ምኩራብ: የእግዚአብሔርን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ!

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ፆም ሦስተኛ ሳምንት “ምኩራብ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሳምንት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መሄዱን፣ በቤተመቅደሱ የማይገባ ንግድ ያደርጉ የነበሩትን “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” ብሎ መገሰፁን፣ የሚሸጡ የሚለውጡትንም መገለባበጡን፣ ደቀ መዛሙርቱም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት አስቀድሞ በትንቢት “የቤትህ ቅናት በላኝ” በማለት የተናገረው እንደተፈጸመ ማስተዋላቸው የሚታሰብበትና የሚተነተንበት ነው (ዮሐ. 2፡13-17)፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክት እስከ ዓለም ፍፃሜ ለሚመጡ ምዕመናን በሙሉ ትርጉም ያላቸው ናቸውና ቅድስት ቤተክርስቲያን ከየዘመኑ ሁኔታ አንፃር ከቃለ እግዚአብሔር እንዳንርቅ ታሪኩን መነሻ በማድረግ ታስተምራለች፡፡ በዚህች አጭር ጽሁፍም የሳምንቱ (የዕለቱ) የወንጌል ንባብ ተብራርቷል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱና በቃና ዘገሊላ ተዓምራቱ አምላክነቱን ገልጦ ህዝቡን ማስተማር ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ሠላሳ ዓመታት በተደጋጋሚ ወደ ቤተመቅደስ መጥቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉት በሥርዓተ ኦሪት መሰረት በተወለደ በአርባኛው ቀን ወደ ቤተመቅደስ መምጣቱ (ሉቃስ 2፡22-40)፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ከዮሴፍና ከእመቤታችን ጋር ለበዓል ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱ ጊዜ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ቤተመቅደስ በመሄድ የኦሪት ሊቃውንትን ሲጠይቃቸውና ሲሰማቸው የነበረ መሆኑ (ሉቃ 2፡41-47) ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ አገልጋዮቹ በሥጋዊ ፍላጎታቸው ምክንያት በቤተመቅደሱ የማይገባ ሥራ እየሰሩ ቢያይም አምላክነቱን ገልጦ የሚያስተምርበት፣ የሚገስጽበት ጊዜ አልደረሰምና በዝምታ አልፏቸው ነበር፡፡

ጊዜው በደረሰ ጊዜ ሊቃናተ አይሁድ ባለመታዘዝ ያረከሱትን መቅደሱን ያነጻ ዘንድ መጣ፡፡ መስዋእተ ኦሪት ይሰዋበት የነበረውን ቤተመቅደስ ያነፃው ጌታ ራሱን የሐዲስ ኪዳን መስዋእት አድርጎ አቅርቧልና ኃላፊ ጠፊ የሆኑትን የብሉይ ኪዳን የመስዋእት እንስሳት ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አማናዊ የሐዲስ ኪዳን መስዋእት የሆነ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ከብሉይ ኪዳን መስዋእት ጋር በማነፃፀር “በበግ በጊደርና በላም ደም እነደነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መስዋእት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሰሩ ልቦናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዐመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው፡፡” እንዳለ የብሉይ ኪዳንን መስዋእት አሳልፎ ራሱን ለዓለም ቤዛ አድርጎ የሰጠ ጌታ የአይሁድ አለቆች በገንዘብ ወዳድነት መስዋእቱን ወዳቃለሉበት ቤተ መቅደስ በመምጣት ቤተ መቅደስን አነፃ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሁለት ጊዜያት ቤተመቅደሱን አንጽቷል፡፡ ከእነዚህ ቀዳሚው በመጀመሪያው ፋሲካ ከጥምቀቱ በኋላ አገልግሎቱን ሲጀምር ያደረገውና በምኩራብ ሣምንት የሚነበበው፣ የሚተረጎመው ነው፡፡ ጌታችን ለሁለተኛ ጊዜ ቤተመቅደሱን ሊያነፃ የሄደው ለመከራና ለሞት ተላልፎ ከመሰጠቱ አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና፣ ማለትም በአራተኛውና የመጨረሻው ፋሲካ ነው (ማቴ 21፡12-17)፡፡  በዚህም ወቅት በተመሳሳይ ገዥዎችንና ለዋጮችን፣ እንዲሁም የቤተመቅደስ አለቆችን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ እናንተ ግን የሌቦችና የወንበዴዎች፣ ቀማኞች ዋሻ አደረጋችኋት” በማለት ገሰፃቸው፡፡ ስለሆነም ትንቢተ ነቢያትን የፈጸመ ጌታ በአገልግሎቱ መጀመሪያና ፍፃሜ ላይ ወደ ቤተመቅደስ የመጣው ቤተመቅደሱን ለማንፃት ነበር፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ የሄደው “የአይሁድ የፋሲካቸው በዓል” በደረሰ ጊዜ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡  እግዚአብሔር ባያዝንባቸውና ይህ የፋሲካ በዓል በትክክል ቢከበር ኖሮ  “የእግዚአብሔር ፋሲካ” (ዘፀ 12፡11) ይባል ነበር፡፡  እግዚአብሔር ለሙሴ የበዓላትን ሥርዓት ሲነግረው በዓላቱን “በዓላቴ፣ የእግዚአብሔር በዓላት” በማለት ጠርቷቸዋል (ዘሌ 23፡2)፡፡ ይሁንና እነዚህን ቅዱሳት ጉባኤያትና በዓላት ሥርዓቱን የሚያቃልሉ፣ በሃይማኖታዊ ህግጋት የማይመሩ “አገልጋዮች” በሚያበላሿቸው ጊዜያት ጌታ በህዝቡና በአገልጋዮቹ አዝኖ “የእኔ” ያላቸውን በዓላትና ጉባኤያት “የእናንተ” ብሎ ይገልፃቸዋል፤ ከፈቃዱ ወጥተዋልና፡፡  “መባቻዎቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች…(ኢሳ 1፡14)” እንዲል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጌታችን በመጀመሪያው ፋሲካ  ቤተመቅደስን ለማንፃት በሄደ ጊዜ የህዝቡና የአገልጋዮቹ ኃጢአት አሳዛኝ ስለነበር ቅዱስ ዮሐንስ በዓሉን “የአይሁድ” በዓል መሆኑን ጠቀሰ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ሲመጣ በቤተመቅደሱ የሚሸጡ የሚለውጡ ሰዎችንና የሚሸጡ የሚለወጡ እንስሳትን አገኘ፡፡ የሚሸጡት እንስሳት እንደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ለኃጢአት ማስተስረያ መስዋእትነት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡ የካህናት አለቆችና ግብር አበሮቻቸውም በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እንስሳት ለመስዋእት ብቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ በመስጠት በምትኩ ገንዘብ እየተቀበሉ አገልግሎቱ መልኩን ቀይሮ ንግድ ሆኖ ነበር፡፡ ለመስዋእት የሚሆኑትን እንስሳት የሚሸጡት ሰዎችም ስለሚያገኙት ትርፍ እንጅ ስለ መስዋእቱ ንጽህና አልነበረም፤ ከጌታ የሚገኝ ሰማያዊ ጸጋን በመሸጥና በመለወጥ በሚያገኙት ትርፍ የቀየሩ ነበሩ፡፡ ሊቁ ቅዱስ አምብሮስ በትርጓሜው እንደገለጠው በሬዎችን ይሸጡ የነበሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለሥጋዊ ክብርና ጥቅም ሲሉ “የሚያስተምሩ” ምንደኛ አገልጋዮችን ይመስላሉ፡፡ በጎችን ይሸጡ የነበሩት ሰዎች መልካም ነገርን ለውዳሴ ከንቱ ሲሉ የሚያደርጉ ጌታችን “ዋጋቸውን በምድር ተቀብለዋል” ያላቸውን ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ይመስላሉ፡፡ ርግቦችን የሚሸጡትም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉትን ሲሞናውያን ይመስላሉ፡፡ የእኛስ አገልግሎት ምን ይመስል ይሆን?

