በልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ‘የሰበካ ጉባዔ’ ኃላፊነት

kale awadi

ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ከማስተማር አንጻር በማንኛውም ቦታ ያለችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የማይተካ ድርሻ አላት። የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ (የሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል) የልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ታላቅ ኃላፊነት አለበት። የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ተግባራዊ መሆንም ይሁን ውጤታማ መሆን በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ እንቅስቃሴና ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ ነው። የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ከወላጆች፣ ከልጆች፣ ከመምህራንና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን የልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ዋነኛ የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፍ አድርጎ ማቀድ፣ መተግበር፣ መከታተልና መመዘን ይኖርበታል።

የሰበካው መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር የሕፃናት እና ወጣቶች ክፍልን በሰበካው መንፈሳዊ አስተዳደር ሥር በማቋቋም ክፍሉ በአጥቢያው ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል እና ሰንበት ት/ቤት በመታገዝ ሥራውን እንዲያከናውን ያደርጋል። ልጆችንና ወጣቶችን መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማር ቀጣይ የቤተክርስቲያን ተረካቢዎችን ማፍራት ከመሆኑ አንጻር ለዚህ አገልግሎት የማይተጋ ሰበካ ጉባዔ ካለ በቤተክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አደጋ እንደጋረጠ ተደርጎ መቆጠር አለበት። ይህንን አለማድረግ ታሪክም ይቅር የማይለው፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ የሚያስጠይቅ ነውና። ይህንን ከባድ ኃላፊነት መሠረት በማድረግ በዚህች የልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት በሚመለከት የዚህ ዙር የመጨረሻ ክፍል በሆነችው የአስተምህሮ ጽሑፍ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ድርሻና ይህንንም ድርሻ በብቃት ለመወጣት ይረዳሉ ያልናቸውን ሃሳቦች እንዳስሳለን።

ሥርዓተ ትምህርት

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ከወላጆችና ከመምህራን ጋር በመሆን ልጆች የሚማሩበትን ማዕከላዊ ወጥነቱን ጠብቆ የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርትን (curriculum) ማተምና ማቅረብ ይኖርበታል። በማዕከል የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት በሌለበት ሁኔታ ሌሎች አጥቢያዎች የሚጠቀሙበትን ሥርዓተ ትምህርት አዳብሮ መጠቀም ይመከራል። ስለዚህ ሥርዓተ ትምህርትም በወላጆች፣ በመምህራንና በልጆች ዘንድ ማስተዋወቅና በቂ ግንዛቤን መፍጠር የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ድርሻ ነው። ቀድሞ የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርትን ከመተግበር በፊት ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል። የሥርዓተ ትምህርቱንም ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ  ከወላጆችና ከመምህራን ጋር በየወቅቱ ምክክር ማድረግ የትምህርቱን ውጤታማነት ይጨምራል።

የትምህርት መርኃግብር

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ልጆችን ለማስተማሪያ የሚሆነውን የጊዜ ሰሌዳ (Time-table) ከመምህራንና ከወላጆች ጋር በመነጋገር ማዘጋጀትና ለሁሉም ማሳወቅ አንዱ ድርሻው ነው። ለሁሉም ወላጆች/ልጆች አመቺ የሚሆን ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ለአብዛኛው የሚቻልበት ጊዜን ማግኘት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ሰንበታት (ቀዳሚትና እሑድ) ለማስተማሪያነት ሊመረጡ ይችላሉ። ሆኖም ግን ሁሉን ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጀ መርሀ ግብር ተቀባይነት ይኖረዋል። ትምህርቱም በሰዓቱ እንዲጀመርና በሰዓቱ እንዲያልቅ ማድረግ ይኖርበታል። በዋዛ ፈዛዛ የሚባክን የትምህርት ጊዜም እንዳይኖር ማድረግ እንዲሁ። በቃለ ዓዋዲው ላይም “የሣምንቱን መርሀ ግብር በማውጣት ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል” በማለት ኃላፊነቱን ያስረዳል።

የመማሪያ ቦታ

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ለሕፃናትና ወጣቶች ትምህርት  የሚያስፈልጉትን የመማሪያ ክፍሎችንና (teaching rooms) ተያያዥ አገልግሎቶችን (በንጽሕና የተያዙ መጸዳጃ ክፍሎች፣ የመጠጥ ውኃ፣ በቂ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የመጫወቻ ሥፍራ፣ ለመጀመሪያ እርዳታ የሚውል ቁሳቁስ (ልጆች በጨዋታ መካከል ሊወድቁ ይችላሉና) ወዘተ) ማዘጋጀት ይኖርበታል። ሕፃናት እና ወጣቶች በቤተክርስቲያን የሚማሩበት ቦታ ደህንነቱ (በሀገሩ ፖሊሲ መሠረት) የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥም ይኖርበታል። ይህንንም ማረጋገጥ ልጆች ደረጃውን በጠበቀና ደህንነቱ በተረጋገጠበት የመማሪያ ቦታ እንዲማሩ ያደርጋል። በተለይ በዕድሜ ተለይተው ለሚማሩ ልጆች የአንዱ ድምፅ ሌላውን እንዳይረብሽ ማድረግ ያስፈልጋል። ነገር ግን ልጆች የሚማሩት በመደበኛው የትምህርት ጊዜ ብቻ ስላልሆነ አጠቃላይ የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ አገልግሎትና እንዲሁም ካህናትና ምዕመናን የሚያደርጓቸው ነገሮች ለልጆች ተስማሚ (child-friendly) እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ከንትርክ፣ ከጭቅጭቅ፣ ከአድማ፣ ኃይለ ቃል ከመነጋገር፣ ከመገርመም እና ከመሳሰሉት የጸዳ የአምልኮ ሥፍራን በመፍጠር ልጆችን በተግባርም ማስተማር ይገባል።

መምህራንና አስተባባሪዎች

ትጋትና ተነሳሽነት ላላቸው መምህራንንና አስተባባሪዎች (teachers and coordinators) ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ማዘጋጀትና መመደብ የሰበካ ጉባዔ ሌላው ድርሻ ነው። ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ሕፃናትን እና ወጣቶችን የሚያስተምሩና በተያያዥ አገልግሎት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ መምህራንና አስተባባሪዎችን የሕፃናት እና ወጣቶች ክፍል ኃላፊው ሲያቀርብለት ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ ከሥነ ምግባር እና ከዝንባሌ አንጻር ገምግሞ ያጸድቃል። በተጨማሪም ለሕፃናት እና ወጣቶች መምህራን እና አስተባባሪዎች በሀገሩ ሕግ መሠረት ከልጆች ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዲያሟሉና አስፈላጊ ማረጋገጫዎችንም እንዲያገኙ ያደርጋል። በአጠቃላይ የሚመደቡት መምህራን በእምነትና በምግባር ለልጆቹ መልካም ምሳሌ የሚሆኑ፣ ለማስተማር ብቁ የሆኑና ወላጆችም እምነት የሚጥሉባቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ የሰበካ ጉባዔ ኃላፊነት ነው። ተምረው የማስተማር ብቃት ያላቸውን በመምረጥ በቂ ሥልጠና ወስደው እንዲያስተምሩ ማድረግም በቃለ ዓዋዲው የተቀመጠ ተግባር ነው። ከዚህ ባሻገር ልጆች የማይገባ ጸባይ ላለባቸው ግለሰቦች እንዳይጋለጡና አካላዊ ወይም ስነ-ልቦናዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከል የሰበካ ጉባዔው ኃላፊነት ነው። ልጆችን ስጋት ላይ የሚጥል አዝማሚያም ከታየ በፍጥነት እርምጃ መውሰድ እንዲሁ የሰበካ ጉባዔ ድርሻ ነው።

የማስተማሪያ ቁሳቁሶች

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ለልጆችና ወጣቶች ትምህርት ግብዓትነት የሚውሉ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን (educational materials) (መጻሕፍት፣ ሰሌዳ፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች፣ ወዘተ) በበቂ ሁኔታና በሚፈለጉበት ጊዜ መቅረባቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም መንፈሳዊ መጻሕፍት የሚገኙበት አነስተኛ ቤተ መጻሕፍት (mini-library) ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህም በቃለ ዓዋዲው “ወጣቶች መንፈሳዊ ዕውቀታቸው እንዲዳብር ልዩ ልዩ የመማሪያ መሣሪያዎች የሚገኙበት ቤተ መጻሕፍት ያቋቁማል” በማለት ተገልጿል። በቂ የማስተማሪያ ቁሳቁስ በሌለበት ሁኔታ ማስተማር ለመምህራን አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም የሚቀርቡት የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለሕፃናት እና ወጣቶች አግባብነታቸውን ማየትና ማረጋገጥም የሰበካ ጉባዔ ድርሻ ነው። እነዚህን የማስተማሪያ ቁሳቁሶች በማሟላት መምህራኑ ማስተማሩ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

ክትትልና ምዘና

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ከወላጆችና ከመምህራን ጋር በመሆን የትምህርቱን አጠቃላይ ሂደት በንቃት መከታተል (monitoring)፣ በየጊዜው መገምገምና (evaluation) ማስተካከያ ሲያስፈልግ በፍጥነት እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በቃለ ዓዋዲውም “ሕፃናትን እና ወጣቶችን በቅርብ እየተከታተለ ያተምራል፣ ይመክራል፣ ይቆጣጠራል።” በማለት ያለው ኃላፊነት ተገልጿል።  በየጊዜውም ስለ ሕፃናት እና ወጣቶች በአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ የሚሰራውን ሥራ ለምእመናን ማስተዋወቅና የምዕመናንም አስተያየት ተቀብሎ ማሻሻያዎችን ማድረግ የሰበካ ጉባዔ ድርሻ ነው። የተማሪዎች ምዘናም በአግብቡ መከናወኑንና መረጃውም ምስጢራዊነቱን በጠበቀ መልኩ መያዙን ማረጋገጥ ይገባዋል። የትምህርቱና የተማሪዎች መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ መያዙንም ማረጋገጥ የሰበካ ጉባዔ ድርሻ ነው።

ዕቅድና በጀት

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት እንዲሁ በዘፈቀደ መከናወን የለበትም። ይህ አገልግሎት እንደተጨማሪ ሥራ ሳይሆን ዋና ሥራ ተደርጎ መወሰድም አለበት። በሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔው ዓመታዊ ዕቅድ (Annual Plan) ውስጥ ተካቶ በቂ ገንዘብና የሰው ኃይል ተመድቦለት መሠራት አለበት። በአጥቢያ ደረጃ የሚኖሩ የሥልጠና ወጪዎች፣ እንደአስፈላጊነቱ የመምህራን የውሎ አበሎች፣ ወዘተ ከሰበካ ጉባዔው የሥራ ማስኬጃ በጀት (Annual budget) በመመደብ መሸፈን ይኖርበታል። በአጥቢያው የሚገኙ ወላጆች ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ በማመቻቸት ወጪዎችን በከፊልም ሆነ በሙሉ እንዲሸፍኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም የሰበካ ጉባዔው ድርሻ ነው። ነገር ግን ልጆችን ማስተማር (ሰው ለልጅ ሲባል ይሰጣል በሚል እሳቤ) አዲስ የመለመኛ ስልት እንዳይሆንና ሌላም “የሙስና” ትኩረት እንድይሆን በጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።

