ጦርነትና ክርስትና: ስለ ሰላም ጸልዩ!

መግቢያ

ጦርነትና ክርስትናን የተመለከተ ጦማር በአስተምህሮ የጡመራ መድረካችን ለመጻፍ ካሰብን ቆየት ብለናል። ይሁንና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይሳካልን ቆየ። ከምክንያቶቹ ዋነኛው በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው አውዳሚ ጦርነትና በጦርነቱ ዙሪያ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ ግለሰቦችና ተቋማት ያራመዱትና እያራመዱት ያለው በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ የሚያሳፍር የጦርነት አታሞ መችነትና ከጣዖት አምልኮ ጋር የሚነፃፀር አርጤምሳዊ ክፋት በጦማር የሚሞገትበት ዐውድ፣ እንዲሁም ለመስማት የተዘጋጀ ተከታታይ (critical mass) የለም ብለን በመገንዘባችን ነው። ይሁንና በመጠበቅ ብዛት ያለችንን የሀሳብና የአመክንዮ ጥሪት በማዘግየት ለመስማት የተዘጋጀ ተከታታይ መጠበቅ ከተንሰራፋው ሀገራዊ እብደት አኳያ ምፅዓትን የመጠበቅ ያህል ስለራቀ “ከመተው መዘግየት” በሚል እሳቤ ይህችን ጦማር ልናጋራችሁ ወደድን።

በዚህ ጦማር ከተዳሰሱት ነጥቦች አንዳንዶቹ ባልተበረዘ አዕምሮ ለሚያነበው ሰው “አሁን ይሄ ምኑ ያከራክራልና በጦማር መግለፅ አስፈለገ?” ሊያስብሉ እንደሚችሉ እንረዳለን። ይሁንና የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት ጨምሮ ልዩ ልዩ የሀሳብ አደባባዮች (platforms for elevated discourse) በጦርነትና በቀል ስሜት እየተናጡ አብደው ያሳበዱበትን ሁኔታ በሚገባ ላስተዋለ ሰው “ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው፣ ሰው ከሀገር ይበልጣል፣ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው እንጂ ሀገር የለም፣ ሰዎች ሀገራትን ፈጠሩ እንጂ ሀገራት ሰውን አልፈጠሩም፣ እግዚአብሔርን እንጂ ሀገርን ማምለክ አይገባም፣ ማስራብ ኃጢአት ነው፣ እያስራቡ መጾም አስመሳይነት ነው፣ መዋሸት በደል ነው፣ በጦርነት ሰዎች ይሞታሉ፣ ከሰይጣን የሰው ልጆች ይሻላሉ” የሚሉና የመሳሰሉ ቀላል እውነታዎች ለብዙዎች የተወሳሰቡ መስለው በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲያከራክሩ ስላየን “ከ ሀ ሁ” ጀምሮ መነጋገር ይጠቅማል በሚል “ቀላል እውነታዎችንም” ማስታወስና ማብራራት ግድ እንደሆነ ይታያል። ስለዚህም በዚህች ጽሑፍ መሠረታዊውን አስተምህሮና ተጨባጭ እውነታን በማጣመር ጦርነት በክርስትና፣ በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሰውን የከፋ ጉዳት እንዳስሳለን።

ጦርነትና ቤተ ክርስቲያን

በምድር ላይ ያለችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ በተጋድሎ ላይ ናት። የክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወትም የተጋድሎ ሕይወት ነው። ይህ ተጋድሎ ግን ከሥጋና ደም (ከሰው ልጅ) ጋር ሳይሆን ከዲያብሎስና ከጨለማ ሠራዊቱ ጋር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።” (ኤፌ 6:11-12) እንዳለው ክርስቲያን የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ለብሶ ሲጋደል ይኖራል።

