እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ታቦር ትመሰላለች፡፡

Debretabor

በአዲስ ኪዳን ከተገለጹት የቤተክርስቲያን ምሳሌዎች መካከል አንዱ ደብረ ታቦር (የታቦር ተራራ) ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን ገልፆበታል፡፡ ይህንን ድንቅ ምስጢር ወንጌላዊ ማቴዎስ ‹‹ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፥ ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፥ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም(ማቴ 17፡1-8)።›› በማለት አስፍሮታል፡፡

በአባቶች አመስጥሮ የታቦር ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ምሳሌው ቤተክርስቲያን በስድስተኛው ሺህ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደምትመሠረት የሚያሳይ ነው (ትርጓሜው በስድስተኛው ወር መልአኩ (ሉቃ 1፡26)….እንደሚለው ነው)፡፡ በደብረ ታቦር ሦስቱን ደቀመዛሙርት ብቻ ይዞ መውጣቱ ምሥጢረ ክህነት ለሁሉም ሳይሆን ለካህናት ብቻ የሚፈፀም ምሥጢር መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ብርሀነ መለኮቱንም የገለፀላቸው ለእነዚህ ብቻ ነበር፡፡

በደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን ገለጸ፡፡ በቤተክርስቲያንም እንደዚሁ የክርስቶስ ማደሪያው ናት፡፡ በደብረ ታቦር ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን ሙሴ ከብሔረ ሙታን ሐዋርያቱ ደግሞ በአካለ ሥጋ ያሉት በአንድነት ከአምላካቸው ጋር ተገኝተዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንና በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ከአምላካቸው ጋር ያላቸው አንድነት ናትና የደብረ ታቦር ምሳሌ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም በቅዳሴ የሚሳተፉት ልዑካን አምስት ናቸው፡፡ ኤልያስና የሙሴ የሁለቱ ቀሳውስት፣ ሦስቱ ደቀመዛሙርት የሦስቱ ዲያቆናት ምሳሌ፣ ጌታችንም የመስዋዕቱ ምሳሌ ናቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶች ይህንን ምሳሌ ከነምስጢሩ እንደዚህ አብራርተው አስተምረዋል፡፡

በዚያ በደብረ ታቦር ተራራ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን:- ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።›› እንዳለው በቤተክርስቲያንም ከቅዱሳንና ከቅዱሳን አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ምንኛ መልካም ነው? የክርስትናም ዓለማው ሰው ይህንን ሰላም አግኝቶ ከአምላኩ ጋር እየተነጋገረ በቤተክርስቲያን ይኖር ዘነድ ነው፡፡

ዕረፍትሽን እያሰብን ሰላም እንልሻለን!

ዕረፍታ ለማርያም

ጥር 21 ቀን እመቤታቸን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የእመቤታችንን ዕረፍት በማሰብ ታከብራለች፡፡ አብ የመረጣት፣ ወልድ የተወለደባት፣ መንፈስ ቅዱስ ያከበራት  ማኅደረ መለኮት (የመለኮት ማደሪያ) የከበረች እመቤት ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ያቺ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› ያላት፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላ ያመሰገነቻት፣ ክቡር ዳዊት ‹‹ልጄ›› ብሎ የዘመረላት፣ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹እህቴ›› ብሎ የተቀኘላት፣ ለወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹እናትህ እነኋት›› የተባለችው የተወደደች እመቤታችን ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙር፣ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ፣ ደገኛው ቅዱስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ፣ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታት፣ ቅዱሳን መላእክትን በምስጋና የመሰላቸው ቅዱስ ያሬድ በማኅሌት ያመሰገኗት ከንግግርና ከቋንቋዎች ሁሉ በላይ የሆነ ምስጢር የተፈፀመባት እመቤት ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ዕረፍቷም በመልክአ ማርያም ‹‹ሰላም ለፀአተ ነፍስኪ እንበለ ፃዕር ወፃማ፡ ያለመጨነቅና ያለፃእር ከሥጋዋ ለተለየች ነፍስሽ ሰላምታ ይገባል›› እንደተባለው ያለመጨነቅና ያለፃእር ነበር፡፡ ያለ አንዳች መጨነቅ ጌታን የወለደቸው እመቤት ያለ አንዳች መጨነቅ ቅድስት ነፍስዋን ከክብርት ሥጋዋ ተለይቶ በቃለ አቅርነት በዝማሬ መላእክት ጌታችን አሳርጓታል፡፡  እርሷ፡-ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ጋር፣ አስራ አምስት ዓመት በዮሐንስ ቤት፣ በአጠቃላይ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ላይ ኖራ ዐርፋለች፡፡ለዚህም በህይወተ ሥጋ በኖረችበት ዘመን ልክ ቅዱስ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያምን በ64 አንቀጽ ከፍሎ 64 ጊዜ ሰአሊ ለነ ቅድስት ብለን እንድናመሰግናት አድርጓል፡፡

በጥር 21 ቀን እመቤታችን ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ፣ ቅዱሳን መላእክትና ደጋግ ቅዱሳን አባቶች በተገኙበት እጅግ ታላቅ በሆነ ክብር ባረፈችበት ዕለት ሐዋርያት በጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲሉ በክርስቶስ ትንሳኤ ያፈሩት አይሁድ የክርስቶስ የሆኑትን ማሳደድ ልማዳቸው ነበርና “እርሷንም እንደ ልጇ ተነሳች አረገች እንዳይሉ፣ ሥጋዋን እናቃጥል” ብለው በክፋት ተነሱባቸው፡፡ ከአይሁድም ወገን የሆነ ታውፋንያ የሚባል ሰው የከበረ ሥጋዋን ለማቃጠል ሲታገል፣ በተዓምራት ተቀጣ፤  ሥጋዋ ከጌቴሴማኒ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ስር እስከ ነሐሴ 14 ቀን ቆይቷል፡፡ ኋላም በልጇ ኃይልና ስልጣን ከሞት እንድትነሳና እንድታርግ አድርጓታል፡፡ ይህም በጥልቀት በጥር 21 እና ነሐሴ 16 ስንክሳር ላይ በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍት ባሰብን ጊዜ በአላዋቂ ልቡና ሊፈጠር የሚችል አንድ ጥያቄ አለ፡፡  እርሱም፡- ከቤተክርስቲያን ወገን ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን (ሄኖክ፣ ኤልያስ…) አሉ፡፡ እርሷ የኃያሉ እግዚአብሔር መቅደሱ፣ እናቱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ሆና እያለች ስለምን ሞትን ቀመሰች? ለምንስ እንደነዚህ ቅዱሳን አላሳረጋትም? የሚል ጥያቄ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ አይመረመርም፣ ፍጡርም የሥራውን አመክንዮ ያለ መንፈስ ቅዱስ አጋዥነት መርምሮ ማወቅ አይቻለውም፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢራት ስንመረምር በጥልቅ መረዳትና መንፈሳዊነት መሆን አለበት፡፡ ማረግ ብቸኛ የፅድቅ ሚዛን አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሴት እንደ ሄኖክ ፃድቅ ነበር፣ መጥምቁ ዮሐንስም እንደ ኤልያስ ባህታዊ፣ ገባሬ ተዓምር ነበር። ሄኖክና ኤልያስ ሲያርጉ ሴትና መጥምቁ ዮሐንስ ግን አርፈዋል። ከዚህ ምድር በሞተ ሥጋ ተለይቶ የነበረው ሊቀ ነቢያት ሙሴም በብሔረ ሕያዋን ከነበረው ከኤልያስ ጋር በደብረ ታቦር በአንድነት ተገልጠዋል፡፡ ማቴ 17፡1-5

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ፍጥረታዊ ሰው ለሚያነሳቸው ክርክሮች የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በአፍም በመጽሐፍም ሲመልሱ ኖረዋል፣ ወደፊትም እንዲሁ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ሞተ ሥጋን ማየቷን ሊቃውንት አባቶቻችን በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ያስተምራሉ፡-

ጌታች የለበሰው የአዳምን ሥጋ መሆኑን ለማስረገጥ፡ በመንፈስ ቅዱስ  የቅዱሳት መጻሕፍትንና የታሪክ ድርሳናትን ስንመረምር “ምድራዊት ሴት ብትሆን ኖሮ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ አምላክ እንዴት ማደሪያው ልትሆን ትችላለች?” የሚሉ ወገኖች ነበሩና የሰው ልጅ መሆኗን፣ ክርስቶስም የለበሰው የአዳምን ሥጋ መሆኑን ለማስረገጥ ነው፡፡ የሥጋን ሞት በመሞቷ የአዳም ዘር መሆኗ (ከሰማይ የመጣች አለመሆኑ) ታወቀ፡፡

