አባቶችን ማክበር፡ እንዴትና እስከምን ድረስ?

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያ ከተስፋፋ በኋላ አንዳንድ ካህናት አባቶችን በአሳፋሪ አገላለፆች ሥምና ፎቶ እያቀናበሩ የሚዘልፉ ጽሑፎችና ምስሎችን ማሰራጨት እየተለመደ መጥቷል። በዚህ መካከል ባላደረጉትና ባልዋሉበት ስማቸው በክፉ የሚነሳ አባቶች አሉ። አንዳንድ ለቤተ ክርስቲያን ቀና አመለካከት የሌላቸው ወገኖችም ምዕመናን በአባቶች ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲቀንስ ለማድረግ ወይም ከተወሰኑት አባቶች ጋር ባላቸው የግል ጉዳይ ተነስተው ክብረ ክህነትን በሚያዋርድ፣ አባትነትን በሚያናንቅ መልኩ ያልተመዘነ ዘለፋን ያቀርባሉ። በአንጻሩ ደግሞ ለአባትነት የሚያበቃ እምነትም ይሁን ምግባር ሳይኖራቸው ተመሳስለው የገቡ ሲሞናውያንና መናፍቃን በሚያደርጓቸው ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ተግባራት ምክንያት የአባቶች ጉዳይ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። በሌላም በኩል ክብርን የሚፈልጉ አንዳንድ ‘ጥቅመኞች’ “አባቶችን እናክብር” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ትዕዛዝ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ ያለ ዐውዱ እየጠቀሱ ያነሱታል። ለእነዚህ ሰዎች “አባቶችን ማክበር” ማለት “እኔን አክብሩኝ፣ ጓደኞቼን አክብሯቸው” ማለት መሆኑ ግልፅ ነው። በዚህም የተነሳ ብዙ ምዕመናን “አባቶችን የምናከብረው እንዴት ነው? አባቶችን ማክበርስ እስከምን ድረስ ነው?” እያሉ ይጠይቃሉ። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር አባቶችን የማክበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳስሳለን።

አባቶች የሚባሉት እነማን ናቸው?

በመጀመሪያ ደረጃ ‘አባት’ ማለት ልጅን የወለደ እና/ወይም ለልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ ያለው ማለት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የሁሉም አባት (የነፍስና የሥጋ) እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ያለው ከሁሉም አስቀድሞና ከሁሉም በላይ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው። በሥጋ የወለደን ደግሞ ወላጅ አባት ይባላል፡፡ የዚህ ጦማር ትኩረት የሆኑት አባቶች ግን በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ካህናትና (ጳጳሳት፣ ቀሳውስት) መምህራን (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን) ናቸው፡፡ እነዚህም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው የሚሆኑ ምዕመናንን ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል እና/ወይም ዘላለማዊ ሕይወት የሚያሰጠውን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም እየመገቡ ለመንግስተ ሰማያት ለማዘጋጀት መንፈሳዊ ኃላፊነትን የተቀበሉና ለዚህም ተጠያቂ ለመሆን በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ቃል የገቡ ሰዎች ናቸው፡፡ በዋናነት አባት የሚያሰኛቸው የአባትነት አገልግሎታቸው ነው።

ቤተ ክርስቲያን ለእነዚህ አባቶች ልዩ ክብር ትሰጣለች፡፡ የክህነት ስልጣናቸውም ጌታችን ለሐዋርያት የሰጠው የማሠርና የመፍታት ልዩና ሰማያዊ ስልጣን ነው፡፡ አብዛኞቹ አባቶች ከዚህ የክህነት መዐርግ ለመድረስ ሲሉ ረጅም ዓመታትን ተምረውና በብዙ ችግሮች አልፈው የመጡ መሆኑንም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ከገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል የተገኙት አባቶች እንደዘመናዊው ትምህርት እናት አባታቸው ቤት ሆነው የተማሩ ሳይሆን አብዛኞቹ ከወላጆቻቸው ርቀው፣ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች የሚባሉት (በቂ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ) እንኳን ሳይሟሉላቸው ከቦታ ቦታ እየተንከራተቱ የተማሩ ናቸው፡፡ በአገልግሎቱም ቢሆን አብዛኞቹ አባቶች በቂ ደሞዝ ሳይከፈላቸው፣ እነርሱ በድህነት እየኖሩ ምዕመናንን ለዘላለም ሕይወት ለማብቃት የሚተጉ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እኛ እውነተኛ አባቶች ስንል እነዚህን ማለታችን ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ የተጠጉትንና የሚነግዱባትን ማለታችን አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ኃላፊነቱን ለሚወስድ ሰው ክህነት ክብር (honor) ሳይሆን መስዋዕትነት (sacrifice) መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

አባቶችን ማክበር በመጽሐፍ ቅዱስ

እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለዓለም ሁሉ ከሰጣቸው ዐሠርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ “በምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም እናት አባትህን አክብር” (ዘጸ 20:12) የሚል ነው። እንዲሁም በዘሌ 19:3 እያንዳንዱ ሰው እናቱንና አባቱን ማክበር እንዳለበት ተጽፏል። ቅዱስ ጳውሎስም እናትና አባትን ስለማክበር ባስተማረበት መልእክቱ (ኤፌ 6: 2-3) “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” በማለት አባትንና እናትን ማክበር ያለውን ዋጋ በአጽንዖት ገልጾታል። ይህ ትዕዛዝ የሥጋ አባቶችን ብቻ ሳይሆን የመንፈስ አባቶችንም ያጠቃልላል። ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱም “ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው” በማለት የአባትነትን ክብር ገልጾታል (1 ጢሞ 5: 1-2)።

ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ “አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ” በማለት ዕውቀትን ከአባቶች መማር እንደሚያስፈልግ አስተምሮናል (1 ዮሐ 2:13)። ቅዱስ ጳውሎስ አባት የሚባለው በሥጋ የወለደን ብቻ ሳይሆን በመንፈስ የእግዚአብሔርን ቃል እየመገበ የሚያሳድግ ጭምር መሆኑን ሲገልጽ “በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሏችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና (1 ቆሮ 4:15)” በማለት አስረግጦልናል፡፡ እርሱም የቀደሙትን ነቢያት “አባቶች” ይላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ነው “እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን ((ሐዋ 13:32)” በማለት የጻፈው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም የአባቶችን ምክር መቀበል፣ ትዕዛዛቸውን መቀበልና የሠሩትን ሥርዓትም መጠበቅ ታላቅ ዋጋ እንዳለው ሲናገር “አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ (ምሳ 22: 28)” በማለት ገልጾታል፡፡ በአንጻሩ አባቶችን መሳደብ ከፍተኛ ቅጣትን እንደሚያስከትል መጽሐፍ ሲናገር “አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል (ዘፀ 21:17)” ይላል። አባቶችን አለማክበር ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ለማወቅ  አባቱን እርቃን አይቶ ያልሸፈነው የኖኅ ልጅና አባቱን ያታለለው ያዕቆብ ባደረጉት ልክ የተቀበሉትን ቅጣት ማስታወስ ይበቃል፡፡

“እናክብር” ስንል ምን ማለታችን ነው?

‘ክብር’ የሚለው ቃል በአንድ (በጥቅል) የሚገለፅ ቢሆንም አራት ዓይነት ክብር አለ፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ክብር ነው፡፡ ይህ አንድ ሰው በሥላሴ አምሳል ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ  ሊሰጠው የሚገባው ከሰብአዊነት የሚመነጭ ክብር ነው፡፡ ይህ ክብር የዕድሜ፣ የጾታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የእምነት፣ የምግባር፣ የስልጣን ወዘተ.. ልዩነት ሳይደረግበት ለሁሉም ሰብአዊ ፍጡር የሚሰጥ ክብር ነው፡፡ እግዚአብሔር ክቡር አድርጎ ፈጥሮታልና። በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ክብር የመዐርግ/የሥልጣን ክብር ነው፡፡ ይህም ክብር ማዕረግ/ስልጣን (ምድራዊም ይሁን መንፈሳዊ) ላለው ሰው የሚሰጥ፣ ከስልጣኑ የሚመነጭ ክብር ነው፡፡ ይህ ክብር አንድ ሰው ስልጣን ሲይዝ የሚሰጠው ከስልጣን ሲወርድ ደግሞ የሚቀር ክብር ነው፡፡ ለሀገር መሪዎች የሚሰጠው ክብር ይህ ዓይነቱ ክብር ነው፡፡ የክህነት ስልጣን ለተሰጣቸው አባቶችም ከክህነታቸው የተነሳ የሚሰጣቸው ክብር በዚህ ክፍል ይጠቃለላል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው ክብር የምግባር/የመልካምነት/የትሩፋት ክብር ነው፡፡ ስልጣን ይዘውም ሆነ ስልጣን ሳይኖራቸው ለመልካም ሥራ የሚተጉ፣ ለሚሠሩት ሥራ ክብር የሚሰጡ፣ ሰውን የሚያከብሩና እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ በተሰጣቸው ጸጋና በተሰማሩበት የሥራ ወይም የአገልግሎት ዘርፍ የሚጠበቅባቸውንና ከዚያም በላይ ያበረከቱ ሰዎች በተጨማሪ የሚሰጣቸው ክብር የምግባር/የስኬት/የመልካምነት ክብር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ተጨማሪ ትሩፋትን ሲሠሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስጠብቁና ሲያሳድጉ፣ ብዙ ምዕመናንን ሲያንጹና ሲያጸኑ ይህን ክብር ይገባቸዋል። በመጨረሻ (በፍጹምነት) ደረጃ ያለው ክብር የቅድስና ክብር ነው። ይህም እግዚአብሔር ላከበራቸው፣ ቤተ ክርስቲያን ላወቀቻቸው ለቅድስና ለደረሱ ቅዱሳት እናቶችና ቅዱሳን አባቶች የምንሰጠው ክብር ነው።  እኛም አባቶችን እናክብር ስልን በእነዚህ በአራት ደረጃዎች በሚገኙ የክብር ዓይነቶች ማለታችን ነው፡፡

አባቶችን የምናከብረው እንዴት ነው?

አባቶቻችንን በማክበራችን ራሳችን እንከበራለን፣ ቤተ ክርስቲያንንም እናስከብራለን፡፡ ነገር ግን አባቶችን የምናከብረው እንዴት ነው? ማክበራችንስ በምንስ ይገለጣል? አባቶች በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር ላይ ጥያቄ ማንሳት ወይም አስተያየት መስጠት አለማክበርን ያሳያልን? በዋናነት መገንዘብ የሚያስፈልገው የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማክበር ለክብረ ክህነት የሚሰጥ ሃይማኖታዊ ዋጋን ያሳያል። አባቶችን ማክበር ማለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ አድሮ የሚፈፅማቸውን ምሥጢራት ከካህናቱ ጉድፍ ጋር እያስተያየን መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ከመናቅና ከማቃለል መጠበቅን ያጠቃልላል። የካህኑን ምግባር ጠልቶ ከምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን መራቅ ወይም መለየት የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ እንደማቃለል ይቆጠራል። ካህናቱም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የግላዊ ስብዕና መገንቢያ ሲያደርጉት ጌታ የሰጣቸውን ክብር በምናምንቴ ነገር ለውጠው “አባትነትን” እያስናቁ መሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል። ለመሆኑ አባቶችን ማክበር እንዴት ይገለጣል?

አባቶችን ማክበር በብዙ ነገር ይገለጣል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አባቶች የሚናገሩትን በጥሞና መስማት/ማዳመጥ ዋነኛው ክብርን የመስጠት መገለጫ ነው፡፡ አባቶች መናገር በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲናገሩም ቅድሚያ መስጠት እንዲሁ የማክበር መገለጫ ነው፡፡ ይህ ለአባቶች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሀሳብ አለኝ የሚል ሰው ሲናገር ማድመጥ ከክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አባቶችን የምናከብረው በመልካም ንግግር/ጽሑፍ ነው፡፡ አባቶችን ስናናግር ወይም ስለአባቶች ስንናገር/ስንጽፍ ሰብአዊ ክብራቸውን፣ የክህነት/የመዐርግ ክብራቸውንና የምግባር ክብራቸውን ጠብቀን ሊሆን ይገባል፡፡ እነርሱን የሚመለከት ጥያቄ ወይም አስተያየት ካለንም ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ለራሳቸው ወይም ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አካል በተገቢው መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ 

በሦስተኛም ደረጃ ልጅ አባቱን የሚያከብረው በሚጠይቁት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት (ምክንያታዊ እና አሳማኝ ሲሆን) በመታዘዝ/በመሳተፍ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አባቶች ሲያዙን በምንችለው ነገር እሺ ብለን ያንንም መፈጸም አባቶችን ማክበር ነው፡፡ ለእነርሱ መታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነውና፡፡ በአራተኛ ደረጃ አባቶችን የምናከብረው እነርሱን በማስከበር ነው፡፡ አባቶች ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲሉ የተለያየ መከራን ይቀበላሉ፡፡ ከዚህም ሰማያዊ ዋጋን ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ያለው ሰው “አባትና እናትህን አክብር” እንደተባለ አባቶችን እንዲያከብር፣ እንዲሁም አባቶችና በመዝለፍና በመስደብ የሚያጣው እንጂ የሚያተርፈው ነገር እንደማይኖር በማስተማር አባቶችን ማስከበር ይገባል፡፡ የአባቱን ጥቃት በዝምታ የሚመለከት ልጅ ከጠላት ጋር እንደተባበረ ይቆጠራልና አባቶቻችን ላይ ጥቃት እንዳይደርስ መከላከል የልጅነት ድርሻችንና አባቶቻችንን የማስከበር ግዴታችን ነው፡፡

የአባትነትን ክብር የቀነሰው ምንድን ነው?