ይህ ተጋድሎ በሥጋ ፍላጎትና በነፍስ ፈቃድ መካከል ያለ ጦርነት ነው። ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?” (ያዕቆብ  4:1-2) ብሎ እንዳስተማረው ዋናው ተጋድሎአችን ከምኞቶቻችን ጋር ነው። እንዲሁም በእውነተኛው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና በሐሳውያን አስተምህሮ መካከል ያለ ተቃርኖ ነው። ይህ ዓይነቱ ተጋድሎ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በሰፊው የሚያተኩርበት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን” (2ኛ ቆሮ 10:3-4) እንዳለው ለዚህ የሚሆነው ሥጋዊ የጦር ዕቃ አይደለም፣ የእግዚአብሔር ዕውቀት እንጂ። እንዲሁም “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ።” (1ኛ ጢሞ 6:12) እንዳለው በመልካም መታመን የምንፈጽመው አገልግሎት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምድር ላይ ግን በመጨረሻው ዘመን “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ… ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና” (ማቴ 24:6-7) እንደተባለ በምድር ላይ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል፣ እየተካሄዱም ይገኛሉ። እነዚህ ጦርነቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱትና እያደረሱት ያለውን ጉዳትና የጦርነት አደጋ ሲደቀን የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ ግን በብዙዎች ዘንድ የግንዛቤ ችግርና የእይታ መደበላለቅ ይስተዋላል። ጦርነትም ቤተ ክርስቲያንን “የሚጠቅማት” የሚመስለው የማህበረሰብ ክፍል ስለሚስተዋል የጦርነትን ጉዳት ማስረዳት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ክፍሎች ጦርነት በቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሕልውና እና አገልግሎት ላይ የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች እና ጦርነትን ከማስቀረትና ከማስቆም አንጻር የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ምን መምሰል አለበት የሚለውን እንዳስሳለን።

ጦርነት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሳቸው ጉዳቶች

በምሥጢራዊ ትርጉሙ ‘ቤተ ክርስቲያን’ ስንል የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሕይወት፣ የክርስቲያኖችን ኅብረት/አንድነት፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና በውስጡ የሚፈጸመውን አገልግሎትና የቤተክርስቲያን ተቋማዊ ሕልውና ማለታችን መሆኑ ይታወቃል። ጦርነት እነዚህ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያደርሳል። ከዚህ ቀጥሎ ጦርነት በእያንዳንዱ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት እንመለከታለን።

ጦርነት የክርስቲያኖችን ሕይወት ያጠፋል፣ አካልን ያጎድላል ቤተሰብን ይበትናል፣ ኑሮንም ያመሰቃቅላል።

ከጦርነት የሚተርፍ ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የሕሊና ስብራት፣ መፈናቀል/ስደት እና የንብረት ውድመት ናቸው። በጦርነት የሚሳተፉ ወይም ጦርነት በሚካሄድበት አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም የዚህ ቀጥተኛ ሰለባ ናቸው። በጦርነት ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ የሚችሉ ወጣቶች ለሞት ይዳረጋሉ። ብዙዎችም የአካል ጉዳተኞች ይሆናሉ። ከአካል ጉዳት በተጨማሪም የሚደርስባቸው የሕሊና ስብራት እጅግ አስከፊ ነው። በጦርነት ቀጣና የሚኖሩ እናቶችና እህቶች አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ ሌሎችም አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል። ሕፃናትም በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ ግፍ በማየት አእምሮአቸው ከመጎዳቱ በተጨማሪ ያለወላጅ/አሳዳጊ ይቀራሉ። አረጋውያንም በጦርነቱ ከሚደርስባቸው ቀጥተኛ ጉዳት፣ ልጆቻቸውን በማጣታቸው በሐዘን ይሰቃያሉ፣ ያለረዳትም ይቀራሉ። በአጠቃላይ በጦርነት ምክንያት የምዕመናን ሕይወት ይጠፋል፣ አካል ይጎድላል፣ አእምሮ ይጎዳል፣ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት በእጅጉ ይመሰቃቀላል።

ጦርነት ባለበት ወጣቶችና ሕፃናት መንፈሳዊ ትምህርትን በሰንበት ትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ መልኩ መማር አይችሉም። ጎልማሶችም በማኅበራት ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል አይችሉም። አረጋውያንም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየተቀበሉ እግዚአብሔርን በመቅደሱ እያመሰግኑ መኖር አይችሉም። በዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነው የሰው ልጆች ሰብአዊ አካልና መንፈሳዊ ሕይወት ይታወካል። ይህም የቤተ ክርስቲያን መፍረስ ነው። እንግዲህ ጦርነት በተካሄደባቸው ሥፍራዎች ስንት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ፈርሰው ይሆን?!