ጌታችን በፍርዱ አድልዎ እንደሌለበት እንዲታወቅ፡ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ግድ ነውና ህይወት የተባለ የክርስቶስ እናት እመቤታችንም እንደ ከበሩ የጌታ ባለሟሎች በሞተ ስጋ ተወስዳለች፡፡ ዛሬም በሥጋ ያለነው ወደፊትም የሚኖሩት ሞትን ይቀምሳሉ፡፡በብሔረ ሕያዋንም ያሉት እንዲሁ፡፡ሞት ለማንም የማይቀር ፍርድ ነውና፡፡ ይህም በመጽሐፈ ዚቅ  ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ፤  ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡›› ተብሎ ተገልጿል፡፡

በምድር የነበራት የኃዘንና የስደት ዘመን እንዲያበቃ፡ እመቤታችን ህይወቷ ከህፃንነቷ ጀምሮ በብዙ ፈተና የተሞላ ነበር፡፡ በተለይም ስምኦን አረጋዊ በቤተመቅደስ ‹‹በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል›› ብሎ እንደተነበየላት (ሉቃ 2፡35) በግብፅ ስደት፣ በቀራኒዮ ስቅለት፣ በአይሁድ ክፋት የደረሰባት መከራና ኃዘን አብቅቶ ወደ ዘላለም ደስታ ትገባ ዘንድ ሞትን ቀምሳለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.2፥10-14/ ›› እንዳለ ኃዘኗ ያልፍ ዘንድ ወደ ዘላለም ደስታም ትገባ ዘንድ ዐርፋለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

አሁን እርሷ፡- በልጇ ቀኝ በክብር ቆማ በከበረ ምስጋና ታመሰግነዋለች፣ የከበረ ስሙን ከፍ ከሚያደርጉት ቅዱሳን ጋርም በመንፈሳዊ አንድነት ታከብረዋለች፣ ከገቡ ከማይወጡበት ሰማያዊ ሀገር ትኖራለች፡፡ ስደት፣ መከራ፣ ኃዘን ከሌለባት ሀገር አለች፡፡ በዕለተ ምጽዓት ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው አክሊል ከሚቀዳጁበት ስፍራ አለች፡፡ ‹‹በአምላካችን ከተማ እግዚአብሔር ለዘላለም ያፀናታል›› እንደተባለ (መዝ 47፡8) በዚያ ከፍጡራን ሁሉ በላይ በሆነ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

እኛም የዕረፍቷን ዕለት በምስጋና በዝማሬ እናከብረዋለን፡፡ ቅዱሳን ያረፉበትን ቀን በደስታ ከበሮ እየመታን እየዘመርን እናከብራለን፡፡ ዕረፍቷን የምናከብረው ለእርሷ ክብርን ለመጨመር አይደለም፤ ራሳችን እንከብርበት ዘንድ ነው እንጂ፤ በረከትን ረድኤትን እናገኝበት ዘነድ ነው እንጂ፡፡ እርሷን ስናከብር – ልደቷን ዕረፍቷን ዕርገቷን ስናከብር – ያከበራትን ልጇንም እናከብራለን፤ በረከቷንም እናገኛለን፡፡

በምድር ላይ በአካለ ሥጋ ያሉ ሰዎችን ልደት በባህላዊ መንገድ ስናከብር፡ በመወለዳቸው ደስ ይላቸው ዘንድ አብረን በመደሰት ነው፡፡ በሕይወተ ሥጋ የተለዩንን ዘመዶቻችንን ስናስብ ደግሞ ‹‹ነፍስ ይማር›› እያልን በመጸለይ ነው፡፡ የቅዱሳንንና የእመቤታችንን ልደትንና ዕረፍትን ስናስብ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡  እነርሱን እያመሰገንን፣ ተጋድሏቸውን እያሰብን፣ ያከበራቸውን አምላክ እያከበርን፣ ክብራቸውንም እያደነቅን፣ በረከታቸው ረድኤታቸው አማላጅነታቸው ይደርሰን ዘንድ እየተማጸንን ነው እንጂ፡፡ የእመቤታችንንም ዕረፍት ስናከብር ይህንን እያስተዋልን ሊሆን ይገባል፡፡ ልመናዋ ፍቅሯ አማላጅነቷ የልጅዋም ቸርነት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡ አሜን፡፡

በፍርድ ቀን የነነዌ ሰዎች እንዳይፈርዱብን ምን እናድርግ?

የነነዌ ከተማ አስቀድሞ በአሦር አማካይነት ከጤግሮስ ወንዝ በስተምሥራቅ (በአሁኗ ኢራቅ ሞሱል ከተማ አቅራቢያ) ተመሠረተች (ዘፍ 10፡11-12)፡፡ ›› ከብዙ ዘመናት በኋላ የንጉሥ ሰናክሬም መቀመጫ ሆነች (2ኛ ነገ 19፡36)፡፡ በዚያን ዘመን ነነዌ በአካባቢው ካሉት ታላላቅ ከተሞች አንዷ ነበረች፡፡ በዚህች ከተማ ታሪክ መሠረት ከ786-746 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ ውስጥ ነቢዩ ዮናስ የነበረበት ዘመን ነበር (2ኛ ነገ 14፡25)፡፡ በነቢዩ ዮናስም እንደተነገረው በዚያን ዘመን ነነዌ የሦስት ቀን መንገድ ያህል እጅግ የምትሰፋና አንድ መቶ ሀያ ሺህ ሕዝብ ይኖርባት የነበረ ከተማ ነበረች (ዮናስ 3፡3 ዮናስ 4፡11)፡፡

በዚያን ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ክፋታቸው ከእግዚብሔር ዘንድ ደርሶ ስለነበር እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደዚያ ላከው፡፡ ‹‹ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ። ›› ብሎ ላከው፡፡ ዮናስ ግን ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ቢሞክርም እግዚአብሔር በድንቅ ተአምራቱ ወደ ነነነዌ መልሶታል፡፡ እንደገናም እግዚአብሄር ለዮናስ ‹‹ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው።›› ዮናስም ሄዶ ‹‹ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች!›› ብሎ ጮኸ፡፡

የነነዌ ሰዎችም ፈጥነው ንስሐ ገቡ፡፡ ‹‹ የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ።  ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።›› እግዚአብሔርም ምህረቱን ላከላቸው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።›› በዚህ ዘመን ፈጥነው ንስሐ በመግባታቸው ከጥፋት ድነዋል፡፡ ነገር ግን ከአንድ መቶ ኃምሳ አመት በኋላ ይህች ከተማ በነቢዩ ናሆምና ነቢዩ ሶፎንያስ አስቀድመው እንደተናገሩት በ612 ዓ.ዓ ጠፍታለች  (ናሆም 1፡8 3፡13 ሶፎ 2፡13-15)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ነነዌ ሰዎች ‹‹የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ›› ሲል ተናግሯል (ማቴ 12፡41 ሉቃ 11፡32)፡፡ ይህ አስደናቂ ቃል ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ የነነዌ ሰዎች ስለምንድን ነው ‹‹በዚህ ትውልድ ላይ ይፈርዱበታል›› የተባለው? ይህ የሚሆነው ስለሚከተሉት አራት ምክንያቶች ነው፡፡

1) የነነዌ ሰዎች በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አመኑ፤ አይሁድ ግን ብዙ ነቢያትና ሕግጋት እያላቸው አላመኑም፡፡

አይሁድ አስቀድሞ በሙሴ አማካይነት የኦሪት ሕግ ተሰጥታቸዋለች፡፡ ቀጥሎም ብዙ ዐበይትና   ደቂቅ ነቢያት አስተምረዋቸዋል፡፡ኋላም መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ጌታ አስተምሯቸዋል፡፡ ነገር ግን በጌታ ለማመን ልባቸው ደነደነ፡፡ የነነዌ ሰዎች ግን እንደ  አይሁድ ብዙ ነቢያት ሳይላኩላቸው ለሀገሩ እንግዳ በሆነውና ከእነርሱ መዳን ይልቅ ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ ብሎ ይሰጋ በነበረው በአንዱ በዮናስ ስብከት ብቻ አምነዋል፡፡ እንደ እናንተ ብዙ ነቢያት ሳይላኩልን በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነን ንስሐ ገብተናል ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡

2) የነነዌ ሰዎች የነቢዩ ስበከት አምነው ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በነቢያት ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት እንኳን አላመኑም፡፡

የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔር በላከው በእግዚአብሔር ነቢይ በዮናስ ስብከት አምነው ንስሐ ገብተዋል፡፡ አይሁድ ግን ነቢዩ ዮናስን የላከው የነቢያት ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል መጥቶ በምድር ተመላልሶ ቢሰብክላቸውም አልተቀበሉትም፡፡ የነነዌ ሰዎች መልእክተኛውን ተቀበሉ፤ አይሁድ ግን መልእክተኞችን የላከውን አልተቀበሉትም፡፡አይሁድ ግን ለሰው ልጅ ሁሉ ቤዛ ሊሆን በመጣው በእግዚአብሔር ልጅ አላመኑምና የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ይመሰክሩባቸዋል፡፡ እኛ መልእክተኛውን ተቀብለን ንስሐ ስንገባ እናንተ ግን የመልእክተኛውን ጌታ አልተቀበላችሁም ሲሉ የነነዌ ሰዎች በአይሁድ ላይ ይመሰክሩባቸዋል፡፡

3) የነነዌ ሰዎች ምንም ተአምራትን ሳያዩ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን እጅግ ብዙ ተአምራትን እያዩ ልባቸው ደነደነ፡፡

የነነዌ ሰዎች ከዮናስ ስብከት በስተቀር አንድም ተአምር ሳያዩ አመነዋል፡፡ አይሁድ ግን አስቀድሞ ነቢያት ከዚያም ጌታ ራሱ እጅግ ብዙ ድንቅ ተአምራትን ቢያሳዩአቸውም አልተቀበሉትም፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው ሌላ ምልክት እንዲያሳያቸው ይሹ ነበር፡፡ የነነዌ ሰዎች እኛ አንድ ተአምር እንኳን ሳናይ አምነን ንስሐ ገብተናል፤ እናንተ ግን እጅግ ብዙ ተአምራት በፊታችሁ ሲደረግ እያያችሁ አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ብለው ይመሰክሩባቸዋል፡፡ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች፣ ምልክት ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር አይሰጣትም” ማቴ. 16፡4 ብሎ ጌታችን የተናገረው ብዙ ተአምራትን አይተው ለማያምኑ ለእንደዚህ አይነቱ ትውልድ ነው፡፡

4) የነነዌ ስዎች በጥቂት ቀናት ስብከት ብቻ ንስሐ ገቡ፤ አይሁድ ግን በብዙ ዓመታት ስበከት ንስሐ አልገቡም፡፡

የነነዌ ሰዎች በነቢዩ ዮናስ የተሰበከላቸው ለጥቂት ቀናት ብቻ ነበር፡፡ በዚያም የአጭር ቀናት ስብከት አምነው ንስሐ ገብተው ሊመጣባቸው ከነበረ ጥፋት ድነዋል፡፡ አይሁድ ግን ጌታ ብቻ ከሦስት አመት በላይ ብዙ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ አስተምሯቸው አልተቀበሉትም፡፡ ስለዚህ የነነዌ ሰዎች እኛ በጥቂት ቀናትና በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነናል ንስሐም ገብተናል እናንተ ግን ለብዙ ዘመናት ብዙ ነቢያት ኋላም ጌታ ራሱ ለዓመታት ቢያስተምሯችሁም አምናችሁ ንስሐ አልገባችሁም ሲሉ ይመሰክሩባቸዋል፡፡

በፍርድ ቀን የነነዌ ሰዎች እንዳይፈርዱብን ምን እናድርግ?

ጌታችን የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሲነቅፋቸው ‹‹ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል (ማቴ 11፡20-24)።›› ያለው ባየነውና በሰማነው ተምረን ንስሐ እንገባ ዘንድ ነው፡፡

በነነዌ ፆም የንስሐ ምስክሮች የሆኑትን የነነዌን ሰዎች ስናስብ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄ ይህ ነው፡፡ እነርሱ በአንድ ነቢይ ስብከት ብቻ አምነው ንስሐ ገቡ፡፡ እኛ ግን ብዙ መምህራን መክረውን፣ አስተምረውን፣ ብዙ ጉባዔያትን ተሳትፈን፣ ብዙ መጻሕፍት እያሉልን ንስሐ ገብተናል ወይ? እነርሱ በጥቂት ቀናት ስብከት ብቻ አምነው ንስሐ ገብተዋል፡፡ እኛ ግን ከሕፃንነት ጀምሮ የእግዚአብሔርን ቃል እየተማርን አድገናል፡፡ በዚህ ለዘመናት የተማርነውን ቃል በሕይወታችን ኖረነዋል ወይ? የነነዌ ሰዎች አንድም ተአምር ሳያዩ አምነው ንስሐ ገብተዋል፡፡ ለእኛ ግን ብዙ ተአምራት በጌታና በቅዱሳኑ ተደርገው እየሰማንና እያየን ልባችን ተሰብሯል ወይ? እንግዲህ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን እንዳይመሰክሩብን “ለጠቢብ ሰው አንድ ቃል ትበቃዋለች” እንደተባለ በተማርነውና ባወቅነው አምነን ንስሐ ልንገባ፣ እንደ ቅዱስ ቃሉም ህይወታችንን ልንመራ  ይገባል፡፡

አሜን እና እልል: ለማንና ለምን?

የ‹‹አሜን›› ነገር:-

ድሮ ድሮ (ያው ድሮ ቀረ እንጂ) ሽማግሌ ወይም ካህን ሲመርቅ ሌላው (ተመራቂው) ‹‹አሜን!›› ይል ነበር፡፡ መራቂው ከተመራቂው ወይ በዕድሜ ወይ በማዕረግ ከፍ የሚልም ነበር፡፡ ተመራቂውም ምርቃቱን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ነበር ‹‹አሜን›› የሚለው፡፡ ምርቃቱም ተመራቂውን ‹‹አሜን›› የሚያስብል፣ ተመራቂውም ‹‹አሜን›› የሚባለውን ታላቅ ቃል በአግባቡ የሚጠቀም ነበር፡፡ በዚያን ዘመን አንድ ሰው ‹‹አሜን›› ሲል ‹‹እንደተባለው ይሁን፣ ይደረግ›› ማለቱ ነበር፡፡ አሜን ‹‹የተረጋገጠና  የታመነ›› ከሚል የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን እንደየአገባቡ ትርጉሙ ‹‹ይሁን›› ‹‹በእውነት›› ‹‹መልካም›› ማለት ነው፡፡  ክርስቶስም እውነት ስለሆነ ‹‹አሜን›› ተብሏል፡፡ ራዕ 3፡14

በብሉይ ኪዳን (ዘዳ 27፡15-26) እንደተገለጸው ሌዋውያን ከፍ ባለች ድምፅ የተለያዩ ኃጢአትና ሕግን መተላላፍ አይነቶች እየጠሩ እነዚህን ያደረገ ‹‹ርጉም ይሁን›› ሲሉ ሕዝቡ ሁሉ ‹‹አሜን›› እንዲሉ እግዚአብሔር ለሙሴ ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም (መዝ 41፡13) ‹‹ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።›› ብሎ ‹‹አሜን›› የሚባለው በምን አይነት ቦታ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ሐዋርያትም ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል በየመልእክታቱ/መጻሕፍቱ ማጠናቀቂያ ላይ በብዙ ቦታዎች ተጠቅመውታል፡፡ (2ኛ ጢሞ 4፡22 ዕብ 13፡25 ራዕ 22፡21) ከእነዚህ ተጨማሪ ለእግዚአብሔር የአምልኮ ምስጋናን የሚገልፁ ታላላቅ ዓረፍተ ነገሮች መጨረሻ ላይ ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል እናገኛለን፡፡ ራዕ 1፡6 7፡12 19፡4 ነህያም እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ሕዝቡ ‹‹አሜን አሜን›› ብለው መልሰዋል፡፡ ነህ 8፡6 ካህኑም ሲመርቅ ‹‹አሜን›› ማለት እንደሚያስፈልግ እንዲሁ ተጽፏል፡፡ ዘኁ 5፡22