በአጠቃላይ ሕፃናትንና ወጣቶችን መንፈሳዊ ትምህርት ከማስተማር አንጻር የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ መንፈሳዊ ትምህርቱ በሥርዓተ ትምህርት መመራቱን፣ የትምህርት ጊዜ ሰሌዳ መዘጋጀቱን፣ የመማሪያ ቦታ መዘጋጀቱን፣ ብቃት ያላቸው መምህራን መመደባቸውን፣ ለትምህርቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። በተጨማሪም የትምህርቱ መርኃግብር በዕቅድ ውስጥ መካተቱንና በቂ በጀት መመደቡን እንዲሁም አስፈላጊው ክትትልና ምዘና መደረጉንና በየጊዜው በቂ መረጃ ለወላጆች በወቅቱ መድረሱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህንን በቃለ ዓዋዲው በግልጽ የተቀመጠ ኃላፊነት በትጋትና በቁርጠኝነት መወጣት ሲገባ አንዴ ወደ ወላጅ ኮሚቴ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት (የራሱ ድርሻ ቢኖረውም) መግፋት አይገባም። መሥራትና ማሠራት ያልቻለ ኃላፊ ካለ ደግሞ በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት መቀየር ይገባል እንጂ ዘመኑን እስኪጨርስ ተብሎ ልጆች መማር ባለባቸው ዕድሜ ሳይማሩ መቅረት የለባቸውም። በተጨማሪም ልጆችንና ወጣቶችን ማስተማር “አዲስ የልመናና ገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልት” እንዳይሆንና ሌላ የሙስና ምንጭ እንዳይሆን ወላጆች ለትምህርቱ መሳካት የሚያደርጉትን ድጋፍ በጥንቃቄ ቢያደርጉት መልካም ነው።

እኛም ስለልጆች መንፈሳዊ ትምህርት በተከታታይ ስድስት ክፍሎች ስናቀርብ የቆየነውን የአስተምህሮ ጦማር በዚሁ አበቃን፡፡  ልጆቻችን በመንፈሳዊ ትምህርት ታንጸው አድገው የቤተክርስቲያን ትጉህ አገልጋዮች እንዲሆኑና በመጨረሻም ለመንግስተ ሰማያት የበቁ እንዲሆኑ  አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ †

ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት የማስተማሪያ ስልቶችና ዘዴዎች

education methods2የነገዋን ቤተክርስቲያን ተረካቢዎች የሚሆኑ ልጆችን በቤተክርስቲያንና በቤተሰብ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርትን እያስተማሩ ማሳደግ የቤተክርስቲያን፣ የመምህራንና የወላጆች ኃላፊነት ነው። ይህንንም ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን የሚማሩበትን ስልትና ዘዴ ማወቅና በሚገባ መተግበር ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በሥርዓተ ትምህርትም ይሁን ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ለልጆች የሚሰጠው መንፈሳዊ ትምህርት ውጤታማ የሆኑ የማስተማሪያ ስልቶችን ሊጠቀም ይገባል። ከዚህም አንጻር ብዙዎች “ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉ የማስተማሪያ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?” ወይም “ልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን እንዴት ብናስተምራቸው ነው ውጤታማ የምንሆነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር የሚረዱ ስልቶችን እና ዘዴዎችን እንዳስሳለን።

የተማሪዎች፣ የትምህርቱና የጊዜው አከፋፈል

መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር ልጆችን በዕድሜያቸው መክፈል ያስፈልጋል። ይህም ከ 5 ዓመት በታች፣ ከ 5-9 ዓመት፣ ከ 10-12 ዓመትና ከ 13-15 ዓመት በመክፈል ሊሆን ይችላል። ብዙ ተማሪዎችና በቂ መምህራን ካሉ ግን በዘመናዊው ትምህርት የክፍል ደረጃቸው (በዓመት) ተለይተው ቢማሩ ይመረጣልሊማሩ። የትምህርት ዘመኑን ደግሞ በክፍለ ወራት  (term) (እንደየሁኔታው በሢሦ ወይም በግማሽ ዓመትም ሊሆን ይችላል) ከፍሎ ማስተማር ይገባል። የትምህርቱንም ይዘት እንዲሁ በትምህርት ዓይነት (courses) ከፍሎ ትይይዝና ተከታታይነት ባለው መልኩ ማዋቀር ያስፈልጋል። በዚህ መሠረት የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት ካለ እርሱን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መጠቀም የተሻለ ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ሥርዓተ ትምህርት ብዙዎችን ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጀና በባለሙያዎች አስተያየት የዳበረ መሆን ይኖርበታል። በግለሰቦች የተዘጋጁ አንዳንድ ሥርዓተ ትምህርቶች ብዙ ውስንነት ስለሚኖርባቸው በዝግጅቱ ብዙ ባላሙያዎች የተሳተፋበትን ሥርዓተ ትምህርት መጠቀሙ ይመከራል።

የማስተማሪያ ዘዴዎች

ልጆችን የማስተማሪያ ዘዴዎች ብዙና የተለያዪ ሲሆኑ በልጆች ትኩረት ላይ በመመስረት በሰባት መደባት ይከፈላሉ። መምህራንና ወላጆች አስቀድመው የልጆችን ትኩረት የሚስበውን የማስተማሪያ ዘዴ ማወቅ ይገባቸዋል። መምህራኑ የልጆቹን ዝንባሌና ፍላጎት እያዩ እነዚህን ዘዴዎች በማቀያየርና በማሰባጠር ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። ሁሉንም ዘዴዎች ተንትኖ ማቅረብ ስለማይቻል ጎልተው የሚታዪትና ብዙ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች እንደሚከተለው በሰባቱ ምድቦች ቀርበዋል።

በማድመጥ ላይ ለሚያተኩሩ: Auditory

በዚህ ምድብ የሚገኙት የማስተማሪያ ዘዴዎች የልጆችን የመስማት/የማዳመጥ ክህሎት የሚጠቀሙ ናቸው። ለአብነት ከሚጠቀሱት ዘዴዎች መካካልም በመተረክ/በትረካ (Stories) መልክ የሚቀርቡ ትምህርቶች የአብዛኛቹን ልጆች ቀልብ ይስባሉ። ነገር ግን ለአዋቂዎች የሚቀርብ አይነት የስብከት ዘዴን የሚጠቀም ከሆነ ትረካውን ቢሆን ዋጋው አነስተኛ ነው። በተጨማሪም በትረካ ዘዴም ቢሆን ል ጊዜ አንድ መምህር ብቻ የሚያስተምር ከሆነ የብዙዎች ፍላጎት ይቀንሳል። መምህሩም ይሰለቻል።

