ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፫)

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

ባለፉት ሁለት ተከታታይ የአስተምህሮ ጦማሮች ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንዳለበትና በግጥም መልእክትና ኪነ-ጥባበዊ ይዘት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን የሚመለከቱ ዳሰሳዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል ደግሞ ከዜማ ስልትና ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ይዳሰሳሉ፡፡

ከዜማ ስልት ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መለያ ከሆኑ መንፈሳዊ ጸጋዎች አንዱ በቅዱስ ያሬድ በኩል የተገለጠው የዜማ ሀብት ነው፡፡ የካሴት መዝሙራት የቅዱስ ያሬድን የዜማ ስልት በመከተል ካልተቃኙ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ ለዛቸው ይጠፋል፡፡ ይሁንና በርካታ የካሴት መዝሙር አዘጋጆች የቤተክርስቲያኒቱ ሀብት የሆነውን ያሬዳዊ ዜማ ባለማወቅ ወይም አውቆ ቸል በማለት፣ ለቤተክርስቲያን እንግዳ የሆኑ፣ መንፈሳዊ መሰረት የሌላቸው፣ ለንግድ ሲባል የሚሸቀጡ ዜማዎችን የመጠቀምን ልማድ እየጨመሩ እንደመጡ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በአሳፋሪ መልኩ የዘፈን ዜማ እየገለበጡ በመዝሙር ካባ ሲነግዱበት ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

የያሬዳዊ ዜማ መሠረቱና ምሳሌነቱ እንዴት ነው?

በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ ፸፬:፲፬ ተብሎ የተፃፈው ንባብ ከሚተረጎምባቸው ትንታኔዎች አንዱ የኢትዮጵያ መለያ የሆነው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ልዩ ስጦታና ለኢትዮጵያ የተሰጠ መላእክትን በምስጋናው መስለን የምንተባበርበት ነው:: ቅዱስ ያሬድ በብዙ ድካምና ጥረት ዜማን ተምሯል፣ ፈጥሯል፡፡ የጸጋ ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ያለመታከት ዜማን ለመማር፣ ለመፍጠር ይተጋ ለነበረው ለቅዱስ ያሬድ በቅዱሳን መላእክት በኩል ሰማያዊ ዜማ ገልጦለታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከመላእክት ያገኛቸው በመደብ ሦስት ይኸውም ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ሲሆኑ አንድ መሆናቸው የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ነው:: ትርጉማቸውም ግዕዝ በአብ ሲመሰል “ርቱዕ ሎቱ ነአኩቶ” ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን ማለት ነው። ዕዝል ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም አራራይ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን የሚያራራ ጥዑም ዜማ ማለት ነው። ጥዑም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተጎናጸፍን ለማስረዳት ነው። የቅዱስ ያሬድ የዜማዎቹ ባህርያት የፊደል ቅርጽ የሌላቸውና ምሳሌነት ያላቸው ፰ ዓበይት ምልክቶች (symbols) አሉት። የእነዚህም ምልክቶች ምሳሌያቸውና ምሥጢራቸው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ መንገላታት የሚያስታውሱ ናቸው።

የዘመናችን የአማርኛ መዝሙራት የዜማ ችግሮች ምንድን ናቸው?

