ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና: አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን!

St Mary new image

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለቅድስት ድንግል ማርያም የምታምነውና የምታስተምረው ጥልቅ ምስጢር ያለው መንፈሳዊ ትምህርትና የምታመሰግነው ምስጋና የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች ላይ ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን ታላቅ ሥፍራ የምትሰጣቸው ሊቃውንት በተለይም ቅዱስ ኤፍሬም፣ አባ ሕርያቆስ፣ ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የእርስዋን ምስጋና በመጻፍና በዜማ አዘጋጅተው ለትውልድ በማስተላለፍ ታላቅ ድርሻን አበርክተዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ሊቃውንት የድንግል ማርያምን ምስጋና ሲደርሱና ሲያደርሱ ብሔረ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን፣ ቅዱስ ወንጌልን፣ የሐዋርያትን አስተምህሮና ትውፊት ጠንቅቀው አውቀው፣ ለድንግል ማርያምም ምስጋና ማቅረብ የሚያስገኘውን ታላቅ ሰማያዊ ክብር ተረድተውት ነው፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር እንደሰማይ ክዋክብትና እንደባሕር አሸዋ ለበዛውና ብዙ ክብርን ስለሚያሰገኘው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና (ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ሰዓታት፣ ማኅሌት ወዘተ) መሠረት የሆኑ አንኳር ነጥቦችን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች እንዳስሳለን፡፡

ንጽሕና: ንጽሕተ ንጹሐን

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የቀደሙት አባቶችን አሠረ ፍኖት ተከትላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ንጽሕተ ንጽሐን ትላታለች፡፡ ይህም “ከንጽሐን ይልቅ ንጽሕት የሆነች” ማለት ነው፡፡ በትምህርቷም ቅድስት ድንግል ማርያም ቀድሞ በሰው ልጅ ይተላለፍ የነበረው መርገም ያላገኛት፣ ሰው በምድር ላይ ሲኖር በበሀልዮ (በማሰብ)፣ በነቢብ (በመናገር)፣ በገቢር (በመተግበር) የሚሠራው ኃጢአት ከቶ የሌለባት ንጽሕት ናት ብላ ታስትምራለች፡፡ ከቀደመው መርገምም ነጽታ ሳይሆን ተጠብቃ ከሀናና ከኢያቄም የተወለደች፣ በቤተመቅደስ ያደገች፣ በመልአኩ ብሥራትም ጸንሳ የወለደች ንጽሕት ናት፡፡ ከእግዚአብሔር የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርዔል ወደ ድንግል ማርያም ገብቶ ‘አንቺ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ 1፡28)” ያላት ንጽሕት ስለሆነች ነው፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ 1፡42)” ብላ በመንፈስ ቅዱስ ያመሰገነቻት ድንግል ማርያም ንጽሕት ስለሆነች ነው፡፡ ወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስም የተዋሐደው ንጽሕት ከሆነችው ነፍሷና ንጹሕ ከሆነው ሥጋዋ ነው፡፡ የእርሷ ንጽሕና አስቀድሞ ከመመረጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር አምላክ ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር (ኢሳ 1፡9)” ብሎ የተናገረው የድኅነት ምክንያት የሆነችው ድንግል ማርያም በንጽሕና ተጠብቃ የቆየች ንጽሕት ዘር መሆኗን ያረጋግጥልናል፡፡

ድንግልና: ዘላለማዊ ድንግልና

ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ያስቀመጡት እውነት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፡፡ (ኢሳ 7፡14)” ብሎ የተናገረውና ቅዱስ ሉቃስም “በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርዔል …ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፡፡ ሉቃ 1፡26″ ሲል የትንቢቱን ፍጻሜ ያረጋገጠው፣ በተጨማሪም ድንግል ማርያም ራሷ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? (ሉቃ 1፡34)” ስትል የጠየቀችው የድንግልናዋ ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው ቅዱሳን አበው “በሁለት ወገን ድንግል ከምትሆን (ድንግል በክልዔ) ተወለደና አዳነን” ብለው ያስተማሩን፡፡ በሁለት ወገን ድንግል ያሏትም በሥጋም ድንግል፣ በነፍስም ድንግል በመሆኗ ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድንግልናዋ ስድስት ጊዜ መሆኑን ሲናገር ከመፅነሷ በፊት፣ በፀነሰች ጊዜ፣ ከፀነሰች በኋላ፣ ከመውለዷ በፊት፣ በምትወልድበት ጊዜ፣ ከወለደችም በኋላ ድንግል ናት ብሏል፡፡ በዚህም የእርሷ ድንግልና ዘላለማዊ ስለሆነ ዛሬም ቅድስት ቤተክርስቲያን “በሀሳብሽ ድንግል ነሽ፤ በሥጋሽም ድንግል ነሽ” እያለች ታከብራታለች፣ ታመስግናታለች፡፡

እናትነት: ወላዲተ አምላክ 

ንጽሕትና ድንግል የሆነችው እናታችን ማርያም በእውነት አምላክን የወለደች ስለሆነች “ወላዲተ አምላክ/የአምላክ እናት/” እንላታለን፡፡ ሌሎች ሴቶች እናት ቢባሉ ቅዱሳን ሰዎችን ወልደው ነው፡፡ የእርሷ እናትነት ግን አምላክን በመውለድ ነው፡፡ ከእርሷ በፊት ከእርሷም በኋላ አምላክን የወለደ አልነበረም፤ አይኖርምም፡፡ ስለዚህም ከሰዎች ልጆች አምላክን የወለደችና የአምላክ እናት የምትባል እርሷ ብቻ ናት፡፡ ይህንንም አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። (ኢሳ 9፡6)” ሲል የተነበየው፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርዔል “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። (ሉቃ 1፡32)” ብሎ የመሰከረው፤ ቅዱስ ኤልሳቤጥም “የጌታዬ እናት…” ብላ የተናገረችው (ሉቃ 1፡43)፤ መልአኩም ለእረኞች “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና (ሉቃ 2፡11)” ሲል ያበሠራቸው ከእርሷ የተወለደው አምላካችን ስለሆነ ነው፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን ያደለንም ከእርሷ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ የከበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመጻሕፍት “የኢየሱስ እናት” የሚል እንጂ “ወላዲተ አምላክ” የሚል የለም የሚሉ የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት የሚጠራጠሩ ናቸው፡፡ ልጇን አምላክ ብለው ካመኑ እርሷን የአምላክ እናት ማለት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለምና፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ብቻ ሳትሆን የሁላችንም እናት ናት፡፡ ይህም ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ለደቀመዝሙሩ ለዮሐንስ “እነኋት እናትህ”፣ ለእመቤታችንም “እነሆ ልጅሽ” ብሎ በዮሐንስ በኩል በሰጠው አደራ ይታወቃል (ዮሐ 19፡36)፡፡ ስለዚህም የእርሷ እናትነት ለአምላክም (በተዋሕዶ) ለሰው ልጆችም (በጸጋ) ነው፡፡

ምልዕተ ጸጋ: ጸጋን የተመላች

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ድንግል ማርያምን “ምልዕተ ጸጋ/ጸጋን የተመላሽ” በማለት ታመሰግናታለች፡፡ በዚህም ሁሉም/ሙሉ ጸጋ የተሰጣት መሆኗን ትመሰክራለች፡፡ ይህንንም የምትለው ከእግዚአብሔር የተላከ ቅዱስ ገብርዔል የተናገረውን አብነት በማድረግ ነው፡፡ መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ “ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ (ሉቃ 1፡28)” ያለው የጸጋ ሁሉ ባለቤት ስለሆነች ነው፡፡ ሊቃውንትም አንዳች የጎደለባት ጸጋ የለም የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም ላይ “ጸጋን አገኘሽ። መንፈስ ቅዱስ አደረብሽ። የልዑል ኃይልም ጋረደሽ ጸለለብሽ። ማርያም ሆይ በእውነት ቅዱስን ወለድሽ። ዓለምን ሁሉ የሚያድን መጥቶ አዳነን፡፡” ብሎ ያመሰገናት መልአኩ “ጸጋን የተመላሽ” ብሎ የተናገረውን አብነት በማድረግ ነው፡፡ ቅዱሳን ጸጋቸው የተወሰነ ነው፡፡ አንዳንዶች ትንቢት የመናገር፣ ሌሎች የማስተማር፣ ሌሎች ድውይ የመፈወስ ጸጋ አላቸው፡፡ የጸጋ ሁሉ መገኛ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው ድንግል ማርያም ግን ምልዕተ ጸጋ ናት፡፡ ምስጋናዋም የበዛው ጸጋዋ ምሉዕ ስለሆነ ነው፡፡

