የሐዋርያዊ ጉዞ መርሆች: ሰባኪ በመምጣቱ ምን ለውጥ መጣ?

sebaki

ከዚህ አስቀድሞ ባስነበብነው የአስተምህሮ ጦማር የሐዋርያዊ ጉዞ አስፈላጊነትና ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች ተዳስሰዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በዝርዝር የዳሰስነው የችግሩን ስፋት፣ጥልቀትና የሚያመጣውን ጣጣ በአግባቡ በማሳየት የመፍትሔ ሀሳብ ለማመላከት ነው፡፡ የተጠቀሱት ችግሮች ሰባክያኑንም፣ ምዕመናንንም፣ በአጠቃላይ ቤተክርስቲያንን የሚጎዱ ከመሆናቸው አንጻር የመፍትሔ ሀሳቦችም የሚጠቅሙት ለሁሉም ነው፡፡ በቅድሚያ ሰባኪ (መምህር) ከሌላ ቦታ የማስመጣት አስፈላጊነቱን ሁሉም አካል ሊያምንበት ይገባል፡፡ የሚመጣበት ዓላማም ንጹሕ ለሆነ የወንጌል አገልግሎት እንጂ ሌላ ዓላማ መሆን የለበትም፡፡ ሰባኪ ማስመጣቱ አስፈላጊ መሆኑ ከታመነበት ትግበራው መሠረታዊ የሚባሉ የአሠራር መርሆዎችን መከተል ይገባዋል፡፡ ለአንድ ችግር መፍትሄ ከመፈለግ በፊት የችግሩን ምንነት፣ መነሻና ያለበትን ደረጃ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሰባክያንን ከማስመጣት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሰራርና አስተሳሰብም የችግሩን ምንጮች፣ መገለጫዎችና የሚያስከትለውን ጉዳት በሚገባ ከመረዳት መጀመር አለበት፡፡ ችግሩን መገንዘብም ሆነ የመፍትሄ አቅጣጫው ከምዕመናን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን አስተዳደር አካላት ድረስ ካልተሳተፉበት ውጤታማ አይሆንም፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያን አካላት ቢከተሏቸው ይጠቅማሉ የምንላቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች በሰባት የትግበራ መርሆች (principles of implementation) ሥር አካተን አቅርበናል፡፡

የትኛው መምህር በየትኛው መዋቅር ይምጣ?

የቤተክርስቲያናችን መምህራን (ሰባክያነ ወንጌል) የተለያየ የማስተማር ጸጋ አላቸው፡፡ ከእውነተኞቹ መምህራን መካከል ማንም መጥቶ በውጭ ወይም በሀገር ውስጥ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ቢያስተምር ዋጋ ያገኝበታል፣ ምዕመናንም ይጠቀሙበታል፣ ይባረኩበታል፡፡ ነገር ግን የመምህራኑ አመራረጥ ባላቸው የማስተማር ጸጋ፣ የአገልግሎት ጊዜና ወጥነት ባለው የመምህራን ስምሪት መመሪያ መሠረት በሚሰጣቸው ምደባ ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡

ሰባክያን የሚመረጡበት መስፈርት ብልሹ መሆን አንዱ የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞ ችግር ነው። በዘመናችን በተለይም ሥጋዊ ጥቅም ባለባቸው ታላላቅ የኢትዮጵያ ከተሞችና በውጭው ዓለም ባለው አሠራር መምህር የሚመረጠው በትውውቅ፣ በጥቅም፣ በመንደርተኝነት ወይም በዝምድና በተሣሠሩ “የደላላዎች” ሠንሠለት አማካይነት መሆኑ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል፡፡ ምዕመኑ ምንም ባላወቀበት ሁኔታ ጥቂት ግለሰቦች የፈለጉትን ሰው የሚልኩበት፣ ያልፈለጉትን ደግሞ የሚገፉበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ የመምህራን ስምሪትን መምራት የሚገባው የቤተክርስቲያኒቱ አካል በሀገር ውስጥና ከሀገር ወጭ ለስብከት የሚሰማሩ መምህራን የሚመሩበትን ሥርዓትና መመሪያ በተሟላ መልኩ ሊተገብረው ይገባል፡፡ በውጭ ሀገር አጥቢያ ቤተክርስቲያናት፣ ሀገረ ስብከቶች ወይም ሌሎች የአገልግሎት ማኅበራት መምህራነ ወንጌልን ሲፈልጉ ሥርዓትን ባለው መልኩ በቤተክርስቲያኒቱ ተቋማዊ አስተዳደር በኩል የሚታወቁ መምህራንን ማስመጣት ይገባቸዋል፡፡ ለየትኛው ቦታ የትኛው መምህር በየትኛው ጊዜ አገልግሎት ይስጥ የሚለው ጉዳይ አሁን ካለው በተሻለ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በአስተምህሮ ምልከታ “የትኛው መምህር ይምጣ?” የሚለው ጉዳይ በአብዛኛው “በአስመጭዎችና ላኪዎች” ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ይመስላል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድም “ታዋቂ (ባለዝና)” እና ብዙ ሰው/ገንዘብ ሊሰበስቡ የሚችሉ መምህራን ላይ የማተኮሩ ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህም “ምን ያህል ገቢ ያስገባል?” የሚለውን እንደ መስፈርት እየተጠቀሙበት ያሉ ያስመስላል፡፡ መምህር የሚመጣው ገቢ ለማሰባስብ ከሆነ ከሆነ በጣም አደገኛ ውጤት እንደሚኖረው የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም መምህራን ሲመረጡ በመንፈሳዊ አገልግሎት መመዘኛነት ቢሆንና በተቻለ መጠንም በክህነት አገልግሎት የሚራዱና ምዕመናንን የሚመክሩ ሊሆኑ ይገባል። ከአማርኛ ውጭ ቋንቋ በሚነገርባቸው የሀገራችን ኢትዮጵያና በውጭ ሀገራት ለአገልግሎት የቋንቋ ጉዳይ መሰረታዊ ስለሆነ የአካባቢውን ቋንቋ (በተለይም የቤተክርስቲያን ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች የሚግባቡበትን ቋንቋ) ማስተማር የሚችሉ መምህራን አንጻራዊ ተመራጭነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

መጥቶስ ምን ያስተምር?

መምህር የሚጋበዘው እንዲያስተምር፣ ሰባኪም የሚመጣው ሊሰብክ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ መምህር ማስመጣቱ ላይ እንጂ “መጥቶ ምንድን (ስለምን) ነው የሚያስተምረው?” የሚለው ጉዳይ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በአብዛኛው መምህሩ ራሱ የፈቀደውን (ልቡ የወደደውን) ወይም ለማስተማር የሚቀለውን  (ብዙ ጊዜ ያስተማረውን ወይም አዲስ ዝግጅት የማያስፈልገውን) አስተምሮ (ሰብኮ) ይሄዳል፡፡ የሚያስተምረው ትምህርት የቤተክርስቲያን ቢሆንም ለምዕመናኑ የበለጠ የሚያስፈልገውን ትምህርት ቢያስተምር ግን መልካም ነው፡፡ አዲስ አበባ እና አሜሪካ ያለው ምዕመን በሕይወት መስተጋብሩ የተለያየ ስለሆነ ከሕይወቱ ጋር የተዛመደ ትምህርት ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ ጊዜ የተሰበከውን መልሶ መላልሶ ከማስተማር ይልቅ በጥልቀት ያልተዳሰሱ አርዕስትን ማስተማርም መልካም ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን በሚገባ የታሰበበትን ትምህርት ማስተማር ይገባል እንጂ በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው መንፈሳዊ ረብ የሌላቸውን ተራ ቀልዶችና መንፈሳዊነት የጎደላቸውን ንግሮች ማድረግ መምህሩንም ቤተክርስቲያንንም ያስንቃል፡፡

ተጋባዥ ሰባክያን የሚሰብኩት ስብከት ምን ያህል ምዕመናንን ያንፃል የሚለው ጉዳይ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም የትምህርቱ ተከታታይነት ማጣትና ተደጋጋሚ መሆን ግን በግልፅ የሚታይ ችግር ነው። በአንድ ወቅት አንድ የእነዚህ ከሌላ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ የሚመጡ መምህራንን ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ምዕመን “ሁሉም መምህራን ትምህርታቸውን ከአዳምና ከሔዋን ይጀምራሉ፡፡ አንዱ አብርሃም ላይ ሲደርስ ጊዜው አልቆ ይሄዳል፡፡ ሌላው የሙሴ መሪነት ላይ ሲደርስ ይሄዳል፡፡ የበረታው ደግሞ ዳዊት ላይ ያደርሰናል፡፡ እንደዚህ እያልን ሁል ጊዜ ከአዳምና ከሔዋን እንደገና እየጀመርን አዲስ ኪዳን ላይ የሚያደርሰን አጥተን ብሉይ ኪዳንን እንደ ዳዊት እየደገምን ነው” ብለዋል፡፡ አዲስ መምህር ሲመጣ ቢያንስ ያለፈው ያስተማረውን ባይደግም መልካም ነው፡፡ ቢቻል ካለፈው የሚቀጥል ትምህርት ቢሰጥ ተመራጭ ነው፡፡ የሚመጣው መምህር እዚያው ላሉት መምህራን (ሰባክያን) አጭር ስልጠና የሚሰጥ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ለጉባዔና ለሌሎች አገልግሎቶች በአቅራቢያው ባሉ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት፣ በማኅበራትና በሌሎችም መድረኮች እንዲያስተምር ነጻነት ሊሰጠውም ይገባል እንጂ በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው “እኛ ያስመጣነው መምህር ከእኛ ደብር ውጪ ማስተማር የለበትም” የሚል ፍጹም መንፈሳዊነትም፣ አስተዋይነትም የጎደለውን አሰራር መከተል አይገባም፡፡