በዘመናችን ያሉ በርካታ የካሴት መዝሙራት ካሉባቸው ችግሮች አንዱ ከዜማ ስልት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በምስጢር ይህን የመሰለ ሰማያዊ ስጦታና አስደናቂ የሆነ ያሬዳዊ ዜማ ግምጃ ቤት ሁና ሳለ ለምስጋና መዝሙር የሚሆን ዜማን ለገበያ ይመቻል ከሚል ሃሳብ ከሠርግ ቤት ዘፈን፣ ለንስሐ መዝሙር የሚሆን ዜማን ደግሞ ከለቅሶ ቤት ሙሾ መውሰድ እንደአባቶች አባባል ‘የአባይን ልጅ …’ ያሰኛል፡፡ የቤተክርስቲያን ለዛ የሌለው ‹‹ዜማም›› ቢሆን ገና ለገና ከሌላ ቦታ አልተቀዳም ተብሎ ቸል መባል የለበትም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት የሌለውን ዜማ ከሌላ ቦታ ወስዶ ለ‹‹ዝማሬ›› ማዋል መንፈሳዊነትን ከመጉዳቱም በላይ የዜማውን ባለቤት የባለቤትነት መብትም መጋፋት ነው፡፡ ስለዚህ በምድራዊም በሰማያዊም ሕግ ያስጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል የዜማ ስልታቸው ከመዝሙር ጋር የሚመሳሰሉ ተብለው በአጥኚዎች ከተቀመጡት መካከል ‹‹ሐና ዘመዴ፣ እመኑ በእርሱ፣ አምስቱን ሐዘናት›› የሚሉትንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም መልኩ ‘ማርያም ድንግል ንጽሕት’ በሚል የተዘመረ አንድ ዝማሬ ዜማው ከአንድ ዘፈን ጋር በቀጥታ ሲመሳሰል ሙሽራዬ የወይን አባባዬ የሚለው ደግሞ ዜማው ለመዝሙር ከዋሉት ዘፈኖች መካከል ይገኛል፡፡

የዜማ ችግሮች ያደረሱት ተጽዕኖስ ምንድን ነው?

የዜማ ችግር ያለባቸው ‹‹መዝሙሮች›› ከመብዛታቸው የተነሳ ወጣቱ ምዕመን ከያሬዳዊ መዝሙሮች ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ያሬዳዊ ባልሆኑ ‹‹መዝሙሮች›› እየተሳበ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ይህንን የለመደ ሰውም የዘፈን ቅላጼ ያላቸው ‹‹ዘማሪያን›› እነዚህን መዝሙሮች ሲዘምሩ ማየትና መስማትም ይናፍቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያኒቱን ዜማ የሚጠቀሙ መንፈሳዊ መዝሙሮች ቸል እየተባሉ መዝሙር መሳይ ዘፈኖች (አንዳንዶች ማኅበራዊ መዝሙራት ይሏቸዋል) እየበዙ መጥተዋል፡፡ ይህ አካሄድ በመጀመሪያ ደረጃ የምዕመኑን መንፈሳዊ ሕይወት ይሸረሽራል፡፡ ሁለተኛም የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት ያደበዝዛል፡፡ ሦስተኛም የሀገርን ታሪክንና ቅርስን ያሳጣል፡፡ ስለዚህ ጌታችን  “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሎ እንዳስተማረን (ማቴ ፮:፳፬) ዓለማዊ ዜማንና ያሬዳዊ ዜማን አንድ ላይ መጠቀም ስለማይቻል መንፈሳዊ የሆነውን ያሬዳዊ ዜማን ብቻ ልንጠቀም ይገባናል ።

የአንድ መዝሙር ዜማ ያሬዳዊ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የአንድ መዝሙር ዜማን ኦርቶዶክሳዊ ነው ወይም አይደለም ለማለት የቤተ ክርስቲያንን የዜማ ስልቶች በትክክል ማወቅን ይጠይቃል፡፡ እኛም ዘወትር ከምንዘምራቸው እና ከለመድናቸው መዝሙራት ለየት ያለውን ሁሉ ያሬዳዊ አይደለም ወደሚል ድምዳሜም እንዳንደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁን የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ዜማ ከመሰረቱ እንዳልለቀቀ ሊመሰክሩ የሚችሉት የዜማ ሊቃውንቱ ናቸው፡፡ የዜማ ችግሮችን ከምንጫቸው ለመከላከል የመዝሙር ዜማ ያሬዳዊ ዜማን በጠነቀቁ ሊቃውንት እንዲዘጋጅ ማድረግ ወይም በእነርሱ ታይቶ እንዲስተካከል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የሚዘምረው ዘማሪም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያሬዳዊ ዜማዎችን ያጠና መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለገቢ ምንጭነት ብቻ ሲባል ‹‹ሰላም ለኪ››ን እንኳን በዜማ ያልተማረ ሰው በካሴት መዘመሩ የመዝሙሮቻችንን የዜማ ችግሮች እየሰፉ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ የተሻለው ሀሳብ ሙያን ለባለሙያ መስጠት ቢሆንም ይህ ባይቻል እንኳ የመዝሙርን ዜማ ከዘፈን ጋር የሚያምታቱ፣ መንፈሳዊ መስዋዕት ከእንክርዳድ ሳይለዩ የሚዘምሩ ግን እግዚአብሔርን ፈርተው “የቄሳርን ለቄሳር፣ እግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” መስጠትን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሳርያዎች መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ገቢረ ተዓምርም የተፈጸመባቸው ናቸው (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: “ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል”(፩ሳሙ ፲:፭):: ቅዱስ ዳዊትም ለዝማሬ የሚያገለግሉትን የዜማ መሣርያዎች በዝርዝር አስቀምጧቸዋል:: “እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት። በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት። በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት። ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።” (መዝ ፻፶:፩-፮):: እኛም ቅዱሳኑ የተጠቀሙበትን የዜማ መሳርያ በመጠቀም ከነፍስ ቁስል የምንፈወስበት የምንረጋጋበት እንዲሆን ምስጢርም እንዲገለጥልን በምስጋናው በሃይማኖት እንደመሰልናቸው በዜማ መሳርያውም ልንመስል ይገባል::

በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈቀዱ የዜማ መሣርያዎች የትኞቹ ናቸው? 

በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑት የዜማ መሣርያዎች መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረጉ ሲሆን ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት: እምቢልታ፣ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የዜማ መሣርያዎች አስተማሪነት እንዲኖረው እኛም በመንፈሳዊ ተመስጦ እንድናመሰግን እንዲህ ባለ ምሳሌነት ታስተምረናለች:: ለምሳሌ ከበሮን ስናይ በመጽሐፍ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮ ይዛ እንዳመሰገነች እንማራለን (ዘጸ ፲፭:፳):: አሰራሩ ምስጢዊ ይዘት እንዲኖረው ልዩ የማህሌት መሳርያ ስለሆነ ከበሮን በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት፣ ሽፋኑ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ የሸፈኑበት ግምጃ፣ ድምጹ የወንጌል፣ ጠፍሩ ጌታችን የመገረፉና በሰውነቱ ላይ የወጣውን ስፍር ቁጥር የሌለውን ሰንበር ምሳሌ፣ ማንገቻው የተገረፈበት ጅራፍ ወይም የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ በማለት ያስረዳል::

በተጨማሪ እንደምሳሌነት ከምንወስዳቸው የዜማ መሣርያዎች በመሳርያነቱ ከእስራኤላውያን ቀጥሎ ለኢትዮጵያውያን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ የዜማ መሳርያ በገና ነው:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ከተቀባ በኋላ ከተሰጡት ሰባት ሀብታት ውስጥ አንዱ ሀብተ በገና ነው። ይህም በገና ሀብተ ፈውስ ያለው ቅዱስ ዳዊት ሲደረድረው ርኩሳን አጋንንት ይርቁ እንዲሁም በሽተኞችም ይፈወሱ እንደነበር ያስረዳናል (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: ይህን ገቢረ ተአምር በመስራት የሚታወቀውን የዜማ መሳርያ ቀደምት አበው ከፍጥረት ሰባተኛ ትውልድ ጀምሮ እንደተገለገሉበት የቤተ ክርስቲያንም ሊቃውንት ቃለ በገናን ድምጸ ማኅዘኒ- ‘የሚያሳዝን ድምጽ’ በሚል ይህም በዮባል ልጆች ኃዘን ምክንያት እንደሆነ ያትታሉ:: ይህም የዜማ መሳርያ ልክ እንደ ከበሮ የራሱ ምሳሌያዊ ትምህርቶች አሉት:: የበገናውን ቅርፅ ስንመለከት ላይኛውና ታችኛው የፈቃደ እግዚአብሔርና የማኅፀነ ድንግል (አንድም የሰማይና የምድር) ግራና ቀኙ የሚካኤልና የገብርኤል (አንድም የብሉይና የሐዲስ) አሥሩ አውታር የዓሠርቱ ቃላት (ትእዛዝ) በሚል ይዘረዝረዋል:: ቤተ ክርስቲያን ሌሎችንም የዜማ መሣርያዎች እንዲሁ የክርስቶስን የማዳን ስራውን እንድናስብ በህሊናችን እንድንስል (ገላ ፫:፩) በምድር ያለን ነገር ግን ፍጹም ሰማያዊ በሆነ ስርዓት ታስተምረናለች::

ማህሌት.jpg

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን በኦርጋን መዘመር ተገቢ ነውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ጊዜውን መዋጀት” በሚል የተሳሳተ መረዳትና “ቴክኖሎጂን እንጠቀማለን” በሚል ትርጉም ኦርጋን እና ጊታር ለመጠቀም የሚፈልጉ ለዚህም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ድጋፍ ያደረገ በማስመሰል ምእመናንን የሚያደናግር ትምህርት ያላቸው አሉ:: ቴክኖሎጂን በመጠቀም ድምጽን እንዲሰማ በዜማ ቀረጻ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለታሪክ ማስቀመጥ እንዲሁም ስራው አድካሚ የሆነ የዜማ መሳርያን በሰለጠነ አሰራር መንፈሳዊ ይዘቱን ባልለቀቀ መልክ እንዲሆን ማድረግ ቢገባ እንጂ የዜማ ቃናውን የመሳርያውን አስተማሪነትና  ትውፊታዊ አጥፍቶ ሊሆን አይገባም:: በ፲፱፻፹፮ ዓም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት በመዝሙር አገልግሎት ከተዘረዘሩት የዜማ መሣርያዎች ወጥቶ “በኦርጋን ልዘምር” የሚል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የጣሰና የቅዱሳን ሐዋርያትን ትእዛዝ እንደጣሰ ሁኖ ከምእመናን የተለየ ነው:: አንዳንድ ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ ይህንኑ ዜማ መሳርያ በማህለቱና በቅዳሴ ጊዜ እንዴት እንደሚውል ያስረዳሉ:: በቤተክርስቲያን ድምጽ ካላቸው ንዋያት ቃጭል ብቻ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት እንደሚውል ከበሮ መቋሚያ እና ጸናጽል የማህሌት ማሳርያዎች ሲሆኑ ሌሎቹም በማኅበርና በግል መዝሙር እንጠቀምባቸዋለን:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን እንዳለ ለእኛም ስንዱ እመቤት ከሆነች ቤተ ክርስቲያን የተሰራልንን ስርዓት መጠበቅ በዚያም መጽናታችን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የመታዘዝ መስዋዕት ነው::

ዜማንና የዜማ መሣርያን በሚመለከት ቀዳሚው መልእክት

የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የዜማ ስልትና የዜማ መሣርያዎችን ስናስብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረታቸውን፣ ታሪካዊ ገጽታቸውን፣ ምስጢራዊ አስተማሪነታቸውንና እንዲሁም ትውፊታው ጠቀሜታቸውን በማስተዋል እንደአባቶቻችን ቆመን ልንገኝ ይገባል እንጂ አባቶች ከሠሩልን ድንበር ወጥተንና የዘመናዊነትን ካባ ደርበን ማንነታችን በማይገልፅና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዲሁም ፍጹም አስተማሪነት በሌለው የዜማ መሳርያ ልንገለገል አይገባም:: “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” (ዮሐ፲:፳፯) እንደሚል እኛም እንደ አባቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረገውን ያሬዳዊ ዜማ እና የዜማ መሣርያ አጠቃቀምን የሚመለከተውን  የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተቀብለን ብንጠብቅ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራችን እንደ አባቶቻችን ወደ መላእክቱ ኅብረት የምንነጠቅበት ይሆናል::

1 thought on “ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፫)

  1. Pingback: ዘማሪ ማስመጣት፡ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የዘማርያን ሚና – አስተምህሮ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s