“ቤተ ክርስቲያን መመሥረት”: ስሁትና ከፋፋይ ልማዶች ይታረሙ!

መግቢያ

በዘመናችን “ቤተክርስቲያን መመሥረት” የሚለው ቃል በአንዳንድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ሲነገር ይሰማል፡፡ በተለይም በውጭው (በዝርወት) ዓለም የየሀገራቱ ህግ ቤተክርስቲያንን እንደማንኛውም ተቋም ሰለሚመለከታት በመጀመሪያ ተሰባስበው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ቢኖረን ብለው የመከሩትና አጥቢያ ቤተክርስቲያኑን በሀገሩ ህግ መሠረት ያስመዘገቡት ካህናትና ምዕመናን ራሳቸውን “መሥራች አባላት (founding members)” በማድረግ እነርሱ ያሉባት አጥቢያ ቤተክርስቲያን በእነርሱ እንደተመሠረተችና እነርሱ ‘ልዩ መብትና ልዩ ጥቅም’ ማግኘት እንዳለባቸው ያስባሉ፣ በተግባርም ያሳያሉ፡፡ ከእነርሱ በኋላ መጥተው የተቀላቀሉ ምዕመናን ደግሞ “ተራ/መደበኛ አባላት (regular members)” ተብለው ከማስቀደስና ገንዘብ ከማዋጣት ውጭ በሌላው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ‘አያገባችሁም’ ይባላሉ። በዚህም የተነሳ በአንዲት ቤተክርስቲያን ሁለት ዓይነት ደረጃ ያላቸው ምዕመናን እንዳሉ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ አለ፡፡ ይህ አስተሳሰብም በምዕመናን ዘንድ ክፍፍልን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር “ቤተክርስቲያን መመሥረት” የሚለውን አገላለፅና ተያይዘው የተፈጠሩ የተሳሳቱ ልማዶችን በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተክርስቲያን ሥርዓት አስረጅነት እንሞግታለን፡፡ አካሄዳችንም ይህ አስተሳሰብ በቤተክርስቲያን የፈጠረውንና የሚፈጥረውን ችግር ማሳየትና የመፍትሔ ሀሳብ መጠቆም ነው፡፡

አጥቢያ ቤተክርስቲያን መመሥረት”

በመጀመሪያ “መመሥረት” የሚለው ቃል ለቤተክርስቲያን ሲውል አዲስ ዶግማ (እምነት)፣ ቀኖና (ሥርዓት) እና አስተዳደር ያለው ተቋም (የሃይማኖት ድርጅት) መፍጠርን ያመለክታል። በአርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት “ቤተክርስቲያን መመሥረት” የሚለው አገላለፅ ለአጥቢያ ቤተክርስቲያንም ይሁን ለቤተክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር የሚስማማ አገላለፅ አይደለም፡፡ “መመሥረት” ማለት አዲስ ሀሳብ አመንጭቶ አስቀድሞ ያልነበረን አዲስ ተቋም እንዲመሠረት ማድረግን ያመለክታል፡፡ እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው የቤተክርስቲያን መሠረትና ራስ በሆነው በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እርሱ “በዚህች አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” (ማቴ 16፡16) ያለው መሥራቿ እርሱ መሆኑን ሲያረጋግጥ ነው፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተክርስቲያን በዓለም ላይ ዞረው አስተማሩ፣ ሰበሰቡ እንጂ አዲስ ቤተክርስቲያን አልመሠረቱም፡፡ በሐዋርያት ስብከት ያመኑ ክርስቲያኖችም ቃለ ወንጌልን የሚማሩበት፣ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበትና ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሠሩ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህንን “ሕንፀታ ለቤተክርስቲያን/የቤተክርስቲያን መታነፅ/” ብላ ታስበዋለች፣ታከብረዋለች፡፡ ከዚህም በኋላ ክርስትና በዓለም ዳርቻ ሁሉ ሲሰበክ ምዕመናን እየበዙ፣ በየቦታውም ሕንፃ ቤተክርስቲያን እያነፁና የቤተክርስቲያንን ተቋማዊ አስተዳደር እያደራጁ ከዚህ ዘመን ደርሰናል፡፡ የሃይማኖታችን መሠረት የሆነው ጸሎተ ሃይማኖትም “የሐዋርያት ጉባዔ በምትሆን በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን” የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታትን አንዲቱን ቤተክርስቲያን ነው። ቅዱስ ጳውሎስም “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ ታንጻችኋል (ኤፌ 2:20)” ያለው በዚሁ ምክንያት ነው።

ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የመሠረታት (መሥራቿ) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የእርሱ ስለሆነች “…ቤተክርስቲያኔን…” ሲል ተናግሯል፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” (ማቴ 21፡13) ያለው እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ” (ሐዋ 23፡20) ብሎ የተናገረው ቤተክርስቲያን የክርስቶስ መሆኗን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ የመሠረታት እንጂ ሰው የመሠረታት ቤተክርስቲያን የለችንም፡፡ ሰው የሚመሠርታት ቤተክርስቲያንም አትኖረንም፡፡ አንድ ጊዜ የተመሠረተች እንጂ በየጊዜው የምትመሠረት ቤተክርስቲያን የለችንም። አስቀድሞ በክርስቶስ ከተመሰረተው መሰረት የተለየች፣ ሰው የመሠረታት “ቤተክርስቲያን” የምትባል ተቋም ካለችም እውነተኛዋ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሳትሆን የግለሰቦች ድርጅት ናት፡፡ በአጭር አነጋገር “መመሥረት” የሚለው አስተሳሰብ ለቤተክርስቲያን አይመጥናትም፡፡ ቤተክርስቲያን አንድ ጊዜ በክርስቶስ ተመሥርታ ለዘላለም የምትኖር ናት እንጂ በየዘመኑ የምትመሠረት አይደለችም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” 2ኛ ቆሮ.3፤11

ቤተክርስቲያን የሁሉም እናት ናት። ልጆችዋም በእናት ቤተክርስቲያን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ይወለዳሉ። ይህ ከታመነ ሰው በእናት ቤተክርስቲያን ዳግመኛ ተወልዶ ይኖራል እንጂ እንዴት እናቱ የሆነች ቤተክርስቲያንን ሊመሠርት ይችላል? አራቱም የቤተክርስቲያን ትርጉሞች “መመሥረት” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ የሚስማማቸው አይደሉም። በመጀመሪያው ትርጉም: ሰውን (ክርስቲያንን) ታስተምረው ይሆናል እንጂ አትመሠርተውም። በሁለተኛው ትርጉም: የክርስቲያኖችን አንድነትን ትቀላቀለዋለህ እንጂ አትመሠርተውም። ይህ አስቀድሞም ያለና የሚኖር አንድነት ነውና። በሦስተኛው ትርጉም:  ሕንፃ ቤተክርስቲያንንም ታንፀዋለህ እንጂ አትመሠርተውም። በአራተኛው ትርጉም: የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋማዊ ልዕልና አስቀድሞ ተቋቁሟል። ስለዚህ መመሥረት የሚለው አገላለፅ ለቤተክርስቲያን የሚውልበት አግባብ አይታይም።

ቤተክርስቲያን ማለት በአንድ አጥቢያ የሚሰበሰቡ ክርስቲያኖች አንድነት ብቻ አይደለም፡፡ በጸሎቷ በሌላ ቦታ ያሉትን፣ በሞተ ሥጋ የተለዩትን፣ በአፀደ ነፍስ (በገነት)፣ በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብጹዓን የሚኖሩትን ቅዱሳን ምዕመናን እንዲሁም ለተልዕኮ በዓለማት ሁሉ፣ ለምስጋና በዓለመ መላእክት የሚፋጠኑትን ቅዱሳን መላእክት የማታስብ ቤተክርስቲያን የለችንም፡፡ ቤተክርስቲያንን በተሰበሰቡት ምድራውያን ልክ የሚያስቡ ሰዎች ከእውነተኛው የቤተክርስቲያን ማኅበር የተለዩ ናቸው፡፡ አስተሳሰባቸውም ምድራዊ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለእነርሱ የባህል መድረካቸው፣ የፖለቲካ አትሮኑሳቸው፣ የንግድ ቤታቸው፣ የመታያ ሰገነታቸው፣ የልብስ ማሳያቸው፣ የማዕረግ መጠሪያቸው፣ የሚወዱትን መጥቀሚያቸው፣ የሚጠሉትን መግፊያቸው ናት፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን በተጋድሎ ያስቀመጡልንን ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ መሠረት በሌለው “መሥራችነት” ሰበብ ለግልና ለቡድን መጠቀሚያ የሚያደርጉ ምንደኞች የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “ክብራቸው በነውራቸው፣ አሳባቸው ምድራዊ” (ፊልጵ. 3:19) በማለት የገለጻቸው ናቸው፡፡

በዚህ ዘመን ያሉ ሰዎች ማኅበር፣ እድር፣ ትዳር፣ ፓርቲ፣ ሌሎች ዓለማዊ ተቋማት ሊመሠረቱ ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ተቋማቱ አዲስ (ለመጀመሪያ ጊዜ) የሚመሠረቱ ከሆኑ ብቻ ነው። በሌላ አካባቢ ላለ ድርጅት ሌላ ቅርንጫፍ ማቋቋም ከሆነ “መመሥረት” አይባልም። ስለዚህ በዓለማዊው አስተሳሰብ እንኳን በሌላ ሀገር/አካባቢ ያለ ተቋምን የመሰለ ድርጅት ማቋቋም “መመሥረት” አይባልም። በዚህ አግባብ ቤተክርስቲያን መመሥረት ማለት አዲስ ዶግማ (እምነት) እና ሥርዓት (መተዳደሪያ ደንብ) ያለው አዲስ የእምነት ተቋም ማቋቋምን የሚያመለክት ነው። ይህም አንዳንድ ከቤተክርስቲያን የወጡ ወገኖች አዲስ የእምነት ድርጅት አቋቁመው በመንግስት አስመዝግበው ህጋዊ ሰውነት እንደሚሰጣቸው ያለ ነው። በአስተምህሮ ልዩነት ከቤተክርስቲያን አንድነት ተለይተው የራሳቸውን ተቋም የሚፈጥሩ ሰዎች ከተመሣረተው መሠረት የወጡ ናቸውና የዚህ ጦማር ትኩረቶች አይደሉም። ይሁንና የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማንነት በምድራዊ ህግጋት በሚሰጣት እውቅና የሚወሰን ወይም የሚገደብ አለመሆኑን መዘንጋት አይገባም።

አጥቢያ ቤተክርስቲያን ማቋቋ

አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሲባል ሦስት ነገሮችን በአንድነት የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ (የምዕመናኑ ኅብረትና አስተዳደሩ)፣ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑና መንፈሳዊ አገልግሎቱ ናቸው፡፡ እነዚህም “ቃለ ዓዋዲ” ተብሎ በሚታወቀው የቤተክርስቲያን ህግ ይተዳደራሉ፡፡ በአንድ አካባቢ አዲስ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሲያስፈልግ በአካባቢው ያሉት ምዕመናንና ካህናት ሆነው የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ በማስፈቀድ የአጥቢያ መንፈሳዊ አስተዳደሩን አቋቁመው ለአገልግሎት መስጫ የሚውል ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሠርተው ይህም በሊቀ ጳጳሱ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ይከብራል፡፡ ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት ዕለትም በየዓመቱ ይከበራል። (ማክበር በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጥ እንጂ ንግስን መነገጃ ለማድረግ ምክንያት የሚፈጥር አይደለም) ከዚህም በኋላ ማንኛውም ምዕመን በአጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔው ሥር በአባልነት ተመዝግቦ በእኩልነት (ያለምንም ልዩነት) በመንፈሳዊ አገልግሎት ይሳተፋል፡፡ አጥቢያ ቤተክርስቲያኗም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር አካል ሆና ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣቸውና በየጊዜው በሚያወጣቸው መመሪያዎች እየተመራች በሀገረ ስብከቱ ሥር ሆና አገልግሎት ትሰጣለች፡፡ በዚህም ካህናትና ምዕመናን እንደየድርሻቸው አገልግሎታቸውን ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ውስጥ “መሥራች አባል” እና “መደበኛ አባል” የሚለይበት ሥርዓት የለም፡፡ ለሁሉም እናት የሆነች ቤተክርስቲያን ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ነው የምታየው፡፡ በቤተክርስቲያን ሁሉም ልጅ ነው እንጂ መሥራችና ኋላ የመጣ የሚባል የለም።