ብፅዕና: ትውልድ ሁሉ የሚያመሰግናት 

ብፁዕ ማለት የተባረከ፣ የበቃ፣ የተመሰገነ ማለት ነው፡፡ ድንግል ማርያም የተባረከች/ቡርክት መሆኗን ከሰማያውያን ወገን የሆነውና ከእግዚአብሔር የተላከው ቅዱስ ገብርዔል “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ 1፡28)” በማለት አመስግኗታል። ከሰዎች ወገን የሆነችውና መንፈስ ቅዱስ የመላባት ቅድስት ኤልሳቤጥም “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው (ሉቃ 1፡42)” በማለት አመስግናታለች፡፡ ብፅዕት ስለመሆኗም ምስክርነት ስትሰጥ “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት (ሉቃ 1፡45)” በማለት አረጋግጣልናለች፡፡ ድንግል ማርያምም ወልድ በተለየ አካሉ በማኅፀኗ ካደረ በኋላ በጸሎቷ “እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል (ሉቃ 1፡48)” ስትል የተናገረችው ምስጋናዋ በቅዱስ ገብርዔልና በቅድስት ኤልሳቤጥ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ያለፈው ትውልድ፣ አሁን ያለው ትውልድ፣ የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ እንደሚያመሰግናት ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ‹‹ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናናንትሽን እናምሰግናለን፤ እናደንቃለን፡፡ እንደ መልአኩ ገብርኤልም ማስጋና እናቀርብልሻለን፡፡ የባህርያችን መዳን በማህፀንሽ ፍሬ ተገኝቷልና። ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔርም አቀረበን” በማለት ያመሰገናት ቅዱስ ገብርዔልን አብነት በማድረግ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም “በእንተ ብዕዕት…” እያለ ያመሰገነው በዚሁ አብነት ነው፡፡

ልዕልና: ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች

ድንግል ማርያም ምልዕተ ክብር ናት፡፡ በዚህም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ/ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነች” ክብርት ናት ይላሉ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በረቡዕ ወዳሴ ማርያም ላይ የክብሯን ታላቅነት ሲናገር “ከቅዱሳን ክብር ይልቅ የማርያም ክብር ይበልጣል፡፡ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና፡፡ መላእክት የሚፈሩትን ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማሕፀኗ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች ከሱራፌልም ትበልጣለች። ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና፡፡ የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት።” በማለት የክብሯን ታላቅነት ከነምክንያቱ አስቀምጦልናል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም “በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሸልና” ሲል የተናገረው የሰማያዊው ንጉሥ ባለሟልና ክብሯ ታላቅ መሆኑን ሲገልጥ ነው፡፡ ልበ አምላክ የተባለ ክቡር ዳዊትም “የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግስቲቱ በቀኝህ ትቆማለች (መዝ 44፡9)” በማለት ትንቢትን የተናገረው የድንግል ማርያም ክብር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሲመሰክር ነው፡፡ በክብር ዐርጋ ከልጇ ከወዳጇ ጋር መሆኗንም በዚህ እናውቃለን፡፡ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስም በራዕዩ “ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች (ራዕይ 12፡1)” ሲል የተናገረው እንዲሁ የክብሯን ታላቅነት ያሳያል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳን አባቶች ክብሯን ለመግለጽ ብዙ ምሳሌዎችን የተጠቀሙት፡፡ ክብሯን የሚገልጥ ምሳሌም ቢያጡ “በማንና በምን እንመስልሻለን?” ብለው አመስግነዋታል። እኛም እንደ እነርሱ እናመሰግናታለን።

አማላጅነት: የምሕረት አማላጅ

ድንግል ማርያም የምሕረት አማላጅ ናት፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረት እያማለደች የምታሰጥ ርህርህት እናት ናት፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው” እንዳላት ቅድስት ቤተክርስቲያንም “እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ከተወደደው ልጅሽ ይቅርታን ለምኝልን” እያለች ትጸልያለች፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነ ሰው የሚቃወመው የለም፤ የሚሳነውም ነገር የለምና (ሮሜ 8፡31)፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ከእርሱ ጋር ያለ ሰው እንኳን ምሕረትን መለመንና ከዚያም በላይ ማድረግ ይችላልና፡፡ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት የወይን ጠጅ ላለቀባቸው በእርሷ አማላጅነት ልጇ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደለወጠ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጽፎታል (ዮሐ 2፡1)። ቅዱሳን በምድር ሲሠሩ የነበሩት የቅድስና ሥራቸው ይከተላቸዋልና (ራዕ 14፡13) እርሷም በቀኙ የምትቆመው ለሰው ልጆች ምሕረትን ለማሰጠት ነው፡፡ በበደሉ ምክንያት የወደቀው የአዳም ዘር ከእርሷ በተወለደው በኢየሱስ ክርስቶስ እንደዳነ ዛሬም ቃል ኪዳኗ የሰውን ልጅ ያድናል፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ኤፍሬም በዓርብ ውዳሴ ማርያም “ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት። ለሰው ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት። ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ከክርስቶስ ፊት ለምኝልን” ሲል ገልጾታል፡፡ እኛንም ከተወደደ ልጇ አማልዳን በምሕረቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተስርይልን። አሜን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s