ጌታችን ቤተመቅደስን ሲያነፃ እንደ ምልክት ከተፈጸሙት ተግባራት መካከል  በቤተመቅደስ ግቢ ይሸጡ (ሸ ጠብቆ ይነበብ) የነበሩትን በጎችንና በሬዎችን ከቤተመቅደስ ማስወጣቱ፣ የገንዘብ ለዋጮችን ገንዘብ መበተኑ፣ ገበታቸውንም መገልበጡ፣ ርግብ ሻጮችንም ርግቦቻቸውን እንዲያወጡ ማዘዙ ይጠቀሳሉ፡፡ ሲያስወጣቸውም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ (ሰርቶ) ከቤተመቅደስ አስወጣቸው፡፡ አባቶቻችን በትርጓሜ ሲያብራሩ ጅራፉን የሰሩት ሐዋርያት እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ የጭፍራውን ሥራ ለአለቃው ሰጥቶ መናገር ልማድ ነውና ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ጌታ ጅራፍ መስራቱን ገለጠ፡፡ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ጌታችን ወደ ቤተመቅደስ የመጣው ለፍርድ ሳይሆን ለማንፃት ነበርና ሻጮችና ለዋጮችን ሰዎች ሳይሆን የሚሸጡትንና የሚለወጡትን ርግቦችን፣ በጎችን፣ በሬዎችን፣ የሰዎቹን የሚለወጥ ገንዘብ ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ ይህን ያደርጉ የነበሩትን ሰዎች ግን በመገሰጽ አለፋቸው እንጅ ፈርዶ አላባረራቸውም፤ የመጣው ለፍርድ አልነበረምና፡፡ በዳግም ምጽዓት ሲገለጥ ግን ለፍርድ ይመጣል፤ በቤተመቅደስ ያልተገባ ስራ የሰሩትንና የሚሰሩትንም ይቀጣል፡፡

ከላይ በተገለጸው መልኩ ቤተመቅደሱ የንግድ ቦታ ሆኖ ነበር፡፡ ሊቃነ ካህናቱም የጥቅም ተካፋይ ስለነበሩ የሚመክርና የሚገስጽ አልነበረም፡፡ ስለሆነም ጌታችን የሚሸጡና የሚለወጡትን ካስወጣ በኋላ  “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው“፡፡ በዚህም አምላክ፣ ወልደ አምላክነቱን ገለጠ፡፡ “የአባታችሁን” ወይም “የአባታችንን” ሳይሆን “የአባቴን” ቤት በማለቱ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሌሎች ሰዎች በጸጋ ሳይሆን በባህርይ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ እግዚአብሔርነቱን፣ አምላክነቱን ገለጠ፡፡ ጌታችን ቤተ መቅደስን እንዳነፃ ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና” (መዝ. 68፡9) በማለት የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን አስተዋሉ፡፡

ሊቃናተ አይሁድ በቤተመቅደሱ ሲሸጡና ሲለውጡ፣ ሥጋዊ የገንዘብ ትርፍና ዝና በማሳደድ የቤተመቅደሱን ክብር ሲያቃልሉ ያደረጉትን ሁሉ ለመንፈሳዊ ዓላማ ያደረጉት ለማስመሰል በቤተመቅደስ ለሚሸጡትና ለሚለወጡት የመስዋእት እንስሳትና ገንዘብ የትክክለኛነት ማረጋገጫ ይሰጡ ነበር፡፡ ዛሬም ተረፈ አይሁድ የሆኑ ምንደኛ አገልጋዮች አሉ፡፡ ንፁሁን መስዋዕት መዝሙሩን፣ ንዋየ ቅድሳቱን፣ በዓለ ንግሱን፣ ጸበሉንና ሌሎችንም መንፈሳውያን እሴቶቻችንን ለገንዘብ ማግኛነት ሲጠቀሙባቸው ዓላማቸውን መንፈሳዊ ለማስመሰል ይሞክራሉ፤ የዋሀንንም ያሳስታሉ፡፡በቤተመቅደሱ ንግድ ሲደረግ፣ አገልጋዮች በቤተመቅደስ የሚቀርበውን መስዋዕት ለሥጋዊ ጥቅም ሲያውሉት፣ በዚያም ምክንያት የከበሩ መንፈሳውያን አገልግሎቶች ሲቃለሉ አርዓያ የሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝምታ አላለፈውም፡፡

ጌታችን “ከእኔ ተማሩ” ብሎናልና በዘመናችን ባሉ ምንደኛ አገልጋዮች መዝሙርን፣ በዓለ ንግስን፣ በጸበል ማጥመቅን፣ ትምህርተ ወንጌልን ለገንዘብ ማግኛነትና ለንግድ ሲያውሏቸው፣ በበዓላት ላይ ከመንፈሳዊ ሥርዓት ይልቅ ሥጋዊ ንግድና ደስታ ሲበዛ፣ የቤተክርስቲያን የከበሩ ንዋየ ቅድሳት በገዛ አገልጋዮቻችን እንደ ሸቀጥ ሲታዩ፣ ጸሎት ለማድረስ ገንዘብ የሚተምኑ ምናምንቴ ሰዎች ሲመጡ ቃለ እግዚአብሔርና በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጋሻነት ልንቃወማቸው ይገባል፡፡ እኛ ዝም ብንልም የቤተ መቅደሱ ባለቤት ዳግም ይመጣል፡፡ የሚመጣው ግን እንደቀደመው ለማንፃት ሳይሆን ለፍርድ ነው፡፡ ስለሆነም ከሚፈረድላቸው እንጅ ከሚፈረድባቸው ወገን እንዳንሆን አገልግሎታችን ለጽድቅና ለበረከት እንጅ ለገንዘብ፣ ለዝና፣ ለታይታ፣ ለከንቱ ውዳሴ አይሁን፡፡ እያንዳንዳችንም የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን እንደ አይሁድ ሊቃናት ለገንዘብና ለዝና ማግኛነት የሚጠቀሙትን ምንደኛ “አገልጋዮች” ለይተን ልናውቅ፣ አውቀንም ልንርቃቸው ይገባል፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

ቅድስት፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንም

ከቅዱስ ያሬድ በተገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ‹‹ቅድስት›› ትባላለች፡፡ «ቅድስት» ማለት «የተቀደሰች፣ የተለየች» ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን በቅዳሴና በማኅሌት ሰዓት የሚነበቡ፣ የሚዜሙ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ስለ ቅድስናና ስለ ቅድስና ሥራ ይሰብካሉ፡፡ ይህች ሰንበት ‹‹ቅድስት›› የተባለችው በባህርይው ቅዱስ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱን፣ የቅድስና አብነት ይሆነን ዘንድም በሥጋው ወራት እንደሰውነቱ በጎ ምግባራትን መስራቱን፣ የቅድስና ተግባር መገለጫ የሆነ ጾምንም መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ በዚህች ሰንበት እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ የተቀደሰ ነገር ያስፈልገዋልና ሰው ሁሉ በቅድስና መንገድ በመመላለስ የክብሩ ባለቤት የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፡፡  እግዚአብሔር “እኔ ቅዱሳን ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” በማለት ስለማስተማሩ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ትምህርት ይሰጥበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ይህች ዕለት “ቅድስት” የተባለችው የተቀደሰች ዕለት የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ የአምላካችንን ቅድስና እና ሰንበትን ቀድሶ በፈቃዱ እንደሰጠን የሚያነሳው ክፍል ነው፡፡ ይህም ከጾመ ድጓው ‹‹ዛቲ ዕለት ቅድስት ይዕቲ፤ ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ፤  ቅዱሳነ ኩኑ እስመ አነሂ ቅዱስ አነ፤ አብ ቀደሳ ለሰንበት›› የሚል ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ይህች ቀን የተቀደሰች ናት፤ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት፤  እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤ አብ ሰንበትን አከበራት ቀደሳት፡፡›› የሚል ነው፡፡ “ቅድስት” የሚለው ስያሜም ሰንበት የዕረፍታችን ቀን እንድትሆን በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔር የባረካት የቀደሳት ዕለት መሆኑዋን የሚያመለክት ነው፡፡

ሰው ለዚህ ለሥጋዊ ህይወቱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት መሥራት እንደሚጠበቅበት ሁሉ መንፈሳዊ ህይወቱን ለማጽናትና ቅድስናን ገንዘብ ለማድረግ ደግሞ ከአምላኩ ጋር ያለዉ ግንኙነት (ኅብረት) ፍጹም የጠበቀ ሊሆን ይገባል። ይህንንም ማድረግ የሚቻለው ከኃጢአት ሥራ በመራቅ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ትሩፋትን በመስራት ጭምር ነው። በጌታችን ትምህርት፣ በሐዋርያት ስብከት፣ በሊቃውንት ትርጓሜ፣ በቅዱሳን ሁሉ ህይወት የተገለጡትን የመንፈስ ፍሬዎች፣ ጾም፣ጸሎት፣ስግደት፣ምጽዋት ወዘተ ገንዘብ ማድረግ ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሰውን (የክርስቲያንን ሰውነት) ለመንፈሳዊነት የሚያበረቱ ናቸው። በቤተክርስቲያን አስተምህሮ አራቱ ዋና ዋና መንፈሳዊ ትሩፋቶች የሚባሉት ጾም፣ ጸሎት፣ስግደት፣ምጽዋት ሲሆኑ የእነዚህም መሠረታዊ ዓላማ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ጾም ለእግዚአብሔር የመታዘዛችን ማሳያ ነው፡፡ ጾም እግዚአብሔር ራሱ ባርኮ የሰጠን ትዕዛዝ ነው፡፡ ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ ጾምን ቀድሶልናል (ማቴ 4፡1)፡፡ እንዴት መጾም እንዳለብንም አብራርቶ አስተምሮናል (ማቴ 6፡16)፡፡ ለአዳምና ለሔዋን በመጀመሪያ የተሰጠው ‹‹ከዚህ ዛፍ አትብሉ›› የሚለውም (ዘፍ 3፡1) ትዕዛዝ የጾም የመጀመሪያው መሰረት ነው፡፡ ስለዚህ ጾም መጾም መታዘዝ ነው፡፡ አለመጾም ደግሞ አለመታዘዝ (ዓመጸኝነት) ነው፡፡ ጌታችንም ‹‹ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል (ማቴ 6፡16)።›› በማለት የጾምን ትዕዛዝ ሰጥቶናል፡፡ ራሱም በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ አርአያ ሆኖናል (ማቴ 4፡1-11)፡፡ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት መጾም ይገባዋል፡፡ በህመምና ይህንን በመሳሰለው ምክንያት መጾም ካልቻለ ደግሞ የሚችለውን ያህል ሊጾም ይገባዋል፡፡ ጾም በፈቃድ ስለሚደረግ መታዘዝ ነው፡፡ ያለፈቃድ ከሆነ ግን ረሀብ ነው፡፡ ለህጉ በፈቃዳችን በመታዘዝ የቅድስና ባሕርይ ተካፋዮች እንሆናለን፡፡

ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ ጋር የሚነጋገረው በጸሎት ነው፡፡ ሰው የሚፈልገውን ነገር ከእግዚአብሔር የሚጠይቀው፣ ለተደረገለትም ነገር ሁሉ ምስጋናን የሚያቀርበው በጸሎት አማካኝነት ነው፡፡ ሰው በሃይማኖት ሲኖር ከአምላኩ ጋር መነጋገር አለበት፡፡ “በስውር ላለው አባትህ ጸልይ (ማቴ 6፡6-9)” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ አለመጸለይ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማቆም ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ ጋር ካልተገናኘ ደግሞ በራሱ ደካማ ፍጡር ነው፡፡ ሰው ቤተክርስቲያን ባስቀመጠችው የጸሎት ሥርዓት ሊመራ ያስፈልገዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ያንን ማድረግ ካልቻለ ግን የሚችለውን ያህል ሊጸልይ ይገባል፡፡ ስለዚህ ጸሎት ሰውና እግዚአብሔርን የምታገናኝ ዋና መግባቢያ ናት፡፡ የማይግባባ ሰው በሕይወት የሌለ ብቻ ነው፡፡ መናገር የማይችልም ቢሆን በምልክት ይግባባል፡፡ ጸሎት (ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር) በሕይወት መኖራችንን ያሳያል፡፡

ስግደት ለእግዚአብሔር የመገዛታችን መገለጫ ነው፡፡ የአምልኮ ስግደት በደሙ ለገዛን እኛም እንደምንገዛለት ማሳያ ነው፡፡ እርሱንም እንደምናመልክ ማስረገጫ ነው፡፡ የማይሰግድ አይገዛምና፡፡ ስግደት አምላካችንን እንደምናከብረው እንደምንወደው የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ለጣኦት አንሰግድም ያሉትም ለዚህ ነው (ዳን 3፡8)፡፡ ሰው በፍርሀት ሆኖ ለእግዚአብሔር ሊሰግድ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው በቅዳሴ ሰዓት ‹‹በፍርሃት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ስገዱ›› የሚባለው፡፡ ሰማያውያን መላእክት ሳያርፉ እንደሚሰግዱለት እኛም በምድር ስንሰግድ የእርሱና በእርሱ መሆናችንን እንገልጻለን (ራዕ 4፡4-8)፡፡ ስግደት የአምልኮ መግለጫ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም (ማቴ 6፡24)።›› እንዳለው የአምልኮ ስግደት ለእግዚአብሔር የመገዛታችን መገለጫ ስለሆነ ለእርሱ ብቻ የሚቀርብ ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡት፣ በቤተክርስቲያንም የምንፈጽማቸው ለቅዱሳን የሚደረጉ ስግደቶች የጸጋ እንጅ የአምልኮ ስግደቶች አይደሉም፡፡

ምጽዋት በሰማያት የሚኖረን መዝገብ ነው፡፡ ምጽዋት ወደ ሰማያዊ ቤታችን ስንሄድ የሚጠቅመን መዝገብ (አካውንት) ነው፡፡ ምጽዋት ብልና ዝገት የማያጠፋው፣ ሌባም የማይሰርቀው ሰማያዊ መዝገብ ነው፡፡ በፍርድ ቀን ዋስትና የሚሆነን መዝገብ ነው (ማቴ 6፡19)፡፡ በምድር መዝገብ (የባንክ አካውንት) እያለን  በሰማይ ግን መዝገብ የሌለን መሆን የለብንም፡፡ ዘወትር ‹‹በሰማያዊው መዝገብ ምን አለኝ?›› እያልን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ በምድር ሌላውን ጠቅሞ በሰማይ ራሱን ይጠቅም ዘንድ ሰው ልቡ የፈቀደውን ያህል ምጽዋት በደስታ ይስጥ፡፡ ያለንን ማካፈል በሰማይ መዝገብ ማጠራቀም ነውና፡፡ ጌታም በወንጌሉ ‹‹ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ (ማቴ 6፡19-20)፡፡›› እንዳለው ምጽዋት የሰማይ መዝገባችን ናት፡፡

ቅድስት በተባለችው የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ) ‹‹ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፡፡ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ፡፡ ሰንበትን አክብሩ፡፡ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደላይ አስቡ፡፡›› የሚል መዝሙር/ትምህርት እናገኛለን፡፡ በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን  ‹‹እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፤ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ/እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ: ምስጋና ውበት በፊቱ: ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡/ (መዝ.95÷5) የሚለው ምስባክ ከዳዊት መዝሙር ይሰበካል፡፡ እነዚህ መዝሙራት የእግዚአብሔርን ቅድስና እና የሰንበትን ቅድስና የሚገልጹ ሲሆን የሰው ልጅም ቅድስናን የቅድስና ሥራን ገንዘብ በማድረግ ማግኘት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

በአጠቃላይ ጾም ለእግዚአብሔር የመታዘዛችን ማሳያ፣ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንግባባበት ቋንቋ፣ ስግደት ለእግዚአብሔር የመገዛታችን መገለጫ፣ ምጽዋትም ሰማያዊ መዝገባችን ናቸው፡፡ ሁሉም በነፍስም በሥጋም ሰውን ይጠቅማሉ፡፡ መንፈሳዊ ትሩፋት የተባሉትም የጽድቅ በር ስለሆኑ ነው፡፡ በወንጌል ያመኑ ምዕመናን ራሳቸውን በምግባርም ካላነጹ እምነታቸው ከአጋንንት አይለይም፡፡ እነዚህ ትሩፋቶች ግን የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት በእምነት የምናገኘውን ጽድቅ በልጅነት ገንዘብ እንድናደርግ፣ የእግዚአብሔርን ፍፃሜ የሌለው ቸርነትም እንድንጠባበቅ ይረዱናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና (1ኛ ተሰ 4፡7)፡፡” እንዳለው የተጠራነው ለቅድስና መሆኑን ማስተዋል ያሻል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ ‘እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ’ የሚል ተጽፎአልና፡፡” እንዳለው የቅድስናን ሥራ ዘወትር ገንዘብ ማድረግ ይገባል፡፡ ከኃጢአት በንስሐ ነጽተን፣ መንፈሳዊ ትሩፋትን ሠርተን በእግዚአብሔር ቸርነት የዘላለም ሕይወትን እንድንወርስ የእርሱ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ዘወረደ፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም

ዐቢይ ጾም ‹‹ዐቢይ›› የተባለው የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነት ጾሞ የመሠረተው ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ካሉት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት ረጅሙ (55 ቀን ያለው) ስለሆነ ደግሞ ‹‹ሁዳዴ›› ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዓቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙትን ስምንት ሣምንታት ለትምህርት፣ ለአዘክሮና ለምስጋና በሚመች መልኩ ልዩ ስያሜዎች ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ሳምንት (ሰንበት) የሚነበቡ፣ የሚተረጎሙ፣ የሚዘከሩ፣ የሚዘመሩ ልዩ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሣዊ ኩነቶችና አስተምህሮዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ የመጀመሪያው ሰንበት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት ዕለት በቤተክርስቲያናችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ከሰማይ ስለመውረዱ የሚነገርበትና የሚዘመርበት በመሆኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሏል፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍል ‹‹ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው (ዮሐ 3፡13)›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ቃል የተናገረው ስለ ሰማያዊው ምሥጢር ለኒቆዲሞስ ባስተማረበት ጊዜ ነበር፡፡

