢለዩም በክርስትና ኅብረት አንድ ላይ መሆናችንን ለማሳየት “መዋዕያነ ዓለም አንትሙ፣ ሰዓሉ ቅድመ ፈጣሪ/ዓለምን ያሸነፋችሁ (ከዚህ በኋላ ለዘለዓለም በሕይወት የምትኖሩ፣ ሞት የማያገኛችሁ) እናንተ ስለ እኛ ጸልዩ” እያልን በጸሎታቸው እንማጸናለን። በሕይወተ ሥጋ ላሉ ሰዎች ግን ስለ መባቸው በጸሎተ ቅዳሴ የኅብረት ጸሎት ይደረግላቸዋል እንጂ “ስማቸውን አንሱ” የሚል ሥርዓት የለንም።
መባ የሚያገቡትን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይቶ መጥራት በቆየው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያልነበረ የቅርብ ጊዜ ልማድ መሆኑን ከልምድም ከመጽሐፈ ቅዳሴ ንባብም መረዳት እንችላለን። ይህ ከሆነ ገንዘብ እየተመኑ “በጸሎት ስምን ማስጠራት” ምን አመክንዮአዊ መሰረት አለው? ይህን ልማድ የሚያስፋፉ ሰዎች ሊያነሷቸው ከሚችሉ መከራከሪያዎች አንዱ “መባ ስለሚያገቡ ሰዎች መጸለይ የሚገባ ከሆነ ስማቸው መጠራቱ ምን ችግር አለው?” የሚለው ነው። “የሚጠራውም ዓለማዊ ስማቸው ሳይሆን ስመ ክርስትናቸው ስለሆነ ለውዳሴ ከንቱ አያጋልጥም” ሊባል ይችላል። እውነትም ስመ ክርስትና ውዳሴ ከንቱን ይቀንሳል። ይሁንና በአንዳንድ ቦታዎች “እነ እገሌኮ ማሰቀደሻ እየከፈሉ ስማቸውን ያስጠራሉ” የሚል ሽንገላን የሚጠቀሙ አሉ። በግልፅም በስውርም መባ ስለሚያገቡት ሁሉ በአንድነት የሚጸለየውን ጸሎት አቃለው በልዩ ክፍያ ስም ለመጥራትም ለማስጠራትም የሚባክኑ ሰዎች “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መባአ/መባ ስለሚያገቡ ሰዎች የሚጸለየውን ጸሎት” ባለማወቅ ያቃልሉታል። እምነት እንደሌለው ሰው ሆነው ለራሳቸው ማጽናኛ በመፈለግ ከምዕመናን አንድነት ሳይታወቃቸው ይለያሉ።
ቤተ ክርስቲያንን መነገጃ አድርገው የሚያስቡ፣ አገልግሎቷም ግንብ መገንባትና የምንደኛ ካህናትንና ምዕመናንን የማይጠግብ ኪስ መሙላት የሚመስላቸው ሰዎች ከገንዘብ ስብሰባ ጋር የተገናኘ ማምታቻቸውን የሚሞግት ማንኛውንም አስተያየት መስማት እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። ስለሆነም ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑበትን “ወፍ ዘራሽ ልማድ” ለመከላከል (ትክክል ለማስመሰል) የማይሄዱበት ርቀት የለም። ለዚያ ሲሉ ቅዱስ ወንጌልን ያጣምማሉ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በልካቸው ይሰፋሉ፣ ውዳሴ ከንቱን ለገቢ ማስገኛ በሚል ያስፋፋሉ። ለማሳመኛ የሚነሱት ነጥቦች ግን ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ጋር በግልፅ ይጋጫሉ፣ አመክንዮአዊ መሠረታቸውም በጣም የደከመ ነው። ከሚቀርቡት ማሳመኛዎች የሚበዙት በራሳቸው አዲሱን ክፉ ልማድ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ለማደናገር በማሰብ ከሌሎች የተለየ አፈፃፀም ካላቸው የመባም ሆነ በችግር ላይ ላሉ ምዕመናን ከሚደረግ ጸሎት ጋር ያምታቱታል። ለዚህም ማሳያ እንዲሆነን የሚከተሉትን የሚገቡ ጸሎቶች ከገንዘብ መሰብሰቢያው ጸሎትን ሸቀጥ የማድረግ ልማድ ለይተን ለማሳየት እንሞክራለን።
መባ ለሚያገቡ ሰዎች መባውን በሚቀበለው ካህን የሚደረግላቸው ጸሎት
ለቤተ ክርስቲያን መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። መባ በመስጠታችንም ውዳሴና ሙገሳ መጠበቅ የለብንም። ምዕመናን ለቤተ እግዚአብሔር የሚሆነውን ልዩ ልዩ መባ በስውርም በግልፅም መስጠታቸው የሚገባ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የቆየ ክርስቲያናዊ ትውፊት መባ የሚሰጥ ሰው ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ መባውን በሚቀበለው ካህን ፊት በትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ እግዚአብሔር መባውን እንዲቀበልለት