ጦርነት የክርስቲያኖችን ኅብረት ይከፋፍላል፣ አንድነት ይንዳል፣ አብሮነትን ይሸረሽራል።

በጦርነት ምክንያት ‘ቤተ ክርስቲያን’ የተባለ የክርስቲያኖች ኅብረት/አንድነት ይፈርሳል። በተለይም በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚኖሩ ምእመናን እና ካህናት ለጦርነቱ ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ባላቸው አስተሳሰብና በሚደርስባቸው ቀጥተኛ አደጋ የተነሳ በተቃራኒ ጎራ ሲሰለፉ የቤተ ክርስቲያን አንድነትም ይናጋል። አንዱ ወገን ጦርነትን የሚደግፍ፣ ሌላው ጦርነትን የሚቃወም ሲሆን በቤተ ክርስቲያን መለያየት ይፈጠራል። አንዱ ወገን የጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ ሆኖ ሌላው ወገን ‘ደስታውን’ የሚገልፅ ሲሆን ‘አንዲት ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው በተግባር አይኖርም። ይህም እየባሰ ሲሄድ በአስተዳደር መከፋፈልንና በማኅበራዊ ሕይወትም መለያየትን ያስከትላል።

የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ ልጆች ከጦርነት ጋር በተያያዘ ጠርዝና ጠርዝ ላይ ሆነው አንዱ ወገን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት “ግፋ በለው!” የሚል ከሆነ፣ በጦርነቱም ወቅት “ከሠራዊቴ ጎን እቆማለሁ” የሚል ከሆነ፣ ያሸነፈ ሲመስለውም “ንሴብሖ” እያለ የሚዘምር ከሆነ ‘ቤተ ክርስቲያን’ የተባለች የክርስቲያኖች ኅብረት ትፈርሳለች። ለጦርነቱ ሃይማኖታዊ ሽፋን ወይም ለግብአትነት የሚውል ድጋፍን በማድረግም በተቃራኒ የሚቆሙ ከሆነ የኅብረታቸው መሠረቱ ይናዳል። በጦርነት ዳፋ ለተጎዱ ወገኖችም ለይተን የምንጮህ ወይም ለይተን የምንደግፍ ከሆነ እንዴት ክርስቲያናዊ ኅብረታችን ሊቀጥል ይችላል?!

ጦርነት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈርስ፣ ንዋያተ ቅድሳት እንዲጎዱ/እንዲዘረፉ፣ አገልግሎት እንዲታጠፍ፣ የቤተ ክርስቲያን ደጆች እንዲዘጉ ያደርጋል።

ጦርነት ባለበት አካባቢ በካህናትና በምዕመናን ላይ በሚደርሰው ሞትና ጉዳት የተነሳ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ይቋረጣል። ብዙ ጥንታውያን ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች ተመተው የመፍረስ አደጋ ይጋረጥባቸዋል። በውስጣቸው ያሉ ጥንታውያን ቅርሶችና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ነዋየ ቅድሳትም ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ይዘረፋሉም። እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የተባለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አደጋ ይደርስበታል፣ በውስጡ ያለው መንፈሳዊ አገልግሎትም ይቋረጣል። የቤተ ክርስቲያን ደጆችም ይዘጋሉ።

በጦርነት ጊዜ ብዙ ምዕመናንና ካህናት መተኪያ የሌላትን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከአጥቢያቸውና ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ። ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርስባቸው ብዙ ገዳማትና አድባራት ይዘጋሉ፣ አገልግሎቶቻቸውም ይታጠፋሉ። ምእመናኑም በሄዱበት ለከፋ ችግር ተዳርገው ለሌሎች ይተርፉ የነበሩት የሰው እጅ ጠባቂ ይሆናሉ። በዕድሜ የገፉ አባቶችም በሚገጥማቸው የጤና ችግር በቀላሉ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ በጦርነት ምክንያት የሚመጣ የቤተ ክርስቲያን ጥፋት ነው። ለእዚህ ሁሉ ምክንያት የሚሆን ጦርነትን የሚደግፍ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት የሚመኝ ጠላት ብቻ ነው።