ከቃላት ባሻገር

ቤተክርስቲያን መመሥረት የሚለው አገላለጽ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ አኳያ ስሁት መሆኑን አይተናል፡፡ በአንጻሩ በየቦታው የማኅበረ ምዕመናንን መሰብሰብ፣ የሕንፃ ቤተክርስቲያን መታነጽ እና የመንፈሳዊም ሆነ አስተዳደራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት የሚያስፈልግ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ለመግለጽ “መመሥረት” ከሚለው ስሁትና እምቅ (loaded) አገላለጽ ይልቅ “ማነጽ” እና “ማቋቋም” የሚሉት አገላለጾች የተሻሉ ናቸው፡፡ ይሁንና መሠረታዊው ነገር ከቃላት አመራረጥ የዘለለ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ መመሥረትም ተባለ ማቋቋም መዘንጋት የሌለበት መሠረታዊ ጉዳይ የቤተክርስቲያን ባህሪያት የሆኑ መገለጫዎችን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችንና አሠራሮችን ማስቀረት ነው፡፡ መሥራች ነን በሚል በየቦታው ከሚፈጸሙ ስሁት አስተሳሰቦችና አሠራሮችም የሚከተሉትን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ማሳያ አንድ: “ብቸኛ ባለቤትነት”

በግለሰቦች መቧደን ራሳቸውን በተለየ ሁኔታ የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ አካባቢ ባለ ልዩ መብትና ልዩ ተጠቃሚ አድርገው የሚያስቡ ግለሰቦችና ቡድኖች የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አሠራር በቡድናዊ ስሜት ሲያውኩ፣ አስተዳደራዊ እርከኖቿንም በብቸኛ ባለቤትነት ስሜት በመቆጣጠር የቤተዘመድ ሰበካ ጉባኤ የሚመስል ቅርጽ በመፍጠር የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊም ሆነ ተቋማዊ ኀልዎት የሚገዳደሩ አሰራሮች በአንዳንድ የሀገራችን ከተሞችና በበርካታ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባቸው የውጭ ሀገራት ከተሞች እየገዘፈ የመጣ ዘመን ወለድ ችግር ነው። እነዚህ አካላት በተግባር አንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያንን የግል ንብረታቸው አድርገው ነገር ግን በየመድረኩ “ቤተክርስቲያን የሁላችንም ናት” እያሉ በቤተክርስቲያንና በምዕመናን ላይ ያላግጣሉ። የተወሰነ ቡድን ለሥጋዊ ጥቅም ለሚገለገልበት ተቋም ሌላውን ምዕመን እያታለሉ ሳይተርፈው በእምነት ስም ቤተዘመድ (ጓደኛሞች) እንደፈለገው ለሚያዙበት “ተቋም” ገንዘብ የሚሰጥበትን ሁኔታን መፍጠር ግልፅ ውንብድና እንጂ ክርስትና አይደለም።

ቤተክርስቲያንን የግላቸው ሥጋዊ ርስት አድርገው ዕድሜ ልክ (እንደ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች) የአጥቢያ ቤተክርስቲያንንም ሆነ ከፍ ያሉ የቤተክርስቲያን የአስተዳደር እርከኖች በአምባገነንነት በመያዝ ሳይሠሩና ሳያሠሩ ተጣብቀውባት ቤተክርስቲያንን የቤተዘመድ ቤት አድርገዋት ይኖራሉ። ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ የሚላቸውንም እሺ ካለ በጥቅም እምቢ ካለ በጥቃት አፍ ያዘጋሉ። በአንዳንድ ሥፍራም በየዓመቱም ‘የምሥረታ/የመሥራቾች በዓል’ (Anniversary) በማዘጋጀት በቤተክርስቲያን ገንዘብ ዓለማዊ ፌሽታ ያደርጋሉ።  ይህም ሳይበቃቸው ሌሎችን ሲዘልፉ፣ ሲያሸማቅቁና ለራሳቸው አምባገነናዊ አሠራር ሲሉ እውነተኞችን ከቤተክርስቲያን ገፍተው ሲያስወጡ ኖረዋል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ “መናፍቅ” የሚል ፍረጃን ያለቦታው በመጠቀም የሚደረግ ማሳደድ ነው። በተቃራኒው ምንፍቅና ያለባቸውን ነገር ግን በጥቅም የተሳሰሩትን አቅፈውና ደግፈው በቤተክርስቲያን መድረክ እንዲፏልሉ ያደርጓቸዋል። በግልፅ መናፍቃን በመሆናቸው ተወግዘው የተለዩትም ይህን ግራ መጋባት በመጠቀም የዋሀንን የበለጠ ያስታሉ። ይህም የቤተክርስቲያንን ገፅታ ከማበላሸቱም በላይ ያለተተኪ እንድትቀር እያደረጋት ይገኛል።  በዚህ አካሄድ የተነሳ ብዙዎች ከቤተክርስቲያን ርቀዋል። መመለስ የሚችሉትም በጥላቻ ምክንያት የመናፍቃን ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል።