ለመሆኑ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ጥቅስ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም ባለመረዳት ለክህደታቸው የሚመች የመሰላቸውን ቃል እየመዘዙ ክደው የሚያስክዱ፣ ተጠራጥረው የሚያጠራጥሩ መናፍቃንም  በአላዋቂ አዕምሮ፣ በኢአማኒ ልቦና ያለ አውዱ በመጥቀስ በተለያዩ ቅዱሣት መጻሕፍት የተመሰከሩ፣ በታሪክ የታወቁ የቅዱሣን ሰዎችን እርገት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክትን ለተልእኮ ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መውረድና መውጣት ለመቃወም ይጠቀሙበታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና የቤተክርስቲያን ታሪክ ግን የቅዱሳን ሰዎችን ዕርገትና የቅዱሳን መላእክትን  ለተልእኮ መውረድና መውጣት ያለጥርጥር ያስረዳናል፡፡ እኛ የሐዋርያትን ፈለግ የምንከተል ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን ከቅዱሳን መካከል ነቢዩ ኤልያስንና ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክን ጨምሮ የተወሰኑ ቅዱሳን ሞትን ሳይቀምሱ ማረጋቸውን፣ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ጸሎትና የእግዚአብሔርን የማዳን ብስራት ይዘው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከምድር ወደ ሰማይ መመላለሳቸውን፣ ሌሎች ቅዱሳንም በስጋ ተነጥቀው (ዐርገው) የሰማያትን ምስጢር በተዓምራት ማየታቸውን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግልም በልጇ ኃይልና ስልጣን ከሞት ተነስታ ማረጓንና በሰማያት፣ በሰማያዊ መዓርግ በልጇ ቀኝ መቆሟን እናውቃለን፤ እናምናለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› የሚለው ቃል ምሥጢሩ ምንድን ነው? ሊቃውንት አባቶች እንዳስተማሩት ይህ የጌታችን ቃል የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ያስረዳል፡፡

  1. ፍጹም ሰው፣ ፍጹም የባህርይ አምላክ ከሆነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማያዊ እውቀት የባህርዩ የሆነ፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀትን ገንዘብ ያደረገ ምድራዊ መምህር የለም፡፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀትን ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ከምድራዊያን መምህራን በራሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ፡ ተመልሶ ወርዶ ያየውን የሚያስተምር የለም፡፡ እርሱ ከሰማይ የመጣው ግን ሰማያዊ ምስጢርን ለማስተማር (ለመግለጥ) የራሱ ባህርይ (የባህርዩ) ነው፡፡
  2. ከጌታችን በቀር በኅልውና ያየውን የሚገልጥ፡ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን መጥቶ የሚያስተምር ምድራዊ መምህር የለም፡፡ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን የራሱን ምሥጢር ያስተማረ እርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  3. ከጌታችን በቀር ከሰማያዊ ዙፋን የወረደ የለም፡፡ ሰማይ የልዕልና ስፍራ፣ የእግዚአብሔር ዙፋን ነው፡፡ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ፣ ሰውንም ለማዳን ከዙፋኑ የወረደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሌላ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ ከዚያ ዙፋንም የወረደ የለም፡፡ ሰውን ለማዳን ከዙፋኑ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  4. ከጌታችን በቀር በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ የለም፡፡ ፍጡራን (መላእክትና ሰዎች) ወደ ሰማይ ቢወጡም ቢወርዱም በራሳቸው ፈቃድ አይደለም፡፡ በራሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ ወደ ሰማይም የወጣ እርሱ ብቻ ነው፡፡ በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
  5. ከጌታችን በቀር በባህርይው መለወጥ የሌለበት፣ አንድ ባህርይ የሆነ፣ ይህንንም በራሱ ፈቃድ የወሰነ የለም፡፡ ከሰማይ የወረደው ወደ ሰማይ የወጣውም አንድ አካል አንድ ባህርይ ነው፡፡ ከሰማይ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ ወርዶ፡ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣ አይደለም፡፡ ልክ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ እንደወረደ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኖ ወጣ ማለት ነው፡፡ አንድ ባህርይ ሆኖ ወርዶ አንድ ባህርይ ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡

ዘወረደ በተባለችው በዚህች የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሰንበት ወልደ እግዚአብሔር ስለ ድኅነታችን መውረዱን እያሰብን ስናመሰግን የመውረዱንም ምክንያት በሚገባ ከመረዳት ጋር ሊሆን ይገባል፡፡ ጌታችን ከሰማይ የወረደው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው፣ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ተመላልሶ ያስተማረው ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ለቤዛነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለአርአያነት ነው፡፡

ለቤዛነት፡- በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው፣ የሰው ልጅ ዳግመኛ እንዳይጠፋ፤ እርሱ ስለእኛ ተሰቅሎ ቤዛ ሊሆነን፤ ዓለም በልጁ ቤዛነት እንዲድን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ስለወደደ ለቤዛነት ከሰማይ ወረደ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉስ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ (መዝ 73፡12)›› እንዳለ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በዓለም እንዲፈርድ አልላከውም፡፡ መድኃኒት ሆኖ እንዲያድነን እንጂ፡፡ ስለዚህ በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ  ስላላመነ ተፈርዶበታል እንደተባለ በስሙ አምነን ቤዛ ይሆነን ዘንድ ወረደ፣ ተወለደ፡፡

ለአርአያነት፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ሊያበራ፣ ብርሀን የሆነውን ሕገ ወንጌልን ሊሠራልን ወረደ፡፡ የሰውንም ልቡና በወንጌል ሊያበራ ወረደ፡፡ ሕግን የሰራ እርሱ የሰራውን ሕግ እየተገበረ አርአያ ሆኖ ሊያስተምረን ወረደ፡፡ ነገር ግን “ክፉ የሚያደርግ ብርሃንን ይጠላል፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሀን አይመጣም፡፡” እንደተባለ ክፉ የሚያደርጉ በብርሃን ክርስቶስ አያምኑም፣ አርዓያ ሆኖ የፈጸመውን ሕግም አይፈጽሙም፤ ብርሀንን ለማጥፋት ይጥራሉ እንጂ፡፡ ክፉ የሚያደርጉ (የጨለማ ሥራ የሚሠሩ) ወደ ጨለማ ይሄዳሉ፡፡ በአንፃሩ እውነትን የሚያደርግ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ ሥራውም በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ እንዲገለጥ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ እንደተባለ መልካም የሚያደርጉ በእርሱ ያምናሉ፡፡ መልካም የሚያደርጉ የብርሃን ልጆች ወደ ብርሃን ክርስቶስ ይመጣሉ፤ በቅዱስ ስሙ ያምናሉ፣ አርዓያነቱንም ይከተላሉ፡፡