በጦርነት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ቀጥተኛ የጦርነቱ ዒላማ የምትሆንባቸው ጊዜያትም አሉ። ይህም በጦርነቱ ከሚሳተፉት አካላት አንደኛው ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት በሚፈርጅበት ወቅት ነው። የዚህ መነሻም ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ገለልተኛ አይደለችም (ከጠላት ጋር ተሰልፋለች) ብሎ ሲያስብ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ፀረ-ቤተ ክርስቲያን የሆነ ሃይማኖታዊ ዓላማ ያላቸው ተዋጊ ኃይሎችም ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያኖችን የጦርነት ዒላማቸው ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ ቤተ ክርስቲያን ላይ ቀጥተኛና ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባታል።

ጦርነት የቤተ ክርስያን ተቋማዊ ሚና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ፣ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ሕልውና ፈተና ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል።

ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም ሰላምን በመስበክ ጦርነትን ከማስቀረት አንጻር ጉልህ ድርሻ አላት። በዚህም ገለልተኝነቷን ጠብቃ የሀሳብ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የበኩሏን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባታል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የሀሳብ ልዩነቶች ወደ ጦርነት ካመሩ ቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ ያልሆነ የኃይል መንገድን በግልጽ ማውገዝ ይጠበቅባታል። ወደ ለየለት ጦርነት ከተገባ በኋላም ቢሆን ቤተክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም ገለልተኝነቷን ጠብቃ የሚዋጉት አካላት ጦርነቱን አቁመው ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የተለየ ተግባራዊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል። ጦርነትም ቢሆን የራሱ ሕግ ስላለው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ያለ ልዩነት ማውገዝና የተጎዱ ወገኖችን ያለ አድልኦ መርዳት ይጠበቅባታል። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ፍትህ እንዲሰፍን እና እውነተኛ እርቅ እንዲደረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል።

ነገር ግን በውጫዊ ጫናም፣ በውስጣዊ ወገንተኝነት፣ በቸልተኝነት ወይም በአስተዳደር ድክመት እነዚህን አለማድረግ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም ያላትን መንፈሳዊ ሚና ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። ለአንድ መንፈሳዊ ተቋም ለሰላም ዘብ በመቆምና ጦርነትን በማውገዝ የሰውን ልጅ መከራ ለማስቀረት በቂ አስተዋጽኦ አለማበርከት መንፈሳዊ ኃላፊነትን መርሳት ነው። ከዚህ አልፎ ገለልተኝነትን ሳይጠብቁ ከአንዱ ጋር መወገን ደግሞ ከመንፈሳዊነት ዐውድ ጨርሶ መውጣት ነው። እንዲሁም ለጦርነት ሃይማኖታዊ ሽፋን መስጠት በጦርነት መተባበር ነው። ይህም የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊና መንፈሳዊ ዓላማ ከማስቀጠል አንጻር የማይሻር ጠባሳ ይኖረዋል። በዚህም የመንፈሳዊያን ተቋማት የሕልውና መሠረታቸው (መሠረታዊ ዓላማቸው) ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

ጦርነት በመንፈሳዊ አገልጋይነት ስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አስመሳዮችን እውነተኛ ማንነትና ዋና ዓላማቸውን ያጋልጣል

በጦርነት ሂደት ውስጥ የሚጋለጡና የተጋለጡ ድብቅ ማንነቶችና ዓላማዎች አሉ፣ ይኖራሉም። በተለይም በቤተ ክርስቲያን በተለያዩ መዋቅሮችና በመንፈሳዊያን ማኅበራት ውስጥ የመሪነት ድርሻ ያላቸው፣ ወይም በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ጉልህ የሚባል ድርሻ ያላቸው አገልጋዮች በጦርነት ወቅት ለሰላም ዘብ ከመቆም ይልቅ በተቃራኒው ከአንዱ ጎራ ተሰልፈው ለጦርነት ቀስቃሽ፣ አዝማች፣ ድጋፍ አሰባሳቢ እንዲሁም ለጦርነቱ ዋና ተከራካሪ ሆነው ሲቀርቡ እውነተኛ ማነታቸው ይጋለጣል። ከዚህም አልፈው ‘እርቅ ይደረግ’ የሚሉ የዋሀን ወገኖችን የሚያሸማቅቁ፣ ለጦርነት የዳረገው ችግር ‘በድርድር ይፈታ’ ብለው የሚወተውቱትንም በመቃወም አንዱ ወገን እስከወዲያኛው መጥፋት አለበት ብለው ሲቀርቡ እውነተኛ ማነታቸው ይጋለጣል። “ጸልዩ በእንተ ሰላም” ብለው የቀደሱ፣ “አትግደል” የሚለውን ትዕዛዝ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሲሰሙ ያደጉ፣ “ቢቻላችሁ ከሰዎች ጋር ሁሉ በሰላም ኑሩ” ብለው የሰበኩ፣ ገዳማትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን ሲደግፉ የነበሩ፣ ብዙ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ያሳተሙ “አገልጋዮች” የጦርነት አታሞ መቺ ሆነው ከማየት በላይ የሚያሳዝን ነገር የለም።

