ኪዳነ ምህረት: የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር!

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ
ኪዳን ምንድን ነው?

እግዚአብሔር አምላክ ዓለሙን ከፈጠረ ጀምሮ ፍጥረታቱን ሁሉ በቸርነቱ በርኅራሄው ይጠብቃል፤ ይመግባል፡፡  የሰው ልጆች ህግን በመተላለፍ፣ ኃጢአትን ሰርተው እግዚአብሔርን ባሳዘኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዝለው ከእርሱ ከልዑል እግዚአብሔር በረከት ጥበቃ እንዳይርቁ ስለባለሟሎቹ ቅዱሳኑ ብሎ በቃል ኪዳኑ ይጠብቃል:: እግዚአብሔር ከከባለሟሎቹ ጋር የሚያደርገው ቃል ኪዳን የቸርነቱን ብዛት ከሚገልጥባቸው መንገዶች አንዱ የሆነ ፍኖተ እግዚአብሔር ነው:: ‘ኪዳን’ በግእዙ ‘ተካየደ’ ትርጉሙም ተማማለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ ማለት ሲሆን እግዚአብሔር አምላክም ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ጋር የገባው ውል ‘ቃል ኪዳን’ ይባላል:: ቃል ኪዳን ማለትም ‘ውል፣ ስምምነት’ ማለት ነው። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን በምህረቱ የሚጠብቅበትን ‘ቃል ኪዳን’ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር እንማራለን:: በተለይም ከቃል ኪዳን ሁሉ የከበረች ስለሆነች በየዓመቱ በየካቲት ፲፮ ስለምናስባት ከ፴፫ቱ የእመቤታችን በዓላት ከሆኑት አንዷ ስለሆነች የእመቤታችን የቃል ኪዳን ዕለትን በተመለከተ እንዳስሳለን::

ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር አምላክ ከመረጣቸው ከወዳጆቹና ከባለሟሎቹ ከቅዱሳኑ ጋር በየዘመናቱ የፈጸማቸው ኪዳናት እንደነበሩ ያስተምሩናል:: በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት መዝሙር “ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ:- ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” (መዝ.፹፱፡፫) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላክ በበደላችን ምክንያት እንዳንጠፋ የሚጠብቀን በዚሁ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው። ለምሳሌ ምድርንና ሥጋ ለባሹን በንፍር ውኃ ዳግመኛ ላያጠፋ ለአባታችን ለኖኅ ቃል ኪዳን ገብቶለታል (ዘፍ.፱፡፩-፲):: ለቀደሙት አባቶችም ለእነ አብርሃም ለቅዱስ ዳዊት ቃል ኪዳን ገብቷል፤ መሃላንም አድርጓል: (ዘፍ.፳፪፡፲፰ ዘፍ.፳፮፡፬ መዝ.፹፱፡፫):: ይህም ቃል ኪዳን እንደ ተርታ ውል ያለ ሳይሆን የፀና የምህረት ቃል ኪዳን ነው:: በብሉይ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት በዓመተ ፍዳ የተፈጸሙ ስለሆኑ የመከራውን ጊዜ ያወሳሉ:: በሐዲስ ኪዳን የተፈጸሙት ኪዳናት ደግሞ ዘመነ ምህረትን የሚያውጁና ጸጋቸውም የበዛ አማናዊ ኪዳናት ናቸው። በአንጻሩ ከቅዱሳኑ ጋር ያደረገው ኪዳን በአምላክ ሰው መሆን ፍጻሜን አግኝቷል::

የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን ለቅዱሳኑ ከሃይማኖታቸው ጽናት ከፍጹምነታቸውና ከሥራቸው ትሩፋት የተነሳ በቅድስና ክብር አክብሮ ለገድላቸው እንዲሁም በተጋድሎ ላሳለፉበት ቦታ ለረገጡት አፈር ሁሉ በረከታቸው ተርፎ ዛሬ እኛ ምእመናን በየመካናቱ እምነቱን በመተሻሸት በመጠጣት ከቅዱሳኑ በረከት እንሳተፋለንል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ምህረት የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ለሚወዱትም ትእዛዙን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን እንደሚያደርግ በመጽሐፍ እንደተጻፈ ከቅዱሳኑ ጋር ውልን የሚያደርገው እኛን የሰው ልጆችን በቅዱሳኑ በጎ ሥራ ለመጥቀም ፈልጎ ነው (ዘጸ ፳:፪-፮):: “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል” ዘዳ ፯:፲፪::

ኪዳነ ምህረት

ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጹም ከከበሩ የእመቤታችን በዓላት አንዱ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የማይጠፋ የዘላለም ኪዳን የሰጠበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ታላቁ የነገረ ማርያም መጽሐፍ እንደሚያስረዳን ጌታችን ካረገ በኋላ እመቤታችን ጌታ ወደ ተቀበረበት ጎልጎታ እየሄደች ትጸልይ ነበር:: ከዕለታት ባንዳቸው በየካቲት ፲፮ ዕለት ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ልጄ ወዳጄ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ ጌታችንም ምን እንዲያደርግላት ሲጠይቃት በስሟ ለሚማጸኑ መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ ለችግረኛ ለሚራሩ በስሟ ቤተ ክርስቲያን ለሚያንጹ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን ለሚሰጡ ምሕረትን እንዲያደርግላቸው ጠየቀችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ በየካቲት ፲፮ እለት ቃል ኪዳን ገብቶላታል:: ይህንን ቃል ኪዳን በነሐሴ ፲፮ ቀን ድግሞታል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም በየዓመቱ የካቲት ፲፮ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምህረት ውል ሰምምነት የተቀበለችበት ቀን በታላቅ መንፈሳዊ በረከት ታከብራለች፡፡ ይህ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የኪዳነ ምህረት በዓል ቀድሞ ለነበሩ ኪዳናት ኪዳነ አዳም ኪዳነ ኖህ ኪዳነ አብርሃም ኪዳነ ዳዊት መደምደሚያ ነው፡፡ ለዚህም የማያልፍ የምህረት ቃል ኪዳንን ስለገባላት ኪዳነ ምሕረት የምሕረት የይቅርታ መሐላ ውል ስምምነት እየታሰበ በመዝሙር፣ በማኅሌትና በቅዳሴ ይከበራል፡፡ ምዕመናንም በዚሁ ዕለት በረከትን ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ይቀበላሉ፡፡

ኪዳነ_ምህረት

በየካቲት ፲፮ ዕለት በስንክሳር እንደተጻፈ “መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድሆችና ለችግረኞች ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላላች:: በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የምህረት ቃል ኪዳን ውስጥ “ስምሽን የጠራ” ሲል በጸሎቱ በእርሷ የተደረገለትን የአምላክ ቸርነት እያሰበ ዘወትርና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በእምነት ጸንቶ በጎ ምግባርን እየፈጸመ ስሟን የሚጠራ ይድናል ማለቱ ነው፡፡ ቅዱሳን የሰው ልጆችን ልመና እንዲያቀርቡ መላእክቱም የቅዱሳኑን ጸሎት በማዕጠንታቸው እንዲያሳርጉ (ራእ ፰:፫-፬) ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነቢዩ ኤልሳዕም የነቢዩ ኤልያስን ስም እየጠራ በመጸለዩ በረከትን አግኝቷል፡፡ የነቢያት ትንቢታቸው፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ የመላእክት እህታቸው፣ የሐዋርያት ሞገሳቸው የሆነችው የድንግል ማርያምን ስም አምኖ ለሚጠራት ከዚህ በላይ ድንቅ ያደርጋል፡፡ እርሷ ለዓለማት ፈጣሪ እናቱ ናትና፡፡

ዝክርሽንም ያዘከረ” ሲል በእርሷ የተደረገለትን ድኅነት እያሰበ፣ በስሟ ለተቸገረ የሚመጸውት የዘላለም ሕይወትን ያገኛል ሲል ነው፡፡ እርሷን እናት ብሎ ያመነና የጠራት ልጅዋንም ወልድ ዋሕድ ብሎ ያምናል ይጠራልና ይህ ቃል ፍጹም እውነት ነው፡፡ “የአምላክ እናት” ብሎ ዝክሯን የሚያዘክር ልጅዋን “አምላክ” ብሎ አምኗልና “ዝክርሽን ያዘከረ ይድናል” የሚለው ቃል ጽኑዕ ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት መባዕን በስሟ የሚሰጡትም እንዲሁ ነው፡፡ ስም መጥራት የማመን የመታመን መገለጫ ነው፡፡ ዝክርን ማዘከርም በእምነት የሚደረግ የትሩፋት ሥራ ነው፡፡ በቅዱሳን ስም የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ማሳነጽ ደግሞ ከሁሉ የከበረ የጽድቅ ሥራ ነው፡፡

በስምሽ ቤተክርስቲያን ያሠራ” የሚለው ሀረግ የምዕመናንን ኅብረት በእምነት ያጸና፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትበትን ቤተ እግዚአብሔር ያሳነጸ፣ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆነውን የሰውን ልጅ የተዋሕዶን ትምህርት አስተምሮ ያሳመነና ያጠመቀ ድኅነትን ያገኛል ማለቱ ሲሆን ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት የተቀመጠ እውነተኛው የጽድቅ ሥራን የሚገልጽ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ምልዕተ ፀጋ ብሎ ያመሰገናት ድንግል የአምላክ እናት እንዲሁም መልዕልተ ፍጡራን በመሆኗ በቅዱሳት መጻሕፍትም ‘ለእስራኤል የማልሁላቸው መሐላ የገባሁላቸው ቃል ኪዳንም ይህቺ ናት" (ኢሳ.፶፱፡፳-፳፩) እንዲሁም በቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው”; (መዝ.፹፮:፫) እንዳለ የእመቤታችን ቃል ኪዳን ከሁሉ ኪዳናት ልዩ ነው:: መልዕልተ ፍጡራን የሆነች እመቤታችን ከተመረጡትም ሁሉ በላይ የተመረጠች ናት:: በዚህም ፍጥረታት ሁሉ ተስፋ የሚያደርጓት ምክንያተ ድኅነት አማናዊት የድኅነተ ዓለም ተስፋ ናትና ከሁሉ ኪዳን በተለየ ‘ኪዳነ ምህረት’ ተብላ ትጠራበታለች::

ይህ ቃል ኪዳን የሚያገለግለው ለማን ነው?