ማሳያ ሁለት: በጊዜና ሁኔታ ያልተገደበ አስተዳደራዊ ስልጣን

በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሥልጣን በዘመን የሚገደብ አይደለም። የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ጳጳሳት ስልጣነ ክህነት በሞተ ሥጋ እንኳ የማይቋረጥ ነው። ይሁንና ይህ መንፈሳዊ ትርጉም ለሥጋዊ የስልጣን አምባገነንነት መሸፈኛ መሆን አይችልም፣ አይገባምም። የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ የሌሎች የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አካላት የኃላፊነት ቦታዎች በጊዜና ሁኔታ የተገደቡ ናቸው። ራስን “መሥራች” አድርጎ በማቅረብ ያልተገደበ አስተዳደራዊ ስልጣንን መፈለግ ከቤተክርስቲያን ትውፊት የተፋታ የስህተት አሠራር ነው።

ይሁንና ለገንዘብና ለታይታ ክብር ሲሉ ቤተክርስቲያንን የሚጠጉ ምንደኛ ካህናትና ምዕመናን የየራሳቸውን ስብዕና ለማጉላት ሲሉ በየአውደምህረቱ በሚያሳዩት ያልተገራ መታበይ ራሳቸውን የቤተክርስቲያን መሥራች አድርገው በማቅረብና ለቤተክርስቲያን ሲሉ ብዙ መከራ መቀበላቸውን (በእውነትም በግነትም) በማቅረብ ከዚህ የተነሳ ስለአጥቢያ ቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ከእነርሱ ውጭ ያለ ካህንም ሆነ ምዕመን ባይተዋር እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ሀሳባቸውን የሚሞግት ካለም ያለአንዳች ርህራሄ ተረባርበው እያባረሩ “ክርስቶስ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግ ነው፣ አንድም ሰው መጥፋት የለበትም” እያሉ በአደባባይ ምፀትን ይናገራሉ። ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ፍጹም ባፈነገጠ፣ ከቤተክርስቲያን ትውፊት ፈጽሞ በተለየ የምድራዊ ካፒታሊዝም እሳቤ እየተመሩ “የሠሩትን ማመስገን ይገባል” በሚል የከንቱ ውዳሴ ናፍቆት በወለደው እይታ የቤተክርስቲያንን አውደምህረት ከመሠረታዊ አስተምህሮ ይልቅ “መሥራች” ወይም “ተጽዕኖ ፈጣሪ” ናቸው ተብለው ስለሚታሰቡ ሰዎች በመዘብዘብ ምዕመናንን ያሰለቻሉ፡፡ አንዳንዶቹ ምንደኛ ሰባክያንም ከፕሮቴስታንቶች በተወሰደ ኢ-ክርስቲያናዊ ልማድ “በዚህ በዚህ ቦታ የራሴን (የራሳችንን) ቤተክርስቲያን ስለከፈትን እየመጣችሁ ተባረኩ” የሚል ዓይነት ፍጹም መንፈሳዊ ለዛ የሌለው ዲስኩር ማሰማታቸው እየተለመደ የመጣ ነውር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ “እኛም የምናዝበት የራሳችን ቤተክርስቲያን ይኑረን በሚል” ጥቂት ምእመናን ባሉበት ከተማ በቁጥር የበዙና ቡድናዊ አደረጃጀትን የያዙ አጥቢያዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አስተዳደር ያልተገደበ ሥጋዊ ስልጣን ምንጭ የሚያደርገው ስሁት ልማድና አሰራር ካልታረመ እንደ አሜባ (Ameoba) መከፋፈሉም በሚያሳዝን መልኩ ይቀጥላል።