በሌላ መልኩ አንዳንድ መምህራን እውነተኛውን ትምህርት ከማስተማር ይልቅ ብዙም ጥልቀት የሌለው ነገር ላይ በማተኮርና የኮሜዲያን ፍርፋሪ የሆኑ እርባና ቢስ ቀልዶችን በመቀለድ የቤተክርስቲያንን መድረክ ለማይገባ ዓላማ ያውላሉ፡፡ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር የማይገናኝ መናኛ ቀልድና ተረታ ተረት በማብዛት እንደ አርቲስት የመወደድ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ በዚህም የቤተክርቲያንን ሀብት ለብክነት፣ የምዕመናንንም ጊዜ እንቶ ፈንቶ ለመስማት፣ የራሳቸውንም የአገልግሎት ዕድል አልባሌ ነገር ይዳርጉታል፡፡ አንዳንዶችም ከማስተማር ይልቅ ቀሚስና ካባ እየቀያየሩ መታየትን ገንዘብ ያደረጉ ይመስላል፡፡ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ማስተማር እንደ ትልቅ “የዕድገት ዕርከን” የሚወስዱትና “ዓለም አቀፍ ሰባኪ” ለመባል የሚተጉ ለዚህም ለደላሎች መማለጃን የሚያቀርቡም “መምህራንም” አይታጡም፡፡ ሀገር ማየት ወይም የተሻለ ገንዘብ ማግኘት መጥፎ ነገር ባይሆንም ይህ ተቀዳሚ ዓላማ ሲሆን ግን ቤተክርስቲያንን ይጎዳታል፡፡

ስለዚህ አንድ መምህር ሲመጣ/ሲላክ “ምንድን ነው የሚያስተምረው?” የሚለው ጥያቄ አስቀድሞ መመለስ አለበት፡፡ ለዚህም የሁሉም ሀሳብ መሰማት ይኖርበታል፡፡ ምዕመኑም “መምህሩ ሲመጣ ምንድን ነው የሚያስተምረን (ምንድን ነው የምንማረው)?” ብሎ ቢጠይቅ መልካም ነው፡፡ አስተባባሪዎችም ይህንን ጥያቄ አስቀድመው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ መምህሩ ምን እንደሚያስተምር እንኳን ሳይነገረው ወደ ቤተክርስቲያን በእምነት የሚመጣው ምዕመን ምን እንደሚማር አውቆ ቢመጣ ደግሞ ምን ያህል የተሻለ ይሆን ነበር?

መቼና ለምን ያህል ጊዜ ይምጣ?

አንዳንድ ሰባክያን በተለይ ወደ ውጭ ሀገር የሚመጡበት ጊዜ ብዙ ያልታቀደበትና የምዕመናንን የሥራ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆን ሌላው የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞ ችግር ነው። የቆይታ ጊዜ ጉዳይ ከሀገር ቤት ሐዋርያዊ ጉዞዎች ይልቅ በውጭ ሀገራት በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ትኩረትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖረው ምዕመን ሩጫ  (የሥራ ጫና) የበዛበት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ ሰው ያለው ጊዜ በጣም አነስተኛ ከመሆኑ አንጻር አብዛኛው ሰው ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄደው በሳምንት አንድ ጊዜ (እሁድ ለቅዳሴ) ነው፡፡ ለሰባክያኑ የሚሰጣቸው የየሀገራቱ የቪዛ ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ሰባክያኑ ያላቸው ጊዜና ለቆይታቸው የሚያስፈልገው ወጭም ከግምት ውስጥ ገብቶ በተጋበዙበት ሀገር መቆየት የሚችሉት ለተወሰነ ጊዜ (ለጥቂት ሳምንታት) ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች መምህሩ የሚመጣበት ጊዜ በጣም ታስቦበት እና ተመክሮበት ሊሆን ይገባል፡፡ መምህሩ የሚመጣበት ወቅት እንደየሀገሩ ሁኔታ ምዕመናን የተሻለ ጊዜ የሚያገኙበት (ለምሳሌ የዓመቱ መጨረሻ) ወይም በቤተክርስቲያን ታላላቅ አጽዋማት (ዐቢይ ጾም ወይም ፍልሰታ) ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ መምህሩ የሚመቸው ጊዜ ብቻ ተወስዶ ወይም ‘ሌሎች አጥቢያዎች መምህር ስላመጡ እኛም እናስመጣ’ ተብሎ በፉክክር የሚመጣ ከሆነ እንዲሁ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡

ማንንና እንዴት ያስተምር?

የተሰበከውን ምዕመን እየደጋገሙ መስበክ ክፋት ባይኖረውም ስብከት የበለጠ ለሚያስፈልገው መድረስ ግን የበለጠ ዋጋ ያስገኛል። የተለመደው የማስተማር ዘዴ በቤተክርስቲያን መድረክ እና በአዳራሽ መምህሩ አትሮኑስ ጀርባ ቆሞ፣ ምዕመናን ከፊቱ ካህናት ከኋላው/ከፊት ለፊት/ ተቀምጠው፣ መጠየቅ እና የሀሳብ መንሸራሸር የሌለበት፣ ሁሉም የሰማውን ‘አሜን እና እልል’ ብሎ የሚቀበልበት የአንድ አቅጣጫ  (one-directional) የትምህርት ፍሰት ነው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ መድረኮች የሚገኘው ምዕመን የዕድሜና የጾታ ስብጥሩ መሠረታዊ ትምህርትን ለማስተማር አያስደፍርም፡፡ የቋንቋም ሆነ የመረዳት ልዩነቶች በአደባባይ ባሉ መድረኮች አይስተናገዱም፡፡ በአጥቢያ ቤተክርስቲያናት በዕድሜ ሕፃናት፣ ታዳጊ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን ይገኛሉ፡፡ በጾታም ወንዶች፣ ሴቶችና ካህናት አሉ፡፡ በትምህርት ደረጃም እንዲሁ ጀማሪዎች፣ ማዕከላዊያንና የበሰሉት አሉ፡፡ በሥራ ሁኔታም ቢሆን ተማሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ጡረተኞች ይኖራሉ፡፡ በትዳርም እንዲሁ ያገቡና ልጆችን የሚያሳድጉ፣ ትዳር ለመመስረት የሚያስቡ፣ ዕድሜያቸው ለትዳር ያልደረሰ አሉ፡፡ በቋንቋም እንዲሁ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ… እንግሊዝኛ የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ እንደየደረጃቸው የተለያየ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የትምህርቱ አሰጣጥ ዘዴም እንዲሁ ሊለያይ ይገባል፡፡ በግል፣ በቡድን፣ በማኅበር፣ በአደባባይ፣ በቃል፣ በጽሑፍ የሚማር ይኖራል፡፡ እነዚህ ሁሉ የምዕመናን ክፍሎችና የማስተማሪያ ስልቶች እያሉ አንድ አይነት ስልት ለሁሉም (one size fits all) መጠቀም ውጤታማ አያደርግም፡፡ ስለዚህ ዘርፈ ብዙ የማስተማሪያ ዘዴዎችንና ጊዜያትን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከሌላ ሀገር/ቦታ የሚመጣውም መምህር እነዚህን ሊጠቀም ይገባዋል፡፡

ለቆይታው የሚያስፈልገው የት ይዘጋጅለት?

በውጭው ዓለም ለማስተማር ለአጭር ጊዜ የሚመጡ መምህራን በምዕመናን ቤት እንዲያርፉ ማድረግ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አልፎ አልፎም ሁሉ የተሟላለት ቤት (ሆቴል) የመከራየት ነገር ይታያል፡፡ ምዕመናንን እውነተኞቹን የቤተክርስቲያን መምህራንን ተቀብለው በቤታቸው በማስተናገዳቸው በረከትን ያገኛሉ፡፡ መምህሩም ቤተሰቡን ለማስተማር ዕድል ያገኛል፡፡ ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ ለሚቆዩ መምህራን በአንድ ምዕመን (ቤተሰብ) ቤት ብቻ መቆየት ምዕመኑ ላይ ጫና እንዳያሳድር፣ ለመምህሩም መሳቀቅን እንዳያመጣ አስቀድሞ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምዕመናኑ መምህራኑን በቤታቸው ተቀብለው የሚያስተናግዱት የሚያገኙትን ዋጋ አውቀውት፣ ተረድተውት፣ አምነውበትና በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ወስነውና ጠይቀው ሊሆን ይገባል እንጂ በጫና ባይሆን ይመረጣል፡፡

ለመምህሩ የሚሆን ማረፊያ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ማዘጋጀት ግን ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ ይህም በብዙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የተለመደ አሠራርና የቤተክርስቲያን ሥርዓትም ነው፡፡ ለዚህም አብያተ ክርስቲያናቱ የእንግዳ ማረፊያ ያዘጋጃሉ፡፡ ለአገልግሎት የመመጡ መምህራንም በዚያው ያርፋሉ፡፡ የመምህራኑ በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ መቆየት ምዕመናንም ባላቸው ጊዜ ሄደው እንዲጎበኟቸው፣ ትምህርት እንዲማሩና ምክር እንዲቀበሉ ያግዛል፡፡ መምህሩም ለማስተማርም ሆነ ለመምከር እንዲሁም ለጸሎት ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ለሆነ መምህር በቤተክርስቲያን ቅጥር ውስጥ ባለ ማረፊያ ውስጥ ማረፍ እውነተኛ እረፍትን ይሰጠዋል፡፡

ላበረከተው አገልግሎት ስንት ይከፈለው?