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የምህረት ቃል ኪዳን የሚያገለግለው በሃይማኖታቸው ጸንተው በመልካም በቅድስና ሥራ በመትጋት ለሚደከሙ ለኃጥአን ነው:: አባታችን ቅዱስ ሕርያቆስም ይህንን በቅዳሴ ማርያም “አዘክሪ ድንግል ለኃጥአን ወአኮ ለጻድቃን:- ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥአን አሳስቢ” በማለት ይገልጸዋል:: አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌው “ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ:- የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ባጠፋን ነበር” በማለት የእመቤታችንን ቃል ኪዳን አማናዊነት ይገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የእመቤታችን የምህረት ቃል ኪዳን አለና በእርሱ ድኅነትን እናገኛለን በማለት በጎ ምግባርን፣ ትሩፋትን ከመሥራት ቸል ማለት አይገባም፡፡ እርሷ የሚላችሁን አድርጉ እንዳለች ልጅዋ የሚለንን ለማድረግና ባልቻልነው ነገር ደግሞ የእርሷን አማላጅነት እንጠይቃለን፡፡

የእመቤታችን የቃል ኪዳን ምልጃ: ታሪክ ዘስምዖን 

አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ለንጹሃን ሳይሆን በኃጢአት ላሉ ለደካሞች የእመቤታችን ቃል ኪዳን መድሃኒት ምህረት ነው ብሎ እንደገለጸው በተአምረ ማርያም ከተመዘገቡትና የእመቤታችንን አማላጅነት ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ በዚህች እለት በየካቲት ፲፮ የሚነገረው የስምዖን (የበላዔ ሰብእ) ታሪክ ነው:: በላዔ ሰብእ አስቀድሞ ቅምር በምትባል ሀገር በአብርሃማዊ ኑሮ የሚኖር ደግ ሰው ነበር:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ቆሮ ፲፩፥፲፬ ላይ “ሰይጣን ራሱን የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ይለውጣል” በማለት እንደገለጸው በበላዔ ሰብእ የቀናው ዲያብሎስም በቅድስት ሥላሴ አምሳል ሦስት ሰዎችን ተመስሎ እንግዳ ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በላዔ ሰብእም እግዚአብሔርን ያስተናገድኩ መስሎት በደስታ ያማረ ምንጣፍ ጎዝጉዞ ወገቡን ታጥቆ የሰባውን ፍሪዳ በመሰዋት አስተናገደው:: በሥላሴ ተመስሎ በቤቱ የተገኘው ዲያብሎስ ግን አዳምንና ሔዋንን በክፋት ስራው እንዳሳተ ስምዖንንም “ልጅህን ሠውተህ እራት አዘጋጅልን” ብሎ ጠየቀው፡፡ ስምዖንም የእንግዶቹን ፈቃዳቸውን ሁሉ ሊፈጽም ቃል ገብቶ ነበርና መሃላውን እያሰበ ልጁን አቅርቦ ሰዋው:: እንደትእዛዛቸው ከቀረበው መስዋዕት አስቀድሞም ቀመሰ:: ከዚህ በኋላ ዲያብሎስም ተሰወረው፡፡

በላዔ ሰብእ የልጁን ሥጋ በመብላቱ ጠባዩ ተለውጦ ከዚያ በኋላ ቤተ ሰቦቹን ጨምሮ ሰባ ስምንት ሰዎችን በልቷል:: በላዔ ሰብእ የሚለው ስያሜውም ከዚሁ ታሪክ እንደምንረዳው ሰውን የሚበላ በሚል ነው:: በዚህም ሕይወት ሲዘዋወር ሳለ ሁለንተናው በቁስል የታመመ ሰው ተመለከተ:: ይህም ሰው በላዔ ሰብእን ‘አምላክን ስለ ወለደች ድንግል ማርያም ብለህ ውሃ አጠጣኝ” ሲለው በላዔ ሰብእም ልቡ ራርቶ ወደ ልቡናው ተመልሶ ለድሀው ያለውን ውኃ ሰጠው፡፡ ይህም በላዔ ሰብእ በመልካም ሥራ ደካማ ሲሆን ነገር ግን የሃይማኖት ልብ እንዳለው የሚያሳይ ነው:: በላዔ ሰብእ ከሞተ በኋላ ነፍሱ በፈጣሪ ፊት ለፍርድ ስትቆም ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት ይህቺን ነፍስ እያስፈራሩ ወደ ሲዖል ወሰዷት:: እመቤታችን ግን ልጄ ወዳጄ ማርልኝ ስትል ለመነችው፡፡ በመልክአ ኪዳነ ምህረት ድርሰት “እንበለ ምግባር ባሕቱ እመ ኢይጸድቅ አነ ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ:- ያለ በጎ ሥራ የምንጸድቅ መንግስተ ሰማያትን የምንወርስ ካልሆነ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ቃል ኪዳንሽ በከንቱ ነበርን?” ተብሎ እንደተጻፈ ሰባ ስምንት ነፍሳትን የበላው በላዔ ሰብእ የእመቤታችን ቃል ኪዳኗ በሚታሰብበት እለት ለድሃው ውኃን ስላጠጣ ነፍሱ በእመቤታችን ቃል ኪዳን አማላጅነት ዳነች::

እግዚአብሔር አምላክ እንኳንስ ለድኅነተ ዓለም ለመረጣት መዓዛ ንጽሕናዋን ቅድስናዋን ለወደደላት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ይቅርና እግዚአብሔርን ከማያውቁ ከአሕዛብ ወገን ከሆነች ከነናውት ሴት ስለ ልጇ ብትለምን ምሕረት የባህሪው ነውና  በልመኛዋ ልጇን ምሮላታል:: ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁላችን አማላጅ እናት ትሆን ዘንድ በቀራዮ ተሰጥታናለችና ለልጆችዋ ምህረትን የምትለምን አዛኝት እናት ነት (ዮሐ ፲፱:፳፮ – ፳፯):: ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ላይ “ወዮ ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው የቀድሞ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ፤ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል ሆይ፤ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት እመቤታችን ለፍጥረት ሁሉ አማላጅ መሠረተ ድኂን መሆኗን መስክሯል::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጥነሽ የምትደርሽ

ጌታችን በወንጌል እንደተናገረው “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ፃድቅንም በፃድቅ ስም የሚቀበል የፃድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም” (ማቴ.፲፡፵፩-፵፪) የበላዔ ሰብእ ሕይወትም እግዚአብሔር አምላክ የምህረት አምላክ እንደሆነ በምክንያት በመረጣቸው ላይ አድሮ ለእኛ ለልጆቹ የሚሰጠው ምሕረቱ መገለጫ ነው::

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ጸሎት “አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወዓጸባ፣ ለዓይን እምቀራንባ:- ማርያም ሆይ በችግርና በመከራ ጊዜ ከዓይን ጥቅሻ ይልቅ ለእርዳታ ፈጥነሽ የምትደርሽ” በማለት ለሚጠሯት ፈጥና የምትደርስ እናት መሆኗን ተናግሯል፡፡ አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል:: አንተ ‘መታሰቢያሽን ያደረገ ስምሽንም የጠራ የዘላለም ድኅነትን ይድናል’ ብለሃታልና” ብሎ እንደገለጸው ዛሬም ስሟን ጠርተው ለማይጠግቡ ሲያወድሷት ለማይሰለቹ ዝክሯን በማዘከር መታሰቢያዋን በማድረግ ዘወትር ተአምሯን በመስማት በማሰማት ለሚተጉ መቅደሷን ለሚሰሩ ፈጥና የምትደርስ አፍጣኒተ ረድኤት ናት።

በአጠቃላይ በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው የኪዳነ ምህረት በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጅዋ ከወዳጅዋ የምህረት ቃል ኪዳንን የተቀበለችበት ነው፡፡ በዚህ ቃል ኪዳንም የምንጠቀመው እኛው ነንና ስለ ቅዱሳኑ ብሎ የሚምር አምላክ ስለ ምህረት ቃል ኪዳኗ ሲል እንዲምረን በቅዳሴ ዘወትር ስሟን እያነሳን “ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን” እያልን እንለምናታለን:: ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ስድሳ አራት ጊዜ “ቅድስት ሆይ ለምኝልን” እያለ፣ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሀን አሥራ ሦስት ጊዜ “ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን” እያለ እንዳመሰገናት እኛም በአባቶቻችን ፈንታ የተወለድን ልጆችዋ ዛሬም እስከ ዘላለሙ ቅድት ሆይ ለምኝልን ብለን እንማጸናታለን፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ እመቤታችን በአማላጅነቷ በረድኤቷ አትለየን፤ በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፬)

እንዴት እንዘምር?13322084_1095910523807229_7837358580726615838_n.jpg

 

 

 

 

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍል የመዝሙርን ምንነትና ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንደሚገባው አውስተናል:: አስተምህሮ በዚህ አራተኛና የመጨረሻ ክፍል ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን እንዴት መዘመር እንዳለብን በመጠቆም ከአዘማመር ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ችግሮችን ታሳያለች፤ መፍትሔዎችንም ትጠቁማለች፡፡

መዝሙር ጸሎት ስለሆነ በማስተዋል በእምነት ልንዘምር ይገባል

መዝሙር ስንዘምር ዜማውን ብቻ በማሰላሰል ሳይሆን የመዝሙሩን ምስጢር አውቀን በእምነት ሊሆን ይገባል:: “አምናችኹም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” እንደሚል (ማቴ ፳፩:፳፪):: ስንዘምር ልባችን ወደ ሌላ ሃሳብ ተወስዶ በሥጋዊ ስሜት የሚቀርብ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ እንደማንሳት እንዲሁ በከንፈር ማክበር ብቻ ይሆንብናል (ዘጸ ፳:፯ ኢሳ ፳፱:፲፫):: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል” (ሉቃ ፲፱:፳፭) እንዳለን ህሊናችን ወደ ሌላ ሃሳብ እንዳይወሰድ ልቡናችንን እየሰበሰብን መዝሙሩም የምእመናንን ልብ ለቃለ እግዚአብሔር የለሰለሰ እንዲሆን የሚያዘጋጅ መሆን አለበት:: መዝሙር ለመላእክትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ላሉ ምግባቸው እንደሆነ ሁሉ በፍጹም እምነት ሳናወላውል ልቡናን በመሰብሰብ ይህን ስጦታ የምንመገበው እግዚአብሔር አምላክ ድካማችንን አለማመናችንን እንዲረዳው በመማጸን ነው::

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በእምነት ባለማወላወል ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ለምነን የምናጣው እንደሌለ ይነግረናል (ያዕ ፩:፮-፰):: ስለሆነም መዝሙር ስንዘምር በልማድ ቃላትን በመደጋገምና ለመርሃ ግብር ማሟያ ለይስሙላ ሳይሆን በእምነትና በተመስጦ መዘመር ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከአገልግሎታችን ሁሉ በላይ ዝማሬያችንን በእምነት ሲሆን ደስ ያሰኘዋል (ዕብ ፲፩:፮):: ለምሳሌ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት እንዳዳናቸው እኛም ከበዓሉ በረከትን እንዲሰጠን ስንለምን (ስንዘምር) እንደ ሦስቱ ህጻናት ባለመጠራጠር በእምነት ለዚያም በሚያበቃ ተጋድሎ እንዲሆን ያስፈልጋል:: በሌላም የጌታችንን መድኃኒታችንን ስቅለት እያሰብን ስንዘምር ክርስቶስን በእውነት የተከተሉትን እያሰብን እኛም በጊዜውም ያለጊዜውም በመታመን በቀራንዮ የነበረውን በህሊናችን እየሳልን ነው (ገላ ፫:፩)::

መዝሙር መስዋዕት ስለሆነ በንጹህ ልብ ሊቀርብ ይገባል

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ስለሆነ በልዑል እግዚአብሔር ፊት የተወደደ መስዋዕት ሁኖ እንዲቀርብ ራስን ለንስሐ በማዘጋጀት ልቡናን በማንጻት ሕይወታችንን ልዑል እግዚአብሔር የሚቀበለው እንዲሆን በማድረግ ሊሆን ይገባል:: መዝሙረኛው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” እንዳለ የዝማሬ መስዋዕታችን ንጹሕ ልብን እንዲሰጠን የቀናውንም መንፈስ በልቡናችን እንዲያኖርልን በመማጸን ነው (መዝ ፶:፲-፲፯ ሉቃ ፲፰:፲-፲፬):: እግዚአብሔር ትሁትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብን ዝማሬ ይመለከታል:: ከቃየልና አቤል መስዋዕት የምንማረው እግዚአብሔር አምላክ ወደ መስዋዕቱ እንደተመለከተና የአቤልን መስዋዕት ንጹህ መስዋዕት አድርጎ እንደተቀበለ ነው::

እኛም በዝማሬያችን በአንድ ልብ በንጹህ ህሊና ቁመት ዝማሬያችንንም መስዋዕት አድርገን ከማቅረብ አስቀድሞ ይህን እግዚአብሔር አምላክ እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም (ሐዋ ፬:፴፬):: ይህም እግዚአብሔር አምላክ ፊቱን ወደኛ እንዲመልስ የሚያደርግ ጸጋንም የሚያሰጥ ነው (፩ጴጥ ፭:፭):: በግርግር በሁከት በመገፋፋት በመለያየት በድፍረት በራስ ሃሳብ/ፈቃድ በመወሰድ ጸጋ አይገኝም (ዕብ ፲፪:፳፰-፳፱ ፪ቆሮ ፲፫:፭ ሚክ ፮:፮-፰ ሮሜ ፮:፩):: “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ” (ኤፌ ፬:፬):: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነታችንን በአገልግሎታችን ወቅት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን ልናቀርብ በዝማሬያችንም ወቅት መዘመራችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ልብ የሚመረምር አምላክ ፊት እንደቆምን በማስተዋል ሊሆን እንዲገባ ያሰተምረናል (ሮሜ ፩፪:፩-፭)::

መዝሙር እግዚአብሔር የሚወደው ንጹህ መስዋዕት ሁኖ ሳለ አንዳንድ መዝሙር ተብለው በሚዘመሩት ዝማሬዎች ፉከራ ያለባቸው የራሳችንን ድካም ኃጢአት የምንመለከትበት ሳይሆን ሌሎችን ብቻ የምንኮንንበት ወይም “የእኛ ይሻላል ከሌላ” የሚል ስሜት ባለበት ሲቀርብ በልዑል አምላክ ፊት መቆማችንን የዘነጋን ያደርገናል:: ክርስትና የራስን በደል እያሰቡ ለሌላውም መልካምን የምንመኝበት ልቡናን ከፍ ከፍ በማድረግ (በመንፈሳዊ ዝግጅት)  የምንኖረው ሕይወት እንጂ በሕይወታችን ስንዝል በሚሰማን ጊዜያዊ ስሜት ወድቀን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕትን ሳይሆን ስሜታችንን ብናንጎራጉር ራሳችንን እናታልላለን:: ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩን ‘እዘምራለሁ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ” (መዝ ፻:፪) “በስፍራ ሁሉ ያለቍጣና ያለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” (፩ጢሞ ፪:፰) የሚለውን ነው:: ስለሆነም መዝሙራችን ከተነሳሂ ልቡና የሚወጣ፣ ተናጋሪውንም አድማጩንም ወደ ንስሃ የሚመራ መሆን አለበት፡፡

በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው በክርስቶስ ጸጋ ያገኘነውን የመዳን ሕይወት በራሳችን የተለየ ችሎታ ያገኘነው አስመስለን በመዝሙራችን ሌሎችን ማቃለል አይገባም፡፡ ይልቁንስ እንደ አባቶቻችን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ በምስጋናና ራስን ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔርን ልናመሰግን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን ልንመሰክር ይገባል፡፡ ትህትናችን ግን ባለማወቅ መጻሕፍትን የሚተረጉሙ ሰዎች እንደሚመስላቸው ክርስቶስን የሚቃወሙትን፣ ቤተክርስቲያንን የሚያቃልሉትን፣ የሚዘርፉትን የሚያበረታታ ወይም “የማይሞቀው፣ የማይበርደው” መሆን የለበትም፡፡ መዝሙራችን ትምህርት ነውና ሰውን በሚያንጽ መልኩ፣ በፍቅር አንድ በሆነ መንፈስ በንጽህና የሚገባውን ክብር እየሰጠን ከተመላለስን በመካከላችን እንዲገኝ አምላካችን ለቃሉ የታመነ አምላክ ነው።

ዘማርያን (መዘምራን) የሚባሉት እነማን ናቸው?

በቤተክርስቲያናችን በቀዳሚነት በዝማሬ የሚታወቁት ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ እነርሱ ያለማቋረጥ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ በማይሰለች ልሳን፣ በማይጠገብ ዜማ አምላካችንን በሰማያት እንደሚያመሰግኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል (ኢሳ ፮:፩-፬)፡፡ በሰማያዊ ልሳን ከቅዱሳን መላእክት ጋር እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የሰማይ መንግስት ምሳሌ በሆነች ምድራዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ ዘማርያን፣ አመስጋኞች ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ የቤተክርስቲያንን ዜማና አዘማመር የተማሩ ሊቃውንት መዘምራን ይባላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሰንበት ት/ቤትና በልዩ ልዩ መንፈሳውያን ማኅበራት መዝሙር የሚዘምሩ ምዕመናን በሰንበት ት/ቤት ወጣት መዘምራን ይባላሉ፡፡ እንደዚሁም ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን በካሴትና በሲዲ እያዘጋጁ ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚያውሉ ምዕመናንም እንዲሁ እየተለመደ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ዘማሪነት ቀሚስ ከመልበስ፣ ፖስተር ከማሰራት፣ ድምጽን በካሴትና በሲዲ ከማስቀረጽ፣ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ እነዚህ እንግዳ መገለጫዎች አንዳንድ አገልጋዮች ዘማሪነትን የገንዘብ ማግኛ ሙያ በማድረጋቸው ምክንያት ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረ ምዕመናን ለመለየት የሚጠቀሙባቸው የንግድ ምልክቶች (trade marks) እንጅ ኦርቶዶክሳዊ ውርስ ያላቸው አይደሉም፡፡ በተለይም ዘማሪ በመባል ታዋቂነትን በማትረፍ (celebrity culture) ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮንም ለሚቆሙለት ልዩ ልዩ ጥቅም፣ ክህደትና ምንፍቅና ሲሉ በመበረዝ ምዕመናንን ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ከቤተክርስቲያን ማኅበር እየለዩ የሚያስኮበልሉ በበዙበት በዚህ ዘመን የዘማሪነት ግብር ትክክለኛ መገለጫዎችን መለየት ካልቻልን ለምዕመናንም በተገቢው መልኩ ካላስረዳን ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ እንደማፍራት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገንዘብን መውደድ የኃጢአት ሁሉ ስር እንደሆነና ይህንን የተመኙ ከሃይማኖት እንደወጡና ራሳቸውን በብዙ ስቃይ እንደወጉ ይመክረናል (፩ጢሞ ፮:፲ ቆላ ፫:፩-፫)::

ስለሆነም ዘማሪነትን ከንግድና ከታዋቂነት ገጽታ ግንባታ (celebrity culture) በእውቀትና በብልሃት መለየትና የሰይጣንን ተንኮል ማፍረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ከሚረዱን አሰራሮች መካከል አንዱ መዝሙራት በግለሰብ ባለቤትነት ከሚወጡ ይልቅ በሰንበት ት/ቤቶችና በማኅበራት እንዲወጡ በማድረግ ማንም የእኔነት ይዞ እንዳይመካባቸውና መውደቂያ እንቅፋትም እንዳይሆኑበት ማገዝ ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱሳን መላእክትም ሆኑ አባቶቻችን መዘምራን መዝሙርን ለአምልኮና ለምስጋና በማኅበር ይዘምራሉ እንጂ አንድን ሰው በሚያገን ወይም ተከታዩን በሚያሰናክል መልኩ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አገልጋይ ዘማርያን በግል መዘመራቸው በራሱ ችግር ነው ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዓላማውን ተረድተው፣ የቤተክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት ጠብቀው፣ ለግል እውቅናና ጥቅም ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ልዕልና የሚዘምሩትን በህሊና ዳኝነት እየተመራን ልናግዛቸው፣ ልናበረታታቸው ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመዝሙር የሚያገለግሉ ሁሉ የቤተክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አክብረው የሚያስከብሩ በሕይወታቸውም አርአያነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል:: አገልግሎቱን የሚሰጡ ለጸሎት የሚተጉ በሥርዓተ ቅዳሴ የሚሳተፉ ሕይወታቸው የሚያስተምር አለባበሳቸውና በሰውነታቸው ላይ የሚያኖሩት ጌጣ ጌጦች ግራ የሚያጋባ መሆን የለበትም:: ዛሬ ላይ እንደልማድ ተወስዶ በተለያየ ማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ ዘማርያን ለሰማያዊው ዝማሬ ለታላቁ አገልግሎት ከተጠራን በኋላ ቀድመን ስንመላለስበት በነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደመከረን እንደክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ ሕይወት በዘፈኑ በስካሩ በጸብ በማይጠቅም የክርክር ሕይወት ልንታይ አይገባም (ቆላ ፪:፰ ያዕ ፫:፩ ሮሜ ፪:፳፩):: ሰይጣን ከመውደቁ በፊት አገልግሎቱ ምስጋና ነበር:: የሰው ልጅም እርሱ በለቀቀው አገልግሎት እንዳይሰማራ ሰማያዊ ከሆነው መዝሙር ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን በሚጋብዝ ከስጦታችን ውጭ እንድንመላለስ ያለበረከት ያለዋጋ እንድንቀር በልቡናችን እንክርዳድን ይዘራል:: “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው” (ሮሜ ፮:፬-፮)::

አዘማመራችን የሚያስነቅፍ መሆን የለበትም

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትን ያለሥርዓት መፈጸም እንደማይገባ ታስተምራለች፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ማለት በመጻህፍት የተጻፈ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ በጽሑፍ ከተቀመጡ ሥርዓቶች ባሻገር በልማድ የዳበሩ ሕግጋት አሉ፡፡ ከአዘማመር እንቅስቃሴያችን ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈጸሙት መዘምራን በግል ወይም በጋራ በሚዘምሩበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ ዓይን ጨፍኖ መዘመር፣ ያለ ልክ መጮህ፣ ከመጠን በላይ መዝለል፣ ከሚገባ በላይ እንቅስቃሴን ያካትታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለፍጥረታት ሥርዓትን እንደሰራላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የቆሮንቶስ ሰዎችን ያለሥርዓት በመሄዳቸው እንደገሰጻቸው እኛም እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ እንደሆነና በቤተክርስቲያን የሚከናወኑ አምልኮታዊ ሥርዓቶች አሰላለፋችንና እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን በመረዳት ወንጌልን የሚሰብክ በአገባብና በሥርዓት ሊሆን ይገባል (፩ቆሮ ፲፬:፵ መዝ ፻፵፪:፮ መዝ ፭:፫ ፩ቆሮ ፲፬:፵)::

በቤተክርስቲያናችን ልማድ በማኅሌትና በመዝሙር ወቅት ስሜታዊ የሚሆኑ አገልጋዮች ቢኖሩ እንኳ የቤተክርስቲያን አባቶች ጸናጽሉን በመጠቀም ምልክት እየሰጡ ያስቆሟቸዋል እንጅ ለነቀፋ አሳልፈው አይሰጧቸውም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለአውዳቸው የሚጠቅሱ የሚቆነጻጽሉ ሰዎች ክቡር ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት ራስን በመናቅ ከዘመረው መዝሙር ጋር በማስመሰል የዋሃንን ለማሳት ይሞክራሉ፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜም ስህተቱን በቃለ እግዚአብሔር የተደገፈ ለማስመሰል እንደሚጥር ይታወቃል፡፡ እኛ ግን እናስተውል፣ ተመስጦና ራስን መናቅ ከስሜታዊነት ጋር አይገናኙም፡፡ ይልቁንም ተመስጦና ስሜታዊነት ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ክቡር ዳዊት በተመስጦ፣ ራስን ዝቅ በማድረግ ዘመረ እንጅ ስሜታዊ አልነበረም፡፡ መዝሙር ስንዘምር ሊኖረን የሚገባው ተመስጦ ብንችል አባታችን ቅዱስ ያሬድ በንጉሡ በአጼ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር በጦር መወጋትን እንኳ እስከማይሰማው ድረስ የተመሰጠውን ተመስጦ ሊመስል ይገባል፡፡

ስንዘምር ሰዎች ምን ይሉናል ብለን ለራሳችን ክብር ከተጨነቅን ለክቡር ዳዊት የተሰጠ ቡራኬ ይቀርብናል፡፡ በዝማሬያችን እግዚአብሔር አምላክ የብርሃን አምላክ ነው ስንል ዓይናችንን ወደ እርሱ በማቅናት (በመጨፈን ሳይሆን መዝ ፻፵፪:፮) በእንቅስቃሰያችንም መገፋቱን መከራ መቀበሉን ስንመሰክር መንፈሳዊ ዋጋም አለን:: ምድራዊ ሥርዓት ልዩ አሰላለፍና ክብር ካለው ለሰማይና ምድር ፈጣሪ የሚቀርበው መላው እንቅስቃሴያችን የድምጽ አወጣጣችን እንደአንድ ልብ መካሪ አንድ ሃሳብ ተናጋሪ ተጨንቀን ተጠበን ሊሆን ይገባል:: በዚህም እግዚአብሔር አምላክ የአቤልን መስዋዕት እንደተመለከተ የእኛንም በመዝሙር የምስጋና መስዋዕት ይቀበልልናል::

በመዝሙር ወቅት የዜማ መሣርያዎች አጠቃቀማችንና አያያዛችን እንዲሁም መዝሙሩን ከጨረስን በኋላ ስናስቀምጣቸው እንዲሁ በሥርዓቱ መሆን አለበት፡፡ በካህናት የማህሌት ዝማሬን ስንመለከት ካህናቱ ከበሮውን ሲመቱ እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን ምስጢርን ጠብቀው ሲጀምር በእርጋታ ምሳሌነቱም አይሁድ ጌታችንን እያፌዙ ለመምታታቸው ዝማሬው ተሸጋግሮ  በፍጥነት ሲመታም ሰንበት እንዳይገባባቸው በዚህም ጲላጦስም ምክንያትን አግኝቶ እንዳያድነው በማለት ያንገላቱበት ምሳሌ ነው:: “በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እንዲል (ቆላ ፫:፲፮)። የከበሮ ሰፊው አፍ (ገጽ)  የመለኮት ምሳሌ ነው ስላልን  ስናስቀምጥም አስተማሪነት እንዲኖረው ወደ ላይ መሆን አለበት:: ይህም ለሚመለከተው እንቅስቃሴያችን ድርጊታችን በመላው ሥርዓታችን ወንጌል የክርስቶስ መስቀል ሁኖ የተዋህዶን ምስጢር አስረጅ ለእኛም ለእግዚአብሔር ተብሎ የተለየን የዜማ መሳርያ የሚገባውን ክብር መስጠታችን ዋጋን የሚያሰጠን ነው::

በአጠቃላይ በዝማሬያችን የሌላውን ተመስጦ በማይነካ አንድ ወጥ በሆነ የእንቅስቃሴ ስልት በሙሉ ስሜታችን ይህን ታላቅ ምስጢር እያስተዋልን የመዝሙሩን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር መዝሙሩን በአንደበታችን እንዳኖረልን ተገንዝበን ልንዘምር ይገባል (ያዕ ፩:፰):: ሌላው በመዝሙር አገልግሎት ልናስተውል የሚገባን የምንዘምረው መዝሙር ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ነው:: ቤተክርስቲያን ሁሉ ነገሯ ሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ለምስጋናም የሚስማማውን ሰርታ አዘጋጅታለች:: በሃይማኖት ጸሎታችን አንዲት ቤተክርስቲያን ብለን እንደመሰከርን ወቅቱን ጠብቀን ከዕለቱ ጋር የሚስማማውን ብንዘምር የአባታችንን ቤት ያወቅን ለእናታችን ቤተ ክርስቲያንም ታዛዦች ነን::

ማጠቃለያ

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ ለሰዎች የሚቀርብ ‘ዝግጀት’ አይደለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ የሥርዓት አምላክ ነውና ለእርሱም የሚቀርብ መዝሙር በሥርዓት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም በሁሉ አገልግሎታችን እና ተሳትፎአችን መንፈሳዊ ዋጋ እንዲያሰጠን ዓመቱን በዘመናት ከፍላ በዝማሬያችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ባደረገና የቅዱሳን አባቶችን አሰረ ፍኖት በተከተለ አካሄድ ሰማያዊውን የዜማ ስልት ተከትለን አስተማሪነት ባለው ምስጋና እንድናመሰግን ሥርዓትን ሠርታልናለች:: እኛም በሁለንተናችን ትምህርቷን መስለን ለቤተክርስቲያንም ሥርዓት የመገዛት መንፈሳዊ ግዴታ አለብን:: በግልም ሆነ በማኅበር ስንዘምር ልናስተውላቸው የሚገቡንን እያስተዋልን፤ ዝማሬያችንም ፍጹም ለልዑል እግዚአብሔር የሚቀርብ ስለሆነ ‘መታዘዝ ከመስዋዕት ይበልጣልና’ በፍጹም ትህትናና በእምነት፤ ለቤተ ክርስቲያንም ሥርዓት በመታዘዝና ዋጋ የሚያሰጠን እንደሚሆን በማሰብ ሊሆን ይገባል:: የመዝሙሩ የምስጢር፣ ቅንብር እና የእንቅስቃሴ ስልት ምስጢሩን የጠነቀቀና ወቅቱን የጠበቀ ሆኖ የዝማሬም ሥርዓታችን ከቤተክርስቲያን ሥርዓት አንጻር በጾም በበዓላት በዘመናት መደብ ሰጥታ እንዳቆየችልን ሁሉ ሊዘመሩ የሚገባቸውን ዝማሬዎች እንደሥርዓቱ ልንከተላቸው ይገባል:: ለዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን  የተከተለ  የመዝሙር ሥርዓት እንዲኖር ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ::

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!

 

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፫)

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

ባለፉት ሁለት ተከታታይ የአስተምህሮ ጦማሮች ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንዳለበትና በግጥም መልእክትና ኪነ-ጥባበዊ ይዘት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን የሚመለከቱ ዳሰሳዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል ደግሞ ከዜማ ስልትና ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ይዳሰሳሉ፡፡

ከዜማ ስልት ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መለያ ከሆኑ መንፈሳዊ ጸጋዎች አንዱ በቅዱስ ያሬድ በኩል የተገለጠው የዜማ ሀብት ነው፡፡ የካሴት መዝሙራት የቅዱስ ያሬድን የዜማ ስልት በመከተል ካልተቃኙ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ ለዛቸው ይጠፋል፡፡ ይሁንና በርካታ የካሴት መዝሙር አዘጋጆች የቤተክርስቲያኒቱ ሀብት የሆነውን ያሬዳዊ ዜማ ባለማወቅ ወይም አውቆ ቸል በማለት፣ ለቤተክርስቲያን እንግዳ የሆኑ፣ መንፈሳዊ መሰረት የሌላቸው፣ ለንግድ ሲባል የሚሸቀጡ ዜማዎችን የመጠቀምን ልማድ እየጨመሩ እንደመጡ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በአሳፋሪ መልኩ የዘፈን ዜማ እየገለበጡ በመዝሙር ካባ ሲነግዱበት ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

የያሬዳዊ ዜማ መሠረቱና ምሳሌነቱ እንዴት ነው?

በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ ፸፬:፲፬ ተብሎ የተፃፈው ንባብ ከሚተረጎምባቸው ትንታኔዎች አንዱ የኢትዮጵያ መለያ የሆነው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ልዩ ስጦታና ለኢትዮጵያ የተሰጠ መላእክትን በምስጋናው መስለን የምንተባበርበት ነው:: ቅዱስ ያሬድ በብዙ ድካምና ጥረት ዜማን ተምሯል፣ ፈጥሯል፡፡ የጸጋ ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ያለመታከት ዜማን ለመማር፣ ለመፍጠር ይተጋ ለነበረው ለቅዱስ ያሬድ በቅዱሳን መላእክት በኩል ሰማያዊ ዜማ ገልጦለታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከመላእክት ያገኛቸው በመደብ ሦስት ይኸውም ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ሲሆኑ አንድ መሆናቸው የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ነው:: ትርጉማቸውም ግዕዝ በአብ ሲመሰል “ርቱዕ ሎቱ ነአኩቶ” ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን ማለት ነው። ዕዝል ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም አራራይ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን የሚያራራ ጥዑም ዜማ ማለት ነው። ጥዑም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተጎናጸፍን ለማስረዳት ነው። የቅዱስ ያሬድ የዜማዎቹ ባህርያት የፊደል ቅርጽ የሌላቸውና ምሳሌነት ያላቸው ፰ ዓበይት ምልክቶች (symbols) አሉት። የእነዚህም ምልክቶች ምሳሌያቸውና ምሥጢራቸው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ መንገላታት የሚያስታውሱ ናቸው።

የዘመናችን የአማርኛ መዝሙራት የዜማ ችግሮች ምንድን ናቸው?

በዘመናችን ያሉ በርካታ የካሴት መዝሙራት ካሉባቸው ችግሮች አንዱ ከዜማ ስልት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በምስጢር ይህን የመሰለ ሰማያዊ ስጦታና አስደናቂ የሆነ ያሬዳዊ ዜማ ግምጃ ቤት ሁና ሳለ ለምስጋና መዝሙር የሚሆን ዜማን ለገበያ ይመቻል ከሚል ሃሳብ ከሠርግ ቤት ዘፈን፣ ለንስሐ መዝሙር የሚሆን ዜማን ደግሞ ከለቅሶ ቤት ሙሾ መውሰድ እንደአባቶች አባባል ‘የአባይን ልጅ …’ ያሰኛል፡፡ የቤተክርስቲያን ለዛ የሌለው ‹‹ዜማም›› ቢሆን ገና ለገና ከሌላ ቦታ አልተቀዳም ተብሎ ቸል መባል የለበትም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት የሌለውን ዜማ ከሌላ ቦታ ወስዶ ለ‹‹ዝማሬ›› ማዋል መንፈሳዊነትን ከመጉዳቱም በላይ የዜማውን ባለቤት የባለቤትነት መብትም መጋፋት ነው፡፡ ስለዚህ በምድራዊም በሰማያዊም ሕግ ያስጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል የዜማ ስልታቸው ከመዝሙር ጋር የሚመሳሰሉ ተብለው በአጥኚዎች ከተቀመጡት መካከል ‹‹ሐና ዘመዴ፣ እመኑ በእርሱ፣ አምስቱን ሐዘናት›› የሚሉትንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም መልኩ ‘ማርያም ድንግል ንጽሕት’ በሚል የተዘመረ አንድ ዝማሬ ዜማው ከአንድ ዘፈን ጋር በቀጥታ ሲመሳሰል ሙሽራዬ የወይን አባባዬ የሚለው ደግሞ ዜማው ለመዝሙር ከዋሉት ዘፈኖች መካከል ይገኛል፡፡

የዜማ ችግሮች ያደረሱት ተጽዕኖስ ምንድን ነው?

የዜማ ችግር ያለባቸው ‹‹መዝሙሮች›› ከመብዛታቸው የተነሳ ወጣቱ ምዕመን ከያሬዳዊ መዝሙሮች ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ያሬዳዊ ባልሆኑ ‹‹መዝሙሮች›› እየተሳበ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ይህንን የለመደ ሰውም የዘፈን ቅላጼ ያላቸው ‹‹ዘማሪያን›› እነዚህን መዝሙሮች ሲዘምሩ ማየትና መስማትም ይናፍቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያኒቱን ዜማ የሚጠቀሙ መንፈሳዊ መዝሙሮች ቸል እየተባሉ መዝሙር መሳይ ዘፈኖች (አንዳንዶች ማኅበራዊ መዝሙራት ይሏቸዋል) እየበዙ መጥተዋል፡፡ ይህ አካሄድ በመጀመሪያ ደረጃ የምዕመኑን መንፈሳዊ ሕይወት ይሸረሽራል፡፡ ሁለተኛም የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት ያደበዝዛል፡፡ ሦስተኛም የሀገርን ታሪክንና ቅርስን ያሳጣል፡፡ ስለዚህ ጌታችን  “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሎ እንዳስተማረን (ማቴ ፮:፳፬) ዓለማዊ ዜማንና ያሬዳዊ ዜማን አንድ ላይ መጠቀም ስለማይቻል መንፈሳዊ የሆነውን ያሬዳዊ ዜማን ብቻ ልንጠቀም ይገባናል ።

የአንድ መዝሙር ዜማ ያሬዳዊ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የአንድ መዝሙር ዜማን ኦርቶዶክሳዊ ነው ወይም አይደለም ለማለት የቤተ ክርስቲያንን የዜማ ስልቶች በትክክል ማወቅን ይጠይቃል፡፡ እኛም ዘወትር ከምንዘምራቸው እና ከለመድናቸው መዝሙራት ለየት ያለውን ሁሉ ያሬዳዊ አይደለም ወደሚል ድምዳሜም እንዳንደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁን የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ዜማ ከመሰረቱ እንዳልለቀቀ ሊመሰክሩ የሚችሉት የዜማ ሊቃውንቱ ናቸው፡፡ የዜማ ችግሮችን ከምንጫቸው ለመከላከል የመዝሙር ዜማ ያሬዳዊ ዜማን በጠነቀቁ ሊቃውንት እንዲዘጋጅ ማድረግ ወይም በእነርሱ ታይቶ እንዲስተካከል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የሚዘምረው ዘማሪም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያሬዳዊ ዜማዎችን ያጠና መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለገቢ ምንጭነት ብቻ ሲባል ‹‹ሰላም ለኪ››ን እንኳን በዜማ ያልተማረ ሰው በካሴት መዘመሩ የመዝሙሮቻችንን የዜማ ችግሮች እየሰፉ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ የተሻለው ሀሳብ ሙያን ለባለሙያ መስጠት ቢሆንም ይህ ባይቻል እንኳ የመዝሙርን ዜማ ከዘፈን ጋር የሚያምታቱ፣ መንፈሳዊ መስዋዕት ከእንክርዳድ ሳይለዩ የሚዘምሩ ግን እግዚአብሔርን ፈርተው “የቄሳርን ለቄሳር፣ እግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” መስጠትን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሳርያዎች መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ገቢረ ተዓምርም የተፈጸመባቸው ናቸው (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: “ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል”(፩ሳሙ ፲:፭):: ቅዱስ ዳዊትም ለዝማሬ የሚያገለግሉትን የዜማ መሣርያዎች በዝርዝር አስቀምጧቸዋል:: “እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት። በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት። በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት። ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።” (መዝ ፻፶:፩-፮):: እኛም ቅዱሳኑ የተጠቀሙበትን የዜማ መሳርያ በመጠቀም ከነፍስ ቁስል የምንፈወስበት የምንረጋጋበት እንዲሆን ምስጢርም እንዲገለጥልን በምስጋናው በሃይማኖት እንደመሰልናቸው በዜማ መሳርያውም ልንመስል ይገባል::

በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈቀዱ የዜማ መሣርያዎች የትኞቹ ናቸው? 

በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑት የዜማ መሣርያዎች መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረጉ ሲሆን ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት: እምቢልታ፣ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የዜማ መሣርያዎች አስተማሪነት እንዲኖረው እኛም በመንፈሳዊ ተመስጦ እንድናመሰግን እንዲህ ባለ ምሳሌነት ታስተምረናለች:: ለምሳሌ ከበሮን ስናይ በመጽሐፍ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮ ይዛ እንዳመሰገነች እንማራለን (ዘጸ ፲፭:፳):: አሰራሩ ምስጢዊ ይዘት እንዲኖረው ልዩ የማህሌት መሳርያ ስለሆነ ከበሮን በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት፣ ሽፋኑ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ የሸፈኑበት ግምጃ፣ ድምጹ የወንጌል፣ ጠፍሩ ጌታችን የመገረፉና በሰውነቱ ላይ የወጣውን ስፍር ቁጥር የሌለውን ሰንበር ምሳሌ፣ ማንገቻው የተገረፈበት ጅራፍ ወይም የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ በማለት ያስረዳል::

በተጨማሪ እንደምሳሌነት ከምንወስዳቸው የዜማ መሣርያዎች በመሳርያነቱ ከእስራኤላውያን ቀጥሎ ለኢትዮጵያውያን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ የዜማ መሳርያ በገና ነው:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ከተቀባ በኋላ ከተሰጡት ሰባት ሀብታት ውስጥ አንዱ ሀብተ በገና ነው። ይህም በገና ሀብተ ፈውስ ያለው ቅዱስ ዳዊት ሲደረድረው ርኩሳን አጋንንት ይርቁ እንዲሁም በሽተኞችም ይፈወሱ እንደነበር ያስረዳናል (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: ይህን ገቢረ ተአምር በመስራት የሚታወቀውን የዜማ መሳርያ ቀደምት አበው ከፍጥረት ሰባተኛ ትውልድ ጀምሮ እንደተገለገሉበት የቤተ ክርስቲያንም ሊቃውንት ቃለ በገናን ድምጸ ማኅዘኒ- ‘የሚያሳዝን ድምጽ’ በሚል ይህም በዮባል ልጆች ኃዘን ምክንያት እንደሆነ ያትታሉ:: ይህም የዜማ መሳርያ ልክ እንደ ከበሮ የራሱ ምሳሌያዊ ትምህርቶች አሉት:: የበገናውን ቅርፅ ስንመለከት ላይኛውና ታችኛው የፈቃደ እግዚአብሔርና የማኅፀነ ድንግል (አንድም የሰማይና የምድር) ግራና ቀኙ የሚካኤልና የገብርኤል (አንድም የብሉይና የሐዲስ) አሥሩ አውታር የዓሠርቱ ቃላት (ትእዛዝ) በሚል ይዘረዝረዋል:: ቤተ ክርስቲያን ሌሎችንም የዜማ መሣርያዎች እንዲሁ የክርስቶስን የማዳን ስራውን እንድናስብ በህሊናችን እንድንስል (ገላ ፫:፩) በምድር ያለን ነገር ግን ፍጹም ሰማያዊ በሆነ ስርዓት ታስተምረናለች::

ማህሌት.jpg

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን በኦርጋን መዘመር ተገቢ ነውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ጊዜውን መዋጀት” በሚል የተሳሳተ መረዳትና “ቴክኖሎጂን እንጠቀማለን” በሚል ትርጉም ኦርጋን እና ጊታር ለመጠቀም የሚፈልጉ ለዚህም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ድጋፍ ያደረገ በማስመሰል ምእመናንን የሚያደናግር ትምህርት ያላቸው አሉ:: ቴክኖሎጂን በመጠቀም ድምጽን እንዲሰማ በዜማ ቀረጻ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለታሪክ ማስቀመጥ እንዲሁም ስራው አድካሚ የሆነ የዜማ መሳርያን በሰለጠነ አሰራር መንፈሳዊ ይዘቱን ባልለቀቀ መልክ እንዲሆን ማድረግ ቢገባ እንጂ የዜማ ቃናውን የመሳርያውን አስተማሪነትና  ትውፊታዊ አጥፍቶ ሊሆን አይገባም:: በ፲፱፻፹፮ ዓም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት በመዝሙር አገልግሎት ከተዘረዘሩት የዜማ መሣርያዎች ወጥቶ “በኦርጋን ልዘምር” የሚል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የጣሰና የቅዱሳን ሐዋርያትን ትእዛዝ እንደጣሰ ሁኖ ከምእመናን የተለየ ነው:: አንዳንድ ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ ይህንኑ ዜማ መሳርያ በማህለቱና በቅዳሴ ጊዜ እንዴት እንደሚውል ያስረዳሉ:: በቤተክርስቲያን ድምጽ ካላቸው ንዋያት ቃጭል ብቻ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት እንደሚውል ከበሮ መቋሚያ እና ጸናጽል የማህሌት ማሳርያዎች ሲሆኑ ሌሎቹም በማኅበርና በግል መዝሙር እንጠቀምባቸዋለን:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን እንዳለ ለእኛም ስንዱ እመቤት ከሆነች ቤተ ክርስቲያን የተሰራልንን ስርዓት መጠበቅ በዚያም መጽናታችን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የመታዘዝ መስዋዕት ነው::

ዜማንና የዜማ መሣርያን በሚመለከት ቀዳሚው መልእክት

የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የዜማ ስልትና የዜማ መሣርያዎችን ስናስብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረታቸውን፣ ታሪካዊ ገጽታቸውን፣ ምስጢራዊ አስተማሪነታቸውንና እንዲሁም ትውፊታው ጠቀሜታቸውን በማስተዋል እንደአባቶቻችን ቆመን ልንገኝ ይገባል እንጂ አባቶች ከሠሩልን ድንበር ወጥተንና የዘመናዊነትን ካባ ደርበን ማንነታችን በማይገልፅና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዲሁም ፍጹም አስተማሪነት በሌለው የዜማ መሳርያ ልንገለገል አይገባም:: “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” (ዮሐ፲:፳፯) እንደሚል እኛም እንደ አባቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረገውን ያሬዳዊ ዜማ እና የዜማ መሣርያ አጠቃቀምን የሚመለከተውን  የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተቀብለን ብንጠብቅ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራችን እንደ አባቶቻችን ወደ መላእክቱ ኅብረት የምንነጠቅበት ይሆናል::

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር: ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፩)

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

“መመካት ቢያስፈልግ ዓለምን የሚያስደምመው ያሬዳዊ ዜማ ኢትዮጵያውያን ትምክህት ነው፡፡”

መንፈሳዊ መዝሙር ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ከምታወርሳቸው ሀብታት አንዱ ሲሆን ለአምልኮትም ታላቅ ድርሻ ያለው ነው:: መዝሙር  ቅዱሳን ሊቃነ መላእክትና ሰራዊቶቻቸው ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ያለዕረፍት የሚያመሰግኑበት ነው (ኢሳ ፮:፩-፭ ኢዮ ፴፰:፮):: መዝሙር ሰውና መላእክት ዘወትር ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ለማመስገን እንደተፈጠሩ እንዲያመሰግኑበትም የተሰጣቸው ልዩ ሀብት፣ ሰማያዊ ዜማ ነው:: አስተምህሮ ባለፉት ሳምንታት ወቅቱን አገናዝባ ለሐዋርያት የተሰጣቸውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳስገነዘበችን በዚህ ዓምድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተሰጣትን ሰማያዊ የምስጋና ስጦታ የሆነውን የመዝሙር ሥርዓትን ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንና እና አገልጋዮች እንዲረዱት በጥቂቱ እናቀርባለን::

እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ ከጸሎትና መጽሐፍትን ከማንበብ ጋር መዝሙር በመዘመር እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ እንዲሁም በመከራቸው ጊዜና ከድል በኋላ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን አስበው በመዝሙር ምስጋናን ያቀርቡ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል (ዘጸ ፲፭:፩-፳ ዘዳ ፴:፲፱ ፴፩:፲፬ ኢሳ ፩:፪ መሳ ፬:፩ መሳ ፭:፫):: በሐዲስ ኪዳንም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከነበሩት ድንቅ መንፈሳዊ ገጽታዎች ቀዳሚውና ዋናው በምስጋና ለዘመናት ተለያይተው የነበሩ ሰውና መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ:- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በሚል በአንድነት ባቀረቡት የምስጋና መዝሙር ነው (ሉቃ ፪:፲፪):: መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ወደ ደብረዘይት ከመውጣታቸው በፊት መዝሙርን አስተምሯቸዋል፤ ዘምረዋልም (ማር ፲፬:፳፮):: ስለዚህም የመዝሙር አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ከጸሎት ከስግደት ከጾም ጋር በሥርዓተ አምልኮታችን ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው::

፩.መንፈሳዊ መዝሙር ምንነቱና ጥቅሙ

መዝሙር ‘ዘመረ’ ‘አመሰገነ’ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና፣ ልመና፣ ማዜም ማለት ነው፡፡ መዝሙር በግልና በኅብረት የሚዘመር፤ ጌታችን ሰውና መላእክት በአንድነት እንደዘመሩ ታናሽ ታላቅ ሳይል ሁሉንም የሚያሳትፍ፤ ዝማሬውም በልዑል እግዚአብሔር ፊት ቆመን አምላካችንን የምናመሰግንበት የምናወድስበት በቁመታችንም ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚያመሳስለን መንፈሳዊ ተግባር ነው (ራዕ ፲፱:፭፣ ፩ቆሮ ፲፬:፪፮):: መዝሙር ለክርስቲያን የዘወትር ተግባር እንደመሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መሠረትነት ጥቂቶችን ምሳሌ አድርገን እንማራለን::

መንፈሳዊ መዝሙር እግዚአብሔርን በቅኔ በሚያምር ዜማ የምናመሰግንበት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” እንዳለ በዚህ የመንፈሳዊ ተግባር እግዚአብሔርን በቅኔ በሚያምር ዜማ እናመሰግነዋለን፤ እናወድሰዋለን (ኤፌ ፭:፲፰-፳):: ቅዱሳን መላእክትም በቤተልሔም በጌታችን ልደት በደስታ እንዳመሰገኑ፣ ትንሣኤውን በምስጋና እንዳበሰሩ፣ ዕርገቱን በምስጋና እንዳጀቡ፣ ዳግም ምጽአቱንም በምስጋና እንደሚያውጁ ሁሉ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተክርስቲያንን ያለማቋረጥ ያገለግሏታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ: ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና” እንዳለ እኛም እንደቀደሙት አባቶች እግዚአብሔር ለኛ ያደረገውን እያሰብን ዘወትር ቀንና ሌሊት በመዝሙር እናመሰግነዋለን:: (መዝ ፵፮:፮-፯)::

መንፈሳዊ መዝሙር የሚያበረታንና የሚያጸናን መንፈሳዊ ኃይል ነው፡፡ መዝሙር በሃይማኖት መከራ ድካም ሲገጥመን ከድካማችን የሚያበረታን፣ መከራን እንዳንሰቀቅ እንዳንፈራ የሚያጸናን የሚያበረታን መንፈሳዊ ኃይል ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በእስር ሳሉ በጸሎት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን በዝማሬም ያመሰግኑ ነበር (የሐዋ ሥራ ፲፮:፳፭):: ዛሬ ላይ በሕይወታችን፣ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ፈተና ሲገጥም በራሳችን ጥበብ በመታለል ሳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትግላችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ጋር ስለሆነ ምድራዊ የሆነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በማድረግ በዝማሬ የእግዚአብሔርን ኃያልነት በመግለጥ ሊሆን ይገባል:: በመዝሙር “በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ሰማኝም።” (መዝ ፻፲፱:፩) እንደሚል፥ ረሃብ ቸነፈር ጦርነት የተፈጥሮ አደጋዎች መንግስት በመንግስት ሕዝብም በሕዝብ ላይ ክፋትን ሲያደርግ በማመስገን የእግዚአብሔር የመከራው ጊዜ እንዲያበቃ እንዲያጥር እንደ ነቢያትና ሐዋርያት ሕይወትም በመዝሙር ወደ እግዚአብሔር መጮህ ለክርስትያኖች የእግዚአብሔርን ኃያልነት የመመስከር እንዲሁም ሐዋርያትን የመምሰልም መገለጫ ነው::

መንፈሳዊ መዝሙር እግዚአብሔር ለእኛ ስላደረገው ሁሉ ደስታችንን የምንገልጽበት ነው:: ‘ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር’ እንዲል (ያዕ ፭: ፲፫):: በመከራና በችግራችን ወቅት ስሙን ጠርተን የለመነውን አምላክ በድልና በደስታችን ጊዜ አብዝተን ልንዘምር እንጂ ልንዘነጋ አይገባም:: እስራኤል በግብፅ ከነበረው መከራ ሲወጡ የአምላክን ታዳጊነት የእስራኤልን ድኅነት በመመልከት ሙሴና ተከታዮቹ በተለይም እኀቱ ማርያም በከበሮ ድምፅ እየታጀቡ በጣዕመ ዜማ “ንሴብሆ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ:-በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ” በማለት ዝማሬን አቅርበዋል (ዘጸ ፪:፩-፲):: ዛሬም በሰርግ በበዓላት በድል ወቅት የቅዱሳንን ተጋድሎና ህይወታቸውን እያሰቡ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን እያደነቅን በሚያምር ለምስጋና በተለየ የዜማ ስልት መዘመር ይገባል::

 ፪. ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርና መገለጫዎቹ

ቅዱሳን አባቶቻችን የሕይወት መስዋዕትን ከከፈሉባቸው አንዱ ትልቁ ርስት ዜማና የዜማ ሥርዓት ነው፡፡ የቀደሙት አባቶች እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንድናከብረው የወሰኑልንን የዝማሬ ሥርዓት ድንበር ሳናፈርስ መንፈሳዊ ዜማና ሥርዓቱን አባቶቻችን ከእግዚአብሔር እንደተቀበሉ በዚህም ምስጋና ከእርሱ ጋር እንደተገናኙ እኛም “በነቢያትና በሐዋርያ መሠረት ላይ ታንጻችኋል” እንደተባልን ከቀደምት አባቶች መሰረት ሳንለቅ ሠርተው ባስረከቡን ወደ ሰማያዊው ኅብረት በምንነጠቅበት የዜማ ሥርዓት ልንጸና ይገባል (ኤፌ ፪:፳ ምሳ ፳፪:፳፰)፡፡

ከቀድሞ ጀምሮ እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛይቱን ሃይማኖት ባጸኑ በነቢያት በሐዋርያት ላይ እያደረ ምስጢርን ገልጾላቸዋል:: በአስተምህሮ ባለፉት ሳምንታት መልዕክት እንደተማርነው ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የተሰወረው ተገልጦላቸው ፍጹም የሆነውን አገልግሎት ጀምረዋል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ትውፊትና ባህል ተቀብላ በታላቁ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ከእግዚአብሔር በተሰጣት ልዩ የዝማሬ ጸጋ ታመሰግናለች::

Qidus Yared.jpg

ቅዱስ ያሬድ ይህን ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከመቀበሉ በፊት በትምህርቱ ተስፋ ቆርጦ፤ እግዚአብሔርም ከስነ ፍጥረት እንዲማር አድርጎት፤ ቅዱስ ያሬድም ራሱን ገስጾ ድካምን እንዲታገስ እውቀትንና ጥበብን እንዲገልጽለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ፤ ጌታችን “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ ፲፮:፲፫) ብሎ እንዳስተማረን በሰው ጥበብ መረዳት የማይቻለውን በአንድ ቀን መዝሙረ ዳዊትን የጸሎት መጻሕፍትንና ትርጓሜ መጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳትን ማወቅ ተሰጠው:: የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ለመቀበል የሰው ልጅ በአቅሙ መጣር እንዳለበት ከሚያስተምሩን ህያው ምስክሮች አንዱ አባታችን ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ሰማያዊ ዜማ የተገለጠለት ሳይጥር፣ ሳይደክም አልነበረም፡፡ ሰባት ጊዜ እየወደቀ እየተነሳ፣ በእግዚአብሔር ኃይል እየታገዘ ለበለጠው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተገባ ሆነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ያሬድ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሁኖ ካህናተ ሰማይ መላእክት በተቀደሰ ዙፋኑ ዙሪያ ከፍ ባለ ዜማ የሚያመሰግኑበትን የዜማ ሀብት የተሰጠው የቤተክርስቲያን ዓምድ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ማኅሌተ እግዚአብሔርን ሲያደርስ ንጉሥ ገብረ መስቀል በጣዕመ ዜማው ስለተሳቡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ መትከላቸውና ቅዱስ ያሬድም ከእግሩም ደም መፍሰሱን ማሕሌቱ እስከሚፈጽም ድረስ አልተሰማውም ነበር፡፡ ይህም ጣዕም ያለው ሰማያዊ የዜማ ስልት ቤተክርስቲያን ዘወትር ጧትና ማታ በስብሐትና በማኅሌት በቅኔ በሰርክ የምታመሰግንበት ነው::

mqdefault

ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ ይዘው በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑት ቅዱስ ያሬድ በምስጋናው ልዑል እግዚአብሔርን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያለ በማመስገኑ ምስጋናውንም የተማረው ከመላእክት መሆኑን በድርሰቱ መስክሯል፡፡ በዚሁም ቤተ ክርስቲያን “አምሳሊሆሙ ለሱራፌል”:- የሱራፌል አምሳላቸው ትለዋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሃልዎተ እግዚአብሔርን ፍጥረተ ዓለምን በአጠቃላይ መሠረተ ሃይማኖትን ነገረ ድኅነትን ክብረ ቅዱሳንን መሠረት አድርጐ በሦስት የዜማ ስልቶች (ግዕዝ፣ዕዝልና አራራይ) ላይ ተመሥርቶ ዘምሯል:: ምድራውያን ካህናት ሰማያውያኑን መስለው ማዕጠንትና መስቀል ይዘው በምስጋና በመንበሩ ፊት ቆመው ማመስገናቸው ይህን መንፈሳዊ ጸጋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር እንደተቀበለችና ይህንንም ስጦታ በክብር እንደጠበቀችው ያስገነዝበናል:: የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተለይታ ከምትታወቅባቸው እና ለኢትዮጵያም ካበረከተቻቸው እሴቶች አንዱ ይህ የዜማ ስጦታ ነው። መመካት ቢያስፈልግ ዓለምን የሚያስደምመው የያሬዳዊ ዜማ ለኢትዮጵያውያን ትምክህት ነው፡፡

አንድን መዝሙር ኦርቶዶክሳዊ ነው የሚያሰኙት የመዝሙሩ መልእክት ፣ የዜማ ስልቱ፣ የዜማው መሳሪያ፣ እንዲሁም ዝማሬውን የምናቀርብበት መልክ ሥርዓቱን ጠብቆ መንፈሳዊነትን ተላብሶ የተገኘ ሲሆን ነው::

፪.፩. የመዝሙሩ መልዕክት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

አንድን መዝሙር ኦርቶዶክሳዊና ልብን የሚመስጥ ነው የምንለው ሌላው እይታ የመዝሙሩ ግጥም መሠረተ ሃይማኖትንና ምስጢርን የጠነቀቀ፤ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ትውፊትና ባህል የጠበቀ ሲሆን ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የምስጋና መስዋዕት በተዋጣለት ድርሰትና ዜማ በነግስና በመልክ ጸሎት እንዳለው በግጥም መልክ መልእክቱንም የተከተለ በምስጢርም የጠለቀ እንዲሆንና ይበልጥ ደግሞ በቅኔ መንገድ ቢቀርብ የበለጠ ይስማማል:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ሁላችን የመዝሙርን መልእክት መመርመር ይገባናል፡፡ መዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይሆን ትምህርትም ስለሆነ ትርጉሙም ከቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር የማይቃረን እንዲሁም ግጥሙ እንደ ሰምና ወርቅ ምስጢርን ጠብቆ የተቀመመ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በቅዱሳት መጻሕፍት የብሉያትንና ሐዲሳትን ምስጢር ጠንቅቆ የተረዳ ስለነበር በዜማ ድርሰቱም ቤተክርስቲያንን በምስጋና ያስጌጠ ዛሬም ላይ ላለው አገልግሎት መንፈሳዊ ተመስጦን የሚያላብስ እንዲሁም ሲሰሙት አጥንትን የሚያለመልም ነው::

በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን እምነቷን የምትገልጽበት ስያሜዎችን የምትሰጥበት በዘመን የማይተኩ መሰረቷን የሚያስገነዝቡ ዕንቁ የሆኑ ቃላትና አገላለጽ አላት:: ዛሬ ላይ በካሴት ተቀርጸው መዝሙር ተብለው በሚወጡ ነገር ግን ፈር የለቀቁ ከቤተክርስቲያን አገላለጽ የወጡ ሥም አጠራሩ የከበረ አምላካችንንና ያከበራቸው ቅዱሳንን ክብር የሚነኩ ወይም የሚያሳንሱ መዝሙሮች ይሰማሉ:: ለምሳሌ በዘወትር ጸሎት መግቢያ ላይ እንደምናየው ቤተክርስቲያን ለጌታችን መጠሪያ እንደቀደምት አበው “የአምላኮች አምላክ የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ” እንላለን እንጂ ይህን ኦርቶዶክሳዊ አጠራርን ትተን ክብርን በሚያሳንስ አጠራር አትጠራውም፡፡ በሌላውም የዝማሬው መልእክት ተስፋ መቁረጥን፤ ምድራዊ ተስፋን፤ ሥጋዊ ድልን በማሰብ የሚደርሱ ናቸው:: እነዚህ ድርሰቶች አስተማሪነት የሌላቸውና የክርስትናን ዓላማ ፈጽሞ ካለመረዳት የቀረቡ ናቸው:: ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም “ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” ብሎ እንዳስተማረን የዝማሬያችን መልእክት ምስጢርን የጠነቀቀ እንጂ በጥሬ ንባብ ብቻ የቀረበ እንዳይሆን ማጤን ያስፈልጋል (፪ቆሮ ፫:፮)::

 ፪.፪. የዜማው ስልት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ያሬዳዊ የዜማ ስልት የተከተለ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በየጊዜው የተነሡ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አባቶች ለመዝሙር ይገለገሉበት የነበረው የዜማ ስልት የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ ለምሳሌ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ድርሰት ብንመለከት ሰዓታቱን እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ የሰጠንን ስጦታ በመጠቀም በያሬዳዊ ዜማ ዘመሩት እንጂ ሌላ ዜማ ለመፍጠር አላስፈለገም:: በመሰረታዊው የጸሎት ስርዓት ቤተክርስቲያን ወቅቱን ያገናዘበ የዜማ ስልት ተከትላ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች:: በቅዳሴ ሥርዓት በጾም ወራት በግእዝ የዜማ ስልት እንዲሁም በበዓላት ጊዜ በዕዝል የዜማ ስልት ይከናወናል፡፡ በዚሁም መሠረትነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባወጣው ደንብ መሰረት መዝሙራት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የሰጣትን የዜማ ስልት የተከተሉ እንዲሆን ደንግጓል፡፡ በአጠቃላይ የያሬድ ዜማዎች በምንዘምረው መዝሙር ላይ እንዲውል እንደ አባቶቻችን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል::

፪.፫. የዜማ መሳሪያዎች: 

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተፈቀዱ የዜማ መሣሪያዎችን የሚጠቀም መሆን ይጠበቅበታል፡፡

እግዚአብሔር ልዩ መስዋዕትን ይፈልጋል፡፡ መዝሙርም ከልብ የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ በቁሳቁስ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ይሁንና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማስፋት የዜማ መሳሪያዎችን መጠቀም ዓላማውን እስከጠበቀ ድረስ ከመንፈሳዊ መስመር አያስወጣንም፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መሰረትነትም የተመሰከረ ነው፡፡ ለኦርቶዶክሳዊ መዝሙር የምንጠቀምባቸው መሳሪያዎች መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸው፣ ለመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተመረጡ ናቸው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ (መዝ ፹፩:፪) “ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር” በማለት ለምስጋና የሚስማሙ የዜማ መሣሪያዎች እንዳሉ ያስረዳናል:: ቅዱስ ያሬድ ዜማን ከመላእክት እንደተማረ እንዲሁም በርካታ ሊቃውንትም ይህንን ሰማያዊ ዝማሬ መሰረት ያደረገ የዜማ መሣሪያዎች እንደተጠቀሙ የቤተክርስቲያን ትውፊት ያስተምረናል:: እነዚህም የመዝሙር መሳሪያዎች ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውና መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከበሮ መቋሚያ እና ጸናጽል የማህሌት መሳርያዎች ናቸው:: ቅዱስ ሲኖዶስ በ ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በግንቦት ወር ላይ ባደረገው ጉባዔ መዝሙር በዋሽንት በከበሮ በጸናጽል በመሰንቆ በበገና በእምቢልታ እንድንገለገል አዟል::

ከበሮ

እነዚህ የዜማ መሳሪያዎች ገድል የተሰራባቸው ገቢረ ተአምር የተፈጸሙባቸው ስለሆኑ የተቀደሱ ንዋያተ ማህሌት መሆናቸውን አውቀን በክብር በንጽህና ልንጠብቃቸው ይገባል:: ይህም የምስጋና የማህሌት መሳሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት ያለው ነው:: “መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እግዚአብሔር ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው” (፪ዜና ፭:፲፪-፲፬ ፪ዜና ፳:፩-፴)። ስለዚህ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለውን የዜማ መሣሪያዎች ወደ ውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል ስለሚያስነቅፍ በተለያዩ መድረኮችም እነዚህን የቤተክርስቲያን የሆኑትን ንዋያት ቦታው በሚፈቅደው ሕግ ልናስከብር ይገባል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/::

፪.፬. የአዘማመር ሥርዓት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

እግዚአብሔር ትሁትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብን የምስጋና መስዋዕት ይመለከታል:: ቃየልና አቤል በእግዚአብሔር ፊት መስዋዕትን እንዳቀረቡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና መስዋዕቱ እንደተመለከተ ይነግረናል እንጂ መስዋዕቱን ብቻ አላለንም እኛም የከንፈራችንን ፍሬ በመዝሙር በተመስጦ በተሰበረ ልብ ሆነን ከማን ፊት ለማን ምስጋና እንደምናቀርብ በመገንዘብ በመዘመር ወቅት መዘመራችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ልብ የሚመረምር አምላክ ፊት እንደቆምን ልናስተውል ይገባል (ዘፍ ፬:፬):: ክቡር ዳዊት ‘እዘምራለሁ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ” (መዝ ፻:፪) እንዳለ እግዚአብሔር ከዜማው በፊት የሚያዜመውን ሰው ሕይወት ይፈልጋልና እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት “በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” (፩ጢሞ ፪:፰) በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምረናል::

መዘምራን.jpgስንዘምርም የምንዘምረውን አውቀን ዜማውን ብቻ ሳይሆን ቃሉን በማስተዋል የመዝሙሩን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር መዝሙሩን በአንደበታችን እንዳኖረልን ተገንዝበን ራሳችንን ልንመክርበት ልንገስጽበት መሆን አለበት:: መዝሙሩም የምእመናንን ልብ በዝማሬው ለቃለ እግዚአብሔር የለሰለሰ እንዲሆን የሚያዘጋጅ መሆን አለበት:: ዝማሬያችን በአንዳንድ ቦታዎች እንደሚታየው ከቤተ ክርስቲያን ባልተለመደ ሥርዓት ዓይንን ጨፍኖ እጅን ያለሥርዓት በማወዛወዝ በሥጋዊ ስሜት የሚቀርብ ወይም ባህላዊ ዘፈንን በሚመስል መልኩ ሳይሆን ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ‘አቤቱ አይኖቻችንን ወደ አንተ አቀናን’ እንዳለው አሰላለፋችንና እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን በመረዳት ወንጌልን የሚሰብክ በአገባብና በሥርዓት ሊሆን ይገባል (መዝ ፻፵፪:፮ መዝ ፭:፫ ፩ቆሮ ፲፬:፵)::

ከዚህ በተጨማሪም የዘማርያንም ሕይወት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነትና ምግባር የሚሰብክ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከመዝሙሩ መልእክት፣ የዜማ ስልት፣ የዜማ መሣርያና የአዘማመር ሥርዓቱ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊትን የጠበቀ ከመሆኑ ተጨማሪ የዘማርያኑ ሕይወትም እንዲሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነትና ምግባር የሚሰብክ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ መዝሙር የተወደደ መስዋዕት ስለሆነ መስዋዕቱን ከማቅረብ አስቀድሞ ራስን ማዘጋጀት ይገባል መስዋዕቱም እንዲሰምር ከዝማሬ መስዋዕት በፊት የራስን ሕይወት በመመርመር የምስጋናው ባለቤት በልዑል እግዚአብሔር ፊት እንደሚቀርብ አውቆ በትህትና በመልካም ሕይወት ማቅረብ ያስመሰግናል፡፡

ማጠቃለያ

አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመፈጸም የቤተክርስቲያንን ሥርዓት መማር ማወቅ ይኖርብናል:: መንፈሳዊ ዜማ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ይህም በመላእክቱ የሚደርስ ከሥጋዊ ስሜት ያልሆነ ልዩ የዜማ ስልት ያለው ማለት ነው:: ለኢትዮጵያውያን ይህ መንፈሳዊ ስጦታ በታላቁ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የተሰጠንና ይህም ስጦታችን ልዩ የዜማ ስልትና ምልክት ያለው ዜማ ነው፡፡ በዚህ ዜማ ልብን በሚማርከው መንፈስን በሚቀድሰው ዜማ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን እናወድሳለን፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘን የምንማረው ለኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ንጉሡ አክዓብ የአባቶቹን ርስት ወስዶ ሌላ ርስት ልስጥህ የሚል ጥያቄን አቅርቦለት ነበር:: ናቡቴ ግን የአባቶቹን ርስት ከመሸጥ ሞትን ነበር የመረጠው:: ናቡቴ ለዚህ ምድራዊ ርስት ይህን መስዋዕት ከከፈለ ዛሬ ላይ ሰማያዊ የሆነውን ስጦታ ቀደምት አባቶች መስዋዕት የሆኑለትን ይህን ሥርዓት ምድራዊ በሆነ አመክንዮ ዜማን ከንግድ ጋር ማያያዝ ለሥጋ በሚመች ስልት በሚቀርብ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ባህል ካልሆነ አገልግሎት ተጠብቀን አባቶቻችን እንደተቀደሱበት ከመላእክቱ ጋር በምስጋና እንደተባበሩ እኛም ተባብረን በምስጋና ሥርዓታችን ከኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት ሳንወጣ ዋጋ የምናገኝበት ሊሆን ይገባል:: የምንዘምረው መዝሙር በቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አባቶች እንዲሁም መምህራን የታረመ ሊሆን ይገባል:: የቤተክርስቲያን መዝሙር የዜማው ባሕልና መሣሪያዎቹ ፍፁም መንፈሳዊ መልእክት ያለው ነውና ይህንንም ታላቅ የሃይማኖት አደራ ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅብናል፡፡

ማኅበረ መላእክት ያለማቋረጥ በትጋት እግዚአብሔርን ያለእረፍት በደስታ እንደሚያመሰግኑ እኛም ረድዔታቸውን እየተማጸንን ሰማያዊ በሆነው የዝማሬ ምስጋና እንድንተጋ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን።

ክፍል ፪ ይቀጥላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ኒቆዲሞስ፡ የትህትና፣ የትጋትና የጽናት አብነት

የኒቆዲሞስ አብነትblue

በዲ/ን  ብሩክ ደሳለኝ (ዶ/ር)

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ ማለት “አሸናፊ/ነት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ሰንበት በዮሐ 3፡1-21 እንደተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ አስተማሪ ስብእና ይነበባል፣ ይተረጎማል፣ ይዜማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ የሰባተኛ ሣምንት መንፈሳዊ ድርሰቱ የኒቆዲሞስን በዓል አስመልክቶ ሲዘምር “ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ ክርስቶስ/ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምሕር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ/ ብሏል፡፡ ይህም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት የሚያመሰጥር ድንቅ ዜማ ነው፡፡ የዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ዓላማም ከኒቆዲሞስ ሕይወት መማር እንችል ዘንድ የኒቆዲሞስን ጠንካራ ስብእና እና መንፈሳዊነት የሚያሳዩ መገለጫዎችን መተንተንና እኛም አርዓያውን እነድንከተል መምከር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኒቆዲሞስ ሕይወት የምንማራቸው ቁም ነገሮችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

አትኅቶ ርዕስ (ራስን ዝቅ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በህዝቡ ላይ የሚመፃደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡ ባለማወቅ ያደነደኑት የትዕቢት ልቦና ትህትናቸውን አጥፍቶባቸው ነበርና ዝቅ ብሎ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሰሩ አስጠንቅቋቸዋል (ማቴ 5: 20 ማቴ 16:6)፡፡

ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙርያው የነበሩት ከእኛ በላይ ማን አዋቂ አለ የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱ በእርሱም የሚቀኑና ጌታችንንም ለመግደልም ዕለት ዕለት የሚመክሩ ሁነው ሳለ ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትህትናውን ተቀብሎ ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡

አልዕሎ ልቡና (ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ ዳግመኛ የመወለድን ምስጢርን ለማወቅ ልቡናውን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡

ለሥጋዊ ሕይወታችን እውቀት እንደሚያስገፈልገን ሁሉ ነፍስም ዕውቀት መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልጋታል (ምሳ. 19፥2)፡፡ ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ ምእመናንን በማነቃቃት ልቡናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ “አልዕሉ አልባቢክሙ/ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” ብሎ የሚያዘው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምስጢር እንዲገለጽልን፣ ከሥጋዊው መብል ሃሳብ ወደ ሰማያዊው መብል ልቡናችንን እንድናነሳ ሲያሳስብ ነው፡፡ ምእመናንም በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ የቅዱስ ኤጲፋንዮስን ትዕዛዝ ሲያሰማ “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” በማለት እንመልሳለን።

መንፈሳዊ መረዳት የሚኖረንና በፈተናዎች ውስጥ ድል መንሳትን የምናገኘው ልቡናን ከፍ በማድረግ ከሁሉም የሚበልጠውን መንፈሳዊውን መንገድ በመከተል ነው፡፡ ግያዝ ከነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ ልቡናው ቁሳዊውን የሚመለከት እንጂ ሰማያዊውን ኃይል የተረዳ አልነበረም፡፡ ነብዩ ኤልሳዕ ግን ይህንን ምስጢር እንዲያይ ገለጸለት (2 ነገ 6:17)፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በጸጋ የተሰጡንን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ልቡናችንን ከፍ ከፍ አድርገን በመንፈሳዊ እውቀትና ልዕልና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት፣ እንዴት በጽድቅ መመላለስ እንዲገባንና ስለምንወርሳት መንግስተ ሰማይ መማር ማወቅ ይገባናል፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ምሳ 9፥11) ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትህትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡

ትግሃ ሌሊት (በሌሊት መትጋት) – ኒቆዲሞስ ቀን እየሠራ በሌሊት ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት ሆነን፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ መድኃኔዓለም ለመማር የሄደው በሌሊት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም ሰንበት በጸሎተ ቅዳሴ የሚዜመው የክቡር ዳዊት መዝሙር  “ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው/በሌሊት ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ፈተንኸኝ፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር” (መዝ. 16፡3)ይህን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሌሊት በባህሪው ሕሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው፡፡ ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን (አባ ቢሾይ) በሌሊት ጸሎት እንቅልፍ እንዳያስቸግራቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ በማሰር ይተጉ ነበር፡፡ ለኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን መምጣት ልጅነትን ለምናገኝበት የምስጢረ ጥምቀት ትምህርት እንደተገለጠለት እኛም በሌሊት በነግህ ጸሎት በመትጋት ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ እውቀት ሰማያዊ ምስጢር ይገለጥልናል፡፡

በዘመናችን ከቀድሞ ይልቅ ፈተና የሚገጥመን በሌሊት ከመትጋት ይልቅ አርአያነት በጎደለው ሕይወት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡ “ሌሊት ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው” እንዳለ ሊቁ ማር ይስሐቅ ራስን በቀንም በሌሊት ከሚመጣ ፈተና መጠበቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንደተናገረው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማንም እንዳይረታው፣ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከእርሱ ጋር እንዲኖር “ለአባቶቻቸው እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የማለላቸውን ምድር እንዲወርስ በሚሔድበት ሁሉ እንዲከናወንለት ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳይል ሃሳቡም እንዲቀና የምጽሐፉን ሕግ ከአፉ እንዳይለይ እንዲጠብቀውም በቀንም በሌሊትም ማሰብ እንደሚገባ ይነግረናል (ኢያ 1:1-8):: ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ “ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ጸሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ እደር’ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።” መዝ 134:1-3 እንዳለ እኛም ከዚህ የፈተና ዓለም ለማምለጥ በኦርቶዶክሳዊ ሰውነት እንድንጸና በትጋት ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀንና በሌሊት ልንገሰግስ በኪዳኑ በማኅሌቱ በቅዳሴው ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክርነት) – ኒቆዲሞስ ማንንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ከሳሾችን አሳፈራቸው፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ›› በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል (ዮሐ.18፥37)፡፡ በተጨማሪም ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል (ማቴ.10፥32-33)፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን›› በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል (ዮሐ 3፡11)፡፡ይህንን ቃል ከራሱ ጋር በማዋሀድ የአይሁድ የፋሲካ በዓል በቀረበበት ወቅት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ የሙሴን ሕግም አጣምመው ሊያስፈርዱበት በሚጥሩበት ጊዜ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክርነቱን አረጋገጠ፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን ባለማወቃቸው ምክንያት የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ ሲመካከሩ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እርሱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡ 

ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል (ዮሐ 7-50-52)፡፡ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው (ሉቃ 12፡ 8)፡፡ ቤተክርስቲያን “ሰማዕታት” እያለች የምትዘክራቸው ቅዱሣን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም (ማቴ 10፡32)፡፡ ሐዋርያው “ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም” እንዳለ እኛም እንደ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክሮች እንሁን (2ቆሮ 13፡8)፡፡

ጽንዐ ሃይማኖት (በሃይማኖት መጽናት) –  ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት ለታላቅ ክብር በቃ፡፡

 በጌታችን ትምህርት ተስበው ተዓምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ የተገኙት ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ቀራንዮ የምግበ ነፍስ ቦታ ናትና ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ፃድቅ ነው፡፡ የክርስትና አገልግሎት ሲመቸን የምንሳተፍበት ፈተና ሲበዛ የምንሸሽበት አይደለም፡፡ ክርስትና በጅምር የሚቀር ሳይሆን እውነትን ሳንፈራ በመመስከር በተጋድሎ የምናሳልፍበት ለፈጸሙትም የድል አክሊል የሚያገኙበት ሕይወት ነው (2ጢሞ 4:8)፡፡ ምሳሌ ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱ አባታችን ቅዱስ እንጦንስ በፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለ35 ዓመታት ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ እንዲሁም በአህዛብ መካከል ክርስትናን በመግለጽ የጽናት ታላቅ አስተማሪ ነው::

ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው (ዮሐ 19፥ 38)፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋህዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምስጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 115) ብሏል፡፡

እኛም እንደ ኒቆዲሞስ፡-

  1. በዕውቀታችን፣ በስልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳፅ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡
  2. የያዝነውን እውነተኛ እምነት በማጠንከር በሃይማኖት ልብ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት በትህትና ለመሳተፍ ልቡናችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
  3. ምድራዊ አመክንዮ ሳያሰናክለን በቀንና በሌሊት ወደ አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለምስጋና መሄድ ይኖርብናል፡፡
  4. እውነትን በማድረግ ሕይወት የሚገኝበትን ቃለ እግዚአብሔርን ያለኃፍረትና ያለፍርሀት ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡
  5. ክርስትና ምድራዊ ስጦታና ተዓምራት በሚገለጥበት በገሊላ ባህር አጠገብ ብቻ ሳይሆን መከራና ስቃይ ባለበት በቀራንዮም መገኘትን ይጠይቃልና በፈተናና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእምነት ልንጸና የበለጠም በመታመን ልናገለግል ይገባል፡፡

ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር