በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ

ምስጢረ ሥጋዌ (አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር) ተረድተው ለሚያምኑት የመዳን መሠረት፣ በከንቱ ፍልስፍና ለሚጠራጠሩት ደግሞ የመሰናከያ አለት ነው፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እርሱም በቃሉ ለሚጠራጠሩና የተፈጠሩበትን ለሚክዱ የዕንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት ነው፡፡” (1ኛ ጴጥ. 2፡8) ያለው ለዚህ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከጌታችን ልደት ጀምሮ በሐዋርያትም ዘመን ከዚያም በኋላ እኛ አስካለንበት ዘመን ድረስ ምስጢረ ሥጋዌ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቹም ምስጢሩን በሚገባ ካለመረዳት ወይም በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት የሚመነጩ ናቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ የተነሱ መናፍቃን ያነሷቸውንና ሐዋርያዊት ጉባኤ በሆነች የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት የተወገዙባቸውን (የተረቱባቸውን) አስተምህሮዎች ካለመረዳት ዛሬም ብዙ ወገኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ተዳስሰዋል፡፡

ወደ ጥያቄዎቹ ከመግባታችን በፊት ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ነጥቦችን ማስተዋል የሚያስፈልግ መሆኑን እናስገነዝባለን፡፡ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ዘይቤ የሰዋስው፣ የጊዜ ቅደም ተከተልን፣ እንዲሁም የድርጊት ቅደም ተከተልን የማይጠንቅቅ  መሆኑን ነው፡፡ የወደፊት ጊዜን በኃላፊ ግስ መግለጽ የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ጠባይ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢሳ 53፡1 ያለውን ብናይ ‹‹በእውነት ደዌያችንን ይቀበላል›› ማለት ሲገባው (ነቢዩ ከጌታችን አስቀድሞ የነበረ ነውና) ‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ›› ይላል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እንዲሁ ‹‹በቀሚሴ ዕጣ ይጣጣላሉ›› በማለት ፈንታ ‹‹ዕጣ ተጣጣሉ›› ብሏል፡፡ መዝ 21፡12 በሌላ በኩል ቅዱሳን ነቢያት መጻዕያትን እንደተፈጸሙ አድርገው መናገራቸው የእምነታቸውን ጽናትና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ያስገነዝበናል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት መተርጉማን አባቶቻችን “መጽሐፍ ምስጢር እንጂ ዘይቤ አይጠነቅቅም” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ የእግዚአብሔርን ማዳን፣ የመንግስተ ሰማያትን ጉዞ ማሳወቅ፣ ማስረዳት እንጂ የቋንቋ ብሂል ማስተማር አይደለም፡፡

ስለሆነም ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበትን ዓላማ፣ በአንዱ መጽሐፍ ያለው ምንባብ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ያለውን ትይይዝ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፉ የቀደምት ሊቃውንትን ትርጓሜዎች አገናዝበን ልንተረጉም ይገባል እንጂ ማናችንም መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን ስሜት ልንተረጉመው አልተፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፡፡ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተናገሩ፡፡” (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21) በማለት አስተምሮናልና፡፡ ማኅቶተ ቤተክርስቲያን፣ ንዋይ ኅሩይ የተባለ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስም “በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ሕግ አገልጋዮች አደረገን፤ ፊደል ይገድላል፣ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል፡፡” (2ኛ. ቆሮ. 3፡6) በማለት መክሮናል፡፡ ስለሆነም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር እንደ አባቶቻችን ልቡናን ከፍ ከፍ በማድረግ፣ በትሁት ስብዕና፣ ከቀደሙት ሊቃውንት በመማር፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ልንመረምር ይገባል እንጂ ቃላትና ፊደላትን ብቻ በመከተል ሳያገናዝቡ የእምነት ድምዳሜ ላይ በመድረስ ሊሆን አይገባም፡፡ ፊደልን በመከተል መንገድ የሄዱት ሁሉም ጠፍተዋልና፡፡

ሁለተኛው ማስተዋል የሚያስፈልገው ነገር ከጥንት ዘመን በነበረው መጽሐፍ ቅዱስና በዘመናችን ባሉት በተለያዩ ቋንቋዎች የታተሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል አንዳንድ ቦታዎች ላይ የቃላትና የትርጉም ልዩነቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ይህም ልዩነት (Translation Bias) በተርጓሚው፣ አስተርጓሚው ወይም በአሳታሚው ዝንባሌ/ተጽዕኖ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀደም ወዳሉት እትሞች ሄዶ ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለምሳሌ በሮሜ 8፡34 (‹‹የሚማልደው››) በዕብ 7፡25 (‹‹ሊያማልድ››) በ1ኛ ዮሐ 2፡1 (‹‹ጠበቃ››) ያሉት ከቀደሙት የመጽሐፍ ቅዱሳት ቅጂዎች ጋር ያላቸውን የትርጉም ልዩነት ማስተዋል ይገባል፡፡

 አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” (ማቴ 27፡46)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በተሰቀለ ጊዜ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለቱን ይዘው በልዩ ልዩ ክህደት ራሳቸውን የሚጎዱ ወገኖቻችን አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በፈቃዱ የተቀበለውን መከራ በግዳጅ የተቀበለ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ሌሎቹም አምላክነቱን ለመካድ መነሻ ያደርጉታል፤ ሌላ አምላክ ያለው (የተፈጠረ) ይመስላቸዋል፡፡ ይሁንና ጌታችን መከራውን ስለ እኛ በፈቃዱ የተቀበለ ሲሆን ዓለማትን የፈጠረ የሁሉ አስገኝ እንጂ በማንም በማን የተፈጠረ አይደለም፡፡ ጌታችን ይህንን የተናገረው ስለ ሦስት ነገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ለአብነት ነው፡፡ በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲያጸኑባችሁ ‹‹አትተወን አበርታን›› እያላችሁ አምላካችሁን ተማጸኑ በችግር በሃዘናችሁም ጊዜ ጥሩኝ ሲለን ነው፡፡ ይህም ‹‹ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና›› ስላለ ነው (ማቴ 11፡29)፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ስለ አዳም ተገብቶ የተናገረው ነው፡፡ ተላልፎ ስለተሰጠለት ስለ አዳምና ስለልጆቹ የተናገረው ቃል ነው፡፡ ስለ አዳም ተገብቶ የአዳምን መከራ ተቀበለ የአዳምን ጩኸት ጮኸ፣ ሕመም የሚሰማማውን ሥጋ እንደለበሰ ለማመልከት ታመመ፣ የባሪያውን መልክ ይዞ በትህትና ሰው ሆኖ ተገልጧልና ራሱን አዋረደ እስከ መስቀል ሞትም እንኳ ሳይቀር ታዘዘ (ፊልጵ 2፡7) ይህ የለበሰው ስጋ ይራባል፣ ይጠማል፣ይታመማልና ጌታም በለበሰው ሥጋ የተቸነከረው ችንኳር ያሰቃያል፣ ያቆስላል ያማልና አምላኬ አምላኬ ብሎ አባቱን ተጣራ።

ሦስተኛቸው ምክንያት የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ የተናገረው ነው፡፡ በዙሪያው ተሰብስበው ለነበሩት አይሁድ ‹‹ይህ ለእኔ ተጽፏልና ሂዱና ሕግና ነቢያትን አንብቡ›› ሲል ነበረ አይሁድ የነቢያትንና የሙሴን መጻሕፍት ያውቁ ስለነበር ይህ የተነገረ ስለ እርሱ እንደሆነ እንዲያምኑ ነበር፡፡  ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ጌታችን ይህን ጸሎት በአዳም ተገብቶ “አምላኬ አምላኬ ተመልከተኝ ለምን ተውኸኝ?” (መዝሙር 21፡1) በማለት እንደሚጸልይ በትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ይኽንን ጸሎት በሚጸልይበት ጊዜ አዳም የተሰጠውን ተስፋ እየጠበቀ “አምላኬ አምላኬ ተመልከተኝ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ እየተማጸነ እንደነበር የቤተክርስቲያን መተርጉማን ያስረዳሉ፡፡ በሌላም መንገድ በማቴ 12፡29 ‹‹ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል?›› ብሎ እንደተናገረው ሰይጣንን ወደ እግረ መስቀሉ አቅርቦ ለማሰርና ምርኮኞችን ለማስመለስ ነው፡፡ ሰይጣን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተዋሕዶ ከልደቱ ጀምሮ ግራ ተጋብቶ ይኖር ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በአምላክነት፣ ሌላ ጊዜ በሰውነት ሲገለጥ አምላክነቱን የተረዳ ሲመስለው ፈርቶ ይሸሽ ነበር፤ ሰውነቱን የተረዳ ሲመስለው ደፍሮ ሊፈትነው ይቀርብ ነበር፡፡ ሰይጣንን አስሮ በአካለ ነፍስ ሲኦልን የበረበረ ጌታችን “አምላኬ አምላኬ” ማለቱን ሲሰማ ሰይጣን ዕሩቅ ብዕሲ (ፍጡር) መስሎት እንደ ቀደሙት ነቢያት ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል እገዛለሁ ብሎ ሲቀርብ በእሳት ዛንጅር አስሮ ቀጥቶታል፣ በሲኦል የነበሩ ነፍሳትንም ነጻ አድርጓል፡፡ (ቆላስይስ 2፡14-15) ስለሆነም አባቶቻችን ጌታችን “አምላኬ፣ አምላኬ” ማለቱ ለአቅርቦተ ሰይጣን (ሰይጣንን አቅርቦ ለማሰር) መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እርሱ ፍጹም ሰው ነውና ‹‹አምላኬ አምላኬ አለ፣ ፍጹም አምላክ ነውና ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› ሲል በቀኙ ለተሰቀለው ወንበዴ ተናገረው፡፡ በዚህም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን አረጋገጠልን፡፡ ‹‹አምላኬ አምላኬ›› ብሎ ሁለት ጊዜ ‹‹አምላኬ›› ያለው ነፍስና ሥጋን፣ ለጻድቃንና ለኃጥአን፣ እንዲሁም ሕዝብና አሕዛብን ለመካስ የመጣ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