ሌላው በዚህ ምድብ የሚጠቀሰው ዘዴ በመዝሙር/በዝማሬ (spiritual Songs) ማስተማር ነው። ልጆች በመዝሙር መልክ የሰሙትን በፍጥነት ይይዙታል። ነገር ግን ንባቡንና ዜማውን ብቻ ሳይሆን ትርጉምንና ምስጢሩንም አብሮ ማስጠናት ይገባል። በሌላ በኩል የልጆች መዝሙር ማጥናትና ማቅረብ ለትምህርትና ለምስጋና እንጂ ልጆችን በየጊዜው መድረክ ላይ እያዘመሩ “ልጆች እያስተማርን ነውና እዩልን!” ለሚመስል ከንቱ ተወዳጅነትን ፍለጋ መዋል የለበትም።

በማንብብና በመጻፍ ላይ ለሚያተኮሩ: Linguistic

ልጆች የተነገሩትን በመጻፍና የተጻፈውንም በማንበብ መንፈሳዊ ትምህርትን ሊማሩ ይችላሉ። መጻፍና ማንበብን (Writing/reading) ማስተማር ብቻውን ግን መንፈሳዊ ትምህርት አይደለም። ማንበብና መጻፍ በጽሑፍ ያለውን ለማወቅ፣ ዕውቀትንም በጽሑፍ ጽፎ ለማስተማር ጠቀሜታው ታላቅ ስለሆነ ልጆች በትምህርት ሰዓትና በቤት ሥራ መልኩ እየጻፉና እያነበቡ መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ ማድረግ ይገባል። በተጨማሪም ልጆች በልጅነታቸው ቅዱሳን መጻሕፍትን (የጸሎት መጻሕፍትን ጨምሮ) እያነበቡ እንዲማሩ ማድረግ ይገባል። ማንበብና መጻፍ ብዙም ፍላጎት ለሌላቸው ልጆች ግን ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀሙ ይመረጣል።

በመመልከት ላይ ለሚያተኮሩ: Visual

ማየትንና መመልከትን ከሚጠቀሙ ዘዴዎች መካከል ስዕል (Paintings/pictures) በቅድሚያ ይጠቀሳል። በጽሑፍ ከሠፈረ ብዙ ሐተታ ይልቅ አንድ ስዕል የበለጠ ያስተምራል። በቤተክርስቲያን ያሉትን ቅዱሳን ስዕላትን በተለየ መልክ በማዘጋጆት ልጆችን በስዕል ማስተማር ይቻላል። በተጨማሪም ንዋየ ቅድሳትንና መንፈሳዊ የዜማ መሣሪያዎችን በማሳየት ስለአገልግሎታቸውና ስለምስጢራቸው ለልጆች በቀላሉ ማስተማር ይቻላል። ሁለተኛው በማየት ላይ የሚያተኩረው የማስተማሪያ ዘዴ በምስል (visuals) ማስተማር ነው። ይህም የልጆችን የአሻንጉሊት ፊልሞችን ይጨምራል። ይህንን ልጆች ይወዱታል። ሆኖም ግን ሱስ እንዳይሆንባቸው አልፎ አልፎ ብቻ መጠቀም ይገባል። በሌላ በኩል በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒርተር /በመቀመሪያ/ ላይ ብቻ የሚያተኩር ትምህርት በቀጣይ የመማር ፍላጎትን ይገድላል። የልጆችንም አዕምሮ ዕድገት ይቀንሳል። ሌላው ልጆች በማየት የሚማሩበት መንፈሳዊ አገልግሎት (ቅዳሴ፣ ጥምቀት፣ ተክሊል፣ ወዘተ) ሲከናወን በማየት ነው። በልጅነታቸው ያዩት መልካም ነገርም በውስጣቸው ተቀርጾ ያድጋሉ።

በማስላት/በስሌት ላይ ለሚያተኮሩ: Logical 

በእንቆቅልሽ (Puzzles) ማስተማር በዚህ መደብ ይጠቀሳል። የስሌት ዝንባሌ ላላቸው ልጆች የስሌት ሰንጠረዥና ሌሎች የአእምሮ ሥራን የሚጠይቁ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በማዘጋጀት ማስተማር ያስፈልጋል። ስሌትን የሚሹ የቤተክርስቲያን ትምህርቶች (ለምሳሌ ባሕረ ሃሳብ) ለወጣቶች በሰንጠረዥ መልክ አዘጋጅቶ ማስተማር ይቻላል። እንዲሁም የቅዱሳንን ስም ከገድላቸው ጋር በማዛመድ፣ የቤተክርስቲያንን አሠራር በፕላስቲክ ጡቦች በመገንባት፣ ዋና ዋና የቤተክርስቲያን ታሪኮችን ከተፈጸሙበት ዘመን ጋር በማቀናጀት እንቆቅልሾችን አዘጋጅቶ ማስተማር ይገባል።

በመሥራት/በድርጊት ላይ ለሚያተኮሩ: Physical

በተሳትፎ/በመስራት (Activities) ልጆችን ማስተማር ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው። ስለጸሎት ለማስተማር እንዲጸልዩ በማድረግ፣ ስለ ምጽዋት ለማስተማር እንዲሰጡ በማድረግ፣ ቅዳሴ አብረው እንዲያስቀድሱ በማድረግ፣ በልጆች ጽዋ ማኅበራት እንዲሳተፉ በማድረግ በመሳተፍ የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡ ክንዋኔዎችንም አስመስለው እንዲሠሩ በማድረግ በድርጊት ማስተማር ይገባል። በተጨማሪም በልምምድ/ሠርቶ በማሳየት/ እንደ መስቀል፣ ጸናጽል፣ ከበሮ፣ መቆምያ እና የመሳሰሉትን ከቀላል ነገሮች እየሠሩ (Demonstration) እንዲማሩ ማድረግ ይገባል።

በማኅበራዊ ተግባቦት ላይ ለሚያተኮሩ: Social

ይህ ዘዴ መንፈሳዊ ዕውቀትን ከማስተማሩ ባሻገር ልጆች የማኅበራዊ ተግባቦት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ያግዛል። ልጆች መርኃግብር ተዘጋጅቶላቸው ቅዱሳን መካናትን እንዱጎበኙ ማድረግ (Excursion) ልጆችን ብዙ ቁምነገር ያስተምራቸዋል። ወጣቶች ትኩረትን በሚስቡ አርዕስት ላይ ውይይት (Discussion) እንዲያደርጉ የውይይት መርኃግብር ማዘጋጀትም እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድርና (Competitions) በጭውውት/ድራማ (role playing) መልክም መንፈሳዊ ይዘት ያለውን ትምህርት ለልጆች ማስተማር ያስፈልጋል።

በራስ/በግል ጥረት ላይ ለሚያተኮሩ: Solitary

አንዳንድ ልጆች በራሳቸው ጥረት መማር (self-study) ያስደስታቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ልጆች ብቻቸውን ሆነው ማንበብ፣ መጻፍ፣ ማሰብ፣ አዲስ ነገርን መፈለግ ስለሚወዱ የማስተማሪያ ስልቱም እንዲሁ ይህንን የሚያበረታታ ሊሆን ይገባዋል። ስለ አንድ ቅዱስ እንዲያጠኑና እንዲጽፉ ማድረግ፣ ስለ አንድ የቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረቱን እንዲፈልጉና እንዲያቀርቡ ማድረግ፣ አንድ መንፈሳዊ ክንዋኔ እንዲተነትኑ ማድረግ፣ ለዚህም የሚሆን በቂ መረጃ መስጠት ለነዚህ ልጆች ጥሩ ማስተማሪያ ዘዴ ነው።

የማስተማሪያ ዘዴዎች አመራረጥ

የማስተማሪያ ስልቶች አመራረጥ በትምህርቱ ይዘት፣ በመምህራን ዝንባሌ/ክህሎት፣ በልጆች ፍላጎትና በመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ለሁሉም ልጆች አንድ አይነት ስልት መጠቀም ውጤታማ አያደርግም። ሁል ጊዜም ተመሳሳይ የማስተማሪያ ዘዴን መጠቀምም እንዲሁ ለልጆች አስልቺ ይሆናል። መምህራን እንደ ተማሪዎቻቸው የዕውቀትና የእድሜ ደረጃ እንዲሁም እንደሚሰጠው የትምህርት አይነት ልዩ ልዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በሁሉም ጊዜና ቦታ ወይም ለሁሉም ትምህርት ፍቱን የሆነ አንድ ወጥ የማስተማሪያ ዘዴ የለም። ይልቁንም የመምህራን የፈጠራ ችሎታ ወሳኝነት አለው።

እያንዳንዱ ልጅ ልዩ የሆነ የመማሪያ ዘዴ ሊስማማው ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሁሉንም ወይም አብዛኛውን የስሜት ሕዋሳት የሚያካትት ትምህርት ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከ3 እስከ 6 ዓመት ያሉት ሕፃናት ብዙ በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ይመሰጣሉ። ከ7 ዓመት በላይ ያሉ ደግሞ በረቀቁ ጉዳዮች ላይም ንቁዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ ዕድሜያቸው የተለያዩ ዘዴዎችን እየቀያየሩ ማስተማር ተማሪዎችን ይስባል፡፡  አሳታፊ የማስተማሪ ዘዴዎች መምህር ተኮር ከሆኑ ዘዴዎች ይልቅ ውጤታማ ናቸው፡፡ ይሁንና ጥቂት ልጆችን ብቻ ማሳተፉ ግን ሌሎች እንደተገለሉ ወይም በዕውቀት ያነሱ እንደሆኑ ይሰማቸውና ትምህርቱን እንዲጠሉት ያደርጋል::

በዝቅተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ የዕውቀት ወይም የቋንቋ ደረጃዎች ያሉትን ልጆች ለይቶ ማወቅና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል:: ተማሪዎች ብዙ እንዲያውቁ ካለ ጉጉት የተነሳ ጫና የሚፈጥሩ መምህራን በተማሪዎቻቸው ብዙም አይወደዱም። በተለይ በምዕራቡ ዓለም ይህ ጉዳይ አይወደድም። ከዚያ ይልቅ ነገሮችን እያዋዙ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ፍላጎት እንዲጨምሩ የሚያደርጉ መምህራን ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ያለበቂ ድጋፍና ክትትል ተማሪዎችን በነጻነት ስም መልቀቁ ትርጉም የለውም:: በአጠቃላይ ግን ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር የመማር ማስተማር ሂደቱን በተመለከተ ቀጣይነት ያለው ምክክር ማካሄዱ አዋጭ የሆኑ ዘዴዎችን ለማግኘትና ለመምረጥ ያግዛል::

የትምህርት አቀራረብ ስልቶች

የተለመደው የትምህርት አቀራረብ ልጆችና መምህራን በአካል (ፊት ለፊት) (face-to-face) ተገናኝተው የሚማማሩበት ሁኔታ ነው። ይህ አቀራረብ ተመራጭ ቢሆንም በመምህራኑና በወላጆች የጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት ባስተማማኝ ሁኔታ ባለበት በውጭው ዓለም ትምህርቱን በቀጥታ በማስተላለፍ (virtual) ልጆቹም መምህራንም ከቤታቸው ሆነው ትምህርቱን ማካሄድ ይቻላል። ወላጆችም ልጆቻቸው የሚማሩትን መከታተል ይችላሉ። ሦስተኛው የትምህርት አቀራረብ ደግሞ ተቀርጾ በተቀመጠ (recorded) መንገድ ነው። ይህም በኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎች ወይም በድረ ገጽ ላይ ሊቀመጥ ይችላል። ልጆች አመቺ ጊዜ በሚኖራቸው ሰዓት ከፍተው ሊማሩበት ይችላሉ። ይህ ግን የወላጆችን ንቁና ቀጣይነት ያለው ክትትል ይጠይቃል።

ማበረታቻ/ሽልማት

ለልጆች ማበረታቻ መስጠት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንደሚያጎለብተው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን አሰጣጡና የስጦታው አይነት ወሳኝነት አለው፡፡ ስጦታ/ሽልማት የሚሰጠው ልዩ ችሎታ ወይም ጥረት ወይም ውጤት ወደፊት በቀጣይነት እንዲደረግ ለማበረታቻ ነው እንጅ ስለተደረገው ለማመስገን ብቻ አይደለም፡፡ ስጦታ ከቃል ምስጋና እስከ ቁሳቁስ ወይም ገንዘብ ሽልማት ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህም እንደ ተሸላሚው ፍላጎትና ዕድሜ ይለያያል፡፡ ያም ሆኖ ስጦታው ላቅ ያለና ለምን እንደተሰጠ ለተቀባዩም ለተመልካቹም መገለጽ አለበት፡፡ የሚደረገው ስጦታም ፍጹም እኩልነትንና ፍትህን ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንድን ልጅ ዛሬ ላደረገው አመስግኖ ነገ ተመሳሳይ ለሠራ ልጅ ምስጋናን መንፈግ አያስፈልግም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሽልማት ላቅ ላሉ ሥራዎች እንጅ በሆነ ባልሆነው ነገር ሁሉ መሰጠት የለበትም::  የአሰጣጡም ሁኔታ እንደየ ሽልማቱ ይለያያል። ሽልማቱ ትልቅ ከሆነ ካህን ወይም ዲያቆን ወይም ሌላ ተሰሚነት ያለው ሰው ቢሰጥ ይመረጣል፡፡ ሽልማት እንደየሁኔታው በቡድንም ሆነ በተናጥል ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሽልማቱ በተሸላሚው ወዲያው ሥራ ላይ ሊውል የሚችል ቢሆን የሚኖረው ዋጋ ይጨምራል፡፡ ገና ላልተከናወነ ሥራም ሽልማት ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ይህም ልጆች ለሽልማቱ ሲሉ ይበልጥ ጥረት እንዲያደርጉ ሊያግዛቸው ይችላል:: ሽልማቱ በመምህራን በቤተ ክርስቲያን እና ወይም በወላጆች ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ተሸላሚውን መምረጥ ግን የመምህራን ሥራ ነው፡፡

ክትትልና ምዘና

መንፈሳዊ ትምህርት ይዘቱ መንፈሳዊ ቢሆንም ክትትልና ምዘና ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም አንጻር በተለያዩ ደረጃዎች የሚማሩ ልጆች የትምህርት አቀባበላቸው ቀጣይነት ባለው መልኩ መመዘን አለባት፡፡ የምዘናው ዋና ዓላማም የተሻለ ትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር የሚያግዝ መረጃ ለመሰብሰብ ነው፡፡ በተጨማሪም በከፍተኛ በመካከለኛና በዝቅተኛ የዕውቀት ደረጃዎች የሚገኙትን ልጆች ለይቶ ይበልጥ በሚስማማቸው መልኩ ትምህርትና ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ በትምህርቱ መጨረሻ ላይ ከሚደረግ ምዘና ይልቅ በየደረጃው የሚደረግ ምዘና የላቀ ዋጋ አለው። ይህ ዓይነቱ ምዘና ለመሻሻል እድል ይሰጣል፡፡ ምዘና ከመደረጉ አስቀድሞ የምዘናውን አይነት፣ ዓላማና ብዛት እንዲሁም የሚደረግበትን ጊዜ ለተማሪዎችና ለወላጆች (ኮርሶች ከመጀመራቸው በፊት) መነገር አለበት::

ምዘናዎች ሙሉ በሙሉ ሽምደዳን/ማስታወስን የሚያበረታቱ ብቻ መሆን የለባቸውም:: ለምዘናዎች በቂ ጊዜና ዝግጅት መሰጠትም አለበት፡፡ እንዲሁም በምዘና ወቅት ምቹ የክፍል ሁኔታዎችም መኖር አለባቸው፡፡  ከምዘና ጋር በተያያዘ ዋናው መታወቅ ያለበት ነገር የሚሰጠው ትምህርት የሚደረገውን ምዘና ይመራል እንጅ ምዘናው ትምህርት አሰጣጡን አይመራም፡፡ በሌላ በኩል በምዘናው ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ልጆች ካሉ የበታችነት እንዳይሰማቸውና ጓደኞቻቸው እንዳያጣጥሏቸው ምዘናው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በስተመጨረሻም የምዘና ውጤቶች በተደራጀና ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ በመረጃ ቋት በቋሚነት መያዝ አለባቸው፡፡

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት በቀጣይነትና በተከታታይነት የሚከናወን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ስለሆነ ክትትልና ምዘናውም እንዲሁ በቀጣይነት የሚከናወን መሆን ይኖርበታል። ራሱን የቻለ ዕቅድና ግብ/ዓላማ ተቀምጦለት አፈጻጸምን (performance)፣  ጥራትን (quality)፣ የአጭር ጊዜ ውጤትን (outputs)፣ የመካከለኛ ጊዜ ለውጥንና (outcome) የረጅም ጊዜ ተጽዕኖን (impact) የሚመዝንና መረጃውንም ሥራ ላይ የሚያውል መሆን ይጠበቅበታል።

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማዎች

Focus areasየልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ስናስብ በቅድሚያ ትኩረታችንን የሚስበው ይዘቱ (‘ምን ይማሩ?’ የሚለው) ነው። ወላጆችም ቢሆኑ ስለልጆቻቸው ትምህርት ሲያስቡ በቅድሚያ ማወቅ የሚፈልጉት ‘ምንድን ነው የሚማሩት?’ የሚለውን ነው። ልጆቻቸውንም ‘ምን ተማራችሁ?’ ብለው ነው የሚጠይቁት። የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት የሚመራበት ሥርዓተ ትምህርትም ተቀዳሚ ትኩረቱ ‘ልጆች ምን ይማሩ?’ የሚለው ጉዳይ ነው። ይህም የሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት ነው። የመምህራን ምደባም ይሁን የትምህርቱ ስልት በትምህርቱ ይዘት ላይ ተመሥርቶ ነው የሚወሰነው። በዚህም መሠረት የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዓላማ ልጆች በመንፈሳዊና በሥጋዊ ሕይወታቸው ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል ነው:: የመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቃትም በእምነታቸው ጽናትና በክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባራቸው ይገለጣል:: እያንዳንዱ መንፈሳዊ ትምህርትና ሥልጠና ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል::

