ደብረ ታቦር፡ የነገረ ተዋሕዶ ማሳያ

Debretabor2.1

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ስለሆነች ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መሳካት የሚያገለግሏት ከፍተኛ ክብር ያላቸውና በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓት የምታከብራቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ሥጋዌና የማዳን ሥራ ጋር የተገናኙ ዘጠኝ ዓበይት በዓላት እና ዘጠኝ ንኡሳን በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል (ማቴ. ምዕ.17፡1 ማር.9፡1፤ ሉቃ.9፡28)፡፡

በዚህ በዓል በተዋሕዶ የከበረ፣ አምላክ ሲሆን በፈቃዱ የሰውን ባሕርይ ያለመለወጥ የተዋሐደ ጌታ መለኮታዊ ክብሩ፣ የተዋሕዶው ፍጹምነት ይነገርበታል፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡ በባሕላዊ ገጽታው ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለሆነ በዓሉ ‹‹ቡሄ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለሆነ ‹‹የብርሃን በዓል›› (Transfiguration) ይባላል፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ስለ ደብረ ታቦር በዓል መንፈሳዊ መሠረትና ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዳስሳለን፡፡

በስድስተኛው ቀን ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ተራራ ወጣ

‹‹ደብረ ታቦር›› የሁለት ቃላት ጥምር ሲሆን ‹‹ደብር›› ማለት ተራራ፣ ‹‹ታቦር›› ደግሞ በናዝሬት አካባቢ በሰማርያ አውራጃ በገሊላ ወረዳ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም ነው፡፡ የደብረ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ  ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ 572 ሜትር ያህል ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ አስቀድሞ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ ተናግሮ ነበር (መዝ. 88፥12)፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ብርሀነ መለኮቱን በመግለጡ ተራሮችም የፈጣሪያቸውን ተዓምራት በማየታቸው የነቢያት ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሳራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነበር (መሳ. 4፥6)፡፡

የዚህም ታሪክ ምሳሌነቱ ባርቅ የጌታችን ሲሳራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል (1ኛ ሳሙ.10፡3)፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ አባታችን ኖኅም ይህንን ተራራ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ የሐዲስ ኪዳን ወንጌል ጸሐፊያን ግን ‹‹ረጅም ተራራ፣ ቅዱስ ተራራ›› ከማለት በስተቀር ‹‹የታቦር ታራራ›› ብለው ስሙን አልጠቀሱትም፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፣ በትውፊትም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፋፍቶ ጽፏል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ሰው የሆነ ንጉሥ ነው፡፡ ጌትነቱና ንግሥናው በጸጋ እንደከበሩ ቅዱሳንና፣ በኃላፊ ስልጣን እንደተሾሙ ምድራውያን ነገስታት በጊዜ የሚገደብ፣ ሰጭና ከልካይም ያለበት አይደለም፡፡ አምላክነት፣ ጌትነት፣ ንግሥና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፤ ከማንም አልተቀበለውም፣ ማንም አይወስድበትም፡፡ የድኅነታችን መሠረቱም የጌታችን ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው መሆን ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር/ እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፣ በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ” (መዝ. 72፡12) ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ ማዕከለ ምድር በተባለች በቀራንዮ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ቤዛነት ዓለሙን ሁሉ አድኗልና፡፡ ይሁንና የጌታችን ነገረ ተዋሕዶ ለብዙዎች ለማመንና ለመረዳት ይከብዳቸዋል፡፡

