ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፫)

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

ባለፉት ሁለት ተከታታይ የአስተምህሮ ጦማሮች ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንዳለበትና በግጥም መልእክትና ኪነ-ጥባበዊ ይዘት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን የሚመለከቱ ዳሰሳዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል ደግሞ ከዜማ ስልትና ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ይዳሰሳሉ፡፡

ከዜማ ስልት ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መለያ ከሆኑ መንፈሳዊ ጸጋዎች አንዱ በቅዱስ ያሬድ በኩል የተገለጠው የዜማ ሀብት ነው፡፡ የካሴት መዝሙራት የቅዱስ ያሬድን የዜማ ስልት በመከተል ካልተቃኙ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ ለዛቸው ይጠፋል፡፡ ይሁንና በርካታ የካሴት መዝሙር አዘጋጆች የቤተክርስቲያኒቱ ሀብት የሆነውን ያሬዳዊ ዜማ ባለማወቅ ወይም አውቆ ቸል በማለት፣ ለቤተክርስቲያን እንግዳ የሆኑ፣ መንፈሳዊ መሰረት የሌላቸው፣ ለንግድ ሲባል የሚሸቀጡ ዜማዎችን የመጠቀምን ልማድ እየጨመሩ እንደመጡ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በአሳፋሪ መልኩ የዘፈን ዜማ እየገለበጡ በመዝሙር ካባ ሲነግዱበት ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

የያሬዳዊ ዜማ መሠረቱና ምሳሌነቱ እንዴት ነው?

በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ ፸፬:፲፬ ተብሎ የተፃፈው ንባብ ከሚተረጎምባቸው ትንታኔዎች አንዱ የኢትዮጵያ መለያ የሆነው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ልዩ ስጦታና ለኢትዮጵያ የተሰጠ መላእክትን በምስጋናው መስለን የምንተባበርበት ነው:: ቅዱስ ያሬድ በብዙ ድካምና ጥረት ዜማን ተምሯል፣ ፈጥሯል፡፡ የጸጋ ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ያለመታከት ዜማን ለመማር፣ ለመፍጠር ይተጋ ለነበረው ለቅዱስ ያሬድ በቅዱሳን መላእክት በኩል ሰማያዊ ዜማ ገልጦለታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከመላእክት ያገኛቸው በመደብ ሦስት ይኸውም ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ሲሆኑ አንድ መሆናቸው የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት ነው:: ትርጉማቸውም ግዕዝ በአብ ሲመሰል “ርቱዕ ሎቱ ነአኩቶ” ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን ማለት ነው። ዕዝል ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም አራራይ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን የሚያራራ ጥዑም ዜማ ማለት ነው። ጥዑም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተጎናጸፍን ለማስረዳት ነው። የቅዱስ ያሬድ የዜማዎቹ ባህርያት የፊደል ቅርጽ የሌላቸውና ምሳሌነት ያላቸው ፰ ዓበይት ምልክቶች (symbols) አሉት። የእነዚህም ምልክቶች ምሳሌያቸውና ምሥጢራቸው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ መንገላታት የሚያስታውሱ ናቸው።

የዘመናችን የአማርኛ መዝሙራት የዜማ ችግሮች ምንድን ናቸው?

በዘመናችን ያሉ በርካታ የካሴት መዝሙራት ካሉባቸው ችግሮች አንዱ ከዜማ ስልት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በምስጢር ይህን የመሰለ ሰማያዊ ስጦታና አስደናቂ የሆነ ያሬዳዊ ዜማ ግምጃ ቤት ሁና ሳለ ለምስጋና መዝሙር የሚሆን ዜማን ለገበያ ይመቻል ከሚል ሃሳብ ከሠርግ ቤት ዘፈን፣ ለንስሐ መዝሙር የሚሆን ዜማን ደግሞ ከለቅሶ ቤት ሙሾ መውሰድ እንደአባቶች አባባል ‘የአባይን ልጅ …’ ያሰኛል፡፡ የቤተክርስቲያን ለዛ የሌለው ‹‹ዜማም›› ቢሆን ገና ለገና ከሌላ ቦታ አልተቀዳም ተብሎ ቸል መባል የለበትም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት የሌለውን ዜማ ከሌላ ቦታ ወስዶ ለ‹‹ዝማሬ›› ማዋል መንፈሳዊነትን ከመጉዳቱም በላይ የዜማውን ባለቤት የባለቤትነት መብትም መጋፋት ነው፡፡ ስለዚህ በምድራዊም በሰማያዊም ሕግ ያስጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል የዜማ ስልታቸው ከመዝሙር ጋር የሚመሳሰሉ ተብለው በአጥኚዎች ከተቀመጡት መካከል ‹‹ሐና ዘመዴ፣ እመኑ በእርሱ፣ አምስቱን ሐዘናት›› የሚሉትንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም መልኩ ‘ማርያም ድንግል ንጽሕት’ በሚል የተዘመረ አንድ ዝማሬ ዜማው ከአንድ ዘፈን ጋር በቀጥታ ሲመሳሰል ሙሽራዬ የወይን አባባዬ የሚለው ደግሞ ዜማው ለመዝሙር ከዋሉት ዘፈኖች መካከል ይገኛል፡፡

የዜማ ችግሮች ያደረሱት ተጽዕኖስ ምንድን ነው?

የዜማ ችግር ያለባቸው ‹‹መዝሙሮች›› ከመብዛታቸው የተነሳ ወጣቱ ምዕመን ከያሬዳዊ መዝሙሮች ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ያሬዳዊ ባልሆኑ ‹‹መዝሙሮች›› እየተሳበ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ይህንን የለመደ ሰውም የዘፈን ቅላጼ ያላቸው ‹‹ዘማሪያን›› እነዚህን መዝሙሮች ሲዘምሩ ማየትና መስማትም ይናፍቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያኒቱን ዜማ የሚጠቀሙ መንፈሳዊ መዝሙሮች ቸል እየተባሉ መዝሙር መሳይ ዘፈኖች (አንዳንዶች ማኅበራዊ መዝሙራት ይሏቸዋል) እየበዙ መጥተዋል፡፡ ይህ አካሄድ በመጀመሪያ ደረጃ የምዕመኑን መንፈሳዊ ሕይወት ይሸረሽራል፡፡ ሁለተኛም የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት ያደበዝዛል፡፡ ሦስተኛም የሀገርን ታሪክንና ቅርስን ያሳጣል፡፡ ስለዚህ ጌታችን  “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሎ እንዳስተማረን (ማቴ ፮:፳፬) ዓለማዊ ዜማንና ያሬዳዊ ዜማን አንድ ላይ መጠቀም ስለማይቻል መንፈሳዊ የሆነውን ያሬዳዊ ዜማን ብቻ ልንጠቀም ይገባናል ።

የአንድ መዝሙር ዜማ ያሬዳዊ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የአንድ መዝሙር ዜማን ኦርቶዶክሳዊ ነው ወይም አይደለም ለማለት የቤተ ክርስቲያንን የዜማ ስልቶች በትክክል ማወቅን ይጠይቃል፡፡ እኛም ዘወትር ከምንዘምራቸው እና ከለመድናቸው መዝሙራት ለየት ያለውን ሁሉ ያሬዳዊ አይደለም ወደሚል ድምዳሜም እንዳንደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁን የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ዜማ ከመሰረቱ እንዳልለቀቀ ሊመሰክሩ የሚችሉት የዜማ ሊቃውንቱ ናቸው፡፡ የዜማ ችግሮችን ከምንጫቸው ለመከላከል የመዝሙር ዜማ ያሬዳዊ ዜማን በጠነቀቁ ሊቃውንት እንዲዘጋጅ ማድረግ ወይም በእነርሱ ታይቶ እንዲስተካከል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የሚዘምረው ዘማሪም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያሬዳዊ ዜማዎችን ያጠና መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለገቢ ምንጭነት ብቻ ሲባል ‹‹ሰላም ለኪ››ን እንኳን በዜማ ያልተማረ ሰው በካሴት መዘመሩ የመዝሙሮቻችንን የዜማ ችግሮች እየሰፉ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ የተሻለው ሀሳብ ሙያን ለባለሙያ መስጠት ቢሆንም ይህ ባይቻል እንኳ የመዝሙርን ዜማ ከዘፈን ጋር የሚያምታቱ፣ መንፈሳዊ መስዋዕት ከእንክርዳድ ሳይለዩ የሚዘምሩ ግን እግዚአብሔርን ፈርተው “የቄሳርን ለቄሳር፣ እግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” መስጠትን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

ከዜማ መሣርያ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው   

የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሳርያዎች መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ገቢረ ተዓምርም የተፈጸመባቸው ናቸው (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: “ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል”(፩ሳሙ ፲:፭):: ቅዱስ ዳዊትም ለዝማሬ የሚያገለግሉትን የዜማ መሣርያዎች በዝርዝር አስቀምጧቸዋል:: “እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት። በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት። በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት። ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።” (መዝ ፻፶:፩-፮):: እኛም ቅዱሳኑ የተጠቀሙበትን የዜማ መሳርያ በመጠቀም ከነፍስ ቁስል የምንፈወስበት የምንረጋጋበት እንዲሆን ምስጢርም እንዲገለጥልን በምስጋናው በሃይማኖት እንደመሰልናቸው በዜማ መሳርያውም ልንመስል ይገባል::

በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈቀዱ የዜማ መሣርያዎች የትኞቹ ናቸው? 

በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑት የዜማ መሣርያዎች መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረጉ ሲሆን ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት: እምቢልታ፣ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የዜማ መሣርያዎች አስተማሪነት እንዲኖረው እኛም በመንፈሳዊ ተመስጦ እንድናመሰግን እንዲህ ባለ ምሳሌነት ታስተምረናለች:: ለምሳሌ ከበሮን ስናይ በመጽሐፍ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮ ይዛ እንዳመሰገነች እንማራለን (ዘጸ ፲፭:፳):: አሰራሩ ምስጢዊ ይዘት እንዲኖረው ልዩ የማህሌት መሳርያ ስለሆነ ከበሮን በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት፣ ሽፋኑ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ የሸፈኑበት ግምጃ፣ ድምጹ የወንጌል፣ ጠፍሩ ጌታችን የመገረፉና በሰውነቱ ላይ የወጣውን ስፍር ቁጥር የሌለውን ሰንበር ምሳሌ፣ ማንገቻው የተገረፈበት ጅራፍ ወይም የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ በማለት ያስረዳል::

በተጨማሪ እንደምሳሌነት ከምንወስዳቸው የዜማ መሣርያዎች በመሳርያነቱ ከእስራኤላውያን ቀጥሎ ለኢትዮጵያውያን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ የዜማ መሳርያ በገና ነው:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ከተቀባ በኋላ ከተሰጡት ሰባት ሀብታት ውስጥ አንዱ ሀብተ በገና ነው። ይህም በገና ሀብተ ፈውስ ያለው ቅዱስ ዳዊት ሲደረድረው ርኩሳን አጋንንት ይርቁ እንዲሁም በሽተኞችም ይፈወሱ እንደነበር ያስረዳናል (፩ኛሳሙ ፲፮:፳፫):: ይህን ገቢረ ተአምር በመስራት የሚታወቀውን የዜማ መሳርያ ቀደምት አበው ከፍጥረት ሰባተኛ ትውልድ ጀምሮ እንደተገለገሉበት የቤተ ክርስቲያንም ሊቃውንት ቃለ በገናን ድምጸ ማኅዘኒ- ‘የሚያሳዝን ድምጽ’ በሚል ይህም በዮባል ልጆች ኃዘን ምክንያት እንደሆነ ያትታሉ:: ይህም የዜማ መሳርያ ልክ እንደ ከበሮ የራሱ ምሳሌያዊ ትምህርቶች አሉት:: የበገናውን ቅርፅ ስንመለከት ላይኛውና ታችኛው የፈቃደ እግዚአብሔርና የማኅፀነ ድንግል (አንድም የሰማይና የምድር) ግራና ቀኙ የሚካኤልና የገብርኤል (አንድም የብሉይና የሐዲስ) አሥሩ አውታር የዓሠርቱ ቃላት (ትእዛዝ) በሚል ይዘረዝረዋል:: ቤተ ክርስቲያን ሌሎችንም የዜማ መሣርያዎች እንዲሁ የክርስቶስን የማዳን ስራውን እንድናስብ በህሊናችን እንድንስል (ገላ ፫:፩) በምድር ያለን ነገር ግን ፍጹም ሰማያዊ በሆነ ስርዓት ታስተምረናለች::

ማህሌት.jpg

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን በኦርጋን መዘመር ተገቢ ነውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ጊዜውን መዋጀት” በሚል የተሳሳተ መረዳትና “ቴክኖሎጂን እንጠቀማለን” በሚል ትርጉም ኦርጋን እና ጊታር ለመጠቀም የሚፈልጉ ለዚህም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ድጋፍ ያደረገ በማስመሰል ምእመናንን የሚያደናግር ትምህርት ያላቸው አሉ:: ቴክኖሎጂን በመጠቀም ድምጽን እንዲሰማ በዜማ ቀረጻ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለታሪክ ማስቀመጥ እንዲሁም ስራው አድካሚ የሆነ የዜማ መሳርያን በሰለጠነ አሰራር መንፈሳዊ ይዘቱን ባልለቀቀ መልክ እንዲሆን ማድረግ ቢገባ እንጂ የዜማ ቃናውን የመሳርያውን አስተማሪነትና  ትውፊታዊ አጥፍቶ ሊሆን አይገባም:: በ፲፱፻፹፮ ዓም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት በመዝሙር አገልግሎት ከተዘረዘሩት የዜማ መሣርያዎች ወጥቶ “በኦርጋን ልዘምር” የሚል የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የጣሰና የቅዱሳን ሐዋርያትን ትእዛዝ እንደጣሰ ሁኖ ከምእመናን የተለየ ነው:: አንዳንድ ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ ይህንኑ ዜማ መሳርያ በማህለቱና በቅዳሴ ጊዜ እንዴት እንደሚውል ያስረዳሉ:: በቤተክርስቲያን ድምጽ ካላቸው ንዋያት ቃጭል ብቻ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት እንደሚውል ከበሮ መቋሚያ እና ጸናጽል የማህሌት ማሳርያዎች ሲሆኑ ሌሎቹም በማኅበርና በግል መዝሙር እንጠቀምባቸዋለን:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን እንዳለ ለእኛም ስንዱ እመቤት ከሆነች ቤተ ክርስቲያን የተሰራልንን ስርዓት መጠበቅ በዚያም መጽናታችን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የመታዘዝ መስዋዕት ነው::

ዜማንና የዜማ መሣርያን በሚመለከት ቀዳሚው መልእክት

የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የዜማ ስልትና የዜማ መሣርያዎችን ስናስብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረታቸውን፣ ታሪካዊ ገጽታቸውን፣ ምስጢራዊ አስተማሪነታቸውንና እንዲሁም ትውፊታው ጠቀሜታቸውን በማስተዋል እንደአባቶቻችን ቆመን ልንገኝ ይገባል እንጂ አባቶች ከሠሩልን ድንበር ወጥተንና የዘመናዊነትን ካባ ደርበን ማንነታችን በማይገልፅና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዲሁም ፍጹም አስተማሪነት በሌለው የዜማ መሳርያ ልንገለገል አይገባም:: “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” (ዮሐ፲:፳፯) እንደሚል እኛም እንደ አባቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረገውን ያሬዳዊ ዜማ እና የዜማ መሣርያ አጠቃቀምን የሚመለከተውን  የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተቀብለን ብንጠብቅ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራችን እንደ አባቶቻችን ወደ መላእክቱ ኅብረት የምንነጠቅበት ይሆናል::

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፡ ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፪)

Digua

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

በመጀመሪያው የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ጦማር ስለ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምንነት፣ ጥቅምና ሥርዓት አይተናል፡፡ በዚያም ክፍል  በተለይም የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር መልእክት (ግጥም)፣ የዜማ ስልት፣ የዜማ መሣርያ አጠቃቀምና የአዘማመር ሥርዓት ምን መምሰል እንዳለበት በሰፊው አቅርበናል፡፡ የዚሁ ርዕስ  ቀጣይና ሁለተኛው ክፍል በሆነው ጦማር ደግሞ  ምእመናን የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ሥርዓትን ለመጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይረዳ ዘንድ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስም በካሴት የሚቀረጹ እና የሚዘመሩ በአማርኛ ቋንቋ የሚቀርቡ  መዝሙራትን እየቃኘን  ከመዝሙር ግጥም (መልእክት)ጋር የተያያዙ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ባለፉት ሦስት አሰርት ዓመታት ውስጥ የአማርኛ መዝሙራት መልካም ዕድገትን ቢያሳዩም ከዕድገታቸው ጋር ተያይዘው የመጡና ትኩረትን የሚሹ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸው ግን የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ከመዝሙር መልእክት (ግጥም) አንጻር በአንዳንድ መዝሙራት የሚታየው ችግር ብዙ መልክ ቢኖረውም በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ችግር የግጥሙ መልእክት መዛባት (ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን፣ ሥርዓትንና ትውፉትን አለመጠበቅ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኪነ-ጥበባዊ ይዘት ደካማ መሆን ናቸው፡፡

የግጥሙ መልእክት መዛባት

የዚህ አይነቱ ችግር የኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮና የመጻሕፍት ትርጓሜ ጠንቅቆ ካለማወቅ፣ በግል ሕይወት ላይ ብቻ ከመመስረት ወይም ከኑፋቄ ትምህርት የተወሰደ መልእክትን ከመጠቀም የሚመነጭ ነው፡፡ እንዲሁም የመዝሙር ካሴቱን ሊገዙ ይችላሉ የሚባሉትን ምድራዊ የኑሮ ሁኔታ ብቻ ያገናዘበ “ገበያ መር” መልክት ላይ ማተኮር የዚህ ችግር አንዱ መሰረት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመዝሙሩ ግጥም የሚያንጸባቀው መልእክት የኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የማይገልጽ ወይም የሚቃረን ሲሆን ይታያል፡፡ እንዲሁም የመዝሙሩ ዓላማ በዝማሬ ሰዎችን በልዕልና ለክርስቲያናዊ ሕይወት (ለንስሐ እንዲሁም ለሥጋ ወደሙ) የሚያበቃ መሆን ሲገባው በምድራዊ ሕይወትና ስኬት ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን ይታያል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረት አድርገን ትርጉማቸው የተዛቡትን ለምሳሌ ያህል ጠቅሰን ለማስረጃነት ያህል ለማሳየት እንሞከራለን፡፡

በአንዳንድ መዝሙራት ላይ “ክርስቶስ ድንጋዩን በኃይሉ ፈነቃቅሎ ተነሳ” የሚል ሀሳብ የያዘን ግጥም እናያለን፡፡ ይህን ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንጻር ስናየው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል እንደተነሳ ነው:: ገጣሚው መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ ትርጉም እያነበበ ስለጻፈው ማስረጃ የሚያደርገው “ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት” ሉቃ ፳፬:፪ የሚለውን ነው:: በማቴዎስ ወንጌል (፳፰:፪) ላይ ግን ድንጋዩን ማን እንዳንከባለለው በግልጽ ተጽፎአል “እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። እንዲሁም “በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ (፩፥፱-፴፩) “በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው”:: በቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ (፩፥፳፬) “ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ ‹መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ› ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ” እንዲል::

ሌሎች ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማንሳት ያህል ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመለከተ “ሰባት ጊዜ ሞቶ ሰባት ጊዜ ተነሳ” የሚል መልእክትን የያዘ መዝሙር በገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያለውን እውነት አያንጸባርቅም፡፡ “አንዱ ሀገር ስትሄድ ኢየሱስ፣ ሌላ ሀገር ስትሄድ ደግሞ አማኑኤል አለችው” የሚለውም እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላደገረችውን እንዳደረገች አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ “ሁሉ ነገር ከእርሱ የማይወጣ…” የሚለውም እንዲሁ አሻሚ ትርጉም የሚይዝ ስለሆነ አንዳንዶችን ለትችት ይጋብዛል፡፡ “ሰው አድርገኝና ሰው ይግረመው” የሚለውም መልእክት እንዲሁ የሰው ንስሐ መግባት ዓለማው ሌላውን ሰው ለማስገረም የሆነ ዓይነት ያስመስላል፡፡ ፍጽምት የሆነች ሃይማኖትን ይዘን “ርትዕት ሃይማኖት አለን” እያልን መዘመር ስንችል ወደታች ወርደን “አልተሳሳትንም” እያልን መዘመርም እንዲሁ ደካማ መልእክትን ነው የሚያስተላልፈው፡፡ “ትክክለኛነት” እና “አለመሳሳት” ይለያያሉና፡፡ በተመሳሳይ “ለነፍሴ ነፍሷ ነሽ” የሚለው አባባልም ግልጽነት ያስፈልገዋል፡፡ አንዳንዶች ይህንን ባልተፈለገ መንገድ ሊተረጉሙት ይችላሉና፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ በዚህ ዘመን እየሰፋ የመጣው ሌላው ችግር “የግለሰብ ሕይወትን” ብቻ የሚያንጸባርቅ መልእክትን ለመዝሙር መጠቀም ነው፡፡ በኃጢአት ይኖር የነበረ ሰው በንስሐ ወደ ቅድስና ሥራ ሲመለስ የሰማይ መላእክት ሳይቀሩ ይደሰታሉ (ሉቃ ፲፭:፯)፡፡ ተነሳሂውም እግዚአብሔርን በመዝሙር ማመስገኑ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የሚዘምራቸው መዝሙሮች መልእክታቸው በእርሱ ምድራዊ ሕይወት ላይ ብቻ ያተኮሩ ከሆኑና ጥሪውም መንፈሳዊ መሆኑን የዘነጋ ሲሆን የቤተ ክርስቲያንን ዓላማ መዘንጋት ያሆናል:: ይህም ዓላማ የሰውን ልጅ ለድኀነት ማብቃት እንዲሁም አምኖ ሲፈጽም በአመነበት እምነት ጸንቶ ከኃጢአት በመጠበቅ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” እንዳለ የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ካለማወቅ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዳይማሩ ሥርዓቷን አውቀው እንዳይገዙ ይከለክላቸዋል፤ በአንጻሩ ፈቃዳቸውን (ስሜታቸውን) የሚከተሉ ምእመናን እንዲበዙ ምክንያት ይሆናል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ “ዘማርያን” ከዘፋኞች በተኮረጀ አሰራር መዝሙርን ከገበያ አንጻር የመቃኘት አካሄድ በግልጽ ይታያል፡፡ ዘፋኞች ከቅጅ መብት አከባበር ጋር በተያያዙና በሌሎችም ምክንያቶች ዘፈኖቻቸውን ለዘፈን ዝግጅት (Concert) ለመጋበዝ በሚያመቻቸው መልኩ እንደሚቃኙ ይታወቃል፡፡ በተለይም ከንግድ እይታ አንፃር የተሻለ ገንዘብ የሚከፈላቸው በዝርወት ምድር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (Ethiopian Diaspora communities) በመሆኑ ዘፈኖቻቸውን ከዚህ ማኅበረሰብ ጋር የማያያዝ አካሄድ አለ፡፡ በተመሳሳይ ራሳቸውን መንፈሳዊ አድርገው የሚያቀርቡ ዘማርያንም ይህንኑ አካሄድ ይከተላሉ፡፡ በዝርወት ምድር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ተራ ተወዳጅነት ለማግኘትና በወንጌልና በዝማሬ በመነገድ የገንዘብ ትርፍ ለማግኜት ሲሉ የመዝሙሮቻቸውን ግጥሞች በዚያው መልኩ ይቃኛሉ፡፡

መዝሙርን ስጋዊ ስሜትን ለማንጸባረቅ፣ ለንግድና ለታዋቂነት መጠቀም ዝማሬውንም የማኅበር ከመሆን ይልቅ “የግል” እንዲሆን ያበረታታል፡፡ በሃይማኖታቸው በነበራቸው ተጋድሎና ጽናት እግዚአብሔር ለነሱ ያደረገላቸውን አስበው ምስጋናን ያቀረቡትን ህዝበ እስራእኤልን፣ ሠለስቱ ደቂቅን፣ በእስር ላይ የነበሩትን ሐዋርያትንም ምሳሌ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ህዝበ እስራእኤል እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት ስላወጣቸው የምስጋናን መዝሙር በኅብረት አቅርበዋል (ዘፀ ፲፮:፩):: በብሉይ ያለው ታሪክን ምሳሌነቱን በምስጢር ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣንበትን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳንን ትንሣኤውን እያሰብን በኅብረት ሆነን በቅኔ ስናመሰግን ዝማሬውም ሁሉን የሰው ልጅ የሚያሳትፍና ዘመንም የማይሽረው ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬ ይሆናል:: መዝሙሮችን ግለሰባዊ ማድረግ የንግድ እንጂ የመንፈሳዊነት ውጤት አይደለም፡፡

