የክልል ቤተክህነት: ለዘላቂ መንፈሳዊ አንድነት ወይስ ለፖለቲካዊ ልዩነት?

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋና አስተዳደሯ “የየብሔረሰቡን ቋንቋና ባህል የዋጀ አይደለም” በሚል መነሻነት የተለያየ ቋንቋ ያላቸውና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን “የየራሳቸው ቤተክህነት ሊኖራቸው ያሰፈልጋል” የሚል አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመደበኛና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ ይህም በምዕመናን አእምሮ ጥያቄን ከመፍጠሩም ባሻገር የቤተክርስቲያንን አንድነትም እንዳይፈታተን ያሰጋል፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር  “የክልል ቤተክህነት ማቋቋም” የሚለውን ሀሳብ በቅዱሳት መጻሕፍትና በሥርዓተ ቤተክርስቲያን አስረጅነት እንዳስሳለን፡፡ አካሄዳችንም ሀሳቡን የሚያነሱትን፣ ቅን ሀሳብም ሆነ መንፈሳዊ ያልሆነ ተልዕኮ የያዙትን ወገኖቻችንን ለመውቀስ ሳይሆን ለመልካም ያሰብነው አገልግሎት ለክፋት እንዳይውል ለማሳሰብ፣ ቤተክርስቲያንን በምድራዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቁርቁስ ውስጥ ማስገባት የፈጠረውን፣ የሚፈጥረውን ጠባሳ ማሳየትና የመፍትሔ ሀሳብ መጠቆም ነው፡፡

የቤተክርስቲያን አስተዳደር 

ቤተክህነት (የክህነት፣ የአገልግሎት ቤት) ስንል አጠቃላይ የቤተክርስቲያንን ተቋማዊ አስተዳደር፣ ካህናትና የክህነት አገልግሎትን ማለታችን ነው። ይህም ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጀምሮ ወረዳ ቤተ ክህነትንና ሀገረ ስብከትን ጨምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ያለውን ያጠቃልላል። የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ በማንኛውም ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ሊሻሻል ይችላል። የቤተክህነት መምሪያዎች፣ የሀገረ ስብከቶች አወቃቀር፣ የወረዳ ቤተክህነቶች አወቃቀር፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳደር፣ የማኅበራትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አወቃቀር ዘመኑን በዋጀ መልኩ በየወቅቱ ይሻሻላሉ። ይህም ሲደረግ የነበረና ለወደፊትም የሚቀጥል ነው። የተሻለ የአስተዳደር መዋቅር መፍጠርም ዓላማው መንፈሳዊ አገልግሎትን ማጠናከር ነው።

ቋንቋና መንፈሳዊ አገልግሎት

ቤተክርስቲያን በሕዝብ ቋንቋ ታስተምራለች እንጂ ቋንቋን ለሕዝብ አታስተምርም። በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች ሀገራት የተለያየ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ (ብሔረሰብ) ከመኖሩ አንፃር ቤተክርስቲያንም ምዕመናን በሚናገሩት ቋንቋ ሁሉ ማስተማርና የመንፈሳዊውንም ይሁን የአስተዳደሩን አገልግሎት በዚሁ ቋንቋ መፈጸም እንደሚገባት የታመነ ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ካህናትና ምዕመናን የመጠየቅ፣ የቤተክርስቲያኒቱም አስተዳደር ደግሞ መልስ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን ከማድረግ ቸል የሚል አስተዳደር በምድር በሰው ፊት፣ በሰማይም በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ ይሆናል። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ቋንቋን  የምትጠቀመው ወንጌልን ለመስበክ እምነትን ለማስፋትና የክርስቲያኖችን አንድነት ለመፍጠር ነው እንጂ ምዕመናንን እርስ በእርስ ለመ(ማ)ለያየት አይደለም። ቤተክርስቲያን አንዱን ቋንቋ ከሌላው ቋንቋ አታስበልጥም፣ አታሳንስምም። ቋንቋን ስትጠቀምም ሰው ስለሚናገረውና ስለሚረዳው እንጂ በማበላለጥ አይደለም። በአንዳንድ አኃት አብያተ ክርስቲያናት በሰንበት ሁለት ቅዳሴ (በተለያዩ ቋንቋዎች) ይቀደሳል። ስብከተ ወንጌልም እንዲሁ ለተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመደበኛነት ይዘጋጃል። በእኛም ሀገር በተለያዩ ቋንቋዎች ወንጌልን የማስተማርና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶችን የመስጠት ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ቋንቋን መሠረት ያደረገ መዋቅር

