ሰማዕታትና ሰማዕትነት: የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነው!

semaetat

ግብጻውያን እና ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት (ሥዕል: ዘሪሁን ገብረ ወልድ)

“ሰማዕት” የሚለው ቃል ዘሩ ‹‹ስምዐ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የሚወጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም “ምስክር” ማለት ነው፡፡ “ሰማዕትነት” ማለትም እንዲሁ “ምስክርነት” ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሰማዕት ማለት የተሰዋ፣ ራሱን መስዋዕት ያደረገ ማለት ነው፡፡ የዚህም ምስክርነት ዋና መሰረቱ ጌታችን በወንጌሉ “በሰው ፊት የሚመሰክርልኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ሁሉ ፊት የሚክደኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እክደዋለሁ (ማቴ 10፡32)” ብሎ የተናገረው ታላቅ ቃል ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሰማዕት ከአቤል ጀምሮ እስከ ህጻናተ ቤተልሔም፣ እንዲሁም የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ፣ መጥመቀ መለኮት ዮሐንስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ በዘመነ ሰማዕታት የነበሩት እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እነ ቅድስት አርሴማ፣ እነ ቅዱስ ቂርቆስ፣ በእኛም ዘመን በተለያዩ ስፍራዎች ሰማዕትነትን የተቀበሉት ግብጻውያን እና ኢትዮጵያውያን እና የመሳሰሉት ይህንን በመመስከር ለታላቅ ክብር ከበቁ ሰማዕታት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብዙ ሰማዕታት ይታሰባሉ፡፡ ስማቸውና የሰማዕትነታቸው ዜናም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲሁም በገድላቸው፣ በድርሳናቸው፣ በመልክአቸው በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊውና የቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውሳብዮስ እንዳለው የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር ነውና የሰማዕታት ገድል መጻፉ ለክርስትና ሃይማኖት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ስለዚህም መዝገበ ምስጢር የሆነችው ቤተክርስቲያናችንም የቅዱሳን ሰማዕታትን ገድላቸውን ለዘመናት ጠብቃ ይዛ አዳዲስ ሰማዕታትም በየዘመናቱ ሰማዕትነትን ሲቀበሉ እነርሱንም ከሰማዕታት ቁጥር እየደመረች ገድላቸውን ለትውልድ ታስተላልፋለች፡፡ ይህንንም የምታደርገው መታሰቢያቸው ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ ምዕመናን ከሰማዕታቱ ተጋድሎና ጽናት ትምህርትን እንዲያገኙ እንዲሁም አምላካችን እግዚአብሔር ለቅዱሳን ሰማዕታት በሰጣቸው ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ተማጽነው ጸጋና በረከትን እንዲካፈሉ ለማስቻል ነው፡፡

ሰማዕትነት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው “ሰማዕት ዘእንበለ ደም” (ደምን ከማፍሰስ በመለስ ያለ ሰማዕትነት) ሲሆን ሃይማኖትን በመመስከር፣ እውነትን በመናገር ያለጥፋታቸው ስደት፣እስራት፣ግዞት፣ስድብ ነቀፌታ ሲደርስባቸው በአኮቴት እና በትዕግስት የሚቀበሉ ቅዱሳን ተጋድሏቸውን ሲፈጽሙ ሰማዕት ዘእንበለ ደም ይባላሉ፡፡ “የደም ሰማዕት” ደግሞ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ክብር፣ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲሉ ያፈሰሱ ናቸው፡፡ይህም የሰማዕትነት የመጨረሻ ደረጃ መገለጫ ነው፡፡ ሁለቱንም የሰማዕታትን ምስክርነት በሚገባ ለመረዳት ስለእነርሱ ምስክርነት አምስት ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ የሰማዕታት ምስክርነት ስለማን/ስለምን ነበር? ምስክርነታቸውስ ለማን ነበር? ምስክርነታቸውን እንዴት መሰከሩ? በምስክርነታቸውስ ምን አተረፉ? እኛስ የእነርሱን ምስክርነት በመዘከራችን ምን እናተርፋለን? በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር እነዚህን ነጥቦች እንዳስሳለን፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው ስለ ክርስቶስ ነበር፡፡

ሰማዕታት በዚህች ምድር ላይ ክርስትናን በቃልና በተግባር ኖረው ክርስቶስንም በቃልና በሕይወት መስክረዋል፡፡ ክርስቲያን ሆነው መገነኘታቸው ብቻ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው በሥጋቸው ብዙ ጸዋትወ መከራን ተቀብለዋል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት ዓላውያን ነገሥታት የየራሳቸውን እምነት በክርስቲያኖች ላይ ለመጫን ባደረጉት የግፍ ተግባር ብዙዎችን ለመከራ ዳርገዋል፡፡ በዚህ መከራ ውስጥ ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ የማመልከውም የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ የሆነውን  ኢየሱስ ክርስቶስን ነው›› በማለት ራሳቸውን ለሰይፍ ለሰንሰለት አሳልፈው የሰጡ የክርስቶስና የክርስትና ምስክሮች ሰማዕታት ናቸው፡፡ የሚያልፈውን ምድራዊ ክብርን ንቀው የማያልፈውን ሰማያዊ ክብር የሚሰጠውን ክርስቶስን መሰከሩ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ ስለ መንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ፡፡” ያለው ምስክርነታቸው ስለ እግዚአብሔር እንደነበር ያስረዳናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር ማለትም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና አርድእት በዓለም ዞረው የሰበኩትን፣ ሐዋርያውያን አበው ከመናፍቃን ቅሰጣ፣ ከዓለማውያን ቁንጸላ ጠብቀው ያቆዩልንን፣ ሐዋርያዊት ኦርቶዶክሳዊት የሆነች የቤተክርስቲያን እውነተኛ መምህራን  ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለማዳን ስራው፣ እርሱ ስለመሰረታት አንዲት ቤተክርስቲያን ክብር፣ በቤተክርስቲያን ስለሚገኘውም የቅዱሳን ኅብረትና የሰማያዊ ምስጢር መዝገብ መመስከር እንዲሁም በምንመሰክረው እውነት ጸንቶ መኖር ማለት ነው፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው ለሁሉም ነበር፡፡

የሰማዕታት ምስክርነታቸው በሚያምኑት ብቻ ሳይሆን በማያምኑ ሰዎችም ፊት ነበር፡፡ በሚከሷቸውና መከራ በሚያደርሱባቸው ሰዎች ፊት የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ይመሰክሩ ነበር፡፡ እውነትንም በመመስከራቸው በሥጋቸው ላይ የተለያየ መከራ ይፈራረቅባቸው ነበር፡፡ በግፍ ይገደሉም ነበር፡፡ ይህንን ምስክርነታቸውን የሰሙ ያዩ ሌሎች  ደግሞ እያመኑ አብረው ሰማዕትነትን ይቀበሉ ነበር፡፡ አምነው ለመመስከር ያልደፈሩትም እንዲሁ እነዚህ ሰማዕታትን እያዩ በእምነታቸው ይጸኑ ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ሰማዕትነት ‹‹ጧፍ›› ሆኖ እየነደዱ ለሌላው ማብራት ነው የሚባለው፡፡ ሰማዕታት ራሳቸው በእሳት በተመሰለ መከራ ውስጥ እያለፉ ሌላውን ወገናቸውን የወንጌልን ብርሀን እያበሩ ከጨለማ ያወጡት ነበር፡፡ ሰማዕታት በመከራ በመጽናት ለሌሎች ብርሃን መሆናቸውን ለማሰብም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት በጧፍ ወይም በሻማ ብርሃን እንዲነበቡ ሥርዓት ሰርታለች፡፡

ሰማዕታት ስለክርስቶስ የመሰከሩት በጽናትና በጥብዐት ነበር፡፡

ሰማዕታት እውነተኛይቱን ሃይማኖት የመሰከሩት በጥብዐት (ፍጽም በመጨከን) እና እስከመጨረሻው በመጽናት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ምድራዊ መደለያዎች ሲቀርቡላቸው እምቢ በማለት ሁሉን እያጡ አምላካቸውን ተከተሉ፡፡ እንደዛሬው ትውልድ “ለጊዜው ምስክርነታችንን ትተን ክፉ ዘመን ሲያልፍ ንስሐ እንገባለን” ብለው የስንፍናን ሀሳብ ለአእምሮአቸው አላሳዩትም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ‹‹ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። (ዕብ 11፡35)›› በማለት ገልጾታል፡፡ በቃላት ለመግለጽ የማይቻሉ መከራዎች ሲደርሱባቸው በቀራንዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ስለሁላችን የሞተውን ጌታቸውን እያሰቡ ይታገሱት ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የጠቀሳቸው የዘመነ ብሉይ ቅዱሳን ሰማዕታት የክርስቶስን መገለጥ ተስፋ አድርገው መከራን እንደተቀበሉ ሞት በተሸነፈበት፣ ትንሣኤ በታወጀበት በዘመነ ሐዲስ ያሉ ቅዱሳን ሰማዕታትም እንዲሁ በየዘመናቸው የመናፍቃንን፣ የአላውያን ባለስልጣናትን፣ እንዲሁም ለገንዘብ ለክብርና ለሥጋዊ ድሎት ብለው መከራ የሚያጸኑባቸውን ተረፈ አይሁድ ሳይፈሩና ሳያፍሩ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል/ይቀበላሉም፡፡ ይህንንም የሚያደርጉ ቅዱሳን በትንሣኤ ዘጉባኤ 30 እና 60 ከሚያፈሩት ምዕመናን የበለጠ ክብር እንደሚጠብቃቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡

ሰማዕታት በምስክርነታቸው ለሌሎች መዳንን ለራሳቸው አክሊልን አተረፉ፡፡

ሰማዕታት በእውነተኛ ምስክርነታቸው ለሥጋቸው ያተረፉት ነገር ቢኖር ሀብት ንብረት ወይም ሥልጣን ሳይሆን መከራን ብቻ ነበር፡፡ በዚያ መከራቸው ውስጥ ግን መክሊታቸውን ያተርፉ ነበር፡፡ የእነርሱን ምስክርነት እየሰሙና እያዩ መከራ ከሚያደርሱባቸው ጭምር የሚያምኑ ነበሩና፡፡ ከእነርሱም ጋር የሰማዕትነትን ጽዋ አብረው ይቀበሉ ነበር፡፡ ምድርም በሰማዕታቱ ደም ትታጠብ ነበር፡፡ በሰማይ ግን የሰማዕትነትን አክሊል አትርፈዋል፡፡ በሰማያዊው መንግስት እንደ ኮከብ አብርተዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ‹‹አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። (ራዕ 6፡9)›› ሲል የገለጸው እንዴት እንደከበሩ ያስረዳናል፡፡

እኛም የእነርሱን ምስክርነት በመዘከራችን በረከትን እናተርፋለን፡፡

ቤተክርስቲያናችን የሰማዕታትን መታሰቢያ የምታደርገው እንድንዘክራቸውም የምታስተምረው ታላቅ ዋጋ ስላለው ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያ ደረጃ የሰማዕታቱ ሕይወት/ተጋድሎ የክርስትና ሕይወት ሕያው ምሳሌ ነውና ሁላችን ከእነርሱ የተጋድሎ ሕይወት ተምረን በእምነታችን እንድንጸና ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ሰማዕት የተጋድሎ ሕይወት ውስጥ የምንማራቸው እጅግ ብዙ ቁምነገሮች አሉና፡፡ የሰማዕታቱ ሕይወት በራሱ የተግባር ወንጌል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሰማዕታቱን በመዘከራችን በረከት ረድኤትን እናገኛለንና ቤተክርስቲያን ይህንን አጽንታ ታስተምራለች፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእርሱ በመመስከር፣ እስከሞት ድረስ ሰማዕትነትን በመቀበል የቤተክርስቲያን ጌጥ ለሆኑ ደቀመዛሙርቱ በሰጠው ዘላለማዊ ቃልኪዳን “ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ በደቀ መዝሙሬ  ስም ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋውን አያጣም፡፡” ማቴ. 10፡42 ያለው ይህን ያመለክታል፡፡ ለጊዜው ደቀ መዛሙርት የተባሉት በጽናት የተከተሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72 አርድዕትና 36ቱ ቅዱሳት አንስት ቢሆኑም የጌታ ቃልኪዳን ፈለገ ሐዋርያትን ተከትለው ለጽድቅ አገልግሎት በትህትና የሚፋጠኑትን፣ ስለ ጽድቅ አገልግሎትም መከራ የሚቀበሉትን እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚገለጡትን ቅዱሳን ሰማዕታት ሁሉ ይመለከታል፡፡

የዘመናችን ሰማዕትነትስ ምንድን ነው?

በየዘመናቱ የተነሱ ቅዱሳን ሰማዕታት ያደረጉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ ተመልክተናል፡፡ እኛም የሰማዕታት ተጋድሏቸውን በማመንና በቃልኪዳናቸው በመታገዝ የራሳችንን መዳን ልንፈጽም ይገባል እንጅ የሰማዕታትን ገድል እየተረክን ብቻ መኖር አይባንም፡፡ የቅዱሳን ቃልኪዳን ተካፋዮች የምንሆነው ከእነርሱ በሥጋ ስለተወለድን ወይም እነርሱ የጽድቅን አክሊል በተቀዳጁባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በመመላለሳችን ብቻ አይደለም፡ አይሁድ የአብርሃምን ሥራ ሳይሰሩ “አብርሃም አባት አለን” በማለት ብቻ እንዳልዳኑ (ዮሐ. 9) ሁላችንም እንደ አቅማችን የጽድቅን ስራ ያለመለገም ልንሰራ ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ አስቀድመን አባቶቻችንና እናቶቻችን ቅዱሳን ሰማዕታት ከእግዚአብሔር የተቀበሏትን አንዲት ሃይማኖት አስቀድመው ለፍርድ የተጻፉ መናፍቃንና ከሃድያን ከሚያመጡት ፈተና ሁሉ እንጠብቃት ዘንድ መጋደል እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል (ይሁዳ 1፡3-5)፡፡ በኃጢአት በተጎሳቆለ ማንነት የሰይጣንንና የመልእክተኞቹን ፈተና መቋቋም አይቻልምና፣ የምንድነውም የጸናች ሃይማኖትን ከኃጢአት ርቀን በምግባርና በትሩፋት ጸንተን በመጠበቅ ነውና፣ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረን የከበሩ ቅዱሳን ሰማዕታትን ልንመስላቸው ይገባል፡፡

ቅዱሳን ሰማዕታት ስለ ጽድቅ (እውነት) አገልግሎትና ስለ ቤተክርስቲያን ያለሃፍረትና ያለፍርሃት እንደመሰከሩ እኛም በዘመናችን ያሉ የመናፍቃን ክህደታቸው፣ የምንደኛ “አገልጋዮች” ሥም አጥፊነትና አስመሳይነታቸው፣ ከእምነትና ከእውቀት የተፋቱ፣ በግልብ ስሜት የሚመሩ የመናፍቃን፣ የሐሰተኛ መምህራን አዳማቂዎች ወሬና ዘለፋ ሳያስፈራን ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠች ሃይማኖት እንድንጋደል ያስፈልጋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ቅዱሳን ሰማዕታት ልጆች ስንሆን ለሥጋዊ ጥቅም፣ ዝናና ክብር ብለን እውነትን ከመመስከር፣ ከሐሰተኞች ጋር ካለመተባበር ወደኋላ ብንል የሰማዕታት በረከት ይቀርብናል፡፡ ሃይማኖታችንን ጠብቀን፣ በበጎ ምግባር አጊጠን፣ የቤተክርስቲያንን እውነት ያለሃፍረትና ያለፍርሃት መስክረን የቅዱሳን ሰማዕታትን በረከት እንድናገኝ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የሰማዕታት እናታቸው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s