አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር፤ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ።

ኖላዊ ሄር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር፤ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ። ዮሐ 10፡11 (በአስተምህሮ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሠረት ከህዳር 15 እስከ ጌታችን ልደት (ታህሳስ 28/29) ድረስ ያለው ወቅት በዘመነ ብሉይ የነበሩ ቅዱሳን ነቢያት የጌታን ልደት በተስፋ እየጠበቁ የገቡትን ሱባኤ፣ የጾሟቸውን አጽዋማት በማሰብ ልዩ ልዩ ክብረ በዓላት ይከበራሉ። ለእያንዳንዱ በዓልም የተለየ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና ትርጓሜ፣ የተለየ የምስጋና መዝሙር ይዘመራል። በጾመ ነቢያት ውስጥ ያሉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ሣምንታት በተለየ መልኩ ይከበራሉ። ወቅቱም ትንቢተ ነቢያትን በማሰብ ዘመነ ስብከት ይባላል። የነቢያት የስብከታቸው ማዕከል የክርስቶስ ሰው የመሆን ተስፋ ነውና። የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሣምንት ስብከት ይባላል፤ ሁለተኛው ሣምንት ብርሃን ይባላል፤ ሦስተኛው ሳምንት ኖላዊ ይባላል። ኖላዊ ማለት ጠባቂ ማለት ሲሆን ቅዱሳን ነቢያት እውነተኛው ጠባቂ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገለጣል ብለው በትንቢት መናገራቸውና ኢየሱስ ክርስቶስም ቸር ጠባቂ መሆኑን እያሰበች ቤተክርስቲያን የምትዘምርበት፣ የምታመሰግንበትና የምታስተምርበት ዕለት በመሆኑ ኖላዊ ተብሎ ተሰይሟል።  በዚህ ዕለት ጌታችን በወንጌሉ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደሆነ ያስተማረበት ዮሐ 10፡1-22 ያለው የወንጌል ክፍል ይነበባል፣ ከተያያዥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢራት ጋርም ይሰበካል፣ ይተረጎማል።

የዚህ የጌታችን ትምህርት መነሻ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ በሌላም በኩል የሚገባ  ሌባ፥ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው።  ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።  ሁሉንም  አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ቃሉን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና(ዮሐ 10፡1-5)። ›› የሚለው ነው።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ‹‹ቸር ጠባቂ›› የተባውን ትምህርት ስለ ሦስት ምክንያቶች አስተምሯል። የቸር ጠባቂ መገለጫዎችን ለይቶ ለማሳወቅ፤  የቸር ጠባቂና የምንደኛን ልዩነት ለማስረዳትና ቸር ጠባቂ እርሱ መሆኑን ለመግለጽ ያስተማረው ነው። በትምህርቱም ሰባት የቸር ጠባቂ መገለጫዎችን አስቀምጧል።  እነዚህም፡-

 1. ቸር ጠባቂ በበሩ ይገባል፤ በበሩም ይወጣል።

ቸር ጠባቂ ወደ በጎች በረት በበሩ ብቻ ይገባል፤ በበሩም ብቻ ይወጣል። በጎቹን ከበረታቸው አውጥቶ ሊያሰማራ በግልፅ በበሩ ይገባል፤ ይዟቸውም በግልፅ (በብርሃን) በበሩ ይወጣል። የሌሊት ጠባቂውም ይከፍትለታል። ሌባ ግን አጥር ጥሶ ቅጥር አፍርሶ ይገባል እንጂ በበሩ አይገባም፤  እንደዚያውም ይወጣል።  በጨለማ ይገባል እንጂ በግልፅ (በብርሃን) አይገባም።  ምንደኛ መምህርም እንደዚሁ እምነትን አጉድሎ ሥርዓትን አፍርሶ ወደ ቤተክርስቲያን በተንኮል ይገባል።

የበጎች በር የተባለውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ያላመነ (በበሩ ያልገባ) እውነተኛ ጠባቂ ሊሆን አይችልምና። እምነትን ሥርዓትን ያልጠበቀ እውነተኛ ጠባቂ ሊሆን አይችልም። በበሩ የገባ (ተመስክሮለት የመጣ) በበሩም መግባትን ያስተማረን ጠባቂ እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በበሩ ይገባሉ፤ በበሩ ይወጣሉ።

 1. ቸር ጠባቂ በጎቹን ያውቃቸዋል፤ እነርሱም ያውቁታል።

ቸር ጠባቂ በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል። እነርሱም ድምፁን ይሰሙታል፤ ያውቁታልም። በትክክለኛው ስማቸው (ግብራቸውን በሚገልፅ) ይጠራቸዋል። እነርሱም ድምፁን ስለሚያውቁ ይሰሙታል። ቃሉን (አስተምህሮውን) ያዉቁታል። ወንበዴ ግን የበጎቹን ስም ከቶ አያውቅም፤። በጎቹም ድምፁን አያውቁትም።  እንደ ይሁዳ ዘገሊላ እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ ያሉት እንደዚህ ሐሰተኛ ጠባቂዎች ነበሩ (ሐዋ 5፡33-39)። አስተምህሮአቸው ከእግዚአብሔር ስላልሆነ ለጊዜው ተከታይ ቢያገኙም ምዕመናን አልሰሟቸውም። እነርሱም ጊዜአቸው ሲደርስ ጠፍተዋል። በጎቹን የሚያውቅ እነርሱም ድምፁን የሚያውቁት እውነተኛ እረኛችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ (መዝ 79፡1)።›› እንደተባለ የቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እርሱ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በጎች የተባሉ ምዕመናንን ሐዋርያዊ ትምህርትን እያስተማሩ በምግባር በሃይማኖት ያጸኗቸዋል።