“ወደ አባቴ፣ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ” (ዮሐ 20፡17)

ይኽንንም ቃል ይዘው ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠሩ፣ ልዩ ልዩ ክህደትንም የሚናገሩ አሉ፡፡ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ቃል የተናገረው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ሲሆን ይህም ፍጹም በተዋሕዶ ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ተዋሕደው ያሉ ሥጋና መለኮት ከትንሣኤም በኋላ ለአፍታም እንዳልተለያዩ ሊያስረዳን ‹‹ወደ አምላኬ›› ብሎ ተናግሯል። አንድም “በተዋሕዶ ለነሳሁት ሥጋ ፈጣሪው ወደሚሆን” አምላክ ዐርጋለው የሚል ትርጉም ይኖረዋል። ወደ አምላኬ አለ፤ ምክንያቱም መለኮት የፈጠረውን ሥጋ ንብረቱ አድርጓልና፡፡ አንድም የተዋሐደውን ሥጋ በመቃብር ጥሎት እንዳልተነሳ ለማጠየቅ ፤ ቀጥሎም አምላካችሁ አለ፤ በጥንተ ተፈጥሮ ሁላችንን ይፈጥረናልና ነው፡፡

እንደዛ ባይሆን ‹‹ወደ አምላካችን›› ብሎ በተናገረ ነበር። ወደ አባታችንና አምላካችን ብሎ በአንድነት ቃል ቢገልጸው ኖሮ እርሱም ሆነ እኛ ከአንድ ወገን መሆናችንን ያስረዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ለመለየት ወደ አባቴና አባታችሁ ፤ ቀጥሎም አምላኬና አምላካችሁ አለን እንጅ:: ስለዚህ ይህ ቃል የሚያመለክተው ክርስቶስ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ነው።  እርሱ ‹‹ወደ አባቴ›› ያለውም ለእርሱ የባህርይ አባቱ መሆኑን ሲገልጽ ነው፡፡ ቀጥሎም ‹‹ወደ አባታችሁ›› ያለው ደግሞ ለእኛ የፈጠረን አባታችን መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡ ሁለቱን ለመለየት ‹‹ወደ አባታቸን›› ሳይሆን ‹‹ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ›› አለ፡፡ ሊቁ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ አለ “ዳግመኛም በተነሣ ጊዜ ከዚህ ከአዳም ባሕርይ ሰው መሆኑን አስረዳ ፈጽሞ ከእርሱ ወደአልተለየው ወደአብም ከማረጉ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ አምላኬ አምላካችሁ አለ፤ ይህን በሰሙ ጊዜ ይህን የተናገረ ሥጋ ብቻ እንዳይመስላቸው ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ አቡየ ብሎ ከዚህ በኋላ አምላኪየ አለ እንጂ፡፡…ከእኔ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ላደረግኹት ለሥጋ ሥርዓት እንደሚገባ እንዲህ አባቴን አምላኪየ ብዬ ጠራሁት ይላል፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 68፡12-13) ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ይህንን ቃል ሲተረጉም እንዲህ አለ፡- “የባሕርይ ልጁ ስለሆነ አቡየ (አባቴ) አለ፤ ለደቀመዛሙርቱ ስለሰጣቸው ልጅነትም አቡክሙ (አባታችሁ) አለ፤ ባሕርየ ትስብእትን ስለሚመስል ባሕርየ አርድእት አምላኪየ አለ ይኸውም ፈጣሪያችሁ ማለት ነው” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡8)

“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና” (ዕብ.7:25)

ይህ ንባብ በብዙ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጅዎች ይገኛል፡፡ ከግዕዙ የተተረጎመው ግን እንዲህ ይላል “ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፣ እንዲኖሩም አያሰናብታቸውም ነበርና፡፡ እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና፡፡ ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል፡፡” (ዕብ. 7፡24-25) ነገር ግን ፊደል ለሚያጠፋቸው፣ ላጠፋቸው ወገኖች ትምህርት ይሆን ዘንድ በአማርኛ ትርጉም የሚገኘውን “ሊያማልድ በሕይወት ይኖራል” የሚለውን መነሻ አድርገን እናስረዳለን፡፡

እነርሱም (ሌዋውያን ካህናት) ሞት ስላለባቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው ፡ ክርስቶስ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ (እግዚአብሔር ስለሆነ) የማይለወጥ ክህነት አለው (ዕብ 7፡24) ፡ ስለእነሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ፡ ስለዚህም ደግሞ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈፅሞ ሊያድናቸው ይችላል (ዕብ 7፡25)፡፡ ‹‹ስለእነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል›› መባሉ ስለክርስቶስ ኃይል የመስዋእቱ ኃይል ከፍ እንዳለ መናገሩ ነው፡፡ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መናፍቃኑ ለምንፍቅና ትምህርታቸው እንዲመቻቸው ‹‹ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ብለው ያጣሙት እንጂ ቆየት ብሎ በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ (1960) ላይ ግን ‹‹ክህነቱ አይሻርምና ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘላለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል›› ነው የሚለው (ዕብ 7፡24-25)

ጌታችን ራሱ መስዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ አንድ ጊዜ ብቻ ራሱን ባቀረበው መስዋዕት ለዘላለም ኃጢዓታችንን ያስተሰርይልናል፡፡ አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደም ያለፈውንም ሆነ የሚመጣውን ትውልድ ለዘላለም ያስታርቀዋል እንጂ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‹‹ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም›› ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና፡፡ ስለዚህ እኛም ፍጹም ድኅነትን ያገኘነው አንድ ጊዜ በሠራልን የክህነት ስራ ነው፡፡ ‹‹በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድራዊ ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል›› (ቆላ 1፡19) ተብሎ እንደተጻፈ ይህ የሠራልን የክህነቱ ሥራው ነው፡፡ ‹‹ዘወትር ሲያስታርቀን የሚኖረው አሁንም ያማልደናል›› ካልን ግን ክርስቶስ ዕለት ዕለት ኃጢአት በሠራን ቁጥር መሞት አለበት ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ ‹‹ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን (ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ) ጋር በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በሕልውና አንድ ስለሆኑ) የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር (የሦስትነትና የአንድነት ስማቸው) ነው አንድም ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣) እግዚአብሔር ‹‹በክርስቶስ ሆኖ›› (ሥጋን ለብሶ ሰው ሆኖ) ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር›› (ኀላፊ ቃል) በደላቸውንም አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን እናማልዳለን› ብሏል› (2ቆሮ 5፡18-21)፡፡

“ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ 8፡34)

ይህ ጥቅስ መናፍቃኑ ለራሳቸው እንዲመች አድርገው የተረጎሙት ነው፡፡ አዲስ ኪዳን ተብሎ 1946 ዓ.ም በአፄ ኃይለስላሴ መልካም ፈቃድ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአብዛኛዎቻችን እጅ ያለውን የተዛባውን የሮሜን 8፡34 ኃይለ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ያስነብበናል ‹‹እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚነቅፋቸው ማነው? እርሱ ካጸደቀ ማነው የሚኮንን? ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ በአብ ቀኝ ተቀምጧል ስለ እኛ ይፈርዳል (ሮሜ 8፡33-35)  ይላል፡፡››

በተመሳሳይ የሊቃውንት ጉባኤ ባሳተመው ግዕዝና አማርኛ ወይም ነጠላ ትርጉም አዲስ ኪዳን እንደሚከተለው ተገልጧል፡፡ ‹‹ወመኑ ውእቱ እንከ ዘይትዋቀሦሙ ለኅሩያነ እግዚአብሔር ለእመ ለሊሁ ያጸድቅ፡፡ ወመኑ ዘይኬንን ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ ወተንስአ እምውታን ወሀሎ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ወይትዋቀሥ በእንቲአነ›› (ሮሜ 8፡33-34) ትርጉሙም ‹‹እርሱ ካጸደቀ እንግዲህ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው? የሚፈርድ ማን ነው? ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፣ ስለ እኛም ይፈርዳል›› ይላል፡፡