ቤተክርስቲያናችንም ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አብነት በማድረግ በቅዳሴና በሌሎችም የጸሎት መጻሕፍት ‹‹አሜን›› የሚባልበትን ሥርዓት ሠርታለች፡፡ በየትኛው ቦታ ምዕመናኑ አሜን ማለት እንዳለባቸው፣ ስንት ጊዜ አሜን ማለት እንዳለባቸው፣ በንባብ ወይም በዜማ አሜን እንደሚባል ጭምር በመጻሕፍቱ አስቀምጣለች፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ‹‹አሜን›› የሚለው ቃል በአደባባይም ይሁን በአውደምህረት፣ በመገናኛ ብዙኃንም ይሁን በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ‹‹ተጠቃሚ›› አግኝቷል፡፡ ነገር ግን የአጠቃቀሙ ጉዳይ በዝግመታዊ ለውጥ (Evolutionary change) ይሁን በአብዮታዊ ለውጥ (Revolutionary change) በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ሌላ አዝማሚያ ተሸጋግሮአል፡፡ ብዙዎች ይህንን ጉዳይ የምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ ወይም ዘመናዊነት ነው ቢሉትም የቃሉ አጠቃቀም ግን በአግባቡ መሆን እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ አሜንን በአግባቡ እንጠቀም የሚለው ሀሳብ የአሜን ቁጠባ ሳይሆን መልእክትን በሚገባ ለማስተላለፍ ከሚል ዓላማ የመነጨ ነው፡፡ ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ‹‹ሲጠቀሙበት›› ይታያል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ቀርበዋል፡፡

የተፅዕኖ አሜን፡ የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› አሜን አስባዩ በመድረክ ላይ ቆሞ ‹‹አሜን በሉ!›› ሲል ወይም በማህበራዊው ሚዲያ ‹‹እገሌን የሚወድ አሜን ይበል›› ሲል የሚባል ‹‹አሜን›› ነው፡፡ ለመሆኑ ሰው የሰማውን/ያየውን ነገር ሲያምንበት አሜን ይበል እንጂ ስለምንድን ነው በግድ ‹‹አሜን በሉ›› የሚባለው? ይህ የሚያሳየው ‹‹አሜን በሉ›› የሚለው ግለሰብ አሜን የሚያስብል ነገር ማቅረብ ስላልቻለ ‹‹አስገድዶ›› አሜን ለማስባልና ሕዝቡ ‹‹አሜን ይልለታል›› ለመባል የሚደረግ ከንቱ ድካም ነው፡፡

የብዜት አሜን፡- የዚህ አይነቱ አሜን ደግሞ አሜንን ብዙ ጊዜ በተከታታይ (ሌላ ቃል በመካከል ሳያስገቡ) ‹‹አሜን አሜን አሜን አሜን አሜን ….›› በማለት ወይም ‹‹አሜን (በቁጥር ይህንን ያህል ጊዜ በል)›› በማለት የሚነገር ወይም የሚፃፍ ሲሆን ብዛቱም እንደ አሜን ባዩና አስባዩ ስሜት የሚወሰን ይሆናል፡፡ በአሜን ብዛት የሚበዛ በረከት ወይም አንድ/ሦሰት ጊዜ ብቻ አሜን በማለት የሚቀር በረከት ይኖር ይሆን እንዴ? ወይስ ለወደፊት ‹‹ይህንን ያህል ጊዜ አሜን በሉ›› የሚል ህግ ያስፈልግ ይሆን?

የትኩረት አሜን፡- የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› ደግሞ አሜን በሚለው ቃል ውስጥ ያሉ ፊደላትን በማጥበቅ ወይም በማርዘም ወይም ሌላ ድምፅ በመስጠት የሚባል ሲሆን ዓላማውም ክረትን ወይም ርዝመትን በመፍጠር ትኩረትን መሳብ ነው፡፡ አምኤኤኤን (Ameeen)፣ አሜንንንን (Amennnnn)፣ አሜ…..ን (Ame….en) የሚሉት የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ‹‹አሜን›› በማለት ፈንታም ከሌላው ተውሶ ‹‹ኤሜን!›› ማለትም ከዚህ ይካተታል፡፡ አሜን የሚለውን በተገቢው ዜማ ማለት እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ አይነቱ አዲስ የመጣ የአሜን አክራሪነት ግን በአግባቡ ሊጤንና ሊጠና የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

የቅብብል አሜን፡- ይህ ደግሞ ተናጋሪው አንድ ቃል/ሀረግ በተናገረ ቁጥር ሌላው ሰው ለእያንዳንዱ ቃል/ሀረግ አጸፋ ‹‹አሜን›› የሚልበት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ‹‹አሜን›› የሚለውም ሰው ምን እንደተባለ እንኳን በአግባቡ ሳይሰማ ‹‹አሜን›› ማለትን እንደ ሥርዓተ ነጥብ (punctuation) ብቻ ይጠቀመዋል፡፡ ‹‹አሜን›› የሚባልለትም ሰው በአሜን ታጅቦ ንግግሩን ይዘልቀዋል፡፡ የእንደዚህ አይነቱ አሜን ‹‹ተጠቃሚዎች›› ካልሆኑ በቀር የዚህ አይነቱን ‹‹አሜን›› ጠቀሜታ የሚያውቅ የለም፡፡

የ‹‹እልል›› ነገር:-

ከአሜን ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው የ‹‹እልል›› ነገር ነው፡፡ ‹‹እልል›› ወይም ‹‹እልልታ›› የደስታ ጩኸት፣ ደስታን የተሞላ ድምፅ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር በእልልታ ይዘምሩ ነበር፡፡ ዛሬም እልልታ የደስታ/የምስጋና መግለጫ እንደመሆኑ መጠን በመዝሙር ወይም ሌሎች ደስ የሚያሰኙ ነገሮች ሲነገሩ እናቶችና እህቶች ‹‹እልል›› ይላሉ፡፡ ይህም በመጽሐፍ  ‹‹አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ።…አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። መዝ 47፡1-5›› ተብሎ እንደተገለጸው በማስተዋል እስከተደረገ ድረስ አግባብ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔርን ክቡር ዳዊት ‹‹ እግዚአብሔርን…. እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት፡፡ መዝ 150፡5›› ብሎ የዘመረው ይህንን እንድናስተውል ነው፡፡  ‹‹እልል›› ለንግሥና ለመዝሙርም፣ ለሠርግና ለዘፈንም አገልግሎት ይውላል፡፡

‹‹እልልታ›› እናቶችና እህቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሉት ነው እንጂ በሌላ አካል ግፊት አይደለም፡፡ አሁን አሁን የሚታየው ግን በመድረክ የቆመው (በሚዲያ የሚፅፈው) ሰው ‹‹እልል በሉ›› እያለ ወይም ራሱ ‹‹እልልልል…..›› እያለ እልል የሚያስብልበት ሁኔታ ነው፡፡ ‹‹እልል›› የምንል ሰዎች በማስተዋል አምነንበትና ከልባችን ‹‹እልል›› ስንል ምስጋና ይሆናል፡፡ ‹‹እልል በሉ›› ስለተባለ ወይም ሌላው እልል ስላለ ብቻ እልል ማለት ግን ውስጣችን ጥያቄ እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡

ጥቂት ማሳሰቢያ፡-

መምህራንና ዘማርያን ነን የምትሉ ወይም በመድረክና በየማህበራዊ ሚዲያው ለመናገር የምትፈጥኑ ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› የማለት ወይም ያለማለትን ነፃነትን ለምዕመናን ብትተውት ምናለበት? በተፅዕኖ ‹‹አሜን›› ወይም ‹‹እልል›› አስብላችሁ የምታተርፉትስ ነገር ምንድን ነው? አሁን አሁንማ ህዝቡ የምትፈልጉትን ስላወቀ ‹‹አሜን/እልል በሉ›› ሳትሉ ቀድሞ ‹‹አሜን/እልል›› ይላል፡፡ ይህ ግን እናንተ ‹‹እልል በሉ!›› እንጂ እያላችሁ ከምትሳቀቁ ብሎ አስቀድሞ መፍትሔ ለመስጠት መሆኑን መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ዓለማችሁ ንግግራችሁ ወይም መዝሙራችሁ እንዲደምቅ  ወይም ተቀባይነት እንዲያገኝ ከሆነ እልልታ ምስጋና እንጂ ማድመቂያ አይደለም፡፡ ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› አስባይ ሰዎች በየመድረኩ ሲበዙ ሳይገባው (‘ገ’ ላልቶ ይነበብ) ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› የሚል ህዝብ ይበዛል፡፡ ጉባዔያትና የሜዲያ ገፆችም ከእውቀት የራቁ የእልል የአሜን አስባዮችና ባዮች መድረክ ይሆናሉ፡፡

 

 

የፈጠረውን ሥጋ የተዋሐደ ጌታ በፈጠረው ውኃ ተጠመቀ

timket2

“ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ::” ሉቃ 3፡21

እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን!

የልደትና የጥምቀት ዘመን በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒ፣ በግእዝ ዘመነ አስተርእዮ፣ በአማርኛ የመገለጥ ዘመን ይባላል። ጥምቀት የሚለው ቃል “አጥመቀ” ከሚለው የግእዝ ቃል/ግሥ የተገኘ ሲሆን በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው። በምሥጢር ትርጉሙ ግን ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ሲሆን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት፣ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት፣ ኃጢአታችን የሚደመሰስበትና ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው። ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚቀበለው ሰው ሁሉ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለማግኘትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ ክርስቲያናዊ የሕይወት መንገድ ነው።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጢባርዮስ ቄሳር (14-37 ዓ.ም) በነገሰ በ15ኛው ዓመት፣ በተወለደ በ30 ዓመቱ፣ በዕለተ ማክሰኞ ከሌሊቱ 10 ሰዓት፣ ዮር እና ዳኖስ የተባሉ ወንዞች በሚገናኙበት በተቀደሰው የዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ማቴ 3፡13-17 ማር 1፡9-11 ሉቃ 3፡ 21-22 ዮሐ 1፡29-34

የተጠመቀውም የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ በሆነው፣ ገና የስድስት ወር ጽንስ ሳለ በማህፀን በሰገደለት፣ በበረሀ ባደገው፣ የመንገድ ጠራጊ በተባለው፣ የንስሐን ጥምቀት በዮርዳኖስ ሲያጠምቅ በነበረውና ኋላም በሄሮድስ ሰማዕትነትን በተቀበለው በደቀ መዝሙሩ በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ነው፡፡ ከውኃ ውስጥ ገብቶ በመውጣትም ተጠመቀ፡፡ ጌታችን የተጠመቀው ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ነበር፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ከሕዝቡ አስቀድሞ ተጠምቆ ቢሆን የኦሪት ጥምቀትን ተጠመቀ እንዳይባል፣ ከሕዝቡ መካከል ተጠምቆ ቢሆን ኦሪትና ሐዲስ ተቀላቅለዋል እንዳይባል፣ አዲስ ልጅነት ለምታስገኘዋ የአዲስ ኪዳን ጥምቀት አርአያ ሊሆን ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ እርሱ ደግሞ ተጠመቀ፡፡ ከሁሉ በላይ የሆነ ጌታ ከሕዝቡ በኋላ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን ሲጠመቅ ሰማይ ተከፈተ (ያልተገለጠ ምስጢር ተገለጠ)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መጥቶ አረፈበት፡፡ አብም ከሰማያት ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› አለ፡፡ አምላክ በተጠመቀ ጊዜ ዮርዳኖስ ሸሸ፤ ተራሮችም እንደኮረብቶች ዘለሉ (መዝ 76፡16)፡፡

ሰዎች በእርሱ ስም ይጠመቃሉ፡፡ እርሱስ በማን ስም ተጠመቀ?  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ መጥምቁ ዮሐንስ እንዴት ብሎ ማጥመቅ እንደሚችል ግራ ገብቶት ‹‹ሌላውን ሰው በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተን በማን ስም አጠምቃለሁ?›› ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡ ጌታም ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሀብ ተሣሀለነ፤ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከፄዴቅ (የቡሩክ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የብርሀን መገኛ ይቅር በለን፡፡ አንተ እንደመልከፄዴቅ ለዓለም ካህን ነህ፡፡)›› ብለህ አጥምቀኝ እንዳለው እንደዚሁ ብሎ አጥምቆታል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን  ለምን መጠመቅ አስፈለገው? በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለፀው ጌታችን ስለ አምስት ምክንያቶች ተጠምቋል፡፡

  1. ጥምቀትን ለመመስረት (ለመባረክ)

‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት አይገባምና (ዮሐ 3፡5)›› ጥምቀትን ለመንግስተ ሰማያት መግቢያ በር አድርጎ ሊመሠርት ተጠመቀ፡፡ ‹‹ያላመነ ያልተጠመቀ አይድንምና ማር 16፡16›› ጥምቀትን የድኅነት መሠረት አድርጎ ሠራት፡፡ ‹‹በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥም አጥምቁ የምትል ትዕዛዝ ሰጥቷልና ማቴ 28፡19›› እርሱ ተጠምቆ እናንተም ተጠመቁ አለን፡፡  በአጠቃላይ ምስጢረ ጥምቀትን ሊመሠርታትና ራሱ ተጠምቆ አርአያ ለመሆን ተጠመቀ፡፡

ምስጢረ ጥምቀትን  እንደዚህ አድርጎ መሠረታት፡፡ ሁላችን ለመጠመቅ ወደ ቤተክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ሊያስተምር በመጀመሪያ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ እኛም ወደ ካህናት ሄደን እንድንጠመቅ አርአያ ለመሆን እርሱ አምላክ ሲሆን ወደ ፍጡሩ ወደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ሄደ:: ሁላችን በውኃ እንድንጠመቅ እርሱም በውኃ ተጠመቀ፡፡ ጥምቀት ለእኛም የክርስትና መግቢያ በር እንድትሆንልን ጥምቀትን የሥራው ሁሉ መጀመሪያ አደረጋት፡፡ እኛም ስንጠመቅ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድልን ለማጠየቅ እርሱ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ እኛ በሥላሴ ስም እንድንጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ ተገለጠ፡፡ ጥምቀት አንዲትና የማትደገም ምስጢር ናትና እርሱም አንድ ጊዜ ብቻ ተጠመቀ፡፡

‹‹…እንደ ምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው ጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን፡፡ ቲቶ 3፡4›› እንዳለ፤ እንዲሁም ‹‹የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ሦስቱም አንድ ናቸው 1ኛ ዮሐ 5፡8፡፡›› እንደተባለ እኛ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ተወልደን ልጆቹ እንሆን ዘንድ ጥምቀትን ሠራልን፡፡ በእርሱ ጥምቀት አማካይነት ጥምቀት ከሰማይ መሆኗን፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ የምትደረግ መሆኗን አሳየን፡፡ ጥምቀታችንንም በጥምቀቱ ባረከልን፡፡

  1. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት እንዲገለጥ

በጌታችን ጥምቀት አምላክ በዮርዳኖስ በአንድነት በሦስትነት ተገልጧል፡፡ አብ በሰማያት ሆኖ በመመስከር ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት›› በማለት እውነተኛ አባት፤ አውነተኛ ልጅ መሆኑን፤  ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ የባህርይ ልጅ መሆኑን፤ በተዋሕዶ የከበረ መሆኑን፤ ‹‹ልጄ›› ብሎ አረጋገጠልን፡፡ ወልድ በማዕከለ ባህር ሥጋን ተዋሕዶ ቆሞ፤ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ፤ እንደሰው ተጠምቆ (ሥጋን ተዋሕዷልና)፤ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ፤ ይመጣል ተብሎ ትንቢት የተነገረለትን ሆኖ በመጠመቅ ተገለፀ፡፡መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል መጥቶ በራሱ ላይ አርፎ፤ ረቂቅ ነውና ለሰው እንዲታይ በርግብ አምሳል ሆኖ ተገለፀ። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድንጠመቅ ይህንን ምስጢር በዮርዳኖስ ገለጠልን። እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ስለ ባህርይ ልጁ በመመስከር፣ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ፊት በትህትና በመቆም፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በመውረድ ከኢአማንያን ተሰውሮ የነበረ የሥላሴ ኀልወት ታወቀ፣ አስተርዕዮ ሆነ፡፡

  1. ትህትናን ለማስተማር

የጌታን የትህተናው ነገር ድንቅ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪ ሲሆን ራሱ በፈጠረው ፍጡር በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ፣ አንዳች ኃጢአት ሳይኖርበት ለሰው ልጅ ሲል ጽድቅን ለመፈፀም ተጠምቆ፣ ሰማያዊው ንጉስ በምድራዊው ሰው ተጠምቆ ፤ እሳትነት ያለው መለኮትን ያለመለየት የተዋሀደ ሥጋ  ፍፁም ሰው ሆኖ ተጠምቆ ፣ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው እርሱ በውኃ ተጠምቆ፣ ፍጡራን በስሙ የሚጠመቁት እርሱ በፍጡር እጅ ተጠምቆ፣ ፈጣሪ የሆነው ራሱ በፈጠረው ውኃ ተጠምቆ (እርሱ በፈጠረው ውኃ እኛም እንድንጠመቅ)፣ ኃጢአት የሌለበትና የሰውን ልጅን ኃጥአት የሚያስወግድ እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ተጠመቀ (ተቆጠረ):: ይህንን ሁሉ ያደረገው ትህትናን ለማስተማር ነው፡፡ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና::” እንዳለ፡፡ ማቴ 11፡29

  1. ትንቢቱና ምሳሌው እንዲፈፀም

ጌታችን  በዮሐንስ ሊጠመቅ ሲመጣ አምላክነቱን በመንፈስ ቅዱስ የተረዳ ዮሐንስ “እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?” ብሎ በከለከለው ጊዜ መምህረ ትህትና ኢየሱስ ክርስቶስ  ‹‹አሁንስ ተው፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› ብሎ መልሶለታል፡፡ ጽድቅን መፈጸም ብሎ ጌታ ከገለፃቸው ውስጥ አንዱ ትንቢተ ነቢያትን መፈጸም ነበርና በዮርዳኖስ በመጠመቅ የነቢያትን ትንቢት ፈጸመ፡፡ ‹‹አንቺ ባህር የሸሸሽ፣ አንተም ዮርዳኖስ ወደ ኋላህ የተመለስህ ምን ሆናችሁ ነው? እናንተም ተራሮች፣ እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችስ እንደ በጎች ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? ከያዕቆብ አምላክ ፊት፣ ከእግዚአብሔር ፊት ምድር ተናወጠች፡፡ መዝ 113፡3›› የተባለውና እንዲሁም ‹‹አቤቱ ውኆች አዪህ፤ ውኆች አይተው ፈሩ፤ የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ፣ ውኆቻቸውም ጮሁ፡፡ መዝ 76፡16 ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈፀም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡

በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁም በብሉይ ኪዳን ብዙ ምሳሌዎች ያሉት ሲሆን የሚከተሉትን ለአብነት ያህል መመልከት ይቻላል፡፡

  • ዮርዳኖስ መነሻው አንድ ሲሆን ከዚያ በደሴት የተከፈለ፤ ኋላም የሚገናኝ ነው፡፡የሰው ዘሩ አንድ አዳም ነው፡፡ ኋላ ሕዝብና አሕዛብ ተብሎ በግዝረትና በቁልፈት ተከፈለ፡፡ በክርስቶስ ጥምቀት ህዝብና አህዛብ አንድ ሆኑ፡፡
  • አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲሄድ መልከፄድቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኮቴት ይዞተ ቀብሎታል፡፡አብርሀም የምዕመናን፣ መልከፄድቅ የካህናት፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ኅብስቱና ጽዋው የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ናቸው፡፡
  • ከሕዝብ ወገን የሆነው ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡ ከአሕዛብ ወገን የሆነውም ሶርያዊው ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡የሕዝብም የአሕዛብም ወገኖች በጥምቀት ይድናሉና፡፡
  • እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ነቢዩ ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደገነት አርጓል፡፡ ምዕመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግስተ ሰማያት ይገባሉና፡፡
  • ዮርዳኖስ በክረምት አይሞላም፡፡ በበጋም አይጎድልም፡፡ በጥምቀትም የሚገኝ ልጅነት ጽኑ ነው፣ አይነዋወጽምም፡፡
  1. የአዳምንና የሔዋንን (የሰው ልጆችን) የዕዳ ደብዳቤ ሊያጠፋ

አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በልተው ከተሳሳቱ በኋላ ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ  መከራ አፀናባቸው፡፡ በመከራቸውም ጊዜ ‹‹ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራችሁን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፡፡ ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ (አዳም የዲያብሎስ ባሪያ ነው) ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት)››ብለው ጽፈው ሰጡት (ይሁንብን አሉ)፡፡ እርሱም በሁለት እብነ ሩካብ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱንም በሲኦል ጥሎታል፡፡ በዮርዳኖስ ያለውን ጌታ ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል፡፡ በሲኦል ያለውን ደግሞ በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸዋል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ መጠመቁ አንደኛው ምክንያት ይህንን የዕዳ ደብዳቤ ለማጥፋት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በጥምቀት ዕለት ፡-

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በጥምቀት ዕለት ‹‹ሖረ ኢየሱስ እምገሊላ ኀበ ዮርዳኖስ›› (ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ) ስትል ታቦታቱን ከመንበራቸው አንስታ ወደ ጥምቀተ ባህሩ በድምቀት ትወስዳለች፡፡ ‹‹…ቆመ ማዕከለ ባህር…›› (በባህር ውስጥ ቆመ) እያለች በመዘመር የጌታን ጥምቀት ታከብረዋለች፡፡ ‹‹…ተጠምቀ በማየ ዮርዳኖስ…. በዕደ ዮሐንስ…›› (በዮርዳኖስ ውኃ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ) እያለች ታመሰግነዋለች፡፡ ‹‹ባህርኒ ርዕየት ወጎየት….›› (ባህር አየች፤ ሸሸችም ) እያለችም የነቢያትን ትንቢት ፍፃሜ ትሰብካለች፡፡

በጥምቀተ ባህር ያለውን ውኃ በመባረክ ምዕመናንንም በተባረከው ውኃ በመርጨት ከበዓሉ በረከት እንዲቀበሉ ታደርጋለች፡፡ ይህ ዳግመኛ ጥምቀት አይደለም፡፡ በዚህ ዕለት በዋናነት በዮርዳኖስ የተጠመቀው አምላክ የሚመሰገንበት ቀን ነው፡፡ ለእርሱም በማህሌት፣ በመዝሙር፣ በቅዳሴ ምስጋና የሚቀርብበት ቀን ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ሁላችንም የምንባረክበትና በረከትን የምናገኝበት ዕለት ነው፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ወይስ ታደርሳለች?

seba segel2

ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ የተጠቀሰች ሀገር ስትሆን በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙር 67፡31 ላይ “መልእክተኞች ከግብፅ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር  ትዘረጋለች” ተብሎ የተቀመጠው ግን በብዙዎች ዘንድ በሰፊው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የመዝሙር ክፍል በግዕዙ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚል ሲሆን በግዕዙና በአማርኛው ትርጉም መካከል ልዩነቶች እንዳሉ አንዳንድ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

ቀደምት አበው እንዳስተማሩትና የግእዝ ቋንቋ ሊቃውንትም እንደሚያስረዱት “በጽሐ” የሚለው የግእዝ ቃል ቀጥታ የአማርኛ ትርጉሙ “ደረሰ” ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ታበጽሕ” የሚለው ቃል “ታደርሳለች” የሚለውን ትርጉም ይይዛል ማለት ነው፡፡ በግዕዙ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለውም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” የሚል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው የአማርኛው ትርጉም ወደ ግዕዙ ቢመለስ ደግሞ “ኢትዮጵያ ትሰፍሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚል ይሆናል፡፡ በግዕዝ “ሰፍሐ” ማለት በአማርኛ “ዘረጋ” ማለት ነውና፡፡ “ትሰፍሕ” ማለት ደግሞ “ትዘረጋለች” ማለት ይሆናል፡፡ ይህም “…ይሰፍሑ ክነፊሆሙ…” ማለት “ክንፋቸውን ይዘረጋሉ” ማለት እንደሆነው ያለ ነው፡፡ስለዚህ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለው “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ከሚለው ይልቅ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” የሚለው የአማርኛው ትርጉም የበለጠ ይስማማዋል፡፡

ይህንን ልዩነት  መተንተን ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት “ታደርሳለች” እና “ትዘረጋለች” በሚሉት ቃላት መካከል ልዩነት ስላለና ልዩነቱም ከመጻሕፍት ምሥጢራት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ነው፡፡ እጅን መዘርጋት ማንም ሊዘረጋ ይችላል፡፡ለመቀበል ወይም ለመስጠት እጅን መዘርጋት አስፈላጊ ቢሆንም እጁን የዘረጋ ሁሉ ግን አይቀበልም ወይም አይሰጥም፡፡ ዘርግቶም ሊቀበልም ላይቀበልም ይችላልና፡፡ ዘርግቶ ሊሰጥም ላይሰጥም ይችላልና፡፡ እጁን የሚያደርስ ግን ወይ ይሰጣል ወይም ይቀበላል፤ አለበለዚያም ሰጥቶ ይቀበላል ወይም ተቀብሎም ይሰጣል፡፡ በጸሎት ጊዜ እጃችንን የምንዘረጋው በእምነት ሆነን ቸርና ለጋስ የሆነው አምላካችን የሚሰጠንን መልስና በረከት ለመቀበል መዘጋጀታችንን የሚያሳይ መሆኑን ነባቤ መለኮት የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አስተምሯል፡፡