ከዚህም አንጻር የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዋና ዓላማዎች የልጆችን እድሜና የቋንቋ ችሎታን ባገናዘበ መልኩ መንፈሳዊ ዕውቀትን፣ በጎ አመለካከትን፣ ክርስቲያናዊ እሴትንና የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው:: እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ ክርስቲያናዊ ስብዕና የሚገነባው በዕውቀት ወይም በምግባር ላይ ብቻ ባተኮረ ትምህርት ሳይሆን በእነዚህ በአራቱም ላይ በሚያጠነጥን ተከታታይና ዘላቂነት ባለው ትምህርትና ተሞክሮ ነው:: በዘመናችን የሚታየው የመንፈሳዊ ሕይወት ዝለት አንዱና ዋናው መነሻ መንፈሳዊ ትምህርቶች ከነዚህ ከተጠቀሱት መሠረታዊ ዓላማዎች በአንዱ (በተለይ በዕውቀት ላይ) ወይም በሁለቱ ላይ ብቻ ስለሚያተኩሩ ነው:: እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የልጆችና መንፈሳዊ ትምህርት ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳስሳለን፡፡

እምነት፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነትን በሚገባ ማሳወቅ

ልጆች በመንፈሳዊው ትምህርታቸው ስለ እግዚአብሔር አምላክነት፣ ስለፍጥረታት አፈጣጠር፣ በአጠቃላይ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ፣ እንዲሁም ስለቤተክርስቲያን ታሪክና ፈተናዎች በቂ ዕውቀትን እንዲጨብጡ ማስቻል ያስፈልጋል::  የልጆች  መንፈሳዊ ትምህርት ማካተት ከሚገባቸው አርዕስት መካከልም የእግዚአብሔር ባሕርይ እና ፈጣሪነት፣ ዓለማትን እንዴት እንደተፈጠሩ፣ የሰው ልጅ አፈጣጠርና የእግዚአብሔር ጥበቃ፣ ቅዱሳን መላእክትና ሰዎች እና ሥራቸው፣ ስለ ከበሩ ንዋየ ቅድሳት (ታቦትና ጽላት የመሳሰሉት)፣ ስለ ጌታችን ሥጋዌ (ሰው መሆን)፣ በነገረ ድህነት የእመቤታችን ድርሻ ክብርና ሕይወት፣ ጌታችን ያስተማረው ወንጌልና ያደረጋቸው ተአምራት፣ የጌታ በራሱ ፈቃድ መሰቀል መሞት እና መነሣት፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱን፣ ጽድቅና ኩነኔ፣ የቤተክርስቲያን ታሪክና የዘመን አቆጣጠር፣ በዓላትና አከባበራቸው…ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡

አመለካከት፡ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ

ልጆች ነገረ ሃይማኖትን በእውቀት ተኮር አሰጣጥ ቢማሩም ቀና አመለካከት ግን ከሌላቸው ጥረቱ ሁሉ ዋጋ የለውም:: ቤተክርስቲያንን የሚያሳድዱ ወገኖቻችን ስለቤተ ክርስቲያን አነሰም በዛ ያውቃሉ:: ለአስተምህሮዋም ሆነ አስተምህሮዋን ለመጠበቅ ሊሰራ ስለሚገባው ተቋሟ ያላቸው አመለካከት ግን ደዌ አለበት:: በመሆኑም የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ዕውቀትን ከማስጨበጥ በተጨማሪ ልጆች ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ታሪካዊ ጉዞ ቅን አመለካከት ወይም አስተያየት እንዲኖራቸው ማገዝ አለበት:: በጎ አመለካከት የብዙ ነገሮች መሠረት ስለሆነ በልጅነታቸው መገንባት ይኖርበታል፡፡

እሴት፡ ኦርቶዶክሳዊ እሴቶችን ማስተማር

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ልጆች ኦርቶዶክሳዊ እሴቶችን ለምሳሌ እምነትን፣ ተስፋን፣ ፍቅርን፣ መረዳዳትን፣ መታገስን፣ ትህትናን፣ ፅናትን፣ መታዘዝን፣ ንጽሕናን ወዘተ ገንዘብ እንዲያደርጉ ማገዝ አለበት::  እነዚህ እሴቶች ለክርስትና ሕይወት መሠረታዊ ነገሮች ስለሆኑ ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሕይወታቸው አካል አድርገው ሊያድጉ ይገባል፡፡ እነዚህንም እሴቶች የሚማሩት በማየትና በመሳተፍ ስለሆነ ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች የቤተክርስቲያን ምዕመናን እነዚህ እሴቶችን በመተግበር ለልጆች አርአያ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ሥርዓት፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንዲፈጽሙ ማስቻል

ልጆች ስለሃይማኖታቸው በቂ ዕውቀትና በጎ አመለካከት ቢኖራቸው በምግባር መተርጎም ካልቻሉ እንዲሁ ዋጋ ቢስ ነው:: ልጆች ሲያድጉ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ሊኖረው የሚገባውን ሥነ-ምግባር ይኖራቸው ዘንድ ያስፈልጋል:: መንፈሳዊ ትምህርታቸውም ልጆች ክርስቲያናዊ ሕይወትን ለመኖር የሚያስችላቸውን ዘዴዎች ሥራ ላይ እንዲያውሉ ያደርጋል:: መንፈሳዊ ትምህርቱ የተለያዪ የክርስትና ሕይወት ተግባራትን እንዲማሩ ያግዛል:: ለምሳሌ ያህል ጸሎት እንዴት እንደሚጀመርና እንደሚፈጸም፣ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ እንዴት መሳለም እንደሚገባ፣ በቅዳሴና በትምህርት ጊዜ ሊደረግ የሚገባ ተሳትፎ፣ ከቅዱስ ቍርባን በፊት፣ ጊዜና በኋላ የሚደረጉ ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች ልጆች መማርና ማወቅ እንዲሁም መፈጸም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንንም ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ሊያገኙ ይገባል። ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን የምናስተምርበት መንገድም ልጆችም ሆኑ ሌሎች ምዕመናን ከምንፈጽመው የሚታይ ሥርዓት ባሻገር ያለውን ታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር በኦርቶዶክሳዊ ለዛ እንዲረዱ በማድረግ ይገባል እንጂ ጌታችን እንደወቀሳቸው ጸሀፍትና ፈሪሳዊያን የሥርዓትን መሰረታዊ ዓላማ በመዘንጋት መሆን የለበትም፡፡