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተብለው የተቋቋሙ መንፈሳዊ ማኅበራት፣ ለወንጌል አገልግሎት ተብለው በምዕመናን ገንዘብ የተመሠረቱና ሃይማኖታዊ ስምን የያዙ መገናኛ ብዙኃን፣ የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለው እንዲያስተምሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ካህናት፣ መምህራንና ሰባኪያነ ወንጌል፣ እንዲሁም በምዕመናን ዘንድ በመንፈሳዊ አገልጋይነታቸው የሚታወቁ ወንድሞችና እህቶች በአንድም በሌላም ምክንያት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጦርነትን መንገድ ልክ እንደ ሰላም መንገድ በድፍረት ሲሰብኩት መስማት ልብን ይሰብራል። “በመስቀሉ ሰላም አደለ” የሚለውን ወደ ጎን ትተው መስቀል ይዘው በገዛ ወገናቸው ላይ የሚፈፀምን የጦርነትን መንገድ የሚተነትኑትን ማየት በእውነት ኅሊናን ይጎዳል። እነዚህ ሁሉ እንግዲህ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱ የጦርነት ሰባኪያን ናቸው። የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩና መጻሕፍትን እየጠቀሱ አንድን ፖለቲካዊ አመለካከት የሚያመልኩና ሌላውም የአምልኳቸው ተሳታፊ እንዲሆን የሚተጉ ናቸው። ከሁሉ የከፋው ደግሞ የእነዚህ ቅስቀሳ የሚሰማና የሚከተል መብዛቱና አንድ እንኳን “ተው ይህ የጥፋት መንገድ ነው” ብሎ የሚገስፅ መጥፋቱ ነው።

የእነዚህ ባለድብቅ ዓላማዎች መጋለጥ ለጊዜው ሕመም ቢፈጥርም ለዘላቂ የምዕመናን መንፈሳዊነት ግን ታላቅ እረፍት ነው። ምክንያቱም ምዕመናን እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት በድብቅ ማንነት ያስተማሩትን ከዚህ በኋላም በድፍረት የሚያስተምሩትን “ራሳቸውን ሳያስተምሩ እንዴት ሌላውን ያስተምራሉ?” ብለው ከሀሰተኞች ራሳቸውን መለየት ይችላሉ። አዎን መግደል ትልቁ ኃጢአት መሆኑን ሲያስተምሩ ኖረው ጦርነትን የሚደግፉ ከሆነ፣ የተራበን አብሉ ሲሉ ኖረው ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ የሚቆጥሩ ከሆነ በእውነትም ራሳቸውን አላስተማሩም። መቼም ቢሆን ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ እንደማያፈራ ይታወቃልና። ኅሊናቸው ስለሚወቅሳቸውም በይሉኝታ፣ በማታለልና በማስገደድ ብዙዎችን የሰይጣናዊ አስተሳሰባቸው ተጋሪ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር መረዳት አይከብድም። ሱሰኛ ሰው ብቻውን ሱሰኛ መባል ስለማይፈልግ የዋሀንን በማስመሰል እንደሚያጠምድ፣ እነርሱም ይህንኑ ለማድረግ “በደረቅና በባሕር ይጓዛሉ”። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ከእነዚህ የክፋት አዝማቾችና ደቀ መዛሙርት በግልፅ እስካለየች ድረስ “የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የነበሩ ያደረጉት” እየተባለ የመጥፎ አርአያ ሆነው በኅሊናም በታሪክም ሲያስወቅሷት ይኖራሉ

ጦርነት ለወንጌል፣ ሰላምና ለፍትሕ የቆሙ እውነተኛ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናንን ጽናት ይገልጣል

በሌላ በኩል በጦርነት ውስጥ የእውነተኞች ጽናት ይገለጣል። ለሰላም ጠበቃ ከመሆን አንጻር፣ ከእውነት ጋርና ለእውነት ብቻ ከመቆም አንጻር፣ የኃይል መንገድን ፈፅሞ ከማውገዝ አንጻር፣ የተጎዱ ወገኖችን ሳያዳሉ ከመርዳት አንጻር፣ እርቅን ከመፈጸምና ፍትህን ከማስፈን አንጻር የእውነተኞች ጽናት እንደ ወርቅ ተፈትኖ የሚያልፍበት ነው። የጳጳሳትና የካህናት አባቶች እውነተኛ ኖላዊነት ተፈትኖ የሚታይበት ነው። በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ግፍ የሚያወግዙ፣ ለእውነት ብቻ የሚቆሙ አባቶች በዚህ ወቅት ከመለካውያን በግልፅ ተለይተው ይታወቃሉ። የምዕመናንም ሕይወት እንዲሁ በፈተና ውስጥ አልፎ በጽናት የሚታይበት ነው። ለሰው ይምሰል ብለው ሳይሆን በእውነት፣ ለእውነት የሚቆሙትን እግዚአብሔር ያያቸዋል፣ እንደ ደጉ ሳምራዊም ይባርካቸዋል። ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ሲጠፉ እነዚህ ግን ጽድቅን ይጎናጸፋሉ።

ከጦነት በፊት፣ በጦርነት ጊዜና ከጦርነት በኋላ ከክርስቲያኖች ምን ይጠበቃል?

ከጦርነት በፊት: ሁሉም ክርስቲያን አንድን አካል በጥፋተኝነት (በጠላትነት) ከመፈረጅና ሌላውን አካል የጽድቅ ሐዋርያ አድርጎ ከመውሰድ ተቆጥቦ የሀሳብ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በጸሎትና በሌሎች አግባብ ባላቸው መንገዶች ሁሉ የራሱን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። በደል የፈፀሙ አካላትን የሚዳኝ ፍትሐዊ የሕግ ሥርዓት ካለም ሁሉም ያለ አንዳች አድልኦ ለፍትህ እንዲቀርቡ፣ የተበደሉም እንዲካሱ የሰላም፣ የእውነትና የፍትሕ ድምፅ መሆን ከሁሉም ክርስቲያን ይጠበቃል። ያን ማድረግ ካልተቻለ በክፋት ከመተባበር መራቅ ይገባል። በአንፃሩ “ይህ የእኔ ነው አትንኩት፣ ያ የእነርሱ ነው ስቀሉት” የሚሉ ለተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ መስፈሪያ የሚጠቀሙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ለይስሙላ “የእርቅ ጥረት” አደረግን ቢሉ መስፈሪያው የተበላሸ ስለሆነ ሰውንም እግዚአብሔርንም አያስደስትም። ይልቁንም በክፋት መተባበር ስለሆነ ልዩነቶችን ከሚያሰፉ መሰል ነገሮች መቆጠብ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ካህናት አባቶችና ምዕመናን ከወገንተኝነት ርቀው ከእውነት ጋር ብቻ ቆመው የጦርነት ቅድመ ምልክቶች ሲታዩ ሰላማዊ መንገድን ብቻ ማበረታታት፣ የጦርነት መንገድን የሚመርጡ አካላትን መገሰፅና ድጋፍ መንሳት ይጠበቅባቸዋል። ማንኛውም ዓይነት የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ለጦርነት ድጋፍ እንዳይውል ማረጋገጥም ያስፈልጋል። እንዲህም በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ከጥፋት ያድኗታል።

በጦርነት ጊዜ: የሰላም መንገዶች ተሟጠው ጦርነት ውስጥ ቢገባ እንኳን ምዕመናንና አባቶች በጸሎት በመትጋትና ገለልተኝነታቸውን በመጠበቅ ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመጀመሪያ ጦርነቱ እንዲቆምና ተዋጊ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥረታቸውን መቀጠል ይገባቸዋል። ይህንን በማድረግ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይችላሉ። ይህንን ማድረግ ባይችሉ እንኳን ለጦርነት የሚውል፣ የዕውቀት፣ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ ባለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት ይችላሉ። ሁለተኛ በጦርነት ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን (ማንም ይፈፅመው ማን) በወንጀልነታቸው በማውገዝና እውነተኛ ፍትሕ እንዲገኝ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ይችላሉ። ሦስተኛ በጦርነቱ የተጎዱ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ የራሳቸውን ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል። ይህም ያለ አንዳች አድልኦና ልዩነት መፈጸም ይገባል። ክርስቲያን ይህንን የሚያደርገው በመጀመሪያ ሰብአዊነት፣ ቀጥሎም የወንጌል ሕግ ስለሚገዛው ነው።

ከጦርነት በኋላ: ጦርነት ከቆመ በኋላ ቢሆን በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት መካከል እውነተኛ እርቅ እንዲደረግ፣ ፍትህ እንዲሰፍን (የበደሉ እንዲጠየቁ፣ የተበደሉ እንዲካሱ)፣ በሕዝብ ደረጃም ማኅበራዊ እርቅ እንዲፈጸምና ዳግመኛ ልዩነትን በኃይል ወደመፍታት የሚመሩ መንገዶች እንዲዘጉ ከማድረግ አንጻር ምእመናና አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የሰላም ሐዋርያ ትሆናለች።

መደምደሚያ

ስለ ጦርነት ክፉነት የማይናገር የለም ማለት ይቻላል። በዓለም ታሪክ የለየላቸው ጨፍጫፊዎችም እንኳ ሳይቀሩ አንዱ ሌላውን ለጦርነት ተጠያቂ ሲያደርጉ ይታያሉ እንጂ በሰለጠነ ዘመን ጦርነትን “እግዚአብሔር የሚሳተፍበት ጠላቶችን የማጥፊያ መንገድ” አድርገው ሲስሉት በብዛት አይታይም። በዚህ ዘመንም በገዛ ወገኑ ላይ የታወጀ ረሃብን የሚደግፍ ወይም በዝምታ የሚያልፍ ሕዝብ አይገኝም። ይሁንና ሁሉም በመሰለው እየተጓዘ ሰላምን ሲገፋና በቀልን ሲያረግዝ በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠሩ ሰዎችን የእሳት ራት የሚያደርግ፣ ሀገርን የሚያወድም፣ የብዙዎችን ተስፋ የሚያጨልም ጦርነት በልዩ ልዩ መልኩ ነግሦ ያለመቋጫ በዓለም ዙሪያ እልፍ አእላፋትን ከሕይወት ሥጋዊ፣ ከሕይወት መንፈሳዊ ሲለይ እናስተውላለን። ይህንን ስናይና ስንሰማ በእውነት የመጨረሻው ዘመን እንደቀረበ ልናስተውል ይገባል።

ጦርነትን እግዚአብሔር ያስቀር/ያርቅ ዘንድ ከመጸለይ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ጉልህ ድርሻ አላት። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም “ጸልዩ በእንተ ሰላም ፍፅምት ወፍቅር ተአምኁ በበይናቲክሙ በአምኀ ቅድሳት” እንደተባለ ሁል ጊዜ ስለሰላም መጸለይ ይገባቸዋል። “ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ (ማቴ 26:52)” የሚለውን የክርስቶስ ቃል መመሪያው አድርጎ የሚኖር አገልጋይና ምዕመን ሰይፍ መጥፊያ እንጂ መፍትሔ አለመሆኑን መርሳት የለበትም። የመፍትሔ ምንጭ እግዚአብሔር እንጂ የሰው ልጅ ኃይል አለመሆኑንም እንዲሁ። ከዚህ በተቃራኒው የሚያስብ፣ የሚናገርና የሚያደርግ እንዲሁም ግፍንና ጦርነትን የሚያወግዙትን የሚያወግዝ ያንን የጥፋት መንገድንም መንፈሳዊነት አድርጎ የሚያቀርብ ሲበዛ ስናይ ግን “አቤቱ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን” ከማለት ውጭ ምን እንላለን?! አቤቱ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን! የየዋሀንን ጸሎት ተቀብለህ ሰላምን ለተራቡና ለተጠሙ ሰላም አድልልን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s