በአሁኑ ሰዓት ቋንቋንና ባህልን መሠረት አድርጎ በተዋቀረው “ክልል (national regional state)” ደረጃ ቤተክህነት ማቋቋም ያስፈልጋል የሚል ጉዳይ እየተነሳ ይገኛል። በሀሳብ ደረጃ ስናየው ቤተክርስቲያን እንኳን በክልል ይቅርና በወረዳም ደረጃ ቤተክህነት ያላት ተቋም ናት። ትክክለኛው ጥያቄ፣ በትክክለኛው ጊዜ፣ ለትክክለኛው ዓላማ፣ በትክክለኛው ጠያቂ፣ ለትክክለኛው መልስ ሰጪ አካል ቢቀርብ ለቤተክርስቲያን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ነገር ግን በአክራሪዎች ክፋት ክርስቲያኖች እየተገደሉ፣ መከራን እየተቀበሉና እየተሰደዱ ባሉበት ወቅት፣ ቤተክርስቲያን እየተቃጠለችና ንብረቶቿ እየተዘረፉ ባሉበት ሰዓት፣ ጥላቻ የተጠናወታቸው ወገኖች ቤተክርስቲያን ላይ አፋቸውን በከፈቱበት በዚህ ወቅት ቅድሚያ ለሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ከሁሉም በፊት ቤተክርስቲያንን የመጠበቅ ሥራ መቅደም ይኖርበታል። ቤተክህነት የሚኖረው ምዕመናን ሲኖሩና በአጥቢያ ደረጃ ቤተክርስቲያን ስትኖር ነውና። ቤተክርስቲያን እሳት ሲነድባት ድምፁን እንኳን ያልሰማነው አካል ድንገት ተነስቶ “የክልል ቤተክህነት ላቋቁም” በማለት ቤተክርስቲያንን በቋንቋዎች ቁጥር ልክ ለመከፋፈል ሲቃጣ  ዓላማው እሳቱን ለማጥፋት ስለመሆኑ እንኳን ያጠራጥራል። የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች “ቤተክርስቲያን ፈርሳለች፣ የያሬዳዊ ዜማን በእኛ ቋንቋ መስማት አንፈልግም፣ ቤተክርስቲያን የመሬት ወራሪ ነች፣ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ንብረት ናት”፣ አልፎ አልፎም ለቤተክርስቲያን መቃጠልና ለክርስቲያኖች መገደል ራሷን ቤተክርስቲያንን “ተጠያቂ ናት” ሲሉ ይሰማል። ቤተክርስቲያንንም በእነዚህም በሌሎች ጉዳዪች ስሟን ሲያጠፉ ይሰማሉ። ይህንን እያዩ የሀሳቡን ዓላማ አለመጠራጠር ይከብዳል። የተባለው “የክልል ቤተክህነት” በቅዱስ ሲኖዶስ ቢፈቀድ እንኳን በሌሎች ቅን እና መንፈሳውያን የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ አባቶች እንጂ በእነዚህ ሊመራ አይገባም።

ቋንቋን መሠረት ያደረገ የቤተክህነት አወቃቀር ሀሳብ ቢተገበር አግላይ እና ከፋፋይ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ ሀሳብ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን የአስተዳደር ብልሽትን ለማስተካከል በሚል ምክንያት መደላድልነት ቤተክርስቲያንን በዘር በተቧደኑ አንጃዎች መዳፍ ሥር እንዳይጥላት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የፖለቲካ አስተዳደርና የቤተክርስቲያን አስተዳደር የተለያየ ዓላማ እንዳላቸው እየታወቀ የግድ ትይዩ አወቃቀር ይኑራቸው የሚለው አስተሳሰብ አደገኛ ነው። ቤተክርስቲያን በሁሉም ቋንቋዎች አገልግሎት ትሰጣለችና በቋንቋዎቹ ብዛት ልክ ቤተክህነት ይኑራት ማለት አይቻልም። ቢሆንም “የክልል ቤተክህነትን” ጉዳይ ማንም ያንሳው ማን ጥያቄው ከጥላቻ ያልመነጨና መለያየትን ግብ ያላደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። ክርስትና ፍቅርና አንድነት እንጂ መለያየትና ጥላቻ አይደለምና። ሆኖም ይህንን ሀሳብ አስፍቶ ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች ማንሳት ይጠቅማል፡፡

ሊፈታ የሚገባው ችግር

ለዘመናት የቆየውና በዚህ ዘመንም መሠረታዊ ችግር ተደርጎ የሚነሳው የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት፣ አስተዳደርና አስተምህሮ የህዝቡን ቋንቋና ባህል ያልዋጀ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ምዕመናን በአገልግሎቱ ተደራሽ ባለመሆናቸው ከቤተክርስቲያን መውጣታቸውና የቀሩትም አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ እያገኙ አለመሆናቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህንንም ችግር መፍታት የሚጠበቅበት የጠቅላይ ቤተክህነትና የየሀገረ ስብከት መዋቅር ሥር የሰደደ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል ጉድለት እንዲሁም የአሠራር ብልሹነት ስላለበት መፍትሔ ሊያመጣ አልቻለም የሚል አመክንዮ ነው። ከዚህ አንጻር ምእመናን ከቤተክርስቲያን እንዲወጡ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ የቋንቋ ችግር ቢሆንም ችግሩ የቋንቋ ችግር ብቻ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ብዙ ሲገለጽ እንደቆየው የቤተክርስቲያን ችግር በዋናነት አስተዳደራዊ (functional) ነው እንጂ መዋቅራዊ (structural) ብቻ አይደለም፡፡ ይህም ችግር በቋንቋ ያልተወሰነ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ሥር የሰደደና የተንሰራፋ ነው፡፡

ከዚህ ችግር ጋር አብሮ መታየት ያለበት ሌላ ዐቢይ ጉዳይ አለ። ይህም ቤተክርስቲያን በተቋም ደረጃ ስለመንፈሳዊ አገልግሎት መጠናከር ትሠራለች እንጂ ይህንን ቋንቋ እንጠቀም ይህንን ደግሞ አንጠቀም ብላ አታውቅም፣ ለወደፊትም አትልም። እንዲህ የሚል አስተምህሮም ሥርዓትም ትውፊት የላትምና። አገልጋዮች በራሳቸው የቋንቋ ውስንነት ምክንያት በአንድ ቋንቋ ብቻ ያስተማሩበት አካባቢ ካለ ሌሎች የአካባቢውን ቋንቋ የሚችሉ አገልጋዮች በቋንቋቸው እንዳያስተምሩ፣ አገልጋዮች እንዳያፈሩ፣ እንዳይቀድሱ፣ እንዳያስቀድሱ፣ የአስተዳደር ሥራ እንዳይሠሩ የሚከለክላቸው ነገር የለም። በጠቅላይ ቤተክህነትም ሆነ በሀገረ ስብከት ያለው አገልግሎትም ከዚህ የተለየ ህግ የለውም። ከቤተክርስቲያን አስተምህሮና ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ ቤተክርስቲያንን የፖለቲካ ሀሳብ ማራገፊያ የሚያደርጉ ሰዎች የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ተጠቅመው የሚያደርጉትን ያልተገባ ንግግርና አሰራር ማረም ግን ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁንና በማሳችን ውስጥ ጠቃሚ የመሰላቸውን አረም እየዘሩ ምዕመናንን ለፖለቲካዊ ዓላማ መጠቀሚያ የሚያደርጉትን ሰዎች መታገል መዋቅር በመቀየር ብቻ የምንፈታው ሳይሆን ሳያውቁ የሚያጠፉትን በማስተማር፣ አውቀው የሚያጠፉትን በማጋለጥና ተጠያቂ በማድረግ መሆን አለበት፡፡

የሚፈለገው ለውጥ

ቋንቋን በተመለከተ ላለው ችግር መፈትሔው ምንም የማያሻማ ነው፡፡ ችግሩ የቋንቋ ጉዳይ ከሆነ መፍትሔው እንዴት የመዋቅር ሊሆን ይችላል? ይልቅስ መፍትሔው ምዕመናን የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱንም በቋንቋቸው እንዲያገኙ፣ አስተዳደሩም በቋንቋቸው እንዲሆን ማድረግ ነው። ለዚህም የሕዝቡን ቋንቋ የሚናገሩ አገልጋዮችንና የአስተዳደር ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ በቋንቋው መጻሕፍትን ማሳተም፣ በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ የሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃንን ማስፋፋትን ይጠይቃል። ከምንም በላይ ደግሞ ይህንን ሊያስፈፅም የሚችል መንፈሳዊ ዝግጅት፣ በቂ አቅምና ቁርጠኝነት ያለውን አስፈፃሚ አካል መፍጠርን ይጠይቃል። ይህንንም ለማድረግ ምን አይነት የአመለካክት ለውጥ፣ የአስተዳደራዊ ስነ-ምግባር መሻሻል፣ የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ ያስፈልጋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ግን ጥናትን ይጠይቃል። የቋንቋና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ተብሎ እየቀረበ ያለው አማራጭ (“የክልል ቤተክህነት ማቋቋም”) የመፍትሔው አካል ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ሌሎችም የተሻሉ አማራጮችም ሊኖሩ ይችላሉ።

እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገው ጉዳይ ግን አስተዳደራዊ ችግሩ በዋናነት  ከቋንቋ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ከቋንቋም በላይ ሥር የሰደደ በመሆኑ አማርኛም የሚናገሩ ምዕመናን ቤተክርስቲያንን እየተው የመጡበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ መፈታት ያለበት ይህ መሠረታዊው የአስተዳዳር ችግር ነው፡፡ ቋንቋን በመቀየር ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ ቤተክርስቲያን በአንድና በሁለት አይደለም በብዙ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ ሀገረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተክህነት፣ አጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ መገናኛ ብዙሀን ወዘተ እንዲኖሯት ማድረግን እንደ አማራጭ እንኳን ሳይታይ ተቻኩሎ “የክልል ቤተክህነት” ማለት ችግሩን በሚገባ ካለመረዳት ወይም ሌላ ዝንባሌን ከማራመድ የመጣ ስላለመሆኑ ማረጋገጫ ያስፈልገዋል።

የመፍትሔው አሰጣጥ ሂደት

በሕክምናው ሙያ የታመመን ሰው ለማከም በመጀመሪያ ደረጃ የበሽታውን ምንነት በትክክል (በሙያው በሰለጠነ ባለሙያና ጥራት ባለው መሣርያ) መርምሮ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ቀጥሎም በሽታውን ለማከም የሚውለውን መድኃኒት ለይቶ ማዘዝን ይጠይቃል፡፡ በመጨረሻም የታመመው ሰው የታዘዘለትን መድኃኒት በታዘዘለት መሠረት መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ በሕግ ሙያም ቢሆን በቂ መረጃና ማስረጃ ሳይሰነድ ፍርድ አይሰጥም። አስተዳደራዊ ችግርንም ለመፍታት እንዲሁ ነው፡፡ ማንኛውንም የቤተክርስቲያን ችግር ለመፍታት ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ነው። ሁለተኛው እንደ ሰው አቅም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም የመፍትሔ አማራጮችን በጥናት በተደገፈ መረጃ ማቅረብ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ህግንና ሥርዓትን የተከተለ የችግር አፈታት ሂደትን መከተል ነው፡፡

በዚህ መሠረት ይህንን ችግር ለመፍታት ይረዳ ዘንድ ያለውን መሠረታዊ ችግር ከነመንስኤዎቹና ያባባሱት ምክንያቶች ያለውን መረጃ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ በባለሙያ እንዲተነተኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ አማራጮችን በማሰባሰብ የመፍትሔ ሀሳቦቹ ለመተግበር የሚያስፈልጋቸው ግብዓትና ቢተገበሩ የሚያመጡት ውጤትና የሚያደርሱት ጉዳት (ካለ) በባለሙያዎች ተጠንቶና በውይይት ዳብሮ ውሳኔ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ለሆነውና ለሚሰጠው  ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም መዋቅርን የሚነኩ ለውጦች ወጥ በሆነ መንገድ መዘጋጀትና መተግበር ስለሚያሰፈልጋቸው ጥንቃቄን ይሻሉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን እየወጡ “እኛ በራሳችን የወደድነውን እናደርጋለን፤ ሌላው ምን ያመጣል?” ማለት ግን ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ዓለማዊነቱ፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጥፋቱ ያመዝናል፡፡