ክፉዎች አይሁድ ጌታን የሰቀሉት የጨለማ ሥራቸው እንዳየይገለጥ ነበር፡፡ ዛሬም አንዲሁ ነው፡፡ የጨለማ ስራቸው እንዳይገለጥ የሚፈልጉ ነውረኞች እውነተኞችን ሲያሳድዱ ይኖራሉ፡፡ የህይወት ባለቤት፣ የብርሃን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነትና ለቤዛነት ከመጣ ከእኛ የሚጠበቀው በፍፁም ፍቅር በተሞላ የአባትና የልጅ ፍርሀት ሆነን ለእርሱ መገዛት ነው፡፡ በዚሁ በመጀሪያው የዐቢይ ጾም ሰንበት በሚሰበከው በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ምስባክ ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሀት፣ ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ/በፍርሀት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ (መዝ 2፡11)›› እንዳለ በፍቅር በተሞላ ፍርሀት ሆነን ጌታችንን ልንገዛለት፣ ልናመልከው ይገባል፡፡ ቤዛ አርአያ ለሆነን ጌታ እንጂ ለሰይጣንና ለስጋችን ፈቃድ እንዲሁም በሥጋ ፈቃድ ለሰለጠኑ ምድራውያን ኃይለኞች ልንገዛ አይገባም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች መልካምን የምናደርገውም ቅጣትን (ሞትን) ፈርተን ሳይሆን እኛን ለማዳን ከዙፋኑ የወረደውንና የእኛን ሥጋ ለብሶ በመልዕልተ መስቀል ላይ ቤዛ የሆነልንን ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ፈርተን (አፍቅረን) ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹ልጅ አባቱን ያከብራል፤ ባሪያም ጌታውን ይፈራል፤ እኔስ አባት ከሆንኩ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንኩ መፈራቴ ወዴት አለ? (ሚክ 1፡6-7›› እንዳንባል ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹በፍርሀት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ›› እንዳለው በፍርሀት ሆነን ለእርሱ ልንገዛ ይገባል፡፡ ፍርሀትም ሲባል ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርሀት አለ፡፡

ሥጋዊ ፍርሀት፡- ሰው ኃጢአትን ሠርቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የመጣበትና ከመጨነቅ የሚመነጭ ፍርሀት ነው፡፡ ረሀብን፣ በሽታን፣ ጦርነትን፣ አደጋን ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ መፍራት ሥጋዊ ፍርሀት ነው፡፡ ምድራዊ ሕግን ስንተላለፍ ፖሊስን የምንፈራው ፍርሀት የሥጋ ፍርሀት ነው፡፡ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ በነበረበት ዘመን ሕዝቡ የአይሁድ ካህናትን ይፈሩ ነበር፡፡ ይህ ፍርሀት ግን ሥጋዊ ፍርሀት ነበር፡፡ የሙሴን ህግ ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝቡን ያሰቃዩት ስለነበር ነው የአይሁድ ካህናት ይፈሩ የነበረው፡፡   እንዲህ አይነቱ ፍርሀት በጤና ጉዳትን በማድረስ ለአእምሮ መታወክ ከመዳረግ ውጭ ምንም አይጠቅምም፡፡ ይህ አይነት ፍርሀት ከክርስቲያኖች ላይ መወገድ እንዳለበት ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።›› በማለት እንዲሁም ለምኩራቡ አለቃ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› በማለት አስተምሯል፡፡ ማቴ 10፡28 ማር 5፡36

መንፈሳዊ ፍርሀት፡- ይህ ፍርሀት ከፍቅር ከማክበር የሚመነጭ ፍርሀት ነው፡፡ እግዚአብሔር አንዲህ እየወደደኝ እንዴት እበድላለሁ የሚል ፍርሀት መንፈሳዊ ነው፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ያህል ውለታ ውሎልኝ እንዴት እተወዋለሁ የሚል ፍርሀት ከዚህ ይመደባል፡፡ ይህ አይነት ፈሪሀ እግዚአብሔር የጥበብ መጀመሪያና ሰውንም ከኃጢአት የሚጠብቅ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹ቅዱሳኑ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩ(መዝ 33፡14)›› እንዳለ እንዲህ አይነቱ ፍርሀት የሕይወት ምግብ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘድን እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው (ምሳ 14፡27)።›› እንዳለው መንፈሳዊ ፍርሀት የሕይወት መገኛ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በሌላም ሥፍራ ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው (መዝ 128፡1)›› እንዳለው መንፈሳዊ ፍርሀት የቅድስና ሥራ ነው።

ለአርዓያ ዓለም ከሰማየ ሰማያት የወረደው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አይሁድ ሊቃናት በማስጨነቅ ሳይሆን በፍቅር እንደሚመራ፣ እንደሚያስተዳድር በመዋዕለ ሥጋዌው አሳይቶናል፡፡ ከተናቁት ጋር በመቆም፣ መምህርና ጌታ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ፣ ንጹሐ ባሕርይ ሲሆን በበደልና በኃጢአት የተዳደፉትን ሰዎች በፍቅር ቀርቦ ወደ ጽድቅ በመመለስ አርዓያነቱን አስመስክሯል፡፡ ይህ እርሱ ፍጹም ፍቅርና ትህትና መንፈሳዊና ሥጋዊ ስልጣናቸውን ለትምክህትና ለከንቱ ውዳሴ ሲሉ ያለ አግባብ ይጠቀሙ ለነበሩ የአይሁድ ሊቃናት ተግባራዊ ተግሳጽ ነበር፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅሩና በትህትናው በጎቹን በመልካም መንገድ የሚመራ እረኛ መሆኑ እረኝነታቸውን ረስተው በበጎቻቸው የሚነግዱ ሊቃናተ አይሁድን ስላወካቸው በቅናት ተነሳስተው ያለ ኃጢአቱ ለመከራ መስቀል አደረሱት፡፡ እርሱ ግን ለመከራ መስቀል በመታዘዝ ሰውን የማዳን ቃልኪዳኑን፣ ፈቃዱን፣ የአባቱን  ፈቃድ፣ የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ፈጸመ፡፡ በመውረዱ በመወለዱ ቤዛነትን አገኘን፤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ተሻገርን፡፡

ዛሬም በቤዛነቱ ያገኘነውን የመዳን ጸጋ በእምነትና በመታዘዝ እየፈጸምን አርዓያነቱን ተከትለን እስከ ዕለተ ምጽዓት እንድንጠብቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ በተለይም በጾማችን ወራት የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማየ ሰማያት ለወረደው፣ በሥጋ ማርያም ለተገለጠው፣ ለሥጋችንና ለነፍሳችን ቤዛ፣ ለህይወታችን መርህ (አርዓያ) ለሆነን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድንገዛ ፈቃዱንም አብዝተን እንድንፈጽም ታዘናል፡፡ የወንጌሉም የምስባኩም (መዝሙረ ዳዊት) ዓላማ ይህንን ማስገንዘብ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የተሾሙ፣ የክርስቶስ እንደራሴዎች የሆኑ ካህናትም ልዩ ሊቀ ካህናት የሆነውን የምስጢራት ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በማድረግ እንደ አይሁድ ሊቃናት መንፈሳዊ ስልጣንን ለትምክህትና ለከንቱ ውዳሴ ከመጠቀም ርቀው በጎች የተባሉ ምዕመናንን በፍቅርና በትህትና፣ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሊመሩ ያስፈልጋል፡፡ በጎች የተባልን ምዕመናንም የክርስቶስ እንደራሴ የሆኑ ካህናት አባቶቻችንን እየታዘዝን በፍቅርና በፍርሃት የእግዚአብሔርን ቃል መሰረት አድርገን ልንኖር ይገባል፡፡ ይህን ስናደርግ ለእኛ ብሎ የወረደ የተወለደ ቤዛም የሆነልንን የክርስቶስን ፈቃድ ፈጽመን በሰማይ ባለች ነፃ በምታወጣ በኢየሩሳሌም በቀኙ ከሚቆሙ ንጹሐን ቅዱሳን ኅብረት እንደመራለን፡፡  በጾማችን ወራት ፈቃዱን ፈጽመን በመንፈሳዊ ፍርሀት ለእርሱ ተገዝተን መንግስቱን ለመውረስ ያብቃን፡፡

የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን

በክርስትና ታሪክ እጅግ የጎላ ታሪክ ካላቸው  ቤቶች መካከል የቅዱስ ማርቆስ እናት (ማርያም ባውፍላ) ቤት ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች፡፡በዚህች ቤት ሰገነት ላይ ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ያካሂዱ ነበር፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ‹‹በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር (ሐዋ 1፡10-14)።›› እንዳለው በዚህች ቤት ሐዋርያት ለጸሎት ይተጉ እንደነበር ‹‹የጸሎት ቤት›› በተባለችው ቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖች ለጸሎት ሊተጉ ይገባል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የወረደላቸውና 71 ቋንቋዎች የተገለጠላቸው በዚህች ቤት ሳሉ ነው፡፡ ሁሉም በተሰባሰቡባት ዕለት መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ ይህም በሐዋርያት ሥራ ‹‹በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር (ሐዋ. 2፡1-4)፡፡›› ተብሎ ተገልጿል፡፡ በማርቆስ እናት ቤተ በጸሎት ይተጉ ለነበሩት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸው ዛሬም በቤተክርስቲያን በጸሎት ለሚተጉ የእግዚአብሔር መንፈስ ጽናትንና ትጋትን ያድላቸዋል፡፡

ስለዚህች ቤት ክብር የተጻፈው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መልአከ እግዚአብሔር  በተዓምራት ከእስር ቤት ካስወጣው በኋላ የተጓዘው ወደዚህችው ቤት ነው፡፡ “ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፡፡” ሐዋ. 12፡12፡፡ ይህች ታላቅ ቤት የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን እና ጽርሐ ጽዮን በሚል ስያሜ የምትታወቀው ናት፡፡ ይህች ቤት ድንቅን ያደረገ ጸሎት የተደረገባት ናትና የእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ በዚህች ቤት የተደረገ ጸሎት ቅዱስ ጴጥሮስን ከሥጋ እስራት እንዳስፈታው በቤተክርስቲያንም የሚደረግ ጸሎት ከኃጢአት እስራት በንስሐ ያስፈታል፡፡

አባቶቻችን ሐዋርያት ከጌታችን ዕርገት በኋላ በቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እግዚአብሔርን በፅናት ደጅ ይጠኑት ነበር፡፡ ይህችም ቤተ-ጸሎት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ሐዋርያት በአንድነት ሆነው በማርቆስ እናት ቤት ሆነው ከአምላካቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ የተሰጣቸው ተስፋ እንደተፈፀመ መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ እኛም ዛሬ በአመፅ፣ በጩኸትና በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በተረጋጋ በሰከነ አዕምሮ በቤተ ክርስቲያን  ደጅ ብንጠና ጸሎታችን ይሰማል፤ የመንፈስ ቅዱስም ሀብት ይበዛልናል፡፡ በዚያች በማርቆስ እናት ቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሐዋርያቱ ጋር ተገኝታለች፡፡ በአማናዊት ቤተክርስቲያንም ከምእመናን ጋር በበረከትና በምልጃዋ ትገኛለች፡፡ ይህች የማርቆስ እናት ቤት ለቤተክርስቲያን በይፋ መጀመር ፈር ቀዳጅ ምሳሌ ናት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህች ቤተ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ትባለለች፡፡

የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል

የሕይወት ውኃ

በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከዐቢይ ጾም መግቢያ አስቀድሞ ባለው ሰንበት የሚሰበከው ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ‹‹የሕይወት ውኃ›› ለሳምራዊቷ ሴት ያሰተማረው ነው (ዮሐ 4፡1-21)፡፡ አስተምህሮም በዚህ ጦማር ስለ የሕይወት ውኃ ከቅዱሳት መጻሕፍት ከሚቀዳው ምስጢር የጠብታ ያህል ለአንባቢያን ለማስታወስ ትወዳለች፡፡ ወደ ዋናው የመጻሕፍት ቃል ከመግባታችን በፊት እስኪ ስለ ውኃ ጥቂት እንበል፡፡ ውኃ በመጀመሪያው ቀን ሰማይና ምድር ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረ ነው፡፡ ሁሉን የሚችል፣ ፈጣሬ ዓለማት አምላካችን እግዚአብሔር በሁለተኛው የሥነ ፍጥረት ቀን ውኃ በጠፈር ተለይቶ ከጠፈር በታችና በላይ እንዲሆን አድርጎ ሰርቶታል፡፡ ውኃ ዛሬም የምድርን ሦስት አራተኛ (75%) ሲሸፍን የሰውነታችን ሁለት ሶስተኛ (67%) ደግሞ ውኃ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተሠራባቸው አራቱ ባህርያተ ሥጋ መካከልም አንዱ ውኃ ነው፡፡ ውኃ ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ (ዕፅዋትን ጨምሮ) እጅግ አስፈላጊ የሆነ ውህድ ሲሆን የተቀመረውም ሃይድሮጂን (H) እና ኦክስጂን (O) ከሚባሉ ንጥረ ነገሮች ነው፡፡ የሰው ልጅም በዚህ ምድር ላይ በአካለ ሥጋ ሲኖር ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች መካከል ውኃ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፡፡

ውኃ በብሉይ ኪዳን በነበሩት የኖህ ዘመን ሰዎች የጥፋት መሳርያ ሆኖ አጥፍቷቸዋል፡፡ ‹‹ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ። በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ (ዘፍ 7፡10-12)።›› እንደተባለው የጥፋት ውኃ የኖኅ ዘመን ሰዎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህም በበደላቸው ምክንያት የመጣና በእግዚአብሔርም ትዕዛዝ የተፈጸመ ጥፋት ነው፡፡

ውኃ ያደፈውን ለማንጻት እንደሚጠቅመው ሁሉ ከኃጢአት ለመንጻትም የንስሐን ጥምቀት ማጥመቂያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ (ሕዝ 36፡25-26)።›› እንደተባለው ውኃ ለንስሐ ጥምቀት ይውላል፡፡ ከንስሐ ጥምቀት በላይ የከበረች ከእግዚአብሔር በጸጋ የምንወለድባት ረቂቅ የልጅነት ጥምቀትም የምትፈጸመው በውኃ አማካኝነት ነው፡፡ ጌታችንም ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።›› (ዮሐ. 3፡5) ብሎ እንዲሁም እርሱ አርአያ ሊሆነን በዮርዳኖስ በውኃ ተጠምቆ ሁላችን በውኃ ተጠምቀን የሥላሴ ልጅነትን እንድናገኝ አርአያ ሆኖ አስተምሮናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማርያ ሲያልፍ “ሲካር” በምትባለው የሰማርያ ከተማ አጠገብ ባለው የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ሆኖ ሳምራዊቷን ሴት “ውኃ አጠጪኝ” ብሏት ነበር፡፡ ሴቲቱ ግን “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን ከሳምራዊት ሴት እንዴት ውኃ ትለምናለህ?” አለችው፡፡ እርሱም ‹‹የእግዚአብሔርን ስጦታ ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር›› ብሏታል፡፡ እርሷም ‹‹ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል›› ብትለው ጌታችን መልሶ ‹‹ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ›› በማለት አስተምሯታል፡፡ ዮሐ 4፡1-14

ይህ የሕይወት ውኃ የተባለው ምንድን ነው? ይህ ከጠጡት ለዘላላም የማያስጠማ ውኃ ምንድን ነው? ይህ ጌታችን የሰጠውና የሚሰጠው የሕይወት ውኃ ምንድን ነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላው ትምህርቱ ‹‹ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል›› ብሎ ተናግሯል። ወንጌላዊው ዮሐንስም ‹‹ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ›› በማለት የሕይወት ውኃ ስለተባለው ምስጢር ማብራሪያውን አክሎበታል፡፡ ዮሐ 7፡37-39

ስለዚህ የሕይወት ውኃ አስቀድሞ በነቢያትም ብዙ ተነግሮአል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ (ኢሳ 58፡1)›› ሲል ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል (ኤር 2፡13)›› በማለት ስለዚህ የሕይወት ውኃ ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዘካርያስም ‹‹በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፤ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል (ዘካ 14፡8)›› በማለት ስለዚህ የሕይወት ውኃ ተናግሯል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ ‹‹በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ። …ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው (ራዕይ 22፡1-2፣ 14) ።›› በማለት ስለዚህ የሕይወት ውኃ በራዕዩ ያየውን መስክሯል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በዓርብ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹ማርያም ድንግል ሙዳየ ዕፍረት፣ ነቅዐ ፈልፈለ ማየ ሕይወት ፍሬ ከርሣ አድኃነ ኩሎ ዓለመ ወሠዐረ እምኔነ መርገመ፤ ድንግል ማርያም የሽቱ መኖሪያና የሕይወት ውኃ  ምንጭ ናት፡፡ የማህፀኗ ፍሬ ሰውን ሁሉ አድኗልና፡፡ ከእኛም እርግማንን አጠፋልን›› ያለውም የሕይወት ውኃ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና የዚህም የሕይወትን ውኃ ያስገኘችው ‹‹ምንጭ›› ድንግል ማርያም መሆኗን ያሳያል፡፡ የሕይወት ውኃን የሚሰጠው እርሱ ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹የሕይወት ውኃ›› ብሎታል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሀን ድርሰቱ ‹‹ኢየሱስም ያንቺን ሥጋ ለበሰ፤ በታላቅ ቃል ጮኸ፤ መጽሐፍ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል እንዳለ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ አለ›› በማለት ዮሐንስ ወንጌላዊ የጻፈውን በመጥቀስ ስለ ሕይወት ውኃ ጽፏል፡፡

ከላይ በተገለጸው መልኩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳምራዊቷን ሴት ምድራዊ ውኃን እንድትሰጠው የጠየቃት ወደ እውነተኛው የህይወት ውኃ የሚመራትን፣ ወደ ዘላለም ህይወት የሚያደርሳትን ቅዱስ ቃሉን፣ እንዲሁም እርሱን በማመን በሚገኝ ጸጋ የሚገኘውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ገንዘብ  እንድታደርግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የተጻፈው ሁሉ በመታገሣችንና መጻሕፍትን በመታመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ እኛ ልንማርበት ተጻፈ” (ሮሜ. 15፡4) እንዳለ ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ያስተማራት ድንቅ ትምህርት በኃጢአታችን ምክንያት የጽድቅን ውኃ ለተጠማን፣ በጎደሎ ምግባርና በተጠራጣሪ ልቦና የመንፈስ ቅዱስን ሀብት ገንዘብ ማድረግ ለተሳነን ለዚህ ዘመን ምዕመናንም የተፃፈ ነው፡፡ አስቀድሞ በነቢይ ‹‹በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ (ኢሳ 44፡3)›› እንደተባለው፣ ኋላም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል (1ኛ ቆሮ 12፡13) ።›› ብሎ እንደገለጸው ለዘላለም የማያስጠማ እግዚአብሔርን ቃል፣ የመንፈስ ቅዱስንም ሀብት ገንዘብ ለማድረግ በንስሐ እየተመላለስን፣ ከኃጢአት ርቀን ህይወት የሆነንን/የሚሆነንን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በልተን፣ ጠጥተን የዘላለም ሕይወትን እንድናገኝ የእርሱ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