መግቢያ
ከዓመታት በፊት የዚህች አጭር ጽሑፍ አዘጋጅ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ታላላቅ አድባራት በአንዱ የሠርክ ጉባዔ ላይ የሚሰጠውን ስብከት በመከታተል ላይ ነበር። የዕለቱ ሰባኪ የመረጡት የትምህርት ርዕስ “ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ” የሚል ነበር። የስብከቱም ይዘት ኢትዮጵያ ድንቅና ጥልቅ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን፣ ሀገሪቷ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር መሆናቸውን፣ ሰውም በመልካም ለመጣው እንግዳ ተቀባይ በክፉ ለመጣበት ግን እንደ ‘አንበሳ’ ጀግና መሆኑ ላይ ያተኮረ ነበር። ከታሪክም የታቦተ ጽዮንን በአክሱም መገኘት፣ የግማደ መስቀሉን በግሸን መገኘት፣ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክና ሀገሪቷም የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር መሆኗን የሚተነትን ነበር። ሰባኪው በስተመጨረሻም “ይህች ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ50 ጊዜ በላይ ተጠቅሳለች” በማለት ይህም የቅድስናዋ ማረጋገጫ ዋነኛው ማስረጃ መሆኑን አስምረውበት ትምህርታቸውን አጠቃለሉ።
ከዚህ ትምህርት ውስጥ የዚህች ጦማር ትኩረት “ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ50 ጊዜ በላይ ተጠቅሳለች” የሚለው ነው። ይህ አነጋገር በወቅቱ በአድማጩ አእምሮ ውስጥ ሦስት ጥያቄዎችን የፈጠረና ለቀጣይ ጥናትም በር የከፈተ ነበር። የመጀመሪያው ጥያቄ “በመጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢትዮጵያ’ ተብላ የተገለፀችውና ዛሬ የምናውቃት ‘ኢትዮጵያ’ ያላቸው ልዩነትና አንድነት ምንድን ነው?” የሚለው ነበር። ሁለተኛው ደግሞ “የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ የተጠቀሰችው በምን ዐውድ (context) ነው?” የሚለው ጥያቄ ነው። ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ “በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ መጠቀስ የአንድ ሀገር ‘የቅድስና ማረጋገጫ’ እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚለው ጥያቄ ነው። ዛሬም እነዚህ ጥያቄዎች ጥቂት በማይባሉ ምዕመናን ልቡና ውስጥ የሚመላለሱ ስለሆኑና ብዙ ብዥታም ስለሚስተዋል በዚህች ጽሑፍ እነዚህን ነጥቦች በሚመለከት አጠር ያለ ዳሰሳ ቀርቧል።
የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ
የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ (The Biblical Ethiopia) አሁን ከምናውቃት ኢትዮጵያ (The Current Ethiopia) ጋር ያላትን አንድነትና ልዩነት በተመለከተ የተለያዩ አስተሳሰቦች እንዳሉ ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ የሚደረጉ ተጠየቃዊ ውይይቶችን ፍሬ አልባ የሚያደርገው ዋነኛ ማሰናከያም የቅዱሳት መጻሕፍትን የታሪክና የመልክዓምድር ገለፃ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ትንቢቶች በዘመናችን ላለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፉክክር የመጠቀም ክፉ ልማድ ነው። በመሆኑም ስለመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያና በየዘመኑ የአስተዳደር ቅርጿ የተቀያየረውን፣ አሁን የምናውቃትን ኢትዮጵያ አረዳድ ለአሁናዊ ፖለቲካዊ ፍጆታ ማዋል የሚፈጥረውን ተፋልሶ በማሳየት እንጀምር።
የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያና የአሁኗ ኢትዮጵያ ያላቸውን ንፅፅር በተመለከተ የተለያዩ ትንታኔዎች አሉ። ከእነዚህ አንዱ ስያሜን የሚመለከት ነው። ኢትዮጵያ የሚለውን በግሪክና በልሣነ ግዕዝ የተቀመጠውን ስያሜ “ኩሽ” በሚል “መስተካከል” አለበት ብለው የሚሞግቱ አሉ። ለዚህም የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ “ኢትዮጵያ” የሚለውን “ኩሽ” በሚል እንደሚጠራው በማንሳት ይሞግታሉ። ሌሎች ደግሞ የአረብኛውን “የጥቁር ሕዝቦች ምድር” የሚል ትርጉም ያለውን ቃል በመጠቀም “ኢትዮጵያ” የሚለውን “ሱዳን” በሚል ተክተው መጽሐፍ ቅዱስን “በሚመቻቸው መንገድ” አሳትመዋል። የእነዚህ “የስም ሽሚያዎች” መሰረታዊ ምክንያት በቅን ልቡና መጻሕፍትን መመርመር ሳይሆን የታሪክ ፉክክር ማድመቂያ ነው።
“ኢትዮጵያ” የሚለውን የቅዱሳት መጻሕፍት ስያሜ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ የፖለቲካዊ ሃይማኖት አቀንቃኞች “ኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት” ለሚሉት መንፈሳዊም፣ ዓለማዊም ረብ ለሌለው አስተሳሰብ መደገፊያ ያደርጉታል። በዚህም የተነሳ ወደ ልዩ አምልኮ እስኪወሰዱ ድረስ ከቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት ይልቅ እንደ አይሁድ መጻሕፍትን በማጣመም ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲደክሙ እናያቸዋለን። በሌላ በኩል በዘመናችን የምናውቃትን ሀገር ኢትዮጵያን በታሪክ አረዳድና በማኅበራዊ አቋም የሚገዳደሩ የፖለቲካ ኃይሎች ደግሞ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ በ”ኩሽ” ወይም ሌላ መጠሪያ በመቀየር ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማኅበራዊ ማገናዘቢያዎች በመለየት ስያሜውን “የሁሉ በማድረግ የማንም እንዳይሆን” አስልተው ሲንቀሳቀሱ እናስተውላለን። በተለይም “ሱዳን” በሚል “የተረጎሙት” ምዕራባውያን ሚስዮናውያን ቅዱሳት መጻሕፍት “ኢትዮጵያ” በማለት የሚገልፁት ቦታና ሕዝቦች አሁን በምናውቃት ኢትዮጵያ ካለውና በእነርሱ አረዳድ ሊፈጥሩት ለሚፈልጉት የታሪክና የትንቢት ምንዘራ (rethoric) “ጋሬጣ” ሆኖ እንዳይጋጭባቸው በመስጋት የፈጠሩት ቅሰጣ (adulteration) ይመስላል። የዚህ ሁሉ ማምታታት ምንጭ ታሪክንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሰረታዊ ጭብጥ አለመረዳት ወይም ይሁነኝ ብሎ ማጣመም ነው።
የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ለታሪክ ሽሚያና ለፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ (rethoric) ማሳመሪያ እየቆነፃፀሉ የሚጠቀሙት ሰዎች የሚያተኩሩት “ስም” ላይ እንጂ “ግብር” ላይ አለመሆኑ የታወቀ ነው። አሁን የምናውቃትን ኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ “ብቸኛ ወራሽ” እንደሆነች፣ አለን ለሚሉት የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብም እንደ መሠረታዊ ግብዓት የሚጠቀሙት ፖለቲካዊ ሃይማኖተኞችም ሆኑ እነርሱን ለመገዳደር ሲባል “ኩሽ” ወይም “ሱዳን” የሚል መጠሪያን መጠቀም የሚመርጡት አካላት የሚዘነጉት መሠረታዊ ጉዳይ ከስም ይልቅ ሌሎች በተግባር የሚታዩ ማኅበራዊ መገለጫዎች (sociological evidence) የመጽሐፍ ቅዱሷን ኢትዮጵያ የተሻለ የሚገልጹ መሆናቸው ነው። “በዘመነ ብሉይ አምልኮተ እግዚአብሔር የነበረባቸው ቦታዎች እነማን ናቸው? ዛሬ ያለን ግብርስ የቃልኪዳን ተካፋይ የሚያደርግ ነው ወይስ ከዓለም የከፋ እንስሳዊነት” ብሎ በአስተዋይነት ከመመርመር ይልቅ ስም ላይ ማተኮር የሚወዱ ብዙዎች ናቸው። ስም ላይ የሚያተኩሩት ሰዎች የቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረታዊ ጭብጥ ያልተረዱ ናቸው። ከሆነው ይልቅ “ነው!” ብለው ላመኑበት ወይም እንዲሆን ለሚፈልጉት “ወራሽነት” ሲሉ መንፈሳዊም ዓለማዊም የሞራል ድንበር ሳይገድባቸው ታሪክና የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ እየቀደዱ በልካቸው ይሰፋሉ። ለዚያም ነው ሰዎችና አኗኗራቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ለመሬት ስም ሰጥተው ከግብሩ የተለየ፣ ከታሪክ የተፋታ ወሬ ይዘው እግዚአብሔርን የእነርሱ ተለዋዋጭ ድንበር አስጠባቂ የሚያስመስሉት።
በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡ ቃል ኪዳኖች የትውልድን ለቃል ኪዳን የተገባ መሆን የሚጠይቁ ናቸው እንጂ በብልጣብልጥነት መጻሕፍትን በመቆነፃፀል የሚፈጸሙ አይደሉም። ይህንንም ለክቡር ዳዊት ቃል ኪዳን የሰጠ አምላካችን እግዚአብሔር በመዝሙረ ዳዊት ያስተማረን ነው። በመዝሙር 88:3 ጀምሮ ጌታ እግዚአብሔር ለክቡር ዳዊት የገባለትን ቃል ኪዳን ከዘረዘረ በኋላ “ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተው፣ በፍርዴም ባይሄዱ ፣ ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፣ ትእዛዜንም ባይጠብቁ ኀጢአታቸውን በበትር በደላቸውንም በመቅሰፍት እጎበኛታለሁ።” (መዝ 88:30-32) ይላል። ለጠቢቡ ሰሎሞንም ተመሳሳይ ቃል ኪዳን ነበር የተሰጠው (1ኛ ነገ 9:1-10)። በዚህም የተነሳ ከማንም በላይ ቃል ኪዳን የተገባላቸው እስራኤል ዘሥጋ በዘርና በቦታ ተመክተው ራሳቸውን “የአብርሃም ልጆች፣ የኢየሩሳሌም ባለርስቶች” አድርገው በመኮፈሳቸው ራሳቸውን ከድኅነት በአፍአ አስቀሩ እንጂ አልተጠቀሙም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የአብርሃም ልጆች ነን” እያሉ ከአብርሃማዊ ግብር ተለይተው በባዶ የሚመኩትን አይሁድ ወቀሳቸው እንጂ አላመሰገናቸውም። (ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8) እኛም የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጓሜ በመንፈሳዊ አረዳድ ልንገነዘበው ይገባል እንጂ እንደ አይሁድ የምድራዊ ፍላጎታችን መጠገኛ በማድረግ ትርጉም ልናሳጣው አይገባም።
የቅዱሳት መጻሕፍት ዓላማ ሰዎችን ለዘለዓለማዊ ሕይወት ማብቃት ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት የተለያዩ ቦታዎችና ሀገራት በልዩ ልዩ ዐውድ (context) ተጠቅሰዋል። ይህ የቅዱሳት መጻሕፍት አገላለፅ ዓላማው በተጠቀሱት ሀገራት ወይም አካባቢዎች ስለነበሩት፣ ስላሉት ወይም ወደፊት ስለሚመጡት ትውልዶች ምድራዊ ባለፀግነት፣ ድህነት፣ ጀግንነትና ስለመሳሰለው ታሪክ መተረክ አይደለም። እነዚህ መገለጫዎች እንደመመዘኛው የሚለያዩ፣ በየጊዜውም የሚቀያየሩ ናቸው። ለምሳሌ በቅዱሳት መጻሕፍት እስራኤል የመንግሥተ እግዚአብሔር፣ ግብፅ ደግሞ የሲዖል ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል። ነገር ግን ትንቢት የተነገረላቸው፣ ሱባኤ የተቆጠረላቸው እስራኤል አዳኛቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰቅለው ሲገድሉት የግብፅ (እስክንድርያ) ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በአንፃሩ “ወልድ ዋሕድ” ብላ በማመን በተዋሕዶ ሃይማኖት የመጽናት ምሳሌ መሆኗን ሊቃውንት ያስተምራሉ። ስለሆነም የብሉይ ኪዳንን ታሪክና ምሳሌ እያነሱ እስራኤልን ሁሉ ቅዱስ፣ ግብፅን ሁሉ ርኩስ አድርጎ የሚስል አስተሳሰብ ከእውነትም፣ ከታሪክም የተጣላ፣ መንፈሳዊ ትርጉም የሌለው ተራ ፍረጃ መሆኑን እንረዳለን። በቅዱሳት መጻሕፍት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የተፃፈውንም የታሪክን ቅብብሎሽ ሳይረዱ፣ ስምና መልክዓምድርን ከግብር (ተግባር) እና የሚታወቅ የማኅበረሰብ መገለጫ በመለየት ለራስ የሚመች ትንታኔ ብቻ በመስጠት የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጓሜ ለፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈፀሚያ ማዋል ሩቅ መንገድ አያስኬድም፣ አይገባምም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢትዮጵያ’ ተብሎ የሚታወቀው ቦታ የዛሬዋ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ሱዳን (ኑቢያ)፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ደቡብ አረቢያንና የመንን የሚያካትት ነበር። በአጠቃላይ ጥቁሩ ሕዝብ ኩሽ ወይም ኢትዮጵ ተብሎ ይታወቅ ነበር። ስለዚህም ነው ጥቁር የነበሩት ሙሴ ያገባት ሴትና ካህኑ አቤሜሌክ ኩሽ (ኢትዮጵያዊው/ው) ተብለው የተጠሩት። ሳባ (Sheba) የኩሽ ልጅ ስለሆነ በተለይም በደቡብ ዓረቢያ ይኖሩ የነበሩት ሳባውያን ተብለው ይታወቁ ነበር። የሳባ ንግሥት ተብሎ የተጠቀሰውም ከዚህ ጋር እንደሚገናኝ የታሪክ ምሁራን ይስማሙበታል። በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ (ኩሽ፣ ኢትዮጵ) ተብሎ የሚታወቀው ከዛሬዋ ኢትዮጵያ እጅግ የሰፋ ቦታን የሚያጠቃልል ነበር። የመጽሐፍ ቅዱሷን ኢትዮጵያ ካርታ የሚስሉ ሊቃውንት የሚያስቀምጡት መግለጫም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ “ኢትዮጵያ” የተጠቀሰችባቸውን ዐውዶች በሚገባ ተረድቶ መንፈሳዊውን በመንፈሳዊ አረዳድ፣ ታሪካዊውንና መልክዓምድራዊውን ገለፃም እንዲሁ በደርዙ መረዳት ይገባል እንጂ “በሳብ ግጥም” አስተሳሰብ፣ መርጦ በመውሰድ፣ መርጦ በመጣል መቆነፃፀል አይገባም።
በዓለማችን ላይ ያሉ ሀገራት ስማቸው፣ ስፋታቸው፣ የሕዝቡም ባሕል በየጊዜው የሚቀያየር ነው። ስማቸውን የቀየሩ ብዙ ሀገራት አሉ። ሰፊ ሀገር የነበሩ ተከፋፍለው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሀገሮች አሉ። የተለያዩ ሀገሮችም ተዋሕደው አንድ ሀገር ሊሆኑ ይችላሉ። ቦታዎችን ከተለያዩ ሀገሮች በማጣመር የሚፈጠሩ ሀገራት ይኖራሉ። አዳዲስ ሀገራትም ሊገኙ ይችላሉ። ይህ ተለዋዋጭ ነገር ነው። ታሪክ ግን የተፈጸመ ነገር ስለሆነ አይቀየርም። የተከፋፈሉ ሀገራት የቀድሞ ታሪካቸውን ይጋሩታል። የተዋሐዱ ሀገራት ደግሞ የቀድሞ ታሪካቸውን ይጠብቁታል። ስማቸውን የቀየሩ ሀገራትም እንዲሁ በቀድሞ ስማቸው የተመዘገበውን ታሪካቸውን ይጠብቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ታሪክም ከዛሬዎቹ ሀገራት ታሪክ አንጻር በዚህ አግባብ ሊታይ ይገባዋል።