መንፈሳዊ ለዛ የሌላቸው ፖለቲካዊ አመክንዮዎች

የክልል ቤተክህነትን ጉዳይ የሚያቀነቅኑ እና ራሳቸውን የእንቅስቃሴው መሪዎች መሆናቸውን ያወጁ ካህናት በቅርቡ በሚዲያ ያስተላለፏቸው መልእክቶች ከመንፈሳዊ እሳቤ ይልቅ “ለወቅቱ የሚመጥን”፣ ስሜት የተጫነው ነበር የሚል ምልከታ አለን፡፡ ችግሮችን አግዝፎ በመናገርና ራስን አስማት በሚመስል መልኩ ብቸኛ የመፍትሔ ምንጭ አስመስሎ የሚያቀርብ፣ በተግባር ያሉት መሠረታዊ ችግሮች የፈጠሩትን ቀቢጸ ተስፋ እንደ መደላድል በመጠቀም መንፈሳዊም ምክንያታዊም ባልሆነ የብልጣብልጥነት መንገድ ወደ ከፋ የችግር አዙሪት የሚመራ ነው፡፡ ይህም የእንቅስቃሴውን ዳራ ያመላክተናል፡፡ ቤተክርስቲያን ለማንም በሚታወቅ መልኩ በነውረኛ አሸባሪዎች እየተቃጠለች፣ ካህናቷና ምዕመናኗ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ባለበት ወቅት ለቤተክርስቲያን ጉዳት ቤተክርስቲያንን ተቀዳሚ ተወቃሽ አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች ከመንፈሳዊ ዓላማ ይልቅ ሊንከባከቡት የሚፈልጉት ፖለቲካዊ እይታ ያለ ይመስላል፡፡ ሕዝብን በጅምላ በመፈረጅ አንዱን የዋህና ቅን፣ ሌላውን መሰሪና ተንኮለኛ፤ አንዱን ጥንቆላን የሚፀየፍ፣ ሌላውን ጥንቆላን የሚወድ፤ አንዱን ተበዳይ ሌላውን በዳይ አድርጎ የሚተነትን እይታ በመንፈሳዊ ሚዛን ይቅርና በዓለማዊ አመክንዮ እንኳ ፍፁም ስህተትና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ቅኝት የሚቆም መዋቅር ወገንተኝነቱ ለመንፈሳዊ አንድነት ሳይሆን ለፖለቲካዊ ልዩነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄውን በቅንነት መመልከት

በመጀመሪያ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ማጠናከርን ዓልመው የሚነሱ ጥያቄዎችን በቅንነት መመልከት የቤተክርስቲያን ትውፊትም ሥርዓትም ነው፡፡ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን ከጠያቂ ግለሰቦች የቀደመም ሆነ የአሁን ማንነት ጋር በማምታታት ጉዳዩን ሳይመረምሩ ማለፍ ለማንም አይጠቅምም፡፡ እንኳን በቤተክርስቲያን ካህናትና አገልጋዮች የሚነሳን ሀሳብ በሌሎች አካላት የሚሰጡ ሀሳቦችንም በቅንነት በመመርመር ለምዕመናን መንፈሳዊ አንድነት የሚበጀውን፣ ዘመኑንም የዋጀውን አሰራር መከተል ይገባል፡፡የጥያቄውን አራማጆች ከጥያቄው ይዘት በወጣ በልዩ ልዩ መንገድ እየተቹ በተመሳሳይ መመዘኛ የባሰ ጅምላ ፈራጅነትን መከተል ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ፣ ከምንም በላይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቅ መሆኑን ተገንዝበን በቅን እይታ ከወንድሞቻችን፣ አባቶቻችን ጋር ልንመካከር ይገባል እንጂ እንደ ወደረኛ መተያየት ፍፁም ስህተት ነው፡፡

በሌላ በኩል የሚነሱ/የተነሱ ጥያቄዎችንና የተጠቆሙ የመፍትሔ ሀሳቦችን አጣሞ በመተርጎም ሌሎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግም አይገባም፡፡ ለምሳሌ ከቋንቋ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት “በክልል ደረጃ የቤተክህነት መዋቅር ቢኖረን” ብሎ መጠየቅ “የክልል ቤተክርስቲያን ለመመሥረት ነው” ተብሎ መተርጎም የለበትም፡፡ ይህ ሀሳብ የዚያ አይነት አዝማሚያ ካለው፤ ከጀርባ ሆኖ የሚዘውረው አካል ካለ፤ ሌላን ግብ ለማሳካት የተቀየሰ ስልት ከሆነ፤ ወይም ቤተክርስቲያንን የሚከፍላት ከሆነ በመረጃ ተደግፎ መቅረብ አለበት፡፡የክልል ቤተክህነት ሀሳብ አራማጆች ፖለቲካዊ ምልከታቸው የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አንድነት ሊጎዳ የሚችለውን ያክል የክልል ቤተክህነት መቋቋምን ከመንፈሳዊ እይታ ሳይሆን ከፖለቲካዊና የማንነት ምልከታ ጋር ብቻ በማገናኘት ደርዝ የሌለው ማምታቻ የሚያቀርቡ ሰዎች አስተሳሰብም ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አንድነት ከባድ ችግር የፈጠረና የሚፈጥር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቋንቋን በተመለከተ ግን የቤተክርስቲያን አንድነት የሚገለጠው በአንድ ቋንቋ በመጠቀም አይደለም፤ በክልል ደረጃ የቤተክርስቲያን መዋቅር ባለመኖሩም አይደለም። የቤተክርስቲያን አንድነት  በዋናነት የሚገለጠው በእምነት (ዶግማ) እና በቀኖና (ሥርዓት) አንድነት ነው።