ይህ ጥያቄ ለብዙዎች “አዲስ ነገር” ሊሆን ይችላል ነገር ግን ለተጋባዥ መምህራን ገንዘብ መክፈል የተለመደ አሠራር ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ በዘመናችን ሰባኪ ማስመጣት በቤተክርስቲያን ላይ የሚፈጥረውን ጫና በባለፈው ጦማር አቅርበናል። ፍጹም የሚባለው የሐዋርያነት አገልግሎት እንደ ቅዱሳን ሐዋርያትና እነርሱን መስለው በየዘመናቱ ቤተክርስቲያንን ያለምድራዊ ዋጋ ያገለገሉ፣ በዚህም አብነታቸው “ዋኖቻችን” የሆኑት ታላላቅ ቅዱሳንን መምሰል ነው፡፡ ስለሆነም ይህን መሰሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ቢቻል ለራስ እየተጎዱ ለሌሎች ብርሃን መሆን፣ ባይቻል ግን ቢያንስ አላግባብ መበልጸግን (unjust enrichment) የሚያመጣ መሆን የለበትም፡፡ ለዚያ ነው ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ለአገልግሎት ሲልካቸው “ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ፡፡ በመቀነታችሁም ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐለቅ አትያዙ፡፡ ለመንገድም ስልቻ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ሁለት ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና፡፡” (ማቴ. 10፡8-10) በማለት ደቀመዛሙርቱን ያስጠነቀቀቃቸው፡፡ ስለሆነም ለወንጌል አገልግሎት የሚጣደፉ አገልጋዮች ቢችሉ ከመጓጓዣ፣ ምግብና መኝታ ውጭ ያለምንም ምድራዊ ክፍያ ቢያገለግሉ ዋጋቸው ታላቅ ነው፡፡ ይሁንና ገንዘብን ማዕከል ያደረገ የኑሮ ዘይቤ በገነነበት ዓለም አገልጋዮችም የእግዚአብሔርን ቃል ለገንዘብ ማግኛነትና ሰዎችን ለማስደሰት እስካልሸቀጡ ድረስ በግልጽ የሚታወቅ፣ ማጭበርበርና ማስመሰል የሌለበት፣ ምክንያታዊ የድካም ዋጋ ቢከፈላቸው የሚያስነቅፍ አይደለም፡፡

ቅዱስ ወንጌል “ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋል” የሚለው ይህን መሰሉን ወጭን የመሸፈን (cost replacement) አሠራር ብቻ ነው፡፡ ፍጹማን የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያትና እነርሱን መስለው በየዘመናቱ ቤተክርስቲያንን በማገልገል የከበሩ ቅዱሳን ግን ለአገልግሎት የሚሆናቸውን ወጭም በራሳቸው እየሸፈኑ የማንም ሸክም ሳይሆኑ ያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምዕመናን በላከው መልዕክቱ “እናንተ ከፍ ከፍ ትሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ አስተምሬአችኋለሁና፡፡ እናንተን አገለግል ዘንድ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት  ተቀብዬ ለምግቤ ያህል ወሰድሁ፤ ከእናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜም ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም፡፡ ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሟሉልኝ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ፤ ወደፊትም እጠነቀቃለሁ፡፡” (2ኛ ቆሮ. 11፡7-9) በማለት የተናገረው ቃል በየዘመኑ ለሚነሱ የወንጌል መመህራን ሁሉ መርህ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡

የመንፈሳዊ አገልግሎት ዋጋው በሰማይ የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሠረው” እንደተባለ ለጊዜውም ሆነ በዘላቂነት ለሚያስተምሩ መምህራን ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ተገቢ ነው፡፡ ይህም የየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑን የገንዘብ አቅምና የተሰጠውን አገልግሎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ቢጠበቅበትም ለምዕመናኑ ግልጽ የሆነ ተቋማዊ አሠራር ሊኖረው ይገባል፡፡ “አጥቢያዎች እንደቻሉ ይክፈሉ” ከተባለ እንደየሁኔታው የተለያየ መጠን እየከፈሉ መምህራኑ የተሻለ ለሚከፍላቸው ቅድሚያ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም ብዙ የመክፈል አቅም የሌላቸው አጥቢያዎች የሚፈልጉትን መምህር በሚፈልጉት ጊዜ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ በጥቂቶቹ ዘንድ እንደሚደረገውም የመምህሩ ክፍያ ባስገባው ገቢ (ፐርሰንት) ከሆነ መምህራኑ በነጻነት ከማስተማር ይልቅ “ምን ያህል ገቢ አስገባ ይሆን?” በሚል የሂሳብ ሥራ እንዲፈተኑ ይጋብዛል፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን በተለይ ወደ ውጭ ሀገር ለሚሰማሩ መምህራን ተገማችነት ያለው የክፍያ አሰራር መመሪያ ሊኖራት ይገባል፡፡

ይሁንና ይህ የክፍያ አሠራር ቤተክርስቲያንን እንደቀጣሪ ተቋም ተጠግተው ብዙ የሥራ እድል ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ በስንፍና የቤተክርስቲያንን ገንዘብ መውሰድን የሚያበረታታ መሆን የለበትም፡፡ አከፋፈሉም ከምዕመናን በተለየ ሁኔታ ካህናት ለአገልግሎት የሚያውሉትን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት እንጂ በሣምንት አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት እንደማንኛውም ምዕመን ወደ ቤተክርስቲያን መጥተው የሚቀድሱትን ወይም የሚያስተምሩትን ካህናት ሊያጠቃልል አይገባውም፡፡ አንዱ በአበል የሚቀድስ፣ የሚያስቀድስ ሌላው ያለ አበል የሚቀድስ፣ የሚያስቀድስበት አሠራር ምንደኞችን እንጂ እውነተኛ አገልጋዮችን አይጠቅምም፡፡ ስለሆነም አፈጻጸሙ እንደየሀገሩና ከተማው ሁኔታ፣ እንደ አጥቢያ ቤተክርስቲያኑ አሠራር፣ እንደ አገልጋዩ የአገልግሎት ትጋትና የገቢ ሁኔታ እየታየ ግልጽ በሆነ አሠራር ሊተገበር ይገባል እንጂ የቤተክርስቲያን አገልግሎት የግለሰቦች መሸላለሚያና ሥጋዊ ጥቅም ማካበቻ መሆን የለበትም፡፡

ሰባኪ በመምጣቱ ምን ለውጥ መጣ?

በአንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ብዙ ሰባክያን መጥተው ሰብከዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ሀብትም የምዕመናኑ ዕንቁ ጊዜም ለዚህ አገልግሎት ውሏል፡፡ ነገር ግን (የሕይወት ለውጥ ጊዜ የሚወስድና ለመለካት የሚያስቸግር ቢሆንም) “ይህ በመደረጉ ምን ለውጥ መጣ?” የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ምን ያህል አዳዲስ ምዕመናን ወደ ቤተክርስቲያን መጡ? ይመጡ ከነበሩት ውስጥ ምን ያህሉ ለንስሐና ለቅዱስ ቁርባን በቁ? ከተማሩት/ከሰለጠኑት ውስጥ ምን ያህሉ ወደ አገልግሎት ተሰማሩ? የምዕመናን ሱታፌ በምን ያህል ተሻሻለ? የተገኘው ለውጥ ከተፈጸመው አገልግሎትና ከፈሰሰው ገንዘብ አንጻር እንዴት ይታያል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ መምህራንን ከሩቅ ሀገር ማስመጣትም ያለውን የመምህራን ችግር ለጊዜው ማስታገሻ መድኃኒት እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ተደርጎ መወሰድም የለበትም፡፡ በቂ ስልጠና ያላቸው መምህራንን በቋሚነት እንዲያገለግሉ ማድረግ ያስፈልጋል እንጂ በየጊዜው ብዙ ወጭ በማውጣት ለአጭር ጊዜ ብቻ መምህራንን እያፈራረቁ ማስመጣት ዘላቂ ለውጥን አያመጣም፡፡

በአጠቃላይ ሰባኪ ለማስመጣት ሲታሰብ አስቀድሞ ‘ሰባኪ ማምጣት ለምን አስፈለገ? ያሉትን ሰባክያን በሚገባ ተጠቅመናል ወይ? ሰባኪ ለማምጣት ለሚወጣው ወጪ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት አለ ወይ? ሰባኪው በቆይታው የሚያስተምረው ትምህርት ትኩረት ምን ላይ ይሆናል? ስብከቱስ በምዕመናን ክርስቲያናዊ ሕይወት ዙሪያስ ምን አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል?’ የሚሉትን ጥያቄዎች በሚገባ መመለስ ይገባል። የማስመጣቱ ሀሳብም ሲታመንበት ሰባቱን የትግበራ መርሆች መጠቀም ይበጃል። በተጨማሪም ለወንጌል አገልግሎት የተጠራ ሰባኪ ሙሉ ትኩረቱን ስብከት ላይ እንዲያደርግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። የስብከት ቦታውም የቤተክርስቲያን ዐውደ ምህረት እንጂ (የተለየ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር) ተራ አዳራሽ መሆን የለበትም። ሐዋርያዊ አገልግሎቱ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የጠነቀቀ፣ ሥርዓቷን የጠበቀ፣ ትውፊቷንም የዋጀ እንዲሆን ሁሉም ምዕመን የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ማድረግ ያስፈልጋል። በመጨረሻም ሰባኪ በመምጣቱ የመጣውን ለውጥ በተቋም ደረጃ በየጊዜው መመዘን ያስፈልጋል እንላለን። †

ሰባኪ ማስመጣት: የዘመናችን ሐዋርያዊ ጉዞና ዓለማዊ ጓዙ

መግቢያ

ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከምትታወቅባቸው ጸጋን የሚያሰጡ አገልግሎቶች አንዱ በቃለ እግዚአብሔር እጦት ለተራቡት ምዕመናን እየተዘዋወሩ የክርስቶስን ወንጌለ መንግስት በማስተማር አዳዲስ ምዕመናንን ማፍራት፣ እንዲሁም ያሉትን ምዕመናን በምግባርና በሃይማኖት እንዲጸኑ የማድረግ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በዘመናችን ሐዋርያትን አብነት ያደረጉ ተዘዋውሮ የማስተማር አገልግሎቶችንና መልካም ማሳ የሆነውን አገልግሎት በሂደት እየወረሩ የመጡትን አረም የሆኑ ክፉ ልማዶች እንዳስሳለን። በቀጣይ በምናወጣው ክፍል ደግሞ የመፍትሔ ሀሳቦችን እንጠቁማለን፡፡

የሐዋርያዊ ጉዞ አስፈላጊነት

ሐዋርያ ማለት “ሖረ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም ዞሮ ማስተማርን የሚገልጽ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀመዛሙርቱን “ሑሩ ወመሐሩ” (እየዞራችሁ አስተምሩ) ብሎ እንደላካቸው ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል፡፡ (ማቴ. 28፡18) ስለሆነም ከቀደሙት ሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ ወንጌልን ማስተማር ትልቅ ዋጋ ያለው፣ መንፈሳዊ በረከት የሚታፈስበት መንፈሳዊ አገልግሎት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና አርድዕት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡ በእነርሱ እግር የተተኩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም እንዲሁ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተዘዋውረው ወንጌልን አስተምረው፣ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት እንዲሰፋ አድርገው፣ ብዙዎችን ወደ ጽድቅ መንገድ መልሰዋል፡፡

ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን፣ ሐዲስ ሐዋርያ የተባሉት አቡነ ተክለሃይማኖትና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው የሆኑ አያሌ ሊቃውንት፣ መነኮሳትና ባህታውያንም እንዲሁ በሀገራች በኢትዮጵያና በአካባቢዋ በየቦታው ዞረው አስተምረዋል፡፡ ይህም ከአገልግሎቶች ሁሉ የከበረ ዋጋ ያለውና ቅዱሳን እንደ ጧፍ ለሌሎች እያበሩ ያለፉበት የጽድቅ መንገድ ነው፡፡ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ “መልካሙን የምስራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?” (ሮሜ 10፡15) ብሏል፡፡ ይህ ዞሮ የማስተማር አገልግሎት በእኛም ዘመን በተወሰነ መልኩም ቢሆን እየተፈጸመ ይገኛል፡፡

ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ጠረፋማ አካባቢዎች

በሀገራችን በኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎች ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች ትምህርተ ወንጌልን የሚያስተምራቸው፣ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን የሚፈጽምላቸው አገልጋይ በማጣት ይቸገራሉ፡፡ በተለይም የአማርኛ ቋንቋን ለመግባቢያነት የማይጠቀሙ ምዕመናን ባሉባቸው አካባቢዎች ችግሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በርካታ ምዕመናንም በቋንቋቸው የሚያስተምራቸው፣ የሚያጸናቸው አገልጋይ በማጣት በነጣቂ ተኩላ በተመሰሉ መናፍቃን ሲወሰዱ ይታያል፡፡ በአንጻሩ በታላላቅ ከተሞችና ሌሎች የአብነት ትምህርት የተስፋፋባቸው የሀገራችን አካባቢዎች በአንድ ደብር እጅግ በርካታ አገልጋዮች “ያለ በቂ አገልግሎት” ሲባክኑ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ቅዱስ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ነገረ ምጽዋትን በሚያስረዳበት አንቀጽ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ምጽዓት ለጻድቃንም ለኃጥአንም “ተርቤ አብልታችሁኛልን?” (ማቴ. 25፡35 እና 42) የሚል ጥያቄ እንደሚያቀርብላቸው ይነግረናል፡፡ የቤተክርስቲያን መተርጉማን እንደሚያስተምሩት ጌታችን “ተርቤ አብልታችሁኛልን?” በማለት እያንዳንዳችንን (በተለይም የወንጌልን አገልግሎት የማዳረስ ግዴታ ያለባቸው መምህራንን) የሚጠይቀው ለቁመተ ሥጋ የሚሆን ምጽዋት ብቻ ሳይሆን ለነፍስ ድኅነት የሚሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ማቅረብን ይመለከታል፡፡ ስለሆነም ትምህርተ ሃይማኖትን የሚያስተምሩ ሁሉ ለጠገበው ለማጉረስ ከመሽቀዳደም ለተራበው ቢደርሱ አገልግሎታቸው የጽድቅ ምጽዋት ይሆንላቸዋል፡፡

ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ዝርወት ዓለም

ከቅርብ ዘመን ወዲህ በቁጥር በርከት ያሉ የቤተክርስቲያናችን ምዕመናን በዝርወት (በውጭው) ዓለም መኖራቸው የአጥቢያ አብያተክርስቲያናት ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ በውጭ ሀገር ያለ የቤተክርስቲያን አገልግሎት በብዙ መልኩ ከሀገር ቤቱ የተለየ ገጽታ አለው፡፡ በቁጥር ቀላል የማይባሉት በውጭ ሀገር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በቂ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አገልጋዮች የሏቸውም፡፡ ከዚያም ባሻገር ከአንዱ ደብር ወደሌላው በመሄድ ለማገልገል የሚመች ከባቢ የለም፡፡ በተለይም አብያተ ክርስቲያናት ቋንቋና ፖለቲካዊ እይታን ወይም የተወሰኑ ግለሰቦችን ማኅበራዊ ትስስር ታሳቢ ባደረጉ መቧደኖች በተመሠረቱባቸው ቦታዎች አልፎ አልፎ በንግስ በዓላት ከሚታይ የአንድነት አገልግሎት በቀር አንዱ የአንዱን ክፍተት የሚሞሉበት አሠራርም ሆነ ልማድ አይስተዋልም፡፡ ሁሉም በሩን ዘግቶ የየራሱን ‘አገልግሎት’ ለመፈጸም መሯሯጥና እርስ በርስ በቅናትና በፉክክር መንፈስ መተያየት የተለመደ “የአገልግሎት” ገጽታ የሆነባቸው ቦታዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

ከዚያም ባሻገር በውጭ ሀገራት ያሉ አጥቢያዎች ከቤተክርስቲያንነት ይልቅ (ባሻገር) ማኅበራዊ መገናኛዎችና የባህልና ፖለቲካ አቋም ማንጸባረቂያ መድረኮች ሲሆኑም ይስተዋላል፡፡ የትክክለኛ አገልግሎት መመዘኛ መስፈርቱም ክርስቲያናዊ መንፈሳዊነትን ከመከተል ይልቅ “የእኛ ወገን ነው ወይስ የእነርሱ ወገን?” የሚል ስሁት መመዘኛ የሆነባቸው ቦታዎች ቀላል የማይባል ቁጥር አላቸው፡፡ ይህ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምልከታን ለአገልግሎት መመዘኛነት የሚያይ መለካዊ አስተሳሰብ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ስም በሚጠሩ አጥቢያዎች በብዙ አላዋቂዎች ድጋፍና አርቆ ማስተዋል አለመቻል መስፈኑ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አንድነት በመሸርሸር የአገልግሎቷን ተደራሽነት በእጅጉ ሲገድበው ይታያል፡፡

በአጭሩ ከአገልጋይ እጥረትም ሆነ በየአጥቢያው ያሉትን አገልጋዮች መዋዋስን የማያበረታታ (የሚያደናቅፍ) አሰራር ከመስፈኑ የተነሳ በብዙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ምዕመናን የሚገባውን ቃለ እግዚአብሔር በተገቢው መልኩ ሲያገኙ አይስተዋልም፡፡ ስለሆነም በውጭ ሀገር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ያሉባቸውን የአገልግሎት ክፍተቶች ለመሙላትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች መምህራንና ዘማርያንን ከኢትዮጵያ (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከልዩ ልዩ የውጭ ሀገራት) ማስመጣት የተለመደ አማራጭ ሆኗል፡፡ ከሀገራቸው ርቀው፣ የቤተክርስቲያንን ጣዕም ናፍቀው ለሚጠባበቁ ሁሉ የእውነተኛ መምህራን በቅርብ መገኘት ለጽድቅ የሚገባውን ፍሬ እንዲያፈሩ ያስችላቸዋልና በአግባቡ የሚፈጸም ተዘዋውሮ የማስተማር አገልግሎት ለሰጭውም ለተቀባዩም ድርብርብ ጸጋን የሚያሰጥ ነው፡፡