ማሳያ ሦስት: ቤተክርስቲያንን የባህልና የፖለቲካ አቋም መገለጫ ማድረግ

በዝርወት ዓለም (diaspora) ካሉ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት በአንዳንዶቹ ግልጽ በሆነ መልኩ የ”መሥራችነት” ስነ-ልቦና ተለይተው ከሚታወቁ ፖለቲካዊ የአወቃቀርም ሆነ የአስተሳሰብ ቡድኖች ጋር የተሳሰሩ ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ካህናትና ምዕመናን በእነዚህ አጥቢያዎች የሚኖራቸው ተሳትፎ የሚወሰነው በመንፈሳዊ መመዘኛ ሳይሆን በቦታው የሚታወቀው “የመሥራችነት ስነ-ልቦና መገለጫ” የሆነውን የፖለቲካም ሆነ የባህል ስብስብ ላይ ባላቸው አመለካከት የተነሳ ነው፡፡ አንድ ካህን ወይም ምዕመን የፈለገ መንፈሳዊ አበርክቶ ቢኖረው በዚያ አጥቢያ ያሉትን መንፈሳዊ መሠረት የሌላቸው የባህልና የፖለቲካ ስነ-ልቦና መገለጫዎች ካልተቀበለ፣ በተለይም ደግሞ ከተቸ ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርጋሉ፣ በሽታው በፀናባቸው ቦታዎችም ሰበብ ፈልገው አውግዘው ይለያሉ፡፡ ነገር ግን በየመድረኩ “ቤተክርስቲያን ሰማያዊት ናት፣ ምድራዊ ነገር አይፈፀምባትም” በማለት በተግባር ከሚያደርጉት የሚቃረን የይስሙላ ዲስኩር ያሰማሉ።

አንዳንዶቹ በመተዳደሪያ ደንባቸው ሳይቀር እነርሱ ይወክለናል የሚሉትን ከፋፋይ ስነ-ልቦና (ምሳሌ: ፖለቲካዊ አቋም፣ የብሔር ማንነት ወይም የፖለቲካዊ ሰንደቅ ዓላማ ምርጫና የመሳሰሉትን) በማካተት ቤተክርስቲያንን በምድራዊ አስተሳሰብ ይገድቧታል፡፡ እነርሱ ይወክለናል የሚሉትን ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ባህላዊ ጨዋታ በቤተክርስቲያን አውደምህረት መንፈሳዊ በሚመስል ማዳቀል ሲያቀርቡ ሀገር ወዳድ፣ የቤተክርስቲያን ጠበቃ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በሌላ ስነ-ልቦና ያሉ ሰዎች ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ባህላዊ ጨዋታዎች ሲያቀርቡ ግን የራሳቸውን ረስተው ይቃወማሉ፡፡ የሚያሳዝነው ከእነርሱ በተመሳሳይ መንገድ ሄደው ሌሎች ይህንኑ ስህተት በሌላ መንገድ ሲደግሙት ለማውገዝ ቀዳሚ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ጦማር ሲያነቡ እንኳን የሌሎቹ እንጂ የራሳቸው አይታያቸውም፡፡ ይህም ከችግር ፈጣሪዎቹ ብዙዎቹ “የሚያደርጉትን የማያውቁ” የዋሀን እንጂ ሆነ ብለው የሚያጠፉ አለመሆናቸውን ሊያሳይ ይችላል፡፡

መደምደሚያ

አጥቢያ ቤተክርስቲያን በሌለበት ምዕመናንን አስተባብሮ ቤተክርስቲያን እንዲተከልና ምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የተቀደሰና ሰማያዊ ዋጋን የሚያሰጥ የጽድቅ አገልግሎት ነው። አጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ከተቋቋመ በኋላ ግን “መሥራች ስለሆንን ልዩ መብት አለን፣ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለብን፣ አዛዥና ናዛዥ ሆነን ዕድሜ ልክ እንኖራለን፣ ማንም አይነቀንቀንም፣ ፈቃዳችንን የሚፈፅመውን በአስተዳደር እናሳትፋለን፣ ፈቃዳችንን የማይፈፅመውን እንገፋለን፣ ሌላው ምዕመን ማስቀደስና ገንዘብ መስጠት እንጂ አስተዳደሩ አይመለከተውም” በሚል የአስተሳሰብ ቅኝት መመራት ወንጀልም፣ በደልም፣ ኃጢአትም ነው። አንዱ ቡድን ራሱን “መሥራች” አድርጎ የሚሾምበት ሌላውን “ተራ አባል” እያለ የሚያሳድድበት ተቋም እንኳን መንፈሳዊውን ምድራዊውን የተቋማት አስተዳደራዊ ስነ-ምግባር አያሟላም። እንደዚህ ዓይነቱ የአስተዳደር ብልሽት ይስተካከል ዘንድ ሁሉም ክርስቲያን የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል እንላለን። ለዚህም ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሲመት ርቀው፣ ራሳቸውን እየጎዱ ቤተክርስቲያንን ያገለገሉ ቅዱሳንና ቅዱሳት አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን። †

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s