ዘማሪ ማስመጣት፡ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የዘማርያን ሚና

ከዚህ ቀደም በተከታታይ ባወጣናቸው የአስተምህሮ ጦማሮች ወንጌልን በየቦታው ተዘዋውሮ የማስተማርን አስፈላጊነትና አገልግሎቱን የሚያጠለሹ ዘመን የወለዳቸው ችግሮችን ዳስሰን እነዚህ ችግሮች በሂደት የሚቀረፉበትን አሠራር ለመዘርጋት ልንከተላቸው የሚገቡ የትግበራ መርሆችን አቅርበናል፡፡ በእነዚህ ሁለት ጦማሮች በዋነኛነት ትኩረት ያደረግነው ሰባክያነ ወንጌል ላይ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግል መንፈሳዊ ካሴቶችን የሚያወጡ እንዲሁም ሌሎች ዘማርያን የሐዋርያዊ ጉዞ አካል መሆናቸው እየተለመደ የመጣ አሠራር ነው፡፡ በዚህም እንደየአቅማቸው ኦርቶዶክሳዊ ይትበሃልና አስተምሮን ጠብቀው መዝሙር በመዘመር፣ ምዕመናንን ወደ ቤተክርስቲያን የሚያቀርቡ በርካታ መዘምራን አሉ፡፡ ይሁንና መዝሙርን በኅብረት ከመዘመር ይልቅ ግለሰባዊ ስብዕና ላይ ያተኮረ “የግል ዘማርያን” ጉዳይ በኅብረት ሥርዓተ አምልኮን የመፈጸም ሐዋርያዊ ውርስ ባላት ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያችን ድንገቴ ልማድ እንጂ በረዥም ጊዜ ልምድ የዳበረ አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ ዘማርያኑ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ ያላቸው ሚና በሚገባ የታሰበበት አይመስልም፡፡

በሐዋርያዊ ጉዞዎች ላይ መዘምራን የእግዚአብሔርን ቃል በዜማና በግጥም በማቅረብ አገልግሎታቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ስለሆነም የመዘምራኑ አገልግሎት የትምህርተ ወንጌል አካል እንጅ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ አሁን በተለመደው አሠራር ግን ከሰባኪ ጋር አብረው የሚጓዙ ዘማሪያን የተወሰኑ መዝሙሮችን በቤተክርስቲያን መድረክ ጉባዔውን ለማድመቅ (ሕዝብን ለማነቃቃት) ከመዘመርና የመዝሙር ቪ/ሲዲ ከመሸጥ ያለፈ ድርሻ ሲያበረክቱ አይታይም፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ምዕመናን ‘የዘማርያኑ መምጣት አስፈላጊነቱ ምንድን ነው?‘ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ “ዓላማው ጉባዔውን ማድመቅ ከሆነ እዛው ያሉት የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ይበቃሉ፤ መዝሙራቸውን እንድንሰማ ከሆነ ደግሞ ከቪ/ሲዲው በተሻለ ጥራት እንሰማዋለን፤ መዝሙራቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ወይም ሀገር ለማየት ከሆነ ደግሞ ይህ የሐዋርያዊ ጉዞ ዓላማ አይደለም” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “በተለይ ወደ ውጭ ሀገር የሚመጡ መዘምራን የሚሰጡት አገልግሎት ከጉዞ ጋር ተያይዞ ከሚወጣው ወጭ አንጻር ሲታይ ሚዘን ላይደፋ ይችላል” ሲሉ ያክሉበታል፡፡ “ማንኛችንም የተጠራነው እነርሱ ሲመጡ እየዘመርን እነርሱ ሲሄዱ ደግሞ እየቆዘምን እንድንኖር ሳይሆን በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት እንድናገለግል ነው” በማለትም ያጠናክሩታል፡፡ እነዚህን ሀሳቦች መነሻ በማድረግ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በሐዋርያዊ ጉዞ የዘማሪያን ሚና እና ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች ተዳስሰዋል፡፡

በሐዋርያዊ ጉዞ የመዘምራን ሚና

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት መንፈሳዊ ይዘቱንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ መዝሙር አንዱ የመንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፍ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው (ኤፌ ፭:፲፰ ቆላ ፫:፲፮)። ለምሳሌ:- ከሁሉም አገልግሎቱ በላይ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት የሚታወቀው በመዝሙሩ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በእስር ቤት ሆነው ሲዘምሩ በእግዚአብሔር ተአምር ከእስር ቤት ወጥተዋል (ሐዋ ፲፮)። ዛሬም በእኛ ዘመን በእምነትና በእውነት የሚቀርብ መዝሙር ታላቅ መንፈሳዊ ኃይልና ዋጋ አለው። ከዚህ አንጻርም ኦርቶዶክሳዊ ዘማርያን በሚከተሉት የአገልግሎት ዘርፎች ሊተጉ ይገባል።

አብሮ በመዘመር  ማመስገን

በጉባዔ መዝሙር መዘመር ብዙ ዘማርያን ሲያበረክቱ የምናየው አገልግሎት ነው። መዝሙር ማዳመጥ መልካም ቢሆንም ከዘማርያኑ ጋር አብሮ መዘመር/ማመስገን ደግሞ እጅግ የተሻለ አገልግሎት ነው። ስለዚህም መዘምራኑ መድረክ ላይ ቆሞ ከመዘመር (መዝሙር ለምዕመናኑ ከማቅረብ) ባሻገር ምእመናኑን መዝሙርን በማስተማር አብረው እንዲያመሰግኑ ሊያደርጉ ይገባል። ይህም በማስተዋልና በጥበብ እንጂ ምእመናኑን “በጭብጨባና በእልልታ” አድማቂ በማድረግ ስሜትን በመቀስቀስ መሆን የለበትም። ብቻን ሆኖ መድረክ ላይ ቆሞ ከመዘመር ይልቅ ከሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን እንደ አንዱ ሆኖ መዘመርን “የግል ዘማርያን” ሊለምዱት ይገባል። በተለይ ከሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ጋር አብረው ከመዘመር ይልቅ ራሳቸውን ሰቅለው “ለብቻችን መድረክ ካልተሰጠን አንዘምርም!” አይነት አንድምታ ያለው ጸባይን የሚያሳዩ ዘማርያን በኅብረት መዘመርን ሊያስቀድሙ ይገባል፡፡ ምዕመኑም ቢሆን የግል እና የኅብረት መዝሙር እየተባለ ረጅም ጊዜ እየተወሰደበት የሚማርበት፣ የሚጸልይበትና የሚሠራበት ጊዜው ለግለሰቦች ታይታ መዋል የለበትም፡፡

ስለ ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬ ማስተማር

ከመዘመር ጎን ለጎን ስለ ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬ ምንነት ማስተማር የመዘምራኑ ድርሻ ሊሆን ይገባል። ኦርቶዶክሳዊ ዘማሪ የተሰጠውን ግጥምና ዜማ የሚጮህ ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን ታሪካዊ አመጣጥ፣ ምስጢር፣ ምንነትና ስልት በሚገባ ያወቀ መሆን ይጠበቅበታል። ስለዚህም ስለኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለማስተማር ዘማርያን የተሻላ ድርሻ ያበረክታሉ። ስለዜማ ስልት፣ ስለ ግጥም/ቅኔ፣ ስለዜማ መሣርያዎች ታሪክና ምስጢር፣ በዝማሬ ስለሚገኘው ዋጋና በአጠቃላይም ስለ ዝማሬ አገልግሎት በቃልና በተግባር ማስተማር ይጠበቅባቸዋል። ለሚዘምር ሰው ስለ መዝሙር ማስተማር ታላቅ ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው።

ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን ማስተማር

ተተኪውን ትውልድ ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን ማስተማር የዘማርያን ድርሻ ነው። በተለይ ለልጆችና ለወጣቶች ኦርቶዶክሳዊ የዝማሬ ሥርዓትን፣ የዜማ ስልቶችን፣ የዜማ መሣርያ መጫወትን ማስተማር ከመዘምራን ይጠበቃል። ዛሬ ላይ ውጥንቅጡ ለወጣው የዝማሬ ‘አገልግሎት’ ምክንያቱ ተተኪ ዘማርያን በሚገባ እየተማሩ ስላላደጉና ማንም ‘ድምፅ አለኝ የሚል’ እየተነሳ ለመዘመር መሞከሩ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ዘማርያን ቤተክርስቲያንን ማገልገልና ዋጋ ማግኘት ከፈለጉ ለተተኪ ዘማርያንን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ መዝሙር ማስተማር ይኖርባቸዋል።

ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች
የዘማርያን በእውቀት፣ በክህሎትና በሕይወት ደካማ መሆን

ከላይ የተጠቀሱትን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ለመፈፀም ዘማርያን በቤተክርስቲያን ያደጉና የዝማሬን ሥርዓት ጠንቅቀው የተማሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንዲሁም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለሌላው ምሳሌ መሆን የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህም ራሳቸውን በምክረ ካህንና በቅዱሳት መጻሕፍት ሊመሩ ይገባል፡፡ በዘመናችን ይህንን የሚያደርጉ ጥቂት ዘማርያን ቢኖሩም በአብዛኛው ግን በድንገት የገባና በመዝሙር ለመጥቀም ሳይሆን ከመዝሙር ለመጠቀም ያሰበ፣ ለገንዘብ፣ ለታይታና ለዝና የሚሮጥ አገልጋይ በዝቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ያልተረዳ፣ የዜማ ስልትና ምስጢሩን ያላጠና፣ የዜማ መሣርያዎችን የመጫወት ክህሎት የሌለው ዝም ብሎ ግጥምና ዜማ እየተቀበለ የሚጮህ “ተጧሪ ዘማሪ” ቦታውን እየያዘ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በቤተክርስቲያን የሚዘምሩ ዘማርያን የሚማሩበት የትምህርት ሥርዓት፣ የሚያገለግሉበት የአገልግሎት መመሪያና ደንብ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡

መዝሙር ለማነቃቂያና ማድመቂያነት መዋሉ

በዘማርያን አገልግሎት እየተለመደ የመጣ ክፉ ልማድ አለ፡፡ አንዳንድ ሰዎች መዝሙርን ከማስተማሪያና ማመስገኛነት ይልቅ ለመነቃቂያና ለመዝናኛነት ሲያውሉት ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ መዝሙር የተሳካ የሚመስላቸው በጭብጨባውና በእልልታው ድምቀት፣ በተፈጠረው ጩኸት ብዛት የሚመስላቸው በርካታ አገልጋዮች በመፈጠራቸው የምዕመናን አረዳዳድም በዚሁ አንጻር እንዲቃኝ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም አሰራር በሂደት ኦርቶዶክሳዊ የስብከት ዘዴንና በጸጥታ ወደብነት የሚታወቀውን አውደ ምህረት የተደባለቀ፣ ስልት የሌለው ጩኸት ቦታ ሲያደርጉት ታዝበናል፡፡ ለወቅቱና ለጊዜው የሚስማሙ ኦርቶዶክሳዊ ለዛ ያላቸውን መዝሙራት ከመዘመር ይልቅ “ሊያደምቁልን” ይችላሉ የሚሏቸውን መዝሙራት ብቻ በመዘመር፣ የባህል ዘፈኖችንና የእማሆይ ቅንቀናዎችን እንደ መደበኛ ወካይ መዝሙር በመዘመር የጉባኤውን ስኬት በሚያገኙት የግብረ መልስ እልልታና ጫጫታ የሚለኩ ብኩን አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እየበዙ ነው፡፡ ምዕመናንም ክፉውንና ደጉን በሚገባ ለይቶ የሚያስተምራቸው ከማጣት የተነሳ ይህን ክፉ ልማድ ለምደው የክፉ ልማዱ ዋና አስቀጣይ ሆነው ሲታዩ ያሳዝናል፡፡ ይህ ሁኔታ ከዜማ ችግሮችም ጋር ይያያዛል፡፡

ይድመቅልን ብለው የባህል ዘፈኖችን መንፈሳዊ ካባ አልብሰው በቤተክርስቲያን አውደምሕረት የሚያቀርቡ ሰዎች ሳይታወቃቸው ቤተክርስቲያንን ለብሔርተኛ ፖለቲከኞች ንክሻ አሳልፈው ይሰጧታል፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙ እንደ ችሎታው እግዚአብሔርን ማመስገኑ የሚገባ ቢሆንም የሕዝባውያኑን ጨዋታ ራሳቸውን እንደ ባለሙያ (professional) የሚቆጥሩ፣ በሰዎችም ዘንድ እንዲሁ የሚታሰቡ አገልጋዮች ሲያደርጉት ለማስተካከል አስቸጋሪ የሆነ ተጣሞ የተተከለ ዛፍን ይመስላል፡፡ ለእነዚህ ዓይነት አገልጋዮች የዝማሬውም ሆነ የትምህርቱ ዓላማ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ቢከተልም ባይከተልም የግላዊ ዝናና ገንዘብ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በገንዘብና በዝና በሰከሩት መካከል ሆነው እንደ ጻድቁ ኖህ ቅድስት ነፍሳቸውን በአመጸኞች መካከል እያስጨነቁ ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን፣ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ያለመበረዝና ያለመከለስ ለማስተማር የሚደክሙ አሉ፡፡

መዝሙር ለገንዘብ ማስገኛነት መዋሉ

መዝሙር ከማመስገኛነት ይልቅ ገቢ ማስገኛነት ተደርጎ መወሰድ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ዘማርያን የአገልግሎታቸው ፍሬ የሚሆነውን ሰማያዊውን ዋጋቸውን አስቀድመው በምድር ላይ ለመኖር ለሚያስፈልጋቸው ነገር ደግሞ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ እንደ አንድ አገልጋይ ደክመው ገንዘብ ማግኘታቸውን የሚቃወም የለም፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ንጹሕ መስዋዕት እንጂ ለንግድ የሚቀርብ ቁሳቁስ አለመሆኑ ነው፡፡ ንጹሑን መስዋዕት ገንዘብን ለማስገኘት ስንጠቀምበት መስዋዕቱም ንጹሕ አይሆንም፣ ገንዘቡም በረከት አይኖረውም፡፡ በመሰል “አገልግሎቶች” የተሰበሰበው ገንዘብም ቤተክርስቲያንን ከመጥቀም ይልቅ ቤተክርስቲያን ገንዘብን በመውደድ በሚመጡ የዓለማዊነት ፈተናዎች እንድትጎዳ ያደርጋታል፡፡ በዚህ መሰል አሠራር ብዙዎች ከክብር ተዋርደዋል፣ ቤተክርስቲያንንም አሰድበዋል፡፡ከመዝሙር ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችን በሌላ ጦማር ማቅረባችን ይታወሳል፡፡