ከሐዋርያዊ ጉዞ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች

ከሚያገለግሉት አገልጋዮች አንጻር ስንመለከተው ተዘዋውሮ የማስተማር አገልግሎት እጅግ ታላቅ የሆነውን የቅዱሳን ሐዋርያትን በረከት የሚያሰጥ፣ የምጽዋትን ግዴታ የሚወጡበት አገልግሎት ነው፡፡ ምጽዋትን የሚሰጥ መንፈሳዊ ዋጋ ለማግኘት እንጂ ከምጽዋቱ የተነሳ ምድራዊ ክብርና ጥቅምን ለማግኘት ሊያደርገው አይገባም፡፡ አገልግሎቱን ከሚፈልጉት አጥቢያ አብያተክርስቲያናት አኳያ ስንመለከተው ደግሞ አዳዲስ ምዕመናንን የሚያፈሩበት፣ የተበተኑትን የሚሰበስቡበት፣ ያሉትን በእምነትም በምግባርም የሚያጸኑበት የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተልዕኮ የሚፈጸምበት አገልግሎት ነው፡፡ ይሁንና ይህን መሰሉ አገልግሎት ወንጌልን መነገጃ፣ አገልግሎትን ኪስ መሙያ ባደረጉ ምንደኛ “አገልጋዮች” እና የጥቅም አጋሮቻቸው የተነሳ መስመሩን እየሳተ ለጽድቅ መዋል የነበረበት አገልግሎት ግልጽ በሆነ መልኩ የንግድና የጥቅም ትስስር መገለጫ እየሆነ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ችግር በአሁኑ ወቅት ለሚያስተውል ሁሉ የተገለጠ ቢሆንም ብዙዎች የችግሩን መነሻና ማሳያዎች ስለማይረዱ ባለማወቅም ሆነ በምንግዴ ተባባሪነት ምንደኞችንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን በሚያስደስት፣ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ግን እንደ ሸቀጥ እንዲቆጠር በሚያደርግ አሳፋሪ አሰራር ተሳታፊ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ዋጋ የሚገኝበትን አገልግሎት ፍርድ በሚያመጣ፣ ጌታችንን በሚያስቆጣ ድፍረት እንዲለወጥ ከሚያደርጉት ስሁት አሰራሮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የቅርቡን እያራቁ የሩቁን መናፈቅ

የቤተክርስቲያንን ገንዘብ አውጥቶ መምህራንን ማስመጣት በራሱ መንፈሳዊ ግብ አይደለም፡፡ በየሀገረ ስብከቱ ያሉ አብያተክርስቲያናትም ራቅ ካለ ስፍራ መምህር ለማስመጣት ከመወሰናቸው በፊት በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ያሉትን ሊቃውንትና ሌሎች ተተኪ መምህራን በአግባቡ መጠቀማቸውን መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡ በቅርብ ያለውን እያራቁ በሩቅ ያለውን መናፈቅ ጤናማ ያልሆነ አገልግሎት ማሳያ ነው፡፡ በተለይም የሊቃውንት መፍለቂያ በሆኑ የሀገራችን ከተሞች እውነተኛውን ትምህርት የሚያስተምሩትን በአጠገባቸው ያሉ ሊቃውንት ትተው “ከአዲስ አበባ የሚመጡ” የሚባሉ ወንጌልን እንደ ንግድ የያዙ “መምህራንን” በብዙ ወጭ ማምጣት ቤተክርስቲያንን ሁለት ጊዜ መውጋት ነው፡፡

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት የሚከተለውን እውነተኛ ታሪክ እናቅርብ፡- በአንዲት የሰሜን ኢትዮጵያ ከተማ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀታቸው የሚታወቁ በርካታ ሊቃውንት ያሉባቸው ጉባኤ ቤቶች አሉ፡፡ ይሁንና ከቤተክርስቲያን ገቢ ማነስና ከአስተዳደሩ ብልሹነት የተነሳ 2,000 ብር በወር የሚከፈላቸው ሊቃውንት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይሁንና በከተማዋ የተሰባሰቡ ወጣቶች ጉባኤ አዘጋጅተው እንደ ዘመኑ ነፋስ ፌስቡክና ዩቲዩብ የሚያውቃቸውን “ከአዲስ አበባ የሚመጣ” መምህር ማምጣት አለብን አሉ፡፡ ያን መምህር ለሁለት ቀናት ጉባኤ ለማስመጣት (በአውሮፕላን ካልሆነ አይመጣም) በወቅቱ ዋጋ ከ3,000 ብር በላይ የአውሮፕላን ቲኬት፣ ከ500 ብር በላይ ለአልጋና ምግብ ወጪ እንዲሁም ለምንደኛው መምህር 15,000 ብር የኪስ ገንዘብ ይከፍሉታል፡፡ ይሄ ሁሉ ወጭ የወጣበት መምህር መጥቶ የረባ ትምህርት ሳያስተምር ከብዙ ቀልድና ጨዋታ ጋር የተሰበሰበውን ወጣት በስሜት አስጨብጭቦ፣ ለራሱ ለማስታወቂያ የሚሆነውን ቪዲዮ ይዞ ይመለሳል፡፡ የሚያሳዝነው እነዚሁ ወጣቶች ጉባኤውን ለማዘጋጀት መግፍኤ ከሆኗቸው ምክንያች አንዱ “የቤተክርስቲያን ሊቃውንት መጥፋትና መሰደድ አሳስቧቸው” ነው፡፡ ነገር ግን ለሚያስተውል ሰው እነርሱ ካደረጉት ተግባር በላይ ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ፣ ሊቃውንቷን የሚያሳንስ ተግባር የለም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በብዙ የውጭ ሀገራት በሚገኙ ሀገረ ስብከቶችና አብያተ ክርስቲያናት ያለ ምንም ወጪ የቤተክርስቲያንን ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን እያሉ በእውቀት ከእነርሱ በእጅጉ ያነሱ መምህራንን ብዙ ወጭ በማውጣት ከሌላ ቦታ ያስመጣሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች እንደታየውም ቀደም ባሉ ዓመታት ተጋባዥ መምህራን እየሆኑ በሚሄዱባቸው ሀገራት በልዩ ልዩ መልኩ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው መኖር ሲጀምሩ “ለንግድ ስለማይመቹ” አብያተ ክርስቲያናቱ እነርሱን በመተው ሌሎችን ማስመጣት ይቀጥላሉ፡፡ ይህ የቅርቡን እየናቁ የሩቁን የመናፈቅ አባዜ የሚያሳየን ነገር ቢኖር በእነዚህ ዘንድ “መምህራንና ዘማርያን ማስመጣት” የሚባለው ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት በመጨነቅ የሚደረግ ሳይሆን መንፈሳዊ ላልሆነ ዓላማ ወይም መንፈሳዊ ነው ተብሎ የሚታሰብን ዓላማ በገንዘብ ለመደገፍ የሚደረግ የገቢ ማስገኛ ስልት (fund raising strategy) ነው፡፡

አገልግሎትን ከገንዘብ ጋር መቀላቀል

መንፈሳዊ አገልግሎት ንግድ መሆን የለበትም፡፡ መምህራንን የሚያስመጡ አጥቢያዎችም አገልግሎቱን ገንዘብ ከመሰብሰብ ጋር ሊያገናኙት አይገባም፡፡ ምንም እንኳ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ቢታወቅም ገንዘብን መሰብሰብ በግልጽ በሚደረግ ጥረት እንጂ በማስመሰል በሚደረግ፣ መንፈሳዊ ዋጋን በሚያሳጣ መልኩ መፈጸም የለበትም፡፡ በብዙ ቦታዎች መምህራንን የማስመጣት ነገር “ከገቢ ማስገኛ” መንገዶች አንዱ (ቀዳሚው) ተደርጎ ይታሰባል፤ በተግባርም ይታያል፡፡ ለማስተማር የሚመጡ ሰዎች የሚመረጡትም ያላቸውን ታዋቂነት በመጠቀም ወይም በደላላ አሰራር ገንዘብ መሰብሰብ የሚችሉ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በተለያየ ቦታ እየተዘዋወሩ ከሚያስተምሩ መምህራንም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ምንደኞች አሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች “አገልግሎቱ” ኑሯቸውን የሚገፉበት የስምሪት መድረክ እንጂ ለመንፈሳዊ ዋጋ የሚደረግ ሱታፌ አይደለም፡፡

ስለሆነም የየራሳቸውን ደላሎች በየቦታው በማሰማራት፣ “ለአገልግሎት” በሚሄዱባቸው ቦታዎችም በድለላቸውና በማጭበርበራቸው ከምዕመናን ከሚሰበስቡት ገንዘብ በፐርሰንት እየተደራደሩ፣ ካልሆነም ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ተጽዕኖ እየፈጠሩ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት ይሰራሉ፡፡ ገንዘብ ማግኘትን ቀጥተኛ ዓላማ ያደረጉ መንፈሳዊ ስራዎች ፈር ለመሳት ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡ ይህ አገልግሎትን ከገንዘብ ጋር የመቀላቀል አሠራርም ከቀጥተኛ መንፈሳዊ ኪሳራነቱ ባሻገር ሐዋርያዊ ሊሆን የሚገባውን ዞሮ የማስተማር አገልግሎት በብዙ መልኩ ያጎድፈዋል፡፡ አገልግሎት ከገንዘብ ጋር ሲቀላቀል የሚያገለግሉት ሰዎችም አገልግሎታቸው የገቢ ምንጫቸው እንጂ የእምነታቸው ፍሬ አይሆንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል?” (ሮሜ. 10፡14) በማለት የጠየቀው የእግዚአብሔርን ስምና ቅዱስ ቃሉን እንደ አማኝ ሳይሆን እንደቅጥረኛ ባለሙያ የሚናገሩትን ይመለከታል፡፡

