እንደ መግቢያ
የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ የእውነተኛ መንፈሳዊ መምህር ትኩረት ምን መሆን እንዳለበት ባስረዳበት መልዕክቱ “አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ (ግሪክ) ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፡፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአህዛብም ስንፍና ነው፡፡” (1ኛ ቆሮ. 1፡23) በማለት አስተምሯል፡፡ ይህንን መንፈሳዊ መመሪያቸው በማድረግ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አውደ ምህረት እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌል የሚሰብኩ እውነተኛውን የሃይማኖት መንገድ የሚያቀኑ አያሌ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አሉ፡፡ በእነዚህ ሊቃውንት አስተምህሮና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ምዕመናን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ በእምነት ጸንተው፣ ምግባር ትሩፋትን ሠርተውና ከምስጢራተ ቤተክርስቲያን ተካፋይ ሆነው ዓለም ሳይፈጠር የተጋጀላችውን መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሱ እሙን ነው፡፡
የእግዚአብሔር የምህረት ቃል ከሚፈስበት አውደ ምህረት እንደ አይሁድ ምልክትን (ተዓምርን) መናፈቅ፣ ወይም ስለ ተዓምር አብዝቶ መጨነቅ አይገባም፡፡ ይሁንና በዘመናችን በእምነት ከሚዳሰስ የወንጌል እውነት ይልቅ በዓይን የሚታይ የማጭበርበርና መሰል ምልክቶች የአንዳንድ የእምነት ቦታዎች መገለጫ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ግሪክ ሰዎች በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ምድራዊ ጥበብን ማውራትና ቤተክርስቲያንን የምድራዊ ጥበብ መመጻደቂያ ቦታ የሚያስመስሉ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይም ጥራዝ ነጠቅ ሰባክያን በዓለም ላይ ያለውን ግሳንግስ ሁሉ (ያዩትንና የሰሙትን) በአውደ ምህረት በመዘብዘብ አላዋቂነታቸውን ከማጋለጣቸውም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚገለጥበትን የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ያሰድባሉ፡፡ እነዚህ መምህራን በቁንጽል መረዳት ያለቦታቸው ከሚተነትኗቸውና ምዕመናንን ግራ ከሚያጋቡባቸው ምድራዊ ጥበቦች አንዱ ፖለቲካ (ሃይማኖታዊ ስብከትንና ምድራዊ ፖለቲካን ያለአግባብ ማዳቀልና መቀላቀል) ነው፡፡
ከዚህም አንጻር በመንፈሳዊው አውደ ምህረት ላይ ፖለቲካንና ስብከትን የሚቀላቅሉ አንዳንድ ሰባኪዎች በየዘመናቱ ነበሩ፡፡ ዛሬም በእኛም ዘመን ምንም ምን ያልተቀላቀለበት ንጹህ መሥዋዕት እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ተናግረው የምዕመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት ማነጽ ሲገባቸው አንዱን የፖለቲካ ቡድን በማሞገስ ሌላውን ደግሞ በመውቀስ ላይ የተጠመዱ አንዳንድ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል አሉ፡፡ ምዕመናኑም በእነዚህ ሰዎች ዓይን ያወጣ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ለፖለቲካ ዓላማ በመጠቀማቸው እያዘኑ ይገኛሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖችም ይህ መጥፎ ጅምር እየሰፋ ሄዶ ቤተክርስቲያኒቱን የፖለቲከኞች መሣርያ እንዳያደርጋት ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የስብከትና የፖለቲካን ልዪነት፣ ግንኙነትና ሰባኪው ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ እንዳስሳለን፡፡
ፖለቲካ ምንድን ነው?
ሰው በተፈጥሮው ፖለቲካዊ ጠባይ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ፖለቲካ ማለት የምድራዊ መንግስት የአመራር ሥርዓትና ስልት ነው፡፡ በአንድ ሀገር አመራር ላይ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም የመንግስት አካላት የሚያደርጉት አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽእኖ ፓለቲካ ሊባል ይችላል፡፡ በመንግስት መዋቅር ስልጣንን መያዝና በዚያም ሕዝብን ማገልገል እንዲሁ ፖለቲካ ሊባል ይችላል፡፡ አንድ ሀገር ስለምትመራበት ጥብብ የሚያጠና የትምህርት ጥናት ዘርፍም የፖለቲካ ሳይንስ ይባላል፡፡ አንድ ሀገር ወይም ሕዝብ በመንግስትነት (ራሱን በማስተዳደር) ከታወቀ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ኀልወት አለው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት፣ በመንግስትና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ፖለቲካ ይባላል፡፡ ይህንን የመንግስት ፖለቲካ የሚመሩ በዚሁ ሙያ የሰለጠኑ፣ ወይም በልምድና በፍላጎት የተሰማሩ ባለስልጣናት፣ ተገዳዳዳሪዎች ወይም ሌሎች ሀሳብ አመንጭዎች (ፖለቲከኞች) አሉ፡፡ መንግስታቸው ከሕዝብ ጋር ወይም ከሌላ መንግስትና ሕዝብ ጋር ሊኖረው የሚገባውን የአመራር ስልት በተማሩት ትምህርትና ባላቸው ልምድ፣ ከሀገሪቱ ህግጋት አንጻር፣ በሥራ ልምዳቸውና ከላይ በሚሰጣቸው አመራር ለቆሙለት ዓላማ ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ ያራምዳሉ፡፡ የፖለቲካ ሥራ በእነዚህ ሰዎች ሲሠራ ያምርበታል፡፡
ስብከትስ ምንድን ነው?
የክርስቶስን ወንጌል ለሕዝብ ማድረስ ስብከት ይባላል፡፡ የወንጌል ሰባኪ ትኩረቱ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ስላለው የአምላክና የአምላኪ፣ የፈጣሪና የፍጡር፣ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲሁም በሰውና በሰው መካከል ስላለው የወንድማማችነት ግንኙነት በሰፊው ተንትኖ ለሰው ማስረዳት፣ በእምነት እንዲጸኑም ማገዝ ነው፡፡ የስብከተ ወንጌል ዓላማው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠነክርና እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ሊያሳድግ የሚችል ፍቅር በሰዎች መካከል እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ ለስብከት የሚያስፈልገውም መንፈሳዊ የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት፣ ሌላውን ሊያንጽ የሚችል መንፈሳዊ ሕይወት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የመስበክ/የማስተማር ጸጋ፣ የስብከት ዘዴ እና የጸና እምነት ነው፡፡ ወንጌልን የሚያስተምር ሰባኪ ስለፖለቲካ ጥናትና እውቀት (የራሱ የሆነ የፖለቲካ አመላካከት) ቢኖረውም ወንጌልን በሚያስተምርበት ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሰባኪ ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያስፈልገውንና ሕይወታቸውን የሚያንጸውን የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የሚያውቀውን ሁሉ ወይም ሰዎች እንዲናገርላቸው የሚፈልጉትን ነገር መስበክ የለበትምና፡፡
እግዚአብሔርን መፍራትና የሀገር መሪዎችን ማክበር
የቤተክርስቲያን አዕማድና ብርሃናት የሆኑት የወንጌል ሰባኪዎች እነ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ወንጌልና በምድራዊ ፖለቲካ መካከል ያለውን ልዪነትና ግንኙነት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ምዕመናን ምንም እንኳን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ነፃ የወጡ ቢሆኑም በሀገር ደረጃ ደግሞ አለቃ የሌላቸው መስለው እንዳይታዩ ይመክሯቸው ነበር፡፡ ‹‹ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ… ሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ (ሮሜ 13፡1-17)›› በማለት ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው፡፡
በዚህም መሠረት እግዚአብሔርን መፍራት የሀገር መሪዎችን ደግሞ ማክበር በቤተክርስቲያን ጥንተ ስብከት የታወቀ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ›› ብሏል (1ኛ ጴጥ 2፡13-14)፡፡ የጥበብ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ሕግጋቱን መጠበቅ ነው፡፡ መሪዎችን ማክበር ማለት ስለሀገር ስለሕዝብ አንድነትና ነጻነት እነርሱ በሚያዙት (በሚያወጡት ህግ/ፖሊሲ/መመሪያ)መሠረት መሠማራት ማለት ነው፡፡ የሀገር መሪዎችን ማክበርና ለሥርዓታቸው መገዛት ማለት ግን የአምባገነን መንግስታት አፈ ቀላጤ የሆኑ ሰዎች እንደሚመስላቸው ግፈኞች የሀገር መሪ ስለሆኑ ብቻ ያለመመርመር መገዛት፣ ያለመጠየቅ መታዘዝ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ክርስቲያኖች “ሰማያዊ ንጉስ እግዚአብሔር፣ ሰማያዊ ሀገር መንግስተ ሰማያት አለችንና ለማንኛውም ምድራዊ ባለስልጣንና ሀገር አንገዛም፣ አንታዘዝም፡፡” በማለት መንፈሳዊ ዓላማቸውን ለምድራዊ አድመኝነት መሸፈኛ እንዳያደርጉት የተነገረ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ባለስልጣኖችን የሚፈራ ሰባኪ የእነርሱ ፍላጎት ተገዢ ይሆናል፡፡ ሰባኪው እነዚህን ጽንሰ ሃሳቦች በጤናማ አእምሮ አስተውሎና ተርጉሞ ለተሰባኪያኑ ቢያሰማ በፖለቲካውና በወንጌል ትምህርት መካከል ሰላምና መስመርን ጠብቆ አብሮ መሥራት ይመሠረታል፡፡
ፍርድ ተጓደለ ደሃ ተበደለ የሚል ስብከት
ሰባኪው ለማንኛውም የፖለቲካ ባለስልጣን ወይም ለማንኛውም ገዥም ይሁን ተገዳዳሪ ቡድን ቋሚ በሚመስል መልኩ ሳይወግን በሕዝብ ዘንድ ‹‹ፍርድ ተጓደለ ደሃ ተበደለ›› ብሎ መምከርም ሆነ መገሰፅ ይችላል/ይገባልም፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ራሱ በራሱ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በሰፈረው እውነት መነሻነት እንጂ በሌላ አካል ተጽእኖ የሌላ መሣርያ በመሆን አይደለም፡፡ ድሃ ሲበደል፣ ሲሰቃይ፣ ሲጮህ እነርሱ ቸል የሚሉትንና ሊያገለግሉት የተሾሙትን ሕዝብ በደል፣ ስቃይና ችግር የማይመለከቱትን ባለስልጣኖች በነሄሮድስ የደረሰውን የእግዚአብሔር መቅሰፍት አስረጅ አድርጎ ቢገስጻቸው የሐዋርያ ወጉ ነው (የሐዋ ሥራ 12፡20-24)፡፡
የወንጌል ሰባኪ የፖለቲካ ባለስልጣኖችን በተግሳጽ ብቻ ሳይሆን በምክርም ማስረዳት ይገባዋል፡፡ የያዙት ስልጣን ከእግዚአብሔር የተገኘ መሆኑን፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ግን በራሳቸው ምንም ሊያደርጉ አለመቻላቸውን (ዮሐ 19፡11) ገልጦ ሊነግራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ ያሉበትም የዳኝነት መድረክ ነገ የሚያልፍና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊያገለግሉበት የተሰጣቸው መሆኑን ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም እውነቱን የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡‹‹ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ›› ብሎ የሚሰብክ ሰባኪ በደልንና ፍርድን በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽርነት መመልከት ይኖርበታል፡፡ አንዱን በዳይ የሚኮንን ሌላውን በዳይ ቸል የሚል ወይም የሚያበረታታ፣ ለአንዱ ተበዳይ የሚጮህ ለሌላው ተበዳይ ግን ጸጥ የሚል ከሆነ ይህ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ አይደለም፡፡
የሰላምን ዋጋ እና የጦርነትን አስከፊነት የሚያሳይ ስብከት
በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለ አንድ ሰባኪ ስለ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ የሚያውቅ መሆን ይኖርበታል፡፡የሰላም እጦት፣ ግጭትና ጦርነት ሀገራዊ ቅርጽ ከመያዛቸው በፊት በግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚጸነሱ ናቸው፡፡ በትዕቢተኞች ሰዎች የሚመሩ ሀገራትም ሌሎችን በግፍ ማስገበርን፣ ማጭበርበርንና ማዋረድን እንደ መልካም ምግባር መደጋገማቸው አይቀርም፡፡ ሰባኬ ወንጌል ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በተያያዘ መልኩ በእውቀትና በመረጃ ተመስርቶ የሰላም እጦት፣ የግጭትና የጦርነት ምንጭ የሆኑ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን ቢነቅፍ፣ ቢተች የተገባ ነው፡፡ የኃያላን ሀገራት መንግስታት በታዳጊው ሀገር መንግስት ላይ የሚያደርጉትን ተጽእኖ ማለት የኢኮኖሚና የወታደራዊ የበላይ ነኝ የሚለው መንግስት በደካማው መንግስት ላይ የሚያሳየውን የትዕቢት ጠባይ በወንጌል ሰባኪው ሊወገዝ ይችላል፡፡
አንዳንድ መንግስታት የራሳቸውን ርዕዮተ ዓለም ሌሎች ሕዝቦችና መንግስታት ሁሉ እንዲይዙላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የእነርሱን ፖለቲካዊ ሃሳብ ተገዥዎችና ምጽዋተኞች እንዲሆኑ በሃይማኖት አሳቦና የሃይማኖት ልብስ ለብሶ መጽሐፍ ቅዱስን አስይዞ ቢጽ ሐሳውያንን በመላክ በሚሰጠው ርዳታ በማስፈራራት በሌላም በብዙ ዓይነት መንገድ ይጥራሉ፡፡ ሃሳቡ ተቀባይ ቢያጣ ርዳታውን ያቆማሉ፡፡ የጥፋት መልእክተኞችን እየላኩ የውስጥ ለውስጥ ብጥብጥ እንዲነሳና ደም እንዲፋሰስ በጎረቤት ያሉ የወንድማማች ሀገሮችን በሃሳብ በመከፋፈል እርስ በእርሳቸው እንዲፋጁ በማድረግ የሚፈጽመትን ሰይጣናዊ ወንጀል ሰባኪው ቢያወግዝ የተገባ ነው፡፡ ያንን የፖለቲካ ሰዎች እንዴት እንደሚመለከቱት ሰባኪው በሰፊው ሊያስረዳ ይገባል፡፡ ይህንንም በቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ሰዎችም ዘንድ በሰፊው ሊያስረዳ ይገባል፡፡
ሰባኪው በዓለም ዙሪያ በየዘመናቱ በተደረጉ ጦርነቶች ለበርካቶች ሞት፣ መቁሰል፣ ስደትና ጉስቁልና ምክንያት የሆነውን ጦርነት እንደገና ለመቀስቀስ የሰውን ደም በከንቱ ለማፍሰስ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦር መሣርያው ገበያ የደራ መሆኑን ገልጦ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን በብርቱ ሊወቅሳቸው ይገባል፡፡ ጦርነት በዓለም በሚገኙ ወገኖቻቻን ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመዘርዘር በአካል ጉድለት የሚገኙ ስንት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዳሉ፣ እንዲሁም ለሰው ልጆች መታወቂያ የሚሆኑና በብዙ ድካም የተሠሩ እቃዎችና የባህል መሣርያዎች እንደወደሙ፣ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች ከነዋሪዎቻቸው ጋር በሃይድሮጂን ቦምብ መጋየታቸውን በአስረጅ ጠቅሶ ጦርነትን ሲያወግዝ በጦርነት ሳቢያ በሰው ደም የሚነግዱ የጦር መሣርያ ቸርቻሪዎችን የፖለቲካ መሪዎችንም ቢገስጽ ሁለገብ ሰባኪ ይሆናል፡፡
ነገር ግን ዓለም እንደልማዱ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማ ካለ ግን የጦር ወዳድ መንግስታት እንደ ኮራዚን እንደ ቤተ ሳይዳ እንደ ሰዶምና ገሞራ ህልውናቸው ጠፍቶ የሚቀር መሆኑን ሰባኪው በማስጠንቀቂያ ቃል ማስረዳት አለበት፡፡ ጦርነት የብዙዎቻችንን ቤት አራቁቶ የብዙዎቻችንንም ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠፋ ከአንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች እንደ ሂትለርና ሞሶሎኒ ካሉ ሰዎች ጭንቅላት የሚመነጭ መርዝ መሆኑን ማስተማር የሰባኪው ድርሻ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ የጦርነት ምንጭ ከሚፈልቅበት የሰዎች ልቦና ይደርቅ ዘንድ መንፈሳዊው ሰባኪ ታላቅ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን የጦርነትን አስከፊነት የሚሰብክ ሰባኪ አንዱን ጦርነት እያወገዘ ሌላውን ቸል እያለ (እየደገፈ) ሳይሆን ለእውነት ብቻ ወግኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላምንም የሚሰብክ ሰባኪ እንዲሁ የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነና ሰዎችም ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ በመምከር መሆን አለበት፡፡
ጠንካራ የሥራ ባህልንና ያለንን ማካፈልን የሚያበረታታ ስብከት
የተወደደው መምህራችን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ባለጸግነትንና ሥልጣኔን አታወግዝም፤ ለምድራዊ ባለጸግነትና ጥቅም ሲሉ ሌሎችን የሚያሳድዱና የሚጎዱትን ግን ታወግዛቸዋለች፣ ትነቅፋቸዋለች፡፡ በዓለማችን ዋነኛው የግጭትና የጦርነት ምንጭ የመሪዎችና የሌሎች ኃያላን እኔ ብቻ ይድላኝ ማለት፣ ራስ ወዳድነትና ለሌላው አለማሰብ ናቸው፡፡ የወንጌል ሰባኪ በእግዚአብሔር ገንዘብ ሰው የሰውን ደም በማፍሰስ፣ ሕይወትን በመቅጠፍ (በጦርነት) ፈንታ ሰው የሚድንበትን፣ በኢኮኖሚም የሚበለጽግበትን የስልጣኔ በር መክፈትና የተራበው የሰው ዘር ምግብ በልቶ እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚያድርበትን መንገድ ብናመላክት እግዚአብሔር የሚደሰት መሆኑን በይፋ መስበክ ይገባዋል፡፡
ስለሆነም መንፈሳዊው ሰባኪ ሰዎች ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲያዳብሩና በድካማቸው ያፈሩትን ሀብትም ያለመሰሰት ለሌሎች እንዲያካፍሉ (ለተቸገሩት እንዲመጸውቱ) ተግቶ ማስተማር ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ምጽዓት ለፍርድ ሲገለጥ ከምግባራት ሁሉ በላይ በደገኛ ምጽዋት የተገለጸ ፍቅርን ይወድዳልና፡፡ ይህም የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ የታሰሩትን መጎብኘት፣ እንግዶችን ያለልዩነት መቀበል፣ ለደሃ አደጉ መሟገትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በድካሙ ያገኘውን ሀብትና ንብረት ለሌሎች በቸርነት የሚያካፍል ማኅበረሰብ ውስጥ ለሀብትና ንብረት ብሎ ሰዎችን የሚገል፣ የሚያፈናቅል፣ የሚያሳድድ ምግባር በጊዜ ሂደት ቦታ ማጣቱ አይቀርምና፡፡
የፖለቲካና የስብከት ልዩነት
ስብከትና ፖለቲካ ዓላማቸው የተለያየ ነውና እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ ፖለቲካና ስብከት የሚለያዩበትን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ በቤተክርስቲያንና በፖለቲካ (በምድራዊ መንግስት ወይም ሌላ ተገዳዳሪ የሀሳብ ባለቤቶች) መካከል መደበላለቅ ለመፍጠር ዛሬም አንዳንድ አድርባዮች ይሞክራሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ፈተና የተጀመረው በእኛ ዘመን አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን ስትጀመር ጀምሮ የነበረና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሚኖር ፈተና ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነውን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከቄሳር ባለስልጣኖች ጋር ለማጣላት የሞከሩ ሄሮድሳውያን ራት አግባዎች ‹‹ለቄሳር ግብር መስጠት ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡ የእነርሱ ሃሳባቸው አይገባም ቢላቸው ከቄሳር መንግስት ጋር ለማጋጨት ነው፡፡ ይገባል ቢላቸው ደግሞ ይህስ ጥሩ የሃይማኖት መምህር አይደለም ብለው አላዋቂውን ሕዝብ ለማወናበድ ነበር፡፡ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የቤተክርስቲያን ምዕመናን አለቃ የለሾች አለመሆናቸወን ሲገልጥ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ግን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባል›› አላቸው (ማቴ 22፡15-22)፡፡ አሁንም ሰባኪው የፖለቲካውንና የወንጌልን ልዩነት አጥርቶ ካወቀ ከስህተቱ ይጠነቀቃል፡፡ ለገዢዎች እንድንታዘዝ ለእነርሱም የሚገባውን ሁሉ እንድናደርግ ቅዱሳት መጻሕፍት አዘዋል፡፡ እንድንሰብክ የታዘዝነው ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ 1፡23)፡፡
ፖለቲካን የሚደግፍ/የሚነቅፍ ስብከት
አንዳንድ ሰባክያን ስለሁላችን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ያስተማረውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲሁም የመሰረታትን ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አሰራር መስበክ፣ መመስከርና ማብራራት ሲገባቸው በየጊዜው የሚነሱ ባለስልጣኖችን (መኳንንቱን) በማሞገስና በማሞካሸት እንጀራቸውን ያበሰሉ (በባለስልጣናቱና በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ተወዳጅነት የሚያገኙ) እየመሰላቸው ወንጌልን ለመስበክ መስቀል ጨብጠው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በቤተክርስቲያን አውደምህረት የፖለቲካ (ፖለቲካን የቀላቀለ) ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊያገለግሉ ሲገባ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት በፖለቲካዊ እሳቤ ለሚደግፏቸው የመንግስት አካላት ወይም ሌሎች ተገዳዳሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስል መንፈሳዊ ለዛ የሌለው ትርክት በመንፈሳዊነት ካባ ያቀርባሉ፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ያከበራቸው ቅዱሳን ገድልና ድርሳን እንዳይነገር ውኃ በማይቋጥር ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ በጸጉር ስንጠቃ የሚቃወሙ በማሳችን ውስጥ የበቀሉ የመንገድ ዳር አረሞችም ዓላማቸው መንፈሳዊ ስላልሆነ “ለምን ነገረ ቅዱሳን በአውደ ምህረት ይተረካል?” በሚሉበት ምንፍቅናን የተሞላ አንደበታቸው የሚወዷቸውን ፖለቲከኞች ነቢይና መልአክ ለማስመሰል ሲጣደፉ እናስተውላለን፡፡ መንፈሳዊውን አውደ ምህረት እንደ ቅዱስ ቃሉ ለመንፈስ ቅዱስ ሀሳብ ከማስገዛት ይልቅ የእኛ ለሚሏቸው ተገዳዳሪ ፖለቲከኞች ፈቃድ ማስፈጸሚያ ያደርጉታል፡፡ በዚህም የተነሳ የበርካታ ምዕመናን መንፈሳዊ አንድነት ይፈተናል፡፡ አድር ባዮቹ አገልጋዮች ግን በቅዱስ መጽሐፍ እንደተነገረው “ለመንጋው የማይራሩ ምንደኞች” ስለሆኑ መንፈሳዊውን አውድ ለስጋዊ ፉክክር በማዋላቸው የተነሳ የሚጠፉት በጎች (ምዕመናን) ጉዳይ አያስጨንቃቸውም፡፡
እነዚህ በወንጌል የሚነግዱ ግለሰቦች ከምድራውያን ጌቶቻቸው ወይም ከጌቶቻቸው ወዳጆች የሚያገኙት ሙገሳ፣ ክብርና ጥቅም ስለሚያሳሳቸው በጥፋት ላይ ጥፋት ሲጨምሩ አይታወቃቸውም፡፡ ይህን የወንጌል ስብከት ሳይሆን ፖለቲካዊ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት የተቀመጡ ምዕመናን ሰባኪዎቹን ይታዘቧቸዋል፡፡ እነዚህ ሰባኪያን በቤተክርስቲያን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ምዕመናን ሊኖሩ እንደሚችሉም መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌሎች ሰባኪዎች ደግሞ የተነሡበትን የስብከታቸውን ርዕስ በሚፈለገው መንገድ ማብራራት ሲያቅታቸው አንዱን የፖለቲካ አመራር በመንቀፍ የሌላውን ደግሞ በመደገፍ የፓርቲ መሪዎች የሚያደርጉትን ዓይነት ስብከት ይሰብካሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ የሰባኪዎች መመሪያን አለማወቅ የቤተክርስቲያንን ዓላማና የአመራር አቅጣጫ አለማስተዋል ነው፡፡ ይህም ቤተክርስቲያንንና ምዕመናንን ከመከፋፈል በቀር አንዳች ጠቀሜታ የለውም፡፡
የፖለቲካዊ ስብከት ምሣሌዎች እንደ ማሳያ
ምሣሌ 1፡ በአንድ ወቅት በአንዲት የኢትዮጵያ ከተማ የመስቀል በዓል የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና የመንግስት ባለስልጣናት ባሉበት በአደባባይ እየተከበረ እያለ አንድ ካህን መልእክት ለማስተላለፍ ወደ መነጋገሪያው ሰገነት መጡ፡፡ በንግግራቸውም “መስቀል ኃይል ነው፣ መስቀል ቤዛ ነው፣ መስቀል መድኃኒት ነው፣ መስቀል ልማት ነው“ አሉ፡፡ እኒህ ካህን ከዘረዘሯቸው ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ መጽሐፋዊና ትውፊታዊ ሲሆኑ የመጨረሻውና “መስቀል ልማት ነው” የሚለው ወለፈንድ አገላለጽ ግን ምንም መንፈሳዊ መሰረት የሌለውና በጊዜው ከነበረው ገዥ ፖለቲካዊ ትርክት አኳያ የምድራውያን ባለስልጣናትን ቀልብ ለመሳብ የተጨመረ የአድር ባይነት መገለጫ ነው፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢር ተተንትኖ በማያልቅበት የከበረ በዓል ላይ ካህኑ ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ ፖለቲከኞችን የሚያስደስት የመሰላቸውን እንግዳ አገላለጽ መጠቀማቸው ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን ለሚያጎነብሱላቸው የፖለቲካ ሹማምንት መሆኑን ያሳብቅባቸዋል፡፡
ምሣሌ 2፡ በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ከተማ የጥምቀት በዓል እየተከበረ እያለ የዕለቱን ወንጌል የሚያስተምሩት መምህር መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ማግባቱን አንስቶ ለመውቀስ እንዳልፈራ እየጠቀሰ ማስተማር ጀመረ፡፡ እየደጋገመም “ዮሐንስ ለሄሮድስ ህገ አራዊት አልታዘዝም አለ“ እያለ ይናገር ነበር፡፡ “ህገ አራዊት” የሚለውን ቃል ከመደጋገሙ የተነሳ ቅዱስ ዮሐንስን የተመለከቱትን ቅዱሳት መጻሕፍት (ወንጌልና ገድለ ዮሐንስን ጨምሮ) ላልተረዳ ሰው የመምህሩ ሀሳብ ከመጻሕፍቱ የሚቀዳ ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን “ህገ አራዊት” የሚለው አገላለጽ አንድ ታዋቂ የሀገራችን ፖለቲከኛ በዘመናቸው የነበረውን መንግስት ለመተቸት የተጠቀሙበት እንጂ ከቅዱስ ዮሐንስ ታሪክም ሆነ ንግግር ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ በዝርወት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢትዮጵያ ጉዳይ የጎላ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የመምህሩ ፍላጎትም ተሰብሳቢዎቹ ሊሰሙት ይፈልጋሉ ብሎ ያሰበውን ፖለቲካዊ ምልከታ በመግለጽ ወገንተኝነትን ማሳየት ይመስላል እንጂ ለጥምቀት ከሚሰጠው የአስተምህሮ ትኩረት ጋር በፍጹም አይሄድም፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱስ ዮሐንስ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ማግባቱን አንስቶ ያደረገው ተግሳጽና ውጤቱ ከጥምቀት ዕለት ይልቅ ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል (ዘመን መለወጫ) የሚስማማ ነው፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ፖለቲካዊ ስብከትን የሚያዘወትሩ ሰዎች ግን የሚጨነቁት ስለ ንግግራቸው ፖለቲካዊ ፋይዳ እንጂ መንፈሳዊ ወቅታዊነት ወይም ተገቢነት (timeliness or appropriateness) አይደለም፡፡ ተነግሮ የማያልቅ ጥልቅ ምሥጢርና አስተምህሮ ባለበት በጥምቀት ዕለት ለበዓሉ ከሚስማማ ትምህርት ይልቅ ለፖለቲከኞች ማባበያ የሚሆን ንግግርን እንደ ወንጌል መናገር መምህሩ ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን ሊያስተላልፉት ለፈለጉት ፖለቲካዊ መልእክት መሆኑን ያስታውቅባቸዋል፡፡
ምሣሌ 3፡ በአንዲት የምዕራባውያን ከተማ ዓመታዊ በዓል እየተከበረ ባለበት የዕለቱ መምህር የዕለቱን ወንጌል፣ ስለ ዕለቱ በዓል ምንነት ከማብራራት ይልቅ ስለ አንድ የፖለቲካ ባለስልጣን ብቻ ሲያወሩ ለማስተማር የነበራቸውን ጊዜ ጨርሰውታል፡፡ ይህንን ባለስልጣን ‹‹ነቢዩ ሙሴ ነው›› ብለው ሲያሞጋግሱ ለሌላው ደግሞ የፈርዖንን ግብር ሰጥተው የራሳቸውን ፖለቲካዊ ንግግር ሲያደርጉ ውለዋል፡፡ ይህንን የሚወዱትን ፖለቲከኛ “ነቢይ” ወይም “በልዩ ሁኔታ ከእግዚአብሔር የተላከ መሲህ” ለማስመሰል የእግዚአብሔርን ቃል እያዳቀሉ ወይም እያጣመሙ የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ትርክት አቅርበዋል፡፡ ከዚህም አልፎ አንድን የፖለቲካ መሪ የባህራንን የዕዳ ደብዳቤ ካጠፋለት ከሊቀ መላእክት ከቅዱስ ሚካኤል ጋር ማነፃፀር የሚያስከትለውን ጉዳት መገመት አያስቸግርም፡፡ ዓመት በዓሉን ሊያከብር የመጣ ምዕመን መማር ያለበት በዕለቱ ቤተክርስቲያን የምታስተላልፈውን መንፈሳዊ አስተምህሮ እንጂ የፖለቲከኞችን ወገንተኛ የአቋም መግለጫ አይደለም፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንን በነቢያትና በሐዋርያት ደገኛ አስተምህሮ ላይ መመስረት ለማስረዳት ዓይነተኛ አጋጣሚ በሆነው፣ እጅግ ብዙ የመጻሕፍት ንባብና ትርጓሜ በሚሰጥበት ቀን አንድ መምህር ጊዜ ተርፏቸው ስለ ወገንተኛ ፖለቲካ የሚያወሩ ከሆነ፣ በተለይም ደግሞ ከምዕመናን ወገን የተወሰኑትን መንፈሳዊ ባልሆነ መነሻ የሚያስከፋና የሚፈርጅ ንግግር የሚናገሩ ከሆነ ትኩረታቸው ለቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን በፖለቲካዊ ኀልዎት የሚወድዱትን ለማሞገስ፣ የሚጠሉትን ለመውቀስ መሆኑ ይታወቅባቸዋል፡፡
እነዚህ ምሣሌዎች ለማሳያነት የቀረቡ ናቸው፡፡ በይዘታቸውም እንደ ቅደም ተከተላቸው በስብከት ጊዜ እንደዋዛ የሚቀርቡ ፖለቲካዊ ምልከታዎችን፣ መንፈሳዊ የት መጣ (መነሻ) የሌላቸውን እምቅ (coded) ፖለቲካዊ ቃላት በመጠቀም የሚተላለፉ ፖለቲካዊ ወገንተኝነቶችን እንዲሁም በአንጻራዊነት ግልጽ ሊባሉ የሚችሉ የፖለቲካዊ ወገንተኝነት ማሳያ የሚሆኑ ንግግሮችን ይወክላሉ ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ምሣሌዎች ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ ሌሎች ብዙ ምሣሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንዳንዶች በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ቆመው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች ሊዋቀሩበት ስለሚገባ ፖለቲካዊ መስፈርት መመሪያ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ ለሚፈልጉት ፖለቲካዊ ሰልፍ በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት የሚቀሰቅሱ፣ የማይፈልጉትን ፖለቲካዊ ሰልፍ ደግሞ በዛው አውደ ምህረት ላይ ሲነቅፉ የሚታዩም አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሚወዱትን ፖለቲከኛ መልአክ እያስመሰሉ የሚጠሉትን ፖለቲከኛ ደግሞ ከሰይጣን ጋር እያመሳሰሉ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ብቻ ሊነገርበት የሚገባውን የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት (የምህረት አደባባይ) የመሸነጋገያ ወይም መወነጃጀያ ሰገነት ያስመስሉታል፡፡ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ፖለቲካዊ ስብከት የሚያሰሙ ሰዎች የቤተክርስቲያንን ለዛ የማይረዱ “ቅኔው ሲያልቅበት ቀረርቶ የጨመረውን” ምስኪን የቆሎ ተማሪ ይመስላሉ፡፡
ትምህርተ ሃይማኖት በሚነገርበት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በሚተነተንበት አውደ ምህረት ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢር ይልቅ ለወገንተኛ ፖለቲካዊ ትርክት ጊዜ የሚተርፋቸው ሰባክያን መንፈሳዊ ዓላማ አላቸው ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ ይህም በመንፈሳዊ እይታ ያለመብሰል ማሳያ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው አስቀድሞ “ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግስትን ትመስላለህን?” (ሐዋ. 1፡6) በማለት የጠየቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማራቸው መንፈሳዊ ትምህርትና ተስፋ ይልቅ በእስራኤላውያን ፖለቲከኞች ዘንድ የትኩረት አቅጣጫ የነበረው ከሮም ቅኝ ግዛት የመውጣት ሀሳብ በልባቸው የበለጠ ቦታ ስላገኘ ነበር፡፡ በእምነት በጎለመሱ ጊዜ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ (ግሪክ) ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፡፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአህዛብም ስንፍና ነው፡፡” (1ኛ ቆሮ. 1፡23) ይላሉ፡፡ የመንፈሳዊ ስብከት ዓላማም የአይሁድን ዓይነት ምልክት ናፋቂነትም ሆነ የግሪክ ሰዎችን ዓይነት በራስ ጥበብ መመካት የሚያስናፍቅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገለጠልንን የእግዚአብሔርን ማዳን መመስከርና ማወጅ ምዕመናንንም ወደ ድኅነት መንገድ መመለስ ነው፡፡
ፖለቲካን በቤተክርስቲያን መስበክ የሚያመጣው ጉዳት
ቅዱሳን አበው በቅዱሳት መጻሕፍት ባስቀመጡት መመሪያ ካልሆነ በቀር በቤተክርስቲያን ስም ወንጌልን እንዲያስተምር የተሰየመው ካህን (ሰባኬ ወንጌል) በተንኮል፣ መመሪያን ባለማወቅ ወይም በሞኝነት ወደማይገባው (ጠብቆም ላልቶም ይነበብ) ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ከዘባረቀ ማንንም ቢደግፍ ድጋፉ፣ ማንንም ቢነቅፍም ነቀፋው ያስነቅፈዋል እንጂ አያስመሰግነውም፡፡ ከራሱም አልፎ ሃይማኖቱን፣ ቤተክርስቲያኑን ያስነቅፋል፡፡ በሌላው ዘንድም እንዲጠላ ያደርጋል፡፡ የቤተክርስቲያን እምነትና ቀኖና ከፖለቲካ ሕግና መመሪያ የተለየ እንደመሆኑ መጠን ስብከትም ከፖለቲካ የተለየ መሆኑን ሰባኪው ማስተዋል አለበት፡፡ እንግዲህ የወንጌል ሰባኪዎች ትምህርተ ሃይማኖትን ብቻ እንዲሰብኩ የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን መመሪያ ነው፡፡
ፖለቲካን በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ መስበክ ብዙ አስከፊ ጉዳቶች አሉት፡፡ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበትን፣ የሰው ልጅ ምግበ ነፍስን የሚያገኝበትንና እግዚአብሔር የሚከብርበትን አውደ ምህረት ለምድራዊ ዓላማ ማዋል እግዚአብሔርን ማሳዘን ቤተክርስቲያንንም ማስወቀስ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሐዋርያት (የእግዚአብሔር መልእክተኞች) እግር የተተኩ ሰባክያን የተላኩበት ዓላማ የላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ለሰው ልጅ ለማድረስ እንጂ የላካቸውን የእግዚአብሔርን ነገር ትተው ለሰው እንዲታዘዙ አይደለም፡፡ ይህን በማድረግ አለን የሚሉትን ሐዋርያዊ ዓላማ አጠያያቂ ያደርጉታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ እግዚአብሔር ረድቶአቸው የእርሱን ቃል ለመስማት ሰምተውም ሕይወታቸውን ለማዳን በእግዚአብሔር ቤት ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ፈንታ አላፊውን ምድራዊ ፖለቲካ መስበክና በመካከላቸው ልዩነትን መፍጠር የሰውን ልጅ በነፍስም በሥጋም መጉዳት ነው፡፡ ይህንን ያዩ/የሰሙ ምዕመናን ደግሞ ከቤተ እግዚአብሔር ሊርቁ ይችላሉ፡፡ ሰባኪውም ምዕመናንን የሚሰበስብ ከመሆን ይልቅ የተሰበሰቡትን የሚበትን ይሆናል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣኖች (ፖለቲከኞች) ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ በሚል ሽፋን የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ለፖለቲካ ቅስቀሳ የሚጠቀሙበት ከሆነም ጉዳቱ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ስለዚህ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ስብከታችን እንደ አይሁድ ምልክትን የሚናፍቅ፣ እንደ ግሪክ ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት በሆነ በምድራዊ ጥበብ መመካትን የሚያመጣ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንስ በስብከታችን ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት የሚመስለውን በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገለጠውን የእግዚአብሔር ማዳን፣ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ከጌታ ተምራ የጠበቀችውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ እምነት በማወጅ፣ በመመስከርና በመተንተን በበረቱ ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔር በጎች (ምዕመናን) በእምነትና በምግባር እንዲጸኑ፣ ከበረቱ ውጭ ያሉት የእግዚአብሔር በጎች (ምዕመናን) ደግሞ ወደ በረቱ እንዲገቡ ማድረግ ይገባናል፡፡ የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረትም ለእግዚአብሔር ቃል ብቻ ልናደርገው ይገባል እንጂ ፖለቲካንና ስብከትን እየቀላቀልንና እያዳቀልን ሰውና እግዚአብሔርን ልናሳዝን አይገባም፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለሐዋርያውያን አበውና በየዘመኑ ለተነሱ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ጥበብ መንፈሳዊን የገለጸ፣ ለሰማዕትነት በፍርድ አደባባዮች ቆመው እንኳ የሚናገሩት ቃለ እግዚአብሔር ለማንኛውም ሥጋዊ ዓላማ እንዳይዛነፍባቸው አንደበታቸውን የጠበቀ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በዘመናችን ላሉ መምህራንና ሊቃውንትም ቃል ኪዳኑን አያርቅብን፡፡ ለህዝባችንም ማስተዋሉን ያድልልን፡፡
ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡
Pingback: ሰባኪ ማስመጣት: የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞና ዓለማዊ ጓዙ – አስተምህሮ
Pingback: “ቤተክርስቲያን መመሥረት”: ስሁትና ከፋፋይ ልማዶች ይታረሙ! – አስተምህሮ
Pingback: ዕቅበተ እምነት፡ ምዕመናንን በማንቃት ወይስ ሐሰተኞችን በማጥቃት? – አስተምህሮ
Pingback: ክርስቲያናዊ አንድነትና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት – አስተምህሮ
Pingback: ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