መፍትሔውን በጥንቃቄ ማበጀት

በተነሳው ጉዳይ ጥያቄ የሚጠይቀውም ሆነ የመፍትሔ ሀሳብ የሚጠቁመው አካልም ቢሆን እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የፈቀደውና ለቤተክርስቲያን/ምዕመናንና ካህናት/ የሚበጃት ይሁን በማለት መንፈሳዊ አካሄድን መከተል ይጠበቅበታል፡፡ጥያቄው የሚነሳውም በውጫዊ አካል ግፊት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ ለሆነ ዓላማ መሆን ይኖርበታል፡፡ የመፍትሔ አማራጮችም ከግል/ከቡድን ጥቅም፣ ከመናፍቃን ተንኮልና ከፖለቲካ ሴራ በጸዳ መልኩ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ሀሳቦች በቅንነት ቢቀርቡም እንኳን አንዳንድ አካላት ይህንን ‘የለውጥ’ አጋጣሚ በመጠቀም ቤተክርስቲያንን ከማዳከም ወይም ከማጥቃት እንደማይቦዝኑ ማስተዋል ያሻል፡፡ በአስተዳደራዊ ጥያቄ ሽፋን የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ሥርዓት የማይገዳቸው አካላት ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈልና ምዕመናንን በመለያየት ነጣጥሎ ለማጥቃት ወይም ምንፍቅና ለማስፋፋት እንዳይጠቀሙበት ፈቃደ እግዚአብሔርን በማስቀደም በጸሎት፣ በመመካከርና በመግባባት ሊሠራ ይገባዋል። ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የሀገር ውስጥና የሀገር ውጭ ሲኖዶስ በሚል በመለያየት መከራ ውስጥ ለቆየችው ቤተክርስቲያን ዛሬ ላይ ደግሞ የዚህ ክልልና የዚያ ክልል ወይም የዚህ ቋንቋና የዚያ ቋንቋ ቤተክርስቲያን የሚል ክፍፍል እንዳይመጣ ሰዎች ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ሊያስቀድሙ ይገባል እንላለን፡፡

ከጊዜያዊ መፍትሄው ባሻገር

የክልል ቤተክህነት ጉዳይ ከአስተዳደራዊ ጥያቄነት ይልቅ በሀገራችን ኢትዮጵያ በነበረው፣ ባለውና በሚኖረው የህዝቦች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር የቤተክርስቲያን ሚና ምን መሆን እንዳለበት ካለመገንዘብ ወይም ቤተክርስቲያንን የፖለቲካዊ ነጥብ ማስቆጠሪያ ሜዳ፣ አልያም የፖለቲካዊ ቂም ማወራረጃ መድረክ አድርጎ ከሚያስብ መለካዊ እና ስሁት እይታ የሚመነጭ ነው፡፡ ስለሆነም ጊዜ ሊሰጠው የማይገባውን አስተዳደራዊ ብልሹነት ማስተካከል እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያን የአስተዳደርና አገልግሎት አካላት፣ ካህናትና ምዕመናን መሰረታዊውን የተቃርኖ ምንጭ በአግባቡ በመለየት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሰማያዊ ተልዕኮና ተያያዥ ማኅበራዊ አበርክቶዎችን በአግባቡ ለሁሉም ማዳረስ እንድትችል ከተቋማዊ የፖለቲካ ወገንተኝነት መለየት እንደሚያስፈልግ ከመረዳት መጀመር አለባቸው፡፡

