ሰማዕታትና ሰማዕትነት: የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው!

semaetat

ግብጻውያን እና ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት (ሥዕል: ዘሪሁን ገብረ ወልድ)

“ሰማዕት” የሚለው ቃል ዘሩ ‹‹ስምዐ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የሚወጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም “ምስክር” ማለት ነው፡፡ “ሰማዕትነት” ማለትም እንዲሁ “ምስክርነት” ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሰማዕት ማለት የተሰዋ፣ ራሱን መስዋዕት ያደረገ ማለት ነው፡፡ የዚህም ምስክርነት ዋና መሰረቱ ጌታችን በወንጌሉ “በሰው ፊት የሚመሰክርልኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ሁሉ ፊት የሚክደኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እክደዋለሁ (ማቴ 10፡32)” ብሎ የተናገረው ታላቅ ቃል ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሰማዕት ከአቤል ጀምሮ እስከ ህጻናተ ቤተልሔም፣ እንዲሁም የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ፣ መጥመቀ መለኮት ዮሐንስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ በዘመነ ሰማዕታት የነበሩት እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እነ ቅድስት አርሴማ፣ እነ ቅዱስ ቂርቆስ፣ በእኛም ዘመን በተለያዩ ስፍራዎች ሰማዕትነትን የተቀበሉት ግብጻውያን እና ኢትዮጵያውያን እና የመሳሰሉት ይህንን በመመስከር ለታላቅ ክብር ከበቁ ሰማዕታት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብዙ ሰማዕታት ይታሰባሉ፡፡ ስማቸውና የሰማዕትነታቸው ዜናም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲሁም በገድላቸው፣ በድርሳናቸው፣ በመልክአቸው በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊውና የቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውሳብዮስ እንዳለው የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነውና የሰማዕታት ገድል መጻፉ ለክርስትና ሃይማኖት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ስለዚህም መዝገበ ምስጢር የሆነችው ቤተክርስቲያናችንም የቅዱሳን ሰማዕታትን ገድላቸውን ለዘመናት ጠብቃ ይዛ አዳዲስ ሰማዕታትም በየዘመናቱ ሰማዕትነትን ሲቀበሉ እነርሱንም ከሰማዕታት ቁጥር እየደመረች ገድላቸውን ለትውልድ ታስተላልፋለች፡፡ ይህንንም የምታደርገው መታሰቢያቸው ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ ምዕመናን ከሰማዕታቱ ተጋድሎና ጽናት ትምህርትን እንዲያገኙ እንዲሁም አምላካችን እግዚአብሔር ለቅዱሳን ሰማዕታት በሰጣቸው ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ተማጽነው ጸጋና በረከትን እንዲካፈሉ ለማስቻል ነው፡፡

ሰማዕትነት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው “ሰማዕት ዘእንበለ ደም” (ደምን ከማፍሰስ በመለስ ያለ ሰማዕትነት) ሲሆን ሃይማኖትን በመመስከር፣ እውነትን በመናገር ያለጥፋታቸው ስደት፣እስራት፣ግዞት፣ስድብ ነቀፌታ ሲደርስባቸው በአኮቴት እና በትዕግስት የሚቀበሉ ቅዱሳን ተጋድሏቸውን ሲፈጽሙ ሰማዕት ዘእንበለ ደም ይባላሉ፡፡ “የደም ሰማዕት” ደግሞ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ክብር፣ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲሉ ያፈሰሱ ናቸው፡፡ይህም የሰማዕትነት የመጨረሻ ደረጃ መገለጫ ነው፡፡ ሁለቱንም የሰማዕታትን ምስክርነት በሚገባ ለመረዳት ስለእነርሱ ምስክርነት አምስት ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ የሰማዕታት ምስክርነት ስለማን/ስለምን ነበር? ምስክርነታቸውስ ለማን ነበር? ምስክርነታቸውን እንዴት መሰከሩ? በምስክርነታቸውስ ምን አተረፉ? እኛስ የእነርሱን ምስክርነት በመዘከራችን ምን እናተርፋለን? በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር እነዚህን ነጥቦች እንዳስሳለን፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው ስለ ክርስቶስ ነበር፡፡

ሰማዕታት በዚህች ምድር ላይ ክርስትናን በቃልና በተግባር ኖረው ክርስቶስንም በቃልና በሕይወት መስክረዋል፡፡ ክርስቲያን ሆነው መገነኘታቸው ብቻ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው በሥጋቸው ብዙ ጸዋትወ መከራን ተቀብለዋል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት ዓላውያን ነገሥታት የየራሳቸውን እምነት በክርስቲያኖች ላይ ለመጫን ባደረጉት የግፍ ተግባር ብዙዎችን ለመከራ ዳርገዋል፡፡ በዚህ መከራ ውስጥ ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ የማመልከውም የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ የሆነውን  ኢየሱስ ክርስቶስን ነው›› በማለት ራሳቸውን ለሰይፍ ለሰንሰለት አሳልፈው የሰጡ የክርስቶስና የክርስትና ምስክሮች ሰማዕታት ናቸው፡፡ የሚያልፈውን ምድራዊ ክብርን ንቀው የማያልፈውን ሰማያዊ ክብር የሚሰጠውን ክርስቶስን መሰከሩ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ ስለ መንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ፡፡” ያለው ምስክርነታቸው ስለ እግዚአብሔር እንደነበር ያስረዳናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር ማለትም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና አርድእት በዓለም ዞረው የሰበኩትን፣ ሐዋርያውያን አበው ከመናፍቃን ቅሰጣ፣ ከዓለማውያን ቁንጸላ ጠብቀው ያቆዩልንን፣ ሐዋርያዊት ኦርቶዶክሳዊት የሆነች የቤተክርስቲያን እውነተኛ መምህራን  ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለማዳን ስራው፣ እርሱ ስለመሰረታት አንዲት ቤተክርስቲያን ክብር፣ በቤተክርስቲያን ስለሚገኘውም የቅዱሳን ኅብረትና የሰማያዊ ምስጢር መዝገብ መመስከር እንዲሁም በምንመሰክረው እውነት ጸንቶ መኖር ማለት ነው፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው ለሁሉም ነበር፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው በሚያምኑት ብቻ ሳይሆን በማያምኑ ሰዎችም ፊት ነበር፡፡ በሚከሷቸውና መከራ በሚያደርሱባቸው ሰዎች ፊት የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ይመሰክሩ ነበር፡፡ እውነትንም በመመስከራቸው በሥጋቸው ላይ የተለያየ መከራ ይፈራረቅባቸው ነበር፡፡ በግፍ ይገደሉም ነበር፡፡ ይህንን ምስክርነታቸውን የሰሙ ያዩ ሌሎች  ደግሞ እያመኑ አብረው ሰማዕትነትን ይቀበሉ ነበር፡፡ አምነው ለመመስከር ያልደፈሩትም እንዲሁ እነዚህ ሰማዕታትን እያዩ በእምነታቸው ይጸኑ ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ሰማዕትነት ‹‹ጧፍ›› ሆኖ እየነደዱ ለሌላው ማብራት ነው የሚባለው፡፡ ሰማዕታት ራሳቸው በእሳት በተመሰለ መከራ ውስጥ እያለፉ ሌላውን ወገናቸውን የወንጌልን ብርሀን እያበሩ ከጨለማ ያወጡት ነበር፡፡ ሰማዕታት በመከራ በመጽናት ለሌሎች ብርሃን መሆናቸውን ለማሰብም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት በጧፍ ወይም በሻማ ብርሃን እንዲነበቡ ሥርዓት ሰርታለች፡፡

ሰማዕታት ስለክርስቶስ የመሰከሩት በጽናትና በጥብዐት ነበር፡፡

ሰማዕታት እውነተኛይቱን ሃይማኖት የመሰከሩት በጥብዐት (ፍጽም በመጨከን) እና እስከመጨረሻው በመጽናት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ምድራዊ መደለያዎች ሲቀርቡላቸው እምቢ በማለት ሁሉን እያጡ አምላካቸውን ተከተሉ፡፡ እንደዛሬው ትውልድ “ለጊዜው ምስክርነታችንን ትተን ክፉ ዘመን ሲያልፍ ንስሐ እንገባለን” ብለው የስንፍናን ሀሳብ ለአእምሮአቸው አላሳዩትም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ‹‹ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። (ዕብ 11፡35)›› በማለት ገልጾታል፡፡ በቃላት ለመግለጽ የማይቻሉ መከራዎች ሲደርሱባቸው በቀራንዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ስለሁላችን የሞተውን ጌታቸውን እያሰቡ ይታገሱት ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የጠቀሳቸው የዘመነ ብሉይ ቅዱሳን ሰማዕታት የክርስቶስን መገለጥ ተስፋ አድርገው መከራን እንደተቀበሉ ሞት በተሸነፈበት፣ ትንሣኤ በታወጀበት በዘመነ ሐዲስ ያሉ ቅዱሳን ሰማዕታትም እንዲሁ በየዘመናቸው የመናፍቃንን፣ የአላውያን ባለስልጣናትን፣ እንዲሁም ለገንዘብ ለክብርና ለሥጋዊ ድሎት ብለው መከራ የሚያጸኑባቸውን ተረፈ አይሁድ ሳይፈሩና ሳያፍሩ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል/ይቀበላሉም፡፡ ይህንንም የሚያደርጉ ቅዱሳን በትንሣኤ ዘጉባኤ 30 እና 60 ከሚያፈሩት ምዕመናን የበለጠ ክብር እንደሚጠብቃቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡

ሰማዕታት በምስክርነታቸው ለሌሎች መዳንን ለራሳቸው አክሊልን አተረፉ፡፡

ሰማዕታት በእውነተኛ ምስክርነታቸው ለሥጋቸው ያተረፉት ነገር ቢኖር ሀብት ንብረት ወይም ሥልጣን ሳይሆን መከራን ብቻ ነበር፡፡ በዚያ መከራቸው ውስጥ ግን መክሊታቸውን ያተርፉ ነበር፡፡ የእነርሱን ምስክርነት እየሰሙና እያዩ መከራ ከሚያደርሱባቸው ጭምር የሚያምኑ ነበሩና፡፡ ከእነርሱም ጋር የሰማዕትነትን ጽዋ አብረው ይቀበሉ ነበር፡፡ ምድርም በሰማዕታቱ ደም ትታጠብ ነበር፡፡ በሰማይ ግን የሰማዕትነትን አክሊል አትርፈዋል፡፡ በሰማያዊው መንግስት እንደ ኮከብ አብርተዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ‹‹አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። (ራዕ 6፡9)›› ሲል የገለጸው እንዴት እንደከበሩ ያስረዳናል፡፡

እኛም የእነርሱን ምስክርነት በመዘከራችን በረከትን እናተርፋለን፡፡

ቤተክርስቲያናችን የሰማዕታትን መታሰቢያ የምታደርገው እንድንዘክራቸውም የምታስተምረው ታላቅ ዋጋ ስላለው ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያ ደረጃ የሰማዕታቱ ሕይወት/ተጋድሎ የክርስትና ሕይወት ሕያው ምሳሌ ነውና ሁላችን ከእነርሱ የተጋድሎ ሕይወት ተምረን በእምነታችን እንድንጸና ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ሰማዕት የተጋድሎ ሕይወት ውስጥ የምንማራቸው እጅግ ብዙ ቁምነገሮች አሉና፡፡ የሰማዕታቱ ሕይወት በራሱ የተግባር ወንጌል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሰማዕታቱን በመዘከራችን በረከት ረድኤትን እናገኛለንና ቤተክርስቲያን ይህንን አጽንታ ታስተምራለች፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእርሱ በመመስከር፣ እስከሞት ድረስ ሰማዕትነትን በመቀበል የቤተክርስቲያን ጌጥ ለሆኑ ደቀመዛሙርቱ በሰጠው ዘላለማዊ ቃልኪዳን “ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ  ስም ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋውን አያጣም፡፡” ማቴ. 10፡42 ያለው ይህን ያመለክታል፡፡ ለጊዜው ደቀ መዛሙርት የተባሉት በጽናት የተከተሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72 አርድዕትና 36ቱ ቅዱሳት አንስት ቢሆኑም የጌታ ቃልኪዳን ፈለገ ሐዋርያትን ተከትለው ለጽድቅ አገልግሎት በትህትና የሚፋጠኑትን፣ ስለ ጽድቅ አገልግሎትም መከራ የሚቀበሉትን እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚገለጡትን ቅዱሳን ሰማዕታት ሁሉ ይመለከታል፡፡

የዘመናችን ሰማዕትነትስ ምንድን ነው?

በየዘመናቱ የተነሱ ቅዱሳን ሰማዕታት ያደረጉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ ተመልክተናል፡፡ እኛም የሰማዕታት ተጋድሏቸውን በማመንና በቃልኪዳናቸው በመታገዝ የራሳችንን መዳን ልንፈጽም ይገባል እንጅ የሰማዕታትን ገድል እየተረክን ብቻ መኖር አይባንም፡፡ የቅዱሳን ቃልኪዳን ተካፋዮች የምንሆነው ከእነርሱ በሥጋ ስለተወለድን ወይም እነርሱ የጽድቅን አክሊል በተቀዳጁባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በመመላለሳችን ብቻ አይደለም፡ አይሁድ የአብርሃምን ሥራ ሳይሰሩ “አብርሃም አባት አለን” በማለት ብቻ እንዳልዳኑ (ዮሐ. 9) ሁላችንም እንደ አቅማችን የጽድቅን ስራ ያለመለገም ልንሰራ ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ አስቀድመን አባቶቻችንና እናቶቻችን ቅዱሳን ሰማዕታት ከእግዚአብሔር የተቀበሏትን አንዲት ሃይማኖት አስቀድመው ለፍርድ የተጻፉ መናፍቃንና ከሃድያን ከሚያመጡት ፈተና ሁሉ እንጠብቃት ዘንድ መጋደል እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል (ይሁዳ 1፡3-5)፡፡ በኃጢአት በተጎሳቆለ ማንነት የሰይጣንንና የመልእክተኞቹን ፈተና መቋቋም አይቻልምና፣ የምንድነውም የጸናች ሃይማኖትን ከኃጢአት ርቀን በምግባርና በትሩፋት ጸንተን በመጠበቅ ነውና፣ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረን የከበሩ ቅዱሳን ሰማዕታትን ልንመስላቸው ይገባል፡፡

ቅዱሳን ሰማዕታት ስለ ጽድቅ (እውነት) አገልግሎትና ስለ ቤተክርስቲያን ያለሃፍረትና ያለፍርሃት እንደመሰከሩ እኛም በዘመናችን ያሉ የመናፍቃን ክህደታቸው፣ የምንደኛ “አገልጋዮች” ሥም አጥፊነትና አስመሳይነታቸው፣ ከእምነትና ከእውቀት የተፋቱ፣ በግልብ ስሜት የሚመሩ የመናፍቃን፣ የሐሰተኛ መምህራን አዳማቂዎች ወሬና ዘለፋ ሳያስፈራን ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠች ሃይማኖት እንድንጋደል ያስፈልጋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ቅዱሳን ሰማዕታት ልጆች ስንሆን ለሥጋዊ ጥቅም፣ ዝናና ክብር ብለን እውነትን ከመመስከር፣ ከሐሰተኞች ጋር ካለመተባበር ወደኋላ ብንል የሰማዕታት በረከት ይቀርብናል፡፡ ሃይማኖታችንን ጠብቀን፣ በበጎ ምግባር አጊጠን፣ የቤተክርስቲያንን እውነት ያለሃፍረትና ያለፍርሃት መስክረን የቅዱሳን ሰማዕታትን በረከት እንድናገኝ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የሰማዕታት እናታቸው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮና መመሪያዎቹ

መንፈሳዊ አገልግሎት ምንድን ነው የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የሚኖረንን ሚና ለማወቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ‹‹መንፈሳዊ (Spiritual)›› እና ‹‹አገልግሎት (Service)›› የሚሉትን ቃላቶች የያዘ ሲሆን ‹‹መንፈሳዊ›› የሚለው ገላጭ የአገልግሎቱን ዓላማና መሪ የሚያሳይ ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ዓላማው የሰው ልጆች ድኅነት ነው፡፡ መሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሰው ልጆች ለመንግስተ ሰማያት እንዲበቁ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ‹‹መንፈሳዊ አገልግሎት›› ሊባል ይችላል፡፡ ይህም የሕይወትን ቃል ያላወቁ ወገኖች እንዲያውቁና እንዲያምኑ ማድረግ፣ ያመኑት ደግሞ እንዲጸኑና መንፈሳዊ ትሩፋትን እንዲሠሩ ማድረግን ያካትታል፡፡

የመንፈሳዊ አገልግሎት መሰረቱ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድና ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያተጋን አምላካዊ መመሪያ ነው፡፡ ከዘመነ አበው ጀምሮ፣ በዘመነ ኦሪትም በቅዱሳን አባቶችና ነቢያት አድሮ የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮንና መመሪያን የሰጠው በፍፁም አንድነትና በልዩ ሦስትነት የሚመሰገን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስም ከሦስቱ አካላት አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ግዕዘ ህፃናትን ሳያፋልስ በትህትና አድጎ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት በተግባር አስተምሮ ለቅዱሳን ሐዋርያት አብነት የሆነ የአገልግሎት ተልዕኮና መመሪያ ሰጥቷቸዋል፡፡ አብነት የሆነው ተልዕኮ ‹‹እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ›› የሚለው ሲሆን መሪ መመሪያው ደግሞ ‹‹ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ›› የሚለው ታላቅ ቃል ነው  (ማቴ 10፡16)፡፡ ጌታችን ይህንን ተልዕኮና መመሪያ የሰጠው ለጊዜው ለደቀ መዛሙርቱ ሲሆን ኋላም በእነርሱ እግር ተተክተው በመንፈሳዊ አገልግሎት ለሚሳተፉ ሁሉ ነው፡፡

የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ

በጌታችን ትምህርት በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ውስጥ በግና ተኩላ ተጠቅሰዋል፡፡ በግ የየዋሀን የእግዚአብሔር ልጆች ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ›› በማለት በእርሱ የሚያምኑትን ‹‹በጎቼ›› ብሏቸዋል (ዮሐ 10፡27)፡፡ እንዲሁም ለደቀ መዝሙሩ ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በጎቼን አሰማራ›› በማለት በጎች የተባሉ በእግዚአብሔር ቤት የሚኖሩ ምዕመናን መሆናቸውን አስተምሮናል (ዮሐ 21፡17)፡፡ በመጨረሻው የፍርድ ቀንም ‹‹በጎችን በቀኙ ያቆማቸዋል›› ያለው በጎች የጻድቃን ምሳሌ ስለሆኑ ነው (ማቴ 25፡33)፡፡ ጌታችን መቶ በጎች ያሉት ሰውን ምሳሌ አድርጎ ያስተማረውም በሰማይ ያሉ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክትንና ጠፍቶ የነበውን የሰውን ልጅ የሚያሳይ ነው (ሉቃ 15፡3)፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የእግዚአብሔር በግ›› ያለው ስለ እኛ በፈቃዱ በተቀበለው ሞቱ ሞትን ስላስወገደልን የመዳናችንም መሰረት ስለሆነልን ነው (ዮሐ 1፡29)፡፡ ክርስቶስም በትምህርቱ ‹‹የበጎች እረኛ እኔ ነኝ›› ያለው ለዚሁ ነው (ዮሐ 10፡27)፡፡ የዋሁ አቤል የበጎች እረኛ እንደነበር ተገልጿል (ዘፍ 4፡2)፡፡ በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እኛ የማሰማርያው በጎች ነን (መዝ 99፡3)›› የተባለውም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የዋሀንን ይመለከታል፡፡

በአንጻሩ ተኩላ የነጣቂዎች፣ የተንኮለኞችና የከሳሾች ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ከሆኑ ተኩላዎች ተጠበቁ (ማቴ 7፡15)›› ያለው ተኩላዎች ተመሳስለው የሚያታልሉ ጉዳትም የሚያደርሱ ስለሆኑ ነው፡፡ ተኩላ እረኛ የሌላቸውን ወይም ሰነፍ እረኛ ያላቸውን በጎች ይነጥቃል (ዮሐ 10፡12)፡፡ በአጠቃላይ ተኩላ የክፉዎች ምሳሌ ሆኖ ነው የሚወሰደው፡፡ ‹‹ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነበር›› የተባለው ጠዋት ሌላ ማታ ሌላ ስለነበር ነው (ዘፍ 49፡27)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከእኔ በኋላ ለመንጋይቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኩላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ፡፡ ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሳሉ።›› (ሐዋ. 20፡29-30) ያለው ከዚያን ዘመን ጀምሮ በእውነተኛ የወንጌል አገልግሎት ጠማማ ነገርን ያስተማሩትንና የሚያስተምሩትን ሁሉ ይመለከታል፡፡ በመንፈሳዊ ተልዕኮ የሚሰማሩ ሰዎች እንደየግብራቸው በበጎችና በተኩላዎች የተመሰሉ ሲሆን እንደ በጎች በእግዚአብሔር የተወደደ ተልዕኮ ለመፈጸም አራት ዋና ዋና ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ማንኛውም አገልጋይ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰማራ ገንዘብ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

የአገልግሎቱ ባለቤትና መሪ ማን እንደሆነ ማወቅ ለእርሱም መታመን

በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልእኮ ላኪው እግዚአብሔር ነው፡፡ ተልዕኮውን ለመፈጸም ፍላጎት፣ እውቀትና ክህሎት ቢያስፈልግም ሰው ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚላከው በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ በእውቀቱ ብዛት አይደለም፡፡ አገልጋይ በሰዎች ጋባዥነት ወደ አገልግሎት ቢቀርብም ሰዎች የተልዕኮው ምክንያት እንጂ ላኪዎች አይደሉም፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የተልዕኮውን ባለቤት (ላኪውን) ማስተዋል እጅግ መሰረታዊና የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ መልእክተኛ የላኪውን ፈቃድ እንደሚፈጽም ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይም የጠራውንና የላከውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሊፈጽም እንጂ የራሱን ፈቃድ ወይም የሌሎች ሰዎችን ፈቃድ ሊፈጽም አይገባም፡፡

የተጠራንበትንና የተላክንበትን ዓላማ (ለምን ተላክን የሚለውን) ማወቅ

እግዚአብሔር ሰውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚልከው ‹‹መንፈሳዊ›› ለሆነ ሥራ ነው፡፡ ይህም እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል በቃልና በሕይወት በመስበክ ሰዎችን ለድኅነት ማብቃት ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ የሚያገለግልበት ዓለማ ሌሎች እንዲድኑ እርሱም በመክሊቱ እንዲያተርፍበት ነው፡፡ ጌታችን በመክሊቱ ምሳሌ እንዳስተማረው የአገልግሎቱ ዋናውም (ጸጋው) ይሁን በአገልግሎቱ የሚገኘው ትርፍ የእርሱ የባለቤቱ እንጂ የአገልጋዩ አይደለም፡፡ አገልጋይ የአገልግሎቱን ዋጋ የዘላለም ሕይወትን ያገኛል፡፡ በጥቂት በመታመኑ በብዙ ይሾማል፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ እምነት እንዲሰፋ፣ መልካም ስነምግባር እንዲስፋፋ፣ ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርስ፣ የእርሱም ጽናቱ ይረጋገጥ ዘንድ ያገለግላል፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ከዚህ የተለየ ዓላማ ከያዘ ‹‹መንፈሳዊ›› መሆኑ ያበቃል፡፡

የተልዕኮው ስፍራ ፈተና የሚበዛበት መሆኑን ማስተዋል

በወንጌሉ እንደተገለጸው የተልዕኮው ስፍራ ‹‹በተኩላዎች መካከል›› እንጂ ‹‹በበጎች መካከል›› አይደለም፡፡ በዚያም ስፍራ የሆነው ቢቻል የተኩላ ጸባይ ያላቸው የበግ ጸባይ እንዲይዙ ለማስቻል ነው፡፡ ይህ ባይሆን ደግሞ ተኩላዎቹ ሌሎች በጎችን እንዳይነጥቁ ለመከላከል ነው፡፡ ይህም ካልተቻለ ደግሞ አገልጋዩ የራሱን ግዴታ እንዲወጣ ይላካል፡፡ ተኩላ ያው ተኩላ ነውና በተኩላ መካከል የሚፈጸም አገልግሎት መሰደብ፣ መከሰስ፣ መንገላታትና መከራ መቀበል ያለበት ተልዕኮ ነው፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ክርስቶስ በጎችን ወደ ተኩላዎች ይልካል፡፡ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ ዲያብሎስ ተኩላዎችን ወደ በጎች ይልካል፡፡ እንግዲህ መንፈሳዊው አገልግሎት እንደዚህ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ነው የሚከናወነው፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መስክ ፈታኝ ቢሆንም አለማገልገል ግን አማራጭ መፍትሔ አይደለም፡፡ ከተኩላዎች ጋር መደራደርም እንዲሁ፡፡

ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሰማራት በግ ሆኖ መገኘት 

ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሰማራት ለራሳችን መልካም (በግ) ሆነን መገኘት ያስፈልጋል፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት በግ ወደ ተኩላ ይላካል እንጂ ተኩላ ወደ ተኩላ አይላክም፡፡ ቢላክም አይጠቅምም፡፡  መንፈሳዊ አገልጋይ እንደ በግ በተኩላ መካከል ሲላክ በዚያው በተኩላ ተበልቶና ጠፍቶ እንዳይቀር መንፈሳዊ ትጋትን ገንዘብ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለማትረፍ እንጂ ዋናውን ለማጣት የሚነግድ ነጋዴ እንደሌለ ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይም ለማትረፍ ካልሆነም ለመትረፍ ሊተጋ ይገባል፡፡

የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ

በመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ ውስጥ ርግብና እባብ ተጠቅሰዋል፡፡ ርግብ የየዋሀን ምሳሌ ናት፡፡ ርግብ የጥፋት ውኃን መጉደል ለኖኅ ያበሰረች፣ በኖኅ መርከብ ውስጥም እንቁላሏን በእባብ አፍ ውስጥ የጣለች የዋህ እንስሳ ናት (ዘፍ 8፡11)፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በርግብ አምሳል እንደወረደ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት (ማቴ 3፡16)፡፡ ርግብ በብሉይ ኪዳን ለኃጢአት ማስተስረያነት መስዋዕት ሆና ትቀርብም ነበር (ዘፍ 5፡7)፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የወለደችልም ቅድስት ድንግል ማርያምም ‹‹መልካሚቱ ርግብ›› ትባላለች (የእሑድ ውዳሴ ማርያም)፡፡

በሌላ በኩል እባብ ልባም፣ ጥበበኛ፣ ተንኮለኛና መርዘኛ እንስሳ ነው፡፡ ‹‹ከምድር አውሬ ሁሉ እባብ ተንኮለኛ ነበር›› እንደተባለ (ዘፍ 3፡1) እባብ ተንኮለኛ አውሬ ነበር፡፡ እባብ በኖኅ ዘመን የርግብን እንቁላል ያልዋጠ (እንዳይጣል)፣ መርዙን ውጭ አስቀምጦ ውኃ የሚጠጣ (እንዳይገድለው)፣ የዕፀ ዘዌን በጥበብ የሚያሳልፍ (እንዳያደክመው) ልባም ፍጡር ነው፡፡ እባብ በገነት፣ በፈርዖን ቤተመንግስት፣ በበረሀ፣ እንዲሁም በመላጥያ ደሴት እንደተገኘ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ በርግብና በእባብ ምሳሌነት ከመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ጋር አብረው የተሰጡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያዎች (መርሆዎች) ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-

እንደ ርግብ የዋህ መሆን (innocence)

ጌታችን እንደ ርግብ የዋህ ሁኑ ሲል ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ታመኑ (የቁራ መልእክተኛ እንዳትሆኑ)፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ሰላምን ስበኩ (ጥልና ክርክር ከእናንተ ይራቅ)፣ በመንፈስ ቅዱስ ተመሩ (የራሳችሁን ፍላጎት ግቱ)፣ ሰው የሚፈልገውን ሳይሆን ለሰው የሚያስፈልገውን በመስበክ አስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ መስዋዕትነት ክፈሉ ማለቱ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹እንደ ርግብ የዋህ ሁኑ›› አለ እንጂ ‹‹ርግብ ሁኑ›› አላለም፡፡ ርግብን መምሰል ያለብን በሦስት ነገሮች ነው፡፡

 • በርህራሄ፡- ይቅር የምንልና በሌሎች ላይ ቂም የማንይዝ በመሆን
 • በየዋህነት፡- የማናታልል የማንጎዳ በመሆን (ርግብ አትዋጋም፣ አትናከስም፣ ግን ትበራለችና)
 • በንጽህና፡- ራሳችንን ከኃጢአት በመጠበቅና በንስሐ ሕይወት በመኖር

እንደ እባብ ብልህ መሆን (intelligence)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያው ‹‹እንደ እባብ ብልህ ሁኑ›› ያለው አገልጋይ ሲያገለግል ዋናውን እንዳያጣ (ራሱን እንዲጠብቅ)፣ ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆን፣ በሌሎች ክፋት ተስቦ እንዳይፈተንና ካለው መንፈሳዊ ጽናት እንዳይወድቅ ለማስገንዘብ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ነጥብ አለ፡፡ ጌታችን ‹‹ብልህ/ልባም›› እንጂ ‹‹ብልጥ ሁኑ›› አላለም፡፡ ሌላውን እንዳንጎዳ ‹‹እንደ እባብ ልባም ሁኑ›› አለ እንጂ ‹‹እባብ ሁኑ›› አላለም፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ከራስ ይልቅ ሌላውን ማስቀደም ይጠይቃልና፡፡ እንደ እባብ ልባም ሁኑ ሲባል በሦስት ነገሮች ነው፡፡

 • ፈጣን ዐይኖች (sharp eyes)፡- ዐይኖቻችንን በእውቀት በማብራት ፈጣን መሆን
 • የማይደለሉ ጆሮዎች (Focused ears)፡- በአስመሰዮች አሉባልታና በወሬ የማይታለሉ፣ የማይረቱ ጆሮዎች እንዲኖሩን
 • በጥበብ መኖር (Wisdom)፡- ራስን በመጠበቅ  እምነታችንን በማጽናት መኖር

ነገር ግን ከእባብ መውሰድ የሌለብን ነገሮችም እንዲሁ አሉ፡፡ የእባብ መብል ትቢያ ነው (ኤሳ 65፡25)፡፡ የእባብ መንገድም በአለት መካከል ነው (ምሳ 30፡19)፡፡ እባብ ቆዳውን ይቀይራል (ማቴ 12፡45)፡፡ እባብ መርዛማ ነው (መዝ 58፡4)፡፡ እባብ ተንኮለኛ ነው (ዘፍ 3፡1-20)፡፡ እባብ የዲያብሎስ ማደርያ በመሆን ለአዳም መሳሳት ምክንያት ስለነበር በእግዚአብሔር ተረግሟል፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉት የእባብ ባህርያት ልንርቅ ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ያለ አገልጋይ የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮና መመሪያዎቹን ሁል ጊዜ ማስተዋልና የአገልግሎቱም መመሪያ ማድረግ አለበት፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ባለቤቱ በመንፈስ የምናገለግለው እግዚአብሔርን መሆኑን፣ የአገልግሎቱም ዓላማ ‹‹መንፈሳዊ›› መሆኑን፣ የአገልግሎቱም መሪ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን፣ የአገልግሎቱም መስክ ለሰው ሕይወት ፈታኝ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ከዚህ ዓይነት ማስተዋል ጋር የዋህነትንና ብልህነትን አመጣጥኖና አዋሕዶ በመያዝ መንፈሳዊ አገልግሎትን መፈጸም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚያስጨንቅ ነገር ሲመጣ ግን በጸሎትና በምልጃ ወደ አገልግሎቱ ባለቤት ማመልከት ይገባል እንጂ ወደ ከንቱ ክርክርና ንትርክ መግባት አያስፈልግም፡፡ መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን ማውረድ ያስፈልጋል እንጂ፡፡ እነዚህን የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮና መመሪያዎች ተጠቅመን በአገልግሎታችን እንድንተጋ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳኑ ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምስጢራዊ ስያሜዎች

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያንን በተለያዩ ስያሜዎች በተለያዩ ዘመናት ሲገልጿት ኖረዋል፡፡  እነዚህ ሊቃውንት ያስቀመጧቸው የቤተክርስቲያን ስያሜዎች በመጻሕፍት የተገለፀውን እውነትና በትውፊት የተቀበሉትን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት በማድረግ የተሰጡ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ዓላማቸውም የቤተክርስቲያኒቱን ምንነታና ማንነት በአጭር ቃላት በገላጭ ቋንቋ ለማስተማርና ለማስረዳት ነው፡፡ እነዚህም ስያሜዎች ከትውልድ ትውልድ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሲተላለፉ ቆይተው ከእኛ ዘመን ደርሰዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች እነዚህ ስያሜዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ አይደሉም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ስያሜዎች ያስቀመጡልን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ የተማሩ፣ የክርስቶስን ወንጌል በጥልቀት ያወቁ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንንም የጠነቀቁ፣ ከማወቅም በላይ በሕይወታቸው የኖሩ ናቸው፡፡ ያስቀመጡልን ስያሜዎችም መጽሀፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።›› እንዳለ እኛ እነርሱን አብነት አድርገን የምንኖር ክርስቲያኖች እነርስ ያስቀመጧቸውን ስያሜዎች ተጠቅመን ስለ ቤተክርስቲያን እናስተምራለን፡፡

የበተክርስቲያን አስተምህሮና ምሥጢር ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ብዙ ስያሜዎችን ለቤተክርስቲያን ሰጥተው አስተምረዋል፡፡ የሚከተሉትን ለምሳሌ ያህል አቀረብን እንጂ ሌሎችም ስያሜዎች ይኖራሉ፡፡ የቤተክርስቲያንን ስያሜዎና መነሻቸውን ለመረዳት ያህን ግን የሚከተሉትን ዋና ዋና ስያሜዎች ከአጭር ማብራሪያ ጋር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ዝርዝሩ ሁሉንም ስያሜዎች የሚያጠቃልል እንዳልሆነ ግን አንባቢው ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “የክርስቶስ ሙሽራ” ትባላለች፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን የዓለምን ኃጢአት በቤዛነቱ ያስወገደ የእግዚአብሔር በግ፣ በተዋህዶ የከበረ ወልደ አብ፣ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ትባላለች፡፡ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅና በጥልቀት የተቀመጠ ነው፡፡«ሙሽራ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ድምፁን ለመስማት አጠገቡ የሚቆሙ ሚዜ ግን የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፡፡ እርሱም አሁን ተፈጽሟል፡፡ እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ላንስ ይገባል፡፡»/ዮሐ 3. /  ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሙሽራ በሙሽሪት እና በሚዜ መስሎ የተናገረው የክርስቶስን፣ የቤተክርስቲያንን እና እንደ ራሱ ያሉ አገልጋዮችን ነገር ነው፡፡ በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት በሙሽራ እና በሙሽሪት /በባል እና በሚስት/ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር የሚያመሳስሉት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡

 • ሙሽሪትን /ሚስቱን/ የሚመርጣት፣ የሚያጫት ሙሽራው /ባል/ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመረጣትና ሙሽራው እንድትሆን ያደረጋት ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡
 • ባል ሚስቱን መጠበቅ፣ መንከባከብ ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ መውደድ ይጠበቅበታል፤ ክርስቶስም ስለ ቤተክርስቲያን ይህንን አድርጓል፡፡ ሚስት ራሷን ለባሏ ራሷን ማስገዛት አለባት፡፡ ቤተክርስቲያንም ለክርስቶስ እንዲሁ ማድረግ አለባት፡፡
 • ሙሽሪት በሰርጓ ቀን ራሷን አስውባ ትቀርባለች፤ ክርስቶስም ቤተክርስቲያንን ወደ ራሱ ያቀረባት ሙሽራው ያደረጋት በሥጋውና በደሙ አንጽቶ፤ ነውሯን አስወግዶና አስውቦ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን እና የሰው ልጆችን ግንኙነት በሙሽራና በሙሽሪት /በባልና በሚስት/ እየመሰሉ በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ብዙዎች አስተምረዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ከነበሩት መካከል በፍቅር ግጥም መልክ የተጻፈው መኅልየ መኅልይ ዘሰሎሞን፣ ትንቢተ ሕዝቅኤል /ምዕራፍ 16/፣ ትንቢተ ሆሴዕ /ምዕ.1/ ተጠቃሸ ናቸው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ በሁለተኛው የቆሮንቶስ መልእክቱ «እናንተ እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ» /11-2/ ብሎ ጽፏል፡፡ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱም እንዲህ ይላል፤ «ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነው ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው፡፡ ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ በቃሉ አማካኝነት በማንፃት እንድትቀደስ. . . አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተክርስቲያን አድርጎ ሊያቀርባት ነው. . . ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይኽንን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እናገራለሁ፡፡» /5-22-32/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮትም በራእይ መጽሐፉ ሰማያዊት ቤተክርስቲያን የሆነች አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን የበጉ ሙሽራ ይላታል፡፡ «ቅድሰቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» /21-1-9/፡፡ ከዚህም አንፃር ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች አባቶቻችን ያስተማሩት በምድር የምናያት ቤተክርስቲያን በሰማይ ያለችው የቅድስት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ነው፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “ስንዱ እመቤት” ትባላለች፡፡

ቤተክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት በመሆኗ መንፈሳዊ ምስጢርን፣ ታሪክንና ትውፊትን በማስተባበር ልዩና እንደ እንቁ የሚያበራ ሥርዓትን ሠርታለች፡፡በረከት ያለበት የትምህርት ቤት ገበታ፣ ከነፍስ የሚያጣምር፣ በጥቂት ጊዚያዊ መቸገር ውስጥ የብዙ ዘመን ሀብታም የሚያደርግ፣ ከራስ አልፎ ትውልድ የሚታነጽበት፣ ዘመንን የሚሻገር/የሚያሻግር ይሄ ይቀረዋል የማይባል የሊቃውንት ዐውድማ  የሆኑ አብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ስንዱ እመቤትነቷን ታሳያለች፡፡ እነዚህ አብነት ትምህርት ቤቶች ቅዱሳን ኒቢያትና ሐዋርያት የሰበኩትን የጌታችንን ቅዱስ ቃል ከነትርጓሜው ሳይፋለስና ሳይዛነፍ በዘመናት መካከል እንዲሻገር በማድረግ ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል አጋዥነት የዓለምን ፈተና፣ የመናፍቃንን ክህደት እያሸነፈች እስከ ምጽዓተ ክርስቶስ ድረስ እንድትቆይ ያግዟታልን።

በዚህ መልክ ቤተክርስቲያን ሁሉን በአግባቡና ለሰው ልጅ መዳን እንዲሆን አድርጋ አዘጋጅታለች፡፡ ለህፃናትና ለወጣቶች ለጎልማሶችና ለአረጋውያን የሚሆን የወንጌል ትምህርትና የምስጋና አገልግሎት አዘጋጅታለች፡፡ ለእህቶችና ለወንድሞች እንዲሆን አድርጋ ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ለሚኖረው ትውልድ መንፈሳዊ መጻሕፍትንና የተለያዩ ቅርሶችን አበርክታለች፡፡ ለአስተዳደር ለሥርዓተ ትምህርት ለሕንፃ ወዘተ ጥበብ መጎልበት የራስዋን ድርሻ አበርክታለች፡፡ ለዚህም ነው የጎደለባት የሌላት ስንዱ እመቤት የምትባለው፡፡

ከዚህ ውጭ ሁሉን ነገር የተሟላላትንና ስንዱ የሆነችውን ቤተክርስቲያን ብዙ ነገር የጎደላትና ኋላ ቀር አድርጎ ማቅረብ የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ እኛ አላወቅነው ይሆናል እንጂ ሁሉን ነገር የጠነቀቀች ቤተክርስቲያን ነው አባቶቻቸን ያስረከቡን፡፡ የእኛ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮና ሥርዓት መሠረቱንና ጥልቀቱን አለማወቅ ራሳችንን አላዋቂ ያደርገናል እነጂ ቤተክርስቲያንን ስንዱ እመቤት ከመባል አያስቀራትም፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ በካህናቱ፣ በመምህራኑና በምዕመናኑ የእውቀት ልክ መለካት የለበትም፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “የጸጋው ግምጃ ቤት ትባላለች፡፡

ቤተክርስቲያን የክርስቶስ የጸጋው ግምጃ ቤት ናት፡፡ ይህም የክርስቶስ ጸጋ በሰፊው የሚገኝባትና የሚታደልባት ናት ለማለት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት ያመኑ፣ ቅዱሣት መጻሕፍትን በተግባር የሚኖሩ ምዕመናንና ምዕመናት የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ያለመከልከል የሚቀበሉበት ዘመን ነው፡፡ ከጸጋ ስጦታዎች ዋና ዋናዎቹ በጥምቀት ከእግዚአብሔር በጸጋ መወለድ፣ በቅብዓ ሜሮን ልጅነትን ማጽናት፣ የክርስቶስ ቅዱስ ስጋና ክቡር ደም በንስሓ በተዘጋጀ ልቦና ቀርቦ በመቀበል ከክርስቶስ ህያውነት የተነሳ ለዘለዓለም ህያው ሆኖ መኖር ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጸጋዎች  በእምነት ለቀረቡ ሰዎች የሚታደሉት በቤተክርስቲያን አማካኝነት ነውና ቅድስት ቤተክርስቲያን የጸጋ ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር የጸጋው ግምጃ ቤት ትባላለች፡፡ ድል ያደረጉ ቅዱሳን በእርስዋ ኖረው የቅድስናን ጸጋ አግኝተዋል፤ ካህናት በእርስዋ ተምረው የምስጋናን ጸጋ ለብሰዋል፤ ሊቃውንት በእርስዋ ኖረው መጻሕፍትን የማወቅና የማስተማር ጸጋ ተቀብለዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ያለው ጸጋ ምንጩ አንድ ቢሆንም እርሱ ግን የተለያየ ነው፡፡ የጸጋ ስጦታን በሚመለከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-

“ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።” ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ጸጋ በቤተክርስቲያን አማካኝነት የባህርይ አምላክ ከሆነው ከክርስቶስ ይገኛልና ቤተክርስቲያን የጸጋ ግምጃ ቤት  ናት፡፡

በሌላም ስፍራ ሐዋርያው “እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር።” ይላል፡፡ ሮሜ 12፡6-8 ሰው በቤተክርስቲያን ሲኖር በእነዚህ ጸጋዎች ተጠቅሞ ያገለግል ዘንድ ቤተክርስቲያን የጸጋ ግምጃ ቤት ተብላለች፡፡

ቅዱስ ኤራቅሊስ “ፍጹም ልጅነትን ድኅነትን የተመላች የቅድስት ቤተክርስቲያንን የክብሯን ብዛት አንደበት ሊናገረው አይችልም፤ በዚህ ምድራውያን ሀብታት አሉ፤ ግን ስለምድራውያን ፈንታ ሰማያውያን ሀብታትን ሰጠን፡፡” በማለት የቤተክርስቲያን ጸጋና ክብር ተነግሮ የማያልቅ መሆኑን ጽፏል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ ምዕራፍ 49፡16

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “አካለ ክርስቶስ” ትባላለች፡፡

ቤተክርስቲያን አካለ ክርስቶስ (የክርስቶስ አካል) ትባላለች፡፡ ለምን የክርስቶስ አካል ተባለች ቢባል ይህ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ እውነት ስለሆነ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።›› ብሎ እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቲያኖችም ኅብረት የክርስቶስ አካል መሆኑን አስተምሯል፡፡ 1ኛ ቆሮ 12፡27-28

በተጨማሪም ‹‹አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።›› በማለት ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል መሆኗን አስረግጦ ጽፏል፡፡  ቆላ 1፡ 18 24-25

እንዲሁም ‹‹ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል።›› ሲል አካሉን ቤተክርስቲያንን የሚጠብቃት ራስ የሆናት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በሰፊው አብራርቷል፡፡  ኤፌ 5፡23 30

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “ባህረ ጥበባት” ትባላለች፡፡

ባሕረ ጥበባትና ስንዱ እመቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል አንዱ የሒሳብ ስሌት ሰርታ የዘመን መቁጠሪያ ሳይንስን (ባሕረ ሐሳብን) ቀምራ አበቅቴና መጥቅን ለይታ የአጿማትና የበዓላትን ዕለታት ወስና ለትውልድ ማስተለለፏ ነው፡፡ በመሆኑ ዘወትር በየዓመቱ ሰባቱን የአዋጅ አጽዋማት ታውጃለች፣

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።  ምሳሌ 1፡7›› እንደተባለ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን መፍራትን በማስተማር የሰው ልጆች ወደ ጥበብ እንዲደርሱ ታደርጋለችና ባህረ ጥበባት ተብላለች፡፡ አንዳንዶች ቤተክርስቲያንን ባለማወቅ ኋላ ቀር አድርገው ቢስሏትም ቤተክርስቲያን ግን የጥበብ ማዕከል ናት፡፡

ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝሙር ‹‹የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል። መዝ 37፡30›› እንዳለ የጽድቅና የጻድቃን መገኛ ቤተክርስቲያን ናትን ባህረ ጥበባበት (የጥበባበት ባህር) ተብላለች፡፡ ከቤተክርስቲያን ውጭ ጥበብ የለም፡፡ ካለም መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማዊ ጥበብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ሕይወት የሚያደርስ ጥበብ አይደለም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልክቱ ‹‹ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። ያዕ 1፡5 3፡17›› እንዳለ ይህች ጥበብና የጥበብ ባለቤት የሚገኙባት ቤተክርስቲያን የጥባብ መገኛ ትባላለች፡፡