ከአብያተክርስቲያናት አስተዳደር ጋር በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መልኩ የሚደረጉ “የገንዘብ ድርድሮች” አገልግሎቱን ቁሳዊ ሲያደርጉት ይታያል፡፡ አንዳንዶቹም በድለላቸውና ምዕመናንን በስሜት በማነሳሳት የሚሰበስቡትን መንፈሳዊ ዋጋ የሌለው የገንዘብ መጠን እየጠቀሱ “ካስገባነው ገቢ አንፃር በኮሚሽን መልኩ ይከፈለን” በማለት እስከመከራከር መድረሳቸው አገልግሎቱ ምን ያክል መስመር እየሳተ እንደመጣ በግልጽ ያሳያል፡፡ ከዚያም ባሻገር ለአገልግሎት ተብለው የሚመጡ መምህራን በልዩ ልዩ መንገድ ሌሎች ንግዶችን ሲያካሂዱ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ያክል አንዳንዶቹ በውጭ ሀገራት ለአገልግሎት በሚመጡበት ጊዜ የመዝሙርም ሆነ የስብከት ካሴታቸውን የቅጅ መብት ከሰጡት አሳታሚ በመደበቅ (በመስረቅ) ወደ ሲዲዎች እንዲገለበጥ ካደረጉ በኋላ የኦሪጂናሉን ስቲከር በመለጠፍ በኦሪጅናል ዋጋ ምዕመናንን “ለበረከት ውሰዱ” በማለት ይነግዳሉ፡፡ ሌሎችም ከምዕመናን በልዩ ልዩ መንገድ በግል ገንዘብ በመቀበል አገልግሎታቸውን ዋጋ ያሳጡታል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ መምህር በአውደ ምህረት “ኢትዮጵያ ሄጄ የማገለግልበት መኪና ብትገዙልኝ ምን አለበት?…ለአገልግሎት እስከሆነ ድረስ አውሮፕላንም እንግዛ ብንል ልታግዙን ይገባል፡፡” በማለት የተናገረውን እንደማሳያ መውሰድ እንችላለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት “መምህራን” ወንጌልን መነገጃ የሚያደርጉ፣ ምዕመናንም የእነርሱን የማይጠግብ ኪስ ለመሙላት የተፈጠሩ የሚመስላቸው ስለሆኑ እንጂ እውነት ስለ አገልግሎት ብለው አይደለም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ምንደኛ ጌታችን በወንጌል “ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ፡፡ በመቀነታችሁም ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐለቅ አትያዙ፡፡ ለመንገድም ስልቻ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ጫማ፣ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና፡፡” (ማቴ. 10፡8-10) ያለውን የሚተረጉምበትን፣ የሚያስተምርበትን ያልተበረዘ ቅዱስ መንፈስ ከወዴት ያገኛል? ይህን ጥቅስ አንስተው “ሲያስተምሩ” (ንግዳቸውን በአመክንዮ ሲደግፉ) እንኳን የመጀመሪያዎቹን ንባባት ትተው “ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋል” የሚለውን እየደጋገሙ የጌታን ቃል ለነውራቸው መሸፈኛ ያደርጉታል፡፡ ጌታችን እንዳለ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም፡፡” (ማቴ. 6፡24) የሚያሳዝነው በምንደኞቹ ምክንያት ደገኛው አገልግሎት መናቁና መፈረጁ ነው፡፡ በአንጻሩ በዘመናችን በእውነት ለመንፈሳዊ ዓላማ የግል ጥቅማቸውን እየተው፣ ራሳቸውን እየጎዱ የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለው በየጠረፉ፣ የተረሱ ምዕመናን ባሉበት ሁሉ የሚያገለግሉ መምህራን ከአጭበርባሪዎቹ የተነሳ “ከኑግ ጋር እንደተገኘ ሰሊጥ” ለትችትና ነቀፋ መጋለጣቸው ያሳዝናል፡፡ ይሁንና መንፈሳዊ አገልጋይ በስህተትም ሆነ በእውቀት የሚፈጠሩ መሰረት አልባ ትችቶች ለአገልግሎቱ ማትጊያ መንፈሳዊ ዋጋዎች ይሆኑታል እንጂ ማደናቀፊያ አይደሉም፡፡

“መምህራንን ተጠቅመን ‘ገቢ ብናስገኝ’ ምን አለበት?” 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በብዙዎች ዘንድ አገልግሎትን ለገንዘብ ማስገኛነት የማመቻቸት ክፉ ልምምድ ቢያንስ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ አገልግሎቱን ለንግድ የሚያውሉት ሰዎችም ሌሎች ማስመሰያዎችን እየፈጠሩ ይናገራሉ እንጂ በግልጽ ገንዘብ የማስገኘት ዓላማን የሚያነብር (legitimize የሚያደርግ) አመክንዮ ማቅረብ አልተለመደም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ነውሩ ሥር እየሰደደ መንፈሳዊነት የጎደለውን አመክንዮ ያለማፈር በአውደ ምሕረት የሚያብራሩ ምንደኞች በዝተዋል፡፡

ለመሆኑ መምህራንና ዘማርያንን ተጠቅሞ ገንዘብ የሚገኝበት መንገድ ለምዕመናን መንፈሳዊ ህይወት ያለው አንድምታስ ምንድን ነው? ምዕመናን ለቤተክርስቲያን አስተዋጽኦ ማድረግ ግዴታችን ቢሆንም አሥራታችንን የምናወጣው ሕገ እግዚአብሔርን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ጠብቀን መሆን አለበት፡፡ ሰው በስጦታው ዋጋ የሚያገኝበት አምኖበት ሲሰጥ እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ፣ ሰው ይይልኝ ብሎ፣ ‘ታዋቂ’ በሚባሉ በሰባኪነት ስም ድለላን ሙያ አድርገው በያዙ ሰዎች የሽንገላ ምርቃትን ለመቀበል መሆን የለበትም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም፡፡ ምጽዋታችሁንም በምታደርጉበት ጊዜ ግብዞች በሰዎች ዘንድ ሊመሰገኑ በምኩራብና በአውራ ጎዳና እንደሚያደርጉት በፊታችሁ መለከት አታስነፉ፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡” (ማቴ. 6፡1-2)

በቁማር የሚገኝ ዕጣ ለማግኘት ሲል ገንዘብ የሚሰጥ፣ ስሙ ስለተጠራና ስለተጨበጨበለት ገንዘብ የሚሰጥ፣ የምንደኛ ደላሎችን የአደባባይ ምርቃት ፈልጎ ገንዘብ የሚሰጥ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በምድር ዋጋውን ስለተቀበለ ሰማያዊ በረከትን አያገኝም፡፡ ይሁንና ምዕመናን ይህን የእግዚአብሔር ቃል በሚገባ እንዳይረዱ ተግተው የሚሠሩ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ለቤተክርስቲያን ገንዘብ መስጠት የሚገባው እልልታና ጭብጨባ ባለበት ሰዓት እንደሆነ የሚያስቡ ይመስላል፡፡ ጌታችን በወንጌል “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግስተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም አትገቡም፤ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክሉአቸዋላችሁ፡፡” (ማቴ. 23፡14) ያላቸው እነዚህን ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን ገቢ ከማሳደግ አኳያ የመምህራነ ወንጌል ድርሻ ድለላና ማጭበርበር ሳይሆን ምዕመናንን በሚገባ ማስተማርና ዋጋ የሚያገኙበትን የጽድቅ ስጦታ እንዲሰጡ መምከር እንጂ የሀሰትን አሰራር ማባዛትና ራሳቸውን እንደ ታዋቂ ሰው (celebrity) ለሽያጭ በማቅረብ የምንደኞችን ካዝና መሙላት፣ የምዕመናንንም ስጦታ መንፈሳዊ ዋጋ ማሳጣት አይደለም፡፡

ሰባክያን የሚመረጡበት መስፈርት ብልሹነት

በዘመናችን ለሐዋርያዊ ጉዞ ሰባክያን የሚመረጡበት መስፈርት ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ በእውቀታቸውና በማስተማር ብቃታቸው ከሚመረጡት ይልቅ በፌስቡክና ዩቲዩብ ባላቸው ታዋቂነት፣ ገንዘብ ለመሰብሰብ ባላቸው የድለላ ችሎታ፣ የሚገባቸውንም የማይገባቸውንም ቀሚስና ቆብ ለማሳመር በሚያደርጉት መኩነስነስ፣ በዘርና ፖለቲካዊ ቡድንተኝነት እንዲሁም በመሳሰሉት ሥጋዊ መመዘኛዎች የሚመረጡት ይበዛሉ፡፡ ሌሎችም አገልግሎቱ ከሚሰጥበት ቦታ ካሉ ሰዎች ጋር (በተለይም ከካህናትና ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አካላት ጋር) ባላቸው ግላዊ ግንኙነት ይመረጣሉ፡፡ ለዚህም ብለው በየአጥቢያ አብያተክርስቲያናት “ተጽዕኖ ፈጣሪ” ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች በአውደ ምህረት የሚሸነግሉ፣ በልዩ ልዩ መንገድ የተጋነነ ግለሰባዊ የስብዕና ግንባታ (personality cult) ለመፍጠር የሚሽቀዳደሙ አሉ፡፡

አብያተክርስቲያናት ከመንፈሳዊ መስፈርት በወጣ መልኩ ሰባክያንን መምረጣቸው በጎ ምግባር የነበራቸው ሰባክያን ሳይቀሩ “የአገልግሎቱን እድል” ለማግኘት ሲሉ በድለላ፣ በማስመሰል አለባበስ እንዲሁም በመሳሰሉት ዋነኞቹን ምንደኞች ለመምሰል ሲሽቀዳደሙ ማየት ልብን ይሰብራል፡፡ አንዳንድ ሰባክያን ለአገልግሎት ከመጡ ተመልሰው የሚጠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ብዙ መንፈሳዊ ያልሆኑ አሠራሮች ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተመልሰው መጠራት የማይችሉ ከሆነም በግልጽም በስውርም የራሳቸውን ጓደኞች ወይም የሥጋ ዘመዶቻቸውን በቀጣይ እንዲጠሩ መደላድል ይፈጥራሉ፡፡ ይህም አገልግሎቱን ፍፁም ቁሳዊና ለብልሹ አሠራር የተመቸ ያደርገዋል፡፡ ይህ ችግር በብዛት የሚስተዋለው ጥቅም በሚበዛበት የታላላቅ ከተሞች ወይም የውጭ ሀገራት አገልግሎት ላይ ነው፡፡ መከራ ባለበት አገልግሎትማ ማን ይሽቀዳደማል!?

ሰባክያን ራሳቸውን በሁሉ ጉዳይ ሊቅ አድርገው የማቅረብ ችግር

ሰባክያን ለሚመረጡበት ስሁት መንገድ ለማገዝ ሰባክያኑን ሁሉን የሚያውቁ አስመስሎ በማጋነን ማስታወቂያ መስራት እየተለመደ ነው፡፡ ትሁት አገልጋይ እንኳ ቢሆን ራሳቸውን እንደ “አስመጭና ላኪ” የሚቆጥሩት አካላት ለንግዳቸው ስለሚፈልጉት አቀራረቡን ለማስተካከል ይከብዳል፡፡ አንዳንዶቹ ሰባክያንም ትዕቢቱ ስለሚጋባባቸው ራሳቸውን በሁሉ ጉዳይ ሊቅ አድርገው በማቅረብ በማያውቁት እየተለኩ ይወድቃሉ፡፡ አንድ መምህር በአውደ ምህረት ስለቆመ ብቻ ራሱን የባህልም፣ የኮሜዲም፣ የፖለቲካም፣ የስነ ልቦናም፣ የጤናም፣ የመሳሰለውም ባለሙያ አስመስሎ ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር በማይገናኙ ጉዳዮች ሳይቀር ትዝብት ላይ የሚጥሉ ረብ የለሽ አስተያየቶችን ሲሰጥ ያሳቅቃል፡፡ ከሚያስተምሩት ምዕመን መካከል እነርሱ ባለማወቅ የሚናገሩበትን ሙያ የሚያውቁ ሰዎች እንዳሉ እንኳ አያስተውሉም፡፡ በዚህም ራሳቸውን ያስገምታሉ፣ ቤተክርስቲያንንም ያሰድባሉ፡፡ ከዓለማዊ ጉዳዮች ባሻገር በመንፈሳዊ ትምህርትም አንድ መምህር ሁሉን ሊያውቅ አይችልም፡፡ የማያውቁትን ሲጠየቁ በጥበብ ከማለፍ ይልቅ በሞኝነትና በድፍረት ያልተረዱትን የሚናገሩ ሲበዙ እናስተውላለን፡፡ የዚህም ምክንያቱ ራስን በሁሉ ጉዳይ ሊቅ አድርጎ የማቅረብ ችግር ነው፡፡

በአገልግሎት ሰበብ ግላዊ ወይም ቡድናዊ ዓላማን ማስፈጸም

የቤተክርስቲያን አገልግሎት በጥቅመኞች፣ እንዲሁም በዘርና በፖለቲካ እይታ ቡድናዊ ስሜትን ፈጥረው ቤተክርስቲያንን በሚያውኩ ሰዎች እጅ በሚወድቅበት ጊዜ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ መንፈሳዊውን አገልግሎት የሚወዱትን ለማመስገን፣ የሚጠሉትን ለመርገም ማዋል ነው፡፡ ይህ ችግር በውጭ ሀገራት በሚገኙ አጥቢያዎች ይበልጥ ይስተዋላል፡፡ ለማስተማር የሚመጡትን መምህራን በጥቅም በመደለል ወይም የተሳሳተና የተዛባ መረጃ በመስጠት የተወሰኑ ሰዎችን ሀሳብ ብቻ እንዲይዙ ያደርጓቸዋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳቸው መምህራኑ በትርፍ ጊዜያቸው ከማን ጋር መገናኘት እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸውም ጭምር የሚከታተሏቸው ሰዎች ይመድባሉ፡፡ በውለታና በጥቅማጥቅም በመደለል፣ ወይም የተጣመመ ‘መረጃ’ (deliberately twisted information) በመስጠት የሚፈልጉትን ሀሳብ ይጭኑባቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ የስብከቱና የትምህርቱ አቅጣጫ ሰዎችን ለመንግስተ ሰማያት ለማብቃት ሳይሆን እንዲወደሱ የሚፈልጓቸውን በውዳሴ ከንቱ በመሸንገል፣ እንዲሰደቡ የሚፈልጓቸውን ደግሞ ያለስማቸው ስም በመስጠት እንዲሁም በግልጽ በመሳደብ እንዲበላሽ ያደርጋሉ፡፡ ቡድናዊ ስሜት ያላቸው ሰዎች መምህራንን በማስመጣትና በመደለል ወይም በማታለል የግለሰቦች ወይም አምባገነናዊ አስተዳደሮች ማኅበራዊ ቅቡልነት መገንቢያ አድርገው ይወስዷቸዋል፡፡ በዝና የሚታወቁ መምህራንን ከሚያስቀድሙባቸው ምክንያቶች አንዱም በተበላሸ አሰራራቸው  የሚተቿቸውን ምዕመናን “አንተ/አንቺ እገሌ ከተባለው ታዋቂ መምህር ትበልጣለህ/ትበልጫለሽ? እነርሱኮ ይደግፉናል፡፡” የሚል ስንኩል አመክንዮ ለመፍጠር ነው፡፡

ምንደኛ የሆኑት መምህራንም “አስመጪና ላኪዎቻቸውን” የሚያስደስት የመሰላቸውን የፖለቲካና የቡድንተኝነት አስተሳሰብ በሥጋዊ ስሜት ተመርተው እየተናገሩ በረከትን ሊያወርሱ ተጠርተው መርገምን ይጭናሉ፡፡ (መዝ. 83፡6) የጥቅም ትስስራቸው ወደሚያደላበት ቡድን በመወገን፣ ሌሎቹም በመረጃ እጥረት ወይም መዛባት ከቤተክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮ ወጥተው የግለሰቦችና ቡድኖች መንፈሳዊ ያልሆነ ተልዕኮ ፈጻሚ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በንግድ ፉክክር ውስጥ ሳይቀር እየገቡ ለአጉራሾቻቸው የንግድ ተቋማት በአውደ ምህረት ማስታወቂያ ይሰራሉ፡፡ አንድ አስተማሪ ይህን መሰሉን ተራ ነገር ሲናገር በሀሳቡ ሊስማሙ የሚችሉት በግላዊ መሳሳብ ከእርሱና ከመሰሎቹ ጋር የሚግባቡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለሌሎቹ ግን አውደ ምህረቱ የማንን ሀሳብ ለማንጸባረቅ እንደዋለ ለመረዳት አይከብዳቸውም፡፡ ለእነዚህ ሰዎች “ከትምህርቱ” በኋላ “ያስተማረን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተመሰገነ ይሁን” ብለው የሚያሳርጉ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ሳይታወቃቸው ይዘልፉታል፡፡ ምዕመናንም ቃለ እግዚአብሔርን በንጹህ ህሊና ከመስማት ይልቅ በሚያውቁትና በሚረዱት ልክ እየመዘኑ ለጽድቅ በተቀመጡበት አደባባይ ለፍርድ ይቆማሉ፡፡ አባቶቻችን በመልክዓ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎት መፋጠናቸውን አስበው ሲያመሰግኑ “ጳውሎስ ወጴጥሮስ ለክርስቶስ ላእካነ ቃሉ/ጳውሎስና ጴጥሮስ ሆይ እናንተ የክርስቶስ የቃሉ መልእክተኞች ናችሁ” ማለታቸው ለሰባክያነ ወንጌል መርህ ሊሆናቸው በተገባ ነበር፡፡ ቅዱስ ቃሉን ለማስተማር የሚቆሙ ሁሉ የክርስቶስ አምሳል፣ የመንፈስ ቅዱስ መልእክተኞች ሆነው ከመንፈስቅዱስ የተገኘውን (የተማሩትን፣ ያመኑትን) ሊያስተምሩ ይገባል እንጂ ነገር አመላላሽ ሆነው ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል የሚወዷቸውን ለመጥቀም፣ የሚጠሏቸውን ለመጉዳት ሊሸቅጡበት አይገባም፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት “ቃለ እግዚአብሔር ቃል ንጹሕ/የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው” (መዝ. 11፡6) ያለው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚነገርን እንጂ በዚህ መልኩ የሚሸቀጠውን አይደለምና፡፡

ውሸት፣ ከንቱ ውዳሴና ሽንገላ

የገንዘብ ጥቅምና የግላዊ ታዋቂነት ፍለጋ ተዘዋውሮ የማስተማርን አገልግሎት መንፈሳዊነት እያጠፉት እንደሆነ ከሚያሳዩ ጉዳዮች አንዱ በዚህ መሰል ትስስር የሚመጡ መምህራን የሚገኙባቸው አውደምህረቶች ላይ የሚታየው የውሸት፣ ከንቱ ውዳሴና ሽንገላ ብዛት ነው፡፡ ምንደኛ አገልጋዮች በደላሎቻቸውና በግል በሚቆጣጠሯቸው በርካታ ተከታዮች ባሏቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት የሌላቸውን ክብር ለራሳቸው በመስጠት በውሸት፣ በከንቱ ውዳሴና በሽንገላ መንፈሳዊውን አውደ ምህረት የቲያትር መድረክ ያስመስሉታል፡፡ መምህራኑ ለአገልግሎት የሚመረጡበት መስፈርት “ታዋቂ” ናቸው በሚል ስለሆነ “የታዋቂነትን” ካባ እንደደረቡ ለመቆየት ውሸትና ከንቱ ውዳሴን ያበዛሉ፡፡ ፎቶአቸውን በፎቶሾፕ በማሳመር ከቢራ ማስታወቂያ የማይተናነስ ግነት በበዛበት መልኩ የጉባኤ ፖስተሮችን ማስተዋወቅ፣ ያላደረጉትን እንዳደረጉ አስመስለው በመናገር ለራሳቸው የሀሰት ክብርን መስጠት፣ የአብያተክርስቲያናትን አገልጋዮች ከልክ ባለፈ ውዳሴ ከንቱ በመካብ በአጸፋው ለመከበር የመፈለግ አዝማሚያዎች በየአውደምህረቱ እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ ይህም በመልካም እርሻችን ላይ እንደበቀለ ተዛማች አረም ነው፡፡

ከባድ የገንዘብ ጫና

በዘመናችን ብዙ የቤተክርስቲያናችን መደበኛ አገልጋዮች እጅግ በጣም አነስተኛ በሆነ ወርኃዊ ደሞዝ እያገለገሉ ቢሆንም የቤተክርስቲያን አገልግሎት ለጥቂቶች ከታላላቅ ደሞዝ ከፋይ መሥሪያ ቤቶች የተሻሉ የገቢ ማግኛ መንገዶች ሆነዋል፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ አንድ የመንግስትም ሆነ የግል መስሪያ ቤት ሠራተኛ ለመስክ ሥራ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ቢያስፈልገው የሚጠቀምበት መጓጓዣና የሚሰጠው አበል እንደ ስልጣን እርከኑ ቢለያይም በአውሮፕላን የመሳፈሪያ ቲኬትና የተጋነነ አበል የሚያገኙት እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በአንጻሩ በመደበኛ በጀት ለሚያገለግሉ አገልጋዮቿ ከመንግስትና የግል ቀጣሪዎች የማይነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ደመወዝ በምትከፍል ቤተክርስቲያን ውስጥ እየተዘዋወሩ ለሚያስተምሩ መምህራን የሚወጣው የአውሮፕላን ቲኬትና የአበል ወጭ በምዕመናን ላይ ከባድ የገንዘብ ጫና የሚፈጥር ነው፡፡ ምንደኛ የሆኑት መምህራን ለመደበኛ ካህናቷ በወር ከምትከፍለው ሃያ እጥፍ በላይ ለአንድና ለሁለት ቀን ጉባኤ ሲጠይቁ ማየት ያልተለመደ አይደለም፡፡ አርቀው ማስተዋል የማይችሉ ሰዎች የክፍያ ጉዳይ አስተያየት ሲሰጥበት “ቢከፈላቸው ምን አለበት?” ይላሉ፡፡ ችግሩ ያለው የተሻለ ገንዘብ መክፈል አለመክፈሉ ላይ ሳይሆን ያለ ተገማች አሠራር ያልተመጣጠነ ክፍያ መጠየቅ አገልግሎቱን በቀጥታም ሆነ በሂደት መስመር የሚያስት በመሆኑ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው” (1ኛ ጢሞ. 6፡10) ያለውም ይህን መሰሉ መርህ አልባ የገንዘብ ንጥቂያ ሃይማኖትን በመካድ የመጠናቀቅ እድሉ ሰፊ ስለሆነ ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት ሩቅ ሳንሄድ በቅርቡ ከቤተክርስቲያን በይፋ ተለይተው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቤተክርስቲያንን ማሳደድን ሥራዬ ብለው የያዙት ወገኖቻችን የሄዱበትን የቀድሞ መንገድ ማስታወስ ይበቃል፡፡

በውጭ ሀገር ባሉ በርካታ አብያተክርስቲያናት አንድን መምህር ለማምጣት ለትራንስፖርትና ለመቆያ ያሉ ወጪዎችን ሳይጨምር ለአንድ ወር አገልግሎት በአማካይ ከሦስት እስከ ሰባት ሺህ የአሜሪካ ዶላር “የኪስ ገንዘብ” ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ክፍያ በዓለማችን ታላላቅ የሚባሉት ድርጅቶች ከሚከፍሉት የሚበልጥ ከመሆኑም ባሻገር በሀገራችን የገጠር አካባቢዎች አንድ ቤተክርስቲያን ማሠራት የሚችል ነው፡፡ የአውሮፕላን ቲኬት፣ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ተሸፍኖለት ለአንድ ወር ይህን የሚያክል ክፍያ የሚገኝበት ሥራ እጅግ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጫና የሚወድቀው በዓለማችን ባሉ ታላላቅ ከተሞች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለውና በብዛት የጉልበት ሥራ በመሥራት በሚተዳደረው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ መሆኑ ደግሞ ምጸቱን ያጎላዋል፡፡ ይሁንና “መምህራን ማስመጣቱን” በዋናነት የሚመሩት አካላት ጫናውን የሚያዩበት መንገድ “ያዋጣል ወይስ አያዋጣም?” በሚል የንግድ ሚዛን እንጂ “በእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት በቀንና በሌሊት እየሠራን የእግዚአብሔርን ወንጌል ሰበክንላችሁ” (1ኛ ተሰ. 2፡9) በሚለው በቃልም በሕይወትም በተገለጠው የቅዱሳን አባቶቻችን  ምክር ስላልሆነ ችግሩ አያሳስባቸውም፡፡

መደምደሚያ

ወንጌልን ተዘዋውሮ የማስተማር አገልግሎት የቤተክርስቲያን መሰረታዊ ተልዕኮ ነው፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የተነሱ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት፣ መናኝ ባሕታውያንና እንደየጸጋቸው በአግባቡ የተማሩትን ትምህርተ ወንጌልን ለሌሎች የሚያዳርሱ ምዕመናንና ምዕመናት እልፍ ዋጋ ያገኙበት፣ የሚያገኙበት የጽድቅ አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ጌታችን በዳግም ምጽዓት በክብር ለፍርድ ሲገለጥ እያንዳንዳችንን “ተርቤ አብልታችሁኛልን?ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልን?” በማለት የሚጠይቀን ደገኛ ምጽዋት ነው፡፡ ዛሬም በዘመናችን ቃለ ወንጌልን ለተራቡ፣ በየጠረፉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት ሁሉ ያለ ዋጋ እንደቅዱሳን ሐዋርያት እየደከሙ ቤተክርስቲያንን በምዕመናን ከዋክብትነት የሚያደምቁ፣ ራሳቸውም ከአላውያንና ከመናፍቃን በሚመጣ ማለቂያ በሌለው መከራ እየተፈተኑ የሚያበሩ የጽድቅ ፀሐዮች አሉ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ የወንጌል አገልግሎትን እንደ አማኝ፣ እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ አርቲስት፣ እንደ አነቃቂ ንግግር አቅራቢ ለመነገጃነት በማቅረብ ለራሳቸው የሥጋ ድልብን የሚያከማቹ፣ ምዕመናንንም ለስህተት አሠራራቸው ባርያ በማድረግ የጽድቁን አገልግሎት መሸቀጫ የሚያደርጉ አሉ፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ‘ታዋቂ’ አድርገው የሚቆጥሩ ወይም ‘ታዋቂ’ ለመሆን የሚጥሩ ምንደኞች ‘አገልግሎታቸው’ በመታየት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ብዙ ሰው የሚያውቃቸው በሞኞች ዘንድም “የቤተክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች” የሚባሉ፣ ራሳቸውም በሐሰት የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች በመጠቀም ለራሳቸው ከንቱ ውዳሴን የሚያዘንቡ፣ ወንጌልን በገንዘብ የሚለውጡ፣ ምርቃትና ጸሎትን የሚሸጡ ሲሞናውያን ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በሁሉም የዓለም ዳርቻ የማዳረስ ግዴታ ያለብን የቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የአስተዳደር አካላት፣ ካህናትና ምዕመናን የጽድቁ አገልግሎት ለመንፈሳዊ ዋጋ እንጂ ለሥጋዊ ብዕልና ታዋቂነት እንዳይውል የመጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ ተዘዋውሮ የማስተማር አገልግሎታችን የጽድቅ እንጀራን ለተራቡ ሁሉ የሚሰጥ ምጽዋት አድርገን የምናቀርብበት ጥበብ መንፈሳዊ እንዲሆንልን የሐዋርያት አምላክ፣ የሠራዊተ መላዕክት ጌታ፣ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