 1. ቸር ጠባቂ በጎቹን ይመራቸዋል፤ እነርሱም ይከተሉታል።

ቸር ጠባቂ በበጎቹ ፊት ፊት ይሄዳል። እነርሱም እርሱን እየተከተሉት ይሄዳሉ። እርሱ ቀድሞ በጎቹ ይከተሉታል። ወደ መሰማርያችውም ይመራቸዋል። አንድ በግ ቢቀርበት ወይም ቢጠፋበት እንኳን ሌሎቹን ትቶ የጠፋውን ይፈልጋል (ሉቃ 15፡2ሌባ ግን ከበጎቹ ኋላ ኋላ ይሄዳል፤ በጎቹንም ሊሠርቅ ከኋላ ሆኖ በጎቹን በአይነ ቁራኛ እየተመለከተ ይከተላል። በጎቹ ቢጠፉም አይገደውም፤ ሊሠርቅ እንጂ ሊመራቸው አልመጣምና። እኛን ወደ ለመለመ መስክ የሚመራን እኛም ድምፁን ሰምተን የምንከተለው እውነተኛ ጠባቂያችን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

የሰቡትና የወፈሩት አንዳንድ በጎች፣ ምስኪኖችንና የከሱትን በጎች እየገፉ ከበረት ሲያስወጡአቸው፣ በቀንዳቸው ሲወጉአቸው፣ ሲያቆስሉአቸው፣ ሲያደሙአቸው፣ የሚጠጡትን ውኃ ሲያደፈርሱባቸው፣ ምግባቸውን ሲረግጡባቸው እያዩ ከመቀመጫቸው ላለመነሳት ዝም ብለው እንደሚያዩ ምንደኞች ያይደለ እውነተኛ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በጎች የተባሉ ምዕመናንን በእውነተኛ ትምህርት ይጠብቋቸዋል። ምንደኛ የሆኑ ክፉ መምህራን ግን በጎች የተባሉ ምዕመናንን አቁስለውና አድምተው ከበረት ያወጧቸዋል፤ በሌሎች ፈተናዎች ምዕመናንን ከመጠበቅ ቸል ይላሉ።

 1. ቸር ጠባቂ በጎቹን ይጠብቃል፤ ይንከባከባቸዋልም።

ቸር ጠባቂ በጎቹን ከክፉ ሁሉ ይጠብቃል፤ የሚያስፈልጋቸውንም ነገር ሁሉ ያውቃል። ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማቸዋል። የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል (ኢሳ 40፡11)። ጭቃውን ሳይጠየፍ ይሸከማቸዋል፤ ይንከባከባቸዋል (ሉቃ 15፡6)። ምንደኛ የሆነ እረኛ ግን የራሱን ፍላጎት እንጂ የበጎቹን ፍላጎት አያውቅም፤ እነርሱም አያውቁትም። በጎቹን ይበትናቸዋል፤ በጎቹን ይጠቀምባቸዋል እንጂ አይጠብቃቸውም፤ አይጠቅማቸውምም። ጠፍተን ሳለ የፈለገን የሚንከባከበንና የሚመግበን ቸር ጠባቂያችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

እንደ ምንደኛ (ቅጥረኛ) በጎቹን በማሰማራት ፈንታ ወደ እረፍት መስክ ራሱን ያላሰማራ፤ በአደራና በጠባቂነት የተሰጣቸውን በጎች እያረዱ እየበሉ አውሬ በላቸው እንደሚሉ ቅጥረኞች ያይደለ፤  በጎች እሰከሚበርዳቸው ድረስ ያለ አግባብ ፀጉራቸውን እንደሚሸልቱ ቅጥረኛ ያልሆነ፤ ታማሚ በጎችን እንዳላከሙ፤ ደካሞችን እንዳላዳኑ፤ ሰባራዎችን እንዳልጠገኑ፤ የጠፉትን በጎች ወደ መንጋው በመመለስ ፈንታ ወሬያቸውን በመሰለቅ በወንበራቸው ተቀምጠው እንዳልሰበሰቡ እረኞች ያይደለ የጠፉትን የሚሰበስብ  የቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እርሱ ነው።

 1. ቸር ጠባቂ ለበጎቹ መልካም መሰማርያን ያዘጋጃል፤ ያሰማራቸዋልም።

ቸር ጠባቂ በጎቹን በመልካም ስፍራ ለማሰማራት መሰማርያን ያዘጋጃል። ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም፤ በለመለመ መስክ ይመራኛል(መዝ 22፡1)።›› እንዳለው ቸር ጠባቂ በጎቹን በለመለመ መስክ ያሰማራቸዋል።  ‹‹በሙሴና በአሮን እጅ ህዝብህን እንደ በጎች መራሀቸው›› መዝ 76፡20 እንደተባለም በበጎ ይመራል። የለመለመ መሰማርያ የተባለም የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የአገልግሎት ዘርፍ ነው።