‹‹ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች። ባሪያዎችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች። አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች። ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ። ምሳሌ 9፡1-6›› በዚህ አስተምህሮ ጥበብ የተባለች ባህረ ጥባበት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ ክርስቶስ በዚች ቤተክርስቲያን ሆኖ ይህንን ያደርጋልና፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “መዝገበ ምሥጢር” ትባላለች፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን የማትመረመርና ጥልቅ የሆነች ‹‹መዝገበ ምሥጢር›› ትባላለች፡፡ ይህም የምሥጢር መዝገብ ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን አንብበው የማይጨርስዋት የምሥጢር መዝገብ ናት፡፡የሰማዩ አምላክ ምሥጢር የሚነገርባት፣ የድኅነት ምሥጢር የሚከናወንባት ስለሆነች መዝገበ ምሥጢር ትባላለች፡፡ ለዚህም የእምነት መሠረት በሆኑት አምስቱ አዕማደ ምሥጢር (ምሥጢረ ሥላሴ፡ ምሥጢረ ሥጋዌ፡ ምሥጢረ ጥምቀት፡ ምሥጢረ ቁርባንና ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን) የጸናች ናትና የምሥጢር መዝገብ መባሏ ተገቢ የሆነ ስያሜ ነው፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰባት ምሥጢራት በቤተክርስቲያን ይፈጸማሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ምሥጢራቱም ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊልና ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በዓይን የማይታዩ በእጅ የማይዳሰሱ ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ ጸጋ ለምዕመናን የሚታደልባቸው የሚፈጸምባቸው ናቸው፡፡

እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሥጢራት እያንዳንዳቸው እጅግ ጥልቅ የሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህን ምሥጢራት ጠብቃና አስጠብቃ፣ አስተምራና አሳውቃ፣ ፈጽማና ተካፋይ አድርጋ የሰውን ልጅ ለዘላለም ሕይወት የምታበቃ ቤተክርስቲያን መዝገበ ምሥጢር ብትባል ያንስባት ይሆናል እንጂ አይበዛባትም፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “የድሆች መጠጊያ” ትባላለች፡፡

በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር በተገለጠ እውነት እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡ በዚህ ረገድ ድህነት ብዙ ዘርፍ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለማስረጃ ያህል ግን የሚከተሉትን እንመልከት፡፡

የእውቀት ድህነት፡- መንፈሳዊ እውቀትን የተራቡ ወደ ቤተክርስቲያን መጥተው ቃለ እግዚአብሔርን ተምረው ከድህነት ይወጣሉና ቤተክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡ እነዚህ ድሆችን መመገብ የመምህራን ድርሻ ነው፡፡

የምግባር ድህነት፡- መልካም ምግባርን የናፈቁና በኃጢአት የተዘፈቁ ወደ ቤተክርስቲያን መጥተው ከእስዋ ተጠግተውና ንስሐ ገብተው ከኃጢአታቸውና ከምግባር ድህነት ይላቀቃሉና ቤተክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡ ይህንን አይነት ድህነት መዋጋት የካህናት ድርሻ ነው፡፡

የመንፈስ ድህነት፡- ያላቸውን ትተው ራሳቸውን በመንፈስ ድሀ ያደረጉ ሰዎች በቤተክርስቲያን ሆነው ‹‹በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።›› እንደተባለ መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉና ቤተክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡

ሥጋዊ ድህነት፡- በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ ምግበ ሥጋን የተራቡ፣ ቀዝቃዛ ውኃ አጥተው የተጠሙ፣ እራፊ ጨርቅ አጥተው የታረዙ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ተጠግተው ጊዜያዊና ዘላቂ ድጋፍ ያገኛሉና ቤተክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡ እነዚህን መርዳት የሁሉም ሕዘበ ክርስቲያን ድርሻ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን የድሆች እንጂ የድህነት መጠጊያ አይደለችም፡፡

 1. እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን “ተጋዳይዋና ድል አድራጊዋ” ትባላለች፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ …) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ በሰማይ ያለችው ቤተክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን ለመቀበል እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊዋ ቤተክርስቲያን (Church Triumphant) ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ ቤተክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተክርስቲያን (Church Militant) ይሏታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «ሰውን ብትታገል ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ቤተክርስቱያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም» እንዳለው በዚህ ዓለም ያለችው ቤተክርስቲያን ሐዋርያት በባሕር ላይ በታንኳ እየሄዱ ሳለ ጌታችን አብሯቸው በመካከላቸውና በታንኳው ውስጥ እያለ፣ ነገር ግን በኃይለኛ ማዕበል ትናወጥ እንደ ነበረችው ታንኳ በተለያዩ ፈተናዎች ትናወጻለች፡፡ አንዳንድ ጊዜም በውስጧ ያለው ጌታ የማይሰማና የተዋት፣ መከራዋን እያየ ዝም ያላት፣ ባለቤት የሌላት እስክትመስል ድረስ በውስጧ ያሉና በተለያዩ ነገሮች ተጨንቀው የሚያማርሩና የሚያዝኑ ልጆቿም ሰሚ የሌላቸው የሙት ልጆች እስኪመስሉ ድረስ ባለቤቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝም ይላል፡፡ ሐዋርያትንም “ስንጠፋ አይገድህምን?” እስኪሉ ያደረሳቸው ይህ ነበር፡፡ ማቴ. 8፡23-27

ቅድስት ቤተክርስቲያን የባለቤቷ የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ስለሆነች ጠባቂዋና ተንከባካቢዋ እርሱ ራሱ ነው፡፡ ምንም እንኳ እርሱ በሚያውቀውና በተለያዩ ምክንያቶች እንድትፈተን ቢፈቅድም እንድትጠፋ ግን አይተዋትም፡፡ ይህ ማለት ግን በውስጧ ያሉ አባላት በጥርጥርና በልዩ ልዩ ፈተናዎች አይሰናከሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን ቤተ ክርስቲያን የራሱ የክርስቶስ አካሉ እንደ መሆኗ ራሷ የሆነ እርሱ ለአካሉ ለምእመናን የሚያስፈልገውን ያውቃል፣ ያዘጋጃል፣ ይሰጣል፡፡

ትንሣኤ፡ በሦስተኛውም ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሐዳት!

Tinase2

«ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፤ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን»

በኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩት ዐበይት በዓላት መካከል የትንሣኤ በዓል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ትንሣኤ (resurrection) የሚለው ቃል ‹‹ተንሥአ›› ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹መነሣት፣ አነሣሥ›› ማለት ነው። እስራኤል ዘሥጋ ያከብሩት የነበረው የፋሲካ (የመሻገሪያ) በዓል ከግብፅ ባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት ምድር የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር። በሐዲስ ኪዳን የሚከበረው የክርስቶስ ትንሣኤ ግን እስራኤል ዘነፍስ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣ ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን፣ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነጻነት በዓላችን ነው። «ትንሣኤ» ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲያመሰጥሩት አምስት አይነት ትርጉም አለው፡፡ እነዚህም፡-

 1.  ትንሣኤ ኅሊና፡ ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ)
 2. ትንሣኤ ልቡና፡ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር
 3. ትንሣኤ ሙታን፡ ለጊዜው የሙታን በሥጋ (በተአምራት) መነሣት  ሲሆን ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል
 4. ትንሣኤ ዘክርስቶስ፡ የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት
 5. ትንሣኤ ዘጉባኤ፡ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ

ትንሣኤ ዘክርስቶስን በተመለከተ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ ከሞት የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ የቤተከርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌም የተመሰለለት፣ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌውም ያስተማረለት፣ መላእክት ያበሰሩት፣ ሰዎችም መቃብሩን አይተው ያረጋገጡት፣ እርሱም ተገልጦ መነሳቱን ያረጋገጠበት ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ አጭር ጽሑፍም እነዚህን የትንሣኤውን ምስጢር የሚገልጡ ክፍሎችን እንዳስሳለን፡፡

አስቀድሞ ስለትንሣኤው በትንቢት ተነገረ

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት «ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው የትንሳኤውን ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው (መዝ 15፡10)፡፡ እንዲሁም ‹‹ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም። ወከመ ኃያል ኅዳገ ወይን። ወቀተሎ ፀሮ በድኅሬሁ።/እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ያለው የጌታን ትንሣኤ ያመለክታል (መዝ 77፡65)። ነቢዩ ሆሴዕም «ኑ÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፤ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፤ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል (ሆሴ 6፡12)» ሲል የትንሣኤውን ምስጢር በትንቢት ተናግሯል፡፡ ነቢዩ ዮናስ በብሉይ ኪዳን የትንሣኤው ምሳሌ ነበር፡፡  ‹‹ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ  ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሎ ጌታችን ያስተማረውም ለዚህ ነው (ማቴ 12፡38-40)።

ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱም ስለትንሣኤው አስተማረ

ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ስለትንሳኤው ብዙ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱና ለሕዝቡ እንዲሁም ለፈሪሳዊያን ጭምር አስተምሯቸዋል፡፡ ‹‹እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል (ማቴ 20፡18-19)›› በማለት ስለትንሳኤው ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል (ማቴ 16፡21)፡፡

በገሊላም ሲመላለሱ «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል (ማቴ 17፡20)፡፡ «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡  ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል (ዮሐ 10፡17)፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም “በሦስተኛውም ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሐዳት” ያለው በገዛ ስልጣኑ መነሳቱን ሲገልጽ ነው፡፡የትንሳኤው በኩርና የሰውን ልጅም የሚያስነሳ እርሱ መሆኑን ሲናገርም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም (ዮሐ 11፡25-26) በማለት አረጋግጦልናል፡፡

ትንሣኤውን ቅዱሳን መላእክት ለሴቶች አበሰሩ

ልደቱ ለእረኞች በመልአክ እንደተበሰረ ትንሣኤውም በመልአክ ለሴቶች ተበሰረ፡፡ ይህም ‹‹ተነስቷል፤ በዚህም የለም›› የሚለው የመላእክት ብስራት በአራቱም ወንጌላት እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ፡ ‹‹መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ።›› በማለት ገልጾታል (ማቴ 28፡5-10)፡፡

