ልብ ወለዳዊ ስብከት: ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው!

መግቢያ (ምክንያተ ጽሕፈት)

ሰባኪው በዘመኑ አገላለጽ ‘ታዋቂ’ ከሚባሉት መካከል አንዱ ነው። በአካልና በማኅበራዊ መገናኛዎች ይሰብካል። በስብከት መካከል እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያነሳቸው ታሪኮች ልብን የሚሰቅሉ፣ የሚማርኩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ ተወዳጅነትን አግኝቷል፣ ተከታይም አብዝቷል። በዚህም የተነሳ በብዙዎች ዘንድ “የኦርቶዶክስ ፈርጥ” ከሚባሉት አንዱ ሆኗል። የእዚህን ሰባኪ ትምህርቶችና ስብከቶች በቅርበት የሚከታተል አንድ ሰው ሰባኪው የሚተርካቸውን ታሪኮች ከምንጫቸው አግኝቶ ለማንበብ ሞከረ። አንዳንዶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ አገኛቸው፣ የተወሰኑትን ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት አገኛቸው። በቁጥር ጥቂት የማይባሉትን ግን ምንጭ አጣላቸው። ምናልባት የክርስቲያኖች እውነተኛ ታሪኮች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ጀመረ።

ነገሩ ግን ሌላ ሆኖ አገኘው። ሰባኪው ልብ ወለድ መጻሕፍትን እና በተለያዩ ድረ ገፆች የሚገኙ የፈጠራ ውጤቶችን ለታሪኮች ምንጭነት እየተጠቀመ እንደሆነ ፍንጭ አገኘ። ይህንንም በስፋት ለማየት ሲሞክር ጥቂት የማይባሉ የሰባኪው ታሪኮች የፈጠራና የልብ ወለድ ታሪኮች (fictional narratives) እንደሆኑ አረጋገጠ። በዚህም የተነሳ “ታዲያ የፈጠራና ልብ ወለዳዊ ታሪኮች ለስብከት ቢውሉ ችግሩ ምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ጠየቀ። አዎን “የሰባኪውን ትምህርት እስካሳመሩለትና የአድማጮቹን ልብ እስከሳቡለት ድረስ ምን ችግር አለው?” የሚለውን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ቢኖሩም “ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በግልፅ በታወቀ ተረት መመስረት ይገባል ወይ?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ልብ ወለዳዊና ሌሎች የፈጠራ ታሪኮችን ለስብከት ማዋል የሚያስከትላቸውን ችግሮች እንዳስሳለን።

ታሪክ እና ምሣሌ

በዚህች የአስተምህሮ ጦማር “ልብ ወለዳዊ ታሪክ” በሚል የተጠቀሱት የውሸት ታሪኮችና በብልሃት የተፈጠሩ ተረቶች እንጂ በግልፅ የታወቁ ምሣሌዎች (parables) አይደሉም። በምሣሌ ማስተማር የተገባ ነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚመሰክሩለት ነው። ምሣሌን ከአማናዊ ታሪክ ጋር ሆነ ብሎ ማምታታትና የልብ ወለዳዊ ስብከት፣ የውሸት ታሪክ መጠቅለያ (መሸፈኛ) ማድረግ ግን ነውር ነው፣ ኃጢአት ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት ምሣሌን ለማስተማር ሲጠቀሙ ምሣሌነቱ ታውቆ እንጂ በማምታታት አይደለምና። ስለሆነም ልብ ወለዳዊ ታሪክን ከምሣሌ ጋር ሆነ ብለው እያምታቱ “የጓደኛ ሌባ ቢያዩት ይስቅ፣ ባያዩት ይሰርቅ” እንደተባለ ውሸቱ ሲታወቅባቸው “ምሣሌ እኮ ነው!” የሚሉ ሳይታወቅ ሲቀር ግን እንደ እውነተኛ ታሪክ የሚያቀርቡ የሀሰት አከፋፋዮችን ልናውቃቸው፣ ልናውቅባቸው ይገባል።