ምንደኛ ግን ራሱን ያሰማራል። በትንቢተ ሕዝቅኤል በምዕራፍ 43 ቁጥር 2 ላይ እንደተገለፀው ክፉ እረኛ ራሱን በበጎቹ መካከል ያሰማራል። ጠቦቶቹንም ያርዳቸዋል፤ ይበላቸዋልም። ‹‹ጮማውን ትበላላችሁ፤ ጠጉሩንም ትለብሳላችሁ፤ የወፈሩትንም ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም (ሕዝ 34፡23)።›› እንዳለ መሰማርያውንና ውኃውን ይረግጣል፤ ያፈርሳልም። ለራሱና ለራሱ ብቻ መሰማርያን ያዘጋጃል። ለእኛ ግን ለነፍስም ለሥጋም የሚሆን መሰማርያን የሚያዘጋጅልን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

 1. ቸር ጠባቂ በጎቹን ያበዛል።

ቸር ጠባቂ በበረት ያሉትንና በውጭ ያሉትን በጎች አንድ ለማድረግ ይተጋል። በውጭ ያሉትን በጎች ወደ በረት ለማስገባት ሌትና ቀን ይሠራል። ይህንንም መርህ በማድረግ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን ለዓለም በመስበክ በጎችን አብዝተዋል። ቅጥረኛ ግን በውጭ ያሉት በጎች በዚያው ቢቀሩ አይገደውም። በበረት ያሉትንም ጭምር በመከፋፈል ከበረት አስወጥቶ ይበትናል። እርሱ ስለራሱ ጥቅም እንጂ ስለበጎቹ ምንም የማይገደው ምንደኛ ነውና። ነገር ግን ‹‹የማሰማሪያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው (ኤር 23፡1)።›› እንደተባለ በመጨረሻው ቀን መጠየቁ አይቀርም። እኛ ግን የጠፉትን የሚፈልግ፣ ያሉትን የሚያፀና እውነተኛ ጠባቂያችን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለን እናምናለን።

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር።  በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር (1ኛ ሳሙ 17፡34)። ›› እንዳለው ከዲያብሎስ ጉሮሮ ከአንበሳም መንጋጋ ያዳነን እውነተኛው ጠባቂያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

 1. ቸር ጠባቂ ስለበጎቹ መስዋእት ይሆናል።

ቸር ጠባቂ ራሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። ተኩላ ሲመጣ ጥሎ አይሸሽም፤ ከበጎቹ ቀድሞ ይዋጋል እንጂ። ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም (ዮሐ 15፡13)።›› እንደተባለ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ መስዋእት ይሆናል። ምንደኛ ግን በጎቹን ስለ ራሱ አሳልፎ ይሰጣል። ተኩላ ሲመጣም በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፤ በጎቹም ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ።

‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ።  ቸር ጠባቂ ነ ስለ በጎቹ ፍሱን ይሰጣል።  ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያልሆኑ ምንደኛ ግን ቅጥረኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፤  ይበትናቸዋልም።  ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎቹም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና።  ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን አውቃለሁ፡፡ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፡፡ አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎች ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ (ዮሐ 10፡11-15)።›› እንዳለ  ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሰጠ እውነተኛ ጠባቂያችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እንደተናገረው ቸር ጠባቂ እርሱ ነው፤ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎቹ ትልቅ ጠባቂ የሆነው እርሱ ነው (ዕብ 13፡20)። የነፍሳችን  ጠባቂ የሆነው እርሱ ነው (1ኛ ጴጥ 2፡23)። የእስራኤል ዘነፍስ ጠባቂ የሆነውም እርሱ ነው (መዝ 79፡1)። እውነተኛም ጠባቂ እርሱ ነው (ዮሐ 10፡7)።

በጎችን የመጠበቅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት

በጎችን የመጠበቅ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር አብሮ ለጠባቂዎች (ለሐዋርያትና ከሐዋርያት ቀጥሎ እስከ ዕለተ ምጽዓት ለሚነሱ እውነተኛ መምህራን) ተሰጥቷል። ‹‹ግልገሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ።›› ብሎ የመጠበቅ ኃላፊነትን በጴጥሮስ በኩል ለሐዋርት ሰጥቷል (ዮሐ 21፡15-17)። ‹‹በጎቼን ከጠባቂዎች እጅ እፈልጋለሁ›› ብሎም በጎችን የመጠበቅ አገልግሎት ተጠያቂነትም እንዳለበት ተናግሯል (ሕዝ 34፡10)። በጎች (ምዕመናን) የክርስቶስ ተከታዮች እንጂ የእረኞቹ ተከታዮች አይደሉም፤  ጠባቂዎችም ባለአደራዎች እንጂ የበጎቹ ባለቤቶች አይደሉምና።

ዛሬስ የጠባቂዎች  ድርሻ ምንድን ነው?

ጌታችን እንዳስተማረው የጠባቂዎች (የካህናትና የመምህራን) ድርሻ የሚከተሉትን ያጠቃልላል።

 1. በበሩ መግባት፡- በተዋሕዶ ላይ መመሥረት፣ በሥርዓት መመራት፣ በእምነት መኖር
 2. በጎቹን ማወቅ፡- በግና ተኩላን ለይቶ ማወቅ፣ የራስንና የሌላውን ለይቶ ማወቅ፣ ለበጎቹም ግልፅ መሆን
 3. በጎቹን መጠበቅ፡- በጎችን ነቅቶ መጠበቅ (እንዳይነጠቁ)፣ ባክነው እንዳይጠፉ መንከባከብ
 4. መሠማርያውን ማዘጋጀት፡- የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት፣ ተግሳፅና ምክር መስጠት
 5. በመልካም ስፍራ ማሰማራት፡- ከፊት ሆኖ በመምራት (በማገልገል) ለሥጋ ወደሙ ማብቃት
 6. አንድነትን ማጠናከር፡- ከውጭ ያሉትን በማምጣትና ከውስጥ ያሉትን በማፅናት አንድነትን ማጠናከር
 7. መስዋዕትነትን መክፈል፡- እውነትን በመመስከር መልካም አርአያ መሆን

የበጎች (የተጠባቂዎች) ድርሻስ ምንድን ነው?

በጌታችን ትምህርት መሠረት በጎች (ተጠባቂዎች) ጠባቂያቸውን በሚገባ ድምፁን ማወቅና እርሱንም መከተል፣ እውነተኛ ጠባቂ ያልሆነውን (ክፉውን እረኛ ወይም ምንደኛውን) መለየትና ከእርሱም  መራቅ፣ ዛሬ እውነተኛ የሆነው ጠባቂያቸው ወደ ምንደኛነት  ቢቀየር እንኳን ቶሎ ነቅቶ መለየት መቻልና ራሳቸውንም መጠበቅ ይኖርባቸዋል። እውነተኛና ቸር ጠባቂያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም በጎች ያድርገን፤ አርአያ የሚሆኑ ደገኞች ጠባቂዎችንም አያሳጣን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች (ዘፍ 35፡13-15)፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።እግዚአብሔርም፡- ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም አለው፡- ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።›› ዘፍ 35፡9-15

ቤቴል (ቤት-ኤል) ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ያቺ ሀውልት እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር የተነጋገረባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ ተገለፀለት፡፡ በቤተክርስቲያንም አምኖ ለቀረበ እግዚአብሔር በረድኤት ይገለፅለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ያዕቆብን ባርኮታል፡፡ በቤተክርቲያንም ተግቶ የጸለየ እግዚአብሔር በረከትን ያበዛለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎታል፡፡ ሰውም ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተቀብሎ አዲስ ማንነትን (ክርስትናን) ይዞ በአዲስ ስም (በክርስትና ስም) ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር በቤቴል ያደረገው ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ለሚደረገው ምሳሌ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቤተል እግዚአብሔር እስራኤል ለተባለው ያዕቆብ ‹‹ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።›› ሲል የዘላለም ኪዳነን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ኪዳን ቤቴል በተባለችው ቤተክርስቲያንም ጸንተው ለኖሩት ለቅዱሳን የተሰጠ ኪዳን ነውና ያቺ እግዚአብሔር ለያዕቆብ የተገለፀባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኗ በተረዳ ነገር ላይ የተመሠረተ እንጂ በአጋጣሚ የተወሰደ አይደለም፡፡

ልክ እንደ ቤቴል ሰውና እግዚአብሔር የሚነጋገሩባት ስፍራ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያች ስፍራ ያዕቆብ የድንጋይ ሐውልትን መትከሉ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበትን ጽኑዕ መሠረት ያሳያል፡፡ ያዕቆብ በሐውልቱ ላይ ዘይትን አፈሰሰ፡፡ ይህም ዛሬም አዲስ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚከብር ያሳያል፡፡ በዚያች ቦታ ላይ ያዕቆብ የመጠጥን መስዋዕት እንዳቀረበ በቤተክርስቲያንም አማናዊው የክርስቶስ ደም ለመስዋዕትነት ይቀርባል፡፡ በቤቴል ያዕቆብ የተከላት ሐውልት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ስንል እነዚህ ሁሉ ትንታኔዎችን በማስተዋል ነው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ ትመሰላለች፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ ትመሰላለች (ዘፍ 22፡12)፡፡

‹‹ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ። የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።

እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።›› ዘፍ 22፡1-14

እግዚአብሔር  አበ ብዙኀን አብርሃምን አንድ ልጅህን  ሠዋልኝ  ባለው ጊዜ የዋሁ ይስሀቅ ሊሠዋበት ያለው ያ የሞርያ ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም በህሊናው ይስሀቅን ቀብሮ እንጨት ፣ ቢለዋ፣ እሳት፣ ይዞ በደብረ ሞርያ ላይ ቢላውን አንሰቶ ሊሰዋው ሲል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማው እንዲህ ብሎ “ አብርሃም አብርሃም ከብላቴናው ላይ እጅህን አንሳ ለምትወደው ልጅህ አልራራህምና አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንክ አውቃለሁ” ባለው ጊዜ ዞር ሲል በዕፀ ሣቤቅ የታሰረ ነጭ በግ አየ፡፡

ይስሐቅ የአዳምና ልጆቹ  ምሳሌ ነው፡፡ በእርሱ ፈንታ እውነተኛው በግ ታርዶ አድኖታልና፡፡ ዕፀ ሣቤቅ የእመቤታችን ምሳሌናት፡፡ ዕፀ ሣቤቅ በይስሐቅ ፈንታ የተሰዋውን ነጭ በግ አሰገኝታለች፡፡ እመቤታችንም ለአዳምና ለልጆቹ ቤዛነት የተሰዋውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡ ነጭ በግ ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በይስሐቅ ፈንታ ተሰውቶ አዳምንና ልጆቹን አድኗልና፡፡

በሞሪያ ተራራው ላይ ይስሐቅ  ያይደለ በጉ እንደተሰዋ በቤተክርስቲያንም የሩቅ ብዕሲ ደም ሳይሆን መለኮት የተዋሀደው ነፍስ የተለየው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ይፈተታል፡፡ ለዚህም ነው ይህች እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያ ተራራ የምትመሰለው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ 18፡1)፡፡

“በቀትርም ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት።” ዘፍ 18፡1-5

አብርሃም ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለባት ያቺ የአብርሁም ድንኳን (ኀይመተ አብርሃም) የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ  ናት፡፡ አብርሃም ሥላሴን በእንግድነት በቤቱ ድንኳን ስር እንደተገኙ በቤተክርስቲያን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድራሉ፡፡

በአብርሃም ድንኳን ውስጥ አብርሃም ምሥጢረ ሥላሴን እንደተማረ በቤተክርስቲያንም ምሥጢረ ሥላሴ ይነገራልና፡፡
በአብርሃም ድንኳን ድሀ ሀብታም፣ ነጭ ጥቁር፣ የተማረ ያልተማረ፣ ኃጥእ ጻድቅ ሳትል እንግዳ እንደተቀበለች ቤተክርስቲያንም ያለ አድሎ ሁሉን በእኩል አይን ትቀበላለች፡፡ በአብርሃም ድንኳን ምግበ ሥጋ ይመገቡባት እንደነበር በቤተክርስቲያንም ሥጋ ወደሙና ቃለ እግዚአብሔር እንመገባለን፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቤተክርስቲያን በአብርሀም ድንኳን ትመሰላለች፡፡

በአብርሀም ድንኳን ውስጥ የነበሩት ሁሉ የየራሳቸው ምሳሌ አላቸው፡፡ አብርሀም የካህናት ምሳሌ ነው፡፡ መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ሲሰዋ የነበረ ነውና፡፡ በአብርሀም ቤት ይስተናገዱ የነበሩት እንግዶች የክርስቲያኖች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ ሲኖር እንግዳ ነውና፡፡ ምግበ ነፍስንም (የእግዚአብሔር ቃልንና የክርስቶስን ሥጋና ደም) ወደ ቤተክርስቲያን ቀርቦ ይመገባል፡፡ አብርሀም ቤት ሳይሠራ በድንኳን ውስጥ እድሜውን ሁሉ ኖሯል፡፡ ፍፁማን አገልጋዮችም እንደ አብርሀም ዓለምንና ጣዕሟን ሁሉ ንቀው ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ይኖራሉና አብርሀም የእነዚህ አርአያ ነው፡፡ ሥሉስ ቅዱስ በአብርሀም ቤት ተገኝተው ቤቱን በበረከት ሞልተውታል፡፡ ዛሬም እንደዚሁ በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ላመኑትና ለታመኑት ሁሉ ድኅነትን ያድላሉ፡፡

ከዚህ ሌላ ሰይጣን እንግዶች ወደ አብርሃም ድንኳን እንዳይሄዱ ይከለክል እንደነበር በትርጓሜ መጻሕፍት ሊቃውንት አስተምረዋል፡፡ ይህም ምሳሌው ክርስቲያኖች ወደ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የተለያዩ ፈተናዎች እያቀረበ ሊያስቀራቸው እንደሚሞክር የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዶች ቢቀሩም ሥሉስ ቅዱስ ተገኝተዋል፡፡ በቤተክርስቲያንም ሰዎች በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያን ሳይሄዱ ቢቀሩ እንኳን እግዚአብሔር አገልግሎቱን እንደሚባርክ የሚያረጋግጥ ምሳሌ ነው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች::

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች (ዘፍ 7፡1)፡፡

በማየ አይህ /በጥፋት ውሃ/ ጊዜ ነፍሳት ከሞተ ሥጋ የዳኑባት ያቺ የኖኅ መርከብ የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ምሳሌነቷም እንደሚከተለው ነው፡፡ ያቺ የኖኅ መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት፡፡ ቤተክርቲያንም ቅድስት ፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማህሌት  የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡ የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ  አምነው ተጠምቀው ሥጋ ወደሙን የተቀበሉ ከሞተ ነፍስ ይድናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ስትመሰል ዓለም ደግሞ በጥፋት ውኃው ትመሰላለች፡፡ በቤተክርስቲያን በጥምቀት ገብተው እንደ ሕጉና ሥርዓቱ የሚኖሩ ሲድኑ እምቢ ብለው በዓለም የቀሩት ደግሞ በኃጥአት ምክንያት (በጥፋት ውኃ) ይጠፋሉና ምሳሌው ገላጭ ነው፡፡

ኖኅ መርከብን እንዲሠራ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመሠረታት ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኖኅ ወደ መርከቡ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ያስተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የሰው ልጅ ሁሉ አምኖ ይድን ዘንድ የድኅነት ጥሪዋን ለሁሉም ነው የምታስተላልፈው፡፡ የኖኅ መርከብ ፈቃደኛ ሆኖ ለመጣ ሁሉ (ለእንስሳትም ጭምር) በቅታለች፡፡ ቤተክርስቲያንም አምኖ ለመጣ ሁሉ የሚበቃ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላት ናት፡፡ የኖኅ መርከብ የጥፋት ውኃ እስጎድል በውስጧ የነበሩትን ጠብቃ አቆይታ የጥፋት ውኃ ከጠፋ በኋላ ወደ መልካም ምድር አድርሳቸዋለች፡፡ ቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖችን በዚህ ምድር ላይ ከኃጢአት ጠብቃ አቆይታ ለሰማያዊ ክብር ታበቃለችና በኖኅ መርከብ መመሰሏ ይህንን ምሥጢር አጉልቶ ስለሚያሳይ ነው፡፡