ይህንን ለራሳቸው እንዲመች አድርገው የተረጎሙትን ጥቅስ በመጠቀም አንዳንዶች ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልደናል›› ይላሉ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፡፡›› (ዮሐ 16፡26) በማለት እውነቱን ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ‹‹አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።›› (ዮሐ 5፡21-23) በማለት እውነተኛ ፈራጅ እርሱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

‹‹ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን››” (1ኛ ዮሐ፡2፡1)

‹‹ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን›› (1ኛ ዮሐ 2፡1)። ይኸንን ኃይለ ቃል የምናገኘው በተለመደው መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያው በቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ላይ ነው። ይህ ሐዋርያ በመጀመሪያቱ መልእክቱ ምዕራፍ አንድ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንዲህ ይላል፡፡ “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፤ በዓይኖቻችንም ያየነውን፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፥ አይተንማል፥እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም፥ ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራችኋለን። ”ካለ በኋላ፥በምዕ 2፡1 “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፥ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤” ብሎአል። እንዲህ የሚለው በስፋት በሁሉ ዘንድ የተሰራጨው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በራሷ ሊቃውንት አስመርምራ፥ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና፥የራሷን መጽ ሐፍ ቅዱስ በ2000 ዓ.ም. በማሳተሟ ችግሩ ተቀርፎአል። እንደተለመደው ይኸንን ገጸ ንባብ፥ለአማርኛው ጥንት ከሆነው ግዕዝ ጋር እናገናዝበዋለን። “ደቂ ቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢተአብሱ፤ልጆቼ ሆይ፥እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ” በማለት የጻፈበትን ምክንያት ካስረዳ በኋላ፡-“ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ጻድቅ ውእቱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፥ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፤(በድሎ ንስሐ የገባ ሰው ቢኖር ኃጢአታች ንን የሚያስተሠርይልን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ የሚልክልን ጰራቅሊጦስ አለን፥ እርሱ ኃጢ አታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ቸር አምላክ ነው)፥ይላል።በመሆኑም፡-“ኢየሱስ ጠበቃ፤” የሚል ንባብም ትርጓሜም የለውም።

“ከእኔ አብ ይበልጣል” (ዮሐ 14፡28)

ጌታ ኢየሱስ ይህንን ያለበት ምክንያት ሥጋን በመልበሱ ህማም፣ ሞት፣ ግርፋት፣ ስቃይ፣ የመስቀል መከራ ስለሚደርስበት ነው ፡፡ አብ ግን ሥጋን ስላለበሰ ህማም፣ ሞት፣ መከራ፣ ስቃይ አያውቀውም /አይደርስበትም/ የለበትም፡፡ በዚህ ምክንያት አብ ከኔ ይበልጣል በዚህ ሰአት እኔ ወደመከራ ግርፋት ስቃይ መሄዴ ነው፤ ወደ አባቴ መሄዴ መልካም ነው፤ እሱ ዘንድ መከራ የለም ግርፋት የለም ስቃይ የለም ሥጋን በመልበሴ በሚደርስብኝ መከራ ምክንያት አብ ከኔ ይበልጣል አለ፡፡ እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከወልድ ጋር አንድ መሆኑን ሲናገር ግን ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› ብሏል (ዮሐ 10፡30)፡፡

ጌታችን ሥጋን በመዋሐዱ ምክንያት እንኳን ከአብ ከመላእክትም አንሶ እንደነበር ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ይነግረናል፡፡ ዕብ 2፡9 ‹‹ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።›› መላእክት ሥጋን ባለመልበሳቸው/ሰው  ባለመሆናቸው/የሚደርስባቸው መከራ እና ስቃይ ባለመኖሩ የመላእክት ፈጣሪ ከመላእክት አንሶ ነበር ተብሎ ተፃፈ ፡፡ ራሱን ባዶ አድርጎ ‹‹በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡›› ፊልጵስዩስ 2፡6

“የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” (1ኛ ቆሮ 11፡3)

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” በዚህ ጦማር የምንመለከተው የዚህን ጥቅስ የመጨረሻውን ሐረግ ” የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” የሚለው ላይ በማተኮር ነው፡፡ ይህንንም በመያዝ አንዳንዶች ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የሚያንስ አስመስለው ይናገራሉና፡፡ እውነታው ግን እንደሚከተለው ነው፡፡

የሴት ራስ ወንድ ነው ሲል የሴት መገኛ ወንድ ነው ማለቱ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው (ዘፍ 2:21)›› እንዳለው። ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ አልፈጠራትም፡፡ ወንድ የሴት እራስ ነው የተባለው መገኛዋ ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ራስ የአካል መገኛና ተመሳሳይ፤ አንድ ባህሪ ወይም መሰረት ነው፡፡ የሴት መሰረቷ (መገኛዋ) ወንድ ነው፡ ይሁን እንጂ ሴት በወንድ አልተፈጠረችም፡፡ ነገር ግን የወንድ እና የሴት አፈጣጠር መቀዳደም ነበረበት፡፡

የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው ሲል ደግሞ የወልድ መገኛ እግዚአብሔር አብ ነው ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ (ዮሐ 16:28)›› እንዳለው። ወልድ ከእግዚአብሔር ወጥቶ መጣ እንጂ በእግዚአብሔር አብ አልተፈጠረም፡፡ የሴት መገኛዋ ወንድ ቢሆንም ሴት በወንድ እንዳልተፈጠረች ሁሉ  የወልድ መገኛው ወይም መሰረቱ እግዚአብሔር አብ ቢሆንም ወልድ በእግዚአብሔር አብ አልተፈጠረም፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸውና፡፡

“በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው” (1ኛ ጢሞ 2፡5)

‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው (1ኛ ጢሞ. 2፡5)›› የሚለውን ቃል ይዘው ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጃችን ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሐዋርያው የተናገረው ቃል ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ግን እንደሚከተለው ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ አንቀጽ ላይ መግለጽ የፈለገው አንድ እግዚአብሔር አለና ማለቱ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ አንድ የሆነ እግዚአብሔር (የዓለም ጌታ) አለ ማለቱ ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ማለቱ በአንድነት እግዚአብሔር ተብለው ከሚጠሩት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው(ማዕከላዊ) የሆነው ማለቱ ነው፡፡ አንድ አለ ብሎ መካከለኛው አንድ ብቻ መሆኑን መግለፁ በተለየ አካሉ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

ምክንያቱም እግዚአብሔር አብ መካከለኛ አይባልም፡፡ ለምን ቢባል ፍፁም አምላክ ብቻ ነው እንጂ ፍፁም ሰው አልሆነም፡፡ ወደፊትም አይሆንምና፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም መካከለኛ አይባልም ምክንያቱም ፍፁም አምላክ ብቻ ነው እንጂ ፍፁም ሰው አልሆነም፡፡ ወደፊትም አይሆንምና፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መካከለኛ ይባላል ምክንያቱም ፍፁም አምላክ ሆኖ ሳለ አምላክነቱን ሳይለቅ ፍፁም ሰው ሆኗልና፡፡ አምላክነትን ሰውነትንም የያዘ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህሪ አንድ ባህሪ በተዋህዶ የከበረ ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ሲል ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው ማለቱ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛ ነው ካለ በኋላ ወረድ ብሎ ከቁጥር 6 – 7 እንዲህ ይላል፡፡ ራሱን ለሁሉ ቤዛ ሰጠ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ በማለት ጌታ በሥጋ ማርያም ተገልፆ በምድር ይመላለስበት በነበረበት በገዛ ዘመኑ ማለትም በሥጋው ወራት ስለሁላችን ራሱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ ሐዋርያው ተናገረ፡፡በሌላም ቦታ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ሲገልጽ እንዲህ አለ፡፡ ዕብ. 9፡15 የፊተኛው ኪዳን ሲፀና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለሆነ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡ የተጠሩት ሰዎች የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ ማለትም መንግስተ ሰማያት ትወርሳላችሁ የዘላለምን ሕይወት ታገኛላችሁ የሚለውን የተስፋ ቃል እንዲይዙ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡ ማለትም የዘላለም የተስፋን ቃል(አዲሱን ኪዳን) የተቀበልነው በፍጡር ሳይሆን በፈጣሪ መካከለኛነት ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ ነው ማለቱ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው በመሆን አዲሱን ኪዳን ለሰው ልጆች የሰጠ በመሆኑ ማዕከላዊ (መካከለኛ) ተብሏል፡፡

“እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሳው” (ሐዋ 2፡32)