ዛሬም ድረስ በዚህ የተነሳ ብዙዎች ስለአንድ ክርስቶስ እየተነጋገሩ የተለያየና የነገረ ድህነትን ምስጢር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያዛቡ እምነቶች አሏቸው፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ወቅትም የተለያዩ የአይሁድ ማኅበራት ስለ ጌታችን ማንነት ባለመረዳት አንዳንዱ ነቢይ ነው ሲል ሌላው ከዮሴፍ ጋር በተናቀች ከተማ በናዝሬት ማደጉን አይቶ ይንቀው ነበር፡፡ ፍጥረታቱን ለሞት ለክህደት አሳልፎ የማይሰጥ ጌታ የአይሁድ ክህደት ደቀመዛሙርቱንም እንዳያውካቸው ነገረ ተዋሕዶን (አምላክ ሲሆን ሰው የመሆኑን ድንቅ ምስጢር) በትምህርትም በተዓምራትም ይገልጥላቸው ነበር፡፡ በትምህርት ነገረ ተዋሕዶን ካስረዳባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ደቀመዛሙርቱን በጥያቄ ያስተማረበት ነው፡፡ ይህም ጥያቄ የጠየቀበት ቦታ ቂሣርያ ይባል ነበር፡፡ አባቶቻችን ይህን የጌታችንን ትምህርት ተስእሎተ ቂሣርያ (የቂሣርያ ጥያቄ) በማለት ይጠሩታል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ደቀመዛሙርቱን ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!›› ብሎ መሰከረ (ማቴ 16፡16)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የመሰከረውን ምስክርነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ይሰሙ ዘንድ፣ ከነቢያት (ሙሴና ኤልያስ) አንደበት ይረዱ ዘንድ፣ በተዓምራት የደነደነ ልባቸውን ይከፍት ዘንድ በተስእሎተ ቂሣርያ ቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት መሠረት የሆነውን የጌታችንን ነገረ ተዋህዶ ከመሰከረ ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራ አወጣቸው (ማቴ 17፡1-10)፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ6ኛው ቀን (ነሐሴ 13 ቀን) ነው፡፡ ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ከታች ያለውን ሁሉ ሲያሳይ ደስ ይላል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፡፡ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅንና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡

አንድም ተራራ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ተራራን በብዙ ጻዕር እንዲወጡት መንግስተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ (ሐዋ. 14፡22) አንድም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታልና፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ (ክርስቶስ) በሰማይ ነውና፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር (ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› እንዲል (ፊልጵ. 3፥20)፡፡ በዚህም መነሻነት ጌታችን በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል ለደቀመዛሙርቱ ነገረ ተዋሕዶውን አስረዳቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ዛሬ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደምታምነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ ሲሆን ሰው መሆኑን አመኑ፣ መሰከሩ፡፡

በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ

ሦስቱ ሐዋርያት በተራራው ሳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲጸልይ ሳለ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ ይህም የመለኮቱን ብርሃን ሲገልጥ ነው እንጂ ውላጤ/መለወጥ አይደለም፡፡ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዳለ /ሚል 3፥6/ በእርሱ ዘንድ መገለጥ እንጂ መለወጥ የለም፡፡ ሦስት ክንድ ከስንዝር አካል ምሉዕ ብርሃን ሆኗል፡፡ ይህም አበቦች ከአዕጹቃቸው እንዲፈነዱ ያለ መገለጥ ነው፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደ በረድ ጸዓዳ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ነገረ ተዋሕዶን እንዲረዱ የተደረገ መገለጥ ነው፡፡ ሰውነቱን አልካዱም፣ አምላክነቱን ግን ተጠራጥረው ነበርና አምላክነቱን ከሰውነቱ አዋሕዶ ነገረ ተዋሕዶን ገለጠላቸው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ32 ዓመት ከ6 ወር ከ13 ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጌታችን ብርሃንነት “በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ” “ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” “በሞት ጥላ መካከል ላሉ ብርሃን ወጣላቸው” እንዳለ ፀሐየ ጽድቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች የተስፋ ብርሃን፣ የእውቀት ብርሃን፣ የዓይን ብርሃን፣ የሕይወት ብርሃን የሆነውን ብርሃኑን ገለጠ፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትንም ብርሃን ያለበሰ እርሱ ነው፡፡ ለመላዕክት፣ ለጻድቃን ለቅዱሳን ሁሉ የጽድቅ ብርሃንን ያደለ የማይጠፋ ብርሃን እርሱ ነው፡፡ ለእርሱ ብርሃንነት ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከተራራው በወረደ ጊዜ የእስራኤልን ዐይን የበዘበዘ ገጸ ብርሃን ምሳሌው ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ የብርሃን መገኛ ለቅዱሳን ብርሃንን የሚሰጥ የብርሃናት አምላክ፣ ሙሴን ብሩህ ያደረገ፣ ለአባ አትናቴዎስም ብርሂት እድን (እጅ) የሰጠ ነው እንጂ፡፡ በቅዱሱ ተራራ ማደሪያውን ያደረገ አምላክ በዚህ ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ «በፊታቸው ተለወጠ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ» ሲል የክርስቶስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራው የብርሃኑም ኃይል ያንፀባረቀው የብሉይ ኪዳን መሪ እንደነበረው እንደ ሙሴ ፊት ብርሃን ያለ አይደለም፡፡ «ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ የፊቱ ቆዳ አንፀባረቀ፣ አሮንና እስራኤልም ይህንን ስላዩ ወደ እሱ ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ ተሸፈንም እያሉ ጮኹ «ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለእነሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ» ይላል (ዘፀ .34፡29-30)፡፡ የሙሴ የጸጋ ነው፤ የክርስቶስ ግን የባህርይ ነው፡፡እንዲሁም «ብሩህ ደመና ጋረዳቸው» ያለው በሲና እንደታየው ያለ አይደለም፡፡ በታቦር የታየው ብሩህ ደመና ነበር፡፡ በደብረ ሲና የተገለጠ የፍጡሩ የሙሴ ክብር ነበር፤ በደብረ ታቦር የተገለጠው ግን የሕያው ባሕርይ የክርስቶስ ክብር ነው፡፡

ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደታዩአቸው ይነግረናል እንጅ የተነጋገሩትን ዝርዝር አላስቀመጠልንም (ማቴ. 17፡3)። ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በትውፊት የከበሩ ናቸውና ከቅዱሳን ሐዋርያት በቃል የተማሩትን የሙሴና የኤልያስ ምስክርነት አቆይተውልናል፡፡ ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ቀጥሎም በእሳት ሠረገላ ያረገውንና በብሔረ ሕያዋን የሚኖረውን ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት እርሱ የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ “እኔ ባህር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብሎ ስለጌታችን አምላክነት ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ነቢዩ ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለኝ ነኝ። እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” በማለት የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክሯል፡፡ ሐዋርያቱ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› ብለውት ነበርና (ማቴ.16፡14)፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ‹‹በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር›› ያለውም የነበራቸውን ክብር ታላቅነት ያስረዳል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሕግ/ከኦሪት ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከታላላቅ ነቢያት የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ለሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ነበርና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና በሚነጋገርበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ‹‹… ጌትነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ አለና በብርሃን ሠረገላ ሆኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ሆኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር (ዘፀ.33፡13-23)፡፡ ይህም በፊት የሚሔድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም አምላክ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” የተባለው ትንቢትም በዚህች ዕለት ተፈጸመ፡፡

ስለምን ሁለቱን ከነቢያት ሦስቱን ከሐዋርያት አመጣ ቢሉ ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኑን ሲያስረዳ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ነቢያት ያስተማሩት ብሉይ ኪዳንና ሐዋርያት የሰበኩት ሐዲስ ኪዳን ይነገራሉና፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መሆናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ በሕግ በሥርዓት ያገቡ ሰዎችም፣ በንጽሕና በድንግልና በምንኩስና የአምላካቸውን ፈቃድ የሚፈጽሙ  መናንያን፣ ባህታውያን፣ መነኮሳት አንድ ሆነው መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ከሕጋውያን ሙሴን ከደናግል ደግሞ ኤልያስን አመጣ፡፡ ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር ተራራ አብረውት እንዲገኙ ያደረገው ደቀ መዛሙርቱ ሙሴ ነው ወይም ኤልያስ ነው በማለት ሲጠራጠሩ እንዳይኖሩ መለኮታዊ ትምህርት ለመስጠትም ነው፡፡

ጴጥሮስም ‘በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው’ አለው

በዚያን ሰዓት ሦስቱ ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ (ሉቃ 9፡32)። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ምስጢረ መለኮት፣ ማለትም የጌታ በብርሃነ መለኮት ማሸብረቅና ልብሶችም እንደበረዶ ነጭ መሆን እንደዚሁም የእነዚህ የቅዱሳን የነቢያት መምጣት እና ከጌታችን ጋር መነጋገራቸውን ከሰማ በኋላ “እግዚኦ እግዚእ ሠናይ ለነ ኃልዎ ዝየ/ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው/“አለ፡፡ ቅዱሳን ነቢያቱ የወትሮ ሥራቸውን እየሠሩ ማለትም ሙሴ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እያስገደለ፤ ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናመ እያቆመ፤ አንተም አምላካዊ የማዳን ሥራን እየሠራህ ገቢረ ተአምራትህን እያሳየህ፤ በዚህ በተቀደሰ ቦታ “በደብረ ታቦር” መኖር ለእኛ እጅግ መልካም ነው”፡፡ “ወእመሰ ትፈቅድ ንግበር በዝ ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ” አምላካዊ ፈቃድህስ ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ አንድ ለአንተ፤ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ ብሎ ጠየቀ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት የእርሱንና የሁለቱን ሐዋርያት ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፤ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ተራራው የወሰዳቸው ብርሃነ መለኮቱን ሊገልጥላቸው እንጂ በዚያ ለመኖር አልነበረምና ቅዱስ ሉቃስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር የተናገረውን ‹‹የሚለውንም አያውቅም ነበር›› በማለት ገልጦታል፡፡

ከደመናም ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት’ የሚል ቃል መጣ

ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ/ልመለክበት የወደድኩት ለምስጢረ ተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት/” የሚል ቃል መጣ፡፡ በዚህም የሥላሴ ምስጢር ለዓለም ለሦስተኛ ጊዜ ተገለጸ፡፡ እግዚአብሔር አብ ደመናን ተመስሎ “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” እያለ፣ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰውም ሆኖ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ደመና ተመስሎ ተገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ደብረ ታቦር ጌታችን ብርሀነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግስቱን የገለጠበት እንዲሁም የስላሴ አንድነትን ሦስትነት የተገለጠበት ብላ ቤተክርስቲያናችን ታስተምራለች፡፡

የደብረ ታቦር በዓል ከዘጠኙ የጌታችን አበይት በዓላተ አንዱ ስለሆነ በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማኅሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው «ሰበሕኩከ በደብር በቅድመ ሙሴ ወኤልያስ ነቢያት ምእመናኒከ» በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርሁልህ›› የሚለው መዝሙር በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ነጎድጓዳማ ድምጽ መሰማቱን የብርሃን ጎርፍም መውረዱን በማሰብ በሀገራችን በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የነጎድጓዱ ምሳሌ አድርገው ጅራፍ በማጮኽ፣ የብርሃን ጎርፍ ምሳሌ አድርገው ችቦ በማብራት ያከብሩታል፡፡

አባቶቻችን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ በዓላትን በትምህርት ከማስተላለፍ ባሻገር ምሳሌነታቸውን በባሕላችን ውስጥ እንድንይዘው በማድረግ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲገለጽ ያደርጋሉ፡፡ ይህን የማይረዱ ሰዎች ግን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በባሕላዊ ጨዋታ በመተካት በበዓለ ደብረታቦር፣ በቤተ ክርስቲያን መሠረታዊውን ነገረ ተዋሕዶ ከማስረዳት ይልቅ ስለባሕል በመጨነቅ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በዓለ ደብረታቦር በዋናነት የነገረ ተዋሕዶ ማሳያ እንጅ የባሕል ትርኢት ማሳያ ቀን አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ባሕል የሚያስፈልገው ለሃይማኖተኛ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ከምንም በላይ መሠረተ እምነቱን ጠንቅቆ ሊያውቅ፣ ከመናፍቃንም ቅሰጣ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ እኛም በዓሉን ስናከብር በምስጋና በመዘመር እንጂ ሌሎች ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸውን ባሕላዊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር መሆን የለበትም፡፡

በአጠቃላይ በወንጌሉ ያመንንና በስሙ የተጠመቅን ክርስቲያኖች የደብረ ታቦርን በዓል ስናከብር ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው” እንዳለው በደብረ ታቦር በምትመሰለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት አክብረን፣ በምግባር በትሩፋት አጊጠን፣ ሕገ ተፋቅሮን አስቀድመን መኖር በሥጋዊ ዓይን መከራ ወይም ድካም መስሎ ቢታየንም ፍጻሜው ግን ዘለአለማዊ ሕይወት ስለሆነ በቤቱ ጸንተን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መኖር መንፈሳዊ ግዴታችን መሆኑ ማወቅ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት ነገረ ተዋሕዶውን በታቦር ተራራ የገለጠ፣ ነቢያት ሐዋርያት የመሰከሩለት የጥበቡ ጸጋ ብዛት የማይታወቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ተዋሕዶውን አውቀን፣ ተረድተን ለሌሎች የምናስረዳበትን ጥበብ መንፈሳዊ ይግለጥልን፡፡ አሜን፡፡

1 thought on “ደብረ ታቦር፡ የነገረ ተዋሕዶ ማሳያ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s