ይህቺ ቅድስት ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ግን ‹‹ታበጽሕ›› (ታደርሳለች) ተብሎ ነው የተነገረላት፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ከሰብአ ሰገል አንዱ በመሆን ሥጦታን ለተወለደው አምላክ በማቅረብ በእውነት እጆቿን (ስጦታን ይዛ) ወደ እግዚአብሔር አድርሳለች፡፡ ይህም ከአምላኳ በነቢያት በኩል ለርሷ  የተሰጠና የተነገረላት ትንቢት ነው (መዝ 67:31)፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት ይህንን “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ … የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታትም እጅ መንሻን ያቀርባሉ፤ የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል” ብሎ ገልጾታል፡፡ (መዝ. 71፡9-10)

ለተወለደው አምላክ በቤተልሔም ተገኝተው አምሐ ካቀረቡት ሦስት ነገስታት (ሰብአ ሰገል) መካከል አንዱ የሆነው ንጉሥ በዲዳስፋ (አንዳንድ ጸሐፊያን ባልዛር ወይም ባዜን ይሉታል) የኢትዮጵያ ንጉሥ እንደነበር የታሪክ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡መልኩም ጥቁር እንደነበርና ከርቤን (አንዳንድ ጸሐፊያን ወርቅን ይላሉ) በአምላኩ በክርስቶስ ፊት እንዳቀረበ ይገልፃሉ፡፡ ዛሬም ድረስ ምዕራባውያን በሚሠሩት የልደት የፊልም፣ተውኔትና በሚሥሏቸው የሰብአሰገል ሥዕሎች ላይ አንዱን (ኢትዮጵያዊውን)ጥቁር አድርገው ይስሉታል፡፡ ይህም አምሐ ካቀረቡት ሦስት ነገስታት መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ እንደነበር ምዕራባውያን ሊቃውንትም ያውቁ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ ትክክል ነው፡፡ ብሉይ ኪዳንን በንግስተ ሳባ አማካኝነት የተቀበለች ኢትዮጵያ ተስፋ ልደቱን፣ የነቢያትን ሱባኤ የምታምንና የምትጠብቅ ስለነበረች ጌታ በተወለደ ጊዜ ከሰብአ ሰገል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያዊ ንጉስና ሰራዊቱ ወደ ቤተልሔም የሄዱት የተቆጠረው ሱባኤ መፈጸሙን ተረድተው እንደነበር ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

ለኢትዮጵያ ነገስታት ስጦታን መስጠት የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ንግስተ ሳባ ስጦታን የክርስቶስ ምሳሌ ለነበረው ለእስራኤል ንጉሥ ለሰሎሞን አበርክታለች፡፡ይህም “ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር” (1ኛ ነገ 10: 10) ተብሎ ተጽፏል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ የነገሠውና ከሰብአ ሰገል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንጉሥ ባልዛር (ባዜን) ደግሞ ለሰማያዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከርቤን አበርክቷል፡፡

ወደ እግዚብሔር የተዘረጉት፣ እንዲሁም የደረሱት የኢትዮጵያ እጆች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ልጅዋ በስደት ሳሉ ተቀብለው አስተናግደዋቸዋል፡፡ በዚህም ብዙ በረከት አግኝተዋል፡፡ ሀገሪቱም ለቅድስት ድንግል ማርያም አስራት ተደርጋ ተሰጥታለች፡፡ ይህም ዛሬም ለእርስዋ ልዩ ፍቅር ያለው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲኖር መሠረት ሆኗል፡፡

ወደ እግዚአብሔር ተዘርግተው ወደ እርሱም የደረሱት የኢትዮጵያ እጆች ክርስትናንም ተቀብለው ተመልሰዋል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 8፡26 ላይ እንደተገለጸው የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ የነበረው ባኮስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ በሐዋርያው ፊሊጶስ ተጠምቆ ክርስትናን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ በቅዱስ ፍሬምናጦስ በኩል ወደ እስክንድርያ የተዘረጋው ከዚያም የደረሰው የኢትዮጵያ እጅ ምስጢረ ክህነትን ይዞ ተመልሷል፡፡በአፄ ዳዊት ዘመንም የተዘረጉት የኢትዮጵያ እጆች ግማደ መስቀሉን ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “መልእክተኞች ከግብፅ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር  ትዘረጋለች” እንዳለ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ የክህነት ውርስን ከግብፅ መልእክተኞች፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ከተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት ተቀብላ፣ በሐዋርያዊ አስተምህሮም ተባብራ (አንድ ሆና) ስለኖረች፣ ስለምትኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ውርስ ተገለጠ፣ ልበ አምላክ የተባለ የንጉስ ዳዊት ትንቢትም ተፈጸመ፡፡

የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጉም እንዲሁም ታሪክን ለራሳቸው ዓላማ የሚበርዙ ልዩ ልዩ መናፍቃን፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች የክቡር ዳዊትን ትንቢት ያለአውዱ እየጠቀሱ አንዳንዶችን ግራ ሊያጋቡ ቢሞክሩም ከላይ በተጠቀሱት ታሪካዊና፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃወች የንጉስ ዳዊት ትንቢት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ብሎም ለኢትዮጵያ ምልክት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የተነገሩ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ዛሬም በጸሎትና በምስጋና የሚዘረጉት የኢትዮጵያ እጆች ወደ እግዚአብሔር ደርሰው ረድኤትን፣ በረከትንና ድኀነትን የዘላለም ሕይወትን ለሕዝቦቿ ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ሰማያዊ ጸጋ በምድራዊ ምቾትና ባለጸግነት የሚመዘን አይደለምና፡፡

 

የዘመነ አስተርእዮ ምስጋና

እንኳን ለዘመነ አስተርእዮ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሠረት ከልደተ ክርስቶስ እስከ ዐቢይ ፆም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) በመባል ይታወቃል፡፡ ዘመነ አስተርእዮ አራት ዓበይት በዓላትን ማለትም የጌታችን ልደት፣ የጌታችን ጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ ተዓምርና የእመቤታችን ዕረፍት ያጠቃልላል፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ይህን ያህላል፣ ይህን ይመስላል የማይባል ጌታ ከድንግል በሥጋ ተወልዶ ስለተገለጠ፣ ለዘመናት በእምነት ካልበሰሉ ምዕመናን አዕምሮ ተሰውሮ የነበረ የሥላሴ ኀልወት (ምስጢረ ሥላሴ) በጌታ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ በገሃድ ስለታየ፣ በሥጋ ማርያም የተገለጠ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ30 ዓመታት በግልጥ ሳያስተምር በየጥቂቱ አድጎ በቃና ዘገሊላ አምላክነቱን ስለገለጠ፣ ቤተክርስቲያናችን ይህንን ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ትለዋለች፡፡

የጌታችን ጥምቀት በዘመነ አስተርእዮ ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ ጥምቀትን ስናከብር ሁሉም እንደተሰጠው ጸጋ በደስታ በማመስገን መሆን ይኖርበታል፡፡ በልዩ ልዩ ባህል ሆ! በማለት ታቦትን አክብሮ ማጀብ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ የነበረ ትውፊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባች ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፤ ምድሪቱም አስተጋባች” (1ኛ ሳሙ. 4፡5) “ዳዊትና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በዜማ መሣሪያዎች  በበገናና በመሰንቆ፣ በከበሮና በነጋሪት፣ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር” (2ኛ ሳሙ. 6፡5) “ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ” (2ኛ ሳሙ. 6፡15) መዝሙር መዘመር ያልለመድን ምዕመናን እንደየባህላችን ሆ! እያልን ታቦታቱን ብናከብር እንከብርበታለን፡፡