እግዚአብሔር የሚለው የመለኮት መጠርያ ሲሆን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫው ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ ወውእቱ ቃል ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ ቃል ወዝንቱ እምቀዲሙ ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ (ዮሐ 1፡2)፡፡ ስለዚህ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው አንዲት በሆኑት በአብ በራሱ እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተነሳ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሳ ተብሎ ይተረጎማል ይታመናል፡፡ ትንቢቱም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው (ወተንስአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለፀሮ በድህሬሁ) እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነሳ እንደሚነቃ ተነሳ የወይን ስካር እንደተወ እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹን በኋላው መታ መዝ( 77፡65)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት እኔ በሶስተኛው ቀን አነሳዋለሁ›› ያለው በራሱ መለኮታዊ ስልጣን እንደሚነሳ ሲናገር ነው (ዩሐ.ወ 2፥19)። በተጨማሪም «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራታለሁ…. እኔ በፍቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ላኖራት ስልጣን አለኝ ደግሞ ላነሳት ስልጣን አለኝ» (ዮሐ 10፥17) ብሏል። ስለዚህን ክርስቶስ የሞትን ማሰሪያ የሚያጠፋ መለኮታዊ ኃይል ያለው አምላክ ስለሆነ ሌላ አስነሺ አላስፈለገውም።

“በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” (ራዕይ 3፡14)

የዚህ አነጋገር ትርጓሜ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት ያለው የነበረው ለማለት ነው፡፡ የቀድሞው ትርጓሜ ‹‹እርሱ እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የነበረው›› ሲል ጽፎታል፡፡ እንግዲህ ከፍጥረት ሁሉ ቀድሞ የነበረ ነው ማለትና መጀመሪያ ተፈጠረ ማለት የሰማይና የምድር ያህል በአነጋገርም ሆነ በሀሳብ የተራራቁ ናቸው፡፡ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጠረው ፍጥረት ቀድሞ መኖሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርነቱ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ የነበረው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) እንዲህ አለ ብለህ ጻፍለት አለ እንጂ የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ፍጥረቱ አላለም፡፡

“እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” (ኤፌ 4፡24)

በእግዚአብሔር ምሳሌ (አርአያ) የተፈጠረው ቀዳማዊ አዳም እንጂ ሁለተኛው አዳም የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልካችን እንደምሳሌችን እንፍጠር በማለት አዳምን ፈጠረ፡፡ ዘፍ 1፡26 ይህ በንጽሕና በቅድስና በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው አዳም ትዕዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱ ተዋረደ ጎሰቆለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለወደቀው አዳም ክሶ የቀደመ ክብሩን ንጽሕናውን ቅድስናውን መለሰለት፡፡ በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረን አምላክ በሐዲስ ተፈጥሮ ፈጠረን፤ በኃጢአት ያረጀው የአዳም ባህርይ በክርስቶስ መስዋዕትነት ታደሰ፡፡ ይህንን ሲያስረዳና ዳግመኛ ወደ ኃጢአት እንዳንመለስ ሲመክረን እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት ልበሱት በእውነት በቅንነት በንጽሕናም አለ፡፡

“ያቺን ሰዓት ልጅም ቢሆን አያውቃትም” (ማቴ 24፡36)

ከፍጡራን ሲለየው ነው እንጂ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ሲለየው አይደለም፡፡ ልብ ቃልና እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር በቃል ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልናገረውም ቢል አያውቀውም እንደማይባል ወልድም ያቺ ዕለት ያቺ ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ በአብ ሰውሬ አቆያታለሁ እንጂ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጂ የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡ ባያውቃትማ ምልክቶቹን ባልተናገረም ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያውቃትም ቀኒቱን ለሰው ልጆች ሊገልጻት አልፈለገም፡፡ ይህም ቀኑ ሩቅ ነው ብለው ችላ እንዳይሉ ቅርብ ነው ብለው የዚህ ዓለም ኃላፊነታቸውን እንዳይዘነጉ ያደረገው ነው፡፡

አንድም ወልድ ቅድመ ተዋሕዶ የነበረ አላዋቂ ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት እያስነሳ የት ቀበራችሁት እያለ ይጠይቅ ነበር (ዮሐ 11)፡፡ አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረች ሴት ስትነካው ማነው የነካኝ እያለ ኃይል ከውስጤ ወጥቷል (ሉቃ 8፡43) ይል ነበር፡፡ ይህን የተናገረው ‹‹ቅድመ ተዋሕዶ አላዋቂ የነበረውን ሥጋ በእውነት እንደተዋሐደ ለማስረዳት ሲል›› ነው፡፡

አንድም አብ ለልጁ በመስጠት አውቋታል፡፡ ወልድ ግን በሥራ አላወቃትም ሲል እንዲህ አለ፡፡ ይህም ማለት የዓለም ፍጻሜ ዕለቱና ሰዓቱ በአብ ልብነት ትታወቃለች እንጂ በወልድ ቃልነት አልተነገረችም፤ ምጽአተ ክርስቶስ ትሁን ትፈጸም አልተባለችም ሲል ነው፡፡  አንድም ወልድ ብቻውን ያለ አብ አያውቃትም ሲል ነው፡፡ ከአብ ተለይቶ እንደማያውቃት ከልቡ የተሰወረች አለመሆንዋን፤ቀኒቱ በአብም ዘንድ የምትታወቅ መሆንዋን ለመግለጽ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ያውቃታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 2፡10 የጌታ መምጫ ቀን በሥላሴ ዘንድ ብቻ መታወቅዋን መግለጹንና ከዚህ ውጭ ግን ከሰማይ መላእክትም ሆነ ከምድራዊያን ወገኖች የተሰወረች መሆንዋን ገልጾልናል፡፡

“ወልድም ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል” (1ኛ ቆሮ 15፡24-28)

ይህንን ይዘው ‹‹ወልድ ለአብ ይገዛል›› የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን የዚህ ቃል ትርጉም እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን እንደሚከተለው ነው፡፡ሁሉን ካስገዛለት (ሥልጣን ከሰጠው) ከወልድ ሞት እንዲያንስ ይታወቃል፡፡ ሞት ከሁሉ በሁሉ ላይ እንዲሰለጥን ያደረገው ወልድ ነውና፡፡ ከሰው ደግሞ ሞት እንዲያንስ ይታወቃል፤በዕለተ ምጽአት ሞት ይሻራል፡፡ ሁሉ ሞትን ድል አድርገው ይነሳሉና፡፡ ለሞት ሁሉ በተገዛለት ጊዜ ያን ጊዜ ወልድም ሁሉን እንዲገዛ ስልጣን ሰጥቶት ለነበረው ለሞት ተገዝቷል፡፡ በዕለተ ዓርብ ጌታ ስለ ሰው ልጆች ለነበረው ለሞት ተገዝቷል፡፡ በዕለተ ዓርብ ጌታ ለሰው ልጆች ብሎ እንደሞተ ሲገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በገዛ ፈቃዱ ሞተ እንጂ እንደሌሎች ሰዎች በግድ የሞተ አይደለም፡፡ ራሱ ወዶ ፈቅዶ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አደረ እንጂ፡፡ ይህም ወዶ ፈቅዶ ያደረገው መሆኑን ጳውሎስ ሲገልጽ ‹‹ሁሉን ላስገዛለት ተገዢ ይሆናል›› አለ፡፡ እንዲገዛ ስልጣን ለሰጠው ለሞት ወዶ ፈቅዶ ራሱን ሰጠ ማለት ነው፡፡

“ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” (ማር 10፡18)

ጌታችን ራሱን ‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ›› ብሏል (ዮሐ 10፡11)፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ከሌለ፤ እርሱ ደግሞ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባህርይ በመለኮት አንድ ካልሆነ እንዴት ‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ ሊል ቻለ?›› ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም ያለው ጠያቂው ምስጋናን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽቶ (ቸር ብለው ቸር ይለኛል ብሎ ነበርና መጣጡ) ነበርና ‹‹ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም›› በማለት የእርሱን ቸር መሆን ሲገልጽ ከእግዚአብሔር በቀር ሰው ቸር ሊባል አይገባውም ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህም ሰውየው በልቡ አስቦ የመጣውን እንዳወቀበት ገልጾለታል፡፡ በተጨማሪም በሉቃስ 11፡27 ላይ  ‹‹ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፥ የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። እርሱ ግን፥ አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ›› የሚለው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የተነሱና የሚነሱ እጅግ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ያለመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሥጋዊ አዕምሮ በራሱ እየተረጎመ የሚሄድ ሁሉ በየዘመናቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት በክርስቲያኖች ላይ ውዥንብር ለመፍጠር ይሞክራል፡፡ ከዚህ ለመጠበቅ እውነተኛውን የሐዋርያትና የሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ አስቀድሞ መማርና ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራዊያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው፣ ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ።›› (ዕብ 13-7-8) እንዳለው ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ዋኖቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለዓለም ሁሉ ያስተማሩት እውነተኛው የወንጌል ቃል እያለ በየዘመናቱ የተነሱ መናፍቃን አስርገው ባስገቡት የስህተት ትምህርት ልንወሰድ አይገባም፡፡ ስለዚህም ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን አምላክ ሰው የሆነበትን ምስጢረ ተዋሕዶ ጠንቅቆ በማወቅና በማመን ለሌሎችም ማስተማር ይገባል፡፡ የጌታችን ተዋሕዶ ምሥጢር በእምነት እንደደከሙት የመሰናከያ አለት ሳይሆን የመዳን መሰረት እንዲሆንልን ስለ መድኃኒታችን የምናምነውን፣ የምንናገረውን እንወቅ። የቤተክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

ምስጢረ ሥጋዌ: ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው!