የቤተክርስቲያን አካላት የሆኑ ምዕመናንና ካህናት በየግላቸው የሚያደርጉት ነቀፌታ የሌለበት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከቤተክርስቲያን መንፈሳዊም ሆነ ተቋማዊ ኀልወት ጋር እየተሳከረ መቅረብ የለበትም፡፡ ይሁንና በሀገራችን ኢትዮጵያ ያሉ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ አካላት የቤተክርስቲያንን ምዕመናንና ካህናትም ሆነ ተቋማዊ ማንነት ለየራሳቸው ፖለቲካዊ ዓላማ ለማዋል መሞከራቸው አይቀርም፡፡ ይህም የሚደንቅ አይደለም፡፡ ታሪክን  በልካቸው ሰፍተው የሚፈልጉትን ብቻ እያዩ ደክመው የሚያደክሙ ሰዎች እንደሚመስላቸው ይህ ቤተክርስቲያንን ለፖለቲካዊ ዓላማ የመጠቀም አካሄድ ትላንት ወይም ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በዘመናት ሁሉ ቤተክርስቲያን እየተፈተነች ያለፈችበት የታሪክ ሂደት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከምድራውያን ነገስታት ድርጎ ይቀበሉበት የነበረውን ዘመን “የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን” አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ፖለቲካንም ሆነ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ በሚገባው ደረጃ የማይረዱ ፊደላውያን ናቸው፡፡ መሰረታዊው ጉዳይ ቀደምት የቤተክርስቲያን መሪዎች፣ ካህናትና ምዕመናን ለየዘመናቸው በሚመጥን ጥበብ ተመርተው ቤተክርስቲያንን ለእኛ እንዳደረሱልን እኛም በዘመናችን ያለውን ከፖለቲካዊ ቁርቁስ የሚወለድ ወጀብ በሚገባ ተረድተን ለዘመኑ የሚመጥን መፍትሄ ማመላከት ይኖርብናል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ባሉት የተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮች የቤተክርስቲያናችንን መንፈሳዊ ማንነት፣ አስተዳደራዊ መዋቅርና እያንዳንዱን ምዕመን በአሉታዊ መልኩ የማጥቃትና የመጉዳት ግልጽ ዓላማ ያላቸውንም ሆነ በሚገባ ሳይረዱ ለቤተክርስቲያን ፈተና የሆኑባትን አካላት እንደቅደም ተከተላቸው ሳንሰለች መጋፈጥና ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቤተክርስቲያንን በግልጽ በጠላትነት ፈርጀው የከበሩ መቅደሶቿን ለሚያቃጥሉ፣ ካህናቷን ምዕመናኗን ለሚያርዱ፣ ለሚገሉ ሰዎች ምንም ዓይነት የአመክንዮ ድርደራ ማቅረብ አይጠቅምም፡፡ ይሁንና ቤተክርስቲያንን እየወደዱ፣ የአስተምህሮዋን ርቱዕነት እየመሰከሩ፣ እንደ አቅማቸውም በግልም ሆነ በቡድን፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ መንፈሳዊ ሱታፌ እያደረጉ በፖለቲካዊ አቋም የተነሳ ከቤተክርስቲያን የሚርቁትን ግን ለመታደግ መረባረብ አለብን፡፡ ይህንንም ለማድረግ ዋና ዋና የሚባሉትን የችግር ምንጮች መለየት፣ በአቅማችን መምከርና ማስተማር እንዲሁም በአመክንዮ መሞገት ያስፈልጋል፡፡

የተማጽኖ ቃል

እስኪ በስህተት ጎዳና የተወናበዱ ወገኖቻችንን እንማልዳቸው፡- በዘመናችን ካሉ መሰረታዊ የቤተክርስቲያናችን ችግሮች አንዱ የመበሻሸቅ ፖለቲካ የወለደው ነው፡፡ የመበሻሸቅ ፖለቲካ በመርህ አይመራም፡፡ መሪ አስተሳሰቡ “ይሄን ነገር እነ እገሌ የሚወዱት ከሆነ እኛ ልንጠላው ይገባል” ከሚል ያልበሰለ እይታ የሚወለድ ነው፡፡ በታሪክ ትንተና እና በፖለቲካዊ ምልከታ ከአንተ/ከአንቺ ከሚለዩ ሰዎች ለመራቅ ስትል ሃይማኖታዊ አስተምህሮህን ዘመን በወለደው የብልጣብልጥ ተረት ወይም ከንፁህ ህሊናህ በሚላተም የኢ-አማኒነት አመክንዮ የበረዝክ ወንድማችን፣ የበረዝሽ እህታችን ለአፍታ ወደ አዕምሮህ ተመለስና/ተመለሽና “በእውነት መንገዴ መንፈሳዊ ነውን?” በማለት ራስህን ጠይቅ/ራስሽን ጠይቂ፡፡ ዛሬ በብሽሽቅ ስሜት ተውጠን የምንጥለው፣ ለሌላ የምንሰጠው ታሪክና መንፈሳዊ ስብእና ከዘመናት በኋላ ብኩርናውን እንደሸጠ እንደ ኤሳው በእንባ ብንፈልገው መልሰን አናገኘውም፡፡