የኪነ-ጥበባዊ ይዘት ደካማ መሆን

ሁለተኛው ችግር የመዝሙሩ ግጥም ወይም ኪነ-ጥበባዊ ይዘቱ ደካማ መሆን ነው፡፡ ለግጥም የሚውሉት ቃላት መንፈሳዊ ገጽታ የሌላቸው ተርታ፣ እንግዳ ወይም ጸያፍ ቃላት ሲሆኑ፣ የግጥሙም መልእክት ፍሰቱን ያልጠበቀና እና መደበላለቅ ሲኖርበት፣ በማኅበረሰቡም ዘንድ ብዙ ጊዜ የተለመዱ ቃላትን ለቤት መምቻነት የሚጠቀም ግጥም፣ ቃላትንና ሐረጎችን በግድ ተጎትቶ ቤት የሚመታ ወይም ጭራሹንም የማይመታ ግጥም መጠቀም፣ እንዲሁም ለዜማ የሚቆረቁሩ ቃላት/ፊደላት ድንገት መጥተው የሚደነቀሩበት ግጥም ያለው መዝሙር ኪነ-ጥበባዊ ይዘቱ ችግር ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ብንመለከት በአንዳንድ በቤተ ክርስቲያን ስም እየታተሙ የሚወጡ የካሴት መዝሙሮች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ድፍረት ባለበት ቃል “ፍቅሬ” “ውዴ” በማለት የሚጠሩ አሉ:: አባቶቻችን ግን በአነጋገራቸው በጸሎታቸው እጅጉን ተጠንቅቀው ሲጠሩትም ማንም በማይጠራበት (‘ጠ’ ጠብቆ ይነበብ) ልዩ በሆነ አጠራር “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና” እያሉ ነው::

የመጀመሪያው ስንኝ “…የሠራዊት ጌታ” ካለ ሁል ጊዜ ሁለተኛው ስንኝ “…ጠዋት ማታ” የሆነ ዓይነት ድግግሞሽ የግጥምን ኪነ-ጥበባዊ ይዘት ያደበዝዛል፡፡ እንዲሁም “ታሪኬን ቀያሪ፣ ከፍ ከፍ በል፣ እንደ ዋርካ ሰፋን፣ ምድርን ከደንናት…ወዘተ” የሚሉ እንደፋሽን በየግጥሙ ደጋግሞ መጠቀምም የመልእክት ድርቀትን ያሳያል፡፡ በምድር የሚኖሩ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶችን እንደጠላት በመቁጠር “ጠላቴ ሆይ…፣ …ጠላቶቼ” ማለትም መንፈሳዊነት አይደለም፡፡ የሥጋዊ ሀብት መሻሻልን ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት “ያከበርከኝ…” የሚል አስተሳሰብም እንዲሁ ሥጋዊ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም፡፡ በምድር ላይ ያሉ ፖለቲካዊ ክስተቶችንም መነሻ በማድረግ ምድራዊ አስተሳሰብን ብቻ የሚያንጸባርቅ ግጥምም እንዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ምድራዊ ሰዎችን ስንጠራ የምናደርገውን ጥንቃቄ ያህለ እንኳን ያልተጠነቀቅን ከሆነ ፍጹም መንፈሳዊውን ነገር እንዳልተገነዘብንና እንዴት በሃይማኖት መመላለስ እንደሚገባንም አለመረዳታችንን ያስረዳል:: በማቴዎስ ወንጌል ፰:፲ ካለው ታሪክ እንደምንማረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ ከለመነውም ጥያቄ የምንማረው ትህትናውን ሃይማኖቱን እንዲሁም ጥበብን ነው:: ጌታችንም ሰምቶ እንደተደነቀና ለተከተሉትም “እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” ነበር ያላቸው:: የመቶ አለቃው ጥበብ ከራሱ ማዕረግ ጋር በማነጻጸር ወታደሮችን የሚያዝ ገዢ ብዙ ሰዎችን የሚያስተዳድር እንዳለውና እሱ ይህን ማድረግ ሲቻለው የሰማይና የምድር ፈጣሪ መድኃኔዓለም ሁሉ የሚገዛልህ አንተን የማይታዘዝህ ማን አለ የሚል ነበር:: ዛሬም ለአምላካችን ለቅዱሳን ያለን ግንዛቤና አጠራር ለዓለም ከምንሰጠው አጠራርና ክብር ለይተን  በሃይማኖት ዓይን ተመልክተን ሊሆን ይገባል::

የመፍትሔ አስተያየት

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ገንዘብና ዝናን ዓላማ በማድረግ መዘጋጀት የለበትም፡፡ እነዚህን ዓላማ አድርጎ የሚነሳ ማንኛውም ሰው ለጊዜው በተጥባበ ስጋ መልካም የሚመስል ስራ ቢሰራ እንኳ ፍፃሜው ሊያምር አይችልም፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎትን በስጋዊ ዓላማ መፈጸም አይቻልምና፡፡ ከዚያ ባሻገር ከኦርቶዶክሳዊ የመዝሙር ግጥም (መልእክት)ጋር ለተያያዙ ችግሮች  ዋነኛ መፍትሔ የሚሆነው የመዝሙሩን ዓላማ ከምድራዊ ጥቅም ይልቅ መንፈሳዊው ላይ እንዲያተኩር ማድረግ፣ የግጥሙን ሥራ የሚሰራው ሰው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚያውቅና (ቢያንስ ለሚጽፈው ክፍል ያለውን) የቅኔ የኪነ-ጥበብም ተሰጥኦ ወይም ልምድ ያለው ቢሆን መልካም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስተማሪነቱ እንዲጎላ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ትምህርቷን ጠንቅቀው የተረዱ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች የመዝሙሩን ግጥም አይተው እርማት ቢያደርጉበት ይበልጥ ይጠቅማል፡፡ እንዲሁም ኦርቶዶክሳዊ ለዛውን እንዲጠብቅ ያደርገዋል፡፡ ጠንከር ያለ የይዘትና የአገላለጽ የስነ-ጽሑፍ አርትኦት (editing) የመዝሙሮችን መልእክት ትክክለኛነት ለማረጋገጥና ኪነጥበባዊ ደረጃውን ለመጠበቅ ይረዳልና ኦርቶዶክሳውያን የመዝሙር ግጥም “ደራሲዎችም” በአግባቡ ቢጠቀሙበት መልካም ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር: ርስታችንን አጥብቀን እንያዝ (ክፍል ፩)

በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ

“መመካት ቢያስፈልግ ዓለምን የሚያስደምመው ያሬዳዊ ዜማ ኢትዮጵያውያን ትምክህት ነው፡፡”

መንፈሳዊ መዝሙር ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ከምታወርሳቸው ሀብታት አንዱ ሲሆን ለአምልኮትም ታላቅ ድርሻ ያለው ነው:: መዝሙር  ቅዱሳን ሊቃነ መላእክትና ሰራዊቶቻቸው ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ያለዕረፍት የሚያመሰግኑበት ነው (ኢሳ ፮:፩-፭ ኢዮ ፴፰:፮):: መዝሙር ሰውና መላእክት ዘወትር ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ለማመስገን እንደተፈጠሩ እንዲያመሰግኑበትም የተሰጣቸው ልዩ ሀብት፣ ሰማያዊ ዜማ ነው:: አስተምህሮ ባለፉት ሳምንታት ወቅቱን አገናዝባ ለሐዋርያት የተሰጣቸውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳስገነዘበችን በዚህ ዓምድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የተሰጣትን ሰማያዊ የምስጋና ስጦታ የሆነውን የመዝሙር ሥርዓትን ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንና እና አገልጋዮች እንዲረዱት በጥቂቱ እናቀርባለን::

እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ ከጸሎትና መጽሐፍትን ከማንበብ ጋር መዝሙር በመዘመር እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ እንዲሁም በመከራቸው ጊዜና ከድል በኋላ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን አስበው በመዝሙር ምስጋናን ያቀርቡ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል (ዘጸ ፲፭:፩-፳ ዘዳ ፴:፲፱ ፴፩:፲፬ ኢሳ ፩:፪ መሳ ፬:፩ መሳ ፭:፫):: በሐዲስ ኪዳንም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከነበሩት ድንቅ መንፈሳዊ ገጽታዎች ቀዳሚውና ዋናው በምስጋና ለዘመናት ተለያይተው የነበሩ ሰውና መላእክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ:- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በሚል በአንድነት ባቀረቡት የምስጋና መዝሙር ነው (ሉቃ ፪:፲፪):: መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ወደ ደብረዘይት ከመውጣታቸው በፊት መዝሙርን አስተምሯቸዋል፤ ዘምረዋልም (ማር ፲፬:፳፮):: ስለዚህም የመዝሙር አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ከጸሎት ከስግደት ከጾም ጋር በሥርዓተ አምልኮታችን ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው::

፩.መንፈሳዊ መዝሙር ምንነቱና ጥቅሙ

መዝሙር ‘ዘመረ’ ‘አመሰገነ’ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ምስጋና፣ ልመና፣ ማዜም ማለት ነው፡፡ መዝሙር በግልና በኅብረት የሚዘመር፤ ጌታችን ሰውና መላእክት በአንድነት እንደዘመሩ ታናሽ ታላቅ ሳይል ሁሉንም የሚያሳትፍ፤ ዝማሬውም በልዑል እግዚአብሔር ፊት ቆመን አምላካችንን የምናመሰግንበት የምናወድስበት በቁመታችንም ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚያመሳስለን መንፈሳዊ ተግባር ነው (ራዕ ፲፱:፭፣ ፩ቆሮ ፲፬:፪፮):: መዝሙር ለክርስቲያን የዘወትር ተግባር እንደመሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መሠረትነት ጥቂቶችን ምሳሌ አድርገን እንማራለን::

መንፈሳዊ መዝሙር እግዚአብሔርን በቅኔ በሚያምር ዜማ የምናመሰግንበት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” እንዳለ በዚህ የመንፈሳዊ ተግባር እግዚአብሔርን በቅኔ በሚያምር ዜማ እናመሰግነዋለን፤ እናወድሰዋለን (ኤፌ ፭:፲፰-፳):: ቅዱሳን መላእክትም በቤተልሔም በጌታችን ልደት በደስታ እንዳመሰገኑ፣ ትንሣኤውን በምስጋና እንዳበሰሩ፣ ዕርገቱን በምስጋና እንዳጀቡ፣ ዳግም ምጽአቱንም በምስጋና እንደሚያውጁ ሁሉ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተክርስቲያንን ያለማቋረጥ ያገለግሏታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ: ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና” እንዳለ እኛም እንደቀደሙት አባቶች እግዚአብሔር ለኛ ያደረገውን እያሰብን ዘወትር ቀንና ሌሊት በመዝሙር እናመሰግነዋለን:: (መዝ ፵፮:፮-፯)::

መንፈሳዊ መዝሙር የሚያበረታንና የሚያጸናን መንፈሳዊ ኃይል ነው፡፡ መዝሙር በሃይማኖት መከራ ድካም ሲገጥመን ከድካማችን የሚያበረታን፣ መከራን እንዳንሰቀቅ እንዳንፈራ የሚያጸናን የሚያበረታን መንፈሳዊ ኃይል ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በእስር ሳሉ በጸሎት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን በዝማሬም ያመሰግኑ ነበር (የሐዋ ሥራ ፲፮:፳፭):: ዛሬ ላይ በሕይወታችን፣ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ፈተና ሲገጥም በራሳችን ጥበብ በመታለል ሳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትግላችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ጋር ስለሆነ ምድራዊ የሆነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በማድረግ በዝማሬ የእግዚአብሔርን ኃያልነት በመግለጥ ሊሆን ይገባል:: በመዝሙር “በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ሰማኝም።” (መዝ ፻፲፱:፩) እንደሚል፥ ረሃብ ቸነፈር ጦርነት የተፈጥሮ አደጋዎች መንግስት በመንግስት ሕዝብም በሕዝብ ላይ ክፋትን ሲያደርግ በማመስገን የእግዚአብሔር የመከራው ጊዜ እንዲያበቃ እንዲያጥር እንደ ነቢያትና ሐዋርያት ሕይወትም በመዝሙር ወደ እግዚአብሔር መጮህ ለክርስትያኖች የእግዚአብሔርን ኃያልነት የመመስከር እንዲሁም ሐዋርያትን የመምሰልም መገለጫ ነው::

መንፈሳዊ መዝሙር እግዚአብሔር ለእኛ ስላደረገው ሁሉ ደስታችንን የምንገልጽበት ነው:: ‘ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር’ እንዲል (ያዕ ፭: ፲፫):: በመከራና በችግራችን ወቅት ስሙን ጠርተን የለመነውን አምላክ በድልና በደስታችን ጊዜ አብዝተን ልንዘምር እንጂ ልንዘነጋ አይገባም:: እስራኤል በግብፅ ከነበረው መከራ ሲወጡ የአምላክን ታዳጊነት የእስራኤልን ድኅነት በመመልከት ሙሴና ተከታዮቹ በተለይም እኀቱ ማርያም በከበሮ ድምፅ እየታጀቡ በጣዕመ ዜማ “ንሴብሆ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ:-በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ” በማለት ዝማሬን አቅርበዋል (ዘጸ ፪:፩-፲):: ዛሬም በሰርግ በበዓላት በድል ወቅት የቅዱሳንን ተጋድሎና ህይወታቸውን እያሰቡ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን እያደነቅን በሚያምር ለምስጋና በተለየ የዜማ ስልት መዘመር ይገባል::

 ፪. ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርና መገለጫዎቹ

ቅዱሳን አባቶቻችን የሕይወት መስዋዕትን ከከፈሉባቸው አንዱ ትልቁ ርስት ዜማና የዜማ ሥርዓት ነው፡፡ የቀደሙት አባቶች እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንድናከብረው የወሰኑልንን የዝማሬ ሥርዓት ድንበር ሳናፈርስ መንፈሳዊ ዜማና ሥርዓቱን አባቶቻችን ከእግዚአብሔር እንደተቀበሉ በዚህም ምስጋና ከእርሱ ጋር እንደተገናኙ እኛም “በነቢያትና በሐዋርያ መሠረት ላይ ታንጻችኋል” እንደተባልን ከቀደምት አባቶች መሰረት ሳንለቅ ሠርተው ባስረከቡን ወደ ሰማያዊው ኅብረት በምንነጠቅበት የዜማ ሥርዓት ልንጸና ይገባል (ኤፌ ፪:፳ ምሳ ፳፪:፳፰)፡፡

ከቀድሞ ጀምሮ እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛይቱን ሃይማኖት ባጸኑ በነቢያት በሐዋርያት ላይ እያደረ ምስጢርን ገልጾላቸዋል:: በአስተምህሮ ባለፉት ሳምንታት መልዕክት እንደተማርነው ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የተሰወረው ተገልጦላቸው ፍጹም የሆነውን አገልግሎት ጀምረዋል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ትውፊትና ባህል ተቀብላ በታላቁ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ከእግዚአብሔር በተሰጣት ልዩ የዝማሬ ጸጋ ታመሰግናለች::

Qidus Yared.jpg

ቅዱስ ያሬድ ይህን ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከመቀበሉ በፊት በትምህርቱ ተስፋ ቆርጦ፤ እግዚአብሔርም ከስነ ፍጥረት እንዲማር አድርጎት፤ ቅዱስ ያሬድም ራሱን ገስጾ ድካምን እንዲታገስ እውቀትንና ጥበብን እንዲገልጽለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ፤ ጌታችን “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ ፲፮:፲፫) ብሎ እንዳስተማረን በሰው ጥበብ መረዳት የማይቻለውን በአንድ ቀን መዝሙረ ዳዊትን የጸሎት መጻሕፍትንና ትርጓሜ መጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳትን ማወቅ ተሰጠው:: የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ለመቀበል የሰው ልጅ በአቅሙ መጣር እንዳለበት ከሚያስተምሩን ህያው ምስክሮች አንዱ አባታችን ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ሰማያዊ ዜማ የተገለጠለት ሳይጥር፣ ሳይደክም አልነበረም፡፡ ሰባት ጊዜ እየወደቀ እየተነሳ፣ በእግዚአብሔር ኃይል እየታገዘ ለበለጠው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተገባ ሆነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ያሬድ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሁኖ ካህናተ ሰማይ መላእክት በተቀደሰ ዙፋኑ ዙሪያ ከፍ ባለ ዜማ የሚያመሰግኑበትን የዜማ ሀብት የተሰጠው የቤተክርስቲያን ዓምድ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ማኅሌተ እግዚአብሔርን ሲያደርስ ንጉሥ ገብረ መስቀል በጣዕመ ዜማው ስለተሳቡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ መትከላቸውና ቅዱስ ያሬድም ከእግሩም ደም መፍሰሱን ማሕሌቱ እስከሚፈጽም ድረስ አልተሰማውም ነበር፡፡ ይህም ጣዕም ያለው ሰማያዊ የዜማ ስልት ቤተክርስቲያን ዘወትር ጧትና ማታ በስብሐትና በማኅሌት በቅኔ በሰርክ የምታመሰግንበት ነው::

mqdefault

ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ ይዘው በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑት ቅዱስ ያሬድ በምስጋናው ልዑል እግዚአብሔርን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያለ በማመስገኑ ምስጋናውንም የተማረው ከመላእክት መሆኑን በድርሰቱ መስክሯል፡፡ በዚሁም ቤተ ክርስቲያን “አምሳሊሆሙ ለሱራፌል”:- የሱራፌል አምሳላቸው ትለዋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሃልዎተ እግዚአብሔርን ፍጥረተ ዓለምን በአጠቃላይ መሠረተ ሃይማኖትን ነገረ ድኅነትን ክብረ ቅዱሳንን መሠረት አድርጐ በሦስት የዜማ ስልቶች (ግዕዝ፣ዕዝልና አራራይ) ላይ ተመሥርቶ ዘምሯል:: ምድራውያን ካህናት ሰማያውያኑን መስለው ማዕጠንትና መስቀል ይዘው በምስጋና በመንበሩ ፊት ቆመው ማመስገናቸው ይህን መንፈሳዊ ጸጋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር እንደተቀበለችና ይህንንም ስጦታ በክብር እንደጠበቀችው ያስገነዝበናል:: የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተለይታ ከምትታወቅባቸው እና ለኢትዮጵያም ካበረከተቻቸው እሴቶች አንዱ ይህ የዜማ ስጦታ ነው። መመካት ቢያስፈልግ ዓለምን የሚያስደምመው የያሬዳዊ ዜማ ለኢትዮጵያውያን ትምክህት ነው፡፡

አንድን መዝሙር ኦርቶዶክሳዊ ነው የሚያሰኙት የመዝሙሩ መልእክት ፣ የዜማ ስልቱ፣ የዜማው መሳሪያ፣ እንዲሁም ዝማሬውን የምናቀርብበት መልክ ሥርዓቱን ጠብቆ መንፈሳዊነትን ተላብሶ የተገኘ ሲሆን ነው::

፪.፩. የመዝሙሩ መልዕክት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

አንድን መዝሙር ኦርቶዶክሳዊና ልብን የሚመስጥ ነው የምንለው ሌላው እይታ የመዝሙሩ ግጥም መሠረተ ሃይማኖትንና ምስጢርን የጠነቀቀ፤ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ትውፊትና ባህል የጠበቀ ሲሆን ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የምስጋና መስዋዕት በተዋጣለት ድርሰትና ዜማ በነግስና በመልክ ጸሎት እንዳለው በግጥም መልክ መልእክቱንም የተከተለ በምስጢርም የጠለቀ እንዲሆንና ይበልጥ ደግሞ በቅኔ መንገድ ቢቀርብ የበለጠ ይስማማል:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ሁላችን የመዝሙርን መልእክት መመርመር ይገባናል፡፡ መዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይሆን ትምህርትም ስለሆነ ትርጉሙም ከቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር የማይቃረን እንዲሁም ግጥሙ እንደ ሰምና ወርቅ ምስጢርን ጠብቆ የተቀመመ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በቅዱሳት መጻሕፍት የብሉያትንና ሐዲሳትን ምስጢር ጠንቅቆ የተረዳ ስለነበር በዜማ ድርሰቱም ቤተክርስቲያንን በምስጋና ያስጌጠ ዛሬም ላይ ላለው አገልግሎት መንፈሳዊ ተመስጦን የሚያላብስ እንዲሁም ሲሰሙት አጥንትን የሚያለመልም ነው::

በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን እምነቷን የምትገልጽበት ስያሜዎችን የምትሰጥበት በዘመን የማይተኩ መሰረቷን የሚያስገነዝቡ ዕንቁ የሆኑ ቃላትና አገላለጽ አላት:: ዛሬ ላይ በካሴት ተቀርጸው መዝሙር ተብለው በሚወጡ ነገር ግን ፈር የለቀቁ ከቤተክርስቲያን አገላለጽ የወጡ ሥም አጠራሩ የከበረ አምላካችንንና ያከበራቸው ቅዱሳንን ክብር የሚነኩ ወይም የሚያሳንሱ መዝሙሮች ይሰማሉ:: ለምሳሌ በዘወትር ጸሎት መግቢያ ላይ እንደምናየው ቤተክርስቲያን ለጌታችን መጠሪያ እንደቀደምት አበው “የአምላኮች አምላክ የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ” እንላለን እንጂ ይህን ኦርቶዶክሳዊ አጠራርን ትተን ክብርን በሚያሳንስ አጠራር አትጠራውም፡፡ በሌላውም የዝማሬው መልእክት ተስፋ መቁረጥን፤ ምድራዊ ተስፋን፤ ሥጋዊ ድልን በማሰብ የሚደርሱ ናቸው:: እነዚህ ድርሰቶች አስተማሪነት የሌላቸውና የክርስትናን ዓላማ ፈጽሞ ካለመረዳት የቀረቡ ናቸው:: ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም “ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” ብሎ እንዳስተማረን የዝማሬያችን መልእክት ምስጢርን የጠነቀቀ እንጂ በጥሬ ንባብ ብቻ የቀረበ እንዳይሆን ማጤን ያስፈልጋል (፪ቆሮ ፫:፮)::

 ፪.፪. የዜማው ስልት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ያሬዳዊ የዜማ ስልት የተከተለ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በየጊዜው የተነሡ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አባቶች ለመዝሙር ይገለገሉበት የነበረው የዜማ ስልት የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ ለምሳሌ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ድርሰት ብንመለከት ሰዓታቱን እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ የሰጠንን ስጦታ በመጠቀም በያሬዳዊ ዜማ ዘመሩት እንጂ ሌላ ዜማ ለመፍጠር አላስፈለገም:: በመሰረታዊው የጸሎት ስርዓት ቤተክርስቲያን ወቅቱን ያገናዘበ የዜማ ስልት ተከትላ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች:: በቅዳሴ ሥርዓት በጾም ወራት በግእዝ የዜማ ስልት እንዲሁም በበዓላት ጊዜ በዕዝል የዜማ ስልት ይከናወናል፡፡ በዚሁም መሠረትነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባወጣው ደንብ መሰረት መዝሙራት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የሰጣትን የዜማ ስልት የተከተሉ እንዲሆን ደንግጓል፡፡ በአጠቃላይ የያሬድ ዜማዎች በምንዘምረው መዝሙር ላይ እንዲውል እንደ አባቶቻችን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል::

፪.፫. የዜማ መሳሪያዎች: 

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተፈቀዱ የዜማ መሣሪያዎችን የሚጠቀም መሆን ይጠበቅበታል፡፡

እግዚአብሔር ልዩ መስዋዕትን ይፈልጋል፡፡ መዝሙርም ከልብ የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ በቁሳቁስ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ይሁንና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማስፋት የዜማ መሳሪያዎችን መጠቀም ዓላማውን እስከጠበቀ ድረስ ከመንፈሳዊ መስመር አያስወጣንም፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መሰረትነትም የተመሰከረ ነው፡፡ ለኦርቶዶክሳዊ መዝሙር የምንጠቀምባቸው መሳሪያዎች መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸው፣ ለመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተመረጡ ናቸው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ (መዝ ፹፩:፪) “ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር” በማለት ለምስጋና የሚስማሙ የዜማ መሣሪያዎች እንዳሉ ያስረዳናል:: ቅዱስ ያሬድ ዜማን ከመላእክት እንደተማረ እንዲሁም በርካታ ሊቃውንትም ይህንን ሰማያዊ ዝማሬ መሰረት ያደረገ የዜማ መሣሪያዎች እንደተጠቀሙ የቤተክርስቲያን ትውፊት ያስተምረናል:: እነዚህም የመዝሙር መሳሪያዎች ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውና መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከበሮ መቋሚያ እና ጸናጽል የማህሌት መሳርያዎች ናቸው:: ቅዱስ ሲኖዶስ በ ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በግንቦት ወር ላይ ባደረገው ጉባዔ መዝሙር በዋሽንት በከበሮ በጸናጽል በመሰንቆ በበገና በእምቢልታ እንድንገለገል አዟል::

ከበሮ

እነዚህ የዜማ መሳሪያዎች ገድል የተሰራባቸው ገቢረ ተአምር የተፈጸሙባቸው ስለሆኑ የተቀደሱ ንዋያተ ማህሌት መሆናቸውን አውቀን በክብር በንጽህና ልንጠብቃቸው ይገባል:: ይህም የምስጋና የማህሌት መሳሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት ያለው ነው:: “መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እግዚአብሔር ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው” (፪ዜና ፭:፲፪-፲፬ ፪ዜና ፳:፩-፴)። ስለዚህ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለውን የዜማ መሣሪያዎች ወደ ውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል ስለሚያስነቅፍ በተለያዩ መድረኮችም እነዚህን የቤተክርስቲያን የሆኑትን ንዋያት ቦታው በሚፈቅደው ሕግ ልናስከብር ይገባል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/::

፪.፬. የአዘማመር ሥርዓት

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡

እግዚአብሔር ትሁትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብን የምስጋና መስዋዕት ይመለከታል:: ቃየልና አቤል በእግዚአብሔር ፊት መስዋዕትን እንዳቀረቡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና መስዋዕቱ እንደተመለከተ ይነግረናል እንጂ መስዋዕቱን ብቻ አላለንም እኛም የከንፈራችንን ፍሬ በመዝሙር በተመስጦ በተሰበረ ልብ ሆነን ከማን ፊት ለማን ምስጋና እንደምናቀርብ በመገንዘብ በመዘመር ወቅት መዘመራችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ልብ የሚመረምር አምላክ ፊት እንደቆምን ልናስተውል ይገባል (ዘፍ ፬:፬):: ክቡር ዳዊት ‘እዘምራለሁ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ” (መዝ ፻:፪) እንዳለ እግዚአብሔር ከዜማው በፊት የሚያዜመውን ሰው ሕይወት ይፈልጋልና እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት “በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” (፩ጢሞ ፪:፰) በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምረናል::

መዘምራን.jpgስንዘምርም የምንዘምረውን አውቀን ዜማውን ብቻ ሳይሆን ቃሉን በማስተዋል የመዝሙሩን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር መዝሙሩን በአንደበታችን እንዳኖረልን ተገንዝበን ራሳችንን ልንመክርበት ልንገስጽበት መሆን አለበት:: መዝሙሩም የምእመናንን ልብ በዝማሬው ለቃለ እግዚአብሔር የለሰለሰ እንዲሆን የሚያዘጋጅ መሆን አለበት:: ዝማሬያችን በአንዳንድ ቦታዎች እንደሚታየው ከቤተ ክርስቲያን ባልተለመደ ሥርዓት ዓይንን ጨፍኖ እጅን ያለሥርዓት በማወዛወዝ በሥጋዊ ስሜት የሚቀርብ ወይም ባህላዊ ዘፈንን በሚመስል መልኩ ሳይሆን ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ‘አቤቱ አይኖቻችንን ወደ አንተ አቀናን’ እንዳለው አሰላለፋችንና እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን በመረዳት ወንጌልን የሚሰብክ በአገባብና በሥርዓት ሊሆን ይገባል (መዝ ፻፵፪:፮ መዝ ፭:፫ ፩ቆሮ ፲፬:፵)::

ከዚህ በተጨማሪም የዘማርያንም ሕይወት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነትና ምግባር የሚሰብክ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከመዝሙሩ መልእክት፣ የዜማ ስልት፣ የዜማ መሣርያና የአዘማመር ሥርዓቱ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊትን የጠበቀ ከመሆኑ ተጨማሪ የዘማርያኑ ሕይወትም እንዲሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነትና ምግባር የሚሰብክ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ መዝሙር የተወደደ መስዋዕት ስለሆነ መስዋዕቱን ከማቅረብ አስቀድሞ ራስን ማዘጋጀት ይገባል መስዋዕቱም እንዲሰምር ከዝማሬ መስዋዕት በፊት የራስን ሕይወት በመመርመር የምስጋናው ባለቤት በልዑል እግዚአብሔር ፊት እንደሚቀርብ አውቆ በትህትና በመልካም ሕይወት ማቅረብ ያስመሰግናል፡፡

ማጠቃለያ

አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመፈጸም የቤተክርስቲያንን ሥርዓት መማር ማወቅ ይኖርብናል:: መንፈሳዊ ዜማ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ይህም በመላእክቱ የሚደርስ ከሥጋዊ ስሜት ያልሆነ ልዩ የዜማ ስልት ያለው ማለት ነው:: ለኢትዮጵያውያን ይህ መንፈሳዊ ስጦታ በታላቁ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የተሰጠንና ይህም ስጦታችን ልዩ የዜማ ስልትና ምልክት ያለው ዜማ ነው፡፡ በዚህ ዜማ ልብን በሚማርከው መንፈስን በሚቀድሰው ዜማ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን እናወድሳለን፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘን የምንማረው ለኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ንጉሡ አክዓብ የአባቶቹን ርስት ወስዶ ሌላ ርስት ልስጥህ የሚል ጥያቄን አቅርቦለት ነበር:: ናቡቴ ግን የአባቶቹን ርስት ከመሸጥ ሞትን ነበር የመረጠው:: ናቡቴ ለዚህ ምድራዊ ርስት ይህን መስዋዕት ከከፈለ ዛሬ ላይ ሰማያዊ የሆነውን ስጦታ ቀደምት አባቶች መስዋዕት የሆኑለትን ይህን ሥርዓት ምድራዊ በሆነ አመክንዮ ዜማን ከንግድ ጋር ማያያዝ ለሥጋ በሚመች ስልት በሚቀርብ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ባህል ካልሆነ አገልግሎት ተጠብቀን አባቶቻችን እንደተቀደሱበት ከመላእክቱ ጋር በምስጋና እንደተባበሩ እኛም ተባብረን በምስጋና ሥርዓታችን ከኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት ሳንወጣ ዋጋ የምናገኝበት ሊሆን ይገባል:: የምንዘምረው መዝሙር በቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አባቶች እንዲሁም መምህራን የታረመ ሊሆን ይገባል:: የቤተክርስቲያን መዝሙር የዜማው ባሕልና መሣሪያዎቹ ፍፁም መንፈሳዊ መልእክት ያለው ነውና ይህንንም ታላቅ የሃይማኖት አደራ ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅብናል፡፡

ማኅበረ መላእክት ያለማቋረጥ በትጋት እግዚአብሔርን ያለእረፍት በደስታ እንደሚያመሰግኑ እኛም ረድዔታቸውን እየተማጸንን ሰማያዊ በሆነው የዝማሬ ምስጋና እንድንተጋ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን።

ክፍል ፪ ይቀጥላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጾመ ሐዋርያት: የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው!

the_twelve_apostles_ethiopianየሐዋርያትን አስተምህሮ የምትከተለው ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉ በሥርዓት እንዲሆን ስለሚገባ ለጾምም ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ በዚህ መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማትን አውጃለች፡፡ ከእነዚህም መካከልም ጾመ ሐዋርያት (የሐዋርያት ጾም ወይም በተለምዶ ሥሙ- የሰኔ ጾም) (The Fast of the Holy Apostles) አንዱ ነው፡፡ ይህ ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው ስለጾሙት አስቀድሞ ‹‹የጰንጤቆስጤ ጾም›› ወይም ‹‹የደቀ መዛሙርት ጾም›› ይባል ነበር፡፡ ከኒቅያ ጉባዔ በኋላ እስከ ዛሬ የምንጠቀምበትን ‹‹የሐዋርያት ጾም›› የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡  ሐዋርያትም የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጾሙ አስተምሯቸው ስለነበር ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀመዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወስድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ (ማቴ 9፥15-16)” በማለት እንዲጾሙ አዟቸዋል፡፡ይህንን አብነት በማድረግ ሐዋርያት ወንጌልን የሚሰብኩትን ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነበር (የሐዋ 13፥3፤4፥25)፡፡ የሐዋርያት ጾም በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ድዲስቅሊያ፣ በኣራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ቀለሜንጦስ፣ እንዲሁም ቅዱስ አትናቴዎስ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክት ላይ ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ሰፍረውና ቆጥረው ባስረከቡን ሐዋርያውያን አበው መሰረትነት የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ የመታዘዝ ምልክት የሆነ የሐዋርያትን ጾም እንጾማለን፡፡

ጾመ ሐዋርያት: ቅድመ ጰራቅሊጦስ

ቀደምት የቤተክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ዕርገት እስከ ኀምሳኛው ቀን (ለ10 ቀናት) ድረስ በጾምና በጸሎት ቆይተዋል፡፡ እነዚህንም 10ቀናት የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እያለ ‹‹ እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤  እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው…ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› (ዮሐ 14፡16-18) ብሎ የሰጣቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ይህንን ጾም በመጾም ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ራሳቸውን አዘጋጅተውበታል፡፡ ዛሬም ካህናት ክህነት ከመቀበላቸው በፊት፣ አዳዲስ ተጠማቂዎችም ከጥምቀት በፊት እንዲሁም ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበላቸው በፊት የሚጾሙት ይህንን አብነት አድርገው ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለመቀበል ራስን በጾምና በጸሎት ማዘጋጀት ያስፈልጋልና፡፡

ጾመ ሐዋርያት: ድኅረ ጰራቅሊጦስ

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላም ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገውታል፡፡ ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የጾሙት ስለሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህም ነው መንፈሳዊ አገልግሎትና ስብከት የዚህ ጾም አንኳር ነጥቦች የሆኑት፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ጾሟልና እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡ አንዳንድ መዛግብት በመጀመሪያዎቹ ዘመናት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ አንድ ሳምንት በኋላ ነበር ይላሉ፡፡ ከዚያም በ258ዓ.ም ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እስከ ሐዋርያት በዓል (The Feast of the Holy Apostles)  (ሐምሌ 5) ድረስ እንዲሆን አባቶች ደነገጉ በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህም  የተረደገው የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም አደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ ነው በማለት ያጠናክሩታል፡፡ መጽሐፈ ድዲስቅሊያ ደግሞ ሐዋርያት 40 ቀን እንደጾሙ ከዚያም በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ እግራቸውን አጥቧቸው ለስብከተ ወንጌል እንደተሰማሩ ያስረዳል፡፡

‹‹እናንተ ስትጦሙ›› እና ‹‹አንተ ግን ስትጦም››

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን ትዕዛዝ መሆኑንም ለሐዋርያቱና ለሚከተለው ሕዝብ ሲያስተምር ‹‹ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴ 6፡16-18›› ብሏል፡፡ በዚህም ትምህርቱ እርሱ የሚወደው ጾም ምን አይነት እንደሆነና እንዲሁም የማኅበርና የግል ጾም መኖሩን ‹‹እናንተ ስትጦሙ›› እና ‹‹አንተ ግን ስትጦም›› ብሎ ለይቶ አስተምሯል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ ጾም እንዴት አይነቱ እንደሆነ ነቢያት አስቀድመው ‹‹የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?›› ብለው ጽፈዋል፡፡ ኢሳ 58፡6-8

‹‹መቼም የማይጾሙ›› እና ‹‹መቼም የማይበሉ››

በቤተክርስቲያናችን ትምህርት ‹‹መቼም የማይጾሙ›› ወይም ‹‹ሁሌም የሚበሉ›› የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም በጾምም ይሁን በፍስክ የሚበሉ ወይም የሚደረጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የሕያው እግዚአብሔርን ቃል መመገብ፣ ለእርሱና ለቅዱሳኑ ምስጋናን ማቅረብ፣ መልካም ነገርን መስማት፤ ማየት፤ ማሰብ፣ መናገርና መሥራት ይገኙበታል፡፡ አንድ ሰው ሁል ጊዜ የእግዚብሔርን ቃል መመገብ ምስጋናውንም ምግብ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ትዕዛዙንም ዘወትር በመፈጸም ለአምላኩ ያለውን ፍቅር ሊገልጽ ይገባዋል፡፡እነዚህ ጾም ሲገባ ምግብን ተክተው የሚገቡ፣ ጾም ሲወጣ ደግሞ ሥጋን ተክተው የሚወጡ አይደሉም፡፡ ሁል ጊዜ ሙሉ የሕይወት ዘመናችንንም ልናደርጋቸው የሚገቡ ናቸው እንጂ፡፡ ስለዚህ ነው ‹‹መቼም የማይጾሙ›› የተባሉት፡፡ ከእነዚህ መከልከል በራሱ ኃጢአት ነውና፡፡

በተመሳሳይ ‹‹መቼም የማይበሉ›› ወይም ‹‹ሁሌም የሚጾሙ›› የሚባሉ ነገሮችም አሉ፡፡ እነዚህም የኃጢአት ሥራዎችና ወደ ኃጢአትም የሚመሩ ነገሮች ናቸው፡፡ ክፉ ማየት፣ ክፉ መስማት፣ ክፉ ማሰብ፣ ክፉ መናገር፣ ክፉ ማድረግና እነዚህም የመሳሰሉት ነገሮች መቼም መበላት ወይም መደረግ የሌለባቸው ስለሆኑ ሁል ጊዜ ከእነዚህ መጾም ያስፈልጋል፡፡ በስህተትም ከእነዚህ የቀመሰ ወይም የበላ ዋናውን ጾም ገድፏልና በቶሎ ወደ ንስሐ ሊቀርብ ይገባዋል፡፡ እነዚህ በጾም ወቅት የሚከለከሉ የጾም ወቅት ሲያልፍ ደግሞ የሚፈቀዱ አይደሉም፡፡ በማንኛውም ጊዜ የሚጾሙ ናቸው እንጂ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ለሔዋን ‹‹መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብሉ (ዘፍ 2፡18›› ሲል መቼም ቢሆን አትብሉ ማለቱ እንደሆነ ያለ ነው፡፡

በጾም ወቅት በፈቃዳችን ሥጋችንን ስለምናደክም ‹‹መቼም የማይጾሙትን›› የበለጠ ልናደርግ፣ ‹‹መቼም ከማይበሉት›› ደግሞ የበለጠ ልንከለከል እንችል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን የጾም ወቅት ሲያልፍ ወደ ነበርንበት እንመለስ ማለት አይደለም፡፡ በጾም ወቅት የነበሩንን መልካም ነገሮች ከጾሙም በኋላ ይዘናቸው ልንቀጥል ይገባል እንጂ፡፡ በጾም ወቅት የተውናቸውን የሚጎዱን ነገሮች ደግሞ ከጾም በኋላ መልሰን ልንይዛቸው አይገባም፡፡ እንደተውናቸው ልንቀጥል ይገባል እንጂ፡፡ ሰለዚህ በጾም ወቅት ያለንን ተሞክሮ በማጽናት ‹‹ መቼም የማይጾሙትን›› መቼም አለመጾም፣ ‹‹መቼም የማይበሉትን›› ደግሞ መቼም አለመብላት ይገባናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ‹‹የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፡- እነሆኝ ይላል። ኢሳ 58፡8-9›› እንደተባለው ይሆንልናል፡፡

‹‹ቀሳውስት ጾም›› ወይስ የክርስቲያኖች ሁሉ ጾም?

የሐዋርያትን ጾም አንዳንዶች ‹‹የቀሳውስት ጾም›› ሲሉት ይሰማል፡፡ ይህም ከአሰያየሙ ጋር የተያያዘ ብዥታን በመጠቀም ላለመጾም የሚፈልጉ ወገኖች ያመጡት አስተሳሰብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ‹‹የሐዋርያት›› የሚለውን ቃል ብቻ በመውሰድ ጥንት ይህንን ጾም ሐዋርያት ብቻ እንጂ ሕዝቡ አልጾመውም፤ ዛሬ ደግሞ በሐዋርያት እግር የተተኩ ካህናት (ቄሶች) ናቸውና ጾሙም የእነርሱ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም ቀሳውስት አበክረው ስለሚጾሙትና በሕዝቡም ዘንድ ይህ ስለሚታወቅም ጭምር ነው ይህ አስተሳሰብ የመጣው፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ይህን የአዋጅ ጾም ጳጳስ፣ ቄስ/መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ሰንበት ተማሪ ምዕመን ሳይል በ40 እና በ80 ቀን የተጠመቀና ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነው ሁሉ እንዲጾም አውጃለች፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል (ፍት.ነገ. 15፡ 586)፡፡

የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል›› እንዳለ (ኤፌ 2፡20) በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ለታነጽን ለእኛ ለክርስቲያኖች የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው፡፡ የሐዋርያት ጾም  ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ስብከተ ወንጌልን ለመፈጸም በየሀገሩ ከመሰማራታቸው በፊት በሁሉም ነገር እግዚአብሔር እንዲረዳቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ እኛም የሐዋርያትን ጾም ስንጾም ሁል ጊዜ በንስሐ ታጥበን እና ነጽተን ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን ቀሪ ዘመናችንን እግዚአብሔር አምላክ እንዲባርክልንና ሰላምን ፍቅርን እና ጤናን እንዲሰጠን መጾም ይኖርብናል:: ይህ የሐዋርያት ጾም በሐዋርያት እግር የተተኩ የቤተክርስቲያንን አገልጋዮችም አገልግሎታቸውን እንዲባርክላቸውና ምዕመኑን ወደ መልካም ጎዳና እንዲመሩ የሚጸልዩበት ጾም ነው፡፡

በአጠቃላይ በሐዋርያት ጾም የሐዋርያት ክብራቸውና አገልግሎታቸው ይታሰባል፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመላበስ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምዕመናን እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ እያሰብን በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ የመታዘዝ ፍርሃት የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ (ፊልጵ. 2፡12) ጾምን በመጾም፣ ጸሎትን በመጸለይ ከእግዚአብሔርና በንፁህ ደሙ ከዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጋር ያለንን ፍጹም አንድነት ልናጸና፣ ራሳችንን ከኃጢአት ከበደል አርቀን በመታዘዝ ጸጋ የጾምን በረከት ልንቀበልበት ይገባል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት ይርዳን፡፡ አሜን፡፡