መንፈሳዊ አገልግሎት ምንድን ነው የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የሚኖረንን ሚና ለማወቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ‹‹መንፈሳዊ (Spiritual)›› እና ‹‹አገልግሎት (Service)›› የሚሉትን ቃላቶች የያዘ ሲሆን ‹‹መንፈሳዊ›› የሚለው ገላጭ የአገልግሎቱን ዓላማና መሪ የሚያሳይ ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ዓላማው የሰው ልጆች ድኅነት ነው፡፡ መሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሰው ልጆች ለመንግስተ ሰማያት እንዲበቁ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ‹‹መንፈሳዊ አገልግሎት›› ሊባል ይችላል፡፡ ይህም የሕይወትን ቃል ያላወቁ ወገኖች እንዲያውቁና እንዲያምኑ ማድረግ፣ ያመኑት ደግሞ እንዲጸኑና መንፈሳዊ ትሩፋትን እንዲሠሩ ማድረግን ያካትታል፡፡
የመንፈሳዊ አገልግሎት መሰረቱ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድና ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያተጋን አምላካዊ መመሪያ ነው፡፡ ከዘመነ አበው ጀምሮ፣ በዘመነ ኦሪትም በቅዱሳን አባቶችና ነቢያት አድሮ የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮንና መመሪያን የሰጠው በፍፁም አንድነትና በልዩ ሦስትነት የሚመሰገን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስም ከሦስቱ አካላት አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ግዕዘ ህፃናትን ሳያፋልስ በትህትና አድጎ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት በተግባር አስተምሮ ለቅዱሳን ሐዋርያት አብነት የሆነ የአገልግሎት ተልዕኮና መመሪያ ሰጥቷቸዋል፡፡ አብነት የሆነው ተልዕኮ ‹‹እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ›› የሚለው ሲሆን መሪ መመሪያው ደግሞ ‹‹ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ›› የሚለው ታላቅ ቃል ነው (ማቴ 10፡16)፡፡ ጌታችን ይህንን ተልዕኮና መመሪያ የሰጠው ለጊዜው ለደቀ መዛሙርቱ ሲሆን ኋላም በእነርሱ እግር ተተክተው በመንፈሳዊ አገልግሎት ለሚሳተፉ ሁሉ ነው፡፡
የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ
በጌታችን ትምህርት በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ውስጥ በግና ተኩላ ተጠቅሰዋል፡፡ በግ የየዋሀን የእግዚአብሔር ልጆች ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ›› በማለት በእርሱ የሚያምኑትን ‹‹በጎቼ›› ብሏቸዋል (ዮሐ 10፡27)፡፡ እንዲሁም ለደቀ መዝሙሩ ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በጎቼን አሰማራ›› በማለት በጎች የተባሉ በእግዚአብሔር ቤት የሚኖሩ ምዕመናን መሆናቸውን አስተምሮናል (ዮሐ 21፡17)፡፡ በመጨረሻው የፍርድ ቀንም ‹‹በጎችን በቀኙ ያቆማቸዋል›› ያለው በጎች የጻድቃን ምሳሌ ስለሆኑ ነው (ማቴ 25፡33)፡፡ ጌታችን መቶ በጎች ያሉት ሰውን ምሳሌ አድርጎ ያስተማረውም በሰማይ ያሉ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክትንና ጠፍቶ የነበውን የሰውን ልጅ የሚያሳይ ነው (ሉቃ 15፡3)፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የእግዚአብሔር በግ›› ያለው ስለ እኛ በፈቃዱ በተቀበለው ሞቱ ሞትን ስላስወገደልን የመዳናችንም መሰረት ስለሆነልን ነው (ዮሐ 1፡29)፡፡ ክርስቶስም በትምህርቱ ‹‹የበጎች እረኛ እኔ ነኝ›› ያለው ለዚሁ ነው (ዮሐ 10፡27)፡፡ የዋሁ አቤል የበጎች እረኛ እንደነበር ተገልጿል (ዘፍ 4፡2)፡፡ በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እኛ የማሰማርያው በጎች ነን (መዝ 99፡3)›› የተባለውም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የዋሀንን ይመለከታል፡፡
በአንጻሩ ተኩላ የነጣቂዎች፣ የተንኮለኞችና የከሳሾች ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ከሆኑ ተኩላዎች ተጠበቁ (ማቴ 7፡15)›› ያለው ተኩላዎች ተመሳስለው የሚያታልሉ ጉዳትም የሚያደርሱ ስለሆኑ ነው፡፡ ተኩላ እረኛ የሌላቸውን ወይም ሰነፍ እረኛ ያላቸውን በጎች ይነጥቃል (ዮሐ 10፡12)፡፡ በአጠቃላይ ተኩላ የክፉዎች ምሳሌ ሆኖ ነው የሚወሰደው፡፡ ‹‹ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነበር›› የተባለው ጠዋት ሌላ ማታ ሌላ ስለነበር ነው (ዘፍ 49፡27)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከእኔ በኋላ ለመንጋይቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኩላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ፡፡ ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሳሉ።›› (ሐዋ. 20፡29-30) ያለው ከዚያን ዘመን ጀምሮ በእውነተኛ የወንጌል አገልግሎት ጠማማ ነገርን ያስተማሩትንና የሚያስተምሩትን ሁሉ ይመለከታል፡፡ በመንፈሳዊ ተልዕኮ የሚሰማሩ ሰዎች እንደየግብራቸው በበጎችና በተኩላዎች የተመሰሉ ሲሆን እንደ በጎች በእግዚአብሔር የተወደደ ተልዕኮ ለመፈጸም አራት ዋና ዋና ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ማንኛውም አገልጋይ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰማራ ገንዘብ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ናቸው፡፡
የአገልግሎቱ ባለቤትና መሪ ማን እንደሆነ ማወቅ ለእርሱም መታመን
በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልእኮ ላኪው እግዚአብሔር ነው፡፡ ተልዕኮውን ለመፈጸም ፍላጎት፣ እውቀትና ክህሎት ቢያስፈልግም ሰው ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚላከው በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ በእውቀቱ ብዛት አይደለም፡፡ አገልጋይ በሰዎች ጋባዥነት ወደ አገልግሎት ቢቀርብም ሰዎች የተልዕኮው ምክንያት እንጂ ላኪዎች አይደሉም፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ የተልዕኮውን ባለቤት (ላኪውን) ማስተዋል እጅግ መሰረታዊና የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ መልእክተኛ የላኪውን ፈቃድ እንደሚፈጽም ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይም የጠራውንና የላከውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሊፈጽም እንጂ የራሱን ፈቃድ ወይም የሌሎች ሰዎችን ፈቃድ ሊፈጽም አይገባም፡፡
የተጠራንበትንና የተላክንበትን ዓላማ (ለምን ተላክን የሚለውን) ማወቅ
እግዚአብሔር ሰውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚልከው ‹‹መንፈሳዊ›› ለሆነ ሥራ ነው፡፡ ይህም እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል በቃልና በሕይወት በመስበክ ሰዎችን ለድኅነት ማብቃት ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ የሚያገለግልበት ዓለማ ሌሎች እንዲድኑ እርሱም በመክሊቱ እንዲያተርፍበት ነው፡፡ ጌታችን በመክሊቱ ምሳሌ እንዳስተማረው የአገልግሎቱ ዋናውም (ጸጋው) ይሁን በአገልግሎቱ የሚገኘው ትርፍ የእርሱ የባለቤቱ እንጂ የአገልጋዩ አይደለም፡፡ አገልጋይ የአገልግሎቱን ዋጋ የዘላለም ሕይወትን ያገኛል፡፡ በጥቂት በመታመኑ በብዙ ይሾማል፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ እምነት እንዲሰፋ፣ መልካም ስነምግባር እንዲስፋፋ፣ ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርስ፣ የእርሱም ጽናቱ ይረጋገጥ ዘንድ ያገለግላል፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ከዚህ የተለየ ዓላማ ከያዘ ‹‹መንፈሳዊ›› መሆኑ ያበቃል፡፡
የተልዕኮው ስፍራ ፈተና የሚበዛበት መሆኑን ማስተዋል
በወንጌሉ እንደተገለጸው የተልዕኮው ስፍራ ‹‹በተኩላዎች መካከል›› እንጂ ‹‹በበጎች መካከል›› አይደለም፡፡ በዚያም ስፍራ የሆነው ቢቻል የተኩላ ጸባይ ያላቸው የበግ ጸባይ እንዲይዙ ለማስቻል ነው፡፡ ይህ ባይሆን ደግሞ ተኩላዎቹ ሌሎች በጎችን እንዳይነጥቁ ለመከላከል ነው፡፡ ይህም ካልተቻለ ደግሞ አገልጋዩ የራሱን ግዴታ እንዲወጣ ይላካል፡፡ ተኩላ ያው ተኩላ ነውና በተኩላ መካከል የሚፈጸም አገልግሎት መሰደብ፣ መከሰስ፣ መንገላታትና መከራ መቀበል ያለበት ተልዕኮ ነው፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ክርስቶስ በጎችን ወደ ተኩላዎች ይልካል፡፡ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ ዲያብሎስ ተኩላዎችን ወደ በጎች ይልካል፡፡ እንግዲህ መንፈሳዊው አገልግሎት እንደዚህ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ነው የሚከናወነው፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መስክ ፈታኝ ቢሆንም አለማገልገል ግን አማራጭ መፍትሔ አይደለም፡፡ ከተኩላዎች ጋር መደራደርም እንዲሁ፡፡
ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሰማራት በግ ሆኖ መገኘት
ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሰማራት ለራሳችን መልካም (በግ) ሆነን መገኘት ያስፈልጋል፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት በግ ወደ ተኩላ ይላካል እንጂ ተኩላ ወደ ተኩላ አይላክም፡፡ ቢላክም አይጠቅምም፡፡ መንፈሳዊ አገልጋይ እንደ በግ በተኩላ መካከል ሲላክ በዚያው በተኩላ ተበልቶና ጠፍቶ እንዳይቀር መንፈሳዊ ትጋትን ገንዘብ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለማትረፍ እንጂ ዋናውን ለማጣት የሚነግድ ነጋዴ እንደሌለ ሁሉ መንፈሳዊ አገልጋይም ለማትረፍ ካልሆነም ለመትረፍ ሊተጋ ይገባል፡፡
የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ
በመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ ውስጥ ርግብና እባብ ተጠቅሰዋል፡፡ ርግብ የየዋሀን ምሳሌ ናት፡፡ ርግብ የጥፋት ውኃን መጉደል ለኖኅ ያበሰረች፣ በኖኅ መርከብ ውስጥም እንቁላሏን በእባብ አፍ ውስጥ የጣለች የዋህ እንስሳ ናት (ዘፍ 8፡11)፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በርግብ አምሳል እንደወረደ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት (ማቴ 3፡16)፡፡ ርግብ በብሉይ ኪዳን ለኃጢአት ማስተስረያነት መስዋዕት ሆና ትቀርብም ነበር (ዘፍ 5፡7)፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የወለደችልም ቅድስት ድንግል ማርያምም ‹‹መልካሚቱ ርግብ›› ትባላለች (የእሑድ ውዳሴ ማርያም)፡፡
በሌላ በኩል እባብ ልባም፣ ጥበበኛ፣ ተንኮለኛና መርዘኛ እንስሳ ነው፡፡ ‹‹ከምድር አውሬ ሁሉ እባብ ተንኮለኛ ነበር›› እንደተባለ (ዘፍ 3፡1) እባብ ተንኮለኛ አውሬ ነበር፡፡ እባብ በኖኅ ዘመን የርግብን እንቁላል ያልዋጠ (እንዳይጣል)፣ መርዙን ውጭ አስቀምጦ ውኃ የሚጠጣ (እንዳይገድለው)፣ የዕፀ ዘዌን በጥበብ የሚያሳልፍ (እንዳያደክመው) ልባም ፍጡር ነው፡፡ እባብ በገነት፣ በፈርዖን ቤተመንግስት፣ በበረሀ፣ እንዲሁም በመላጥያ ደሴት እንደተገኘ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ በርግብና በእባብ ምሳሌነት ከመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ጋር አብረው የተሰጡ የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያዎች (መርሆዎች) ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
እንደ ርግብ የዋህ መሆን (innocence)
ጌታችን እንደ ርግብ የዋህ ሁኑ ሲል ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮ ታመኑ (የቁራ መልእክተኛ እንዳትሆኑ)፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ሰላምን ስበኩ (ጥልና ክርክር ከእናንተ ይራቅ)፣ በመንፈስ ቅዱስ ተመሩ (የራሳችሁን ፍላጎት ግቱ)፣ ሰው የሚፈልገውን ሳይሆን ለሰው የሚያስፈልገውን በመስበክ አስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ መስዋዕትነት ክፈሉ ማለቱ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹እንደ ርግብ የዋህ ሁኑ›› አለ እንጂ ‹‹ርግብ ሁኑ›› አላለም፡፡ ርግብን መምሰል ያለብን በሦስት ነገሮች ነው፡፡
- በርህራሄ፡- ይቅር የምንልና በሌሎች ላይ ቂም የማንይዝ በመሆን
- በየዋህነት፡- የማናታልል የማንጎዳ በመሆን (ርግብ አትዋጋም፣ አትናከስም፣ ግን ትበራለችና)
- በንጽህና፡- ራሳችንን ከኃጢአት በመጠበቅና በንስሐ ሕይወት በመኖር
እንደ እባብ ብልህ መሆን (intelligence)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያው ‹‹እንደ እባብ ብልህ ሁኑ›› ያለው አገልጋይ ሲያገለግል ዋናውን እንዳያጣ (ራሱን እንዲጠብቅ)፣ ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆን፣ በሌሎች ክፋት ተስቦ እንዳይፈተንና ካለው መንፈሳዊ ጽናት እንዳይወድቅ ለማስገንዘብ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ነጥብ አለ፡፡ ጌታችን ‹‹ብልህ/ልባም›› እንጂ ‹‹ብልጥ ሁኑ›› አላለም፡፡ ሌላውን እንዳንጎዳ ‹‹እንደ እባብ ልባም ሁኑ›› አለ እንጂ ‹‹እባብ ሁኑ›› አላለም፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት ከራስ ይልቅ ሌላውን ማስቀደም ይጠይቃልና፡፡ እንደ እባብ ልባም ሁኑ ሲባል በሦስት ነገሮች ነው፡፡
- ፈጣን ዐይኖች (sharp eyes)፡- ዐይኖቻችንን በእውቀት በማብራት ፈጣን መሆን
- የማይደለሉ ጆሮዎች (Focused ears)፡- በአስመሰዮች አሉባልታና በወሬ የማይታለሉ፣ የማይረቱ ጆሮዎች እንዲኖሩን
- በጥበብ መኖር (Wisdom)፡- ራስን በመጠበቅ እምነታችንን በማጽናት መኖር
ነገር ግን ከእባብ መውሰድ የሌለብን ነገሮችም እንዲሁ አሉ፡፡ የእባብ መብል ትቢያ ነው (ኤሳ 65፡25)፡፡ የእባብ መንገድም በአለት መካከል ነው (ምሳ 30፡19)፡፡ እባብ ቆዳውን ይቀይራል (ማቴ 12፡45)፡፡ እባብ መርዛማ ነው (መዝ 58፡4)፡፡ እባብ ተንኮለኛ ነው (ዘፍ 3፡1-20)፡፡ እባብ የዲያብሎስ ማደርያ በመሆን ለአዳም መሳሳት ምክንያት ስለነበር በእግዚአብሔር ተረግሟል፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉት የእባብ ባህርያት ልንርቅ ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ያለ አገልጋይ የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮና መመሪያዎቹን ሁል ጊዜ ማስተዋልና የአገልግሎቱም መመሪያ ማድረግ አለበት፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ባለቤቱ በመንፈስ የምናገለግለው እግዚአብሔርን መሆኑን፣ የአገልግሎቱም ዓላማ ‹‹መንፈሳዊ›› መሆኑን፣ የአገልግሎቱም መሪ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን፣ የአገልግሎቱም መስክ ለሰው ሕይወት ፈታኝ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ከዚህ ዓይነት ማስተዋል ጋር የዋህነትንና ብልህነትን አመጣጥኖና አዋሕዶ በመያዝ መንፈሳዊ አገልግሎትን መፈጸም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚያስጨንቅ ነገር ሲመጣ ግን በጸሎትና በምልጃ ወደ አገልግሎቱ ባለቤት ማመልከት ይገባል እንጂ ወደ ከንቱ ክርክርና ንትርክ መግባት አያስፈልግም፡፡ መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግ ችግሮችን በመፍታት ሰላምን ማውረድ ያስፈልጋል እንጂ፡፡ እነዚህን የመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮና መመሪያዎች ተጠቅመን በአገልግሎታችን እንድንተጋ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳኑ ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