መግቢያ
በሥላሴ አምሳል ተፈጥሮና በሥላሴ ስም ተጠምቆ ክርስቲያን የሆነ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር በመሠረታዊነት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገዋል። እንደየዘመኑም ስልጣኔ የውኃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የመጓጓዣ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ያስፈልጉታል። የእነዚህንም ወጪ ለመሸፈን ሥራን ይሠራል። ከሥራውም ሊጠቀምበት የሚችለውን ሀብት/ገንዘብ ያገኛል። ካገኘውም የእግዚአብሔርን ድርሻ (አሥራቱን በኩራቱን መባውን) ከሰጠ በኋላ ለቤተሰቡ ወጪ ይጠቀምበታል፣ ልጆችን እያስተማረ ያሳድግበታል፣ ኢንቨስት ያደርገዋል፣ ለወደፊት ያስቀምጠዋል፣ ወይም የተቸገሩትንም ይረዳበታል። ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገነ መሥራቱንም ጤናና አቅም እስካለው ድረስ ይቀጥላል።
ይሁንና በዘመናችን በክርስቲያኖች የግል ሕይወት ከገንዘብ ማግኛ መንገዶች፣ ከገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። ችግሮቹም በብዛት ስለገንዘብ ካለው የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ከግለሰቦች ገንዘብ ወዳድነትና ከገንዘብ አጠቃቀም ችግሮች የሚመነጩ ናቸው። በዚህ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚሰሙ ስብከቶችም በብዛት ችግሩን የሚኮንኑና ግለሰቦችን የሚፈርጁ እንጂ መፍትሔን የሚያመላክቱ አይመስልም። ምዕመናንም ገንዘብ እንዲሰጡ እንጂ ገንዘባቸውን እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው በቂ ትምህርት እየተሰጠ አይደለም። ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በክርስትና ሕይወት ያለውን ገንዘብን የሚመለከተውን አስተምህሮ፣ ተያያዥ ችግሮችን እና የመፍትሔ ሀሳቦችን እንዳስሳለን።
ገንዘብና ክርስትና
ገንዘብ የሰው ልጆች የሚገበያዩበት መሣሪያ (tool) እና የሀብት መጠን መለኪያ ነው። ገንዘብ የማግኛ ዋናው መንገድም ሥራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ (2ኛ ተሰሎ 3:10)” በማለት ክርስቲያን ሠርቶ ሀብት/ገንዘብ ማፍራት እንዳለበት በዚህም ለሥጋዊውና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ሊጠቀምበት (ሊገዛበት) እንደሚገባ በማያሻማ ሁኔታ ይገልፃል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በተግሳጹ (የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተግሳጽ አንቀጽ 20) ስለገንዘብ በሰፊው አስተምሯል። በተለይም ገንዘብን መውደድ፣ ለገንዘብ መገዛትንና በገንዘብ (ገንዘብን ለማግኘት) የማይገባ ነገር ማድረግን መንፈሳዊ ሕይወትን እንደሚጎዱ በጥልቀት አስተምሯል። እኛም እነዚህን በዝርዝር ቀጥሎ እናያቸዋለን።
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው።
ገንዘብን መውደድን በሚመለከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው (1ኛ ጢሞ 6:10)” በማለት ገልፆታል። ይህ ሲባል ግን የክፋት ሁሉ ሥር የተባለው ገንዘብ ራሱ ሳይሆን ገንዘብን መውደድ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ምክንያቱም ገንዘብ በራሱ የክፋትም ሆነ የጽድቅ ሥር ሊሆን አይችልም። ክፋትም ይሁን ትሩፋት የሚሆነው የሰው ልጅ የገንዘብ አጠቃቀም ነው። ሐዋርያው “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁ ይብቃችሁ (ዕብ 13:5)” በማለት ያስተማረው ይህንን ያጠናክረዋል። ሰው ገንዘብን ከወደደ ልቡን በገንዘብ ላይ ያደርግና “በፍፁም ልብህ፣ በፍፁም ነፍስህ፣ በፍፁም አሳብህ አምላክህን ወደድ” እና “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” (ማቴ 22:37) የሚሉትን ሕግጋት ይዘነጋል። ገንዘብን ያለመውደድ ሲባልም ገንዘብን መጥላት ይገባል ማለት አይደለም። ሁሉንም አመዛዝኖ ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን በማስቀደም መጽናት ይገባል ማለት ነው እንጂ።