በአጭር አገላለፅ ታሪክ ማለት በሆነ ዘመን የተፈጸመና የሚታወስ ክስተት ማለት ነው። ከታሪክ በጎውንም ክፉውንም መማር ይቻላል። በስብከትም ሆነ በሌላ መንገድ ታሪክን በመጠቀም በጎውን ለመድገምና ለማጽናት፣ ክፉውንም ለማራቅና እንዳይደገም ለማድረግ መስራት የተገባ ነው። ይህ የሚሆነው ግን እውነተኛ ታሪክን በብልሃት ከተፈጠረ ተረት ጋር በማምታታት መሆን የለበትም። ልብ ወለዳዊ የፈጠራ ታሪኮችን አብዝተው ከሚጠቀሙ “መምህራን” መካከል አንዳንዶቹ በየሚዲያው እየቀረቡ የለየለትን ጥንቁልናና የመተት አሰራር ወይም በብልሃት የተፈጠረ ተረት “የአባቶቻችን ታሪክ፣ የእውቀት ደረጃችን ማሳያ” እያሉ ሲያቀርቡት መስማት እየተለመደ መጥቷል። እንደ እውነተኛ ታሪክ ዘመን እየቆጠሩ፣ የታወቁ ስሞች እየጠሩ የሚያቀርቡትን ስብከትም ሆነ ዲስኩር በተመለከተ “ይሄ ነገር እውነተኛ ታሪክ ነው ወይስ ፈጠራ ነው?” ተብለው በየሚዲያው ሲጠየቁም ለማጭበርበር እንዲመቻቸው “ታሪክም፣ ልብ ወለድም ነው” የሚል ማፈር የሌለበት መልስ ይሰጣሉ። እኛ ግን ታሪክ ሌላ፣ ልብ ወለድ ሌላ፣ ምሣሌ ሌላ መሆኑን ልናስተውል ይገባል። የዚህች አስተህምሮ ጦማር ትኩረት ለእውነተኛ መምህራንና ምዕመናን ይህን ክፉ ልምምድ የሚለዩበትንና ከክፋት የሚርቁበትን አመክንዮ ማሳየት እንጂ የጥንቆላ ጠበቆች፣ የልብ ወለዳዊ ታሪክ አምራቾችን ንግግር እየተከተሉ “የአባቶቻችሁ ታሪክ ይህ አይደለም፣ ጥንቆላና ተረትም እውቀት አይደለም” በማለት ማረም አይደለም። ሁሉም የየራሱ አባት አለው: አባቴ የሚለውን መለየት፣ እውቀት የሚለውን መረዳት ለእያንዳንዱ የተተወ ነውና።

የፈጠራ ታሪኮችና መንፈሳዊ አስተምህሮ

በመንፈሳዊ ትምህርት ውስጥ እውነተኛ ታሪኮች (real narratives) ጉልህ ድርሻ አላቸው። እነዚህ ታሪኮች በእውነት የተፈጸሙና ምንጭ የሚጠቀስላቸው (factual) ናቸው። እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈሩ፣ በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ (አንዳንድ የፈጠራ ታሪኮችም በመጻሕፍት መልክ እንደተሰነዱ ልብ ይሏል)፣ እንዲሁም በገሀዱ ዓለም ባሉ የክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የተገለጡ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ታሪኮች ምንጫቸውን በተገቢው መንገድ ጠቅሶ፣ እውነተኝነታቸውን ለይቶ ለማስተማሪያነት መጠቀም ከሁሉም መምህራን ይጠበቃል። ከዚህ ውጭ ግን ከዓለም የተቃረሙ ወይም በሰዎች የተፈጠሩ ትርክቶችን ለመንፈሳዊ ትምህርት ማዋል መንፈሳዊነትን ይሸረሽራል።

የተፈጠሩ ታሪኮችንና በብልጣብልጥነት የተቀመሙ ሀሳዊ “ተዓምራትን” “ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ምዕመናን (አባቶች) የተናገሩት” በማለት፣ ወይም ጥያቄ እንዳይነሳ አስቀድሞ “ይህ የበቁት ብቻ የሚደርሱበት ምሥጢር ነው” በማለት ወይም “በዘመናዊ ዕውቀት ይህንን መረዳች አይቻልም” በማለት እውነት ያልሆኑና ያልተፈጸሙ ታሪኮችን እውነትና የተፈጸሙ አስመስሎ ማቅረብ ምዕመናንን ማታለል በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይም መቀለድ ነው። እንደዚህ ዓይነት የፈጠራ ታሪኮችም ዓላማቸው መንፈሳዊ አይደለም። ብዙውን ጊዜ በማጭበርበር መክበር ወይም ታዋቂ መሆንን ወይም የተወሰነ ወገንን ብቻ መጥቀምንና ሌላውን ማሳነስን ግብ ያደረጉ ናቸው። እነዚህ አይነት የልብ ወለድና ሌሎች የፈጠራ ታሪኮችና ተረቶች በእውነተኛው አስተምህሮ ውስጥ የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። ይህንንም የምንለው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

የልብ ወለድ ታሪኮች የሰው ልጅ ፈጠራዎች ናቸው

የልብ ወለድ ታሪኮችና የፈጠራ ትርክቶች የሰው ልጅ አእምሮ የፈጠራቸው እንጂ በእግዚአብሔር ኃይል በቅዱሳን ተራዳኢነት የተፈጸሙ አይደሉም። በዚህም የተነሳ የፈጠራቸው ሰው ይደነቅባቸው ካልሆነ በቀር እግዚአብሔር ሊከብርባቸውና ቸርነቱም ሊገለጥባቸው አይችልም፣ አልተፈጸሙምና። ስለዚህ በሐሰት የተፈበረኩም ይሁን የተኮረጁ የፈጠራ ታሪኮች እግዚአብሔር ስለማይከብርባቸው፣ የምዕመናንንም ሕይወት ስለማያንጹ ከቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሊርቁ ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ቤት የእውነት ዓምድ ነው” እንዳለ የእርሱን ቤት ለእውነተኛው አስተምህሮ ብቻ ልናደርግ ይገባናል።

ውሸት ኃጢአት ነው

ሁሉም ክርስቲያን ውሸት ኃጢአት መሆኑን ያውቃል ብለን እናምናለን። ነገር ግን በዚህ ዘመን በብዙዎች ዘንድ የታወቁ ውሸቶችን በልዩ ልዩ የሽንገላ ማሸጊያዎች እየጠቀለሉ ለትርፍ የሚነግዱባቸው ሲሞናውያን በቁጥርም በዓይነትም መጨመራቸውን አስተውለናልና ጀማሪን እንደማስተማር “ውሸት ኃጢአት መሆኑን” ማስታወስ ሳያስፈልግ አይቀርም። ስለሆነም “ለሀገር ፍቅር”፣ “ለገፅታ ግንባታ”፣ “አባቶችን ለማስከበር”፣ “ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና” ለመሳሰሉት በሚሉ መሸንገያዎች ተጀቡነው በእምነት ስም ከሚቀርቡ የውሸት ጥቅሎች ራሳችንን መለየት ይገባናል። ቅዱስ መጽሐፍ እንዳለ “ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፣ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።” (ምሣሌ 12:22) “በጥንት ዘመን የተደረገ ታሪክ ነው”፣ “አንድ አባት/እናት እንደ ነገሩኝ”፣ “ይህን የትም ተጽፎ አታገኙትም” በሚሉ ቃላት የተጠቀለሉ ታሪኮችን በመመርመር እውነቱን እውነትን ለሚፈልግ ሁሉ ማሳወቅ ይገባል።

የልብ ወለድ ታሪኮች እውነተኛ ታሪኮች አይደሉም

እውነተኛው መንፈሳዊ አስተምህሮ በተጨባጭ እውነት (fact) ላይ እንጂ በልብ ወለዳዊ ታሪክ (fiction) ወይም በሐሰት ትርክት (fake narrative) ላይ የተመሠረተ አይደለም። ስለዚህም ያልተፈጸሙ፣ ያልተደረጉ የልብ ወለድ ታሪኮችና ሌሎች የፈጠራ ታሪኮች ምንም ያህል የእውነተኛው ዓለም ነፀብራቅ ቢሆኑም ተጨባጭ እውነት አይደሉም። ስለዚህም ለመንፈሳዊ አስተምህሮ ሊውሉ አይገባም እንላለን። ለመንፈሳዊ አስተምህሮ የሚሆነው እውነተኛው ታሪክ እያለልን ስለምን ነፀብራቁን እንሻለን?!

የልብ ወለድ ታሪኮች ዓላማ መንፈሳዊ አይደለም

የልብ ወለድ ታሪኮችና የፈጠራ ትርክቶች (fake narratives) ተቀዳሚ ዓላማ መንፈሳዊ አይደለም። ብዙዎቹ ዓላማቸው የፈጠራቸው ሰው የወሰነላቸው ነው። እንግዲህ ለመንፈሳዊ ዓላማ ተብሎ ያልተዘጋጀን ነገር ለሌላ ዓላማ ማዋል ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ነገር ግን አንዳንድ ቀሳጥያን የልብ ወለድ ታሪኮችን በማሽሞንሞን እውነተኛ ታሪክ አስመስለው ያቀርባሉ። ዓላማቸውም ርካሽ ተወዳጅነትን ማትረፍ ነው። ሌሎችም ጥራዝ ነጠቅ የሆነ የሳይንስ ዕውቀትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በመቀላቀልና በማምታታት በአድማጮቻቸው ዘንድ “ባለምጡቅ አእምሮ” መስለው መታየት ነው። እንግዲህ እናስተውል! ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንመጣው እግዚአብሔርን ልናመልክና ቅዱሳኑን ልናከብር እንጂ አንዳንድ ግለሰቦችን ለማንገሥ አይደለም።

የፈጠራ ታሪክ ለመንፈሳዊ አስተምህሮ አይሆንም

ልብ ወለዳዊና የፈጠራ ትርክቶችን በመንፈሳዊው ዐውድ እውነተኛ ታሪክ አስመስሎ ማቅረብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ምክንያቱም ይዘታቸው የተሟላ ምሳሌነታቸውም አስተማሪ ያልሆኑ ናቸውና። በእውኑ የሰው ልጅ በገሀዱ ዓለም ያለን ሰው እንጂ በምናቡ ዓለም ያለን ገፀ ባሕርይ ምሳሌ ሊያደርግ ይችላልን?! ልብ ወለድ እንደ ምድራዊ የጥበብ ሥራ የራሱ ቦታ አለው። የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ግን የፈጠራ ሳይሆን የእውነት አውድ ነው። ይህ ማለት ግን መምህራንና ምዕመናን ልብ ወለድ ታሪኮችን አይጻፉ፣ አያንብቡ፣ አይመልከቱ ማለት አይደለም። የሚጠቅማቸውን ራሳቸው ያውቃሉ። እኛ እያልን ያለነው ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ልብ ወለዳዊ ድርሰትን ከመንፈሳዊ አስተምህሮ ጋር መቀላቀል አላዋቂነት፣ ድፍረትና ሰውንም መንፈስ ቅዱስንም መናቅ ነው።

መንፈሳዊ አስተምህሮን ‘ልብ ወለድ’ ያደርጋል

ልብ ወለድ ታሪኮችንና የፈጠራ ትርክቶችን ለመንፈሳዊ ትምህርት እንዳሉ መጠቀም አጠቃላዩን መንፈሳዊ ትምህርትን የሰው ልጅ ፈጠራ ያስመስሉታል። አድማጮችም የፈጠራ የሆነውን እና እውነተኛውን ታሪክ ለመለየት ይቸገራሉ። በዚህም የተናሳ እውነተኛው አስተምህሮ ሳይቀር እንደፈጠራ ታሪክ ሊቆጠር ይችላል። መምህራንም እንደ እውነተኛ መምህር ሳይሆን እንደ ልብወለድ ተራኪ (Artist) ሊታዩ ይችላሉ። መንፈሳዊ ሕይወትም የእውነት ሕይወት ሳይሆን የትወና ሕይወት ሊመስል ይችላል። ይህም አጠቃላዩን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዎች ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። እንዲህ አይነቱን አደጋ ለመከላከል አስቀድሞ ልብ ወለድ ታሪኮችና የፈጠራ ትርክቶች ከተጨባጭ እውነታ ጋር እንዳይቀላቀሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

እውነተኛ ታሪኮች እንዲረሱ ያደርጋል

ልብ ወለድ ታሪኮችንና የፈጠራ ትርክቶችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማስገባት ወይም የመንፈሳዊ ስብከት አካል አድርጎ ማቅረብ የምዕመናንን ሕይወት የሚያንጹ እውነተኛ ታሪኮች እንዲረሱ ያደርጋል። በቅዱሳን ገድላትና ድርሳናት፣ በስንክሳርና በመጽሐፈ መነኮሳት ጭምር ያሉ የብዙ ቅዱሳን ታሪኮች ቦታ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ሊቃውንትም ያመሰጠሯቸው ምሳሌዎች ይዘነጋሉ። በአንጻሩም የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት በቃላት ውበት የተከሸኑ ነገር ግን ውስጣቸው ከንቱ ከሆኑ የፈጠራ ትርክቶች ጋር የፉክክር መድረክ ያደርገዋል። ታዳጊ ወጣቶችም ከእውነተኛ ታሪኮች አስተማሪነት ይልቅ የፈጠራ ትርክቶች ውበት/ማራኪነት ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ አቅጣጫቸውን ያስታል። ይህም እየቆየ ሲሄድ የእምነቱን ስፍራ ፍልስፍና ይወርሰውና ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ያለው የቤተ ክርስቲያን እጣ ፈንታ ይደርሰናል።

ለሐሰትኛ ትምህርት በር ይከፍታል

ያልተፈጸመን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ ማቅረብ በራሱ የሐሰት አስተምህሮ ነው። በመንፈሳዊው ዐውደ ምሕረት ወይም የቤተ ክርስቲያን መምህር ሆኖ ይህንን ማድረግ እውነት የሚሰበክበትን መንፈሳዊ ዐውድ የሐሰት አስተምህሮን ማለማመድ ነው። በሐሰት የተጀመረ በክህደት እንደሚያልቅ ደግሞ የታወቀ ነው። ስለዚህ ‘ሰው አያውቀውም’ ወይም ‘አይጠይቅም’ ብሎ ከዓለም የተቃረመ የፈጠራ ታሪክን በእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ማቅረብ ድፍረት ነው። ሐሰትነቱ አይታወቅም ብሎም የሐሰት ትርክት ፈጥሮ እውነት አስመስሎ ማቅረብም ታላቅ ኃጢአት ነው። ስለሆነም ከዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ መቆጠብ ይገባል።

የሰባክያንን ተአማኒነት ያሳጣል

በሚታወቀው ያልታመነ ሰባኪ በማይታወቀው እንዴት ይታመናል? ነገር ለማሳመር ብለው የፈጠራ ታሪክን ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር ቀላቅለው የሚሸቅጡ “መምህራን” በአድማጮቻቸው ዘንድ ትዝብትን ብቻ ሳይሆን አለመታመንንም ያተርፋሉ። በሥጋዊ ፍለጋ በሚታወቀው ምድራዊ ተረት ያልታመነ በሥጋዊ ጥበብ ብቻ በማይታወቀው መንፈሳዊ አስተምህሮ እንዴት ሊታመን ይችላል?! ይህን ለማስረዳት አንድ እውነተኛ ገጠመኝ እንጥቀስ። በአንድ ወቅት አንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያስተምር “ታዋቂ” ወጣት ሰባኪ በዝርወት ዓለም የተወለዱ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን በሚያስተምርበት ወቅት በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ማስተማሪያ ተረትን ራሱ የፈፀመው ታሪክ አስመስሎ ሲያቀርብ ከጉባኤው ታዳሚዎች አንዱ ሰባኪው የሚተረከውን ታሪክ Google አድርጎ ይከታተለው ነበር። ታሪኩ (A barber’s story: does God exist?) የሚልና በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው። ወጣቱ ሰባኪ ግን የራሱን ጸጉርና ጺም እያሳየ፣ ጸጉሩን ሊቆረጥ ሄድኩበት የሚለውን የውበት ሳሎን አድራሻ ሳይቀር እየጠቀሰ Google ላይ ያለውን ታሪክ ያለማዛነፍ የራሱ ገጠመኝ እንደሆነ አድርጎ በሀሰት ተርኮ ጨረሰ። ወጣቱ ሰባኪ ታሪኩን የራሱ ለማስመሰል የሄደበት ርቀት ታዳሚውን በጣም አስገረመው። ይህ ታዳሚ ወጣቱን ሰባኪ “ከዚህ በኋላ ይህንን ሰው ማመን ይከብደኛል” ቢል ሊፈረድበት ይችላል? በሚታወቀው ያልታመነ ሰባኪ እንዴት በማይታወቀው ሊታመን ይችላል?!

የመፍትሔ ሀሳቦች

የክርስቲያን አእምሮ ታሪክን የሚጠብቅ ወይም ታሪክን የሚሠራ እንጂ የውሸት ታሪክን የሚፈጥር መሆን የለበትም። ወጣቱ ትውልድም ሥራ ፈጣሪነትን እንጂ ውሸት ፈጣሪነትን እንዳይማር ሁሉም ውሸትንና የፈጠራ ታሪኮችን ሊያወግዝ ይገባል። ከዚህ አንጻር የልብ ወለዳዊና የፈጠራ ታሪኮችን ከመከላከል አንጻር የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ መምህራንና ምዕመናን የየራሳቸው ድርሻ አላቸው።