ቅዱስ ማርቆስ፡ ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው (ማር 16፡5) በማለት አስፍሮታል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ፡ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ (ሉቃ 24፡4-9) ብሎ መልአኩ እንደነገራቸው አስፍሮልናል።

ቅዱስ ዮሐንስ፡ መግደላዊት ማርያም ሁለቱን መላእክት እንዳየችና ከእነርሱም ጋር እንደተነጋገረች ሲገልጽ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት (ዮሐ 20፡10-13)›› ብሏል።

ደቀ መዛሙርቱም መቃብሩን አይተው መነሳቱን አረጋገጡ

ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የትንሣኤውን ዜና ከሴቶች ከሰሙ በኋላ ወደ መቃብሩ በመግባት የጌታችንን መነሳት አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም (ዮሐ 20፡3-8)›› ሲል ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም ይህንን የጴጥሮስን ወደ መቃብር ገብቶ የጌታን ትንሳኤ ማረጋገጡን ሲገልጽ ‹‹ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ (ሉቃ 24፡12)›› ብሏል።

ጌታችን ራሱ ተገልጦ ትንሣኤውን አረጋግጦልናል

ከትንሣኤ በኋላ ጌታችን በተለያየ ጊዜ ተገልጧል፡፡ አስቀድሞ ለማርያም መግደላዊት በመቃብሩ ስፍራ ተልጦላታል፡፡ እርሷም ያየችውን ለደቀ መዛሙርቱ ተናግራለች (ዮሐ 20፡14-17) ፡፡ ወደ ኤማሁስ ይሄዱ ለነበሩት ሁለቱ ደቀመዛሙርትም መንገደኛ መስሎ ተገጦላቸዋል (ሉቃ 24፡13-31)፡፡ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በተሰበሰቡበት ተገልጦ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ካላቸው በኋላ ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጥተውት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በልቷል፤ አስትምሯቸዋልም (ሉቃ 24፡ 42-43)፡፡ በማዕድ ተቀምጠው ሳለም ለአሥራ አንዱ ተገለጧል፤ተነሥቶም ያዩትን የተነገራቸውን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ እንደነቀፈ ተጽፏል (ማር 16፡14)። ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደጻፈው ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ሁለት ጊዜ (የመጀመሪያው ጊዜ ቶማስ በሌለበት) በተዘጋ ቤት ተገልጦላቸዋል (ዮሐ 20፡19-31)፡፡ከዚያም በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ተገልጦላቸዋል (ዮሐ 21፡1-25)፡፡ እነዚህ ለማሳያነት ቢገለጹም ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ እስከ ዕርገቱ ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የተገለጠባቸው ጊዜያቶች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡

እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች መሰረት በማድረግ ከዐበይት በዓላት አንዱ የሆነው የትንሣኤ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ይህም ከጥንት አበው የነበረውን የአከባበር ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡ የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው የተነሡ ምእመናን ማክበር ቀጠሉ፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀንስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ግን ተቋርጦ አያውቅም፡፡ የትንሣኤ በዓል የሚከበረው ‹‹ዘመነ ትንሣኤ›› የሚባሉትን ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉትን ሰባቱን ቀናት ጭምር ይዞ ነው፡፡ እነዚህም ዕለታት የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ  አላቸው፡፡

 1. ሰኞ፡ ፀአተ ሲኦል ማዕዶት (ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት ለማስገባቱ መታሰቢያ)
 2. ማክሰኞ፡ ቶማስ (በቶማስ ጥያቄ መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ)
 3. ረቡዕ፡ አልዓዛር (ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ)
 4. ሐሙስ፡ የአዳም ሐሙስ (የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ)
 5. ዓርብ፡ ቤተክርስቲያን (በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ)
 6. ቀዳሚት፡ አንስት (እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ በሌሊቱ ወደ መቃብሩ ለገሠገሱት ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ)
 7. እሑድ፡ ዳግም ትንሣኤ (የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት) ዮሐ 20፡24

የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ ታላቅ ትርጉም አለው፡፡ በእርሱ ትንሣኤ ታላቅ ጸጋ አግኝተናልና። በእርሱ ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል። ምድራዊያን የነበርን ሰማያዊያን፣ ሙታን የነበርን ሕያዋን፣  ሥጋዊያን የነበርን መንፈሳዊያን ሆነናል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ?» ማለት ችለናል (1ኛቆሮ 10፡55)፡፡ “ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና (1ኛ ተሰ 4፡14)” እንደተባለ በእርሱ ትንሣኤ ማመናችን ለድኅነታችን መሰረት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ‹‹አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና (1ኛ ቆሮ 15፡20-22)›› እንደተባለው የእርሱ ትንሳኤ ለእኛ ትንሳኤ በኩር ነው፡፡ እንዲሁም “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለንና (ሮሜ 6፡5)” እንዳለው ክርስቶስ በትንሣኤው ለእኛም ትንሣኤ መሰረት ሆኖናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ (1ኛ ጴጥ 1፡3)›› እንዳለው የጌታችን ትንሣኤ ለማያልፍ ርስት ዳግመኛ የተወለድንበት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ታላቅ የትንሣኤ ጸጋ አስመልክቶ «በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን(ኤፌ 2፡6-7)» ብሏል።

ዛሬ የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ (ትንሣኤ ዘክርስቶስን) ስናከብር ትንሣኤ ኅሊና የተባለ በእርሱ ላይ ያለንን እምነትና በእርሱም መታመናችንን በማጽናት፣ ትንሣኤ ልቡና የተባለ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና በንስሐ ሕይወት እየታደሱ መኖርን ገንዘብ በማድረግ፣ እርሱ ሕይወታችንና ትንሣኤያችን መሆኑን በማስተዋልና ትንሣኤ ዘጉባዔ ለተባለው ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት በሚነሣበት የዘለዓለም ትንሣኤ በቀኙ የሚያቆመንን እምነትና ምግባር አስተባብረን በመያዝ ራሳችንን እያዘጋጀን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም እናደርግ ዘንድ የትንሣኤውን ብርሃን ያሳየን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን!

ስቅለት፡ ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ሰቀሉት!

seklet

ሰሙነ ሕማማት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የሰውን ልጅ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት በፈቃዱ የተቀበላቸው ጸዋትወ መከራዎች የሚታሰቡበት ሳምንት ነው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች ክርስቶስ የዋለልንን ውለታ እያሰብን እጅግ የምናዝንበት፣ የምናለቅስበት፣ የምንሰግድበት ከሌሎች ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ አምላካችንን የምንማጸንበት፤ ጧት ማታ ደጅ የምንጠናበት፤ የክርስቶስን ተስፋ ትንሣኤ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእምነትና በተስፋ የምንጠብቅበት  በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ልዩ ተምሣሌታዊ ምስጢራትና አዘክሮ የሚፈጸምበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ  ሳምንት ያሉ እያንዳንዳቸው ቀናት ስያሜና ከስያሜው ጋር የተያያዘ ምስጢር አላቸው፡፡ ይህም፡-

 1. ሰኞ: አንጽሆተ ቤተመቅደስ፣ መርገመ በለስ
 2. ማክሰኞ:  የጥያቄ ቀን፣ የትምህርት ቀን
 3. ረቡዕ:    የምክር ቀን፣መልካም መዓዛ ያለው ቀን፣ የእንባ ቀን
 4. ሐሙስ:   ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምስጢር_ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣ የነፃነት ሐሙስ
 5. ዓርብ:    የስቅለት ዓርብ፤ የድኅነት ቀን፣ መልካም ዓርብ
 6. ቅዳሜ:    ቅዳም ሥዑር፣ ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ

ከእነዚህ ሁሉ ግን ዓርብ የስቅለት (crucifixion) ቀን እጅግ ልዩ ናት፡፡ የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ወይም ‹‹መልካም ዓርብ›› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. 27፥1-57)፡፡ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት አይሁድ ጲላጦስ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

በግብረ ሕማማት‹‹የማይሞት መለኮት ስለ እኛ የሞትን ጽዋ ተቀብሎ በሰውነቱ ሞተ! ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡›› እንደተባለ ስለኛ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ ፈቃዱ ነበርና በአይሁድ ጭካኔ ምክንያትነት ሞት ተፈረደበት፡፡ ይህ የስቅለት ዕለት ሙሉ ምስጢሩና ሥርዓቱ በግብረ ሕማማቱ በስፋትና በጥልቀት እንደሰፈረው ነው፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ያህል ይህ የስቅለት ቀን የሚከተሉት የተከናወኑበት ነው፡፡

ፍኖተ መስቀልጌታችን 15ቱን ምዕራፎች መከራ እየተቀበለ የተጓዘበት ነው፡፡

ጌታ በጲላጦስ ፊት ከቆመበት ቦታ ጀምሮ እስከ መካነ ትንሣኤው ድረስ በዕለተ ዓርብ የሆነው ዐሥራ አምስት የመከራ መስቀል መንገድ ምዕራፎች (ፍኖተ መስቀል) አሉ፡፡ እነዚህም የጲላጦስ ዐደባባይ (ለፍርድ የቆመበት)፣ የተገረፈበት፣ በመጀመሪያ የወደቀበት ቦታ፣ እመቤታችን እያለቀሰች ልጇን ያገኘችበት ቦታ፣ ቀሬናዊ ስምዖን የጌታን መስቀል የተሸከመበት ቦታ፣  ቤሮና /ስራጵታ/ በመሐረብ የጌታን ፊት የጠረገችበት ቦታ፣ የጎልጎታ መቃረቢያ፣ የጌታችንን ሥቃይ ሴቶች አይተው ያለቀሱበት ቦታ፣ መስቀል ይዞ የወደቀበት፣ ልብሱን የገፈፉበት፣ጌታን የቸነከሩበት፣ የተሰቀለበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋውን ያወረዱበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋውን የገነዙበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋው የተቀበረበት ቦታ ናቸው፡፡ እነዚህም ምዕራፎች የጌታችንን መከራና የማዳኑን ሥራ ሲያሳስቡን ይኖራሉ፡፡