ጠቢቡ ሰሎሞን “ገንዘብን የሚወድ ገንዘብ አይጠግብም (መክ 5:10)” እንዳለው የማይጠገብ ነገር መጨረሻ የለውምና የክፋት ሥር መባሉም ለዚህ ነው። ከሐዋርያት አንዱ የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ አምላኩን የሸጠው ለገንዘብ ባለው ልዩ ፍቅር ነበር። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው ዮሴፍን ለግብፅ ነጋዴዎች የሸጡትም እንዲሁ ለገንዘብ ነበር። ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ገንዘብን የሚወዱ ይሆናሉ (2ኛ ጢሞ 3:2)” እንዳለው ዛሬም ገንዘብን መውደድ እውነተኛዋን እምነት እስከ መካድ የሚያደርሳቸው፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲነግዱ የሚያደርጋቸው ብዙዎች መኖራቸውን እንገነዘባለን። በአንጻሩ የአባቶቼን ርስት በገንዘብ አልሸጥም ብሎ ሰማዕትነትን እንደተቀበለው ናቡቴ የቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገው በገንዘብ በኩል የሚመጣን የሰይጣን ፈተና ተቋቁመው በኑሮአቸው ሁሉ የእውነት ምስክሮች የሆኑና የሚሆኑ ቅዱሳን ምዕመናን የእምነት ጽናት ተምሳሌት ናቸው።
ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ “ለገንዘብና ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም (ማቴ 6:24)” ያለውም ሰው መገዛት ያለበት ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለማስተማርና ሰው በገንዘብ ሊገዛበት እንጂ ለገንዘብ ሊገዛለት እንደማይገባ ለማስገንዘብ ነው። ስለዚህም የሰው ልጅ ሁሉን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር እንጂ ሠርቶ ለሚያገኘው ገንዘብ ሊገዛ አይገባውም። ለገንዘብ መገዛት ማለት ገንዘብ ማግኘትን ብቻ ግብ አድርጎ መኖር፣ ከእምነት ይልቅ ገንዘብን መውደድ፣ ከባልንጀራ ይልቅ ገንዘብን መውደድ፣ ገንዘብን ማምለክ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ፍቅር ይለያል። ጌታችን “አትችሉም” ያለው አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት (ሁለት አምላክ ማምለክ) የማይቻለው ስለሆነ ነው። ነገር ግን ‘ለገንዘብ አትገዙ’ ማለት ‘ለገንዘብ አትሥሩ፣ ስለገንዘብ አታስቡ’ ማለት አይደለም፣ ገንዘብን አታምልኩት፣ ለገንዘብ ብላችሁ ከቅን ህሊናችሁ፣ ከጸናች ሃይማኖታችሁ አትለዩ ማለት ነው እንጂ። ለገንዘብ መገዛትም ‘ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ (ዘፀ 20:1)’ ያለውን ትዕዛዝ መሻር ስለሆነ ከአምልኮተ ጣኦት ይመደባል።
የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለም።
በክርስትና አስተምህሮ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚወገዘው ተግባር ሳይሠሩ ገንዘብ ማግኘት ወይም ገንዘብ ለማግኘት መሞከር ነው። በስርቆት፣ በሙስና፣ በማታለልና ይህንን በመሳሰሉት መንገዶች የራስ ያልሆነን ገንዘብ ማግኘት ወንጀልም ኃጢአትም ነው። ክርስቲያን ገንዘብ ማግኘት ያለበት በመሥራት ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ያስተምረናል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከእርሱ ዘንድ መጥተው “እኛ ደግሞ ምን እናድርግ” ያሉትን ጭፍሮች ሲገስፅ “ደሞዛችሁ ይብቃችሁ (ሉቃ 3:14)” ማለቱ ሰው ሠርቶ የሚያገኘው ሊበቃው እንደሚገባ ያስተምረናል። ያልተለፋበት ገንዘብም እንደ ጉም የሚተን ብኩን መሆኑን ብዙዎች የሚመሰክሩት ነው። ሁሉም በልክ መሆን እንዳለበትና የሰው ልጅም ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ጌታችን ሲያስተምርም (ሉቃ 12:15) “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል።
ገንዘብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናል።
የሰው ልጅ ሠርቶ በላቡ ያገኘውን ገንዘብ ለሥጋዊና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል እንጂ ኃጢአትን ለመሥራት ወይም ሌላውን ወንድሙን/እህቱን ለመጉዳት ማዋል የለበትም። ይልቁንም የራሱን ኑሮ ለመምራት፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት ሊያውለው ይገባል። ይህንንም ሲያደርግ ብልና ዝገት በማያገኙት በሰማይ መዝገብን ያከማቻል። ጌታችን “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና (ማቴ 6:21)” በማለት ያስተማረው ገንዘቡን (ያለ ከንቱ ውዳሴ) የሚመጸውት ልቡም በሰማያት (መዝገቡ ባለበት) ይሆናል ማለቱ ነው። “ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል (ምሳ 37:16)” የተባለውም ለዚህ ነው። ክርስቲያን ገንዘቡን ለእውነትና በእውነት ብቻ መጠቀም አለበት። ሐናንያና ሰጲራ የሚባሉ ባልና ሚስት ገንዘባቸውን ለሐዋርያት ኅብረት ለመስጠት ወስነው ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን በማታለላቸው ተቀጥተዋል (ሐዋ 5:1-10)። በሌላም በኩል ባልተገባ መንገድ (በጥንቁልና) ባገኘው ገንዘብ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመግዛት የተመኘው ሲሞንም እንዲሁ ከገንዘቡ ጋር ጠፍቷል (ሐዋ 8:20)።
ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ አታድንም!
የገንዘብ ባለጠጋ ሆኖ የተወለደ የለም። ሀብትም የመንፈሳዊ ጸጋ መለኪያ አይደለም። ማንኛውም የሰው ልጅ ጠንክሮ ከሠራም ባለጠጋ መሆን ይችላል። ነገር ግን ባለጠግነትን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። አንዳንድ ባለጠጎች ብዙ (ጊዜ) ገንዘብ በመስጠት ጽድቅ የሚገኝ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ባለጠጋ በምድር ‘ተድላን’ ስላገኘ ወደ መንግስት ሰማያት የማይገባ ይመስላቸዋል። ባለጠግነትን ብቻ የመጨረሻ ግብ አድርጎ አግባብ ባልሆነ መንገድ ለመክበር መሞከርም ለክርስትና ሕይወት ታላቅ ፈተና መሆኑ እርግጥ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና (ምሳ 23:4-5)” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ጌታችንም በትምህርቱ “ለባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው፣ ባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል (ማቴ 19:23)” ብሎ ያስተማረው ባለጠግነት የክርስትና ሕይወት ፈተና መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ጌታችን ይህንን የተናገረው ከአምላኩ ይልቅ ገንዘቡን ይወድ ስለነበረው አይሁዳዊ ነበር። ይህንንም ሲል ሰው ከአምላኩ ይልቅ ሀብቱን ከወደደ ወይም በሀብት ብዛት ጽድቅን ለማግኘት ካሰበ መንግስተ ሰማያት መግባት ከባድ ነው ለማለት እንጂ በእውነት ሠርቶ ሀብታም የሆነ፣ እውነተኛ እምነት ያለውና መልካም ምግባር ያለው ባለጠጋ መንግስተ ሰማያት አይገባም ማለቱ አይደለም። በተጨማሪም በዘርና በዘሪው ምሳሌ ሲያስተምርም “በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል (ማር 4:19)” በማለት የተረጎመላቸው ባለጠግነት የክርስትና ሕይወት ዕድገት ማነቆ መሆኑን ሲያስገነዝበን ነው።
ሐዋርያው ያዕቆብ ስለባለጠጎች በተናገረበት መልእክቱ “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል (ያዕ 5:1-6)” በማለት ባለጠግነትን መውደድ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል አስተምሯል። በተመሳሳይም ጠቢቡ ሰሎሞን “በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል፣ በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች” ብሎ ስለባለጠግነት በጥበብ አስተምሮናል። በተጨማሪም “በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና” በማለትም ስለ ገንዘብ አጠቃቀም ተናግሯል (ምሳ 11:28 13:11 17:16)።
ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ አታድንም። ጠቢቡ ሰሎሞን ስለዚህ ሲናገር “በቍጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች (ምሳ 11:4)” ብሏል። የሰው ልጅም በገንዝቡ ከመመካት ወጥቶ ገንዘብ ማግኘት እንዲችል ጤናና ጉልበት፣ እውቀትን ጥበብን የሰጠውን እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ይገባዋል። ስለዚህ ነው እግዚአብሔር ለባለሟሉ ለሙሴ “ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ (ዘዳ 8:18)” በማለት የተናገረው። ባለጠግነት ከእግዚአብሔር ቁጣ እንደማያድን፣ ይልቁንም የተሰጠንን ባለ ጠግነት ለተቸገሩት ካላካፈልን መጨረሻችን የዘላለም ሞት መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ካስተማረን የነዌ ታሪክ መማር እንችላለን።
ለድሃው ደሃ ስለሆነ ብቻ አይራራለትም!
የገንዘብ ደሀ ሆኖ እንዲኖር ተፈርዶበት የተወለደ ሰው የለም። ነገር ግን ሰው ያለውን ዕውቀትና ጉልበት ተጠቅሞ ተግቶ ካልሠራ ወይም ያገኘውን ሀብት ባአግባቡ ካልያዘ ደሃ መሆኑ አይቀርም። በተፈጥሮአዊና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ደሃ የሚሆኑ ሰዎችም አሉ። ሰው በዚህ ምድር በድህነት ስለኖረ ብቻ በሰማይ ጽድቅን አያገኝም፣ አይኮነንምም። “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” የሚለውም ከምድራዊ ድህነት ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም። በሀብታሙ ሰው በነዌ ደጅ የነበረው ደሃው አልዓዛር ጽድቅን ያገኘው ደሃ ስለነበር ብቻ አልነበረም። ነዌም የተኮነነው ሀብታም ስለነበረ አይደለም። አልዓዛር በእምነቱ፣ በንጽሕናው ጽድቅን አገኘ። ነዌም በትዕቢቱና በስግብግብነቱ ተኮነነ (ሉቃ 16:19)። ስለዚህ ነው ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው “እግዚአብሔር ለሁሉም እንደየሥራው ይሰጠዋል፣ ለድሃው ደሃ ስለሆነ አይራራለትም፣ ለባለጠጋውም ባለጠጋ ስለሆነ አይፈርድበትም” የሚለው። በእርግጥ ገንዘብ የሌለው ደሃ ብዙውን ጊዜ በረሃብና በመቸገር ሲኖር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የሚሠሯቸውን ሌሎች ኃጢአቶችን ላይሠራ ይችላል። በሌላም በኩል ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የሚሠጡትን ያህል መስጠት አይችልም። ነገር ግን ሁሉም ሰው ኃጢአትን ይሠራል፣ በአቅሙም ሌላውን ወንድሙን መርዳት ይችላል። ስለዚህ ምድራዊ ድህነትም ይሁን ሀብት የጽድቅ መስፈርቶች አይደሉም።
የገንዘብ አጠቃቀም ጥበብ