የቤተ ክርስትያን አስተዳደር የመምህራን ስልጠና መምህራኑ ትምህርታቸውን ምንጭ በሚጠቀስለትና በተጨባጭ እውነታ ላይ እንዲመረኮዝ ማስቻል ይጠበቅበታል። እንዲሁም በቂ ክትትል በማድረግ ከዚህ የሚወጡት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለበት። ጥንቆላን እንደጥበብ፣ ኮከብ ቆጠራን እንደ ሳይንስ አድርገው የሚያቀርቡ፣ ውሸትን እየፈበረኩ አንዴ ‘ከሰማይ ወረደ’ ሌላ ጊዜ ‘ከምድር ፈለቀ’ እያሉ ምዕመናንን የሚያታልሉትን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይጠበቅበታል። እውነተኛውን ታሪክ አዛብተው የሚያቀርቡትንም እንዲሁ። ለገንዘብ ሲሉ ተራራን የሚበልጥ ውሸት በሚዲያ የሚያቀርቡትንም መገሰፅና የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። በመድረክና በሚዲያ “የቤተ ክርስቲያን መምህራን” ተብለው የመዓርግ ስም ደርድረው፣ በአለባበስ ተኩነስንሰው የተናገሩት የፈጠራና የውሸት ታሪክ የማይታረም ከሆነ የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት የቀልድና የቧልት መድረክ ያስመስለዋል፣ የምዕመናን እምነት ይሸረሸራል፣ ቤተ ክርስቲያንም በዓለማውያን ዘንድ ሳይቀር ትዝብት ውስጥ እንድትገባ ያደርጋታል፣ እያደረጋትም ይገኛል።

የቤተ ክርስቲያን መምህራን ትምህርታቸውን በተጨባጭ እውነታ ላይ ብቻ ማድረግ፣ ለሚጠቅሷቸው ታሪኮች ምንጫቸውን በሚገባ መመርመር፣ ማመሳከር፣ በግልፅ ማስቀመጥና የፈጠራ ታሪኮችን በመንፈሳዊው ዐውደ ምሕረት ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ከማኅበራዊ ሚዲያና ከዓለማዊ መጻሕፍት የሚቃረሙ ታሪኮችንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ማምጣት የለባቸውም። ተአማኒ ምንጭ የማይጠቀስላቸውንና ባለቤታቸው የማይታወቅ የውሸት ታሪኮች፣ የፈጠራ ትርክቶችን፣ ተረቶችንና ቀልዶችን በመድረክ ላይ ከማቅረብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። አንድ መምህር የተናገረው የፈጠራ/የውሸት ታሪክ የሁሉም መምህራን አገልግሎት ላይ ጥላ እንደሚያጠላ ሊታወቅ ይገባል። ስለዚህ ሌሎች መምህራንም ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ወንድማዊ ምክር መስጠትና ድርጊቱንም የሚፈፅሙ ሲገኙ ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል። ይህንን በማድረግ አርአያነታውን ማሳየት ይኖርባቸዋል።

ምዕመናንም ምንጭ ያልተጠቀሰለትና የፈጠራ የሚመስል ታሪክ ሲሰሙ የሚነገረውን ሁሉ ሰምቶ ዝም ከማለት ተላቀው የሰሙትን ና ያነበቡትን በእውነተኛው አስተምህሮ መነፅርነት መመርመር፣ መምህራኑንም የተናገሩትንና የፃፉትን ምንጭ እንዲያቀርቡ መጠየቅ፣ ተገቢውን ግብረ መልስም (feedback) መስጠት፣ እንዲሁም በየደረጃው ላለ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ቀልድ መስማት የሚያሳቅቅ እንጂ የሚያስቅ አለመሆኑንም ማስተዋል ይገባል። ሰባኪ ዐውደ ምሕረት ላይ ለሚያስተምረው ካልተጠየቀና ሁል ጊዜ ‘አሜን፣ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን” ብቻ የሚባል ከሆነ “አለመጠየቅን” ይለማመድና ራሱን የሁሉ ነገር አዋቂ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌን ያዳብራል። ስለዚህ መጠየቁ ጥቅሙ ለሚያስተምረውም ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ሁሉ ተደርጎ ተገቢው ምላሽ የማይገኝ ከሆነና የፈጠራ ታሪክ የሚቀጥል ከሆነ እውነታውን መግለጥና ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ከዚህ አይነት ቅሰጣ መጠበቅ ይገባቸዋል። ይህ በአንድ ልብ፣ በቅንነትና በመናበብ ሲከናወን የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የእውነት አውድ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል። የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር በፊቱ የሚያስፀይፈውን ውሸተኛ ከንፈር የምንለይበትን፣ ራሳችንንና ቤተ ክርስቲያናችንም ከዚህ ክፉ ልማድ መለየት የምንችልበትን ጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድለን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s