በተጨማሪም የጥፋት ውኃው እየሞላ ሲሄድ የኖኅ መርከብ ከምድር ከፍ ከፍ እያለች ትሄድ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፈተና ሲበዛባት በውስጥዋ የሚኖሩት (በፈተና የሚፀኑት) የሚያገኙት ክብር እንደዚሁ ከፍ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ኖኅን አሰበ፣ የጥፋት ነፋስን አሳለፈ፣ ውኃውም ጎደለ፡፡ በቤተክርስቲያን ላይም የሚመጣውን ፈተና እንደዚሁ እግዚአብሔር ያሳልፋል፡፡

የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌዎች

መግቢያ

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ በድንገት የተቋቋመች አይደለችም፡፡ ይህች አውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እንደ ወሃ ደራሽ በድንገት የደረሰችም አይደችም፡፡ አማናዊቷ ቤተክርስቲያን እንደ ወፍ ዘራሽ በድንገት የተመሠረተችም አይደለችም፡፡ ዓለም ከተፈጠረበት ዘመን ከተቆጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምሳሌዎች እተመሰለች (በምሳሌዎች እየተገለጸች)  በጥላ ውስጥ የነበረችና የኖረች ናት እንጂ፡፡

ሌሎች ራሳቸውን ቤተክርስቲያን የሚሉ ድርጅቶች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ መሥራቾቻቸው ሰዎች ሰለሆኑ በድንገት ወይም በጥናት በሰው ሀሳብ የተመሠረቱና የሚመሠረቱ ናቸው፡፡ ያ የተመሠረቱበት ሀሳብና ዓላማ ሲያረጅ መታደስ ያስፈልጋቸዋል፤ አለበለዚያ ይፈርሳሉ፡፡ እንደ ምድራዊ ተቋም በሰው አስተሳሰብ የሚመሩ ናቸውና፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶች ህገ ደንቡ ወይም አሠራሩ ወይም አመራሩ አልመች ሲላቸው ተገንጥለው ሌላ የራሳቸው ‘ቤተክርስቲያን’ ይመሠርታሉ፡፡ እንደዚያ እንደዚያ እያለ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነት ድርጅቶች ለመመሥረት በቅተዋል፡፡ አማናዊት ቤተክርስቲያን ግን እንደዚህ አይደለችም፡፡ ዘላለማዊና አንዱ አምላክ የመሠረታት ዘላለማዊትና አንዲት ናት እንጂ፡፡

የክርስቶስ ሐዋርያት ክርስቲያን ተብለው (ሐዋ 11፡26)፣ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ ደም ተዋጅታና (ሐዋ 23፡20) አማናዊት ሆና እስክትገለጥ ድረስ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት ዘመን ብዙ ምሳሌዎች ነበሯት፡፡ ምሳሌ ያው ምሳሌ ነው፡፡ እውነተኛውን ነገር ለማስረዳት እንጂ ለመተካት የሚቀርብ አይደለም፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ለእውነኛይቱ የክርስቶስ ቤተከርስቲያን እንጂ ለሌሎች ራሳቸውን ቤተክርስቲያን ብለው  ለሰየሙት ድርጅቶች የሚስማሙ አይደሉም፡፡ ለመረዳት ያህል በሕገ ልቡናና በዘመነ ኦሪት ሥርዓተ አምልኮ ይፈጽምባቸው ከነበሩት የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ይቀጥላል

ቤተክርስቲያን ዘላለማዊትና የማትታደስ ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ዘላለማዊትና የማትታደስ ናት፡፡

ዘላለማዊነት አንዱ የቤተክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዘላለማዊት ናት፡፡ መሠረቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ነውና እርሷም ዘላለማዊት ናት፡፡ በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር ያላቸው አንድነት ዘላለማዊ ነውና ቤተክርስቲያንም ዘላለማዊት ናት፡፡ ዘላለማዊ ናት ስንል ዘላለማዊነቷ በመጠበቅ (ጠብቆ ይነበብ) እንጂ በመታደስ (እየታደሰች) አይደለም፡፡ ክርስቶስ የምታረጅ፣ የምትለወጥ ወይም የምትጠፋ ቤተክርስቲያን አልመሠረተም፡፡ የማያረጅ ነገር ደግሞ አይታደስም፡፡ ሁል ገዜ አዲስ ነውና፡፡ ከዚህ ውጭ ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት ግን የሚከተሉትን መሠረታዊ ስህተቶች/ክህደቶች ያስከትላል፡፡

 1. ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- ሐዋርያዊ መሠረት አያስፈልጋትም በየጊዜው ሌላ መሠረት ያስፈልጋታል ማለት ነው፡፡
 2. ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- መሥራቿ አጉድሎ ነው የመሠረታት ናትና እኛ እናሟላት እንደማለት ነው፡፡
 3. ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- በእርሷ የነበሩ በእርሷ የኖሩ አልፀደቁም እንደማለትም ነው፡፡
 4. ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- የምትፈጽማቸው ምሥጢራት ለድኅነት አያበቁምና ይሻሻሉ ማለት ነው፡፡
 5. ቤተክርስቲያን ትታደስ ማለት፡- እኛ ከቀደሙት የተሻልን ነንና የተሻለች ቤተክርስቲያን እንመሥርት እንደማለት ነው፡፡

ስለዚህ ቤተክርስቲያን ትታደስ የሚለው አስተሳሰብ መሠረታዊ ስህተት ነው፡፡ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት የሚቀየሩ ወይም የሚሻሻሉ አይደሉም፡፡ ጸንተው የሚኖሩ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሁለት በቤተክርስቲያን ዘንድ እድሳት የሚያስልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም የቤተክርስቲያን አስተዳደርና የክርስቲያኖች ሕይወት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር በየጊዜው እየታዩ ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ አስተዳደሩን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡  የምዕመናን ሕይወት ደግሞ በንስሐ እየታደሰ ይኖራል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሰውን የምታድሰው ቤተክርስቲያን እራሷ አትታደስም፡፡

ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

አዎን! ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ . . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡

ከትንሣኤው በኃላም “ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኃለሁ ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና እንዲህም አላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኃቸው ይሰረይላቸዋል ይቅር ያላላችኃቸው ግን አይሰረይላቸውም” ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 22፡፡

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለዋል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሐዋሪያት ሥራ 20 ፥ 28፡፡ በማለት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ልትመራ እንደሚገባ አስገንዝቦናል ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ልብ ይልዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊት ናት ስንል ሐዋርያዊት የሆነችው በሦስት ነገሮች ነው፡፡

በሢመት ሀረግ፡- ከሐዋርያት አንስቶ ያልተቋረጠ የሢመት ሀረግ መኖሩ ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው የክህነት ስልጣን ሳይቋረጥ በቀጥታ እየተላለፈ መምጣቱ አንዱ የሐዋርያዊትነቷ መገለጫ ነው፡፡

በትውፊትና በምሥጢር፡-  ቤተክርስቲያን የሐዋርትን ትውፊት ተቀብላ መተግበሯ ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሲኖዶስ አላት፡ እንደ ሐዋርት ታጠምቃለች፡ እንደ ሐዋርያት ትቀድሳለች፡ ሥጋና ደሙን ታቀብላለች፡፡ ሐዋርያት የሠሩትን እንደ ሐዋርያት አድርጋ ትሠራለች፡፡ ከሐዋርያት የተለየ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፡፡ ይህ የሐዋርያዊትነቷ ሌላው መገለጫ ነው፡፡

በመጻሕፍት ትርጓሜ፡- ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ስላላት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሐዋርያት እንደተረጎሙት አድርጋ ትተረጉማለች፡፡ ሐዋርያት እንዳስተማሩት አድርጋ ታስተምራለች፡፡ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አታስተምርም፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡- አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ስርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። . . .በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን? ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? የሚለው መጠይቅና መልሰ የቤተ ክርስቲያን እርከናዊ መዋቅር ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያስገነዝበናል ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን ያሳያል ምክንያቱም ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ናቸውና። ስለዚህ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ ይህ ሐዋርያዊ ውርስ ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት ለመስጠት ነበር ሐዋርያትም ግራ ቀኙን አድምጠው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተዋል።ሐዋርያትና ቀሳውስት ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኃል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳችውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ፡፡ ” የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 22 – 29፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ፍልስጤም ወደ ሌሎቹ የሮማ ግዛቶች ግዛትዋን እያሰፋች በመጣች ግዜም መዋቅርዋ፤ ሐዋርያዊ ሠንሰለቱ እንደተጠበቀ ነበር፤ ከቤተ አይሁድም ከቤተ አሕዛብም የመጡ ከሐዋርያት የሰሙ ከሐዋርያት የተማሩ ሐዋርያውያን አባቶች በሐዋርያት መንበር እየተተኩ ሠንሰለቱ ሳይበጠስ ቀጥሉዋል እንደ ኤሬኒዮስ ናኤጲፋንዮስ አገላለጽ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ደቀ መዝሙሩ የነበረው ሊኖስ ሲሆን (የዚህ አባት ስም በ2ኛ ጢሞቲዎስ 4 ፥ 21 ላይ ተጠቅሱዋል) አውሳብዮስ ግን የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሴ መንበር ቀሌምንጦስ ነው ይላል፡፡ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ቅዱስ ማርቆስ አሰተምሮ ያሳመነው፣ ያጠመቀውና በክህነት የወለደው ጫማ ሰሪ የነበረው አናንያስ ነበር የተሰየመው ፤ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ እንዲሁም ሌሎችም ከሐዋርያት በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የማስተዳደር ስልጣንን ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምንለው በሐዋርያው በቅዱስ ፊልጶስ አማካይነት በ34ዓ.ም ጥምቀትን ተቀበለች፥ በኃላም በአራተኛው ምዕተ ዓመት በሲኖዶስ ሕግ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ሥር የተዋቀረች በመሆኑ ነው፡፡ የራስዋ መንበር ባለቤት የሆነችውም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዓመጽ ተገንጥላ ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሥርዓቱ ነው፡፡ ለዚህም አባቶቻችን አያሌ ዘመናት በትእግስት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጠንተዋል፡፡ይህም የሐዋርያዊ ውርስ ሠንሰለቱ እንዲጠበቅ የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡

 

ቤተክርስቲያን ኲላዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ላዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ኲላዊት ናት ሲባል የሁሉ (አለም አቀፋዊት- Universal) እና ከሁሉ በላይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህም በጸሎተ ሃይማኖት “እንተ ላዕለ ኩሉ” በሚለው ይታወቃል፡፡ ቤተክርስቲያን የሁሉ እንደሆነች ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ ናት፡፡ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ወገን ናት የዚህ ወገን አይደለችም የማትባል በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎጥና በቀለም እንዲሁም በቦታ የማትከፋፈል የሁሉና በሁሉ ያለች ናት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆንዋን እንዲህ ሲል ገልጾታል“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ገላቲያን 3 ፥ 28፡፡

 

ቤተክርስቲያን የሁሉ ናት (አለም አቀፋዊት ናት) ስንል በአምስት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

በመልክአ ምድር (Geography)፡- ቤተክርስቲያን የዚህ ሀገር ወይም የዚህ አካባቢ ናት አይባልም፡፡ በክርስቶስ ያመነ የተጠመቀ ሁሉ (ከማንኛውም የዓለም ክፍል ቢመጣ) የሚገባባትና የሚኖርባት ቤት ናት እንጂ፡፡

በሰው ፀባይ (Personal attributes):- ቤተክርስቲያን የዚህ ዘር፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የዚህ ጾታ ወይም የዚህ እድሜ ክልል ናት አይባልም፡፡ የሁሉም ናት እንጂ፡፡ በቤተክርስቲያን ሰው እምነቱ እንጂ ሰብአዊ ማንነቱ አይጠየቅም፡፡

በጊዜ/በዘመን (Time horizon)፡- ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ለነበረው ትውልድ፣ አሁንም ላለው ትውልድ፣ ወደፊትም ለሚኖረው ትውልድ ናት፡፡ ቤተክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል የሁሉም ትውልድ ናት ማለትም ነው፡፡

በማዕረጋት (Hierarchical):- ቤተክርስቲያን የፓትያርኩም፡ የጳጳሳቱም፡ የቀሳውስቱም፡ የዲያቆናቱም፡ የምዕመናኑም ናት፡፡ ሁሉም በቤተክርስቲያን የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

በሰማይና ምድር (Earth and Heaven)፡- ቤተክርስቲያን በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉት አንድነት ስለሆነች የሁለቱም ናት፡፡ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ስለሆነች የክርስቶስ ለሆነ ሁሉ ናት፡፡

ቤተክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል በቃ የሁሉ ናት ተብሎ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሁሉም ናት ማለት ሁሉም በቤተክርስቲያን የየራሱ የአገልግሎት ድርሻ አለው ማለት ነው፡፡ ፈተና ቢያጋጥማትም የሚመለከተው ሁሉንም ነው ማለት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡

ክርስቶስ በቅዱስ ደሙ መሥርቷታል፤ አንጽቷታል፤ ቀድሷታልና ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ኤፌሶን 5 ፥ 26፡፡የቤተ ክርስቲያን ቅድስና የተገኘው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ወደ እርስዋ የገቡ ርኩሳን ይቀደሳሉ እንጂ በውስጥዋ ያሉ ሰዎች በኃጢአት በክህደት ቢረክሱ እርስዋ አትረክስም፡፡ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በእርሱ ያመኑ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የተጠለሉ ሁሉ ቅድስናን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ቤተክርስቲያን ቅድስት (የተለየች) ናት ስንል ስለ አራት ነገሮችን ያመለክታል፡፡

አንደኛ፡ በደሙ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ነውና ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡ 1ጴጥ 1፡15-16 ሐዋ 23፡20 ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ናትና ቅድስት ናት፡፡ እርሱም መሠረቷ አካሏና ጉልላቷ ስለሆነ ቅድስት ናት፡፡

ሁለተኛ፡-ቤተክርስቲያን የቅድስና ሥራ (አገልግሎት) የሚፈጸምባት የጸሎት ቤት ናትና ቅድስት (የተለየች) ናት፡፡ የተለየችው ለቅድስና ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በቅድስት ቤተክርስቲያን የቅድስና ያልሆነ ሥራ መሥራት አይገባም፡፡

ሦስተኛ፡- ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ የሰው ልጆች ምሥጢራትን ተካፍለው (ተጠምቀው ንስሐ ገብተው ሥጋና ደሙን ተቀብለው) ቅድስና ያገኙባታልና ቅድስት ናት፡፡ የቅድስና መገኛ ስፍራ ናትና ቅድስት ናት፡፡

አራተኛ፡- ቤተክርስቲያን ቅድስት የሆነችው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ቅድስት ናት፡፡ ወደ ሰማያዊት መንግስት የምታደርስ በምድር ላይ ያለች የክርስቲያኖች ቤት ናትና ቅድስት ናት፡፡ በምድር ላይ ለእግዚአብሔር የተለየች ቅድስት ናት፡፡

አንዳንድ ወገኖች ብዙ ኃጢአት የሚሠሩና በደልን የሚፈፅሙ ሰዎች በቤተክርስቲያን ስላሉ ቤተክርስቲያን የምትረክስ (ቅድስናዋ የሚቀንስ) ይመስላቸዋል፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች በጊዜው በንስሐ ካልተለመሱ ራሳቸው ይረክሳሉ እንጂ ቤተክርስቲያን አትረክስም፡፡ የቤተክርስቲያን ቅድስናዋ ዘላለማዊና የማይለወጥ ስለሆነ አትረክስም፡፡ ሰው ቢያከብራት ራሱ ይከብራል፡፡ ባያከብራት ደግሞ ራሱ ይረክሳል፡፡ ይህም በአፍኒንና በፊንሐስ እንዲሁም በሐናና በሳጲራ እንደሆነው ነው፡፡ ሐዋ 5፡1 1ኛ ሳሙ 2፡12 ለምሳሌ በቆሻሻ ላይ የፀሐይ ብርሀን ቢወጣበት ቆሻሻው ይሸታል እንጂ የፀሐይ ብርሀኑ ምንም አይሆንም፡፡ የቤተክርስቲያን ቅድስናም ልክ እንደ ፀሐይ ብርሀን ነው፡፡