ብዙ ሰው አተኩሮ የሚተጋው ገንዘብ ለማግኘት ነው። ስለገንዘብ አጠቃቀም ግን ብዙም ትከረት አይሰጥም። በዘመናችን ያሉ ሰባክያነ ወንጌልም የሚያተኩሩት ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እንዲሰጡ መወትውቱ ላይ ነው እንጂ ምዕመናን በገንዘባቸው እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አይደለም። ዋናው መሠረታዊው ጥያቄና ክርስቲያናዊው አስተምህሮ ሊያተኩርበት የሚገባው ግን “በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያለው የገንዘብ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት?” የሚለው ነው። የክርስቲያን ቤተሰብ የገንዘብ አጠቃቀም በዕቅድ የሚመራና ቅድሚያ መሰጠት ላለባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለገንዘብ አጠቃቀም በብዙ ምሳሌዎች ያስተምራል። ጠቢቡ ሰሎሞን (ምሳሌ 6:6-8) “አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች” በማለት የገንዘብ አጠቃቀምን (በተለይም መቆጠብን) ከገብረ ጉንዳን መማር እንዳለብን ይነግረናል። እንዲሁም (ምሳ 21:20) “የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል። አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል” በማለት ጠቢብ የከበረ መዝገብ እንዳለው ያስረዳል። ክርስቲያንም በገንዘብ አጠቃቀም ችግር ምክንያት ወደ ብድር መግባት እንደሌለበት ሲናገር (ምሳሌ 22:7) “ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” ብሏል። በአጠቃላይ የገንዘብ አጠቃቀም የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ሊያተኩር ይገባል።
ከሰጠኸኝ ሁሉ ከአሥር አንዱን እሰጥሃለሁ።
ክርስቲያን ሠርቶ ከሚያገኘው አሥራት (10% ወይም ከአሥር አንድ) ለእግዚአብሔር ይሰጥ ዘንድ ይገባዋል (ዘፍ 28:22)። መቼም የጸጋ ሁሉ ምንጭ የሆነ አምላክ የእኛን ምድራዊ ገንዘብ እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና በቸርነቱ የሰጠንን፣ የባረከልንን ገንዘብ በተራቡ፣ በተጠሙ፣ በታመሙ፣ በተቸገሩ፣ በተሰደዱ፣ በማጣት በተጨነቁ ሰዎች አድሮ ይቀበለናል። ለእነዚህ ሰዎች በልግስና የምንሰጠው ምጽዋትም ለባለጸጋው አምላካችን እንደምንሰጠው እንደሚቆጠር ጌታችን በወንጌል ተናግሯል። በምድር ያለች ቤተ ክርስቲያንን የጽድቅ አገልግሎት ስንደግፍ ለቤተ ክርስቲያን አምላክ እንደሰጠነው ይቆጠራል። ይህም ቤተ ክርስቲያን ለምትፈጽመው መንፈሳዊ (የወንጌል) አገልግሎት እንዲውል ነው። ይህ ማለት ግን የተቀረውን 90% የእኛ ስለሆነ “እንደፈለግን እንጠቀምበት” ማለት አይደለም። ሁሉም ገንዘብ የእግዚአብሔር ስለሆነ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ሕይወታችን እናውለው ማለት ነው እንጂ።
ከዚህ ውጭ በሃይማኖት ስም ለሚያታልሉና የራሳቸውን ጥቅም ለሚያሳድዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ምዕመናን ሠርተው ያፈሩትን ገንዘባቸውን መስጠት የለባቸውም። ምዕመናንም አሥራታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሚሠጡት ተምረው፣ ተረድተውና አምነውበት በራሳቸው ፈቃድ እንጂ ተወትውተው (ተገደው) መሆን የለበትም። ከአሥራት ጋር በተያያዘ ሌላው ጉዳይ ምእመናን በየአጥቢያው ቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ ያላቸው አመኔታ (trust) መቀነስ ነው። የሚሠጡት አሥራት ለተፈለገው የወንጌል አገልግሎት እንደሚውል ማረጋገጫ ይፈልጋሉ። ይህንንም በግልጽና በዘመናዊ አሠራር ማረጋገጥ ይገባል እንጂ “የምዕመናን ድርሻ መስጠት ብቻ ነው፣ ሌላው አይመለከታችሁም” በማለት ኋላቀርና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር የማይሄድ ምላሽን መስጠት አይገባም። ምዕመናንን አስራት እንዲያወጡ የምትጠይቅ እያንዳንዷ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለተቸገሩት ገዳማትና አድባራት በልግስና ልትሰጥ ይገባል እንጂ በግለሰቦች የምናወግዘው ስግብግብነት በተቋም ደረጃ እንዲደገም መፍቀድ የለብንም። በግልፅ በሚታወቅ አሰራር እያንዳንዱ አጥቢያ ከሙዳየ ምጽዋቱ ለድሆች መመጽወት፣ ከመብዓው ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ማካፈል እንዳለበት መዘንጋት የለበትም። ይሁንና በዘመናችን ያሉ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ለምዕመናን ግላዊ ሕይወት አርአያ የሚሆን አሰራር ስለማይከተሉ ሁላችንም በየአቅማችን ይህን መሰል የአስተሳሰብ ልዕልና ቃለ እግዚአብሔርን መነገጃ በሚያደርጉ ብልጣ ብልጥ አገልጋዮች እንዳይደፈን ልንጥር ይገባናል።
ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ስጡ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ (ሮሜ 13:7)” እንዳለው ክርስቲያን ሠርቶ ከሚያገኘው ገንዘብ ለመንግስት የሚገባውን ክፍያ (ግብር ወይም ቀረጥ) በወቅቱና በአግባቡ መክፈል ይጠበቅበታል። ይህ መንግስት ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ወጪ ለመሸፈን የሚውል ነውና። የመንግስትን ግብር ወይም ቀረጥ ማስቀረት ወይም ላለመክፈል ህጋዊ ያልሆነ አሠራርን መከተል (ለምሳሌ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ በርካታ የሀገራችን ሰዎች እንደተለመደው ለማጭበርበር በማሰብ የእጅ በእጅ ካሽ ክፍያን መጠቀም) ኃጢአትም ወንጀልም ነው። ከመንግስት ለሚገኘው አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ አለመክፈል ከሌብነት ተለይቶ አይታይም። ይህም “አትስረቅ” ያለውን ትዕዛዝ መተላለፍ ነው። ስለዚህ ክርስቲያን የመንግሥትን ድርሻ ሳንቲም ሳያስቀር መስጠት ይኖርበታል። የመንግስትን ድርሻ በሚገባ ሳይከፍሉ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ገንዘብ መስጠትም ከተጠያቂነት አያድንም። ለሁሉም የሚገባውን እንደሚገባው መስጠት ያስፈልጋል እንጂ።
ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝመሩ ለጢሞቴዎስ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል” (1ኛ ጢሞ 6:7-8) እንዳለው ሰው በምድር ላይ ሲኖር ለኑሮ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ለማሟላት ገንዘብን ይጠቀማል። ለዚህም “በመጠን ኑሩ” (1ኛ ጴጥ 5:8) እንደተባለው ሁሉንም በልክና በእቅድ መምራት ያስፈልጋል። የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሚያስፈልጉበት መጠንና ጊዜ ገዝቶ ሳያባክኑ በአግባቡ መጠቀም ከክርስቲያን ይጠበቃል። በማኅበራዊ ጉዳዮችም የሚደረገው ተሳትፎ እንዲሁ በአግባቡና በዕቅድ ሊሆን ይገባዋል። ይህም እንደየቤተሰቡ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ቤተሰቡ ከትምህርት ይሁን ከልምድ በሚያገኘው ክህሎት ላይ ተመስርቶ በማቀድ፣ በመተግበርና በመመዘን ሊመራው ይገባል። ጌታችንም በወንጌሉ (ሉቃስ 14:28) “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ገንዘቡን የማይቈጥር ማን ነው?” በማለት ሰው የሚያቅደውንና ለሚያደርገውን ነገር ሁሉ ባለው ገንዘብ ልክ መሆን እንዳለበት አስተምሯል።
መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና (ዕብ 13:16) እንዳለው ሰው ያለውን ሊያካፍል ይገባዋል። ክርስቲያን ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ የራሱ የሆኑት ቤተሰቦቹን ሊደግፍ ይገባዋል (1ኛ ጢሞ 5:8)። ከላይ እንደተገለፀው ሌሎችም የተቸገሩና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን አቅሙ በፈቀደለት መጠን ሊደግፋቸው ይገባል። በዚህም በምድር የወገኖቹን ችግር ለመፍታት የራሱን ድርሻ ያበረክታል። በሰማይም ለዘላለም ሕይወት የሚሆነውን መዝገብ ያከማቻል። እነዚህን ወገኖች መደገፍ እየቻሉ አለመደገፍ ከኃጢአት እንደሚቆጠርም ማስተዋል ያስፈልጋል (ያዕ 4:17)። ይህ የትሩፋት ሥራዎች ተብለው የሚታወቁትን መፈጸም ስለሆነ ልዩ ትኩረት ሊደረግበትም ይገባል። ለቤተ ክርስቲያን አሥራት ሰጥቻለሁና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አልደግፍም ማለትም አይቻልም። በተጨማሪም ይህ አገልግሎት ውዳሴ ከንቱን እንዳያመጣ ሰማያዊ ዋጋን ብቻ ዓላማ አድርጎ መፈጸም ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ 9:7) “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ያለውም ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። የተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራት የሚሰሩትን በጎ አገልግሎት ተጠያቂነት ያለበት አሰራርን በመከተል በገንዘብ መደገፍም በዚህ ሥር የሚታይ ነው።
በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው።
ክርስቲያን ለነገ ሕይወቱ ተስፋ የሚያደርገው እግዚአብሔርን ነው። ነገር ግን የራሱም ድርሻ ስላለው “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም እንዲህ እናደርጋለን በሉ (ያዕ 4:17)” እንደተባለው ለወደፊት እና ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ (Saving)፣ እንዲሁም ባለው ገንዘብ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት (investment) ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር ሠርቶ ለራስም ተጨማሪ ገንዘብን ማግኘት ይችላል። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። ‘ለማግኘትም ለማጣትም ጊዜ አለው’ እንደተባለ ይህንን ማድረግ ይገባል። ለነገ ብሎ ገንዘብ ማጠራቀም የእምነት ማነስ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይልቁንም ነገም እኖራለሁ ብሎ በእግዚአብሔር የመታመን እንጂ። ጠቢቡ ሰሎሞን (ምሳ 13:22) “ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች” ያለውም ቁጠባ ለመጪው ትውልድ ድረስ እንደሚጠቅም ያስረዳናል። በተጨማሪም (ምሳ 10:4-5) “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉህ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል” በማለት ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም ገንዘብን የመቆጠብ ጥበብን አስተምሯል።
በአጠቃላይ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብና ጉልበት ተጠቅሞ በመሥራት ገንዘብ ማግኘት (ሀብት ማፍራት) ይገባዋል። ያፈራውንም ሀብት መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወቱን ለሚጠቅም ዓላማ ሊያውለው ይገባል። ይህንንም ሲያደርግ እግዚአብሔርን በመፍራትና የሰውንም ልጅ በማክበር ሊሆን ይገባዋል። ከዚህ ውጭ ባልተገባ መንገድ ገንዘብን ለማግኘት መሞከር፣ በተገባ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ላልተገባ ዓላማ ማዋል፣ ገንዘብን መውደድ፣ ለገንዘብ መገዛትና የመሳሰሉት መንፈሳዊምና ሥጋዊ ሕይወትን የሚጎዱ ናቸው። በተጨማሪም ክርስቲያን ገንዘብን ለማግኘት ተግቶ ከመሥራት ጎን ለጎን ባገኘው ገንዘብም ቁም ነገር ሠርቶበት ለማለፍ መትጋት ይኖርበታል እንላለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
LikeLike