በአካል የማናውቃችሁ በቤተክርስቲያን አካልነት ግን የምናውቃችሁ ፍቁራን፡- ሳይታወቃቸው የሰይጣንን የቤት ስራ የሚፈጽሙ ሰዎች የቤተክርስቲያንን አውደምህረትም ሆነ ሌሎች መገለጫዎች አንተ/አንቺ በማትስማሙበት የታሪክና የፖለቲካ አረዳድ ሲያበላሹት በማየታችሁ ሰዎቹን የተቃወማችሁ መስሏችሁ በመናፍቃንና በመሰሪ ተሃድሶአውያን የለብ ለብ ስብከት እጃችሁን ስትሰጡ ማየት ያንገበግባል፡፡ በእውነት ያሳሰባችሁ ታሪካችሁና እምነታችሁ ቢሆን ኖሮ በራሳችሁ መረዳት ታሪካችሁን እየተረካችሁ ከቅዱሳን አባቶቻችሁና እናቶቻችሁ ያለመቀላቀል የተቀበላችሁትን ነቅ የሌለበት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ  ታሪካችሁንም እምነታችሁንም በሚያጠፋ አረም ባልለወጣችሁት ነበር፡፡ ሰይጣን ቅን በሚመስል ተቆርቋሪነት ገብቶ፣ የሌሎችን ስህተት ተጠቅሞ እናንተን ከበረቱ ሲያስወጣችሁ አይታያችሁም?!

በአንፃሩ ደግሞ የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት ጭምር በመጠቀም የራሳቸውን የታሪክና የባህል አረዳድ በሌሎች ላይ እንደ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሊጭኑ የሚፈልጉ ሰዎችን መምከር፣ ማስረዳትና መገሰፅ ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ ብዙዎቹ የድርጊታቸውን ምንነትም ሆነ ውጤት በአግባቡ የሚረዱ ሳይሆኑ ዓለም ሁሉ በእነርሱ መነጽር የሚያስብ የሚመስላቸው የዋሀን ናቸው፡፡ በክርስቶስ አካሎቻችን የሆናችሁ ፍቁራን ቤተክርስቲያንን የማንም የባህልም ሆነ የቋንቋ የበላይነት መገለጫ መድረክ አድርጋችሁ አትመልከቷት፡፡ በተለይም ደግሞ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር እየሸቀጣችሁ የእኔ የምትሉትን የባህልም ሆነ የፖለቲካ ቡድን ለመጥቀም የምታደርጉት ከንቱ ድካም እግዚአብሔርን የሚያሳዝን፣ ቤተክርስቲያንን የሚያደማ መሆኑን እወቁ፡፡ በዚህ አካሄድ የምታልሙትን ማግኘት አትችሉም፡፡ በአንተ/በአንቺ ምክንያትነት ሰይጣን ከበረቱ የሚያስወጣቸውን ደካማ ምዕመናን ነፍስ ዋጋ ጌታ ከእጅህ/ከእጅሽ እንደሚቀበል አትርሱ፡፡ የታወቁ መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ጸጋዎቻችንን የእኔ ለምትለው/ለምትይው ምድራዊ ቡድን መገበሪያ አድርጋችሁ የምታቀርቡ በዚህም በክርስቶስ አካሎቻችሁ የሆኑትን በፖለቲካዊ አቋም ከአንተ/ከአንች የተለዩትን ወገኖች የምትገፋ/የምትገፊ ወድማችን/እህታችን አስተውሎታችሁን ማን ወሰደባችሁ?!

እባካችሁ ወደ ልባችሁ ተመለሱ! እባካችሁ ወደ ልባችን እንመለስ! በቤተክርስቲያን እየተሰበሰብን ለመንፈሳዊ አንድነታችን እንትጋ እንጂ ፖለቲካዊ መከፋፈልን ወደ ቤተክርስቲያን አስርገን አናስገባ፡፡ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ባለማወቅ፣ የሃይማኖትና የፖለቲካን መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ መስመር ባለመረዳት ፖለቲካዊና ባህላዊ አስተሳሰባቸውን በሌሎች ላይ ሊጭኑ የሚሞክሩትን እንዲሁም በሰበብ አስባቡ ቤተክርስቲያንን ለፖለቲካዊ ዓላማ የሚያዳክሙትን ሁሉ በያለንበት በአቅማችን የቀናውን መንገድ ልናመለክታቸው ይገባል፡፡ ለዚህም የቤተክርስቲያን አምላክ፣ በሚፈለገው መጠን በማይረዱት ምድራዊ ቋንቋ ለዘመናት የቤተክርስቲያንን ትምህርት በመንፈሳዊ እዝነ ልቦና እየተረዱና እየጠበቁ ያኖሩልን የደጋግ እናቶቻችን እና አባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡†

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s