በእኛ ዘመን ታሪክ እንኳ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች። በቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሱት ማኅበራዊና መንፈሳዊ መገለጫዎችም ዛሬ ኤርትራ በሚባለው ሀገር የነበረውንና ያለውን የማኅበረሰብ እምነትና ታሪክም የሚያካትት መሆኑ ግልፅ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ ቅዱሳት መጻሕፍቱ በተፃፉበት ጊዜ የነበረውን የማኅበረሰብ መገለጫ የሚያሳይ እንጂ በየዘመናቱ በሚቀያየር የሀገራት ፖለቲካዊ ድንበር (political boundary) ጋር እየተቀያየረ የሚኖር (shifting demarcation) አይደለም። ይሁንና “አስቀድሞ የተወሰነ፣ በአመክንዮ የማይለወጥ” ሀሳብ ያላቸው ፓለቲካዊ ሃይማኖተኞች “ስምን በመያዝ ብቻ” እግዚአብሔርንም ሰውንም ማታለል የሚቻል ይመስላቸዋል። በማስተዋል የሚራመድ፣ መንፈሳዊ ልብ ያለው ሰው ግን እያንዳንዱን የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ እንደ አገባቡ በመረዳት ራሱንና በዙርያው ያሉትን ለማነጽ ይደክማል እንጂ በስም መሸፈንን ብቻ ገንዘብ አያደርግም። ይህን ታሳቢ በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ የተጠቀሰችባቸውን ዐውዶች ለማሳየት እንሞክር።
የመጽሐፍ ቅዱሷ ‘ኢትዮጵያ’ የተጠቀሰችባቸው ዐውዶች
ብዙ መምህራን ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ50 ጊዜ በላይ መጠቀሷን ያስተምራሉ። ነገር ግን በምን ዐውድ እንደተጠቀሰች በጥልቀት የሚያብራሩ ጥቂት ናቸው። በዚህም የተነሳ ጥቂት የማይባሉ ምዕመናን “ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ጊዜ ተጠቅሳለች” የሚለውን እንጂ “በምን ዐውድ ነው የተጠቀሰችው?” የሚለውን ጠለቅ ብለው አይመለከቱትም። ነገር ግን የበለጠ ጠቃሚ ነጥብ ያለው ‘ይህን ያህል ጊዜ ተጠቅሳለች’ የሚለው ላይ ሳይሆን የተጠቀሰችባቸውን ዐውዶች ለይቶ ማወቁ ላይ ነው። ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችባቸውን ዐውዶችና (context) የጥቅሶቹንም ይዘት (content) እንደሚከተለው እናቀርባለን።
ጦርነት፣ ቁጣ፣ ሁከትና ተያያዥ ጉዳዮች
ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሰችባቸው ዐውዶች አብዛኛውን (20 ጊዜ) የሚይዘው ይህ ከጦርነትና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከተው ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ሌሎችን በጦርነት ያጠቃችበት፣ በሌሎች አካላት በጦርነት የተጠቃችበት፣ ኢትዮጵያውያን በጦርነት የወደቁበትና የሸሹበት፣ በአንጻሩም ድል ያደረጉበት፣ ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጎን በጦርነት የተሰለፉበት እንዲሁም ሊመጣባቸው ስላለው ጦርነት ትንቢት የተነገረበትን ያጠቃልላል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሁከት እንደሚሆን፣ ኢትዮጵያውያን በሰይፍ እንደሚወድቁ የተነገሩትን ትንቢቶች ያካትታል። ይህ በብዙ ዘመናት የነበረ ታሪክን የሚያመለክትና በመጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢትዮጵያ’ ተብላ የተገለጸችውን የሚመለከት ነው። የዘመናችን መምህራን እነዚህን በሚመለከት ብዙም ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም። ኢትዮጵያ በዚህ ዐውድ የተጠቀሰችባቸውን ጥቅሶች ከዚህ በታች ይመልከቱ።
መልክዓ ምድር፣ አቅጣጫና ወሰንን ለማመልከት
ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መልክአ ምድራዊ ገጽታን፣ አቅጣጫን፣ ወሰንን፣ ማዕድንን (ለምሳሌ ጳዝዮን)፣ ወንዝን (ለምሳሌ ግዮን) … ወዘተ ለመግለጽ 12 ጊዜ ተጠቅሷል። በዚህም ዐውድ በአብዛኛው የነገሥታት የግዛት ወሰንን ለማመልከት የተጠቀሰ ሲሆን የነገሥታቱ የግዛት ወሰን ጥቁር ሕዝብንም ያካትት እንደነበር የሚያሳይ ነው። በጥንት ዘመን የነበረው የግዛት ወሰን በሕዝብና በሀገር ይገለፅ ነበር። ስለዚህም ይመስላል ይህ አገላለጽ የተለመደ የነበረው። እነዚህም ጥቅሶች በጥንት ዘመን ኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀውን ሕዝብና ቦታ በሚገባ ያሳያሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ዐውድ የተጠቀሰችባቸውን ጥቅሶች ከዚህ በታች ይመልከቱ።
የሕዝብ እምነትና አምልኮ ጋር በተያያዘ
ኢትዮጵያ (እንደ ሕዝብና ሀገር) ከእምነትና ከአምልኮ ጋር በተያያዘ 10 ጊዜ ተጠቅሳለች። እነዚህም ደገኛ ሃይማኖትን፣ የጸና ቃልኪዳንን የሚያሳዩ በዳዊት መዝሙር፣ በትንቢትና በመጽሐፈ መቃብያን የተጠቀሱት ናቸው። ከእነዚህም መካከል ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች (ታደርሳለች)’ የሚለውና ‘ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው’ የሚሉት ይገኙበታል። በዚህ ዐውድ የሚገኙ ዝርዝር ጥቅሶችን ከዚህ በታች ይመልከቱ።
የባለታሪኮችን ማንነት ለመግለፅ
በመጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ የሚለው ስም የባለታሪኮችን ማንነት ለመግለፅ የዋለባቸው 9 ቦታዎች አሉ። በዚህ ዐውድ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ያገባትን ኢትዮጵያዊት ሴት፣ ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክ፣ የኢትዮጵያ ንግሥት የነበረችው ህንደኬን፣ ጃንደረባው ባኮስን፣ የኢትዮጵያ ነገሥታትን ለመግለጽ ተጠቅሷል። በዚህ አውድ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የኩሽ (የጥቁር) ማንነትን ለማመልከት የተጠቀሰ ነው። በግልፅ ‘ኢትዮጵያውያን’ ተብለው በመጽሐፍ ቅዱስ ባይገለጹም የሳባ ንግሥታት እና ከሰብአ ሰገል አንዱ የሚጠቀሱት በዚሁ አግባብ ነው። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በገላጭነት የተጠቀሰባቸውን ጥቅሶች ከዚህ በታች ይመልከቱ።
በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀስና ቅድስና
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስራኤል 2431 ጊዜ፣ ግብፅ 725 ጊዜ፣ ባቢሎን (ኢራቅ) 265 ጊዜ፣ ፍልስጤም 243 ጊዜ፣ ሊባኖስ 75 ጊዜ፣ ሶርያ 71 ጊዜ፣ ፋርስ (ኢራን) 32 ጊዜ፣ ግሪክ 26 ጊዜ ሲጠቀሱ ጭራሽ ያልተጠቀሱም ብዙ ሀገሮች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ በኋላም ብዙ ሀገሮች ስማቸው፣ ወሰናቸው፣ የሕዝብ ስብጥራቸው፣ ታሪካቸው ተቀይሯል። ሰፊ የነበሩት ተከፋፍለው ብዙ ሀገራት ሆነዋል። በአብዛኛው ክርስቲያን ሕዝብ የነበራቸው አሁን እንደዚያ አይደሉም። በአንጻሩ ደግሞ አሕዛብ ይባሉ የነበሩት ክርስቲያን ሆነዋል። የሀገር ቅድስና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመጠቀስ ብዛት ቢሆን ብዙ የተጠቀሱት ይቀድሙ ነበር። ጭራሹን ስማቸው ያልተጠቀሰው ደግሞ ተስፋ የሌላቸው በሆኑ ነበር። ነገር ግን ሀገርን የሚቀድሰው የሕዝቡ እምነትና አምልኮ፣ የቅዱሳን ተጋድሎና የእግዚአብሔር በረከት ስለሆነ በመጽሐፍ ጥቅስን ከመቁጠር ይልቅ መጽሐፍትን በጥልቀት መረዳትና በእምነት መጽናት ይበጃል።
የእግዚአብሔርን መንግሥት እንስበክ!
ሃይማኖት ሰው እግዚአብሔርን አምኖ እርሱንም ብቻ እያመለከ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖርበትና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግስት (ሰማያዊ ሀገር) የሚወርስበት ነው። ይህም የሰው ልጅ እግዚአብሔርንና ባልንጀራውን የሚያፈቅርበት መሠረት ነው። በሃይማኖት የሚኖር ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እየጠበቀ ለእግዚአብሔር ይገዛል። በሥጋም ሲኖር ከሰው ሁሉ ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር ይጠበቅበታል። በመጨረሻም በእግዚአብሔር መንግሥት ለዘላለም ለመኖር የሚያበቃው ይህ የጸና ሃይማኖት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማም ይህንን ማስረገጥ ነው። ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩ ሀሳቦች በመንፈሳዊው ዓይን ሊታዩ ይገባል።
ሀገር የሚባለው በተወሰነ (ሰው በወሰነው) የምድር ክፍል የሚኖር ሕዝብን፣ የሚኖርበትን የየብስ፣ የውኃና የአየር ክልልን፣ የሕዝቡን ታሪክ የአኗኗር ባሕልና የሚተዳደርበትን ባሕላዊና ዘመናዊ አስተዳደር የሚመለከት ነው። በክርስትና የሚኖር ሰው ሀገሩን ቢወድ መልካም ነው። ክርስትና እንኳን የራስ የሆነን ቀርቶ ሌላውንም እንድንወድ የሚያደርግ ነውና። የሀገርንም ዕድገትና ብልፅግና ተስፋ ማድረግ የተገባ ነው። ይህንንም በፖለቲካው መድረክ መስበክ ይቻላል። ነገር ግን ይህ የሀገር ፍቅር ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ሊቀላቀል አይገባውም። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ቅዱስ ቃልም የምድራዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆን የለበትም። በሃይማኖታዊ መድረኮች ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባልተናነሰ መልኩ ሁሉም የሚመቸውን ፖለቲካዊ ውግንና የሚያንቆለጳጵስ “የሀገር ፍቅር” የሚሰብክ ከሆነ ግን ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ ማዋል ነው። በኢትዮጵያውያን መካከል ያሉ የአስተሳሰብ ልዩነቶች የወለዷቸው ግጭቶችን ለመተንተን፣ የታወቀ ውሸትንም ለመሸፈን ሳይቀር አንዱን ባለቃልኪዳን ሌላውን ከቃልኪዳን የተለየ አድርገው የሚተነትኑ፣ በንግግራቸውም ራሳቸውን “የእግዚአብሔር አማካሪዎች” አስመስለው የሚያቀርቡትን ዲያብሎስን የሚያስንቁ የሀሰት ፈጣሪዎች አስተውለናል። ይሕ ደግሞ መንፈሳዊም መጽሐፋዊም እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ይልቁንስ ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድ መድኅን ክርስቶስን ከሕግ ውጭ በጭካኔ ለመግደል የተጠቀሙበትን መደላድል የፈጠረና የሚፈጥር የክፋት ሠራዊት እርሾ ነው።
ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት የሆነች፣ ስለሰማያዊውና ዘላለማዊው መንግስት የሚማሩባት ዐውደ ምሕረት ናት እንጂ ስለ አላፊዎቹ ምድራዊ ሀገራት ታሪክና አስተዳደር የሚሰበክባት አይደለችም። የቦታ መቀደስ ሰውን የሚቀድስ፣ እንዲሁም ሰው በተሰጠው ቅድስና ቦታን የሚቀድስ ቢሆንም ሕዝብ ፊቱን ወደ ኃጢአት ከመለሰ ይህ ጸጋ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። ከዚህ አንጻር በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችውን ኢትዮጵያ ከተጠቀሰችበት ዐውድ ውጭ መጠቀም አግባብ አይሆንም። በተጨማሪም መልካም የማይመስል ይዘት ያለውን እየተው መልካም መልካሙን ብቻ መጥቀስ ሚዛናዊነት የሚጎድለው አካሄድ ነው። በፍርድ ቀንም ቢሆን ‘ለእያንዳንዱ እንደየሥራው’ ዋጋውን ይከፈለዋል እንጂ ጽድቅ ሰው በምድር በኖረበት ሀገር መስፈርትነት በጅምላ አይታደልም።
የሃይማኖት ካባ የደረቡ ፖለቲከኞች ግን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ፖለቲካዊ ውግንናን መስበክ መገለጫቸው ስለሆነ በዘመናችን የፖለቲካ ድንበር “ኬንያዊ” ከሚባል ክርስቲያን ይልቅ ክርስቶስን የማያውቅ “ኢትዮጵያዊ” “የቃል ኪዳን ተካፋይ” እንደሆነ አስመስለው ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ ብዙዎች ምድራዊ ሰንደቅ ዓላማን እስካሳዩዋቸው ድረስ በየዘመኑ በሚነሱ “ከሰማይ የወረደ መልእክት” ይዘናል በሚሉ “ንጉሥ(ንግሥት) ነን”፣ “አጥማቂ ነን”፣ “ባሕታዊ ነን” በሚሉ አላዋቂዎች ግብስብስ ስብከት እየተነዱ ሳይረዱት ከቀናች ሃይማኖት ለመውጣት ሲፋጠኑ ማየት የተለመደ ሆኗል። በተረታቸው ታውረው ጌታቸውን ኢየሱሰ ክርስቶስን እንደሰቀሉት አይሁድ የሚጓዙ በየጊዜው እየበዙ ነው። ስለዚህ ልባችንን እና ህሊናችንን ወደ እግዚአብሔር መልሰን በርትዕት እምነትና ክርስቲያናዊ ስነምግባራት ልንጸና ይገባል።
==========================================
ጦርነት፣ ቁጣ፣ ሁከትና ተያያዥ ጉዳዮች
- 2ኛ ነገስት 19፥9 እርሱም፦ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ደግሞ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥
- 2ኛ ዜና 12፥3 ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ።
- 2ኛ ዜና 14፥9 ኢትዮጲያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው ወደ መሪሳም መጣ።
- 2ኛ ዜና 14፥12 እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ።
- 2ኛ ዜና 14፥12 እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ።
- 2ኛ ዜና 14፥13 አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ።
- 2ኛ ዜና 16፥8 ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥
- ኢሳ 20፥3 እግዚአብሔርም አለ፦ ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥
- ኢሳ 20፥4 እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።
- ኢሳ 20፥5 እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል
- ኢሳ 37፥9 እርሱም፦ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ ሰማ። በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥
- ኢሳ 45፥14 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ። በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።
- ኤር 46፥9 ፈረሶች ሆይ፥ ውጡ ሰረገሎችም ሆይ፥ ንጐዱ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፋጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ።
- ሕዝ 30፥4 ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።
- ሕዝ 30፥5 ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
- ሕዝ 30፥9 በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ እንደ ግብጽም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል እነሆ፥ ይመጣልና።
- ሕዝ 38፥5 ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥
- ዳን 11፥43 በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል።
- ናሆ 3:9 ኢትዮጵያና ግብጽ የማይቈጠር ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ።
- ሶፎ 2፥12 እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ።
መልክዓ ምድር፣ አቅጣጫና ወሰንን ለማመልከት
- ዘፍ 2፥3 የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።
- 2ኛ ዜና 21፥16 እግዚአብሔርን የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ።
- መጽ. አስቴር 1፥1 በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ።
- መጽ. አስቴር 3:12 ፤ በመጀመሪያውም ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ወዳሉ መቶ ሀያ ሰባት አገሮች፥ በየአገሩ ወዳሉ ሹማምትና አለቆች ወደ አሕዛብም ሁሉ ገዢዎች እንደ ቋንቋቸው በንጉሡ በአርጤክስስ ቃል ሐማ እንዳዘዘ ተጻፈ፥ በንጉሡም ቀለበት ታተመ።
- መጽ. አስቴር 8፥9 በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ።
- ኢዮ 28፥19 የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
- ኢሳ 18፥1 በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥
- ሕዝ 29፥10 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
- ሶፎ 3፥10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።
- 2ኛ ዕዝራ 3:2 ንጉሡ ዳርዮስ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ላሉ ሰዎች ደግ በዓል አደረገ።
- ዮዲት 1:10 ናቡከደነፆር እስከ ኢትዮጵያ አውራጃ ድረስ በግብፅ ወደሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ ላከ።
- 1ኛ መቃ 25:9 ከሳባና ከኖባ ከህንደኬና ከኢትዮጵያም ወሰናቸውና አውራጃቸውም ጋር ሁሉ ተሰምታ ትጠፋለች።
የሕዝብ እምነትና አምልኮ ጋር በተያያዘ
- መዝ 67፥31 መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
- መዝ 71፥9 በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።
- መዝ 73፥14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።
- መዝ 86፥4 የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ።
- ኢሳ 11፥11 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብጽ፥ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፥ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፥ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደ ገና እጁን ይገልጣል።
- ኢሳ 43፥3 እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ።
- ኤር 13፥23 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።
- አሞ 9፥7 የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር፦ እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
- ዕን 3፥7 የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።
- 1ኛ መቃ 34:9 የኢትዮጵያ ሰዎች…እግዚአብሔር እንደሆንኩ ያውቁኛል።
የባለታሪኮችን ማንነት ለመግለፅ
- ዘኁ 12፥1 ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።
- ዘኁ 12፥1 ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።
- ኤር 38፥7 በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር።
- ኤር 38፣10 ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክም። ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው።
- ኤር 38፥12 ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፦ ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ አለው ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ።
- ኤር 39፥16 ሂድ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል።
- ሐዋ 8፥27 ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤
- ሐዋ 8፥27 ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤
- 1ኛ መቃ 34:2 የኢትዮጵያ መንግሥትም በእስክንድርያ መንግሥት ላይ ትጸናለች።
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን በጣም እናመሰግናለን በጣም ጥሩ ነው በዚሁ ቀጥሉበት።
LikeLike