ሕማማተ መስቀልጌታችን 13ቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡

ዕለተ ዓርብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መተላለፋችን የቆሰለበት፣ ስለ በደላችንም የደቀቀበት፣ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መስዋዕት ያደረገበት፤ በእርሱም ቁስል እኛ የተፈወስንበት፤ በሞቱም የሞት ስልጣን የተሻረበት ዕለት ነው፡፡ የሕይወት ባለቤት፣ የሕያዋን ሁሉ አምላክ በፈቃዱ በሥጋ ሞቷልና የሞትን ስልጣን አጠፋልን፡፡ ይህ ዕለት አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት፣ እኛም እነዚህን እያሰብን የምንሰግድበት፣ በተደረገልን ቤዛነት እየተደነቅን ፍቅራችንን አምልኮታችንን የምንገልጥበት ዕለት ነው፡፡ የበረቱ ቅዱሳን ሙሉ ሕይወታቸውን፣ ትዳራቸውን ደስታቸውን ትተው ዕለት ዕለት የሚያስቡትን መከራ መስቀል፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንም በየዕለቱ የምታስበውን፣ የምታዘክረውን መከራ መስቀል እኛ ደካሞች ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ሣምንት በልዩ ሁኔታ የምናስብበት ልዩ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ልዩ ወቅት ስለበደላችን እያነባን መድኃኒት የሆነንን የክርስቶስን 13ቱን ሕማማተ መስቀል እናስባለን፡፡ እነዚህም 13ቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት፡ አስሮተ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)፣ ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)፣ ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ)፣ ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድ መረገጥ)፣ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋር መላተም)፣ ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)፣ ተቀሰፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)፣ ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)፣ አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)፣ ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)፣ ተቀንዎ በቅንዎት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ ሮዳስና አዴራ በተባሉት ችንካሮች መቸንከር)፣ ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይ መሰቀል) እና ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞትን መጠጣት) ናቸው፡፡ በስቅለት ዕለት ለእኛ ሲል እነዚህን ሕማማተ መስቀል መቀበሉን እያሰብን የአምልኮ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡

አጽርሐ መስቀልጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል የተናገረበት ነው፡፡

ይህ ዕለት ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል (የፍቅር ቃላት) የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ እነዚህም ቃላት በየራሳቸው ጥልቅ ምስጢር ያላቸው ሲሆኑ የማዳኑ ሥራም አካል ናቸው፡፡ ሰባቱ ቃላትም:  ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስላማ ሰበቅታኒ/አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ (ማቴ.27፤46)፣ አማን ዕብለከ እሙን ፈድፋደ ከመ ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት (እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ)(ሉቃ.23፤43)፣ አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ (አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ) (ሉቃ.23፤46)፣ አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ (አባት ሆይየሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው) (ሉቃ.2334)፣ ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ (እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ) (ዮሐ.19፤26-27)፣ ጸማዕኩ (ተጠማሁ) (ዮሐ.19፤30) እና ተፈጸመ ኩሉ (ተፈጸመ) (ዮሐ.19፤30) የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡ በስቅለት ዕለት እነዚህ በንባብና በዜማ እያልን እንሰግድለታለን፡፡

የስቅለት ተአምራትበሰማይና በምድር ሰባት ተአምራት የተከናወኑበት ነው፡፡

በዕለተ ዓርብ በሰማይ ሦስት ተአምራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚህም የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መልበስ፣ የክዋክብት መርገፍ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በመስቀል ላይ ያለውን የአምላካቸውን እርቃን ላለማሳየት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ይህንን ‹‹ፀሐይ ፀልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወክዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ አይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ›› ሲል ገልጾታል፡፡ እንዲሁም በምድር አራት ተአምራት ታይተዋል፡፡ እነዚህም የቤተ መቅደስ መጋረጃ መቀደድ፣ የዐለቶች መሰንጠቅ፣ የመቃብሮች መከፈት፣ የሙታን በአጸደ ሥጋ መነሳት ናቸው (ማቴ.27፤45-46)፡፡ እነዚህ ተአምራት በመስቀል ላይ የተሰቀለው ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ለሰው ልጆች ያረጋገጡ ምልክቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ተዓምራት አይተው በጌታችን ያመኑ ነበሩ፡፡ ከሰቃዮቹ ወገን የሆኑት እንኳ በትህትናው፣ በተዓምራቱ ተማርከው አምነው ምስክሮቹ (ሰማዕታት) ሆነዋል፡፡

ዕርቀ ሰላምሰባቱ መስተፃርራን (ጠበኞች) የታረቁበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. 2፥10 ቈላ. 1፥20)፡፡ የስቅለት ቀን የገነት በር የተከፈተበት በአንጻሩ ደግሞ ሲኦል የተበረበረበችበት ነው፡፡ በአዳም በደል ምክንያት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችው ገነት የተከፈተችበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሰልጥና የነበረችው ሲኦል የተበረበረችበት፣ ነፍሳት ከሲኦል ወጥተው ወደ ገነት የገቡበት ነው፡፡ የስቅለት ዕለት የገነት መዘጋት ያበቃበት፣ የሲኦልም መሰልጠን ያከተመበት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ጥልን በመስቀሉ ገደለ» ሲል የገለጸው (ኤፌ. 2፥16) በእነዚህ መካከል የነበረው ጥል ማብቃቱንና ፍጹም ሰላም መስፈኑን ያሳያል፡፡

የሰው ልጅ ድኅነትየሰው ልጅ ከዲያብሎስ እሥራት የተፈታበት ዕለት ነው፡፡

የስቅለት ዓርብ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ የስቅለት ዓርብ የሲኦል አበጋዝ ዲያብሎስ በንፋስ አውታር የታሠረበትና ስልጣኑ የተሻረበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ታስሮ የነበረው አዳም የተፈታበትና ወደ ገነት የተመለሰበት ናት፡፡ በመጀመሪያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲፈረድበት ወንጀለኛ የነበረው በርባን ተፈታ፡፡ ጌታችን በሥጋው ሲሞት ደግሞ አዳምና ልጆቹ በሙሉ ተፈቱ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ “በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ፤ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ፤ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ፤ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” እንዳለ፡፡ እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ “ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ ወወረደ ኀበ እለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ” በሥጋ ሞተ በመንፈስ /በመለኮት/ ግን ሕያው ነው እርሱም ደግሞ ሄደ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው” (1ጴጥ.3፡18) እንዳለው ጌታችን በሲኦል እስራት የነበሩትን ነፍሳት ነፃ አወጣቸው፡፡

የመስቀል ስጦታዎችየምንጠመቅበት ማየ ገቦ፣ የምንድንበት ሥጋውና ደሙን እንዲሁም የምታማልድ እናት የተሰጠንበት ነው፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. 19፥34)፡፡ ዕለተ ዓርብ ተጠምቀን ድኅነት የምናገኝበት ውኃ ከጎኑ የፈሰሰበት፣ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ያገኘንበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹ በነገው ዕለት ስለ ዓለም የሚቆረሰው ሥጋዬ የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው›› እንዳለ (ማቴ 27፡27)፡፡ ቤተክርስቲያንም የተዋጀችው በዚሁ በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ በዚህ ዕለት አርማችን መስቀሉ፣ ማኅተማችን ደሙ፣ ሕይወታችን እርሱ ሆነዋል፡፡ ሥጋውንና ደሙን በመስቀሉ ላይ አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ሥር ድንግል ማርያም በዮሐንስ አማካኝነት እናት እንድትሆነን፣ እኛም ልጅ እንድንሆን የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ እናቱ እናት እንድትሆነን በይፋ የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ ‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ 19፡36) ብሎ ሰጠን፡፡ ርህርህት እናት ከመሰቀል ሥር በዕለተ ዓርብ አግኝተናል፡፡

በአጠቃላይ የስቅለት ዓርብ ጌታችን የቤዛነቱን ሥራ የፈጸመበት ነው፡፡ በቤተልሔም የተጀመረው የሰውን ልጅ የማዳኑ ሥራ የተጠናቀቀበት፣ ጌታም ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ የሠራበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ዓርብ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የተባለው የተፈጸመበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በመስቀል ላይ ‹‹ተፈጸመ›› ያለው (ዮሐ 19፡30)፡፡ እኛም በዚህ ታላቅ ዕለት ጌታችን ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ እያሰብን፣ ስለ ኃጢአታችንም እያዘንንና እያለቀስን፣ ስለ ማዳኑም ሥራ ምስጋናን እያቀረብን ስንሰግድ እንውላለን፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን ‹‹አቤቱ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበን›› እያልን እንማፀናለን፡፡ እርሱም ዳግመኛ በመጣ ጊዜ እንዲያስበን የጾማችንን ፍጻሜ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ማኅተምነት ማተም ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የእርሱ ቸርነት የቅድስት ድንግል እመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