ሰማያዊ ዜግነት: አገራችን በሰማይ ነው!

የእግዚአብሔር መንግሥት በሰማይ ናት፣ በዚህ ዓለም አይደለችም። የምንኖርባት መሬት ጊዜያዊ መቆያ ናት። ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው የእግዚአብሔር መንግሥት በሰማይ እንደሆነች በተደጋጋሚ ተናግሯል። አስቀድሞ ለኒቆዲሞስ “እውነት እልሀለሁ: እንደገና ካልተወለዳችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት አታዩም” (ዮሐ 3:3) ብሎታል። ይህም የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ለመሆን አዲስ መንፈሳዊ ማንነትን መያዝ እንደሚያስፈልግ ሲያስተምረው ነው። እንዲሁም ለደቀ መዛሙርቱም ስለ ጸሎት ሲያስተምራቸው ስትጸልዩ “መንግሥትህ ትምጣ” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ያስተማረው የእርሱ መንግሥት ከዚህ ዓለም ስላልሆነች ነው። በዚህ ዓለም ብትሆንማ ወዴት ትመጣለች!? ይህችም ዘላለማዊ መኖሪያችን በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር መንግሥት ስለሆነች ነው ‘መንግሥትህ ትምጣ’ ብለን የምንጸልየው (ማቴ 6:10)።

ጌታችን በጲላጦስ አደባባይ ለፍርድ በቀረበበት ሰዓትም ጲላጦስ ጌታችንን “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” ሲለው ጌታችን መልሶ:- “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ብሎታል (ዮሐ 18:35-36)። በእውነት የክርስቶስ መንግሥት በዚህ ዓለም አይደለችም፣ በእርሱ የምናምን እና የምንታመን ክርስቲያኖችም ከዚህ ዓለም አይደለንም።

አገራችን በሰማይ ነው!

ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን” (ፊልጵ 3:20) በማለት የጻፈውን መሠረት በማድረግ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች አ(ሀ)ገራችን በሰማይ መሆኑን አበክራ ታስተምራለች። ሰማያዊት አ(ሀ)ገራችን እግዚአብሔር ለዘለዓለም ነግሦ የሚኖርባት፣ ቅዱሳን በክብር የሚኖሩባት፣ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀችው መንግሥተ ሰማያት ናት። ክርስቲያኖች አገራችን በዚህ ዓለም አይደለም፣ ዜግነታችንም ሰማያዊ እንጂ ዓለማዊ አይደለም። “አገራችን” ብለን የምንጠራው በሰማያት ያለችውንና ዘወትር የምንናፍቃትን መንግሥተ ሰማያትን እንጂ በሞተ ሥጋ ስናርፍ የምትቀረውን፣ ክርስቶስ ሲመጣ የምታልፈውን፣ አንዳንዴም በሰዎች አለመስማማት ፈርሳ የምትሰራውን፣ በምድር ላይ ያለችውን ጊዜያዊ መኖሪያችንን አይደለም። ዜግነታችንም የሚቆጠረው በሰማይ ካሉ ቅዱሳን ጋር እንጂ በዚህ ዓለም ካሉ ዓለማውያን ጋር አይደለም። መንፈሳዊ መሻታችንም ስለ ሰማያዊቷ አገራችን እንጂ ስለምታልፈው ምድራዊ መኖሪያችን ሊሆን አይገባም።

ከተማችን በሰማይ ናት!

በክርስቶስ ለምናምን እንደፈቃዱም ለምንኖር ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ‘የእኛ’ የምንላት ከተማ የለችንም። ከተማችን በሰማይ ያለችው ኢየሩሳሌም ናት። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህች ከተማ ሲናገር “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፣ እርስዋም እናታችን ናት።” (ገላ 4:26) በማለት ገልጿታል። እኛ ክርስቲያኖች እናት የሆነች ከተማ በሰማይ አለችን። ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።” (ራእይ 21:1-2) በማለት ስለ ሰማያዊቷ ከተማችን ጽፏል። ይህች አዲስና ቅድስት ከተማ እያለችን በዓለም ብልጭልጭ ያጌጠች ምድራዊ ከተማን የምንናፍቅ ሊሆን አይገባም።

አባታችን አብርሃም በድንኳን እየኖረ ሰማያዊቷን ከተማ ይጠባበቅ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።” (ዕብ 11:8-10) ብሏል። የእኛም ተስፋችን ይህች እግዚአብሔር የሠራልንና የፈጠረልን ከተማ (ሰማያዊት ኢየሩሳሌም) ናት።

ዘላለማዊ ቤታችን በሰማይ ነው!

አገራችን በሰማይ፣ ከተማችን ሰማያዊት፣ ዜግነታችን ሰማያዊ የሆንን ክርስቲያኖች ዘላለማዊ ቤታችንም በሰማይ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና” (2 ቆሮ 5:1) ያለውን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ሁሉ በሰማይ ያለውን የዘላለም መኖሪያቸውን ተስፋ እንዲያደርጉ ታስተምራለች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል “ልባችሁ አይታወክ፣ በእግዚአብሔር እመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፣ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፣ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፣ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጀሁላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐ• 14:1-3) ብሏል። የተዘጋጀልን ዘላለማዊ ቤት በሰማይ ስላለን በምድር ላይ ለጊዜያዊ ማረፊያ ብዙ አንድከም። በተለይም ጊዜያዊ መኖሪያችን (ሀገርም ሆነ ከተማ) እንደ ጣዖት እያመለክን የምንገድልለት፣ የምንሰዋለት (“ሰ” ላልቶ ይነበብ) ከሆነ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “ሀሳባችን ምድራዊ፣ ክብራችን በነውራችን” (ፊልጵ 3:18-21) እያደረግን መሆኑን መረዳት አለብን። ስለሆነም ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እያለን ግንበኞች የሚሠሩት ፈራሽ ሕንፃ የሕይወታችን ግብ አይሁን።

ልባችን በሰማይ ነው!

ሰማያዊ ዜጋዎች የሆንን ክርስቲያኖች ልባችን ሀገራችን ባለችበት በሰማይ ነው። መዝገባችንንም በሰማያዊት ሀገራችን እናኑር፣ ገንዘባችንንም በሰማያዊው መዝገባችን እናጠራቅም። የእንግድነት ዘመናችንን ጨርሰን ወደ ሀገራችን ስንመለስ ይጠቅመናልና። ጌታችን በወንጌሉ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።” (ማቴ 6:19-21) እንዳለው ገንዘባችንና ልባችን በሰማያዊት ሀገራችን ይሁን! የእኛ ባልሆነው አገርና ከተማ መዝገብን ብናከማች ይጠፋል፣ ይሠረቃልም። ባልታሰበ ሰዓት ጥለነውም እንሄዳለን። ስለዚህ በዘላለማዊት አገራችን መዝገብን እናኑር።

የሰማያዊ ዜግነት መብትና ኃላፊነቶች

አገራችን በሰማይ ነው ስንል ዘላለማዊ መኖሪያችን መንግሥተ ሰማያት ናት፣ ዜግነታችንም ሰማያዊ ነው፣ አምላካችም እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። በዚህ ምድር ላይ አንድ ሰው የአንድ አገር ዜጋ ሲሆን ሊያከብራቸው የሚገቡ ሕግጋትና መመሪያዎች (laws and regulations) ይኖራሉ። እንደዜጋም የሚከበሩለት መብቶች (rights) እና የሚደረግለት ጥበቃ (protection) ይኖራል። እንዲሁም የሚጠበቅበት ኃላፊነቶች (responsibilities) ይኖራሉ። ዜግነቱን የሚያረገግጥ ማኅተም ያለው “መታወቂያም” ይኖረዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።” (ቆላ 3:2) እንዳለው የክርስቲያኖች ዜግነታች በሰማይ ስለሆነ ዜጋ በሆንባት በእግዚአብሔር መንግሥት እነዚህ ሁሉ አሉን።

የሰማያዊ ዜግነት መብቶች

ሰማያዊ ዜግነት ያለን ክርስቲያኖች የዜግነት ማኅተማችን በጥምቀት ያገኘነው የሥላሴ ልጅነታችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “አሁን እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ። (ኤፌ 1:13)” ብሏል። እንዲሁም “ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። (ገላ 4:7)” በማለት የልጅነት መብታችንን አስተምሮናል። ልጆችም ስለሆንን ከኃጢአት አርነት ወጥተን፣ ለእግዚአብሔርም ተገዝተን፥ የቅድስናን ፍሬ እናፈራለን፣ የዚህ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወታችን ነው። (ሮሜ 6:22) ሰማያዊ ዜግነት ስላለንም ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ነን እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደለንም። (ኤፌ 1:9) ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራን የእርሱን በጎነት እንድንናገር የተመረጥን ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየን ወገን ነን።፤ 1ኛ ጴጥ 2:9

የሰማያዊ ዜግነት ኃላፊነቶች

ከሰማያዊ ዜግነት ግዴታዎች አንዱ በሰማያዊው ንጉሥ በእግዚአብሔርን ማመንና ለእርሱም መታመን ነው። እግዚአብሔር ለሙሴ “አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ። (ዘዳ 7:9)” እንዳለው ለሰማያዊው ንጉሥ ካልታመንን ሰማያዊ ዜግነት አይኖረንም። ጌታችንም “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። (ማቴ 22:37)” ብሎ እንዳስተማረው አንዱ የሰማያዊ ዜግነት ግዴታ ለእርሱ መገዛት ነው። ለምድራዊ ዕውቀትና ለርካሽ ታዋቂነት እየተገዛን ሰማያዊ ዜግነት የለም።

ሁለተኛው የሰማያዊ ዜግነት ግዴታ ትዕዛዛቱን መጠበቅ ነው። ይህም የእግዚአብሔር ‘ሕገ መንግሥት’ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን። (1ኛ ዮሐ 3:22-24)” ብሎ እንዳስተማረው ሰማያዊ ዜግነታችን የሚጸናው እርሱን ስንወድና ትእዛቱን ስንጠብቅ ነው (ዮሐ 14:15)። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛም ልንወደው ይገባል (1ኛ ዮሐ 4:19)። ሰማያዊ ዜግነታችን እውን የሚሆነው ‘ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ’ እያሉ በከንፈር በማምለክ ሳይሆን እርሱ የሚለውን በማድረግ ነው (ሉቃ 6:46)። ትዕዛዛቱን እየሻርን፣ የገዛ ወገናችን ላይ ግፍ እየፈጸምን “ሰማያዊ ዜግነት አለን” ብንል ራሳችንን እናታላለን፣ እውነትም በእኛ ዘንድ የለችም።

ሦስተኛው የሰማያዊ ዜግነት ግዴታ መንፈሳዊ አገልግሎት መፈጸም ነው። ጌታችንየሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። (ዮሐ 12:26)” እንዳለው ሰማያዊ ዜግነት በደስታ እግዚአብሔርን ማገልገልን፣ በሐሤትም ወደ ፊቱ መግባትን ይጠይቃል። (መዝ 100:2)። ጌታችን “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። (ማቴ 5:16)” እንዳለው ሰማያዊ ዜግነት በመልካም ምግባር ለሌሎች አርአያ መሆንን ይጠይቃል። በመንፈሳዊነት ስም ፍጹም መለካዊነትን (ለምድራዊ ባለስልጣናት በማጎብደድ ከመንፈሳዊ ምግባር መራቆትን፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለምናጎበድድላቸው ባለስልጣናት መገበሪያ ማድረግን) እያራመድን ‘ሰማያዊ ዜጎች ነን’ ብንል ሰማያዊው ንጉሥ “አላውቃችሁም” ይለናል።

አራተኛው የሰማያዊ ዜግነት ግዴታ እምነትን መጠበቅና በእምነት መጽናት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ሲያስተምር “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። (1ኛ ጴጥ 3:15)” ብሏል። ቅዱስ ጳውሎስም “ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። (ቆላ 4:5-6)” በማለት እንደ ሰማያዊ ዜጋ የሚጠበቅብንን አስተምሮናል። ቅዱስ ያዕቆብም “ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት። (ያዕቆ 1:3)” በማለት ሰማያዊ ዜጎች ፈተና ሲደርስባቸው ማድረግ ስላለባቸው ነገር ጽፏል።

ሰማያዊ ዜጎች በዚህ ዓለም ግን መፃተኞች ነን

ሰማያዊ ዜግነት ያለን ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም እንግዶች መጻተኞችና ስደተኞች ነን። የእኛ ባልሆኑ ነገሮችም ልንጣላ አይገባም። ክቡር ዳዊት ስለዚህ ሲናገር “አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም። (1 ዜና መዋዕል 29:15)” በማለት ሰማያዊ ዜጎች በምድር ላይ መጻተኞች መሆናችንን ተናግሯል። ቅዱስ ጳውሎስም “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። (ዕብ 11:13-15)” በማለት ሰማያዊ ዜጎች ቅዱሳን በምድር ላይ መጻተኞች ሆነው ማሳለፋቸውን በሰፊው አስተምሯል። ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ። (1ኛ ጴጥ 2:11)” በማለት በምድር መጻተኞች ለነበሩ በሰማይ ዜጎች ለሆኑ ክርስቲያኖች አስተምሯል።

እንግዲህ ከሁለት አንዱን እንምረጥ! የምድራዊት ሀገር ዜጎች ሆነን፣ በምድራዊት ሀገር ኖረን፣ ለምድራዊት ሀገር ለመሞት ወይም ሰማያዊት ሀገርን ተስፋ አድርገን፣ በምድር ላይ መጻተኞች ሆነን፣ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ። ስለሰማያዊቷ ሀገር እየተናገሩ በምድራዊቷ ሀገር በተድላና ደስታ መኖር ክርስትና አይደለም። ምድራዊቷንና አላፊዋን ሀገር ዘላለማዊ አድርጎ ማቅረብም አታላይነት ነው። ስለሰማያዊት ሀገር የሚፈጸመውን መንፈሳዊ አገልግሎትም ለምድራዊ ዓላማ መጠቀምም እንዲሁ ግብዝነት ነው። ስለዚህ አገራችንና ዜግነታችን ከወዴት እንደሆነ እንለይ። በምድር ላይ ዜጎች ሆነን በሰማይ መጻተኞች ለመሆን ሳይሆን በምድር ላይ መጻተኞች ሆነን በሰማይ ዜጎች ለመሆን እንወስን። ለዚህም እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። በሰማያዊት ሀገር ከብረው የሚኖሩ ቅዱሳን ረድኤትና በረከትም ትጠብቀን። አሜን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s