ይጸለይለታል። ያለ ከንቱ ውዳሴ በቅንነት የሚቀርብ መባ ኃጢአትን የሚያስተሰርይ፣ ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ጸጋ ከምታቀርበው ሰማያዊ አምሃ ከቅዱስ ቁርባን ጋር ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ ስለሆነ መባውን የሚሰጠው ምዕመን በካህኑ ጸሎት ተማጽኖ “አቡነ ዘበሰማያት” ይቀበላል/ይጸልያል። ይህ ጸሎት ምንም ከንቱ ውዳሴ የለበትም። የሚጸለየውም በግል ካህኑና መባ አቅራቢው ባሉበት እንጂ በአዋጅ፣ በጭብጨባ አይደለም። ስለሆነም ገንዘብ ተምነው “ስም ለማስጠራት” ከሚያደርጉት ክፉ ልማድ ጋር መምታታት የለበትም።
በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክህነትና የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት ከድለላና ምዕመናንን በማጭበርበር ገንዘብ ከመሰብሰብ “ችሎታ” ጋር የተምታታባቸው ብዙዎች ናቸው። “ጨረታ እናጫርታለን፣ በማነቃቃት ምዕመናን ገንዘብ እንዲሰጡ እናደርጋለን፣ ምርቃት እንመርቃለን” እያሉ በየዐውደ ምሕረቱ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ለተለያዩ በጎም ሆነ በግልፅ የማይታወቁ ዓላማዎች ገንዘብ መሰብሰብ የተለመደ ነው። ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በልግስና ቢሰጡ መልካም ነው። ይህንንም የሚያስተባብሩ ግልፅ አሰራርና ተጠያቂነት ያላቸው ካህናትም ሆኑ ምዕመናን መኖራቸው መደበኛ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያን አካላት ማገዝ እንደሚችሉ ይታወቃል። ይሁንና ምዕመናን ልዩ ልዩ መባ የሚሰጡት አምነውበት፣ ለጽድቅ በሚበጅ ግልፅ አሰራር እንጂ ኮሚሽን በሚቆረጥለት፣ የግለሰቦች “ገንዘብ የመሰብሰብ ጸጋ” እየተባለ ደርዝ የሌለው ከንቱ ውዳሴ በሚዘንብበት፣ “ምርቃት” በገንዘብ የሚሸጥ በሚመስልበት የአጭበርባሪዎች መንገድ አይደለም። መባ ስለሚያገቡ ሰዎች በካህን የሚደረግ ጸሎት ኢያቄምና ሐና የተወደደች ልጃቸውን ድንግል ማርያምን እንደ ስዕለታቸው ለቤተ መቅደስ በሰጡበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ያደረገውን ዓይነት ከንቱ ውዳሴ የሌለበት ጸሎት እንጂ “ለማነቃቃትና” ለማጭበርበር የሚግተለተል የአስመሳዮች የሽንገላ ምርቃት መሆን የለበትም። ስለሆነም ምዕመናን መባቸውን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ለማግኘት በቅንነት ሊሰጡ ይገባል እንጂ “ታዋቂ፣ ብዙ ተከታይ ያላቸው” በሚባሉ የዐውደ ምሕረት ደላሎችን ፊት የሽንገላ ውዳሴና ምርቃትን ሊናፍቁ አይገባም።
በልዩ ልዩ ችግር ላሉ ምዕመናን የሚደረግ ጸሎት
ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን እናት ናት። እናት ለልጆችዋ እንደምትጨነቅ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ ላሉ ልጆቿ ትጸልያለች። እናት ልጆቿን በእናትነት በሰጠቻቸው በቁልምጫ ስማቸው እንደምትጠራቸው ቤተ ክርስቲያንም በጸሎት የምታስባቸውን ልጆቿን በስመ ጥምቀታቸው (በክርስትና ስማቸው) እየጠራች በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ትጸልይላቸዋለች። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ሃይማኖቱ በታሠረ ጊዜ እንደጸለየችለት (ሐዋ 12:5)፣ ጸሎቷም ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ የቅዱስ ጴጥሮስን የእሥር ሰንሰለት የሚፈታ መልአክ እንደተላከለት ዛሬም በቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል፣ የተቸገሩትን ይረዳል። ነገር ግን የተቀደሰውን ጸሎት እንደ ሸቀጥ በገንዘብ መተመንና “በችግራችሁ ጊዜ ስማችሁን እየጠራን እንድንፀልይላችሁ ይህንና ያን ክፈሉ” እያሉ ማምታታት የቤተ ክርስቲያንን ቅን አገልግሎት ጥላሸት የሚቀባ ነውር እንጂ ሌላ ስም የለውም። ለተቸገረው ያለ ዋጋ የምትጸልይ እንጂ ጸሎትን መደራደሪያ የምታደርግ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን አልተቀበልንም።
በ2002 ዓ.ም. በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በወቅቱ አዲስ ከተቋቋመች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር ሲወያዩ የተናገሩት አባታዊ መልዕክት ከእውነተኛ አባቶቻችን የተቀበልናትን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የምታጸና ናት። ይቅርና በውጭ ሀገር በሀገር ቤትም ቢሆን አዲስ ደብር መትከል ከባድ የገንዘብ ወጭ እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ሰይጣንም በገንዘብ እጥረት እያሳበበ አብያተ ክርስቲያናትን ከሚያስተምሩት ወንጌል እንደሚለያቸው ከልምዳችን ተረድተናል። ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው አዲስ ደብር ለመትከል የሚፋጠኑ አገልጋዮችም ወደ አባታችን ቀርበው ለክርስትናና ለፍትሃት ምን ያክል ማስከፈል እንዳለባቸው ለማማከር ጠየቋቸው። አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሲመልሱ እንዲህ አሏቸው “አይ ልጆቼ! አሁን በዚህ ቦታ ክርስትና ከሚነሳና ፍትሃት ከሚያስደርስ ምዕመን ገንዘብን መሰብሰብ ትፈልጋላችሁ? ብንችልስ እኛ እየከፈልን የጠፋው ሁሉ እንዲመለስ፣ በሥጋ የተወለደው ሁሉ ድጋሚ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያለ ዋጋ እንዲወለድ፣ የሞቱት ምዕመናን ሁሉ በጸሎተ ፍትሃት እንዲታሰቡ ማድረግ አለብን።” አሏቸው። ይህም አባታዊ ትዕዛዝ ብዙዎችን አሳምኖ አቡነ ጴጥሮስ ይህን ትምህርት ባስተማሩበት ቦታ ገንዘብ ተምኖ “ይህን ካልከፈላችሁ ክርስትና ማስነሳት፣ ፍትሃት ማስፈታት አትችሉም” የሚል ሲሞናዊ እንዳይኖር፣ ቢኖርም እንዳያድግ አደረገ። ይህን መሰል መልካም ዘር በተዘራባት እርሻ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ጸሎትን በገንዘብ ተምኖ “የሚሸጥ”፣ ምዕመናንንም ሳይረዱት ከጽድቅ ጎዳና አውጥቶ በውዳሴ ከንቱ ጠልፎ የሚጥል እንክርዳድ ከየት መጣ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደተናገረው “ጠላት ሰው ይህን አደረገ”። (ማቴ. 13:28)
በረከት በማስመሰል አይገኝም!
“የክርስትና ስማችሁ በቅዳሴ እንዲጠራ መባ ስጡ” የሚሉት ሰዎች በምዕመናን ደካማ ጎን በመግባት የመባ ጸሎትንም ሲያሻሽሉ ታዝበናል። ከዚህም የተነሳ በአንዳንድ አጥቢያዎች “ስም ለማስጠራት የሚከፈለውን ዓመታዊ ወጭ” ከፍለው ስማቸውን በምድር እያስጠሩ ከሰማይ መዝገብ የሚያስፍቁ የዋሀን ይታያሉ። አንዳንዶቹም ከፍለው ያገኙት “ስምን የማስጠራት መብት” ምድራዊ ገንዘባቸውን የሚጠብቁበት መድኅን ይመስላቸዋል። ከላይ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ የመባ ጸሎት መባ ያቀረበውን ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አንድነት የሚደምር እንጂ ምድራዊ በረከትን የሚለምን አይደለም። ይሁንና የጸሎትን ይዘት ለጥቅማቸው የሚቀይሩ ሰዎች በፈጠሩት ልማድ ስማቸውን ለሚጠሩላቸው ባለጸጎች የሚፀልዩት መጤ ጸሎት “ቤታቸውን በበረከት ሙላላቸው፣ ባለጸግነታቸውን ጠብቅ” የሚል ይዘት ያለው ነው። እግዚአብሔር ቸር መጋቢ ነው። ለደሃውም ለባለጸጋውም ያለመከልከል የሚሰጥ የማያልቅበት ሰጭ ነው። መባ ለሚሰጡም በረከትን እንደሚሰጥ የታመነ ነው። ነገር ግን በማስመሰል ጸሎት ከንቱ ውዳሴ የሚፈልጉ ባለጸጎችን እንጂ እግዚአብሔርን ማታለል አይቻልም። በረከት በማስመሰል አይገኝምና።
መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም!
መባ ስለሰጡት ቤተ ክርስቲያን እንደምትጸልይ፣ ጸሎቱም ውዳሴ ከንቱን ከሚያመጣ ልማድ የተለየ መሆኑን አይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ “አባቶች በጸሎት እንዲያስቧችሁ ስመ ክርስትናችሁን አምጡ” የሚል ልማድ እየተስፋፋ ነው። ከላይ እንደተገለጠው ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት የከበረ ስጦታ የላትም። መባ ስለሚያገቡት ሁሉ የምታደርገው ጸሎትም በረከትን ያሰጣል። ምዕመናንንም የምታውቃቸው በስመ ጥምቀታቸው ስለሆነ መባ ስለሚያገቡት ለመጸለይ ስመ ክርስትናቸውን መያዝ ክርስቲያናዊ ትውፊት ነው። ይሁንና በጸሎት የሚነግዱ “አገልጋዮች” በማስመሰል የሚሄዱበት አካሄድ ምዕመናን እንዲጸለይላቸው መባ እንዲሰጡ በመገፋፋት የበረከትን በር ይዘጋል። በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ፣ በቤተ ክርስቲያንም ትውፊት መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ ጸሎት እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም። እንዲጸለይልኝ ብሎ መባ መስጠት “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ለመግዛት” በማሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።” ብሎ የረገመውን ሲሞን የተባለውን ጠንቋይ መምሰል ነው። (ሐዋ. 8:8-25)
ምዕመናን መባ በመስጠታችን የምንጠቀመው በእግዚአብሔር ፊት የቀና ልብ ይዘን ስንቀርብ እንጂ በስሌት አስተሳሰብ ጸሎትን በመባ ለመግዛት በሚያስብ ሲሞናዊ አካሄድ መሆን የለበትም። እንዲጸለይላችሁ “ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በሚል ማነቃቂያ ገንዘብ ከሚሰበስቡ ሰዎች እንኳ ምን ያህሉ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ ቃል የገቡትን ጸሎት እንደሚያደርጉ እግዚአብሔር ይወቅ! ይበልጥ የሚያሳዝነው በጎ ያደረጉ መስሏቸው ይህንን ልማድ ያስፋፉ ሰዎች ምዕመናንን እንደሚሸለቱ በጎች ለሚቀራመቱ ሀሰተኛ ካህናትና መምህራን አጋልጠው መስጠታቸው ነው። ዛሬ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑ፣ የማይራሩ ሰዎች ራሳቸውን “ሰባኬ ወንጌል፣ ባህታዊ፣ አጥማቂ፣ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጅ” እያሉ የሚጠሩና የሚያስጠሩ በየቦታው በምዕመናን ላይ የሚያደርሱትን በደል ማየት ያሳምማል። በሐሰተኞች ወይም አርቀው በማያዩ ቅን አገልጋዮች ጉትጎታ እንዲጸለይለት መባ መስጠትን የተለማመደ ምዕመን የጨካኞች መረብ ውስጥ መውደቁ የሚደነቅ አይደለም።
ማጠቃለያ
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። በቅንነት የምናቀርበውን መባችንን በምድር ካህናት፣ በሰማይ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይቀበሉናል። ቤተ ክርስቲያንም መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ትጸልያለች። ይሁንና መባ መስጠት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚደምረን፣ ከሚያርገው መሥዋዕተ እግዚአብሔር የሚያሳትፈን የትህትና አገልግሎት እንጂ በዘመናችን እየተለመደ እንደመጣው ክፉ ልማድ “በቅዳሴ ጊዜ ስማችንን ለማስጠራት” ወይም “አባቶች እንዲጸልዩልን” የምንሰጠው ቀብድ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መጻሕፍት ከምዕመናን መካከል በስም ተለይተው የሚጸለይላቸው በዕለቱ መታሰቢያ የሚደረግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩት ናቸው። ይህም የሚደረገው በሞተ ሥጋ ቢለዩንም በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ምዕመናን አንድነት ከሆነች ኦርቶዶክሳዊት ማኅበር እንዳልተለዩ ለማሳየት ነው። ከዚያ ባሻገር የተለየ ችግር የደረሰባቸውን ምዕመናን በክርስቲያናዊ ልማድ በጸሎት ስማቸውን እያነሱ ማሳሰብ ይገባል እንጂ ገንዘብ ተምኖ “ስማችሁ እንዲጠራ መባ ስጡ” ማለት የለየለት ክህደት ነው። ስለሆነም መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ በመስጠት ጸሎትን በገንዘብ በሚተምን ሲሞናዊ ክፋት መተባበር የለብንም። ጸሎት በገንዘብ አይሸጥምና።
ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ። አሜን።
ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።