ከዚያም ባሻገር እንደ እናቶች ልማድ በቅንቀና “እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ነይ ነይ እምዬ ማርያምና የመሳሰለውን በመዘመር ብናገለግል ዋጋ እናገኝበታለን፡፡ እነዚህ ሁለቱ ከመደበኛ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሰንበት ተማሪዎች ውጭ ያሉ ምዕመናን ሲያደርጓቸው ደስ ያሰኛል፡፡ እስራኤል ዘሥጋ እንደየችሎታቸው ከንጉሥ እስከ ጭፍራ በታቦቱ ፊት እንደየአቅማቸው አመሰገኑ እንጅ  ምስጋናን ለሌዋውያን ብቻ ትተው አምላካቸውን በሚመሰግኑበት ቀን ተመልካች አልሆኑም፡፡ እንደዚሁም ጥምቀት ሁሉም በየችሎታው እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት እንጅ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ልብሰ ተክህኖና የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው ለተመልካች የሚያቀርቡበት አውድ አይደለም፤ መሆንም የለበትም፡፡ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና ነው እንጂ ለታደመው ሰው የሚቀርብ ትርኢት ስላልሆነ ሁሉም እንደየጸጋው ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መደበኛ መዘምራን ከሌላው ምዕመን የበለጠ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ የአንዲት ሀገር ሹመኞች የሚያደርጉት በጎ ሥራ ሀገርን የሚያስመሰግን፣ ያልተገባ ስራቸውም ሀገርን የሚያስነቅፍ እንደሆነ ሁሉ ሳይገባው በቤቱ ለአገልግሎት የተጠራ ሁሉ አገልግሎቱን በጥንቃቄ ሊፈፅም ይገባዋል፡፡ የባህል ሆታዎችንና ቅንቀናዎችን ለሚያምርባቸው ለምዕመናን ሲሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ደግሞ በአቅማቸው የቤተክርስቲያንን ቀኖና ተከትለው ወቅታዊ የዘመነ አስተርዕዮ መዝሙራትን በመዘመር በዓሉን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራት ለዘመነ አስተርዮ የሚስማሙና የቤተክርስቲያንን ጥልቅ ምስጢራት የያዙ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ “ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ የሚያከብረው የለም” እንደሚባለው አገልጋዮች የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ሳይጠብቁ ሌላ ሲያቃልለው ለማስጠበቅ “ዘራፍ!” ማለት ብቻ ሞኝነት ይሆናል፡፡

በዘመናችን ግን አንዳንዶች አገልጋዮች ባለማወቅ፣ አንዳንዶች የሚደምቅላቸው ስለማይመስላቸው፣ ሌሎች ደግሞ የሲዲ ሽያጭና የሞቅ ሞቅ ጫጫታ ህሊናቸውን አውሮት በጥምቀት ዕለት ከበዓሉ ምስጢር ጋር የማይያያዙ፣ የቤተክርስቲያንን ወግና ሥርዓት የሚያደበዝዙ የሽያጭ “መዝሙራትን” ሲያቀርቡ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ይህን መርህ አልባ አዳማቂነት በተቻለ መጠን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የዘመነ አስተርዕዮ መዝሙራትን ከነትርጉማቸው ምዕመናን እንዲያውቋቸው ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በጥምቀት ሰሞን የሚዘመሩት የጥምቀት መዝሙራት ብቻ ሳይሆኑ፣ ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ የቃና ዘገሊላ ተዓምራቱን የሚያዘክሩ ናቸው፤  ምስጢራቸው የተያያዘ ነውና፡፡  የመዝሙሮቹን ምስጢር የተረዳ ሰው የቤተክርስቲያን የሆነውን አምሃ ትቶ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ጨዋታ ሲፈልግ አይውልም፡፡

ስለሆነም ሁላችንም አቅም በፈቀደ መጠን የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራትን በመዘመር፣ ይህን ማድረግ የማንችል ደግሞ ባህላዊ ሆታዎችን ወይም ቅንቀናወችን እያቀረብን ብናከብረው መልካም ይሆናል፡፡ ሌዋውያንን እንዲመስሉ የሚጠበቅባቸው መደበኛ አገልጋዮች (ሰንበት ት/ቤትን ጨምሮ) ሆ! ሲሉ አልለመድንም፣ አልተማርንም፣ አባቶቻችንም አላሳዩንም፡፡ ስለሆነም መደበኛ አገልጋዮች በደመቀበት ከመዋል አባቶቻችን እንዳስተማሩን ያሬዳዊ የሆኑትን የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራትን በአንድነት በመዘመር የቅዱስ ያሬድ በረከት እንዳያመልጠን እንትጋ፡፡ የተባረከ ዘመነ አስተርዕዮ ለሁላችን፡፡

ይህ የአስተምህሮ ጦማር እይታ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የታያችሁን አካፍሉ፡፡ “ኩሎ አመክሩ፤ ወዘሰናየ አጽንዑ/ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” እንደተባለ ከመረመርን በኋላ መልካም የሆነውን እንይዛለን፡፡ ምርመራችንም በእውነት፣በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት፣ በቤተክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት መመራት አለበት እንጅ በመርህ የለሽ አዳማቂነት መቃኘት የለበትም፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

(Email: tewahdo@astemhro.com)

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሰሎሞን ቤተመቅደስ ትመሰላለች፡፡

ምሳሌ 7 የሰሎሞን ቤተመቅደስ

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሰሎሞን ቤተመቅደስ ትመሰላለች (1ኛ ነገ 9፡1)፡፡

‹‹ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው፡- በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። …እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። መልሰውም፡- ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።›› 1ኛ ነገ 9፡1-8

ከደብተራ ኦሪት ቀጥሎ እግዚአብሔር  አምላክ እንደልቤ ብሎ ያከበረው ቅዱስ ዳዊት በዘመኑ ለአምላኩ ቤተ መቅደስ ሊሠራ ቢፈልግም ቤተመቅደስ የሆነ የኦርዮን ሠውነት አፍርሰሃልና አትሠራም ነገር ግን ልጅህ ይሠራዋል ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ንጉሥ ሠሎሞንም ቃል እንደተገባለት ውብና ያመረ በወርቅ የተለበጠ ቤተ መቅደስ ሠርቷል፡፡ ይህችም ቤተ መቅደስ ለአማናዊቷ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ›› እንዳለ በዚያች ቤተመቅድስ እግዚአብሔርና ሰው ተገናኝተዋልና የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በዚህች ቤተመቅደስም ክርስቶስ ተገኝቶ ባርኮ ከወንበዴዎች አፅድቶ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ያለው የአማናዊት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ስለሆነች ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ለእርሱ ስንታዘዝ ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን ትዕዛዙን የማንጠብቅና በእርሱም ላይ የምናምጽ ከሆነ ‹‹እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ›› እንዳለ እድል ፈንታችን የዘላለም ሕይወት አይሆንም፡፡ የማንታዘዝ ከሆነ ‹‹ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ›› እንዳለ በምድር ያለችው ቤተክርስቲያን ለፈተና ትዳረጋለች፡፡ ከእርሱ ፈቀቅ የምንል ከሆነ ‹‹እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ።›› እንዳለ በእኛም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ስንኖር እግዚአብሔርን ፈርተን እርስ በእርስም በፍቅር እየኖርን ሊሆን ይገባል፡፡ በጥልና በክርክር ወይም በዘረኝነትና በመከፋፈል የምንኖር ከሆነ ግን የዚህ ትንቢት መፈፀሚያ መሆናችን አይቀርም፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብተራ ኦሪት ትመሰላለች፡፡

ምሳሌ 6 ደብተራ ኦሪት2

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብተራ ኦሪት ትመሰላለች (ዘፀ 40፡1)፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ።›› ዘፀ 40፡1-6

ይህች በብሉይ ኪዳን የነበረች ደብተራ ኦሪት ምሳሌነቷ በሐዲስ ኪዳን ላለችው አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች፡፡

ምሳሌ 5 ደብረ ሲና.png

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች (ዘፀ 34፡1)፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን። በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር።›› ዘፀ 34፡27-29

ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ በቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖች በጾምና በጸሎት ተግተው ሰማያዊ ክብርን (ቃል ኪዳንን) ያገኛሉና ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ተራራ ተመስላለች፡፡ በደብረ ሲና ተራራ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ በቤተክርስቲያንም በጾምና በጸሎት የተጉ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉና ምሳሌነቱ ትክክለኛና ተገቢም ነው፡፡ ሙሴ ከደብረ ሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እያበራ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን የኖረ ሰው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ሲሄድ በመላእክት ታጅቦ እንደዚህ እያበራ ነውና ምሳሌነቱ ጽኑዕ ነው፡፡