በዘመናችን ለአባቶች የሚሰጠው ክብር በአጠቃላይ ሲታይ የቀነሰበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከሐሜት ባሻገር አባቶችን በስም እየጠቀሱና ፎቶአቸውን እየለጠፉ በየማኅበራዊ ሚዲያው መዝለፍም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ‘ለምን ሆነ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እንደ አስተምህሮ ምልከታ ችግሩ ከአራት ነገሮች ይመነጫል፡፡ የመጀመሪያውና መሠረታዊው ችግር የተቺዎቹ ችግር ነው፡፡ በመንፈሳዊ ዕውቀትና ምግባር አለመብሰል መሠረተ ቢስ የሆነ የሠፈር ወሬ/ሀሜትን በማኅበራዊ መገናኛ ለማሠራጨት ይዳርጋል፡፡ ሀሜቱ እውነት ቢሆን እንኳ “ለማጥቂያነት የሚውል” እንጂ መንፈሳዊ ስብዕናን የሚፃረር በከሳሽነት ብቻ ጽድቅ የሚገኝ የሚያስመስል አሰራር ነው። በተጨማሪም የትዕቢትና የንቀት መንፈስ አባቶችን ለመዳፈር ይዳርጋል።

አንዳንዶች ምናልባት በዘመናዊ ትምህርት የገፉ ሲመስላቸው አባቶችን እንደ ኋላ ቀር ሊመለከቱ ይችላሉ። ነገር ግን አባቶች ከዘመናዊው ትምህርት የሚበልጥ ሰማያዊ ምስጢር የያዘውንና ሰውንም ለሰማያዊ ጸጋ የሚያበቃውን ትምህርት ተምረው ከዚህ እንደደረሱ ማስተዋል ያስፈልጋል። በሌላም በኩል ከአባቶች ሁል ጊዜ ፍጹምነትን መጠበቅ ሌላው የተቺዎቹ ችግር ነው። አባቶች እንደሰው አውቀውም ሳያውቁም (በየዋህነት) መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ወደ ንስሐ እንዲመጡ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጡ ትችቶችን መሰንዘር አይገባም። በሌላም በኩል የአባቶችን ኃጢአት በመግለጥ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ የሚመስላቸው ወገኖችም አሉ። የአባቶችን ኃጢአት በመግለጥ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ መሞከር እረኛን እያሳደዱ በጎችን ለመጠበቅ እንደመሞከር ነው። በአብዛኛውም የሚስተዋለው ይህ ነው። ይህንንም ችግር ለመፍታት መሠረታዊው መፍትሔ መንፈሳዊ ትምህርትን በተጠናከረ መልኩ ለሁሉም ማስተማር ነው።

ሁለተኛው ችግር የአባቶች ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን “አባት”፣ “ካህን” ወይም “መምህር” መባልን እንደ ግብ የሚወስዱ፣ የአባትነትን ካባ ለምድራዊ ክብር መሸፈኛነት የሚጠቀሙ ሰዎች በዝተዋል። ምንም እንኳ ምዕመናን አባቶቻቸውን ማክበር የሚገባቸው ቢሆንም “አክብሩን” ማለትን የማንኛውም ተዋስኦ መጀመሪያ የሚያደርጉ ሰዎች ከቅዱሳን ታሪክ ይልቅ የሣጥናኤልንና የክፉዎቹን መምህራነ አይሁድ ፈለግ የተከተሉ ናቸው። ሳጥናኤል በዓለመ መላእክት በስልጣን የሚበልጣቸውን ሊቃነ መላእክትና ሠራዊተ መላእክት “ለክብሬ ስገዱ” እንዳለ አባትነትን ለመንፈሳዊ ተልእኮ ሳይሆን “ሰዎችን ለማስገበር” የሚጠቀሙ ምንደኞች ሞልተዋል። ክፉዎች መምህራነ አይሁድ መንፈሳዊ ስልጣናቸውን በየአደባባዩ “አባት ሆይ! አባት ሆይ! መምህር ሆይ! መምህር ሆይ!” ለመባል በማዋላቸው አባትነትንም መምህርነትንም አዋረዱ እንጂ አላስከበሩትም። ስለሆነም የሁሉ አባት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “መምህራን፣ አባቶች፣ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ” በማለት አስተምሯል። (ማቴ 23:6-12) የዚህም መሠረቱ አባትነትን፣ መምህርነትን ወይም ሊቅነትን መቃወም ሳይሆን ለአገልግሎት፣ ለመከራ የተሸከሙትን መስቀል (አሰረ ክህነት) ለምድራዊ ክብርና ምዕመናንን ዝቅ አድርጎ ለማየት መጠቀም መንፈሳዊ መሰረት እንደሌለው፣ ይልቁንም ሣጥናኤልንና ሊቃናተ አይሁድን የሚያስመስል ክፉ መንፈስ መሆኑን ማስገንዘብ ነው።

“አክብሩን” ማለትን የነገራቸው ሁሉ አልፋና ዖሜጋ የሚያደርጉ የዘመናችን ካህናትና መምህራን ጌታችን ጻፎችና ፈሪሳውያንን የገሰፀበትን ትምህርት (ማቴ 23:1-39) ይመልከቱና ራሳቸውን ይመርምሩ። በእነዚህ የፈሪሳውያን የግብር ልጆች ዘንድ ቤተክርስቲያንን ከሚያሳድድ፣ አስተምህሮዋን ከሚያበላሽ መናፍቅ ይልቅ በእነርሱ ሐማዊ እይታ እንደ መርዶክዮስ የማያጎነብስላቸውን ሰው መስቀል የሚፈልጉ የተለሰኑ መቃብሮች ናቸው። (መጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 3) ሊቃናተ አይሁድ ለግል ክብራቸው ሲሳሱ የዘመነ ብሉይ ስልጣናቸው በዓይናቸው ላይ እንደተወሰደችባቸው በማስተዋል የጸጋ ስጦታቸውን በትህትና ሊጠብቁት ይገባል እንጂ “ራሳቸውን ከወንድሞች የተለዩ” አድርጎ በሚስል ትዕቢት ተይዘው አባትነትን፣ መምህርነትን፣ ሊቅነትን ሊያዋርዱ አይገባም።

ማንም ሰው ፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በመረጃ የተደገፉ ታላላቅ የስነ-ምግባር ጉድለቶችና የእምነት ሕፀፆች ሲስተዋሉ ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን ባላቸው ቅናት የተነሳ ወደ አጸፋ ምላሽ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ውስጥ ካህን ሳይሆኑ ካህን መስለው በመግባት እነዚህን የጎሉ ጥፋቶችን በመፈጸም ምዕመናን ካህናት ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲቀንስ የሚያደርጉ ተኩላዎችም አሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር እንደዚህ አይነት ችግር የሚፈጥሩ ‘አባቶች’ ላይ በጊዜው እርምት ቢወስድ ችግሩን መቀነስ ይቻላል፡፡ ሦስተኛው የችግሩ ምንጭ የአስተዳደር ድክመት ነው፡፡ ምዕመናን ጥያቄያቸውን፣ አስተያየታቸውንና አቤቴቱቸውን ሰምቶና መርምሮ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ አስተዳደር ሲታጣ የሚቀጥለው እርምጃ ችግር አለበት የሚባለውን ወገን ጥፋቱን ወደ አደባባይ በማውጣት “ማኅበራዊ ተቀባይነትን ማሳጣት” ይሆናል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ አስተዳደር መፍጠር ነው፡፡

አራተኛው የችግሩ ገፊ ምክንያት የዘመናዊነት ተፅዕኖ ነው፡፡ በዓለም ያሉ ፖለቲከኞች ወይም ታዋቂ ሰዎች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረገው ዘመቻ ለውጥ ያመጣ ስለሚመስለን ጥፋት አለባቸው የምንላቸው አባቶች ላይም ተመሳሳይ አካሄድን ለመከተል ይዳዳናል፡፡ ቴክኖሎጂውም በእጃችን ስልኮች ላይ ስላለ ጽፎ ለመለጠፍ ቀላል ነው፡፡ ጽፈው የለጠፉትም ማንም ሳይጠይቃቸው ሲቀር፣ ይልቁንም የተጻፈባቸው ሰዎች ማኅበራዊ ተቀባይነታቸው የቀነሰ ሲመስላቸው ይህችን አካሄድ ለመጠቀም የሚፈልጉ አሉ፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን ከዚህ አካሄድ ምን ያተርፋል? ቤተክርስቲያንስ ምን ይተርፋታል? የሚለውን መጠየቅ ይገባል፡፡ የሰው ልጅ የመናገርና የመጻፍ መብቱ የተከበረ ቢሆንም በአግባቡና በሥርዓቱ፣ ክርስቲያናዊ ሕይወትንም በሚያንጽ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡

ስለአባቶች በሚዲያ መጻፍ/መናገር

አባቶችንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን በሚመለከት እውነተኛውን መረጃ ለምዕመናን ማድረስ አስፈላጊም ተገቢም ነው። ምዕመናንም በዚህ መረጃ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ተረድተው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ይጠቅማቸዋል። መልካም የሚያደርጉ አባቶችን ሥራቸውን (ሥርዓትን በተከተለና ከከንቱ ውዳሴ በራቀ መልኩ) ለምዕመናን ማሳወቅ ጠቃሚ ነው። የአባቶችን የግል ኃጢአት (ንስሐ የሚገቡበትን) አደባባይ ማውጣት ግን ክርስቲያናዊ ጠባይ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ ወይም አስተምህሮ ሲፋለስ ደግሞ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማሳወቅ ይገባል። መፍትሔም በዚህ በኩል ስለሚገኝ ወደ ሌላ አማራጭ መሄድ አስፈላጊ አይደለም። በሌላ በኩል ባልተጣራ ወይም በፈጣራ በተገኘ መረጃ ወይም በጥላቻ የአባቶችን ስም ማጥፋት ኃጢአትም፣ በደልም ወንጀልም ነው።

የአባቶችን ስም በሚዲያ በክፉ ማንሳት ብዙ ጉዳቶች አሉት። በመጀመሪያ የአባቶችን ስም በክፉ ማንሳት ይህንን የሚያደርገውን አካል መንፈሳዊ ሕይወት ይጎዳል። በወንጀልም ሊያስጠይቅ ይችላል። በሁለተኛ ደረጃ ስማቸው በክፉ የተነሳው አባቶች በሰው ዘንድ ተቀባይነታቸው ስለሚቀንስ የአባትነት ድርሻቸውን በሚገባ እንዳይወጡ ሊያደርጋቸው ይችላሉ። ከዚህም አልፎ ለስነ-ልቡና ስብራትና ለአእምሮ ህመም ሊዳርጋቸው ይችላል። አልፎ አልፎም ተስፋ በመቁረጥ አገልግሎታቸውን ሊተው ይችላሉ። በመጨረሻም የአባቶች ስም በክፉ መነሳቱ ምዕመናን በአባቶች ላይ ያላቸው አመኔታ እንዲሸረሸር ያደርጋል። የአባቶችን አገልግሎት በጥርጥር እንዲመለከቱት ሊያደርጋቸው ይችላል። በአጠቃላይ የአባቶችን ስም በሚዲያ በክፉ ማንሳት ጉዳቱ ብዙ ነው።

ማስተዋል የሚፈልጉ ጉዳዮች

በአባቶችና በአገልግሎታቸው ላይ ሥርዓት በጠበቀ መልኩ አስተያየት መስጠት አባቶችን አለማክበር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ አባትነት የራስን ነውር ለመሸፈን የሚከለል ጭምብል አይደለም። ከአባቶች መካከል ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ሳያስከብሩና የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ በራሳቸው አንደበት “አክብሩኝ” የሚሉና በተላላኪዎቻቸውም “አባቶች ይከበሩ” የሚያስብሉ ግለሰቦችንም ልናውቅባቸውና ቤተ ክርስቲያንን ከእነዚህ ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ቅዱስ ቃሉም በግልጽ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ (ሮሜ13፥7) ይላል እንጂ ክብርን ለሚፈልግ ሁሉ ክብርን ስጡ አይልም፡፡ የቤተ ክርስቲያንን እምነት (አስተምህሮ) የሚያፋልሱ ወይ በመሸለም፣ ዝም ብለው የሚመለከቱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የሚያፈርሱ ወይም ሥርዓት ሲፈርስ ዝም ብለው የሚመለከቱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት የሚዘርፉ ወይም የሚያዘርፉ፣ ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን የልጅነት መብት የሚጥሱ ወይም ሲጣስ ዝም የሚሉ፣ በምዕመናን ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት የሚያደርሱ ወይም ጥቃት ሲደርስ የማይከለክሉ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም ለግል/ለቡድን ጥቅም የሚነግዱ ….ወዘተ አባቶች ሲያጋጥሙን “አባቶችን እናክብር” የሚለውን አስተሳሰብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ሂደት ውስጥ የሚጠበቅብንን ድርሻ ሳናበረክት እንዳንቀር በማስተዋል መጓዝ ያስፈልገናል፡፡ ከሁሉም በፊት እምነታችንና ቤተ ክርስቲያናችንን ልናስቀድም ይገባናል፡፡

ለአባቶቻችን ሥጋዊ ሕይዋት መልካም ነገርን ብንመኝም እነርሱን ማክበራችን ግን ብዙ ገንዘብ በመክፈል/በመስጠት፣ በዘመናዊ/ቅንጡ ቤት በማኖር፣ ውድ መኪና በመሸለም፣ በብዙ ገንዘብ የሚገዙና ውበትን የሚያጎናጽፉ የውጭ ሀገር አልባሳትን በመለገስ፣ ብዙ ወጭ አውጥቶ ድግስ ደግሶ በመጋበዝ፣ ውድ መጠጦችን ገዝቶ በማበርከት አይገለጥም። እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ይህንን ለመሰለው የቅንጦት ነገር ሲያውሉ ዝም ማለት ወይም መተባበር አባቶችን ማክበር ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ማራቆት፣ ሌቦችን ማድለብ ነው። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለድካም ዋጋቸው ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍላቸውና ሌሎች ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲሟሉላቸው ማድረግና እኛም ለዚሁ የሚውል አስራት በኩራታችንን በወቅቱ መክፈል አባቶቻችንን የምናስከብርበት አንዱ መንገድ ነው።

የችግሩ መፍትሔ ምንድን ነው?

አባቶቻችንን ብናከብር ክብር የምናገኘው ራሳችን ነን፡፡ ባናከብራቸውም ክብርን የምናጣው ራሳቸን ነን፡፡ አባቶችንም የምናከብረው ለእነርሱ ክብርን ለመጨመር ሳይሆን የክርስትናችን አንዱ መገለጫ ስለሆነ ነው። አባቶችን ስናከብር ቤተ ክርስቲያን ትከበራለች፣ ምዕመናንም ይበዛሉ፡፡ ካላከበርን ደግሞ እንን ሰው ከዓለም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ ይቅርና ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ሰውም ተመልሶ ወደ ዓለም ሊሄድ ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓትና የመከባበር ምሳሌ ስለሆነች በቤተ ክርስቲያን አንዱ ሌላውን ሊያከብር ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሕዝበ ክርስቲያን አባቶችንም ሆነ ሌላው ወገኑን እንዲያከብር ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ አባቶችም እርስ በእርሳቸው በመከባበርና ሌላውንም በማክበር ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምእመናንም ክብርን መስጠት ያለባቸው ክብር ለሚገባቸው አባቶች እንጂ ክብርን ለሚፈልጉ ‘የስም አባቶች’ መሆን የለበትም።

በምግባርና በእምነት የደከመ ሲኖርም በጸሎት፣ በመካከርና በትምህርት በማገዝ እንጂ በትችት፣ በዘለፋና በስድብ ማነጽ እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ ወይም የክህነት ለምድ የለበሱ መናፍቃንና ሲሞናውያን እንቅስቃሴ ሲታይ መፍትሔው መሆን ያለበት አባቶችን በጅምላ መፈረጅ ሳይሆን በጋራ መመካከርና የሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ተገቢውን እርምጃና እርምት እንዲወስድ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይም በዘመናዊነትና በሉላዊነት ተፅዕኖ ምክንያት የመጣውንና የሚመጣውን ምስቅልቅል ገፅታ ለመከላከል ለሁሉም ክርስቲያን በተለይም ለወጣቱ ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊ ትምህርትን በተከታታይና በቀጣይነት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ አልፈው፣ ሕግና ሥርዓትን ተላልፈው፣ በማንአለብኝነት አባቶችን ያለስማቸው ስም፣ ያለግብራቸው ግብር እየሰጡ ስም የሚያጠፉ አጉራ ዘለሎችን ግን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ በማድረግ አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል እንላለን፡፡

ወርኃ ጽጌ፡ ክርስቶሳውያን ስለጽድቅ ይሰደዳሉ፣ ሄሮድሳውያን ጽድቅን ያሳድዳሉ!

Image result for እመቤታችን ስደት eotcmk
የእመቤታችንና የጌታችን ስደት

እንኳን ለወርኃ ጽጌ አደረሳችሁ፡፡ ወርኃ ጽጌ ማለት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ያለው ወቅት ሲሆን በዚህ ጊዜ በቤተክርስቲያን በማቴ. 2፡13-15፣ በዮሐንስ ራዕይ 12፡1-18፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠው የስደት ወራት የሚታሰብበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሰማይና የምድር ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናቱ በድንግል ማርያም እቅፍ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በመከራ፣ በረሃብ ለ3 ዓመት ከ6 ወር መሰደዳቸውን እናስባለን፡፡ ጌታችን አምላክ ሲሆን በፈቃዱ የተሰደደው ከገነት በኃጢአቱ የተሰደደ የአዳምና የእኛን የአዳም ልጆች የኃጢአት ስደት ሊክስልን (ቤዛ ሊሆነን ነው)፡፡ እመቤታችንም የአምላክ እናት ስትሆን የስደትን መከራ በመቀበሏ ስደትና መከራ ለክርስቲያኖች ክብር እንጂ ውርደት አለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ ከእመቤታችን ጀምሮ እግዚአብሔር ለወደዳቸው ቅዱሳን የሰጠው ታላቅ ጸጋ ስለ ጽድቅ፣ ስለ እውነት፣ ስለ ሃይማኖት መሰደድን ነውና፡፡

ለዚያ ነው የተናገረውን የሚፈጽም ቤዛችን፣ አርአያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስደትን ባርኮ ባስተማረበት የአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡” (ማቴ• 5:10) ያለው፡፡ ስለ ጽድቅ መሰደድ ማለት ከሀገር ሀገር መሰደድ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንና በኑሯችን ሁሉ የእውነት ምስክሮች ሆነን መኖር ማለት ነው፡፡ ስለ እውነተኝነታችን፣ ሃይማኖታችንን ስለመጠበቃችን ከከሀድያን፣ ከመናፍቃን እንዲሁም ከሌሎች በሀሰት መነቀፍ፣ መሰደብ፣ መዋረድ ቢመጣብን ደስ ሊለን እንጂ ልንከፋ አይገባም፡፡ የክብር ባለቤት፣ ስደትን የባረከ ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ እኔም እየዋሹ ክፉውን ሁሉ በሚናገሩባችሁ ጊዜ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትንም አድርጉ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ብዙ ነውና፤ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ ነቢያትንም እንዲሁ አሳደዋቸው ነበርና” (ማቴ. 5፡11-12) በማለት የሰጠንን ቃልኪዳን በማሰብ ልንጸና ይገባል፡፡

በኃጢአታችን ምክንያት የሚደርስብንን ነቀፋና ስድብ ግን በንስሃ ማስወገድ አለብን እንጂ የኃጢአትን ዋጋ ለጽድቅ የተከፈለ መስዋእትነት አስመስለን ራሳችንን በሀሰት ለማጽደቅ ልንሞክር አይገባም፡፡ “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው ሁሉ የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” እንደተባለ (ገላትያ 6:7)፡፡ ስለሆነም የእመቤታችንን ስደቷን፣ መከራዋን በምናስብበት በዚህ ወራት እኛም ስለጽድቅ በመነቀፍ የጽድቅን ዋጋ እንድንቀበል በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጣብንን ፈተናም በግብዝነት ራሳችንን ጻድቅ ለማስመሰል ከመጠቀም ተቆጥበን በንስሐ ታድሰን የመንግስተ እግዚአብሔር ወራሾች እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡

ስለ ጽድቅ የተሰደዱ የክርስቶስ ምስክሮች

“ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና”(ማቴ. 5፡10) የሕይወታቸው መመመሪያ በማድረግ አማናዊ ጽድቅ ስለሆነ ስለክርስቶስ ፍቅር ምድራዊ መከራን በቅንነት በመቀበል ሰማያዊ ዋጋ ካገኙ አዕላፋት ቅዱሳን መካከል በዘመነ ጽጌ መካከል ጥቅምት 14 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸውን የምናከብርላቸውን ሁለት ዐበይት ቅዱሳን ታሪክ ስለ ጽድቅ የተሰደዱ/የሚሰደዱ ክርስቶሳውያን ማሳያ አድርገን እንመልከት። እነርሱም አቡነ አረጋዊ እና ጻድቁ ገብረክርስቶስ ናቸው።

አባታችን አቡነ አረጋዊ በሀገራችን ኢትዮጵያ የወንጌልን ብርሃን ካበሩት ዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው ሮም ሲሆን ከኬልቄዶን ጉባኤ (451 ዓ.ም.) በኋላ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከቀደሙ አባቶች ርትዕት ሃይማኖት በተለየ መልኩ የንስጥሮስን ክልኤ ባህርይ (ሁለት ባሕርይ) አስተምህሮ በመከተል የተዋሕዶን አስተምህሮ በሚከተሉ አባቶች ላይ በነገስታት ተደግፋ መከራ ስታጸና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ስለጽድቅ ሀገር አቋርጠው ተሰደዱ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ገዳማትን በማስፋፋት፣ ሥርዓተ ምንኩስናን በማጽናት የጠበቋትን ርትዕት ሃይማኖት አስፋፍተዋል፡፡ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ስላስገዙ ጌታ እግዚአብሔር ስጋውያን ፍጥረታት እንዲገዙላቸው በሰጣቸው ጸጋ ክፉ ዘንዶ እንኳ ታዞላቸው የደብረ ዳሞን ተራራ ለመውጣት ተጠቅመውበታል፡፡ በጸሎታቸው፣ በመንፈሳዊ ተጋድሏቸው እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኙት ስለ ክርስቶስ ስም መከራን ሳይሰቀቁ ተቀብለዋልና ሞተ ሥጋ ሳያገኛቸው ከአምስቱ ዓለማተ መሬት አንዷ ወደሆነችው ወደ ብሔረ ህያዋን እንደ ኄኖክና እንደ ኤልያስ ተነጥቀዋል፡፡ ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክርስቶስ ተሰድደዋልና የመንግስተ ሰማያት አረቦን (መያዣ) ወደሆነች ብሔረ ህያዋን ለመግባት ክብር በቁ፡፡ እኛም የስደት ነገር ጎልቶ በሚታሰብበት በወርኃ ጽጌ፣ በየዓመቱ ጥቅምት 14 ወደ ብሔረ ህያዋን መነጠቃቸውን እያሰብን እንዘክራቸዋለን፡፡

ጻድቁ ገብረክርስቶስ የቁስጠንጥንያ ንጉስ የነበረው ቴዎዶስዮስ ልጅ ነው፡፡ ሚስት አግብቶ የአባቱን ንግስና ወርሶ እንዲኖር በሰርግ ዳሩት፡፡ እርሱ ግን ምድራዊ ደስታን የናቀ ነበር፣ ስለ ክርስቶስ በፈቃዱ መነቀፍንም ይፈልግ ነበር፡፡ ከጫጉላ ቤትም የተዳረችለትን ሚስቱን በግብር ሳይደርስባት ህገ እግዚአብሔርን እየጠበቀች እንድትኖር አደራ ብሏት ወደ ምናኔ ወጣ፡፡ በአንዲት ቤተክርስቲያንም 15 ዓመት በመንፈሳዊ ተግባር ተጠምዶ ኖረ፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ራሱን ዝቅ አድርጎ እንደ ኃጢአተኛ ከቤተክርስቲያኑ ውጭ ይኖር ነበር፡፡ ከ15 ዓመት በኋላ እመቤታችን ቤተክርስቲያኑን ለሚያስተዳድረው ቄስ ተገልጣ የገብረክርስቶስን ማንነት አሳወቀችው፤ አክብሮ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲያስገባውም ነገረችው፡፡ ይህን በራዕይ የተረዳው ጻድቅ ገብረክርስቶስ ግን ክብሩ በመገለጡ አዘነ፡፡ እመቤታችንን በጸሎት ለምኖ ክብሩ ወደማይታወቅበት ቦታ በመርከብ ተሰደደ፡፡

የጌታ ፈቃድ ሆኖ ወደ አባቱ ሀገር ደረሰ፡፡ በአባቱ ቤት ደጃፍ ከድሆች ጋር ለ15 ዓመት ውሾች እያሰቃዩት ኖረ፡፡ በአባቱ አገልጋዮች ያለበደሉ መከራ ሲጸናበት ምንም ምን የበቀል ልብ አልነበረውም፡፡ ጥቅምት 14 በሞተ ስጋ ሲለይ እናትና አባቱ በበራቸው የነበረው ደሃ ልጃቸው መሆኑን እግዚአብሔር በተዓምራት ገለጸላቸው፡፡ ጻድቅ ገብረ ክርስቶስም ገድሉን ጽፎ በክርታስ ይዞ ተገኘ፡፡ ስለ ጽድቅ የተሰደደው ጻድቅ ገብረክርስቶስ ነፍሱ በገነት አረፈች፤ ከጌታ በተቀበለው ቃልኪዳንም በምግባር የደከምን ኃጢአተኛ ልጆቹን መታሰቢያውን እያደረግን የመንግስተ ሰማያት ወራሾች እንድንሆን ይረዳናል፡፡ እኛም ክርስቶሳውያን መሆናችን እንዲገለጥ እንደነዚህ ቅዱሳን በአቅማችን ስለጽድቅ ተሰድደን (ተነቅፈን) የመንግስተ እግዚአብሔር ባለቤት እንሆን ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንጸናና ልንተጋ ይገባል፡፡

ጽድቅን የሚያሳድዱ አመጸኞች 

ስለ ጽድቅ መሰደድ የክርስቶስ ወገን፣ የእመቤታችን ወዳጅ የሚያደርግ ሲሆን ጽድቅን ማሳደድ ደግሞ በአንፃሩ የሄሮድስ ክፋት ተካፋይ ያደርጋል። ጽድቅን ማሳደድ ማለት ከሀሰት ወግኖ እውነትን መግፋት፣ በጽድቅ አገልጋዮች ላይ መከራን ማጽናት፣ ራስንም ከጽድቅ ሥራ ከልክሎ የኃጢአት አገልጋይ መሆን ማለት ነው። ለዚህም በወርኃ ጽጌ ታሪካቸው የሚተረክላቸውን ሦስት አካላት መነሻ እናደርጋለን፡፡ እነርሱም ሄሮድስ፣ የሄሮድስ ወታደሮችና ኮቲባና ቤተሰቦቿ ናቸው።

በመጀመሪያ ከክፉ ታሪኩ የምንማርበት የጽድቅ አሳዳጅ የጽድቅ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን ከተወደደች እናቱ ጋር በግፍ ያሳደደ ሄሮድስ ነው። በማቴ. 2፡3-13 በተጻፈው መሰረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ሰብአ ሰገልም “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?” ብለው ሲፈልጉት ስላየ ርጉም ሄሮድስ ደነገጠ፡፡ ሄሮድስ ርጉም ነውና የሚያስጨንቀው ጽድቅና እውነት ሳይሆን ምድራዊ ክብሩና አለቅነቱ ነው፡፡ ሌላ ንጉስ መጥቶ የሚገለብጠው ስለመሰለው “ሳያድግ ልግደለው” ብሎ ጌታችንን አሳደደው፡፡ እርሱን ያገኘ መስሎትም እልፍ ሕፃናትን አስገደለ፡፡ ሄሮድስ ጽድቅን ለክብሩ ብሎ በማሳደዱ አልተጠቀመም፡፡ ይልቁንም አሟሟቱ እንኳ ከፍቶ ሰውነቱ ተልቶ ሞተ፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቀዋል፡፡ እውነትን በሀሰት አሳድዷልና ነፍሱ ትቅበዘበዛለች፡፡ ሄሮድስ ለምድራዊ ክብር ሲሉ እውነተኞችን የሚያሳድዱ ምድራውያን ባለስልጣናትን ይመስላል፡፡ ከዚያም ባሻገር ለሰማያዊ ክብር በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ለአገልግሎት ተሹመው ልብስና ሥም ብቻ ለሚከልለው መንፈሳዊነት ለጎደለው ክብራቸው ሲሉ የጽድቅ፣ የክርስቶስ መልእክተኞች የሆኑ ቅዱሳንንና እውነተኞች ምዕመናንን ያለእውነት በሀሰት ከቤተክርስቲያን የሚያርቁ የዘመናችን የጽድቅ ጠላቶችም ተረፈ ሄሮድሳውያን ናቸው፤ ፍጻሜአቸውም ከሄሮድስ የከፋ ይሆናል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ መማሪያ የሚሆኑን የሄሮድስ ወታደሮች ናቸው፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች እውነትን ከሀሰት መለየት የማይችሉ ለህሊናቸው ሳይሆን ለቀጠራቸው ለሄሮድስ የሚታዘዙ የእውነት ጠላቶች ናቸው፡፡ እመቤታችን ከጌታ ጋር በተሰደደች ጊዜ በርሃ ለበርሃ እየተከታተሉ መከራ ያጸኑባቸው ነበር፡፡ ይህን የሚያደርጉት እውነት ገብቷቸው ሳይሆን እንደ አምላክ የሚገዙለትን የሄሮድስን የረከሰ ሀሳብ በመሙላት ሹመትና ሽልማት ማግኘት የሚፈልጉ ህሊናቸውን ለጥቅም፣ ወይም ለጊዜያዊ የማስመሰል ክብር ያስገዙ ናቸው፡፡ የአምላክን እናት በበርሃ እያሳደዱ በውኃ ጥም እንድትቀጣ ሲያደርጉ እነርሱም ይጠሙ ነበር፡፡ በተዓምረ ማርያም እንደተመዘገበው ጌታችን በተዓምራት በበርሃው መካከል ለእናቱ፣ ለዮሴፍና ለሰሎሜ ንጹህ ምንጭን አፈለቀላቸው፡፡ ይህች ምንጭ ለተሳዳጆች መልካም መጠጥ ሆነችላቸው፡፡ አሳዳጆቹ ሊጠጧት ሲጠጉ ግን መራራ ትሆንባቸው ነበር፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለምድራውያን ባለስልጣናት እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለግላዊ ጥቅምና ዝና ለሚያውሉ ምንደኞች ሲሉ እውነተኞችን የሚያሳድዱ የሀሰት መልእክተኞች የሄሮድስን ወታደሮች ይመስላሉ፤ ፍጻሜአቸውም ከሄሮድስ ወታደሮች የከፋ ይሆናል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ እመቤታችን ጌታን ይዛ በመከራ ውስጥ ምግብና መጠጥ ስትለምናቸው በማያውቁት በመፍረድ እመቤታችንን “አንቺ መልክሽ ያማረ ነው ፀባይሽ ክፉ ቢሆን ነው እንጂ የተሰደድሽው በነገስታት ቤት ትኖሪ ነበር” ብለው ያሳዘኗት ክብር ይግባውና ፈጣሬ ዓለማት ክርስቶስንም ካዘለችበት አውርደው በጥፊ የመቱት ኮቲባና ቤተሰቦቿም የሚያስተምር ታሪክ አላቸው፡፡ ባላወቁት ፈርደው የተቸገሩትን ገፍተዋልና፣ የግፍ ግፍም ፈጽመዋልና ጌታችን በተዓምራት ወደ ዝንጀሮ እንዲቀየሩ አደረጋቸው፣ የቤታቸው ውሾችም አባረሩዋቸው፡፡ በሲዖል፣ ኋላም በገሀነመ እሳትም ከዚህ የባሰ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ ኮቲባና ቤተሰቦቿ በምድራዊ መከራ ያለበደላቸው የሚሰቃዩ ነዳያንን የሚንቁ የሚገፉ እንዲሁም የጽድቅ አገልጋዮችን ያለስማቸው ስም የሚሰጡ በማያውቁት እየገቡ በችግራቸው ላይ ተጨማሪ ፍዳን የሚያጸኑባቸውን ርህራሄ የሌላቸው ሰዎችን ይመስላሉ፤ ፍጻሜአቸውም ከኮቲባና ቤተሰቦቿ የከፋ ይሆናል፡፡

ክቡራን ክርስቶሳውያን ጌታችንን የሚያስመስለን፣ ከእመቤታችን የስደት በረከት የሚያጋራን፣ የመንግስተ ሰማያት ወራሾች የሚያደርገን ስለ ጽድቅ መሰደድም ሆነ የረከሰ ሄሮድስን የሚያስመስለን፣ ከቅዱሳን በረከት የሚለየን፣ የገሀነም ልጆች የሚያደርገን ጽድቅን ማሳደድ የየዕለት ሕይወታችን አካል መሆናቸውን ማስተዋል ይገባናል። ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረን “የእግዚአብሔር መንግስትስ እነኋት፣ በመካከላችሁ ናት።” (ሉቃ• 17:21) ስደት ስለ ጽድቅ መሰደድ በአጠገባችን ያለ እንደሆነው ሁሉ ጽድቅን ማሳደድም በመካከላችን ነው፡፡ ጽድቅን ከሚያሳድዱት ክፉዎች ጋር ሆነን በሲዖል በገሀነመ እሳት እንዳንጣል፣ ስለጽድቅ ከሚሰደዱት ጋር ሆነን የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች እንሆን ዘንድ ማስተዋልንና ጽናትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡

ስደት ወደ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ ነው!

በምድራዊ ኑሮአችን ስለ ጽድቅ እንደ አቅማችን መከራ ብንቀበል ምድራዊ ስደትና መከራ የሚያልቅ፣ የተቆረጠ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። የወርኃ ጽጌን ታሪክ አመስጥረው ከጻፉልን ቀደምት አባቶቻችን አንዱ የሰው ልጆችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ እናትነት የተቀበለው (ዮሐ. 19፡26፣ ራእይ 12:1~ፍፃሜ) ፍቁረ እግዚእ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ አንዱ ነው፡፡  ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ሃይማኖት ምስክርነቱ፣ እውነትን ከመናገሩ የተነሳ ምድራውያን ባለስልጣናት ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት (በስደት) እንዲወሰድና እንዲታሰር አደርገውት ነበር፡፡ ጻድቅና ቅዱስ ዮሐንስ ግን ስደት ወደማታልፍ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ እንደሆነ ያውቅ ነበርና በግዞቱ አልተከፋም ነበር፡፡ ይልቁንስ በግዞት በመታሰሩና እንደ ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት ተዘዋውሮ ወንጌልን ባለማስተማሩ ያዝን ይተክዝ ነበር፡፡ የለመኑትን የማይነሳ ጌታም በራዕይ ሰማያዊ ምሥጢርን ገልጾለት ዮሐንስ ራዕይ የምንለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጽፏል፡፡ በሥጋ የተሰደደው ስደት ሞት ሳያገኘው ወደ ብሔረ ሕያዋን ከመሄድ አልከለከለውም፡፡ ይልቁንም ወደ መንግስተ ሰማያት መሸጋገሪያ ሆነው እንጂ፡፡

ይህ የከበረ ሐዋርያ ዮሐንስ የእመቤታችንን (እንዲሁም የቤተክርስቲያንን) የስደቷን ርዝመት ነገር በተናገረበት አንቀጽ እነዲህ አለ “ሴቲቱም በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች፡፡” (ዮሐ. 12፡6) ይህ 1260 ቀን፣ ወይም 42 ወራት፣ ወይም ሦስት ዓመት ከስድስት ወር የእመቤታችን የስደት ወቅት ርዝማኔ ነው፡፡ መተርጉማነ ሐዲስ አባቶቻችን እንዳስተማሩን እነዚህ የስደት ቀናት በቁጥር ተለይተው መታወቃቸው ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፣ መከራ የሚቀበሉ ቅዱሳን የሚቀበሉት ምድራዊ መከራ የሚያልፍ፣ የሚቆጠር መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንጻሩ ስለ ስሙ በመሰደዳቸው፣ መከራ በመቀበላቸው ጌታችን የሚሰጣቸው ሰማያዊ መንግስት ግን የማታልፍ፣ ዘመን የማይቆጠርባት፣ ዘላለማዊት ናት፡፡ የስደቱ ዘመን (42 ወራት) በሌሎች ቅዱሳን ሕይወትም የተፈጸመ ነው፡፡

በኦሪት ዘጸአት የተመዘገበው የእስራኤል ዘሥጋ ስደት 42 ዓመታትን ወስዷል፡፡ ከእስራኤል መካከል እግዚአብሔርን ያስደሰቱት ስደቱ፣ መከራው አልፎላቸው ከነዓን ገብተዋል፡፡ አሳዳጃቸው ፈርኦንና ሰራዊቱ ግን በመቅሰፍት ጠፍተዋል፡፡ በመጽሐፈ ነገስት የተመዘገበው ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ስለ ደሃው በመሟገቱ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገሩ ኤልዛቤልና አክአብ ያሳደዱት ስደት 42 ወራትን ወስዷል፡፡ ኤልያስ ስደቱ አልፎለት፣ ወደ ብሔረ ሕያዋን መሸጋገሪያ ሆኖት በክብር አረገ፡፡ አሳዳጆቹ ኤልዛቤልና አክአብ ግን ሞተዋል፣ መታሰቢያቸውም ተረስቷል፡፡ በቀጣይ ቀናት በቤተክርስቲያናችን እንደሚመሰከረው እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር የተሰደደችው ስደትም ተፈጽሟል፤ ከሄሮድስ ሞት በኋላ ወደ ናዝሬት፣ ወደ ገሊላ ተመልሰዋል፡፡ አሳዳጃቸው ሄሮድስ ግን ክፉ ሞትን ሞቷል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እኛም እያንዳንዳችን የእውነት፣ የእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ምስክሮች ልንሆን ይገባል፡፡ የጽድቅ ምስክሮች ከመሆናችን ተነሳ መከራን ስደትን ለመቀበል እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን የበቃን የምንሆንበት ጊዜ ከመጣ በደስታ ልንቀበለው ይገባል፡፡ ስደት፣ መከራ ወደ መንግስተ ሰማያት የምንሸጋገርበት ድልድይ እንጂ ተስፋ እንደሌላቸው የምንቅበዘበዝበት ቅጣት አይደለምና፡፡

የእመቤታችን ስደት ማብቃትና ወደ ገሊላ መመለስ

በየዓመቱ ኅዳር 6 በወርኃ ጽጌ ፍጻሜ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር፣ እንዲሁም ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በሄሮድስ ምክንያት የደረሰባቸው ስደትና መከራ አልፎ ደብረ ቁስቋም በተባለች ቦታ ያረፉበት ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንደፃፈልን “ሄሮድስም በሞተ ጊዜ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ በግብፅ ሀገር ለዮሴፍ በሕልም ታየው፡፡ እንዲህ ሲል ‘የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ’፡፡” (ማቴ. 2፡20) ባለው መሰረት አረጋዊ ዮሴፍ ሰሎሜ እያገዘችው የሚያገለግላትን ቅድስት ድንግል እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር ይዞ ከስደት መመለሳቸውን እናስባለን፡፡

የእመቤታችን (እንዲሁም የቤተክርስቲያን ስደት) ቀኑ በእግዚአብሔር ዘንድ በቁርጥ የታወቀ ነበር፡፡ ይሁንና አንዱ ስደት ሲቆም ሌላው መከተሉ በቅዱሳን ሕይወት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ስደታቸውም የክብር መሰላል ሆኗቸው ከክብር ወደክብር የሚሸጋገሩበት ነው፡፡ ቅዱሳን በሕይወታቸው አንዱን መከራ (ስደት) በድል ሲወጡ የሚያገኙት የማያልቅ ጸጋ አለ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በቅዱሳን ሰዎች ተጋድሎ ሰይጣን ሲሸነፍ በሰማያት ታላቅ ደስታ ያደርጋሉ፡፡ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም በስደቷ እግዚአብሔርን አላማረረችም፡፡ ስለሆነም ሰይጣንን በትዕግስቷ በጸሎቷ አሸነፈችው፡፡ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስም የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ የሆነች እረፍትን በደብረ ቁስቋም አሳረፋት፡፡ ደብረ ቁስቋም ግን ምሣሌ እንጂ አማናዊ (ሰማያዊ) የእረፍት ቦታ አይደለችም፡፡ ስለሆነም ከደብረ ቁስቋም እረፍት በኋላ እመቤታችን ከአምስቱ ታላላቅ ሀዘኖቿ አራቱን አስተናግዳለች፡፡

ከእመቤታችን ሕይወት የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር በክርስትና ሕይወታችን፣ እውነተኞች በመሆናችን ከሚመጣብን መከራ አንዱ ሲያልፍ ራሳችንን ለሌላ መከራ ማዘጋጀት እንጂ አንዲት ፈተና ስላለፍን በትዕቢት ተይዘን ራሳችንን በግብዝነት ማጽደቅ እንደማይገባ ነው፡፡ ያን አድርገን እስከ መጨረሻው ከጸናን ቅዱሳን ሐዋርያት “በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንገባ ዘንድ ይገባናል” (ሐዋ. 14፡22) በማለት የመከሩንን አስበን የድኅነትን ነገር መቀለጃ ከሚያደርጉ አላዋቂ መናፍቃን የማታለል ትምህርት ርቀን ተስፋ የምናደርጋትን አማናዊት ደብረ ቁስቋም (መካነ እረፍት) ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን ሊያወርሰን የታመነ አምላክ አለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ከልጇ ጋር ደረሰባትን የ3 ዓመት ከ6 ወር ስደትና መከራ በትዕግስት በፈጸመች ጊዜ የልዑል እግዚአብሔር ኃይሉ ጥበቃው አልተለያትም ነበር፡፡ በጉዞዋ ሁሉ ይረዷት የነበሩት ቅዱሳን መላእክትም ከበዋት ያመሰግኑ ነበር፡፡ ለዚያ ነው ቤተክርስቲያናችን “መንክረ ግርማ ኃይለልዑል ጸለላ፤ አማን መላእክት ይኬልልዋ (2)” (በሚያስደንቅ ግርማ የልዑል ኃይል ጋረዳት፣ በእውነት መላእክት አመሰገኗት (2) )እያለች በከበረ ዜማ የምታመሰግነው፡፡ ይህ በእመቤታችን ሕይወት የተገለጠ የልዑል እግዚአብሔር ጥበቃ፣ የቅዱሳን መላእክት ረዳትነት በክርስቶስ አምነው ስለ ሥሙ፣ ስለሰጠን ደገኛ ሃይማኖት ብለው መከራ መቀበልን፣ መነቀፍን በደስታ ለሚቀበሉ ሁሉ የተሰጠ ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ጽድቅን ከሚያሳድዱ ሄሮድሳውያን ተለይተን ስለ ጽድቅ ከተሰደዱ/ከሚሰደዱ ክርስቶሳውያን ጋር ተባብረን፣ በጸሎታቸው በቃልኪዳናቸው ተደግፈን በሕይወታችን እንድናስደስተው ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደቷ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