ክህሎት፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ማድረግ

ልጆች በቤተክርስቲያን በሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት መንፈሳዊ አገልግሎትን ለመፈጸም የሚሆኑ ክህሎቶችን እየተማሩ ማደግ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ኦርቶዶክሳዊ (ያሬዳዊ) ዝማሬን ማጥናትና ማቅረብ፣ የቅዳሴ ተሰጥኦ መቀበል መቻል፣ በአገልግሎት ጊዜ የሚደረጉ ዝግጅቶች ማስተናገድ፣ በቋንቋቸው መጻፍና መናገር፣ ለታናናሾቻቸው የተማሩትን ማስተማር፣ መንፈሳዊ መርሐግብሮችን ማስተባበርና የመሳሰሉትን ክህሎቶች እያዳበሩ ሊያድጉ ይገባል፡፡ ማንኛውም ትምህርት በሚገባ ሊተረጎም የሚችለው ተማሪዉ ለትምህርቱ የሚገባ በቂ ልምምድ አድርጎ አስፈላጊውን ክህሎት ሲይዝ ነው፡፡ በቃል ከማስተማርም ሆነ በገቢር ከማሳየት ባሻገር ልጆችና ህጻናት በቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተሳተፉ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያን ሽህ ዘመናትን ተሻግራ ለዘመናችን ከነትውፊቷ የደረሰችው ልጆችና ወጣቶችን እንደ መርሐ ግብር ማሟያና በሚያይ አሰራር ሳይሆን በገቢር በሚያሳትፍ አሰራር ነው፡፡ ታላላቅ አባቶቻችን ቅዱሳን በጉባኤ ሲገኙ ከእነርሱ ይልቅ ወጣቶች የሆኑ ረድኦቻቸው (ረዳቶቻቸው) እንዲያስተምሩ፣ መናፍቃንንም እንዲረቱ ያደርጉ የነበሩት (ለምሳሌ ቅዱስ አትናቴዎስ) ከእውቀትና ምግባር ባሻገር የክህሎትን ትምህርት እየሰጧቸው ነበር፡፡

ሥነ-ምግባር፡ በክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ማጎልበት 

ልጆች በልጅነታቸው ቤተክርስቲያን ሄዶ ማስቀደስን፣ እንደየአቅማቸው መጾምና መጸለይን፣ ምፅዋት መስጠትን፣ ሥራን ጠንክሮ መሥራትን፣ ሰውን ማክበርን፣ ከሌሎች ጋር ለምሳሌ ከጓደኛ ከጎረቤት ጋር በሰላም መኖርን…ወዘተ እየተማሩ ሊያድጉ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጥፎ ከሆኑ ምግባራት ይርቁ ዘንድ በምክንያት ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ መልካም ነገርን ሲያደርጉ ጠቀሜታውን በሚገባ ተረድተውት እንዲያደርጉ፤ መልካም ያልሆነውን ሲተውት ጉዳቱን በሚገባ ተረድተውት እንዲሆን ማድረግ የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ትኩረት መሆን ይኖርበታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መልካም ምግባራት ለክርስቲያን ህይወት መሰረታዊ የድህነት (የመዳን) መፈጸሚያ መንገዶች ናቸው እንጂ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው “ስንችል” ብቻ የምንፈጽማቸው ከድህነታችን ጋር ያልተያያዙ የምንግዴ ትእዛዛት አይደሉም፡፡

ጥበብ፡ ጥበብን የሕይወታቸው መርህ እንዲያደርጉ ማስቻል

የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ቀጣይ ሕይወታቸውን በማስተዋልና በጥበብ መምራት እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡ ውጥንቅጥ በበዛበት ዓለም እምነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በልጅነታቸው ይህንን ጥበብ ከቤተክርስቲያን መማር ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በእምነት ከማይመስሏቸው ጋር አብሮ መኖርን፣ ስለሃይማኖታቸው ለሚጠይቋቸው ሁሉ በተገቢው ሁኔታ በጥበብ ማስረዳት መቻልን፣ በክርስትናቸው ምክንያት ፈተና ቢገጥማቸው በማስተዋልና በጥበብ ማለፍ መቻልን፣ በሥራ፣ በትዳር ሕይወትና በማኅበራዊ ኑሮ አርአያ መሆንን …. ወዘተ በቤተክርስቲያን ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት ሊያገኙትና በሕይወት ተሞክሮአቸው ሊያዳብሩት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የልጆች መንፈሳዊ ትምህርት እውነተኛ እምነትን፣ በጎ አመለካከትን፣ ክርስቲያናዊ እሴትን፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ክህሎትን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባርንና በጥበብና በማስተዋል መኖርን ተቀዳሚ ዓላማዎች ሊያደርግ ይጠበቅበታል። ልጆች የሚማሩበት ሥርዓተ ትምህርትም በእነዚህ ዓላማዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆን ይኖርበታል። የሚያስተምሩት መምህራንም በእነዚህ ዓላማዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። የማስተማሪያ ስልቱም እነዚህን ዓላማዎች የሚያሳካ መሆን ይጠበቅበታል። ትምህርት በዓላማ ከተመራ ውጤታማነቱ አጠያያቂ አይሆንም። ዓላማዎቹ በግልጽ ካልታወቁ ግን ወጅብ እንደሚያማታው ውኃ ሲዋልሉ መኖር ይሆናል። †