Incarnation_cover

ምስጢረ ሥጋዌ “ቃል ስጋ ሆነ… በእኛም አደረ” በሚለዉ የወንጌል ቃል ላይ የተመሰረተ ታላቅ የክርስትና ሃይማኖት ምስጢር ነዉ (ዮሐ 1፥14)። ይህ ምስጢር አምላካችን የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል በሥጋ በመወለዱ (ሰው በመሆኑ) አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰው አምላክ የሆነበት ልዩ ምስጢር ነው፡፡ የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት ከመጣበት ሞት የዳነበት ምስጢር ነው፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ‹‹ተዋሕዶ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘችበት እኛም “ክርስቲያን” የተባልንበት ምስጢር ነው፡፡ ሰማያዊው “ነገረ እግዚአብሔር” ለሰው ልጅ የተገለጠው በዚህ ምስጢር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ ታላቅነት ሲናገር “የተነገረውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፣ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62፡4)

የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት

ወልደ እግዚአብሔር፣ ወልደ ማርያም (የእግዚአብሔር አብ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡ የመጀመሪያው (ቀዳማዊ) ልደት ዘመን ከመቆጠሩ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢር (አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ) የተወለደው ልደት ነው (መዝ 2፥7 መዝ 109፥3 ምሳ 8፥25)፡፡ ሁለተኛው (ደኀራዊ) ልደቱ ደግሞ  ዓለም ከተፈጠረ አዳም ከበደለ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደው ልደት ነው (ገላ 4፥4 ኢሳ 7፥14 ኢሳ 9፥6 ዘፍ 3፥15 ፤18፥13 ፤ 12፥8 ፣ መዝ 106፥20)፡፡ ዘመን የማይቆጠረለት፣ በቅድምና ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ፣ ዓለምንም በአምላክነቱ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አካላዊ ቃል መለኮታዊ አካሉን፣ መለኮታዊ ባሕርይውን ሳይለቅ በተለየ አካሉ ንጽሕት፣ የባሕርያችን መመኪያ ከምትሆን  ከድንግል ማርያም በሥጋ በተወለደ ጊዜ አምላካዊ አካልና ባሕርይን ከሰው አካልና ባሕርይ ጋር ያለመጠፋፋት፣ ያለመቀላቀል ተዋሐደ እንጅ አካሉም ባሕርይውም አልተለወጠም፡፡

ሊቁ አባታችን ቅዱስ ፊሊክስ የጌታችንን ቀዳማዊና ደኀራዊ ልደቱን በተናገረበት አንቀጽ “ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው በኋላ ዘመን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረ እርሱ ነው፤ እርሱ ሰውም ቢሆን አንድ አካል፣ አንድ ገፅ፣ አንድ ባሕርይ ነው” በማለት ሁለቱን ልደታት አስተምሯል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ፊሊክስ 38፡10 በተጨማሪም ቅዱስ ናጣሊስ “ከእግዚአብሔር አብ በተወለደው በቀዳማዊ ልደቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፤ ከድንግል በተወለደው በደኃራዊ ልደቱ የሰው ልጅ ሆነ፡፡ እርሱ አንዱ በመለኮት ከአብ ጋር አንድ የሚሆን የሚተካከል ፍጹም አምላክ ነው፤ እርሱ ብቻ ከድንግል በተወለደው ልደት በሥጋ ከሰው ጋር አንድ የሚሆን ፍጹም ሰው ነው፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ናጣሊስ 46፡3-4)

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?

ምስጢረ ሥጋዌ አምላክ ሰው የሆነበት ሰውም አምላክ የሆነበት ምስጢር ነው ስንል ‹‹አምላክ ለምን ሰው ሆነ?›› የሚለውን በመጻሕፍት ማስረጃነት መዳሰስ ያሻል፡፡ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በሙሉ መርምሮ የሚያውቅ ባይኖርም በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠውና በሊቃውንት አስተምህሮ በተተነተነው መሠረት አምላክ ሰው የሆነባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ቤዛ ለመሆን (ኢሳ 64፥6 ኢሳ 53፥5 ዕብ 9፥26 ዮሐ 10፥15-18) (‹‹የወደቁትን ያነሳ ዘንድ፣ በክብር ከፍ ያደርገን ዘንድ››)፣ አርአያ ለመሆን (ዘፍ 3፥12 4፥8 13፥3፣ መዝ 61፥4 ማቴ 11:29 2ኛ ጴጥ 2፥21)፣ ፍቅሩን ለመግለጥ (ሆሴ 14፥4) (ዮሐ 3፥16) (1ኛ ዮሐ 4፥19፣ ሮሜ 5፥8፣ ኤፌ 2፥4)፣ አምላክ መኖሩን ለመግለጽ (ሮሜ 1:19-20 ዮሐ 14:8-9 ዮሐ 1:18)፣ የሰይጣንን ጥበብ ለመሻር (ዕብ 2:9;14;15) እና እነዚህን የሚመስሉት ናቸው፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ አምላክ ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ሲያስረዳ “ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከሕይወት የተገኘ ሕይወት፤ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን ወደዚህ ዓለም የላከው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የእኛን ባሕርይ ይዋሐድ ዘንድ ጌትነቱንም ወደማወቅ ያደርሰን ዘንድ ነው፡፡” ብሏል፡፡ ዮሐ. 6፡55፣ ዮሐ. 11፡25፣ ገላ. 4፡4፣ ኤፌ. 2፡16፣ ሐዋ. 4፡12 (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ 15፡2) ቅዱስ እለእስክንድሮስም “እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምን አተጋው? በጨርቅ ይጠቀለል ዘንድ፣ በበረት ይጣል ዘንድ፣ ከሴት (ከድንግል) ጡት ወተትን ይተባ ዘንድ፣ በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው? ሕግ አፍራሽ ጲላጦስ ይዘብትበት ዘንድ፣ በመስቀል ይሰቀል ዘንድ፣ በመቃብር ይቀበር ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ይነሣ ዘንድ ምን አተጋው? በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን ያድነን ዘንድ፣ ለእኛ ብሎ አይደለምን?” በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት በአንክሮ ገልጾታል፡፡ ኢሳ. 7፡14፣ ፊልጵ. 2፡5-9፣ 1ኛ ቆሮ. 1፡21-25 (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ እለእስክንድሮስ 16፡2-3)

አምላክ እንዴት ሰው ሆነ?

ቅድመ ተዋሕዶ (ከተዋሕዶ በፊት) ሁለት ባሕርያት ሁለት አካላት ነበሩ፡፡ እነዚህም መለኮትና ትስብዕት (ሰው) ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ፈጣሪ፣ በባሕርይ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሲሆን በሁሉም ቦታ ያለ፣ ዘላለማዊ፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ ሁሉን የፈጠረ ነው፡፡ በአንጻሩ ትስብዕት (ሰው) ደግሞ አራት ባሕርያተ ሥጋ (ከአፈር፣ ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኃ የተሠራ) እና ሦስት ባሕርያተ ነፍስ (ልባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት) ያለችው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሲሆን ውሱን፣ የሚደክም፣ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚታመም፣ የሚያንቀላፋ፣ የሚሞት ነው፡፡

ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ሲባል ረቂቅ መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፣ ግዙፍ ሥጋ ግዙፍነቱን ሳይለቅ ማለትም ግዙፍ ሥጋ ረቂቅ መለኮትን ግዙፍ ሳያደርገው፣ ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ሳያረቀው በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ማለት ደግሞ መለኮት የእርሱ ያልሆነውን የሥጋ ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ፣ ሥጋም የእርሱ ያልሆነውን የመለኮት ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ቴዎዶስዮስ “ከተዋሕዶ በኋላስ ሁለት ባሕርይ አንልም፤ እንደ ንጹሐን አባቶቻችን ክርስቶስ (መለኮትና ትስብእት) በአንድ አካል ሁለተኛ የሌለው አንድ እንደሆነ እንናገራለን እንጂ፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ 82፡37) ቅዱስ ቄርሎስም “የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ” በማለት አንድ አካል አንድ ባህርይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አምላክ ሰው የሆነው ያለመለወጥ (ዘእንበለ ውላጤ) ነው፡፡ ይህም በቃና ገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ እንደተለወጠው ሳይሆን የመለኮትነቱ አካል፣ ባሕርይ ወደ ትስብዕት አካል፣ ባሕርይ ሳይለወጥ፣ የትስብዕትም አካል፣ ባሕርይ ወደ መለኮትነት ሳይለወጥ ነው በተዋሕዶ አምላክ ሰው፣ ሰውም አምላክ የሆነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ አምላክ መለወጥ የሌለበት መሆኑን ሲናገር “ሁሉን የፈጠረ ነው፤ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ፤ ሰውም ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ እግዚአብሔር ቃል ነውና እርሱ መቸም መች አንድ ነው፤ የመለኮቱ ባሕርይ ወደ ሰውነቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤ የሰውነቱ ባሕርይም ወደ መለኮቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤ ደንግል ማርያም አንድ አካል ሆኖ ወለደችው እንጂ፤ ሰብአ ሰገልም አንድ ባሕርይ ሁኖ ሰገዱለት እንጂ፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ 60፡17)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለመመለስ (እንበለ ሚጠት) ነው፡፡ የሙሴ በትር እባብ ከሆነች በኋላ ተመልሳ በትር እንደሆነችው መመለስ (ሚጠት) የሌለበት ነው፡፡ ምስጢረ ተዋሕዶ የተፈጸመው ያለመቀላቀል (ዘእንበለ ቱሳሔ) ነው፡፡ ይህም ወተትና ውኃ ሲቀላቀሉ ሌላ ሦስተኛ መልክ ያለው ነገር እንደሚሰጡት ሳይሆን መለኮትና ትስብዕት የተዋሐዱት በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ነው፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ስለተዋሕዶ ምስጢር ሲናገር “የምናምንባት ሃይማኖት ይህች ናት፤ መስሎ በመታየት በሐሰት አልተወለደም፤ ባሕርይን እውነት በሚያደርግ በከዊን ነው እንጂ፤ ይኸውም በተዋሕዶ እግዚአብሔርም ሰውም መሆን ነው፤ እርሱ ሰው የሆነ አምላክ ነውና፡፡” በማለት አስረድቷል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ 84፡13)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለማደር (ዘእንበለ ኅድረት) ነው፡፡ ሰይፍ በሰገባው፣ ዳዊትም በማኅደሩ እንደሚያድር መለኮትም በሥጋ ላይ አደረበት የሚል የንስጥሮስ ክህደት በተዋሕዶ ዘንድ የተወገዘ ነው፡፡ የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረበው ወይም እንጀራ በእንጀራ ላይ እንዲሚደራረበው ሳይሆን ያለመደራረብ (ዘእንበለት ትድምርት) ነው፡፡ የተዋሕዶ ምስጢር ሥጋና ነፍስ ተዋሕደው ኖረው በሞት ሰዓት እንደሚለያዩትም ሳይሆን ያለመለያየት (ዘእንበለ ፍልጠት) ነው፡፡ ስለዚህም ነገር ሊቁ ቅዱስ አዮክንድዮስ “ሥጋ በሠራው ሥራ ሁሉ መለኮት አንዲት ሰዓት ስንኳን በማናቸውም ሥራ ከእርሱ እንዳልተለየ እናምናለን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ሰው በሆነ ጊዜ መለኮቱን ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ አንድ እንደ አደረገ እናምናለን፡፡ መለኮትም ከትስብእት ጋር ከተዋሐደ በኋላ ከሥራ በማናቸውም ሥራ አንድነታቸው ፈጽሞ አልተለየም፤ መለየት የለባቸውምና፤ ለመለኮት ጥንት እንደሌለው ከትንሣኤው በኋላ ለትስብእትም እንዲሁ ፍጻሜ የለውም፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ (ዕብ. 13፡8) )ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አዮክንድዮስ 44፡4-5)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ እንጨትና ዛቢያው (መቁረጫው) ተዋደው በኋላ እንደሚነጣጠሉትም ሳይሆን ያለመነጣጠል (ዘእንበለ ቡዐዴ) ነው፡፡ በዚህም አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር እጅግ ድንቅ ነው፤ ዓለምን ከፈጠረበት ምስጢርም ይበልጣል ይላሉ ሊቃውንት፡፡ አምላክ በተዋሕዶ ሰው ስለሆነበት ምስጢር ቅዱስ መጠሊጎን ሲናገር “የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ነፍስን ሥጋን ነስቶ ሰው ሆነ ባልን ጊዜም ስለዚህም ነገር ቢሆን እነዚያ እንደሚያምኑ መቀላቀል የለበትም፤ የቃል ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ወደመሆን የሥጋ ባሕርይም የቃል ባሕርይን ወደመሆን አልተለወጠም፤ ሁለቱ ባሕርያት ያለመለዋወጥ ባለመቀላቀል ጸንተው ይኖራሉ እንጂ” በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ. 1፡1-18፣ ዮሐ. 3፡18፣ 1ኛ ቆሮ. 8፡6) (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ መጠሊጎን 43፡6)

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው!

በተዋሕዶ የከበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡ ፍጹም አምላክነቱ አምላካዊ መስዋእትን ሲቀበል (ሉቃ. 2፡11)፣ ወጀቡን ጸጥ ሲያደርግ (ማቴ 8፡ 23)፣ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን ሲፈጥር (ዮሐ 9፡6)፣ ኃጢአትን በስልጣኑ ሲያስተሰርይ  (ማር. 2፡5)፣ በተዘጉ ደጆች ሲገባ (ዮሐ 20፡26)፣ ውኃውን ወይን ጠጅ ሲያደርግ (ዮሐ 2፡1-11)፣ እንዲሁም በአብና በመንፈስ ቅዱስ፣ በመላእክት እና በሰዎች ምስክርነት (ማቴ. 3፡16-17፣ ማቴ. 17፡5፣ ሉቃ 2፡11 ኢሳ 9፡6 ማቴ 2፡11) ታውቋል፡፡በእነዚህና በመሳሰሉትም ጌታችን እኛን ያከብረን ዘንድ ሰው ሆነ እንጂ ከአምላክነቱ ያልተለየ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ምስጢር ዘቅዱስ ቴዎፍሎስ “ሰው ሆኖ ከድንግል ተወለደ፤ ከኃጢአት በቀር የኛን ሥራ ሁሉ በመሥራት መሰለን፤ ልዩ ድንቅ በሆነ ባሕርይ ሰው በሆነ ጊዜ በመታየቱ የሰውን ባሕርይ አከበረ፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎፍሎስ 69፡7)

ፍጹም ሰው መሆኑም እንዲሁ በግዕዘ ሕፃናት ሲወለድ (ማቴ. 2፡11)፣ በታንኳ ውስጥ ተኝቶ ሲያንቀላፋ (ማቴ 8፡23)፣ ምራቁን ወደ መሬት እንትፍ ሲል (ዮሐ 9፡6)፣ ሠርግ ቤት ተጠርቶ ሲሄድ (ዮሐ 2፡1)፣ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ በአንዲት ቤት ሲታይ (ማር. 2፡1)፣ ከትንሣኤ በኋላ ሲመገብ (ሉቃ 24፡42) እና በመሳሰሉት ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው የሆነ አምላክ›› መሆኑን እናምናለን፣ እናውቃለንም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ይህንን ድንቅ ምስጢር “ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ፣ ቀዳማዊ ሆነ፤ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፤ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፤ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡ (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም)

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው!

ቅዱሳት መጻህፍት በተዋሕዶ የከበረው ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የባሕርይ አምላክ መሆኑን ያረጋግጡልናል፡፡ ለምሳሌም ያህል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እርሱ ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው” (ሮሜ 9፡5) ብሎ ፍጹም አምላክነቱን ሲመሰክር ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ ደግሞ “እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” (1ኛ ዮሐ 5:20) በማለት የባህርይ አምላክነቱን አረጋግጦልናል፡፡ ትንሣኤውን ተጠራጥሮ የነበረው ቶማስም “ጌታዬ አምላኬም” ሲል መስክሮ (ዮሐ 20:28) የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል” (ራዕ 1:8) በማለት ጌታችን “እኔ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” (ማቴ 22: 31) ያለውን አጠናክሮ አስፍሮታል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጌታችንን ያለመለየት፣ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ሲያስረዳ “የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ቢነገርም በእውነት ሰው ሆኗል፤ አምላክ እንደመሆኑም ያውቀው ዘንድ የሚቻለው ሰው የለም፤ ስለዚህም አብሲዳማኮስ ተባለ፤ ይኸውም ከሁለት አንድ የሆነ ማለት ነው፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሰው ነው” ብሏል፡፡  (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡21)

የተዋሕዶን ምስጢር በምን እንመስለዋለን?

የተዋሕዶን ነገር ጠንቅቀው የሚገልጹ ምሳሌዎች ባይገኙም ምስጢሩን ለሰዎች ለማስረዳት ያህል አባቶቻችን ያስተማሩንን ፍጹም ያልሆኑ ምሳሌዎች (ምሳሌ ዘየሐፅፅ፣ ከሚመሰልለት የሚያንስ ምሳሌ) እንጠቀማለን፡፡ የተዋሕዶ ምስጢር ከምሳሌዎች በላይ መሆኑን ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሲናገር “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደ ሆነ፣ ከቅድስት ድንግልም መወለዱ እንዴት እንደ ሆነ አትጠይቀኝ፤ እርሱ በባሕርይው ከአብ ተወልዶዋልና፤ ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ተወልዶዋልና አምላክ ነው፤ ሰውም ነው” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶጦስ 53፡16) ቅዱስ ኤፍሬምም “ከሕሊናት ሁሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፣ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፤ ከእርሷም እርሱ ፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤፍሬም 47፡2) በማለት እንደተናገረው የተዋሕዶ ነገር ከምሳሌዎች በላይ እጅግ ድንቅ ነው፡፡እነዚህም ምሳሌዎች ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሥነ ፍጥረት የተገኙ ናቸው፡፡

ሙሴ ባያት ዕፀ ጳጦስ:-  ሐመልማሉ የትስብእት ምሳሌ ነበልባሉ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው ሐመልማሉ ነበልባሉን ሳያጠፋው በአንድነት ታይተዋል (ዘፀ 3:2)፡፡ አንዱ አንዱን ሳያጠፋ እንደታዩ ሥጋ ከመለኮት ጋር ሳይጠፋፉ አንድ የመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡

በኢሳይያስ ፍሕም:  ምሳሌነት ደግሞ እሳት የመለኮት ከሰል የሥጋ ምሳሌ ናቸው፡፡ እሳቱ ተለውጦ ከሰል ፤ ከሰሉ ተለውጦ እሳት አልሆነም፡፡ ሁለቱም ከሰል ከሰልነቱን እሳትም እሳትነቱን ሳይለቅ ተዋሕደው ፍሕም ሆነዋል (ኢሳ 6:6)፡፡

የጋለ ብረት ምሳሌነት፡- አንድን ብረት ከእሳት ባስገቡት ጊዜ ብረትነቱን ሳይለቅ እሳቱም እሳትነቱን ሳይለቅ በብረቱ ቅርፅ ልክ እሳት ይሆናል፡፡ ይህንንም እሳትና ብረቱ ስለተዋሐዱ የጋለ ብረት ብለን እንጠራዋለን እንጂ ብረት ወይም እሳት ብቻ ብለን አንጠራውም፡፡  ይሁንና ብረት እሳት ሲነካው በቀላሉ ስለሚቀጠቀጥ ይህ “ምሳሌ ዘየሐፅፅ” ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ስለዚህ ምሳሌ ሲናገር “በእግዚአብሔር ቃል በረቂቅ ባሕርይ የሆነውን ተዋሕዶ አንካድ፤ ብረት ከእሳት በተዋሐደ ጊዜ ከእሳትም በመዋሐዱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ እንዲያደርግ፤ ብረት በመዶሻ በተመታ ጊዜ ከእሳት ጋር በአንድነት እንደሚመታ ግን ከመዶሻው የተነሣ የእሳት ባሕርይ በምንም በምን እንዳይጎዳ ሰው የሆነ አምላክ ቃል በመለኮቱ ሕማም ሳይኖርበት በሥጋ እንደታመመ እንዲህ እናስተውል፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 73፡12)

የሰው ነፍስና ሥጋ ውሕደት ምሳሌ፡- የሰው ልጅ ከእናቱ ማሕፀን ሥጋና ነፍስን ነስቶ ፅንስ ከሆነበት ቀን ጀምሮ ይህ ነፍስ ነው ይህ ሥጋ ነው ብሎ መለያየት እንደማይቻል ሁሉ ሥጋና መለኮትም ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ሥጋ ነው ይህ መለኮት ነው፤ ይህ ሥጋዊ ሥራ ነው ይህ መለኮታዊ ሥራ ነው ተብሎ መክፈል አይቻልም፡፡ ነገር ግን ነፍስና ሥጋ በሞት ስለሚለያዩ ይህም “ምሳሌ ዘየሐፅፅ” ነው፡፡

የወልደ እግዚአብሔር የተዋሕዶ ስሞች

የእግዚአብሔር ወልድ የተዋሕዶ ዋና ዋና ስሞች የሚባሉት አማኑኤል፣ ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ናቸው፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ከእኛ ጋር ስለኖረ የወጣለት ስም ነው (ኢሳ 7፡14 ማቴ 1፡23)፡፡ ኢየሱስ ማለት ደግሞ መድኀኒት ማለት ነው፡፡ ደቂቀ አዳምን ሊያድን ሰው ሁኗልና ከእግዚአብሔርም በቀር መድኀኒት ሆኖ ዓለምን ሊያድን የሚችል የለምና (ኢሳ 45:20-24፤ሆሴ 13:4፤ቲቶ 1:3)፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ማለት መሲህ፣ የተቀባ፣ ሹም፣ የተሾመ፣ ባለስልጣን ማለት ነው፡፡ የተቀባ የተሾመ ሲባል ግን ለእርሱ ቀቢ ሿሚ ኖሮት አይደለም ቀቢውም ሿሚውም ተቀቢውም ተሿሚውም አንድ እርሱ ነው እንጂ (ዮሐ 4:25-30)፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለክርስቶስ ሲናገር “ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ለዘላለሙ የሚኖር፤ ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነውና ስለርሱ ስንናገር ያልተፈጠረ ነው እንላለን፡፡ (መዝ. 102(101)፡ 25-27፣ ዕብ. 1፡1-14) ሰው ነው ያልነውም ስለ እኛ ባደረገው ተዋሕዶ ደካማ ባሕርያችንን ስለተዋሐደ ነው” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ 35፡2-3)

በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የተነሱ የኑፋቄ ትምህርቶች

በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ እጅግ ብዙ የኑፋቄ ትምህርቶች አሉ፡፡ እነዚህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ መልካቸውን የሚለዋውጡ ናቸው፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሱስ “ሰው ብቻ ነው” ብለው አምላክነቱን የካዱ፣ መለኮትነት የለውም፣ ሰው ብቻ ነው የሚሉ መናፍቃን ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ “መለኮት ብቻ ነው” ብለው ሰውነቱን (ሰው መሆኑን) የካዱና ሰው መስሎ በተአምራት ተገለጠ የሚሉ (ግኖስቲክስ) ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በእውነት ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ከሥጋዌ (ሰው ከመሆን) በኋላም መለኮት ከሥጋ ለቅጽበተ ዓይን እንኳ የተለየበት ጊዜ የለም፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት የአምልኮ ስግደትና ያቀረቡለት መብዓ ፍጹም አምላክነቱን ያሳየናል፡፡ ፍፁም አምላክ እንደመሆኑ ስግደትን፣ አምሐን ተቀበለ፤ ፍፁም ሰው እንደመሆኑም “ሕፃን” ተባለ፡፡ (ማቴ. 2፡9-11)

ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ የተነሱ “ልጅነት ተሰጠው” የሚል አስተሳሰብ ይዘው እርሱ ሲወለድ ሰው ብቻ ነበር፣ በጥምቀት ወቅት መለኮት አደረበት የሚል የስህተት ትምህርት ያስተማሩ መናፍቃንም ነበሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሥጋ ማርያም ሲወለድም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሰረበት አንቀጽ አስተምሮናል፡፡ (ሉቃ. 2፡32) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘምን የተነሳው አቡሊናርዮስ ኢየሱስ ክርስቶስ “በሥጋ ሰው በነፍስ መለኮት” ነው በማለት አእምሮው መለኮት ነው የሚል የስህተት ትምህርት ሲያስተምር በቅርብ ዘመን የተነሳው ቶማሲየስ ደግሞ “ሰው ለመሆን ሲል መለኮቱን ወሰነው/ተወው” የሚል ስህተትን ካስተማሩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ኑፋቄን ያስተማረው በቁስጥንጥንያ ጉባዔ የተወገዘው ንስጥሮስ ነው፡፡ ንስጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል ነው” በማለት የኅድረት ኑፋቄን ሲያስፋፋ ነበር፡፡ ማርያም የወለደችው ሰው ነው፣ መለኮት አደረበት ብሎ ኅድረትን ያስተማረ እርሱ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን በወንጌሉ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ. 1፡14) እንዳለ በስጋ ማርያም በተጸነሰ ጊዜም ከአምላክነቱ ሳይለይ በእኛ ማደሩን መስክሮልናል፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ የኅድረት ትምህርት የተወገዘ መሆኑን ሲናገር “ክርስቶስ አምላክ ያደረበት ሰው እንደሆነ የሚናገር ቢኖር የተወገዘ ይሁን፤ አምልኮተ እግዚአብሔርን የዘነጋ ያ ሰው የባሕርይ ገዥ ክርስቶስን ከተገዦች እንደ አንዱ አደረገው፡፡” ብሏል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አቡሊዲስ 42፡19 በዚያው ወቅት የተነሳው አውጣኪ ደግሞ “አንድ (ሦስተኛ) ባህርይ (የሰውና የመለኮት ቅልቅል)” የሚል ፍልስፍናን ይዞ ብቅ አለ፡፡ አውጣኪ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋም ከመለኮትም የተለየ (የሁለቱ  ቅልቅል) ሦስተኛ ባህርይ ያዘ” ሲል ክህደትን ሲያስተምር ነበር፡፡

ለቤተክርስቲያን ሁለት መከፈል ምክንያት የሆነው ግን “ሁለት ባህርይ አንድ አካል” የሚለው የኬልቄዶናውያን ምንፍቅና ነበር፡፡ ይህ ኑፋቄ ከንስጥሮስ ትምህርት “ሁለት ባህርይ” የሚለውን ሀሳብ የወሰደ፣ የምዕራባውያኑ አስተምህሮ፣ ለቤተክርስቲያን ሁለት መከፈል ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በ451 ዓ.ም በሊዮ እና በንግስቲቱ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ጉባዔ እውነተኞቹ አባቶች ላይ መከራ በማድረስ ይህንን ኑፋቄ ተቀብሎ ስለተጠናቀቀ ቤተክርስቲያናችን አትቀበለውም፡፡ ስሙንም “ጉባዔ አብዳን” ወይም “ጉባዔ ከለባት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ ከእነዚህ ኑፋቄዎች ተርታ የሚመደበው በኢትዮጵያ ያለው “ጸጋና ቅባት” የሚባለው ነው፡፡ ይህም አልፎንሶ ሜንዴዝ የተባለ ፖርቹጋለዊ በሸዋ እና በጎጃም ላሉ “ካህናት” ያስተማረው ሲሆን “ኢየሱስ  በእናቱ ማሕጸን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ በጸጋ አምላክነትን (ቅባቶች: የባሕሪይ አምላክነትን ይላሉ) አገኘ” ይላሉ:: ይህም ምስጢረ ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን የሚያፋልስ ክህደት ነው፡፡

የተዋሕዶ አስተምህሮስ ምንድን ነው?

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የሆነ ሥግው ቃል ነው ብላ ታምናለች፤ ታስተምራለች፡፡ መለኮት ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በሥጋ ተወለደ፤ መለኮትና ትስብዕት የተዋሐዱት ያለመለወጥ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለያየት፣ ያለመነጣጠል ነው በማለት ቅዱስ ቄርሎስ እንዳስተማረው ታምናለች፡፡ ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደው ወልድ ድኅረ ዓለም በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ በማለት አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር ተዋሕዶ ነው ትላለች፡፡ ይህም የኦርየታል አብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ ነው፡፡ ይህንን ምስጢር ያመሰጠሩት ሊቃውንት ምስጢረ ሥጋዌን በሃይማኖተ አበው በብዙ መልኩ ገልፀውታል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፡፡

ስለተዋሕዶ ነገር ቅዱስ አትናቴዎስ “አሁንም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ሰምተህ ዕወቅ፤ አምላክ ብቻ ከሆነማ እንደምን በታመመ ነበር? ወይስ እንደምን በሰቀሉት ነበር? ወይስ እንደምን በሞተ ነበር? ይህ ሥራ (ሕማም፣ ሞት) ከእግዚአብሔር የራቀ ነውና (ዘዳግ. 32፡40-49)፡፡ ሰው ብቻ ከሆነ በታመመ በሞተ ጊዜ ሞትን እንደምን ድል በነሣው ነበር? ሌሎችንስ በነፍስ በሥጋ እንደምን ባዳነ ነበር? ይህ ከሰው ኀይል በላይ ነውና (1ኛ ቆሮ. 5፡13፣ ዕብ. 5፡1-4) ፡፡ እርሱ ታሞ ሞቶ ፍጥረቱን አዳነ፣ ሞትንም ድል ነሳ፤ ሰው የሆነ አምላክ ነውና” በማለት አስተምሮናል፡፡ (ሉቃስ 24፡5፣ ዮሐ. 5፡26-27፣ ሮሜ. 8፡3-4) (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 27፡6-8)

ቅዱስ ኤራቅሊስም “እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንዲህ እናምናለን፡፡ መለየት መለወጥ የሌለበትን አንዱን ሁለት አንለውም፤ ሁለት ገዥ፣ ሁለት መልክ፣ ሁለት አካል፣ ሁለት ግብር፣ ሁለት ባሕርይ ነው አንለውም፤ እንደተናገርኩ ሰው ሆነ እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፡፡ ይህን ገልጠን እናስተምራለን፤ ቃልን ከሥጋ አንድ አድርገን አንዲት ስግደትን እንሰግድለታለን፡፡” በማለት የተዋሕዶ አስተምህሮ አንድ አካል አንድ ባህርይ መሆኑን ገልጾታል (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48፡6-7)፡፡ ቅዱስ አፍሮንዮስም “እንግዲህ እንጠበቅ መለኮትንም ከሥጋ አንለይ፡፡…አንድ ጊዜ የጌትነቱን ነገር ይናገራል፤ አንድ ጊዜም የሕማሙን የሞቱን ነገር ይናገራል፤ እግዚአብሔር ነውና የጌትነቱን ነገር ያስተምራል፤ የእግዚአብሔርም ቃል ነው፤ ሰውም እንደመሆኑ የሰውነቱን ነገር ይናገራል፤ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፡፡” በማለት መለኮትና ትስብዕት ፍጹም መዋሐዳቸውን አስተምሯል (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አፍሮንዮስ 51፡8-9)፡፡

አምላክ ሰው በመሆኑ ለመላእክትም ታያቸው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ስለዚህ ነገር ሲናገር “በስጋ ተወልዶ ለመላእክት ታያቸው፤ ሰው ሳይሆን አላዩትም ነበርና በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ተገባው ሰውንም ስለወደደ በምድር ሰላም ሆነ አሉ፤ በአሕዛብም ዘንድ ተነገረ፤ በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ እንደሆነ ዓለም ሁሉ አመነበት፡፡ ብሏል፡፡ (ሉቃ. 2፡14፣ 1ኛ ጢሞ. 3፡16)  ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 79፡56 ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም “አገልጋይ ይሆን ዘንድ ወደ እዚህ ዓለም ከመጣ ከወልድ የተነሣ የአባቱ አገልጋዮች መላእክት እጅግ አደነቁ፤ በመለኮቱ ግን ማገልገል የለበትም፤ በወገቡ የታጠቀውን ማድረቂያ አይተው መላእክት አደነቁ፤ ስሙ ከፀሐይና ከጨረቃ በፊት የነበረ እርሱ አገልጋይ ሆነ፡፡” በማለት የአምላክ ሰው መሆኑ በመላእክትም ዘንድ የተደነቀ መሆኑን ተናግሯል  (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ 88፡9)፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ቅዱስ ዲዮናስዮስ እንደተናገረው “ሰው ከመሆኑ በፊት ሰው ከሆነም በኋላ ካንድ ወልድ በቀር የምናውቀው አይደለም፡፡” የሚል ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዲዮናስዮስ 93፡2)

ምሥጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርሰቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል በተዋሕዶ መወለዱን የሚያስረዳ አምላካችን የሰይጣንን ተንኮል ያፈረሰበት የማይመረመር አምላካዊ ጥበብ ነው፡፡ ጌታችን ሰው የሆነውም አባታችን አባ ሕርያቆስ “ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፤ ሳይወሰን ፀነስሽው፣ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀንሽ ተወሰነ” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 46) ብሎ እንዳስተማረው ሰው ከመሆኑ የተነሳ ከአምላክነቱ ምንም ምን የጎደለበት የለም፤ ሰው ሲሆን በአምላክነት ወዳልነበረበት ዓለም የመጣ ሳይሆን እንደ አምላክነቱ በእቅፉ ወደተያዘች ዓለም የተጎሳቆለውን የሰውን ባሕርይ በቸርነቱ ያከብር ዘንድ ከኃጢአት በቀር የሰውን ባሕርይ ተዋሕዶ ፍፁም ሰው ሆነ እንጂ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋዌውን ነገር በአግባቡ ያልተረዱ ብዙዎች ለእኛ ብሎ በፈቃዱ ያደረገው ቤዛነት “የመሰናከያ ዓለት” ሆኖባቸው በክህደት ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት፣ አባቶቻችንም እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ እናምናለን፣ እንመሰክራለንም፡፡ የወልድን ሥጋዌውን ማመን የመዳናችን መሰረት ነውና፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር