የክርስቲያን ደሴት

የክርስቲያን ደሴት የሚለው አገላለጽ በብዙዎች ዘንድ በተለያየ መንገድ የሚጠቀስ ሀረግ ሆኗል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ጽሑፎች እንዲሁም በአንዳንድ መዝሙራትም ጭምር ይህንን አገላለፅ የመጠቀሙ ነገር የበለጠ እየተለመደ መጥቷል። ይህ አገላለጽ በዋናነት ለፖለቲካዊ ዓላማ የሚውል በመሆኑ በተለያዩ አካላት ዘንድ በድጋፍም በተቃውሞም የተለያየ ትርጉም ሲሰጠውም አስተውለናል። ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ስላለው መንፈሳዊ ትርጉምና አንድምታ በተገቢ መልኩ ተብራርቶ ቀርቧል ማለት አይቻልም። የዚህች የአስተምህሮ ጦማር ዓላማም በመንፈሳዊ እሳቤ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነትና በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ይህ አገላለጽ ያለውን ትርጉም ማብራራት ነው።

በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ (Lexical definition) ደሴት (Island) ማለት በውኃ የተከበበ ምድር/የብስ ማለት ነው። ይህም በወንዝ፣ በሐይቅ፣ በባሕር ወይም በውቂያኖስ ውኃ የተከበበና ብዙውን ጊዜ በውኃ ከተሸፈነው መሬት ከፍ ያለ ምድር ነው። መጠኑም የውኃው መጠን ሲጨምር (ሲሞላ) የሚቀንስ፣ የውኃው መጠን ሲቀንስ (ሲጎድል) የሚጨምር ነው። ደሴት ብዙውን ጊዜ ከባሕር በሚነሱ ነፋሳትና ወጀቦች ይመታል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ በላዩ ያሉት አፈርና ዕፅዋት ወደ ውኃው ተጠርገው ሊገቡ ይችላሉ። በሌላ መልኩ ደሴት ለመርከበኞችና ለሌሎች የባሕር ላይ ተጓዦች የማረፊያ ቦታ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስም ብዙ ደሴቶችን እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ራእዩን ያየባትና የጻፈባት የፍጥሞ (Patmos) ደሴትና ቅዱስ ጳውሎስ የሰበከባት የመላጥያ (Malta) ደሴት ይገኙበታል። በቤተ ክርስቲያናችን ከሚታወቁት ከአሥራ አራቱ ቅዳሴያት አንዱን የደረሰው ቅዱስ ኤጲፋንዮስም የደሴተ ቆጵሮስ (Cyprus) ሊቀ ጳጳስ ነበር። ዛሬም በኢትዮጵያ ብዙ ገዳማትና አድባራት የሚገኙባቸው የጣና ሐይቅና የዝዋይ ሐይቅ ደሴቶችም ተጠቃሽ ናቸው።

በተለያዩ አካላት ዘንድ “የክርስቲያን ደሴት” የሚለው አገላለፅ ነው ብለው የሚያምኑትን ወይም እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ምድራዊ ሃይማኖት ቀመስ ፖለቲካዊ ድንበር ለማመልከት ወይም በተቃውሞ ለመተቸት ቢውልም በመንፈሳዊው ዐውድ ግን “የክርስቲያን ደሴት” የሚለው አገላለፅ የሚገባት እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ናት እንላለን። ለእውነተኛ ክርስቲያኖችም ደሴታቸው (ማረፊያቸው) አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና፣ ኩላዊት የሆነችው በዚህች ምድር ላይ ያለችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች የክርስቲያን ደሴት ብትባል የተገባ ነው። ይህንንም አማናዊ ምሳሌነቷን ለማስረዳት የሚከተሉትን ንጽጽሮች (Analogies) እንመልከት።

1. ደሴት በውኃ የተከበበ ነው።

ደሴት በውኃ/በባሕር የተከበበ ምድር/የብስ ነው። የተከበበ ነው ሲባልም ደግሞ ዙሪያውን (360 degree) ነው። በባሕር በተመሰለ ዓለም የተከበበችው በተጋድሎ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ናት። በዓለም፣ በዓለማውያንና በዓለማዊ አስተሳሰብ ተከብባ መንፈሳዊነትን የምታስተምር ደሴት እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት። በዓለም ተከብባ የሰውን ልጅ ለቅድስና የምታበቃዋ ደሴት ቤተ ክርስቲያን ናት።

ዓለም በጥላቻ፣ በጦርነትና በበቀል ሲነዳ፣ አብራ ተሳፍራ ወደ ወሰዷት የምትነዳ የመለካውያን ቋት ሳትሆን “በጊዜውም አለጊዜውም” ጥላቻን፣ ጦርነትንና በቀልን አውግዛ በማዕበል መካከል የክርስቶስን ሰላም የምትሰብክ እውነተኛ፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ማለቂያ በሌለው የዓለም ጥላቻ ውስጥ የፍቅርና የይቅርታ ወደብ ያለባት እውነተኛ የክርስቲያን ደሴት ናት። በዓለም የተከበበች ብትሆንም እግዚአብሔርን ብቻ እያመለከች የምትኖረው ደሴት ቤተ ክርስቲያን ናት።

2. ደሴት ከፍታ ያለው ምድር ነው።

ደሴት በውኃ ከተሸፈነው ምድር ከፍ ያለ ነው። በውኃ ውስጥ ያለው መሬት ዝቅ ያለ ስለሆነ ለውኃው ማደሪያ ሆኗል። ደሴት ግን ከፍ ያለ ስለሆነ ከባሕሩ ወለል በላይ ከፍ ብሎ ይታያል። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው እምነትና ምግባርም እንዲሁ በሁሉም መስፈርት ከዓለም ሀሳብ ጋር የማይወዳደር ሰማያዊ ዋጋን የሚያስገኝ ነው። እንዲሁ ወደ ሰማያዊ ከፍታ (ጽድቅ) የሚያደርሱ ምስጢራት የሚፈጸሙት በዚችው ቤተ ክርስቲያን ነው። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች ደሴትና ከዓለም ከፍ ብላ የምትገኝ ለሰማያዊ ክብር የምታበቃ ናት።

ጌታችን በወንጌል “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።” (ማቴ 5:14) እንዳለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ያልተበረዘ ወንጌል በሰማያዊ አገልግሎት፣ በፍጹም መንፈሳዊ ሥርዓት የምትገልጥ በመሆኗ ከምድር ከፍ ብላ የምትታይ የክርስቲያኖች ደሴት ናት። የክርስቲያን ደሴት መሆን በጩኸት ብዛት “ናት! ናት!” በማለት የሚገኝ እንዳልሆነ ግን መረዳት ያስፈልጋል። ከስም በላይ ግብር የተሻለ ገላጭ ነውና። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በእምነት ብቻ የምትገለጥ አለመሆኗን ተገንዝበን የምናምነውን እምነት ከምግባር ጋር መግለጥ የቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች የሆንን የምዕመናንና የካህናት ግዴታ ነው።

በሌብነት በተሞላ ዓለም የሌብነትና የማጭበርበር ሰርቶ ማሳያ የሚመስል የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ በጣዖት አምልኮ በተተበተበ ማኅበረሰብ ለራሳቸውና ለጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጭፍን ግለሰባዊና ተቋማዊ አምልኮን የሚያለማምዱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ማኅበራት፣ በጥላቻ በተሞላ፣ በቂም በቀል በረከሰ ማኅበረሰብ ውስጥ ጥላቻን የሚያሰማምር፣ ቂምን የሚንከባከብ አስተሳሰብን “የቤተ ክርስቲያን” አስመስሎ የሚሸቅጥ “አገልጋይና ተገልጋይ/ካህንና ምዕመን” በበዛበት ከምድር ከፍ ብላ የልዕልና ማሳያ መሆን ያለባት ቤተ ክርስቲያን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በተቃርኖ “በሸለቆ ውስጥ መደበቋ” ከስያሜ በላይ ሊያሳስበን ይገባል።

3. ደሴት ልዩ የማረፊያ ስፍራ ነው።

ደሴት ለባሕር ተጓዦች ማረፊያ ነው። ደሴት ሰው አድካሚውን የባሕር ጉዞ ጨርሶ ልቡን የሚያሳርፍበት ስለሆነ ልዩ ማረፊያ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ቤተ ክርስቲያንም የዓለም ፈተናና ኃጢአት ያደከማቸው ሰዎች የሚያርፉባት የምሕረት ዐውድ ናት። ከኃጢአት ማሠሪያ በንስሐ ተላቀውም ለሰማያዊው ክብር የሚያበቃቸውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉባት የቅድስና ደሴት ናት። በመጨረሻም ክርስቲያኖች ከሥጋ ድካም ሲያርፉ ሥጋቸው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠባበቅባት ጊዜያዊ ማረፊያቸው ናት። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች ደሴት (ማረፊያ) ናት።

ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ክፋት የምናርፍባት የክርስቲያኖች ደሴት እንጂ የዓለምን ክፋት “በጥቅስ አስደግፈን” በልዩ ሁኔታ የምናሽግባት የነጋዴ መካዝን አይደለችም። ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ከዓለም የተለየ ድምፅ ፈልገው እንጂ በዓለም የሚያውቁትን ክፋት አለባበስና አነጋገር በቀየሩ በግብራቸው ግን ተመሳሳይ የሆኑ ሰዎችን ድምፅ ፈልገው እንደማይመጡ መረዳት የአገልጋዮች ኃላፊነት ነው። አገልግሎታችን ለተቸገሩት ማሳረፊያ እንጂ እረፍት ፈልገው የመጡትን ከዓለም የተረፈ ቀንበር ማሸከሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል።

4. ደሴት ነፋስና ወጀብ የሚበዛበት ነው።

ደሴት ብዙ ጊዜ ከባሕር በሚነሱ ነፋሳትና ወጀቦች ይመታል። ቢሆንም ግን አይሰጥምም። ቤተ ክርስቲያንም ከዓለም በሚነሱ ክፉ አስተሳሰቦችና ክፉ አሳቢዎች ስትፈተን ትኖራለች። መሠረቷ ግን ክርስቶስ ስለሆነ ጸንታ በመኖሯ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ይገለጣል። በደሴት ላይ የሚመጡ ነፋሳትና ወጀቦች በዕፅዋትና በሌሎች በደሴቱ ላይ ባሉ አካላት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፣ የተወሰኑትንም ወደ ባሕር ጠርገው ያስገባሉ። በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚመጡ ፈተናዎችም እንዲሁ የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ሕይወት ይጎዳሉ፣ አንዳንዶችንም ወደለየለት ዓለማዊነት ይወስዳሉ።

5. ደሴት ከዋናው ምድር የራቀ ልዩ ስፍራ ነው።

ደሴት ከዋናው ምድር (Main land) የራቀ ጸጥታ ያለበትና አትኩሮትን ለሚሹ ሥራዎች የሚመች ስፍራ ነው። ደሴት ብዙውን ጊዜ ከዋናው የብስ/ምድር የራቀ ሌላ (ብዙውን ጊዜ አነስተኛ) ምድር ስለሆነ ጫጫታና ሁካታ የለበትም። በአንጻሩ በደሴት ባለው የአየር ጠባይ ብዙውን ጊዜ ከበድ ስለሚል በብዙዎች አይዘወተርም። እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያንም የክርስቲያን ደሴት ናት ስንል ጫጫታና ሁካታ ከሞላበት ዓለም ርቃ የምትገኝ፣ ሰውም ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርባት የጸሎት ስፍራ ናት ማለታችን ነው። በአንፃሩ በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው ከዓለም የባሰ በቀለኝነት፣ ጭፈራ፣ ገንዘብን መውደድ፣ የጥላቻ አስተሳሰብና ተግባር የሚታይበት ቦታ ደሴትነቱ በክርስቶስ ስም ለተጠሩ ክርስቲያኖች ሳይሆን የክፉ ግብር ልጆችን ለሚወክሉ ሰቃልያነ እግዚእ ነው። የቤተ ክርስቲያን ዐውድ ግን መንፈሳዊ ነገር ብቻ የሚነገርበት ስለሆነ ከዓለማዊ አስተሳሰብ የራቀ ነው። ይህም ለዓለማዊ (ለሥጋ) አካሄድ የማይመቹ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደትና ምፅዋትን ገንዘብ አድርጉ፣ ምድራዊውን ተድላ ሳይሆን ሰማያዊውን ሕይወት አስቡ የሚል ነው።

6. ደሴት የአእዋፍ ልዩ ዝማሬ የሚሰማበት ስፍራ ነው።

ደሴት በስነ-ሕይወት የበለጸገና ብዙ ዕፅዋትና አእዋፋት የሚኖሩበት ስለሆነ ልዩ የሆነ የአእዋፍ ዝማሬ ዕለት ዕለት ይሰማበታል። በዙሪያው ያለው ባሕር ግን የወጀብ ድምፅ ሲያናውጠው ይውላል፣ ያድርማል። ቤተ ክርስቲያንም የሰማያውያን መላእክት ዝማሬና የሰው ልጆች ምስጋና ዕለት ዕለት የሚሰማባት አውድ ስለሆነች የክርስቲያኖችና የክርስትና ደሴት ናት። የአእዋፋቱ ዝማሬ ከደሴቱ በሚርቀውና በተቀረው የባሕር ክፍል እንደማይሰማው ሁሉ መንፈሳዊ ዝማሬም በዓለም ሳይሆን በደሴቲቱ በቤተ ክርስቲያን ነው የሚሰማው። ባሕር ወጀብ ሲያናውጣት እንደሚኖረው ሁሉ ዓለምም በዓለማውያን አሥረሽ ምቺው ስትናጥ ትኖራለች። ከክርስቲያን ደሴትነት ተነጥላ በአልጠግብ ባይ ክፉዎች የምትዘወር የዘመናችን ርኩሰት መገለጫ የሆኑ ግብራትን ያለ ፀፀት የሚፈፅሙ ምዕመናንና ካህናት የበዙባት፣ በስም ግን “የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን” የምትባል ስብስብም ዓለምን የምትመስል፣ ራሷንም ከዓለም ውርደትና ክፋት መነጠል ካልቻለች “ነኝ!” በማለት ብቻ “የክርስቲያን ደሴት” ሆኖ መቀጠል እንደማይቻል የታወቀ ነው።

7. ወደ ደሴት ለመድረስ ባሕሩን ማለፍ ይጠይቃል።

ከዋናው የብስ ወደ ደሴት ለመድረስ ባሕሩን መሻገር (ማቋረጥ) የግድ ነው። ለዚህም ጀልባ ወይም መርከብ ያስፈልጋል። በባሕር ውስጥም ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደ አዞና አሳ ነባሪ ያሉ አደገኛ የባሕር አራዊትን ማለፍ ይጠይቃል። የጸሎት ቤት ወደሆነችው ቤተ ክርስቲያን ለመድረስም የተለያዩ የዓለምን ፈተናዎች ማለፍ ይጠይቃል። በባሕር አራዊት የተመሰሉ የዲያብሎስ ሽንገላዎችንም ማለፍ ይጠይቃል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች የዓለምን ፈተና አልፈው የሚደርሱባት ልዩ ስፍራ ስለሆነች የክርስቲያን ደሴት መባልዋ ተገቢ ምሳሌ ነው። መጠንቀቅ የሚገባው ሰዎች ከባሕር አራዊት ሸሽተው ወደብ ሊያደርጓት የሚመጡባትን ቤተ ክርስቲያን አደገኛዎቹ የባሕር አራዊት መደበቂያ አድርገው የበለጠ ጉዳት እንዳያደርሱ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ደሴት ናት።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን “የክርስቲያን ደሴት” እንድትሆን መርጧታል። ጌታ በወንጌል “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል። እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት።” (ማቴ 21:13) እንዳለ የክርስቲያን ደሴት እንድትሆን በጸጋው የለያትን (የቀደሳትን) ቤተ ክርስቲያን “ሰይጣንን የሚያስናፍቅ” የጥላቻ ስብከት ሰገነት፣ ይቅር ባይነትን የሚገፋ ደርዝ የሌለው ጦረኝነት ማስተላለፊያ ዐውድ፣ ዓለማውያን ለክፋታቸው ማስተሰረያ የሚመረኮዟት ምርኩዝ የሚያደርጉት ሰዎች ዋጋቸው ምን ይሆን?!

ስለዚህ በባሕር በተመሰለ ዓለም ውስጥ ክርስትናን የምትሰብክ፣ ሰማያዊውን አምላክ የምታመልክ፣ በምድር ላይ ሰማያዊ ምሥጢራትን የምትፈጽምና ለሰማያዊ ክብር የምታበቃ ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ደሴት ናት እንላለን። በዓለም ውጣ ውረድ የደከሙት መጥተው በንስሐ ዕረፍት የሚያገኙባትና ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙባት በባሕር ውስጥ ከፍ ያለች ተራራ (ደሴት) እርስዋ ናት። ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም ድካም በሞተ ሥጋ ሲያልፉም ዐጽማቸው የሚያርፍባት፣ በትንሣኤ ዘጉባኤም የሚነሱባት የምሕረት አደባባይ ቤተ ክርስቲያን ናት። የዓለም ፈተና ቢበዛም የማትናወጥ ባሕር ውስጥ የጸናች ደሴት ናት። በዓለምና በዓለማዊ አስተሳስብ ያለ ሁሉ ወደዚህች የክርስቲያን ደሴት መጥተው ለነፍሳቸው ዕረፍትን ሊያገኙ ይገባል እንላለን።

የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር በደሴት የተመሰለች ቤተ ክርስቲያንን አጽንቶ ይጠብቅልን። አሜን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s