የመፍትሔ ሀሳቦች

ከመዝሙርና ከዘማርያን ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍና የዝማሬ አገልግሎትን ሰማያዊ ክብር የሚያስገኝ ለማድረግ ከቤተክርስቲያን አስተዳደር፣ ከመዘምራንና ከምእመናን ብዙ ይጠበቃል። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። ከሁሉ በፊት ዘማርያንን ከመተቸት ይልቅ ተተኪ ዘማርያን በቂ መንፈሳዊ ዕውቀት፣ የዝማሬ ክህሎትና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሕይወት እንዲኖራቸው ማገዝ ይገባል፡፡በቅድስት ቤተክርስቲያን ያለው የመዘምራንን አገልግሎትና መንፈሳዊ አበርክቷቸው የሚመራበት መመሪያና ደንብ ማዘጋጀትና ሥራ ላይ ማዋል እንዲሁ አገልግሎቱ እንዲጠናከር ይረዳል፡፡ የኦርቶዶክሳዊያን ዘማርያንን ማኅበራት በማጠናከር የዝማሬ አገልግሎትና ዘማርያኑ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙና ያሬዳዊ ዝማሬም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ስለሚያስችል ዘማርያኑ ሊተጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በተለይም የኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን ምንነት፣ ዓላማና ጥቅም እንዲሁም ሥርዓት ለምዕመናን በሚገባ በማስተማር እውነተኛውን ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራትን መለየትና መዘመር እንዲችሉ ማድረግ የሁሉም አገልጋዮች ድርሻ ነው፡፡ ያልተገቡና ከሥርዓት የወጡ መዝሙራትን በመለየት መዝሙራቱ እንዲስተካከሉ፣ ዘማርያኑ ደግሞ እንዲማሩ በማድረግ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ማስከበር ቸል መባል የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዝም እየተባለ ሲተው እየተለመደ መጥቶ የወደፊቱ ትውልድ ሥርዓት ይመስለዋልና፡፡ በተጨማሪም ለርካሽ ታዋቂነትና ለዓለማዊ ጥቅም የሚሯሯጡ “የግል ዘማርያንን” እና ከእነርሱ ጋር የጥቅም ቁርኝት የሚፈጥሩ የተለያዩ አካላት የቤተክርስቲያንን አውደምህረት ለዚህ ዓላማ እንዳይጠቀሙበት መጠበቅ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የሚኖረው የዘማርያን አገልግሎት የትምህርተ ወንጌል ተጨማሪ ሳይሆን አንዱ አካል ተደርጎ መታሰብ ይኖርበታል፡፡ በሐዋርያዊ ጉዞ የሚሳተፉ ዘማርያን ከሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ከምዕመናን ጋር መዝሙር በመዘመር እግዚአብሔርን ከማመስገን ጎን ለጎን ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬንና ስለ ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬ የሚመለከተውን የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለሕፃናትና ለወጣቶች እንዲሁም ለምዕመናን እንዲያስተምሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ዘማርያኑም የአገልግሎት ድርሻቸው አውደምህረት ላይ ከመዘመር ያለፈ ታላቅ መንፈሳዊ አበርክቶ ያለው መሆኑን ሊያስተውሉት ይገባል፡፡ አገልግሎታቸው ፈር እንዳይስት የሚሰጣቸው አስተያየት ለቤተክርስቲያን አገልግሎትና ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው መጠንከር እንደግብአት የሚጠቅም ሰለሚሆን “የተቺዎች ወይም የምቀኞች ምልከታ” በሚል ንቀው በመተው መንፈሳዊ ዋጋቸውን እንዳያጡ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ መልኩ የወደፊቱን ከማያይ ትችትና ነቀፋ ይልቅ በመማማርና አብሮ በማገልገል ዘማርያን በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ይቻላል። አጥንትን በሚያለመልም እውነተኛው ያሬዳዊ ዝማሬ የቅዱሳንን አምላክ አመስግነን፣ ቅዱሳኑንም አክብረን የዘላለም ሕይወትን እንድንወርስ የዝማሬ ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s